Skip to main content

የባሕል ጽንፈኝነት እና ሐገር

በእዚኽ ንዑስ ክፍል ባሕልን ከእምንቃኝበት አግባብ አንጻር ፤ አመቺ ኹኔታን ለመፍጠር ፤ ባሕልን እንደ ሰው ልጅ ውቅር የእሚገልጹትን ሦሥት ነጥቦች አስቀምጠን እንጀምር።


የመጀመሪያው  ፤ አብዛኛው ባሕል በኃሳብ መሳሪያነት በሰው ልጆች የተገነባ ኃሳባዊ ውቅር ቢሆንም ፤ አብዛኛው የሰው ልጅ ባሕል ፤ በሆንታዊ እቅድ የተገነባ አይደለም።


የሰው ልጅ ፥ አብዛኛውን ባሕሉን ፤ ባሕል የእሚባል እና ይኽን ይኽን ጉዳይ የእሚከውን ውቅር ልፍጠር ብሎ ፤ የሆነ ቅድመ ንድፍ አዘጋጅቶ አይደለም የፈጠረው ። ይልቁንም የሰው ልጅ ተፈጥሮዋዊ ባሕሪው የሆነውን ፤ የእማያቆም መልካም ብሎ የእሚያስበውን ነገር በእማያቆም ኹኔታ የመፈለግ  ዝንባሌው እየነዳው ሲኼድ የገነባው ነገር ነው ።


አርስታትል ይኽ መልካምን የመፈለግ ተፈጥሮዋዊ የሰው ልጆች ዝንባሌ ፤ የማሕበረሰብ ወይንም የአንዳች ዓይነት የጋርዮሽ ተቋም መሠረት መሆኑን የተገነዘበበትን አግባብ እንደ እዚኽ አስቀምጦታል ፦


“እያንዳንዱ ሐገር/መንግሥት አንድ የሆነ ዓይነት ጋርዮሽ/ማሕበር ነው ፤ የትኛውም ጋርዮሽ/ማሕበር ደግሞ አንድ መልካም ነገርን ግብ የእሚያደርግ ነው ፤ ምክንያቱም ፦ የሰው ልጅ ግብር ፤ ል ግዜ መልካም ነው ብሎ ያሰበውን ነገር ማግኘትን ታሳቢ የአደረገ ስለ ሆነ ።”


 “Every state is a community of some kind, and every community is established with a view to some good; for mankind always act in order to obtain that which they think good. [1]“


ይኽን ስእንል የሰው ልጅ ፤ ማገናዘቢያ እንደ ሌላቸው ደመ ነፍሳዊ ፍጥረታት ፤ በደመ ነፍስ ብቻ የእሚመራ ነው እያልን ወይንም የሰው ልጅ ጥቅሙን ከጉዳቱ የእሚያመዛዝንበት አዕምሮ ባለቤት መሆኑን እየካድን ሰአይሆን ፤ የሰውን የማገናዘብ እና የመተንተን ውስንነት ታሳቢ እያደረግን ነው።


የሰው ግብሩ አንዳችን መልካም ታሳቢ የአደረገ መሆኑ እሙን ቢሆንም ፤ የተግባራቱን ተዛማጅ ውጤቶች በሙሉ አስቀድሞ የመረዳት እና የመተንተን ውስንንነት የአለበት መሆኑ ግልጽ ነው።


አንዱን ዓይነት በአንድ ሕዝብ ዘንድ ያለ የአለባበስ ባሕል ብንወስደው ፤ የእዚያኽ አለባበስ ባሕል ባለቤት የሆነው ሕዝብ ያንን አለባበስ ተሰብስቦ ፤ አለባበሳችን ይኽን ይምሰል ብሎ ፤ አስቀድሞ አቅዶ ፣ ተወያይቶ እና ወስኖ የእሚያመጣው አይደለም። በተለያዩ ምክንያቶች ፤ በእዛኽ ሕዝብ መካከል ያሉ ግለሰቦች ፤ ይሻለኛል ወይንም ይበጀኛል የእሚሉትን ነገር ሲያደርጉ ፤  ያለ ሆንታዊ እቅድ ፤ አንዱ ዓይነት አለባበሳቸው ፤ በግዜ ኺደት ባሕላቸው እና የሕዝባቸው መገለጫ ይሆናል እንጂ።


ያንን የአለባበስ ባሕል በማምጣት ኺደት ውስጥ አንዳች ዓይነት የጥቅም እና የጉዳት ስሌት ፤ በተለይ በግለሰቦች ደረጃ እንደ ነበር ግልጽ ቢሆንም ፤ ያ የአለባበስ ባሕል በግዜ ኺደት ፤ የእሚላበሰውን ፖለቲካዊ ፣ ኢከነሚያዊ እና ስሜታዊ ህልውና ፤ በማሕበረሰቡ መሪዎች አስቀድሞ ታስቦበት እና ታቅዶ የመጣ እንደ አልሆነ ግን ለብዙዎቻችን ግልጽ ነው።


ኹለተኛው ፤ ባሕል ምንም እንኳን በሰው ልጆች በኃሳብ መሳሪያነት ቢወቀርም ፤ በእንግሊዘኛው አባባል ፦ ሙሉው ከክፍልፋዮቹ ድምር በላይ ነው ( The whole is greater than the sum of its parts ) እንደ እሚባለው ፤ ባሕል አንድ ግዜ ተዋቅሮ ከሰነበተ ፤ ተሰባስበው ከአዋቀሩት ሰዎች እና ኃሳባት በላይ እጅግ የላቀ ኃይል ነው ።


ለምሳሌ ፦ በሒሳብ ቀመር 5 ጠጠር እና 5 ጠጠር ፤ ኹል ግዜ 10 ጠጠር ይሆናሉ ፤ ሰዓትን እንደ ምሳሌ ብንወስድ ግን ፤ ሰዓቱ ከአካላቱ ድምር በላይ ነው ።


ሰዓት ፦ ማሰሪያው ፣ መስታወቱ ፣ መቁጠሪያ ዘንጎቹ ፣ ወዘተ ፤ ጥርቅምቅም ወይንም ድምር በላይ ነው ፤ ስለ እዚኽ ፦ ሙሉው (ሰዓቱ) ተቀነባብረው ከአመጡት (ማሰሪያው ፣ መስታወቱ ፣ የመቁጠሪያ ዘንጎቹ ፣ ወዘተ) ስብስብ በላይ ነው ።


እንደ እዚኹም ባሕል ፤ አንድ ግዜ በሰው በኃሳብ መሳሪያነት ከተዋቀረ በኋላ ፤ የራሱን ሰው ሰራሽ ‘ስብዕና’ ተላብሶ እና ከአዋቃሪዎቹ ሰዎች እና ኃሳቦቻቸው በላይ ፤ እጅግ ዓይሎ ሊገኝ የእሚችል ውቅር ነው።


እነ እዚኽ ኹለት የባሕል ባሕሪያት ስለ ባሕል ልናነሳ ወደ ፈለግነው ሦሥተኛ ነጥብ ያመጡናል ፤ እርሱም ፦ ይኽ ፤ በአብዛኛው ያለሆንታዊ ቅድመ እቅድ የተመሠረተ እና ከተመሠረተ በኋላ እጅግ የተባዛ የህልውና ጥንካሬ የእሚይዝ ባሕል ፤ አዎንታዊ የእሚባሉ ማሻሻያ እና ለውጦችን ፤ የመቃወም ፣ የመግፋት ፣ የማምከን ከፍተኛ አቅም የአለው መሆኑ ነው።


እነ እዚኽ ሦሥት የባሕል በኃሪያት በአንድ ላይ ተዳምረው ፤ ማለትም ፦ በአብዛኛው ያለ ሆንታዊ እቅድ መመሥረት ፣ ከተመሠረቱ በኋላ የተባዛ አቅም መላበስ እና አሉታዊ ሆኖ ሲገኝ ማሻሻያ እና ለውጦችን ፦ የመቃወም ፣ የመግፋት እና የማምከን አቅም ፤  ባሕል አሉታዊ በእሚሆንበት ግዜ ፤ በሰው ልጆች ላይ የእሚያስከትለውን ጉዳት እጅግ ጉልህ አድርጎታል።


የሰው ልጅ በፖለቲካ ታሪኩ እነ እዚኽን መሠረታዊ ባሕሪያት በእሚጋሩ አሉታዊ ባሕላቱ የደረሰበት አበሳ ቁጥር ስፍር የለውም።


ባሪያ እና ጨዋ አለ በእሚል ባሕላዊ አስተሳሰብ በባሪያ ስረዓት ሰውን እንደ ንብረት መያዝ እና ጉልበትን መበዝበዝ ፣ በኃይማኖታዊ እምነት ልጆችን ለተለያዩ አማልክት መሰዋት ፣ በባሕላዊ ልምድ ሴት ልጆችን ያለ እድሜያቸው መዳር ፣ የሴት ልጅ ግርዛት ፣ ወዘተ ፤ እያልን ፤ ያለ ቅድመ ጥናት ፤ መሠረታዊ የሆነው የሰው ፍላጎት መነሻቸው የሆኑት እንደ ማሕበረሰብ እና ባሕል ያሉ የሰው ልጅ ተቋሞች ፤ በመሥራቹ ሰው ላይ ያደረሱትን ሰቆቃ መዘርዘር እንችላለን ።


ይኽም በመሆኑ ፤ ባሕላት አንድ ግዜ ወደ መሆን ከመጡ በኋላ ፤ በሰዎች ፍላጎት እና አስተሳሰብ አኃድነት እንዳልተገነቡ ኹሉ ፤ የግንባታቸው አህድ የሆነው ሰው ፤ የእሚኖረው የተናጠል እና የጋራ አቅም ፤ ከእነ እዚኽ የራሱ ሥራ ከሆኑት ውቅሮች አንፃር እጅግ መንምኖ ፤ እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ንዑስ ማሕበር ፤ እነ እዚኽ ራሱ ከአቋቋማቸው ተቋማት በእሚመነጩ ፤ ከላይ ከዘረዘርናቸው እና ከአልዘረዘርናችው ብዙ ችግሮች አዳኝ አጥቶ የዳከረበት ኹኔታ ትርክት ሆኗል ፤ አብዛኛው የሰው ልጅ ማሕበራዊ እና ፖለቲካዊ ታሪክ ይዘት ።


ይኽንንም አሳዛኝ ኹኔታ ፤ ማለትም ፦ እንደ ባሕል ፣ ማሕበረሰብ ፣ ወዘተ ፤ ያሉ የሰው ልጆች ማሕበራዊ ውቅራት ያልሆንታዊ እቅድ ተመስርተው እና በእሚኖራቸው የተባዛ አቅም እና አዎንታዊ ለውጥን እና ማሻሻያን ለመግፋት በአላቸው ልማድ  ፤ በሰው ልጅ ላይ ያደረሱትን ሰቆቃ ከተገነዘቡት ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው ፤ ማሕበራዊ ውል በእሚል ርዕስ ስለ ዴሞክራሲያዊ ማሕበረሰብ አደረጃጀት መጽሐፍ የጻፈው ጃን ጃክ ሩሶ ፤ ይኽን ታዋቂ መጽሐፉን በእሚከተለው ዓረፍተ ነገር ይጀምረዋል ፦


“ የሰው ልጅ ነጻ ሆኖ ተወልዷል ፤ በእየስፍራው ግን በቀንበር ስር ይገኛል ።”

“Man is born free, and everywhere he is in chains. [47]“


በእርግጥ ሩሶ ይኽን የእሚለው ፤ የሰው ልጅ ነጻ ሆኖ ቢወለድም ፤ ብቻውን የመኖር አደጋ አስፈርቶት እራሱን ነጻነቱን ለእሚገድቡ ፤ አንዳንዴም ለእሚያሰቃዩት ፤ የፖለቲካ ስረዓት አስገዝቷል ለማለት ነው።


የሩሶ አውድ ያ ቢሆንም ፤ ባሕልም እንደ ፖለቲካዊ ስረዓት እራሱን በግለሰቦች ላይ በአሉታዊ መልኩ የመጫን አቅም ስላለው ፤ ባሕል መስመር ሲስት ፤ መስመር እንደ ሳተ የፖለቲካ ስረዓት የዜጎችን ሕይወት ከማገዝ ይልቅ ሊያደናቅፍ እንደ እሚችል ማሳያ መሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ።


ከእነ እዚኽ በሺ ለእሚቆጠሩ ዓመታት ከቆዩ እና በእየ ዘመኑ በእሚኖረው እና በእሚለዋወጠው የሰው ግንዛቤ እና ኹናቴ ፤ ባሕሪያቸው ከእሚቀያየረው ባሕላዊ ኹኔታዎች ከእሚመነጩ ሰቆቃዎች ፤ ለመውጣት ከመፈለግ ነው ፤ ህዳሴ (Reinassance) በአውሮፓ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አከባቢ የጀመረው ፥ አርስታትል እንደ አለው ፦


‘የሰው ልጅ ግብሩ መልካም ብሎ የእሚያስበውን ነገር ለማግኘት … ’

ከመፈለግ የእሚነሳ ነውና ።


የአውሮፓውም ህዳሴም ፤ ከሌሎች የሰው ልጆች ተቋማት ጋር ፤ ያለ ሆንታዊ እቅድ ተመስርቶ ፣ ከግንባታ አህዶቹ ፥ ሰዎች እና ኃሳባቸው በላይ እጅግ የተባዛ አቅም ይዞ እና አዎንታዊውን የለውጥ ማሻሻያ ወይንም አዲስ አካኼድ በሙሉ በአለው የተባዛ አቅም እየገፋ ፤ የሰውን ልጅ ሕይወት አክብዶ የነበረውን ባሕል በዋናነት በአመክንዮ የመታገል አካኼድ ሆኖ ነበር።


ህዳሴው ሲመጣ ፤ ከላይ በዘረዘርናቸው የባሕል መሠረታዊ ባሕሪያት ምክንያት ፤ የተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍሎች ፤ እንደ ሌሎች የማሕበረሰብ ተቋማት ፤ ለአብዛኛው አሉታዊ ባሕላቸው ከአመክንዮ ይልቅ መንፈሳዊ እና የውርስ (ከአባቶቻችን የወረስነው) የእሚል ግርድፍ ምክንያት እያቀረቡ ፤ በአሉታዊ ባሕላቸው ምክንያት በሰው ልጆች ላይ ሲያስቀጥሉ የነበሩትን መከራ ፤ አሳማኝ ምክንያንት በማቅረብ ለማስቀረት ፤ የአስተሳሰብ እና የአደራረግ ለውጥን ግድ የእሚል አካኼድ ሆኖ ነበር የመጣው።


በእዚኽ መልክ የመጣው የአውሮፓ ህዳሴ ፤ በተሳካባቸው ሐገራት ፤ ባሕልን ጨምሮ ሌሎቹ የሰው ልጆች ማሕበረ ኢከነሚያዊ ተቋሟትን ፤ በመጠየቅ እና በመመርመር ፤ ይሻላል እና ይበጃል በእሚለው መልኩ ፤ እንደ ገና ማዋቀር በመቻሉ ፤ በሰው ልጅ ፖለቲካዊ ታሪክ ውስጥ በአጭር ግዜ ፤ ፈጣን የእሚባል ዙሪያ መለስ የማሕበረ ኢከነሚ መሻሻል እና እድገት አምጥቷል።


ከእዚኽም የተነሳ የሰው ልጅ ፖለቲካዊ ታሪክ ከጀመረበት ፤ ከክርስቶስ ልደት በፊት 3,500 ዓመት ጀምሮ ወይንም በጠቅላላው ወደ 5,500 ከእሚጠጋው የሰው ልጅ ማሕበራዊ ታሪክ እድሜ ውስጥ ፤ ባለፉት 500 ዓመታት በሰው ልጆች ማሕበራዊ ህይወት ላይ የታየው መሻሻል ከእዚኽ ቀደም ከነበሩት ኹሉ በብዙ እጥፍ የላቀ ነው ።


በዓለፉት 500 ዓመታት ፤ ከእነ እዚኽም አምስት መቶ ዓመታት በቅርቦቹ 300 ዓመታት ፤ የሰው ልጅ በኢከነሚ ፣ በፖለቲካዊ አደረጃጀት ፣ በእውቀት ፣ በጤና ፣ ወዘተ ፤ ያስመዘገበው እመርታ ፤ አንዳንዶቹ ስኬቶቹ እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ የእማይቻሉ እና ልብ ወለድ የእሚመስሉትን ኹሉ ያስቻለ ነበር ።

የተሳካላቸው እና በአለፉት 3 እና 4 መቶ ዓመታት ፤ የፖለቲካ ሳይንስ ወደ ሰፊው ሕዝብ ግንዛቤ በአመጣቸው መርሆች ተመርኩዘው መሐበረሰባቸውን እና መንግሥታቸውን እንደ ገና ያደራጁ ሕዝብ ፤ እጅግ ፈጣን በእሚባል ግዜ[1] ፤ ራሳቸውን ከድህነት ፣ ከበሽታ ፣ ከበደል ፣ ከጭቆና አላቀው ወደ ኃብት ፣ ጤንነት ፣ ፍትሕ እና ነፃነት አሻጋግረዋል ። 

 

በሰው ዘንድ ፍፁም የእሚባል ነገር በአይኖርም ፤ የህዳሴው ለውጥ ጥልቀት እና ፍጥነት ፤ ከአምስት መቶ አመት በፊት ከነበረው ሰአይሆን ፤ ከእዚያኽን ግዜ አንስቶ በእየ መቶ ዓመት ልዩነት ላይ ያሉ ትውልዶች እንኳን ፤ በመካከላቸው የአለው ርቀት እረዥም እንዲሆን የአደረገ ነው ። ወይንም ፥ አዳም ስሚዝ እንደ አለው ፤ ዛሬ አንድ መለስተኛ ባለመዋል(ጭሰኛ) ቤት ውስጥ ያለ ምቾት በአንድ ልዑል እልፍኝ ውስጥ ከእሚገኝ ምቾት ጋር የተቀራረበ ነው[2] ፦

 

“ …በልዑሉ ማጀት የአለው ቁሳቁስ … ከአንድ ትጉህ እና በመጠን ነዋሪ ጭሰኛ ማጀት ቁሳቁስ  ብዙም አይበልጥም”

 

“...that the accomodation of a ... prince doesn’t always exceed that of an industrious and frugal peasant. [48]“

 

ይኽ ለአዳም ስሚዝ ዘመን ሲሆን ፤ ዛሬ በሰለጠነው ዓለም የእሚኖር አንድ መደበኛ ዜጋ የእሚኖረው ኑሮ ፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት ሉዕላን ይኖሩት ከነበረው ኑሮ የእሚሻልበት ደረጃ ላይ ደርሷል ።

 

በእዚኽ በእኛ ዘመን ፤ መካከለኛ የገቢ ደረጃ ላይ ያሉ ዜጎች ፤ እንደ የእለት ተእለት የኑሮ አስፈአጊ ቁስ አድርገው የእሚያዩዋቸው ፦ ቴሌቭዥን ፣ ከምፒውተር ፣ ዘመናዊ የእጅ ስልኮች ፣ መኪና ፣ የተለያዩ ዓይነት የምቾት እና የመገልገያ የቤት እቃዎች ፤ የዛሬ 50 እና 100 ዓመት ነገሥታት እና ርዕሳነ-ብሔራት ማጀትም ውስጥ የእማይገኙ ናቸው ።

 

ሆኖም ይኽ አዲሱ እመርታ ወይንም ህዳሴ ግን በኹሉም የዓለም ሕዝብ ዘንድ በተቀራራቢ መልኩ አልተሰራጨም ።

 

የሰውን ልጅ ማሕበረ ኢከነሚያዊ ኹለንተና ፤ በተነጻጻሪነት በአጭር ግዜ በአዎንታዊ መልኩ ማሻሻል የቻለው ህዳሴ ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በተመሳሳይ ወይንም በተቀራራቢ መልኩ መሰራጨት አለመቻሉ ፤ ስለ ህዳሴው የእሚነግረን ነገር አለ ።

 

በእዚኽ ረገድ የመጀመሪያው ፤ ሕዳሴው የሰው ልጆች ለሕዳሴው ግብዓት የእሚሆኑ ብዙ ተዛማጅ እውቀቶች እንዲ ዳብሩ የእሚፈልግ ወይንም ማሕበረሰቡ አንዳች ዓይነት ማሕበራዊ የእድገት ደረጃ ላይ እንዲ ደርስ የእሚፈልግ መሆኑ ነው።

 

በተፈጥሮዋዊ ባሕሪው ተመራማሪ የሆነው ሰው ፤ ብዙኽ ሺ ዓመት በፈጀው ፖለቲካዊ ታሪኩ ፤ እንደ ፕሌቶ ፣ አርስታትል እና ኮንፊሸስ ባሉ ሊህቃን ከጥንት ጀምሮ እንደ ሌሎቹ መስኮች ኹሉ ማሕበረሰብን እንደ አንድ የጥናት ርዕስ ውስዶ ሲያጠና እና ሲመረምር ቢቆይም እና የጥንታዊው ጥናት እና ምርምር ውጤት የሆኑት ግንዛቤዎች ለዛሬው ማሕበራዊ ሳይንስ ለደረሰበት የእድገት ደረጃ ከፍተኛ ግብዓት ቢሆኑም ፤ በአውሮፓዊያን ሕዳሴ የዳበረው እውቀት ፤ በይዘቱ ከእዚኽ ቀደሞቹ እጅግ የተብራራ እና በሳይንሳዊነት መመዘኛው ላቅ ያለ ደረጃ ላይ የእሚገኝ ነው።

 

ይኽም ማለት ፤ ምንም እንኳን የአውሮፓ ህዳሴ አንዱ እና ዋነኛ መገለጫው ሕዝባዊነት ወይንም ሕዝባዊ መሠረት መያዝ ቢሆንም ፤ የአውሮፓ ሕዳሴ እንዲሳካ እና ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖረው ፤ ከእርሱ በፊት ከነበሩት የስልጣኔ ደረጃዎች ይልቅ ፤ የሕዳሴውን ሳይንስ በአግባቡ የተረዱ እና ከተለያየው የሕዛባቸው ኹኔታ ጋር ማዋደድ የእሚችሉ ወይንም የሕዝባዊውን ወይንም የሕዝባቸውን ትምሕርት የመቀበል አቅም መገንባት የእሚችሉ ፤ የለውጥ ሐዋሪያትን የእሚፈልግ ነው።

 

ኹለተኛው ፤ ህዳሴው ከቀደመው ስልጣኔ ይልቅ ፤ በይዘቱ ሰፊ እና ውስብስብ በመሆኑ ፥ ወይንም በረዥም ዘመን የታሪክ ጉዞ የተቀመረ በመሆኑ ፤ ህዳሴውን መሸከም የእሚችል ፤ ዘርፈ ብዙ የሆነ ማሕበራዊ እድገት የእሚጠይቅ መሆኑ ነው።

 

ከ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት የነበረው እና ቀዳሚው (Classical Period) የእሚባለው ስልጣኔ ፤ በተነጻጻሪነት አብዛኛው የዓለም ሕዝብ ፤ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ የማሕበራዊ እድገት ደረጃ ላይ በእሚገኝበት ደረጃ ላይ የመጣ በመሆኑ ፤ አንድ ሕዝብ በእዚያኽ ዘመን መመዘኛ ፤ ከኋላ ቀርነት ወጥቶ ዘመናዊ ለመባል ፤ ይኽን ያኽል የሰፋ እና የተወሳሰበ ፤ የአስተሳሰብ እና የአደራረግ ማስተካከያ እንዲያደርግ አይጠበቅበትም።

 

ስለ እዚኽ ፤ የቀደመው ስልጣኔ በጥቂት ማሻሻያ እና በአጨር ግዜ ሊተገበር የእሚችል ሲሆን ፤ ይኽ ዳግማዊው ስልጣኔ ወይንም ህዳሴ ግን ከእዚኽ በተለየ ፤ ሰፊ እውቀት የእሚጠይቅ ነው።

 

ሦሥተኛው ፤ ህዳሴው የስፋቱን እና የውስብስብነቱን ያኽል ፤ ሊለውጠው እና ሊያሻሽለው የእሚፈልጋቸው ነባራዊ ስረዓቶችም ፤ ከቀዳሚው ግዜ ይልቅ ፤ የደረጁ እና የተወሳሰቡ የነበሩ መሆኑ ነው።

 

ህዳሴው ፤ የዛሬ አምስት መቶ ዓመት አከባቢ ሲጀምር ፤ በአብዛኛው የዓለም ክፍል የተመሠረቱ እና የተደላደሉ አንዳንዴም በሺ የእሚቆጠሩ ዓመታት የቆዩ ፤ ለውጥ አደጋ ውስጥ የእሚጥላቸው ብዙ ዓይነት የሰው ተቋሞች የነበሩ በመሆናቸው ፤ የለውጥ ኃሳብ አራማጆቹ ከፊል በስጋት ከፊል ደግሞ በጥቅመኝነት ምክንያት ነባራዊውን ወግ ለመጠበቅ ከእሚፈልጉ ወግ-አጥባቂያን ጋር አንዳንዴ ሆን ብለው አንዳንዴም ሳያስቡት በኃሳብ የመጋጨት እና የኃሳብ ግጭቱም ወደ አካላዊ ግጭት እንዲያመራ የእሚያደርገው ነበር።

 

እነ እዚኽ ሦሥቱ የህዳሴው በኃሪያት ፤ ምንም እንኳን የሕዳሴው መሠረታዊ ኃሳቦች በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ፤ ከሞላ ጎደል ሰፊ ተቀባይነት የአላቸው ቢሆኑም ፤ ተግባራዊነታቸው ወጣ ገባ እንዲሆን አድርጎታል።

 

 ህዳሴውን የእሚመጥን ማሕበረሰባዊ እድገት እና የሕዳሳውን ሳይንስ በአግባቡ የተረዱ ሊህቃን ያሉዋቸው ማሕበረሰባት ፤ ሕዳሴውን በብዙ ፈተናም ቢሆን ገንብተው ለፍሬ ያበቁ ሕዝብ ፤ ለሐገራቸው ሕዝብ አንጻራዊ ረፍት ሲያረጋግጡ እና ለሌላው የዓለም ሕዝብ የተራራ ላይ ከተማ ሲሆኑ ፤ ህዳሴው የእሚፈልገው ማሕበራዊ የእድገት ደረጃ ላይ ሳይደርሱ ወይንም የሕዳሴውን ኃሳብ በአግባቡ ተረድተው ሊተገብሩ የእሚችሉ ሊህቃን ሳይኖራቸው ፤ ሕዳሴው ወይንም የሕዳሴው መርሕዎች ፤ በዓለም ዓቀፍ ተቀባይነታቸው ምክንያት ፤ ህዳሴውን ለመተግበር የተነሱ የፖለቲካ ማሕበረሰባት ደግሞ በተሰነካከለ የህዳሴ ጉዞ ላይ እንዲሆኑ አድርጓል።

 

ይኽም በመሆኑ ወይንም ህዳሴው የራሱ የሆነ ኺደት የአለው በመሆኑ ፤ ኺደቱ በአግባቡ ከአልተካኼደ የለውጥ ወይንም የዳግማዊ ስልጣኔውን እውን የማድረጉ ጉዳይ ሊከሽፍ የእሚችል ፤ በአንዳንድ ፅንፍ ምክንያቶች ደግሞ ሐገርን ለብጥብጥ እና ለውድቀት የእሚዳርግ መሆኑ የታየ ነው ።

 

ከእዚኽም የተነሳ ፤ ዳግማዊ ስልጣኔ በተደራጀ እና ትርጉም በአለው መልኩ ከመጣ ቢያንስ ኹለት መቶ ዓመታት በላይ የአለፈ ቢሆንም ፤ ቀላል የእማይባለው የዓለም ሕዝብ ፤ 50 እና 60 ዓመታት ወይንም ከእዚያኽ በላይ በፈጁ በተሰነካከለ እድሜ ጠገብ የለውጥ ኺደት ውስጥ ሲሆን ፤ የተወሰነው ደግሞ ሙሉ ለሙሉ በሩን ዘግቶ በአለበት እየረገጠ ነው ።

 

ይኽን መሰል በኃሪ የአለውን ህዳሴ በአግባቡ በማሕበረሰብ ውስጥ ሰርጾ ፤ የእሚጠበቅበትን ውጤት እንደ አያመጣ ፤ ደንቃራ ከእሚሆኑ ነገሮች አንዱ እና ዋነኛው የባሕል ጽንፈኝነት ነው።  የባሕል ጽንፈኝነት የማሰናከያ ምክንያት የእሚሆነው በእሚከተሉት ኹለት ተጠቃሽ ምክንያቶች ነው ፦

 
  • የመጀመሪያዎቹ በሶሲዮሎጂ አጠራር ፤ የባሕል አንጻራዊያን (Cultural Relativist) የእሚባሉት የእሚያራምዱት የባሕል ‘ነፃነት’ በእሚል ሽፋን የእሚካኼድ የባሕል ፅንፈኝነት ሲኾን
  • ኹለተኞቹ ደግሞ ፤ ያልተመረመሩ ሕዝባዊ መሠረት የአላቸው ልማዳዊ አስተሳሰቦች ናቸው
 

ይኽም ማለት ፦ በሆንታዊ ጥናት እና በሆንታዊ ምርጫ የእሚደረስበት ይኽ የህዳሴ ቀመር ወይንም ዳግማዊ ስልጣኔ ፤ ሳይንሳዊ መርህ የእሚከተሉ እና ልማዳዊ አስተሳሰብ የያዙ የባህል አክራሪ ተቃዋሚዎች አሉት ፤ ማለት ነው።

 

የሳይንሳዊ ተቃዋሚዎቹን የሐሳብ መሠረት ለመረዳት ፤ በሶሲዮሎጂ መስክ የአለውን ፅንሰ ኃሳብ በአጭሩ ማስቀመጥ ያግዛል ።

 

በሶሲዮልጂ የሰዎች ባሕል እንደ አንድ የጥናት ርዕስ በእሚጠናበት ወቅት ፤ ባሕላዊ ቋሚዎች ወይንም ዓለም ዓቀፋዊ ባሕላት (Cultural Universals) እና ባሕላዊ አንጻሮች (Cultural Relatives) የእሚባሉ ኹለት የአመለካከት መደቦች አሉ። እነዚኽ ኹለት የባሕል ምልከታዎች ፤ በእሚከተለው መልኩ ይገለጻሉ ፦

 

“ዓለም ዓቀፋዊ ባሕላት ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በኹሉም ሕዝብ ዘንድ የእሚስተዋሉ ልማዶች እና ባሕሪያት ናቸው ።”

 

“Cultural universals are patterns or traits that are globally common to all societies. [49]“

 

“አንፃራዊ የባሕል ምልከታ አንድን ባሕል ከራስ ባሕላዊ መነፅር አንፃር ሰአይሆን ፤ በራሱ መመዘኛ መሠረት የማየት ልማድ ነው ።”

 

“Cultural relativism is the practice of assessing a culture by its own standards rather than viewing it through through the lens of one’s own culture. [49]“

 

እነ እዚኽ ኹለት የባሕል ምልከታዎች ሲጠቃለሉ ፤ የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የእሚጋራቸው ባሕላዊ እሴቶች (ሙዚቃ ፣ ትዳር ፣ ወዘተ ) ያሉት ሆነው ፤ ከማሕበረሰብ ማሕበረሰብ በአቀራረባቸው የእሚለዩ (የአመጋገብ ፣ የአለባበስ ፣ ወዘተ) ባሕላዊ ልዩነቶች ያሉት በመሆኑ ፤ ኹሉም ማሕበረስብ ተመሳሳይ የሰርግ ፣ የጭፈራ ፣ ወዘተ ፤ ባሕል እንደ አለው እና በተመሳሳይም አንድ አንድ የባሕል ልዩነቶች እንደ አሉት መገንዘብ እና ያንን ማክበር ተገቢ ነው የእሚል ነው ።

 

ስለ እዚኽ ፦ ጤናማው የባሕል ምልከታ ፤ ሰው በመሆናችን የእምንጋራቸው ነገሮች እንደ አሉ ሆነው ፤ ለምሳሌ ፦ በዓለም ላይ ባሉ በኹሉም የሰው ማሕበረስባት ዘንድ ትዳር እና ሰርግ የእሚታወቁ ናቸው  ፤ ከከባቢ ከባቢ የአሉትን ፤ እንደ ልዩ የሰርግ አሰራረግ ባሕል የአሉትን ልዩነቶችን ወይንም መሰል በሕላዊ ልዩነቶች  ፤ መኖራቸውን ተገንዝበን ልዩነቱን ተቀብለን እንኑር የእሚል ነው ።

 

ይኽ ሳይንሳዊ የባሕል አንፃራዊነት ምልከታ ግን ፤ አንዳንድ ግዜ በአንዳንድ ሰዎች ፤ ትንሽ ገፋ ይደረግና ፤ የባሕል ልዩነትን እንደ መንፈሳዊ ቀኖና ልዩነት ወይንም ባሕልን ሊሻሻል እና ሊለወጥ እንደ እማይችል እሴት በማየት ፤ ለምሳሌ ፦ ዓለም ዓቀፋዊ ሰብዓዊ እሴቶችን ኹሉ ሳይቀር ፤ የባሕልን ልዩነት ለማክበር ሲባል እንዲሻሩ የእሚጠይቅ ይሆናል ፦

 

“ፅንፈኛ የባሕል አንፃራዊነት ፤ ማንኛውም የስነ ምግባር  ትክክለኛነት ወይንም ገዢነት መመዘን የአለበት ከእየ ባሕሉ አንፃር ነው ማለት ይፈልጋል።”

 

“Radical cultural relativism would hold that culture is the sole source of the validity of a moral right or rule. [49]“

 

በእዚኽም አካኼዳቸው ፤ ፅንፈኛ የባሕል አንፃራዊነት ምልከታ አራማጆች ፤ ባሕል አንፃራዊ በመሆኑ ፤ ከባቢያዊ ባሕላዊ እሴቶችን የእሚጋፋ ማንኛውም አመለካከት ፀረ ባሕል በመሆኑ ወይንም የባሕል ወረራ ወይንም ቀኝግዢ (Cultural Imperialism) በመሆኑ ልንታገለው ይገባል ይላሉ ።

 

በሌላ አገላለፅ ፤ ፅንፈኛ የባሕል አንፃራዊያን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ያሉ ፤ ኹሉም ሰው ሊቀበላቸው ይገባል የእሚባሉ ምንም ዓይነት እሴቶች የሉም ፤ ይኽን ማለትም የባሕል ወረራ (Cultural Imperialism) ነው ይላሉ ።

 

ይኽ ደግሞ ፤ ባሕልን የስሁትነት እና የእውነት ብቸኛ መመዘኛ መሳሪያ በማድረግ ፤ በአንድ ባሕል ውስጥ ፤ ወንድ እና ሴት ልጅ እኩል አይደሉም የእሚል ባሕላዊ እሴት ከአለ ፤ የዘመናዊ ዴሞክራሲያዊ መርህ ፤ ሰው ኹሉ በሰውነቱ እኩል በመሆኑ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቱ በእኩልነት ይከበርለት ማለት ወይንም በወንድ እና ሴት እኩልነት የእያማያምነውን ባሕል ልክ አይደለኽም ብሎ መንቀፍ የባሕል ወረራ ነው ወደ እሚል ዓይነት ድምዳሜ ይመራል ።

 

ወይንም የሴት ልጅ ግርዛት ፤ ለሴት ልጅ ስነ ምግባር አስፈላጊ ነው የእሚለውን ባሕል ፤ ይኽን መሰሉ ባሕል ፤ ጎጂ ባሕል ነው ብሎ መንቀሳቀስ የባሕል ወረራ ነው ብሎ ያስብላል ። በአጠቃላይ ባሕል ፤ ምንም ይኹን ምን ፤ ይኽን ባሕል መተናኮስ ፤ ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ጥቅም እንኳን ቢኖረው መደረግ የለበትም የእሚል ነው ፤ የባሕል አንፃራዊያን ፅንፈኝነት ።

 

ይኽ አካኼድ ደግሞ የባሕል አንጻራዊነት ምንም እንኳን ሳይንሳዊ ነኝ ቢልም ፤ ባሕልን አጓጉል በማግነን እና ፋይዳውንም በማወሳሰብ ፤ ባሕል የእሚጠየቅ ፣ የእሚፈተሽ እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የእሚሻሻል ሰአይሆን ፤ ያለ እና የነበረ ፤ በአለበትም ሊቀጥል የእሚገባው ፤ ማሕበራዊ ተቋም እንደ ሆነ አድርጎ በማቅረብ ፤ ባሕልን ጸረ ህዳሴ ያደርገዋል።

 

ለምሳሌ ፦ የዘመናዊ ስልጣኔ ወይንም የህዳሴው መሠረት የሆኑ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች  ፤ ሰው ከባሕል ፣ ከቋንቋ ፣ ከኃይማኖት ፣ ከዘር ወይንም ከሌሎቹ የቅርፅ ልዩነቶቹ በአሻገር በሰውነቱ እኩል ነው በእሚለው አስተሳሰብ (Cultural Universalism) ላይ የተመሠረተ ነው ፦

 

“የዘመናዊው ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ስረዓት ደግሞ ሰዎች ኹሉ ፤ በባሕላዊ ወይንም ስፍራዊ ልዩነታቸው ሳይወሰኑ ፤ በአንድነት የእሚጋሩዋቸው ፤ ሰብዓዊ (ሰዋዊ ፥ ሰው በመሆናቸው) የእሚባሉ መብቶች ፤ ባለቤት እንዲሆኑ የእሚያስችሉዋቸው ወጥ የሆኑ አንድነት/ተመሳሳይነት አላቸው በእሚለው ውጥን ላይ ነው ።”

 

“The modern system of international human rights treaties is based on the concept of universalism which holds that there is an underlying human unity which entitles all individuals, regardless of their cultural or regional antecedents, to certain basic minimal rights, known as human rights. [50]“

 

ከእዚኽ መረዳት እንደ እምንችለው ፤ የፅንፈኛ የባሕል አንፃራዊነት አስተሳሰብ ፤ ልዩነትን የማክበር ጉዳይ ብቻ ሰአይሆን ፤ ልዩነትን በማክበር ስም ብዙ ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ፋይዳ የአላቸውን ፤ የሰብዓዊ መብት ዓይነት ዓለም ዓቀፍ ድንጋጌዎችን እንኳን መግፋት የእሚፈልግ ፅንፍ ነው ።

 

ምንም እንኳን ፤ ለአንዳንድ ሰው ይኽን መሰሉ በኃላዊ አንጻራዊነት እጅግ ኋላ ቀር እና የተሸነፈ አስተሳሰብ ነው ብሎ ሊያስብ ቢችልም ፤ የሰው ልጅ በጠቅላላው ፤ ሰውን በሰውነት እኩል ነው ብሎ ለመቀበል በጠቅላላው የዘገየ መሆኑን ስንረዳው ፤ አኹን በእኛም ዘመን ፤ አክራሪ የባሕል አንፃራዊያን ኃሳብ ምን ያህል አፍራሽ ሚና ሊጫወት እንደ እሚችል ያሳየናል ።

 

ሰው ኹሉ በሰውነቱ እኩል እና ክቡር በመሆኑ ማንኛውም መንግሥት የዜጎቹን በህይወት የመኖር መብት ማክበር አለበት ብሎ የዓለም ሕዝብ መስማማት ላይ የደረሰው ከ5ሺ ዓመታት በእሚበልጠው የፖለቲካ እድሜ ውስጥ ገና ‘ትናንትና’ በ 1950 አከባቢ ነው ፦

 

“እስከ ኹለተኛው የዓለም ጦርነት ድረስ ፤ የግለሰቦች የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ጉዳይ ፤ የአንዲት ሐገር ሉዓላዊ ክልል ተደርጎ በመወሰድ ለእየ ሐገራቱ አስተዳደር መልካም ፈቃድ የተተወ ጉዳይ ነበር ። በኹለተኛው የዓለም ጦርነት የተከሰተው ጭፍጨፋ ይኽን ነባራዊ ኹኔታ እንዲቀየር አነሳስቷል ።”

 

“Until the Second World War, the protection of human rights of individuals was seen as a sovereign prerogative of the state and therefore as a domestic rather than an international concern. The atrocities of the Second World War provided the impetus to change the status quo. [50]“

 

እንደ ዓለም ሕዝብ ከመሰል ኋላ ቀርነት ዱር ውስጥ ገና እየወጣን ስለሆነ ፤ የፅንፈኛ የባሕል አንፃራዊነት ፤ ልዩነትን ማክበር በእሚል ካባ የእሚቃወማቸው ኢከነሚያዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ባሕላዊ መሻሻሎች ለአልተዘጋጁ የለውጥ ኃይሎች የእሚደቅኑዋቸው ፈተናዎች በቀላሉ የእሚታዩ አይደሉም ።

 

ጽንፈኛ የባህል አንጻራዊያን በነገሡበት ፤ በአርብቶ አደር ጋጣ የእሚያልፍ ትልቅ እና ሰፊ መንገድ ሲሰራ ፤ መንገዱ ለአርብቶ አደሩ ማሕበረሰብ ምን ዓይነት ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ፋይዳ ያመጣል ሰአይሆን ፤ ለዘመናት የቆየውን የአርብቶ አደርነት የኑሮ ዘይቤ አስቀየረ በእሚል ይተቻል ፣ የዘመናዊ ልብስ እና ሌላም ልማድ ወደ ኋላ ቀር ማሕበረሰብ ደጅ ሲደርስ ፥ እራቁት የመኖር ባሕላዊ እሴታቸውን ተፈታተነ በእሚል ይተቻል ።

 

በአጠቃላይ ፤ ይኽ በዘመናዊ የማሕበራዊ ሳይንስ ጥናት የተገኙ እና አዋጭነታቸው በተግባር የተፈተኑ ስልቶችን ፤ የባሕልን አንፃራዊ ልዩነት ለማስጠበቅ በእሚል ለማስቀረት የእሚደረገው ጥረት ፦ ስነምግባር አጠፋ ፣ ኃይማኖት አሳደፈ ፣ ጎጂ ባሕል አስተዋወቀ ፣ ወዘተ ፤ በእሚል የተለያየ መልክ የአለው ‘ሳይንሳዊ’ ተቃውሞ መልክ የያዘ ነው ።

 

እነ እዚኽ መሠረት የለሽ ተቃውሞዎች ደግሞ ፤ በለውጡ ኃይል በአግባቡ ካልተመከቱ እና ሕዝብ የለውጡን ሰአይሆን የተቃውሞ ኃሳብ ከገነነበት ፤ የለውጡ ኺደት ወይንም ህዳሴው ቀላል የእማይባል እና ዓመታትን የእሚጠይቅ ፤ አንዳንዴም ለውጡን የእሚቀለብስ ፈተና ይገጥመዋል ።

 

ከላይ እንደ አልነው ፤ ከእዚኽ ሳይንሳዊ መልክ ከአለው ተቃውሞ በአሻገር ፤ የህዳሴው መገለጫ የሆኑት እንደ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያሉት አስተሳሰቦች እና አደራረጎች ፤ ተቃውሞ የእሚደርስባቸው ፥ ሕዝብ በያዙዋቸው ልማዳዊ አስተሳሰቦችም ነው ።

 

እዚኽ ንዑስ ክፍል መግባያ ላይ እንደ አልነው ፤ እንደ ባሕል ያሉ ሰው ሰራሽ ተቋሞች ያለ ቅድመ እቅድ የመፈጠር እና እጅግ የተባዛ አቅም የመያዛቸው ጉዳይ ብቻ ሰአይሆን ፤ አንድ ግዜ ከተመሠረቱ እና በአንድ ማሕበረሰብ ፖለቲካዊ ፣ ኢከነሚያዊ እና ማሕበራዊ መዋቅር ውስጥ ተሰራጭተው ከጎለበቱ በኋላ ፤ ራሳቸውን እንደ ግዜ አመጣሽ ክስተት ሰአይሆን ፤ ከጥንትም የነበሩ እና ሊነኩ የእይማገባ በማስመሰል ፤ አዎንታዊ ለውጦችን የእሚጋፉ ይሆናሉ ።

 

አክራሪ የባሕል አንፃራዊያንን አመቺ መደበቂያ ስፍራ የእሚሰጣቸውም ፤ እንደ እዚኽ ያሉት ያልተመረመሩ ልማዳዊ እና ሰፊ ሕዝባዊ መሠረት የአላቸው ፤ በአንድም በሌላ መልኩ ባሕላችን ሳይጠየቅ ፣ ሳይመረመር ፣ ሳይፈተሽ ፤ በአለበት መቀጠል አለበት የእሚሉ ፤ አስተሳሰቦች በመኖራቸው ነው ።

 

ይኽ አመለካከት ግን ልክ አይደለም ፤ ምክንያቱም ፦ በዓለም ላይ የእሚገኝ የትኛውንም ባሕል ፣ ኃይማኖት ፣ ልማድ ፣ ወዘተ ፤ ብንወሰድ በአንድ ወቅት ያልነበሩ እና ግዜ አመጣሽ መሆናቸውን ለመገመት ወይንም ለመረዳት ብዙም አንቸገርም ።

 

ስለ ሁኔታው ትንሽ አትኩረት ሰጥተን ስናስበው ፤ ባሕል የእሚሆነው በአንድ ዘመን ላይ የነበረ የስልጣኔ ደረጃ እንደ ሆነ እንረዳለን ። መጓዝ መሠረታዊ የሰው ተፈጥሮዋዊ ባሕሪ ቢሆንም ፤ የመጓጓዟ መንገዶች ግን ከግዜ ወደ ግዜ እየተሻሻሉ ዛሬ የደረሱበት ደረጃ ላይ ደርስዋል ።

 

ስለ እዚኽ ፦ አንድ ሰው ፤ ከጥንት አባቶቼ በፈረስ ነው ይጓዙ የነበረውና አኹን በሞተር በእሚነዳ በማንኛውም የመጓጓዣ መኪና አልሳፈርም ቢል ፤ ብዙም ተቀባይነት እንደ እማይኖረው ፤ አንዳንድ ባሕላችን ፣ ቅርሳችን ፣ ወጋችን ፤ የእምንላቸው ነገሮች ፤ በአንድ ወቅት የተሻለ አሰራር ስለ ነበሩ የዳበሩ እንጂ የተለየ ልዩ እሴት የሌላቸው እንደ ሆኑ እንዘነጋለን ።

 

ከእንደ እዚኽ ዓይነት መደናገር ሊያስከትል ከእሚችለው አሉታዊ ተፅኖ ለመላቀቅ ፤ በእኔ እምነት ፤ ስልጣኔ ፣ ቴክኖሎጂ ፣ ዘመናዊነት እና ባሕል የእሚባሉት ፅንሰ ኃሳቦች ውስጥ ያሉትን ፤ ተዛምዶ እና ልዩነቶች መረዳት ተገቢ ይመስለኛል ።

 

በአማርኛ ስልጣኔ የእምንለው በእንግሊዘኛ Civilization የእሚለውን ቃል ነው ፤ የእዚኽ የኢንግሊዘኛ ቃል ስርወ ቃሉ civil  የእሚል  የላቲን መሠረት የአለው ቃል ሲሆን ፤ በጋራ በሰላማዊ ኹኔታ የእሚኖር ሰውን ወይንም በእዚኽ ኹኔታ በአንድ ላይ የእሚኖሩ ሰዎች ወጋቸውን ፣ ሕጋቸውን ፣ ወዘተ ፤ የእሚወክል ቃል ነው ።

 

ይኽ ቃል ስልጣኔ (Civilization) ለእሚለው ቃል መሠረት የሆነበት ምክንያት ፤ የመጀመሪያው የቃሉ አንፃራዊ ትርጉም ፤ በአግባቡ በተቀነባበረ ከተማ ወይንም መንደር ውስጥ ከመኖር ይልቅ ፤ በኋላ ቀር ኹኔታ ተበታትነው የእሚኖሩትን ሰዎች የእሚንጠል ወይንም የእሚለይ ወካይ ቃል በመሆኑ ነው ።

 

 በእየ ደኑ እና በየዱሩ የእሚኖሩ ማሕበረሰባት ፤ በአንድ ከተማ ወይንም መንደር ፤ በሆነ ስረአት እና ሕግ እየተመሩ ከእሚኖሩ ሰዎች አንፃር ኋላቀር ወይንም ያልሰለጠኑ በመሆናቸው ፤ ቃሉ ስልጣኔ ለእሚለው ኃሳብ መነሻ ሆኗል   ።

 

ከእዚኽም በመነሳት civilization ፦ የመላቅ ፣ የመሻል ፣ የመጥራት (rarefied) እና የበለጠ የመሆን ትርጉም በዋናነት ያንጸባርቃል ። 

 

የአማርኛውም ቃል ፤ ስልጣኔ ፤ ስረወ ቃል ስልጥን የእሚል ሲሆን ፤ መላቅን ፣ መሻልን እና የበላይ መሆንን የእሚያሳይ ነው ። በእዚኽ አንፃር ፤ በአማርኛው ቃል እንደምታ ፤ በማንኛውም ረገድ የተሻለውን ፣ የተራቀቀውን እና ምርጡን ነገር ኹሉ ስልጣኔ እንለዋለን ።

 

 የሰው ልጅ ፤ የእሚያደርገውን ነገር በሙሉ የእሚያደርገው መልካም የእሚለውን ነገር ለማግኘት በእሚል ታሳቢ ነው በእሚለው ኃሳብ ላይ ከተስማማን ፤ ስልጣኔን ስልጣኔ የእሚስብለው አዲስ የሆነ እና የተሻለ አዎንታዊ ፋይዳ የአለው አደራረግ መሆኑ ነው ።

 

ልብስ መልበስ ልብስ ከአለ መልበስ የእሚሻል ከሆነ ፤ ልብስ መልበስ አንድ የስልጣኔ ደረጃ ነው ። ኃሳብን በጽሑፍ ማስፈር ከአለ ማስፈር የተሻለ ፋይዳ ከአለው ፤ ኪነ ጽሑፍን ማዳበር አንድ የስልጣኔ ደረጃ ነው ።

 

ስለ እዚኽ  ፤  በጤናማ የአዕምሮ ፍርድ ፤ ለሰው ልጅ ኑሮ ፣ ጤና እና ደስታ የተሻለ የእሚባለውን አሰራር እና አደራረግ ጽንሰኃሳብ ስልጣኔ እንለዋለን ።

 

 እንግዲኽ ፤ በዋናነት ስልጣኔ የእምንለው የአስተሳሰብ እመረታ ሲሆን ፤ ይኽ አዲስ የእሚመጣው አስተሳሰብም ፤ የሰውን ልጅ ኹለንተና ፤ ለተሻለ ኑሮ ፣ ጤና እና ደስታ ሲያበቃ ነው ። ስለ እዚኽ ስልጣኔ ፤ እየበዛ የእሚኼድ ከዘመን ወደ ዘመን በልቦናችን ላይ እየተሻሻለ እና እየጠራ የእሚኼድ የእውቀት ብርሀን  ነው ።

 

ቴክኖሎጂ ደግሞ አንድን የስልጣኔ ደረጃ የእሚያስችል የአሰራር ዘዴ ነው ። ስልጣኔ ያመጣውን ፤ የአስተሳሰብ እመርታ ወደ ተግባር የእምናወርድው በቴክኖሎጂ ነው ።

 

ልብስ መልበስን ቴክኖልጂ አያስተምረንም ፤ ውስጣዊ ግንዛቤያችን ወይንም ስልጣኔያችን ፤ ልብስ መልበስ እንደ አለብን ከአሳመነን በኋላ ፤ ቴክኖሎጂያችን ፤ ልብሱን እንድ እናመርት ያስችለናል ።  

 

  ስለ እዚኽ ፦ ቴክኖሎጂ ፤ ስልጣኔ  ወይንም የአስተሳሰብ እመርታ የፈጠረው ግብ የእሚተገበርበት ክህሎት፣ ብልኃት እና ዘዴ ነው ።

 

ከእዚኽ የተነሳ ፤ በአንድ የስልጣኔ መስመር ውስጥ በጣም ብዙ ቴክኖሎጂያዊ ደረጃዎች ይኖራሉ ።

 

ሰው ልብስ መልበስ ጠቃሚ ነው ብሎ ከወሰነ ወይንም ልብስ መልበስን እንደ መልካም ነገር ከቆጠረ በብዙ ሺ ዓመታት ተቆጥረዋል ፤ ልብስ የእምናመርትበት ቴክኖሎጂ ግን ፤ በተፈጥሮ የአለውን ቅጠል ምንም እሴት ሳንጭምርበት አንስቶ ከማገልደም ጀምሮ አኹን እስከ አለንበት በከምፒውተር የታገዘ ልብስ ማምረቻ ማሽን እስከ መጠቀም ድረስ የተለያየ ነው ። የመልበስ ስልጣኔ በእየ ዘመኑ የእሚያድጉ የተለያዩ ልብስን የማምረቻ ቴክኖሎጂዎችን ፈጥሯል ።

 

ከእዚኽ የተነሳ ፤ ዘመናዊነት ምንም እንኳን ከስልጣኔም ጋር ሊያያዝ ቢችልም በዋናነት  ግን ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር የተያያዘ ነው ።

 

ዘመናዊነት ፤  በአንድ ዘመን የእሚኖር ሕዝብ ፤ በእርሱ ዘመን ወይንም ከእርሱ በፊት የእሚኖሩ ፤ በየትኛውም የዓለም አከባቢ የእሚኖሩ ሕዝብ ፤ የደረሱበትን የስልጣኔ እና ስልጣኔውንም ያስቻሉበት ወይንም ያስቀጠሉበትን የተሻለ የእሚባለውን ቴክኖሎጂ ባለቤት እና ተጠቃሚ መሆን ማለት ነው ።

 

 ትናንት የሰው ልጅ ፤ ልብሱን በቤቱ ሸምኖ ይለብስ ከነበረ እና ዛሬ አብዛኛው ልብስ ፤ ቁልፉ ከአንዱ የዓለም ክፍል ፣ ዚፑ ከሌላው የዓለም ክፍል ፣ ጨርቁ ከሌላ የዓለም ክፍል መጥቶ ፤ በሌላው የዓለም ክፍል ደግሞ በአንድ ትልቅ ፋብሪካ የእሚመረትበት ዘመን ከሆነ እና ይኽም አመራረት ለሰው የተሻለ ጥቅም የእሚሰጥ ከሆነ ፤ በፋብሪካ በዘመናዊ መልክ የተመረተውን ልብስ የእሚለብስ ሰው ፤ በቤቱ እራሱ የሸመነውን ልብስ ከእሚለብሰው ሰው ይልቅ ዘመናዊ ነው ማለት ነው ።

 

 ባሕል የእምንለው ወይንም ባሕል የእሚሆነውም ፤ በአንድ ዘመን የመጣ ስልጣኔ እና ስልጣኔውም የተተገበረበት ቴክኖሎጂ ነው ። በአንድ አከባቢ እና ሕዝብ ፤ ለብዙ ግዜያት የቀጠለ ስልጣኔ እና ቴክኖሎጂ ባሕል ይሆናል ።

 

ከጥንት ጀምሮ የእሚሉት አንዳንድ መሳጭ አባባሎች ፤ ባሕልን ተፈጥሮዋዊ እና ብቸኛ መንገድ የማስመሰል ባሕሪ ቢኖራቸውም ፤ ባሕል ፥ በአንድ ወቅት በአንድ አከባቢ ፤ በወቅታዊ አማራጭነት የተጀመረ የስልጣኔ አስተሳሰብ ወይንም አደራረግ(ቴክኖሎጂ) ነው ።

 

ባሕል ተፈጥሮዋዊ ወይንም መለኮታዊ ነገር አይደለም ፤ በአንድ ወቅት ተመራጭ የነበረ አደራረግ ወይንም ፋሽን ነው ። ባሕልን ለየት የእሚያደርገው ፤ ለረዥም ግዜ ከመዘውተሩ የተነሳ በሰዎች ስብዕና ውስጥ ጠንካራ መሠረት መያዙ ነው እንጂ ባሕል የአንድ ወቅት ስልጣኔ ያመጣው አደራረግ ነው ።

 

እንደ ሰው ግን ፤ ቃላትን እንደ አውዱ እያዛመድን ፤ ተመሳሳይ ቃላት እንኳን የተለያየ ትርጉም እንዲኖራቸው የማድረግ ፤ ላቅ ያለ የቋንቋ ችሎታ ያለን በመሆኑ ፤ አንዳንድ ግዜ ወይንም በተለያየ አውዱ አንዱ ጽንሰ ኃሳብ የእሚወክለው ቃል ሌላውን ጽንሰ ኃሳብ በወከለበት ኹኔታ ስንጠቀምበት እንገኛለን ።

 

አንዳንዴ ስልጣኔ ስንል ፤ ቴክኖሎጂ ማለታችን ይሆናል ወይንም ዘመናዊ ስንል አንዱን ቴክኖሎጂ እያመለከትን ነው ። አንዳንድ ግዜ ደግሞ አንድ ባሕልን ስንገልጽ ስለ አንድ የሆነ የስልጣኔ ደረጃ እያወራን ነው ። ስለ እዚኽ ፤ ጽንሰ ኃሳቦች የአላቸውን ልዩነት ያኽል ተዛማጅነትም ስለ አላቸው ፤ ትርጉማቸው ቃላቶቹን እንደ እምንጠቅምበት አውድ የእሚወሰኑበትን ኹኔታ ይፈጥራል ።

 

እንደ እዚኽ ያሉ የአውድ ልዩነቶችም ስልጣኔን ብሎም ዘመናዊ ቴክኖሎጂን እንዲሁም ባሕል ጋር ተያይዘው የእሚቀርቡ ትችቶች ፤ ለምሳሌ ፦ ስልጣኔ ባሕላችንን እያበላሸ ነው ሲባል ፤ ምንም እንኳን አባባሉ አዲሱ እና የተሻለው የስልጣኔ ደረጃችን ያረጀውን የስልጣኔ ደረጃችንን እያስረጀ ነው የእሚል እንደምታም ሊኖረው ቢችልም ፤ ኃሳቡ የተገለፀበት አግባብ ግን እየተጠቃን እና እየተሸነፍን ስለ እሚያመስለው ፤ አባባሉን አዟዙሮ ለመገንዘብ ለእማይጥር ሰው አሉታዊ ስሜት በመጫር ወደ አልተገባ አቅጣጫ ሊመራው ይችላል ።

 

በእርግጥ አዲስ ስልጣኔ ኹሉ እንከን የሌለበት እና ፍፁም ነው ማለት አይደለም ፤ ልክ አዲስ ነገር ኹሉ መጥፎ እንዳልሆነው ኹሉ ።

 

እንዲያውም ፤ አንዳንድ ግዜ ጥንታዊ ነገር የተሻለ በአይሆንም ፤ የቆየ በመሆኑ ብቻ የእሚፈጥርብን ስሜታዊ እሴት (Sentimental Value) አለው  ።

 

አሮጌ ፣ አላስፈላጊ ብለን የእምንጥላቸው ነገሮች እንዳሉ ኹሉ የጥንቱን የጠዋቱን ብለን ፈልገን ፣ በርብረን የእምናወጣቸው ነገሮች አሉ ።

 

ለምሳሌ ፦ የጥንቱን የብራና ላይ ጽሑፍ ስናይ ፤ አባቶቻችን ኃሳባቸውን በጽሑፍ ለማስፈር ፦ ክስተብርኃኑን (Enlightenment) ያገኙበት ፣ ከዛም ቆዳውን ያለሰለሱበት ፣ ቀለሙን የቀመሙበት  ፣ ይኽ ኹሉ ፈተና እየ አለባቸውም ራሳቸውን በእውቀት አዳብረው ኃሳባቸውን ለመግለፅ አድካሚውን የብራና ጽሑፍ ለመጻፍ ያሳዩት ትጋት ፣ ወዘተ ፤ ተደማምሮ ፤ ምንም እንኳን ይኽን የብራና ጽሑፍ ለመጻፍ የታለፈው ያ ኹሉ ውጣ ውረድ ዋና ውጤት የሆነው ኃሳብ ወይንም ጽሁፉ በእጅ ስልካችን በአንድ ትንሽ ሰነድ ውስጥ ቢኖርም ፤ ወደ ሚውዝየም ኼደን ይኽን ብራና በመስታወት ሳጥን ውስጥ ተቀምጦ ለማየት ደስ እያለን ብር ከፍለን እንጎበኘዋለን ።

 

የእዚኽ ጥንታዊ የስነ ጽሑፍ ባሕላችን ውበት ወይንም የእዚኽ የአንድ ዘመን ስልጣኔያችን ውበት የመነጨው ግን ፤ እንደ ፈር ቀዳጅነቱ ካስተዋወቀው የቴክኖሎጂ እምረታ እንጂ ከሌላ ነገር አይደለም ። በዓይነ ህሊናችን ራሳችንን እነርሱ ወደ ነበሩበት ዘመን በመውሰድ ፤ የነበረባቸውን ኢከነሚያዊ ፣ ፖለቲካዊ እንዲኹም የቴክኖሎጂ ውስንነት አስበን ፤ ይኽን ተግዳሮት የተወጡበት አካኼድ ወይንም የአስተሳስባቸው ተሻጋሪነት እያስድሰተን እንአደንቀዋለን እንጅ ፤ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዘን ፤ የብዙ ዘምን ድካም ውጤት የሆነውን የእነርሱን ሥራ ፤ በእዚኽ ዘመን በጣም በርካሽ እና በፍጥነት ልንሰራው እንደ እምንችል ሳይገባን ወይንም ሳንአውቀው ቀርተን አይደለም ።

 

የብራናውን ዘመን ስልጣኔያችንን እንወደዋለን ማለትም ፤ በእዚኽ ዘመን እንደ ገና የኋሊት አሽቆልቁለን ፤ የወረቀት እና የኤልክትሮኒክ መጻፊያዎችን ትተን ወደ ብራናው እንመለስ ማለትም አይደለም።

 

ያለፈው ወይንም ጥንታዊ አደራረግ ፥ ስልጣኔ ወይንም ባሕል ከሆነው እና እንደ ብራና ላይ ጽሑፍ ፤ ከነበረበት ኹኔታዊ ውስንነት ራሱን የአሻገረበትን አካኼድ እያደነቅን በአለበት ስንወደው ፥ አንዳንዶቹ ባሕሎቻችን ደግሞ መሻሻል ወይንም መተው የእሚገባቸው ፤ በጣም የተወሰኑት ደግሞ ባሉበት መቀጠል ያለባቸው  መሆናቸውን እንገነዘባለን ።  

 

አንዳንዱ ባሕል ደግሞ ጎጂ ስለ ሆነ  ሊወገዝ እና ፈጽሞ ሊተው የእሚገባው  ልማድ ነው ። ከሴት ልጅ ግርዛት በላይ ለእዚኽ ተገቢ ምሳሌ ማቅረብ አይቻልም ።

 

ሴት ልጅን መግረዝ ፤ ጥሩ ስነምግባር ያላብሳታል ብለው የአሰቡ የተለያዩ ሕበረተሰቦች ፤ በዓለም ዙሪያ ሴት ልጆቻቸውን ለረዥም ግዜ ሲያስገርዙ ኖረዋል ። አኹን የደረስንበት ሳይንሳዊ ዕውቀት ደግሞ ፤ ሴት ልጅን መግረዝ ፤ በሰዓቱ አካሏ በመቁሰሉ ከእሚሰጣት ህመም በአሻገር መልካም ባሕሪ እንዲኖራት ምንም አይፈይድም ብሎ አሳውቆናል ።

 

ስለ እዚኽ ፦ ሴት ልጅን መግረዝ ፤ የቆየ ፤ በተለያዩ የዓለም ክፍል ላይ ባሉ ማሕበረሰባት የእሚዘወተር እና ብዙ ትክክል ነው ብለው የእሚያምኑበት ሰዎች ቢኖሩም ፤ አንዳንዴም የግርዘቱን ሥራ ሞያዬ እና የገቢ ምንጨ ብለው የያዙት ሰዎች ከጥቅማቸው አንጻር ልማዱ እንዲቀጥል ብዙ ሊሉ ቢችሉም ፤ የሴት ልጅ ግርዛት ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ጎጂ ልማድ ተብሎ ፤ እንዲያውም በአንዳንድ ሐገራት በሕግ የእሚያስቀጣ ድርጊት ሆኗል ። ስለ እዚኽ ፦ ጎጂ ባሕሎች እንደ አሉና እነ እዚኽንም ጎጂ ባሕሎች ለማስወገድ መሥራት ተገቢ መሆኑን ማወቅ አለብን ።

 

ኹለተኛው ፦ አንዳንዱ ባሕል ፤ በይዘቱ ምንም ጉዳት በአይኖረውም ፤ ከደረስንበት ዘመን አንጻር ጎታች ፣ አዘግይ እና እማያዋጣ ስለሆነ ሊሻሻል ወይንም ሊለወጥ ይገባል ።

 

ኩታ ከላይ የእሚደረብ ባሕላዊ ልብስ ነው ፤ ቀለል ባለ አማርኛ ነጠላ ወይንም ጋቢ ሆኖ ፤ በሆነ የአስተጣጠፍ መንገድ ከላይ የእሚደረብ ልብስ ነው ።

 

አኹን በአብዛኛው ኢትዮጲያ ኩታ በኮት ተተክቷል ። ምክንያቱም ፦ ኩታ የእሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ኹሉ ፤ ኮት በተሻለ ኹኔታ ስለ እሚሰጥ ። ኩታም ኮትም ዓላማቸው ፤ በዋነኛነት ሰውነትን ማሞቅ ነው ። አንድ ግዜ ሰውነት ከሞቀ በኋላ ግን ፤ ኩታ ዚፕ ወይንም ቁልፍ ስለ ሌለው ትንሽ ነፋስ ቢያስፈልግ ፤ የአለው አማራጭ ወይ ኩታውን እንዳለ ማውለቅ ነው ከአልሆነም እንዳለ መተው ነው ።

 

ኮት ወይንም ጃኬት ግን ቁልፍ እና ዚፕ ስለ አለው ፤ እንደ አየሩ ኹኔታ በመክፈት እና በመዝጋት አየር ከአስፈለገ ማንሸራሸር ከአልሆነም ማስቀረት ይቻላል ። ሲለበስ የአለው ቅለት ፣ ለማጠብ መመቸት ፣ መርከስ ፣ ቆሻሻ መቻል ፣ ወዘተ ፤ እያልን ኮት እና ኩታን አወዳድረን ፤ ኮት ከኩታ እንደ እሚሻል ማሳየት እንችላለን ።

 

ስለ እዚኽ አንድ አዲስ ከውጭ የመጣ ኮት የእሚባል ነገር ፤ ከኩታ እጅግ ተሽሎ ፤ ለብዙ ዓመታት አባቶቻችን ሲጠቀሙበት የነበረውን ኩታ በማስረጀት ኮትን በማዘመን ወይንም የበለጠ ጠቃሚ በማድረግ ፤ በፈቃዳችን የቆየውን ትተን አዲሱን እንድንይዝ አድርጎናል ፤ ይኽም አንዳንድ ባሕሎች ዘመን አምጥቶ ዘመን የእሚሽራቸው ነገሮች መሆናቸውን ያሳየናል ። 

 

ኩታም በግዜው ፤ ከቆዳ የተሰሩ ለውበትም ፣ ለጠረንም ፣ ለምቾትም የእማይመቹ የነበሩ ደበሎዎችን ተክቶ ወይንም በአዲስ እና የተሻለ አማራጭነቱ ቁርበትን አስረጅቶ ነው በኮት እስኪተካ ባሕል ሆኖ የቆየው ።

 

ሰውን ኹሉ ፤ እንዴት ኩታ ትለብሳላችሁ ፤ ለምን ኮት አትለብሱም እያልን ግልፅ ማስገድድ እስከ አልአደረግን ፤ ሰዎች አማራጭ ቀርቦላቸው ፤ ልክ ቁርበቱን ትተው ወደ ኩታ እንደ መጡት ኹሉ ፤  ኩታን ትተው ወደ ኮት ቢዞሩ ፤ ምንም ችግር የአለው አይመስልም ።

 

ፅንፈኞች ግን ፤ የካፒታሊዝም ኢምፔሪያሊዝም ፤ በፋብሪካ የእሚመረቱ ምርቶቹን ለማራገፍ እና የሽመና የጎጆ እንደስትሪያችንን በማክሰም ባሪያ ሊያደርገን ነው ፣ ወዘተ ፤ ዓይነት ፤ ኢከነሚክስ ይሁን ፅንፈኛ የባሕል አንፃራዊነት ያልለየ ነገር በማቅረብ ፤ ይኽን መሰሉን ሽግግር መቃወም ዋና ተግባራቸው ያደርጉታል ።

 

በተነፃፃሪ ደግሞ ፤ አንዳንዱ ባሕል ዘመን ተሻጋሪ ነው  ። በእኛ ሐገር ኹኔታ የአቦጊዳ ፊደል የአለው እሴት ፤ በዓለም ላይ ካሉ ፊደላት ኹሉ ጋር ተነፃፅሮ የራሱ አቅም ስለ አለው ፤ አኹን በዓለም ላይ ያሉ ፊደላት የአቦጊዳን ፊደል በቀላሉ ሊተኩት አይችሉም ። ምክንያቱም ፦ በዓለም ላይ ካሉ የተለያዩ የመጻፊያ መንገዶች ፤ በቅለት እና ብዙ ቋንቋዎችን ቋሚ በሆነ መልኩ በመወከል ፣ ያነባበብ ስህተትን በማጥፋት ፣ ወዘተ ፤ ከየትኛውም የፊደል ስረዓት የእሚበልጥ ከአልሆነ የእይማይተናነስ ሥራ መሥራት ይችላል  ።

 

ስለ እዚኽ ፦ የአቦጊዳ ፊደል ብዙም ጥብቅና ሰአያስፈልገው ፤ በያዘው ዘመን ተሻጋሪ እሴት ፤ ከብራና ወደ ወረቀት ስንሸጋገር እንደ ገናም ከወረቀት ወደ ከምፒውተር እና ኤልክትሮኒክ መጻፊያዎችም ስንሸጋገር ፤ ፋይዳው ይልቁንም እየጎላ እንጂ እየደበዘዘ በአለመኼዱ ፤ የባሕል አንፃራዊያን ድጋፍ ሰአያስፈልገው ፤ ከመቼውም ግዜ በላይ ጠንክሮ ፤ ከዘመኑ ጋር ዘምኖ አለ ።

 

ይኽን ዓይነቱን የተፍታት አመለካከት በባሕል ላይ ሊኖረን የእሚችለው ግን ፤   ባሕል መገልገያችን መሆኑን ወይንም የባሕል ዓላማው እኛን መጥቀም መሆኑን ፥ ወይንም እኛ የባሕላችን ተጠቃሚዎች እንጂ ለባሕላችን ጠቃሚዎች አለ መሆናችንን የእምንቀበል ከሆንን ብቻ ነው ።

 

ያን ግዜ ፤ ባሕላችን ከጠቀመን ልናስቀጥለው ፣ ካጎደለብን ልናሻሽለው ፣ ከጎዳን ደግሞ ልናስወግደው የእሚገባ አንድ ቁስ (ማሕበራዊ እና የእማይዳሰስ ቁስ)  አድርገን በመቁጠር ፤ የባሕላችን ተገዢ ሰአይሆን የባሕላችን ተጠቃሚ መሆን እንችላለን   ።

 

ነገር ግን ፤ ባሕል በአንድ የዘመን ወቅት የነበረ የስልጣኔ እና የስልጣኔው ቴክኖሎጂ እንደ ሆነ ሰአይሆን ፤ እንደ አንድ ሚስጥራዊ ወይንም ምትኃታዊ ኃይል አይተነው ፤ በሳይንሳዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ እውቀት እየመዘንን ፤ ባሕላችንን ብልጫ በእሚሰጠን መልኩ ከማስተዳደር ይልቅ ፤ በአለበት እንዲረግጥ ከአደረግነው ፤ ባሕላችን የእኛ መሳሪያ ሰአይሆን እኛ የባሕላችን መሳሪያ እንሆናለን ።

 

እንዲኽ ዓይነቱ ዝበታዊ (Superstitious) የባሕል ምልከታ ደግሞ ፤ የባሕል ወይንም የስልጣኔ ፋይዳው የሰውን ልጆች ህይወት ማሻሻያ መሳሪያ መሆኑን ከመገንዘብ ስለ እማይመነጭ ፤ ሳይንሳዊ ከሆነው የባሕል እና የሕብረተሰብ አስተሳሰብ ፍፁም ተቃራኒ ፣ ፀረ  እድገት እና ልማት በመሆን ፤ በተዘዋዋሪ ራሱን ፀረ ሰው የእሚያደርግ ይሆናል ። የተሻለውን ጥቅም ለሰው የእሚከለክል ባሕል ፀረ ሰው በመሆኑ ።

 

የባሕል ጽንፈኞች ባሕላችን እንደ አይቀየጥ ወይንም እንደ አይበላሽ በእሚል ብዙ ቢሉም ፤ የሌላ ባሕል ተጽኖ ያልተገኘበት ንጹህ ባሕል ፤ እንደ ፓፓዋ ኒዊ ጊኒ (Papua New Guinea) ያሉ እና ከሕዝቡ ባሕሪ እና ከእሚኖሩበት ቦታ የተነሳ ፤ ከሰፊው የዓለም ሕዝብ ጋር ሳይቀላቀሉ ለረዥም ግዜ ተነጥለው ከቆዩ ጥቂት ኪስ ቦታዎች ከእሚኖሩ ሕዝብ በስተቀርም ፤ ማግኘት አይቻልም ። እዛም ቢኾን ፤ በዋናነት ጥንታዊውን በዱር የመኖር እና መሰል ኋላ ቀር ባሕላቸውን በዋናነት ያንፀባርቃሉ ማለት እንጂ ፤ ከሌላው ዓለም የወረሱት ምንም ተጨማሪ ባሕል የለም ማለት አይደለም ።

 

ዓለም  ፤ በንግድ ፣ በጦርነት ፣ በኃይማኖት መተሳሰር ከጀመረች በጣም ብዙ ሺ ዓመታት አልፈዋል ። በእዚኽም ትስስር ምክንያት ፤ ስልጣኔ ተወራርሰናል ።

 

የእኛ ብቻ የእምንለው ፤ ከሌላ ከማንም ምንም ያልተጨመረመበት ፤ ጽድት ንጽት ያለ ባሕል የለም ፤ ቢኖርም እንኳን በጣም ጥቂት ነው ። ከእዚያኽም በላይ እንደ አፍላል ውኃ የእሚጋልበው ግሎባላይዜሽን በእዚኽ ንጥ፟ልነት ከመኖር ፤ በግዴታ ውዴታ ማውጣቱ የእማይቀር በመሆኑ ረዥም እድሜም አይኖረውም ። ምንም እንኳን ሐገር በቀ፟ል የሆነ የእኛ ብቻ ነገር ቢኖርበትም ፤ ብዙው ባሕላችን ከሌላ አከባቢ የመጣ እና ከእኛ ጋር የተቀየጠ ነው ።

 

ለምሳሌ ፦ በአብዛኛው የአፍሪካ ልብስ ተብለው የእሚታወቁት አለባበሶች እና የጨርቅ ዓይነቶች ፥ዳሺኪ (Dashiki) ፤ ምንም እንኳን ከጥንተ ጥንተ በአፍሪካዊያን ዘንድ የነበሩ ቢመስሉም ፤ በአፍሪካ የጨርቅ ኢንደስትሪ የተመረቱ ሰአይሆን ከቀኝ ገዢዎች ፋብሪካ የመጡ እና  በአፍሪካዊ ቃና የተዘጋጁ በመሆናቸው ከቀኝ ግዛት በኋላ የመጡ እና የቀኝ ግዛት ትሩፋቶች ናቸው ።

 

ስለ እዚኽ ፦ ባሕል እንደ ማንኛውም መገልገያ ፤ እያስቀጠልነው ፤ እያሻሻልነው አንዳንዴም ከእነ አካቴው እየተውነው የእምንኼደው ፤ ወቅታዊ መገልገያችን ነው ።

 

በእርግጥ ፤ ባሕልን መፍጠር  ፣ መጠበቅ ፣ ማሻሻል ሰአይሆንም መተካት ፤ የትምህርት ኺደት ስለ ሆነ እንደ ማንኛውም መደበኛ ትምህርት ወይንም ከእዛኽ በጠነከረ ደረጃ የራሱ ፈተና አለው ።

 

መማር ቀላል ተግባር አይደለም ፤ አለመማር ከእሚያስከትለው ጉዳት ይልቅ ፤ መማር የእሚያመጣብን ፈተና ይሻላል ማለት እንጂ ።

 

“መማር ውድ ነው ካልኽ ፤ መኃይምነትን ሞክረው !”[3]

 

ባሕልም ፤ ምንም ኪሳራ ሳያስከትል በአለበት መቀጠል ከቻለ እሰየው ነው  ፤ ምክንያቱም ፦ ነባራዊ ባሕል እና አዲስ ባሕል ሲጋጩ ወይንም አዲስን ባሕል በእምንማርበት ግዜ ፤ የእሚፈጥረው ንዝረት ( Cultural Shock )  የእሚያስከትለው ፤ ኢከነሚያዊ ፣ ስነ ልቦናዊ አንድ አንዴም ፖለቲካዊ ጫና ፤ በባሕል አጥኝዎች ዘንድ በደንብ የታወቀ ጉዳይ ነው  ። 

 

ማንኛውንም መልካም ትምህርት ለመማር የእምንከፍለው ኢከነሚያዊ ፣ ስነ ልቦናዊ ወይንም ሌላ ዋጋ ፤ በኋላ ላይ ከእሚሰጠን ጥቅም አንፃር እጅግ የተሻለ እና መተኪያም የሌለው በመሆኑ ፈተናው ቀላል በአይኾንም ፤ ሊሰራ የእማይወድ አይብላ ስለ ሆነ ፤ ወገባችንን አጥብቀን እንገባበታለን እንጂ ። አርስታትል መማር በጥረት እና በግረት የእሚገኝ ነገር ስለ መሆኑ እንደ እዚኽ ይላል ፦

 

“... መማር መዝናኛ አይደለም ፥ ይልቁንም በህመም የታጀበ ነው።”

 

“…for learning is no amusement but is accompanied with pain. [1]”

 

 እንደ እዚያኹም አሮጌውን ትቶ አዲሱን አሰራር መቀበል የእሚፈጥረው የባሕል ግጭት ንዝረትም ተመሳሳይ ፈታኝነት አለው ።

 

ሶሲዮሎጂስቶች የባሕል ንዝረት ( Cultural Shock ) የእሚሉት ፤ በተለይ ፥ ለረዥም ግዜ ተነጥለው የቆዩ እና ከለውጥ ጋር ራሳቸውን ቶሎ የማላመድ ክህሎት ያል አዳበሩ ሰዎች ወይንም ማሕበረሰባት ፤ በተለይ በእዚኽ ዘመነ ግሎባላይዜሽን ፤ በእየግዜው አዲስ ነገር እንዲማሩ እና ራሳቸውን ከአዲስ አሰራር ጋር እንዲያስተዋውቁ በእሚያደርገው ጫና የእሚፈጥረው ግራ መጋባት እና ተስፋ መቁረጥ ቀላል አይደለም ።

 

 ዘመናዊነት ወይንም ዘመኑ የደረሰበትን የተሻለ አሰራር ማዳበር ፤ ያንን ዘመናዊነት ያስቻሉትን ፤ የአስተሳሰሰብ እመርታዎች እና አሰራሮች(ቴክኖሎጂዎች)መማር እና ከእዚኽ በፊት የለመዱትን አሰራር መተው ይፈልጋል ።

 

ኹለቱም ፥ የማንኛውም ለውጥ አካል የሆኑት ፤ ያለፈውን አስተሳሰብ እና አሰራር መተው እንዲኹም አዲሱን አስተሳሰብ እና አሰራር መገንዘብ እና መቀበል ፤ የእየ ራሳቸው ስነልቦናዊ እና ኢከነሚያዊ ጫና አላቸው ። ይኽን መሰሉ ለውጥ የእሚያመጣውን ስነ ልቦናዊ እና ኢከነሚያዊ ጫና ያልተረዳ እና በአግባቡ ያል አስተናገደ ግለሰብም ሆነ ማሕብረሰብ ፤ በመለወጥ እና በአለመለወጥ መካከል ዋልሎ የመቅረት አደጋ ያጋጥመዋል ።

 

ከላይ እንደ አልነው ፤ ሰው በባሕሪው ፤ የተሻለ መልካም ነው ብሎ ያሰበውን ነገር ለማግኘት የመሥራት መሠረታዊ እና ተፈጥሮዋዊ ዝንባሌው ፤ የስልጣኔ ፣ የቴክኖሎጂ ልቀት እና የዘመናዊነት ብሎም የባሕሉ መሠረት ናቸው ብለናል ።

 

የተሻለ ነገር መፈለግ ወይንም ስልጣኔ ደግሞ ፤ የሌለን ነገር በማምጣት ላይ ብቻ የአተኮረ ሰአይሆን የነበረን አሰራር እና ልማድ ማሻሻል ወይንም መተው የእሚጨምር ነገር ስለሆነ ፤ የራሱ ድርብ ፈተና አለው ።

 

“... ፥ የተማሩትን መተው አዲስ ነገር እንደ መማር ያኽል ከባድ ነው።”

 

“…, just to as unlearn is as hard as to learn. [1]”

 

በተለይ ደግሞ አኹን አብዛኛው የዓለም ሕዝብ የእሚገኝበት የስልጣኔ ደረጃ ፤ ኋላ ቀር የእሚባለው እንኳን ፤ የብዙ ዘመን የስልጣኔ እና የእድገት ውጤት በመሆኑ ፤ ወደ ስልጣኔ መጀመሪያ አከባቢ እንደ ነበሩት ለውጦች ቀለል ያለ አይደለም ።

 

 ሰው ፍራፍሬ ለቅሞ እና አድኖ ራሱን ከእሚመግብበት ፤ በአንድ ቦታ ተቀምጦ አርሶ እና እንስሳት አርብቶ ወደ እሚኖርበት የስልጣኔ ደረጃ በጥቂት ወራት እና ዓመታት ውስጥ አልተሸጋገረም ።  ከፍራፍሬ ለቃሚነት እና የዱር እንሰሳ አዳኝነት ወጥቶ ወደ ስኬታማ ገበሬነት እስኪሻገር ምናልባት በመቶዎች የእሚቆጠሩ ዓመታት ፈጅቶበታል  ። አኹን እንኳን በአለንበት ዘመን አርብቶ አደሮችን ፤ አርሶ አደሮች ለማድረግ የአለው ፈተና ቀላል አይደለም ።

 

 አንድ ገበሬ ፤ ከእሚኖርበት አከባቢ አንፃር የትኞቹን ሰብል መዝራት እንደ አለበት ፣ መቼ መዝራት እንደ አለበት ፣ ወዘተ ፤ የአለው እውቀት ፤  በጣም በብዙ ዘመን ሙከራ እና ስህተት ተጣርቶ እንደ ተላለፈለት መገመት ይቻላል ። ዛሬ እጅግ ኋላ ቀር ነው ፣ አድካሚ ነው ፣ አዋጭ አይደለም የእምንለው የሐገራችን ባሕላዊ ግብርና (የእርሻውም ሆነ የእንስሳት እርባታው) የብዙ ዓመታት እውቀት ፣ ቴክኖሎጂ እና ድክመት ውጤት ነው ። ከዘመኑ አንጻር ኋላ ቀር ነው ማለት ፤ ተራ ፣ የተናቀ ነው ማለት አይደለም ።

 

ወይንም ምን አልባት ዛሬ ላይ ሆነን ፤ እነ እዛኽ አንድ ትልቅ ቤት የእሚፈልጉ ከምፒውተሮችን ከዛሬዎቹ ዴስክታፕ እና ላፕታፕ ከምፒውተሮች  ጋር አነጻጽረን ፤ ልናዋድቅቸው እንችላለን ፤ ነገር ግን የድሮዎቹ ከምፒውተሮች ኋላ ቀር ናቸው እንጂ በራሳቸው የሰው ልጅ 5,000 ዓመት ታሪክ ጉዞ  ውጤቶች መሆናቸውን መገንዘብ አለብን ።ማንኛውም የከምፒውተር ኢንጂነር ዋጋቸውን ይረዳል ፤ ዘመን የተሻለ ነገር አምጥቶ ከአገልግሎት ቢያስወጣቸውም ።

 

በተመሳሳይም ፤ እጅግ ኋላ ቀር የእምንለው ግብርናችን እንኳን የብዙ ዘመን ሳይንሳዊ እውቀት ዉጤት መሆኑን መገንዘብ አለብን ። ከተማ ውስጥ የእሚኖር አንድ ባለ ዲግሪ እንደው ዘው ብሎ ፤ ኋላ ቀር የእምንለው የሐገራችን ፤ ግብርና ውስጥ መግባት አይችልም ፤ ማወቅ እና መማር የእሚጠበቅበት ነገሮች አሉ ።

 

ስለ እዚኽ ፦ ለውጥ ብለን ፣ ስልጣኔ ብለን ወደ አዲስ እና የተሻለ አሰራር ስንኼድ ፤ ኋላ ቀር እና የእማያዋጣ የእምንለው አሰራር ራሱ በብዙ ትምህርት እና ልምድ የተገኘ ነገር ስለ ሆነ ፤ ይኽን እውቀት እና ልምድ በሰዎች ውስጥ ማስረጀት በራሱ የእሚፈጥረውን ስነ ልቦናዊ ጫና መገንዘብ ተገቢ ነው ።

 

 ለውጥ አስፈላጊ እና ሊሸሹት የእሚችሉት ነገር አይደለም እንጂ ለውጥ ቀላል ነገር አይደለም ።

 

ዋጋ ቢያስከፍልም ፣ ቢያታግልም ፣ ቢፈታተንም ፤  ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ ስለ እሚበልጥ ስልጣኔ እና ዘመናዊነት ተመራጭ ነው እንጂ ።

 

ለውጥ የቀደመውን አሰራር ማስረጀት ብቻ ሰአይሆን ፤ አዲስ ነገርንም መማር ፤ ከእዛኽም ጋር በግለሰብም ሆነ በማሕበረሰብ ደረጃ አዲሱን አሰራር የእሚያስተናግድ ፤ መዋቅራዊ እና ኢከነሚያዊ ለውጥ ይፈልጋል ።

 

የጀመርነውን የግብርና ምሳሌ እንቀጥልበት እና ሰው ፤ አድኖ እና ፍራፍሬ ለቅሞ ራሱን ከመመገብ ፤ ወደ ግብርና ለመሸጋገር ብዙ ፤ የግንዛቤ ፣ የኑሮ ዘይቤ ብሎም የባሕል ለውጥ ማምጣት እንደነበረበት እና እንዳመጣም አይተናል ። ነገር ግን አኹን ደግሞ ግብርና ወደ ንግድ ግብርና(Commercialized farming)፤  የተለወጠበት ዘመን ላይ እንገኛለን ።

 

የመጀመሪያው ገበሬ ፤ ሰብል ቢያመርት ፣ የእንስሳት ተዋጾ ቢያመረት ፤ የእሚያመርተውን ኹሉ የእሚያመርተው ፤ እርሱ እና ቤተሰቡን ለመመገብ ነው ። የአኹኑ  ኹለተኛው ግብሬ ግን ፤ ለመሸጥ ወደ ማምረት ተሸጋግሯል ።

 

ለምን ለመሸጥ ወደ ማምረት  ተሸጋገረ ቢባል ፤ ስልጣኔ እና ቴክኖሎጂ ስልተ ምርትን በከፍተኛ ኹኔታ በመአሸጋገር ፤ ድሮ 20 ገበሬዎች ከእነ ቤተሰቦቻቸው ተሰባስበው የእሚያመርቱትን የምርት መጠን ፤ ዛሬ አንድ ገበሬ ብቻ ሊያመርትበት ወደ እሚችልበት ደረጃ ላይ በመምጣታችን ነው ።

 

ስለ እዚኽ ፤ ኢከነሚያዊ ትንታኔው ፤ እነ እዚኽ  ሐያ ገበሬዎች ራሳቸው ምርታቸውን ከእሚያመርቱ ፤ ከአንዱ ጎረቤታቸው ላይ ለቤት ፍጆታቸው የእሚበቃቸውን ቢገዙ ወደ እሚቀላቸው ኹኔታ ውስጥ ያስገባቸዋል ።   ይኽም ፤ ስልጣኔ እና ቴክኖሎጂ ፤ የእሚያመጡት የስልተ ምርት ለውጥ ፤ ከስነ ልቦናዊ ተጽኖ አልፎ መሠረታዊ የሆነ ፤ የኢከነሚያዊ መዋቅር ለውጥ በአስገዳጅ ኹኔታ አመጣ ማለት ነው ።

 

ምክንያቱም ፦ ግብርናቸው ትርጉም አልባ የሆነባቸው እነ እዚያኽ 20 ገበሬዎች ፤ ለረዥም ግዜ የእሚያውቁትን እና ከቤተሰብ ቤተሰብ የተሸጋገረላቸውን ፥ ምናልባትም የእሚወዱትን የግብርና ሥራ ፤ በአክሳሪነቱ ምክንያት ትተው ራሳቸውን እና ልጆቻቸውን ፤ ወደ አዲስ የሥራ መስክ ከማሸጋገር ውጭ ፤ ኢከነሚያዊው ኹኔታ በአሉበት እንዲ ቀጥሉ አይፈቅድላቸውም ።

 

ይኽን ፤ ለውጥን እና ስልጣኔን በአስፈሪ ኹኔታ ለመሳል እንድ እንጠቀምበት ሰአይሆን ፤ የለውጥ አስተዳደር (Change managment) ፤ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ እና በአንዳንድ መስኮች ፤ መዋቅራዊ ለውጥ (structural change) በእሚያስፈልጋቸው ሐገራት ውስጥ ፤ ስልጣኔ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ፤ የእሚያመጡትን ስነ ልቦናዊ እና ኢከነሚያዊ ጫና ፤ በጥራዝ ነጠቅ ትንታኔ እና በመንጠር ሰአይሆን ፤ ሳይንሳዊ በሆነ ትንታኔ እንዴት እንደ እሚሰራ ማስቀመጥ ተገቢ መሆኑን ለማሳየት ነው ።  አለበለእዚያኽ ብርቱኳን ብለን የተከልነው ነገር ከሽፎ እንጆሪ እንዳይሆንብን ያሰጋል ።

 

ለውጥ መልካም እና አስፈላጊ ነገር ነው ፤ ለውጥ ግን በጉጉት የእሚገኝ ወይንም ወፍ ዘራሽ ዛፍ አይደለም ። መልካም እና አስፈላጊ የሆነውን ያኽል እውቀት ፣ ትጋት እና ጽናት ይፈልጋል ።

 

በዘመናችን ፤ እንደ እዚኽ ዘርፈ ብዙ ባሕሪ እና ስረጸት የአለው ባሕል ፤ ባሕልን በተመለከተ በማሕበረሰብ ውስጥ በልማድ የተያዙ እና ዘመናዊ የማሕበረሰብ ሳይንስ መርሆዎችን የእሚገፉ እና የእሚያመክኑ አስተሳሰቦች ፤ በሕዝብ ዘንድ ልማዳዊ ወግ አጥባቂነት ከእላይ በገለጽነው መልኩ በአሉታዊነት እንዲጠናከር ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሶሻሊስት አብዮተኞች ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።  

 

የሶሻሊስት አብዮተኞች ፤ የእሚከተሉት የማርክሲስት ርዕዮት ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ አስተሳሰብ በሳይንሳዊ መንገድ በነጻነቱ ዴሞክራሲ በአደባባይ የተረታ በመሆኑ ፤ ይኽንን ርዕዮታዊ ሽንፈት በጸጋ ለመቀበል በተለያየ የራሳቸው ምክንያት የአልፈቀዱት ሶሻሊስቶች ፤ በነጻነቱ ዴሞክራሲ ላይ ርዕዮታዊ መሠረት የአለው ውጤታማ ሙግት ከማድረግ ይልቅ ፤ የነጻነቱን ዴሞክራሲ ፦ የቀኝ ገዢዎች ስረዐት ነው ፣ በባርነት የበለጸጉት የዘረኞቹ የምዕራብ አውሮፓዊያን ስረዓት ነው ፣ በነጻነት ስም የባሕል እና የስነ ምግባር ልሽቀት የእሚፈቀድ ስረዓት ነው ፣ ወዘተ ፤ የእሚሉት መሠረት የለሽ የማጥላላት ፕሮፖጋንዳቸው እንደ ሰደድ እሳት ተስፋፋስቶ ፤ ህዳሴው በከሸፈባቸው ወይንም በዘገየባቸው ኋላ ቀር ሐገራት ወይንም ማሕበረሰባት ውስጥ ፤ የግራ ዘመሞቹ ጸረ ካፒታሊዝም የሐሰት ፕሮፖጋንዳ የጽንፈኛ የባሕል ወግ አጥባቂነት ዘመናዊ ማጠናከሪያ ሆኖ እናገኘዋለን።

 

ይኽ የከሳሪዎቹ የሶሻሊስቶች የጥላቻ ዘመቻ ፤ የስልጣኔ ጀመሪዎች ምዕራባዊያን በአይሆንም ፤ ዘመናዊ ስልጣኔ ወይንም ሕዳሴው ጎምርቶ አኹን ለእሚገዛበት ደረጃ የበቃው በምዕራባዊያን ዘንድ በመሆኑ ፤ ምዕራባዊያንን በእዚኽ መልኩ እንዲ ጠራጠሩ እና እንዲ ጠሉ በማድረግ ፤ ቀስ በቀስ የዘመናዊ ስልጣኔ እና ልማት ቁልፍ የኾኑ የምዕራባዊያንን ሳይንሳዊ ዕውቀቶች ወደ መጥላት እና መቃወም እያመራ ሕዝብን በባሕል ጠባቂነት ስም የስልጣኔ ተቃሚዎች ሲያደርግ የእሚስተዋልበት ግዜ ቀላል አይደለም ።

 

ለምሳሌ ፦ በሐገራችን ኢትዮጲያ በ1960 አከባቢ የተማሪ አብዮተኞች ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሴት ተማሪዎች ሊካኼድ የነበረ የፋሽን ትዕይንት (Fashion Show) የባሕል ወረራ ነው በእሚል ይኽንን ትዕይንት ለማስቆም በአነሱት ረብሻ ዩኒቨርስቲውን አስዘግተውት ነበር ፦

 

“በመጋቢት 21, 1960 (እ.አ.አ. በማርች 30 1968 ዓ.ም.) … ለትዕይንቱ ታዋቂ የኢትዮጵያ ወይዛዝርት እና ሟዴሎቹ ወደ ዩንቨርስቲው መጡ ፤ ተማሪዎች “የምዕራባዊያን ፋሽን የኢትዮጲያን እና የአፍሪካን ባሕል እየበከለ ነው” ብለው እየተቃወሙ እንቁላል ወረወሩባቸው። ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የዩኒቨርስቲው አመራሮች ትምህርት መቋረጡን አስታወቁ ...”

 

“On March 30, 1968, … prominent Ethiopian women and the models arrived at the university for the occasion, students threw eggs, protesting that “western fashion were prostituting Ethiopian and African cultures.” A few hours later, the authorities announced the closure of the university, … [51]”

 

የኢትዮጲያ ተማሪ አብዮተኞች ፔንጤዎችንም የኢምፔሪያሊስት እምነት ተከታዮች በእሚል ይደበድቡ እንደ ነበር በወቅቱ ታሪክ የተመዘገበ ነው።

 

ርዕዮታዊ ክርክሩን ወደ ጎን ትተን ፤ ነውጠኞቹ ሶሻሊስቶች በፍርደ ገምድልነት ምዕራባዊያን ፦ ቀኝ ገዢዎች ፣ አምላከ ከኃዲያን ፣ ስነምግባር ቢሶች ፣ አጓጉል አለበባሶች አምጪ ፣ የአድንዛዥ እፆች ፣ የዘረኝነት ፣ የባሪያ ስረዓት ፣ ወዘተ ፤ ምንጭ ናቸው ብለው የእሚሰነዝሯቸው ክሶችን ጠጋ ብለን የመረመርናቸው እንደ ሆን ፤ መሠረተ ቢስ እንደ ሆኑ እናስተውላለን።

 

ይኽን ለማሳየት ቀኝ ግዛት እና አጉል አለባበስ ፣ አደንዛዥ ዕፅ ፣ ወዘተ ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በተለያየ ወቅት የነበራቸውን ገጽታ እንመልከት ፦

 

   ኝ ግዛት 


ቀኝ ግዛት ማርክሲስቶች ስግብግብ ካፒታሊስት በእሚሉዋቸው ምዕራባዊያን ያለተጀመረ ስለ እዚኽም በአውሮፓዊያን ዘረኝነት እና ስግብግብነት ጋር የተናጠል ግንኙነት የሌለው ፤ እንዲኹም ቀኝ ግዛትን እና የባሪያ ንግድን ፤ ከእነ አስከፊ በኃሪያታቸው በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በሕገ ለማገድ ቀዳሚዎቹ እና ዋነኛዎቹ አውሮፓዊያን መሆናቸውን ነው ታሪክ የእሚነግረን። 


እንደ እምናስታውስው ፤ ብሔራዊ ፅንፈኝነት በእሚለው ክፍል ላይ እንደ አስቀመጥነው ፤ ለዘመናዊው ቀኝ ግዛት መጀመር ምክንያት የሆነው ፤ በብዝበዛ መክበር የፈለጉ የካፒታሊስት አውሮፓ ነገሥታት እና መሣፍንት የአደረጉት አሰሳ ሰአይሆን ፤ ከኢፍትሐዊ ተፅዕኖ እና እንደ ድህነት ካሉ የማሕበራዊ ቀውሶች ለመውጣት የእግር አውጭኝ ትንቅንቅ የአደረጉት ተራው የአውሮፓ ሕዝብ እንቅስቃሴ ነው ።


በግዜ ኺደት ይኽ ፍትኃዊ እና ሕዝባዊ ፍላጎት መልኩን ቀይሮ ወደ ቀኝ ግዛት ብዝበዛ እና ረገጣ ቢቀየርም ፤ በእዚኽ መልኩ የጀመረው የአውሮፓ ሕዝብ እንቅስቃሴ በግዜ ኺደት ወደ ቀኝ ግዛት እና ባሪያ ንግድ ተጣሞ ያደገው ፤ የአውሮፓ ሕዝብ ወይንም ምዕራባዊያን ወይንም የካፒታሊስት ስረዓት መነሻ የሆኑት አውሮፓውያን ፤ ከሌላው የዓለም ሕዝብ የከፉ ፤ ስግብግብ ፣ ከኃዲ አምላኪያን ፣ ወዘተ ፤ ስለ ሆኑ አይደለም።


በምዕራባዊያን የተፈፀመው የቀኝ ግዛት ፤ የሰው ልጅ ቴክኖሎጂያዊ አቅም በዳበረበት ወቅት መሆኑ ተፅኖውን አጎላው እንጂ ፤ ወረራ እና ጦርነት ፤ ስለ እዚኽም ቀኝ ግዛት ጥንታዊ ከሆኑ ፖለቲካዊ ክስተቶች አንዱ የነበረ ነው ።


የዓለምን ታሪክ ወደ ኋላ ኼደን ብንቃኝ ፤ የግብጽ ስልጣኔ በፋርስ ተወሯል ፣ ፋርስ በግሪክ ተወሯል ፣ ግሪክ በጣሊያን ፣ ጣሊያን በስተመጨረሻ  ፤ በተለያየ አቅጣጫ በተለያየ ኹኔታ ሲቀነጣጠብ ከቆየ በኋላ ፤ በስተመጨረሻ ከውስጥ ዘብጦ እና ከሰሜናዊ አውሮፓ በመጡ ቪስጎትስ በእሚባሉ ተወሮ ፈራርሷል  ። በሩቅ ምሥራቅ ብናይም ፤ የቻይና ስልጣኔ በሞንጎል ፤ ሞንጎልም በኋላ በእስልምና ፣ ወዘተ ፤ ተወረዋል  ።


ይኽም ብቻ ሰአይሆን ቀኝ ግዛትን እንደ ስረዓት አውሮፓዊያን አስጀመሩት ብእንል እንኳን ፤ እንደ ማንኛው አስከፊ ስረዓት ፤ ሰፊው የአውሮፓ ሕዝብ ልክ እንደ ቀኝ ተገዢው ሰፊው ሕዝብ በተለያየ ምልኩ የስረዓቱ ሰለባ የሆነበት ብዙ አጋጣሚ ስለ ነበር ፤ ቀኝ ግዛት እና አስከፊነቱ መያያዝ የነበረበት ፤ ከስረዓቱ አራማጆች ጋር እንጂ ከመላው የአውሮፓ ሕዝብ ጋር አልነበረም።


በአጠቃላይ የዓለምን ሕዝብ ታሪክ የተመለከትን እንደ ሆነ ፤ የተለያዩ ሕዝብ በሌሎች ሕዝብ ላይ በመዝመት ፦ ኃብታቸውን በመዝረፍ ፣ ባሕላቸውን በማራከስ ፣ በባርነት በማጋዝ ፤ ምንም እንኳን የድልነሺዎቹ ስልጣኔ ከተሸናፊዎቹ የተሻለ የእሚሆንበት ግዜ ቢኖርም ፤ ተሸናፊዎች ያልተገነዘቡትን እና ያልፈቀዱትን አዲሱን የተሻለውን መንገድ ያለበቂ ግንዛቤ አስገድዶ በመጫን እና መሰል ተግባሮች በመፈፀም ፤ የሰለጠኑ ሕዝብ ያልሰለጠኑ ሕዝብ ላይ ጫና ማድረጋቸው ፤ በሰው ልጆች ታሪክ ኹሉ ውስጥ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በስፋት በኹሉም ዘመን ሲስተዋል የነበረ ክስተት ነው።


ይኽም ዓይነቱ ዓለም ዓቀፋዊ ጋጠወጥነት ነው ፤ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ፤ በመጀመሪያ ሊግ ኦፍ ኔሽንስ በኋላም የተባበሩት መንግሥታትን ወደ መመሥረት ያመጣው ።


ምን አልባት ፤ ዘመናዊ ቀኝ ግዛት የቅርብ ግዜ ትዝታ በመሆኑ እና ጉዳቱ በቴክኖልጂ ምክንያት ከእዚኽ ቀደም ከነበሩት ተመሳሳይ ዓለም ቀፍ ክስተቶች በተለየ እና ሰፋ ባለ መልኩ በመጉላቱ ፤ ቀኝ ግዛትን የምዕራባዊያን እና የእነርሱ ብቻ ዘረኝነት መገለጫ አድርጎ በስህተት አስመስሎት ከአልሆነ በስተቀር። 


ይኽም በመኾኑ እና እንደ ቀኝ ግዛት ያሉ አሉታዊ ፖለቲካዊ ስረዓቶች እድሜ ጠገብ የሰው ልጅ ፖለቲካዊ ታሪክ አካል በመኾናቸው ፤ በዓለም ላይ አውሮፓዊያን ብቻ ሰአይሆኑ ብዙ ሕዝብ እና ሐገራት በቀኝ ገዢ ፖሊሲ እየተመሩ ብዙ ሌሎች የዓለምን ሕዝብ በድለዋል።


ለምሳሌ ፦ የሐገራችንን የኢትዮጵያን ታሪክ ብዕንመለከት ፤ የአውሮፓዊያን የቀኝ ግዛት ማስፋፋት የጎዳንን ያኽል ወይንም ከእርሱ በባሰ ኹኔታ ፤ የቱርክ ከግራኝ አህመድ ወረራ አንስቶ እስከ የቀይ ባሕርን ወደቦች መውረር ያደረሰችው ጥቃት ፤ ከኤርትራ ችግር አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ በተለያየ መልኩ የኢትዮጵያን እድገት የእሚፈታተኑ ኹኔታዎች የፈጠረ የታሪካችን አካል ነው ።


እንደ እሚታወቀው ፤ ከግራኝ መሸነፍ በኋላ ቱርኩች ያደረጉት ፤ የቀይ ባሕር ወደቦችን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ በሰሜን በኩል ጥቃት መሰንዘር ነው ። ይኽን መሰሉ ፤ የውጭ ጣልቃ ገብነት ደግሞ ፤ በውስጣዊ ፖለቲካ አንጃን እያበረታታ አመፅን አቀጣጥሏል ።


ታሪካዊ ቅደም ተከተሉ ይኽን ቢመስልም ፤ ለረዥም ግዜ በጋጠወጥ ሶሻሊስቶች በአብዛኛው የሐገራችን ፖለቲካ ትንታኔ ወቅት የእሚቀርበው ታሪክ ፤ እንዴት ፦ የእንግሊዝ መንግሥት ፤ ከቱርክ የምፅዋን ወደብ መልቀቅ በኋላ ፤ የእንግሊዝ መንግሥት ከአጼ ዮሐንስ ጋር የገባውን ውል በማፍረስ ፤ ወደቡን ለጣሊያን እንደ ሰጠ እና ይኽም ለኤርትራ መገንጠል ፣ ወዘተ ፤ ምክንያት እንደ ሆነ ነው ።


አጼ ዮሐንስ በእርሳቸው በኩል የአለውን የውሉን ግዴታ ፤ ብዙ ዋጋ አስከፍሏቸው ሳለ ቢጠብቁትም ፤ እንግሊዞቹ ብዙም ሳይጨነቁ ቃላቸውን ማጠፋቸው የእሚታወቅ ቢሆንም ፤ ቱርክ የቀማችውን ወደብ ቢሆንም ፤ ከቱርክ ቀምተው ለኢትዮጵያ መመለስ የነበረባቸው ፤ እነርሱ እንደ እሚሉት ፤ ይኽን ያለ አደረጉት ፤ በወቅቱ በነበረው የኃይል ሚዛን ሳቢያ ፤ ወደቡ ወደ ታሪካዊ እና ፍትሐዊ ኢትዮጵያዊያኖች ቢመለስ ፤ ብዙም ሳይቆይ ተመልሶ በቱርክ ወይንም በሌላ የእነርሱ ተቀናቃኝ ኃይል እጅ መውድቁ ስለ እማይቀር ነው የእሚል ነው ፦


“የጎርደን ፤ የትኛውንም የኢትዮጵያን የባሕር ደጆች ለኢትዮጵያ አስልፎ መስጠት ፤ ወደቡ በቀላሉ በሌላ የእንግሊዝ ተቀናቃኝ የሆነ የአውሮፓ ቀኝ ገዢ ኃይል እጅ ይወድቃል ከእሚል ምክንያታዊ ስጋት የመነጨ ፖሊሲ የነበረ ነው ።”


“ But Gordon’s policy was based on the justified suspicion that any cessation of coastal territory to Ethiopia might result in its undesired control by other European power. [52]“

 

የዓለም ዓቀፍ ፖለቲካ በእዚኽ መልኩ ውስብስብ የሆነ በመሆኑ ፤ አንዳንድ ግዜ ውሳኔዎች ወይንም አካኼዶች ፤ ከግልፅ ጥላቻ በአይመነጩም ፤ ለምሳሌ ፦ በእኛ ልዩ ታሪክ ፤ ይኽ ኹኔታ ፤ በቅርብ ምክንያትነት ፦ የአድዋ ጦርነት ፣ የጣሊያን ወረራ ፣ የኤርትራ መገንጠል ፣ ወዘተ ፤ በማስከተል ብዙ ጉዳት የአደረሰብን በመሆኑ እና ታሪኩም በጽንፈኞቹ ማርክሲስቶች ፤ ቀኝ ግዛት እና አውሮፓዊያን ‘ያጠፉት’ ጥፋት እንጂ ከእነርሱ ቀድመው የነበሩ ታሪኮች እና ተዛማጅ ፖለቲካዊ ምክንያት ሳይቀርብልን ስለ ቆየ ፤ ኹኔታው በማሕበረሰባችን ውስጥ ፤ በተወሰነ ደረጃም ቢሆንም ምዕራባዊያን የብሔራዊ ጠላታችን ናቸው የእሚል ዓይነት ጉምጉምታ እንዲኖር አድርጓል ፤ በስህተት ።


ይኽም በመኾኑ ፤ ከዝበት የጸዳ ታሪካዊ ትንተና ሳይሆን ፤ የሰሻሊዝም አደርባይነት ፕሮፖጋንዳ ፤ በአግባቡ ከአልተመከተ ፤ ፀረ ምዕራባዊያን እና ምዕራባዊ ሳይንስ ኾኖ ሊወጣ ይችላል ።


ሚዛናዊ ሆነን የዓለምን ታሪክ የቃኘን እንደሆነ ፤ አስቀድመን እንደ አልነው ይኽን መሰሉ ‘ክዳት’ አውሮፓዊያን በኢትዮጵያ ላይ የአደረሱት ፤  የኢትዮጲያ ብቻ ገጠመኝ እና ‘የክፉዎቹ’ አውሮፓዊያን መገለጫ አለ መሆኑን እንገነዘባለን ። 


በዓለም ላይ ፦ ያልተከዳ ፣ ሴራ ያልተፈጸመበት ፣ መከራ ያላየ ፣ ያልተበዘበዘ ሐገር ማን አለ ? ኢፍትኃዊነትን ለቀኝ ግዛት ፣ ለካፒታሊዝም እና ለምዕራባዊያን ብቻ ማላበስ ፤ ከማሕበራዊ ሳይንስ መርህ እና ከታሪካዊ እውነታዎች የተፋታ ነው ።


በአውሮፓ እንኳን ብንመለከት ፦ ፈረንሳዮች ጣሊያንን ወረዋል ፣ ጀርመኖች ራሺያን እና ፈረንሳይን ወረዋል ፣ ቱርኮች በአውሮፓ ባልካን የእሚባሉትን አከባቢ ነዋሪ የሆኑትን አውሮፓዊያን ወረዋል ፣ ወዘተ ። መውረር ብቻ አይደለም ፤ አንዳንዶቹ ፤ የብዙ ዘመን ቃል ኪዳን አፍርሰው እጅግ አሳዛኝ የጅምላ ጭፍጭፋ አካኺደዋል ፣ ወርቅ እና የተለያዩ ብዙ ዋጋ የአላቸው ኃብት ዘርፈዋል ።


ትልቋ ቻይና ፤ በ1930ዎቹ ፤ የተለያዩ የአውሮፓ ቀኝ ግዢ ኃይሎች ፣ የጃፓን መንግሥት እና የቻይና ነፃ አውጭዎች የተፋጠጡባት ነበረች ። በእዚኽ በ1930ዎቹ አከባቢ ፤ የትልቋ ቻይናን ፖለቲካዊ ድባብ አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ እንደ እዚኽ ያስቀምጠዋል ፦


“በቻይና ዘውድ ፈቃድ በቻይና የሰፈሩ የምዕራብ ሰፈራዎች በአንድ ወገን ፤ የጃፓን ወታደራዊ አስተዳደር እና በግዚያዊነት የተዋቀረው የአከባቢው መንግሥት መካከል ውጥረት ከግዜ ወደ ግዜ እያየለ ኼዷል ።“


“ Friction and irritation have become more and more marked in the relations between the municipal authorities of Western settlements and concessions in China on the other hand, and the Japanese military administration and the provisionally constitued local governments in Occupied China on the other. [53]“


ከእዚኽ ዘገባ እንደ እምንመለከተው ፤ የወቅቱ የጃፓን መንግሥትም ልክ እንደ አውሮፓዊያኖቹ በቻይና ላይ የራሱን ተፅኖ ለማሳረፍ ሲጥር እንደ ነበር ነው ። የጃፓኑ መንግሥት ግን በእዚኽም ብቻ አላበቃም ፤ ማንቹሪያ የተባለችውን የቻይናን ግዛት በወኪል ሲመራ ቆይቶ ፤ በኋላ ላይ መላው ቻይናን ወሮ ፤ ለጥቂት ግዜ ቢኾንም ፤ ትንሿ ጃፓን ትልቋን ቻይናን ቀኝ ይዛ ብዙ አሰቃቂ ወንጀል ፈጽማለች ።


በእዚኽም ወቅት ፤ የወቅቱ የጃፓን መንግሥት በቻይና ሕዝብ ላይ በአደረሰው እጅግ አሰቃቂ በደል ምክንያት ቻይናዎች በጃፓን መንግሥት ላይ የአላቸው ቂም እስከ ዛሬም በተለያየ መልክ የእሚንጸባረቅ ነው።


ያ ብቻም አይደለም ፤ እነ እዚኽ በቻይና የሰፈሩ የአውሮፓ ነጋዴዎች ፤ የቀደመው ኢስት ኢንዲስ የእሚባለው ካምፕኒያቸው ፈርሶ ወደ ቻይና ከመምጣታቸው በፊት ፤ ከእዚኽ  የዓለም ዓቀፍ ንግድ የእሚያገኙት ገንዘባቸውን በሐገራቸው እንግሊዝ ፖለቲካ ውስጥ ያልተገባ ጫና ሊፈጥሩበት ሲሞክሩ ነበር ፦


“ዘመናዊው ዓለም ዓቀፉ የቻይና ሰፈራ የጀመረው ፤ ኢስት ኢንዲየስ የእሚባለው ካምፕኒ በቻይና የነበረው ሞኖፖሊ ሲያበቃ ነው ። በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ እና በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ፤ የእንግሊዝ ‘ቱጃሮች’ ከእዚኽ የኢስት ኢንዲያ ካምፕኒ በሙስና የአገኙትን ገንዘብ በመጠቀም ኢንግሊዝን የመግዛት አዝማሚያ ስለ አመጡ  ፤ የተነሳው አመፅ ነው እ.አ.አ. የ1832ን ዓ.ም. የምርጫ ሕግ መሻሻል ያመጣው ።”


“ The modern international settlements in China arose with end of East India Co.’s monopoly in the China trade. The British reform movement of the late 18th and the early 19th centuries, which culminated in the electoral reforms of 1832, was partly a revolt against the British ‘nabobs’ who had amassed huge fortunes in the service of the British East India Co., and threatened to rule Britain through the corrupting use of their riches. [53]“


ይኽም ማለት ቀኝ ግዛት እንደ ስረዓት ፤ ፀረ ሕዝብነቱ ቀኝ በእሚገዛቸው ሕዝብ የተወሰነ ሰአይሆን ፤ መነሻ በሆነባቸው ሐገራትም ይኽን ስረዓታዊ ፀረ ሕዝባዊነት ሲያራማድ የነበረ ነው ። በቻይና ኮንሴሽን የእሚባል ውል ከቻይና የዘውድ ስረዓት ጋር ተዋውለው ፤ ከእዚኽ ከእሚያገኙት ኃብት ፤ እነርሱ በቻይና ኮንሴሽን እየኖሩ የሐገራቸው እንግሊዝ ፖለቲካ በገንዘብ መግዛት ይፈልጉ ነበር ፤ የወቅቱ የአውሮፓ ተጽኖ ፈጣሪዎች ።


ቀኝ ግዛት በእዚኽ መልኩ በመሠረታዊነት በተሳሳተ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ እና ሰለባዎቹን የጎዳውን ያኽል የፈፃሚዎቹንም ሐገራት ሰፊ ሕዝብ የጎዳ ስለሆነ ነው  ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተወግዞ የጠፋው ።


ይኽም በመሆኑ ፤ ቀኝ ግዛት የምዕራብ አውሮፓዊያን ብቻ ኃጢያት ያልሆነ እና ስረዓቱ እንደ ስረዓት መጥፎ በመሆኑ ፤ ለቀኝ ተገዢው እጅግ መጥፎ ቢሆንም ፤ ቀኝ ገዢ ለነበሩት ሐገራት ሰፊ ሕዝብም ብዙ አስከፊ ገጽታ የነበረውን እና ካፒታሊዝም የአስወገደው ስረዓት እንጂ ካፒታሊዝም የፈጠረው ስረዓት እንደ አልሆነ መገንዘብ አለብን።


ቀኝ ግዛት እና ባርነት ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በሕግ ተደንግጎ የተከለከለው ፤ በማርክሲዝም ምክንያት ሳይሆን ፤ ገብጋባ ቀኝ ገዢዎች በተባሉት በራሳቸው ምዕራባዊያን ግንባር ቀደም መሪነት ነው።


የሶሻሊስት ፕሮፓጋንዲስቶች የእሚዘነጉት ወይንም መናገር የእማይፈልጉት ነገር ቢኖር ፤ እንግሊዝ በዘመናዊ ባሪያ ንግድ ቀዳሚ ተዋናይ የነበረች ብትሆንም እና የአሜሪካ ጥቁሮች በእዚኽ የባሪያ ንግድ ምክንያት ወደ አሜርካ እንደ ኼዱ ኹሉ ፤ በእነ እዚኽ ምዕራባዊያን ጉያ ውስጥ የዳበረው የዴሞክራሲያዊ እና የካፒታሊስት ስረዓት ፤ የፈጠረው የአስተሳሰብ እመርታ ፤ በዓለም ላይ የባሪያን ንግድ በሕግ በመከልከል የመጀመሪያዋ ሐገር ታላቋ ብሪታኒያ እንደ አደረጋት እና አሜሪካኖች ከሐገራቸው የባሪያን ስረዓት ለማስቀረት ፤ አራት አመት የፈጀ እና ወደ 600 ሺ መታደሮችን ህይወት የቀጠፈ የእርስ በእርስ ጦርነት እንደ አካኼዱ ነው።


ቀኝ ግዛትን ከካፒታሊዝም ጋር በማዳበል ፤ ምዕራባዊያን ለትርፍ እና ለስግብግብ ኃብት ማጋበስ ከአልሆነ ሰብዓዊ እሴት የላቸውም ብለው የእሚከሱት ሰዎች ሐገራት ፤ የራሳቸው ዜጎች ላይ እጅግ አስከፊ ረገጣ በእሚያደርጉበት በ19ኛው ምዕተ ዓመት ፤ የዘመናዊ ቀኝ ገዢዎች ‘እናት’ ብሪታኒያ ባርነትን እ.አ.አ. በ1833 ዓ.ም. በሕግ አግዳ ነበር ፦


“ብሪታኒያ ባርነትን በቀኝ ግዝቶቿ ሕገ ወጥ መሆን እ.አ.አ. በ1833 ዓ.ም. ደንግጋ ስለ ነበር …”

“ Since Britain had outlaeed slavery in its colonies in 1833, ... [38]“


እ.አ.አ. በ1831 ዓ.ም በአሜሪካ ፤ ዊልያም ሎይድ ጋሪሰን (William Lloyd Garrison) የእሚባል ነጭ አሜሪካዊ ፤ ባርነት በአሜሪካ ቀርቶ ፤ ነጮችም ጥቁሮችም እኩል የሆኑባት አሜሪካ እንድትሆን ፤ ወደ 250, 000 አባላት የአሉት እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምሮ ነበር ።


ለእዚኹ ዓላማ ብሎ ባቋቋመው ፤ ነፃ አውጭው (The Liberator)  በእሚለው ጋዜጣው ፤ የመጀመሪያው እትም መግቢያ ላይ ፤ ባርነትን ከአሜሪካ ለማስወገድ የእሚያደርገውን ትግል እንዲኽ ብሎ ጀምሯል ፦


“ የቋንቋዬ ጠንካራነት ብዙዎች እንደ እሚቃወሙት አውቃለሁ ፤ ግን ይኽን መሰሉ ጠንካራ ቋንቋ ለመጠቀም ምክንያት የለምን ? እንደ እውነት ሸካራ እና እንደ ፍትሕ የእማያወላውል እሆናለሁ ። በእዚኽ ጉዳይ ላይ ፤ ለዘብተኛ አሳቢ ፣ ጸሀፊ እና ተናጋሪ መሆን አልፈልግም ። አይሆንም ! አይሆንም ! ቤቱ በእሳት እየነደደበት ያለን ሰው እስኪ ለዘብ ብሎ የድረሱልኝ ጥሪ እንዲያቀርብ ንገረው ፣ ወይንም ሚስቱን ክብሯን ከእሚደፍር ሰው ለዘብ ብሎ እንዲያድናት ንገረው ፣ እሳት ውስጥ የወደቀባትን ልጇን ለዘብ ብላ እንድታወጣው ለእናቱ ንገራት ፤ - ነገር ግን በአኹኑ ዓይነት ጉዳይ ለዘብ እንድል ግድ አትበለኝ ። ቆርጫለሁ - አላወላውልም - ምክንያት አልደረደርም - አንዲት ኢንችም አላፈገፍግም - ደግሞም እሰማለ።“


“ I am aware that many object to the severity of my language; bug is there not cause for severity ? I will be as harsh as truth, and as uncompromising as justice. On this subject, I don’t wish to think, or speak, or write with moderation. No! No! tell a man whose house is on fire to give a moderate alarm; tell him to rescue his wife from the hands of a ravisher; tell the mother to gradually extricate her babe from the fire into which it has fallen; - but urge me not moderation in a cause like the present. I am in earnest – I will not equivocate – I will not excuse – I will not retreat a single inch – AND I WILL BE HEARD. [38]“


ይኽ እንግዲኽ ፤ በካፒታሊስቶቹ ጎራ ፤ ለፍትሕ እና ለእውነት ፤ በነፃ ዜጎች በራሳቸው ማሕበረሰብ ላይ የተደረገ ሰላማዊ ትግል ነው ። ይኽ ሰላማዊ ትግል በምድረ አሜሪካ ፤ ማሕበረሰቡን ከፍሎ ፤ ባሪያ ማሳደር መብቴ ነው የአለው የሕብረተሰብ ክፍል ፤ ባሪያ አታሳድርም ከእሚለኝ እገነጠላለሁ ሲል ፤ ባሪያም አታሳድርም አትገነጠልም ያሉት ጋር በመጋጨቱ የአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት ተካኺዷል ፦


“አሜሪካ እ.አ.አ. ከ 1861 አንስቶ እስከ 1865 ዓ.ም. የቀጠለ እና ከ600,000 በላይ የወታደሮችን ህይወት የቀጠፈ ፤ አስከፊ የእርስ በእርስ ጦርነት አካኺዳለች ። እ.አ.አ. በ1863 ዓ.ም. ግጭቱ የሕብረቱን አንድነት ለማስጠበቅ ብቻ ሰአይሆን ባርነትን ከተዋኃዱት የአሜሪካ ግዛቶች (ዩናይትድ ስቴትስ) ለማስወገድ የተደረገ ግጭት ሆኖ ነበር ። በእዚኽ ትግል ሰሜኑ ድል የተቆናጠጠው ለአራት አመት ከተዋጋ በኋላ ነው ። ሕብረቱን ማዳንም ተቻለ ፤ ባርነትም እንደ ተቋም እንዲፈርስ ተደረገ ።”


“ Beginning in 1861 and continuing until 1865, the United States engaged in a brutal Civil war that claimed the lives of over 600,000 soldiers. By 1863, the conflict had become not only a war to save the Union, but also a war to end slavery in the United States. Only after four years of fighting did the North prevail. The Union was preserved, and the institution of slavery had been destroyed in the nation. [38]“


የትኛው የዓለም ሕዝብ ወይንም ሐገር ነው ፤ አናሳ ፣ ደካማ እና በገፅታ ከእነርሱ የእሚለዩ ማሕበረሰባት ነፃ ለማውጣት የዛሬ 150 ዓመት ከግማሽ ሚልየን በላይ የእሚሆኑ የራሱን ሐገር ወጣቶች እሚሰዋ ጦርነት የአደረገው?


በዘረኝነት የእሚከሰሱት ፤ የምዕራባዊያን ደጅ አዛማቾቹ ብሪታኒያ እና አሜሪካ ፤ እ.አ.አ. በ1833 እና በ 1865 ዓ.ም. ባርነትን ሲያግዱ ፤ በዓለም ላይ የብዙ ሐገራት መንግሥታት የራሳቸውን ሕዝብ ተጠቂ የእሚያደርግ የባርነት ንግድ ላይ ይሳተፉ ነበር ።


በዋናነት ጸረ ቀኝ ግዛት የሆነው እና መላው ዓለም ከሞላ ጎደል የእሚቀበለው ዓለም ዓቀፍ ስረዓት ንድፍ መሠረት የሆነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የእርሱ ቀዳሚ ሊግ ኦፍ ኔሽንስ ለመመሥረቱ እና ለመቀጠሉ ወሳኝ ሚና የተጫወተቸው እና የእምትጫወተው የሰሜን አሜሪካዋ ፤ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ነች ።


አደንዛዥ ዕፅ  ክህደተአምላክ ፣ አጓጉል አለባበስ ፣ ወዘተ 


ምንም እንኳን ፤ ምዕራባዊያን ከሌላው የዓለም ሕዝብ የከፋ ወይንም የተለየ ክፋት እና ዘረኝነት በአይኖርባቸውም ፤ የቀኝ ግዛት እና ዘረኝነት ፤ በአንዳንዶች ከእነርሱ ጋር እንደ ተያያዘው ኹሉ ፤ ነፃነት እና ዴሞክራሲ ማለት ቅንጦት ወይንም ቅብጠት የእሚመስላቸው አንዳንዶች ፤ ሐጢያት ራሱ ኤደን ገነት ውስጥ ሰአይሆን ፤ የፈረንሳዩዋ ፓሪስ ወይንም የእንግሊዟ ለንደን ውስጥ የጀመረ አስመስለው ፤ ምዕራባዊያን እና እነርሱ ጋር የዳበረው ነፃነትን የስነ ምግባር ልሽቀት ጋር አዳብለው ሊያቀርቡት ይፈልጋሉ ።


የሕዝብን ነባራዊ ባሕል ከተመለክትነው ግን ፤ ከንቅሳት ጀምሮ ፤ ሐፍረተ ስጋን ብቻ ሲሸፍን ፥ የቀረውን የአካል ክፍል ግልጥ አድርጎ የእሚተው ፤ የመዋብ እና የአለባበስ ስረዓት ፤ የሰው ልጆችን የምርጫ ነፃነት ከእሚያከብረው የዲሞክራሲ አሰራር ከመምጣቱ እና ዘመናዊው ቀኝ ግዛት ከመስፍፋቱ ብዙ መቶ ወይንም ሺ ዓመታት አስቀድሞ ነበር ።


አካልን የእሚያሳይ ዘመናዊ ልብስ መልበስ ፤ ዴሞክራሲያዊ ነፃነት ያመጣው የሞራል ውድቀት ከሆነ ፤ አብዛኛው የሰውነታቸውን ክፍል ግልጥ አድርገው የእሚኼዱት ፤ ዘመናዊው ስልጣኔ በበራቸውም የአላለፈው ፤ የሐገራችን ሕዝብስ በምን ሊወቀሱ ነው ?


ዴሞክራሲያዊ ነፃነት ፤ ከእዚኽ በፊት በባሕላችን የሌለ እንደ ሲጋራ እና ሀሺሽ ማጨስ ያሉ ፤ ጎጂ ልማዶችን ያመጣብን የእሚመስላቸውም አሉ ። እውነታው ግን ፤ አልኮልን ጨምሮ ሌሎች አደንዛዥ ዕጾች ፤ የአንድ የስልጣኔ ደረጃ ውጤቶች ናቸው ።


ይኽን ዓረፍተ ነገር የእሚያነብ ሰው ፤ ከመቼ ወዲኽ ነው ፤ አስካሪ መጠጥና አደንዛዥ ዕጽ መጠቀም ስልጣኔ የሆነው ? ሊል ይችላል ።


ስልጣኔ ከላይ እንደ ተረጎምነው ፤ የሰው ልጆች የተሻለ ብለው ያሰቡት ነገር እንደ ሆነ አስቀምጠናል።በእዚኽም መሠረት ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ሰዎች ፤ ከምግብ እና ውኃ በአለፈ ፤ ስሜታቸውን በተለያየ መልኩ የእሚቀይሩ ነገሮችን እንደ መዝናኛነት ወይንም እንደ መነቃቂያነት መጠቀም ተገቢ ነው ብለው ከአሰቡ ብዙ ሺ ዓመታት ተቆጥረዋል ። ከእዚኽም ፍላጎት እና እምነት በመነሳት ፤ አስካሪ መጠጥን እና የተለያዩ ዕጾችን ፤ በተለያየ መልኩ ቀምሞ መጠጣት እና መጠቀም ፤ በዓለም ላይ ባሉ ፤ በተለያዩ  ሕዝብ እንደ ዓለም ዓቀፍ የጋራ ልምድ የሆነ ፤ በመካከላቸው ባለው የቦታ ርቀት እና ብዙ ከባቢያው ልዩነቶች ሳይወሰን  ፤ በብዙ ሕብረተሰባት ዘንድ ፤ የነበረ ጥንታዊ ልማድ ነው ።


አስካሪ መጠጥ በባሕሉ ውስጥ የሌለው ሕዝብ ጥቂት ነው ።


እነ እዚኽ ስሜትን ቀያሪ ዕጾችን ፤ ለመዝናኛነት ወይንም ለመነቃቂያነት የመጠቀም ፍላጎት ፤ እንደ እየ አከባቢው የተለያየ መልክ ይዞ እናገኘዋለን ። ሲጋራ ማጨስ ፤ የዓለም ሕዝብ የተማረው ከደቡብ አሜሪካ ጥንታዊ ሕዝብ ነው ።


አብዛኛው ዓለም ደቡብ አሜሪካ የእሚባል ቦታ መኖሩን ሳያውቅ በፊት እና ስለ ሲጋራ እስከ እነ መፈጠሩም ሳያውቅ ፤ ደቡብ አሜሪካ ላይ የእሚኖሩ ሕዝብ ለብዙ ሺ ዓመታት ሲጋራ ሲያጨሱ ነበር   ። ከእነርሱ በብዙ እጥፍ ሰለጠነ እና የተሻለ የማሕበራዊ እድገት ደረጃ ላይ ነው የእሚባለው አውሮፓ ፤ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ቀኝ ገዢ ሆኖ ደቡብ አሜሪካ ሲደርስ ፤ ሲጋራ ማጨስ የእሚባል አስገራሚ ሱስ ተምሮ መጣ ። አንድ ጸሀፊ እንደ አለውም ፤ አውሮፓዊያን ስልጣኔ እናስተምራለን ብለው ሲጋራ ማጨስ ተምረው መጡ ።


የትምባሆን አጀማመር አንድ ጸኅፊ እንደ እዚኽ ያስቀምጠዋል ፦


“ትምባሆ እና የሰው ልጅ ዝምድና ፤ ከቅድመ ታሪክ ጀምሮ ልክ እንደ ምግብ እና ሻይ የነበረ ነው ። … ሰዎች ከጠቃሚዎቹ ተክሎች (ቲማቲም ፣ ድንች ፣ በቆሎ ፣ ካካዋ እና የጎማ ተክል) በተዋወቁበት አግባብ ነው ያወቁዋቸው። … ትምባሆ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ5000 – 3000 በአሉት ግዜያት እንደ ሰብል መመረት ጀምሮ ነበር ። ክርስቶፈር ከለምበስ እ.አ.አ. በ1492 ዓ.ም. ሰሜን አሜሪካ ሲደርስ ፤ በመላው አሜሪካ (ኪውባን ጨምሮ) በጥቅም ላይ ውሎ ነበር ።”


“Tobacco and mankind have been associated in the smae way as food and tea since before history began.... Men came across them ( along more useful plants such as tomatoes, potatoes, maize, cocoa and rubber) ... Tobacco is thought to have been cultivated since about 5000 – 3000 B.C. The use of tobacco was unibersal throughout the American continents (and Cuba) by the time that Christopher Columbus arrived in North America in 1492. [54]“


ከኼሮይን ጋር የምዕራቡ ዓለም የተዋወቀው ፤ ትምባሆ እንደ እሚጨስ ከደቡብ አሜሪካዊያን ከተማሩ ከብዙ መቶ አመታት በኋላ ወደ ሩቅ ምሥራቅ ሲመጡ ነው ።


ስለ እዚኽ ፤ ሲጋራ ማጨስ ፣ ሀሺሽ መጠቀም እና መሰል መዝናኛዎች ወይንም መነቃቂያዎች ፤  ቀኝ ገዢ የሆኑት የምዕራባዊያን ዴሞክራሲያዊ ነፃነት ያመጣቸው ችግሮች ሳይሆኑ ፤ ከዴሞክራሲያዊ ስረዓት ውጭ የነበሩ ሕዝብ ፤ በሺ ለእሚቆጠሩ ዓመታት ሲጠቀሙባቸው የነበሩ ፤ መነሻቸው ምክንያት የሰው ተፈጥሮዋዊ ዝንባሌ እና የእሚኖርበት አከባቢ ውኽደት ውጤት የሆነ እና ከዴሞክራሲያዊ ስረዓት ጋር ወይንም ከምዕራባዊያን ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ልማዶች ናቸው ።


የጋራ የሰው ልጅ ዝንባሌ የሆነው ከምግብነት ያለፈ የማነቃቃት ይዘት የአላቸውን ተክሎች በተለያየ አግባብ ቀምሞ የመጠቀም ፍላጎት ፤ በአካባቢዎች ልዩነት የፈጠረው ልማድ ነው ።


ቢበዛ ፤ በዴሞክራሲያዊ ነፃነት ታግዞ የተፈጠረው ፤ የካፒታሊዝም ስረዓት ፤ ዘመናዊ የመጓጓዣ ቴክኖሎጂ የአንድ አከባቢን አስካሪ ወይንም አነቃቂ ንጥረ ነገር ለሌላው አከባቢ እንዲ ዳረስ ኹኔታ አመቻችቷል ተብሎ ቢወቀስ እንጂ የባዕድ እና ጎጂ ሱሶች አምጪ(አመንጪ) ተብሎ ሊወቀስ አይችልም  ።


እውቀትን ፣ መድኃኒትን ፣ ቴክኖሎጂን ፣ ወዘተ ፤ ያመጣልንን የትራንስፖርት ቴክኖሎጂን ፤ ክፉውንም ነገር አጓጓዘ ብለን በጭፍን መውቀሱ ብዙም ምክንያታዊ አይደለም ፤ እንደ ሰው የእሚበጀንን ነገር የመምረጥ ኃላፊነት ስለ አለብን ። 


መቼም ኹላችንም እንደ እምንስማማው ፤ ሰው ዘመናዊ የእምንላቸውን ቴክኖሎጂዎች ፦ ከምፒውተር ስለ ተጠቀመ ፣ መኪና ስለነዳ ፣ በፋብሪካ የተመረተ ልብስ ስለ ለበሰ ፣ ዘመናዊ ቤት ውስጥ ስለኖረ ፣ ወዘተ  ፤ ሲጋራ ወይንም ሀሺሽ ማጨስ አይጀምርም ።  ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ከጎጂ ልማድ ከእምንላቸው አደንዛዥ ዕጾች መጠቀም ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የላቸውም ፤ እያንዳንዱ ሰው ቴክኖሎጂውን ለምን እንደ እሚጠቅምበት የመወስን መብት እና ኃላፊነት አለበት ።


ጎጂ ልማዶች አብረው ይተላለፋሉ ብለን ፍራቻ ፤  ከዓለም ሕዝብ ጋር ያለንን ባሕላዊ ፣ ኢከነሚያዊ እና የፓለቲካ ትስስር አንበጥስም ። ያም ብቻ ሰአይሆን ፤ በዓለም ላይ የአለው ልምድ የእሚያሳየን ወደ አስከፊ የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነት እራሱን በእሚጎዳ አኳኋን የእሚገባው የሕብረተሰብ ክፍል የስልጣኔ ትሩፋት የሆነው የኢከነሚያዊ እድገት ተጠቃሚ ያልሆነው እና በእዚኽ አንፃርም እለታዊ ኑሮው በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የእሚገኘው የሕብረተሰብ ክፍል ነው ።


ስለ እዚኽ ፦ ልክ ኢከነሚያዊ እና ስሜታዊ ቁርኝቱ ፤ ምክንያት የለሽ የባሕል ወግ አጥባቂነትን እንደ እሚያመጣው ፤ በታሪካዊ አጋጣሚ በሶሻሊስቶች ፕሮፖጋንዳ ምክንያት በአውሮፓዊያኖች ላይ የተያዘው ጥርጣሬ እና ጥላቻም መሰል ምክንያተ ቢስ ወግ አጥባቂነትን አበረታቷል ።


ባሕልን በተመለከተ የአነሳናቸውን ኃሳቦች ለማጠቃለል ፤ የሰው ልጅ ስሪት የሆኑት ማሕበረሰባት እና ባሕሎች ፤ ከተፈጥሮዋዊ የሰው ልጅ መልካም ፍላጎቶች የመነጩ ሆነው ከመጡ በኋላ ፤ በግዜ ኺደት እየተወሳሰቡ ኼደው ፤ ከታሰቡለት መልካም ግብ ይልቅ የማሕበራዊ ሰቆቃ ውጤት ሆነው ለብዙ ዘመናት የቆዩበት ብዙ አጋጣሚ አለ።


ይኽን የቆየ ከአሉታዊ ባሕላዊ ወግ አጥባቂነት የእሚመጣ ማሕበራዊ ሰቆቃ ፤ አኹን ዓለም በደረሰችበት የማሕበራዊ ሳይንስ እውቀት መሠረት ፤ ትርጉም በአለው ደረጃ መቅረፍ የተቻለው ፤ ሰዎች ከእሚኖሩበት ከባቢ እና ባሕላዊ ሁኔታ በላይ ፤ በሰውነታቸው የእሚጋሩዋቸው መሠረታዊ ፤ ሰብዓዊ (ሰዋዊ) ባሕሪዎች አሉ ፤ እነ እዚኽን ሰዋዊ (ዓለም ዓቀፋዊ) መብቶች እና ግዴታዎችን ማክበር እና ማስከበር ፤ የአንድ ፖለቲካዊ ስረዓት አንኳር ሆኖ ማሕበረሰብ ሲዋቀር ፤ የሰው ህይወት ፣ ነፃነት ፣ ንብረት የተከበረበት በእዚኽም ከፍተኛ ቁሳዊ ኃብት የበዛበት ማሕበረሰብ መፍጠር ይቻላል በእሚል አስተሳሰብ ነው ።


ባሕላዊ ወጥነት (Cultural Universals) ወይንም ከባሕላዊ ልዩነት የእሚሻገሩ ፤ ሰዎች ሰው በመሆናቸው የእሚጋሩዋቸው ተፈጥሮዋዊ ባሕሪያት እና እሴቶች አሉ እና የአንድ ሐገር ውቅርም ይኽንን ታሳቢ እና ማዕከል የአደረገ መሆን አለበት በእሚል አስተሳሰብ ላይ ነው ።


ይኽ አስተሳሰብ ግን ፤ ገሚስ የለም ፥ ይኽ ባሕላዊ ወጥነት አለ የእሚባለው አስተሳሰብ ፤ የየባሕሉን የስነምግባር መመዘኛ የእሚያፈርስ እና የባሕል ልዩነትን የእሚደፈጥጥ በመሆኑ ፤ የባሕል ወጥነት ሰአይሆን ፤ ኹሉም ባሕል ፤ የየእራሱን የስነ ምግባር ሕግ ደንግጎ የመኖር ‘ሉዓላዊ’ መብቱ ይከበር የእሚሉ ፤ ፅንፈኛ የባሕል አንፃራዊያን ( Radical Cultural Relativists) ፥ ሰብዓዊ የሆኑ የመናገር ወይንም የፆታ እኩልነት መብቶች እንኳን ፤ እያንዳንዱ ባሕል ሲፈልግ ያክብራቸው ሳይፈልግ ይተዋቸው በእሚል ፤ የዴሞክራሲያዊ በእዛኽም የዘመናዊውን ዳግም ስልጣኔን የእሚቃወሙ ሲያደርጋቸው ፤


ገሚሶቹን ደግሞ ፤ በልማዳዊ አስተሳሰብ ወይንም በሶሻሊስቶች የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ምክንያት በሕዝብ የተያዙ ፤ ባሕላዊ እና ልማዳዊ አስተሳሰቦች ፤ ዴሞክራሲ እና በዴሞክራሲ ላይ የተመሠረተው የካፒታሊዝም ስረዓት ፤ ቀደምት እና ታሪካዊ ባሕላችንን እያጠፋ ነው በእሚል ግንዛቤ ፤ የብዙ ልፋት ውጤት የሆኑ የማሕበራዊ ሳይንስ ፤ የፖለቲካ እና የኢከነሚ መርሆችን ፤ ለባሕል በአላቸው ቀናዊነት ይገፉዋቸዋል ።


በእነ እዚኽ ኹለት ፤ ፅንፈኛ የባሕል አንፃራዊያን እና በልማዳዊ አስተሳሰብ በሕዝብ ውስጥ ሊኖሩ የእሚችሉ ያልተመረመሩ ፤ በሌላ ባሕል የመጠቃት ወይንም ተገዢ የመደረግ ስሜት ( Wrong perception of cultural imperialism) ፤ የባሕልን ህልውና ማስቀጠል ወይንም አንድን ባሕል ከመቀየጥ ማዳን አንድ የፖለቲካ ስረዓት የስልጣን ምንጭ እና ግብ እንዲሆን በር ይከፍታሉ ።


ይኽ የባሕልን ‘ቅዱስነት’ ማስቀደም ፤ ከእሚፈይደው ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ፋይዳ አንፃር ሰአይሆን ፤ በአንድም በሌላም ምክንያት የባሕልን ህልውና መሠረት ሲያደርግ ፤ የባሕል ፅንፈኝነት እንለዋለን ።

ለባሕል ፅንፈኛውም ፤ ሐገር ማለት የእዚኽ ባሕል መኖሪያ ወይንም የተጽኖ ክልል ነች ።


በእርግጥ እንዲኽ ዓይነቱ የፖለቲካ አስተሳሰብ ፤ በጣም ደካማ እና ተጋላጭ የሆነ ማሕበረሰብ ፈጥሮ ፤ ከፖለቲካው ምህዳር በእየግዜው እየተጠረገ የእሚወጣ በመሆኑ ፤ በፖለቲካው መስክ በራሱ የአለው ድርሻ ጥቂት ቢሆንም ፤ በአንድ ሐገር ውስጥ ከሌሎች የፖለቲካ ፅንፈኛ አስተሳሰቦች ጋር ተደምሮ ፤ ድህነት ፤ ድንቁርና ፣ ኋላቀርነትን ለማስቀጠል አጋዥ ሊሆን ይችላል ማለት ነው ።


ለባሕል ፅንፈኛውም ፤ ሐገር ተፈጥሮዋዊ እኩል ነጻነት የአላቸው ዜጎች ፤ ይኽን ተፈጥሮዋዊ ነጻነታቸ በሕግ አግባብ ብቻ እየገሩ ፤ ሕይወታቸውን ለማቆየት እና ኑሮዋቸውን ለማሻሻል የእሚችሉባት መኖሪያቸው ሰአትሆን ፤ አንድ ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ባሕል ሕልውናውን ማስቀጠል እንዲችል ሕዝቡን በባሕሉ መሠረት የእሚያሳድርባት ፤ የባሕሉ የተፅኖ ክልል ነች ።




 

[1] የሰው ልጅ ከተፈጠረ ጀምሮ ፤ ባለፈው 500 ዓመታት ያስመዘገበው ከቀደሙት 5 ሺ ዓመታት ይበልጣል።

 
 
 

[2] አዳም ስሚዝ መጻፉን የጻፈው በ18ኛው መቶ ክፍለዘመን ስለሆነ ጭሰኛ እና ልዑል ያለው።

 
 
 

[3] ይኽ አባባል በተለይ በስነትምህርት (Pedagogy) ሞያተኞች ዘንድ በስፋት የእሚታወቅ ቢሆንም ፤ ማን ለመጀመሪያ ግዜ እንደ አለው ርግጠኛ ምንጭ የለም ይባላል።