ዝርዝር ጉዳዩን ትተን አንጓ አንጓው ላይ ብን አተኩር ፤ የኢትዮጲያን ፖለቲካዊ ዝግመት ፦ ኢትዮጲያ ከአክሱም ውድቀት አንስቶ የአልተሳካ ሕዝባዊ መንግሥት የመመሥረት ጥረት ውስጥ የአለ፟ች ሐገር በእሚለው አንድ ዓረፍተ ነገር ልንገልጸው እንችላለን።
በእርግጥ ለእዚኽ የአልተሳካ ሕዝባዊ መንግሥት የመመሥረት ጥረት ኢትዮጲያዊያን በራሳቸው ብቻ ተጠያቂ ናቸው ማለት አይደለም።
የአክሱም ነገሥታት ፤ እንደ ማንኛውም የዓለም ሕዝብ ፤ የዓለምን ፖለቲካ ከአናወጠው የክርስትና የሰብዓዊነት መልዕክት በምንም መልኩ ራሳቸውን የእሚያድኑበት መንገድ አልነበረም። ይኽም በመሆኑ ፤ እንደ ሌላው የክርስቲያን መንግሥት የሰብዓዊነት መልዕክቱ በፈጠራባቸው ግራ መጋባት መንግሥታቸው ተዳክሞ ፤ ጎጠኝነቱ ተበራክቶ መቀጠል ስለ አቃታቸው ፤ ወደ ሸዋ ዞረው እንደ ገና ለማንሰራራት መሞከራቸው የእሚያስመሰግናቸው እንጂ የእሚያስወቅሳቸው አይደለም።
አክሱማዊያኑ ወደ ሸዋ በእሚያደርጉት ዝውውር በተፈጠረው ክፍተት ወደ ስልጣን የመጣው የዛግዌ ስርወ መንግሥት በወቅቱ የፖለቲካ እውቀት ሸማቂ (Opportunist) ሊባል የእሚችል ቢሆንም ፤ ወቅቱ በፈቀደለት ኹኔታ ከ3 መቶ ለእሚበልጡ ዓመታት ፤ በአስቸጋሪ ኹኔታ የፖለቲካ ስልጣኑን አስጠብቆ ሐገር መምራት ስለ ሞከረ ፤ ስረዓታዊ ውድቀት አጋጥሞት መደናበር ውስጥ ለገባ ማሕበረሰብ ፤ ጥሩ እና ይበል የእሚያሰኝ ተግባር የፈጸመ ነው።
ከዛግዌም በኋላ ፤ አስክሱማዊያን በሸዋ አንሰራርተው ፤ ክርስትና ከፈጠረባቸው መደናገር ወጥተው እና የዛግዌውን መንግሥት ከስልጣን አውረደው ፤ ወደ መንበረ ስልጣናቸው ከተመለሱ በኋላ ፤ የክርስትና ውርሳቸውን ሳይለቁ ቤተክርስቲያኒቱን ግን በመንግሥት ስር እንድትገዛ አድርገው ፤ ሕዝባዊ መንግሥት በአይሆንም ፤ ከአክሱም ውድቀት በፊት ወደ ነበሩበት ጥንካሬ መመለሳቸውም እንደ እዚኹ መልካም የእሚባል ታሪክ ነው።
በሸዋ ከአንሰራሩም በኋላ ፤ ክርስትና የፈጠረው መደናበር የፈጠረው ፖለቲካዊ ክፍተት የዓለምን ፖለቲካ በከፍተኛ ደረጃ ቀይሮ ፤ ሰብዓዊያኑ ተሳዳጅ ኢሰብዓዊያኑ አሳዳጅ ከሆኑበት የጨለማው ዘመን ፖለቲካዊ ጨለማ ለመውጣት ፤ ከአውሮፓ እና ከሌሎች መንግሥታት ጋር የእሚያደርጉት ትብብር ፤ በአልተጠበቀ አዲስ ታሪካዊ ክስተት ፤ መልኩን ቀይሮ ኢትዮጲያ በታሪኳ አይታ የእማታውቀው ፖለቲካዊ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቷ ፤ የነገሥታቱ ስሕተት ሳይሆን ፤ ማንም ሊጠብቀው የእማይችል ችግር በመሆኑ ፤ ከአቅም በላይ የሆነ መጥፎ አጋጣሚ ከማለት ውጭ ሌላ ሊባል የእሚቻል ነገር የአለ፟ አይመስልም።
እስከ እዚኽ ግዜ ድረስ ማለትም ፤ እስከ 18ኛው ምዕተ ዓመት ድረስ ፤ የሰለጠነው የክርስቲያኑ ዓለም ፤ በክርስትና የሰብዓዊ መልዕክት ምክንያት ተደናብሮ ፤ ከ5ኛው ምዕተ ዓመት ጀመሮ ፖለቲካዊ ጭለማ ውስጥ ወይንም ፍልስፍናዊ ስኮላስቲዝም ውስጥ የቆየ በመሆኑ ፤ የኢትዮጲያ ነገሥታት ፤ በጠላት እና በኋላ ቀርነት ተከበው ፤ የክርስትና ውርሳቸውን ሰአይለቁ ፤ በእሚያውቁት መንገድ ሐገራቸውን ተከላክለው ከመኖር ውጭ ምንም አማራጭ አልነበራቸውም።
በእዚኽ ኹኔታ ውስጥ እያሉ ፤ ዓለም ከታሪካዊው የጨለማ እና ከፍልስፍናዊው ሶኮላስቲሲዝም ዘመን ወጥቶ ፤ በሰብዓዊነት መርህ የተቃኘ አዲስ የማሕበረ ኢከነሚ ቀመር ይዞ ሲመጣ ፤ ከመጥፎ አጋጣሚነት በስተቀር ኢትዮጲያዊያን ተወቃሽ ሊሆኑ በእማይችልበት አኳኋን ፤ የዓለም ዓቀፉ ፖለቲካ በኢትዮጲያ ላይ በአሳደረው አሉታዊ ተጽኖ ምክንያት ፤ ኢትዮጲያ ሐገራዊ አቅሟን አጠናክራ ይኽን አዲሱን በሰብዓዊነት መርህ የተቃኘውን አዲስ የማሕበረ ኢከነሚ ቀመር ተረድታ መተግበር የእምትችልበት አቅም ይዛ መገኘት አልቻለችም።
ይኽም ኹኔታ ፤ የሸዋ መዝመም ከአልነው ሸዋ እስከ አንሰራራችበት ዘመን ድረስ ፤ ሐገሪቱ በተለየ መጥፎ የታሪክ አጋጣሚ የተንኮታኮተውን ፤ ለሕዝባዊ መንግሥት ቅድመ ኹኔታ የሆነውን ፤ ጠንካራ ብሔራዊ መንግሥት በመገንባት ላይ ተወስና እንድትቀር አደረጋት ።
ድህረ ምንሊክ ይኽ ብሔራዊ መንግሥቱን ዳግም የማደላደል ትልም ፤ ሊቀለበስ በእማይችል መልኩ ቢጠናቀቅም ፤ የነበረብን የፖለቲካ ሳይንስ ማህይምነት ፤ ከዘመነ ኃይለ ሥላሴ እስከ ኢሕአዴግ ፤ የተለያየ ምክንያት እየ አቀረብን ፤ በሰብዓዊነት አግባብ የተቃኘ የማሕበረ ኢከነሚ ቀመር ወይንም ሕገመንግሥት ሳይሆን በወግ አጥባቂ እና በሶሻሊስታዊ አምባገነናዊ መንግሥትታት አስተሳሰብ የተቃኘ ሕገመንግሥት ስንመርጥ እና ስንተገብር ስለ ቆየን ፤ ምንም እንኳን የአለፈው መቶ ዓመት ኢትዮጵያ ከ1 ሺ ዓመት ወዲህ ከነበረችበት መጥፎ የዓለም ዓቀፍ ምህዳር አንጻር በጣም የተሻለ እና ለኢትዮጲያ የእሚመች ቢሆንም ፤ በመሠረታዊ የፖለቲካ ሳይንስ ግንዛቤ እጥረት ምክንያት ለሕዝባዊ መንግሥት መሠረት የሆነው ሕዝባዊ ሕገመንግሥት መቅረጽ እና ማጽደቅ ተስኖን ቆይተናል።
በእዚኽ መጽሐፍ ውስጥ ደጋግመን እንደ አልነው ፤ የሕዝብ ፖለቲካዊ ዝግመት ፤ ከማሕበረሰባዊ ስብስብነት ወደ ብሔራዊ ሐገርነት ፤ ከብሔራዊ ሐገርነት ወደ ሕዝባዊ ሐገርነት በመሆኑ ፤ ኢትዮጲያ ከአክሱም ጀምሮ ብሔራዊ ሐገር የእሚያስብላትን ኺደት የአለፈች በመሆኑ ፤ የክርስትና የሰብዓዊ አስተምህሮ ከአመጣው መደናበር አንስቶ ፤ እስከ ዛሬ ድረስ የኢትዮጲያዊያን የፖለቲካ ግብ ሕዝባዊ መንግሥት ማቋቋም ቢሆንም ፤ ከእላይ በዘረዘርናቸው ታሪካዊ ምክንያቶች በአግባቡ ሰአይሳካ ቀርቷል።
በእዚኽ ዘመን ብሔራዊ ግንባታዋን በአግባቡ ለአጠናቀቀች እንደ ኢትዮጲያ ለአለች ሐገር ፤ ሕዝባዊ መንግሥት ለማቋቋም ደግሞ ፤ በዋናነት የዜጎችን ተፈጥሮዋዊ ሰብዓዊ መብት እያከበረ የእሚያስከብር መንግሥት የእሚቋቋምበትን ሕገመንግሥት መንደፍ እና ማጽደቅ መተኪያ የሌለው ቀዳሚ ተግባር ነው።
ይኽም በመሆኑ ፤ በእዚኽ የመጽሐፉ መጨረሻ ምዕራፍ ላይ ፤ በኢትዮጲያ ከሕግ እና ሕገመንግሥት አንጻር የነበሩንን ታሪካዊ እውነታዎች በመቃኘት ፤ የኢሕአዴግ ሕገመንግስት ችግር ላይ አተኩረን (አኹን በሥራ ላይ የአለው ሕገመንግሥት እርሱ በመሆኑ) እስከ አኹን በኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ ሕገመንግሥታት ፤ ከሕዝባዊነት አንጻር የነበረባቸውን ችግሮች በመንቀስ ፤ እድሜ ጠገቡን የኢትዮጲያ የሕዝባዊ መንግሥት ጥያቄ ሊመልስ የእሚችለው ሕገመንግሥት ንድፍ አቅጣጫ ጠቋሚ በሆነ ዓይነት በማስቀመጥ ይኽን ምዕራፍ እና መጽሐፉን እንጨርሳለን።