Skip to main content

ኃይማኖታዊ ጽንፈኝነት እና ሐገር

ኃይማኖት  ፤ ሰው በልዩ አምላካዊ ብርኃን  ይቀበለው (ተቀበልኩት ይበል) ወይንም በአዕምሮ ፍርድ ደረስኹበት ይበል ፤ ከተመራማሪ የሰው ተፈጥሮዋዊ ባሕሪ ለእሚመነጩ ፦ እኔ ማን ነኝ ? ለምን ተፈጠርኹ ? የሰው በህይወት የመኖር ዓላማው ፥ ግቡ ምንድን ነው ? ማነው የፈጠረኝ ? ይኽ በዙሪያዬ የእማየው ቁሳዊውን ዓለም ማን ፈጠረው? እንዴት ተፈጠረ? ለምን ተፈጠረ? ወዘተ ፤ የእሚሉትን የሰው ልጅ የእድሜ ዘመን ጥያቄዎች ፤ በአጠቃላይ ፦  ሰው  ፡  ራሱን  ፣ ሊመራበት የእሚገባውን መርህ ፣ በዙሪያው የአለውን ቁሳዊ ዓለም እና ይኽ ራሱን የእሚጨምረውን ዓለም የእሚያንቀስቅሰውን መርህ ወይንም ኃይል ፤ ለመረዳት ወይንም ለመግለፅ የእሚጠቀምበት ፤ ከተመራማሪነቱ የእሚመነጩ ጥያቄዎችን ለመመለስ የእሚያስችለው ፤ ኃሳባዊ መዋቅር ነው ።


ይኽ እነ እዚኽን ዘመን የእማይሽራቸውን ፤ ተመራማሪው ሰው የእሚጠይቃቸውን ፤ ጥያቄዎች የሰው ልጅ የእሚመልስበት ኃሳባዊ መዋቅር ወይንም ኃይማኖት ያልነው ፤ ምንም እንኳን በዋናነት ፤ ያለ እና የነበረ እንዲኹም ለዘላለም የእሚኖር (ኢሙውታዊ) ኹሉን ቻይ አምላክን መዓከል በአደረገ መልኩ የእሚዘጋጅ ቢሆንም ፤ ከጥንት ጀምሮ ከኢሙውታዊው እና ከኹሉን ቻዩ አምላክ እሳቤ ውጭ ፤ ይኽ ዓለም እና እኛ ፤ ያለ ፈጣሪ ተፈጥረን የእምንኖር ነን በእሚል ፤ እነ እዚኹኑ ዘመን አይሽሬ የሰው ልጅ ጥያቄዎች ፤ አምላከ-ከኃዲነት (Atheism) በእሚባል የኃሳብ መዋቅርም ለመመለስ የእሚጣር በመሆኑ ፤ በእዚኽ ክፍል አምላክ አምላኪውንም አምላክ ከኃዲውንም በአንድነት ደርበን ፤ እንደ ኃይማኖት ነው የእምናያቸው ።


ምን አልባት አንዳንድ ሰዎች ፤ አምላከ-ከኃዲነትን ፤ ከእምነት በተቃራኒ በሳይንሳዊ እውቀት ላይ የተመሠረተ እና የዘመናዊ ሳይንሳዊ እውቀት መዳበር የአመጣው አድርገው በማየት ፤ ብዙ ግዜ የሰው ልጅ በሳይንሳዊ መንገድ ሳይሆን በእምነት ከእሚይዛቸው እና ጥንታዊ ከሆኑ ኃይማኖታዊ ቀኖናዎች ጋር አብሮ መዳበል የለበትም ሊሉ ይችላሉ ።


እውነታው ግን ክህደተ-ዓምላካዊነት ፤ እንደ አምላክ አማኙ ኃይማኖት ከሳይንስ ሰአይሆን ከፍልስፍናው ጎራ የእሚመደብ እንደ እዚኹም ዘመናዊ ክስተት እና በሳይንሳዊ እወቀት ከመዳበር ጋር የእሚያያዝ ሰአይሆን በጥንታዊ እና በኋላ ቀር ሕዝብም ሊስተዋል የእሚችል በመሆኑ ፤ በአመክንዮ ሰአይሆን በእምነት ላይ የተመሠረተ ፤ ስለ እዚኽም ፦ ከእምነት ዓይነት የእሚፈረጅ ነው።


ክህደተ አምላካዊነት ፍልስፍና እንጂ ሳይንስ አይደለም ። ያም ማለት ፤ ክህደተ-አምላካዊው አምላክ የለም ብሎ ሲያምን ወይንም ይኽ እኛን የእሚጨምረው ዓለም ያለ ፈጣሪ እንዲኹ በራሱ ግዜ ያለ እና የእሚኖር ነው ሲል ፤ አምላክ አለ ፥ ዓለምንም እኛንም የፈጠረን እርሱ ነው ከእሚለው የተለየ ሳይንሳዊ ማስረጃ ስለ አለው ሰአይሆን ፤ በፖለቲካዊ እና ግላዊ ምክንያት አምላክ የለም ብሎ ማመኑ ይበጀኛል ብሎ ስለ መረጠ ብቻ እንጂ ፤ አምላክ አለመኖሩን እና ዓለምም ያለ አምላክ እንዲሁ እንደ አለች የነበረች መሆኑን የእሚያስረዳ ሳይንሳዊ መረጃ ስለ አለው አይደለም ።


ዓለም በእግዚአብሔር ተፈጥራለች ብሎ የእሚለው ሰው ፤ ይኽን ዓለም የፈጠረውን እግዚአብሔርን ማሳየት እንደ እሚቸገረው ፤ ዓለም ያለ እግዚአብሔር ተፈጥራለች የእሚለው ሰው ፤ ከምንም እና ከአለማንም እንዴት ይኽ ውስብስብ ዓለም ሊፈጠር እንደ እሚችል ማሳየት አይችልም።


ይኽም ብቻ ሰአይሆን ፤ ክህደተ_ዓምላካዊነት እንደ አምላክ አማኙ በሳይንስ ላይ የተመሠረተ ከአለመሆኑ በአሻገር የሰው ልጅ በሳይንሳዊ እውቀት መራቀቁ የአስከተለው አዲስ ክስተት ሰአይሆን ፤ ሳይንስ የዛሬው ደረጃ ላይ ሳይደርስ ፤ ቢያንስ ከ2000 ዓመታት ገደማ ቀደም ብሎ ጀምሮ ፤ ለምሳሌ ፦ በጥንታዊ ግሪኮች እና በኋላም በሮም ክህደተ-ዓምላክ ይስተዋል እንደ ነበር በጉዳዩ ላይ የተሰራ ጥናት እንደ እዚኽ ይላል ፦


“…እንደ ልዩ ነገር ግን ወጣ ያለ ክስተት ፤ ፍልስፍናዊ ክህደተ-ዓምላክ በጥንታዊ ግሪከ-ሮማን ዘመን ነበር ።”

“… atheism did exist in Graeco-Roman Antiquity as a specific, yet exceptional form of philosophical atheism. [2]“


ከክርስቶስ ልደት 500 ዓመት በፊት ይኖር የነበረው አርስታትል ፤ ከግሪክ ፈላስፎች ቀዳሚዎች ጎራ የእሚመደበው ታለስ ፤ በዓለም ላይ የአለው ነገር ኹሉ ፤ ከውኃ ነው የወጣው ብሎ እንዳስተማረ ዘግቧል ፦


“ታለስ… መርኹ[1] ወኃ ነው ይላል … ምናልባት ኃሳቡን ኹሉም ነገር በጠል መረስረሱን እና ሙቀት ራሱ በእንፋሎት አማካኝነት መመንጨቱን እና በእዚያኽም መቀጠሉን ተመልክቶ ይኾናል … በድጋሚም የኹሉ ነገር ዘር በውስጡ እንፋሎት/ጠል እንደ አለው ተመልክቶ እና የጠል/እንፋሎት ኹሉ ምንጩ ውኃ በመኾኑም ይሆናል ።”

 

“Thales, …, says the principle is water …getting the notion perhaps from seeing that the nutriment of all things is moist, and that heat itself is generated from the moist and kept alive by it … He got his notion from this fact, and from the fact that the seeds of all things have a moist nature, and that water is the origin of the nature of moist things [3].”

 

ምንም እንኳን ይኽን የታለስን አስተምህሮ እንደ ክህደተ-ዓምላክ ዕምነት ዓይነተኛ ምሳሌ አድርገን ልንወስደው በአንችልም ፤ አምላክን ሳይሆን ውኃን የሕይወት እና የዓለም ምንጭ አድርጎ በመውሰዱ ፤ ስለ እዚኽም ፦ ከአምላክ ውጭ ዓለምን ሊረዳ የእሚሞክር በመሆኑ ፤ ከክህድተ-አምላክ ወይንም ከቁሳዊነት (Materialism) ጎራ የእሚፈረጅ ነው ።

 

ከክርስቶስ ልደት 1ሺ ዓመት ገደማ ፤ ቀደም ብሎ እንደ ኖረ የእሚታመነው ፤ የእሥራኤሉ ንጉሥ ዳዊት ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ፤ መዝሙረ ዳዊት 14፡1  ላይ ፦

 

“ሰነፍ በልቡ፡— አምላክ የለም ይላል።”

 

ብሎ አስቀምጧል ። በእዚኽም ፤ በኃይማኖታዊ መጽኃፍት ራሱ ፤ ክህደተ-አምላክ በጥንት ዘመንም የእሚታወቅ መኾኑን እንረዳለን ።

 

በእዚኽም ዘመን ፤ ከስልጣኔ ርቀው በጣም ኋላ ቀር በኾነ የኑሮ ዘይቤ ውስጥ እየኖሩ ፤ አምላክ የለም ብለው የእሚያምኑ ሕዝብም እንደ አሉ ፤ በዓለም ዙሪያ እየዞሩ የሰዎችን ባህል የእሚያጠኑ ሰዎች ይዘግባሉ ፦

 

“አንዳንድ በአፍሪካ የእሚገኙ የድንኮች ነገዶች ፤ ምንም ዓይነት ኃይማኖታዊ ባሕል ፣ ልማድ ፣ ምልክት ፣ አፍቅሮት ወይንም ዓምላክ የላቸውም ።”

 

“Certain Pygmy tribes of Africa had no observable cult or rites; they had no totem, no fetishes, and no gods; [4]“

 

እነ እዚኽም ታሪካዊ ማስረጃዎች ፤ ከላይ እንደ አልነው አምላክ የለም ብሎ መካድ ፤ የአንድ የኾነ ዓይነት ስልጣኔ ደረጃ መገለጫ ሰአይኾን ፤ በዘመን እና በቴክኖልጂ ደረጃ የእማይወሰን ፤ ብሎም አምክንዮ ሳይሆን እምነት መሠረቱ የሆነ ፤ የግለሰቦች የአስተሳሰብ መዋቅር ምርጫ መሆኑን አስረጂዎች ናቸው ።

 

እንዲያውም ክህደተ አምላክ የዘመናዊነት መገለጫ የእሚመስላቸው ሰዎች በደንብ ከአስተዋሉ ፤ ኋላ ቀር በእሚባለው በቀደመው ዘመን የሰው ልጅ ክህደተ-አምላክን ጨምሮ በጠቅላላው ኃይማኖታዊ ጥያቄዎች ላይ የተመራመረውን እና የተለያዩ መላምቶችን የአስቀመጠውን  ያኽል ፤ አኹን ዓለም በተለያየ ቴክኖሎጂ  ሰልጠኗል በእምንልበት ዘመን ነዋሪው ሰው እንደ እማያደርገው ይመለከታሉ ።

 

አኹን የአለው ዘመናዊው ሰው ፤ የዘመኑ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ በእሚሰጠው አቅም ፤ ቀደምቶቹ ያሉቱን በርብሮ እየ አወጣ አዲስ አስመስሎ ያቀርባቸዋል እንጂ ፤ ቀደምቶቹ በኃይማኖት ፤ በአምላክ በመማመኑም ሆነ አምላክን በመካዱ ጎራ ፤ የእሚባሉትን በሙሉ ብለው ጨርሰውታል ማለት ይቻላል ።

 

ለእዚኽም ነው ፤ ኃይማኖት ፥ አምላክን የእሚያምነው እና አምላክን የእሚክደው ፤ በፍልስፍናው መስክ የልዕለ ተፈጥሮ ትንታኔ (Metaphysics) በእሚለው ዘርፍ ስር እንጂ በሳይንስ ስር የእማይካተተው ።

 

ይኽን መሰል መልክ የአለው ኃይማኖት (ኃሳባዊ መዋቅር) ፤ መልስ ከእሚሰጥባቸው ጥያቄዎች ፈታኝነት እና ብዛት አንፃር ፤ ከማሕበረሰብ ማሕበረሰብ ፣ ከሰው ሰው ፣ ከዘመን ዘመን ፤ እንደ ማሕበረሰቡ ፣ እንደ ግለሰቡ እና የእሚገኙበት ዘመን እንደ ፈቀደው የግንዛቤ መጠን ፤ ለእነዚኽ ዙሪያ መለስ የሰው ልጅ ተመራማሪነት ውጤት ለሆኑ ጥያቄዎች የእሚሰጣቸው መልሶች የተለያዩ ናቸው ።

 

ለምሳሌ ፦ በጃፓኖች የሺንቶ እምነት አፈ ታሪክ ፤ ወደ 4 ሺ የእሚጠጉት ደሴቶቻቸው የተፈጠሩት ወይንም ሐገራችን ጃፓንን ማን ፈጠራት ለእሚለው የጥንት ጃፓኖች ጥያቄ ( ከነበረባቸው የመልከዓ ምድር እውቀት ውስንነት የተነሳ ፤ ጃፓን ዓለማቸው በመሆኗ ) ፤ የሺንቶ ኃይማኖታቸው የእሚሰጠው መልስ ፦ ባል እና ሚስት የነበሩ ዓማልክት ፤ በሰማይ ላይ ከተንሳፈፈ ድልድይ ላይ ኾነው ፤ በጌጣጌጥ ያሸበረቀ ጦራቸውን ሲዘረጉ ፤ ከጦሩ ላይ በጠል የተሰራ እንጥብጥቢ እየወረደ የጃፓን 4 ሺ ደሴቶች እንደ ተፈጠሩ የእሚል ነው ፦

 

“በመጀመሪያ አማልክት ነበሩ ፤ ይላል ከጃፓኖች ታሪክ በጥንታዊነቱ ቀዳሚ የሌለው ታሪክ ። እነርሱም ወንድ እና ሴት ዓማልክት እየሆኑ ሲዋለዱ እና ሲሞቱ ቆይተው ፤ በስተመጨረሻ ኢዛናጊ እና ኢዛናሚ የእሚባሉት ዓማልክት  ፤ በእድሜ ጠና በአሉት ዓማልክት ጃፓንን እንዲፈጥሩ ታዘዙ። እናም ፤ በተንሳፋፊው ሰማያዊ ድልድይ ላይ ቆመው ፤ በጌጣጌጥ ያሽቆጠቆጠውን ጦራቸውን ወደ ምድር አምዘገዘገው በአየር ላይ አንሳፈፉት ። ከእዚኽም ጦራቸው የወረደው ነጠብጣብ የተቀደሱት ደሴቶች (ጃፓን) ኾኑ ። ከእዚያኽም በኋላ ፤ ኢዛናጊ እና ኢዛናሚ ፤ የውሻ አሳዎች በውኃ ውስጥ ሲራቡ አይተው ስለ ርቢያ በመማራቸው ፤ የጃፓንን ዘር/ሕዝብ ወለዱ ።”

 

“In the beginning, says the oldest of Japanese histories, were the gods. Male and female they were born, and died, until at last two of them, Izanagi and Izanami, brother and sister, were commanded by the elder deities to create Japan. So they stood on the floating bridge of heaven thrust down into the ocean a jeweled spear, and held it aloft in the sky. The drops that fell from the spear became the Sacred Islands. By watching the tadpoles in the water the gods learned the secret of copulation; Izanagi and Izanami mated, and gave birth to the Japanese race. [4]“ 

 

የጅብራልታር ጥበት (straits of Gibraltar) የእሚባለው ፤ በሰሜናዊ ምዕራብ አፍሪካ እና በደቡባዊ ምዕራብ አውሮፓ መካከል ያለ ጠባብ የባሕር መተላለፊያ ፤ የሜድትራኒያን ባሕር ወደ አትላንቲክ ውቂያኖስ የእሚቀላቀልበት በር ነው ።

 

በእዚኽ ፦ በኹለቱ አህጉሮች መሐከል የእሚገኝ ይኽ ጠባብ መተላለፊያ ላይ ደግሞ ፤ በሰሜኑም በደቡቡም ጫፍ ላይ ኹለት ትልልቅ ተራሮች ያሉ ሲኾን ፤ የግሪክ ባለ ብዙ ዓማልክት እምነት አፈታሪክ እነ እዚኽን ኹለት ተራሮች ፤ ከብዙዎቹ ዓማላክቶቻቸው ፥  አንዱ የኾነው ፥ ኼርኩለስ የተባለው ዓምላካቸው ፤ ከሰማይ ላይ ወርውሮ እንደ ተከላቸው ይናገራል  ፦ አትላንቲክ ውቅያኖስ ውስጥ ያሉ ጭራቆች ወደ ሜድትራኒያን ባሕር እንደ አይመጡ ።

 

የከዋክብትን እንቅስቃሴ ከጥንት ጀምሮ ሲከታተሉ እና ሲመዘግቡ ለነበሩ ባቢሎናዊያን ፤ የከዋክብት አወጣጥ እና አሰላለፍ ፤ አምላክ በሰማያዊው ሰሌዳ ላይ ፤ ሚስጥራዊ መልዕክት የእሚያስተላልፍበት መንገድ ነው ።  

 

 ዘመናዊው ኬሚስትሪ ፤ በዓለም ላይ የአሉት ነገሮች ኹሉ ከ109 ንጥረ-ነገሮች (Elements) ተፈጥሯል ብሎ ፔሬዲክ ቴብል እንደ ቀመረለን ፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ ፤ በአብዛኛው በቀደመው ዓለም ፤ ፈጣሪ በዓለም ላይ የእሚታየውን ነገር ኹሉ ፦ ከውኃ ፣ ከአፈር ፣ ከእሳት እና ከአየር ነው የሰራው ብለው ነበር የእሚያምኑት ።

 

 እንደ ሔሮድተስ ዘገባ ፤ ግብፆች ፤ የእህልን እና የወይንን ምርታማነት የእሚቆጣጠሩት ፤ ከምድር በታች የእሚኖሩት ዲመትር እና ዳይናሰስ (በኋላ ግሪኮች ባከስ ብለው የሰየሙት) የእሚባሉት ዓማልክት ናቸው ብለው ያምኑ ነበር ። ሔሮድተስ አያይዞም ፤ በመጀመሪያ  ሰው ስጋው ሲሞት ነፍሱ አይሞትም ያሉት ፤ ግብፆች ናቸው ይላል ። አያይዞም ፤ ግሪኮች (ሔለኖች) ፥ ይኽንን አስተምህሮ ከግብፆች እንደቀዱት ይነግረናል ፦

 

“ግብፆች ፤ ዲመትር እና ዳይናሰስ በታች የአለውን ዓለም የእሚገዙ ናቸው ይላሉ ፤ እንዲኹም የሰው ልጅ ነፍስ ኢሙውታዊ እንደኾነ መጀመሪያ ያስተማሩት ግብፆች ናቸው ።… ይኽንንም አስተምህሮ ሔለናዎች የራሳቸው ፈጠራ እንደኾነ አቀናብረው አቀረቡት … “

 

“The Egyptians say that Demeter and Dionysos are rulers of the world below; and the Egyptians are also the first who reported the doctrine that the soul of man is immortal,...This doctrine certain Hellens adopted, some earlier and some later, as it were of their own invention ... [5]“

 

ከእነ እዚኽ ዓለም ዓቀፍ የኃይማኖት ታሪኮች ልንረዳው እንደ እምንችለው ፤ ሰዎች ስለ ራሳቸው እና ስለ አከባቢያቸው የእሚፈጠርባቸውን ጥያቄ ፤ ከጥንት ጀምሮ በራሳቸው መንገድ አንዳንዴም ከሌሎች እየተማሩት ከላይ በአስቀመጥነው መልኩ አምላክን መዓከል በአደረገ እና አምላክን በካደ አኳኋን ሲመልሱ ኖረዋል ።

 

ምንም እንኳን በታሪክ እንደ እምናየው እና ዛሬም በእኛ ዘመን እንደ እምናውቀው ፤ ክህደተ-አምላካዊኑ እንደ ጋጠወጥ (Eccentric) ክስተት እንጂ እንደ አማኞቹ ወይንም አምላካዊያኑ አውራ ጎዳናውን ይዘው እና ትልቅ ማሕበራዊ ኃይል ሆነው ፤ የሰውን ልጅ ማሕበራዊ ፣ ኢከነሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሕይወት ላይ የጎላ ተጽኖ የእሚያደርግ ኃይል ሆነው አልመስተዋላቸው እንደ ተጠበቀ ቢሆንም ።

 

እንግዲኽ ለተመራማሪው ሰው ፤ ዙሪያ መለስ ምላሽ የኾኑት እነ እዚኽ ፤ ቀጥር ስፍር የሌላቸው ጥያቄዎች እና መልሶቻቸው በግዜ ኺደት ፤ በዋናነት በአምላካዊያኑ ወይንም አምላክን በእሚያምኑት ፤ በአምላካዊ መገለጥ ወይንም ተገልጦልኛል በእሚሉ ሰዎች እየዳበሩ መጥተው ፤ ዛሬ ላይ በይዘታቸው ረቀቅ ያሉ ፤ በባሕሪያቸው ማዕቀፋዊ አሰራሮችን በመተንተን እንጂ ጠባብ ከባቢያዊ ተራሮችን እና ወንዞችን በመግለፅ ያልተወሰኑ እና መርኾች ላይ ያተኮሩ ፤ ዘመናዊ ኃይማኖቶች ላይ አድርሰውናል ።

 

ከእዚኽም የተነሳ ፤ ኃይማኖት መሠረታዊ በሆነው የሰው ልጅ ጠያቂነት እየተነዳ ፤ በብዙ ዘመናት ፣ በብዙ ድካም እና በብዙ ኃብት የተገነባ  ፤ ለሰው ልጅ ሕይወት እጅግ ሰፊ ፖለቲካዊ ፣ ኢከነሚያዊ እና መንፈሳዊ ፋይዳ የአለው ፤ ተቋም ሆኗል።

 

ይኽን መሰል ገጽታ የአለው ኃይማኖት አንድ ግዜ ከዳበረ እና በሰው ልጅ ማሕበረ ኢከነሚ ውስጥ ትልቅ ፋይዳ የአለው ተቋም ከሆነ በኋላ ፤  በአምላክ አማኙም ሆነ በክህደተ-አምላካዊውም ዘንድ ተከታዮቹን ፤ በዋናነት ፦

 
  • በስብከት ኃይል በመሳብ ።
  • ከቤተሰብ ቤተሰብ በውርስ መልክ በመተላለፍ ።
  • በተለይ ጥቂት ቀደም ባሉ ግዜያት ፤ በተለያዩ የማስገደጃ መንገዶች
 

ያፈራል።

 

ይኽም ማለት ፤ ሰዎች ሲፈጠሩ የኾነው ኃይማኖት ተከታይ ተደርገው አልተፈጠሩም ማለት ነው።

 

የትኛውም የኃይማኖት ተከታይ ዛሬ የያዘውን ኃይማኖት የያዘው ፦ በራሱ ግላዊ ምርጫ ወይንም ደግሞ ቤተሰቦቹ በውድ ወይንም በግድ ተቀብለው ያስተላለፉትን ኃይማኖት ከቤተሰብ በውርስ መልክ ተቀብሎ እንጂ ፤ በተፈጥሮው የሆነው  ኃይማኖት ተከታይ ሆኖ የተወለደ ሰው የለም።

 

ፈጣሪም (ተፈጥሮም) ፤ ኃይማኖታችንን መርጠን እንድ እንገባበት ስለ ፈለገ ፤ ኃይማኖታችንን የእምንመርጥበት ተፈጥሮዋዊ አቅም እንጂ ኃይማኖታችንን የፍጥረታችን አንድ አካል አድርጎ አልፈጠረንም ። ኃይማኖትን የምርጫ ጉዳይ የአደረገው ፈጣሪያችን ወይንም ፍጥረታችን ራሱ ነው ።

 

በእዚኽ መጽሐፍ ኃይማኖትን በእዚኽ መልኩ መግለጽ የአስፈለገው ፤ ፊደል ለቆጠረውም ፊደል ላልቆጠረውም ሰው ፈታኝ የሆኑ መንፈሳዊ ጉዳዮችን በመዳሰስ ፣ ፊደል የቆጠረውንም ፊደል ያልቆጠረውንም አማኝ በቀናዒነት መሙላት የእሚችል እና በእዚኽ መጽሐፍ የጠቀስናቸው እና ያልጠቀስናቸው ብዙ ልዩ በኃሪያት የአሉት ኃይማኖት ፤ አንድ ግዜ በአንድ ማሕበረሰብ ውስጥ ከተደላደለ በኋላ ፤ በመሠረታዊ የዜጎች ተፈጥሮዋዊ የማሰብ ፣ ኃሳብን የመግለጽ እና በኃሳብ ዙሪያ የመሰባሰብ መብቶችን በእሚያከብር ስረዓት ከአልተገራ ፤ ኃይማኖታዊ ንጽህናን ለማስጠበቅ እና እውነተኛውን ኃይማኖትን ለማስፋፋት በእሚል ራሱን ወደ ፍጹማዊ የፖለቲካ ስረዓት መቀየር የእሚችል አደገኛ ተቋም በመሆኑ ነው።

 

ኃይማኖት በእዚኽ መልኩ አደገኛ የእሚሆነው ደግሞ ፤ ምንም እንኳን ኃይማኖት ፤ የአምላክን ድንጋጌ እና ቃል መቀበል በእሚባል ዋና ፅንሰ ኃሳብ ላይ የተንጠለጠለ ቢሆንም ፤ ትክክለኛው አምላክ የትኛው ነው ? ትክክለኛው የአምላክ ድንጋጌ የትኛው ነው ? ወዘተ ፤ የእሚሉ ጥያቄዎችን እያስከተለ ፤ የተለያዩ ሰዎች እነ እዚኽሁኑ ጥያቄዎች ጠይቀው ፤ እንደ መረዳታቸው ፣ እንደ ፍላጎታቸው እና እንደ ምርጫቸው የተለያየ መልስ እንዲሰጡ የእሚጋብዝ በመሆኑ ፤ የሰው ልጆችን ፤ የማሰብ ፣ የመምረጥ እና የማድረግ ችሎታ መቆጣጠር እና ሰዎችን አንድ ዓይነት ነገር ብቻ እንዲያስቡ ፣ አንድ ዓይነት ነገር ብቻ እንዲ መርጡ ፣ አንድ ዓይነት ነገር ብቻ እንዲያደርጉ ማድረግ ከአልተቻለ ፤ በኃይማኖቱም መስክ ፤ ሰዎችን ኹሉ አንድ ዓይነት ኃይማኖት እንዲከተሉ እና ለአንዱ ዓይነት ኃይማኖት ብቻ እንዲቀኑ ማድረግ የእማይቻል ስለሆነ ነው።

 

በሌላ አገላለጽ ፤ ኃይማኖታዊ ልዩነት ፦ በኃይማኖት መሠረታዊ ባሕሪ እና በሰው ልጅ በተናጠል የማሰብ ፥ የመምረጥ እና የማድረግ መብት ምክንያት ፤ ሊጠፋ የእማይችል እና ኹል ግዜም አብሮን የእሚኖር ነገር በመሆኑ ፤ ኃይማኖታዊ ነጻነትን ከማክበር ውጭ ኃይማኖታዊ አንድነትን ለማምጣት በኃይል መሥራት መጨረሻው ማሕበራዊ ቀውስ ነው።

 

ኃይማኖት በአምላክ የእሚገለጥልን ፣ ከቤተሰቦቻችን ወይንም ከአከባቢያችን የእምንወርሰው ፣ በአዕምሮ ፍርድ ልክ ነው ብለን የእምንገባበት ፤ የራሳችን ምርጫ ውጤት እንጂ ፤ ውስጣችን የተገመደ ፍጥረታዊ ማንነታችን በአለመሆኑ ፤ ኃይማኖታዊ ወጥነት የእሚቻል ነገር አይደለም ።

 

እውነታው ይኽ ቢሆንም ቅሉ ፤ የሰው ልጅ ግን በታሪክ ዘመኑ ኹሉ ፦ ኃይማኖት ለማስፋፋት ፣ እውነተኛውን ኃይማኖት ከውድቀት እና ከአሳቾች ለመከላለክል ፣ አሳቹን ወይንም የኑፋቄ አስተማሪውን ለማጥፋት ፣ ወዘተ ፤ በእሚሉ ምክንያቶች ፤ ከመሠረታዊ የሰዎች ተፈጥሮ ባሕሪ በተጻራሪ ፤ በእሚያደርገው የኃይል አካኼድ በዘመኑ ኹሉ ኃይማኖትን የማሕበራዊ ቀውስ ምንጭ ሲያደርግ እንደ ኖረ ፤ በዓለም ላይ በኹሉም የኃይማኖት ዓይነት ተከታዮች የተፈጸሙ ብዙ ማሳያ ታሪኮች አሉ ።

 

በሰው ልጅ አምስት እና ስድስት ሺ ዓመታት የስልጣኔ ዘመን ታሪክ ፤ ኃይማኖት ማሕበረሰባዊ ተቋም ኾኖ ከደረጀበት ግዜ አንስቶ አኹን እስከ አለንበት ዘመን ፤ በኹሉም ኃይማኖት  ተከታዮች ዘንድ ፤ ኃይማኖት ፦ እውነተኛውን እና አንዱን ኃይማኖት አራምዳለሁ ወይንም እከላከላለሁ በእሚል የምድራዊውን መንግሥት አቅም ሲጠቀም ፤  የተቃወማቸውን ኃይማኖታዊ አስተሳሰቦች እና የአስተሳሰቡን ተከታዮች ፤ አጥፍቶ ማጥፋት ላይችል ፤ ያለምንም ርህራኼ ሲያስገድል እና ሲያሳድድ ፤ በእዚኽም ፅንፈኛ አካኼዱ ብዙ ማሕበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ሲፈጥር በመኖሩ ፤ ኃይማኖታዊ ፅንፈኝነት ፥ እንደ ሽፍትነት ፣ እንደ ወንጀል ፣ እንደ ድህነት ኹሉ ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለሰው ልጆች ማሕበረስባት ኹሉ የማሕበራዊ ሰላም እና ልማት ሳንካ ሆኖ የቆየ ችግር ስለ መሆኑ ፤ ከጥንታዊ ጣዖት አምላኪያን ጀምሮ እስከ ዘመናዊዎቹ ክርስትና እና እስልምና ታሪክ ውስጥ በስፋት ሲታይ ቆይቷል ።

 

በእዚኽ ረገድ ታዋቂ ከኾኑ ታሪኮች አንዱ ፤ የጅብራልታርን ተራሮች ከሰማይ ላይ ወደ ምድር ወርውሮ የተከላቸው ኼርኩለስ ዓይነት ለቁጥር የእሚያታክቱ ብዙ ዓማልክት ይመለኩባት በነበረችው ግሪክ ፤ ከክርስቶስ ልደት 500 ዓመት በፊት  የነበረው ፤ የዘመናዊ ፍልስፍና አባት  ሶቅራጠስ ፦ በሐሰት ፥ ኃይማኖትን በመካድ እና ወጣቶችን ከዓማልክት በማራቅ ክስ ተከሶ ፤ በ70 ዓመቱ በሞት የተቀጣበት ታሪክ ነው ።  

 

የሶቅራጠስ ሙግት በእሚለው መጽሐፍ ላይ ፤ የሶቅራጠስ ተማሪ የነበረው ፕሌቶ እንደ አስቀመጠው ፤ ሶቅራጠስ ከቀረበበት እና የሞት ፍርድ ከአስፈረደበት ክስ አንዱ ፤ እንደ ሶቅራጠስ ያሉ ነገረ-ፈጆች ወይንም ነገር መርማሪዎች ፤ ከምርምራቸው ብዛት አምላክን ወደ መካድ የእሚመጡ ፤ አምላከ-ከሐዲያን ናቸው የእሚል ነበር ። በእዚኹ የክስ መከላከያው ላይ ስለ እዚኽ ጉዳይ ሶቅራጠስ እንዲኽ ብሏል ፦

 

“. . . አድማጮቻቸው ፤ በእነዚኽ ጉዳዮች ላይ የእሚመራመሩ ሰዎች ፤ በአምላክ አያምኑም ብለው ስለ እሚያስቡ ነው ። “

 

“…  For their listeners hold that investigators of these things also do not believe in gods. [6]“

 

በእዚኽ ሶቅራጠስ እያለ የአለው ፤ ክሳችሁን እውነት ያስመሰለው ፤ አብዛኛው አድማጫችሁ እንደ ሶቅራጠስ ያለ የነገር መርማሪ ሰው ፤ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣውን ዙሪያ መለስ ኃይማኖታዊም ሆነ ሌሎች መልሶች የእሚፈትሽ በመሆኑ ፥ ብዙዎች ሳይመረምሩ እንደ አምላክ ድንጋጌ የእሚቀበሉውዋቸውን ብኺሎች የእሚፈትሽ በመሆኑ ፤ በስህተት እና በዝበት ፤ አምላከ-ከኃዲ ተድርጎ ስለ እሚወሰድ ነው ።

 

በእዚኹ ታሪክ ፤ ከሶቅራጠስ ከራሱ የክስ ማስተባበያ እንደ እምንረዳው ግን ሶቅራጠስ የግሪኮችን አፈታሪክ ፤ ኃይማኖታዊ የኾኑትንም ያልኾኑትንም የእሚመረምር እና ጉድለት አለባቸው ብሎ ሲያስብም የእሚተች እንጂ ፤ እነርሱ እንደ እሚሉት አምላክ የለም ብሎ የካደ እንደ አልነበረ ነው ። ለእዚኽ የእሚቀጥለው የሶቅራጠስ ንግግር ማስረጃ ነው ፦

 

“. . . በዚየስ ፊት እጠይቃችኃለሁ ፤ ለኹላችኹም እንዲኽ ነው የእምመስላችሁ ? እኔ ዓምላክ የእሚባል የለም ብዬ አምናለሁ ?”    

 

“ … But before Zeus, is this how I seem to you? Do I believe there is no god? [6]“

 

በእዚኽ በተጠቀሰው ክፍል ላይ ፤ ሶቅራጠስ በግልፅ ከአደረገው ማስተባበያ በአሻገር የተጠቀመባት ፦ ‘በዚየስ ፊት እጠይቃችኃለሁ ፥’ የእሚለው ሐረግ ፤ ዚየስ በግሪኮች የዓማልክት ሰንሰለት አናት ላይ የእሚገኝ ዓምላክ በመኾኑ ፤ የሶቅራጠስ አባባል በእኛ ዘመን አንድ ሰው ፤ ‘በእግዚአብሔር ይዤአችኋለሁ እውነቱን ተናገሩ’ ብሎ ከእሚጠይቅበት ኹኔታ ጋር ተመሳሳይ በመኾኑ ፤ ሶቅራጠስ በጥያቄው ውስጥ በፈጣሪ እንደ እሚያምን እያመላከተ ለመኾኑ ምንም ጥርጥር የለውም ።

 

ከእዚያኽም በአሻገር በሪፐብሊኩ[2] ውስጥ ሶቅራጠስ በአንድ እና መልካም አምላክ እንደ እሚያምን እጅግ በግልጽ ተቀምጧል።

 

ነገር ግን ፤ ሶቅራጠስ በግሪክ ኃይማኖታዊ አፈታሪክ እና ከእዚያኽም ጋር በተያያዙ ጎጂ ልማዶች እና ባሕሎች ላይ ፤ የእሚያቀርባቸው ትችቶች ብዙ ተከታይ ስለ አፈራለት እና ይኽም ግሪኮች ባሕላዊ ኃይማኖታችን በእዚኽ አሳች ምክንያት ሊናቅ ነው ብለው ስለፈሩ ፤ በዘመናቸው ፍርድ ቤት ከሰው እና ጥፋተኛ ብለው በሞት እንዲ ቀጣ አድርገውታል።

 

ይኽ ዓይነቱ ፤ የፅንፈኞች መገለጫ የኾነው ፤ በካዮችን ወይንም ኃይማኖትን አጥፊዎችን ማጥፋት የእሚለው አካኼድ ግን እድሜ ጠገብ እና ኃይማኖታዊ  ድንበር የእማይከለክለው ልማድ ነው ። 

 

ጥንታዊያኑ እና ጣዖት ወይንም ብዙ ዓማልክት ዓምላክያን (polytheist) በእሚያደርጉበት አግባብ ፤ ዘመናዊው ሰው እና የፍቅር አንድ አምላክ እናመልካለን የእሚሉትም (monotheist) ሲያደርጉት የነበረ ነው ።

 

ሶቅራጠስን ፥ ግሪኮች ፤ ለኃይማኖታቸው ቀንተው ሞት ከፈረዱበት 500 ዓመት በኋላ የመጣው ክርስትና ፤ ጅማሮው ላይ ፤ በአንዳንድ ሮማዊያን ኢምፐረሮች ዘመን እጅግ የተጠላ ኃይማኖት ከመኾኑ የተነሳ ፤ እነ እዚኽ ዓይነቶች ኢመፐረሮች በሮም በነገሡባቸው ዓመታት ፤ ነገሥታቱ ክርስቲያኖችን ሲያሳድዱ ፣ ሲያሰቃዩ እና ሲገድሉ መልካም ነገር እንደ አደረጉ ይቆጥሩ ነበር  ።   

 

እ.አ.አ. በ64 ዓ.ም  መነሻው በደንብ በእማይታወቅ የእሳት ቃጠሎ የሮም ከተማ በእሳት ስትጋይ  ፤ የሮም ሕዝብ ኔሮ የእሚባለው ኢመፐረር ከተማውን እንደ ገና ለማሰራት ሲል ኾን ብሎ እንደ አቃጠለው በመጠርጠራቸው  በንጉሳቸው ላይ ስለ አቄሙ ፤ ኔሮ የሕዝቡን አመኔታ ለማግኘት የአቃጠሉት እነ እዚኽ የእምትጠሉዋቸው ክርስቲያኖች ናቸው በማለት ፤ በሮም የእሚገኙ ክርስቲያኖችን ጨፍጭፎ ነበር ። ይኽንንም ታሪከ እ.አ.አ. ከ56 – 120 ዓ.ም. የኖረው ታሲተስ የእሚባለው የሮም ታሪክ ጸሐፊ እንዲኽ ዘግቦታል ፦

 

“በሰው የእሚሰጥ ማንኛውም ስጦታ ፣ በልዑል የእሚቀርበው ድርጎ ፣ ለዓማልከት የእሚቀርቡ መስዕዋቶች ፤ ኹሉ እስከ አኹን በኹሉ ቦታ ከእሚታመነው ፤ በኔሮ ላይ ከቀረበው ውንጀላ[3]  ኒሮን ነጻ የእሚያወጣው ነገር አልተገኘም። የተስፋፋውን አሉባልታ ለማጥፋት ፤ በአስጸያፊ ወንጀላቸው ምክንያት በኹሉ ስፍራ የእሚጠሉትን እና በተለምዶ ክርስቲያን ተብለው የእሚታወቁትን ፤ በሐሰት የእዚኽ ጥፋት ተጠያቂዎች በማድረግ ፤ እጅግ በጣም ለየት ያለ ማሰቃየት ከአደረሰባቸው በኋላ በሞት ቀጣቸው። የእዚኽ ስም ጀማሪ ፤ በጥቤሪያስ የንግሥና ዘመን ፤ ጴንጤናዊው ጲላጦስ የይሁዳ በጅሮንድ በነበረበት ግዜ ፤ በወንጀል ተከሶ በሞት የተቀጣው ክርስቶስ ነው ፤ ይኽ የኑፋቄ ወረርሽኝም ከእዚያኽ በኋላ ለግዜው ጋብ ከአለ በኋላ ፤ በተፈለፈለበት በይሁዳ ብቻ ሰአይሆን ፤ ከአራቱም የምድር መዓዘናት ኹሉ ፤ በሰዎች ኹሉ ዘንድ አስጸያፊ እና የተጠላው ነገር ኹሉ የእሚፈስባት ሰርጥ ወደ ሆነችው ፤ አስጸያፊው ነገር ኹሉ ሰፊ ሕዝባዊ ተቀባይነት እና ተከባሪነት ወደ እሚያገኝባት ፤ ሮምም ተስፋፋ። መጀመሪያ በግልጽ ከእነርሱ ጎጥ የሆኑት ተያዙ ፤ ከእዚያኽ በእነርሱ አማካኝነት ሌሎች በስውር የሆኑ ብዙዎች ታወቁ ፤ ከእዛ ኹሉም ጥፋተኛ ተብለው ፤ ሮምን አቃጠሉ ስለ ተባሉ ብቻ ሰአይሆን ፤ የሰው ልጅ ዘር ኹሉ ጠላት በመሆናቸው አና ሰዎችን የእሚጠሉ በመሆናቸው ፤ ተፈረደባቸው። እነ እዚኽም ፤ ተሰቃይተው ከመገደላቸው በተጨማሪ ፤ እጅግ ብዙ የከፋ ማንጓጠጥ እና ጨዋታ ተደረገባቸው ፤ ምክንያቱም ፦ አንዳንዶቹ በዱር አውሬ ቆዳ ተሸፍነው በውሾች እየተበሉ እንዲሞቱ ተደረጉ ፣ አንድ አንዶቹ በመስቀል ላይ ተሰቅለው እንዲንጠለጠሉ ተደረጉ ፣ አንድ አንዶቹ በእሚቀጣጠል ልብስ ተጠቅልለው ፤ ለዓይን ያዝ ሲያደርግ ፤ በእሳት እየተቃጠሉ ብርሐን እንዲሰጡ ተደረጉ።” 

 

 

“But not all the relief that could come from man, not all the bounties that the Prince could bestow, not all the atonements which could be presented to the gods availed to acquit Nero from the hideous charge, which was still universally believed. Hence to suppress the prevailing rumor, he transferred the guilt upon fictitious criminals, and subjected to most exquisite tortures, and doomed to executions singularly cruel those people who, for their detestable crimes were already in truth universally abhorred and known to the vulgar by the name Christians. The founder of this name was Christ, one who in the reign of Tiberius suffered death as a criminal, under Pontius Pilate Imperial Procurator of Judea, and, for a while, the pestilent superstition was quelled, but revived again and spread, not only over Judea, where this evil was first broached, but even through Rome, the great gulf into which, from every quarter of the earth, there are torrents forever flowing of all that is hideous and abominable amongst men : Nay, in it the filthy glut of iniquity never fails to find popular reverence and distinction. First therefore were seized such as freely owned their sect, then, a vast multitude by them discovered; and all were convicted, not so much for the imputed crime of burning Rome, as for their hate and enmity to humankind. To their death and torture were added the aggravations of cruel derision and sport; for, either they were disguised in the skins of savage beasts and exposed to expire by the teeth of devouring dogs; or they were hoisted up alive, and nailed to crosses; or wrapt in combustible vestments, and set up as torches, that, when the day set, they might be kindled to illuminate the night. [7]“

 

እንግዲኽ ይኽ ክርስቲያኖችን በእዛኽ ዘመን በሕዝቡ እንደ እዚኽ እስኪ ጨከንባቸው ድረስ የአስጠላቸው እና ስማቸውን ያስጠፋው ተግባራቸው ፤ ሌላ ክፉ ተግባር ሰአይኾን  ፤ በወቅቱ የነበረውን የሮማውያን  የዓምልኮ ልማድ የእሚቃወሙ በመኾናቸው ነው ። ለምሳሌ ፦  ሮማዊያን በጣም ተወዳጅ የነበረው እና በግፍ የተገደለው ቄሳር የእሚባለውን የሮም ንጉሥ ፤  ዓምላክ በማድረግ እጣን ያጥኑለት እና ይሰግዱለት ስለ ነበር  ፤ ክርስቲያኖች ይኽ አግባብ አይደለም ብለው በእዚኽ የአምልኮ ልማድ ለመሳተፍ ፈቃደኛ በአለመሆናቸው ነው  ።

 

ክርስትናም በተራው ፤ እንደ ኒሮ ባሉ የሮማ ነገሥታት ከደረሰበት እንዲኽ ዓይነት አስከፊ ስደት እና በሕዝብ ዘንድ እጅግ የተናቀ ፣ የተጠላ እና ለማንኛውም ችግር ተጠያቂ ከኾነበት ኹኔታ ወጥቶ ፤ በአርሜኒያዊ ንጉሥ ቲርዴት በኋላም በኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ኢዛና እና የሮማው ቄሳር ቆስጠንጢን አማካኝነት የነገሥታት ኃይማኖት በእዛኽም ፤ የሐገራቱ ሕዝባዊ እና መንግሥታዊ ኃይማኖት በመኾን   ሲከበር ፤ ከጥቂት ግዜ በኋላ ፤ በክርስቲያኖች መካከል የተፈጠሩ ክርክሮች ጦር አማዘው ደም ያፋሰሱበት ፣ የሌሎች ኃይማኖት ተከታዮችን መስቀል ወይንም ሰይፍ (ክርስትና ወይንም ሞት) የእሚያስመርጥ ፣ ለኃይማኖታዊ ክብር ብዙ ጦርነቶች የተካኼዱበት ኃይማኖት ኾነ ።

 

እነ እዚኽ ሦሥት የአርመን ፣ የሮም እና የኢትዮጵያ ነገሥታት ፤ በእዛኽን ወቅት  (እ.አ.አ. ከ301 እስከ 350 ዓ.ም.)  አብዛኛው ይታወቅ የነበረው እና ተጽኖ ፈጣሪው ዓለም ነገሥታት በመኾናቸው ፤ ክርስትና የዓለም ኃይማኖት ኾነ ማለት ይቻላል ።

 

ሆኖም ፤ ክርስትና በእዚኽ መልኩ የኃይማኖቱን ዓለም ማማ ከተቆጣጠረ በኋላ ፤ በመጀመሪያ በራሱ የእምነት በረት ውስጥ ፤ የእሚነሱ የቀኖና ልዩነቶችን ለማስታረቅ ወይንም የመከፋፈል አደጋን ለመከላከል የኼደባቸው መንገዶች መፍትሔ ሳያመጡለት በመቅረታቸው ፤ በግዜ ኺደት ተሳዳጅ የነበረው እና የፍቅር ወንጌል የእሚሰብከው ክርስትና እምነት ተከታዮች ፥ ከእሚወቅሱዋቸው ጣዖት አምላኪያን ያልተናነሰ ጭቆና እና የመብት ረገጣ ፤ ከእነርሱ የተቃረነ ቀኖና በእሚሰብኩ ክርስቲያኖች ላይ እንደ አደረሱ እና በግዜ ኺደትም የሌሎች እምነት ተከታዮች ላይ ተመሳሳይ በደል እንደ ፈጸሙ ፤ የክርስትና እምነት ስርጭት እና እድገት ታሪክ ስንቃኝ እናስተውላለን ።

 

ክርስትና በኢየሩሳሌም ከጀመረ በኋላ ፤ በአይሁድ እምነት ሽማግሌዎች ከኢየሩሳሌም እንዲወጣ ስደት ስለ መጣበት ፤ ለመጀመሪያ ግዜ ከእሥራኤል ውጭ የዓለም ስርጭቱ ማዕከል የአደረጋት ከተማ ፤ አንጾኪያ የእምትባል በዛሬዋ ቱርክ ውስጥ የእምትገኘን ከተማን ነው ።

 

ከአንጾኪያ በኋላ ፤ በወቅቱ የዓለም ታላላቅ ከተማዎች በነበሩት እና የታላቋ ሮም ግዛት ውስጥ በእሚገኙት ሮም እና አሌክሳንደሪያ እንደ አንጾክያው ዓይነት ትልልቅ መዓከላት ተፈጠሩ ።

 

ከእዚያኽም ፤ የሮማው ንጉሥ ቆንስጠንጢን ክርስቲያን ሲሆን ፤ ዛሬ የቱርክ ዋና ከተማ የሆነችውን እና በኋላ ኢስታንቡል የተባለችውን እና በቀደም ግን ቆንስጠንጢን በስሙ ኮንስታንቲኖፖል ያላትን ከተማ ፤ የክርስትና ሌላው መዓከል በማድረጉ ፤ ኮንስታንቲኖፖል አራተኛ የክርስትና መዓከል ሆነች ።

 

እነ እዚኽ ከኢየሩሳሌም ውጭ የእሚገኙ አራት የክርስትና መዓከላት ፤ ማለትም ፦ አንጾኪያ ፣ ሮም ፣ አሌክሳንደሪያ እና በኋላም ኮንስታንቲኖፖል ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ አራት ትላልቅ የክርስትና መዓከላት ሆኑ ።

 

እነ እዚኽ አራት ዓለም ዓቀፍ የክርስትና መዓከላት ግን ፤ ጅማሮዋቸው ላይ በስመ ክርስቲያን ፤በቀኖና አንድ ነን ብለው ስለ እሚያምኑ ፤ በተለያዩ ኃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ፤ በሮማው ኢምፐረር አስተባባሪነት እየተሰበሰቡ የእሚወስኑበት አንድ የጋራ ኃይማኖታዊ ጉባኤ አቋቋሙ ።

 

በኋላ በኢትዮጲያ ታሪክ ላይ እንደ እምናየውም ፤ የኢትዮጲያ ዖርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም ፤ መሥራቿ አባ ሰላማ ፤ በአሌክሳንደሪያው ጳጳስ አትናስያስ የጵጵስና ዘመን ፤ ቤተክርስቲያኗን በአሌክሳንደሪያ መንበር ስር እንድትሆን ስለ አደረገ ፤ በኋላ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ኢትዮጲያ ፤ ከአሌክሳንደሪያው መንበር ስር ከመ፟ያዝ በይፋ እስክትወጣ ድረስ ፤ ከ1,500 ዓመታ በላይ በእዚኽ ፤ የመጀመሪያዎቹ የዓለም አራት የክርስትና መንበራት አንዱ በነበረው በአሌክሳንደሪያው መንበር ስር ነበረች ።

 

እንግዲኽ እነ እዚኽ አራት የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ የክርስትና መዓከላት እየተገናኙ እንዲወያዩ ያስገደዳቸው ፤ አይቀሬ የሆነው ኃይማኖታዊ ልዩነት በመሐከላቸው እየተፈጠረ አብረው በአንድነት መቆሙን የእማይቻል እየ አደረገባቸው ስለመጣ ነው ።

 

በእዚኽ ረገድ ፤ የመጀመሪያውን ዓለም ዓቀፋዊ የክርስቲያኖች ጉባኤ ለማስጠራት ግድ የአለው በእኛ ሐገር አርዮስ የእሚባለው እና በላቲን ኤርየስ (Arius) የእሚባለው ጳጳስ ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጥረት እንጂ ፈጣሪ አይደለም ብሎ በማስተማሩ ነው ።

 

ዓለም ዓቀፋዊው የክርስቲያኖች ጉባኤ እ.አ.አ. በ325 ዓ.ም. በጉዳዪ ላይ መክሮ አርዮስን በማውገዝ ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እንጂ ፍጥረት አይደለም ብሎ በመወሰን ቢጠናቀቅም ፤ ጉባኤው በድምጽ ብልጫ ኑፋቄ ብሎ ያወገዘው የአርዮስ አስተምህሮ ፤ ተገንጥሎ ወጥቶ የራሱ አዲስ አንጃ ከመመሠረት አላገደውም።

 

ከእዚያኽ በተጨማሪም ይኽ ጉባኤ ፤ በክርስትናው በረት ውስጥ የእሚነሱ ልዩነቶች ኹሉ መደምደሚያ አልነበረም ። ከእዚያኽ በኋላ ፤ መሰል ብዙ ጥያቄዎች እየተነሱ ፤ ይኽ ዓለም ዓቀፋዊ ጉባኤ ለተከታታይ በመቶዎች ለእሚቆጠሩ ዓመታት ሲሰበሰብ ነው የኖረው ፤ ምክንያቱም ፦ በእዚያው በኮንስታንቲኖፖል የተወገዘው የአርዮስ አስተምህሮ ትክክለኛ ቀኖና ነው ተብሎ እርሱን የተቃወሙት እንደ አሌክሳንደሪያው አትናሲያስ ያሉት የኃይማኖት አባቶች ለብዙ ስደት ተዳርገዋል።

 

እነ እዚኽ ዓለም ዓቀፋዊ የክርስትና መዓከላት ግን ፤ በኃይማኖታዊ ቀኖና ብቻ አይደለም የመለያየት አደጋ እየገጠማቸው የመጣው ይልቁንም ከግዜ በኋላ ፤ የትኛው ከተማ የኹሉም ዋና መዓከል መሆን አለበት በእሚለው ሳይስማሙ ቀርተው ፤ በተለይ ሮም እና ኮንስታንቲኖፖል በአላንጣ እስከ እሚሆኑበት ደረጃ ድረስ መጡ ።

 

እ.አ.አ. በ 384 ዓ.ም. አከባቢ ቲዎደሲየስ በተባለው የሮም ኢምፐረር ፤ ኮንስታንቲኖፖል የዓለም ዓቀፍ ክርስትና መዓከል መሆን አለባት ሲባል ፤ በዓመቱ የሮም ሲኖዶስ ተሰብስቦ ይኽንን የኢምፐረሩ ውሳኔ በእዚኽ መልኩ ተቃወመ ፦

 

“የሮም ቅድስት ቤተክርስቲያን ፤ ከሌሎች የዓለም ቤተክርስቲያናት ይልቅ ቀዳሚነት ያላት መሆኑ ፤ በማንኛውም የሲኖዶስ ጉባኤ የእሚወሰን አይደለም ፤ ነገር ግን በወንጌል ውስጥ በጌታችን እና በአዳኛችን 'አንተ ጴጥሮስ ነህ ፤ በእዚኽች ዓለትም ላይ ቤተክርስቲያኔን እመሰረታለሁ' በአለው ግዜ ቀዳሚ መሆኗ የተነገረ በመሆኑ እዚኽ ጋር 'የሮማውን ቤተክርስቲያን ቀዳሚነት' በእዚኽ ስፍራ ላይ ለመጀመሪያ ግዜ ተጠቅሶ እናገኘዋለን ።”

 

 

“The Holy Roman Church takes precedence over the other churches, not on the ground of any synodal decisions, but because it was given the primacy by the words of our Lord and Redeemer in the gospel, when he said, ‘Thou art Peter, and upon this rock I will build my church.’” Thus, we have the first mention of the “primacy of the Roman Church. [8]“

 

ይኽንንም የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል የሮማው መንበር ጳጳሶች ወስደው እና በራሳቸው መንገድ ተርጉመው ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ፤ በሐዋሪያው ጴጥሮስ ተመስርታለች ተብላ የእምትታመነው የሮማዋ ቤተክርስቲያን የዓለም ቤተክርስቲያናት መዓከል እንድ ትሆን ወስኗል ብለው ፤ የኮኖስታንቲኖፖልን የዓለም ቤተክርስቲያናት መዓከልነት አንቀበልም አሉ።

 

 እንግዲኽ ፤ በእነዚኽ አራት ዓለም ዓቀፍ መንበራት የተጀመረው ፤ የድንጋጌ  እና የአስተምኽሮ ልዩነቶችን በውይይት መፍታት ሳይሳካ ቀርቶ ፤ ከእዚኽን ግዜ አንስቶ በክርስትናው ዓለም ኃይማኖታዊ ልዩነቶች እየሰፉ በመምጣታቸው ቤተክርስቲያን መከፋፈል ጀመረች ።

 

ሮም እና ኮንስታንቲኖፖል ፤ ምንም እንኳን ኹለቱም እኩል የሮም ኢምፓየር ዋና ከተሞች የነበሩበት ግዜ ቢኖርም በመኻከላቸው ፤ ግፊያው እየጠነከረ መጥቶ ፤ ሮም እንደ መንግሥት ከወደቀች በኋላ ፤ የሮማው የክርስትና መንበር ጠንክሮ ፤ በመንግሥት አልባዋ አውሮፓ ለእሚቀጥሉት 1ሺ ዓመታት ፤ የመጨረሻው ምድራዊም መንፈሳዊም ስልጣን ኾነ ።

 

በግዜ ኺደት ኃይሉ እየበረታ መጥቶ ፤ የኮንስታንቲኖፖል ባላንጣውን ጥቂት በእማይባሉ መቶ ዓመታት ትግል አሸንፎ ፤ ዓለም ዓቀፍ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የኾነው የሮም መንበር ፤ በአውሮፓ በእያንዳንዱ ግለሰብ ህይወት ውስጥ የእሚወስን ፣ ነገሥታት የእሚሾም እና የእሚሽር ፣ እንደ መስቀሉ ጦርነት ያሉ ዘመቻዎችን ማካኼድ የእሚችል ፤ ትልቅ ስልጣን ኾነ ።

 

ስለ እዚኽ በአውሮፓ ምድር ፤ የሮም መንበር መንፈሳዊውን እና ምድራዊውን ስልጣን በማዳበል ፤ መላውን መኃበራዊ እንቅስቃሴ የእሚመራ ሆኖ ፤  የሮም መንበር ያልተቀበለው ፦ ባላባት ፣ ንጉሥ ፣ መጋቢ ፣ ሰው ፣ ትዳር ፤ በአጠቃላይ ምንም ዓይነት ማሕበራዊ እንቅስቃሴ መኖር እና መካኼድ የእማይችልበት ደረጃ ላይ ደረሰ ።

 

መንበሩም ፤ በእዚኽ ገደብ የለሽ ስልጣኑ ከኃዲዎች ወይንም አሳቾች የእሚላቸውን ፤ ከመንበሩ አስተምህሮ ውጭ ያሉ መነኮሳትን ሳይቀር ፤ ክምር አጣና ላይ አስሮ እስከ ማቃጠል ፣ አመነዘሩ የተባሉ ንግሥቶችን አንገት እስከ መቅላት ድረስ የደረሰ አሰቃቂ ተግባሮች ውስጥ ገባ ።

 

እነዚኽ እና መሰል ተግባሮች ግን ከሕዝብ ግንዛቤ መጨመር ጋር ተያይዞ ፤ እንደ ጀርመናዊ ማርቲን ሉተር ያሉትን የካቶሊክ መነኮሳት ፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደሉም ብለው የእሚሉዋቸውን የሮም መንበር አሰራሮች ከመቃወም ሊያስቆም አልቻለም ።

 

ይልቁንም መንፈሳዊውም ምድራዊም ስልጣን በሆነችው የሮማ መንበር ላይ ተቃውሞው እየበረታ ፥ በእየግዜው የብዙ ሕዝብ ድጋፍ እያገኘ ፤ በእንግሊዘኛ ተቃዋሚዎቹ (The Protestants) በእኛ ሐገር በተለምዶ ጴንጤቆስጤ[4] የእሚባሉትን አዲስ የክርስትና ጎራ (Sect) እየፈጠረ መጣ ።

 

ልዩነቱም ከግዜ ወደ ግዜ እየከፋ መጥቶ ፤   በ17ኛው እና በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ፤ መነሻቸው ኃይማኖት የኾኑ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ አውሮፓን አስገባ ።

 

የአውሮፓ ሰዎች በኃይማኖታዊ እና ሌሎች ጉዳዮች ከሮም ቀኖና ጋር የእማይስማማ አስተሳሰብ ስለ ያዙ በእሚደርስባቸው ስደት ፤ ሐገራቸውን ፣ ቤተሰባቸውን ፣ ደብራቸውን ጥለው ፤ መሰደድ ጀመሩ ። ሰሜን አሜሪካን ከመሠረቱ ሰዎች ከፊሎቹ ፤ ከካቶሊክ እምነት ውጭ የኾነ የክርስትና እምነት ተከታይ በመኾናቸው ፤ የደረሰባቸው ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ስደት ሽሽት በመጡ ሰዎች የኾነውም በእዚኹ ምክንያት ነው ።

 

የሮም መንበር ራሱን በአውሮፓ ብቻ  የወሰነም አልነበረም ፤ ለምሳሌ ፦ ከግራኝ ወረራ በኋላ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እና በፖርቱጋል ካቶሊኮች መካከል የተፈጠረው እና በኢትዮጵያ ውስጥ ከአጼ ዘድንግል እስከ አጼ ሰሶንዮስ ዘመን ወደ እልቂት ያመራው ውዝግብ ፤ የጀስዊት ቄሶቹ ኢትዮጵያ ከአሌክሳንደሪያ መንበር ወጥታ ወደ ሐዋሪያው ጴጥሮስ ወደ መሰረታት ፤ ‘እውነተኛ’ ወደ ኾነችው የሮም መንበር መምጣት አለባት በማለታቸው እና ኢትዮጵያዊያን ኦርቶዶክሶች ደግሞ የአሌክሳንደሪያዋ የማርቆስ መንበር ነች እጣ ፈንታችን በማለታቸው ነበር ።

 

በእዚኽ መልኩ ክርስትና በራሱ በረት ውስጥ ራሱ ፤ ከውይይት ጀምሮ ከማውገዝ እና መነጠል ፤ በእሳት እስከ ማቃጠል ድረስ የእሚደርስ እርምጃ ቢወስድም ኃይማኖታዊ ልዩነትን እና መከፋፈልን ሊያጠፋ አልቻለም ።

 

በጣም የእሚገርመው ፤ በወቅቱ የነበሩት የሮም መንበር የክርስቲያን ኃይማኖታዊ ፅንፈኞች ፤ እነርሱ በአይኹድ ፣ ኃጢያት ሰሩ ወይንም ከትክክለኛው የካቶሊክ አስተምህሮ አፈነገጡ በእሚሉዋቸው ካቶሊኮች ፣ አዲስ በመጡት የተለያዩ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ላይ ብዙ ስደት ሲያደርሱ ፤ እነርሱ ወንጌል ለመስበክ ወደ ጃፓን የለአኩዋቸው ሚሽነሪዎች በተመሳሳይ በጃፓን ባህላዊ እምነት ተከታዮች ፤  ኃይማኖታችንን አሳደፋችሁ በእሚል በወቅቱ በነበሩት የባዕድ አምልኮ ተከታይ የጃፓን ነገሥታት ለእጅግ አሰቃቂ ስቃይ ይዳረጉ ነበር ።

 

ሞንተስኪው የተባለው የፈረንሳይ ፖለቲካ ሳይንቲስት እንደ ዘገበው ፤ አንዲት የ10 ዓመት አይኹዳዊት ብላቴና ፤ በአይኹድነቷ ምክንያት በስፔናዊያን የካቶሊክ እምነት ተከታዮች በእሳት ተቃጥላ እንድትሞት ስትደረግ ፤ የአዘነ አንድ አይኹዳዊ ይኽን ብሏል ፦

 

“መርማሪዎቹን እንዲኽ አላቸው ፦ ‘የጃፓን ንጉሠ ነገሥት ክርስቲያኖችን ቀስ እያለ በእሚነድ እሳት አቃጠላቸው ፤ እየ አላችሁ ታማርራላችሁ ። እርሱ ግን እንዲኽ ብሎ ይመልሳል ፤ እናንተ የእናንተ ዓይነት እምነት የእማይከተሉት ላይ የእምታደርጉትን ነው እኛም የእኛ ዓይነት እምነት የእማይከተሉት ላይ ያደረግነው ፤ ስለ እዚኽ ማማረር ያለባችሁ በደካማነታችሁ ላይ ነው ፤ እርሱ ነውና እኛን ከማጥፋት የከለከላችሁ እና እኛ እንድ እናጠፋችሁ ያስቻለን ።

 

‘እውነታው ግን እናንተ ከእዚኽ  ንጉሠ ነገሥት በላይ ጨካኝ መኾናችሁ ሊመሰከር ይገባል ። እኛ እናንተ የእምታምኑትን የእምናምነውን ነገር ግን እናንተ የእምታምኑትን ኹሉ የእማናምነውን ለሞት ዳርጋችኹናልና ። እኛ የእምንከተለው ፤ እናንተ ራሳችኹ እግዚአብሔር ይወደው የነበረውን እንድኾነ ታውቃላችሁ ። እኛ ደግሞ እግዚአብሔር ከእዚኽ ቀደም ብቻ ሰአይኾን  ዛሬም ይወደዋል ብለን እናምናለን ፤ እናንተ ግን ከእዚኽ ቀደም እንጂ ዛሬ አይወደውም ትላላችሁ ፤ እንዲኽም ብላችሁ ስለ እምታምኑ ፤ እግዚአብሔር ከእዚኽ ቀደም ይወደው የነበረውን እምነት ዛሬም ይወደዋል ብለው ያመኑትንና በቀላሉ ይቅር ሊባሉ የእሚችሉትን ሰዎችን ፤ በሰይፍ እና በእሳት እንዲሞቱ ታደርጋላችሁ ።’

 

‘ለእኛ ጨካኝ ናችሁ ፤ ለልጆቻችን ደግሞ ከእዚኽ እጅግ የከፋ ናችሁ ፤ ምክንያቱም ፦ በአሕዛብ ሕግ እና በተፈጥሮ ሕግ የተሰጣቸውን ምሪት ተከትለው አማልክት ናቸው ብለው ያመኑትን በመከተላቸው በእሳት እንዲቃጠሉ ስለ እምታደርጉዋቸው ።’

 

‘እንዲኽ በማድረጋችሁ ፤ ኃይማኖታቸውን በመሠረቱበት መንገድ ምክንያት ፤ ከመሐመድ ተከታዮች ይልቅ የነበራችኹን ብልጫ ታጡት አላችሁ ። ይኽን ያኽል ተከታይ አለን ብለው ሲኩራሩባችሁ ፤ ይኽን ኹሉ ያገኛችኹት በሐኬተኞች ኃይል ነው ፤ ኃይማኖታችኹንም ያስፋፋችኹት በሰይፍ ነው ትላቹዋላችሁ ፤ እንደ እዛኽ ከኾነ ለምን የእናንተን በእሳት ታፀኑታላችሁ ?

 

‘ወደ እናንተ እንድ እንመጣ ግድ ስትሉን ፤ ምንጫችን ነው ብላችሁ የእምትመኩበትን እንቃወማለን ። እናንተም ፤ ምንም እንኳን ኃይማኖታችን አዲስ ቢኾንም ከመሎኮት ነው ትላላችሁ ፡ ይኽንም እንዲ ያስረዳላችሁ ፤ በቅሎ ለእዚኽ የደረሰው በአረማውያን መካከል በብዙ መከራ አልፎ ፤ በሰማዕታት ደም ነው እዚኽ የደረሰው  ትላላችሁ ፤ ዛሬ ግን ያሳድድዋችሁ እንደ ነበሩት አረማዊያን (ዶክሌሺያኖች) እኛን ዛሬ ታሳድዳላችሁ ።’

 

‘እናንተም እኛም በእምናመልከው በፀባዖት እግዚአብሔር ሰአይኾን  ፤ የእርሱን መልካም ምሳሌ እንድትከተሉ ሰው ኾኖ ስጋን ለበሰ በእምትሉት ክርስቶስ እንለምናችኋለን ፤ እርሱ በምድር ላይ ቢኖር ኖሮ እንደ እሚያየን እንድ ታዩን ። እኛን የክርስቶስ ተከታይ ኹኑ እያላችሁ እናንተ እርሱን አትከተሉም ?

 

‘ክርስቲያን መኾን በአትወዱ ግን ፤ ቢያንስ ሰው ኹኖ ተፈጥሮ በእምታድለው ስስ የፍትኽ ግንዛቤ እንደ እሚመራ እንጂ መልካም ጠባይ የእሚያስተምረው ኃይማኖት እና መገለጥ የእሚሰጠው ብርኃን እንዳለው ሳትኾኑ ፤ ተመልከቱን።

 

‘ሰማይ እውነቱን እንድታዩ ይኽንን ትልቅ ፍቅር ከአሳያችሁ ፤ ዋነኛውን ፀጋ ተቀብላችኋል ፤ እናም የአባቶቻቸውን ውርስ የተቀበሉ ልጆች ፥ በአልተቀበሉት ይጠሉ ዘንድ ይገባል ?

 

‘ይኽን እውነት ከተቀበላችሁ ፤ በአነጋገራችሁ ከእኛ አትሰውሩት ። ንያቱም እንደ ዚኽ ይነቱ እውነት በልብ እና በአዕምሮ ላይ መንገሥ እንጂ ዛሬ እናንተ እንደ ምታደርጉት በግርፊያ ብዛት ራሱን በሰዎች ላይ ለመጫን የሚፈልግ ደካማ አይደለም

 

‘ጠቢብ ብትኾኑ ኖሮ ፤ እናንተን ለማታለል አለመፈለግ እንጂ ሌላ ምንም ጥፋት የሌለብንን ሰዎች ለሞት አትዳርጉንም ነበር ። ክርስቶሳችሁ የእግዚአብሔር ልጅ ከኾነ ፤ ሚስጥረ ኃይማኖቱን ለማርከስ በአለመፍቀዳችን ይሸልመናል ብለን ተስፋ አለን ፤ እኛም እናንተም የእምናገለግለው እግዚአብሔር ደግሞ ፤ ከእዚኽ በፊት ራሱ የሰጠውን ኃይማኖት ዛሬም አልተወውም ብለን በማመናችን ለሞት ስለተዳረግን እንደ እማይቀጣን እናምናለን ።

 

‘እናንተ የተፈጥሮ ብርኃን ከመቼውም ግዜ በላይ ፍንትው ብሎ በበራበት ዘመን ትኖራላችሁ ፤ ፍልስፍና የሰውን ማስተዋል በአበራበት ፣ የወንጌላችሁ ስነምግባራዊነት ይበልጥ ተቀባይነት በአገኘበት ፣ የሰዎች ልጆች የየግል መብት ከበአለንጀሮቻቸው አኳያ የአለው ስልጣን ይበልጥ በተብራሩበት ዘመን ትኖራላችሁ ። ስለ እዚኽ ፦ እናንተ የቀደመው ዝበታችሁ ሳይታወቅ ከስሜታችሁ የእሚቀላቀለውን ነገር ማራገፍ ከአልቻላችሁ ፤ ትምህርት በጀ የእማይላችሁ ፣ የትኛውም የብርኃን እና የመመሪያ መጠን የእማይደርሳቸው መኾናችሁ መመ፟ስከር አለበት ፤ ለእንደ እዚኽ ዓይነቶቹ ሰዎች ስልጣን የእምትሰጥም ሐገር እጅግ አሳዛኝ መኾን አለባት ።

 

‘ኃሳባችንን በግልፅነት እንድ እንነግራችሁ ትፈልጋላችሁ ? እናንተ ፥ እንደ ኃይማኖታችሁ ጠላት አድርጋችሁ ሰአይኾን  የእምትወስዱን እንደ እናንተ ጠላት አድርጋችሁ ነው የእምትወስዱን ፤ ባይኾን ኖሮ ኃይማኖታችሁ በእዚኽ ዓይነት መሐይምነት እንዲዝግ አትፈቅዱም ነበር ።

 

‘በአንድ ነገር እንድ እናስጠንቅቃችሁ ግድ ነው ፤ ወደ ፊት በእሚመጣው ዘመን ፤ እኛ በኖርንበት ወቅት በአውሮፓ የእሚኖሩ ሰዎች ስልጡኖች ነበሩ ከተባለ ፤ እናንተ እንደ አረማውያን በአፍራሽ ማስረጃነት ትቀርባላችሁ ፤ ስለ እናንተም የእሚኖራቸው ግንዛቤ ዘመናችኹን እንደ አዋረዳችሁ እና በአጋሮቻችሁ ላይ ጥላቻ እንደ አስፋፋችሁ የእሚናገር ይሆናል ።’”

 

“You complain,” says he to the Inquisitors, “that the Emperor of Japan caused all the Christians in his dominions to be burned by a slow fire. But he will answer, we treat you who do not believe like us, as you yourselves treat those who do not believe like you; you can only complain of your weakness, which has hindered you from exterminating us, and which has enabled us to exterminate you.

 

“But it must be confessed that you are much more cruel than this emperor.You put us to death who believe only what you believe, because we do not believe all that you believe. We follow a religion which you yourselves know to have been formerly dear to God. We think that God loves it still, and you think that he loves it no more: and because you judge thus, you make those suffer by sword and fire who hold an error so pardonable as to believe that God still loves what he once loved.21

 

“If you are cruel to us, you are much more so to our children; you cause them to be burned because they follow the inspirations given them by those whom the law of nature and the laws of all nations teach them to regard as gods.

 

“You deprive yourselves of the advantage you have over the Mahometans, with respect to the manner in which their religion was established. When they boast of the number of their believers, you tell them that they have obtained them by violence, and that they have extended their religion by the sword; why then do you establish yours by fire?

 

“When you would bring us over to you, we object to a source from which you glory to have descended. You reply to us, that though your religion is new, it is divine; and you prove it from its growing amidst the persecutions of Pagans, and when watered by the blood of your martyrs; but at present you play the part of the Diocletians, and make us take yours.

 

“We conjure you, not by the mighty God whom both you and we serve, but by that Christ, who, you tell us, took upon him a human form, to propose himself as an example for you to follow; we conjure you to behave to us as he himself would behave were he upon earth. You would have us become Christians, and you will not be so yourselves.

 

“But if you will not be Christians, be at least men; treat us as you would, if having only the weak light of justice which nature bestows, you had not a religion to conduct, and a revelation to enlighten you.

 

“If heaven has had so great a love for you as to make you see the truth, you have received a singular favour; but is it for children who have received the inheritance of their father, to hate those who have not?

 

“If you have this truth, hide it not from us by the manner in which you propose it. The characteristic of truth is its triumph over hearts and minds, and not that impotency which you confess when you would force us to receive it by tortures.

 

“If you were wise, you would not put us to death for no other reason than because we are unwilling to deceive you. If your Christ is the son of God, we hope he will reward us for being so unwilling to profane his mysteries; and we believe that the God whom both you and we serve will not punish us for having suffered death for a religion which he formerly gave us, only because we believe that he still continues to give it.

 

“You live in an age in which the light of nature shines more brightly than it has ever done; in which philosophy has enlightened human understanding; in which the morality of your gospel has been better known; in which the respective rights of mankind with regard to each other and the empire which one conscience has over another are best understood. If you do not therefore shake off your ancient prejudices, which, whilst unregarded, mingle with your passions, it must be confessed that you are incorrigible, incapable of any degree of light or instruction; and a nation must be very unhappy that gives authority to such men.

 

“Would you have us frankly tell you our thoughts? You consider us rather as your enemies than as the enemies of your religion; for if you loved your religion you would not suffer it to be corrupted by such gross ignorance.

 

“It is necessary that we should warn you of one thing; that is, if any one in times to come shall dare to assert that in the age in which we live, the people of Europe were civilised, you will be cited to prove that they were barbarians; and the idea they will have of you will be such as will dishonour your age and spread hatred over all your contemporaries. [9]“

 

ይኽ ዓይነቱ የወቅቱ የሮማ ካቶሊክ ፅንፈኝነት ፤ ምንም እንኳን ከ15ኛው እስከ 18ኛው ክፍለ ዘመን አውሮፓ በአብዛኛው የክርስቲያን አህጉር ብትኾንም ፤ ከሮም መንበር ቀኖና ውጭ ያሉ የክርስትና አስተምህሮቶች ፤ ያለ ምንም ርኅራኼ እና ማመንታት የእሚደረገውን የሮምን መንበር ጥቃት ሽሽት ስለ እሚሰደዱ ፤ ይኽ የኃይማኖት ግጭት የአውሮፓ ሰቆቃ ዋነኛ ምንጭ ኾኖ ነበር ።

 

ከእላይ እንደ አልነው ይኽ ግን የሮማው ካቶሊክ ችግር ብቻ አልነበረም ፤ ክርስትና በኢትዮጵያም ውስጥ የራሱ መሰል ታሪኮች አሉት ። የሰርጌው ሐብለሥላሴ ታሪክ እንደ እሚነግረን ፤ የንጉሥ ካሌብ ጦር አዛዥ አብረኃ ፤ በአረቢያዋ መካ ፤ ካባ የእሚባለው ቦታ ላይ የነበረውን የጣዖት አምልኮ አስቀርቶ ቤተክርስቲያ ሊያቋቁም እንደነበረ እና በእዚኽም ኺደት ፤ ኹኔታው ከነብዩ መሐመድ አያት ጋር ግጭት ውስጥ እንደ አስገባው ይነግረናል[5] ። 

 

በእዚኽ መጽሐፍ ምዕራፍ ሦሥት ላይ በዝርዝ እንደ እምናየውም ፤ የአክሱሙ ስርወ መንግሥት መዓከሉን ከአክሱም ወደ ሸዋ ከአዛወረ በኋላም ፤ ኃይማኖታዊ ግጭት ፤ የፖለቲካው ታሪኩ ዋነኛ አካል ነበር ።

 

በእዚኽ መሰሉ ኃይማኖታዊ ሰጣ ገባ እየጋመ የመጣው የኢትዮጵያ ክርስቲያናዊ መንግሥት እና የአረቦች ግንኙነት ፤ ከነብዩ መሐመድ መምጣት በኋላ ፤  የንጉሥ ካሌብ ጀነራል አብረኃ ፤ ሊያፈርሰው አቅዶ ጦር ያዘመተበት የካባ አምላኪዎች ፤ እንደ አብረኃ ኹሉ በእዚኽ በካባ የእምታደርጉት አምልኮ ልክ አይደለም ብለው የተቃወሙትን ነብዩ መሐመድን እና ተከታዮቻቸውን ፤ በመቃወማቸው ምክንያት ከገዛ ከተማቸው እንዲሰደዱ አድርጎ ፤ በኢትዮጵያ ንጉሥ ስር እንዲጠለሉ አደረጋቸው ።

 

በእዚኽ አግባብ በስደት የጀመረው እስልምና ፤ ኃይሉ ሲደረጅ ፤ ጅማሮው ላይ ያሳደዱትን የመካን ጠባቂ ቁሬሾችን ከማሳደድ ጀምሮ ፤ የበላይነቱን በኃይል የእሚያስረግጥ ብቻ ሰአይኾን ፤ ጣዖት አምላኪዎችን እና ሳቱ የእሚላቸውን ሙስሊሞች ፤ ማጥፋት ተገቢ የኾነ ኃይማኖታዊ ትዕዛዝ የአደረገ ኃይማኖት ነው የኾነው ።

 

ይኽ በዓለማችን ፤ በተከታይ ብዛት ከክርስትና ቀጥሎ ትልቁ ኃይማኖት ፥ እስልምና ፤ ከውልደቱ አንስቶ እስከ አኹን በሰልፍ እና በጦርነት የእሚኖር ኃይማኖት ሆኗል ። ምንም እንኳን እስልምና የሰላም ኃይማኖት እንደኾነ ብዙ ቢነገረንም ፤ በእስልምና ስም በእዚኽ ዘመን የእሚሰሩ ብዙ ወንጀሎች እንደ አሉ ኾነው የዓለም ኃይማኖቶችን ያጠኑ እንደ ፕሮፌሰር ፈርጉሰን ያሉ ሰዎች  ፤ እስልምና ሌሎች ኃይማኖት ተከታዮች ላይ የአለውን አቋም ፤ እንደ እዚኽ ያስቀምጡታል ፦

 

 እስልምና ከእውነተኛው የእስልምና ውጭ ናቸው የእሚላቸው ሦሥት ኃይማኖታዊ ጎራዎች አሉት እነርሱም ፦ የሳቱ ሙስሊሞች ፣ በመጽሐፉ የእሚያምኑ (ክርስቲያን እና አይኹድ) እና አረማውያን ወይንም ጣዖት አምላኪያን ። ይኽንም ተከትሎ ፤ እስልምና ፥ የሙስሊም መንግሥት ፤ በእነዚኽ በሳቱ ሙስሊሞች እና ከእስልምና ውጭ ባሉ ሦሥት የእምነት ጎራዎች ውስጥ ያሉ ሰዎች ላይ የእሚከተሉትን አቋሞች መያዝ አለበት ይላል [10]  ፦

 
  • ሙስሊም ኾነው ፤ የስሕተት ትምህርት የተቀበሉ ወይንም መከፋፈል ያመጡ ሙስሊሞችን ፤ ለማጥፋት ጅኃድ ማወጅ አለበት።
  • የመጽሐፉ አማኝ የኾኑ (አይኹድ እና ክርስቲያኖች) ፤ ለሐገሪቱ ኢማም ስልጣን መገዛት አልፈልግም ከአሉ ፤ እነርሱን በጅኃድ ማጥፋት አለበት።
  • ጣዖት አምላኪዎችን በሙሉ በጅኃድ እስላም ማድረግ ወይንም ማጥፋት አለበት።
  • የእሚያስፈራ የጦር ሠራዊት በመገንባት በዙሪያው ያሉ ሙስሊም ያልኾኑ ሐገሮችን ማስፈራራት አለበት።
 

ከእነዚኽ ፥ የእስልምና አስተምህሮዎች እንደ እምንረዳው ፤ እስልምና ከመንፈሳዊ አስተምህሮው በተጓዳኝ ፤ ኃይማኖታዊ መሠረት የአለው ፍፁማዊ አምባገነን የኾነ የፖለቲካዊ መዋቅር የሚደነግግ በመኾኑ ፥ የእስልምና እምነት የበላይነት በአለበት ሕዝብ እና ሐገር ፤ የሰዎች ተፈጥሮዋዊ የማሰብ እና የመምረጥ መብት ፥ በኃይማኖታዊ ቀኖና ብቻ ሰአይኾን  በፖለቲካዊ አወቃቀር የእሚጨፈልቅ ፀረ ሕዝባዊነት በስሪቱ ውስጥ የያዘ የፖለቲካ ኃይል ነው ።

 

አንዳንድ ሰዎች ፤ ከዘመናዊ አስተሳሰብ ጋር ለማስታረቅ ወይንም ነገር ለአለማካረር በእሚል ሰበብ ፤ የመጽሐፉ አማኞች በኃይማኖታቸው ምክንያት የእሚጣልባቸውን ለየት የአለ ግብር ከከፈሉ እና ለኢማሙ ከተገዙ እንዲኖሩ ይፈቅዳል እና እስልምና ፀረ ክርስትና ወይንም ፀረ አይኹድ አይደለም ቢሉም ፤ የእስልምና ፖለቲካዊ ደርዝ ፤ ራሱን ከኃይማኖታዊ ቀኖናነት አሳልፎ ፥ በዜጎች መካከል ሰብዓዊ እኩልነትን የእማያከበር ፣ ጣዖት አምላኪያንን በህይወት የመኖር መብት የእሚገፍፍ እና በእዚኽም ፤ የሕዝብን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት የእሚከለክል ፖለቲካዊ አስተሳሰብ የያዘ ስለ መኾኑ ከላይ ካለው አቋም መረዳት ይቻላል ።

 

ከእዚኽ ተነስተን እንደ እምናየው ፤ ኃይማኖታዊ ቀንዓናዊነት (Zealotism) ወይንም በዘመናዊ አነጋገር (Modern Vernacular) ኃይማኖታዊ ፅንፈኝነት (Religious Extremism or fanaticism) እድሜ ጠገብ ማሕበራዊ ችግር እንደ ኾነ እና በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በኹሉም የኃይማኖት እምነት ተከታዮች ዘንድ የእሚስተዋል  እንደ ኾነም ነው ። ምንም እንኳን አንዳንድ ግዜ ከተከታዮቹ ዝበት በሌላ ግዜ ደግሞ ከኃይማኖቱ መሠረታዊ ዝበት የእሚመነጭ ቢኾንም ።

 

ከላይ ከተቀመጡት ዓለም ዓቀፍ እና ዙሪያ መለስ ታሪካዊ ልምምዶች ተነስተን ፤ ስለ ኃይማኖታዊ ፅንፈኝነት የእሚከተሉትን ኹለት ዋና ዋና ነገሮች ማለት እንችላለን ፦

 

የመጀመሪያው ፦ ኃይማኖታዊ ፅንፈኞች ፤ ለፅንፈኝነታቸው የእሚያቀርቡዋቸው ምክንያቶች በአዕምሮ ፍርድ እና በታሪክ አስረጂነት ውድቅ የሆኑ መሆናቸውን ነው ።

 

ኃይማኖታዊ ፅንፈኞች ለኃይማኖታዊ ፅንፈኝነታቸው ከእሚያቀርቡት ምክንያት አንዱ ፤ የእነርሱ ኃይማኖት ቀደምት እና ብቸኛው የእውነት መንገድ ሲሆን ከእነርሱ ውጭ ያሉት ኃይማኖቶች ደግሞ ግዜ አመጣሽ እና የተሸቃቀጡ መሆናቸውን ነው።

 

ስለ እዚኽ ፦ በእነርሱ ምናብ ቀደምት እና እውነተኛውን ኃይማኖት በማንኛውም መንገድ መጠበቅም ሆነ ማስፋፋት ለብቸኛዋ እምነት መቆም ወይንም መወገን ስለ ሆነ ትክክል ነው ወይንም ሰዎች በግዜ አመጣሹ እና በተሸቃቀጡት ኃይማኖቶች እንደ አይበከሉ የእዚኽን ግዜ አመጣሽ እና ሽቃጭ ኃይማኖት ተከታዮች መግደል ፤ ሰዎቹን እንደ መርዳት ወይንም ከስህተት እንደ መታደግ በመሆኑ ለቋሚውም ለሙዋቹም ውለታ በመዋል ሰውን የመውደድ መገለጫ ነው።  

 

እውነታው ግን ምንም እንኳን በኃይማኖቶች መካከል በእድሜ መቀዳደም ሊኖር ቢችልም ፤ በተለይ ከባለፈው 2 ሺ ዓመት ወዲኽ ፤ ኃይማኖት ኹሉ ግዜ አመጣሽ ከመሆኑ አንጻር ስንመለከተው ፤ ይኽን መሰሉን አመለካከት ምክንያት በማድረግ በኃይማኖት ስም በሰዎች ላይ ወንጀል መፈጸም ፤ ቀደምት እና እውነተኛውን ኃይማኖት ከመያዝ ጋር ሰአይሆን ፤ በቀደምት እና እውነተኛ እምነት ስም የእሚመጣ ኃይማኖታዊ ፅንፈኝነት ወይንም ስነ ምግባረ ቢስነት ጋር የእሚያያዝ ነው።

 

ይኽም ብቻ ሰአይሆን ፤ ቀደምትነት የትክክለኛነት ወይንም የእውነተኝነት ማሕተም አይደለም። በዓለም ሕዝብ ታሪክ ፤ ትናንት የጠሉትን ፣ የተቃወሙትን ፣ ተከታዮቹን የአሳድዱበትን እና የገደሉበትን ኃይማኖት ተቀብለው ራሳቸው ቀድሞ ለአሳደዱት ኃይማኖት ብዙ ዋጋ የከፈሉ ሰዎች ብዛት ቀላል አይደለም ።

 

ለማሳያነት ፤ አውሮፓ ወደ ክርስትና ሳትመጣ በፊት ፤ ፍራንክ የእሚባሉት የአውሮፓ ሕዝብ የጦር አበጋዝ የነበረ ኮልቪስ የእሚባል እና ክርስትናን ያሳድድ የነበረ ሰው ወደ ክርስትና ለመምጣት ጥምቀት ሊወስድ ሲል ፤ አጥማቂው ቄስ እንዲኽ እንደ አለው በታሪክ ተጽፏል ፦

 

“አንገትህን ዝቅ አድርግ ።  እስከ አኹን ያቃጠልኸውን አምልክ ፤ ስታመልክ የነበረውን ደግሞ አቃጥል ።”

 

“Bend your neck. Worship what you burned and burn what you worship. [8]“

 

ስለ እዚኽ ፦ ቀደምት እና ብቸኛው እውነተኛ ኃይማኖት ሊኖር ቢችልም እንኳን ፤ እንዲኹም እኔ አኹን የያዝኹት ኃይማኖት ብቸኛው እውነተኛው እና ቀደምቱ ኃይማኖት ነው ብሎ ማመን በራሱ ችግር በአይኖርበትም ፤ ቀደምት እና እውነተኛውን ኃይማኖት ለማስጠበቅ ወይንም ሰዎችን ከስህተት ለማዳን ፥ግዜ አመጣሽ የተባለውን ኃይማኖት ተከታዮች ማሳደድ መፈለግ በምንም መልኩ ቢቀመጥ እውነተኛውን እና ቀዳሚውን እምነት ከመያዝ ጋር ማያያዝ አሳማኝ አይደለም።  

 

እንደ ገናም ኃይማኖታዊ ፅንፈኞቹ ፤ ለፅንፈኝነታቸው ምክንያት ፤ አኹን የደረስንበትን ስልጣኔ ተወቃሽ በማድረግ ፤ የሳይንስ እውቀት መጎልበት እና የቴክኖሎጂ መራቀቅ ፤ እንደ ዴሞክራሲያው የመንግሥት አስተዳደር ያሉ ዘመናዊ የስነ መንግሥት መርህዎች ፣ ዘመናዊ የመረጃ መለዋወጫ ቴክኖሎጂዎች (ቴሌቭዥን ፣ ኢንትርኔት ፣ ፊልም ፣ ወዘተ) ፣ ወዘተ ፤ ቀዳሚውን እና እውነተኛውን እምነታችንን አጠፋ ቢሉ ፤ ኃይማኖታዊ ፅንፈኝነት ከጥንትም የነበረ ፣ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ እድገት የአልተወሰነ እና አንዳንዴ እንዲያውም በኃይማኖታዊ ጽንፈኞቹ የተወገዘው ቴክኖሎጂ ውሎ አድሮ የኃይማኖቱ አጋዥ መሳሪያ ሆኖ የታየበት የታሪክ አጋጣሚ ቀላል በአለመሆኑ ይኽም ምክንያታቸው መሠረተ ቢስ ነው ።

 

ሩቅ ሳንኼድ ፤ የዘመናዊ ሕትመት በእነ ጉተንበርግ መጀመሩ ፤ መጽሐፍ ቅዱስ በቀላሉ እየታተመ ለምዕመናን እንዲ ዳረስ በማድረግ ፤ ምዕመናን መጽሐፍ ቅዱሱን በግል በማንበብ በግላቸው እየተረጎሙ ለስህተት እንዲዳረጉ ያደርጋል በእሚል ፤ ከቤተክርስቲያን ብዙ ግፊያ ሲደርስበት እንደነበር በብዙ ይታወቃል ። የአኹኑ ዘመን ክርስትና ደግሞ ፤ መጽሐፍ ቅዱስን በዓለም ላይ በእሚነገሩት ቋንቋዎች ኹሉ ተርጉሞ ፤ በዘመናዊው የሕትመት መሳሪያ ብዙ መጽሐፍ አትሞ ለማድረስ ብዙ ይደክማል ።

 

ይኽም የክርስትና ታሪክ ፤ ሳይንሳዊ እውቀት እና ቴክኖሎጂ ወይንም በጠቅላላው ዘመናዊነት ፤ አሳማኝ በአልሆነ መልኩ ፤ በኃይማኖታዊ ጽንፈኞች የስህተት ማስቻያ መንገዶች ተብለው ሲነቀፉ እንደነበሩ ማሳያ ነው ።

 

ከእዚኽ በተጨማሪም ፤ እነ ሶቅራጠስ ሐሰተኛ ኃይማኖት አመጡ ተብለው በሞት የተቀጡት ፣ ኔሮ ክርስቲያኖችን ከእነ ሕይወታቸው በእሳት ያቃጠለው ፣ ክርስትና ምዕራብ እና ምሥራቅ በእሚል የተከፈለው ወይንም እስልምና ከመካ የተሰደደው ሳይንስ በተንሰራፋበት እና ቴክኖሎጂ በረቀቀበት ዘመን አይደለም ።

 

ይኽም ማለት ፤ ኃይማኖታዊ ፅንፈኞች ዘመናዊነትን ወይንም ተራማጅነትን እንደ ኃይማኖታዊ ውድቀት ምንጭ አድርገው መመልከታቸው እና መተቸታቸው ፤ እውነተኛ የችግሩ ምንጭ የኾነውን የእነርሱን ጠባብነት ፣ ጨለምተኝነት ፣ ምንደኝነት መሸፈኛ እንጂ እነዚኽ መሻሻሎች በራሳቸው የኃይማኖት ልዩነት እና የስህተት ኃይማኖት መፍለቂያ ምንጭ መኾናቸውን አያሳይም ።

 

ይኽም በመሆኑ ኃይማኖታዊ ፅንፈኝነት ፤ ኃይማኖታዊ ፅንፈኞቹ ሊሉ እንደ እሚፈልጉት ብቸኛ እና ቀዳሚ የሆነውን የአምላክ እምነት ለማስጠበቅ እና ለማስቀጠል ከአላቸው ቀናዒነት ወይንም ሰዎች ለስህተት እንደ አይጋለጡ ለሰዎች ከአላቸው አሳቢነት ወይንም ሰው ወዳድነት የእሚመንጭ ሰአይሆን ይልቁንም ፤ ኃይማኖታዊ ፅንፈኝነት የአንዱ ኃይማኖት ተከታዮች ፦ ስጋት ፣ ዕብሪት ፣ ምንደኝነት የእሚመነጭ መሆኑን ነው የእሚያሳየን  ።

 

ብዙ ግዜ ፅንፈኛ ኃይማኖተኞች አዲስ አስተሳሰብ ወይንም አደራረግ የእሚፈሩበት ምክንያት ፤ የስህተት ትምህርት መጥቶ ከእውነቱ እና ከትክክለኛው መንገድ በላይ ተቀባይ በመኾን ፤ ስነ ምግባር ያበላሻል ፣ ሐገር ያፈርሳል ፣ ዓምላክን ያስክዳል ፣ ወዘተ ፤ ከእሚል ፍራቻ ስለ እዚኽም ጠባብነት ወይንም ጨለምተኝነት ነው ። ገፋ ከአለም እና ከእዚኽ ዓይነት ምናባዊ ስህተት ፍራቻ ከአለፈም ፤ ቤተ መቅደሳችን ይወሰዱብናል ፣ ተሰሚነታችን ይቀንሳል ፣ ደሞዛችን ይቀንሳል ፣ ወዘተ ፤ ከእሚል ዕብሪት እና ምንደኝነት ነው ።

 

እነ እዚኽ የመበከል ወይንም ጥቅምን የማጣት ፍራቻዎች ደግሞ በግዜ ኺደት ራሳቸውን ለእውነተኛው እና ብቸኛው ኃማኖት መጋደል ክብር ነው ብሎ ወደ ማስተማር እና መንቀሳቀስ ይመጣሉ ።

 

 መግቢያ ላይ እንደ አልነው ፤ ልክ በፖለቲካው መስክ ፅንፈኞች ራሳቸውን አርበኛ አድርገው ለማቅረብ እንደ እሚፈልጉት ፤ በኃይማኖታዊ ሰመዓትነት ስም ኃይማኖታዊ ፅንፈኛ በመኾን ፤ ሰዎች የወደዱትን ኃይማኖታዊ አስተሳሰብ እንዲ ይዙ እና እንዲ ያራምዱ መፍቀድ ፤ አደርባይነት ፣ ለሆድ ማደር ፣ ምድራዊ መኾን ፣ ወዘተ ነው ፤ በእሚል እሳቤ ፤ ኃይማኖትን የእሚያሳድፉ ወይንም ስህተት የእሚያስፋፉ በእሚሉዋቸው እና እነርሱ እውነትኛው እና ትክክለኛው አንዱ ኃይማኖት ከእሚሉት ውጭ የአለውን ፤ ሌላውን ኃይማኖት ወይንም ተከታይ ማሳደድ ተገቢ ነው ብለው እንዲ ሞግቱ ያደርጋቸዋል ፤ ይኽም አሳፋሪውን ኃይማኖታዊ ፅንፈኝነታቸውን በኃይማኖታዊ ሰመዓትነት ስም እንዲሸፍኑት ያደርጋቸዋል ።

 

የየትኛውም ኃይማኖት ተከታዮች ወይንም አስተማሪዎች መገንዘብ ያለባችው ግን ፤ ስህተት የእሚሉት አስተምህሮ እንዳይስፋፋ የአላቸው ብቸኛ መሳሪያ ፤ ማስተማር ፣ መምከር እና መገሰጽ ብቻ መሆኑን ነው ።

 

ከእዚኽ ውጭ በኃይል እና በአፈና ፤ ኃይማኖትን አስፋፋለሁ ፣ ኃይማኖትን ከስህተት እከላከላለሁ ወይንም አሳቾችን አሳድጄ አጠፋለሁ ብሎ ማሰብ ፤ በተለይ በእዚኽ ዘመን ፤ ራስን ወደ ኃይማኖታዊ ፅንፈነት በመቀየር ፤ የማሕበረሰብ ቀውስ እና አለመረጋጋት ምንጭ ከመሆን ውጭ በየትኛውም መልኩ ምንም መልካም ነገር ሊከውን የእማይችል መሆኑን ነው ።

 

ክርስትናን እና እስልምናን ብንወሰድ ፤ ለኃይማኖታቸው የቀኑ ሰዎች ኢየሱስን ሰቅለውታል ፤ ክርስቲያኖችን አሳደዋል፤ በተመሳሳይ ለነበራቸው ባሕላዊ ዓምልኮ የቀኑ የመካ ቁሬሾች  ነብዩ መሐመድን ከገዛ ከተማቸው አሳደዋቸዋል ።

 

ይኽ የወቅቱ የኃይማኖት ፅንፈኞች አካኼድ ግን ፤ በወቅቱ ከፈጠረው ሰብዓዊ ችግር ውጭ ፤ እነ እዚኽን ትልልቅ ኃይማኖቶች ዛሬ ከደረሱበት ደረጃ ሊገታቸው አልቻለም ። 

 

የማስገደድ አቅም የአለው ኃይማኖታዊ ቁጥጥር ፤ በኃይማኖታዊ ጥራት ስም ብዙ አሰቃቂ ወንጀል ከመፈጸም ያለፈ ምንም ፋይዳ ሲፈይድ በሰው ልጆች ታሪክ አልታየም ፤ በተለይ በእዚኽ ዘመን ።

 

 ሲጀምሩ ተሳዳጅ የነበሩት ፤ በዓለም ላይ ትልልቅ የእሚባሉት ኃይማኖቶች ፤ ክርስትና እና እስልምና ፤ በኃይማኖታዊ ቀንዓናዊነት ፤ ሰዎችን በእሳት አቃጥለዋል ፣ በሰይፍ ገድለዋል ፣ ገልብጠው ገርፈዋል ፣ ወዘተ ፤ ከእዚኽም የተነሳ ሐገር ተበጥብጧል ፥ የብዙ ሰዎች ህይወት እና ኃብት ያወደሙ ብዙ ጦርነቶች ተካኺደዋል ፤ ይኽንም ኹሉ ወንጀል ፈፅመው ግን በወቅቱ ከፈጠሩት ኹካታ ውጭ ፤ ኃይማኖታቸው እንደ አይከፈል ወይንም አዳዲስ ኃይማኖታዊ ጎጦች እንደ አይፈጠሩ ወይንም ሰዎች ‘በግዜ አመጣሽ አና ሽቃጭ’ ኃይማኖት እንደ አይበከሉ መከላከል አልቻሉም ።

 

በአጠቃላይ የኃይማኖትን ንጽኽና በምድራዊ ጉልበት ለማረጋገጥ መሞከር አፍራሽ ኾኖ ነው የተገኘው ።

 

ሌላው ስለ ኃይማኖታዊ ፅንፈኝነት ማለት የእምንችለው ነገር ፤ አንዳንድ የተንጋደዱ ማሕበራዊ ወይንም ፖለቲካዊ ፖሊሲዎች ፤ ለኃይማኖታዊ ፅንፈኝነት ችግር ጥሩ የመራቢያ አረንቋ የመኾናቸውን ጉዳይ ነው ።

 

የፖለቲካ ሳይንስ እንደ እሚያስረግጥልን ፤ ሰው ፖለቲካዊ ወይንም ማሕበራዊ ፍጥረት ነው ። ያም ማለት ሰው ፤ ማበር ፣ መተባበር እና መቀላቀል ተፈጥሮዋዊ ባሕሪው ነው ። ይኽም ተፈጥሮዋዊ ሰዋዊ ባሕሪያችን ነው ፤ የሰው መንግሥት ወይንም የአንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ህልውና መሠረት ወይንም አያያዥ ገመድ የኾነው ።

 

ሰው ፤ ማሕበራዊ ወይንም ፖለቲካዊ ፍጥረት ባይኾን እና ኃይማኖቱ ፣ ነገዱ ፣ ፆታው ፣ ባሕሉ ፣ የእሚናገረው የኾነው ቋንቋው ፣ ወዘተ ፤ ሳይ አግደው ፤ በሰውነቱ ብቻ ተባብሮ የመኖር ተፈጥሮዋዊ ፍላጎት እና ምክንያት በአይኖረው ኖሮ ፤ ሐገር ወይንም ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ የእሚባለው ነገር አይኖርም ነበር ።

 

ይኽም በመሆኑ ፦ ወይንም በእዚኽ ሰብዓዊ ባሕሪያችን ምክንያት ፤ በዴሞክራሲያዊ ማዕቀፍ ውስጥ ፤ ሰዎችን በቅርፅ በእሚያለያያቸው መገለጫዎቻቸው ለማስተባበር ከመሞክር ይልቅ ሰዎችን ፤ በሰውነታቸው ለማስተባበር መሞከር በቀላሉ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኛል ። ምክንያቱም ፦ የአንድነት መልዕክት ፤ ከማንኛውም ጎጠኝነት መልዕክት ይልቅ ፥ ለሰዎች ተፈጥሮዋዊ ስነልቦና ቅርብ ስለ ኾነ ።

 

ይኽንም ማለት ፤ ሰዎች የአላቸውን የቅርፅ ወይንም የቆዳ ቀለም ፣ የቋንቋ ፣ የባሕል ፣ ወዘተ ፤ ልዩነት አይፈልጉትም ወይንም ይተውታል ማለት ሰአይሆን ፤ ሰዎች በባሕሪ ደረጃ ፤ ኹኔታዊ የኾነው የቅርፅ ልዩነታቸው ፤ ተፈጥሮዋዊ በኾነው ሰብዓዊ አንድነታቸው ላይ ጣልቃ እየገባ ፤ ማሕበራዊ መስተጋብራቸውን እና ትብብራቸውን እንዲያስተጓጉልባቸው አይፈልጉም ።

 

ምክንያቱም ፦ በእዚኽ መልኩ ማሕበራዊ መስተጋብራቸው ሲስተጓጎል ፤ ከማሕበረሰብ የእሚያገኙትን ዘርፈ ብዙ ጥቅም የእሚያጎድልባቸው በመሆኑ ።

 

በእዚኽ መልኩ ሊያለያያቸው የእሚፈልገውንም ማንኛውም ፤ ፖለቲካዊም ኾነ ሌላ ኃይል ፤ በአዕምሮ ብስለት በእውቀት ቃላት ሰድረው ወይንም በተግባር ተደራጅተው ሊቃወሙት በአይችሉ እንኳን ፤ በልባዊነት እንደ ህልውናቸው አደጋ እና ጠላት አድርገው ማየታቸው አይቀርም ።

 

በአንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ውስጥ ፤ የሰብዓዊ አንድነት ኃሳብ ፥ ትክክለኛዎቹን አራማጅ ከአገኘ ገዢው ኃሳብ ነው ።

 

ከእዚኽም የተነሳ ፤ የጎጥ ጠባቦች ፤ በአንድ ፖለቲካዊ ምሕዳር ውስጥ በተለያየ ምክንያት የሰብዓዊ አንድነት አስተሳሰብን ተጭነው የበላይነት ሲኖራቸው ፤ ለማንኛውም ፅንፈኛ ነገር ግን የሰብዓዊ አንድነት መልዕክት ላለው ኃይል ገዢውን መሬት አመቻችተው ይሰጡታል ማለት ነው ።

 

ለምሳሌ ፦ በሐገራችን ኢትዮጵያ ፤ እንደ እሚታወቀው ፥ በነገድ እኩልነት ስም ፤ ሕገ-መንግሥታችን እና ፖለቲካዊ አወቃቀራችን ፤ ከሰዎች ተፈጥሮዋዊ ባሕሪ በተቃራኒ ፤ በነገዳዊ ልዩነት ላይ ያተኮረ ኾኗል።

 

በእዚኽም ምክንያት ፦ በባሕሪው ከቅርፅ ልዩነት በአሻገር በሰብዓዊ ማንነቱ መተባበር እና መያያዝ የእሚፈልገው እና የታሪክ አጋጣሚ ፤ ይኽን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቱን በነገዳዊ ፅንፈኞች የተነፈገው የሐገራችን ሕዝብ ፤ ይኽን ተፈጥሮዋዊ መሻቱን እና ፍላጎቱን ለማርካት ሲል ፤ የአንድነት ነገር ግን ፅንፈኛ መልዕክት ለአላቸው ፤ እንደ ኃይማኖት ፅንፈኞች ላሉ ጽንፈኞች ምርኮኛ መኾኑ የእማይቀር ጉዳይ ነው ።

 

ምክንያቱም ፦ ሰዎችን ከተፈጥሮ ሰብዓዊ ፍላጎታቸው ፤ ከማሕበራዊ ወይንም ፖለቲካዊ ፍጥረታቸው በተቃራኒ ፤ በቋንቋችሁ ፣ በባህላችሁ ወይንም በሌላው ማሕበራዊ ጠባያችሁ ከአላጥርኋችሁ በማለቱ እና ይኽም የሰዎችን ተፈጥሮዋዊ ሰብዓዊ ፍላጎት ፤ ለአንድ የፖለቲካ አስተሳሰብ መስዕዋት በማድረጉ ፤ ይኽን መሰሉ ኋላ ቀር ፖለቲካዊ ርዕዮት የጣለውን የሰብዓዊ አንድነትት ወርቅ ፦ የሰዎች ኹኔታዊ ልዩነትን ጥሶ ፤ ሰዎችን ፥ ፅንፈኛ እንኳን ኾኖ ፤ በሰብዓዊነታቸው በማስተባበር ፤ ይኽን ተፈጥሮዋዊ ፍላጎታቸውን ለእሚያረካው ፤ በእዚኽ ንዑስ አውድ ፥ ለፅንፈኛ ኃይማኖተኝነት ሕዝቡን እና ሐገሪቷን አሳልፎ የእሚሰጥ ያደርገዋል ።

 

ኃይማኖታዊ ፅንፈኝነት ፤ ጥቁር ኹን ነጭ ፣ የእዚኽኛው ቋንቋ ተናጋሪ ኹን የእዚያኛው ፣ የእዚኽ ነገድ ኹን የእዚያኛው ፤ “እውነትኛዋን እና አንዲቷን ኃይማኖት” ከተቀበልኽ እንቀበልኃለን የእሚል የአንድነት መልዕክት ሊያዝል ሲችል በሌላ በኩል ደግሞ እንደ እዚኽ ያለ ማሕበራዊ ልዩነት የተቀበሉትን ምዕመናቸውን ደግሞ ይችኽ “እውነተኛዋን እና አቃፊዋን ኃይማኖትኽን” በኃይል አስፋፋ ፣ ከኃሰተኞች ጠብቅ ፣ ወዘተ ፤ የእሚሉት መልዕክቶቹ ስለሆኑ ጽንፈኛ የእሚያደርጉት ፤ በጎጠኝነት የተወጠረ ማሕበረሰብ ለአንዳንዱ ኃይማኖታዊ ፅንፈኝነት አመቺ ምህዳር ነው ።

 

  ይኽም በመኾኑ ፤ እንደ ኢሕአዴግ ሕገመንግሥት ዓይነት አፍራሽ አሰራሮች እና አስተሳሰቦች ጥሩ የመራቢያ አረንቋ እየፈጠሩሉት ፤ ከእነ ድንቁርና ፣ በሽታ ፣ ድኽነት ፣ የተፈጥሮ አደጋ ጋር በማበር ኃይማኖታዊ ፅንፈኝነት የሰዎችን ምድራዊ ሰቆቃ ሲያፋፍም ኖሯል ።

 

የክስተብረኃን (Enlightenment)  ዘመን የፖለቲካ ሳይንስ አስተሳሰብ ፤ ኃይማኖታዊ ፅንፈኝነትን የገታው ፤ የመንግሥትን ስልጣን ምንጭ ፤ የሰዎች ተፈጥሮዋዊ ነፃነት በማድረጉ እና የመንግሥትም ሚና የዜጎችን ተፈጥሮዋዊ መብት ማክበር መኾኑን በማስቀመጥ ነው[6] ። 

 

ይኽ ሳይንሳዊ ኃሳብ ፤ መንግሥት እና ኃይማኖት እንዲለያዩ ፤ እና የኃይማኖት ጉዳይ ፤ ተፈጥሮዋዊ በኾነው ፤ የዜጎች የማሰብ ፣ የመናገር (ኃሳብን የመግለፅ) እና በኃሳብ ዙሪያ የመሰባሰብ ተፈጥሮዋዊ መብት ስር የእሚካተት እንዲኾን አስቻሎታል ።

 

በእዚኽም መንግሥትን የፅንፈኛ ኃይማኖተኞች መሳሪያ ከመኾን አውጥቶ ፤ ገለልተኛ የኾነ  ፤ የዜጎችን ተፈጥሮዋዊ መብት ማስከበሪያ መሳሪያ በማድረግ ወደ ተገቢው ሕዝባዊ አገልግሎት መልሶታል ።

 

ይኽንም ተከትሎ ፤ በዘመናዊ ማሕበራዊ አወቃቀር ውስጥ ፤ ኃይማኖት ሰዎች እንደ እሚያቋቁሙዋቸው ሌሎች ማንኛውም ፦ የፖለቲካ ፣ የንግድ ፣ የሥራ ወይንም ሌሎች ማሕበራት ፤ በዜጎች ተፈጥሮዋዊ የነፃነት መብት የእሚዳኝ ሆኗል ።

 

ይኽ ዓይነቱ ዘመናዊ ማሕበራዊ አወቃቀር ፤ መንግሥታዊ አቅምን ከፅንፈኞች እጅ መቀማት ብቻ ሰአይኾን  ፤ ኃይማኖታዊ ነፃነትን በማክበሩ ፤ ፅንፈኞች በተከታዮቻቸው ዘንድ የኃሳብ የበላይነት እንደ አይኖራቸው በማድረግ ማሕበራዊ አረንቋቸውን የእሚያደርቅ ነው ።

 

በእርግጥ ፤ በኃይማኖት ነጻነት ስም መንግሥት ፤ ራሳችኹን ግደሉ የእሚል ኃይማኖት ቢመጣ ፤ የኃይማኖት መብት ነው ብሎ ሰዎች በኃይማኖት ስም እየተሰባሰቡ ራሳቸውን እንዲገድሉ ሊፈቅድላቸው አይችልም  ወይንም ሰዎች  በኃይማኖት ስም እየተሰባሰቡ ፤ ሰውነታቸውን በስለት ቢቆራርጡ ፣ ልጆቻቸውን በእሳት ቢያቃጥሉ ፣ ወይንም ሌሎችን ቢገድሉ እና መሰል ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ቢፈጽሙ ፤ የኃይማኖት መብት ነው ብሎ ዝም አይላቸውም ። ሰዎች ላይ ቀጥተኛ ጉዳት የእሚያደርስ ኃይማኖት ማገድ የመንግሥት ሥራ ነው ።

 

የዓለም ሕዝብ በብዙ ሺ ዓመት የፖለቲካ ታሪኩ ፤ ኃይማኖትን በተመለከተ የተማረው ነገር ቢኖር ፤ ኃይማኖት ፤ የሰውን ልጅ ሕይወት እና ንብረት በግልጽ እስከ አልጎዳ ድረስ ፤ በግለሰቦች ምርጫ ያለ ምንም አስገዳጅነት ፤ ኹሉም የፈለገውን ኃይማኖት እንዲይዝ መፍቀድ እና በእዚኽም መንግሥትን ከኾነው ኃይማኖት ጠባቂነት ይልቅ ፤ መሠረታዊ እና ተፈጥሮዋዊ  የሆኑትን የሰውን ልጆች ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጠባቂ ማድረግ ፤ ያም ማለት መንግሥትን እና ኃይማኖትን በመለያየት ፤ ኃይማኖቶች በቤተ እምነታቸው ‘አጥር’ ተወስነው እንዲቀሩ ማድረግ ፤ ኃይማኖቶች በተሻለ ኹኔታ እውነተኛ ተከታይ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ብቻ ሰአይኾን ፤ የትኛውንም ኃይማኖት ለመከተልም ኾነ ለማራመድ የእሚያስችለውን ፤ የሕዝብን ጸጥታ እና ሰላም ለማረጋገጥ ብቸኛው አማራጭ መኾኑን ነው ።

 

በእዚኽም ማሕበረሰብ ፤ ሰላማዊ ኃይማኖቶች ሕጋዊ ከለላ የእሚሰጥ እና ራሱን ከፖለቲካዊ ጎጥ ያፀዳ መንግሥትን ማዋቀር ወደ የእሚያስችለው የአወቃቀር ዘዴ ሲመጣ ፤ ኃይማኖታዊ ልዩነቶች ማሕበረሰብን አከፋፍለው እንደ አያጋጩ እና ኃይማኖታዊ ፅንፈኞች ለፅንፈኝነታቸው አመቺ ማሕበራዊ ምህዳር እንደ አያገኙ በማድረግ ፤ ኃይማኖትን የግጭት እና የፅንፈኞች መሳሪያ እንደ አይሆን መግታት ይችላል ።

 

ስለ እዚኽ መንግሥታዊ አወቃቀሮች ወይንም አስተሳሰቦች ፤ ሰዎች በማሕበራዊ የቅርጽ ልዩነት ላይ በመከፋፈል ፤ ለኃይማኖታዊ ጽንፈኞች አመቺ አረንቋ ከመፍጠር ይልቅ ፤ የዜጎችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት በሰውነታቸው ብቻ የእሚያከብሩ በመሆን ፤ ሐገራዊ አንድነትን እያጠናከረ ኃይማኖታዊ ጽንፈኞችን መራቢያ አረንቋ የእሚያሳጣ መሆን ነው የአለበት ።

 

ስለ ኃይማኖት ፣ ኃይማኖታዊ ልዩነት እና ኃይማኖታዊ ጽንፈኝነት ይኽንን ከአልን ፤ ኃይማኖታዊ ፅንፈኛው ሐገርን የእሚረዳበት እና ሐገር መሆን አለባት ብሎ የእሚያምንበትን አግባብ አይተን ይኽን ንዑስ ክፍል እንደምድመው ።

 

ኃይማኖታዊ ፅንፈኛ ፤ ሐገርን ፣ ሕዝቦቿን እና ሐገራዊ ኃብቷን ፤ የኾነው ኃይማኖት ማካኼጃ ፣ ማስፋፊያ እና መጠበቂያ መሳሪያ መሆን አለባቸው የእሚል ወይንም የእሚያደርግ በመሆኑ ፤ ከእላይ በአልነው አግባብ ፤ ከመሠረታዊ የሰዎች ሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት በተቃራኒ በመቆም ፤ በዜጎች መካከል በኃይማኖታዊ እምነታቸው መሠረት ልዩነት በማድረግ ዜጎችን በሰብአዊነታቸው በእኩልነት የእማይቀበል ነው ።

 

ይኽም ሐገርን ፤ የሕዝብ መኖሪያ ሳትኾን ፤ የኾነው ኃይማኖት ተከታዮች መኖሪያ እና ሐገሪቷንም ሆነ ሐገራዊ መንግሥቷን እና ኃብቷን የእዚኹ ኃይማኖት ማካኼጃ የእሚያደርግ ጽንፈኛ ነው።

 


 
 

[1] አርስቶትል በእዚኽ አውድ መርኹ የእሚለው ፤ ኹሉ ነገር የሚሰራበት ንጥረ ነገር እና በስተመጨረሻም የሚኾነው ፤ ወይንም የነገር ኹሉ መጀመሪያ እና መጨረሻ የሚለውን ነገር ነው ፤ ወይንም ኹሉም ነገር ከውኃ ይወጣል በስተመጨረሻም ወደ ውኃነት ይለወጣል ፤ የእሚል ነው በእዚኽ አውድ ።

 
 
 

[2] በፕሌቶ እንደ ተጻፈ የእሚነገርለት እና በዋናነት የሶቅራጠስን የስነ መንግሥት ፍልስፍና በድራማዊ ሙግት ተምሳሌት የእሚያቀርብ መጽሐፍ ነው።

 
 
 

[3] የብዙ ነዋሪዎችን ህይወት እና መላ ንብረት ያወደመውን እሳት ያስነሳው ኔሮ ሆን ብሎ ነው የእሚለውን ሕዝባዊ ውንጀላ።

 
 
 

[4] በአማርኛ ጴንጤቆስጤ የእሚለው የግሪኩ ፔንቴ (Pente) ወይንም ሐምሳ የእሚለውን ቃል መሠረት የአደረገ ነው ። እናም ሙሉ በአማርኛው ጴንጤቆስጤ (Pentecoste) ተብሎ የእሚነበበው ቃል በአለ ሐምሳ ወይንም የሐምሳኛው ዓመት አውደ አመት ከእሚል የግሪክ ቃል የመጣ ነው። ይኽም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ፤ በአለ ሐምሳ ከእሚባለው እና በሐሪያት ሥራ ምዕራፍ 2 ላይ ፤ የኢየሰሱ ደቀመዛሙርት ተሰብስበው በአሉበት መንፈስ ቅዱስ ከወረደበት ቀን ጋር የእሚያያዝ ነው።

 
 
 

[5] የእዚኽን ታሪክ ዘርዘር ባለ መልኩ በምዕራፍ ሶስት ላይ እናየዋለን።

 
 
 

[6] የዚኽን ሐሳብ ዝርዝር ፤ ሳይንሳዊ ሕገመንግሥት በሚለው ክፍል ላይ እንመለስበታለን።