የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ነጻነት እና ይኽንንም ነጻነት ለግል ጥቅም ማዋል መፈለግ ፤ የፖለቲካ ማሕበረሰባት የህልውና መሠረት ነው። አንድ የፖለቲካ ማሕበረሰብ ይኽን በተረዳበት እና በተገበረበት ልክ ፤ የእዚያ ማሕበረሰብ መሠረት እና ቀጣይነት አስተማማኝነት ብሎም ልማት ይኖረዋል። ይኽ ድረ ገጽ ፤ ይኽን ድንቅ እና ታላቅ ኃሳብ ፤ ከኢከነሚ ፣ ከፖለቲካ ፣ ከጂኦፖለቲካ እና ከዓለም ዓቀፍ ግንኙነት አንጻር የእሚያብራሩ ጽሑፎች እና መጽሐፍትን ያቀርባል።
ይኽ ገጽ ፤ ሕገክራሲ በእሚል የጻፍኩትን መጽሐፍ መሠረት አድርጎ ፤ የነጻነት ዴሞክራሲ እሳቤን እና ፋይዳውን በሐገር ደረጃ ለማስረጽ ይጥራል። ይኽንም የእሚያደርግበት ዓላማ ፤ በአጭር ቃል ፤ ኢትዮጵያን ከዘመናዊኝነት ማማ ላይ ለማውጣት በማሰብ ነው።
የእዚኽ ድረ ገጽ መነሻ ገጽ (Home Page) ላይ ፤ ጽሑፎች እና መጽሐት በእሚለው ኩላብ (Link) በመጫን የእሚጋሩትን ጽሑፎች እና የእሚተዋወቁትን መጽሐፍት ማየት ይቻላል።
ዜጎቾ የተፈጥሯዊ መብታቸውን ፦ ግላዊ ነጻነታቸውን ፣ የንብረት ባለቤትነታቸውን እና የሕይወታቸውን ዋስትናን ከማረጋገጥ የተሻለ የአንድ ሐገር ዜጋ የእሚሆኑበት ምክንያት የላቸውም !
የዜጎችን ግላዊ ፦ ነጻነት ፣ የንብረት ባለቤትነት እና የሕይወት ዋስትና በእኩልነት ለኹሉም ዜጎች ማክበር የፍትሕ ቀዳሚ እና አንኳር ተግባር ነው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በእዚኽ የፍትሕ ማዕቀፍ ውስጥ ፤ ለማሕበረ ኢከነሚ መሻሻል የእሚሠሩ ፤ የፈቃደኛ ዜጎች ስብስብ መሆን አለባቸው።
ሰው ነጻ ሆኖ ተወልዷል ማለት ፤ በተፈጥሮ ሕግ ብቻ ሲወሰን ፤ ከሌላ ከማንም ሰው ፈቃድ ሳይጠይቅ ፤ እራሱን እና የእርሱ የሆነውን ነገር እንደ አሻው ማድረግ ይችላል ማለት ነው።
የተፈጥሮ መብት ፦ ሰዎች ኹሉ በእኩልነት ፤ ሰው ብቻ ሆነው በመፈጠራቸው የተጎናጸፏቸው ፦ በሕይወት የመኖር ፣ ነጻነት ፣ የእራስን ዓላማ መከተል ፣ ወዘተ ዓይነት ሰብዓዊ መብቶች ናቸው።
የተፈጥሮ ሕግ ፦ ሰዎች ተፈጥሮ ነጻነታቸው በመጠቀም እንደ እነሱው በተፈጥሮ ነጻ በሆነው ሌላ ሰው መብት ፦ ሕይወት ፣ ነጻነት እና ንብረት ላይ አግባብ የሌለው ጉዳት እንደ አያደርሱ የእሚከለክል አመክንዮዋዊ ገደብ ነው።
የጦርነት ኹኔታ ፦ ሰዎች የተፈጥሮን ሕግ ተላልፈው ፤ አንዳቸው በአንዳቸው ፦ ሕይወት ፣ ነጻነት እና ንብረት ላይ ጉዳት ሲያደርሱ የእሚገቡበት ኑሮን አስጊ የእሚያደርግ የግጭት ሁናቴ ነው።
የተፈጥሮ ኹኔታ - ቅድመ መንግሥት ሰዎች የእሚገኙበት ኹኔታ ሲሆን ፤ የተፈጥሮ ሕግን አስከ አከበሩ ሠላማዊ የሆነ ፤ የተፈጥሮ ሕግ በእሚጣስበት ግን ፤ ሰው ኹሉ እርስ በእርሱ የእሚዋጋበት እና ስረዓት አልበኝነት የእሚሥፍንበት ኹኔታ ነው።
የፖለቲካ ስልጣን ፤ በተፈጥሮ እኩል ነጻ የሆኑ እና የተፈጥሮ መብት ባለቤት የሆኑ ሰዎች ፤ በተፈጥሮ ኹኔታ ውስጥ በቋሚነት ከእሚጋፈጡት የእርስ በእርስ መብት ጥሰት አደጋ እና እርሱም ከእሚያስከትለው አስፈሪው የጦርነት ኹኔታ ለመዳን ፤ እራስን የመከላከል መብታቸውን ፤ የጋራ ለማድረግ ከመፈለጋቸው ይመነጫል።
የፖለቲካ ስልጣን በዋናነት እና በቀዳሚነት ፤ ሰዎች በተፈጥሮ ኹኔታ ውስጥ የእሚጋረጥባቸውን የተፈጥሮ መብት ጥሰት ለመከላከል ነው የእሚያዘው።
የፖለቲካ ስልጣን የዜጎችን ተፈጥሯዊ መብት ከሕገ ወጥ ገፈፋ ከመከላከል አልፎ ፤ እርሱ እራሱ የመብት ገፋፊ ከሆነ ፤ ሰዎች መጀመሪያዊኑ በተፈጥሮ ኹኔታ ውስጥ የሸሹትን የመብት ጥሰት መልሶ በማምጣት የጦርነት ኹኔታን በመመለስ የሰውን ሕይወት አስጊ እና አስቀያሚ ስለ እሚያደርግ ፤ የፖለቲካ ስልጣን መብት ጥሰት ውስጥ መግባት የለበትም።

በእዚኽ ክፍል ፤ ፖለቲካዊ ስረዓቶችን ከሐገር አንጻር በዋናነት ለምን ዴሞክራሲያዊ እና ጽንፈኛ ብዬ እንደ ከፈልኳቸው በአጭሩ ተቀምጧል።

ይኽ ክፍል ኃይማኖት በሐገር ግንባታ ውስጥ ዓይነተኛ ሚና ሊኖረው ቢችልም መስመር ስቶ ፖለቲካ ልቆጣጠር ሲል ጽንፈኛ በመሆን ሐገር አጥፊ የእሚሆንበትን አግባብ ይቃኛል።

ፖለቲከኞች ከኃይማኖታዊ ጽንፈኛ ባልተናነሰ ፤ የተሳካ አምክንዮዋዊ ምክንያት ሊያቀርቡባቸው በእማይችሉባቸው ጉዳዮች ላይ አክራሪ ሲሆኑ ይታያሉ።

ብሔርተኝነት በተለይ ነገዳዊ ብሔርተኝነትም ከአመክንዮ በተፋታ መልኩ የፖለቲካ መነሻ እና መጨረሻ በመሆን ወደ ዘረኝነት ሊዘቅጥ ይችልላ።

ጂንጎይዝም በሐገር ፍቅር ስም ፤ የእኛ ሐገር ከሌሎች ሐገር በላይ ነች በእሚል ፤ ጸበኛ የሆነ የውጭ ግኑኝነት ነው። ጂንጎዝም በፖለቲከኞች ሲቀነቀን ሐገር የማድቀቅ አቅም አለው።

ለዴሞክራሲያዊ ሐገር የተፈጥሮ መብት ጥላው በመሆኗ ፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እስከ ሌለ ከኹሉም ጋር ተስማምቶ የመኖር አቅም ያለው እና በባሕሪው የሠላም ኃይል ነው።

ዴሞክራሲያዊነት ለማሕበራዊ ሠላም እና መረጋጋት ብቻ ሳይሆን ፤ የዘላቂ ኢከነሚያዊ ዕድገት መሠረት በመሆኑም ፤ በዘርፉ ወደር የለውም።