
ፖለቲካን አደገኛ ከእሚያደርጉት ልዩ በኃሪያቱ አንዱ ፤ ትክክለኛን አሰራር በማወቅም ሆነ በአለማወቅም ለዕኩይ ዓላማ ለማዋል የአለው ልዩ አቅም ነው ።
ይኽም የፖለቲካ ልዩ ባሕሪ ከእሚገለፅበት መንገድ አንዱ የሐገር ፍቅር ነው ። ሰዎች ሐገራቸውን ይወዳሉ ፤ መውደዳቸውም ተገቢ እና አስፈላጊ ነገር ነው ።
የሐገር ፍቅር ፤ የሰው ልጆች ከአቋቋሙዋቸው ተቋማት ጋር የእሚኖራቸው ስሜታዊ ቁርኝቶች መካከል የእሚመደብ እና ምክንያተኝነትን እስከ አልጋረደ እና መጠኑን እስከ አላለፈ ድረስ ተገቢ እና አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው ።
የሐገር ፍቅር ፤ ሰዎች ለሐገራቸው መስዕዋትነት እንዲከፍሉ ፣ ለሐገራቸው እድገት መልካም አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ፣ ሐገራቸውን ከጥቃት እና ከአደጋ ለመከላከል የእሚያነሳሳው ቁጭት እንዲ ፈጠርባቸው ፣ ወዘተ ፤ የእሚያደርግ በመሆኑ ፤ የአንድ ሐገር ዜጎች ሐገራቸውን መውደዳቸው ተፈጥሮዋዊ እና ይበል የእሚባል ብቻ ሰአይሆን መንግሥታትም ዜጎቻቸው ጤናማ የሐገር ፍቅር እንዲ ኖራቸው መሥራት አለባቸው ።
ዜጎች ጤናማ የሆነ ሐገራዊ ወይንም ብሔራዊ ፍቅር እንዲ ኖራቸው ማድረግም አንዱ የመንግሥት ሥራ ነው ።
በሌላ መልኩ ደግሞ ፤ ዜጎች ለሐገራቸው የአላቸው ፍቅር በሕዝብ ባህላዊ አስተሳሰብ ወይንም በፖለቲካ ኃይላት ቅስቀሳ ፤ ወደ ጠብ አጫሪ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሊቀየር ይችላል ። ይኽ በሐገር ፍቅር ስም የእሚደረግ ጠብ አጫሪ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ነው ጂንጎይዝም በመባል የእሚታወቀው ።
ጂንጎይዝም ለእሚለው ቃል ፤ በእንግሊዘኛ መዝገበቃላት ላይ የእምናገኘው ትርጉም ፦
“በጠብ አጫሪነት እሳቤ የእሚመራ የውጭ ጉዳይ ፓሊሲን መሠረት የአደረገ ሐገር ወዳድነት”
“extreme chauvinism or nationalism marked especially by a belligerent foreign policy”
የእሚል ሲሆን ፤ ከመዝገበቃላት በአሻገር ፤ ከፖለቲካዊ እንደምታው አንፃር ሲተሮገም ደግሞ ፦
“ጂንጎይዝም ፈር የለቀቀ ብሔራዊ ስሜት እንደ ሆነ እንረዳለን ። ብሔራዊ ስሜት ፤ የአርስታትልን ድጋፍ የእሚያገኘው መልካሙ አማካይ ነው ብለን በማሰብ ፤ ጂንጎይዝም ወደ ቅዠት መሰል ፅንፍ የተገፋው ብሔራዊ ስሜት በመሆን ፤ ሰለባዎቹን ፍፁም አዕምሮ ቢስ እና ወራዳ የእሚያደርጋቸውን ነው ።”
“ Jingoism we understand to be the excess of nationalism. Asumming nationalism to be the virtuous mean which might have won the approval of Aristotle, then Jingoism is the excess of that feeling carried to a point of absurdity where its victim becomes wholly irrational as well as immoral. [55]“
በእዚኽም ፦ ጂንጎይዚም አዕምሮን የማስጣል አቅም ስለአለው ፤ ጂንጎይስት የሆኑ ሰዎች እንደ ሰው ከማገናዘብ እና በሰብዓዊነት ከመመራት ወጥተው ፤ ለሐገር ፍቅር በእሚል ምክንያት ፤ የሰውን ልጅ ህይወት እና ክብር ከመጤፍ ወደ እማይቆጥር ወደ ወራዳ ተግባር ውስጥ የእሚገቡበት ኹኔታ ነው ።
Jingoism (ጂንጎይዝም) ወይንም ምትኩ የሆነው chauvinism (ሾቨኒዝም) የእሚሉት የእንግሊዘኛ ቃላት ምንጭ ፤ እንዲኽ ዓይነቱን አቅጣጫ ከእሚያንጸባርቅ ዘፈን እና በእዚኽ ፀበኛ አርበኝነት ባሕሪው ከእሚታወቅ ግለሰብ ስም የተወሰዱ ናቸው ፤ በቅደም ተከተል ።
Jingo(ጂንጎ) የእሚለው ቃል ፤ ትክክለኛው ትርጉሙ ይኽ ነው ብሎ ለማስረገጥ ቢያስቸግርም ፤ እንግሊዝ በጦር ኃይል ከዓለም ላይ የእሚወዳደራት የለም እና እንዝመት የእሚሉ ወታደሮች ፤ ከእሚዘፍኑት ዘፈን አዝማች ላይ የተገኘ እንደ ሆነ ፤ የብሪታኒካ ኢንሳይክሎፒድያ ይነግረናል ፦
“መዋጋት አንፈልግም ፥ ነገር ግን በጂንጎ ፣ እንድ እንዋጋ ከሆንን
መርከቡም አለን ፣ ሰውም አለን
ገንዘቡም ደግሞ አለን”
“We don’t want to fight, yet by jingo, if we do,
We’ve got the ships, we’ve got the men,
And got the money, too.”
Chauvinism (ሾቨኒዚም) የእሚለው ቃል ፤ ሕዝባዊ መንግሥት ለመመሥረት የተጀመረውን የፈረንሳይን አብዮት ፤ የፈረንሳይን ታላቅነት በዓለም ዓቀፍ መድረክ ማሳየት በእሚል ለውጦ ፤ የፈረንሳይን ተስፋፊነት ፖለሲ በአዲስ መልክ ያስጀመረው የናፖሊዮን ወታደር ከነበረ ፤ ኒኮላስ ሾቨን (Nicolas Chauvin)ከእሚባለው ታማኝ የናፖሊዮን ወታደር ስም የተወሰደ ቃል ነው ።
ሾቨን ፤ ናፖሊዮን ይኽን የተስፋፊነት ጦርነቱን በእሚያደርግበት ወቅት የእርሱ ወታደር የነበረ እና በእዚኽ ናፖሌናዊ ጦርነት በነበረው ተሳትፎ ወደ አሥራ ሰባት ግዜ የመቁሰል አደጋ ያጋጠመው እና ከእዚኽም የተነሳ ከፍተኛ የአካል ጉዳት የደረሰበት ፥ ለእዚኽም መስዕዋትነቱ ፤ በናፖሊዮን የክብር ጎራዴ የተሸለመ የናፖሊዮን ወታደር ነበር ።
ሾቨን ፤ ይኽን ያህል ዋጋ ከከፈለ በኋላ ግን ፤ የናፖሊየን አዕምሮ ቢስ የመስፋፋት እና የፈረንሳይን የበላይነት ማሳየት የጂንጎይዝም ፖሊሲ ፤ ከውስጥም ከውጭም ናፖሊዮንን እንዲጠላ አድርጎት ናፖሊዮንን ከስልጣን ካወረደውም በኋላ ፤ ሾቨን የናፖሊዮን ደጋፊ እና አክባሪ ነበር ።
በእዚኽ መልኩ ከስልጣን ለተወገደው መሪው ፥ ናፖሊዮን ፤ በነበረው ‘ጭፍን’ ታማኝነት ይቀለድበት ስለ ነበር ፤ ስሙ በግዜ ኺደት ፤ በሐገር ፍቅር ስም ከምክንያት እና ከስነ ምግባር ውጭ የሆኑ ተግባራትን ከማድረግ ለእማይመለሱ ሰዎች ወይንም ለእንደ እዚኽ ዓይነት ፖለቲካዊ እምነት ስያሜ ለመሆን በቅቷል ።
ጂንጎይዝም ወይንም ሾቨኒዝም የእሚሉት ቃላት ፤ ምንም እንኳን ከዘመናዊ ክስተት ወይንም ግለሰብ ስም ቢወሰዱም ፤ የወከሉት ኃሳብ ፦ ዓዕምሮን የእሚጋርደው እና ህሊናቢስ የእሚያደርገው ፤ የተጋነነ የሐገር ፍቅር ፤ በሰው ልጅ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ የነበረ ፖለቲካዊ ቀውስ ነው ።
ከእዛኽም በአሻገር ጅንጎይዝም ወይንም ሾቨኒዝም ፤ እንደ አንድ ፡ ከሐገር ፍቅር ጋር የተያያዘ የተሳሳተ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በግለሰብ ወይንም በጥቂት የፖለቲካ ቡድኖች ብቻ ተወስኖ የእሚቀር ክስተት ሰአይሆን ፤ አንዳንድ ግዜ ፤ በተለያዩ ታሪካዊ ምክንያቶች ወይንም የጂንጎይዝምን ፖለቲካ የአንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ቀዳሚ አጀንዳ እንዲሆን ግፊት በእሚያደርጉ የፖለቲካ ኃይላት ቅስቀሳ ፤ ወደ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ደረጃ ማደግ የእሚችል ነው ።
ይኽን መሰል ገጽታ የአለው ጂንጎይዝም አደጋው የእሚመነጨው ፤ በዋናነት ከተገቢው እና ከአዋጭው መንገድ የሕዝብን እና የመንግሥትን ትኩረት በቋሚነት ማሳት በመቻሉ ነው።
አንድ ሕዝብ እና መንግሥት ደግሞ በእዚኽ መልኩ የትኩረት አቅጣጫ መዋዠቅ ውስጥ እንዲ ገባ ፤ ለእዚኽ የትኩረት መዋዠቅ ተጋላጭ መሆን አለበት ።
በሌላ አገላለጽ ፤ ጂንጎይዝም በውስብስብ ማሕበራዊ ትብትብ ውስጥ በተያዘ እና በእዚኽ ማሕበራዊ ትብትብ በተዳከመ ማሕበረሰብ ውስጥ የእሚከሰት ወይንም ብዙ ቀዳሚ ምክንያቶች በአዳከሙት ማሕበረሰብ ላይ የእሚበቅል የማሕበረ ኢከነሚ ቀውስ ውጤት የሆነ የፖለቲካ አረም ነው።
ምንም እንኳን እያንዳንዳቸውን ፤ የጂንጎይዝም መፍለቂያ አረንቋን ሊፈጥሩ የእሚችሉ ችግሮች መዘርዘር ቢያስቸግርም ፤ በእኔ እምነት የእሚከተሉት ዋነኛዎቹ ናቸው፦ በሐገር ደረጃ የዳበረ የሥራ እና የምርታማነት ስነ ልቦና አለመኖር ወይንም ኢከነሚያዊ ቀቢጸ-ተስፈኝነት መንሠራፋት ፣ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለዜጎች በሙሉ ክፍት መሆኑ ፣ የፖለቲካ ውስብስብነት ፣ ተሰሚነት እና አቅም የአላቸው ፖለቲከኞች በጀብደኝነት ስሜት ፣ ተስፋ በመቁረጥ ፣ ወዘተ በእሚገቡበት ትምክኽት ፣ እንደ እዚኽ ዓይነት ፖለቲከኞች ጉዳዩን ከዘመናዊ የሕዝባዊ ፖለቲካ ባሕሪ የተነሳ ፤ በተለይ ከፕሮፖጋንዳ ጋር አያይዘውት ጂንጎይዝምን የፖለቲካ አጀንዳቸው ሲያደርጉት ፤ የእሚሉት ዋነኞቹ ናቸው።
በእዚኽ ዝርዝራችን መሠረት ፤ ሕዝብን እንደ ሕዝብ ለጂንጎይዝም ፖለቲካ ተጋላጭ እንዲሆን ከእሚያደርጉት ነገሮች ቀዳሚው ፤ ሕዝብ እንደ ሕዝብ መሠረታዊ እና የእማይቀየሩ የኢከነሚ እና የፒለቲካ መርሆች ላይ የፀና እምነትን እንደ ባሕል ሳያዳብር ሲቀር ነው ።
ምንም እንኳን ፤ የሰው ልጆች በምድር ላይ እስከ አሉ ድረስ ፤ አታላዮች እና ተታላዮች ኹሌም መኖራቸው የእማይቀር ቢሆንም ፤ ማሕበረሰብ እንደ ማሕበረሰብ በቋሚነት ፤ ለምሳሌ ፦ ወደ ኢከነሚያዊ እድገት የእሚያመጣው ብቸኛ መንገድ ፤ ጠንክሮ በሞያ በመሥራት እና ገቢን መሠረት የአደረገ የወጪ ቁጥጥር እና የቁጠባ አካኼድ በመከተል ነው የእሚለውን ግንዛቤ ፤ በአንድም በሌላም ምክንያት በባሕል ደረጃ መስርቶ ሳያቆም ሲቀር እና ምትኃታዊ ወይንም ገጠመኛዊ የሆኑ ማሕበራዊ እድገት አስተሳሰቦች ፤ በማሕበረሰቡ ውስጥ በእሚገኙ በአንዳንድ ዜጎች ወይንም ንዑስ ቡድናት እንደ እሚገኙ የአመለካከት ችግሮች ሰአይሆን የመሐበረሰቡ ስነ ልቦናዊ መዋቅር ጠቅላላ ወይንም ዋነኛ መገለጫ ሲሆኑ ፤ ሕዝብ እንደ ሕዝብ እንደ ጂንጎይዝም ላሉ ለፖለቲካዊ ሸፍጦች የአለው ተጋላጭነት ይጨምራል ።
በአቋራጭ ፣ በሎተሪ ፣ ድንገት በእሚገኝ የከበረ ማዕድን ፣ ወዘተ ፤ ከመቅስፈት ተወንጭፎ የኃብት ማማ ላይ መቀመጥ ምኞት ፤ የግለሰቦችን ህይወት ከሐዲድ እንደ እሚያስወጣው ፤ አንዳንድ ግዜ መሰል ኢከነሚያዊ ቀቢጸ ተስፈኝነት ጠቅላላ ማሕበረሰብን ያሳተበት ግዜ ቀላል አይደለም ።
ከአውድ አንፃር የትኩረታችን መዓከል ቀቢፀ ተስፈኝነቱ ቢሆንም ትኩረታችን ተፃራሪው ጨልምተኝነቱም በተመሳሳይ ሐገራትን ያደከመበት ታሪክ መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ።
‘የተቃዋሚዎቹ የሥራ ስነ ምግባር እና የካፒታሊዝም መንፈስ (The Protestant Work Ethic and the Spirit of Capitalism [56])’ በእሚለው መጽሐፉ ላይ ፤ ታዋቂው ሶሲዮሎጂስት ማክስ ዌበር ፤ የካፒታሊዝም መሠረቱ ፤ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ላይ የተመሠረቱ ፦ የትጋት ፣ ግዜን ሰስቶ የመጠቀም ፣ ገንዘብን የመቆጠብ ፣ ወዘተ ፤ ባሕላት ናቸው ይላል ።
ይኽንንም ለማሳየት ፤ የአሜሪካ መሥራች አባቶች ከእሚባሉት ግንባር ቀደም የሆነው ፤ ቤንጃሚን ፍራንክሊን ፤ ለአንድ የሐገሩ ወጣት ፤ የጻፈውን ምክር አዘል ደብዳቤ በካፒታሊስት ስረዓት ምሥረታ መባቻ ላይ መሥራች ሊህቃኑ የነበራቸውን ይኽን እምነት ያሳያል ብሎ ይጠቅስዋል ፦
ልብ በል ፤ ብድር ገንዘብ መሆኑን ። አበዳሪዬ ፤ በመክፈያው ቀን ክፍያውን ሳይቀበለኝ ቢቀር ፤ የእዚያን እለቱን ወለድ ወይንም በእዚያኽ ገንዘብ ብሰራ የእማገኘው ገንዘብ ሰጥቶኛል ማለት ነው ። ጥሩ ተበዳሪ እና ትልቅ የብድር መጠን በአለበት ሰው ዘንድ ይኽ ትልቅ ገንዘብ ነው ።
ልብ በል ፤ ገንዘብ ወላድ ፤ ተባዢ ባሕሪ እንደ አለው ። ገንዘብ ገንዘብን መውለድ ይችላል ፣ ልጆቹም ብዙ የልጅ ልጆች መውለድ ይችላሉ ፤ እያለ ይቀጥላል ። አምስት ብር ተመልሶ ሲመጣ ስድስት ይሆናል ፥ እንደገናም ተመልሶ ሲመጣ ሰባት ብር ከሦሥት ሳንቲም ይሆናል ፤ እያለ እያለ መቶ ብር እስኪ ሆን ይቀጥላል ። በበዛ ቁጥር ፤ ተመልሶ ሲመጣም ብዙ እየሆነ ነው ፤ በእዚኽም ትርፉ በፍጥነት ይጨምራል ። አንዲት ወላድ ከብት የእሚገድል ፤ እስከ ሺ ትውልድ የእሚደርሰው ትውልዷን ይገድላል ። ሐያ አምስት ሳንቲምንም የእሚገድል ፤ ይኽ ሐያ አምስት ሳንቲም ሊያመጣ የእሚችላቸውን ብዙ መቶ ብሮች ይገድላል ።
ይኽን አባባል ልብ በል ፤ ክፍያውን በግዜ የእሚፈፅም ሰው የሌላው ሰው ቦርሳ ጌታ ነው የእሚለውን ። እከፍላለኹ ብሎ ቃል በገባው ሰዓት እከፍላለኹ የአለውን መጠን የእሚከፍል ሰው ፤ በጓደኞቹ ኪስ ኹሉ የአለውን ትርፍ ገንዘብ መሰብሰብ ይችላል ። ይኽ ደግሞ አንዳንድ ግዜ ትልቅ ዋጋ አለው ። ከትጋት እና ከቁጠባ ቀጥሎ ፤ አንድን ወጣት በተግባሩ የእሚያሳየው ሰዓት አክባሪነት እና ፍትኃዊነት እንደ እሚያሳድገው ምንም አያሳድገውም ፤ ስለ እዚኽ ፦ በፍፁም የተበደርኸውን ገንዘብ ቃል ከገባህበት ሰዓት እላፊ አንተ ጋር አታቆየው ፤ አለበለዚያ ጓደኞችህ ቦርሳቸውን ለዘላለም ይዘጉብኃል ።
ጥቃቅን የሆኑ ፤ ብድርህን የእሚያበላሹ ተግባሮችን አትኩርባቸው ። የመዶሻህ ድምፅ ከማለዳ 11 ሰዓት ወይንም በምሽት 2 ሰዓት አበዳሪህ ሲሰማ ፤ ለቀጣዩ ስድስት ወር እና ከእዚያኽ በላይ ያስተማምነዋል ፤ ነገር ግን መሥራት ሲኖርብህ ከረንቡላ ስትጫወት ቢያይኽ ወይንም ድምፅህን መሽታ ቤት ከሰማው ፤ እንደ ወጉ በየወሩ ሰአይሆን ብድሬን ዛሬውኑ ክፈለኝ ብሎ በነጋታው ይልክብኃል ።
ከእዛኽም በአሻገር ፤ እዳ እንደ አለብህ አለ መርሳትህን እና እንደ ታማኝ ሰው ጠንቃቃ ሆነህ ስትታይ ፤ የበለጠ ብድር ማግኘት የእምትችል ሰው ያደርግኃል ።
የእራስህ የሆነውን ኃብት በጥንቃቄ እወቅ እና በመጠን ኑር ። ብዙ ተበዳሪዎች የእሚወድቁበት ስህተት ይኼ ነው ። ይኽን ለማስቀረት ፤ ገቢ እና ወጪህን በአግባቡ መዝግብ ። ቢያስጨንቅህም ፤ እያንዳንዱን ጥቃቅን ወጪ ሳይቀር ከዘረዘርኽ ፤ አንድ መልካም ነገር ታስተውላለህ ፤ እንዴት ትንሽ እና ጥቃቅን ወጭዎች በአንድ ግዜ ትልቅ እንደ እሚሆኑ ትገነዘባለህ ፤ በእዚኽም ብዙ ሳይጎዳህ ልታስቀረው የእምትችለውን ወጪ ታውቃለህ ።
በአጭሩ ፤ ወደ ኃብት የእሚያደርሰው መንገድ ከፈለከው ፤ ወደ ገበያ እንደ እሚወስደው መንገድ ግልፅ ነው ። በዋናነት ፤ በኹለት ቃላት ላይ ይቆማል ፤ ትጋት እና ቁጡብነት ፤ ማለትም ፦ ግዜን ወይንም ገንዘብን አታጥፋ ይልቁንም ተጠቀምባቸው ። በታማኝነት ማግኘት የእሚችለውን ኹሉ የእሚያገኘውን እና ማስቀመጥ የእሚችለውን ኹሉ የእሚያስቀምጠው (አስፈላጊ ወጪዎችን ካወጣ በኋላ ) በእርግጠኝነት ኃብታም ይሆናል ።”
“Remember, that time is money. He that can earn ten shillings a day by his labor, and goes abroad, or sits idle, one half of that day, though he spends but sixpence during his diversion or idleness, ought not to reckon that the only expense; he has really spent, or rather thrown away, five shillings besides.
Remember, that credit is money. If a man lets his money lie in my hands after it is due, he gives me the interest, or so much as I can make of it during that time. This amounts to a considerable sum where a man has good and large credit and makes good use of it.
Remember, that money is of the prolific, generating nature. Money can beget money, and its offspring can beget more, and so on. Five shillings turned is six, turned again it is seven and three pence, and so on, till it becomes a hundred pounds. The more there is of it, the more it produces every turning, so that the profits rise quicker and quicker. He that kills a breeding sow, destroys all her offspring to the thousandth generation. He that murders a crown, destroys all that it might have produced, even scores of pounds.
Remember this saying, the good paymaster is lord of another man’s purse. He that is known to pay punctually and exactly to the time he promises, may at any time, and on any occasion, raise all the money his friends can spare. This is sometimes of great use. After industry and frugality, nothing contributes more to the raising of a young man in the world than punctuality and justice in all his dealings; therefore, never keep borrowed money an hour beyond the time you promised, lest a disappointment shut up your friend’s purse for ever.
The most trifling actions that affect a man’s credit are to be regarded. The sound of your hammer at five in the morning, or eight at night, heard by a creditor, makes him easy six months longer; but if he sees you at a billiard-table, or hears your voice at a tavern, when you should be at work, he sends for his money the next day; demands it, before he can receive it, in a lump.
It shows, besides, that you are mindful of what you owe; it makes you appear a careful as well as an honest man, and that still increases your credit. Beware of thinking all your own that you possess, and of living accordingly. It is a mistake that many people who have credit fall into. To prevent this, keep an exact account for some time both of your expenses and your income. If you take the pains at first to mention, it will have this good effect: you will discover how wonderfully small, trifling expenses mount up to large sums; and will discern what might have been, and may for the future be saved, without occasioning any great inconvenience.
In short, the way to Wealth, if you desire it, is as plain as the way to Market. It depends chiefly on two words, industry and frugality, i.e., waste neither time nor money, but make the best use of both. He that gets all he can honestly, and saves all he gets (necessary expenses excepted) will certainly become rich; [56]“
አንድ ሰው ፤ የትኛውንም የኢከነሚክስ ሳይንስ እውቀት እና ከፍተኛ የንግድ ሥራ ልምድ ቢኖረው ፤ በእዚኽች የሰንበት ትምህርት ቤት ምክር ከእምትመስለው በቤንጃሚን ፍራንክሊን በምክር መልክ ከቀረበቸው ኃሳብ ውጭ ፤ በእውነት እና በዘላቂነት ካፒታሊስት ሊሆን አይችልም ።
ይኽ ማለት ፤ በውርስ ፣ በሎተሪ ፣ በማጭበርበር ወይንም በመሰል ገጠመኝ ኃብት ያገኘ ሰው የለም ሰአይሆን ፤ ጉልበቱን እና ካፒታሉን በአትራፊ ሥራ ላይ በትጋት እና በቁጥብነት ሳያውል ኃብት አግኝቶ ፤ አቆይቶ ሊያባዛው ወይንም ዘላቂ ካፒታሊስት ሊሆን የእሚችል ሰው የለም ፤ ለማለት ነው ።
የኢከነሚክስ ሳይንስ አባት የእሚባለው አዳም ስሚዝም ይኽን ያስቀምጣል ፦
“ የአንዲት ሐገር ዓመታዊ የሥራ መጠኗ ነው ፤ በእዛች ሐገር ውስጥ ለአሉት ዜጎች ዓመታዊ ቀለባቸው ፤ ይኽ ሐገራዊ ዓመታዊ ቀለብ ቀጥታ በሐገራዊ ሥራ የእሚመረተው ወይንም በተመረተው ነገር ከሌላ ሐገር ምርት ጋር የእሚለወጥ ሊሆን ይችላል ።”
“The annual labor of every nation is the fund which originally supplies it with all necessaries and conveniences of life which it annually consumes, and which consist always either in the immediate produce of that labor, or in what is purchased with that produce from other nations. [48]“
በእርግጥ ይኽን መሰሉን ፤ ሳይንሳዊ መርህ ወስደው የኢከነሚክስ መሐይማን ማርክሲስቶች በካርል ማርክስ መሪነት ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ መኼዳቸው ቢታወቅም ፤ ቅሉ ፥ የማሕበረሰብን ኢከነሚያዊ ጤና እና ህልውና የእሚያረጋግጡ ፦ በመልካም ሥራ የመትጋት ፣ ግዜን በስስት መጠቀም ፣ የገንዘብ ቁጠባ ፤ ወዘተ ፤ የመሳሰሉት ኃሳቦች ፤ በሕዝብ ውስጥ ሰርፀው በቀላሉ በእማይወዘወዙበት ደረጃ መሆን አለባቸው ።
በተለያየ ምክንያት ፤ ይኽ በእማይሆንበት እና ማሕበረሰብ በእነዚኽ እሴቶች ላይ ፤ የተደላደለ የህሊና ወይንም የስነምግባር ባሕል ሳያዳብር በእሚቀርበት ግዜ ፤ ማንኛውም ፅንፈኛ ፖለቲካዊ አካኼድ ፤ ጂንጎይዝምንም ጨምሮ ፤ ሕዝብን አወዛውዞ ከመንገድ ሊያስወጣው ይችላል ።
ምክንያቱም ፦ ጂንጎይዝሙ የእንግሊዘኛው ቃል ዋርሞንገር (Warmonger) ወይንም ይኽንኑ ቃል ወደ አማርኛ ብንመልሰው ከሰርቶአደሩ በተነጻጻሪ ጦርአደሩ ወይንም በጦርነት ድል በእሚገኝ ኢከነምያዊውም ሆነ ሌላ ግዳይ ወይንም ምርኮ የመከብር አካኼድን ሊጠቀም የእሚችል በመሆኑ።
ፖለቲካ እንደ ሌላው የሞያ መስክ ፤ በሞያ የብቃት ማረጋገጫ የእሚተዳደር ማሕበራዊ ተቋም ስለ አልሆነ ፤ ማንም ተነስቶ ሊሳተፍበት የእሚችል ነው ።
ፖለቲካ እንደ ማንኛውም የሳይንስ መስክ ፤ ሳይንስ ቢሆንም እና ፖለቲከኛውም ፤ እንደ ማንኛውም ሞያተኛ ፥ ሞያተኛ ቢሆንም ፤ በፖለቲካው መስክ እንደ ሌላው መስክ ፤ ለተሳትፎ ቅድመ ኹኔታ ማስቀመጥ አለ መቻሉ የተለየ ያደርገዋል ።
ለምሳሌ ፦ በህክምናው ዓለም ፤ አንድ ሰው ሕጋዊ ዶክተር ከመሆኑ እና እየመረመረ መድኃኒት ማዘዝ ከመጀመሩ በፊት ፤ ቢያንስ ሰባት አመታት ህክምናን በሳይንሳዊ ቲየሪ እና በተግባር ደረጃ እውቅና በአለው የትምህርት ተቋም ውስጥ አጥንቶ ፤ በጥናቱ መሠረት በቂ እውቀት አዳብሮ እንደ ሆነ እና እንደ አልሆነ ለማወቅ ፈተና ተፈትኖ ፤ ይኽንንም ፈተና ከአለፈ ነው እውቅና የአለው ሐኪም ወይንም ዳክተር የእሚሆነው ።
ከእዚኽ ዓይነቱም ማጣራት በኋላ ሾልከው የእሚያመልጡ ያልበቁ ኃኪሞች በአይጠፉም ፤ አንድ ሰው ሕጋዊ የህክምና ፈቃድ ሲኖረው በአብዛኛው ፤ የግል ባሕሪው ችግር ከሌለበት ፤ የእሚያስፈልገው የእውቀት መሠረት አለው ተብሎ ይታመናል ።
ፖለቲካ ግን እንደ መስክ ከእዚኽ የተለየ ነው ፤ አንድ ሰው ተነስቶ የፖለቲካ ሊቅ ነኝ ሲል ፤ አይ የፖለቲካ ሳይንስ ዲግሪ የለህምና ፖለቲከኛ አይደለህም ወይንም የፖለቲካ ሳይንስ ድግሪ አለህ እና ሰርተፊኬት የአለው ፖለቲከኛ ነህ ማለት አይቻልም ።
ምክንያቱም ፦ ፖለቲከኛነት የፖለቲካ ሳይንስ እውቀት የእሚፈልግ ቢሆንም ፤ በመርህ ደረጃ በመሠረታዊ የፖለቲካ ባሕሪ ምክንያት ፦ የሰዎችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ፤ በአላቸው የፖለቲካ ሳይንስ እውቀት ደረጃ መገደብ አይቻልም ። ይኽም በመሆኑ እና የፖለቲካ መስክ ለኹሉም የሐገር ዜጎች በእኩልነት ያለምንም ሌላ ተጨማሪ መመዘኛ ክፍት በመሆኑ ፤ በአንድ ሐገር ውስጥ የእሚገኝ ማንኛውም ዜጋ ተነሰቶ ፖለቲከኛ የመሆን እድል አለው ፤ የፖለቲካ ስልጣን በአጭር የመክበሪያ መንገድ አድርጎ የእሚወስደውን ወይንም ሌላውን አባያ ጨምሮ ።
ይኽ ደግሞ ፤ በዘመነ ሕዝባዊ ፖለቲካ ፤ የዴሞክራሲ ተቋማት እና የመንግሥት ሕግ የማስከበር አቅም በአልዳበሩበት ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ውስጥ ፤ የፕሮፖጋንዳ አጠቃቀምን የተረዳ የተደራጀ የምዝበራ ቡድን ወይንም ልዩ ሕዝብ የመቀስቀስ ተሰጥዖ የአለው አንድ ጀብደኛ ፖለቲከኛ ፤ በቀላሉ የፖለቲካ ስልጣን መያዝ እንዲችል በር መክፈቱ የእማይቀር ነው ።
ኃይ ባይ በሌለበት ወይንም በአንድ መሐበረሰብ ውስጥ ጠንካራ ፓለቲካዊ ፣ ኢከነሚያዊ እና ሕዝባዊ ተቋማት በሌሉበት ኹኔታ ፤ ዘመን ያመጣቸው የአደረጃጀት ግንዛቤዎች ፤ የስነምግባር ችግር በአላቸው ሰዎች እጅ ከገቡ ፤ በእነዚኽ እኩያን ለፖለቲካ ስልጣን መያዣነት ሊውሉ ይችላሉ ። የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች ፤ ከተራ ዘራፊነት ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ያሉበት ዘመን ላይ እንገኛለን ።
የአሜሪካን ፤ የፌደራል ምርመራ ጽህፈት ቤት (Federal Bureau of Investigation) ፤ ስለ ተደራጁ የወንጀል ቡድኖች በድረ ገፁ ላይ እንደ እዚኽ ይላል ፦
“የፌደራል ምርመራ ቢሮ ፤ የወንጀል ድርጅትን ፤ የራሱ የሆነ የእሚታወቅ የስልጣን ተዋረድ ወይንም መሰል ተነፃፃሪ መዋቅር የአለው እና በጉልህ ወንጀል ድርጊት ላይ የተሰማራ የግለሰቦች ስብስብ ወይንም ቡድን ብሎ ይተረጉመዋል ።”
“The FBI defines a criminal enterprise as a group of individuals with an identified hierarchy, or comparable structure, engaged in significant criminal activity.”
ይኽም ማለት ፤ የተደራጁ የወንጀል ቡድኖችም ፤ የፖለቲካ ስልጣንን በመያዝ ምዝበራ ማካኼድ ይቻላል ብለው ከአመኑ እና ማንነታቸውን ተርድቶ ሊያስከትሉ የእሚችሉትን ችግር አስቀድሞ በመረዳት ፤ ይኽን ከማድረግ ፤ በአግባቡ ሊያግዳቸው የእሚችል ዴሞክራሲያዊ እና ሕጋዊ ኃይል ከሌለ ፤ የአደረጃጀታቸው አቅም ፤ በተለይ በፕሮፖጋንዳ ከታገዘ ፤ ጂንጎይስቱን ጨምሮ ቦዘኔውን የመንግሥት ስልጣን ወንበር ላይ ሱፍ አልብሶ ሊያስቀምጠው ይችላል ።
ሆኖም ግን ፖለቲካ ፤ ማንም ዘው ብሎ ሊገባበት የእሚችልበት መስክ ቢሆንም ፤ ከሌሎች መስኮች እጅግ በላቀ ደረጃ ውስብስብ ፣ ሰፊ እና ፈታኝ የሆነ መስክም ነው ። ማንም ያለምንም የእሚታወቅ ቅድመ ኹኔታ ሊገባበት ቢችልም ፤ በቀላሉ ውጤታማ የእሚኾንበት አይደለም ።
ይኽም የፖለቲካ ውስብስብነት ፤ ፖለቲከኞችን እና ፖለቲካዊ ኃሳቦችን የመመዘኑን እና የመለየቱን ሥራ ትንሽ ከባድ ስለ እሚያደርገው ፤ የፖለቲካ ማሕበረሰባትን ተጋላጭነት ከፍ የእሚያደርገው ሌላው ምክንያት ነው ።
ጃን ዣክ ሩሶ ፤ የተባለውን የፈረንሳይ የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪ ፤ ዘመናዊ የሰው ልጅ የደረሰበት የአስተሳሰብ እመርታ ነፀብራቅ ነው ሊባልለት የእሚችለውን እና ማሕበራዊ ውል (Social Contract) የእሚለውን ጽሑፍ ያነበበ ሰው ፤ ሩሶ ከእዚኽ ታሪካዊ ጽኹፉ ትንሽ ቀደም ባለው ሌላ ጽሁፉ ፤ የሰው ልጅ ምክንያታዊነት ማደግ ፤ የልዩነት እና የጭቆና ምንጭ ነው ብሎ መጻፉን ሲያነብ ፤ የፖለቲካው መስክ ፤ እንኳን ለመደበኛው ፖለቲከኛ እና ለሰፊው ሕዝብ ፤ እንደ ሩሶ ላሉ ስመ ጥር የፖለቲካ ሳይንስ ሊህቃን እና ፈላስፎች ውስብስብነቱ እና ስፋቱ አደናጋሪ ኹኔታ መፍጠር የእሚችል መሆኑን የእሚያሳይ ይመስለኛል ።
ሩሶ ፤ ዲስኩር በአልኩልነት ላይ (Discourse on inequality) በእሚለው መጽሐፉ ላይ ፤ ማሕበራዊ ቀውስ ምንጩ አልኩልነት ነው ፤ የአልኩልነት ምንጩ ስልጣኔ ነው ፤ የስልጣኔ ምንጩ ደግሞ ግንዛቤ ነው የእሚል ኃሳብ አቅርቧል ።
የእዚኽ ዓይነቱ አስተሳሰብ ፖለቲካዊ እንደምታው ደግሞ ግልፅ ነው ፦ በማሕበረሰብ ውስጥ የእሚታይ ፤ ከሰው ልጆች ተሰጦ ፣ ትጋት ፣ ግንዛቤ ፣ ወዘተ ፤ ልዩነት የእሚመጣው ፤ አልኩልነት (እኩል አለ መሆን) የመጣው ከስልጣኔ ነው ፤ የሰው ልጆች ስልጣኔ መሠረቱ ደግሞ የሰዎች ግንዛቤ ማደግ ነው ፤ ስለ እዚኽ የማሕበራዊ ቀውስ መንስኤ የሆነው አልኩልነት እንዲጠፋ ፤ ስልጣኔን እና የሰው ግንዛቤ እድገት መግታት አለብን የእሚል ፤ እንደ እሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም ።
ሩሶ ፤ ማሕበራዊ እድገት ነው በሰዎች መካከል የነበረውን ተፈጥሮዋዊ እኩልነት ያጠፋው ወይንም አልእኩልነትን ያመጣው ይላል ፦
“የሰው ልጅን አዕምሮ በቋሚነት የእሚያሰቃዩ ፦ በኑሮ ዘይቤ መካከል የአለው ትልቅ ልዩነት ፣ የአንዳንዶች ልክ አልባ ሥራፈትነት ፣ የአንዳንዶች ገደብ የለሽ ሰራተኝነት ፣ ስሜታዊ ምኞቶቻችንን ለማነሳሳት እና ለማርካት የአለው አመቺነት ፣ ሰውነታቸውን ከመጠን በላይ እያሞቀ እና አልፈጭ እያለ የእሚያስቸግራቸው የተትረፈረፈው የኃብታሞች ምግብ ፣ በተቃራኒው ደግሞ ብዙ ግዜ ለርኃብ ማስታገሻ እንኳን የእማይበቃው ፍርፋሪው እናም እድሉን ሲያገኙ በመስገብገብ በልተው ራስቸውን ለቁንጣን እንዲ ዳርጉ የእሚያደርጋቸው የነዳያን ምግብ ፤ እነ እዚኽ ኹሉ ፥ የእሚያስመሹን ፤ ኹሉ ዓይነት ከመጠን ማለፎች ፤ ያልተመጠነው ማንኛውም ጉጉት ፣ መዛል ፣ የዓዕምሮ ድካም ፣ በኹሉ ዓይነት የህይወት ኹኔታ ውስጥ ያሉ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ህመሞች እና ጭንቀቶች ፤ እነ እዚኽ ገዳይ የሆኑ ፤ አብዛኛዎቹ ችግሮቻችን የራሳችን ሥራ ውጤት መሆናቸውን እና ኹሉንም ሊባል በእሚችል ደረጃ ተፈጥሮ የደነገገችልን ቀላል ፣ ወጥ እና የተነጠለ ኑሮ በመኖር ልናስወግደው እንደ እምንችል ግልፅ ማስረጃዎች ናቸው ።”
“The great inequality in manner of living, the extreme idleness of some, and the excessive labour of others, the easiness of exciting and gratifying our sensual appetites, the too exquisite foods of the wealthy which overheat and fill them with indigestion, and, on the other hand, the unwholesome food of the poor, often, bad as it is, insufficient for their needs, which induces them, when opportunity offers, to eat voraciously and overcharge their stomachs; all these, together with sitting up late, and excesses of every kind, immoderate transports of every passion, fatigue, mental exhaustion, the innumerable pains and anxieties inseparable from every condition of life, by which the mind of man is incessantly tormented; these are too fatal proofs that the greater part of our ills are of our own making, and that we might have avoided them nearly all by adhering to that simple, uniform and solitary manner of life which nature prescribed. [57]“
ቀጠል አድርጎ ይኽን ልናስቀረው እንችል የነበረውን ሰቆቃ ያስቻለውን ልዩነትን ያመጣው ስልጣኔ ወይንም ማሕበራዊ እድገት ፤ በተራው ፥ ያስቻለው እነ ሶቅራጠስ የእሚሟገቱለት ግንዛቤ ነው ፤ በማለት ግንዛቤን ማሳደግ የወንጀል ያኽል ሲኮንነው ይገኛል ።
ለሩሶ የሰው ልጅ ምክንያታዊነት ወይንም ግንዛቤ ፤ እነ ሶቅራጠስን መሰል ፈላስፎች እንደ እሚሉት የሰውን ልጅ ከእንሰሳ የእሚለይ እና ከተለያዩ አደጋዎች ጠብቆ ህልውናውን ያስቀጠለለት አይደለም ። የሰው ልጅ ፦ የማወቅ ፣ የመማር ፣ የመመራመር እና የመሻሻል ምንጭ የሆነው ግንዛቤው ጎጂ እንጂ ጠቃሚ ባለ መሆኑ አላስፈላጊ ነውም ፤ ለመኖር ማገናዘብ አያስፈልገንም ብሏል ፦
“ምንም እንኳን ሶቅራጠስ እና የእርሱን መሰል አዕምሮ የአላቸው ፤ መልካም ጠባይን በምክንያታዊነት መጨበጥ እንችላለን ቢሉም ፤ የመኖሩ ጉዳይ በምክንያታዊነቱ ላይ ብቻ ቢደገፍ ኖሮ ፤ የሰው ልጅ ህልውና ገና ጥንት ያበቃ ነበር ።”
“Although it might belong to Socrates and other minds of the like craft to acquire virtue by reason, the human race would long since have ceased to be, had its preservation depended only on the reasonings of the individuals composing it. [57]“
የሰው ልጅ ግንዛቤው እየጨመረ ፤ በእዚያኽም ምርታማነት እና ስልጣኔው ሲያድግ ፤ ፍላጎቱ እየበዛ እና የእሚያስፈልገውን ነገር ኹሉ በራሱ ሥራ ብቻ ከማሙዋላት ይልቅ የራሱን ትርፍ ምርት ከሌሎች ትርፍ ምርት ጋር መቀያየርን የበዙትን ፍላጎቶቹን ማሟያ መንገድ ሲያደርገው ፤ ጭቆና እና አልኩልነት ተከስቷል ይላል ሩሶ ፦
“የሰው ልጆች ፤ በገጠራማ ጎጃቸው ረክተው እስከ ቀሩ ድረስ ፥ ከእንስሳት ቆዳ ተገኝቶ በእሾህ ወይንም በአሳ አጥንት የእሚሰፋው ልብስ ይበቃኛል እስከ አሉ ድረስ ፣ ራሳቸውን በላባ እና በዶቃ ፣ ሰውነታቸውን የተለያየ ቀለም በመቀባት ብቻ እስከ አስዋቡ ድረስ ፣ ትኩረታቸው ቀስት እና ደጋናቸውን ማሻሻል እና የተሳሉ የድንጋይ መሳሪያዎች ማዘጋጀት እና የአሳ ማጥመጃ ጀልባ እና እንደ ነገሩ የሆኑ የሙዚቃ መሳሪያ መሥራት ላይ እስከ አተኮሩ ፤ በሌላ አገላለፅ ፤ በአንድ ሰው ብቻ የእሚተገበሩ ተግባራት ብቻ ሲሰሩ ፤ ራሳቸውን የሕብረት ሥራ ባልሆኑ ተግባራት ላይ በወሰነቡት ወቅት ፤ ተፈጥሮ በወሰነችላቸው ዘመን እና ከነፃ እና እኩል ማሕበራዊ መስተጋብር የእሚገኘውን ደስታ እያጣጣሙ ፣ ጤነኛ ፣ እውነተኛ እና ደስተኛ ህይወት ነበራቸው ። ነገር ግን ፤ ልክ አንዱ ሰው የሌላውን ሰው እርዳታ መፈለግ ከጀመረበት ሰዓት አንስቶ ፣ ለአንዱ ሰው ለኹለት ሰው የእሚበቃ ስንቅ የመኖሩን ጥቅም ከተረዳበት አንስቶ ፤ እኩልነት ጠፋ ፣ የንብረት ባለቤትነት ተጀመረ ፣ ሥራ ከሰው የእማይነጠል ሆነ ፣ ትላልቅ ደኖች የሰው ልጅ በላቡ የእሚያጠጣቸው ወገግ ያሉ ማሳዎች ሆኑ ፤ ባርነት እና ሰቆቃም አብሮ ከሰብሎቹ ጋር ለማቆጥቆጥ ግዜ አልፈጀበትም ።”
“So long as men remained content with their rustic huts, so long as they were satisfied with clothes made of the skins of animals and sewn together with thorns and fish−bones, adorned themselves only with feathers and shells, and continued to paint their bodies different colours, to improve and beautify their bows and arrows and to make with sharp−edged stones fishing boats or clumsy musical instruments; in a word, so long as they undertook only what a single person could accomplish, and confined themselves to such arts as did not require the joint labour of several hands, they lived free, healthy, honest and happy lives, so long as their nature allowed, and as they continued to enjoy the pleasures of mutual and independent intercourse. But from the moment one man began to stand in need of the help of another; from the moment it appeared advantageous to any one man to have enough provisions for two, equality disappeared, property was introduced, work became indispensable, and vast forests became smiling fields, which man had to water with the sweat of his brow, and where slavery and misery were soon seen to germinate and grow up with the crops. [57]“
ከእዚኽ የሩሶ መጽሐፍ ዋና ዋና ነጥቦቹን አውጥተን ለማየት እንደ ሞከርነው ፤ ዓለም ኹሉ እስከ ዛሬ የእሚያደንቅለትን እና የሰው ልጅ ከባርነት ለመውጣት ፤ ተፈጥሮዋዊ ነፃነቱን በተፈጥሮ ሕግ አግባብ የእሚያከብርለት ማሕበራዊ ውል ማሰር ነው የአለበት ብሎ ፤ ማሕበራዊ ውል የእሚለውን መጽሐፍ የጻፈው ሩሶ ፤ ድንገት ዞሮ ብሎ በፍትሕ እንድ እንኖር ከእውቀት እንራቅ የእሚል ፤ ፀረ እውቀት እና ፀረ ስልጣኔ የፍትሕ መላምት ይዞ ሰንብቶ ነበር ።
ከሩሶ ሌላ ፤ በቅርቡ የዓለም ታሪክ ፤ ማርክሲዝም ይዞ የመጣው ፍልስፋና ፤ የፖለቲካን ውስብስብነት እና ስፋት ከእዚኽም የተነሳ አምታችነት ፤ የፖለቲካን ውስብስብነት እና አምታችነት ማሳያ ሆኖ እንደ ኹለተኛ ምሳሌ መቅረብ ይችላል ።
ምንም እንኳን ማርክሲዝም ፤ በተጠላለፉ እና ውስብስብ ፖለቲካዊ ፍልስፍናዎች እና መዋቅሮች ቢሸፋፈንም ፤ የከምኒዝም የኢከነሚ ፖሊሲ ፤ ‘ቀምቶ እኩል መካፈል’ በእሚል ማባበያ ፤ በነውጠኛ የፖለቲካ ቡድን የተቀማው የሕዝብ እና የግል ኃብት ፤ በእዚኽ ማባበያ በነጣቂ አብዮት ወደ ስልጣን የመጣውን አምባገነን ቡድን ለማጠናከር ይውላል በእሚል ተራ አገላለፅ ሊቀመጥ ይችላል ።
በእርግጥ ይኽ አገላለፅ ፤ ሕብረተስባዊነት ፣ ማሕበራዊ ፍትሕ ፣ ሰፊው ሕዝብ የሆነው የሠራተኛው አምባገነንነት ፣ ወዘተ ፤ የእሚሉት የከምኒዝም ማባበያዎች አደናግሮዋቸው ከምኒዝምን እንደ ፍትኃዊ ፖለቲካዊ ስረዓት የእሚመለከቱ ስዎችን ቅር ሊያሰኝ ይችላል ።
እውነታው ግን ፤ ከምኒዝም የግል ንብረት ዘረፋ ነው ብሎ አግዶ ፤ የሰዎችን ብሎም የሐገራትን ንብረት በአደባባይ የእሚዘርፍ የዘረፋ ስረዓት ነው ።
የፖለቲካ ውስብስብነት ግን ብዙዎችን ፤ በማርክሲዝም የተለፈፈው ሕዝባዊነት እና እኩሉነት አማሏቸው ፤ ማርክሲዝምን ለራሳቸው እና ለሐገራቸው ጥፋት እንዲ ያራምዱ አድርጎዋቸዋል ።
ከሶሻሊዝም እና ከሊህቃን ጋር ጉዞ ወደ ባርነት (The road to serfdom : with the intellectuals and socialism) በእሚል ርዕስ ፤ የከምኒስቶች የማሕበራዊ ፍትሕ አካሔድ መጨረሻው ሕዝባዊ ባርነት ነው የእሚሆነው ብሎ ፍሬድሪክ ሔይክ በጻፈው መጽሐፍ መግቢያ ላይ መቅድም የጻፈው ዋልተር ዊልያምስ ፤ ከምኒዝም የሕዝባዊ መንግሥት ፍልስፍና ለእሚመስላቸው ሐቀኛ የሕዝብ ተቆርቋሪዎች ይኽን ማሳሰቢያ ያስቀምጥላቸዋል ፦
“በጎ አሳቢ ሶሻሊስቶች ፤ ሐይክ እንደ እሚለው እውነተኞች ከሆኑ ፤ ባለ እንጀራን ወይንም ወንድም ዜጋን ከራስ ኪስ ገንዘብ አውጥቶ መርዳት ሊደነቅ እና ሊመሰገን የእሚገባው መሆኑን ማወቅ አለባቸው ። ባለ እንጀራን ወይንም ወንድም ዜጋን ለመርዳት የሌላ ሰው ኪስ ውስጥ እጅን ማድረስ ግን ፤ ሌብነት እና በየትኛውም የህሊና ፍርድ ሊወገዝ የተገባው ነው ።”
“Well-intentioned socialists, if they are honest people as Hayek contends, should be able to appreciate that reaching into one’s own pocket to assist one’s fellow man is laudable and praiseworthy. Reaching into another’s pocket to do so is theft and by any standard of morality should be condemned. [58]“
ከኃብታም ዘርፌ ለድኃ አከፋፍላለኹ በእሚል የእሚመራ ሕዝባዊነት እና ሕጋዊ ፍትሕ በአይኖርም ፤ ሰዎች ግን በማርክሲዝም አምታችነት ፤ ለእዚኽ ኃሳብ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል ። ይኽ የከምኒዝም ኃሳብ በፅንሰ ኃሳብ ደረጃም ብቻ ሰአይሆን ፤ ከምኒዝም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ፤ የዘረፋ መረብ ዘርግቶ ፍፁማዊ አምባገነን የሆነውን የፖለቲካ ስልጣኑን ለማጠናከር ዓለምን ሲዘርፍ የነበረ የዘረፋ መዋቅር እንደነበር የከምኒዝምን እንቅስቃሴ የእሚከታተሉ ሰዎች ያውቃሉ ።
በስታሊን የእሚመራው የራሻው ከምኒስት ፓርቲ ፤ የስፔን ሶሻሊስቶችን ማገዝ በእሚል ወደ ስፔን ፖለቲካ እጁን ከአስገባ በኋላ ፤ ከግምጃ ቤታቸው 500 ቶን ወይንም 500,000 ኪሎ ግራም ወርቅ በመዝረፉ ፤ ኹለቱ ሐገራት ለረዥም ዘመን የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ሰጣ ገባ ውስጥ ቆይተዋል ፦
“እ.አ.አ. በ1936 ዓ.ም. የስፔን የእርስ በእርስ ጦርነት ሲጀምር ፤ ከ500 ቶን በላይ የእሚሆን ስፔን ባንክ የነበረ ወርቅ - በእዚያን ግዜ በነበረው ዋጋ ወደ 500 ሚልዮን ዳላር የእሚያወጣ - ለጥበቃ በእሚል ወደ ሶቭየት ተወስዷል ። … ወርቁ ሲተላለፍ ምንም ውል ያልነበረ ሲሆን ፤ ጉዳዩ የተፈፀመው በስታሊን እና በስፔን ጠቅላይ ሚንስተር ካባሌሮ መካከል በተደረገ ሚስጥራዊ የቴሌግራም ልውውጥ ነበር ። ይኽ ግንኙነት ለመካኼዱ የነበረው ብቸኛ ማስረጃ ፤ በስታሊን ለኤን.ኬ.ቪ.ዲ ሰላይ አሌክሳንደር ኦርሎቭ የተላከው ፤ የእሚከተለውን ትዕዛዝ የያዘው ቴሌግራም ነው ፦
‘… የስፔንን የወርቅ ክምችት ወደ ሶቭየት ሕብረት ለማጓጓዝ ፤ ከስፔን መራሒ መንግሥት ጋር ሥራ … ይኽ ሥራ በእጅግ ከፍተኛ ሚስጥራዊነት ይሰራ … ስፓኞች ለጭነቱ ደረሰኝ እንድ እትፈረም ከጠየቁህ እምቢ በል ። እደግመዋለሁ ፤ ምንም ዓይነት ሰነድ ለመፈረም እምቢ በልና ፤ ሕጋዊ ደረሰኝ ሞስኮ ባለው የመንግሥት ባንክ ተፈርሞ ይመጣል በል ።”
“In the outbreak of the Spanish Civil War, in 1936, more than 500 tons of the Bank of Spain’s gold – with a value at that time of more than $500 million was shipped to the Soviet Union to keep it safe. … the agreement on the gold shipment was never documented because the correspondence mostly relied on coded telegraph between Stalin and Spanish Prime Minister Caballero. The only evidence of this communication was from Stalin to his NKVD spy Alexander Orlov, containing the following order:
… arrange with the head of the Spanish Government, Caballero, for the shipment of the gold reserves of Spain to the Soviet Union … This operation must be carried out with the utmost secrecy … if the Spaniards demand from you a receipt for the cargo, refuse. I repeat, refuse to sign anything and say a formal receipt will be issued in Moscow by the State Bank. [59]“
ይኽ በዛሬው ገበያ ወደ 20 ቢልዮን ዳላር በላይ የእሚያወጣ የስፔን ወርቅ ፤ ሞስኮ ከገባ በኋላ ፤ ሞስኮው ለስፔን የሰጠችው እርዳታ ወጪ በወርቁ ተሸፈነ በእሚል ስፓኞች ወርቃቸውን ሳያዩት[2] ቀርተዋል ።
ምንም እንኳን እንደ ስታሊን ያሉ ጥቂት የከምኒስት ከፍተኛ አመራሮች ፤ ከምኒዝም የዘረፋ ስረዓት እንደ ሆነ ባይጠፋቸውም ፤ ቀላል የእማይባሉ የዘመናዊ ከምኒዝም ፍልስፍና ተከታዮች ፤ አንዳንዴ እንዲያውም የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራንን እና ፖለቲከኞችን ጨምሮ ፤ በብዙ ታላላቅ ቃላት የተሽቆጠቆጠው የከምኒዝም የኢከነሚ ፖሊሲ ፤ የኢከነሚያዊ ፍትሕ መንገድ መንግሥታዊ ዘረፋ ነው የእሚል እንደሆነ ፤ አውቀው ወይንም በቸልተኝነት ይዘነጉት እና ቀጥተኛ እና ትክክለኛውን የሥራ ፣ የቁጠባ እና የፅናቱን መንገድ ትተው ፤ አዲስ ግኝት የአገኙ እየመሰላቸው ፤ እንደ መንግሥታዊ ዘረፋ የአለውን የኪሳራ መንገድ አስመርጧቸዋል ።
ይኽም በመሆኑ ፤ ማርክሲዝም በፍልስፍና ረገድ ሲጠናም ሆነ በተግባር ሆኖ በተገኘበት አግባብ ሲፈተን ፤ መንግሥታዊ ዘረፋ መሆኑ ቢታወቅም ፤ የዓለም ላብአደሮች ተነሱ በማለት ራሱን ለዓለም ጭቁን ላብአደሮች ተቆርቋሪ እና ተስፋ አምጭ አስመስሎ በማቅረብ ፤ ከአንድ ዓለም ዓቀፋዊ ማዘዣ ጣቢያ እየተመራ የዓለምን ሕዝብ በሙሉ በሶሻሊዝም አብዮት እሳት ማጥመቅ አለብኝ የእሚለው አካኼዱ ፤ ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እጅግ ተጠናክሮ በወጣው የራሺያ መንግሥት እየተመራ ስለ ነበር ፤ የከምኒዝም ጂንጎይዝም ከፍልስፍና አልፎ ከከምኒዝም ውጭ ላሉ ኹሉም ዓይነት የፖለቲካ ስረዓቶች ራሱን ጠላት አድርጎ በማቅረቡ ፤ በተለምዶ ቀዝቃዛ ጦርነት የእሚባለውን አስጀመሯል ።
የቀዝቃዛው ጦርነት ፤ ምንም እንኳን በዋናነት በዋሽንግተን እና በሞስኮው መካከል የእሚደረግ ቢሆንም ፤ የጦርነቱ ዋና ሜዳዎች ግን ከአሜሪካ እና ከራሺያ ውጭ ያሉ ሌሎች የዓለም ሐገራት ነበሩ ።
ከፍተኛ የኒውክለር ቦንብ ክምችት የአላቸው እነ እዚኽ ኹለት የዓለማችን ኃያላን ሐገራት ፤ ቀጥታ እና ግልፅ ጦርነት የማድረጋቸው ስጋት የቀዝቃዝው ጦርነት በቆየበት ዘመን ኹሉ ትልቅ የስጋት ምንጭ የነበረ ቢሆንም ፤ ጦርነቱ እስኪ ያልቅ ድረስ ጦርነቱ የተካኼደው ሌሎቹን የዓለም ሐገራት በዴሞክራሲያዊ ወይንም ሶሻሊስታዉ መንግሥት ስር ለማድረግ በኹለቱ ኃያላን መካከል በእሚደረገው ግብግብ ነበር ።
ከምኒስቶቹ ሲሳካላቸው ፤ የሶሻሊስት አብዮት አስነስተው ፤ ከሞስኮው የእሚታዘዝ አብዮታዊ መንግሥት በስልጣን ላይ እንዲ ወጣ ያደርጋሉ ፤ አሜሪካኖቹ ሲሳካላቸው መንግሥቱ ዘውዳዊ ይኹን ዴሞክራሲያዊ ወይንም ሌላ የሞስኮ ቅርንጫፍ የሆነ መንግሥት እንዳይሆን ያደርጋሉ ።
ቀዝቃዛው ጦርነት የተካኼደበትን አግባብ ስናየው ፤ ከምኒዝም ጠብ አጫሪው ወይንም ደራሹ ፤ ዴሞክራሲ ሰላም ፈላጊው ወይንም ተከላካዩ እንደ ነበረ እንረዳለን ።
ይኽ የኹለቱ ኃያላን ሐገራት የወኪል ጦርነት በአንዲት ታሪካዊ ስህተት ፤ ዓለም ዓቀፋዊ ይዘት የአለው እና ከአንደኛው እና ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት ከአደረሱት ውድመት በላይ ብዙ ጉዳት የእሚያደርስ ጦርነት ያስነሳል ተብሎ በጣም በእሚሰጋበት ወቅት ፤ ጆርጅ ኬነን የእሚባል የአሜሪካ ዲፕለማት ፤ የከምኒዝም ፍልስፍና ችግር የመፍጠር እንጂ ዘላቂ እና ተሻጋሪ አቅም መገንባት ስለ እማይችል ፤ ይኽን ጂንጎይስት ወይንም በእኛ ብቻ ልክ ነን ወይንም እኛ እንበልጣለን በእሚል እብሪት ተቃራኒን ሐገር ፤ በኃይል የመ፟ጫን ፍላጎት ፣ ጦርነት ናፋቂነት ፣ ጦርአዳሪነት (warmongering) ፤ ግልፅ እና ሙሉ ጦርነትን ውድ ከአደረግንበት ፤ የማተራመስ አካኼዱ በግዜ ኺደት የአለውን አቅም አሟጦ ስለ እሚያስጨርሰው ፤ ግልፅ እና ቀጥታ ጦርነት ውስጥ ሳንገባ ይኽን ስጋት መመከት እና ከእዛኽም ማስወገድ እንችላለን የእሚል ስልት ቀይሶ ነበር ።
በፈረንጆቹ በ1946 ዓ.ም. በሞስኮው የአሜሪካን አምባሳደር የነበረው ጆርጅ ኬነን (George Kennan) ይኽን ኃሳቡን በዝርዝር ያሰፈረበት ፤ ረጅሙ ቴሌግራም በመባል የእሚታወቀው ሰነድ ነው ።
በእዚኽ ሰነድ ላይ የተቀመጠው ኃሳብ ፤ የከሚንዚም ባሕሪያዊ ወይንም ርዕዮታዊ ጂንጎይዝም ፣ ከምኒስት ለሆነው እና ለአልሆነው ዓለም ጋርጦት የነበረውን አደጋ እና ይኽም ዓለም ዓቀፍ ይዘት የነበረው ከምኒዝም ለብዙ ዓስርት ዓመታት በዓለም ሕዝብ ላይ ጋርጦት የነበረው አደጋ የተቀለበሰበትን አግባብ የእሚተነን በመሆኑ ፤ የፖለቲካን ስፋት እና ውስብስብነት ከማሳየቱ በአሻገር ፤ ጂንጎይዝም ደርሶበት የነበረውን ፅንፍ እና መሰል ጂንጎይዝም ፤ ለአራማጁ ማሕበረሰብ የአለውን አፍራሽ ሚና እና የጂንጎይዝም ሰለባ የሆኑ ሐገራት ጂንጎይዝምን መከላከያው መንገድ ፤ ውስጣዊ እድገትን ማፋጠን እና አጉራ ዘለሉ ለጥቃት እንዳይነሳ የመከላከል አቅም መገንባት ነው በማለት ስለ እሚያስረዳ ፤ ከተነሳንበት ግብ አንጻር ወይንም የጂንጎይዝምን አካኼድ አሉታዊ ተጽኖ እና ማገጃውን መንገድ ስለ እሚያስተምር ተመልክተነው ማለፉ ጠቃሚ ይሆናል ።
በጆርጅ ኬነን ሰነድ ላይ የተቀመጠው ዋና ኃሳብ ፦ በሥራ እና በቁጠባ ሰአይሆን ፤ በአብዮት ነው የኋላ ቀርነትን እዳ ማስወገድ የእሚቻለው ብለው የፖለቲካ ስልጣን የያዙት ከምኒስቶች ፤ መጥፋት የአለበት የታሪካዊ ስህተት/ደረጃ ነው ብለው የእሚረግሙት የካፒታሊዝም ስረዓት ፤ እነርሱ ከእሚያደንቁት እና ገነባነው ከእሚሉት የሶሻሊስት ስረዓት የተሻለ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ፤ በፕሮፖጋንዳ አስማት ከሕዝባቸው እይታ ሊሰውሩት በአለ መቻላቸው ፤ ማለትም የመንግሥት ተቀባይነት ምንጭ የሆነው ፤ ይኽ ድንቅ ፣ ዕፁብ ያሉለት የሶሻሊዝም አብዮት ትርክት የለፈፈውን ተስፋ ማሳካት አለመቻሉ በግልፅ እየታየ መሆኑ ፤ የሕዝብ ይሁንታ እያሳጣቸው ስለ ሆነ ፤ እየተከተሉ ያሉት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ፤ ከካፒታሊዝሙ ስረዓት ጋር በሰላም ለመኖር መፈለግ በሐገር ውስጥ የአላቸውን ተቀባይነት ስለ እሚያሳጣባቸው ፤ ይኽን ውስጣዊ ደካማነታቸውን እያጋለጠባቸው ከአለው የካፒታሊስት ዓለም ጋር አብሮ በሰላም መኖር እንደ እማይቻል አድርገው እርሱን በባለአንጣነት በመፈረጅ ፤ ካፒታሊስቱን ዓለም ማጥፋት አለብን የእሚል ወይንም ጂንጎይዝም ነው የእሚል ነው።
ይኽም ቀለል በአለ አገላለጽ ፤ ምንም እንኳን ይኽ የማርክሲስቶች አካኼድ ፤ ጆርጅ ኬነን ከእሚያቀርበው ፖለቲካዊ ምክንያት በአሻገር ርዕዮታዊ መሠረት ቢኖረውም ፤ በዋናነት በአሜሪካ የእሚወከለው የካፒታሊዝም እና የዴሞክራሲ ስረዓት ፥ የከሚንስቱን ስረዓት ደካማነት በማጋለጡ ምክንያት ፤ ዓለም ዓቀፉ የከምኒዝም ማዘዣ የነበረቸው ሞስኮ ፤ ይኽንን የእምትከተለውን አክሳሪ ማሕበረ ኢከነሚ ስረዓት ደካማነት የእሚያጋልጥባትን የምዕራባዊያን ካፒታሊስታዊ እና ዴሞክራሲያዊ ስረዓት በጠላትነት በመፈረጅ ፀረ ካፒታስት ስለ እዚኽም ጸረ አሜሪካ የሆነ የጂንጎይዝም አካኼድ ትከተል ነበር ፤ ማለት ነው።
ከምኒስት ሞስኮ ይኽንን ጂንጎይስት ጸረ ካፒታሊዝም ህልሟን ለማሳካት ፤ የተለያዩ ጸረ ሐገር እና ጸረ ሕዝብ የሆኑ ስልቶችን ትከተል ነበር።
ከእነ እዚኽም ስልቶቹ መካከል አንዱ ፦ በመላው ዓለም በእሚገኙ ሐገራት ውስጥ የእሚገኙ ማናቸውንም ማሕበራዊ ቁርሾዎችን እየፈለጉ ፤ ሕዝብን በሕዝብ ላይ በማስነሳት ፤ ዓለምን የጦርነት አውድማ ማድረግ ፤ የካፒታሊዝም ስረዓት መኖሪያ እንደ አያገኝ እና እንደ አይስፋፋ ያግደዋል በእሚል ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ፤ ለካፒታሊስት ኢከነሚያዊ እድገት አስፈላጊ የሆነው የሕግ የበላይነት እንደ አይሰፍን ሰፊ ሥራ ሲሰሩ ነበር ።
ይኽ የሞስኮ ስልት ባዶ ስልትም ብቻ ሰአይሆን ፤ በተፈጥሮ እና በሰብዓዊ ኃብት እጅግ ኃብታም በሆነችውን ራሺያ ላይ አዛዥ በነበረ የፖለቲካ ኃይል የእሚመራ በመሆኑ ፤ ይኽንን ዓለምን በማተራመስ ፤ ሲሆን የዓለምን ሐገራት መንግሥታትን ከሞስኮው በሚመራው ከሚንተርን ስር ማድረግ ፤ ሰአይሆን ደግሞ አለመረጋጋትን በማንገስ የካፒታሊስት ማሕበረ ኢከነሚን መስፋፋት መግታት ስልታቸውን ለማስቻል ያደራጁት ኃይል ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ሰርጎ ያልገባበት ፖለቲካዊ ፣ ማሕበራዊ ፣ ኢከነሚያዊ ተቋማት አልነበረውም።
ከእዚኽም የተነሳ ፤ ለአብዛኛዎቹ የወቅቱ ፖለቲካ ተንታኞች ፤ ችግሩ ከግልጽ እና እጅግ አውዳሚ ጦርነት ውጭ የእሚፈታ እስከ አይመስላቸው ድረስ ፤ ጉዳዩ የዓለምን መጻዒ በጽልመት የሞላ ጉዳይ ነበር።
የጆርጅ ኬነን ፤ የአስተሳሰብ ልቀትም ፤ ቃታ ሳንስብ ፤ ራሳችንን ለሕዝብ የእሚጠቅም መንግሥት ማድረግ ከቻልን እና ዓለም በከምኒስት አነሳሽነት በቀላሉ የጦርነት አውድማ መሆን እንደ አትችል መከላከል የእሚችል ወይንም የከምኒስቱ ጎራ ቀጥታ ከማጫሩ በፊት ኹለት ግዜ እንዲያስብ የእሚያስገድደው ጠንካራ የጦር ሠራዊት ከገነባን ፤ ይኽ የከምኒስትን ጂንጎይስት የማተራመስ እቅድ ማሳደብ (Contain) ማድረግ እንችላለን ፤ ምክንያቱም ፦ በእዚኽ መልኩ ልናሳድበው ከቻልን አቀጣጣይ ነዳጅ ይጨርሳል ብቻ ሰአይሆን ፤ በዓለም ዓቀፉም ሆነ በራሺያ ሕዝብ ዘንድ ፤ ማርክሲዝም ሲሰብክ የነበረውን ተስፋ ወደ ተግባር መቀየር እንደ እማይችል እየታየ ሲመጣ ፤ ተቀባይነት እያጣ መኼዱ አይቀርም የእሚል ነበር ።
ይኽ ጂንጎይዝምን የማሳደብ አካኼድ አዋጭ ሆኖ ፤ ረጅሙ ቴሌግራም ከተጻፈ ከ45 ዓመታት በኋላ ፤ ውስብስቡ ዓለም ዓቀፍ የማርክሲዝም የማተራመስ ሴራ ፤ በድኃ ሐገራት ውስጥ ብቻ እየፈነጨ ቆይቶ ፤ ከአሜሪካ እና ከምዕራቡ ዓለም አንድ ጥይት እንኳን በቀጥታ ሳይተኮስበት ፤ በ’አንድ’ ለሊት ፈራርሶ ፤ እ.አ.አ. ከ1991 ዓ.ም. በኋላ ፤ የእዚኽ የማርክሲስት ዓለም ዓቀፍ ጂንጎይዝም ማዘዣ መዓከል የነበረው የሶቭየት ሕብረት መንግሥት ከስሞ ነበር ።
በመላው ዓለምም ፤ አሜሪካንንም ጨምሮ የዘረጋቸው መረቦች ፤ ባሉበት መረባቸው ተቆራርጦ ቀልጠው ቀርተዋል ።
ጆርጅ ኬነን ፤ እ.አ.አ. በ1946 ዓ.ም. በሞስኮው የአሜሪካ አምባሳደር በነበረበት ወቅት ያስተላለፈውን ቴሌግራም እና እርሱንም አስከትሎ የራሻ ጠባይ መነሻዎች (The source of Russia’s conduct [60]) በማለት በጻፋቸው ጽሁፎች የሶቭየት ሕብረት መሪዎች ጂንጎይዝም የእሚመነጨው ስርዓታቸው በተነፃፃሪነት ካለው ደካማነት ነው ብሎ እንደ እሚያምን ኹኔታውን በእዚኽ መልክ ያስቀምጣል ፦
“የክረምሊኑ መንግሥት የዓለምን ጉዳዮች የእሚመለከትበት እብደት መነሻው ባሕላዊ እና ልማዳዊ የሆነው በራሻ የአለው የደህንነት ስጋት ነው ... ራሻዊያን በኢክኖሚያዊ ድርጅታቸው ሻል ከአሉት ምዕራባዊያን ጋር መገናኘት ሲጀምሩ ፤ የበለጠ ብቃት ከአላቸው ፣ የበለጠ ኃይል ከአላቸው እና ላቅ ያለ ማሕበራዊ አደረጃጀት ከአለው ከእዚኽ ማሕበረሰብ የእሚገጥማቸው ውድድር ስጋት አጭሮባቸዋል ። ይኼን መሰሉ ስጋት ግን ፤ የራሽያን ሕዝብ ከእሚያጠቃው በላይ የራሻን መሪዎች ያጠቃል ፤ ምክንያቱም ፦ ኹሉም የራሻ መሪዎች ያለ ልዩነት ፤ አመራራቸው ኋላ ቀር መሆኑን እና ስነ ልቦናዊ መሠረቱም ተሰባሪ እና የለበጣ ስለ ሆነ ፤ ከምዕራብ መንግሥታት ጋር ግንኙነት መቀጠሉን ወይንም መነፃፀሩን መቋቋም እንደ እማይችል ስለ እሚገነዘቡ ነው ። በእዚኽም ምክንያት የውጭ ጣልቃ ገብነት ሲያሰጋቸው ፣ በሐገራቸው እና በምዕራቡ ዓለም የእሚደረግ ቀጥታ ግንኙነት ሲያሰጋቸው ፣ ራሻዊያን ከሐገራቸው ውጭ የአለው እውነት ምን እንደ ሆነ ካወቁ ወይንም የውጩ ዓለም በራሺያ ውስጥ የአለው እውነታ ምን እንደ ሆነ ከአወቀ ፤ የእሚፈጠረው ችግር ሲያሰጋቸው ነው የኖሩት ። ከእዚኽም በመነሳት የደህንነት ዋስትናቸውን ፤ በትዕግስት በተሞላ ነገር ግን አውዳሚ ትግል በማድረግ ፤ ተፎካካሪያቸውን በማጥፋት እንጂ ከተፎካካሪያቸው ጋር በመቻቻል ወይንም በስምምነት በሰላም በመኖር ላይ ለማረጋገጥ አይፈልጉም ።”
“At bottom of Kremlin's neurotic view of world affairs is traditional and instinctive Russian sense of insecurity. …, as Russia came into contact with economically advanced West, fear of more competent, more powerful, more highly organized societies in that area. But this latter type of insecurity was one which afflicted rather Russian rulers than Russian people; for Russian rulers have invariably sensed that their rule was relatively archaic in form fragile and artificial in its psychological foundation, unable to stand comparison or contact with political systems of Western countries. For this reason, they have always feared foreign penetration, feared direct contact between Western world and their own, and feared what would happen if Russians learned truth about world without or if foreigners learned truth about world within. And they have learned to seek security only in patient but deadly struggle for total destruction of rival power, never in compacts and compromises with it. [61]“
በእርግጥ በታሪካዊ ምክንያት የተገለለ እና ኋላ ቀር የሆነ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ የአላቸው ሐገራት ለዓለም ዓቀፍ ፖለቲካ በእሚጋለጡበት ወቅት ንፅፅራዊ ኋላ ቀርነታቸው የሐገራዊ አለመረጋጋት ምክንያት ሊሆን መቻሉ የእሚታወቅ ቢሆንም ፤ ይኽን ንፅፅራዊ ኋላ ቀርነት ምክንያት አድርጎ ጂንጎይዝም ላይ የተመሠረተን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሐገር ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አስኳል ማድረግ ፤ ትክክለኛው ለእዚኽ ችግር መፍትኼ የእሚኾን ምላሽ ግን አይደለም ።
ምክንያቱም ፦ የውስጥ ደካማነት የእሚፈጠረው ስጋት እንደ ተጠበቀ ሆኖ ፤ የሰለጠነው ሌላው ዓለም ደካማነታችንን አጋለጠበን በእሚል ፤ የሐገርን ድንበር ዘግቶ እና ፀረ ስልጣኔ ወይንም ፀረ-ምዕራባዊያን የሆነ የጂንጎይዝም ጠብ አጫሪነት መከተል ፤ የችግሩ ምንጭ የሆነውን ተነፃፃሪ ኋላቀርነት ለማስቀረት ከመሥራት ይልቅ አትኩሮትን የችግሩ ቅርንጫፍ የሆነውን ፤ አሳጭ ተፎካካሪን ማጥፋትን ታሳቢ እንዲያደርግ ያደርገዋል ፥ ይኽ ደግሞ ዓይነተኛ የአክሳሪው የጂንጎይዝም አካኼድ ነው ።
ሞስኮን ማዕከሉ የአደረገው ፤ ዓለም ዓቀፍ ከምኒዝምም በውስጥ ጉዳዩ ላይ ከማተኮር ይልቅ ወይንም በተፈጥሮ እና በሰብዓዊ ኃብት ባለጠጋ የሆነችውን የራሺያ ኃብት ሐገራዊ ልማትን ለማረጋገጥ ከማዋል ይልቅ ፤ በእጁ ላይ የአለውን ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኃበት ፤ ኋላ ቀርነታችንን ያጋልጡብናል የአላቸውን የሰለጠነውን ዓለም ሐገራት የማጥፋት አካኼድ ላይ ለማዋል መርጧል ።
ይኽ ጆርጅ ኬነን የተገነዘበው የሞስኮ አካኼድ ፤ ማርክሲስታዊ መሠረት የአለው ጂንጎይዝም ወይንም ከማርክሲስት ርዕዮት የእሚመንጭ ጂንጎይዝም የመሆን እድል ቢኖረውም ፤ ጆርጅ ኬነን እንደ እሚለው የወቅቱ የሞስኮ መሪዎች ተነጻጻሪ ኋላ ቀርነታቸውን ለመሸፈን ሊሆን ይችላል ርዕዮታዊ የሆነው የማርክሲስት ጂንጎይዝም የእሚጠቀሙት።
እንደ እሚታወቀው ማርክሲዝም በተቃራኒ የመደብ ትግል አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ፍልስፍና በመሆኑ ፤ በርዕዮት ደረጃ ከእርሱ ውጭ ያሉ መንግሥታትን በመሉ በሙውታዊ ጠላትነት ፈርጆ ለማስጥፋት ቆርጦ የእሚሰራ በመሆኑ ፤ በፍጥረቱ ራሱ ጂንጎይስት ነው። ይኽ የማርክሲዝም ርዕዮታዊ ጂንጎይዝም ግን ወስጣዊ ድካማቸውን ለመሸፈን ጂንጎይስት መሆን የመረጡ የፖለቲካ ኃይላት ፤ ተፈጥሮዋዊ የሆነውን የማርክሲዝም ጅንጎይዝም ውስጣዊ ደካማነታቸውን ለመሸፈን ጂንጎይስት ወይንም ጦርአዳሪ መሆን የእሚፈልጉ የፖለቲካ ኃይላት ፤ ለእራሳቸው ጅንጎይዝም ለምድ አድርገው ሊጠቀሙት አይችሉም ማለት አይቻልም።
ያም ሆነ ይኽ ፤ ይኽ በሞስኮ መሪነት በከሚንተርን ይቀነቀን የነበረ የማርክሲዝም ጂንጎይዝም ፤ ጆርጅ ኬነን ይኽን ምክረ ኃሳቡን በጻፈበት ወቅት ፤ ዓለም በጦርነት የዛለችበት እና እንደ ከምኒዝም ያለ ምድራዊ ገነት ሰባኪ ጆሮ የእሚያገኝበት ወቅት በመሆኑ ፤ ከሞስኮው አቅም ጋር ተዳምሮ የአስጊነቱን መጠን ከፍ አድርጎት ነበር ፦
“ይኽ ውጥን (ተፎካካሪን ማጥፋት) ነው እንግዲህ ፦ የራሺያን ወታደራዊ አቅምን እና የፖሊስን አቅም ለማሳደግ ፣ የራሽያን ሕዝብ ከቀረው ዓለም መነጠል ፤ ያንንም በቀጣይነት ተንሰራፊ የሆነ የራሻን የተፅዕኖ ክልል የማስፋት ፓሊሲ ጫና ፤ የራሺያ መሪዎች ተፈጥሮዋዊ እና ልማዳዊ ዝንባሌ የሆነው ። ይኼ ግን አዲስ ክስተት ሰአይሆን ፤ ብዙ መቶ አመታትን ያስቆጠረ እና በእየግዜው እየጨመረ የመጣ የተዛባው የራሻዊያን ብሔራዊ ስሜት የእሚያምታታቸው የመከላከል እና የማጥቃት ፅንሰ ኃሳቦች ናቸው ። አኹን ግን ፤ በዓለም ዓቀፍ ማርክሲዝም ለምድ ተሸፍኖ ፤ በጦርነት ለፈረካከሰው እና ለእሚያጣጥረው ዓለም ፤ ሐሰተኛ በማር የተለወሰ ተስፋ ይዞ ስለ መጣ ከእዚኽ በፊት ከነበሩት ኹሉ አደገኛ እና አስመሳይ ያደርገዋል ።”
“This thesis provides justification for that increase of military and police power of Russian state, for that isolation of Russian population from outside world, and for that fluid and constant pressure to extend limits of Russian police power which are together the natural and instinctive urges of Russian rulers. Basically, this is only the steady advance of uneasy Russian nationalism, a centuries old movement in which conceptions of offense and defense are inextricably confused. But in new guise of international Marxism, with its honeyed promises to a desperate and war torn outside world, it is more dangerous and insidious than ever before. [61]“
እንደ ጆርጅ ኬነን ፤ ሞስኮን ማዕከሉ የአደረገው ማርክሲስታዊ ጂንጎይዝም በጊዜያዊነትም ቢሆን የጥንካሬው ምንጭ ፤ አብዛኛው ዓለም ከገባበት ቀውስ የተነሳ ጆሮ ማግኘት መቻል ብቻ ሰአይሆን ፤ በዓለም ላይ ብዙ የተፈጥሮ ኃብት የአላትን እና በቆዳ ስፋቷ ቀዳሚ በሆነችው ራሺያ አዛዥ መሆኑም ጭምር ነው ፦
“ይኽ የፖለቲካ ኃይል ፤ በዓለም ላይ ታላቅ ከእሚባሉት ሕዝብ መካከል በሆኑት ሕዝብ ኃይል እና በብሔራዊ ድንበራቸው ውስጥ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ትልቅ ከሆኑት ጎራ የእሚያስመደብ የተፈጥሮ ኃብት ላይ እንደ አሻው የማዘዝ ስልጣን የአለው ሲሆን ፤ ይኽም ደግሞ ጥልቅ እና ጠንካራ በሆነ የራሻዊያን ብሔራዊ ስሜት የእሚታገዝ ነው ። ከእዚኽ በተጨማሪም ፤ አስገራሚ የሆነ ራስን የማላመድ እና አካኼድን እንደ ኹኔታው መቀየር የእሚችል ፤ በታሪክ እስከ ዛሬ ድረስ ታይቶ በእማይታወቅ ደረጃ የህቡ እንቅስቃሴ ለማድረግ ከፍተኛ ልምድ እና ክህሎት በአላቸው ሰዎች የእሚመራ ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እጅግ የተብራራ እና ረዥም ርቀት ባሉ ሐጋራት መድረስ የእሚችል መዋቅር አለው ።”
“This political force has complete power of disposition over energies of one of world's greatest peoples and resources of world's richest national territory and is borne along by deep and powerful currents of Russian nationalism. In addition, it has an elaborate and far-flung apparatus for exertion of its influence in other countries, an apparatus of amazing flexibility and versatility, managed by people whose experience and skill in underground methods are presumably without parallel in history. Finally, it is seemingly inaccessible to considerations of reality in its basic reactions. [61]“
ከእዚኽ የጆርጅ ኬነን ግምገማ ልንረዳ እንደ እምንችለው ፤ የፖለቲካ ውስብስብነት ፤ ብዙ የተማሩ ሰዎችን እና ሰፊ ሐገራዊ ኃብትን ፤ በከምኒዝም ፍልስፍና ምክንያት ወይንም ለምድ ለእዚኽ እኩይ ተግባር በቀጣይነት ለብዙ አስርት ዓመታት ማሰማራት አስችሏል ።
ጂንጎይዝም እንደ አንድ የፖለቲካ አቅጣጫ አንድ ግዜ ‘ከነገሠ’ በኋላ ፤ ስፋቱ እና ውስብስብነቱ ፤ አራማጆቹን ራሱ የማናወዝ እና የመረጃ አሰባሰብ ሆነ የመረጃ ትንተና አቅማቸውን የማዛባት አቅም አለው ። ይኽም የጂንጎይዝም ፖለቲካዊ ደርዝ የሞስኮ መሪዎችን ፤ ከገኃዱ እውነታ እንዲፋቱ ፤ አድርጓቸዋል ብሎ እንደ እሚገምት ጆርጅ ኬነን ያስቀምጣል ፦
“ከእዚኽ በላይ የተቀመጠው የፓርቲው ሶቭየት (ደርግ ፥ ሸንጎ ፥ መማክርት ፥ ወዘተ) መስመር ፤ በእሚያራምዱት ሰዎች በሙሉ የለበጣ እና የውሸት አካኼድ እንደ ሆነ ተደርጎ መታሰብ የለበትም ። አብዛኛዎቹ ፤ ከራሻ ውጭ ስለ አለው ዓለም እውቀት የሌላቸው እና ጥያቄ ለመጠየቅም ፤ በሌሎች ላይ ስነ ልቦናዊ ተደጋፊነት ስለ አለባቸው ራሳቸውን በራሳቸው በቀላሉ አናውዘው ፤ ለራሳቸው የእሚመቻቸውን እና የማይጎረብጣቸውን ነገር ብቻ ለማመን ምንም ችግር የለባቸውም ። በስተመጨረሻም ፤ በእዚኽች ታላቅ ምድር (በራሻ) ላይ ፤ ያልተዛባ እና ትክክለኛ መረጃ የእሚያገኘው ሰው ማን እንደ ሆነ የማወቁ ጉዳይ ያልተፈታ እንቆቅልሽ ነው ። ምሥራቃዊ ሚስጥረኝነት እና ሴራ በአጠላበት በእዚኽ መንግሥት ውስጥ ፤ የመረጃ ምንጮችን የማደፍረስ እና የመመረዙ አጋጣሚ ህልቆቢስ ነው ። የወል እውነት ለእሚባለው ነገር ራሻዊያኖች የአላቸው ንቀት - ለነገሩ እስከ እነ አካቴው መኖሩንም አይቀበሉም -- ማንኛውም የእሚነገራቸውን ኃቅ አንዱን ወይንም ሌላውን ስውር ወይንም ድብቅ ዓላማ ማካኼጃ አድርገው ነው የእሚወስዱት ። ከእዚኽም ተነስተን ፤ ይኽ መንግሥት ራሱ በሴራ ውስጥ ያለ ሴራ አድርገን እንድ እናስብ የእሚያስገድዱን ምክንያቶች አሉ ፤ እኔም ስታሊን ራሱ ስለ ውጭው ዓለም ተጨባጭ መረጃ ይደርሰዋል ብለው ለማመን ከእሚቸገሩት ሰዎች መካከል ነኝ ።”
“It should not be thought from above that Soviet party line is necessarily disingenuous and insincere on part of all those who put it forward. Many of them are too ignorant of outside world and mentally too dependent to question [apparent omission] self-hypnotism, and who have no difficulty making themselves believe what they find it comforting and convenient to believe. Finally, we have the unsolved mystery as to who, if anyone, in this great land actually receives accurate and unbiased information about outside world. In atmosphere of oriental secretiveness and conspiracy which pervades this Government, possibilities for distorting or poisoning sources and currents of information are infinite. The very disrespect of Russians for objective truth--indeed, their disbelief in its existence--leads them to view all stated facts as instruments for furtherance of one ulterior purpose or another. There is good reason to suspect that this Government is actually a conspiracy within a conspiracy; and I for one am reluctant to believe that Stalin himself receives anything like an objective picture of outside world. [61]“
እንደ ጆርጅ ኬነን ምክር ፦ ፖለቲካዊ ውስብስብነት ፣ ደካማነትን የእሚያጋላጥ በአላንጣ ፣ ደካማነትን መቅረፍ የእማይችል ርዕዮት ፣ እነ እዚኽ ኹኔታዎች ተደራርበው የእሚፈጥሩት መረጃን በአግባቡ የመተንተን ችግር ፣ ወዘተ ፤ ብዙ ብቁ ባለሞያዎች እና ሰፊ ቁሳዊ ኃብት ይዞ ፤ ጅንጎይስት የኾነውን ከምኒዝም የማሸነፊያው መንገድ ወይንም እንደ አሜሪካ ያለ የጂንጎይዝምን ጠብ አጫሪነት መከላከል የእሚፈልግ ማሕበረሰብ ፤ የመጀመሪያ ማድረግ የአለበት ፤ ለጠበኛው ወገን ቀላል ዒላማ ሆኖ ለአለመገኘት በትዕግስት መሥራት ነው ፤ በወታደራዊ መስኩ ፦
“በእነዚኽ ኹኔታዎች ውስጥ ፤ ሶቭየት ሕብረትን በተመለከተ ፤ በአማካይ መጥፋት የሌለበት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቢኖር ፤ የረዥም ግዜ ፣ ትዕግስተኛ ነገር ግን ፅኑ እና ንቁ የሆነ የራሺያን ተስፋፊነት የእሚያሳድብ ነው ።”
“In these circumstances it is clear that the mean element of any United States policy toward the Soviet Union must be that of a long-term, patient but firm and vigilant containment of Russian expansive tendencies. [60]“
ምክንያቱም ፦ እንደ ጆርጅ ኬነን እምነት ፤ ጠብ አጫሪ በአብዛኛው ፤ ጠብ መጫር ስረዓታዊ ባሕሪው ቢሆንም ፤ በቀላሉ ማሸነፍ የእማይችላቸውን እና እንዲያውም ትልቅ ዋጋ የእሚያስከፍሉትን ጠብ ከማጫር የእሚቆጠብ ነው፦
“ባለ አንጣው (እንደ ራሻው ሶቭየት ዓይነቱ ባለ አንጣ ለሆኑት) በቂ የመከላከያ አቅም ከገነባ እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ይኽን ኃይሉን ለመጠቀም የአለውን ዝግጁነት ከአሳየ ፤ ይኽን ኃይሉን የመጠቀም አጋጣሚው የመነመነ ነው ። ኹኔታዎች በአግባቡ ከተያዙ ፤ ክብርን የእሚያስከፍል ግብግብ አይፈጠረም ።”
“Thus, if the adversary has sufficient force and makes clear his readiness to use it, he rarely has to do so. If situations are properly handled there need be no prestige-engaging showdowns. [61]“
ጠብ በማጫር ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት የእሚሰራው ጂንጎይስት ፤ በእዚኽ መልኩ ጠብ ማጫር እጅግ ውድ ኾኖበት ጠብ ከማጫር በእሚቆጠብበት ግዜ ፤ እንደ ጆርጅ ኬነን እይታ ፤ ምንም እንኳን ራሻ እንደ ሐገር ትልቅ ፤ የሰው ኃይል እና የተፈጥሮ ኃብት ቢኖራትም ፤ በእዚኽ አፍራሽ አቅጣጫ ላይ የእሚፈሰው ይኽ ኃብት በግዜ ኺደት ፤ የስረዓቱን ውስጣዊ ብልሽት ማጋለጡ እና ሕዝባዊ መሰላቸት እና መሰል አሉታዊ እንደምታዎችን በማስከተል ፤ ውስጣዊ ደካማነቱን ማጋለጡ አይቀርም ፦
“ የሶቭየቱ ስረዓት ፤ እንደ ሐገራዊ ኃይል ፤ ስኬታማነቱ ገና በተግባር አልተረጋገጠም ። ስረዓቱ እንደ ስረዓት ፤ ተከታታይ የሆኑ በግለሰብ እና በቡድን ደረጃ የእሚደረጉ የስልጣን መተካካቶችን መቋቋም መቻሉን ማሳየት አለበት ። የሌኒን መሞት አንዱ ይኽን መሰሉ የመተካካት ኺደት ነበር ፤ ውጤቱም ለቀጣዩ 15 ዓመት ሐገሪቱን ሰባብሯት ነው የአለፈው ። ኹለተኛው የስታሊን ሞት ወይንም መገለል ነው የእሚሆነው ። ይኽም እንኳን የመጨረሻው ፈተና አይሆንም ። የሶቭየቱ መንግሥት ፤ በቅርቡ ያደረጋቸው የመስፋፋት ኺደት ፤ ልክ የዛሩ መንግሥት ላይ ያሳረፈውን ዓይነት ጫና በሶቭየቱም ላይ ማሳረፉ አይቀርም ። እኛ በእዚኽ ያለን ሰዎች ፤ አንድ የእምንስማማበት ኃቅ ቢኖር ፤ የአኹኑ የራሻ ሕዝብ ፤ ከእርስ በእርሱ ጦርነት በኋላ ከከምኒዝም አስተምህሮ ጋር የተቃረነበት ወቅት የለም ። በራሻ አኹን እና ለግዜው ፤ ፓርቲው ውጤታማ የአምባገነን አስተዳደር መዋቅር ሆኗል ፤ ነገር ግን እንደ በፊቱ ዓይነት ተስፋ ሰጪ እና አነቃቂነቱ ቀርቷል ። ስለ እዚኽ ውስጣዊ ጤናው እና የእንቅስቃሴው ዘላቂነት እንደ ተረጋገጠ ተደርጎ መወሰድ የለበትም ።”
“Success of Soviet system, as form of internal power, is not yet finally proven. It has yet to be demonstrated that it can survive supreme test of successive transfer of power from one individual or group to another. Lenin's death was first such transfer, and its effects wracked Soviet state for 15 years. After Stalin's death or retirement will be second. But even this will not be final test. Soviet internal system will now be subjected, by virtue of recent territorial expansions, to series of additional strains which once proved severe tax on Stardom. We here are convinced that never since termination of civil war have mass of Russian people been emotionally farther removed from doctrines of Communist Party than they are today. In Russia, party has now become a great and--for the moment--highly successful apparatus of dictatorial administration, but it has ceased to be a source of emotional inspiration. Thus, internal soundness and permanence of movement need not yet be regarded as assured. [61]“
አንድ ግዜ ወደ ጂንጎይስት ፖለቲካዊ አባዜ ውስጥ የገቡ ስረዓቶች ደግሞ ከእዚኽ አፍራሽ አባዜ በቀላሉ እና በቶሎ መውጣት አይችሉም ። የጂንጎይዝም ፖለቲካ ሊጋግረው የእማይችለውን የተስፋ ዳቦ ስብከት ይዞ እስከ ቀጠለ ድረስ ፤ ይኽንን የፖለቲካ ስረዓት የተሸከመ ማሕበረሰብ እና መሪዎቹ ከገቡበት ፖለቲካዊ መናወዝ ለመውጣት የእሚቸገሩ ሲሆን ፤ ይኽም በቀጠለ ቁጥር ፤ ጂንጎይስቶች ሐገራቸውን ይበልጥ እያዳከሙ ነው የእሚኼዱት ፦
“ በእዚኽ መልኩ ፤ የፍርኃት እና የግዳጅ ጥላ አጥልቶበት እየሰራ የአለው ፤ የተዳከመ እና የዛለ ሕዝብ ፤ በቅርብ ግዜ ይኽንን ችግር እንዴት ሊያስተካክለው እንደ እሚችል መገመት ያስቸግራል ። እነ እዚኽ ችግሮች ደግሞ እስከ አልተወገዱ ድረስ … የራሻ ኢከነሚ ተጋላጭነቱ ይቀጥላል ፤ በሆነ ደረጃም ራሺያ ፤ ጉግት የእሚፈጥረውን እና ከእዚኽ ቀደም የነበራትን የፖለቲካ ሳቢነት እያነፀባረቀች ነገር ግን የእምትሰጣቸውን ተስፋዎች በተግባራዊ ቁስ እና ኃብት መደገፍ የእማትችል ፤ ደካማ ያደርጓታል ።”
“It is difficult to see how these deficiencies can be corrected at any early date by a tired and dispirited population working largely under the shadow of fear and compulsion. And as long as they are not overcome, Russia will remain economically a vulnerable, and in a certain sense an impotent, nation, capable of exporting its enthusiasms and of radiating the strange charm of its primitive political vitality but unable to back up those articles of export by the real evidence of material power and prosperity. [60]“
ስለ እዚኽ ፦ በተበላሸ ትንታኔ ፥ በኃይል ትግል መርህ ብቻ የበላይነቱን ስለ አገኘ ወደ ስልጣን የመጣው ሶቭየት ፤ የገነባውን ስረዓት ብልሹነት ለመሸፈን ፤ ከእርሱ የእሚሻሉ ስረዓቶችን በሙሉ ፤ በጠላትነት ፈርጆ ለማፍረስ ቢንቀሳቀስም (ጂንጎይስት ቢሆንም) ፤ በመሳሪያ የታገዘ አመፅ የማካኼድ አቅሙ ፤ በጥሩ የመከላከያ ሠራዊት ከተገታ ፤ የስረዓቱ ብልሹነት ከውስጥ እየገዘገዘው ራሱን በራሱ እንዲጥል ያደርገዋል ።
ይኽ ከላይ የተቀመጠው የጂንጎይስት ማሳደቢያ መንገድ ግን ፤ ግማሹ እና ወደ ውጭ የአለው ጂንጎይዝምን የመከላከያ መንገድ ነው ። አንድ የጂንጎይዝም አፍራሽ ፖለቲካ ሰለባ የኾነ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ፤ የተደቀነበትን የጂንጎስት ጠብ አጫሪነት አደጋ ሙሉ በሙሉ ማሸነፍ የእሚችለው ፤ በውጭ የአለውን ጂንጎስት ጠብ ማጫርን ውድ አድርጎበት ፤ የራሱ ውስጣዊ ችግሩ እስኪጥለው መጠበቅ እንደ አለበት ኹሉ ፤ ወደ ውስጥ ወደ ራሱ ማሕበርሰብም ውስጥ ግማሽ አትኩሮቱን በማድረግ ፤ ውስጣዊ ጤናውን እና ጥንካሬውን ለማረጋገጥ መሥራት አለበት ።
ይኽም ማለት ፤ ጂንጎይዝምን መከላከል በራሱ ብቻ የፖለቲካ ግብ ሊሆን አይችልም ፤ ስለ እዚኽ ጂንጎይዝምን ተከላካዩ ሐገርም ጂንጎይዝምን መከላከል የእሚለው ተገቢ ግን ግዜያዊ አጀንዳ ሳይጋርደው ፤ ከፊል አትኩሮቱን ወደ ውስጥ በማድረግ ፤ የራሱን ውስጣዊ ችግሮች ለመፍታት እና ራሱን ለማጠናከር መሥራትም አለበት ። ይኽንን ጆርጅ ኬነን በእዚኽ መልኩ ያስረዳል ፦
“እኛ ጤና እና ብርታት እናግኝ እንጂ ፤ የታመመው የዓለም ክፍል በራሱ ሥራ ተጠልፎ ይወድቃል ። ይኽን ለማድረግ ምንም ዓይነት የጠብ ስልት ፣ ወታደራዊ ጠብ አጫሪነት ፣ ግብግብ … ዓለም ዓቀፋዊ ፋይዳችንን ለማሳየት መፈክር ማሰማት አይጠበቅብንም ።”
“Let us find health and vigor and hope, and the diseased portion of the earth will fall behind of its own doing. For that we need no aggressive strategic plans, no provocation of military hostilities, no showdowns . . . and no pat slogans with a false pretense to international validity. [62]“
“ብዙው ነገር በማሕበረሰባችን ጤናማነት እና ብርታት ላይ ይወሰናል ። ዓለም ዓቀፍ ከምኒዝም እንደ ጥገኛ ጭንቁር የተበላሸ አካል የእሚመገብ ነው ። ይኽም ነጥብ ፤ የሐገር ውስጥ እና የውጭ ፖሊሲ የእሚገናኙበት እና የሐገራችንን ውስጣዊ ችግር ለመፍታት ፤ በራስ መተማመናችንን ፣ ስርዓት አያያዛችንን ፣ ሞራላችንን እና ሕብረተሰባዊ መንፈሳችንን ለማሻሻል ደፈር ያሉ እና ቆራጥ ውሳኔዎችን የእምንወስንበት ኹኔታ ከፈጠርን ፤ እነ እዚኽ ተግባሮቻችን ከአንድ ሺ የዲፕሎማሲያዊ ደብዳቤዎች እና የጋራ መግለጫዎች በላይ በሞስኮ ላይ ድል ይሰጡናል ።”
“Much depends on health and vigor of our own society. World communism is like malignant parasite which feeds only on diseased tissue. This is point at which domestic and foreign policies meets Every courageous and incisive measure to solve internal problems of our own society, to improve self-confidence, discipline, morale and community spirit of our own people, is a diplomatic victory over Moscow worth a thousand diplomatic notes and joint communiqués. [61]“
ጆርጅ ኬነን እንደ አለው አሜሪካ በሐገር ውስጥ የዴሞክራሲያዊ ስረዓቷ እንደ ተገነባበት የሰብዓዊነት መርህ እንጻር የሐገር አቋሟን ለማስተካከል ስትጥር ፤ የራሻው ከምኒስት ፓርቲ በአሜሪካ ውስጥ የአሉ የራሷን የአሜሪካን ዜጎች ተጠቅሞ የእሚያደራጃቸው የራሺያ ከምኒስት ተከታዮች እና በሠራተኛ መብት ስም የሞስኮው ደጋፊ የሆኑ አሜሪካኖች ራሳቸው እንኳን ለአሜሪካዊ ዴሞክራሲያዊ ስረዓት የእሚጋርጡትን የባንዳነት አደጋ መፍታት እንደ እሚጀምሩ ያምናል ፦
“ትክክለኛውን አደጋ ፤ ከሶቭየት ጦር በስተጀርባ ፣ ከቀን ሠራተኛው ፣ ግራ ከተጋቡት የአሜሪካ ግራዘመም ጋጠወጦች በስተኋላ የተመሸገው አደጋ ፤ ራሳችንን በትክክል ማየት እስከ እምንጀምር እና ከዝበታችን ፣ ከግብዝነታችን እና ከዝርክርክነታችን ራሳችንን ማፅዳት ከአልቻልን ልንፈታው አንችልም ።”
“The real threat to our society,” Kennan argued, “the threat which has lain behind the Soviet armies, behind the Daily Worker, and behind the aberrations of confused American left-wingers, will not be overcome until we learn to view ourselves realistically and purge ourselves of some of our prejudices, our hypocrisies, and our lack of discipline. [62]“ (The original source is ‘measures short of war’ but I think I should use … Containment and the primacy of diplomacy: George Kennan’s Views,)”
ስነ አጠቃልለው ፤ የጆርጅ ኬነን ትንተና ዋናው ጭብጥ ፤ ማርክሲዝም ፀረ-ካፒታሊዝም አቋም ይዞ በንቃት በመሥራት ካፒታሊስት መንግሥታትን ኹሉ ከዓለም ላይ ለማስወገድ እየሰራ እና ይኽንን ጠብ አጫሪነቱን ማስፈጸም የእሚችልበት ብዙ የሰው እና የቁስ ኃብት በአለው አመራር እየተመራ ቢሆንም ፤ የከምኒዝምን ጂንጎይዝም ፤ በዘላቂነት መመከት የእሚቻለው ፤ በግዚያዊው የአደጋ ስጋት ሳይዋጡ ወይንም ሳይወሰዱ ፤ መከላከልን ታሳቢ አድርጎ ነገር ግን የውስጥን ጤናማነት እና ጥንካሬ ማረጋገጥ ላይ በማተኮር መሆኑን አስቀምጧል ።
የፖለቲካ ልዩ በኃሪ ያስቻለውን በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የተከሰተውን ጂንጎይዝም በአስተማሪነቱ ምክንያት ትንሽ ሰፋ ያለ ሽፋን ሰጥተን ብናየውም ፤ ጂንጎይዝም በማርክሲስታዊ ርዕዮት ብቻ የተወሰነ ሰአይሆን ፤ ከእላይ እንደ አልነው በአብዛኛው ፖለቲካዊ ስረዓቶችም ውስጥ ሊከሰት የእሚችል ችግር ነው ።
በሰፊው እና ውስብስቡ ፖለቲካ የታጀበው ጂንጎይዝም ፤ የማርክሲም መሪዎችን ራሱ ፤ ራስን ወደ ማናወዝ (Self Hypnotism) ውስጥ አስገብቷቸው እንደ ነበረው ኹሉ ፤ በእኛም ሐገር ወግ አጥባቂ የዘውድ ስረዓት መሪ የነበሩትን ፤ አጼ ኃይለ ሥላሴ ወግ አጥባቂ ቀኝ ዘመም ቢኾኑም እንኳን ፤ በማርክሲዝም ፍልስፍና የተቃኘ የቅኝ ግዛት ትንታኔ ላይ በመመሥረት ፤ በኢትዮጵያ የጂንጎይዝም ፖለቲካ አራማጅ የሆኑበትን ኹኔታ ፈጥሮ ነበር ።
የማርክሲዝም ሌኒንዝም ፍልስፍና እንደ እሚለው ቀኝ ግዛት ፤ የድሆችን ጉልበት በመበዝበዝ ኃብት የእሚያካብተው የካፒታሊዝም ማሕበረ ኢከነሚ የመጨርሻ ደረጃ በመሆኑ ፤ ቀኝ ግዛት ሌላው ወይንም የመጨረሻው የካፒታሊዝም ደረጃ ነው ። ማርክሲዝም ፤ ይኽን የእሚልበትን ምክንያት ወደ ጎን እንተወው እና በእዚኽ ድማዳሜው ላይ ተመርኩዞ ፤ በካፒታሊስቱ ዓለም ላይ የጂንጎስት የውጭ ፒሊሲውን የእሚያራምድበት ምክንያት ፦ የካፒታሊዝም ስረዓት መዓከል የሆኑ ሐገራት ፤ ለኃብት ከአላቸው ስግብግብነት የተነሳ ፦ በወራሪነት ፣ በዘረኝነት ፣ ማዕድን ለመዝረፍ ፖለቲካዊ ቀውስ በማስነሳት ራሳቸውን ይጠምዳሉ ብሎ በመክሰስ ነው ።
ባህላዊ ፅንፈኝነት በእሚለው ክፍል ላይ እንደ አየነው ግን ፤ ቀኝ ግዛት ዘመናዊ እና ልዩ ክስተት ሰአይሆን ከጥነትም የነበረ መሆኑን እና ድህነት እና መገለል አዝሎዋቸው ፤ በርኃብ እና በበሽታ እያለቁ አሜሪካ ኼደው የሰፈሩ እንግሊዞች ፣ ወዘተ ፤ ታሪኮች አጣቅሰን ፤ ምንም እንኳን በኋላ ላይ ቀኝ ግዛት የብዝበዛ ስረዓት ወደ መሆን ቢለወጥም ብዝበዛን እና ዘረፋን ታሳቢ አድርጎ እንደ አልተጀመረ ለማየት ሞክረናል።
ስለ እዚኽ ፦ ቀኝ ግዛት ከምዕራብ አውሮፓዊያን እና ከካፒታሊዝም ስረዓት ጋር ብቻ ተያይዞ የእሚመጣ ችግር አለ መሆኑን መገንዘብ ይገባል ።
ኹለተኛ ፤ ቀኝ ግዛት የምዕራብ አውሮፓ ነጮች የዘረኝነት ፖሊሲ ሰአይሆን ፤ ነባራዊ የኋላ ቀር ኃያላን መንግሥታት አስተሳሰብ መሆኑን ነው ። በታሪክ ዓለምን ለመግዛት የሞከሩ በጣም ብዙ ሕዝብ አሉ ። ዛሬ ጭር ያሉት ሞንጎሎች ከቻይና ጀምረው ፤ በራሺያ አልፈው እስከ ፖላንድ ድረስ ለመግዛት መጥተዋል ፣ አረቦች ፥ ቱርኮች ፥ ፐርዥያኖች እግራቸው የደረሰበትን ፦ ጥቁሩን ፣ ቡናማውን ፣ ነጩን ፣ ቢጫውን ኹሉ ለመግዛት ሞክረዋል ወይንም ገዝተዋል ።
ስለ እዚኽ ፦ የተወሰኑ አውሮፓዊያን የተወሰነ ፅንፈኛ የዘረኝነት ዝንባሌ ቢያሳዩም ፤ የአውሮፓዊያን ቀኝ ግዛት ፤ ነጮች ለጥቁር ወይንም ከእነርሱ ውጭ ለአለ ሕዝብ ከአላቸው ንቀት እና ጥላቻ የመነጨ ሰአይሆን ፤ የነባራዊ ቀኝ ግዛት ዓይነት እና በእዚኽ በእኛ ዘመን እንዲከሰት የአደረገው የራሱ የሆነ ፤ ከዘረኝነት አመለካከት ውጭ የሆነ መነሻ ምክንያት የአለው ነው ።
እውነቱ ይኽ ቢሆንም ፤ ማርክሲስታዊ የሆነው የዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ትንታኔ ፤ ለምሳሌ ፦ የካፒታሊስት ሐገራት በመዓድን ኃብት ከበለጸጉ እና ድኃ ከሆኑ የዓለም ሐገራት ጋር የእሚያደርጉት ግንኙነት በዋናነት ፤ እነዚኽ ድኃ ሐገራት በልጽገው ማዕድናቸውን ራሳቸው እንደ አያለሙ ፤ በእነ እዚኽ ሐገራት ውስጥ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በመፍጠር ፤ መዓድናቸውን ለበለጸጉ ሐገራት እየሸጡ እንዲኖሩ ማድረግን ታሳቢ የአደረገ ነው ፤ ይላል።
ይኽን መሰሉ ትንታኔ ደግሞ በራሳቸው የውስጥ ፖለቲካ ምክንያት ውስጣዊ ፖለቲካቸው አልረጋጋ የአላቸው ወይንም የቤት ሥራቸውን የአልሰሩ ፖለቲከኞች ፤ ውስጣዊ ችግራቸውን ለመሸፈን ፤ ራሳቸውን እና ሕዝባቸውን በጂንጎይዝም ለማናወዝ በር ይከፍትላቸዋል።
ይኽን ለማሳያነት የቀረበውን ፤ የመአድን ኃብት ባለቤትነትን የጂንጎይዝም ፖለቲካ ማራመጃ የእሚደረግበት አግባብ በደንብ ከፈተሽነው ግን ፤ አንድ ካፒታሊስት ሐገር በቋሚነት ሊያራምደው የእሚችለው የውጭ ጉዳይ ወይም የኢከነሚ ፖሊሲ እንደ አልሆነ እንረዳለን።
መዓድን የእሚገኝባቸው ድኃ ሐገራት ፤ በፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ለመሆናቸው አንዱ ምክንያት የውጭ ሐገር ካፒታል ማዕድኑን ለመጠቀም ካለው ፍላጎት የመነጨ ሰአይሆን ፤ ውስጣዊ ፖለቲካ ኃይላት የሐገራቸውን የመዓድን ኃብት ተቆጣጥረው በብቸኝነት ለመሸጥ ከእሚያደርጉት ግብግብ የእሚመነጭ ነው ። በሌላ አገላለፅ ፤ ውስጣዊ ፖለቲካዊ ቀውስ ማዕድኑን ምክንያት ያደርገዋል እንጂ ፤ የካፒታሊስቱ ‘ስግብግብነት’ በድኃ ሐገራት ውስጥ በመዓድን ፍለጋ ምክንያት በራሱ የመረጋጋት ችግር የእሚሆንበት አጋጣሚ ትንሽ ነው ።
ሩቅ ሳንኼድ ፤ በነዳጅ ኃብታቸው የታወቁትን ሳውዲ አረቢያ እና ኢራንን ማየት እንችላለን ። እነ እዚኽ ኹለት ሐገራት ፤ ኹለቱም በዋናነት የሙስሊም ሐገራት ሲሆኑ ፤ የአንደኛው መንግሥት የዘውድ ስረዓት መሆኑ እና ሌላኛው እስላማዊ ሕዝባዊ መንግሥት መባሉ እንጂ ፤ በይዘታቸው ኹለቱም ፤ ዴሞክራሲያዊ ያልሆኑ እስላማዊ እና አምባገነን መንግሥታት ናቸው ።
ቢሆንም ፦ የሳውዲ አረቢያው መንግሥት ፤ ከነዳጅ ውጭ ፤ ውኃ እንኳን የሌለበት ምድረበዳ የሆነውን ሐገር ፤ ከነዳጅ ሽያጭ በእሚያገኘው ገንዘብ ፤ በተነፃፃሪነት ፤ ከብዙ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምሥራቅ ሐገራት የተሻለ ሐገር አድርጎ ገንብቶበታል። ከእዚኽም የተነሳ ፤ ቁጥሩ ቀላል የእማይባል የአከባቢው ሐገራት ሥራ አጥ ሳውዲ አረቢያ ለመሰደድ ብዙ ዋጋ ይከፍላል ።
በተቃራኒው ፤ በነዳጅ ኃብቷ ፤ በዓለም ላይ አራተኛ የሆነችው እና የተሻለ የተማረ ሰው እና ሌላም ተፍጥሮዋዊ ኃብት ባለቤት የሆነችው ኢራን ደግሞ ፤ ከእዚኽ ተፈጥሮዋዊ ስጦታ የእምታገኘውን ኃብት በአግባቡ መጠቀም ተስኗት ፤ የስደተኛ መዳረሻ ከመሆን ይልቅ ፤ አንዳንድ ዜጎቿ ጥለዋት የእሚሰደዱዋት ሐገር ሆናለች ።
ይኽም ብቻ ሰአይሆን ፤ ብዙ የዓለም ክፍል የየራሱ ትልልቅ የመዓድን ክምችት አለው ። ስለ እዚኽ ፦ በእየ ሐገራቱ የእሚገኝ ማንኛውም የመዐድን ኃብት እንደ ማንኛውም ኃብት ፖለቲካዊ ፋይዳ ቢኖረውም ፤ ዘመናዊ ፖለቲካ በእርሻ መሬት እና ለፋብሪካ ጥሬ ዕቃነት በእሚፈለጉ መዓድኖች ፍላጎት አይመራም ።
መዕድን የእማይወጣበት የዓለም ክፍል የለም ፤ ኬናዳ ፣ ቻይና ፣ አውስትራሊያ ፣ ራሺያ ወዘተ ፤ ነዳጅን ጨምሮ ትልልቅ የማዕድን ኃብት እና በእነ እዚኽ ኃብቶች ዙሪያ የተገነቡ ኢንደስትሪዎች በሐገራቸው ውስጥ አላቸው ። አሜርካኖች የመላ ሐገራቸውን የነዳጅ ፍላጎት በአሜሪካ እና በአጎራባች ውቂያኖሶች ውስጥ ከእሚወጣ ነዳጅ መሸፈን ይችላሉ ፤ ከማንም ሐገር ነዳጅ ሳይገዙ።
ስለ እዚኽ ፦ ማዕድን ከጥንትም የነበረ ንግድ እንጂ አዲስ ካፒታሊዝም የወለደው ወይንም አፍሪካን ለመበዝበዝ የመጣ አይደለም ።
ምናልባት ፤ በአፍሪካ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት እና የመሠረተ ልማት አቅርቦት ችግር ስለ አለ ፤ ለማዕድን ሥራ የእሚመጣው ድርጅት ፤ ብዙ ኃብት ከማፍሰሴ እና በእራሴ ላይ ትልቅ የመድህን ስጋት ስለ እምፈጥር ፤ ማዕድን ለማውጣት የእምከፍለው ክፍያ ሌላው ዓለም ላይ ከእምከፍለው የቀነሰ ይሁን ሊል ይችላል ።
እንደ እዚያም ከአልሆነ ፤ በአማጽያን ቁጥጥር ስር የአሉ አከባቢዎች ፤ የጦር አበጋዞቹ በእሚያደርጉት የተናጠል ስምምነት እና የጦር መሳሪያ ወይንም መሰል ቁሳቁሶች ለማግኘት በተለያዩ አደገኛ ደላሎች አማካኝነት የጥቁር ገበያ የመዓድን ንግድ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ።
ይኽን የዋጋ ቅነሳ ወይንም የአደገኛ ደላሎች እና የተንከራታች ካፒታል ትስስር የእሚፈጥረውን የጥቁር ገበያ ማዕድን ንግድ የፈጠረው የካፒታሊስቱ በዝባዥነት ሰአይሆን ፤ የእኛው ፖለቲከኞች ትምህርት ቤት ስለ አልገነቡ ብዙው ወጣት ሥራ ስለ ሌለው በርካሽ ለመሥራት መስማማቱ ፣ መንገድ ፣ ጤና ፣ ዴሞክራሲያዊ ተቋም አለ መኖር ፣ ወዘተ ፤ አንድ ኢንቬስተር የእኛን ማዕድን በርካሽ እንጂ በውድ ልሥራ ቢል በኢከነሚያዊ መስኩ የእማያዋጣ በማድረጉ እና የፖለቲካ ስረዓታችን ልዩነታችን በሰላም የእምንፈታበት ፖለቲካዊ ሟደል ስላልፈጠረልን የእሚመጣ ነው ።
ቴክኖሎጂ ጸጉር በእሚሰነጥቅበት በእዚኽ ዘመን ፤ ማዕድናችንን ለማልማት የውጭ ኢንቨስተር ፈላጊ መሆናችንም የራሳችን የውስጥ ችግር እንጂ የባላንጣ ጉዳይ አይደለም።
ይኽ ብቻ ሰአይሆን ፤ ቀኝ ግዛት ራሱ ጂንጎይዝም ስለሆነ ፤ ለቀኝ ገዢ ሐገራት ራሱ የኪሳራ ምንጭ የነበረ መኾኑ በታሪክ የተመዘገበ ነው ። ለምሳሌ ፦ ጣሊያን ምንም እንኳን የዘመናዊውን የቀኝ ግዛት ቅርጫ ለመቀላቀል አርፋጇ ሐገር ብትኾንም ፤ ቀኝ ግዛትን ያስፋፋችበት መንገድ ሐገራዊ እዳ ላይ የጣላት ነበር ፦
“ … ጣሊያን ራሷን በውን ካሉ ጠላቶች ብቻ ሰአይሆን በምናብ ሊኖሩ ይችላሉ ተብለው ከታሰቡ ጠላቶችም መከላከል እንደ አለባት ተሰማት ። ስለ እዚኽ ፦ ትልቅ የባሕር ኃይል ወደ መገንባት እና ወታደር ወደ መመልመል ገባች ። ይኽም መላውን የጣሊያንን ወሽመጥ ወደ ወታደር ካምፕነት ለወጠው ። እያንዳንዱ ዜጋ ደግሞ እነ እዚኽን ምንም አምራች ያልሆኑ ሰዎች ለመደጎም ፤ በላቡ ከእሚያገኛት የእጅ ወደ አፍ ገቢው ማዋጣት ግድ ሆነበት። ወታደር ደግሞ አንድ ግዜ ከተሰበሰበ ፤ በቤተመንግሥት ደጅ ላይ ዘብ ሆኖ ከመቆምና ወታደራዊ ትርዒት ከማሳየት ያለፈ ሥራ ሊገኝለት ይገባል ። ስለ እዚኽ ፦ የጣልያን መንግሥት ዓይኑን ወደ አፍሪካ አነሳ ። የእዚኽ ፖሊሲ ውጤት ምን እንደ ሆነ ደግሞ ኹላችንም እናውቀዋለን ፤ ጣልያን ከአቅሟ በላይ በብድር ያዘበጣት ነበር ።”
“... Italy felt herself bound to protect it against not only actual but also possible foes. She therefore set to work to create a large navy and to enforce conscription. The result of this that the whole peninsula is military camp. Every citizen, morever, has to support out of the meagre proceeds of his toil a number of absolutely unproductive persons. But for soldiers some kind of work other than that of standing sentry outside palaces or of marching about parade grounds must be found. The Italian Government, therefore, turned its eye towards Africa. We al know the outcome of that policy which had burdened Italy with debt out of proportiin to her means. [55]“
ኃቁ ፤ ይኽ ሆኖ ሳለ ፤ ማርክሲስታዊው የቅኝ ግዛት ትንታኔ በመከተል ፤ ከእዚኽ በፊት ቀኝ ተገዝተው የነበሩ እና ከቀኝ ግዛትም በኋላ ፤ ትርጉም የአለው ፖለቲካዊ እና ማሕበራዊ እድገት ማስመዝገብ ያልቻሉ ፤ አንዳንድ የዓለም ሐገራት የፖለቲካ ኃይሎች ፤ የፖለቲካ ስረዓት ውድቀታቸውን ለመሸፈን ፤ ራሳቸውን ዓለም ዓቀፍ ሰብዓዊ መብት ተሟጓች ወይንም ደግሞ የቀኝ ግዛት ቅሬታዎችን አስወጋጅ አድርገው ፤ በሐገር ወዳድነት ስም ፀረ ምዕራባዊያን የሆነ አቋም አራምደዋል ።
ኃይለ ሥላሴም ከታሪካዊ መንገዳቸው እጅግ ወጥተው ፤ ራሳቸውን የእዚኽ ዓለም ዓቀፍ ጸረ ኢምፔሪያሊዝም መሪ አድርገው የማቅረብ አካኼድ ይዘው ነበር ። ፓሮን ሮማን ፕሮቼዝካ የተባለ አንድ ጸሐፊ ኃይለ ሥላሴ ፤ በአንድ ወቅት እንዲኽ እንዳሉ ዘግቧል ፦
“የጥቁሮች ኹሉ ብቸኛው መሪ እና የፍሪካ ንጉሠ ነገሥት ነኝ ፥ በነጮች የተያዙ የጥቁር ግዛቶችም የእኔ ናቸው።… እኛ አፍሪካዊያን አውሮፓዊኖች በሙሉ የውጭ ዜጎች እንደ ሆኑ ሰአይሆን እንደ ጠላታችን ልናያቸው ይገባል።”
“I am the only African Emperor, and the leader of all Negro peoples, including those still under foreign sway,...We must regard all Europeans not only as foreigners but as enemies. [63]“
ከእዚኽም ተከትለው የእሚገቡባቸው የትብብር ስምምነቶች እና በሕዝቡም ውስጥ እንዲንቀሳቀስ የአደረጉት አስተሳሰብ ፤ ዓለምን ነጻ የማውጣት ዓይነት ምኞት የእሚንጸባረቅበት ነበር ፦
“አዲስ የተቀሰቀሰው የኢትዮጲያዊነት መንፈስ ፤ መላውን የጥቁር ሕዝብ አስተባብሮ በአንድ አመራር ስር የማድረግ ነው ። ... ይኽ በኢትዮጲያ ውስጥ እያየለ የመጣው የመነቃቃት ስሜት ፤ ከኢትዮጲያ ጋር በእሚዋሰኑ የእንግሊዝ ግዛቶች ተዛምቶ ፤ የተለያዩ ነገዶች ሊያሳምጽ ይችላል የእሚል እሳቤ ተይዟል።”
“The newly awake Ethiopian movement it to unite all the colored people in Africa under its leadership. ... The opinion held in England, that there is danger in the rash of events in Abyssinia, and that the tribes in the various proctorates and colonies abutting on the Abyssinian borders could become taken with the anti-alien fever. [63]“
ሌላው ፤ ይኼው ጸሐፊ የእሚነግረን ፤ ኃይለ ሥላሴ በብዙ መልኩ ከተወዳጁዋቸው እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ብዙ እገዛ ከአደረጉ የአውሮፓ ሐገራትን በጠላትነት በማየት እና የጥቁር ሕዝብ መሲህ ነኝ በእሚል አካኼድ ፤ የቆዩ የእርሳቸው እና የኢትዮጲያ አውሮፓዊ ወዳጆችን የእሚያገለል እና ቅር የእሚያሰኝ የንግድ ስምምነት ከጃፓን ጋር እንደ አደረጉ ይነግረናል ፦
“ዋጋው እያሻቀበ የእሚኼድ መሬት እና ስፋት የአለውን ማንኛውንም መሬት ለውጭ ዜጋ አንፈቅድም የእሚለውን ፤ እስከ ዛሬ ድረስ በሐበሾች ዘንድ ከነበረው ልማድ በወጣ መልኩ ፤ በኢትዮጲያ የውጭ ጉዳይ ምኒስትር ሚንስተር እና በጃፓን መንግሥት በተካኼደ (በከፊል ሚስጥራዊ) ስምምነት ፤ ኢትዮጲያ በጃፓኖቹ እጅ 4 ½ ሚልየን ኤክር (ወደ 1.8 ሚሊየን ኼክታር) መሬት ለጃፓን ሰፋሪዎች እና አልሚዎች አኑራለች.... በነጭ ዘር ላይ የእሚደረግ የቀለማም ሕዝብ የጋራ የትግል ግንባር ፤ የጃፓኑ ልዑል ልጅት በሆነቸው ፤ ልዕልት ማሳኮ እና በኢትዮጲያዊ ልዑል ልጅ አየለ መካከል በእሚደረገው ጋብቻም እንዲጀመር ታስቧል።”
“Contrary to the principle hitherto observed by the Abyssinians, of not permitting the leasing to foreigners continuous tracts of land of any appreciable area, Ethiopia has placed 4 ½ million acres of land at the disposal of the Japanese colonists and planters, in pursuance of the (partly secret) agreements made between the Abyssinian foreign minister and Japanese government… the united revolt of the colored peoples against the white races, was to have been inaugurated by the marriage of Princes Masako, a daughter of the Japanese prince Kurado, to the Ethiopian prince lij Ayele. [63]“
ምንም እንኳን አጼ ኃይለ ሥላሴ ፤ ‘ሕይወቴ እና የኢትዮጲያ እርምጃ’ ቅጽ አንድ መጽኃፋቸው ላይ ይኽንን ጃፓንን የእሚመለከተውን ክስ ፤ የወቅቱ የፋሺስት ጣሊያን መንግሥት እርሳቸውን በአውሮፓዊያን ዘንድ እንዲጠሉ ለማድረግ ለዓመታት ሲያስነዛው የነበረ ፕሮፖጋንዳ እንደ ነበር እና ኢትዮጲያ በእዛን ወቅት ከጃፓን ጋር የተለመደውን እና ከሌሎች ሐገራት ጋር የእምታደርገውን የንግድ ስምምነት ከማድረግ የዘለለ ፤ ምንም ዓይነት መሰል እና ምስጢራዊ የትብብር ስምምነት እንዳልመሠረተች ቢከላከሉም :-
“ኢጣሊያ እኛ የስልጣኔ ሥራ ነው እያልን የእምንሰራውን ኹሉ በሌላ አሳብ እየተረጎመች በዓለም ፊት ማውራቷን አልዘነጋውም። ይኽንም የእሚያስረዳ ነገር በ1923 ዓ.ም. ስለ ተደረገው የዘውድ በዓላችን መልክተኞቻቸውን ለላኩት መንግሥታት ኹሉ ጉብኝት ለመመለስ ፤ ለእንግሊዝና ለፈረንሳይ ለጣሊያን አልጋ ወራሻችንን ፤ ለሌሎቹም መንግሥታት መልዕክተኛ ስንልክ ከእነ እዚኹ መንግሥታት ለአንደኛው ለጃፓን መንግሥት የዉጭ ጉዳይ ሚንስትራችንን ብላቴን ኅሩይን ወደ ቶክዮ ልከን ነበርና መልዕክቱን ፈጽሞ ሲመለስ ፤ ኢጣሊያኖች ኢትዮጲያና ጃፓን ልዩ የምስጢር ውል ተዋዋሉ ፤ ከእዚኽም በቀር 3 ሚሊዮን ኼክታር መሬት ኢትዮጵያ ለጃፓን ኩባንያ የኮንሴሽን ሰጠች እያሉ በጋዜጣ ያወሩ ጀመር። እንደ እዚኽም ማውራታቸው ጎርቤታቻችን የሆኑት እንግሊዝና ፈረንሳይ እንደ እነርሱ በእኛ ላይ የእሚቀኑ ስለ መሰላቸው ይሆናል እንጂ ይህን የመስለ ምስጢርና የኮንሴሽን ውል አለመዋዋላችንን ሳያውቁት ቀርተው አልነበረም። ኢትዮጲያ እና ጃፓን ከእዚኽ አስቀድሞ እንደ ሌሎች መንግሥታት የንግድ ውል ከመዋዋል በቀር ፤ ለምስጢርና ለኮንሴሽን ውል ይቅርና መነጋገር እንኳን የላቸውም። ከዚኺም የባሰ ነገር የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽ ከጃፓን መስፍኒት ጋራ ሊጋባ ነው ብለው በጋዜጣ አወጡ። [64]“
በእዚኽ በጃፓኑ ጉዳይ ላይ የፓሮን ሮማን ፕሮቼዝካ ክስ ወይንስ የአጼ ኃይለ ሥላሴ መከላከያ ነው ትክክል የእሚለውን ጉዳይ ለማጣራት ምና አልባት የኢትዮጵያን ወይንም የጃፓንን ቤተ መንግሥት መዛግብት ማጣራት የእሚፈልግ ይኹንና ፤ የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ግን ፤ በሐገር ውስጥ በሥራ ላይ የእሚገኙ የተለያዩ የውጭ ሐገር ዜጎች ብዙ አስተዳደራዊ በደሎች እየደረሰባቸው ፤ ለእሚያቀርቡት አቤቱታ ፤ የኃይለ ሥላሴ መንግሥት የእሚሰጣቸው ምላሾች ፤ እናንተም ጥቁሮችን በአሜሪካ እንዴት ነው የእምታደርጓቸው የእሚል እና ራስን የዓለም ጥቁሮች ነፃ አውጪ አድርጎ የማቅረብ እንደ ነበር ፓሮን ሮማን ፕሮቼዝካ ይላል ፦
“የውጭ ሐገር ባንዲራ በእምታውለበለብ (ዲፕሎማቲክ መኪና) የእሚጓዝ የነበረው ሚንስተር … ከመኪናው ተጎትቶ መጥቶ በኢትዮጵያ ፖሊሶች ተደበደበ።”
“The minister who was driving a car bearing the flag ... was dragged out of the car by Ethiopian policemen and flogged. [63]“
ይኽ ዓይነቱ ክስተት ፤ ለምሳሌነት ተጠቀሰ እንጂ ተመሳሳይነት የአላቸው ብዙ ፤ ለሥራ ጉዳይ አዲስ አበባ በነበሩ ነጭ አውሮፓዊያን ላይ መስል ማንገላታቶች መከሰት ጀምረው ነበር ። በአጠቃላይ ፤ የ1928 የጣሊያን ወረራ ከመጀመሩ አስቀድሞ ፤ ኢትዮጲያ በኃይለ ሥላሴ መሪነት ፤ ከአውሮፓዊያን ጋር የዝና እሽቅድድም በማድረግ ፤ አውሮፓዊያንን እና አሜሪካንን ፤ በዲፕሎማሲው መስክ በጠላትነት ያየችበት ወቅት ነበር ።
ምናልባትም ፤ ሞሶሎኒ ኢትዮጲያን ሊወር ሲመጣ ፤ ኢትዮጲያ በተባበሩት መንግሥታት የአደረገቸው ፤ በሕግ አምላክ ጩኸት የዝሆን ጆሮ የገጠመው ፤ ኃይለ ሥላሴ ለዓመታት የተከተሉት ፤ የተሳሳተ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ውጤት ሊሆን ይችላል ።
እዚኽ ጋር ሊሰመርበት እና እንደ ስህተት ሊታይ የእሚገባው ነገር ፤ ኃይለ ሥላሴ ፥ የቀኝ ግዛትን መቃወማቸው ፣ ለጥቁሮች መብት መቆርቆራቸው ሰአይሆን ፤ በሐገራቸው ዴሞክራሲያዊ የእሚባል ሕገ መንግሥት ሳያቋቁሙ እና ምንም እንኳን በኢትዮጲያው ውስጥ ፤ በእርሳቸው በራሳቸው ምስክርነት ፤ ከአጼ ቴውድሮስ ጀምሮ ባርነት በአዋጅ የተከለከለ ቢሆንም ፦
“ይኽም የባርነት ነገር ከእዚኽ በላይ እንደ አስረዳነው በልማድ ፀንቶ የቆየ ነበር እንጂ በፍጥረት ጌታና ባሪያ ተብሎ የተለየ ነገር አለመኖሩ በሰው ልብ የታወቀ ስለመሆኑ ፤ ከ1845 እስከ 1906 ዓ.ም. በኢትዮጲያ የነገሡት አጼ ቴውድሮስ ፣ አጼ ዮሐንስ ፣ አጼ ምንሊክ በኢትዮጲያ ባሮች እንደ አይሸጡና እና እንደ አይገዙ አዋጅ አድርገው ነበር። [64]“
የባሪያን ንግድ የማስቆሙ ነገር ከአዋጅ የአለፈ ተግባር ላይ ሳይውል እና የዓለም ሕዝብ የባሪያን ንግድ አስቁሙ ብሎ እየወቀሳቸው ፤ ማለትም ፦ በሐገር ውስጥ ሊሰራ የእሚገባው ብዙ ሥራ እያለ ፤ ምንም ይኼ ነው የእሚባል ሐገራዊ ጥቅም በእማያስገኝ መልኩ ፤ ያለግዜው እና ያለ ቦታው ራሳቸውን የአፍሪካ አዳኝ አድርገው የአቀረቡበት ፥ ግብዝነታቸው ወይንም የጂንጎይስት አካኼዳቸው ነው ።
በጠብ አጫሪነት ሊጋጩዋቸው ከእሚፈልጉዋቸው አውሮፓዊያን አንጻር እዚኽ ግባ የእሚባል ኢከነሚያዊ እና ወታደራዊ አቅም ሳይኖራቸው በዓለም ዓቀፍ ደረጃ አዲስ ፀረ-ኢምፔሪያሊዝም ጎራ ፈጥረው ፤ የእዚያኽ ጎራ መሪ ለመሆን መፈለጋቸው እና ይኽንንም ለማሳካት ፤ በሐገራቸው ያሉ የትልልቅ ሐገራት ዜጎች ሲበደሉ እያዩ እንደ አላዩ ማለፍ ፣ በቀኝም በግራም ከከበቡን ቀኝ ገዢዎች ጋር ሊዳኝ የእማይቻል የጠብ አጫሪነት ባሕሪ መከተላቸው ነው ።
በቀላሉ ፤ ከፍትሕ ፍለጋ ይልቅ ኹኔታው ያመቸ ሲመስል የተተገበረ ጂንጎይዝም ነበር ። ምክንያቱም ፦ ሐገር ውስጥ ፤ ለዲፕሎማሲ ሥራ ፣ ለንግድ ፣ ወዘተ ፤ የመጡ ነጮች ላይ ወከባ እና እንግልት በማድረስ ፤ ፍትሕን በማጓደል አርበኝነት ወይንም የመብት ተሟጋችነት የሌለ በመሆኑ።
በጠቅላላውም የፖለቲካ ውስብስብነት ፤ እነ ሩሶን መሰል ላቅ ያሉ የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪዎችን እንኳን ያንዠዋዠወ ፤ ለድኃ መቆርቆር በእሚል በማርክሲዝም ፍልስፍና ብዙዎን ለዘረፋ እና ለአማባገነናዊ መንግሥት ግንባታ ደማቸውን እና ላባቸውን የአላግባብ የአስከፈለ ፣ እንደ ኃይለ ሥላሴ የአሉ የሐገር መሪዎችን ከብሔራዊ ጥቅማቸው በተጻራሪ አጉል የጀብደኝነት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንዲከተሉ የአደረገ በመሆኑ ፤ የፖለቲካ ውስብስብነት ፤ ፖለቲከኞችን እና የእሚመሩትን ሕዝብ ግራ በማጋባት ወደ ጂንጎይዝም ሊመራ ይችላል።
የፖለቲካው ውስብስብነት ፖለቲከኞችን እና የእሚመሩትን ሕዝብ ወደ ጂንጎይዝም መምራት ብቻ ሰአይሆን ፤ ፖለቲከኞች በአሰቡት ልክ ሳይከውኑ ሲቀሩ እና ሕልማቸው ሲመክንባቸውም ተበሳጭተው ፤ የጂንጎይዝምን አቅጣጫ ሊከተሉ እንደ እሚችሉ የዓለማችን ታሪክ ያሳየናል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ፤ ውስጣዊ የፖለቲካ ችግር ዐይናቸውን ወደ ውጭ እንዱያማትሩ እና በኺደትም የጂንጎይዝም አካሔድ ውስጥ እንዲገቡ ያደረጋቸው ሌላው ንጉሠ ነገሥት ፤ አጼ ቴውድሮስ ናቸው ።
በዘመነ መሣፍንት በጎበዝ አለቃ እየተመራች ውጥንቅጥ ውስጥ የነበረችውን ኢትዮጵያ ፤ በአንድ ሕጋዊ መዓከላዊ መንግሥት አስተዳደር ስር አድርገው ፤ ወደ ኋላ ከቀረችበት አውጥተው የእሚገባት የስልጣኔ ማማ ላይ ለማውጣት የነበራቸው ግብ ፤ በተደጋጋሚ በደረሰባቸው ውስጣዊ አመፅ ፤ በፈለጉት መጠን መስመር አልይዝ ስለ አላቸው፤ በመሰላቸት ፥ ኃሳባቸውን እና ኃይላቸውን በሙሉ ፤ በምዕራብ በሱዳን በኩል ከግብፅ ፤ በሰሜን ምሥራቅ የምፅዋን ወደብ ይዘው የባሕር በርን የዘጉቡንን ቱርኮች ፤ በአጠቃላይም የእስልምና አምባገነኖችን ፤ ከዓለም የፖለቲካ መድረክ ላይ ማውረድ እቅዳቸው አድርገው የተነሱት አጼ ቴውድሮስ ፤ የጂንጎይዝም አካኼድ ተከትለው ነበር ።
በእዚኽ አካኼዳቸው ፤ ውስጣዊ ኹኔታው ያስቆጣቸው አጼ ቴውድሮስ ፤ የዲፕሎማሲ መርህን በሙሉ እየጣሱ ፤ ለእዚኽ ለጀመሩት አዲስ ዓለም ዓቀፍ ዓላማ ፤ እንግሊዝን እንደ ኹነኛ አጋር አይተው፤ የእሚያስፈልገውን እገዛ እንድ እታደርግላቸው ፤ የእንግሊዝ ዜግነት የአላቸውን ሰዎች በማገት ያቀረቡት ጥያቄ ፤ በእንግሊዞች ፥ ያሰሩዋቸውን ሰዎች ይፍቱዋቸው እና እንደራደራለን ቢባሉ እንኳን ችላ በማለታቸው ፤ በተፈጠረው መካረር ፤ እስረኞችን ለማስፈታት የመጣው ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀ እና ከ20 ሺ የእማያንስ ወታደር አስከትቶ የመጣ የታላቋ ብሪታኒያ ጦር ጋር ፤ በክዳት የመነመነው ጦራቸውን ይዘው ሊገጥሙ ስለ አልቻሉ ራሳቸውን እንደ ሰው እናውቃለን ።
ይኽን ኹኔታ ፤ አሜሪካዊው የኢትዮጵያ ታሪክ አጥኚ ፤ ሐሮልድ ማርከስ (Harold Marcus) እንደ እዚኽ አስቀምጦታል ፦
“ታላቋ ብሪታኒያን እንደ ህይወት ማዳኛ ታንኳ በማየት ፤ የፀረ-ሙስሊም አጋርነት የእሚባለው ኃሳብ አጠንክረው ያዙ (አጼ ቴውድሮስ )። በእዚኽም እምነታቸው መሠረት ፤ እሳቸው እና ንግሥት ቪክቶሪያ እስልምናን በጋራ ያጠፋሉ ፤ በእዚኽም ኺደት የኢትዮጵያ አንድነት ተረጋግጦ ፤ በሐገር ውስጥ ያሉት የለውጥ እንቅስቃሴያቸውን የእሚቃወሙት ወግ አጥባቂዎች ይጠፋሉ ። ይኽ የአጋርነት እቅዳቸው በለንደን ችላ ሲባልባቸው ፤ የኋይትሆልን አትኩሮት ለመሳብ ፤ የተወሰኑ የቆንስላ ሰራተኞችን እና ሚሽነሪዎችን በማሰር ፤ የአንበሳውን ጭራ ረገጡ ። የውጭ ጉዳይ ጽህፈት ቤቱ እርቅ ቃና ባለው አኳኋን ፤ ሆርሙዝ ራሰም በእሚባል ኤደን በእሚገኘው ቢሮ ውስጥ የመንግሥት ሠራተኛ የሆነ እና በእዚኽ መሰል ትልልቅ ጉዳዮች ላይ ድርድር ለማድረግ አቅም በሌለው ሰው ፤ በኤደን የእሚገኘው የውጭ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ፤ የንግሥቲቱ ፊርማ የሌለበት የተለሳለሰ ደብዳቤ ፤ አስይዞ ወደ ንጉሡ ይልካል በጥር ወር እ.አ.አ. 1866 ዓ.ም. ። በኹኔታው የተበሳጩት ቴውድሮስ ፤ ደብዳቤውን ይዞ የመጣውን መልዕክተኛ በማሰር ፤ ከሚሲዮኒያዊያኖቹ አንዱን ወደ ለንደን ፤ የጦር መሳሪያ አሰራር አዋቂዎች እና የተለያዩ መሳሪያዎች በእርዳታ እንዲጠይቅ ላኩት ።
በእሚያስገርም ኹኔታ ፤ ለንደን ጥያቄውን በመቀበል ፤ የአገቱዋቸውን ሰዎች ምፅዋ ወደብ ላይ ሲያቀርቡ የጠየቁትን እርዳታ እንደ እሚያገኙ እና ይኽን በአያደርጉ ግን የክብርነቷን ሰዎች ለማስመለስ ጦር እንደ እምትልክ መለሰች ። አጼው ይኽንን ማስጠንቀቂያ እ.አ.አ. በጥር 1867 ዓ.ም. የተቀበሉ ቢሆንም ፤ ወደ ባሕሩ በር የእሚያደርሰው መንገድ ግን ከእርሳቸው እጅ ወጥቶ ነበር በእዚያኽን ወቅት ። በእዚያኽን ወቅት ፤ ራሳቸውንም ሆነ ግዛታቸውን መታደግ የእማይችሉበት ደረጃ ላይ እንደ ደረሱ በመረዳታቸው እጅግ ተመረው ነበር ። በእዚኽም ፤ እንግሊዝ መጥታ እንድ ትወራቸው እና ንግሥናቸውን በእዚኽ መልኩ እንዲያልቅ የፈለጉ በእሚመስል አኳኋን ፤ እ.አ.አ. በሚያዚያ 16, 1867 ዓ.ም. ለተቀበሉት ፤ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ምንም መልስ ሳይሰጡ ቀሩ ።”
“He clung to the idea of an anti-Muslim entente, especially with Great Britain, as a life raft. He and Queen Victoria would reign over the destruction of Islam, in the process reuniting Ethiopia and defeating his nation’s reactiinary internal enemies. Since his demarche had been ignored by London he decided to get Whitehall’s attention by imprisonong some minor diplomatic personnel and a few missionaries, there by stepping on the lion’s tail. The Foreign Office was conciliatary enough to draft an innocuous letter for Queen Victoria’s signature, which was delivered to the emperor in January 1866, by Hormuz Rassam, an official of the Aden civil service not empowered to undertake serious negotiations. A frustrated Tewdros detained the envoy and sent one of the missionaries to London with requests for armament experts and equipment.
London was surprisingly willimg to meet the demands in return for delivery of thd hostages to Mitsiwa; otherwise, it threatened to send an army to Ethiopia to retrieve Her Majesty’s subjects. The emperor received this warning in January 1867, when no longer controlled the route to the coast. By then, he was deeply embittered by the realization that he could save neither himself nor his empire. As if inviting a British invasion to end his reign, he sent no reply to the Foreign Ofiice ultimatum that he received on 16 April 1867. [65]“
ከእዚኽ በኋላ ፤ ከመጣው የእንግሊዝ ጦር ጋር በአደረጉት ግጭት ፤ ድል የራቃቸው አጼ ቴውድሮስ ፤ በታሪክ እንደ እምናውቀው በብዙ ታሪካዊ ምክንያቶች ህልማቸው ሳይሳካ የቀረው አጼ ቴውድሮስ ፤ በመቅደላ ላይ ራሳቸውን ሰው ።
በእዚኽ የአጼ ቴውድሮው ታሪክ ፤ የውስጡ ፖለቲካ መበላሸት ፤ አጼ ቴውድሮስን ዐይናቸውን ፤ በውጭ ባላንጣቸው ላይ እንዲያሳርፉ እንደ አደረጋቸው እና ወደ ጂንጎይዝም ስቦ እንዳስገባቸው እናያለን ።
አንዳንድ ጠንካራ መሪዎች ፤ የፖለቲካ ውስብስብነት እና ስፋት በእሚፈጥረው ድባብ ውስጥ ሆነው ሕዝባዊ አካኼዶችን በተናጠል የእሚወስኑበት አጋጣሚ ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ብዙ የተባለለትን እና የኒኮላስ ሾቨን መሪ የነበረውን ናፖሊዮን ፤ ራሱንም ሆነ መላ የፈረንሳይን ሕዝብ የጎዳ የጂንጎይስት እንቅስቃሴ እንዲያደርግ የአደረገውን ዓይነት የጂንጎይስት አካኼድ እንዲከተሉ አድርጓቸዋል።
ናፖሊዮን ፤ በግል ህይወቱ ፥ ለመሪነት የተፈጠረ የእሚያስብል ዓይነት ፤ ድንቅ ስብዕና የተላበሰ ፤ ኮርሲካ በእምትባል ፤ ከፈረንሳይ በስተደቡብ በእምትገኝ የሜድትራኒያን ትንሽ ደሴት የተወለደ እና በአሳየው የላቀ ወታደራዊ አመራር ክህሎት ፤ ከተራ ዜግነት ፦ በአጭር ግዜ የጀነራልነት ማዕረግ የአገኘ ፤ ከእዚያኽም የፈረንሳይ ንጉሥ ሆኖ ፤ የራሱ ስርወ መንግሥት ማቋቋም የቻለ ሰው ነበር ። ስለ ናፖሊዮን የተጻፈ አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ ናፖሊዮንን እንደ እዚኽ ይገልጸዋል ፦
“… ቁጥብ እና ታታሪ ሲሆን ፤ ከየትኛውም መዝናኛ ይልቅ ጥናት የእሚያስደስተው ፣ የታዋቂ ጽሐፊያንን መጽሐፍ ማንበብ የእሚወድ ፣ ረቂቅ ሳይንስን በማጥናት የተጠመደ ፣ ሌሎችንም ነገሮች ለማወቅ ጉግት የአለው ፣ ጥልቀት የአለው የሒሳብ እና ጂዖግራፊ (መልከዓ ምድር) እውቀት የአለው ፤ ዝምተኛ ፣ ብቸኝነቱን የእሚወድ ፣ የእማይጨበጥ ፣ ቁጡ ፣ በጣም ትምክህት የእሚያጠቃው ፣ ትንሽ ጠጠር ያሉ ምላሾችን የእሚናገር ፣ ማለቂያ የሌለው ጉግት የአለው እና ኩራት ኖሮት በምላሹ ፈጣን እና ያልተገራ ፤ ይኽ ወጣት ሊበረታታ ይገባዋል ።”
“... reserved and studios, he prefers study to any type of amusement, finding pleasure is the reading of good authors; very applied [to the study of] abstract sciences, little curious as others, [having] a thorough knowledge of mathematics and geography; quite, loving his solitude, capricious, arrogant, extremely inclined to egoism, speaking little spirited in his answers, quick and harsh in his replies having much pride and bottomless ambition, this young man needs to be encouraged. [66]“
ይኽን መሰል ስብዕና የተላበሰውን ናፖሊዮንን በአጭር ግዜ የፈረንሳይን የስልጣን መሰላል እንዲ ወጣጣ በር የከፈተለት ፦ ከተለመደው ለየት ያለ የጦር ስልት አዋቂነቱ ነው።
የፈረንሳይ አብዮት በዋናነት ፤ የዘውድ ስረዓትን አስወግዶ በሕዝባዊ መንግሥት መተካት በእሚል መሪ ኃሳብ የተካኼደ ስለ ነበር ፤ የመላው አውሮፓ ዘውዳዊ ስረዓቶች ፤ የፈረንሳዩ አብዮት ለሐገራቸው ተመሳሳይ አብዮት በተምሳሌትነ ያገለግላል የእሚል ስጋት ስለ አጫራባቸው ፤ የፈረንሳይ ዘውድ ስረዓትን የሻሩትን የፈረንሳይ አብዮተኞች አስወግደው ፤ ዘውዳዊ ስረዓቱን መመለስ ግቡ የአደረገ ጦርነት ፤ ከፈረንሳይ አብዮተኞች ጋር ገብተው ነበር።
ይኽም በአውሮፓ ወግ አጥባቂያን እና በፈረንሳይ አብዮተኞች መካከል የእሚካኼደው ጦርነት ግን ፤ ኹለቱም በአለ አንጣዎች ሳይሸናነፉ ፤ ለረዥም ግዜ ተፋጠው እንዲቆዩ ያደረጋቸው ሆነ።
ናፖሊዮንም በተለየ የጦር ስልት አዋቂነቱ ፤ የፈረንሳይ አብዮታዊ መሪዎች ፤ ከወግ አጥባቂው የአውሮፓ የዘውድ መንግሥታት ጋር ከተጠመዱበት እና ድል ከራቀው የቆየ ጦርነት ፤ በተለያየ ግንባር ድል ማስመዝገብ እንዲችሉ ስለ አደረጋቸው ፤ የናፖሊዮን ዝናና እና ተቀባይነት እየጎላ እንዲመጣ አደረገው ።
ከእዚያኽ በኃላ ግን ፤ በጦር ስልት አዋቂነት ፤ ከግዜ ወደ ግዜ ዝናው እና አቅሙ እየጨመረ የመጣው ናፖሊዮን ፤ በአብዮተኞቹ መዳከም ፤ አብዮተኞቹን በኃይል ከፖለቲካው መስክ በማስወገድ ፤ ራሱን አዲስ የፈረንሳይ ንጉሥ ማድረግ እንዲችል የተመቻቸ ኹኔታን ስለ ፈጠረለት ፤ የአብዮተኞቹን የሕዝባዊ መንግሥት አስተሳሰብ በመተው ፤ ናፖሊዮን ቀዳማዊ ተብሎ ነገሠ ።
ናፖሊዮን ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ፤ ከእንግሊዝ በስተቀር መላው አውሮፓን በመቆጣጠር ፤ ራሻን ሳይቀር ያካተተ ፤ አህጉራዊ ስረዓት ( Continental System) የእሚባል ፤ የጋራ ኢከነሚያው ትስስር ፈጥሮ ፤ በቁጥጥሩ ስር ሊያስገባት የአልቻላትን የእንግሊዚን ኢከነሚ ለማዳከም በእንግሊዝ ላይ በእዚኽ የጋራ ስረዓት የኢከነሚ ማዕቀብ ጣለ ።
በእዚኽም መሠረት ፤ ራሺያን ጨምሮ ፤ መላው አውሮፓ ከእንግሊዝ ጋር ምንም ዓይነት የንግድ ልውውጥ ውስጥ እንዳይገቡ ከለከለ ።
ራሺያ ፤ ከእዚኽ ማዕቀብ የተነሳ ፤ በሐገሯ ውስጥ በተፈጠረ የዋጋ ግሽበት እና መሰል ኢከነማዊ ችግሮች ፤ ማዕቀቡን ችላ በማለት ፤ ከእንግሊዝ ጋር የንግድ ልውውጥ በመቀጠሏ የተቆጣው ናፖሊዮን ፤ 600 ሺ ጦር ይዞ ፤ ያለ በቂ እቅድ እና ዝግጅት ራሺያ ላይ ዘመተ ።
ምንም እንኳን ወደ ሞስኮው የእሚያደርገውን ግስጋሴ ለመግታት ከራሻዊያኖች የገጠመውን ዉጊያ አሸንፎ ሞስኮ ቢደርስም ፥ ራሻዊያኖች በአደረጉት ስልታዊ ማፈግፈግ ፤ ሞስኮን በጠቅላላ በእሳት አጋይተው ትልቁ የናፖሊዮን ጦር ስንቅ ማግኘት የእማይችልበትን ኹኔታ ስለ ፈጠሩበት ፤ ስንቁ ያለቀበት እና የተዳከመው የናፖሊዮን ወታደር በራሻ በረዶ ፣ በርኃብ ፣ በወረርሽኝ እና ኮሳክ በእሚባሉት የራሻ ተዋጊ ነገዶች በእሚጣልበት አደጋ በፍጥነት ተመናምኖ ፤ ይዞ ከዘመተው 600 ሺ ወታደር 500 ሺው አልቀው ከእርሱ ጋር የተመለሱት 100 ሺ ብቻ ነበሩ ።
ናፖሊዮን በራሺያ በእዚኽ ኹኔታ ተቀርቅሮ በነበረበት ፤ ሌሎቹ የአውሮፓ ሐገራትም እንደ ራሺያ አምፀው ስለ ጠበቁት ፤ ወደ ፓሪስም ከተመለሰ በኋላ የተነሱበትን የአውሮፓ ነገሥታት ማሸነፍ ስለ አልቻለ ፤ ዙፋኑን በፈቃዱ እንዲ ለቅ ተገዶ ፤ ኤልባ በእምትባል ደሴት ላይ እስረኛ ሆነ ።
ናፖሊዮን ግን ፤ በሾቨንዚሙ ሰክሮ ስለነበር ፤ ከታሰረበት ደሴት 1 ሺ ሰዎች ይዞ በማምለጥ ፤ ተመልሶ ወደ ፓሪስ ሲመጣ ፤ ሕዝቡ በታላቅ ደስታ ስለ ተቀበሉት ፤ በፈረንሳይ የነበረው አዲሱ የዘውድ ንጉሥ በድንጋጤ ሸሸ ።
ከእዚኽም በኋላ ፦ ናፖሊዮን እንደ ገና ጦር አደራጅቶ ፤ አውሮፓዊያን በአንድ ላይ ተሰብስበው ሳያጠቁት በፊት ፤ በየተራ ሊያሸንፋቸው በማሰብ አስቀድሞ ጦርነት ጀመረ ።
በእዚኽም ራሱ በጀመረው ጦርነት ፤ ዋተርሉ በእሚባለው ቦታ ላይ ፤ በእንግሊዝ እንዲሁም በፕራሻ ጦር እገዛ በመሸነፉ ፤ ተይዞ በምንም መልኩ ሊያመልጥበት በእማይችልባት ፤ ቅድስት ኼለና በእምትባል ፤ ከደቡብ አፍሪካ ወደ ምዕራብ ፤ በሺ ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ በነበረች ፤ ድንጋያማ ደሴት ላይ ታስሮ ህይወቱ በእዚያኽ አለፈ ።
ምንም እንኳን ናፖሊዮን የትልቅ ጭንቅላት ባለቤት ቢሆንም እና ለመምራት የተፈጠረ የእሚያስብለው ዓይነት ስብዕና የተላበሰ ሰው ቢሆንም ፤ ከግል ዝናው እና የፈረንሳይን የበላይነት ለማሳየት ከአለው ፍላጎት ያለፈ ይኽ ነው የእሚባል ፖለቲካዊ ውቅር ስለ አልነበረው ወይንም ጂንጎይስት ስለ ሆነ ፤ የግል ሕይወቱን እና የፈረንሳይን ፖለቲካ በሙሉ የፈረንሳይን የበላይነት በሌሎች ላይ ለመጫን በአሰበ መልኩ ስለ ቃኘው ፤ የስልጣን ዘመኑን ለራሱም ሆነ እወዳታለሁ ለእሚላት ፈረንሳይ አሳዛኝ ዘመን አድርጎት አለፈ ።
ሕዝብ እንደ ሕዝብ በመሠረታዊ ዕሴቶች ላይ ወደ ባሕልነት የደረሱ የፀኑ አቋሞች በአልያዘበት ወቅት ፤ ከፖለቲካ አሳታፊነት ፣ ከፖለቲካ ውስብስብነት እና ስፋት ፣ ክስተት የሆኑ ጠንካራ አመራሮች መዛል ወይንም ጀብደኝነት ብቻ አይደለም የሕዝብ ተጋላጭነት የእሚባባሰው ፤ ነገር ግን ከዘመናዊ ሕዝባዊ ፖለቲካ በኃሪም ነው ።
እንደ እሚታወቀው ፤ አኹን አኹን ሕዝባዊነት ወይንም ሕዝበኝነት (Populism) በጠቅላላው ፤ መርህ አልባ ሕዝባዊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ወይንም የመንጋ በኃሪ የአለው የፖለቲካ እንቅስቃሴን የእሚወክል አሉታዊ አካኼድ እንደ ሆነ እየቀረበ ቢኼድም ፤ ኃሳቡ በአንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ውስጥ ያሉ ሰዎች የእሚኮረኩራቸውን አጀንዳ በማራመድ የሕዝብን ድጋፍ የማሰባሰብ ወይንም ሕዝብን የማስተባበር አካኼድ ነው ።
ስለ እዚኽ ፦ ሕዝብ ነው መንግሥት በእሚለው የዴሞክራሲያዊ መንግሥት ፅንሰ ኃሳብ ላይ መግባባት ከአለ ፤ ሕዝበኝነት ወይንም ሕዝባዊነት ፤ በራሱ አፍራሽ ወይንም አሉታዊ የፖለቲካ ባሕል አይደለም ፤ እንዲያውም ዴሞክራሲያዊ እና ሕዝብን ያከበረ አካኼድ ተብሎ ሊወደስ የእሚገባው ነው ።
ስለ እዚኽ ፦ ዘመናችን የሕዝባዊ ፖለቲካ ዘመን ስለ ሆነ ፤ የሕዝበኝነቱ ፖለቲካ ይዘት እንጂ ሕዝበኝነት በራሱ የእሚኮነን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዳልሆነ ከአስቀመጥን ፤ ዘመናዊው የሕዝባዊ ፖለቲካ በመሪዎች እና በፕሮፖጋንዳ አቅም ፤ በእኩይ መሪዎች እንደ ጂንጎይዝም ላሉ አፍራሽ ፖለቲካዊ አቅጣጫዎች ፤ በተቃራኒው በመልካም መሪዎች ወደ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ ስረዓት ግንባታ እንዴት ሊኼድ እንደ እሚችል የተወሰኑ ታሪካዊ ማሳያዎችን እንመልከት ።
ሒትለር የትግል ሕይወቴ በእሚለው መጽሐፉ ፤ አይሁዶች ሰው ኽሉ እኩል ነው ብለው ፤ የጀርመንን ሕዝብ የበላይነት አደጋ ውስጥ እያስገቡት ነው ፤ ይኽ እየሆነ የጀርመን ሙህራንም ፈዘዋል ብሎ ፤ ቀላል የእማይባል ሕዝባዊ እንቅስቃሴ የእሚመራ ሕዝበኛ ወይንም ሕዝባዊ ፖለቲከኛ ሆኖ ነበር ።
ሒትለር ፤ አይሁድ ሰው ኹሉ እኩል ነው ብለው ፤ የጥቁር ሕዝብ በእውቀት እየጎለበተ መምጣቱን እንደ ማሳያ ያቀርባሉ ፤ ይኽ ዓይነት ጥቁርን ሕዝብ ከጀርመን ሕዝብ ጋር እኩል ነው ማለት ፤ ወንጀል ነው በማለት የእሚከተለውን ብሏል ፦
“ከግዜ ወደ ግዜ ያሸበረቁት ጋዜጦቻችን ፤ ፍልስጤማዊውን (ያልተገረዘውን ፣ ያልሰለጠነውን ፣ ኋላ ቀሩን) ጀርመናዊ ለማነፅ እያሉ ፤ በአንዱ የዓለም ጥግ ወይንም ጫፍ ፤ በእዚያኽ አከባቢ ለመጀመሪያ ግዜ ኔግሮ (ጥቁር) ጠበቃ ፣ አስተማሪ ፣ ፓስተር ፣ አንዳንዴ እንዲያውም በትልቅ ዖፔራ ላይ መሪ ድምፃዊ ሆነ ወይንም እንደ እዚኽ ያለ ነገር ሆነ ፤ የእሚል ዜና ይዘው ይወጣሉ ። በእዚኽ ግዜ ዐለት-ራስ የሆነው ቡርዥዋ ይኽንን ያስቻለውን የዘመናዊ ትምህርት ዘዴ የእሚያዳንቀውን ማስታወቂያ በአድናቆት እና በግርምት ሲመለከት ፤ ብልጣብልጡ አይሁድ ፤ ሰው ኹሉ እኩል ነው ፤ የእሚለውን ኃሳብ ሕዝብ ውስጥ ለማስረፅ የእሚያግዘው አዲስ ማስረጃ እንደ አገኘ ያያል ። ለደፈረሰው የቡርዣ ጭንቅላት ይኽ የታተመለት ማስረጃ በምክንያተኝነት ላይ የተፈፀመ ኃጢያት መሆኑን እና በሚልዮን የእሚቆጠሩ የሰለጠነው ዘር አካል የሆኑ ሕዝብ ከባህላዊ እድገታቸው ጋር በእማይመጥን ኹኔታ ውስጥ ሲገኙ ፤ ከውልደቱ ጦጣ የሆነውን ፍጥረት አሰልጥኖ እና ይኽ ጦጣ ከመሰልጠኑ የተነሳ ጠበቃ እስኪ መስል ድረስ ማድረስ ፤ ወንጀለኛ የሆነ እብደት እንደ ሆነ አይወግግለትም ።”
“From time to time our illustrated papers publish, for the edification of the German philistine, the news that in some quarter or other of the globe, and for the first time in that locality, a Negro has become a lawyer, a teacher, a pastor, even a grand opera tenor or something else of that kind. While the bourgeois blockhead stares with amazed admiration at the notice that tells him how marvelous are the achievements of our modern educational technique, the more cunning Jew sees in this fact a new proof to be utilized for the theory with which he wants to infect the people, namely that all men are equal. It does not dawn on the murky bourgeois mind that the fact which is published for him is a sin against reason itself, that it is an act of criminal insanity to train a being who is only anthropoid by birth until the pretense can be made that he has been turned into a lawyer; while, on the other hand, millions who belong to the most civilized have to remain in positions which are unworthy of their cultural level. [40]“
በተቃራኒው ደግሞ እንደ አብረሐም ሊንከን ያሉ ፤ ሰዎች ኹሉ እኩል ሆነው ተፈጥረዋል የእሚሉ መሪዎች ፤ ይኽን መርህ ለማስከበር ሕዝባቸውን በማስተባበር ወይንም ሕዝበኛ ሆነው ፤ እንደ ሒትለር ዓይነቱን ሰው በሰውነቱ ከእማይቀበል የፖለቲካዊ አስተሳሰብ ወኪል የሐገራቸው ዜጋ ጋር የእርስ በእርስ ጦርነት አካኺደዋል ።
በአሜሪካ የባሪያን ስረዓት ለማስወገድ በተደረገው የእርስ በእርስ ጦርነት ላይ አንዱ እና ትልቁ ከተባለው የጌትስበርግ ጦርነት በኋላ ፤ በእዚያ ጦርነት የተሰውትን ወጣት ወታደሮች ለማሳረፍ የተዘጋጀውን ታሪካዊ የቀብር ስፍራ ለመቀደስ በስፍራው ተገኝቶ ፤ የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት አብረሐም ሊንከን የአደረገው ታሪካዊ ንግግር ፤ የወቅቱን ሕዝባዊ መንፈስ ይዘት የእሚገልፅ ነው ፦
“ከዛሬ ሰማንያ ሰባት ዓመት በፊት አባቶቻችን በእዚኽ አሁጉር ላይ ፤ በነፃነት ዕሳቤ ተፀንሳ ፥ ሰዎች ኹሉ እኩል ሆነው ተፈጥረዋል ለእሚለው ውጥን የእምትተጋ አዲስ ሐገር መሠረቱ ።
እኛም ዛሬ ፤ በእዚኽ ውጥን የተመሠረተችው ይኽችኽ ሐገራችን ፤ ለነገሩ ማንኛውም በእዚኽ ውጥን ላይ የተመሠረተች እና ለእዚኽ የተሰጠች ሐገር ፤ ፀንታ መቆም ትችል ትሆን ወይንም አትሆን የእሚያሳይ የእርስ በእርስ ጦርነት እያደረግን ነው ። ያችኽ ሐገር ትኖር ዘንድ ፤ የእዚኽ ጦርነት አንድ ትልቅ ግንባር በነበረው ውጊያ ላይ ሕይወታቸውን ለሰጡ ስዎች አካል ዘላለማዊ ማረፊያ ይሆን ዘንድ ይኽንን ቦታ ለመቀደስ በእዚኽ ተገናኝተናል ። ይኽንንም ማድረጋችን በአጠቃላይ የተገባ እና ትክክል የሆነ ነገር ነው ።
ለእኛ ለህያዋኖቹ … ይኽን ህልም ለማሳካት የእሚቀረው ትልቅ ሥራ ቀርቶልናል - ከእነዚኽ የተከበሩ ሰማዕታት ለእዚኽ ግብ የአላቸውን የመጨረሻ መሰጠት በማበርከታቸው ተበረታትተን - እኛም በትልቅ ቆራጥነት የመጨረሻ መስዋዕትነት የከፈሉበት ይኽ ጉዳይ ከስሞ ሞታቸው ከንቱ እንደ አይሆን ታላቅ መሰጠት በማሳየት - ይኽችኽ ሐገር ፤ በእግዚአብሔር ስር ሆና አዲስ የነፃነት ውልደት እንድ እታደርግ እና - የሕዝብ መንግሥት ፣ በሕዝብ ፣ ለሕዝብ ፤ የእሚለው ከምድር ላይ እንድ አይጠፋ ለማድረግ ።
አብረሐም ሊንከን ፤ የጌትስበርግ ንግግር ፤ ህዳር 19, 1963 እ.አ.አ (በኢትዮጵያ ህዳር 9, 1956) ”
“Four score and seven years ago our fathers brought forth on this continent, a new nation conceived in Liberty, and dedicated to the proposition that all men are created equal.
Now we are engaged in a great civil war, testing whether that nation, or any other nation conceived and so dedicated, can long endure. We are met on a great battlefield of that war. We have come to dedicate a portion of that field, as a final resting place for those who here gave their lives that nation might live. It is altogether fitting and proper that we should do this.
It is for us the living … to be here dedicated to the great task remaining before us – that from these honored dead we take increased devotion to that cause for which they gave the last full measure of devotion – that we may highly resolve that these dad shall not have died in vain – this nation, under God, shall have a new birth of freedom – and that government of the people, by the people, for the people, shall not perish from the earth. [38]“
ሰው ኹሉ እኩል አይደለም ብሎ ጦርነት የእሚገባው እና የለም ሰው ኹሉ እኩል ነው ብሎ ጦርነት የእሚገባው ፤ በአስተሳሰብ ዘንድ ተፃራሪ ቢሆኑም እንኳን ኹለቱም ቀላል የእማይባል ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ፈጠረው ፤ በሰፊ ሕዝባዊ ድጋፍ የተድረጉ ነበሩ ።
ይኽም በመሆኑ ፤ ሕዝበኛው ወይንም ሕዝባዊው ትክክል የእሚሆንበት እና ትክክል የእማይሆንበት ግዜ አለ ፤ የእዚኽም ፍረጃ በባሕሪው አንፃራዊ ነው ።
አንድ የፖለቲካ መሪ ፤ በአቀራረብ ችሎታ ፣ በጠንካራ እና ሳቢ ስብዕና በመላበስ ፣ በፕሮፖጋንዳ ጥበብ ፣ ወዘተ ፤ ሕዝብን ወደ ዴሞክራሲ ፣ እድገት እና ፍትሕ ሊመራ እንደ እሚችለው ኹሉ ፤ እነዚኹን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ መፍጠሪያ ዘዴዎች ተጠቅሞ ሕዝባዊ መነቃቃቱን የራሱን የግል ስልጣን እና ዝና ለመያዝ ፣ በጀብደኝነት ተነስቶ ሕዝብን ለጦርነት ሊጋብዝ ወይንም ጂንጎይስት ሊሆንበት ይችላል ።
አዶልፍ ሒትለር ፤ የሰው ልጅ ኹሉ በተፈጥሮ እኩል ነው የእሚለው ዓለም ዓቀፍ የአይሁድ ሴራ ሐገራችንን ሊቀማን ነው ፣ በአንደኛው የዓለም ጦርነት እንድ እንሸነፍ የአደረጉን ከምኒስቶች ናቸው ፣ የጀርመን ሕዝብ አንደኛ ደረጃ ሕዝብ ሆኖ ሳለ ሰው ኹሉ እኩል ነው የእሚለው የአይሁድ የስህተት ትምህርት የጥቁር ቄስ ኹሉ እያመጣብን ነው ፣ ወዘተ ፤ በእሚሉ ቅስቀሳዎች ፤ እንደ ሌላው የዓለም ሕዝብ ኹሉ ሰላም ወዳድ የሆነውን የጀርመን ሕዝብ ፤ የሒትለር በጠላቶቹም ጭምር የተመሰከረለት ልዩ የፕሮፕጋንዳ እና የሕዝባዊ እንቅስቃሴ አመራር አቅም ፤ የጀርመን ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር አነቃንቆ ፤ ብዙ አሳዛኝ ወንጀል እንዲፈፅሙ አድርጎዋቸዋል ። ከእዛኽም አልፎ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኃብት ፤ እነርሱንም ሆነ የዓለምን ሕዝብ አስከፍሏል ።
ኹሉም የጀርመን ሕዝብ ፤ እንዲያውም አብዛኛው የጀርመን ሕዝብ ሒትለርን ሙሉ በሙሉ ይደግፈው ነበር በአይባልም ፤ ቀላል የእማይባል ቁጥር የአለው ሕዝብ ሒትለርን ደግፎት ነበር ። እስከ ዛሬም ፥ በጀርመን ብቻ ሰአይሆን በተለያየ የዓለም ክፍል ፤ ኒዮናዚ (Neo-Nazi) በእሚል ስያሜ ስር የእሚንቀሳቀሱ ፤ የሒትለርን ኃሳብ እና የእርሱን ኃሳብ የእሚመስሉትን ተመሳሳይ ጂንጎይስት አስተሳሰቦች የእሚደግፉ አሉ ።
ስለ እዚኽ ሕዝበኝነት ወይንም ሕዝባዊነት በራሱ ስህተት አይደለም ፤ ሆኖም ግን ፤ በዴሞክራሲያዊ እሴት ያልታነፀ እና በዴሞክራሲያዊ ተቋማት ያልተጠናከረ ማሕበረሰብ ግን ፤ ለአሉታዊ ሕዝበኝነት ሊጋለጥ ይችላል ።
የእሚታወቅ እና የእሚሻል መተኪያ የሌለው ሕዝባዊ ፖለቲካ ከእሚሰራበት መንገድ አንዱ እና ዋነኛው ደግሞ ፕሮፖጋንዳ ነው ።
ፕሮፓጋንዳ የእሚለው ቃል ምንጩ ላቲን ሲሆን Propagate ወይንም ማሰራጨት ወይንም ማስረጽ የእሚል ትርጉም ካለው የእንግሊዘኛ ቃል ጋር ተመሳሳይ ስር የአለው ቃል ነው ።
ፕሮፓጋንዳም የዛሬውን ትርጓሜ ሊይዝ የቻለው ፤ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እ.አ.አ. በ1622 ዓ.ም. የወንጌል ስርጭቱን(ፕሮፓጋንዳ ወይንም Propagation) ሥራ የእሚቆጣጠረውን ከሚቲ በእዚኽ ቃል በመሰየሟ ነው ።
የእዚኽ ከሚቲ ወይንም ማሕበር ሙሉ ስም በላቲን (Sacra Congregatio de propaganda Fide or in English “Congregation for the propagation of the faith” “በአማርኛ የኃይማኖት ስርጭት ጉባኤ” ) የነበረ ሲሆን ፤ በግዜ ኺደት ማንኛውንም የሐሳብ ማሰራጨት ሥራ ፕሮፖጋንዳ በእሚል መጠራት እንደ ተጀመረ ፤ የዘርፉ አጥኝዎች ይላሉ ፦
“ ስለ እዚኽ ፦ የመጀመሪያው የፕሮፖጋንዳ ተቋም ፤ የኃይማኖታዊ አስተሳሰቦችን ስርጭት ለማሻሻል የተቋቋመ አካል ነበር ። ከእዚያኽም ‘ፕሮፖጋንዳ’ የእሚለው ቃል ፤ በአጭር ግዜ ውስጥ ፤ ማንኛውንም ቀኖና የእሚያሰራጭ ተቋም የእሚጠራበት ሆነ ፤ ከእዚያኽም ቀኖናው ራሱ የእሚጠራበት ሆነ ፤ በስተመጨረሻም ስርጭቱን ለማሳካት በሥራ ላይ የእሚውሉ ዘዴዎች መጠሪያ ሆነ ።”
“The first propoganda institute was therefore simply a body charged with improving the dissemination of a group of religious dogmas. The word ‘propoganda’ soon came to be applied to any organization set up for the purpose of spreading a doctrine; then it was applied to the doctrine itself; and latly to the methods employed in effectuating the dissemination. [67]“
ምንም እንኳን አኹን አኹን ፤ ልክ እንደ ሕዝባዊነቱ ፥ ፕሮፓጋንዳ የእሚለው ቃል ውሸት ፣ ማጋነን ፣ መደለል የመሰሉ አሉታዊ እንደምታ የአላቸው ሕዝብን የማደናገሪያ መንገዶች መግለጪያ ቃል ቢሆንም ፤ ዘመናዊውን ፖለቲካን ያለ ፕሮፖጋንዳ መሥራት አይቻልም ።
ሕዝባዊ መንግሥት ለመመሥረት ፤ ሕዝብ ፥ የሕዝባዊ መንግሥትን አስተሳሰብ ፤ አንኳር ነጥቦች በቀላል እና ግልፅ ቋንቋ መረዳት እና ድጋፉን መስጠት አለበት ። ይኽን ማድረግ የእሚቻለው ደግሞ የሕዝባዊ መንግሥት መርሆችን ለሕዝብ ተደራሽ በእሚሆን መልኩ በማሰራጨት ወይንም በፕሮፖጋንዳ ነው ።
ምክንያቱም ፦ ፕሮፖጋንዳ ፤ በባሕሪው ሰፊ ሳይንሳዊ ትንታኔ ላይ የተመሠረቱ ፤ ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ አስተሳሰቦችን ፤ ፖለቲከኛ ያልሆነው ሰፊው ሕዝብ ሊረዳው እና ድጋፉን ሊቸረው በእሚችል መልኩ ማቅረብ ነው ።
ይኽ ዓይነቱ ማቅለል ፤ የመጀመሪያው ኃቀኛ ግቡ ፤ ሕዝብን ከአለ አስፈላጊ ውስብስብ ትንታኔዎች መታደግ እና ጭብጡን ወይንም አንኳር ነጥቡን ማቅረብን ታሳቢ የአደረገ ስለ ሆነ ፤ በአብዛኛው ግቡ የሕዝብን ስሜት የመኮርኮር ወይንም የንግድ ማስታወቂያ ዓይነት ይዘት እንዲ ይዝ ያስገድደዋል ።
ይኽ ፤ የፕሮፖጋንዳ ባሕሪ ግን ፤ ሐቀኛ ያልሆነውን ፖለቲከኛ ፤ የፕሮፖጋንዳ አዘገጃጀት እና አቀራረብ ከገባው ፤ ወይንም እሚያሰለጥነው ከአገኘ እና ፕሮፖጋንዳውን በፕሮፖጋንዳ የእሚመክት ከሌለ ፤ በጣም ቀላል ነገር ግን አጥፊ ፕሮፖጋንዳ በመሥራት ፤ በአቋራጭ በሕዝባዊ እንቅስቃሴ ወደ ስልጣን ሊመጣበት ይችላል ።
ስለ ራሱ የተዋጣለት የፕሮፖጋንዳ ሊቅ እንደ ሆነ የእሚናገረው እና የፕሮፖጋንዳ አዋቂነቱን ፤ የአሜሪካው ማዕከላዊ የመረጃ ድርጅት (CIA) በባሕሪው ላይ በአደረገው ጥናት ፦
“የፕሮፖጋንዳ ጥበብ ሊቅ ነው ።”
“He is a master of the art of propoganda. [68]“
ብሎ የመስከረለት ሒትለር ስለ ፕሮፖጋንዳ እንዲኽ ይላል ፦
“... ብቃት በአለው እና በፀና ፕሮፖጋንዳ መንግሥተ ሰማይን እንኳን ሲዖል እንደ ሆነ ለሕዝቡ ማቅረብ ይቻላል ወይንም በተቃራኒው እጅግ ሰቆቃ የሞላበትን ህይወትም ገነት እንደ ሆነ አድርጎ ማቅረብ ይቻላል”
“...by an able and persistent use of propaganda heaven itself can be presented to the people as if it were hell and, vice versa, the most miserable kind of life can be presented as it were paradise. [40]“
ምክንያቱም ፦ እንደ ሒትለር ገለፃ ፤ ኃይ ባይ ከሌለ ፤ በፕሮፖጋንዳ የእሚቀርቡት ኃሳቦች ፤ መርህ ተኮር ሳይንሳዊ ትንታኔ ሰአይሆን ፤ ስሜት ኮርኳሪ ኃሳቦች በመሆናቸው ነው ፦
“የፕሮፖጋንዳ ዓላማው ሰዎችን እውቀት ማስጨበጥ ወይንም ማስተማር አይደለም ፣ ይልቁንም የሕዝቡን አትኩሮት በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንዲያርፍ ማድረግ ነው ። ... የፕሮፖጋንዳ ሳይንሳዊነት በረገበ ቁጥር እና በዋናነት የሕዝብን ስሜት ላይ ያተኮረ በእሚሆንበት ግዜ ስኬታማነቱ የጎላ ይሆናል።”
“The purpose of propaganda is not the personal instruction of the individual, but rather to attract public attention to certain things ...The more modest the scientific tenor of this propaganda and the more it is addressed exclusively to public sentiment, the more decisive will be its success. [40]“
ይኽ መሰሉ የፕሮፖጋንድ ቅለት እና ሕዝብን ፤ የተማረ ያልተማረ ፣ ኃብታም ድኃ ወይንም ማንኛውንም ማሕበራዊ አጥር ሳይጠብቅ ፤ ሕዝብን የማወዛወዝ አቅሙ ፤ ኃላፊነት በእማይሰማው እና ለግዜያዊ ጥቅም ፤ ምንንም ነገር ለመሰዋት ዝግጁ የሆነ ፤ እንደ ተደራጁ የወንጀል ቡድን ወይንም ጂንጎይስት ዓይነት ፖለቲከኞች እጅ ላይ ፤ ተከላካይ ማሕበራዊ ተቋም በሌበት ማሕበረሰብ ውስጥ ከገባ ከፍተኛ አፍራሽ ሚና ሊኖረው ይችላል ።
ሒትለር እንደ እሚለው ፤ የፕሮፖጋንዳን የሰውን አዕምሮ የመቆጣጠር አቅም ያልተረዳ ሰው ነው ፤ በፕሮፖጋንዳ ኃይል አዕምሮዋቸው የእሚታወሩ ሰዎችን የእሚወቅሰው ፦
“አንድ ሰው ፤ የእዚኽን ግዙፍ ስረዓት(የፕሮፖጋንዳ ስረዓቱን ነው)የሕዝቡን ዓዕምሮ ለመመረዝ የእሚሰራበትን መንገድ ከተረዳ በኋላ ፣ ሞኝ ከሆነ ብቻ ነው ፤ እንዴት ይታለላሉ ብሎ ሰለባዎቹን (የፕሮፖጋንዳ ስረዓቱ ሰለባዎችን)ሊወቅስ የእሚችለው ። “
“Having once understood the working of the colossal system for poisoning the popular mind, only a fool could blame the victims of it. [40]“
አኹን የአለንበት ዘመን ፤ መረጃ የማቀነባበር እና የማሰራጨት አቅማችንን በከፍተኛ ደረጃ ስለ አሳደገው ፤ ከእዚኽ ቀደም በየጓዳው በሽኩሹክታ የእሚባሉ ፤ አሳፋሪ ንግግሮች አደባባይ የወጡበት ነው ። ከቻልክ ፤ ዋሽ ፣ አታልል ፣ ስረቅ ፣ ቀማ ፣ ወዘተ ፤ የእሚሉ መጽሐፍት በግልፅ ታትመው በዓለም ዙሪያ እየተሰራጩ ነው ።
“የማማለል ኪን” ( The Art of Seduction ) እና “48ቱ የኃይል መርሆች” (48 Principles of Power) የእሚባሉትን መጽሐፍት የጻፈው ፒተር ግሪን (Peter Greene) ፤ ያለ ምንም መሸፋፈን ፥ ከርዕሱ ጀምሮ ፥ የማማለል ኪን (The Art of Seduction) በማለት ፤ በግልጽ በአደባባይ ፤ ቦዘኔ የእሚያሰለጥንበት ዘመን ላይ ነን ።
ይኽ ሰው የማማለል ኪን ወይንም ጥበብ ብሎ ለቦዘኔዎች ስልጠና ሲሰጥ ፤ ሴት ልጅን እንዴት እንደ እሚያመጥምዱ ወይንም ገንዘብ እንዴት እንደ እሚያጭበረብሩ አይደለም ፤ እንዴት አድርገው የፖለቲካ ስልጣን በመወስለት እንደ እሚይዙም ጭምር ነው ። የማማለል ኪን በእሚለው መጽሐፉ መግቢያ ላይ እንደ እዚኽ ይላል ፦
“ሰለባዎችህ በራሳቸው ዓለም ውስጥ ነው የእሚኖሩት ፣ ዓዕምሮዋቸው በእለታዊ ኑሮ ኃላፊነት እና ጭንቀት ተይዟል ። የአንተ ፥ የመጀመሪያ ግብ ፤ ከእዚኽ ዝግ ከሆነው ዓለማቸው እነርሱን ቀስ በቀስ እየለየህ ፤ ዓዕምሮዋቸውን በአንተ ኃሳብ መሙላት ነው።”
“Your victims live in their own worlds, their minds occupied with anxieties and daily concerns. Your goal in this initial phase is to slowly separate them from that closed world and fill their minds with thoughts of you. [69]“
ስለ እዚኽ ፦ የሕዝባዊ ፖለቲካ መተኪያ የሌለው የዘመኑ የፖለቲካ አካኼድ እና ይኽ ሕዝባዊ ፓለቲካ የእሚሰራበት ዋነኛ መንገድ ፕሮፖጋንዳ በመሆኑ ፕሮፖጋንዳ አስፈላጊ ነገር ነው በዘመናዊ ፓለቲካዊ ምሕዳር ውስጥ ። ነገር ግን ፕሮፖጋንዳ አስፈላጊ ቢሆንም ፥ ፕሮፖጋንዳ ቀላል እና በጣም አቅም የአለው መሆኑ ፣ ስነ ምግባር በአደባባይ በፕሮፖጋንዳ መሳሪያነት እንደ ሞኝነት መቅረቡ ፣ ሰዎች በአንድም በሌላም ምክንያት ፤ ከመሥራት ፣ ከመቆጠብ ፣ ከትዕግስት እና ከፅናት ውጭ ፤ ድንቁርናን ፣ ኋላ ቀርነትን እና መኃይምነት ፤ በአመፅ ፣ በረብሻ ወይንም በሆነው ‘ሳይንሳዊ ቀመር’ መሻገር እንችላለን ብለው ማሰባቸው ወይንም እንደዛ ብለው መለፈፍ መቻላቸው ፤ ዴሞክራሲያዊ ከልካይ ኃይል ከሌለ ፤ የእነዚኽ ፖለቲካዊ እና ማሕበራዊ ኹኔታዎች ድምር ውጤት ፤ ጂንጎይስቱን ጨምሮ ቲያትረኛ ፖለቲከኞችን ወደ ስልጣን ሊያመጣ ይችላል ።
ደስ ሲላቸው አንድ ቀን ድንገት አጃቢዎቻቸውን አስከትለው ፤ በቴሌቭዥን እየተቀረፁ ፤ ጎዳና ላይ የእሚያልፈውን ሰው እያስቆሙ ፤ ፓስፖርትህ የታለ እያሉ ይጠይቁ የነበሩት የሊብያው ጋዳፊ ፥
ወይንም በአለኝ ልዩ የመፈወስ አቅም ፤ ኤች አይ ቪን ሳይቀር እፈውሳለሁ ብለው ፤ ሕዝባቸውን በ’ህክምና’ ድንኳናቸው ደጅ ላይ አሰልፈው ይውሉ የነበሩት የጋምቢያው ፕሬዘዳንት ፤ ያያህ ጃሜህ ፥
ወይንም ምንም የህክምና እውቀት ሳይኖራቸው ፤ ለቀዶ ጥገና ህክምና ዶክተሮች ፤ በቀዶ ህክምና ወቅት ሊከተሉት ስለ እሚገባ ጥንቃቄ ማብራሪያ የእሚሰጡት ፦ የቀድሞው የዩጋንዳ ፕሬዝደንት ዶ/ር ማርሻል ጀነራል ኢድያሚን ዳዳ
እና መሰል ሰዎች ፤ በሚልየን የእሚቆጠሩ ፤ አነሰም በዛም በእየ ሞያው መስክ አንቱ የተባሉ ሰዎች ባፈሩ ሐገራት ፤ በእዚኽ ትያትረኛ ባሕሪያቸው ወደ ፖለቲካ ስልጣን የእሚመጡት ፤ በእሚታዘዛቸው የወታደር ኃይል ተደግፈው ብቻ ሰአይሆን ፤ የፖለቲካ ልዩ ባሕሪ ፣ የፕሮፖጋንዳ አቅም ፣ የመደራጀት አቀም ፣ ወዘተ ፤ ከሰከነ አዕምሮ ባለቤት ከሆነው ከሰፊው ሕዝብ አንፃር የተሻለ ፖለቲካዊ ብልጫ ስለ እሚሰጣቸውም ጭምር ነው ።
እነ ሒትለር እና መሶሎኒ መሰል ሰዎችም እጅግ ሰለጠኑ በእሚባለው ማሕበረሰብ ውስጥ ሳይቀር ፤ ነባራዊውን ሕዝባዊ እና ዘመናዊ መዋቅር ትርምስምሱን አውጥተው ወደ ስልጣን የመጡት በእዚኹ አግባብ ነው ።
ለእዚኽም ነው ፤ እነ እዚኽ መሪዎች ፤ ራስ እና እግሩ በእማይታወቀው ዲስኩራቸው ወደ ፖለቲካ ስልጣን ከመጡ በኋላ ፤ ከሕዝብ አስተዳዳሪነት ይልቅ ወደ ቲያትረኝነት የእሚለወጡት ።
አብዛኛዎቻችን እንደ እምንገነዘበው ፤ የመንግሥት ባለ ስልጣናት ፤ እንደ ቲያትረኛ ሊያስደምሙን ፣ እንደ ሰርከስ ሊያዝናኑን ወይንም የምትኃታዊ ኃይል ባለቤት ሆነው የሆነ ከአዕምሮ በላይ የሆነ ተዓምር እንዲያሳዩን አይደለም የእምንፈልጋቸው ።
ይልቁንም ፤ በእሚታወቅ ሳይንሳዊ የኢከነሚክስ እና የማሕበራዊ ስረዓት መርሆዎች እየተመሩ ፤ እንደ ማሕበረሰብ ለመቀጠል የእሚያስፈልገንን ፖለቲካዊ መረጋጋት ፣ ኢከነሚያዊ እድገትን ማስቻል ወይንም ማመቻቸት ዓይነት ፤ ተጨባጭ ፣ የእሚታዩ እና የእሚለኩ ሥራዎችን እንዲ ሰሩልን ነው ።
ያም ሆኖ ግን ፤ የተሻለው ዜጋ ከራሱ ፤ ከሥራው እና ከሌላው ኃላፊነቱ በአሻገር ፤ ከላይ በጠቀስናቸው የፖለቲካ ኃይሎች የፕሮፖጋንዳ ትብብር ደንዝዞ ፤ የሐገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር በጂንጎይስት ወይንም በጸረ-ስልጣኔ አስተሳሰብ ሲተበተብ ፤ በእውቀትም በልምድም በእሚያንሰው ዜጋ ፣ ከያኒ በሆኑ ባለ ስልጣናት ሲጭበረበር ፣ ሲገዛ ፤ ብሎም ሲጨቆን ማየት ፤ የዓለም ታሪካዊ ክስተት ሆኗል ።
በእዚኽ ኹኔታ ውስጥ ፤ አንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ፤ ዘላቂ ፋይዳ የእማይሰጠውን ጂንጎይዝም ሊደግፍ ይችላል ።
እስከ አኹን ያልነውን ለማጠቃለል ፤ ጂንጎይዝም ሐዲዱን የሳተ የሐገር ፍቅር ነው ። የሐገር ፍቅር ለሐገር ህልውና እና ለዜጎች እርካታ አስፈላጊ ሲሆን ፤ ሐገራት ወይንም ፖለቲዊ ማሕበረሰባት ፥ በተግባር የተፈተኑ እና ወደ ባሕልነት ደረጃ የተቀየሩ ፤ የሥራ ፣ የቁጠባ ፣ የመልካም ጉርብትና ፣ ወዘተ ፤ እሴት ሳያዳብሩ ሲቀሩ ፤ ራሳቸውን ለተለያየ ፖለቲካዊ ሸፍጦች ተጋላጭ ያደርጋሉ ።
ሕዝብ ፤ በእዚኽ መልክ ተጋላጭ ሲሆን ፤ እንደ አሳታፊነት ፣ ውስብስብነት እና ስፋት ፣ ፕሮፖጋንዳ ፣ ወዘተ ፤ ያሉት ልዩ የፖለቲካ በኃሪያት ፤ ግራ የተጋቡ ፣ የተታለሉ ፣ አቋራጭ የእሚፈልጉ ፣ የተቆጡ ወይንም ድል ያሰከራቸው ፤ ሕዝብ እና ፖለቲከኞች ፤ ከሌሎች ሐገራት ወይንም ሕዝብ ጋር የእሚኖራቸው ግንኙነት ፤ ታሪካዊ ጠላትነትን ፣ የበላይነትን ፣ ስግብብነትን ፣ ወዘተ ፤ ታሳቢ የአደረገ ወይንም ጂንጎይስት ይሆናል ።
ምንም እንኳን ሕዝብ ፤ በፖለቲካ ውስብስብነት ፣ በፖለቲከኞች ልዩ ስብዕና ፣ በፕሮፖጋንዳ ፣ ወዘተ ፤ ተታሎ እና ተስቦ ጂንጎይዝምን ሊደግፍ ቢችልም ቅሉ ፤ በታሪክ አጋጣሚ በሐገር ስም በተካኼዱ የጅንጎይዝም ፖሊሲ ኢፍትሐዊ ጥቅም ያጋበሱ የፖለቲካ ቡድኖች መኖራቸው የታወቀ ቢሆንም ፤ ጂንጎይዝም ለሰፊው ሕግ አክባሪ የሕብረተሰብ ክፍል የእማይበጅ አፍራሽ አቅጣጫ ነው ።
ይኽም በመሆኑ ፤ ጂንጎይስቱ ፥ ነፍሴን እስከ መስጠት እወዳታለኹ የእሚላትን እና ለእርሱ ምትሐታዊ ባሕሪ ያላት ሐገሩ ፤ እንደ ኹኔታው ፦ ታሪካዊ ጠላቶቿን መበቀል ያለባት ፣ ወይንም ከሌሎቹ የዓለም ሐገሮች የበላይ እና የተሻለች በመሆኗ ሌሎቹ ሕዝብ እና ሐገሮች በሙሉ ለእርሱ ሐገር መገዛት የአለባቸው ፣ ወይንም የእርሱ ሐገር ከሌሎቹ ሐገሮች ሁሉ ምርጥ በመኾኗ እና ሕዝቦቿም ከሌሎች በላቀ ኹኔታ የሰለጠኑ በመሆናቸው ፤ ሌሎች ሐገሮች እና ሕዝብን የማስልጠን ኃላፊነት የአለባቸው ፣ ወዘተ ፤ ዓይነት የተዛባ የውጭ ግንኙነት እይታ የአለው እና ይኽ የተዛባ የውጭ ግንኙነት እይታውም ፤ የሐገሩ ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ፖሊሲ ዋነኛ ማጠንጠኛ የሆነበት ነው ።
በዋናነትም ፤ ለጂንጎይስቱ ፦ ሐገር ማለት ፤ በእጁ ላይ ያለች የጠብ መጫሪያ እና መምሪያ መሳሪያ ነች ።[1] ይኽ ማክስ ዌበር የጠቀሰው የቤንጃሚን ፍራንክሊን ደብዳቤ ፤ ምንም እንኳን የእዚኽ መጽሐፍ አንባቢ ፤ ማክስ ዌበር ከጠቀሰበት አውድ አንጻር እንዲያነበው ስለ ተፈለገ ፤ ከማክስ ዌበር መጽሐፍ ቢጠቀስም ፤ ማክስ ዌበር የጠቀሰው ደብዳቤ ያልተሟላ ስለሆነ ፤ መጨረሻዎቹ አከባቢ ከዋናው የቤንጃሚን ፍራንክሊንን ደብዳቤ የተወሰደ እና የተጨመረ ክፍል አለው። ስለ እዚኽ ፦ ወደ መጨረሻዎቹ አንቀጾች አከባቢ ፤ በማክስ ዌበር መጽሐፍ ላይ ከተጠቀሰበት ጋር ይለያያል።
[2] ስታሊን ፦ እንድ ሰው የራሱን ጆሮ ማየት እንደ እማይችለው ስፓኞች ወርቃቸውን መልሰው አያዩትም እንደ አለ ይነገራል። አንተ ጠንክረህ ሰርተህ ገንዘብ ስትሰበስብ ፤ አንተ ጠንክረህ ሰርተህ የሰበሰብከውን ገንዘብ ከኪስህ ለማውለቅ በአንተ ልክ ወይንም ከአንተ በላይ ጠንክረው የእሚሰሩ ሌሎች ኪስ አውላቂዎች አሉ የእሚባለውን አባባል በፖለቲካውም ረገድ ልብ ማለት ተገቢ ነው።