የሰው ልጅ ታሪክ ፤ በኹለት ዋንኛ መደቦች ተከፍሎ ይጠናል ።
የመጀመሪያው ቅድመ-ታሪክ ሲባል ፤ ዓለም በእግዚአብሔር ሰአይሆን ፤ በዝግመታዊ ነገር ግን ድንገታዊ ዑደት ነው የተፈጠረችው ብለው በእሚያምኑት ቡድኖች ትንታኔ መሠረት ፤ የዛሬው ማሕበራዊ[1] ፍጥረት የሆነው ሰው ፤ የዛሬውን ሰብዓዊ ቁመና ከመያዙ በፊት ፤ የዛሬውን ሰው እስኪ ሆን ድረስ የአለፈበትን የመፈጠር ኺደት የእሚያጠናው ነው ።
ቅድመ ታሪክ ፤ በዝግመታዊ የለውጥ ቲየሪ መሠረት ፤ ከ 13.5 ቢልየን ዓመታት አስቀድሞ ፤ ህይወት አልባ በነበረው የአቧራ ጉም ወይንም ጢስ ውስጥ ፤ ታላቁ ፍንዳታ (The Big Bang) ተካኺዶ ፤ በፍንዳታዉ በተቀጣጠለው ኬሚካላዊ ዑደት ፤ ከጥቃቅን ህዋሳት አንስቶ ፤ በረዥም ግዜ ኺደት የዛሬ 4.5 ቢልየን ዓመታት ገደማ የአቧራው ብናኞች ወደ አንድ ጥጥር ዓለትነት እየተቀየሩ ምድረ መሬት (Planet Earth) እንደ ተፈጠረች ፤ ከ3.8 ቢልዮን ዓመታት አስቀድሞ ደግሞ ህይወት የአላቸው ህዋስ አካላት መታየት እንደ ጀመሩ ፤ እነ እዚኽም ህዋሳት እንደገና ሌላ በቢልየን የእሚቆጠሩ ዓመታት ውስጥ በቆየ ለውጥ እነ ሉሲን መሰል ፍጥረቶችን የዛሬ 1.6 ሚልዮን ዓመታት በፊት አምጥተው ፤ ከእዚያኽም ከብዙ የመፍጠር እና የማጥፋት ኺደት በኋላ ፤ ከዛሬ 40 እና 50 ሺ ዓመታት ገደማ በፊት ፤ ዛሬ ሰው ብለን የእምናውቀው ሰብዓዊ እና ማሕበራዊ ፍጡር ጋር የእሚቀራረቡትን እና ኒያንደርታልስ በመባል የእሚታወቁትን ፍጥረታት አመጣ ፤ ተብሎ ይታመናል ።
ኒያንደርታልስ የእሚባሉት ሰው መሰል ፍጥረታት ፤ ከዛሬው ሰው ጋር እጅግ ተቀራራቢ የኾኑት (ነገር ግን ከዛሬው ሰው በእሚገባ የእሚለዩት) ሰው መሰል ፍጥረታት የዛሬ 40 እና 50 ሺ ዓመታት ገደማ ከመጡ በኋላ ፤ የመጀመሪያውን ከ30 ሺ ዓመታት በላይ የሆነውን ግዜ ፤ በምድር ላይ በነበረ እንደ ግግር በረዶ በአሉ አስቸጋሪ ተፈጥሮዋዊ ኹናቴዎች እንቅስቃሴያቸው የተገታ እና መሠረታዊ ፍጥረታቸውም ይኽ ነው የእሚባል ማሕበራዊ ተግባር መከወን የእሚያስችላቸው የነበረ በአለመኾኑ ከዛሬው ሰው ጋር የእሚነፃፀር ማሕበራዊ ታሪክ አልነበራቸውም ይላል የቅደመ ታሪኩ የሰው ዝግመታዊ አመጣጥ ጥናት።
ይኽ በእንዲኽ እንደ አለ ፤ በእዚኽ የቢልየን ዓመታት ዝግመት ዑደት ከተፈጠሩት ሰው መሰል ፍጥረታት ጋር የእሚያገናኘው ይኽ ነው የእሚባል ገመድ የአልተገኘለት ጠቢቡ ሰው (Home Sapiens, or in English ‘The wise man’) የእሚባለው ሰው የዛሬ 10ሺ ዓመታት ገደማ ሲከሰት ፤ ሌሎቹ እንደ ኒያንደርታል ያሉት ሰው መሰል ፍጥረታ ድንገት እልም ብለው ከምድረ ገጽ ስለ ጠፉ (They go extinct) ፤ የዝግመት ሳይንስ የዛሬው ሰው ወይንም ማሕበራዊ ሰው ከ10 ሺ ዓመታት ገደማ ጀምሮ እንደ ነበረ ነው የእሚያውቀው ።
ስለ እዚኽ ፦ ቅድመ-ታሪክ ከማሕበራዊ ርዕስነት ይልቅ የተፈጥሮ ሳይንሳዊነቱ የእሚያመዝነውን እና በቢልየን እድሜ የእሚቆጠረውን ፤ ከአቧራ ጉምነት እስከ ታሪክ ሰሪው ሰብዓዊ ማሕበራዊ ሰውነት የአለውን የስነፍጥረት ኺደት የእሚያጠና የተፈጥሮ ታሪክ ዘርፍ ነው ።
ሠንጠረዥ 4፡ የፖለቲካዊው ሰው ዝግመታዊ አፈጣጠር የግዜ ሰሌዳ በዝግመታዊ አፈጣጠር ትንታኔ መሠረት።
ስለ እዚኽ ፦ በዝግመታዊያኑ ቲየሪ መሠረት ፤ የእሚደመረው ተደምሮ የእሚቀነሰው ተቀንሶ ፤ የዛሬው ታሪክ ሰሪው ማሕበራዊው ወይንም ፖለቲካዊ ሰው ከእነ የተሟላ ሰዋዊ ተክለ ቁመናው እና አዕምሯዊ ብቃቱ ጋር የተፈጠረው ወይንም የተከሰተው ፤ የዛሬ 10 ሺ ዓመት ነው ።
ስለ እዚኽ ፦ የቅድመ ታሪኩን የሰው ልጅ አመጣጥ ጠቅለል አድርገን ስናስቀምጠው ፤ ከዛሬ 13.5 ቢልየን ዓመት እስከ ዛሬ 10 ሺ ዓመት የተካኼደው የ13.5 ቢልየን ዓመታት ኺደት ወይንም ‘ታሪክ’ ፤ የአቧራ ብናኙ እንደ ሰው የአሉ ውስብስብ ፍጥረቶችን ባዮሊጂካሊ ለመፍጠር የኼደበት ዑደት ሲሆን ፤ በእዚኽ የቢልየን ዓመታት ዑደት ፤ ወደ መጨረሻ አከባቢ እንደ ሊሲ የአሉ ፍጥረታት እና በኋላም ላይ እንደ ኒያንደርታልስ የአሉ ሰው መሰል ፍጥረቶች ቢከሰቱም ፤ ከዛሬው ሰው ጋር የጎላ ልዩነት የነበራቸው ብቻም ሳይኾኑ በኺደት ስለ ጠፉ እና ከዛሬው ሰው ጋር በቀጥታ የእሚያገናኛቸው ነገር በአግባቡ ስለ እማይታወቅ ፤ የዛሬው ሰው የተከሰተው በሳይንሳዊ መንገድ ከየትኛው የሰው መሰል ፍጥረታት የትውልድ ሐረግ እንደ እሚዘዝ በአልተረጋገጠ መልኩ ፤ የዛሬ 10ሺ ዓመት ገደማ ነው ፤ የእሚል ነው ።
ዩቫል ኖኻ ኀራሪ (Yuval Noah Harari) የተባለው ሰው ፤ የዝግመታዊ ለውጥ መላምት ሆሞሳፒየነስ ወይንም ጠቢቡ ሰው እና ኒያንደርታልስ የእሚባሉትን እና ከጠቢቡ ሰው ቀደም ብለው የነበሩትን ሰው መሰል ፍጥረታት እንደ እዚኽ ያነፃፅራቸዋል ፦
“በአለፉት 10 ሺ ዓመታት ፤ ሆሞ ሳፕየንስ (ጠቢቡ ሰው) ብቸኛው የሰው ዘር እንደሆነ ተቀባይነት የአለው ከመሆኑ የተነሳ ሌላ አማራጭ ማሰብ አይቻልም ። እኛን መሳይ ወንድም እና እህት በፍጥረት ውስጥ አለ-መኖሩ ፤ ራሳችንን የፍጥረት ጉልላት አድርገን ለማየት ያቀልልናል ፥ በእኛ እና በሌሎች እንስሳት መካከል ትልቅ ገደል አለ ። … ኒያንደርታል የእሚባሉት ከሩቅ እኛን መሳይ በመሆናቸው ችላ ለማለት ያስቸግራሉ ፥ በቅርበት ሲታዩ ግን ፤ ከእኛ ጋር የአላቸው ልዩነት ደግሞ በጣም የሰፋ በመሆኑ ይቀርቡናል ለማለት ያስቸግራል ።“
“Over the past 10,000 years, Homo Sapiens has grown so accustomed to being the only human species that it’s hard for us to conceive of any other possibility. Our lack of brothers and sisters make it easier to imagine that we are the epitome creation, and a chasm separates us from the rest of animal kingdom....Neandertals They were too familiar to ignore, but too different to tolerate. [73]“
በእዚኽም ፦ በቅድመ ታሪክ ትንታኔም መሠረት ፤ የዛሬው ሰው ልጅ ፖለቲካዊ ታሪክ ህፀፅ ፤ የዛሬ 10 ሺ ዓመት ገደማ ጀምሯል ፤ ማለት ነው ።
በእዚኽ በቅድመ ታሪክ ከእሚጠኑት መካከል ከኾኑት እና ከዛሬ 1.6 ሚልየን ዓመታት ገደማ በፊት አንስቶ ነበሩ የእሚባሉት ፤ እነ ሉሲ አንስቶ የዛሬ 10 ሺ ዓመት ገደማ ብቻውን እስከ ቀረው ጠቢቡ-ሰው ወይንም ሆሞ ሳፕየንስ ድረስ ፤ የነበሩት ሰው መሰል ፍጥረታት ፤ እንደ ሰው ማሰብ ፣ መናገር እና መጻፍ የእማይችሉ ስለ ነበሩ እና ከሆሞ ሳፕየነስ ጋር የአላቸው የዝምድና ገመድ በውል ስለ እማይታወቅ ፤ እንዲኹም ከደመነፍሳዊ እንስሳት የአለፈ ማሕበራዊ ብሎም ፖለቲካዊ ህልውና ስለ አልነበራቸው ፤ ለአኹኑ የሰው ልጅ የፖለቲካ ታሪክ ጥናት ምንም የእሚያበረክቱት ነገር የለም ።
ኹለተኛው የታሪክ ጥናት መደብ ፤ ድህረ ታሪክ (የኋለኛው ታሪክ) ወይንም በተለምዶ ታሪክ ፤ የእሚባለው ነው ።
ይኽ የታሪክ ጥናት መደብ ፤ የዛሬው ሰብዓዊ እና ማሕበራዊ ፍጡር የሆነው ሰው (እኛ) ፤ የእሚያስብ ፣ የእሚናገር እና ፈርጀ ብዙ ተግባራት የእሚተገብረው ሰው ፤ እንዲኹም ከሌሎቹ ሰው መሰል ፍጥረታት በመሠረታዊነት የእሚለውየው ፤ ታሪኩን በጽሑፍ ማስፈር ከጀመረበት ወይንም የሰው ልጅ ስነ ጽሑፍን ከአዳበረበት ግዜ አንስቶ የአለውን የሰውን ታሪክ የእሚያጠና ነው ።
ኹላችንም እንደ እምናውቀው ፤ የስነፍጥረት መላምት ኹለት ነው ። አንደኛው ፤ ከእላይ ጠቅለል አድርገን ለማስቀመጥ የሞከርነው የዝግመታዊ ለውጥ ቲየሪ/መላምት (Evolutionary Theory) ሲሆን ፤ ኹለተኛው ፥ ከእርሱ በተቃራኒ የእሚገኘው እና በእግዚአብሔር ፈጣሪነት የእሚያምነው የፍጥረት ቲየሪ/መላምት (Creationism Theory) ነው ።
በፍጥረታዊያኑ መሠረት ፤ እግዚአብሔር ፦ የዛሬ 8 ወይንም 7 ሺ ዓመት ቀደም ብሎ ዓለምን እና ሞላውን በአምስት ቀን ፤ ሰውን በስድስተኛው ቀን እንደ ፈጠረ እና እግዚአብሔር ያን ግዜ የፈጠረው ሰው ፤ ዛሬ የአለው ሰው መሆኑን እና ፖለቲካዊ ታሪኩም እዚያው ፤ ማለትም የዛሬ 8 እና 7 ሺ ዓመታት አከባቢ እንደ ጀመረ ይታመናል።
እነ እዚኽ ኹሉት ተቃራኒ የስነ ፍጥረት መላምቶች ፤ ፖለቲካዊው ሰው በተፈጠረበት አግባብ ላይ ልዩነት ቢኖራቸውም ፤ ማለትም ፦ አንዳቸው ፤ ዓለም ብሎም ሰው ፤ ያለ ፈጣሪ በቢሊየን በእሚቆጠሩ ዓመታት በተደረጉ የዝግመታዊ ለውጥ (Evolution) ኺደት ተፈጠሩ ቢሉም እና ሌላኛዎቹ በእግዚአብሔር በስድስት ቀን ተፈጠሩ (Creationist) ብለው ቢያምኑም ፤ ስለ ሰው ልጅ ስልጣኔ ታሪክ የግዜ ሰሌዳ በተመለከት ግን ልዩነት የላቸውም።
ምክንያቱም ፦ የሰው ልጅ ታሪክ አጥኝዎች ፤ በእሚያምኑት የስነ ፍጥረት መላምት ሰአይገደቡ ፤ የእሚስማሙት አንድ ጉዳይ ፤ በተለምዶ ታሪክ ብለን የእምናጠናው ክፍለ ግዜ የጀመረው ፤ የሰው ልጅ ስነ ጽሑፍን ከአዳበረበት ከዛሬ 5,200 ዓመታት ገደማ አከባቢ ጀምሮ ነው በእሚለው ነው ።
በሌላ አገላለፅ ፤ የታሪክ ጥናት የእሚሸፍነው ፤ ዝግመታዊያኑ ተፈጥሮ በቢልየን በእሚቆጠሩ ዓመታት በማንሳት እና በመጣል የዛሬ 10,000 ዓመት ገደማ አመጣችው የእሚሉትን ሆሞሳፒየነስ (ጠቢቡ ሰው) ወይንም በአምላክ ፈጣሪነት የእሚያምኑት እግዚአብሔር በታላቅ ጥበቡ የዛሬ 8 እና 7 ሺ ዓመት ገደማ በአንድ ቀን ፈጠረው ብለው የእሚያምኑት ፍጥረት አምላክ የሆነው ሰብዓዊው ሰው ታሪካዊ ድርጊት ነው ።
ይኽም ድህረ ታሪክ የእሚባለው ታሪክ የእሚያጠናው የዛሬ 5,200 ፤ ይኽ ፖለቲካዊው ፣ ሰብዓዊው ፣ ጠቢቡ ሰው ስነ ጽሑፍ ከጀመረበት ግዜ አንስቶ የአለውን ነው ።
ስለ እዚኽ በእነዚኽ ኹለት የስነ ፍጥረት ቲየሪዎች ወይንም መላ ምቶች መካከል ፤ ታሪክን በተመለከተ የአለው ልዩነት ፤ በማን ፣ በምን ያኽል ግዜ እና እንዴት ተፈጠርን? የእሚለው ጥያቄ ላይ ነው እንጂ ፤ ፖለቲካዊ እና ማሕበራዊ ስልጣኔ ባለቤት የሆነው ሰው ፥ ወይንም በእዚኽ ንዑስ ክፍል ርዕስ ላይ ፖለቲካዊው ሰው የአልነው ወይንም የዛሬው እኛ የእምናውቀው ታሪካዊው ሰው ላይ የአላቸው ልዩነት ከዛሬ 5200 ዓመታት ቀደም ብሎ ፤ ማለትም የሰው ልጅ ስነ ጽሑፍ ሳይጀምር በፊት ባለው ታሪክ ላይ ነው።
በእዚኽም ላይ የአላቸው ልዩነት እዚኽ ግባ የእሚባል አይደለም።
ምክንያቱም ፦ እንደ ዝግመታዊያኑ መሠረት ፤ ፖለቲካዊው ሰው ከዛሬ 10 ሺ ዓመት በፊት ተከሰተ ሲሉ ፤ ፍጥረታዊያኑ ደግሞ እንደ ስሌታቸው ፤ እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው ከዛሬ 6,700 – 7,800 ገደማ በአለው ግዜ ውስጥ ነው ይላሉ ።
ይኽም ማለት ፤ ፖለቲካዊ ሰው በተከሰተበት ዘመን ላይ የአላቸው ልዩነት ፤ ከ2 ሺ ዓመታት ትንሽ የእሚበልጥ ሲሆን ፤ ይኽም የ2 ሺ ዓመታት ልዩነት ፤ ኹለቱም መላምቶች የሰው ልጅ ስነ ጽሑፍ አዳበረ ብለው ከእሚያምኑበት ፤ ከክርስቶልስ ልደት 3,200 ዓመታት በፊት ወይንም ከዛሬ 5,200 ዓመት ቀደም ብሎ በአለው ዘመን በፊት በመሆኑ ፤ በሰው ልጅ ፓለቲካዊ ታሪክ ጥናት ላይ የአለው ፋይዳ እምብዛም ነው ።
ምክንያቱም ፦ ከዛሬ 8 ሺ ዓመት በፊት የነበረ ይኽ ነው የእሚባል የፓለቲካዊ ማሕበረሰብ የስልጣኔ ታሪክ በዓለም ላይ የሌለ በመሆኑ ፤ የሰው ልጅ እንደ ዝግመታዊያኑ እምነት የዛሬ 10 ሺ ዓመት ይከሰት ወይንም እንደ ፈጣሪ አማኞቹ የዛሬ 8 ሺ ዓመት ይከሰት ፤ በእዚኽ መካከል በአለው የ2 ሺ ዓመት ፤ ማለትም ከዛሬ 8 – 10 ሺ ቀድም ብሎ በነበሩት ዓመታት ፤ የተከወኑ ከቁጥሩ የእሚገቡ ፖለቲካዊ ታሪኮች ወይንም ስልጣኔዎች አልነበሩም ።
ስለ እዚኽ ፦ የእዚኽ የማሕበራዊው ሰው ወይንም የፖለቲካዊው ሰው ፤ ትርጉም የአለው ታሪክ ፤ ሰዎች በእሚያምኑበት የስነ ፍጥረት መላምት ሰአይወሰን ፤ በግርድፉ የ5 እና 6 ሺ ዓመት እድሜ የአለው ነው ።
በእዚኽ ረገድ ፤ በዓለማችን ፥ በስልጣኔው ጥልቀት እና በቆይታ ዘመኑ ፤ የመጀመሪያ የእሚባለው ፤ ከክርስቶስ ልደት በፊት ፤ የዛሬ 3,200 ዓመታ ገደማ የደረጀው የግብፅ ስልጣኔ[2] ነው ።
በተመሳሳይ ወቅት ፤ በዛሬዎቹ ደቡባዊ ኢራቅ እና በሰሜን ምዕራብ ኢራን የሜስፖታሚያ ስልጣኔ እና በዛሬዋ ፓኪስታን ፤ የኢንዱስ ሸለቆ ስልጣኔዎች ቢኖርም ፤ በብዙ መልኩ የግብፅ ስልጣኔ ከእነዚኽ ኹለት እኩያ (contemporary) ስልጣኔዎች የላቀ ነበር ።
ታሪካዊ ስልጣኔ ፤ በቀዳሚነት እና በዋናነት በእነዚኽ ሦሥት አከባቢዎች ከጀመረ በኋላ ፤ በንግድም ፣ በጦርነትም በስደትም ወደ አራቱም አቅጣጫዎች በዓለም ላይ ተስፋፍቷል ። ከእዚኽም የተነሳ ፤ በዓለም ላይ የመጡ ኹሉም ስልጣኔዎች ፤ የእነዚኽ ሦሥት ቀዳሚ ስልጣኔዎች ‘የመንፈስ’ ልጆች ናቸው ።
በእዚኽ አግባብም ፤ ስልጣኔ ድንበር አቋርጦ ባሕር ተሻግሮ ሲኼድ ፤ በደረሰቦት ቦታ የበለጠ እየተሻሻለ እና እየጠራ ዛሬ የአለንበት ደረጃ ላይ ደርሷል ።
ታዋቂው ፤ የእንግሊዙ አይዛክ ኒውተን እንደ አለው ፦
“ከሌሎች የተሻለ ፤ አሻግሬ ማዶ ማየት የቻልኹት ፤ ከእኔ በቀደሙት ትላልቅ ሰዎች ትከሻ ላይ ስለቆምሁ ነው”
ወይንም የእዚኽ አባባል የመጀመሪያ ባለ ታሪኮቹ ግሪኮች ፦
“በረጅሙ ሰው ትከሻ ላይ የቆመው ድንክዬ ፤ ከረጅሙ ይልቅ አድማሱ ይሰፋል”
እንደ እሚሉት ፤ የኋለኞቹ ስልጣኔዎች ቀዳሚውን ስልጣኔ ግብዓት እየ አደረጉ ፤ በቀዳሚው ስልጣኔ መሠረት ላይ የራሳቸውን አስተዋፆ እና ማሻሻያ በማድረግ ፤ የሰው ልጅ ስልጣኔ ራቁቱን በደን ውስጥ ከእሚኖርበት አንስቶ ዛሬ የደረሰበትን የዴሞክራሲ ፣ የኢንደስትራላይዜሽን እና የመረጃ ቴክኖሎጂ ደረጃ ላይ አድርሰውታል ።
አኹን የአለንበት የስልጣኔ ምዕራፍ ፤ ፅንሰ ኃሳቡን የአገኘው ከአውሮፓ መሆኑ እና የአውሮፓዊያንም ስልጣኔ መሠረቱን የአደረገው ከግሪክ እና ሮም በመሆኑ ፤ ሮም በተለይም ግሪክ ፥ የስልጣኔ ኹሉ መሠረት እንደ ሆኑ ቢመስለንም ፤ የዓለም ጥንታዊ ታሪክ ጥናት እንደ እሚያመለክተን ፤ ሮማዊያን ፥ የእነርሱም የስልጣኔ መሠረት የሆኑት ግሪኮች ፤ በሮማዊያን እና ግሪክች ስልጣኔ ውስጥ አስደናቂ የኪነ ህንፃ ጥበቦች እያልን የእምን አደንቃቸውን እንደ ፓርቴኖን የአሉት ውብ ህንፃዎች ፣ የእነ ፓይታጎረስ የሦሥት ማዕዘን (ትሪያንግል) ቴረም እና የእነ ሚልተስ ስነ ከዋክብት ፣ ወዘተ ፤ አብዛኛውን ከግብፅ እና የተወሰኑትን ከፋርስ የተማሩዋቸው ናቸው ።
አርስቶትል የልዕለ ተፈጥሮ ፍልስፍናውን በአስቀመጠበት መጽሐፍ ላይ ስለ እዚኽ ጉዳይ ይኽን ይላል ፦
“ለእዚኽም ነው ኪነ ሒሳብ በግብጽ የተቆረቆረው ፤ ምክንያቱም ፦ በእዚያኽ ቀሳውስቱ ከመደበኛ ተግባር ተፈትተው ለጥናት ግዜ ስለ ነበራቸው።”
“This is why the mathematical arts were founded in Egypt; for there the priestly caste was allowed to be at leisure. [3]”
በሌላም ምሳሌ ፦ የታላቁ የጥንታዊቷ ግሪክ ደራሲ የሆመር ሥራዎች የሆኑት ፤ ኢሊየድ (Illiad) እና ኦድየሲ (Odyssey) የእሚባሉት ገድሎች ፤ ምንም እንኳን በጽሑፍ በመቅረብ ደረጃ የእሚቀድማቸው በአይኖሩም ፤ የእሚዘግቡት ታሪክ ፤ ራማያን (Ramayan) እና መኃባኃራታ (Mahabaharata) ከእሚባሉት ፤ የህንድ ሳንስክሪት ታሪኮች ጋር ተመሳሳይነት የአላቸው በመሆናቸው ፤ ለእነዚኽ የጽሑፍ ገድል መነሻ የኾኑት አፈ ታሪኮች ፤ ቢያንስ በግሪክም በህንድም የጋራ ምንጭ የአላቸው ከአልሆነም ከህንድ ወደ ግሪክ የተወራረሱ ሊሆኑ እንደ እሚችሉ ይገመታሉ ።
ኤን. ጄ. አለን (N.J. Allen) የተባለ ፤ በኹለቱ ገድሎች ላይ ያተኮረ ንፅፅራዊ ታሪካዊ ጽሑፍ የአሳተመ ሰው ፤ ገድሎቹ ተመሳሳይ የአፈ ታሪክ ምንጭ ሊኖራቸው እንደ እሚችል እንዲኽ ይላል ፦
“የእኔ ሙግት ፤ ትርክትን በተመለከተ ፤ የሳንስክሪቱ እና የግሪኩ ገድላዊ ባህል ወደ አንድ መነሻ የእሚመለስ ነው ፤ … “
“My argument is that, as narratives, the Sanskrit and Greek epic traditions go back to a common origin, … [74]“
ስለ እዚኽ ፦ በሰው ልጅ 6 ሺ ዓመት ገደማ ፤ የስልጣኔ ታሪክ ፥ ቀዳሚው እና ትርጉም የአለው ስልጣኔ ፤ የግብፅ ስልጣኔ ሲሆን ፤ በኋላ የመጡት የግሪክ ብሎም የሮም ስልጣኔዎች መሠረታቸው በዋናነት ግብፅ ነበረች ፤ ምንም እንኳን የሜሶፕታሚያ እና የኂንዱ ሸለቆ ስልጣኔዎች ፤ በተወሰነ ደረጃ ፤ ለኋለኞቹ የግሪክ እና የሮም ስልጣኔ የራሳቸው ግብዓት ቢኖራቸውም ።
አውሮፓዊያን ወይንም ‘አርያኖች’ ከእነርሱ በፊት የነበሩት ፤ የግብፅ እና የባቢሎን ስልጣኔ ወራሽ ስለ መኾናቸው ፤ ዊል ዱራንት (Will Durant) የተባለው የታሪክ ጽኃፊ እንደ እዚኽ ይላል ፦
“‘አርያኖች’ ስልጣኔን አልቆረቆሩትም ፤ ከባቢብሎን እና ከግብፅ ወረሱት እንጂ ። ግሪክ ስልጣኔን አልጀመረቸውም - ይልቁንም ከአስጀመረቸው ስልጣኔ በላይ ብዙ ወርሳለች ፤ ግሪክ ከእርሷ ቀድሞ ለ3 ሺ ዓመታት የዳበረ የኪን እና ሳይንስ እውቀት ወደ ከተሞቿ በጦርነት እና ንግድ አጋጣሚ ፤ በመምጣት የፈጠራት ‘የስለት’ ልጅ ነች ።”
“The “Aryans” did not establish civilization – it inherited it from Babylon and Egypt. Greece did not begin civilization- it inherited far more civilization than it began; it was the spoiled heir of three millenniums of arts and sciences brought to its cities from the Near East by the fortunes of trade and war. [4]“
በእዚኽም አግባብ ፤ የኋለኞቹ ስልጣኔዎች የቀደሙትን ስልጣኔዎች እየተመሮኮዙ እና በእነርሱም እየተስፈናጠሩ ፤ የሰው ልጅ የስልጣኔ ጉዞ ከዛሬ 6 እና 5 ሺ ዓመት ጀምሮ ዛሬ የአለንበት ደረጃ ላይ ደርሷል ። አኹን የአለንበትን ዘመናዊ ዓለም ስልጣኔ (The Modern World Civilization ) ፤ በቀዳሚነት የመሩት እንግሊዞች ከእነዚኽ ኹሉ ከእላይ ከዘረዘርናቸው ቀደምት ስልጣኔዎች (ከግብፅ ፣ ፋርስ ፣ ህንድ ፣ ግሪክ ፣ ሮም ብኋላም መካከለኛው አውሮፓ) ብዙ በመማር ነው ፤ ከትንሿ ደሴታቸው ተነስተው ፤ ዓለምን በእውቀት እና በቴክኖሎጂ መዓዛ ለመሙላት የበቁት ።
ከእነርሱም በመቀጠል፤ የእነርሱ ቀጥተኛ ልጆች የሆኑት አሜሪካኖች ፤ በእንግሊዝ እጅግ የዳበረውን ኢከነሚያዊ እና ፖለቲካዊ እውቀት ይዘው ፤ አሜሪካን የአኹኑ ዓለም ቅናት አድርገው ገንብተዋታል ።
በአጠቃላይ ፤ ስልጣኔን በራሱ ጀምሮ በራሱ የፈፀመ ሕዝብ የለም ፤ ኹሉም ከእርሱ ከቀደሙት ተምሮ እና እርሱን አስቀጥሎ ወይንም አሻሽሎ ነው ፤ ዛሬ የደረስንበት የደረስነው ።
አኹን በዓለም ላይ የእሚገኘው ስልጣኔ ፤ የምዕራባዊያን ‘የግል’ ንብረት ሰአይሆን የዓለም ሕዝብ የብዙ ሺ ዓመታት ጉዞ ውጤት የሆነ ፤ የዓለም ሕዝብ ኹሉ የጋራ ኃብት ነው ፤ ምንም እንኳን አንዳንዶች ሕዝብ ከአንዳንዶቹ በተለየ ስልጣኔን በማዳበር እና በማስተላለፍ ውስጥ ፤ የተሻለ ወይንም የበለጠ ሚና ቢኖራቸውም ።
ዴሞክራሲ በዋናነት የግሪክ ግኝት ነው ፤ የግሪክን ዴሞክራሲ የአስቻለ ወይንም የግሪክ ዴሞክራሲን ለማፍራት የእሚያስፈልገውን ቀዳሚ ስልጣኔ ያዘጋጀው ግን የግብፅ ስልጣኔ ነው ። የግሪክ ዴሞክራሲም በተራው ፤ እንደ ወረደ ተቀብለነው አይደለም የዛሬው ዴሞክራሲ ላይ የደረስነው ። በካንተርበሪው (Canterbury) ጳጳስ አደራዳሪነት ከተፈረመው ማግና ካርታ አንስቶ እስከ ጆን ሎክ ፤ ወደ ሦሥት መቶ ዓመት በቆየ ፈታኝ ኹኔታ ፤ በእንግሊዝ በመጀመሪያ ዳብሯል ።
ዴሞክራሲ በእንግሊዝ በአሳለፈውም ኺደት ብቻም አይደለም የዛሬውን ቅርፅ የያዘው ፤ ይልቁንም አትላንቲክን ተሻግሮ በምድረ አሜሪካ ነው ዴሞክራሲ ዛሬ የያዘውን ቅርፅ እና ፋይዳ የያዘው ።
ስለ እዚኽ ፦ አንድ ሰው የእሚቀበለዉ የስነ ፍጥረት መላምት ዝግመታዊዉን (Evolutionary) የስነ ፍጥረት መላምት ይሁን ወይንም ፍጥረታዊዉን (Creationism) የስነ ፍጥረት መላምት ፤ በእዚኽ መልኩ ተወራራሽ የሆነው የፖለቲካዊዉ ወይንም የታሪክ ሰሪው ሰው ስልጣኔ ትርጉም በአለው መልኩ የጀመረው የዛሬ 5 እና 6 ሺ ዓመት ገደማ ፤ በዋነኛነት በግብፅ እና በሜሶፕታሚያ አከባቢ ነው ። ነገር ግን ፤ ስልጣኔ በእዚያኽ ከጀመረ በኋላ ፤ በተለያየ መንገድ ወደ ሌላው የዓለም ክፍል ተሰራጭቶ ፤ በእየቦታው እና በእየዘመኑ እየተሻሻለ የዛሬው ስልጣኔ ላይ ደርሷል ።
ድሕረ ታሪክም ይኽንን ፖለቲካዊው ፣ ጠቢቡ ሰው ወይንም ሆሞ ሳፒየንስ ፤ ስነ ጽሑፍን ከአዳበረበት ግዜ አንስቶ የአለውን ታሪክ የእሚያጠናው ፤ ኹለተኛው የታሪክ ዘርፍ ነው።
ይኽም በመሆኑ ፤ ስለ ሰው ልጅ መንግሥት ስእንነጋገር እንግዲህ ፤ ይኽ ፖለቲካዊው ወይንም ማሕበራዊ ሰው ፤ ይኽንን ከዛሬ 6 ሺ ዓመታት ቀደም ብሎ በግብጽ ተጀምሮ ዛሬ ላይ የደረሰውን የሰው ልጅ ስልጣኔ ዓይነት ፣ መጠን ፣ ጥልቀት እና ቆይታ ፤ ከወሰኑ የሰው ተቋማት መካከል ዋነኛ ስለ ሆነው መንግሥት ስለ እሚባለው የሰው ተቋም እየተነጋገርን ነው ማለት ነው።