የኢትዮጲያ ሕዝብ ከአክሱም ውድቀት አንስቶ እስከ ዛሬ በአመርቂ ኹኔታ የአልተሳካ የሕዝባዊ መንግሥት የመመሥረት ትግል ሲያካኼድ የኖረ መሆኑን እና ይኽንን ትግል አንድ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ማድረስ ከአለበት ደግሞ በሕዝባዊ መንግሥት አስተሳሰብ የተቃኘ ሕገመንግሥት ከመንደፍ መጀመር በስተቀር ሌላ ምንም አማራጭ የለውም የእሚለውን እሳቤ ለማስረዳት ፤ መጽሐፉ ፦
የእሚሉትን ጥያቄዎች በእሚመልሱ አራት ምዕራፎች ተጠናቅሯል። እነርሱም ፦ ሐገር ፣ የሰው መንግሥት ፣ ኢትዮጲያ እና ሕዝባዊ ሕገመንግሥት ፤ የእሚሉ አራት ምዕራፎች ናቸው።
የመጀመሪያው ሐገር የእሚለው ምዕራፍ ስለ ሐገር ኹለት መሠረታዊ ጽንሰ ኃሳቦችን እና በሐገር ግንዛቤ እና ግንባታ ላይ ፖለቲካዊ ርዕዮቶች የአላቸውን ሚና በማስቀመጥ ፤ የነጻነቱ ዴሞክራሲን ሐገራዊ ግንዛቤ ተመራጭነት ለማሳየት ይሞክራል።
በእዚኽ ምዕራፍ የእሚቀርበው ፤ ሐገርን የእሚመለከተው የመጀመሪያው ጽንሰ ኃሳብ ፤ ዋንኛ ግብ ፦ ሐገር ፥ የሰው ልጅ ውቅር ወይንም የሰው ልጅ ተግባር ውጤት መሆኗን ማስረገጥ ነው።
ሐገርም የሰው ልጅ ውቅር ነች ስእንል ፤ በሰዎች የተሰራ የራሷ ኃሳባዊ እና ቁሳዊ ክፍል የአላት ፤ የሰው ልጆች ውቅር ነች ወይንም ሐገር ሰው ሰራሽ ሕንጸት እንጂ ተፈጥሮዋዊ ፍጡር አይደለችም እያልን ነው።
ኹላችንም እንደ እምንገነዘበው ፤ ኢትዮጲያዊያኖቹ ከመኖራቸው በፊት ኢትዮጲያ አልነበረችም ፤ ኢትዮጲያዊያኖች መኖር ከአቆሙም ኢትዮጲያ አትኖርም ፤ ስለ እዚኽ ፦ ኢትዮጲያ የኢትዮጲያዊያን ውቅር ወይንም ሕንጸት ለመሆኗ ጥርጥር የለውም።
በርግጥ ኢትዮጲያ የሆነውን መልክዓ ምድር እና ኢትዮጲያዊ የሆኑትን ሕዝብ ፤ ሰዎች አልፈጠሩዋቸውም ። የኢትዮጲያዊነት ቁሳዊ መሠረት የሆኑት መሬቱ እና ሕዝቧ ፤ በፈጣሪ ወይንም በተፈጥሮ የተፈጠሩ ናቸው ። በተፈጥሮ የእሚገኘውን ባዶ መሬት እና የሰውን ልጆች ወስዶ ግን ፤ ኢትዮጲያ የእሚባለውን ጂኦግራፊያዊ ክልል እና ኢትዮጲያዊያን የእሚባሉትን ዜጎቿን የአካተተችውን ፖለቲካዊት ኢትዮጲያ የፈጠሩት ግን ፤ ራሳቸው ኢትዮጲያዊያኖች ናችው።
ኹለተኛው በእዚኽ በመጀመሪያው ምዕራፍ ውስጥ የአለው ጽንሰ ኃሳብ ፤ አንድን ውቅር የወሰድን እንደሆን ፤ ለምሳሌ ፦ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እንደ ማሳያ በእንጠቀም ፤ አካላዊ እና ንድፈ ኃሳባዊ ክፍፍል የአላቸው መሆኑ ነው።
አብያተ ክርስቲያናቱ ታንጸው ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት ከመሆናቸው ወይንም አካላዊ ክፍላቸው ከመታነጹ በፊት ፤ አካላዊ ቅርጻቸውን በንድፍ ደረጃ በማስቀመጥ ነው ግንባታው የተጀመረው። ስለ እዚኽ አብያተ ክርስቲያናቱ ፤ ኃሳባዊ እና ቁሳዊ ክፍል አላቸው።
ሐገርም በተመሳሳይ የሰው ልጅ ውቅር እንደ መሆኗ ፤ ቁሳዊ አካልዋ ማለትም የሐገር ድንበሯ እና በእዝያኽ ድንበር ውስጥ የእሚኖሩት ሕዝብ አንድ የፖለቲካ መሐበረሰብ ከመሆናቸው በፊት ፤ ይኽን ቁሳዊ አካሉን ወደ መሆን እንዲመጣ ግድ ያለ እና ምን መምሰል እንደ አለበት የደነገገ ኃሳባዊ ምክንያት እና ንድፍ ወይንም የሐገር ኃሳባዊ አካል ወይንም ክፍል አለ።
ይኽ የሐገር ኃሳባዊ ምክንያት እና ንድፍ ወይንም ኃሳባዊ አካል ፤ ሐገርን የእሚረዳበት አግባብ ፤ በተለይ አኹን በእምንገኝበት ዘመን ርዕዮታዊ ደርዝ የአለው ነው። ስለ እዚኽ ፤ ሐገር ለኃይማኖተኛው ፣ ለማርክሲስቱ ፣ ለብሔር ጽንፈኛው ፣ ለባሕል ጽንፈኛው ፣ ለጂንጎይስቱ እና ለዴሞክራሲያኑ የተለያየ ትርጉም የአላት ናት።
ይኽም በመሆኑ ፤ በእዚኽ በመጀመሪያው ምዕራፍ በእዚኽ ዘመን ጉልህ ስፍራ የአላቸው ፖለቲካዊ ርዕዮቶች ሐገርን የእሚረዱበትን አግባብ በመዘርዘር ፣ በመተንተን እና በማነጻጸር ፤ የዴሞክራሲያዊው ርዕዮት ሐገርን የእሚረዳበት አግባብ ፤ የተሻለ ማሕበራዊ እና ኢከነሚያዊ ፋይዳ የአለው መሆኑን ለማስቀመጥ እና ሐገር ምንድነች የእሚለውን ጥያቄ ከነጻነቱ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ አንጻር ከእነ ፋይዳው ለመመለስ እሞክራለሁ።
ይኽንንም ለማድረግ ፤ ምዕራፉ ፦
በእሚሉ በሦሥት ዋና ዋና ንዑስ ርዕሶች ተከፍሏል።
ጽንፈኛ ርዕዮቶች የእሚለው ዋና ንዑስ እንደ ገና በተከታይ አምስት ንዑሶች ይከፈላል ፦
የተለያዩ በዘመናችን የእሚስተዋሉ ፖለቲካዊ ርዕዮቶች ወይንም ርዕዮት መሰል የአስተሳሰብ ዘዬዎች ሐገርን የእሚረዱበትን አግባብ እና የዴሞክራሲያዊን ርዕዮት የሐገር አረዳድ ብልጫ በእዚኽ በመጀመሪያው ምዕራፍ ከዳሰስን በኋላ ፤ በኹለተኛው ምዕራፍ ፤ የሰው ልጅ ሐገርን ለማስተዳደር የእሚያቋቁማቸውን የተለያዩ የመንግሥት ዓይነቶች እንቃኛለን።
የእየ ሐገራት መንግሥታት ፤ ልክ እንደ ሐገር የሰው ልጅ ውቅሮች በመሆናቸው ፤ የራሳቸው ኃሳባዊ እና አካላዊ ውቅር አላቸው። የመንግሥትን አካላዊ ውቅር የእሚወስኑት የመንግሥት ኃሳባዊ ውቅራት ፤ አንድ የእሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር ኹሉም የስነ መንግሥት ጽንሰ ኃሳቦች አነሰም በዛም ፤ መንግሥት ለምን ያስፈልጋል ? ለእሚለው ጥያቄ የእሚያቀርቡት የራሳቸው መልስ የአላቸው መሆኑ ነው።
ይኽ ኹለተኛው ምዕራፍም የመንግሥትን ኃሳባዊ ውቅር ወይንም መንግሥት ለምን? ጥያቄ ፤ ከተለያዩት መንግሥታዊ ትርክቶች አንጻር በማብራራት ፣ በመተንተን እና በማነጻጸር ፤ የነጻነቱ ዴሞክራሲ መንግሥት ለምን ? ለእሚለው ጥያቄ የእሚሰጠውን መልስ እና ይኽም መልስ የተሻለ የሆነበትን ምክንያት በማቅረብ ላይ የአተኮረ ነው ።
ይኽንንም ለማድረግ ፤ ምዕራፉን ፦
በእሚሉ በኹለት ዋና ዋና ንዑሶች ከፍለን እናየዋለን።
ፖለቲካዊ ሰው እና ስልጣኔው በእሚለው በመጀመሪያው ንዑስ ለማስቀመጥ የተሞከረው ፤ የሰው ልጅ መንግሥት ስእንል ታሪክ ሰሪውን ፤ ማለትም ፦ ማሰብ ፣ መናገር ፣ መጻፍ የእሚችለውን ፤ የዝግመታዊ ለውጥ አማኞች ሆሞሳፒየንስ የእሚሉትን ወይንም በፈጣሪ የእሚያምኑ ሰዎች አምላክ በአምሳያው የፈጠረው የእሚሉትን ሰው ፤ መንግሥት እያልን መሆኑን ነው ።
ከእዛኽ በመቀጠል ፤ መንግሥት በእሚለው ንዑስ ስር ፤ ይኽ ፖለቲካዊው ሰው ፤ መንግሥትን ለመመሥረት በታሪክ የአዳበራቸውን የተለያዩ መንግሥት መመሥረቻ ትርክቶች ፣ በእነ እዚኽ ትርክቶች የመንግሥትን ስልጣን የእሚያስቀምጥበትን አግባብ ማነጻጸር እና በስተ መጭረሻም ፤ እነ እዚኽን መንግሥታዊ ትርክቶቹን በተጻፉ ሕገ መንግሥት ወይንም የመንግሥት ማዋቀሪያ ሰነድ አግባብ ለማስቀመጥ የኼደበትን ታሪካዊ ዝግመት ለማስቀመጥ መሞከር ነው።
ለእዚኽም መንግሥት የእሚለው ዋና ንዑስ ፦
በእሚሉ ሦሥት ተከታታይ ንዑሶች ይከፈላል።
በእነ እዚኽ ኹለት ምዕራፎች ፤ የሐገር ኃሳባዊ አካል በሆኑት ርዕዮቶች ፤ ሐገር የእምትገለጽበት እና ሐገርን የእሚያስተዳድሩ መንግሥታት የእሚዋቀሩበትን አግባብ ከተነተንን ፤ ከአነጻጸርን እና ዘመናዊ ዴሞክራሲ ሐገርን የእሚረዳበት እና ሐገርን የእሚያስተዳድረው መንግሥት ሊዋቀርበት ይገባል የእሚልበትን አግባብ ብልጫ ከአሳየን በኋላ ወደ ሦሥተኛው የመጽሐፍ ምዕራፍ እንሻገራለን።
ሦሥተኛው የመጽሐፉ ምዕራፍ ሙሉ ለሙሉ የኢትዮጲያ ፖለቲካዊ ታሪክ ላይ በማተኮር ፤ በምዕራፍ አንድ እና ኹለት ላይ በመሠረትነው የዴሞክራሲያዊው ርዕዮት መነጽር ፤ የኢትዮጲያን ፖለቲካዊ ዝግመት ፤ ኢትዮጲያዊነት በእጭነት ወይንም በሕጸጽነት ከጀመረበት ከቅድመ አክሱም ጀምሮ አኹን እስከ ደረሰበት ግዜ የአለውን ታሪክ በመቃኘት ፤ ከአክሱም ውድቀት ማግስት የአለው የኢትዮጲያ ሕዝብ ፖለቲካዊ ትግል ፤ ሕዝባዊ መንግሥትን ለማቋቋም የተደረገ ትግል ነበር የእሚለውን ኃሳብ ፤ ከኢትዮጲያ ታሪክ ውስጥ ለማሳየት ይሞክራል።
ይኽንንም ለማድረግ ፤ በኢትዮጲያ ፖለቲካዊ ዝግመት ውስጥ ወሳኝ ኹነት የተካኼደባቸውን ዓመታት በአንድ ላይ በእሚያደርግ ዘዬ ፤ ታሪኩን ከጥንተ ጥንተ እስከ ዛሬ በዘጠኝ ክፍል በእሚከተለው መልኩ ይከፋፍላል ፦
በእዚኽ ምዕራፍ ፤ በነጻነቱ ዴሞክራሲ አግባብ ፤ ሐገር ማለት ፦ ዜጎች ተፈጥሮ በእኩልነት በአጎናጸፋቸው ነጻነት ተጠቅመው ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ እና ኑሮዋቸውን ለማሻሻል የእሚመሰሩቷት ማሕበር ነች ፤ መንግሥትም ይኽንን የዜጎችን ነጻነት እና ንብረት አክብሮ አስከባሪ ሕዝባዊ ተዋካይ መሆኑን በማስረገጥ ፤ ኢትዮጲያም በዓለማችን ላይ እንደ አለች አንዲት ጥንታዊ ሐገር ይኽንን ዓይነት ይዘት እና ፋይዳ የአላት ሐገር ለማድረግ በአለፈው 2ሺ ዓመት ስትታገል መቆየቷን ከአየን በኋላ ፤ ይኽን የብዙ ዘመን የኢትዮጲያን ፖለቲካዊ ትግል ወይንም ጉዞ ፤ ትርጉም በአለው መልኩ ልእናሳካ የእምንችለው ፤ ሕዝባዊ ሕገመንግሥት መንደፍ በመጀመር መሆኑን በማመን ፤ በምዕራፍ አራት ላይ ሕዝባዊ ሕገመንግሥት ንድፍ እናስቀምጣለን።
በአራተኛው እና የመጨረሻው ምዕራፍ ፤ የሕዝባዊ ሕገመንግሥቱን ንድፍ ከኢትዮጲያ የሕገመንግሥት ጋር በማቆራኘት ለማቅረብ ፤ ምዕራፉ ፦
በእሚሉ ሦሥት ንዑሳን ክፍሎች ተከፋፍሏል።
ሕግ እና ሕገመንግሥታዊነት በኢትዮጲያ በእሚለው ንዑስ ፤ ሕግ እና ሕገመንግሥታዊነት በኢትዮጲያ የነበረውን ታሪካዊ ዝግመት ይቃኛል።
የኢሕአዴግ ሕገመንግሥት እና ችግሮቹ በእሚለው ንዑስ ፤ አሁን በሐገራችን የአለው የኢሕአዴግ ሕገመንግሥት ከዴሞክራሲያዊነት አንጻር የአሉበትን ችግሮች ፤ የተመረጡ ሦሥት አንኳር ነጥቦችን ማሳያ አድርጎ በማቅረብ ለማሳየት ይሞክራል።
የአከላለል መርህ እና ሕገመንግሥት በእሚለው ሦሥተኛው ንዑስ ስር በመጀመሪያ የአከላለል መርሕ ሐተታ በእሚል ንዑስ ርዕስ ስር ፤ በንድፍ የእሚቀርበው አዲሱ የኢትዮጲያ ሕገመንግሥት ንድፍ ፤ አኹን በአለው የሐገራችን አከላል አግባብ ሊሰራ ስለ እማይችል ፤ አዲስ የአከላለል መርሕ መከተል አለብን በእሚል ይኽ አዲሱ የአከላለል መርኽ ምን መምሰል እንደ አለበት የእምናይበት ነው።
ሦሥተኛው ፤ የሕገመንግሥት ንድፍ የእሚለው ንዑስ ክፍል ፤ ኢትዮጲያ የዘመናት ትግሏ ወደ ሆነው የሕዝባዊ መንግሥት ባለቤትነት መሻገር ከአለባት ፤ ዘመኑን የእሚመጥነው የኢትዮጲያ ሕገመንግሥት የቱ ዓይነት ሊሆን እንደ እሚገባው ለማመልከት ፤ ዘመናዊ ኢትዮጲያን የእሚመጥን የሕገመንግሥት ንድፍ ያቀርባል።