አዕምሮዋዊ ፍርድ እንደ እሚነግረን ወይንም ተፈጥሮ ለሰው ልጅ ያጎናፀፈው ፥ አካላዊ እና አዕምሮዋዊ ብቃት ፤ ዓለም እና ሞላዋን ፦ እንስሳቱን ፣ ዕፅዋቱን እንዲሁም የተፈጥሮ ኃብቱን በበላይነት ለራሱ ጥቅም ለመጠቀም በእሚያስችልበት ኹኔታ ተዘጋጅቶ መገኘቱ እንደ እሚያስረዳን ፤ ምድር እና ሞላው የሰውን ልጅ የመኖር ኺደት እንዲያግዝ እና እንዲያሻሽል ተደርጎ የተፈጠሩ መሆኑን ነው።
አንድ አረንጓዴ ተክልን ብንወስደው ፤ አፈጣጠሩ ፥ መሬትን እና በመሬት ውስጥ የእሚገኙትን መዓድናት ፣ ውኃን እና ከባቢያዊ አየሩን ተጠቅሞ እንዲያድግ እና ራሱን እንዲያባዛ ስለአቀናጀለት ፤ መሬቱ ፣ መዓድናቱ ፣ ውኃው እና ከባቢያዊ አየሩ ለተክሉ የተፈጠሩ እንደ ሆነ እንገነዘባለን።
እንሰሳውንም ብእንወስደው ፤ እንደ ፍጥረቱ ዓይነት አረንጋዴ ተክል በሊታውም (The Herbivores) ሆነ ስጋ በሊታው (The Carnivores) ፤ ለሕይወት የእሚያስፈልገውን እና ራሱን ለማባዛት የእሚችልበትን ኹኔታ በተፈጥሮ ተመቻችቶለት እና ከተፈጥሮው ጋር ተቀናጅቶ ስለ እምናይ ፤ እንሰሳው በህይወት ለመኖር እና ራሱን ለማባዛት የእሚያስፈልጉት ነገራት በተፈጥሮ እንደ ተሰጡት እንረዳለን።
የሰማይ በራሪው ወፍ እና ባሕር በርባሪው የዓሳ ዝርያም ፤ ተፈጥሮ ሕይወቱን የእሚያስቀጥልበትን እና ራሱን የሚያባዛበትን ኹኔታ ከተፈጥሮው ጋር በተቀናጀ መልኩ አቅርቦሎት ስለ እምናይ ፤ አዕዋፍ እና አሳዎች በህይወት ለመኖር እና ራሳቸውን ለማባዛት የእሚያስፈልጉዋቸው ነገራት በተፈጥሮ እንደ ተሰጡዋቸው ስለ እምንረዳ ፤ የአየር ንብረቱ እና የውኃው አካል ለአዕዋፍ እና ለአሳ ዝርያዎች ተፈጥሯል እንላለን።
በአጠቃላይ ፤ የስነ ህይወት (Biology) መስክ እንደ እሚያስተምረን ፤ ሕይወት የአላቸው ፍጥረታት የየትኛውንም ሌላ ፍጥረትን ፈቃድ ሳይጠይቁ ፤ ለተፈጥሮዋቸው እና ለመራባት የእሚያስፈልጋቸውን ከባቢ (Habitat) ፤ በተፈጥሮ ውስጣቸው በተጻፈው ሕግ እየተመሩ ፤ መርጠው እንዲኖሩበት ፣ ምግባቸውን እንዲ ያገኙበት እና እንዲ ራቡበት ሆኖ ከተፈጥሮዋቸው ጋር በተቀናጀ መልኩ አለ ።
እንደ ገናም በሌላ የተፈጥሮ መርህ ፤ ፍጥረታት በህይወት ለመቆየት ፤ በምግብ እና በተመጋቢ ተከፋፍለው ፤ የምግብ ሰንሰለት ወይንም ተዋረድ (Food chain or Pyramid) የእሚባለውን ይሰራሉ ።
በእዚኽ የምግብ ሰንሰለት ወይንም ተዋረድ ፤ አረንጓዴ ተክሉ ከመሬት የእሚገኘውን ንጥረ ነገር ፣ ውኃ እና አየሩን ምገው ራሳቸውን ያሳድጋሉ ፣ ሳር በሊታው እንሰሳም ተፈጥሮ በአቀረበችላቸው መኖሪያ እና ምግብ አሸብርቀው ያሉትን እፅዋት ይመገቡዋቸዋል ፣ እንስሳ አዳኙም እንሰሳ በተፈጥሮ የአሸበረቁትን እፅዋት ተመግበው የሰቡትን እንሳሳት ይመገቡዋቸዋል ።
ሳሩ ከመሬት ንጥረ ነገር ውስዶ እንዲያድግ የአስቻለው በተፈጥሮ በውስጡ የያዘው የሕይወት ስረዓት ነው ፤ ስለ እዚኽ ፦ ተፈጥሮ ንጥረ ነገሩን ፣ ውኃውን እና አየሩን ለዕፅዋቱ ምግብ አድርጎ ሰጥቷል እንላለን ። ሚዳቋዋን ሳሩን ተመግባ እንድታምር የአደረገው በውስጧ የአለው የሕይወት ሕግ ነው ፤ ስለ እዚኽ ፦ ተፈጥሮ ሳሩን ለሚዳቋዋ ምግብ አድርጎ ሰጥቷል እንላለን ፤ አንበሳውን እንደ ሚዳቋዋ ሳር ሰአይሆን ሚዳቋዋን እንዲመገብ የአደረገው በውስጡ የአለው የሕይወት ሕግ ነው ፤ ስለ እዚኽ ፦ ተፈጥሮ ሚዳቋዋን ለአንበሳው ምግብ አድርጎ ሰጥቷል እንላለን።
በምድራችን ላይ የሕይወት ዑደት በተዋቀረበት በእዚኽ አግባብ ፤ የሰው ልጅ ከሰው በስተቀር ፤ ዓለም እና ሞላዋን ለእራሱ ጥቅም የህዋውን ፣ የየብሱን እና የባሕሩን ፍጥረት በሙሉ እንዲጠቀም ፤ ተፈጥሮ የሰውን ልጅ የላቀ አዕምሮ እና የተመቸ ተክለ ሰውነት በማጎናፀፍ ወይንም ከሌሎቹ ምድራዊ ፍጥረታት የላቀ የሕይወት ሕግ በውስጡ በማኖር ፤ በእዚኽም የምድር እና የሌሎች ፍጥረታት ኹሉ ገዢ እንዲሆን ተፈጥሮ እርሱንም አከባቢውንም አመቻችታ ፈጥራለታለች ፤ ስለ እዚኽ ፦ እኛም ይኽን ተከትለን ፤ ዓለም እና ሞላዋ ፦ እንስሳቱ ፣ ዕፅዋቱ እንዲኹም የተፈጥሮ ኃብቱ ለሰው የተፈጠረ ነው ፤ እንላለን ።
ሰው ከሌሎች ፍጥረታት ኹሉ ፤ በግንዛቤው እና በአደራረጉ ልቆ ፤ ዓለምን እና ሞላዋን ለጥቅሙ እንዲጠቀም ወይንም ዓለምን እንዲገዛ ተፈጥሮ ልዩ ባሕሪ አላብሳዋለች ፤ ይኽም ምድር እና ሞላዋ ለሰው ልጅ ተፈጥረዋል የእሚለውን አመክንዮዋዊ ድምዳሜ ያስከትላል ።
የሰው ልጅ በእዚኽ መልኩ ፤ ተፈጥሮን ከመግዛት በአሻገር ፤ እርስ በእርሱ (ሰው ከሰው) ጋር የአለውን ግንኙነት የእሚዳኝበት ፤ በሌሎች ፍጥረቶች ከእሚታየው የላቀ ፤ አስገራሚ ፤ ከዘመን ዘመን እየላቀ የእሚሔድ እና ስልጣኔንም የእሚያስችል የሰው መንግሥት አለው ።
በእርግጥ ሌሎቹም ፍጥረታት ፤ የራሳቸው መንግሥት አላቸው ወይንም የአላቸው አሉ ፤ የእነዚኽ ፍጥረታት መንግሥት ግን ፤ ከሰው መንግሥት በይዘቱ በጣም የተለየ ነው ።
የንቦችን መንግሥት ብእንወሰድ ፤ በታሪክ የዛሬ 5 ሺ ዓመት የነበራቸው መንግሥት ባሕሪ እና ዛሬ የአላቸው መንግሥት ባሕሪ አንድ ነው ። በፍጥረት ደረጃ ፤ ሠራተኛው ንብ ድንጉላ መሆን አይችልም ፣ ንግሥቲቱም ሠራተኛ መሆን አትችልም ፣ የንግሥቲቱ እና የሠራተኛው ንብ ተግባርም ከታወቀበት ግዜ አንስቶ ተቀይሮ አያውቅም ፤ ያም ብቻ ሰአይሆን የንብ መንጋ ፤ ማር ከማምረት ውጭ በሌላ ተግባር ተሰማርቶ ታይቶ አይታወቅም ።
የሰው ልጅ መንግሥት ግን ፤ ምንም እንኳን ከተፈጥሮ ዝንባሌ ቢመነጭም ፤ ሌሎች እንስሳት ጋር በሌሉ እና የሰው ልጅ ጋር ብቻ በአሉ ፦
ምክንያት ፦ ሰው ከሰው ጋር የአለውን ግንኙነት የእሚገዛበት ፤ ይዘቱ እና ቅርፁ እንደ ተዋናያኖቹ ግንዛቤ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መንገድ የእሚያድግ እና ተፅኖ የእሚፈጥር ፤ ከሌሎች ምድራዊ ፍጥረታት መሰል ‘መንግሥት’ በባሕሪው እና በውስብስብነቱ የእሚለይ እና የእሚልቅ መንግሥት ነው።
የሰው መንግሥት ፤ በሰው ሰፊ የተፈጥሮ ቁመና የእሚመዘን ፤ ሰፊ እና ባለ ብዙ ፈርጅ ነው ።
ይኽም ምዕራፍ ለሰው ልጆች ጥቅም በምድራዊ ፍጥረት ኹሉ ላይ የእሚገዛውን ሰውን ፤ የእርስ በእርስ ግንኙነቱን የሚዳኝበትን መንግሥት ፤ የሰው ስልጣኔ ከጀመረበት አንስቶ አሁን እስከ አለንበት እና ተመራጭ እስከ እሚባለው ፤ በነፃነት ዴሞክራሲ እስከ የእሚቋቋመው ፤ ሕገመንግሥታዊ መንግሥት (Constitutional Government) የአለውን ኺደት ፤ የሰው መንግሥት በእሚል ፤ የጎላ ፖለቲካዊ እንደምታ በአላቸው ኹነቶች ላይ በማተኮር ያቀርባል ።