ሕ ገ ክ ራ ሲ

marketing-image

ትሩፋት 2 ፡ በኢትዮጲያ ፦ ስነመለኮት እና ፖለቲካ

አንድ የስነ መለኮት ተማሪ ስለ ሥላሤ እንደ እዚኽ እንደ ቀለደ ይነገራል ፦

“ሥላሤን ለመካድ ሞክር የዘላለም ህይወትን ታጣለህ ፤ ሥላሤን ለመረዳት ሞክር አዕምሮህን ታጣለህ።”

የሥላሤ አስተምህሮ በክርስትና እምነት ውስጥ ክርስትና በዓለም ላይ መስፋፋት ከጀመረበት ግዜ አንስቶ ብዙ የአከራከረ እና የዓለምንም ታሪክ በወሳኝነት ከወሰኑ ክስተቶች አንዱ የሆነ ነው። ብሩስ ሼሊ የተባለ የቤተክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ ፤ የሥላሤ ጽንሰኃሳብ በቤተክርስቲያን ውስጥ ከተፋፋመ እና የሰውን አዕምሮ መቆጣጠር ከጀመረ በኋላ ፤ ከ5ኛው ምዕተ ዓመት በፊት በኮንስታንቲኖፖል ይኖር የነበረ አንድ ጳጳስ በኹኔታው በመገረም እና በመሰላቸት ከእዚኽ በታች የአለውን ነገር እንደ አለ ይዘግባል ፦

“አንድ ጳጳስ ኮንስታንቲኖፖል በውይይት እየተናጠች መሆኑን እንደ እዚኽ ገልጾታል ፡

በእዚኽ ከተማ አንድን ሰው መልስ ከጠየከው ፤ ሰውየው ወልድ አምላክ ተወልዷል ወይንስ አልተወለደም ይልኃል። የዳቦው ጥራት መልካም መሆኑን ከጠየቅኽ ፤ “እግዚአብሔር አብ ከፍ ይላል ፤ ወልድ አምላክ ደግሞ ዝቅ ይላል” የእሚል መልስ ታገኛለኽ ። ሰውነት መታጠብ መልካም እንደ ሆነ ኃሳብ ብትሰነዝር ፤ “ወልድ አምላክ ከመፈጠሩ በፊት ምንም አልነበረም” የእሚል መልስ ይሰጥኃል።”

“One bishop described Constantinople as seething with discussion :

If in this city you ask anyone for change, he will discuss with you whether God the Son is begotten or unbegotten. If you ask about the quality of bread, you will receive the answer that “God the Father is greater, God the Son is less.” If you suggest that a bath is desirable, you will be told that “there was nothing before God the Son was created. [8]”

በመላው የክርስትናው ዓለም ውስጥ ከፍተኛ ኹነት የነብረው ይኸው የሥላሤ አስተምህሮ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ታሪክ ውስጥም ከፍተኛ ቦታ የአለው ነው። የሥላሤ አስተምህሮ በኢትዮጲያ የመጀመሪያ ሊባል የእሚችለውን የእርስ በእርስ ጦርነት በአጼ ሰሶንዮስ ዘመን ከአስከተሉት ጉዳዮች አንዱ እስከ መሆን ደርሷል።

በእዚኽ መጽሐፍ ውስጥ በኹለተኛ ትሩፋትነት ይኽንን የሥላሤውን ኃሳብ ለማብራራት የፈለግኹት በኹለት ምክንያት ነው ፦

  • በዘመናዊው ኢትዮጲያ ከሞላ ጎደል በአኹን ሰዓት ብዙም አከራካሪ የአልሆነው አስተምህሮ ለምን በእዚያኽ ወቅት ከፈተኛ አከራካሪ ኃይማኖታዊ ርዕስ በመወሆን ወደ ፖለቲካዊ ግጭት ሐገሪቱን እንድታመራ እንደ አደረጋት የመረዳቱን ጉዳይ ለማገዝና
  • አጼ ፋሲለደስ በስተመጨረሻ በጉዳዩ ላይ የአቀረበው ዳኝነት ፤ የአስተሳሰብ ልቀቱን ስለ እሚያሳይ ፤ የነገሥታቶቻንን ታሪክ ለማውሳት በማሰብ ነው።

ምንም እንኳን ሥላሤ እጅግ አከራካሪ እና ውስብስብ ጉዳይ የነበረበት ታሪክ ቢኖርም ፤ በእዚኽ ዘመን ለእምንኖር ሰዎች ጉዳዩ እንደ ተባለው ዓይነት ውስብስብ አይመስልም።

ሥላሤ ማለት ምን ማለት ነው ?

ሥላሤ ማለት እግዚአብሔር አንድም ሦሥትም ወይንም በሦሥትነት አንድነት በአንድነት ደግሞ ሦሥትነት አለው ማለት ነው። ክርስትና እግዚአብሔር አንድ ብቻውን አምላክ እንደ ሆነ ወይንም በአኃዱ አምላክ ቢያምንም ፤ እግዚአብሔር ፦

  • እግዚአብሔር አብ
  • እግዚአብሔር ወልድ
  • እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ

እንደ ሆነ እና አብ ፣ ወልድ ፣ መንፈስ ቅዱስ በስብዕና ሦሥት ቢሆኑም በመለኮትነት አንድ ናቸው ብሎ ያምናል።

እግዚአብሔር አብ ፣ እግዚአብሔር ወልድ እና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መካከል መለኮታዊ እኩልነት ፣ የባሕሪ ፍጹምነት ፣ ፍጹም መስማማት እና በእዚኽ አንድነት አለ ብሎ ያምናል።

ይኽ አስተሳሰብ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ስነ መልኮት ጥናንት እስኪብራራ እና በመጽሐፍ ቅዱሳዊ መንገድ እስኪረጋገጥ ድረስ ፤ ከእላይ እንደ አልነው ሕዝብን በእጅጉ አከፋፍሎ ብዙ ጉዳዮችን አስከትሏል።

ከመጽሐፍ ቅዱሱ ማብራሪያ ውጭ በአመክንዮ ደረጃ ፤ እግዚአብሔር ኹሉን ቻይ ነው ወይንም የእሚሳነው ነገር የለም ከአልን ፤ እግዚአብሔር እንዴት አንድም ሦሥትም ይሆናል የእሚለው ጥያቄ ብዙም ቦታ የአለው አይሆንም ፤ ምክንያቱም ፦ እግዚአብሔር እግዚአብሔር ከሆነ እና ኹሉንም ማደረግ የእሚችል ከሆነ ፤ አንድም ሦሥትም መሆን ይችላል።

እግዚአብሔር አንድም ሦሥትም ሊሆን ይችላል ብቻ ሰአይሆን ፤ ኹሉን ቻይ ከሆነ ፤ አምላክ ሆኖ ሳለ ሰው ሆኖ መምጣት እና እንደ ሰው ኖሮ እንደ ሰው ሞቶ ፤ ሞትንም አሸንፎ መነሳትም ይችላል ፤ ኹሉን ቻይ እና የእሚሳነው ነገር የሌለው አምላክ ነውና።

ለእዚኽም ይመስላል ፦ ሐዋሪያው ጳውሎስ ፤ ሞቶ የቀረውን ወይንም ከሙታን የአልተነሳውን ኢየሱስ ከሙታን በእግዚአብሔር ኃይል በመነሳቱ እግዚአብሔር በአባቶቻችን መሲኽ እና አዳኝ እልክላችኋለው የተባለለት እርሱ ነው ብሎ በመስበክ ፤ እግዚአብሔር መሲኽ አድርጎ የላከውን ኢየሱስን ሰቅላችሁታል በእሚል እኛን በሕዝብ አስጠልተኸናል ብለው ፤ ፈሪሳዊያን በሮም ፍርድ ቤት ሲከሱት ፤ ከሞት በመነሳቱ መሲኽ መሆኑን መቀበል እና አለመቀበል ሌላ ነገር ነው ፤ ነገር ግን እናንተ ኹሉን በእሚችል አምላክ አማኝ የሆናችኹ ሰዎች ለምንድ ነው ፤ እግዚአብሔር ሙታንን ማስነሳት ይችላል የእሚለው አባባል እንግዳ የሆነባችኹ ? የአላቸው ፦

ሐዋሪያት ሥራ 26፡8

“እግዚአብሔር ሙታንን የእሚያስነሣ እንደ ሆነ ስለ ምን በእናንተ ዘንድ የእማይታመን ነገር ሆኖ ይቆጠራል።”

ሐዋሪያው ጳውሎስ በእዚኽ ክፍል እያለ የአለው ፤ ስለ መሲኹ የተነገረው ትንቢት በሙሉ በእርሱ ስለ ተፈጸመ ኢየሱስ መሲኹ ወይንም ክርስቶስ ነው ብሎ ለማመን ምን አልባት የተብራራ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንታኔ ወይንም ሰፋ ያለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የስነ መለኮት እውቀት ይፈልግ ይሆናል ፤ አንድ በእግዚአብሔር ኹሉን ቻይነት ለእሚያምን አማኝ ፤ እግዚአብሔር የሞተን ሰው ማስነሳት ይችላል የእሚለው አባባል ጥያቄ ሊፈጥርበት የእሚገባ ጉዳይ ግን ሊሆን አይገባም እያለ ነው።

በተለምዶ ሰው ይወለዳል ፣ ይኖራል ከእዛኽም ይሞታል ፤ አንድ ግዜ ከሞተ ፣ መሞቱንም ለማረጋገጥ ጎኑ በጦር ሲወጋ ምንም ምላሽ ሳይሰጥ ደም እና ውኃ ከፈሰሰ እና ሦሥት ቀን ከቆየ በኋላ ግን አቅሉን ስቶ ነው ፣ ተዳክሞ ነው ፣ ደንዝዞ ነው ፣ ወዘተ ፤ ሳይሆን ድብን ብሎ ሞቶ በመሆኑ ፤ ከእዚያኽ በኋላ ይነሳል የእሚባል ነገር የለም ። የእሚታወቀው የሰው ልጅ የሕይወት ታሪክ ይኽ ነው ፤ ነገር ግን አንድ በኹሉን ቻይ አምላክ አማኝ ፤ ከሞተ ሦሥት ቀን የሆነውን ስለ እዚኽም መሞቱ አጠራጣሪ የአል ሆነውን ሰው ያስነሳል የእሚለው ጥያቄ ሊሆንበት አይገባም ፤ ብሎ እየተከራከረ ነው ጳውሎስ።

ስለ እዚኽ ፤ የስነ መለኮቱን ወይንም የመጽሐፍ ቅዱሱን ትንታኔ ውስጥ ሳንገባ ፤ እግዚአብሔር ኹሉን ቻይ በመሆኑ ፤ አንድም ሦሥትም መሆን ይችላል ፣ ሰው ሆኖ መምጣት ይችላል ፣ ሰው ሆኖ ሞቶም ከሞት መነሳት ይችላል የእሚባለው አባባል ፤ እንደ ተቃርኖ እና የእማይቻል መታየት የለበትም።

ኃይማኖት ማለትም ከተፈጥሮ በላይ የሆነ እና በተፈጥሮ ሕግ የእማይመራ ኃይልን ወይንም እግዚአብሔርን የማመን ጉዳይ ነው። እግዚአብሔር ሥላሤ ነው ፣ እግዚአብሔር ከሥላሤው አንዱን ፥ ወልድን ሰው ሆኖ ወደ ምድር እንዲመጣ እና በእግዚአብሔር ጸጋ ለሰው ኃጢያት እንዲሞት እና ሰውንም ከዘላለም ሞት እንዲያድን ሞትን አሸንፎ እንዲነሳ አድርጓል የእሚለው ፤ ኹሉን ቻዩ እግዚአብሔር ሊያደርገው የእሚችል እና በአመክንዮ ደረጃ እንዴት ሊያደርገው ይችላል ብለን እንድንጠራጠር ሊያደርገን የእሚገባ ጉዳይ አይደለም።

ከእዛኽም በአሻገር ፤ ግንዛቤያችንን ትንሽ ለመርዳት ፤ በእኔ እምነት ፤ አንዳንድ ሰዎች የሥላሤን ኃሳብ ለማሳየት የእሚጠቀሙበት ውኃ የእሚገኝበት ሦሥት የተለያየ ቅርጽ ፤ የሥላሤን ጽንሰኃሳብ በግሩም ኹኔታ የእሚገልጸው ይመስለኛል።

ውኃ ፥ በመላው ዓለም የእሚገኘው ውኃ እንደ አንድ ፦ በቅርጽ ደረጃ ፦ በትነትነት ፣ በፈሳሽነት ፣ በጠጣርነት ይገኛል ፤ ሆኖም በዓለም ላይ የአለው የውኃ አካል አንድ ነው። በትነት መልክ የአለው ውኃ በፈሳሽነት መልክ ወይንም በጠጣርነት (በርዶነት) ከአለው ውኃ ጋር አንድ ዓይነት ነው።

ስለ እዚኽ ውኃ አንድ ነው ፤ ነገር ግን ሦሥትም ነው። በሦሥትነቱ አንድነት አለው ፤ በአንድነቱም ሦሥትነት አለው።

እያንዳንዳቸው ውኃ የእሚገኝባቸው ሦሥቱም ቅርጾች የእራሳቸው ልዩ ጠባይ የአላቸው ሲሆን ፤ በአንድ ግዜም ውኃው በአንዱ ቦታ በፈሳሽነት ፣ በሌላው ቦታ በጠጣርነት ወይንም በበረዶነት እንደገና በሌላው ቦታ በትነት መልክ ይገኛል ፤ አንዳንዴም በአንድ ቦታ በሦሥቱም ቅርጽ ሊገኝ ይችላል ፤ ይኽ አንድም ሦሥትም ሦሥትም አንድም የሆነ ውኃ ግን ፤ በይዘት ወይንም በፍጥረት ደረጃ ሦሥቱም አንዱ ያው ኹለት ሀይድሮጅን እና አንድ ኦክሲጅን የሆነው (H2O) የውኃ ሞለኪውል ነው።

ኹሉን ቻይ አምላክ የፈጠረው እና በአይናችን የእምናየው እና በእጃችን የእምንዳስሰው ውኃ ይኽን መሆን ከቻለ ፤ ውኃን ራሱ የፈጠረ የእማይታየው ኹሉን ቻዩ አምላክ ፤ በአንድነት ሦሥትነት ፣ በሦሥትነት አንድነት የመኖሩ ጉዳይ ብዙም ሊያከራክር አይገባውም በአመክንዮ (Logic) ደረጃ።

የሥላሤን አስተምህሮ ትልቅ ታሪክ ወሳኝ ኃሳብ የአደረገው ግን ይኽን መሰሉ አመክንዮዋዊ ክርክር ሰአይሆን ፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወይንም ስነመለኮታዊው የሥላሤ ትንታኔም ነው።

ይኽም ማለት ፤ መጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር አንድ ብቻ እንደ ሆነ ደጋግሞ በእሚያስረግጥበት መጠን እና ጥልቀት እግዚአብሔር ራሱን በአብ ፣ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስብዕና ውስጥ የእሚገልጥ በመሆኑ እና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአለውን የክርስትና አስተምሕሮ እግዚአብሔር ራሱን እንደ አንድ አምላክ እና በሥላሤነት እንደ አብ ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ከገለጸበት አንጻር ውጭ ማቅረብ የእማይቻል በመሆኑ ነው።

ይኽም ማለት አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ አማኝ የእግዚአብሔርን አንድነት እና ሥላሤነት በእኩልነት ከአልተቀበለ በመጽሐፍ ቅዱስ አማኝ ሊሆን አይችልም ማለት ነው።

እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱሱ ውስጥ ፤ ራሱን በሥላሤነት የገለጸበት ብዙ ክፍል ማንሳት ይቻላል ፦

እግዚአብሔር አብን እና እግዚአብሔር ወልድ አንድ ስለመሆናቸው ፦

    • ዮሐንስ 1፡1 “በመጀመሪያ ቃል ነበረ ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።”
    • ዮሐንስ 14፡8-11 “ፊልጶስ - ጌታ ሆይ ፥ አብን አሳየንና ይበቃናል አለው። ኢየሱስም አለው ፦ አንተ ፊልጶስ ፥ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል ፤ እንዴትስ አንተ ፦ አብን አሳየን ትላለህ? እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የእምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም ፤ ነገር ግን በእኔ የእሚኖረው አብ እራሱ ሥራውን ይሠራል።”
    • ዮሐንስ 17፡20-21 “ኹሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ ፥ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለ እሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነ እዚኽ ብቻ አልለምንም ፤ አንተ እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ ፥ አንተ ፥ አባት ሆይ ፥ በእኔ እንደ አለህ እኔም በአንተ ፥ እነርሱ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ። እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ ፥ …”
    • ኤፌሶን 6፡23 “ከእግዚአብሔር አብ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምና ፍቅር ከእምነት ጋር ለወንድሞች ይኹን።”
  • እግዚአብሔር አብ ፣ እግዚአብሔር ወልድ እና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የእማይጋጭ መስተጋብር እንደ አላቸው ፦
    • ዮሐንስ 15፡26 “ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የእምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የእሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል።”
    • ዮሐንስ 16፡13 “ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ኹሉ ይመራችኋል ፤ የእሚሰማውን ኹሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይናግርምና ፤ የእሚመጣውን ይነግራችኋል። እርሱ ያከብረኛል ፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና። ለአብ የአለው ኹሉ የእኔ ነው ፤ ስለ እዚኽ ፦ ለእኔ ከአለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልኹ።”
    • ኤፌሶን 2፡18 “በእርሱ ሥራ (በኢየሱስ) ኹላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና።”
    • 2 ቆሮንጦስ 13፡14 “የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔር ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከኹላችሁ ጋር ይኹን። አሜን።”
  • እግዚአብሔር አብ ፣ እግዚአብሔር ወልድ ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድ ስለ መሆናቸው ፦
    • ማቴዎስ 28፡19,20 “ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው ፦ …እንግዲኽ ኺዱና አሕዛብን ኹሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኹ ፥ ያዘዙኋችኹንም ኹሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው ፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ኹል ግዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።”
  • ወልድ ወይንም ሰው የመጣው ኢየሱስ አምላክ እና ጌታ ስለመሆኑ ፦
    • ዮሐንስ 20፡28 “ቶማስም ፦ ጌታዬ አምላኬም ብሎ መለሰለት። ኢየሱስም ፦ ስለ አየኸኝ አምነኃል ፤ ሳያዩ የእሚያምኑ ብፁዓን ናቸው አለው።”
    • ዮሐንስ 13፡13 “እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ ፤ እንዲኹ ነኝና መልካም ትላላችሁ።”
    • ፊልጵስዮስ 2፡6 “እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደ እሚገባ ነገር አልቆጠረውም ፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረግ ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። … ይኽም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ኹሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ ፥ መላስም ኹሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰከር ዘንድ ነው።
    • ቆላስያስ 2፡9 “በእርሱ የመለኮት ሙላት ኹሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና።”
    • ዕብራዊያን 1፡4-12 “ከመላእክት ይልቅ እጅግ የእሚበልጥ ስምን በወረሰ መጠን እንዲኹ ከእነርሱ አብዝቶ ይበልጣል። ከመላእክትስ ፦ አንተ ልጄ ነህ ፥ እኔ ዛሬ ወልጄኃለኹ ፥ ደግሞም ፦ እኔ አባት እሆነዋለኹ እርሱም ልጅ ይሆነኛል የአለው ከቶ ለማን ነው? ደግሞም በኩርን ወደ ዓለም ሲያገባ ፦ የእግዚአብሔር መላዕክት ኹሉም ለእርሱ ይስገዱ ይላል። ስለ መላእክትም ፦ መላእክቱን መናፍስት አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የእሚያደርግ ይላል ፤ ስለ ልጁ ግን ፦ አምላክ ሆይ ፥ ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል ፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው። …ደግሞም ፦ ጌታ ሆይ ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትኽ ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው ፤ እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ ፤ ኹሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ ፥ እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጡማል ፤ አንተ ግን አንተ ነህ ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም ይላል።”

እነ እዚኽ ለማሳያነት ከአዲስ ኪዳን ብቻ ተወስደው ቀረቡ እንጂ ፤ ብሉይ ኪዳንም ሆነ አዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ራሱን በአንድነት ሦሥትነት ፤ በሦሥትነት አንድነት የገለጸበት አግባብ በስፋት የእሚስተዋልበት ነው።

ይኽም የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር በአንድነት ሦሥትነት እና በሦሥትነ አንድነት ራሱን የገለጸበት አግባብ ፤ በልማዳዊው የዓምልኮ ስረዓት የዓማልክት ስብስብ ወይንም አንድ ዓምላክ በእሚል የተለመደውን አስተሳሰብ ስለ ተቃረነ ፤ ይኽ ልዩ ክርስቲያናዊ መልዕክት የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃናትን ይኽን ኹኔታ በአግባቡ እና የእሚግባቡበት ትርጓሜ ገለጻ እንዲያስቀምጡ ግድ ስለ አላቸው ፤ ብዙ ታሪካዊ ሚና የአለውን የሥላሤ አስተምህሮ አስከተለ።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአለውን የሥላሤ አስተምህሮ በስህተት ተርጉሞ ፤ የመጀመሪያው ኃሰተኛ አስተማሪ ተብሎ ፤ በወቅቱ በነበረው ዓለም ዓቀፋዊ የክርስትና ሊህቃን መማክርት የተወገዘው ሰው ፤ በአማርኛ አርዮስ ተብሎ የእምናውቀው አሪየስ ነው።

ከእዚያኽ ግዜ አንስቶም ነው ኦርቶዶክስ (Orthodox) የእሚለው ስያሜ የመጣው ። ዓለም ዓቀፋዊው የክርስትና ሊህቃን መማክርት ትክክል ነው የእሚለው አስተምህሮ የእሚቀበሉት ኦርቶዶክስ ሲባሉ ፤ በዓለም ዓቀፋዊው የክርስትና ሊህቃን መማክርት ስህተት ነው ተብሎ የተወገዘውን አስተምህሮ የእማይቀበሉ ደግሞ ኃሰተኞች ወይንም ንፉቅ (Heretic) ተባሉ።

አርዮስ ምንም እንኳን አብ ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ፤ በመጽሐፍ ቅዱሱ ውስጥ በአግባቡ መገለጣቸውን ቢቀበልም ፤ በሥላሤ ውስጥ ተዋረድ (Subordination) አለ በእሚል ፤ እግዚአብሔር አብ የኹሉም ራስ የሆነ ዋናው አምላክ ሲሆን ፤ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ግን በዋናው አምላክ ፥ አብ ፤ የተፈጠሩ አናሳ እና አጋዥ አማልክት ናቸው የእሚል አስተመህሮ ይዞ መጣ።

ይኽም እግዚአብሔርን አንድነት የአለው ሦሥትነት ፤ ሦሥትነት የአለው አንድነት ሳይሆን ፤ አንድነት የሌለው ሦሥትነት ወይንም ብዙ አማልክት ከማድረጉም በላይ ወልድን (ኢየሱስን) እና መንፈስ ቅዱስን ፤ ከአብ ዝቅ በማድረግ እና ፍጡራን ወደ መሆን ዝቅ ስለ አደረጋቸው ፤ እ.አ.አ. በ325 ዓ.ም ፤ ኒስያ (Nicaea) በእምትባለው እና በዛሬዋ ቱርክ ውስጥ በእምትገኝ ከተማ በኢምፐረር ቆንስጠንጢን ጠሪነት የተሰበሰበው የወቅቱ የዓለም የቤተክርስቲያን ሊቃውንት በተሰበሰቡበት ጉባኤ ፤ የአርዮስ አስተምህሮ ንፋቄ ነው ተብሎ ተወገዘ።

የኒስያው ጉባኤም የአርዮስን አስተምህሮ ኑፋቄ ብሎ ከአወገዘ በኋላ ፤ ኦርቶዶክሳዊ የሆነው የሥላሤ አገላለጽ ይኽ ነው ብሎ ፤ የእሚከተለውን እና እስከ ዛሬ ድርስ ፤ በሮማ ፣ በምሥራቅ ክርስቲያኖች እና በአንግሊካኖች የእሚታመንበትን ከእዚኽ በታች የአለውን የእምነት መግለጫ አወጣ ፦

“ኹሉን ቻይ በሆነው ፤ ሰማይንና ምድርን እንዲኹም የእሚታየውንም ሆነ የእማይታየውንም ኹሉ ነገር በፈጠረው ፤ በአንድ አምላክ አብ አምናለኹ።

ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ከእግዚአብሔር አብ በተወለደው የእግዚአብሔር ብቸኛ ልጅ ፤ በአንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አምናለኹ። አምላከ አምላክ ፣ ብርኃነ ብርኃን ፣ በእውነት አምላክ ፣ የተወለደ እንጂ የአልተፈጠረ ፤ ከአብ ጋር አንድ ዓይነት ይዘት በአለው ፤ ኹሉ በእርሱ በሆነው ፤ ለእኛ ለሰዎች እና ለመዳናችን ሲል ፤ ከሰማይ በወረደ ፤ ከድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ስጋን ለብሶ በተወለደ እና ሰው በተደረገ (በሆነ) ፤ በጴንጢናዊው ጲላጦስ ለእኛ ሲል በተሰቀለ ፤ በመስቀል መከራን በተቀበለ እና በተቀበረ ፣ በሦሥተኛውም ቀን እንደ ገና በተነሳ ፤ እንደ ቃሉም ወደ ሰማይ በአረገ እና በአብ ቀኝ በተቀመጠ ፤ በክብርም ዳግም ተመልሶ በእሚመጣ ፤ በሕያዋን እና በሙታን ሊፈርድ በአለው እና ለመንግሥቱም ፍጻሜ በሌለው አምናለኹ።

በመንፈስ ቅዱስ ፤ ጌታ እና ሕይወት ሰጪ ፤ ከአብ እና ከወልድ በእሚወጣ ፤ ከአብ እና ከወልድ ጋር እኩል በእሚመለክ እና በእሚከበር ፤ በነብያቱ ውስጥ አድሮ በተናገረ አምናለኹ።

በአንዷ ቅድስት ካቶሊክ (ዓለም ዓቀፍ) እና ኃዋሪያዊት ቤተክርስቲያን አምናለኹ። ከኃጢያት ለመንጻት ፣ ከሙታን ትንሳኤን ለማግኘት እና የእሚመጣው ዓለም ተካፋይ ለመሆን ፤ አንዲት ጥምቀትን እቀበላለኹ። አሜን።”

“I believe in one God the Father Almighty; Maker of heaven and earth, and of all things visible and invisible.

And in one Lord Jesus Christ, the only-begotten Son of God, begotten of the Father before all the worlds. God of God, Light of Light, very God of very God, begotten, not made, being of one substance with the Father; by whom all things were made; who, for us men and for our salvation, came down from heaven, and was incarnate by the Holy Ghost of the Virgin Mary, and was made man; and was crucified also for us under Pontius Pilate; he suffered and was buried, and the third day he rose again, according to the Scriptures; and ascended into heaven, and sitteth on the right of the Father; and he shall come again, with glory, to judge both the quick and the dead; whose kingdom shall have no end.

And I believe in the Holy Ghost, the Lord and Giver of Life; who proceedeth from the Father and the Son; who with the Father and the Son together is worshiped and glorified; who spake by the Prohets. And I believe in the one Holy Catholic and Apostolic Church. I acknowledge one Baptism for the remission of sins; and I look for the resurrection of the dead, and the life of the world to come. Amen. [8]”

ይኽ ከእላይ የአለውን የኔሲያውን ጉባኤ የእምነት መግለጫ ያስከተለው የአርዮስ የኢየሱስ ፍጥረት ነው ትምህርት ፤ ቤርሙዴዝ የእሚባለው ፖርቹጋላዊ አጼ ገላውዴውስን እንደ መንፈሳዊ አባት ሆኖ ፤ የሮማውን ጳጳስ የበላይነት ተቀበል ሲለው ፤ አንተ አራት አምላክ አለ የእሚል አርዮሳዊ በመሆንህ ፤ አንተ የፍራንኮቹ መንፈሳዊ አባት ነህ እንጂ የእኔ መንፈሳዊ አባት አይደለኽም የአለውም ። ገላውዴዎስ ይኽንን የአለው ቤርሙዴዝ ይኽንን የአርዮስን የሥላሤ አስተምህሮ የእሚከተል ስለ መሰለው ነው፦

“…እንዲኽ ብዬ ለአቀረብኩለት ግብዣም ፤ እንደ ልጅነቱ መጠን ምን እየመለሰ እንደ ሆነ ሳያገናዝብ ፦ አንተ የእኛ መንፈሳዊ አባት አይደለህም ፥ የአንተ አባትነት ለፍራንኮች ነው ፤ አሪያናዊ (የአርዮስ ተከታይ) በመሆንህ እና አራት አምላክ አለ ብለህ የእምታምን በመሆንህ ከእዚኽ በኋላ እኔ የአንተ መንፈሳዊ አባት ነኝ ስትል እንዳልሰማህ ፤ ብሎ መለስለኝ ። እኔም መለስ ብዬ ፤ ሀሰት ተናገርኽ እኔ አሪያናዊ አይደለኹም ፤ አራትም አምላክ የለኝም ፤ ለቅዱሱ አባት አልታዘዝም እያለ ስለ ሆነ ምንም ማድረግ አልችልም ፤ ልረግመው እና ላወግዘው እንደ ሆነ እና ከእዚኽ በኋላ እርሱን ለመመለስም ሆነ በሌላ ጉዳይ ላናግረው እንደ እማልፈልግ ነገርኹት እና ለመኼድ ስነሳ ፤ እንደ እዚኽ አለኝ አንተው ራስኽ ትወገዛለኽ እንጂ እኔ አልወገዝም አለኝ ።”

To which he, not considering what he was saying, like a young boy, replied as follows: “ You are not our father, nor a prelate, but Patriarch of the Franks, and you are an Arian, for you have four Gods, and you are not in future to call yourself my father.” I turned and told him he lied, for I was not an Arian, and had not four Gods; and that as he would not obey the Holy Father, I held him to be excommunicate, and accursed; and that I would no longer be with him, or speak to him; and with that I got up to go. He replied that I was excommunicated, not he [113]“

በእርግጥ አጼ ገላውዴዎስ ቤርሙዴዝን ምን አልባት በስህተት ሊሆን ይችላል ፤ አንተ የአርዮስ ተከታይ በመሆንህ አራት አምላክ አለ ብለህ የእምታምን በመሆንህ አንተ የፍራንኮች የነፍስ አባት ነህ እንጂ የእኛ የኢትዮጲያዊያን የነፍስ አባት አይደለህም የአለው ፤ ምክንያቱም ፦ የእዛን ወቅቱ የሮማው ካቶሊክ ቤተክርስቲያን እንደ ኢትዮጲያው ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የአርዮስን ትምህርት ኑፋቄ መሆኑን የእሚቀበል በመሆኑ።

ምን አልባት ግን ገላውዴዎስ ፤ በአርዮስ ቀኖና ምክንያት የኢትዮጲያ ነገሥታት ፤ በተለይ ኢዛና ከሮማን ኢምፐረር ቆንስጣንጢኖስ ጋር የገባው ንትርክ በታሪክ እውቀት ደረጃ የእሚያውቀው ከሆነ ፤ ሮማዊያን አርያናዊን ናቸው የእሚለውን እምነት ከእዚኽ ታሪካዊ እውቀቱ የመጣ ሊሆን ይችላል።

ስትዋርት ሙኑሮ ኼይ ፤ ዳግማዊ ቆንስጣንጢኖስ ለኢዛና ፤ ፍሬምናጦስ (የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መሥራች እና የመጀመሪያው ጳጳስ) የአርዮስን ትምህርት እንዲቀበል ወደ እኛ ላከው የእሚል ደብዳቤ እንደ ጻፈለት ይነግረናል ፦

“እ.አ.አ. 356 ዓ.ም. ዳግማዊ ኢምፐረር ቆስጠንጢኖስ ከእርሱ ጋር አብሮ የኑፋቄው የአርዮስ አስተምህሮ ተከታይ ሆኖ ፤ በእርሱ የአሌክሳንደሪያ ጳጳስ ተደርጎ ወደ ተሾመው የካውፖውዲሺያው ኢጲስቆጶስ ጆርጅ ጋር ፤ ፍሬምናጦስ ለቀኖና ምርመራ እንዲልከው የእሚጠይቅ ደብዳቤ ጻፈለት። እንደ እዚኽ በአለው የቸርች ፖለቲካ ፤ አክሱም ፥ አሌክሳንደሪያ መጀመሪያ የያዘችውን አቋም በማጽናት ፤ የቆስጠንጢኖስን ማሻሻያ ለመቀበል እምቢ ያለች ይመስላል። እ.አ.አ. 451 ዓ.ም. ከተካኼደው የካሊሲዱኑ ጉባኤ በኋላ ፤ ዓለም ዓቀፏ (ካቶሊክ) ቤተክርስቲያን ስትከፈል ፤ አክሱም ከግብጽ እና ከአብዛኛው ምሥራቃዊያን ጋር በመሆን መልከኞቹ ወይንም ዘውዳዊዋ ቤተክርስቲያን ከእምትባለው ተለይተው ፤ ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ድረስ የእምትከተለውን በክርስቶስ ስጋወ ሚስጥር ላይ የያዘችውን የተዋሕዶን እምነት ፤ በመያዝ ተለዩ።”

“In about 356AD the emperor Constantius II wrote to Ezana trying to persuade him to submit Frumentius to doctrinal examination by his own appointee to Alexandria, the bishop George of Cappadocia, who, with the emperor, subscribed to the Arian heresy. In such matter of church politics, Aksum seems to have followed Alexandria’s lead, and refused to adopt Constantius’ proposed changes. After the Council of Chalcedon in 451 the international church was divided, and Aksum, with Egypt and much of the east, split from the so-called melkite or imperial church and followed the Monophysite interpretation of Christ’s nature which Ethiopia still retains. [86]”

ይኽን መሰል መልክ የነብረው የአርዮስ አስተምህሮ ፤ ከእላይ እንደ አየነው በኒሲያው ጉባኤ ቢወገዝም ፤ ዳግም ተምልሶ አንሰራርቶ ፤ የኒሲያውን ጉባኤ ከጠራው ከቆስጦንጦን ጀምሮ ከእርሱ በኋላ የመጡ ሦሥት ተከታታይ ኢምፐረሮች እንደ ትክክለኛው የሥላሤ ትምህርት ተቀብለውት ፤ የአርዮስን የሥላሤ አስተምህሮ ወይንም የኒስያውን የእምነት አዋጅ አንለቅም ያሉ ክርስቲያኖችን ሲያሳድዱ ነበር።

የአሌክሳንደሪያ ጳጳስ በመሆኑ የኢትዮጵያ ጳጳስ የሆነው እና የኒስያው የእምነት አዋጅን በማጽደቅ እና በማስረጽ ትልቅ ስፍራ የነበረው አትናሲያስ ፤ የኒስያውን የእምነት አዋጅ አልክድም ወይንም የአርዮስ የሥላሤ አስተምህሮ አልቀበልም በማለቱ ፤ 48 ዓመት በቆየው የጵጵስና ዘመኑ ፤ በአራት የሮም ኢምፕረሮች አምስት ግዜ እና በድምሩ ለ17 ዓመታት ለቆዩ ግዜያት የተጋዘ እና 6 ግዜ የሞት ግድያን ሴራ ሽሽት ከአሌክሳንደሪያ ያመለጠ ጳጳስ አድርጓታል።

ማለትም ፦ ምንም እንኳን ቆስጠንጢን እራሱ በጠራው ጉባኤ የተሰበሰበው የወቅቱ የዓለም ዓቀፍ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ጉባኤ ፤ አርዮስን ቢያወግዘውም ፤ አርዮስ እና ተከታዮቹ በአላቸው ፖለቲካዊ ቅርበት ፤ የሮም ኢምፕረሮችን ጆሮ አግኝተው ራሳቸውን ከኃይማኖታዊው ጉባኤው ውጭ በፖለቲካ ኅይል የኃማኖቱን መንበር ተቆናጠው ፤ የኒሲያው አዋጅ ተከታዮችን ቢያንስ ለ50 ዓመታት በውሸት ክስ ሲያሳስሩ ፣ ሲያሰድዱ ነበር።

አትናሲያስም የኦርቶዶክስነት አባት የተባለው እና በላቲን “አትናሲያስ ከዓለም ጋር በፀብ ላይ or Athanasias against the world” የእሚል የክብር ስም የተሰጠው ፤ በከፍተኛ ፖለቲካዊ ስደት ውስጥ ኦርቶዶክሳዊ ኃይማኖታዊ እምነቱን ለ48 ዓመት ይዞ በመጽናቱ ነው።

አትናስያስ ከኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋር በልዩ ኹኔታ ስለ እሚዛመድ እና ሮማዊያኖች ወይንም የሮም ኢምፐረሮች አርያናዊ የሆነበት ዘመን በመኖሩ ፤ ገላውዴውስ ይኽንን በታሪክ የእሚያውቀው ከሆነ ፤ ቤርሙዴዝን አንተ አርያናዊ ነኽ ሲለው ፤ ምን አልባት ይኽ ታሪካዊ እውቀቱ የተሳሳተ ተጽኖ ፈጥሮበት ይሆናል።

የአርዮሱ ኢየሱስ አናሳ አምላክ እና የዋናው አምላክ የአብ ፍጡር እና አጋዥ እንጂ ከአብ ጋር እኩል የሆነ አምላክ አይደለም የእሚለው አስተምህሮ የኒሲያውን ጉባኤ ለማስጠራት እና የኒስያውን ጉባኤ አዋጅ ከአስከተለ በኋላ ወይንም ትክክለኛ የእሚባለውን የሥላሤ ቀኖና (The Orthodoxy) ከአመጣ በኋላ ፤ ይኽ አስተምህሮ በራሱ ፤ ሌሎች ተከታይ ጥያቄዎችን የአስነሳ ሆነ ፦

  • የኢየሱስ ሰውነት እና አምላክነት በምን ዓይነት አግባብ ነው በኢየሱስ ውስጥ ተዋደው ያሉት?
  • ኢየሱስ አምላክ ከሆነ በሰው ውስጥ (በማሪያም ውስጥ) እንዴት ሊጸነስ ቻለ ?

በአጭሩ በክርስትናው ስነ መለኮት ውስጥ ስነክርስቶስ (Christology) እና ስነማሪያም (Mariology) የእሚባሉትን አስተመህሮዎች አስከተለ።

በእዚኽ ረገድ ሦሥት ኦርቶዶክሳዊ የአልሆኑ አስተምህሮዎች ተነስተው ፤ እ.አ.አ. በ381 ፣ 431 እና በ451 ዓ.ም. በኮንስታንቲኖፖል ፣ በኤፌሶን እና በካልሲዱን ከተማ በተካኼዱ የዓለም ዓቀፍ ቤተክርስቲያን ጉባኤ ፤ ልክ እንደ ኒስያኑ ጉባኤ ፤ የስህተት ወይንም የኑፋቄ ትምህርቶቹን የእሚያወግዙ የእምነት መግለጫዎች በማውጣት ተጠናቀዋል።

የተነሱት የስህተት ወይንም የኑፋቄ አስተምህሮዎች ፤ በአፖሊናሪስ ፣ በኔስቶሪየስ እና በኢቲክየስ ወይንም አውጣኬ የቀረቡ ሲሆን ፤ የንፋቄ ትምህርቶቹ እና የዓለም ዓቀፍ ቤተክርስቲያን ተወካይ የሆኑ ሊቃውንት የአቀረቡዋቸው ውግዘቶች ጠቅለል በአለ መልኩ ከእዚኽ በታች የአሉት ናቸው ፦

  1. አፖሊናሪስ ወይንም አፖሊናሪዮስ (Apollinaris or Apolinarios) - ክርስቶስ የሰው አካል ፣ እንደ ሰው ስሜታዊ ነፍስ ኖሮት ፤ እንደ ሰው ዓይነት አመዛዛኝ አዕምሮ ሳይሆን ቃሉ ወይንም በግሪኩ ሎጎሱ አዕምሮውን የተካበት ኹኔታ ነው ፤ ፍጹም ሰው እና ፍጹም አምላክነቱ በእርሱ ውስጥ ተዋህደው የእሚገኙበት አግባብ ነው አለ።

አፖሊናሪስ የግሪክ ፈላስፋው ፕሌቶ ፤ የሰው ልጅ አካል ፣ ነፍስ (ስሜት) አና መንፈስ (አዕምሮ) አለው የአለበትን አግባብ ተከትሎ ፤ የኢየሱስ አካል እና ነፍስ(ስሜት) የሰው ሲሆን ፤ መንፈሱ ወይንም አዕምሮው ነው አምላክ ወይንም ሎጎሱ (ቃሉ) የሆነው ፤ እንደ አለ ነው ፤ ስነ መለኮቱ የእሚለው።

ይኽንንም የስነክርስቶስ ወይንም ምስጢረ ስጋ ለማስረዳት ፤ አፖሊናሪስ ስነቃል እና ስነልቦናዊ ትንታኔ እንደ አቀረበ ይነገራል።

በስነ ቃሉ ተምሳሌትነት ፤ ከኹለት ቃላት ተዋሕደው የእሚፈጠሩ ቃላት ፤ ለምሳሌ ፦ ቤተ + መጽሐፍት = ቤተመጽሐፍት በእሚፈጠሩበት አግባብ ነው ፤ የኢየሱስ ሰውነት (ሰብዓዊነት) እና አምላክነት የተወኃዱት ፤ እንደ እዛ ከአልሆነ ኹለት የእየራሳቸው ልዩ ጠባይ ወይንም ባሕሪ የአላቸው ነገራት ሊዋኃዱ አይችሉም ፤ በእሚል።

በስነልቦናዊውስ ተምሳሌትነት ፦ ፕሌቶ በስነ ምግባር አስተምህሮው ፤ ሰው = አካል + ነፍስ (ስሜት) + መንፈስት (አዕምሮ) የአለው ሆኖ ፤ አዕምሮ ሲበስል ነው ስሜታዊነቱን ገርቶ ሰውን የእሚያጎለብተው የእሚለውን ተከትሎ ፤ የክርስቶስ አዕምሮ ፤ ፍጹም የሆነው አምላካዊው አዕምሮ ከአልሆነ ወይንም ሰዋዊው አዕምሮ በአምላካዊው አዕምሮ (ቃሉ ወይንም ሎጎሱ) ከአልተተካ በስተቀር ፤ ከኃጢያት የነጻ ሕይወት ሊኖር አይችልም ነበር አለ።

እ.አ.አ. 381 ዓ.ም. በኮንስታንቲኖፖል የተሰበሰው የአብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ይኽን የአፖሊናሪስ አስተምህሮ የኢየሱስን ፍጹም ሰውነት የእሚቃረን ነው በእሚል ኑፋቄ (Heresy) ነው ብሎ አወገዘው።

መንፈሱ ወይንም አዕምሮው ሰው ያልሆነ ሰው ፤ ሙሉ ወይንም ፍጹም ሰው ሊባል የእማይችል በመሆኑ ፤ የኢየሱስ አዕምሮ የሰው አይደለም የአምላክ ነው ማለት ፤ ኢየሱስ ፍጹም ሰው አይደለም እንደ ማለት በመሆኑ ነው ይኽ የአፖሊናሪስ አስተምህሮ ስሁት ወይንም ኑፋቄ የተባለው። ምክንያቱም ፦ የክርስቶስን ፍጹም ሰውነት እና ፍጹም አምላክነት አለመቀበል ፤ ከመጽሐፍ ቅዱሱ አንጻር ስህተት በመሆኑ።

ለአፖሊናሪስ የስነክርስቶስ መላምት መቃወሚያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከአሉ ጥቅሶች አንዱ ይኽ ነው ፦

ሉቃስ 2፡52 “ኢየሱስም ደግሞ በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር።”

በጥበብ ያድግ ነበር ካለ ፤ አፖሊናሪስ እንደ እሚለው የኢየሱስ አዕምሮ የሰው አዕምሮ ሰአይሆን የአምላክ አዕምሮ ወይንም ሎጎስ ነበር ማለት አይቻልም ማለት ነው። ስለ እዚኽ ኢየሱስ ፤ ከኃጢያት ንጹ ቢሆንም ፤ በሰውነቱ ፍጹም ወይንም ሙሉ ፤ በአካል ፣ በስሜት እና በአዕምሮ ሰው ነበር ማለት ነው ፤ ልክ ፍጹም አምላክ እንደ ሆነው።

  1. ኔስቶርየስ (Nestorius) - እንደ ኔስቶርየስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው እና ፍጹም አምላክ ወይንም ሙሉ በሙሉ ሰው እና ሙሉ በሙሉ አምላክ ሆኖ ፤ እነ እዚኽ ኹለት የኢየሱስ ክርስቶስ ማንነቶች ሕብር (Harmony) ኖራቿቸው በጋራ የእሚንቀሳቀሱ (Synchronized) የአደረጉ ሰአይሆን ፤ እንደ ትዳር አይነት የኹለት ሰዎች ጥምረት ነው።

እንደ ኔስቶሪየስ ፦ ኢየሱስ ክርስቶስ ፤ ፍጹም ሰው እና ፍጹም አምላክ ተፈጥሮ የያዘ አንድ ስብዕና ሰአይሆን የአለው ፤ እንደ ሰዋዊው እና እንደ አምላካዊው ተፈጥሮው እንደ እዛው ኹለት ስብዕና የአለው ነው።

ከእዚኽም የተነሳ ኢየሱስ ፤ ኹለት የተለያየ ተፈጥሮ የአላቸው ፤ ኹለተ የተለያዩ ስብዕናዎች የአለው በመሆኑ ፤ እነ እዚኽ ኹለት የተለያየ ተፈጥሮዎች እና ስብዕናዎች ፤ ልክ በትዳር እንደ ተጣመሩ ሰዎች ፤ አብረው ለመኖር የተስማሙ እና በእየ ባሕሪያቸው እና እንደ አመቺነቱ ራሳቸውን የእሚገልጹ ናቸው።

ይኽም በመሆኑ ፤ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሲሞት ፤ መከራውን የተቀበለው እና የሞተው ፤ ሰዋዊው የሆነው ኢየሱስ ነው እንጂ አምላክ የሆነው ኢየሱስ አይደለም ፤ ምክንያቱም ፦ አምላክን መከራ ሊነካው ስለ እማይችል።

ኢየሱስ ተዓምር ሲያደርግ ተዓምር የእሚያደርገው ስጋን ለብሶ የመጣው የሰው ልጁ ኢየሱስ ሳይሆን ፤ መለኮት የሆነው ኢየሱስ ነው።

ይኽም በመሆኑ ፤ ማርያምን ወላዲት አምላክ ልንላት አይገባም ፤ ምክንያቱም ማሪያም ሰው በመሆኗ አምላክን ልተሸከም አትችልም ፤ ማሪያም ጸንሳ የወለደችው ሰው የሆነውን የኢየሱስን ክፍል ነው አለ።

እንደ እዛ ከአልሆነ እንደ ኔስቶሪየስ ፦

“እንዲኽ ብሎ ሞገተ ፤ ማሪያምን “የአምላክ እናት ወይንም ወላዲትአምላክ” ማለት መለኮት ከሴት መወለድ ይችላል እንደ ማለት ወይንም እግዚአብሔር የሦሥት ቀን እድሜ ሊኖረው ይችላል እንደ ማለት ነው።”

“He insisted that calling Mary “Mother of God” was tantamount to declaring that the divine nature could be born of a woman, or that God could be three days old. [8]”

የኔስቶሪያን አስተሳሰብ ተከትሎ ማርያም ወላዲት አምላክ አይደለችም ከተባለ ፤ ኢየሱስ ሰው ሆኖ ከተወለደ በኋላ ፤ አምላካዊው ማንነቱ ከውልደቱ በኋላ ነው የተዋኃደው የእሚል ድምዳሜ ግድ ይላል ፤ ይኽ ግን በመጽሐፍ ቅዱሱ መሠረት ስህተት ነው የእሚሆነው ፤ ምክንያቱም ፦ ኢየሱስ በማሪያም ውስጥ ከተፈጥሮዋዊ አሰራር ውጭ ወይንም ወንድ እና ሴት ሳይገናኙ ፤ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተጽንሶ እንደ እሚወለድ እና የእግዚአብሔር ልጅ (አምላክ) እንደ እሚሆን በግልጽ የተቀመጠ በመሆኑ።

ማቴዎስ 1፡18-23

“የኢየሱስ ክርስቶስም ልደት እንዲህ ነበረ። እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ግዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። … ከእርሷ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛኽን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ልጅም ትወልዳለች ፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። በነብይ ከጌታ ዘንድ ፦ እነሆ ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች ፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይኽ ኹሉ ሆኗል ፥ ትርጓሜውም ፦ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው።”

ሉቃስ 1፡30 – 35

“መልአኩም እንዲህ አላት፦ ማርያም ሆይ ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋን አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆም ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልዳለሽ ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል ፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል ፤ በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል ፥ ለመንግሥቱም መረጨረሻ የለውም። ማርያምም መልአኩን ፦ ወንድ ስለ እማላውቅ ይኽ እንዴት ይሆናል? አለችው። መልአኩም መልሶ እንዲኽ አላት ፦ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለ እዚኽ ደግሞ ከአንቺ የእሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።”

ማርያም ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ የሆነው ኢየሱስ እንደ ወለደች በመጽሐፍ ቅዱሱ መሠረት ግልጽ ነው ፤ የኢየሱስ ጽንሰቱም ውልደቱም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በመሆኑ ፤ ማርያም እንዴት መለኮትን ልትወልድ ቻለቸ ወይንም መጀመሪያ እና መጨረሻ የሌለው አምላክ እንዴት ይወለዳል ሊባል አይችልም ፤ ምክንያቱም ፦ ይኽ የሆነው በእግዚብሔር ኃይል የሆነ ተዓምር በመሆኑ።

ስለ እዚኽ ፦ የኔስቶሪየስ የስነክርስቶስ አስተሳሰብ ፦ ኢየሱስ ክርስቶስ ከጽንሰቱ ጀምሮ ሙሉ ሰው እና ሙሉ አምላክ ነበር ከእሚለው ወይንም አምላክ እራሱን አዋርዶ የባሪያን መልክ ያዘ ፤ በባሕሪውም ሰው ሆነ ከእሚለው ጋር ስለ እሚቃረን ፤ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ431 ዓ.ም. በኤፌሶን የተሰበሰበው የቤተክርስቲያን ሊቃናት ጉባኤ ፤ ኢየሱስ ፍጹም ሰው እና ፍጹም አምላክ ሆኖ የአለ፟ እና ይኽም ኹለት ተፈጥሮ በአንድ ስብዕና የእሚገኝ እንጂ ሰዋዊ እና አምላካዊ የተላዩ ስብዕናዎች የያዘ አይደለም ብሎ አስወገደው።

ማርያምም በእግዚአብሔር መንፈስ ኃይል ወይንም በጸለላት የእግዚአብሔር መንፈስ ፤ ሰው ለመሆን የመጣውን አምላክ ጸንሳ ወልዳለች ፤ ስለ እዚኽ ወላዲት አምላክ መሆን አለባት ፤ ማርያም ወላዲት አምላክ ከአልሆነች ወልድም የልዑል ልጅ ሊባል አይቻልም ፤ ምክንያቱም ፦ መጽሐፍ ፤ ከአንቺ የእሚወለደው የልዑል ልጅ ይባላል ስለ እሚል በግልጽ ።

  1. ኢቲክየስ(Eutyches) ወይንም በእኛ ሐገር አውጣኬ ፡ የእሚባለው ጳጳስ ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ፤ ልክ ማር በዉቂያኖስ ውስጥ ጠብ ሲል ሟሙቶ ከውኃው ሊለይ እንደ እማይችልበት አግባብ ፤ የኢየሱስ ሰውነት (ሰዋዊ ማንነት) እንደ ውቅያኖስ ግዙፍ ከሆነው አምላክነቱ ውስጥ ሲገባ ሟሙቶ ፤ አንድ አዲስ ውሕድ ማንነት ተፈጥሯል አለ።

ኢቲክየስ ወይንም አውጣኬስ የኢየሱስ ሰውነት በአምላክነቱ ተውጦ ጠፍቷል እና ኢየሱስ ሰው እና አምላክነት የተዋኃዱበት ፤ ከአምላክም ከሰውም የእሚለው አዲስ ውሕድ ነው የእሚል በመሆኑ ተወግዟል።

ይኽንን የኢቲክየስ ወይንም አውጣኬስ አስተምህሮ በካልሴዶን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ451 ዓ.ም. የተሰበሰበው የቤተክርሲያን ሊቃውንት ጉባኤ በእዚኽ መልኩ አወገዘው ፦

“ከኮንስታንቲኖፖል ብዙም በእማትርቀው በእዚኽች ከተማ ፤ ወደ 400 መቶ የእሚሆኑ ኢጲስቆጶሳት ተሰብስበው ... የእሚከተለውን አዲስ ትርጉም አስቀመጡ ፦

እኛ ኹላችን በአንድ ድምጽ ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ እና ተመሳሳይ መሆኑን ፤ በአምላክነት እና በሰውነቱ ሙሉዕ መሆኑን ፤ እውነተኛ አምላክ እና እውነተኛ ሰው ፤ … እነ እዚኽም ኹለት ፍጥረቶቹ ፤ ሳይቀላቀሉ ወይንም ሳይምታቱ ፣ ሳይለወጡ ፣ ሳይከፍሉ ፣ ሳይለያዩ ፤ የፍጥርቶቹ መለያየት በውህደቱ ሳይቀየር ፤ ነገር ግን የእያንዳንዱ ፍጥረት ይዘት እንደ ተጠበቀ ሆኖ በጋራ ግን አንድ ስብዕና መሆኑን እናውጃለን።”

“At this town not far from Constantinople, nearly four hundred bishops gathered … set forth a new definition:

We all with one voice confess our Lord Jesus Christ one and the same Son, at once complete in Godhead and complete in manhood, truly God and truly man, … acknowledged into two natures, without confusion, without change, without division, or without separation; the distinction of natures being in no way abolished because of the union, but rather the characteristic property of each nature being preserved and coming together to form one person. [8]”

ከኢትዮጲያ ፖለቲካ አንጻር ፤ የሥላሤ አስተምህሮ እና እርሱንም ተከትሎ የመጡት የስነክርስቶስ እና የስነማርያም ወይንም ምስጢረ ስጋዌ የእሚባሉት አስተምህሮቶችን በተመለከተ የእሚከተሉት ኹለት ጉዳዮች ወሳኝ ናቸው ፦

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፡

የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በግብጿ ቤተክርስቲያን ስር የነበረች በመሆኑ ፤ የካልሴዱኑን ጉባኤ የእምነት መግለጫ የእማትቀበል እና በእዚኽም አቋሟ ፤ በቁጥር ከእሚበዛው እና ዓለም ዓቀፋዊ ከተባለው ጉባኤ የተነጠለች መሆኑ ነው።

ይኽም ማለት ፦ እንደ ኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እምነት ፤ የክርስቶስ ሰዋዊው ባህሪው እንደ ውቅያኖስ በተለቀው አምላካዊው ባሕር ውስጥ ገብቶ ተውጧል ብላ የእምትል ነች:-

“በመካከለኛው/ቅርቡ ምሥራቅ አከባቢ የአሉ፟ ቀላል የእማይባሉ ክርስቲያኖች የካልሴዶኑን ሥራ አልተቀበሉም። ሰዋዊው እና አምላካዊው ተፈጥሮዎቹ በጋራ ተጣምረው በኢየሱስ ውስጥ አንድ ስብዕና ፈጥሯል ከማለት ይልቅ የአምላካዊ እና የሰዋዊው ተፈጥሮ ሊለያዩ በእማይችሉበት ኹኔታ ተዋህደው የፈጠሩት አዲስ ዓይነት ተፈጥሮ ነው የአለው አሉ። ይኽ ተዋህዶዋዊ (አንድ ተፈጥሮ) ነው እንግዲኽ የተዋህዶ አብያተ ክርስቲያናት ከሌላው ምሥራቃዊ ኦርቶዶክሳዊያን ተገንጥለው እንዲወጡ ምክንያት የሆነው። ይኽ ደግሞ የቢዛንቲየም ኃይል በምሥራቃዊ የግዛቷ ክፍል መዳከም ጋር ተያይዞ ፤ የተዋህዶው ቀኖና የኮፕት ቤተክርስቲያን የእምትባለውን እና ዛሬ በግብጽ ውስጥ ትልቁ ክርስቲያናዊ ተቋም የሆነችውን እና ከእርሷ ጋር የተዛመዱትን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ፣ እንዲኹም በሶሪያ ያዕቆባዊያን የእሚባሉትን እና አብዛኛዎቹ ተከታዮቹ በደቡባዊ ሕንድ የአሉ፟ትን ቤተክርስቲያን አስከተለ።”

“Numbers of Christians in the Near East, however, rejected the work of Chalcedon. They held that instead of the divine and human natures joining to form one person in Jesus, he possessed but one nature in which divine life and human were indistinguishable. This Monophysite (one nature) teaching was an important factor contributing to the breaking away of the Monophysite Churches from the rest of Eastern Orthodoxy. Coupled with the decline of the Byzantine power in the outlying areas of the Eastern Empire, Monophysite doctrine led to the Coptic Church, the largest Christian body in Egypt today, with a related church in Ethiopia, and the so-called Jacobite Church of Syria, which has most of its adherents in South India. [8]”

የጀስዊት ቄሶች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ እና ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋር የቀኖና ክርክር ውስጥ ሲገቡ ፤ በኢትዮጲያ ቤተክርስቲያን ላይ ከእሚያነሷቸው ትችቶች አንዱ ፤ የኢትዮጵያዋ ቤተክርስቲያን ፤ ዓለም ዓቀፉ የቤተክርስቲያን መማክርት ያወገዘውን የአውጤቅያን ፤ የውህድ አዲስ ተፈጥሮ ኑፋቄ ተቀብላለች የእሚል መሆኑ ነው።

ይኽም የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን የኮፕት ክርስቲያን ወይንም የአውጣቄን ኑፋቄ የተቀበለች በማስባል በእዚኽም የኢትዮጲያን ዲፕሎማሲ በመካከለኛው ዘመን ላይ ለአሉታዊ ጫና እንዲጋለጥ አድርጎታል።

ስነክርስቶስ (ሚስጥረ ስጋዌ) እና የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጲያ ፖለቲካ

በስነ ክርስቶስ ላይ የተነሱ እነ እዚኽ ሦሥት ኑፋቄዎች የተመለከትን እንደሆነ ፤ ሦሥቱም ኢየሱስ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ወይንም ሰውነቱ እና አምላክነቱ በእርሱ ውስጥ ተዋህደው የእሚገኙበትን ኹኔታ ከተቀበሉ በኋላ ወይንም በኢየሱስ ፍጹም ሰውነት እና ፍጹም አምላክነት ላይ ተስማምተው ከአበቁ በኋላ ፤ ሰውነቱ እና አምላክነት በእንዴት በአለ አኳኋን ነው የአሉት ወይንም የተዋኃዱት በእሚለው ጉዳይ ላይ ብቻ የእሚለያዩ መሆኑን ነው።

ልዩነታቸውን በቀላል ምሳሌ እን አስቀምጠው ቢባል ፤ በኢየሱስ ውስጥ አምላክነት እና ሰውነት ፦

  • ናቡከነደጾር የአውሬ አዕምሮ ተሰጠው እንደ እሚለው እና አካሉ የሰው ሆኖ ሳለ እንደ አውሬ ለሰባት አመት ኖረ እንደ እሚለው ፤ ኢየሱስ አካሉ የሰው አዕምሮው የአምላክ ሆነ። በዘመናዊ አገላለጽ ቢትልስ ቮልስዋገን ላይ የዘመናዊ ማርሴዲስ ቤንዝ ሞተር ተገጥሞ እንደ ማለት ነው።
  • የተለያዩ ነገር ግን ከግዜ በኋላ አንድ ላይ ለመኖር የተስማሙ ፤ እንደ ትዳር ወይንም የንግድ ሽርክና ዓይነት ግንኙነት
  • እንደ ማር እና እንደ ውኃ ውሕድ (እንደ ስኳር እና ሻይ) ፤ ሊለይ የእማይችል ቅይጥ

በአለ ኹኔታ ነው የእሚገኙት የእሚል ነው።

ኔስቶሪየስ እንደ ትዳር ወይንም በንግድ ሽርክና ሲመስለው ፣ አፖሊናሪስ እንደ ልቦና እና ሰውነት(አካል) ያለ ውሕደት ነው የአላ፟ቸው አለ ፤ ከእነርሱ የተለየው አውጥኬ ደግሞ ጥምረቱ ተዋህዶ ውቅያኖስ ውስጥ እንደ ሟሟ ማር አዲስ ይዘት ፈጥሯል የእሚል ሆነ።

እነ እዚኽ የተለያዩ የውህደት ዓይነት መላምቶች ፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር የስህተት አስተምህሮ ሊያስከትሉ የእሚችሉ ቢሆንም (ለምሳሌ ፦ ሰውነቱ አምላክነቱ ውስጥ ተዋህዶ ተውጧል ከተባለ ፤ ኢየሱስ ሰውም አምላክም የአልሆነ ፤ የሰው እና የአምላክ ውህድ ልዩ ነገር ነው የእሚሆነው ፤ ይኽ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱሱ ውስጥ ከአለው አቀራረብ ጋር የእሚጋጭ ነው ) ፤ ከአይርዮስ በስተቀር ሦሥቱም ከእሚስማሙበት የኢየሱስ ፍጹም ሰውነት እና ፍጹም አምላክነት በአሻገር ፤ በኢየሱስ ውስጥ አምላክነቱ እና ሰውነቱ በምን ዓይነት አግባብ እንደ ተወኃዱ ፤ በመጽሐፍ ቅዱሱ ውስጥ በግልጽ የአልተቀመጠ እና በምርምርም ሊደረስበት የእሚችል በአለመሆኑ ፤ አንድ አማኝ ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው እና ፍጹም አምላክ መሆኑን ከመናገር በአሻገር ፤ ውሕደቱ በምን መልኩ እንደ አለ ርግጠኛ አቋም መያዝ የእሚችል አይመስልም።

ለምሳሌ ፦ ኹሉም ክርስቲያን ሰው ነፍስ እንደ አለው ያምናል ፤ የሰው ነፍስ ምን አይነት እንደ ሆነ ? ከስጋዊ አካሉ ጋር እንዴት እንደ ተዋኃደ ? በየትኛው የሰውነት ክፍል ውስጥ ነፍስ እንድ እሚገኝ ? ማንም ሰው መገመት እንጂ ይኽ ነው ማለት የእሚችለው ጉዳይ አይደለም።

ነፍስ እስትንፋስ ነው ? ደም ነው ? አዕምሮ ነው ?

ማንም በእርግጠኝነት መናገር አይችልም።

በአጭሩ ፤ ጳጳሳቱ የሳቱት ፤ በእርግጠኝነት ሊያስቀምጡ የእማይችሉት ነገር ላይ እርግጠኛ ድምዳሜ ለማስቀመጥ በመሞከራቸው ነው።

ኢየሱስ ፍጹም ሰው እና ፍጹም አምላክ መሆኑን ከአመኑ ፤ አምላክነቱ እና ሰውነቱ የተዋኃዱበትን አግባብ ለመተንተን መሞክር አጉል ጸጉር ስንጠቃ እንጂ አንዳችም የእሚበጅ የስነ መለኮታዊ ምርምር አይደለም። የራሳችን ነፍስ ከስጋችን ጋር እንዴት በአለ መንገድ እንደ ተዋኃደ የእማናውቅ ሰዎች ፤ በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ሰውነቱ እና አምላክነቱ እንዴት እንደ ተዋኃደ ለማብራራት መሞከር ፤ ግብዝነት ከአልሆነ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም።

ቃሉም በጠቢቡ ሰለሞን አማካኝነት ይኽንን ማሳሰቢያ ያስቀምጣል ፦

መክብብ 11 ፡ 5 “የነፋስ መንገድ እንዴት እንደ ሆነች አጥንትም በእርጉዝ ሆድ እንዴት እንድትዋደድ እንደ እማታውቅ ፥ እንዲኹም ኹሉን የእሚሠራው የእግዚአብሔር ሥራ አታውቅም።”

እግዚአብሔር በተመሳሳይ ኢዮብን እንዲኽ ብሎ ሲገስጸው እናገኛለን ፤ በኢዮብ 38፡1-5

“እግዚአብሔርም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰ እንዲኽም አለ ፦

ያለ እውቀት በእሚነገር ቃል ምክርን የእሚያጨልም ይኽ ማነው ?

እንግዲኽ እንደ ሰው ወገብኽን ታጠቅ ፤ እጠይቅኃለው ፡ አንተም ተናገረኝ።

ምድርን በመሠረትኹ ጊዜ አንተ ወዴት ነበርኽ ?

ታስተውል እንደ ሆንኽ ተናገር።

ብታውቅስ መሠፈሪያዋን የወሰነ ፥ በላይዋስ የመለኪያ ገመድ የዘረጋ ማን ነው?”

በአጠቃላይም ፡ ምርምር መልካም ቢሆንም ፤ በሳይንሳዊ መንገድ በእርግጠኝነት ሊታወቅ የእማይችል ነገር ላይ ወይንም የእምነቱ መጽሐፍ በግልጽ በእማይደነግገው ጉዳይ ላይ ፤ ርገጠኛ አቋም ይዞ መከፋፈል እና መጣላት ተገቢ አይደለም ፤ ለእዚኽም ይመስላል ሐዋሪያው ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንጦስ 4፡6 ላይ

“ከተጻፈው አትለፍ …”

የአለው።

አጼ ፋሲለደስም ፤ ከእርስ በእርሱ ጦርነት በኋላ ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ከተቀበልን በኋላ ፤ ይኼ ውሕደት በኹለት ተፈጥሮ ነው ወይንም በአንድ ተፈጥሮ የእሚለው ክርክር ተራ የጸጉር ስንጠቃ እና በእዚኽም ልዩነት ላይ ተመስርቶ ሐገር የእሚያፈርስ ግጭት ውስጥ መግባት አይገባም የአለው ፦

“ … ፋሲለደስ ፤ የአባቱ አማካሪ የነበሩትን መኳንንቶች እና አለቆች ከሰበሰበ በኋላ ፤ የእሚከተለው ድምዳሜ ላይ ደረሱ … በዕምነት ጉዳይ ሮም እና አሌክሳንድሪያ አንድ መሆናቸው ፤ ኹለቱም ክርስቶስ ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ መሆኑን የእሚቀበሉ መሆናቸው እና እነ እዚኽ ደግሞ በአንድ ተፈጥሮ ነው ወይስ በኹለት ተፈጥሮ ውስጥ ነው የእሚለው ክርክር ብዙም ዋጋ የሌለው የቃላት ክርክር በመሆኑ ፤ በእዚኽ ልዩነት ሐገር ማፍረስ እንደ እማይገባ አስቀመጡ ።”

“Basilides, after he had summoned the nobility and chiefs of his father’s Counsellors together, held a Council, wherein it was concluded … the Romanists and Alexandrians were of the same Opinion in points of Faith, That both affirmed that God was true Christ, and true Man, as for the asserting of One or Two Natures, they were words of little Moment, and not worth of the Ruin of a Mighty Empire. [104]“

ይኽንንም ትሩፋት የጨመርኩበት አንዱ ምክንያት ፤ አጼ ፋሲለደስ በቀላል አገላለጽ “ኹለቱም ክርስቶስ ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ መሆኑን የእሚቀበሉ መሆናቸው እና እነ እዚኽ ደግሞ በአንድ ተፈጥሮ ነው ወይስ በኹለት ተፈጥሮ ውስጥ ነው የእሚለው ክርክር ብዙም ዋጋ የሌለው የቃላት ክርክር በመሆኑ ፤ በእዚኽ ልዩነት ሐገር ማፍረስ እንደ እማይገባ አስቀመጡ” የአለው ጉዳይ ፤ ሰፊ ታሪካዊ ዳራ የአለው እና አባባሉም የአጼ ፋሲለደስ የግንዛቤ ልቀት የእሚያሳይ መሆኑን በአግባቡ ለማሳየት በማሰብ ነው።

ታሪካዊ እውነታው ይኽ ቢሆንም ፤ የቀድሞ አባቶቻችን እንደ ዳግማዊ ቆስጦንጢኖስ የአሉትን የአርዮስ ተከታይ የሆኑ የቢዛንቲየም ኢምፐረሮች ወዲያ በማለታቸው መልካም ቢያደርጉም ፤ እርባና ቢስ በሆነው የአውጢክን ስጋወሚስጥር (Christology) ላይ አቋም ይዘው ፤ ራሳቸውን ከሰፊው የክርስትና ማሕበረሰብ ከሌሎች የምሥራቅ ክርስቲያኖች ጋር ሆነው መነ፟ጠ፟ላቸው ፤ በፖለቲካው ዘንድ የጎዳን ይመስላል።