ሕ ገ ክ ራ ሲ

marketing-image

4.1.1. ሕግ-መንግሥት እና ሕግ በቀደምት ኢትዮጵያ

አንድ ማሕበረሰብ ፤ እርስ በእርሱ እየተመጋገበ እና እየተጋገዘ ወደ ጋራ ጤንነት እና ብልፅግና ማደግ የእሚችለው ፤ የእርስ በእርስ መስተጋብሩን በእሚያዋቅርበት እና በእሚዳኝበት መንገድ ወይንም ሕግ-መንግሥት እና ሕገ ጥራት ልክ ነው ።

በእዚኽ መጽሐፍ ምዕራፍ ኹለት ላይ ለማለት እንደ ተሞከረው ፤ የፖለቲካ ማሕበረሰባት የእርስ በእርስ መስተጋብራቸውን የእሚያዋቅሩበት አግባብ ሕገ-መንግሥት (Constitution) ሲባል ፤ እያንዳንዱ የውቅሩ ወይንም የማሕበረሰቡ አባል በእዚኽ ውቅር ውስጥ በእሚኖርበት ወቅት የእሚዳኝበት መርሕ ደግሞ ሕግ ይባላል ።

ሕግ እና ሕግ-መንግሥት በልቦና ደረጃ በሰው ልጅ ማሕበረሰብ ውስጥ ፤ ከጥንተ ጥንትም መኖራቸው ቢታወቅም ፤ የሰው ልጅ እነ እዚኽን የልቦና መረዳቶች በጽሑፍ ማስፈር የጀመረው ፤ እንደ ማሕበረሰብ ብዙ ከኖረ በኋላ ፤ በጣም ከረፈደ ነው ።

ዘግይቶም እነ እዚኽን የልቦናውን ግንዛቤዎች በጽሑፍ ማስፈር ሲጀምርም ፤ ሕግን ለብቻ ፥ ሕገመንግሥትን ለብቻ አድርጎ ሰአይሆን ፤ ኹለቱንም በአንድ ላይ ነበር የእሚያቀርባቸው ። ይኽም በመሆኑ ፤ የሰው ልጅ መጀመሪያ በተጻፈ ሕግ መዳኘት ጀምሮ ፤ በኺደት ፖለቲካዊ ግንዛቤው እያደገ ሲመጣ እና ሕገ-መንግሥት ከሕግ መሠረታዊ ልዩነት እንደ አለው መገንዘብ ሲጀምር ፤ ሕገ-መንግሥቱን ከሕጉ በመለየት ለብቻው ማስቀመጥ ጀምረ ።

በእዚኽ መልኩ ከለያቸውም በኋላ ፤ ፅንሰ ኃሳባቸው ዳብሮ ችግር ፈቺ እስኪሆኑ እና ከፋም ለማም አንድን ማሕበረሰብ ፤ በአግባቡ አያይዘው እና ህልውናውን አስጠብቀው የእሚያቆዩ መመሪያዎች እስኪሆኑም በጣም ብዙ ግዜ ወስደዋል ።

እኛ ኢትዮጵያዊያን ፤ አኹን ከአለንበት ኋላ ቀርነት የተነሳ ፤ ፖለቲካዊ ታሪካቸው ብዙም ትኩረት ከእማይሰጣቸው ሕዝብ መሐከል ብንሆንም ፤ በሕግ እና ሕገ-መንግሥት ረገድ ከብዙው የዓለም ሕዝብ ቀደም የአሉ፟ እና እንደ ታሪካዊ ኃብት ብዙ ሊጠኑ የእሚገባቸው ፤ ጥንታዊ ሕግ እና ሕገ-መንግሥት አሉን ።

በተለይ ወደ ዘመናዊ ፖለቲካ ለመሸጋገር በአደረግነው ትግል ነባራዊውን ስረዓት በኋላ ቀርነት እና ፀረ-ለውጥነት የመፈረጅ ከፍተኛ ዝንባሌ ስለ ነበረ ፤ የጥንታዊ ኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት እና ሕግ የነበሩትን ክብረ-ነገሥት እና ፍትሐነገሥት ፤ እንደ ጎጂ እና ኋላ ቀር ባህሎች እያየን በማጣጣላችን ፤ ይኽ አካኼድ በታሪካዊ አረዳዳችን ላይ አሉታዊ ተፅኖ ከማሳረፉ በተጨማሪ የእነ እዚኽን ሰነዶች ዋጋም አራክሶብናል ።

እንደ እንግሊዛዊው የታሪክ ተመራማሪ እና ጸሐፊ ዋሊስ ባጅ (Sir E.A. Walis Budge) ፤ ክብረ-ነገሥት በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ፤ ማለትም ከክርስቶል ልደት በኋላ ከ 500 እስከ 600 በአሉ፟ት ዓመታት ውስጥ እንደተቀናበረ ይገምታል ፦

“ከእዚኽ ቀደም በ ፦ ዲልማን ፣ ትራምፕ ፣ ዞተንበርግ ፣ ራይት እና ቤዞልድ የተጻፉትን በጥንቃቄ መዝነን ፤ የነገሩን የመሆን እድል ከግምት ውስጥ ስናስገባ ፤ የመጀመሪያ የክብረ መንግሥት ቅንብር ስድስተኛው ምዕተ ዓመት ላይ ነው ብንል ብዙ የእምንሳሳት አይመስለኝም ።”

“Weighing carefully all that has been written by Dillman, Trump, Zotenberg, Wright, and Bezold, and taking into account the probabilities of the matter, it seems to me that we shall not be far wrong if we assign the composition of the earliest form of the Kebra Nagast to the sixth century A.D. [79]“

ይኽንን የዋሊስ ባጅን ኃሳብ ይዘን ፤ ክብረ-ነገሥቱ እንደ እሚለው በኢትዮጵያ ውስጥ ከአክሱም ዘምን ጀምሮ የእሥራኤሉ ንጉሥ ዳዊት ልጅ የሆነው የጠቢቡ ሰለሞን የልጅ ልጆች ናቸው በኢትዮጵያ መንገሥ የአለባቸው የእሚለው አሰራር ከዘመነ አክሱም ጀምሮ መኖሩ በብዙ የሐገር ውስጥ ሰነዶች እና ልማድ ስለ እሚታወቅ ፤ ኢትዮጵያ ከዛሬ 1,400 ዓመታት ጀምሮ ፤ የፖለቲካ ስልጣኑን ማን መያዝ እንደ አለበት የእሚደነግግ የተጻፈ ሕገ-መንግሥት ነበራት ማለት እንችላለን ።

አንድ ሰው ስለ ክብረ-ነገሥት ምንም ዓይነት አመለካከት ይኑረው ፤ ኢትዮጵያ ግን በእዚኽ መልኩ የእሚመራ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ከእዚያኽን ግዜ አንስታ መሥርታ ነበር ማለት ደግሞ ፤ ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ፖለቲካዊ ልህቀት ብዙ ይነግረናል ።

ግሪኮች ብዙ የስልጣኔ ሥራ ሰርተዋል ፤ እንደ እዚኽ ዓይነት ረዥም ዘመን የቆየ የስልጣን ውርስ መመሪያ በ6ኛው ምዕተ ዓመት ወይንም ከእዚያኽ በፊት አልነበራቸውም ፤ ታላቋ ሮም ዘመናዊው ዓለም የተነሳባት መሠረት ሆና ሳለ ፤ በታላቅነቷ በቆየችባቸው ብዙ መቶ ዓመታት እንደ ክብረ ነገሥት የአለ፟ ብዙ ትውልድን የተሻገረ የስልጣን ውርርስ መመሪያ አልነበራትም ።

ይኽም ፤ ክብረ-ነግስትን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ፤ በስነ መንግሥት ሰነድነት ትልቅ ስፍራ የእሚሰጠው ሰነድ ያደርገዋል ።

ከእላይ እንደ አልኹት ፤ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ግዜ የአለፈበት ቤተሰባዊ ስልጣን ማስከበሪያ ነው ተብሎ በብዙ ትችት እንዲናቅ ቢሆንም እና በኢትዮጵያ ውስጥ መንገሥ የአለበት ፤ ከንግሥት ሳባ ከቀዳማዊ ምንሊክ የእሚወለደው ዘር ብቻ ነው ማለቱ ፤ ለዘመናዊ ሕዝባዊ መንግሥት አስተሳሰብ የእማይመጥን መሆኑ በአያከራክርም ፤ ክብረ-ነገሥት ግን ፤ የኢትዮጵያ የስልጣን ውቅር መሠረት በመሆን ኢትዮጵያን የመሰለች የአፍሪካ ፈርጥ ሐገር ገንብቶ አቆይቷል ።

ከእዛኽም በአሻገር ፤ ክብረ-ነገሥት በኢትዮጵያ መንገሥ የአለበት የጠቢቡ ሰለሞን ዘር ብቻ ነው የእሚለው ዘመን ዓለፍ የፖለቲካ አስተሳሰብ ግርዶሽ እየሆነብን ፤ በክብረ-ነገሥት ውስጥ የተንፀባሩቁ ብዙ የበሰሉ አስተሳሰቦችን አብረን እንድንቃቸው አድርጎናል ።

በእርግጥ እንደ እዚኽ ስል ፤ ክብረ-ነገሥት በውስጡ በዘመናዊ የፖለቲካ እና የአስተዳደር ሳይንስ የእማይታወቁ መርህዎችን ይዟል ለማለት ወይንም ክብረ-ነገሥት በዘመናዊ የሕዝባዊ መንግሥት ሕገ-መንግሥት ውስጥ ከእሚንፀባረቀው እውቀት እና ጥበብ ፤ የተሻለ እውቀት እና ጥበብ ይዟል ለማለት ሰአይሆን ፤ እንደ ጥንታዊ (Classical Period) ሰነድ ፤ የዘመናዊ ፖለቲካ ሳይንስ የእማይቃወማቸው እና አንዳንዶቹም ለዘመናዊ ፖለቲካ ሳይንስ መሠረት የሆኑ ኃሳቦችንም ይዟል ለማለት ነው ።

የክብረ-ነገሥትን ስነ መንግሥታዊ ፍልስፋና ጨምቀን ፤ ቀለል ባለ መንገድ እነ አስቀምጠው ከተባለ የእሚለው ፦ በአንድ ሐገር የእሚነግሥ ሰው መንገሥ የአለበት ፍትሕን ለማስፈን ነው ፤ ይኽን ማድረግ የእሚችለው ወይንም በነገሠበት ሐገር ፍትኽ አስፋኝ ነጋሢ መሆን የእሚችለው ደግሞ በእግዚአብሔር ንጉሥ እንዲሆኑ ከተሾሙት ንጉሥ ዳዊት እና ልጁም ጠቢቡ ሰለሞን የተወለደ እንደ ሆን ነው ፤ ነው የእሚለው ።

ይኽንም የአለበትን ምክንያት ሲያስረዳ ፦ እግዚአብሔር ለዓለም ሕዝብ የተለያየ ክህሎት እና ሞያ ሰጥቷል ፤ በእዚኽም ፦ አንዳንዱን ሕዝብ በአብዛኛው ኢንደስትሪያሊስት ፣ አንዳንዱን ሕዝብ በአብዛኛው ነጋዴ ፣ አንዳንዱ ሕዝብ በአብዛኛው ሐገር መሪ ፣ ወዘተ ፤ አድርጓል ። ስለ እዚኽ በአምላክ ፀጋ ክፍፍል ፤ ሐገር የመምራት ጥበብ ያልተሰጠው ሕዝብ መሐል የአለ ሰው ሐገር ወደ መምራት ከመጣ ፤ ያለ ስጦታው እና ያለ ሞያው የመጣ መሪ በመሆኑ ፍትሕን ያዛባልና ፦ በሐገራት ላይ ፍትሕ እንዲሰፍን ከእግዚአብሔር ዘንድ ይኽ ፀጋ የተሰጠው ብቻ ሊመራ ይገባል የእሚል ነው ።

ይኽ ደግሞ ወይንም የክብረ ነገሥት ማጠንጠኛ የሆነው የፍትኽ አስተሳሰብ ደግሞ ማንም የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ ሊመሰክር እንደ እሚችለው ፤ የፖለቲካዊ ፍልስፍና እና የፖለቲካ ሳይንስ ማጠንጠኛ ነው ።

እስከ ዛሬ ድረስ ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ፤ አንደኛ ደረጃ የእሚባሉት ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ፤ የፖለቲካ ፈላስፎች እና ሳይንቲስቶች በአንክሮ የእሚያጠኑት ፤ የሶቅራጠስ ፖለቲካዊ ፍልስፍና በእሚል በተማሪው በፕሌቶ የተጻፈው ሪፐብሊኩ (The Republic) የእሚለው መጽሐፍም ፤ እነ እዚኽኑ ፍትኽ ምንድ ነው እና በአንዲት ከተማ ፍትሕ የእሚሰፍነው ምን ዓይነት ንጉሥ ሲነገሥ ነው የእሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ የእሚሞክር ነው ።

ይኽ ሪፐብሊኩ የእሚለው መጽሐፍ ፤ ሶቅራጠስ አርጤምስ የእምትባለው የግሪክ አምላኪት በዓል በእሚከበርበት ቀን ፤ ፀሎቱን ለማድረስ እና በበዓሉ ላይ የእሚደረገውን ትርዒት ለመመልከት ከኼደበት ፤ ወደ ከተማ ሊመለስ ባለበት ሰዓት ላይ ፤ ፖሊማርከስ የተባለው ፈላስፋ ከእርሱ ጋር በአቅራቢያው ወደ አለው መኖሪያ ቤቱ እንዲኼድ ግድ ብሎት ፤ በፖሊማርከስ ቤት ኬፋሎስ ከእሚባለው የእድሜ ባለፀጋ እና ኃብታም ከሆነው ፤ የፖሊማርከስ አባት ጋር በእሚያደርገው ውይይት ነው የእሚጀምረው ።

በእዚኽም ውይይት ላይ ፤ ኬፋሎስ ሶቅራጠስን እንደ እዚኽ ይለዋል ፦ አንዳንድ ሰዎች እድሜ ሲገፋ ፤ ሰውነት ከወጣትነት እሳት ስሜቶች ስለ እሚላቀቅ ፤ የተረጋጋ እና የሰከነ ነው ይላሉ ፤ ለእኔ ግን ሰው ወጣትም ሆነ ሽማግሌ ፤ በመልካም ስነ ምግባር የታነፀ ሕይወት ኖሮ ተስፋ የልቦናው ስንቅ ከአልሆነ ፤ ኑሮ እዳ ነው የእሚሆንበት ይላል ፦

“እርሱም አለ ፦ ‘ተስፋ በፍትሕ እና በቅድስና የእሚኖረውን ሰው ነፍስ ደስ ታሰኘዋለች ፥ የእድሜ ዘመኑ ሞግዚት እና የጉዞውም አጋር ነች ፦ ተስፋ ነች ረፍት አልባውን የሰው ነፍስ መመለስ የእምትችለው ።”

“Hope,’ he says, ’cherishes the soul of him who lives in justice and holiness and is the nurse of his age and the companion of his journey; – hope which is mightiest to sway the restless soul of man. [22]“

ኬፋሎስ ይኽንን ሲል ፤ ሶቅራጠስ ይኽንን የኬፋውሎስ አባባል ወዲያው ያዝ አድርጎ ፦

“እኔም ፥ ለኬፋለስ ደህና ብዬ መለስኩ እና ፦ ስለ ፍትሕ ከተነሳ ፥ ይኽ ፍትሕ የእሚባለው ነገር ምንድነው? አልኹት ።”

“Well said, Cephalus, I replied; but as concerning justice, what is it? [22]“

በማለት ፤ ቀሪው የመጽሐፉን አጀንዳ ኹሉ የእሚወስነውን ጥያቄ በማቅረብ የእሚጀምረው ።

በእዚኽ የፍትሕ ጥያቄ የተጀመረው ሪፐብሊኩ ፤ በእዚያን ወቅት በፖሊማርከስ ቤት በነበሩት የተለያዩ ፈላስፎች እና በሶቅራጠስ መካከል ፤ ፍትሕ ምንድነች ፣ ፍትሕስ የሰፈነባት ከተሟ የቷ ነች ወይንም ምን ዓይነት ንጉሥ ቢነግስ ነው ፍትሕ የሰፈነባት ከተማ የእምትኖረው የእሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የእሚሞክሩበት ነው ።

ምንም እንኳን ክብረ-ነገሥት በተለየ ታሪካዊ ምህዳር ውስጥ እና በተለየ ግለ ሰባዊ ፈተና ቢሆንም ፤ ልክ እንደ ሪፐብሊኩ ፍትሕን የእሚያሰፍነው ነጋሢ የቱ ነው ብሎ ነው የእሚጀምረው ።

ክብረ-ነገሥት ፤ ሲጀምር በምዕራፍ 2 ላይ እንዲኽ ብሎ ይጀምራል ፦

“እኔ በጉድጓድ ውስጥ ተጥዬ ሳለኹ ስለ እዚኽ ነገርና ስለ አርሜንያው ንጉሥ ስንፍና አሰብኹ ። ህሊናዬም ሊያስብ የእሚችለውን ያህል የነገሥታት ከፍታቸው በምንድነው ? በሠራዊት ብዛት ? በእዚኽ ዓለም ኃብት ባለ ጸግነት ? ወይስ በተሾሙበት ሐገር ብዛት ነው? አልኹ ። ከጸሎት በእሚተርፈኝ ሰዓት ዘወትር ይኽን እያሰብኩ ህሊናዬ ያውከኝ ነበር ። ስለ ነገሥታት ክብርም አስብ ነበር።”

ይኽን የክብረ-ነገሥት መክፈቻ ጥያቄ በመጠየቅ የእሚጀምረው ፤ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ 257 ዓ.ም — 331 ዓ.ም የኖረው ፤ ተዓምረኛው (ወይንም ክሳቴብርሀን Illuminator) ጎርጎርዮስ የእሚባለው የአርሜኒያ ጳጳስ ነው ።

ጎርጎርዮስ ፤ ይኽንን የመክፈቻ ጥያቄ በማቅረብ የእሚጀምረው ፤ ከዓለም ዙሪያ የመጡ 318 የኦርቶዶክስ (የክርስትና) ኃይማኖት ሊቃውንት በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት በተሰበስቡበት ጉባዔ ላይ ነው ።

ጉባኤውም ልክ ፤ በሪፕብሊኩ ላይ በሶቅራጠስ እና በሌሎቹ ፈላስፎች መካከል እንደ ነበረው ዓይነት ውይይት ፤ በጎርጎርዮስ እና በሊቃውንቱ መካከል እየተካኼደ ፤ ፍትኽን ማስፈን የእሚችለው ነጋሢ የቱ መሆኑን ለመለየት የተካኼደ ነው ።

የጎርጎርዮስ ጉባኤተኞች ከሶቅራጠስ ጉባኤተኞች የእሚለዩት ፤ ጉባኤተኞች የክርስትና እምነት ሊቃውንት በመሆናቸው እና ጥያቄውንም ለመመለስ የእሚፈልጉበት ማዕቀፍ ፤ እንደ እነ ሶቅራጠስ አዕምሮዋዊ ፍርድን ብቻ መሠረት የአደረገ ሰአይሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቀኖናዎችን መሠረት የአደረገ በመሆኑ እንጂ ፤ ሊመልሱት የፈለጉት መሠረታዊ ፖለቲካዊ ጥያቄ ‘ፍትሕ ምንድነች?’ የእሚለውን ፤ እድሜ የአልሻረውን የፖለቲካ ሳይንስ ጥያቄ ነው ።

የክብረ-ነገሥቱ ዋና ጥያቄ ፦

‘የነገሥታት ክብራቸው በምንድነው?’

የእሚለው ነው ፤ ለእዚኽም ነው መጽሐፉ ፤ ክብረነገሥት የተባለው ።

ይኽም ክበረ ነገሥት ሊመልሰው የእሚፈልገው ፤ የነገሥታት ክብራቸው በምንድነው የእሚለው ጥያቄ ፤ በመጽሐፉ አውድ ሲመነዘር ይዘቱ ፦ ነገሥታት ፍትሕን ማጓደል የለባቸውም እና ይኽ እንዳይሆን ፤ ነገሥታትን የእሚያስከብራቸው ወይንም የሕጋዊ ስልጣናቸው ምንጭ ምንድነው የእሚለው ጥያቄ ነው ።

የክብረ-ነገሥት መክፈቻ የሆነውን ይኽንን ጥያቄ ጎርጎርዮስ ላይ ያጫረበት ደግሞ ፤ ይኽ ነው የእሚባል ወንጀል ሳይፈፅም ፥ የክርስትና እምነት ተከታይ በመሆኑ ብቻ ፤ ለ15 ዓመታት ፤ በግፍ በጉድጓድ እስር ቤት ውስጥ ተጥሎ በመታሰሩ ፤ በእዚኽ በደረሰበት ኢፍትኃዊ በደል ተቆጭቶ ፦ መንግሥት ለመሆኑ ማን ነው? የመንግሥት ስልጣን ምንጭስ ከሰበሰበው ጦር ብዛት? ሰፊ ግዛት በስሩ ከመሆኑ? ወይንስ ብዙ ኃብት ስለ አለው የእሚመጣ ነው? ለንግሥና የእሚያበቃው መመዘኛ የቱ ነው ? ወዘተ ፤ ብሎ እንዲጠይቅ ስለ አደረገው ነው ።

ከእላይ እንደ አልኹት ፤ ክብረ-ነገሥት ፍጹም እና ስህተት የሌለበት ወይንም በእዚኽ ዘመን የእማይታወቁ ጥበባትን የያዘ መጽሐፍ ነው ለማለት ሰአይሆን ፤ በይዘቱ በዓለም ላይ ተደንቀው ከእሚጠኑ ጥንታዊ (Classical Period) የፖለቲካ ሳይንስ መጽሐፍት ጋር የእማይተናነስ ነው ለማለት ነው።

ሶቅራጠስ አርጤምስ የእምትባለውን ጣዖት ሊያመልክ በመኼዱ ወይንም የመንግሥት ባለስልጣኖች ፤ የጋራ ሚስቶች ይኑራቸው ልጆቻቸውም አባታቸው አይታወቅ ስላለ ወይንም አርስታትል ባርነት የተፈጥሮ ኹኔታ ነው ስላለ ፤ ኋላ ቀር እና የዝበታዊያን ትምህርት ብለን ፤ የፕሌቶን ሪፐብሊክ እና እንዲኹም የአርስታትልን ፖለቲክስ ከአልናቅን ፤ ለሰዎች የተለያየ ሞያን የእሚሰጥ እግዚአብሔር የጠቢቡን ሰለሞን ልጆች የሕዝብ ማስተዳደር ጥበብ ሰጥቷዋቸዋል እና ነጋሢ መሆን የአለባቸው እነርሱ ብቻ ናቸው በእሚል የእሚሳሳተውን እና ከእዛኽ በአሻገር ግን ብዙ ቁምነገሮች የያዘውን ክብረ-ነገሥት ፤ እንደ ርካሽ ማየት የለብንም ።

ክብረ ነገሥት ለእዚኽ ፤ ፍትሕን የእሚያሰፍኑ ነገሥታት የትኞቹ ናቸው ? ለእሚለው ጥያቄ የሰጠው መልስ ምንም ይሁን ምን ፤ ትክክለኛውን ሳይንሳዊ የእምንለውን ፤ የሕገመንግሥት ጥያቄ ጠይቆ ፤ ለእዚያኽም መልስ የሰጠና ፤ ለረዥም ዘመናትም ፤ የኢትዮጵያ ነገሥታት እየነገሡ ኢትዮጵያን መሰል ታሪካዊት ሐገር ማቆየት እንዲችሉ በማድረግ የአገለገለ ሰነድ በመሆኑ ፤ የቀደምት ኢትዮጵያ ሕገመንግሥት ነበር ።

ይኽም ደግሞ ክብረ ነገሥትን ፤ በዓለም ላይ ከነበሩ ቀዳሚ ሕገመንግሥቶች ዝርዝር ውስጥ የእሚያስገባው እና ምናልባትም በይዘቱ ጥራት እና በአንጋፋነቱ ፤ ከቀደምት ሕገመንግሥቶች ኹሉ ቀዳሚውም ሊሆን እንዲችል የእሚያድርገው ነው ።

ጎርጎርዮስም ከላይ የጠየቀውን ፤ ይኽን ዓለማቀፋዊ ይዘት የአለውን የሰው ልጆችን ኹሉ የእሚመለከት ጥያቄ ፤ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ አውድ አጥብቦት ፤ በኢትዮጵያ ማን ፤ በምን እየተመራ መንገሥ እንዳለበት ያስቀምጣል ።

ስለ እዚኽ ፦ ይኽ ከሆነ ፤ ኢትዮጵያ የዛሬ 1,400 ዓመት ገደማ ጀምሮ የሕገመንግሥት ባለቤት ነበረች ብእንል ብዙም አንሳሳትም ።

ኹለተኛው ፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የአለው ፤ የኢትዮጵያ ስነመንግሥት ሰነድ ፤ ፍትሐነገሥት ነው ። ፍትሐነገሥት ፤ የወቅቱ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አስተዳደር ሕግ ፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ እና ሌሎች ማሕበራዊ ጉዳዮች ለምሳሌ ፦ ትዳር ማስተዳደሪያ ሕግ ነው ።

ፍትሐነገሥት ሲጀምር እንዲኽ ብሎ ይጀምራል ፦

“የሰማዕት ዘመን ከተፈፀመ በኋላ … ቆስጠንጢኖስን ንጉሥ በአደረጉት ጊዜ እርሱ እኔ መንግሥትን አልሻም አላቸው ። የክርስቶስ መንገድ እና የዓለም መንገድ ልዩ ነውና ። የክርስቶስ መንገድ እና የተረጋገጠች ትዕዛዙ ግን ፦ ጠላቶቻችሁን ውደዱ ፣ ለእሚቀሙዋችሁም በጎ አድርጉ … ይኽን እና የእሚመስለውን ትላለችና ። … ይኽን ትዕዛዝ እተው ዘንድ ፍርድንና ያለ ምሕረት በጊዜው ዕዳ መክፈልን አዝዝ ዘንድ ፣ ለተበደለውም ከበዳዩ መበቀልን አዝዝ ዘንድ እንዴት ይቻለኛል ። [95]”

ይኽ ፍትሐነገሥት የእሚጀምርበት ‘የሰማዕታት ዘመን ከተፈፀመ’ በኋላ የእሚለው ሐረግ ፤ ብዙዎቻችን በታሪክ እንደ እምናውቀው[1] ፤ ከክርስቶስ ማረግ በኋላ በሮም ቆንስጠንጢን ክርስቲያን እስኪሆን ድረስ ፤ ክርስቲያኖች በሮም በተለያየ ወቅት ፤ ለአውሬ እንዲበሉ እስከ መስጠት የእሚያደርስ መከራ ይደርስባቸው የነበረበትን ወደ 300 አከባቢ የእሚጠጋ ዓመታት የቆየውን ዘመን ነው።

ይኽ የሰማዕት ዘመን እንደ አበቃ እና የሮማው ኢምፐረር ቀስጦንጢን የመስቀል ቅርፅ የአለው ብርኅን በሰማይ አየኹ ብሎ ክርስቲያን ከሆነ በኋላ ፤ በግዜ ኺደት ክርስትና ተሳዳጅ ከሆነበት ወጥቶ መንግሥታዊ ኃይማኖት በመሆን ፤ የሮም ነገሥታት እና መላው የሮም ግዛት ውስጥ የእሚኖሩ ሰዎች ኹሉ የህይወት መመሪያ ሆኗል ።

ይኽንም ተከትሎ ፤ የሮም ኢምፐረር የሆኑ የተለያዩ ነገሥታት ከነበረባቸው መንፈሳዊ እውቀት ማነስ የተነሳ ፤ ክርስትናቸው ወይንም የመጽሐፍ ቅዱስ አማኝ መሆናቸው ከሕግ ማስከበር ሥራ የእሚያግዳቸው ስለ መሰላቸው ፤ ንግሥናውን ትተው እንደ መደበኛ ዜጋ ሆነው ለመኖር መዳዳት ጀምረው ነበር ።

በእዚኽም መሰል ኃይማኖታዊ ቅናታቸው ፤ ከእላይ በአለው የፍትሐነገሥት መጀመሪያ ላይ የአለው ክፍል እንደ እሚለው ፤ ‘ጠላቶቻችሁን ውደዱ ፣ ለእሚቀሙዋችሁም በጎ አድርጉ’ የእሚለው የክርስትና አስተምህሮ ፤ በፍትሕ ሕግ አግባብ ፤ በደለኛን በበደሉ እንዳይቀጡ የእሚያግዳቸው አድርገው መቁጠር ጀምረው ነበር ።

ይኽም የመንፈሳዊ እውቀት ማጣት ፤ ነገሥታትን ግብር እያስፈታ ያለ ቦታቸው ወደ መንፈሳዊ ዓለም የእሚመልስበት ኹኔታ እና በእዚኽ መልኩ የነገሥታት ግብር መፍታት የእሚያስከትለው ዘርፈ ብዙ ችግር የአሳሰባቸው የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ፤ ለእዚኽ ችግር መፍትኼ ለመስጠት ፤ ተሰብስበው የክርስቲያን ነገሥታት ለምን በመንበራቸው መቆየት እንደ አለባቸው እና እንደ ክርስቲያን ሐገረ ገዢም ፤ ሐገርን እንዴት በፍትሕ ማስተዳደር እንደ አለባቸው የእሚደነግግ ፤ የክርስቲያን ነገሥታት በፍትኽ (ፍትሐ-ነገሥት) ሕዝባቸውን የእሚዳኙበት ፤ የሕግ ረቂቅ ነው ፍትሐ-ነገሥት ።

በአጭሩ ፍትሐ-ነገሥት ማለት የክርስቲያን ነገሥታት ፤ በፍትሕ[2] የእሚዳኙበት መጽሐፍ ማለት ነው ።

ይኽ ፤ አንድ የክርስቲያን ንጉሥ በፍትሕ በአግባብ ማስተዳደር እንጂ ከእርሱ የእሚጠበቀው ፤ ክርስቲያን ስለ ሆነ ንግሥናውን እንዲተው መጽሐፍ ቅዱስም የአዕምሮ ፍርድም አያስረዱም በእሚል በወቅቱ የክርስትና እምነት ሊቃውንት የተዘጋጀው ፍትሐነገሥት ፤ በውስጡ የያዝቸው ድንጋጌዎች ፦ መጽሐፍ ቅዱስን ፣ ከመንፈሳዊ እውነት ጋር የእማይጋጩ ምድራዊ ፍልስፍናዎችን እና ከእርሱ በፊት የነበሩ የሮማዊያንን ሕግ መሠረት የአደረገ ነው ።

ፍትሐ-ነገሥት በእዚኽ መልኩ ዓለም-ዓቀፋዊነት ቢኖረውም ፤ ከኢትዮጵያ ነገሥታት ውጭ ሌሎች የክርስቲያን ነገሥታት ሲጠቀሙበት አይታይም ፤ ይኽም ፍትሐነገሥትን ከኢትዮጵያ ጋር በልዩ ኹኔታ የተቆራኘ ያደርገዋል ።

መጽሐፉ በይዘቱ ፤ እንደ ማንኛውም ጥንታዊ መጽሐፍ አኹን ከአለንበት ዘመን አንፃር ኋላ ቀር ወይንም የእማያስኼዱ መርህዎችን የያዘ ቢሆንም ፤ የዛሬውን ሳይንሳዊ ሕግ የእሚመጥኑ እና ለዛሬው ሳይንሳዊ ሕግ መሠረት የሆኑ እና ዓለም ዓቀፋዊ በሆነ አግባብ የተሰናዱ የሕግ ፅንሰ ኃሳቦችን የያዘ ነው።

ፍትሐነገሥት ከእሚያነሳቸው ጉዳዮች ብድር ፣ ንግድ ፣ የንግድ ትርፍ ፣ ዓመፅ ፣ ወዘተ ፤ ተጠቃሽ ሲሆኑ ፤ በእነዚኽም ጉዳዮችም ላይ ፤ መጽሐፍ ቅዱስን ፣ የተለያዩ ምድራዊ የፍልስፍና ዕውቀቶችን ፣ ከእርሱ ቀደም የነበረውን የሮም ሕግ እና የአዕምሮ ፍርድ በመጠቀም ሕግ ይደነግጋል ።

ለኹሉም ነገር አስቀድሞ ሕግ ማውጣት እንደ እማይቻል በመገንዘብም ፤ የአላካተታቸው ጉዳዮች ሲገጥሙ ዳኞች የልቦናቸውን ፍርድ መጠቀም እንደ እሚገባም እና አስፈላጊ ከሆነም ሕጉን ራሱ ሊቃውንት ሊያሻሽሉት እንደ እሚችሉ ይደነግጋል ።

በአጠቃላይ ሰነዱ ፤ መሻር የነበረባቸውን ኃሳብ ይዞ ቢገኝም ፤ በሳል የሕግ እውቀት የእሚንፀባረቅበት ሰነድ ነው ።

ለምሳሌ ፦ ፤ በአንቀፅ 38 ላይ ፤ ሕጋዊ የብድር ስምምነት ፦ ማበደር እና የመበደር መብት በአላ፟ቸው ሰዎች ፤ በእሚታወቅ የእዳ እና የትርፍ ክፍያ መጠን በግልፅ የተቀመጠ ሲሆን ብቻ ሕጋዊ እንደሚሆን ይላል ፦

“ የብድር ስምምነት ግን ያንን ገንዘብ በማወጣጣት መብት በአላ፟ቸው ሰዎች መካከል ይገባል ። በታወቀ ገንዘብ ላይ ፣ በቋሚ ሚዛን ከታወቀ ፣ ትርፉም በልክ ከአልሆነ ወይንም ከእዚኽ በሌላ ቢሆን እውነተኛ አይሆንም ። [95]”

ከእላይ እንደ አልነውም ፤ ሕጉ ለዛሬው ዘመናዊ ፖለቲካዊ ሳይንስ መሠረት የሆኑ ፤ ምድራዊ የፍልስፍና እውቀቶችን እንደ ተንተራሰ ከእሚያሳዩት ነገሮች አንዱ ፤ ስለ ሰው ልጅ ተፈጥሮዋዊ ነፃነት እና እኩልነት የእሚያወራበት ክፍል ነው ።

ለምሳሌ ፦ ምንም እንኳን ስለ ባሪያ አስተዳደር የእሚለው ነገር ቢኖርም ፤ ባርነት በመርህ ደረጃ ስህተት መሆኑን አንቀፅ 31 ላይ ይደነግጋል ፦

“ ሰዎች ኹሉ በጥንተ ተፈጥሮ በነፃነት አንድ ናቸውና ። መጣላትና የፈረስ ጉልበት እርስ በርሳቸው ይገዙ ዘንድ (መገዛትን) ታመጣባቻዋለች እንጂ ። የጠብና የማቸነፍ ሕግ ድል የሆኑትን ድል ለአደረጉት ባሮች (ተገዦች) ታደርጋቸዋለችና ። [95]”

ይኽ በፍትሐነገሥት የተቀመጠ ኃሳብ ፤ ባርነት ተፈጥሮዋዊ ሰአይሆን በጦርነት ብርታት (በፈረስ በዘመናዊ ቋንቋ በወታደራዊ ኃይል) በሰዎች ላይ የእሚጫን መሆኑን በግልፅ በማስቀመጥ ፤ ሰው ኹሉ በተፈጥሮ ነፃ እና በነፃነቱም እኩል መሆኑን የእሚያውጅ በመሆኑ ፤ የመጽሐፉን ፍልስፍናዊ መሠረት ማሳየት ብቻ ሰአይሆን የፍልስፍናውንም ጥራት የእሚያሳይ ነው ።

ምንም እንኳን ባሪያ አታሳድሩ ብሎ ባይደነግግም ፤ የሰው ባሪያ ስለ ሌለ ፤ ባሪያን ነፃ ማውጣት መልካም ግብር እንደሆነ እና ይኽንንም የእሚለው ደግሞ ሰው በተፈጥሮ በነጻነት ሕግ ሊኖር ስለ እሚገባው ነው በማለት ይአስቀምጣል ፦

“ከትሩፋት ወገን የእምትሆን ነፃ ማውጣትስ ፤ እርሷን ይአደርጉ ዘንድ የእምትገባ ናት ። ፍፁም ምፅዋት ናትና ፤ ለሰው ስልጣን መስጠትም ፤ በጥንታዊ የተፈጥሮ ጠባዩ ፍርድ ራሱን ይገዛ ዘንድ ነው ። [95]”

ፍትሐነገሥት ፤ እንደ ማንኛውም የሕግ ማዕቀፍ ሙሉ እና ፍፁም በአይሆንም ፤ ትልቅ የፍትሕ ግንዛቤ የተንፀባረቀበት ፤ የኢትዮጵያንም ሕዝብ ታሪካዊ የእድገት ደረጃ የእሚያንፀባርቅ የሐገር ኃብት ነው ።

የመጀመሪያው የ1923ቱ የኃይለ ሥላሴ ሕገ-መንግሥትን ጨምሮ አንዳንድ ሰነዶች እና ሰዎች ፤ ፍትሐነገሥትን ሕገ-መንግሥት ነበር የማለት አዝማሚያ ቢያሳዩም ፤ ፍትሕነግስት መደበኛ ሕግ እንጂ የሕገ-መንግሥት ቅርፅ አልነበረውም ። ምንም እንኳን ፤ ለዘመናዊው ሕገ-መንግሥት መሠረት የሆኑ ፤ ሰው ኹሉ በተፈጥሮ እኩል ነፃ ነው የእሚሉትን መሰል ድንቅ ኃሳቦች ቢይዝም ።

ከእዚያኽ ኹሉ በተጨማሪም ፤ ፍትሐነገሥት እንደው ለይስሙላ ተፅፎ የተቀመጠም ሰአይሆን ፤ በፍትሐነገሥት እውቀት አንቱ የተባሉ ኢትዮጵያዊ የሕግ ሊቃውንት የተፈጠሩበት እና ነገሥታቱ ለዳኝነት ሲቀመጡ ፤ ፍትሐ-ነገሥት እየተጣቀሰ ብይን የእሚሰጥበት ፤ ለረዥም ዘመን ሐገር የአስተዳደረም ሰነድ ነው ።

በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትሐ-ነገሥት ለረዥም ዘመን በሥራ ላይ ከመዋሉ የተነሳ ፤ በእንግሊዘኛው (Common Law) ወይንም የወል ሕግ የእሚባለውን ልማድም አስጀምሮ የነበረ ነው ። እንደ እሚታወቀው ፤ የወል ሕግ ዋናው ዓላማ ፤ ምንም እንኳን ቋሚ የተጻፈ ሕግ ቢኖርም ፤ ከችሎት ችሎት በአተረጓጎም ልዩነት የተለያየ ብይን እንደ አይሰጥ ፤ አንድ የክስ ዓይነት በአንድ ችሎት አንድ ግዜ ከተስተናገደ በኋላ ፤ ተመሳሳይ ክሶች ኹሉ ተመሳሳይ ብይን እንዲያገኙ የእሚያደርግ ነው ።

በእዚኽም መሠረት ፤ ለምሳሌ ፦ በፍትሐነገሥት ‘እንደ ዘውዴ ጎሹ ሚስት’ የእሚለው የወል ሕግ አንዱ ነበር ።

ሌሎች በፍትሐነገሥት ላይ የተመረኮዙ የፍርድ ውሎ መተንተኛዎች ከአስቀመጡት ሳቢ አገላለፆች መካከል ፦

  • ብኩን በመሆኑ ቤተሰቡን ችላ የአለውን አባት ሲወቅስ ፤ “ላዝማሪ ፣ ለዘዋሪ ለመሸታ እያወጻጻ እሚያጠፋ“ይለዋል
  • የግል ኃብቱን አንድ ሰው ሲያወርስ እንዴት ብሎ ኑዛዜ ማስቀመጥ እንደ አለበት ሲያስቀምጥ “የወገቤን ሰይፍ ፣ የክንዴን ጋሻ ፣ የእጄን ጦር ፣ የጭኔን ፈረስ ለእገሌ ሰጥቻለሁ ብሎ ለይቶ የእሚያዝ” መሆን እንደ አለበት ይላል
  • በዝርፊያ ወይንም በቅሚያ የተገኘን ኃብት የእኔ ነው ማለት እንደ እማይቻል ሲያስቀምጥ “በፈረስ አንገት በጦር አንደበት” የተገኘ እንደው ይላል ፤ በፈረስ ዘምቶ በጦር ወግቶ የተወሰደ ኃብት የእኔ ነው ማለት አይቻልም ለማለት ።
  • ከሌባ እቃ መግዛት ወይንም ሌባን ሸሽጎ መካፈል ጥፋተኛ እንደ እሚያስብል ሲያስቀምጥ “የሌባ ዋሻ የቀማኛ ጋሻ” መሆን ይለዋል የክሱን ዓይነት
  • አለመግባባት ከአለ፟ ፤ ከመጣላት በፍርድ ቤት መዳኘት እንደ እሚገባ ሲመክር “ዘንግ አቀንቶ ዳኛ አውጥቶ መከራከር” ይላል [127]“

እነ እዚኽ ደግሞ ፤ በዘመናዊው ዓለም መመዘኛ እንኳን በኢትዮጵያ የነበረውን መንግሥት የእሚያስከብሩ የፍትሕ ልምዶች ናቸው ።

አንድ አንድ ሰዎች ግን ፤ ይኽን ታላቅ ጥበብ የተንፀባረቀበት ሰነድ ፤ በሰነዱ ዓለም ዓቀፋዊነት ምክንያት ፤ ከውጭ የተቀዳ በመሆኑ እንደ ሐገራዊ ጥበብ ሊታይ አይገባውም የእሚል ትችት ሲያነሱ ይሰማል ። እነ እዚኽ ሰዎች የአልገባቸው ግን ፤ የአንድ ሕዝብ ታላቅነት የእሚመዘነው ጥራት የአላቸውን ፍልስፍናዎች እና የሳይንስ እውቀቶች ተረድቶ ፤ በሥራ ላይ ለማዋል በአለው አቅም እንጂ ፤ በፈጣሪነቱ ላይ ብቻ የእሚወሰን አለመሆኑን ነው ።

ጥበብ ወይንም ፍልስፍና እና እውቀት ፤ በባሕሪያቸው ዓለም ዓቀፋዊነት የአላቸው ናቸው ። ፍትሐነገሥት ውስጥ የተካተቱት እውቀቶች ፦ የአሌክሳንደሪያ ፣ የሮም ወይንም የይኹዳ ብቻ ጥበቦች አይደሉም ፤ ከእነ እዚኽ ኹሉ ቦታዎች የተውጣጡ ናቸው ። ዓለምም ዛሬ የደረሰበት ስልጣኔ ላይ የደረሰው ፤ ከእርሱ በፊት እና ከእርሱ ሌላ ያሉትን ጥበባት በመማር እና በመተግበር እንጂ ፤ እየ አንዳንዱ የሰለጠነው አከባቢ የራሱ የሆነ የጥበብ ሞኖፖሊ ስለ አለው አይደለም ።

ስለ እዚኽ ፍትሐነገሥት ሐገር በቀል አይደለም ተብሎ የቀድሞ አባቶቻችን የእሚያስወቅስ ሰአይሆን ፤ ዓለም የደረሰበትን ጥበብ አስገብተው በመጠቀማቸው አንቱ ሊያስብላቸው የእሚገባ ነው ። ጥበብን አውቆ ለመጠቀምም ጥበበኛ መሆን ይጠይቃልና።

አርስታትልም እንደ እዚኽ ይላል ፦

“በእራሱ ኹሉንም ነገር የእሚያውቀው እርሱ ምርጥ ነው ፥

ሰዎች መልካም ምክር ሲመክሩት በጄ የእሚለው ደግሞ መልካም ነው ፤

በእራሱም የእማያውቀው ወይንም የሌላውንም ጥበብ በጄ የእማይለው ፣

እርሱ እርባና ቢስ ፍጥረት ነው።”

“For best is he who knows all things himself,

Good, he that hearkens when men counsel right ;

But he who neither knows, nor lays to heart

Another’s wisdom, is a useless wight. [128]”

ምንም እንኳን ከእላይ እንደ አጣቀስነው ፤ ፍትሐ-ነገሥት ስለ ራሱ የ4ኛው ምዕተ ዓመት ገደማ ሰነድ እንደ ሆነ የእሚናገር ቢሆንም ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በሥራ ላይ ውሎበት የነበረባቸው ግዜያት ታሪካዊ ማስረጃ እስከ አሁን የተገኘው ፤ ከአጼ ዘራ ያቆብ የንግሥና ዘመን ማለትም ከ15ኛው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ አከባቢ በመሆኑ ፤ ፍትሐነገሥት በኢትዮጵያ ውስጥ ፤ እስከዛሬ በተገኘ ታሪካዊ ማስረጃ መሠረት ፤ የ500 ዓመታት በላይ እድሜ አለው ማለት ነው ።

ይኽም በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ፤ ቢያንስ የዛሬ 500 ዓመት አንስቶ ፤ ፍትሐነገሥትን መሰል ትልቅ የሕግ ማዕቀፍ ተገንዝቦ በሥራ ላይ ማዋል የእሚችል ማሕበራዊ አቅም የነበረው ነበር ማለት ነው ።

በእዚኹ ዘመን ፤ አውሮፓዊያኖቹም ከሮም ውድቀት በኋላ ከነበረው የ1000 ዓመት የጭለማው ዘመን ወደ ሕዳሴው ለመግባት የጀመሩበት ወቅት በመሆኑ ፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ዳሰሳ ላይ እንደ አልነው ፤ በክፍል አምስቱ እና ስድስቱ የታሪካችን ምዕራፍ ፤ ያንን ያኽል መጠነ ሰፊ አደጋ ባይጋረጥብን ኖሮ ፤ እኛም እንደ ማንኛውም ዘመናዊ አውሮፓዊ የዘመናዊነቱን መሰላል ፤ በተመሳሳይ ፍጥነት መወጣጣት የእምንችልበት ማሕበራዊ የእድገት ደረጃ ላይ ነበርን ማለት ነው ።

የዘመናዊው ዓለም ማሕበራዊውም ሆነ ቴክኖሎጂያው ልህቀት መፍለቂያ የሆኑት እንግሊዞች ፤ በእዚኽ ዘመን ላይ ልክ እንደ ኢትዮጵያው የአውሮፓን ስልጣኔ በስፋት ወደ ሐገራቸው የእሚያስገቡበት ግዜ ነበር ። ስለ እዚኽ ፤ ከሌላው እና ከእነርሱ በፊት ከነበረው ጥበብ ተውሰው የዛሬውን ዘመናዊ ዓለም ስልጣኔ ያስጀመሩትን እንግሊዞች ፤ የተቀዳ እውቀት ነው የእነርሱ እውቀት ብለን ካልወቅስናቸው ፤ የ15ኛው ምዕተ ዓመት ኢትዮጵያዊያን ፤ ከሮም ፣ ከአሌክሳንደሪያ ፣ ከይሁዳ ፣ ወዘተ ፤ ጥበብ አመጡ በማለት ልናዋድቃቸው የእምንችልበት አግባብ የለም ።

በመጨረሻም ፦ ምንም እንኳን ፤ እነ እዚኽን ታሪካዊ ሐገራዊ የስነ መንግሥት ሰነዶች ፤ ከእላይ ለማሳያነት ያነሳኋቸውን እና ሌሎችም ብዙ ድንቅ ኃሳቦች የያዙ ቢሆኑም ፤ በታሪካችን ሰንካላነት ምክንያት በጅምር የቀሩ የጥበብ ሥራዎች በመሆናቸው ፤ ኃይለ ሥላሴ ወደ ዘመናዊ ሕገ-መንግሥት እና ሕግ ወደ ማርቀቅ ሲገቡ ፤ እነ እዚኽን ሰነዶች ፤ እንዳሉ ወደ መደርደሪያ መልሰን ነው ፦

  • በፍትሕብሔር ሕግ
  • በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ
  • በንግድ ሕግ እና
  • በ1923ቱ የኃይለ ሥላሴ ሕገመንግሥት

የተካናቸው ።

ምናልባት ክብረ ነገሥት እና ፍትሐነገሥት ፤ በተረጋጋ ፖለቲካዊ እና ሐገራዊ ምህዳር ውስጥ የእሚዳብሩበት አጋጣሚ ስለ አልነበረ ፤ በኋላ ላይ እነርሱን ከማዳበር አዲስ መጀመሩን ተመራጭ አድርጎት ይሆናል ።

  1. በመጽሐፉ ምዕራፍ አንድ ኃይማኖታዊ ፅንፈኝነት በእሚለው ንዑስ ክፍል ላይ ኔሮ የተባለው የሮማ ቄሳር ክርስቲያኖችን በእሳት እንደ አቃጠለ ፣ በአውሬው እንዲበሉ እንደ አደረገ ፣ ወዘተ ፤ ማንሳታችን ይታወሳል። ↑

  2. ፍትሕ ፦ የክብረ ነገስት እና የፍትሐነገስት ዋነኛ ማጠንጠኛ ነው። ↑