ሕ ገ ክ ራ ሲ

marketing-image

3.2.10. ማጠቃለያ

በዘጠኝ ክፍል ከፋፍለን የአየነው የኢትዮጲያ ታሪክ ፤ በአለፈው ኹለት ሺ ዓመታት በእየዘመኑ በዓለም ዓቀፉ ማሕበረሰብ በነበረበት የስልጣኔ ደረጃ አንጻር ኢትዮጲያ የነበረችበትን ደረጃ ፤ ማለትም ፦የኢትዮጲያ የማሕበረ ፖለቲካዊ ዝግመት ታሪክ ወይንም ፍሰት በተመሳሳይ ዘመን ከሰለጠነው የዓለም ሕዝብ አኳያ ከእዚኽ በታች በአለው ግራፍ የእሚገለጽ ይመስለኛል።

ይኽ ከእላይ የአለው የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ዝግመት የእሚወክለው ግራፍ የተቀመረበት እሳቤ ይኽን ይመስላል ፦ በአንድ ዘመን ላይ አንድ ሕዝብ ከሌላው የዓለም ሕዝብ ፖለቲካዊ ዝግመት አንጻር የአለው ደረጃ ፤ ከ0 እስከ 10 በአሉ፟ ውጤቶች የእሚገለጽ ይሆናል ፥ 0 ዝቅተኛው 10 ከፍተኛው በመሆን።

በእዚኽም ኺደት ዋነኛ መመዘኛ ሕዝባዊ ጠባያት (Attributes)፤ አንድ ሕዝብ ከተበታተነ ማሕበረሰብነት ወደ አንድ ብሔራዊ መዋቅር የተሻገረበት የመጀመሪያው ሲሆን ፤ ኹለተኛው ደግሞ ከብሔራዊ ሐገርነት ወደ ሕዝባዊ ወይንም ወደ ዴሞክራሲያዊ ሐገርነት የተሻገረበት ደግሞ ኹለተኛው።

በእዚኽ ኺደትም ለምሳሌ ፦ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሆነው ሕዝብ የስልጣኔ ደረጃቸው በአንዱ ዘመን ላይ ብሔራዊ ሐገራት የመመሥረት ደረጃ ላይ ከአደረሳቸው ፤ በእዚያኽ ዘመን ብሔራዊ ሐገር ለመመሥረት የበቁትን ሕዝብ ፤ ከዘመኑ ዓለም ዓቀፍ የጠንካራ ብሔራዊ ሐገርነት መመዘኛ አኳያ እንደ ገነቡት ጠንካራ ብሔራዊ ሐገር ግምታዊ መጠን ከ1 እስከ 10 በአለ፟ ነጥብ 10 እንሰጣቸዋለን ፤ በተለያየ ታሪካዊ ምክንያት በእዚያኽ ዘመን እንደ ብሔራዊ ሐገርነት ሰአይሆን እንደ አንዳች ዓይነት ማሕበረሰባዊ ስልጣኔ እንኳን የአልተጀመሩትን 0 እንሰጣቸዋለን።

በእዚኽም መሠረት ፤ የመጀመሪያው የታሪካችን ክፍል ብለን በአየነው ቅድመ አክሱም ኢትዮጲያዊነት እንደ ስልጣኔ በወቅቱ ከእሚገኙት የዓለም ስልጣኔዎች ጋር የእሚወዳደር እና ዓለም ዓቀፋዊ እውቅና የነበረው ማሕበረሰብ በመሆኑ ፤ በወቅቱ ከነበረው ሰለጠነ ከእሚባለው ዓለም ጋር በእኩልነት የእምንታይበት ስለ ነበር ፤ የወቅቱ የኢትዮጵያ ኹኔታ ከሌላው ዓለም አንጻር መሳ ለመሳ ወይንም 10 ከ 10 የእሚሰጠው ነበር ።

ይኽም ቅድመ አክሱም የአልነው ክፍል ሲጠናቀቅ ፤ ኢትዮጲያ ከስልጣኔ ወደ አንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብነት በዘመነ አክሱም ከተሸጋገረች በኋላ ፤ በዓለም ላይ ከነበሩ አራት ኃያላን መንግሥታት አንዷ የነበረች በመሆኑ ፤ ቀዳሚ ስልጣኔዎች መካከል ተመድባ በመመዘኛችን መሠረት 10 ነጥብ የእሚሰጣት ነው።

ክፍል ኹለት ብለን በአየነው የሐገራችን ታሪክ ፤ አክሱም እና መሰል የወቅቱ ክርስቲያናዊ ኃያላን መንግሥታት ፤ የክርስትና መልዕክት ፖለቲከኞቻቸውንን መደናገር ውስጥ በማስገባቱ ምክንያት ፤ በዓለም ላይ ከነበሩ አራት ኃያላን ይመደብ የነበረው መንግሥት ፤ እንደ ሮማ አቻው መንግሥት ፤ ኹነኛ አዲሱን የሰብዓዊነቱን አስተሳሰብ የእሚመጥን የመንግሥት ቀመር በማጣት ከውስጥ የዘበጠበት እና ይኽም ሌሎች ክርስቲያናዊ የአልሆኑ መንግሥታት በተጠናከሩበት ዘመን በመሆኑ ፤ በእዚኽ ዘመን የነበረው የአክሱም መንግሥት ከመጥፋት የእማይተናነስ ውድቀት ውስጥ ስለ ነበር ፤ የዓለም ስልጣኔ ፈቅዶ ከነበረው ደረጃ በጣም ዝቅ ብሎ ስለ አለ ፤ የማሽቆልቆል ማሳያ የሆነ 3.5 የእሚል ነጥብ ተሰጥቷል።

ከእዛም ክፍል ሦሥት በአልነው ዘመነ ዛግዌ ፤ አዲስ የፖለቲካዊ መዓከል እንዲፈጠር እና ሐገር ከነበረችበት ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እንድትወጣ የእራሱ በጎ ሚና የነበረው በመሆኑ ፤ በአክሱም ውድቀት ከገባንበት ውጥንቅጥ የተወሰነ ወደ ላይ ስቦ አ­ውጥቶናል።

ቢሆንም የዛግዌው ስርወ መንግሥት በነበረበት ዘመን ተሻጋሪ የተቀባይነት ችግር ያሰበውን ያኽል መራመድ ተስኖት የነበረ ስለሆነ የወቅቱ የኢትዮጲያ መንግሥት ከዓለም ዓቀፍ የወቅቱ መንግሥታዊ ቁመና አንጻር ተነጻጻሪ በአለመሆኑ ፤ በጎ የእሚባል ነገር ግን ተወዳዳሪ የአልነበረ የእሚለውን ለማሳየት 7 ነጥብ ይዟል።

ክፍል አራት በእሚል ፤ በሐገር ውስጥ ተቀባይነት የማጣቱ ጉዳይ በዛግዌ ላይ የፈጠረበትን ችግር አስታኮ በገነባው አዲስ አቅም የዛግዌውን መንግሥት አስወግዶ ሕጋዊ የኢትዮጲያ ነጋሢ በእሚል ወደ ዙፋን የመጣው ከአክሱም ወደ ሸዋ የዞረው አክሱማዊው ስርወ መንግሥት ወደ ስልጣን ዳግም የመጣበትን ታሪክ የቃኘንበት ክፍል ላይ ፤ የሸዋው መንግሥት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ በአጭር ግዜ ውስጥ በጥቁር አፍሪካ ተወዳዳሪ የእማይገኝለት እና በአውሮፓ ስሙ የናኘ መንግሥት በመገንባቱ ፤ የወቅቱ የሸዋ መንግሥት ከነባራዊው የዓለም ስልጣኔ አንጻር መሳ ለመሳ ለመቆም የእሚችል በመሆኑ ፤ ይኽን ማንሰራራቱን ለማሳየት 10 ነጥብ ተሰጥቷል።

ክፍል አምስት በእሚል በአየነው ታሪክ ላይ ፤ ይኽ የሸዋ ማንሰራራት ግን ፤ የዓለምን ታሪክ በወሳኝነት በቀየረው የአውሮፓ ሕዳሴ እና የዘመናዊ ቀኝ ግዛት ጅማሮ ምክንያት ፤ ከፍተኛ የህልውና አደጋ ስለ ገጠመው ፤ መላ ሐገሪቱ ራቁት ቀርታ ስለ ነበር ፤ የሸዋ ውድቀት ዘመን ፤ ከዓለም ዓቀፉ ማሕበረሰብ አንጻር ኢትዮጵያ እንደ ሐገር በአትፈርስም ፤ እንደ ሐገር የመቀጠሏ ጉዳይ ፤ በአራት ትላላቅ ፖለቲካዊ ክስተቶች የሕልውና አደጋ ውስጥ ገብቶ የነበር በመሆኑ ፤ ይክን ኹኔታ የሸዋ መውደቅ በእሚል ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ሌሎች ሐገራት እያንሰራሩ ከነበረበት ኹኔታ አንጻር ኢትዮጲያ የደረሰባትን ታሪካዊ ውድቀት ለማሳየት 2 ነጥብ ተሰጥቷል።

ከእዚኽ ትርምስ በኋላ ፤ በክፍል ስድስት ፤ ከጎንደር ዳግም ወደ ሸዋ በእሚል ፤ የሸዋው ነጋሢ መዓከሉን ወደ ጎንዶር በማዞር ፤ እንደ ገና ማንሰራራት አድርጓል።

ይኽ ቢሆንም የጎንደር ማንሰራራቱ ብዙም ሳይቆይ እንደ ገና ወደ መራኮት በመግባት ፤ ነጋሢው መዓከሉን ወደ ቀድሞዋ ሸዋ በማዞር እንደ ገና ሸዋን አንሰራርቷል። ከጎንደር ወደ ሸዋ በእሚደረገው ሽግግር ውስጥ ብዙ ውጣ ውረድ ቢኖርም ፤ ኢትዮጲያ ከሸዋ መክሰም ጋር ተያይዞ ገብታበት ከነበረው ማሽቆልቆል ፤ በእየደረጃውም ቢሆን የወጣችበት ኹኔታ የአለ፟ በመሆኑ ፤ ምንም እንኳን በዓለም ዓቀፉ መመዘኛ ኋላ ቀር ብትሆንም ፤ ቢያንስ ቀኝ ግዛትን መቋቋም የቻለ ብቸኛ አፍሪካዊት ሐገር የነበረች ስለ ነበር ፤ ከዓለም ዓቀፍ መመዘኛ አንጻር ከአማካይ በላይ የእምትገኝበት ኹኔታ ለማሳየት ሲባል ፤ ዘመነ ጎንደር እና ዘመነ ሸዋ በእሚል 4 እና 6 ነጥብ በቅደም ተከተል ተሰጥቷል።

የኢትዮጲያ ፖለቲካዊ መዓከል ዳግም ወደ ሸዋ ከዞረ እና ከረጋ በኋላ ፤ የኢትዮጲያ ፖለቲካዊ ኃይላት በተነጻጻሪነት ለኢትዮጲያ አመቺ በሆነ የዓለም ዓቀፍ ፖለቲካ ውስጥ ሆነው ፤ ኢትዮጲያን ከዘመናዊነት ባቡር ላይ በማሳፈር ፤ ኢትዮጲያ በታሪክ ኹለት ግዜ እንደ ነበረችው ፤ ከቀዳሚ ስልጣኔዎች ጎራ ለማሰለፍ ሦሥት መንግሥታት የሞከሩ ቢሆንም ፤ በ20ኛው ክፍለ ዘመን በስልጣን ላይ በቆዩበት መቶ ዓመት ፤ አንድ ወደ ፊት እና ኹለት ወደ ኋላ እያሉ ፤ ከተወሰኑ የማሸብረቂያ ለውጦች (Cosmetic Changes) በስተቀር የተፈለገውን መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት አልቻሉም።

ከግማሽ በላይ የእሚሆነው የ20ኛው ክፍለ ዘመን የያዙት ኃይለ ሥላሴ ፤ በኢከነሚው ዘርፍ ትርጉም የአለው የዘመናዊነት ቃና የአለው ለውጥ ያመጡ ቢሆንም ፤ ለውጡ መሠረታዊ እና የእሚፈልገውን ያኽል ሰአይሆን ፤ በአብዛኛው ነባራዊውን መዋቅር ዘመናዊ የማስመሰል እንጂ ዘመናዊ የማድረግ ስለ አልነበረ ፤ ለውጡ ይበል የእሚያስብል ቢሆንም በተፈለገው መጠን እና ፍጥነት የተከናወነ በአለመሆኑ ፤ የሐገሪቱን ኹኔታ ብዙም አላሸጋገረውም።

በኹለተኛው የ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በኋላ የመጡት ፤ በዋናነት በኢትዮጲያ የተማሪዎች ሕብረት ጥላ ስር (የሐገር ውስጥ የተማሪዎች ሕብረት ፣ በሰሜን አሜሪካ የእሚገኙ የኢትዮጲያ ተማሪዎች ሕብረት እና በአውሮፓ የእሚገኙ የኢትዮጲያ ተማሪዎች ሕብረት) በእሚል የተሰባሰቡት የኢትዮጲያ ሊህቃን እና የነቁ ወታደሮች ፤ የግራ ዘመሙን የፖለቲካ ርዕዮት መመሪያቸው አድርገው የኢትዮጲያን ማሕበረ ኢከነሚ የተነተኑበት እና የኢትዮጲያን ማሕበራዊ ቀውስ ይፈታል ብለው የአስቀመጡዋቸው የመፍትኼ ኃሳቦች ፤ በአለውፈው 50 ዓመት ተተግብረው ፤ በአይተገበሩም ወይንም ኢትዮጲያ ከአለ እነሱ የፖሊሲ አማራጭ ውጭ በነበረችበት ብትቀጥል ኖሮ ዛሬ ልትገኝበት ከእምትችለው ደረጃ ሊያሻሽላት አልቻለም ፤ ምናልባትም ወደ ኋላ ጎትቷት ከአልሆነ።

እነ እዚኽ ሊህቃን ፤ በግራ ዘመም ፖለቲካዊ ርዕዮታቸው ላይ ተንተርሰው ፤ የኢትዮጲያ ኋላ ቀርነት መንስኤ ናቸው የእሚሏቸውን ጉዳዮች ከእዚኽ በታች በተቀመጡት አምስት የግራ ዘመም ፖለቲካዊ አባባሎች የእሚገለጹ ናቸው ፦

  1. ፊውዳሊዝም ወይንም በሐገሪቱ ሕጋዊ የመሬት በአለቤቶች ጥቂት የመንግሥት ባለምዋሎች በመሆናቸው ፤ ከእነርሱ ውጭ የአለው ሰፊው ሕዝብ (ጭቁኑ ወይንም ገበሬው) የእነርሱ መሬት ላይ በጭሰኝነት እንዲሰራ መገደዱ ገበሬውን የደኃ ደኃ አድርጎታል።
  2. ኢምፔሪያሊዝም ወይንም በሐገር ውስጥ የእሚደረጉ የውጭ ሐገር ኢንቨስትመንቶች የሐገሪቱን ኃብት በውጭ በአለ ኃብቶች ቁጥጥር ስር እንዲገባ አድርጎ ሐገሬውን ደኃ አድርጎታል።
  3. ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ወይንም የመንግሥትን ስልጣን ለግል ኃብት ማካበቻ አድርጎ መጠቀም (ሙስና) እና የእርሱ ተዛማጅ የሆነው ኮምፕራዶር ካፒታሊዝም (የውጭ ኢንቨስተሮችን ወደ ሐገር ውስጥ የእሚስብ አደገኛ ደላላ ልንለው እንችላለን) የለውጥ ማነቆ ሆኗል።
  4. ንዑስ ከበርቴነት ወይንም የሠራተኛን ጉልበት በመበዝበዝ ዓለም ዓቀፍ ኃብታም ለመሆን በጅማሮ ላይ የአሉ፟ ሐገራዊ በአለ ኃብቶች ወይንም ከበርቴዎች ፤ በአብዛኛው በችርቻሮ ፣ በማከፋፈል ንግድ ላይ የአሉ፟ ነጋዴዎች እና ጥቂት በግል በአክሲዮን ማሕበር ዘመናዊ የንግድ ድርጅቶች ማንቀሳቀስ የጀመሩ በአለ ኃብቶች በግዜ ከአልተቀጩ አድገው ዓለም ዓቀፍ ቡርዣ ይሆናሉ።
  5. የነገድ ጭቆና ወይንም በነገዳቸው ምክንያት ለፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ጭቆና የተጋለጡ ነገዶች ፤ በእዚኽ ነገዳዊ ጭቆና ምክንያት ለኢከነሚያዊ እና ፖለቲካዊ ብዝበዛ በመጋለጣቸው ፤ የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል የእሚለውን መብት ተጎናጽፈው በኢትዮጵያ ውስጥ መኖር አለባቸው ወይንም ራሳቸውን ከኢትዮጲያ ኢምፓየር አላቀው በዓለም ዓቀፉ ሶሻሊዝም ስር መግባት አለባቸው።

እንግዲኽ የዛሬ 50 እና 60 ዓመት ዋነኛ የኢትዮጲያ ማሕበረ ኢከነሚ ችግሮች እነ እዚኽ ናቸው ተብሎ ፤ ሳር ቅጠሉ ኹሉ ፦ በአላባቶች ይውደሙ እና መሬት ላራሹ ይኹን ፣ ኢምፔሪያሊዝም ይውደም እና የውጭ ሐገር ኢንቨስተሮች ንብረት ይወረስና መንግሥት ያስተዳድረው ፣ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊስም የእርሱም የቅርብ ዘመድ ኮምፕራዶር ካፒታሊዝም ወይንም አደገኛ ደላልነት ይውደመና የሐገርን እና የሕዝብን ኃብት ለውጭ ነጋዴ የእሚሸጡ ደላሎች እና የመንግሥት በአለ ስልጣኖች ለፍርድ ይቅረቡ ፣ ንዑስ ካፒታሊዝም ይውደምና ስግብግብ ሆነው ለራሳቸው የአልተገባ ኃብት ለማጋበስ ሲሉ ሠራተኛውን በርካሽ ደሞዝ የእሚያሰሩ እና ሰው ሰራሽ የዋጋ ውድነት ለመፍጠር እቃ/ሸቀጥ እየ አጎሩ ዋጋ የእሚያስወድዱ ሐገራዊ ነጋዴዎች ንብረታቸው ይወረስ እና ለፍርድ ይቅረቡ እና በኢትዮጲያ ውስጥ የብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል ይከበር ፤ የእሚሉት መፈክሮች ፋሽን ሆነው የኃይለ ሥላሴ መንግሥት በአመጽ እንዲወገድ መንገድ ከጠረጉ በኋላ ፤ እነ እዚኽ የግራ ዘመሞቹ መፈክሮች ከደርግ ግዜ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ በተለያየ መልኩ ተተግብረዋል።

እነዚኽ የፖለቲካ ፕሮግራሞች በጥንቃቄ እና በስፋት በአለፉት 50 ዓመታት በኢትዮጲያ ውስጥ ቢተገበሩም ፤ የኢትዮጲያ ኋላ ቀርነት በመዋቅር ደረጃ የኃይለ ሥላሴ መንግሥት በስልጣን ላይ በነበረበት ደረጃ ላይ ነው አኹንም።

ዛሬም 80 በመቶ በላይ የእሚሆነው የኢትዮጲያ ገበሬ ከእጅ ወደ አፍ የእሚኖር እና የዛሬ 2 ሺ ዓመት አክሱማዊያን አባቶቹ ይጠቀሙ የነበረውን ዝናብ ጠብቆ በበሬ አርሶ ፣ በእጁ በትኖ ዘርቶ ፣ በእንስሳት እና በበትር ወቅቶ ፤ በከረጢት በእንሰሳ ጀርባ ላይ ወደ ሳምንታዊ ገበያ አውጥቶ ሸጦ ፤ ለምግቡ ጨው እና ለላምባው ዘይት ገዝቶ የእሚኖርበትን የግብርና ዘዬ የእሚከተል ነው።

በመንግሥት እና በግል ዘርፉ ተቀጣሪ ሆኖ በከተማ የእሚኖረው የኢትዮጲያ ሠራተኛ በዓለም ላይ ደኃ ከእሚባሉት የእሚመደብ እና በመካከለኛ ደረጃ ላይ የእሚገኝ ተቀጣሪ ሠራተኛ ብዙዎቹ መሠረታዊ የኑሮ ቁሳቁሶች ቅንጦት የሆኑበት እና ይኽንም ዓይነት ኑሮ የእሚኖረው ዓለም ዓቀፋዊ ምርታማነት እና በተነጻጻሪ የመሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ በረከሰበት ዘመን ነው።

እነ እዚኽ የግራ ዘመም መርሆች መከተል ከጀመርን 50 ዓመት ገደማ ቢሆንም ፤ በሚልየን የእሚቆጠሩ የኢትዮጲያ ሕዝብ በእየ አምስት እና አስር አመቱ አስቸኳይ ዓለም ዓቀፋዊ የምግብ እርዳታ ከአልተደረገላቸው ለርኃብ የእሚጋለጡ ናቸው ።

በአለፈው 50 ዓመት ፤ ከዴሞክራሲ እና ሰብአዊነት አንጻር ፤ የነበሩት መንግሥታት ኹሉ ፤ በተናጠልም ይኹን በቡድን የዜጎች ዴሞክራሲያዊ እና ሰብአዊ መብት መፍቀድ እና መጠበቅ አንጻር ፤ በኃይለ ሥላሴ መንግሥት ከነበረው አንጻር ይኽ ነው የእሚባል መሻሻል አላሳየም።

በእዚኽ በአለፈው 50 ዓመት ግን ከእኛ ጋር ተቀራራቢ ደረጃ ላይ የነበሩ ብዙ ሐገራት ፤ ቻይና ፣ ጃፓን ፣ ደቡብ ኮሪያ ፣ ወዘተ ፤ በኢከነሚያዊው ልማቱ መስክ እጅግ ተመንጥቀው ፤ ዛሬ ላይ የዘመናዊነት ሠርቶ ማሳያ ናቸው ።

ይኽን ስል ፤ ሰዎች ስለ ሆንን እና ከተግባር ውጭ መሆን ስለ እማንችል ፤ ኃይለ ሥላሴ በምንሊክ ዘመን የአልነበሩ ነገሮችን እንደ አስተዋወቁ ኹሉ ፤ ደርግ በኃይለ ሥላሴ ዘመን የአልነበሩ እና የአሻሻላቸው እንደ እዚኹም ኢሕአዴግ በደርግ ዘመን የአልነበሩ እና እርሱ የአመጣቸው አዲስ መሻሻል የሉም ለማለት ሳይሆን ፤ በእዚኽ ኃምሳ ዓመት ፤ ስንችል የታለመውን ዓይነት መዋቅራዊ ሽግግር አላደረግንም ለማለት ነው።

በ50 ዓመት ውስጥ በአግባቡ ከተመራን ፤ እንደ ኢትዮጵያዊያን የዓለማችን አንደኛ ደረጃ ሐገራት ተርታ ለመሠለፍ የመቻላችን ጉዳይ ፤ ቀላይ በአይባልም የተዓምር ያኽል የእሚከብድ አይደለም።

ከግብርና መር ኢከነሚ ወደ ኢንደስትሪ ከእዛም ወደ አገልግሎት መር ኢከነሚ አልተሸጋገርንም ፤ ከወግ አጥባቂ ማሕበረሰብ ወደ ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ስረዓት አልተሸጋገርንም ፤ ይልቁንም ስማቸው ብቻ የተቀየሩ መሠረታዊ የሐገሪቱ ችግሮች እንደ ድንጋይ አፍጥጠው አኹንም አሉ ለማለት ነው።

ከሸዋ ማንሰራራት ጀምሮ ፤ በእዚኽ ኹኔታ በአለንበት ለመርገጣችን ምክንያቱ ደግሞ ሌላ ምንም ሰአይሆን ፤ የዘመናዊ ፖለቲካን የተረዳንበት እና የተገበርንበት መንገድ ፤ ስህተት የአለው በመሆኑ ነው። ያም ማለት ፤ በዘመናዊ ፖለቲካ ስም የኢትዮጲያ ግራ ዘመሞች የፖሊሲ ምርጫ ፤ ምንም እንኳን በተወሳሰቡ ፖለቲካዊ ቃላቶች ፤ ፊውዳሊዝም ፣ ኢምፔሪያሊዝም ፣ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ፣ ኮምፕራዶር ካፒታሊዝም ፣ ቡርዥዋ ፣ ወዘተ ፤ ራሱን ወጥሮ የዘመናዊ ፖለቲካዊ ሊህቅ በመምሰል ራሱን እና ትውልድ ሲያደናብር ቢኖርም ፤ የኢትዮጲያን ፖለቲካዊ ማሕብረሰብ አንድ ጋት እንኳን ሊያሻሽል አልቻለም።

ለእዚኽም ምክንያቱ ፦ የኢትዮጲያ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ፤ እንደ ሌላው የደረጀ እና ጠንካራ ብሔራዊት ሐገር እና መንግሥት ባለቤት ማንኛውም ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ፤ ዋንኛው ችግሩ ሌላ ሰአይሆን ፤ በእዚኽ መጽሐፍ ውስጥ ዴሞክራሲን በገለጽንበት አግባብ ፤ የሰዎችን ወይንም የዜጎቹን ተፈጥሮዋዊ መብቶች በተፈጥሮ ሕጉ አግባቡ የእሚያከብር ፖለቲካዊ መዋቅር መፍጠር ፤ የዘመናዊውን ማሕበረ ኢከነሚ ትሩፋቶች መቆናጠጫ ብቸኛ መንገድ መሆኑን ፤ የተረዱ እና እርሱንም ለመተግበር እድል ያገኙ የፖለቲካ ሊህቃን በአለመፈጠራቸው ነው።

ግራ ዘመሞቹ የሐገራችን ሊህቃን ፤ ከእዚኽ ይልቅ ፦

በፊውዳሊዝም ውስጥ የነብረውን እና ጥቂት የመንግሥት ባለመዋሎች ብቸኛ የመሬት ባለቤት እንደ ሆኑ የእሚያደርገውን መቃወም እና የኢትዮጵያ መሬት የኹሉም ኢትዮጲያዊያን የጋራ ንብረት በመሆኑ ፤ ዜጎች በሕግ አግባብ ለኑሮ እና ለሥራ የእሚያስፈልጋቸውን መሬት እንዲያገኙ ከመታገል ይልቅ (አስቀድመን እንደ አልነው በአንዳንድ ጥናቶች መሠረት ዘመነ ፊውዳሊዝም በእሚባለው ዘመን እራሱ መሬት አልባ ገበሬ በኢትዮጵያ ፤ ከጠቅላላው ገበሬ 25% ብቻ የነበረ መሆኑ እንደ ተጠበቀ ሆኖ)፤ በአመክንዮዋዊ ታማኝነት እና ጽንፈኝነት (Ideological loyalism and fanaticism, if not infantilism) ፊውዳሊዝምን በመታገል ስም ፤ የዜጎችን ተፈጥሮዋዊ መብት አካል የሆነውን ንብረት የማፍራት እና ንብረትን በፈለጉት መልክ የማስተዳደር መብት በማገድ ፤ ዜጎች የሌሎችን የመሬት መብት ባለቤትነት መብት ሳይጋፉ ፤ የመሬት ባለቤት ሆነው መሬቱን በማልማት ሐገራዊ ምርታማነት እንዳያሳድጉ ተደረጉ።

ኢምፔሪያሊዝምን በመታገል ስም ፤ የውጭ በአለ ኃብቶች በሐገር ውስጥ ወዋዕለ ነዋያቸውን አፍስሰው የሥራ እድል እና የውጭ ምንዛሪ እንደ አያስገኙ በማገዳችን ፤ በዓለም ዓቀፍ የንግድ ትስስር ውስጥ ገብተን የእምናገኘውን የሞያ ውርስ እና ሌሎች ተዛማች ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንደ አናገኝ ፤ ራሳችንን በራሳችን ከዓለም ዓቀፉ ማሕብረሰብ ነጥለን ፤ የርዳታ ጠባቂ እንድንሆን ስለ አደረጉን። ኢምፔሪያሊዝምን በተለይ ካፒታሊስታዊ ኢምፔሪያሊዝምን እንታገላለን ብለው ፤ ደምሥራቸው እስኪገታተር የኢትዮጵያ አብዮተኞች ኢምፔሪያሊዝም ይውደም ሲሉ ፤ ደርግ ወደ ስልጣን ወጥቶ በኢትዮጵያ የአለ የውጭ ሐገር ዜጎች ኢንቨስትመንትን ሲወርስ ፤ በኢትዮጵያ የነበረው ኢንቨስትመንት መጠን 13.5 ሚልየን ዳላር ብቻ ነው የነበረው [122]።

በአብዮተኞቹ እንደ ትልቅ ነገር የተወገዘው ኢምፔሪያሊዝም ከሌለ ደግሞ የእርሱ ውላጅ የሆኑት ቢሮክራሲያዊ እና ኮምፕራዶር ካፒታሊዝምም ሐገርን በእሚያሰጉበት ኹኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ የሉም ማለት ነው።

ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም በመታገል ስም ፤ ምሁሮቻችን እና ሊህቃኖቻችን ፤ በኢትዮጲያው ውስጥ የሕክምና ዶክተር ከመሆን ይልቅ በካፒታሊስቶቹ ሐገር ታክሲ መንዳት ይሻላል እያሉ ሐገር ጥለው እንዲሰደዱ በማድረግ ፤ የእማያምሩ ወይንም የእማያፍሩ ሰዎችን ሰብስበን በሶሻሊሲታዊ የደሞዝ እርከን የመንግሥት እና የሕዝብን ኃላፊነት ላይ እየሰገሰግን ፤ ይኽም አላዋጣ ሲለን ፤ እውርን እውር ቢመራው እንደ እሚለው በአቅም ግንባታ ስም በለብለብ ስልጠና ብቃት የአላቸውን የሕዝብ አገልጋይ ለመፍጠር የእማናደርገው ጥረት ኹሉ አልሰምር ብሎ ፤ ከወደብ እቃ ወደ መሐል ሐገር ለማስገባት ወራት የእሚፈጁባት ኩሽማንኩሽ የአፈጻጸም ደረጃ የአለባት ሐገር አደረግናት።

በአለ ኃብትነትን ቡርዡዋ የእሚል እንደ ጭራቅ የእሚያስፈራ ቃል ለጥፈንበት ፤ ሰዎች ጉልበታቸውን እና ኃብታቸውን አፍስሰው በሐገራቸው ላይ የተከበሩ ኃብታሞች እንደ አይሆኑ አድርገን ፤ በእርዳታ እና የተፈጥሮ ኃብታችንን ይኼ ነው የእሚባል እሴት ሳንጨምር እንደ ወረደ ወደ ውጭ ከመላክ የእምናገኘውን የውጭ ምንዛሪ ፤ በእዚኽም በእዚያኽም እየቀነጣጠቡ ፤ ቀላል የእማይበል ኃብትን ወደ ውጭ ሐገር የማስተላፍ ችግር ፈጠርን።

የብሔር ጭቆና የእሚል የድንጋይ ዘመን የፖለቲካ ፍልስፍና እንከተላለን ብለን ፤ የዜጎችን የመናገር ፣ የመምረጥ ፣ የመመረጥ ፣ የመንቀሳቀስ ፣ ኃብት የማፍራት ፣ መብት በእግር ሙቅ የእሚያስር ስረዓት ዘርግተን ፤ መላ ሐገሪቱን በመኃይምነት እና በጠባብነት እስር ቤት አስረን ፤ ራሳችን የዓለም መሳቂያ አደረግን።

ይኽም ኹኔታ ፤ ድሕረ ምንሊክ የአለቸው ኢትዮጲያ ፤ ምንም እንኳን ጠንካራ መንግሥት እና የተወሰነም ቢሆን የልማት ጥረት የእሚያደርግ መንግሥት የአለባት ብትሆንም ፤ የዘመናዊ ፖለቲካን ትሩፋት ማጣጣም የተሳናት እና በዘመናዊነት ጣር ውስጥ የአለ፟ች ኢትዮጲያን የፈጠረ ነው።

ብዙ ፈተና ቢደርስበትም የኢትዮጲያ ብሔራዊ መንግሥት በአለፉት 100 ዓመታት ህልውናውን አስጠብቆ በመቆየቱ እና ከሌላው የዘመኑ የዓለም ሕዝብ አንጻር ፤ የዘመናዊነትን ትሩፋት በአግባቡ እያጣጠመ ሳይሆን ፤ የዘመናዊነት ትልሙ በተሳሳተ ርዕዮት ምክንያት ጣር ውስጥ የአለ፟ በመሆኑ ፤ ይኽንን ለማሳየት ፤ ዘመነ ኃይለ ሥላሴ ፣ ዘመነ ደርግ እና ዘመነ ኢሕአዴግ በማለት ክፍል ሰባት ፣ ስምንት እና ዘጠኝ የአልነውን የታሪካችንን ክፍል ፤ ወደ ዘመናዊነት በተሳሳተ ጎዳና የእሚጓዝ ጠንካራ መንግሥት የእሚለውን ለማሳየት እና ከሌላው የዓለም ሕዝብ አንጻር የአለውን ጉድለት ለማሳየት 7 ነጥብ ተስጥቷል።