ከላይ በአስቀመጥነው መልኩ ፥ ትርጉም የአለው ፤ የሰው ልጅ ማሕበራዊ ስልጣኔ ፤ ከዛሬ 5,200 ዓመታት ገደማ በግብፅ በዋናነት ከጀመረ በኋላ ፤ እንደ ዓለም አካላይ ወንዝ ከስፍራ ስፍራ በመሸጋገር እና በማደግ ፤ የሰው ልጅ ፍራፍሬ ለቅሞ እና የዱር እንሰሳት አድኖ ከመመገብ ፤ አርሶ ራሱን ወደ እሚመግበት እና እንስሳት አርብቶ ወደ እሚኖርበት የግብርና አብዮት ሲሸጋገር ፤ ከእዚያኽም አልፎ ስልተ ምርቱን በኢንደስትሪ አብዮት አሻሽሎ የምርት አቅሙን ሲያጎለበት እና አኹን በአለንበት የመረጃ ዘመን ላይ ሲደርስ ፤ መንግሥትን እንደ አንድ አስፈላጊ ማሕበራዊ ተቋም ከተረዳበት እና መንግሥትን ማቋቋም ከጀመረበት ግዜ አንስቶ ፤ የአቋቋማቸው የተለያዩ የመንግሥት ዓይነታት ፤ በእዚኽ የስልጣኔ ግስጋሴው ላይ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል ።
በሰው ልጅ ፖለቲካዊ ታሪክ እና ስልጣኔው ላይ ይኽን መሰል ከፍተኛ ሚና የነበረው መንግሥት ፤ መንግሥታዊ ትርክት ዋነኛ ግብዓቱ በመሆኑ ፤ አንድን መንግሥት ከተመሠረተበት እና ከእሚመራበት ትርክት ነጥሎ ማየት ፤ የእሚታሰብ ነገር አይደለም።
መንግሥት ከአለ ትርክት አለ ወይንም መንግሥትን የአለ ትርክት መአሰብ አይቻልም። ምንም እንኳን መንግሥት ያለ ቅድመ ትርክት እንዲኹ በግብታዊነት ሊቋቋም ቢችልም ፤ ከተቋቋመ በኋላ ግን አንዳች ዓይነት የራሱ ትርክት ሊኖረው ግድ ነው።
መንግሥታዊ ትርክት የእምንለው ፤ አንድ መንግሥት የመ፟መ፟ስረቻ ምክንያቱን ወይንም አስፈላጊነቱን ፣ የእሚመራባቸውን እሴቶች እና መርህዎች ፣ የስልጣን ምንጩን ፣ የስልጣኑን ድንበር ፣ ድርጅታዊ አወቃቀሩን ፣ ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ሚናውን ለእራሱ እና ለእሚመራው ወይንም ለእሚገዛው ሕዝብ የእሚያቀርብበት ሐተታ ማለታችን ነው።
ይኽን መሰል ሚና የአለውን መንግሥታዊ ትርክት ለመቃኘት ፤ ይኽ ንዑስ ክፍል በሦሥት ተከፍሎ ፦
በእሚያስቃኝ መልኩ ይቀርባል።