ሕ ገ ክ ራ ሲ

marketing-image

ማስታወቂያ

በእዚኽ መጽሐፍ ውስጥ ስለ እሚገኙ ኹለት የአቀራረብ ጉዳዮች አንባቢን ማስታወቅ ተገቢ ይሆናል።

የመጀመሪያው በመጽሐፍ ውስጥ የእሚገኙ ከፍተኛ ቁጥር የአላቸው በእንግሊዘኛ ከተጻፉ መጽሐፍት የተጠቀሱ ጽሁፎች እና የአማርኛ ትርጉማቸው አብረው አንድ ላይ የእሚገኙ መሆናቸውን ነው።

የእንግሊዘኛውን ማጣቀሻ ከእነ አማርኛ ትርጉሙ ጋር አብሮ በመጽሐፍ ውስጥ ማስቀመጥ ምንም እንኳን መጽሐፉን ቢያረዝመውም እና ድግግሞሽ ቢመስልም ፤ የእንግሊዘኛውን ጽሑፍ በእኔ ትርጉም ከእነ አማርኛ ትርጉሙ ጋር ማስቀመጥ የአስፈለገበት  ምክንያት ይኽ መጽሐፍ ለአማርኛ ተናጋሪዎች ታስቦ የተዘጋጀ በመሆኑ እና የተጠቀሱት የእንግሊዘኛ መጽሐፍት የአማርኛ ትርጉም የሌላቸው[1] በመሆኑ ፤ ማጣቀሻዎቹን በአማርኛ ብቻ ተርጉሞ ማስቀመጥ ለማጣቀስ የእማይመች በመሆኑ ነው ።

ከእዚያኽም በአሻገር ፤ በእንግሊዘኛ የተጻፈን ነገር ማንበብ እና መረዳት የእሚችለው አንባቢ ፤ በእኔ የአተረጓገም ምክንያት ሊኖሩ የእሚችሉ ክፍተቶች ከአሉ አንባቢው በራሱ ዋናውን የእንግሊዘኛውን ጽሑፍ አንብቦ የራሱን ግንዛቤ እንዲይዝ ነው።

ኹለተኛው የአቀራረብ ጉዳይ ፤ ጠብቀው እና ላልተው ሲነበቡ ፤ የትርጉም ልዩነት ስለ እሚያመጡ ፤ በአንዳንድ የአማርኛ ቃላት ውስጥ ስለ እሚገኙ ፊደላት ነው።

ለምሳሌ ፦ “ሊገባ” የእሚለው የአማርኛ ቃል ፤ “ገ”ን አጥብቀን እና አላልተን በእምናነብበት ግዜ ፤ ምንም እንኳን የቃሉ ፊደላት አንድ ዓይነት ቢሆኑም ፤ ቃሉ የተለያዩ ትርጎሞች ይኖሩታል።

“ገ” ላልቶ በእሚነበብበት ግዜ “ሊገባ” የእሚለው ቃል  መግባት ከእሚለው ግስ ጋር የተዛመደ ፤ ሦሥተኛ ሰው እና ተባዕት ነጠላ ጾታን (Third person singular masculine) ከውጭ ወደ ውስጥ የመግባት ኺደት ላይ መሆንን የእሚያመለክት (He/it is about to come in) ቃል ይሆናል።

“ገ” ጠብቆ ሲነበብ ደግሞ ቃሉ እንደ አውዱ ድርብ ትርጉም የአለው ቃል ይሆናል ፦

  • ሊገ፟ባ ፡ በመጀመሪያው አውድ ፤ ከውጭ ወደ ውስጥ ለመግባት ታስቦ መሆኑን ለመጀመሪያ ሰው ብዙ ቁጥሩ በጥያቄ (are we about to enter ?) እና ሦሥተኛ ሰው ብዙ ቁጥር እና ኹለተኛ ሰው ነጠላም ብዙም ቁጥር (Third Person plural and second person singular/plural) ይውላል (you wish you were in, they wish they were in )። በዓረፍተ ነገር ምሳሌነት ለማሳየት ፦
    1. ሊገ፟ባ ነው (ወደ ውስጥ ሊገ፟ባ ነው)? [በብዙ ቁጥር ወደ ውስጥ መገባት ሊጀመር መሆኑን መጠየቅ](are we going in?)[2]
    2. ሊገ፟ባ ? [ በድምጽ ቅላጼ የእሚወሰን ሆኖ ፤ ሊገ፟ባም ታስቦ ኖሯል ? ብሎ በምጸት ነጠላም ሆነ ብዙ ቁጥር አመልካች የመጠየቅ] (you wish you came in, they wish they came in)
  • ሊገ፟ባ ፡ በኹለተኛው አውድ ደግሞ መግባት ከእሚለው ቃል ጋር በፍጹም በተለየ ፤ ተገቢነት (appropriateness) ከእሚለው የግስ ገላጭ ጋር የተያያዘ ትርጉም ያዘለ ቃል ይሆናል ።
    1. ሊገ፟ባው ይችላል ። [ሰውየው ወይንም ነገርየው ሽልማቱን ወይንም ተግሳጹን ማግኘቱ ትክክል ሊሆን ይችላል ፡ He/it might deserve it ]

 በእዚኽ መልኩ ጠብቀው እና ላልተው ሲነበቡ ፤ የአተረጓገም ልዩነት የእሚፈጥሩ ፊደላትን ለመለየት ፤ በማይክርሶፍት ዊንዶውስ (Windows 10, Version 2004 (OS Build 19041.867) Professional Edition) የአማርኛ መጻፊያ/መተየቢያ የተዘጋጀውን ፤ በፊደላት አናት ላይ የእሚቀመጥ አግድሞሽ ኹለት ነጥብ “ ፟ “ የእሚጠብቁትን ፊደላት ለማሳየት ተጠቅሜአለሁ።

በእዚኽም መሠረት ፤ “ሊገባ” የእሚለው ቃል እንደ ማሳያ ብንወስደው ፤ “ገ” በእማይጥብቅበት ፤“ገ” ያለ ማጥበቂያ ምልክቱ እንዲሁ “ሊገባ” ሆኖ ይቀመጣል ፤ “ገ” በእሚጠብቅበት ፤ “ገ” ከአናቱ ላይ የአግድሞሹ ኹለት ነጥብ “ገ፟” በእዚኽ መልኩ ተቀምጦ “ሊገ፟ባ” ሆኖ ይቀመጣል።

  • ሊገባ ፡ ገ ላልቶ ሲነበብ።
  • ሊገ፟ባ ፡ ገ ጠብቆ ሲነበብ።

ማለት ነው።

 

[1] ቢያንስ መጽሐፉ በእሚጻፍበት ወቅት ማግኘት አልተቻለም።

[2] ይኽ አንዳንድ ግዜ ፤ በወጣት ዘዬ (Slang) ፤ በነጠላም በብዙ ቁጥር ኹለተኛ ሰው (Second person singular or plural) ወደ አንድ ቦታ ሊገባ ወይንም ሊገቡ መሆኑን መጠያቂያ ሊሆን ይችላል ፤ ለምሳሌ ፦ ሊገ፟ባ ነው ?(are you (guys) going in?) ።