ሕ ገ ክ ራ ሲ

marketing-image

ትሩፋት 1 ፡ በኢትዮጲያ ፦ ስዋሰው እና ፖለቲካ

የሰውን ልጅ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ከሌሎች እንሰሳት ስብስብ የተለይ እና የላቀ ከአደረጉት ባሕሪያቱ አንዱ የቋንቋ ክህሎቱ እና በቋንቋ አማካኝነት መከወን የእሚችላቸው ህልቆቢስ ተግባራት ናቸው።

ከእዚኽም የተነሳ በአንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ውስጥ በአንድ ቋንቋ መግባባት እና በቋንቋ አጠቃቀሙ ላይ የጋራ መስማማት መኖሩ የፖለቲካ መኃበረሰባትን ጤና እና እድገት በከፍተኛ ደረጃ ይወስናል።

በእርግጥ ፖለቲካ ሳይንስ ቋንቋን በአይፈጥረውም ፤ በማሕበረሰብ የተፈጠረውን ቋንቋ ከእነ ስዋሰው ሕጉ በአግባቡ አውቆ በአግባቡ መጠቀም አለበት ፤ በተለይ ደግሞ እንደ ሕገ መንግሥት በአለ በሐገር እና በነዋሪዎቿ ወይንም በሕዝቧ እጣ ፈንታ ላይ ከፍተኛ ሚና የአለው ሰነድ ፤ ቋንቋን ተደራሽ እና አሻሚ በአልሆነ እንዲኹም መሠረታዊ የሆኑ የቋንቋውን ስዋሰው ሕግ በተከተለ መልኩ መጠቀም ይጠበቅበታል።

የአውሮፕላን በረራ ሞያተኞች ፤ በሰማይ ላይ የአንድ ዲግሪ ልዩነት ወይንም ስህተት ፤ የአውሮፕላኑን መድረሻ ፤ በእዚኽኛው እና በእሚቀጥለው ከተማ መካከል ሊለያዩት ይችላል እንደ እሚሉት ፤ በሕገ መንግሥት ላይ የልታሰበበት እና በቋንቋው ስዋሰው ያለተፈተሸ ቃል አጠቃቀም ፤ ወደ ታች ሲወርድ ብዙ አሻሚ አንዳንዴም አጨቃጫቂ ትርጓሜዎችን ሊያስከትል ይችላል።

በመጥፎ የታሪክ አጋጣሚ የዛሬዋን የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቅርጽ የወሰነው ትውልድ ፤ በእንግሊዘኛው (You cannot teach an old dog a new trick ወይንም የአረጀውን ውሻ አዲስ ጨዋታ ልታስተምረው አትችልም) እንደ እሚባለው ፤ ከማርክሲስታዊ የፖለቲካ ርዕዮት ፤ ከማርክሲስቱም አፍላነት እና እጅግ ብዙ ግራ መጋባት የአለበት የመጀመሪያውን አከባቢ ማርክሲዝም ስለሆነ የእሚያውቁት ፤ ማርክሲስት አይደለንም እያሉ እና ማርክሲዝምን ለይስሙላ ሰአይሆን ከምርም እያወገዙ ፤ በፖለቲካው ሕይወት ጅማሮዋቸው ላይ የተቀረጸባቸው አስተሳሰብ ዛሬም ድረስ ስለ እሚገዛቸው ፤ ኢሕአዴግ የትውልዱ ተቀናቃኝ የሌለው (De facto) ወኪል ሆኖ የፖለቲካ ስልጣን ሲይዝ ያረቀቀው ሕገመንግሥት ፤ ቀዳሚዎቹ ማርክሲስቶች አልፍተው አልፍተው ፤ ይኽ እማይታኘክ ስለ እዚኽም ትርጉም አልባ አስተሳሰብ ነው ብለው የወረወሩትን የብሔር ጥያቄ ፤ እንደ ዋነኛ የሕገ መንግሥቱ አንኳር ወስዶ በመንቀሳቀሱ ፤ በፖለቲካዊ ስትራቴጂክ አስተሳሰብ ደረጃ የነበረበትን ብዥታ ወይንም ግራ መጋባት ፤ ብሔር እና ሕዝብ የእሚሉትን ቃላት ግራ በገባው ወይንም በተሳሳተ መልኩ እንዲ ያስቀምጥ አድርጎታል።

ታሪካዊ ስሕተቶች በእዚኽ መልኩ ሲፈጸሙ ደግሞ ፤ ታሪካዊ ስህተቶችን በስህተትነት ነቅሶ ማስቀመጡ ፤ በእዚኽ ስህተት በማሕበረሰብ ውስጥ የተዘራውን የመደናገር አረም ከመንቀሉም በአሻገር ወደፊት ተመሳሳይ ስሕተት ለአለመሥራት እንደ ማሳሰቢያ ይሆናል ብዬ ስለ አመንኹ ፤ “ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች” በእሚለው ሐረግ መሳይ ቃል ላይ ፤ የአሉ የስዋሰው እና የፖለቲካዊ አስተሳሰብ ችግሮች ናቸው ብዬ የእማምናቸውን ጉዳዮች ለማስቀመጥ ስለ አሰብኩ ፤ ይኽንን ጉዳይ በመጽሐፉ ውስጥ እንደ አንድ ርዕስ ማስቀመጥ ሳይሆን እንደ ትሩፋት የመጽሐፉ መጨረሻ ላይ ማስቀመጡ ተገቢ ይሆናል በእሚል ፤ ይኽንን ትሩፋት አስገብቼዋለኹ።

በእዚኽ “ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች” በእሚለው ሐረገ-ቃል ላይ የአለው ችግር ፤ ከአማርኛ ስዋሰው ብቻም ሰአይሆን ከፖለቲካዊ አስተሳሰብ ጋር የአለውን ችግር አብሮ ማየት በጣም አስፈላጊ ነው ፤ ምክንያቱም ፦ በእኔ እምነት የቋንቋ ስዋሰዋዊ ስህተቱ በዋነኛነት ከፖለቲካዊ አስተሳሰብ ስህተት የመነጨ በመሆኑ።

የእዚኽ ሐረገ-ቃል “ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝብ” የእሚለው ቃል ወይንም አስተሳሰብ ምንጩ ፤ በመጽሐፉ ምዕራፍ አንድ ላይ ስለ ብሔራዊ ጽንፈኝነት ስእናይ እንደ አነሳነው ፤ የዘመናዊ ሕዝባዊ ፖለቲካ መግነን ጋር የተያያዘ ነው።

በአጭሩ የራስን እድል በእራስ የመወሰን መብት ዓለም ዓቀፋዊነት እያገኘ ሲመጣ ፤ ሐገር የእምትባለው መዋቀር የቡርዥዋ ስሪት በመሆኗ መጥፋት የአለባት እና የዓለም ወዛደሮች ኹሉ ከብሔራዊ ስሜት ተላቀው በማርክሲዝም ርዕዮት ከእሚመራው የዓለም ዓቀፉ የላብ አደሩ የመደብ ትግል ጋር መሰለፍ አለባቸው የእሚለው ማርክሲዝም ፤ በእሚከተለው ጸረ ሉዓላዊት ሐገር የማርክሲዝም ርዕዮት መሠረት ፤ እጅግ ታዋቂነት እና ተቀባይነት እያገኘ የመጣውን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት በምን ዓይነት መልኩ ሊያስተናግደው እንደ እሚገባ ፤ ይኽ ነው የእሚባል ርዕዮታዊ መፍትኼ ሊያገኝለት አልቻለም።

ምክንያቱም ፦ የማርክሲዝም ጸረ ሐገር ርዕዮት የራስን እድል በራስ መወሰን ከእሚለው መብት ጋር በፍጹም ሊታረቅ የእማይችል በመሆኑ።

ከማርክሲዝም ውጭ ለዓሉት ዴሞክራሲያዊያን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በዋነኛነት ፤ በአንድ አከባቢ የእሚኖር ሕዝብ ፤ ራሳቸውን ከቀኝ ግዛት አላቀው ፤ በእሚኖሩበት አከባቢ በዋናነት ከቀኝ ግዛት ነጻ ወጥተው በመሰላቸው መንገድ ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ የመጣ መብት አድርገው ስለ ወሰዱት ወይንም መብቱን ከሕዝብ ፦ ነገዳዊ ፣ የቋንቋ ፣ የባሕል ፣ ወዘተ ፤ ማንነት ጋር እና ከጽንፈኛ ብሔርተኝነት ጋር ሰአይሆን ከእነ እንደ እዚኽ ዓይነቶቹ የቅርጽ ልዩነቶች በአሻገር እና የዜጎችን የጋራ ተጠቃሚነት ታሳቢ በአደረገ መልኩ ፤ በአንድ አከባቢ የአለ፟ ሕዝብ የጋራ መብት አድርገው ስለ ወሰዱት ፤ መብቱ ለማን ነው መሰጠት የአለበት የእሚለው ጉዳይ ብዙም ብዥታ እና ግራ መጋባት አልፈጠረባቸውም። ምክንያቱም ፦ መብቱን ከሕዝብ ጋር በተናጠል ወይንም ከመሲሕያዊ ጀብደኝነት ጋር ሰአይሆን በአንድ በተወሰነ ከአከባቢ ከቀኝ ግዛት መላቀቅ ለአለበት ሕዝብ ጋር ስለ አያያዙት ።

ለማርክሲስቶቹ ግን ይኽን መብት በእዚኽ መልኩ መቀበሉ ፤ ጸረ ሐገር ከሆነው ከማርክሲስታዊ አስተሳሰብ ጋር ቀጥታ ስለ እሚጋጭባቸው ፤ በአንድ የተወሰነ አከባቢ የእሚኖር ሕዝብ ከቀኝ ግዛት ተላቆ የራሱን እድል በራሱ መወሰን የእሚለውን ይኽን እጅግ ታዋቂነት እና ተቀባይነት የአፈራ ኃሳብ እንደ ወረደ መቀበል ፤ የሉዓላዊት ሐገርን ጽንሰ ኃሳብ መቀበል ስለ ሆነባቸው ፤ በውስጣቸው መከፋፈል ፈጠረ።

አንዱ ወገን ይኽን መብት ፤ የተጨቆነ ሕዝብ የራስን እድል በራስ መወሰን በእሚል ለመገንጠል በእሚያደርጉት ጥረት አብዮት መቀስቀሻ መሳሪያ በመሆኑ ፤ የመገንጠል እንቅስቃሴው በማንኛውም ሕዝብ ወስጥ ሶሻሊስታዊ ወገንተኝነት በአላቸውን የፖለቲካ ኃይላት እስከ ተመራ ድረስ ልንደግፈው ይገባል አለ። በእዚኽ ጎራ ሌኒን ዋነኛው ነው።

ሌላው ወገን ይኽ መብት የተጨቆነ ሕዝብ ለመገንጠል በእሚያደርገው እንቅስቃሴ ሶሻሊስታዊ አብዮት ለማስነሳት ያግዛል በእሚል ልንጠቀምበት የእምንችል ቢሆንም ፤ ለኹሉም ዓይነት ሕዝብ መሰጠት የለበትም ፤ ምክንያቱም ፦ አንዳንዱ ሕዝብ የእሚገኝበት የታሪካዊ የእድገት ደረጃ ፤ በጣም ኋላ ቀር በመሆኑ ፤ እንደ እዚኽ የአለው ሕዝብ በአለበት ሆኖ ወደ ተሻለ የታሪካዊ እድገት ደረጃ ላይ እንዲመጣ ማድረግ እንጂ ፤ ከእነ እሚገኝበት ኋላ ቀርነት በሶሻሊስታዊ አመራር ስር በኋላ ትመጣለህ በእሚል ፤ እንዲገንጠል ብንፈቅድለት ፤ የታሪክን ጎማ ወደ ኋላ መንዳት በመሆኑ አፍራሽ ነውና ፤ መብቱ እንደ ኹኔታው ነው መሰጠት የአለበት የእሚል ሆነ። የእዚኽኛው ጎራ መሪ ሮዛ ሉክሰምበርግ ናት ልንል እንችላለን ።

እንደ ገና ሌላው እና ሦሥተኛው ወገን ፤ የተጨቆነ እና አቅሙ የአለው ሕዝብ ለመገንጠል በእሚያደርገው እንቅስቃሴ ሶሻሊስታዊ አብዮት ለማስነሳት ያግዛል በእሚል ፤ የራስን እድል በእራስ መወሰን የእሚለውን መብት ከቋንቋ ፣ ከባህል ፣ ወዘተ ፣ ማንነት ጋር ማያያዝ ሊመጣ ስለ እሚችል እና ይኽም ጠባብነት ፣ ተገንጣይነትን አንዳንዴም ሕዝብን በሕዝብ ላይ በማስነሳት የዘር ጭፍጨፋ በማፋፋም ፤ የሶሻሊስትን አብዮት ወይንም የሠራተኛውን አብዮት ስለ እሚጋርድ ፤ የራስን እድል በራስ መወሰን በፍጹም ለባህል ፣ ለኃይማኖት ፣ ለቋንቋ ፣ ማሕበረሰብ መሰጠት የሌለበት እና በአጠቃላይም የብሔር ጭቆናን ጥያቄ በብሔርተኝነት ለመመለስ መሞከር አፍራሽ በመሆኑ ፤ የብሔር ጭቅና ከአለም መፈታት የአለበት ዴሞክራሲያዊ ስረዓት በመገንባት እንጂ በብሔርተኝነት እንቅስቃሴ መሆን የለበትም የእሚል ሆነ። የእዚኽ ጎራ መሪ ጆሴስ ስታሊን ነው ልንል እንችላለን።

የከባቢያዊ ወይንም በአንድ አከባቢ የእሚኖሩ ሰዎች ከቀኝ ግዛት ለመውጣት ሊጠቀሙበት የእሚችሉት የጋራ መብት የሆነው ፤ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ፤ በማርክሲስታዊ ጸረ ሐገር እና ጸረ ቡርዣ አስተሳሰብ ምክንያት ከቦታ እና ከቀኝ ግዛት አስተሳሰብ ተላቆ ከሕዝብ ልዩ ጠባይ ጋር ሲተሳሰር ፤ ማርክሲስቶችን በመብቱ አረዳድ እና አተገባበር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን እንዲ ለያዩ የአደረጋቸው ፤ ይኽ መብት የእሚገባው የልዩ ጠባይ ሕዝብ ባለቤት እንዴት የአለው ሕዝብ ነው? በእሚለውም ጥያቄ ላይ ነው።

ይኽንም ተከትሎ የተለያዩ የማርክሲስቱ ጎራ ፖለቲከኞች ብሔር ማን ነው የእሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የተለያየ ትርጉም ይቀምሩ ጀመሩ።

ቀደም ብለን በምዕራፍ ሦሥት ላይ እንደ ዓየነው ፤ ጆሴፍ ስታሊን ብሔርን በእዚኽ መልኩ ተረጎመው ፦

“ብሔር ምንድ ነው ?

ብሔር በቀዳሚነት አንድ ጋርዮሽ ነው ፤ አንድ የተወሰነ የሕዝብ ጋርዮሽ ነው።

ይኼ ጋርዮሽ ግን የዘር ወይንም የነገድ ጋርዮሽ አይደለም። ዘመናዊ ብሔራዊ ጣሊያን ከሮማኖች ፣ ከቲውቶንስ ፣ ከኢትሩስካን ፣ ከግሪክ ፣ ከአረብ ፣ ወዘተ ፤ የተወጣጣች ነች። ብሔራዊት ፈረንሳይ ፤ ከጎውሎች ፣ ከሮማኖች ፣ ከብሪትኖች ፣ ከቲውቶኖች ፣ ወዘተ ፤ የተውጣጣች ነች። ተመሳሳይ ነገርም ስለ ብሪትሾች ፣ ስለ ጀርመኖች እና ስለ ሌሎችም መባል ይችላል የተለያየ ዘር እና ነገድ ከአላቸው ሕዝብ ተወጣተው ለተመሠረቱ ብሔራዊ ሐገራት ።

ስለ እዚኽ ፦ ብሔር ከዘር ወይንም ከነገድ ጋር የተያያዘ ነገር አይደለም ፤ በታሪክ ኺደት የተዋቀረ የሕዝብ ጋርዮሽ ነው። …. ብሔር ማለት ድንገታዊ ወይንም ግዜያዊ ስብስብ ማለት ሳይሆን የረጋ የህዝብ ጋርዮሽ ነው።”

“What is a nation?

A nation is primarily a community, a definite community of people.

This community is not racial, nor is it tribal. The modern Italian nation was formed from Romans, Teutons, Etruscans, Greeks, Arabs, and so forth. The French nation was formed from Gauls, Romans, Britons, Teutons, and so on. The same must be said of the British, the Germans and others, who were formed into nations from people of diverse races and tribes.

Thus, a nation is not a racial or tribal, but a historically constituted community of people…. a nation is not a casual or ephemeral conglomeration, but a stable community of people. [125]”

ስታሊን ብሔር ነገድ እና ጎሳ ማለት አይደለም ከአለ በኋላ ፤ የብሔር መገለጫ ናቸው የአላቸውን ባሕሪያት በመዘርዘር ብሔርን እንደ ገና በእዚኽ መልኩ ተረገሞው ፦

“ብሔር በታሪክ ኺደት የተዋቀረ ፣ በጋራ ፦ ቋንቋ ፣ መኖሪያ ስፍራ ፣ ኢከነሚያዊ ሕይወት ፣ ላይ የተመሠረተ በጋርዮሽ ባሕል የእሚንጸባረቅ ስነልቦናዊ ውቅር የአለው ፤ የረጋ የሕዝብ ጋርዮሽ ነው።”

“A nation is a historically constituted, stable community of people, formed on the basis of common language, territory, economic life, and psychological make-up manifested in a common culture. [125]”

ይኼኛውም የስታሊን ትርጉም ምንም እንኳን ብሔር ማለት የግድ አንድ የጋራ መኖሪያ ቦታ የአላቸውን እና የጋራ መግባቢያ ቋንቋ የአላቸው ሕዝብ መሆናቸውን ቢያስቀምጥም ፤ ብሔር ማለት ነገድ እና ጎሳ ማለት ሳይሆን በታሪክ ኺደት በተለይ ደግሞ በማርክሲስታዊ የታሪክ ቁሳዊነት መሠረት ድሕረ ካፒታሊዝም የተፈጠረ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ (Political Economic Society) መሆኑን በግልጽ የእሚያስረግጥ ነው።

በአጭሩ የስታሊን የብሔር ትርጉም ዛሬ የእምናውቃቸውን ሉዓላዊ ሐገራት የእሚወክል እንጂ በኢሕአዴጉ ሕገመንግሥት ውስጥ ብሔር የእሚለው ቃል የወከለውን ኃሳብ የያዘ አይመስልም ወይንም አይደለም።

ለእዚኽም ነው የእነ ሮዛ እና የእነ ስታሊን የብሔር ግንዛቤ ፤ ብሔራዊ ሶሻሊዝም (National Socialism) ወይንም ብሔራዊ ሐገራትን በግዜያዊነት ተቀብሎ ፤ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ አግባብ በመምራት ወደ ካፒታሊዝም ስረዓት ማሸጋገር በእሚል የተቃኘው።

የስታሊን ተቃዋሚዎች ደግሞ ብሔር ከቦታ ጋር የእማይያያዝ ፤ ፖለቲካዊ ፋይዳ የአለው ሰአይሆን በዋናነት የባሕል ራስ ገዝነት ጋር የእሚያያያዝ ፤ የባሕል ቡድን ነው የእሚሉ ሆኑ። ስታሊን የእርሱን የብሔር ትርጓሜ ከእሚቃወሙት ሰዎች አንዱን ማለትም ስፕሪንገር የእሚባለውን ሰው ብሔርን የተረጎመበትን አግባብ በመጽሐፉ ላይ በእዚኽ መልኩ ጠቅሶታል ፦

“እንደ ስፕሪንገር ፤ ብሔር ተመሳሳይ አስተሳሰብ እና አነጋገር የአላቸው ሰዎች ስብስብ ነው። ባሕላዊ ጋርዮች የአላቸው የዘመናዊ ሰዎች ስብስብ የሆነ እና ከምድሩ ጋር ምንም ትስስር የሌለው ነው።”

“According to Springer, “ a nation is a union of similarly thinking and similarly speaking persons.” It is “a cultural community of modern people no longer tied to the soil. [125]”

እንደገናም ኦቶ ባወር የእሚባለውን ጸሐፊ በብሔር ላይ ለሰጠው ትርጓሜ ስታሊን እንደ እዚኽ ይጠቅሰዋል ፦

“ብሔር ማለት በጋርዮሽ እጣ ፈንታቸው ምክንያት ወደ አንድ የጋራ ጠባይ የተገመዱ ሕዝብ ስብስብ ነው።”

“A nation is an aggregate of people bound into a community of character by a common destiny. [125]”

ይኼኛውም የብሔር ትርጉም ቢሆን በእኛ ሐገሩ እንደ ተስተዋለው በተናጠል ከቋንቋ ወይንም ከባሕል ቡድን ወይንም ከነገድ (Ethnicity) ጋር የተያያዘ አይመስልም።

ከእላይ እንደ አየነው ፤ ለስታሊን ብሔር ማለት ከነገድ ጋር የእሚያያዝ አይደለም ማለቱ በግልጽ የተቀመጠ ነው። የእርሱ ተቃዋሚዎችም ቢሆኑ ፤ አንጻራዊ የሆነ የጋራ ጠባይ ነው ብሔርን ብሔር የእሚያስብለው ቢሉም ፤ ለምሳሌ ፦ እንግሊዞች እና አይሪሾች አንድ ቋንቋ ቢናገሩም አንድ ብሔር ሊባሉ አይችሉም ስለ እሚሉ ፤ የእነርሱም የብሔር ግንዛቤ ከእኛ ሐገሩ የብሔር ግንዛቤ እጅግ የተለየ መሆኑ ግልጽ ነው።

ስታሊን ኦቶ ባወርን እንደ እዚኽ ይጠቅሰዋል ፦

“‘ብሔር ምንድ ነው?’ ብሎ ይጠይቃል ፤ ‘የጋራ ቋንቋ መኖር ነው አንድ ሕዝብን ብሔር የእሚያደርገው ?’ ይኽ ከሆነ ግን እንግሊዞች እና አይሪሾች … አንድ ቋንቋ ይናገራሉ ፤ ነገር ግን አንድ ሕዝብ አይደሉም።”

“’What is a nation?’ He asks, ‘Is it a common language which makes people a nation? But the English and the Irish … speak the same language without, however, being one people: … [125]”

በአጭሩ ፤ የጋራ ጠባዩን የብሔሩ መገለጫ ቢያደርጉም ፤ የጋራ ጠባዩ የፖለቲካዊ ሕይወታቸው ነጸብራቅ ወይንም የእርሱ ተረፈ ምርት እንጂ ፤ በእራሱ በአንጻራዊነት ከሌላው ወገን የተለየ የጋራ ጠባይ መኖር የብሔር ኹነኛ መገለጫ ነው እያሉ አይደለም።

ስለ እዚኽ ፦ የስታሊን ተቃዋሚውም ትርጓሜ ፤ የሕዝብን አንጻራዊ ልዩነት የብሔርነት መገለጫ ቢያደርግም እና ብሔር በመኖሪያ ቦታ የእማይወሰን ፤ የጠባይ እና የአስተሳሰብ መቀራረብ ቢያደርገውም ይኽም የብሔር ትርጓሜ በእኛ ሐገር ለብሔር ከተሰጠው ትርጓሜ ጋር አብሮ የእማይኼድ ነው ፤ ምክንያቱም የብሔርነት መሠረቱ አንጻራዊ የሕዝብ ጠባይ ተቀራራቢነት ነው ቢሉም ፤ አንጻራዊ ተመሳሳይ ባሕሪ የአለውን ሕዝብ ኹሉ እንደ አንድ ብሔር የእማይገነዘቡ ናቸው ፤ ከእዚኽም ትርጓሜያቸው ተነስተው ብሔር ፖለቲካዊ ተቋም ሰአይሆን ባሕላዊ ተቋም ወይንም አደረጃጀት እንደ ሆነ የእሚገነዘቡት።

በአጭሩ የስታሊን ተቃዋሚ ሶሻል ዴሞክራቶች ከስታሊኑ የብሔር ትርጓሜያቸው የእሚለዩበት ዋናው ምክንያት ፤ ብሔር የባሕል እንጂ የፖለቲካ ቡድን አይደለም በእሚለው እምነታቸው ነው። ይኽንም ተከትለው ፤ ብሔር ለባሕላዊ ህልውና የእሚያስፈልግ እንጂ ለፖለቲካዊ ፋይዳ የእማያስፈለግ አደረጃጀት እንደ ሆነ ለማስቀመጥ የእሚፈልጉ ናቸው። ስታሊንም ፦ ብሔር በዋናነት ባሕላዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ አደረጃጀት ነው ብሎ ሲያበቃ ፤ ብሔርተኝነት በፖለቲካዊውም ሆነ በባሕላዊ ደርዙ የመደራጃ መሠረት ሲሆን ፤ በተለይ ለተራማጅ ማርክሲስታዊ ፖለቲካ መጥፎ የሆነ የፖለቲካ አካኼድ ነው የእሚል ነው።

እንደ እሚታየው የማርክሲስቶቹ ይኽን መሰል የብሔር ትርጓሜ ፤ የኧኛ ሐገሩ ኢሕአዴግ የብሔር ትርጓሜ እጅግ የእሚለይ ነው።

ስለ እዚኽ የእራስን እድል በራስ የመወሰን መብት በአንድ አከባቢ የእሚኖሩ የኹሉም ዓይነት ሕዝብ (ከዘር ፣ ከነገድ ፣ ከቋንቋ ፣ ከባሕል ፣ ወዘተ ፤ ልዩነታቸው በአሻገእር) ከቀኝ ግዛት መላቀቂያ የጋራ መብት ሲሆን በሐገራዊ ሉዓላዊነት ምክንያት ዓለም ዓቀፋዊ የሠራተኛ አብዮት ማድረግ የእሚለውን ማርክሲዝም ስለ እሚገታው ፤ መብቱን ከቦታ አላቆ ለሆኑ የአንጻራዊ የጋራ ጠባይ ለተላበሰ ሕዝብ ለመስጠት በመፈ፟ለጉ ፤ ይኽን መብት የእሚሰጠውን ሕዝብ በምን መልኩ መለየት አለበት የእሚለው ጥያቄ ፤ የብሔርን ወይንም የሐገርን ትርጉም የአል አግባብ በማወሳሰብ ወደ ፍሬ አልባ የቃላት ንትርክ እንዲያመራ አድርጎታል።

ከእዚኽ የተነሳ እስከ አኹንም በዓለም ላይ እንደ People, Nations, Nationalities , Nation State, State, Citizens, ወዘተ ፤ የአሉት የእንግሊዘኛ ቃላት ፤ በግራ ዘመሞች ዘንድ ህልም እንደ ፈቺው ነው የእሚል ትርጉም ነው የአላቸው።

በእዚኽ የተደናበረው የማርክሲዝም ትምህርት ቤት የተኮተኮቱት እና የኢትዮጲያ መሠረታዊ ችግር የብሔር ጭቆና ነው የአሉት የሐገራችን የ60ዎቹ ዘመን ፖለቲከኞች ፤ በእዚኽ አስተሳሰባቸው ተቃኝተው ሕገ መንግሥት ወደ ማርቀቅ ሲመጡ ፤ የማርክሲዝሙ ቁንጮዎች ራሳቸው በአግባቡ የእሚያስማማ ትርጉም ሊይዙበት የአልቻሉትን የብሔር ጽንሰኃስብ ይዘው ፤ “ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝብ” የእሚል ቃለ ሐረግ ይዘው መጡ።

ለእዚኽም ይመስለኛል ስታሊን እንደ እዚኽ የአለው ፦

“ስለ እዚኽ ፦ ብሔርተኛ ዓይነቱ አደረጃጀት የብሔርተኛ ጠባብ ጭንቅላት መፍለቂያ እና የቆሞ መበስበሻ ትምህርት ቤት ነው።”

“Therefore, the national type of organization is a school of national narrow-mindedness and stagnation. [125]”

ብሔር ማለት Nation ነው ብሔረሰብ ደግሞ Nationality እና ሕዝብ People ነው የአሉት የሐገራችን ፖለቲከኞች ፤ በሦሥቱ መካከል የአለውን ልዩነት እንዴት ይገልጹታል ሲባል ፤ ብሔር ከፖለቲካዊ ንቃቱ እና አደረጃጀቱ (መጠን እና ስፋት) ከብሔረሰብ ያንሳል ፤ ሕዝብ ደግሞ ፖለቲካዊ ንቃት እና አደረጃጀት በአይኖረውም ዓለም ዓቀፋዊ እውቅና የአላቸው ሐገራትን ድንበር ተሻጋሪ አሰፋፈር የአለውን ሕዝብ እንደ እሚሉ ይነገራል።

እነ እዚኽን ቃላት ግን በየትኛውም መደበኛም ሆነ የፖለቲካ ሳይንስ መዝገበ ቃላት ላይ በእዚኽ መልኩ ተተርጉመው አናገኛቸውም።

ማንም ሰው ሊያጣራ እንደ እሚችለው በእንግሊዘኛው Nation እና Nationality በእሚሉት ቃላት መካከል የአለው ተዛምዶ አንዱ በእዚኽ ጉዳይ ብሔር (Nation) የስብስብ ስም (Collective Noun) ሲሆን ሌላኛው ወይንም Nationality የእዚያኽ ስብስብ አባል የሆነ ሰው የእሚጠራበት ስም ነው።

ለምሳሌ ፦ የሰውየው Nation ኢትዮጲያ ከሆነ Nationalityው ኢትዮጵያዊ ይሆናል እንጂ Nation ከ Nationality በቁጥር ፣ በፖለቲካዊ ንቃት እና ተሳትፎ ፣ ወዘተ አነስ የእሚል ነው የእሚል ትርጓሜ ፤ በመደበኛ የአማርኛም ሆነ የእንግሊዘኛ ቋንቋ መዝገበ ቃላት ላይም ሆነ በፖለቲካ ሳይንሱ ረገድ የእሚታወቅ እውቅና የአለው ትርጓሜ የለም።

በእርግጥ Nationalities ሲሆን ብዙ ቁጥር ሆኖ ፤ የተለያዩ Nations አባላትን የእሚያመልክት ይሆናል ፤ ከእዚያኽ በዘለለ ግን Nations ከ Nationalities የእሚያንስ አደረጃጀት ፣ ፖለቲካዊ ንቃት ፣ ወዘተ ፣ የአላቸውን የጋራ ጠባይ ቡድን ናቸው የእሚል ምንም ዓይነት ትርጉም የለም።

ይኽም ደግሞ በእዛው በኢሕአዴጉ ሕገመንግሥት ራሱ ላይ ዜግነት የእሚለውን የአማርኛውን ቃል Nationality ብሎ በእንግሊዘኛ ሲተረጉመው በግልጽ የእሚታይ ነው።

ስለ ዜግነት ጉዳይ የእሚደነግገው አንቀጽ 6 የኢሕአዴጉ ሕገመንግሥት በአማርኛ እና በእንግሊዘኛ በከፊል ይኽን ይመስላል ፦

“አንቀጽ 6 ፤ ስለ ዜግነት

  1. ወላጆቹ/ወላጆቿ ወይም ከወላጆቹ/ከወላጆቿ አንደኛው ኢትዮጲያዊ/ኢትዮጲያዊት የሆነ/የሆነች የኢትዮጵያ ዜጋ ነው/ናት።
  2. የውጭ ሐገር ዜጎች የኢትዮጵያ ዜግነት ሊያገኙ ይችላሉ።”

“Article 6 Nationality

  1. Any person of either sex shall be an Ethiopian national where both or either parent is Ethiopian.
  2. Foreign nationals may acquire Ethiopian nationality.”

በእዚኽም Nationalityን በአንድ በኩል ብሔረሰብ በሌላ በኩል ደግሞ ዜግነት ብሎ በመተርጎም እና በመጠቀም ሕገመንግሥቱ ፤ የአለበትን የቋንቋ እና የጽንሰ ኃሳብ ግድፈት በግልጽ አሳይቷል።

ብሔር የእሚለው የግዕዝ ቃል ፤ በአማርኛው ሐገር ወይንም ክፍለ ሐገር የእሚለውን የእሚወክል ወይንም በዋናነት ስፍራን ወይንም ቦታን አመልካች እንጂ አንጻራዊ የጋራ ልዩ ጠባይ የአላቸው ሕዝብን አመልካች አይደለም። በእርግጥ በአንድ አከባቢ የእሚኖር ሕዝብ አንጻራዊ ልዩ ባሕሪ ሊላበስ ይችላል ፤ ይኽ ማለት ግን አንጻራዊ ባሕሪያዊ ልዩነት የግዕዙ ብሔር የእሚገልጸው ኃሳብ ነው ማለት አይደለም።

እንደገናም ብሔር ሐገር ወይንም ክፍለ ሐገር ከእሚለው ትርጓሜው ከፍ ሲል ዓለምን ወይንም ምድርን እና ሞላዋን የእሚወክል ቃል ነው ብሔር ፤ ከእዛም ነው እግዚአ + ብሔር ፤ የዓለም ኹሉ ጌታ (አዶናይ) የእሚለው የእግዚአብሔር ስያሜ የመጣው።

በእዚኽ አንጻር Nation የእሚለው የእንግሊዘኛው ቃልም ፤ ከግዕዙ ብሔር ጋር ተመሳሳይ ትርጉም የአለው ይመስላል። ምንም እንኳን Nation የእሚለው ቃል በዋናነት ተወላጅ የእሚል እንደምታ የአለው ናሽዮ (Natio) የእሚል የላቲን ቃል ነው ምንጩ ቢባልም ፤ ይኽ ተወላጅ የእሚለው ቃል የትውልድ ስፍራን (Place of Origin) አመላካች እንደ ሆነ ነው የእሚታየው።

ይኽም በመሆኑ ፤ የኢሕአዴጉ ሕገመንግሥት ብሔር ብሎ የእሚጠራው ሕዝብ በመደኛ ቋንቋ ነገድ (Ethnicity) የእምንለውን በመሆኑ እና በእዚኽ ሕገ መንግሥት ብሔር ተብለው የተጠሩት እና ፖለቲካዊ ማንነት እንዲላበሱ የተደረጉት የማሕበረሰብ ክፍላት ወይንም ሕዝብ ፤ ከእላይ የአየናቸው ማርክሲስቶች ቃሉን ከተረጎሙበት መንገድ ጋር የእማይስማማ በመሆኑ ፤ ቃሉ በእሚታወቁት ትርጓሜዎች ከአሉት እንደ ምታ ውጭ በኢሕአዴጉ ሕገመንግሥት ውስጥ እንደ ተቀመጠ ይመስላል።

ብሔር የእሚለውን ቃል በአማርኛ ውስጥ ስንጠቀምበት የኖርነውም ቦታ በእሚያመልክትበት አግባብ ነው።

ለምሳሌ ፦

  • ብሔራዊ ፈተና - ሐገር ዓቀፍ ፈተና
  • ብሔራዊ ባንክ - የሐገሪቱን ባንኮች የእሚያስተዳድር ባንክ
  • ብሔራዊ ቡድን - የሐገሪቱ የስፖርት ቡድን
  • ብሔራዊ በዓል - ሐገር ዓቀፍ በዓል
  • ርዕሰ ብሔር - ፕሬዝደንት
  • ወዘተ

ከእላይ እንደ አልነው ፤ ከባቢ ልዩ ጠባይን ሊያስከትል ይችላል ወይንም ያስከትላል ፤ ያ ማለት ግን ልዩ ጠባይ የልዩ አከባቢ ባለቤትነት መብት ያረጋግጣል ማለት አይቻልም ወይንም ይኽን አይነት አባባል ጸረ ሕዝብ ነው።

በአማርኛ በትክክል በኢሕአዴግ ሕገመንግሥት ውስጥ የተቀመጠውን ብሔር የእሚለውን ኃሳብ ሊወክል የእሚችለው ቃል ነገድ የእሚለው ነው። አቢሲኒካ የእሚባለው የኢንተርኔት የአማርኛ መዝገበ ቃላት ነገድን እንደ እዚኽ ይተረጉመዋል ፦

“ከአንድ አባት ብዙ ኾኖ ተወልዶ … ሕዝብን ኾኖ ቋንቋውም አንድ የኾነ ሕዝብ ነገድ ይባላል…”

ብሔር ሐገር ወይንም አከባቢ ወይንም ምድሩን ወካይ ቃል ከሆነ ደግሞ በተለመደው የአማርኛ ወይንም የግዕዝ የቃላት ርቢ ሕግ ፤ ብሔረሰብ ፦ የብሔር እና የሰብ ውሕድ የሆነ ፤ የአንድ ሐገር/አከባቢ/ክፍለሐገር ተወላጅ ወይንም ነዋሪ የእሚያመለክት ቃል ነው የእሚሆነው።

ብሔርሰብ (National) ፤ የአንድ ብሔር ፣ ሐገር ፣ ክፍለ ሐገር ወይንም መሬት ነዋሪ ወይንም ተወላጅ ሰው ነው የእሚሆነው።

ብሔረሰብ ልክ ግለሰብ ስንል ፤ ግል እና ሰብ የእሚሉቱን ኹለቱን ቃላት አዋህደን ፤ አንድ ነጠላ ሰው ለማለት እንደ እምንጠቀምበት ወይንም ማሕበረሰብ ስንል ደግሞ ማሕበር እና ሰብ የእሚሉትን ቃላት አዋህደን የሰዎች ማሕበር ለመግለጽ እንደ እምንጠቀምበት ፤ የእዚያኽ ብሔር ሰው የእሚል ትርጉም የአለው ውህድ ቃል ነው።

  • ግለሰብ = ግል + ሰብ > አንድ ነጠላ ሰው
  • ማሕበረሰብ = ማሕበር + ሰብ > የሰዎች ማሕበር
  • ሕብረተሰብ = ሕብረት + ሰብ > የሰዎች ሕብረት

እንደ እዚኽ አድርገን ስናየው ብሔረሰብ ተብሎ በኢሕአዴግ ሕገመንግሥት ላይ የተቀመጠው ቃል Nationality ከእሚለው ቃል ጋር ተስማሚ ሆኖ እናገኛወለን ፤ ቀጥታ ቃል በቃል ትርጉም አንጻር።

የእዚኽ ችግሩ ግን ብሔረሰብ ማለት National ነው ካልን ፤ ኹለት ችግሮች ይከተላሉ ፦

  1. ብሔርሰብ ከብሔር የእሚልቅ ነው የእሚለው ማብራሪያ በሬ ወለደ ዓይነት ማብራሪያ ይሆናል።
  2. የለም ብሔርሰብ ከብሔር የእሚልቅ ነው የእሚል ማብራሪያ የለም ከተባለ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች የእሚለው ገለጻ ፍጹም ትርጉም አልባ የቃላት ድግግሞሽ ይሆናል።

ብሔረሰብ የእሚለውን National የእሚል ነው ብለን ከተቀበልን ፤ አምሐራን እንደ ማሳያ ብንወሰድ ፤ “ብሔር ፣ ብሔረሰብ” የእሚለው ቃለ-ሐረግ “የአማራ ሕዝብ ፣ እያንዳንዱ አምሐራ” እያልን ነው የእሚሆነው ፤ ይኽ ደግሞ ትርጉም አልባ ነው የእሚሆነው ምክንያቱም ፤ የአማራ ሕዝብ የእያንዳንዱ አምሐራ ስብስብ ነው ፤ እያንዳንዱ አምሐራ ማለትም አንድ የአምሐራ ሕዝብ ማለት ነው ፤ ይኽም ደግሞ አንድ ዓይነት ነገርን በተለያየ አገላለጽ የእሚያስቀምጥ አላስፈላጊ ድግግሞሽ ነው።

የኢትዮጲያ ሕዝብ እና እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ ማለትም አንድ እና ተመሳሳይ ገልጻ እንደ ሆነው ማለት ነው።

በቋንቋ ስዋሰው መሠረት Nation የስብስብ ስም ሲባል (Collective Noun) ፤ Nationality የእሚለው እና የኢሕአዴጉ ሕገመንግሥት ብሔረሰብ ለእሚለው ቃል በምትክነት የተጠቀመበት ቃል የወል ስም (Common Noun) የሆነ እና የስብስብ ስም ለሆነው Nation (ብሔር) አሀድ የሆኑት የስብስብ ስሙ አባላት የእሚጠሩበት የወል ወይንም የጋራ ስም በመሆኑ ፤ ኹለቱም አንድ እና ተመሳሳይ ነገርን በስብስብነት እና በተናጠል አባላት ደረጃ የእሚገልጹ እንጂ በኹለቱ መካከል ምንም የትርጉም እና የደረጃ ልዩነት የአለው አይደለም።

Nation being a collective name, contains a number of Nationals which constitute it. Therefore, A Nation is a collection of the Nationals, and the Collection of the Nationals constitute the Nation. If that is so, there is no inherent difference between the two, except the difference in their form of expression, the one is the whole sum of the constituents, whereas the other is the individual parts of the whole. In this understanding, logic dictates that, the use of Nations and Nationalities as if they are two separate entities, will only be regarded as quite a logical as well as grammatical blunder.

የብሔር እና የብሔረሰቡን ጉዳይ በእዚኽ እናሳርግ እና የእዚኽን ሐረገቃል ሦሥተኛ ቃል የሆነውን ሕዝብ የእሚለውን ቃል እንውሰድ።

ሕዝብ ልክ እንደ የኢሕአዴጉ ሕገመንግሥት ብሔር ብሎ እንደ ተረጎመው Nation እንደ እሚለው ቃል የስብስብ ስም (Collective Noun) የሆነ እና በባሕሪውም ኹሉን አካታች የሆነ ቃል ነው።

ለምሳሌ ፦ የዓለም ሕዝብ ማለት እንችላለን ፤ የዓለም ብሔር/ነገድ ወይንም በእንግሊዘኛው The Global Nation ማለት ግን አንችልም። ምንም እንኳን Nation ወይንም ብሔር እንደ ሕዝብ ፤ የስብስብ ስም (Collective Name) ቢሆንም ፤ ኔሽን ውስን የሆነ የሰዎችን ስብስብ የእሚወክል ሲሆን ሕዝብ ግን ከማንኛውም ገደብ የተላቀቀ እና ማንኛውንም የሰው ስብስብ መወከል የእሚችል ቃል በመሆኑ።

ይኽም በመሆኑ ምንም እንኳን በልማድ ሕዝቦች ሲባል የእሚሰማ ቢሆንም በስዋሰው ሕግ መሠረት ሕዝቦች አይባልም ፤ ምክንያቱም ሕዝብ የእሚለው ቃል በባሕሪው እንደ መጨረሻ ትልቁ ከረጢት ፤ ማንኛውንም ዓይነት የሰው ልጅ ስብስብ የዓለምንም የቅርጽ ልዩነት የእሚወጥ ቃል በመሆኑ።

በአንድ ቦታ ላይ ፦ ነጭ ፣ ጥቁር ፣ ቡናማ እና ቢጫ የቆዳ ቀለም የአላቸው ሰዎች ፤ ከእነ እዚኽም ፈንጠር ብለው የወታደር የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች ፣ ከእነርሱ ትንሽ ራቅ ብለው የስፓርት ትጥቅ የለበሱ የተለያዩ ሐገራት የስፖርት ቡድኖች ፣ ከእዚያኽም ፈንጠር ብለው የአንድ ነገድ ሕዝብ ፣ ከእዚያም አለፍ ብለው የአንድ ጎጥ/ጎሳ ነዋሪዎች ቢሰበሰቡ ፣ በአጠቃላይ ምንም ዓይነት የሰው ልጆች ስብስብ ፤ በውስጡ በነጠላም ሆነ በቡድን ብዙ ዓይነት ልዩነት ቢያቅፍ ፤ ምንም ሳንቸገር እነ እዚኽን የሰዎች ስብስብ ፤ በፖለቲካዊ እና በባሕላዊ አወቃቀራቸው ሳንወሰን ሕዝብ በእሚለው ቃል ልንጠራው እንችላለን።

ሕዝብ ማንኛውንም የሰው ልጅ ስብስብ ለመግለጽ የእምንጠቀምበት የስብስብ ስም (Collective Noun) የሆነ ቃል በመሆኑ ፤ ሕዝቦች ብሎ ብዙ ቁጥር ማለት ትርጉም አልባ እና ስህተት ነው በቋንቋ ስዋሰው ።

ሕዝብ የእሚለውን ቃል ማንኛውንም የሰው ስብስብ የእሚወክል እንዳይሆን ከተፈለገ የእሚደረገው ፤ ከፊቱ ወይንም ከኋላው እንደ ቋንቋው ስዋሰው መለያ (It would be qualified) እንዲገባበት ይደረጋል ፤ ለምሳሌ ፦

  • የኢትዮጲያ ሕዝብ
  • የአሜሪካ ሕዝብ
  • የኬንያ ሕዝብ

ይኽም በመሆኑ የኢትዮጲያ ሕዝቦች አይባልም ፤ ይልቁንም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ።

ስለ እዚኽ ፦ ሕዝብ ነገድን ፣ ጎጥን ፣ ወዘተ ፣ አካታች እና እንደ አውዱም የአንዱ ነገድ ሰዎች በሙሉ ሕዝብ ተብለው መጠራት ይችላሉ ፤ እንጂ ሕዝብ የእሚባሉት ከብሔር እና ከብሔርሰብ ሲበልጡ ነው የእሚባል ነገር የለም።

ሕዝብ የእሚለው ቃል ይኽን ዓይነት ትርጓሜ ከሆነ የአለው ፤ የኢሕአዴጉ ሕገመንግሥት በኢትዮጲያ ውስጥ ሕዝብ የእሚባሉ እና ሕዝብ የእማይባሉ የሰዎች ስብስብ አሉ ወይንም በኢትዮጲያ ውስጥ ከሌላው የዜጎች ስብስብ በተለየ ለብቻቸው ሕዝብ የእሚባሉ የዜጎች ስብስብ አሉ የአለበት አግባብ ፈጽሞ ስህተት ይሆናል።

በእነዚኽ ምክንያት ፦ በኢሕአዴግ ሕገመንግሥት ላይ ፦ እኛ የኢትዮጲያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፤ የእሚለው አገላለጽ ፤ ከፍተኛ የሆነ የጽንሰ ኃሳብ እና የስዋሰው ስህተት የአለበት ነው።