ሕ ገ ክ ራ ሲ

marketing-image

4.1.2. ሕግ እና ሕገመንግሥት በዘመናዊ ኢትዮጵያ

ክብረ-ነገሥት እና ፍትሐ-ነግስት የኢትዮጵያን ሕዝብ እና መንግሥት ለረዥም ግዜ ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ ፤ ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን አንስቶ ፤ ክብረ-ነገሥት በ1923ቱ የኃይለ ሥላሴ ሕገ-መንግሥት እና ፍትሐ-ነገሥት ከ1920ዎቹ መጀመሪያዎች አከባቢ መውጣት በጀመሩት ፦ የወንጀለኛ መቅጫ ፣ የፍትሐ-ብሔር እና የንግድ ሕግጋት ተተኩ ።

በእዚኽ መልኩ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ፤ ክብረ-ነገሥት እና ፍትሐ-ነገሥት በቅደም ተከተል በዘመናዊ ሕገ-መንግሥት እና በተለያዩ ሕግጋት ከተተኩ በኋላ ፤ ኹለቱም ሰነዶች የእየራሳቸው የእድገት እና የለውጥ አቅጣጫ ወስደዋል ።

የመጀመሪያው የኃይለ-ሥላሴ ዘመናዊ ሕግ-መንግሥት በ1923 ዓ.ም. በሥራ ላይ ከዋለበት ግዜ አንስቶ ፤ አኹን እስከ አለንበት ግዜ በኢትዮጵያ አንድ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ እና ኹለት የሕገ-መንግሥት ለውጦች ተካኺደዋል ።

ፍትሐ-ነገሥትን የተኩት እንደ ፍትሐ-ብሔር ፣ ወንጀለኛ መቅጫ ፣ የንግድ ሕግ ፣ የቤተሰብ ሕግ ፣ ወዘተ ፤ በርከት የአሉ ማሻሻያዎች ፣ ለውጦች እና ጭማሪዎች እየተደረገባቸው ፤ ከእየ ግዜው ኹናቴ ጋር ለማጣጣም ይሞከራል ።

በሕገ-መንግሥቶች ረገድ ያሉት ጅማሮዎች ፣ ማሻሻያዎች እና ለውጦች ግን ይዘታቸው ሲታይ ፤ በዘመን አስገዳጅነት ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ሕገ-መንግሥት አልባ መንግሥት መሆን የእማይቻልበት ዘመን ላይ በመሆናችን ፤ ይኽንን ዓለም ዓቀፋዊ ግዴታ ለመወጣት ሲባል የእሚተገበሩ እንጂ ፤ የዘመናዊ ሕዝባዊ ሕገ-መንግሥት ፅንሰ ኃሳብ ለሕዝብ የአለውን ፋይዳ በማድነቅ እና ሕዝብንም የእዚኽ ተጠቃሚ ማድረግን ግብ የአደረጉ አይደሉም ።

በዋናነት የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ስረዓቶች የእሚባሉት ፤ የዘውዱ ፣ የደርጉ እና የኢሕአዴጉ ሕገ-መንግሥታት ፤ በተለያዩ ደካማ ፖለቲካዊ ስሌቶች እና በእሚከተሉዋቸው ርዕዮቶች ምክንያት ፤ መሠረታዊ የሕዝባዊ ወይንም የዴሞክራሲያዊ መርህዎች የእሚጥሱ ናቸው ።

ይኽን ለማሳየት ፤ በእዚኽ ንዑስ ክፍል በዘመናዊ ኢትዮጵያ በኃይለ-ሥላሴ እና በደርግ ዘመን የነበሩትን ሕገ-መንግሥታት ዋና ዋና ይዘት እና የኢሕአዴግን ሕገ-መንግሥት በዝርዝር ለብቻው በእሚቀጥለው ንዑስ ክፍል ፤ ለማየት እንሞክር ።

በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው እና ከ1923ቱ የአጼ ኃይለ ሥላሴ ንግሥና ወይንም በዓለ ንግሥና ጋር ተያይዞ የተዋወቀው ሕገ-መንግሥት ፤ ለአምስት ዓመትም በሥራ ላይ ሳይቆይ በ1928 ዓ.ም. ኢትዮጵያ በጣሊያን በመወረሯ እና የጣሊያንም ወረራ ከአምስት ዓመት በኋላ ሲነሳ ሐገር ማረጋጋቱ ብዙ ፈተና ስለነበረበት ብዙም የተሰራበት ሕገ-መንግሥት አልነበረም ።

የጣሊያኑ ወረራ ከአበቃ እና የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ፤ የጣሊያኑን ወራሪ ኃይል ከኢትዮጵያ በማስወጣት ረገድ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት አጋዥ የእንግሊዝ ሠራዊት ፤ ከሐገር ከወጡ በኋላ ፤ ይኸው የ1923ቱ የአጼ ኃይለ ሥላሴ ሕገ-መንግሥት ፤ በዋናነት የነጋሢ ዘሩ ከንጉሥ ሰኃለ ሥላሴ እንዳይወጣ የእሚለውን ኃሳብ በእሚያጠናክር መልኩ በ1948 ዓ.ም. ተሻሻለ ።

እነ እዚኽ ኹለቱም የኃይለ-ሥላሴ ሕገ-መንግሥታት ፤ የነጋሢው ዘር በተመለከተ ፤ ክብረ ነገሥቱ እንደ እሚለው ፤ በዘውዱ የስልጣን አስተዳደር መማክርት እየተወሰነ ሕጋዊ የዙፋኑ ወራሾች ከንጉሥ ሰለሞን ዘር የተወለዱት ከንጉሥ ሳህለ ስላሤ የልጅ ልጆች መሆን አለባቸው ፤ የእሚል ነው ።

ምንም እንኳን ይኽ አሰራር ፤ በሕዝብ ፈቃድ የንጉሡን ስልጣን መገደብ በእሚቻልበት ግዜ ፤ ሕገ-መንግሥታዊ የዘውድ ስረዓት ወይንም ዴሞክራሲያዊ የዘውድ ስረዓትን የእማይከለክል ቢሆንም ፤ የመጀመሪያዉም ሆነ የተሻሻለው የአጼ ኃይለ ሥላሴ ሕገመንግሥት ግን የንጉሡ ስልጣን በሕግም በአሰራርም መገደብ የእማይቻል አድርጎ በግልፅ ስለ ደነገገው ፤ ስረዓቱ ሕገ-መንግሥታዊ የዘውድ ስረዓት እንደ አይሆን አድርጎታል ።

ከእዚያኽም በአሻገር ፤ በኃይለ-ሥላሴ ሕገ-መንግሥት ምንም እንኳን እንደ ዘመናዊ ሕዝባዊ ሕገ-መንግሥታት ፤ ቁጥጥር እና ሚዛን (Check & Balance) እንደ እሚባለው ፤ የብሔራዊ መንግሥትን ስልጣን ፤ በሕግ አውጪ ፣ በሕግ ተርጓሚ እና በሕግ አስፈጻሚ የእሚከፋፍል ቢመስልም ፤ ከፍርድ ቤቶቹ[1] ወይንም ከሕግ ተርጓሚዎች በስተቀር ፤ ኹለቱ ትላላቅ የብሔራዊ መንግሥት ቅርንጫፎች ፤ በአሠራር እና በሕግ ፤ ቀጥታ በንጉሡ የእሚታዘዙ በመሆኑ ፤ ተቋሟቱ የአጋዥነት እና የማሟያነት ሥራ ከመሥራት የአለፈ ፤ ነገር መከወን የእሚችሉበት አቅም አልነበራቸውም ።

ሕግ አውጭው ፤ ታችኛው እና ላይኛው ቤት በእሚል ፤ ፓርላማ ወይንም የሕዝብ እንደ ራሴዎች ምክርቤት እና ሴነት አለው ።

ሆኖም ግን ፤ ለታችኛው ቤት የሕዝብ እንደራሴ ሆኖ ለመመረጥ ፤ የተወሰነ የንብረት ባለቤትነት ግዴታ ስለ እሚያስቀምጥ ፤ ይኽን የመኖሪያ ቤት ባለቤትነት ቅድመ ኹኔታ ማሟላት የእማይችሉትን ዜጎች ከመመረጥ መብት የአገለለ ነበር (አንቀፅ 96) ። ይኽም በመሆኑ መሠረታዊውን የሕዝባዊ ዴሞክራሲ መርሕ የሆነውን የዜጎችን የመመረጥ መብት የእማያከብር ነበር ።

ኹለተኛ ፤ ሴኔቱ በንጉሡ የእሚመረጡ ሰዎች የእሚሰየም በመሆኑ እና ማንኛውም ሕግ ለማፅድቂያ ፊርማ ወደ ንጉሡ ጋር ከመኼዱ በፊት ፤ በኹለቱም የሕገ መወሰኛ ቤቶች ፤ ማለትም ፦ የሕዝብ እንደ ራሴዎች ምክር ቤት እና በሴኔቱ በአብላጫ ድምፅ ማለፍ ስለ አለበት ፤ የንብረት ባለቤት ሆነው ተመራጭ የሆኑ የሕዝብ እንደ ራሴ ምክር ቤት አባላት ፤ የእሚያወጡት ሕግጋት በቀላሉ ፤ በንጉሡ በቀጥታ በእሚሰየሙት ሴናተሮች ተሸንፎ ሊወድቅ ይችላል ።

እንደገናም ፤ አንድ ሕግ ኹለቱንም የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቶች አልፎ ንጉሡ ጋርም ቢደርስ ፤ ንጉሡ ሕጉን ከማሻሻል እስከ መሻር ድረስ ፍፁም ስልጣን የአላቸው በመሆኑ (አንቀፅ 88 እስከ 92) ፤ የሕገ መወሰኛው ምክር ቤት ሕግ በማውጣቱ ረገድ አለኹ ለማለት እና የማገዝ ሥራ ለመሥራት ከአልሆነ ፤ ምንም ስልጣን የሌለው ነበር ።

በመንግሥት አስፈጻሚውም ረገድ ፤ ንጉሡ የመሰላቸውን ሰው በፈለጉበት ቦታ ላይ መሾም የእሚችሉ በመሆኑ ፤ የሐገሪቱ የፖለቲካ ስልጣን ኹሉ ተሰብስቦ የንጉሡ ጠረጴዛ ላይ ነው የነበረው ።

በአጭር ቋንቋ ፤ ሕዝብ በተወሰነም ደረጃ እንደራሴዎቹን በመምረጥ የስልጣን ባለቤት እንደሆነ እንዲ መስል ተደርጓል ፤ በእዚያኽም መሠረት የእሚሰራ ይመስላል ፤ ነገር ግን ፓርላማው የንጉሥ ሕግጋት ላይ ማህተም ከማሳረፍ የአለፈ እውነተኛ ሕግ የማርቀቅ እና የማፅደቅ ስልጣን ፤ በስም እንጂ በተግባር አልነበረውም ።

በእዚኽም ፓርላማው አለ ከመባል የአለፈ ሕጋዊ ስልጣን የሌለው በመሆኑ ፤ የመንግሥት አስፈጻሚዎች በቀጥታ በንጉሡ ፍላጎት ብቻ የእሚሾሙ በመሆኑ ፤ ሐገሪቱ እንደ ማንኛውም ፍፁማዊ እና አምባገነናዊ አስተዳደር በአንድ ሰው ፈቃድ እና ፍላጎት ነበር የእምትመራው ።

ይኽ ንጉሡን የመጨረሻው ስልጣን ባለቤት የአደረገ ሕገ-መንግሥት ፤ ምንም እንኳን ብዙ ትልልቅ ለውጦችን ቢያስመዘግብም ፤ መንግሥታቸው በሕዝብ ተጠያቂ የማድረጉን እና የመንግሥትን የእርስ በእርስ ቁጥጥር እና ሚዛን መርህ (check and balance) የዘነጋ በመሆኑ ፤ ጠቅላላ የሐገሪቱን መንግሥት ፤ በባለሙዋልነት ስነልቦና ተጠፍሮ የተያዘ ስለ አደረገው ፤ ሕዝባዊ ግፊቶችን ማድመጥ እና መልስ መስጠት የእሚያስችለው ተቋማዊ አቅም እንዳይኖረው አድርጓል ።

የዘመናዊ ሕገ-መንግሥት ዋናው መርህ ፤ መንግሥት በሕዝብ የእሚሾም እንጂ በሕዝብ ላይ የእሚሾም መሆን የለበትም ብቻ ሰአይሆን ፤ ተጠያቂነቱም ለሕዝብ ነው የእሚል ነው ።

የኃይለ ሥላሴ ሕገ-መንግሥት መንግሥትን በሕዝብ የእሚሾም (በከፊልም ቢሆን) አድርጎ ፤ ተጠያቂነቱን ግን በቀጥታ ለንጉሡ የአደረገ በመሆኑ ፤ ሕዝብ የእማይጠይቀው መንግሥት ደግሞ ሕዝብን የእማይሰማ በመሆኑ እና የሕገ-መንግሥት ግብ የሆነውን ተጠያቂነት ማስቀረቱ አንዱ ችግሩ ሲሆን ኹለተኛው ዓለመማከል የእሚለውን የሳይንሳዊ ሕገ-መንግሥት መርህ ችላ በማለት ንጉሡን የስልጣን ማዕከል በማድረጉ ፤ መንግሥታቸው በከፍተኛ ዝግመት እና የቁም እርጅና ተመቶ ፤ ብዙ ሊሰሩ የእሚገባችው ሥራዎች ቢኖሩም እንኳን ፤ እጅግ እያረጁ በኼዱት ንጉሥ የመሪነት ሚና ተወስኖ መንቀሳሰቀስ ያቃተው እንዲሆን አድርጎት ነበር ።

በጥሩ ጅማሬ የነበረ ነገር ግን ፤ ከልክ የአለፈ ዝግመት እና የቁም እርጅና ከውስጥ ያጎበጠውን የኃይለ ሥላሴን መንግሥት ፤ በዓለም ዓቀፍ ከምኒዝም መሪነት በተቀጣጠለ አብዮት በወታደራዊ አደረጃጀት ግንባር ቀደም መሪነት የመንግሥት ግልበጣ አድርጎ ወደ ስልጣን የመጣው ደርግ ፤ እያዘገመም ቢሆን በሐገር ደረጃ ብዙ የቁስ እና የዕውቀት ካፒታል ገንብቶ የነበረውን ይኽን የንጉሡን መንግሥት መዋቅር ፤ ለደህንነት ስጋት በእሚል ፤ ሙሉ በሙሉ ካከሰመ በኋላ ፤ በውትድርናው መስክ ካላቸው የሻለቅነት ማዕረግ እና ውስን የፖለቲካዊ ንቃት ውጭ ፤ ይኽ ነው የእሚባል የሕዝብ አስተዳደር እና የፖለቲካ ዕውቀት የሌላቸውን ወታደሮች ፤ በውጭ ከምኒስት አማካሪዎች እየተረዱ ሐገር የእሚመሩበት የሞስኮ ወኪል መንግሥት ሆነ ።

ደርግ በ1966 ዓ.ም. ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ፤ የኃይለ ሥላሴን ሕገ-መንግሥት ሙሉ በሙሉ ሽሮ ፣ ፓርላማ እና ሴኔቱን አፍርሶ ፤ ከ17 ዓመት እድሜው ውስጥ ፤ ለመጀመሪያዎቹ 13 ዓመታት ምንም ዓይነት ሕገ-መንግሥት እና የሕዝብ ተወካዮች ተቋም ሳይኖረው ከቆየ በሗላ በ1979 ዓ.ም. የካቲት 15 ላይ ፤ የራሱን ሕገመንግሥት እና ለኢትዮጵያ ደግሞ 3ኛውን ሕገመንግሥት አስተዋወቀ ።

እንደ እዚኽ ዘግይቶ ፤ በ17 ዓመት ጠቅላላ የስልጣን ቆይታው ከ13ኛ ዓመቱ በኋላ የመጣው የደርግ ሕገ-መንግሥት ፤ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት (አንቀፅ 4) የእሚመራ ነበር ።

ዴሞክራሲያዊ መዓከላዊነት ደግሞ የመንግሥት ስልጣን አወቃቀር መመሪያ በእሚሆንበት ግዜ ከእሚያመጣቸው አሰራሮች አንዱ ፤ በመሠረታዊነት በሕዝብ ምርጫ የእሚመሠረት የሕግ መወሰኛ ምክርቤት የቡርዥዋ ዴሞክራሲ ብሎ የእሚነቅፍ በመሆኑ ፤ በሕዝብ ቀጥታ ተመርጠው የእሚመጡ ተወካዮች አይኖሩትም ፤ ይልቁንም ለምሳሌ ፦ መዓከላዊ የከምኒስት ፓርቲ ከአባላቱ መካከል እጩዎችን ለሕዝብ ያቀርብና ፤ መዓከላዊው ከምኒስት ፓርቲ ያቀረበውን እጩ ሕዝብ ተሰብስቦ መረጥኩ ይላል።

በሌላ አገላለፅ ፤ ሕዝብ ኢሠፓ የመረጣቸውን ይመርጣል ወይንም ሕዝብ የተመራጮች (ኢሠፓ መርጦ ያመጣቸውን እጭዎች) መራጭ እንጂ ፤ የእንደራሴዎች (ራሱ የፈለጋቸውን እና ይወክሉኛል የእሚላቸውን) መራጭ አልነበረም (It was pre-elected candidates’ selection, not a direct election) ።

ይኽም ማለት ፤ የዴሞክራሲ መሠረት የሆነው የዜጎች ቀጥታ የመምረጥ እና የመመረጥ መብት ፤ ከአምባገነኑ የዘውድ ስረዓትም በከፋ መንገድ ፤ ከዜጎች ሙሉ በሙሉ የተነፈገበት ነበር ።

ደርግ ፤ በርዕዮት እና በሕገ መንግሥት ደረጃ ፤ የአንድ ፓርቲ ስረዓት አራማጅ በመሆኑ ፤ ዜጎች የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) አባላት ከአልሆኑ እና ለእሚወዳድሩበትም ወንበር በኢሠፓው መዓከላዊ ኮምቴ እጩ ተድርገው ከአልቀረቡ ፤ ለመንግሥታዊ ኃላፊነት መመረጥ አይችሉም ። (አንቀፅ 3 እና አንቀፅ 6) ።

በሌላ አገላለፅ ፤ በሐገሪቱ የመጨረሻው ስልጣን ባለቤት የኢሠፓ አባላት እንጂ የኢትዮጵያ ዜጎች በአለመሆናቸው ፤ የኢሠፓ አባላት ደግሞ የሐገሪቱን 1/10 እንኳን ስለ እማይሞሉ ፤ 90% በላይ የእሚሆነው ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፖለቲካ ስልጣን ተወዳዳሪነት በሕገ መንግሥት ደረጃ ያገደ ፍጹም አምባገነን እና ጨካኝ ሕገ-መንግሥት ነበር የደርግ ሕገ-መንግሥት ።

ሌላው ፤ ከዴሞክራሲያዊነት አንጻር ብዙ ሊተች የእሚችለው የደርግ ሕገ-መንግሥት ፤ በሐገሪቱ የመጨረሻው ሕግ ሶሻሊስት ሌጋሊት የእሚባለው መሆኑ (አንቀፅ 5) የሕገ-መንግሥቱን ፀረ ሕዝባዊነት ከእሚያሳዩት ነጥቦች ኹለተኛው ነው ።

በሶሻሊስት ሌጋሊቲ መሠረት ፤ የሰዎች ተግባር ሕጋዊ እና ሕገወጥ ተብሎ የእሚፈረጅበት መመዘኛ ፤ ከመደበኛ የፍትሕ ሕግ (Civil Code and Civil Rights) አንፃር ሰአይሆን የዜጎቹ ተግባር ከማርክሲዝም ርዕዮት አንፃር በአለው ፋይዳ ነው ። ለምሳሌ ፦ አንድ ግለሰብ ሕጋዊ እና ተፈጥሮዋዊ የመናገር ነፃነት መብቱን ተጠቅሞ ሶሻሊዝም ትክክለኛ ርዕዮት አይደለም ብሎ መጻፍ እና መናገር አይችልም ፤ ምክንያቱም ፦ ይኽ ‘የተፈጥሮ ሕግ’ የሆነውን የማርክሲዝም ፍልስፍና መቃወም ስለሆነ ፤ በሶሻሊስት ሌጋሊት መሠረት ሕገ ወጥ ተግባር ነው።

ስለ እዚኽ ፦ የደርግ ሕገ-መንግሥት ፤ ኢትዮጵያዊያን የመምረጥ እና የመመረጥ መብት አላቸው ቢልም (አንቀፅ 50) ፣ ኃሳባቸውን የመግለፅ መብት አላቸው ቢልም (አንቀፅ 47) ፤ እነ እዚኽን መብቶች ለይስሙላ የደረደራቸው እንጂ ፤ ዜጎች በዴሞክራሲያዊ መዓከላዊነት እና በሶሻሊስት ሊጋሊቲ ተከርችመው የማርክሲዝም አገልጋይ ባሮች ከመሆን ውጭ ምንም መብት እንዲኖራቸው የእሚፈቅድ አልነበረም ። በተግባርም የታየው ይኸው ነው ።

ይኽ ፀረ ዴሞክራሲ የሆነው ፤ የደርግ ሕገመንግሥት ከ4 ዓመት ትንሽ ለበለጠ ግዜ በትክክል ሳይሰራ በ1983 ዓ.ም. የደርግ መንግሥት ተወግዶ ፤ ለ16 ዓመታት የትጥቅ ትግል ሲያደርግ የነበረው ኢሕአዴግ መጣ ። የደርግን ከስልጣን መወገድ ተከትሎ የመጣው ኢሕአዴግ ለ4 ዓመት በሽግግር መንግሥትነት ቀጥሎ ፤ በ1987 ዓ.ም. ፤ ለኢትዮጵያ 4ኛውን እና አኹን በሥራ ላይ የአለውን የኢትዮጵያን ሕገመንግሥት አፅድቆ በሥራ ላይ አዋለው ።

በ1987 ዓ.ም. የፀደቀው የኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት ፤ ምንም እንኳን ዓለም ብዙ ከተራመደች እና የኢትዮጵያም ሙህራንም ብዙ ዓለም ዓቀፍ ልምድ ከአዳበሩ በኋላ የወጣ ቢሆንም ፤ ከእርሱ ቀደም ከነበሩት ሕገ-መንግሥታት የጨለመበት ሕገ-መንግሥት ሆኖ ነው የተገኘው ።

የኃይለ ሥላሴ እና የደርግ ሕገ-መንግሥታት ፤ በኃይል በተደረጉ የመንግሥት ለውጦች የተወገዱ በመሆናቸው እና መሠረታዊ ግድፈታቸውም ፤ ከሕዝባዊ መንግሥት ምሥረታ ግብ አንፃር በቅርፅ እንጂ በይዘት ከኢሕአዴጉ ሕገ-መንግሥት ስለ እማይለይ ፤ በእሚቀጥለው ንዑስ ክፍል ፤ የኢሕአዴግን ሕገ-መንግሥት የትኩረት መዓከል በማድረግ የአሉ፟በትን ግድፈቶች የእምንዘረዝርበት ስለ ሆነ ፤ የኢሕአዴጉን ሕገ-መንግሥት ዝርዝር በእዚኽ ክፍል አናየውም ።

ሆኖም ፤ የአሁኑን ጨምሮ የነበሩትን 4 የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥታት ስናነፃፅር ፤ በኢትዮጵያዊያን ለኢትዮጵያ ጥቅም ተብለው የተረቀቁ ሰአይሆን ፤ ፍልስፍናው ይቀያየር እንጂ አንድ የሆነ የፖለቲካ ኃይል ራሱን ፤ በሕዝባዊ ሕገ-መንግሥት ስም ፤ ፍፁም የፖለቲካ ስልጣን ባለቤት ለማድረግ የኼደባቸው መንገዶች ነበሩ ።

ይኽም በመሆኑ ፤ በእኔ እምነት ከኃይለ ሥላሴ ጀምሮ እንደ ኢትዮጵያ ሕዝብ ፤ ከጠንካራ መዓከላዊ መንግሥት ወደ ሕዝባዊ መንግሥት ለመሸጋገር ያደረግነው ጥረት በሙሉ ፤ በእውነተኛ ሕዝባዊ ሕገ-መንግሥት ሰአይሆን ለስልጣናቸው ሲሉ ማስመሰያ ሕገ-መንግሥታትን በእሚያስተዋውቁ አምባገነናዊ የፖለቲካ ኃይላት እየተጠለፈ እስከዛሬ ድረስ ግቡን የአልመታ ጥረት ሆኗል ።

ሦሥቱም ሕገ-መንግሥቶች ፤ የዜጎችን ፦ የመናገር ፣ የመሰብሰብ ፣ ኃብት የማፍራት ፣ በነፃነት የመንቀሳቀስ ፣ ወዘተ ፤ መብት እናከብራለን ይሉና ፤ እነ እዚኽን መብቶች የዜጎች ኢከነሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት እንደ አያረጋግጡ በፍፁማዊ ንጉሥ ፣ በሉዓላዊ ፓርቲ እና በሉዓላዊ ነገድ የእሚሻሩ ያደርጉዋቸዋል ።

በኃይለ ሥላሴ ግዜ ኹሉም መብቶች ለዜጎች ተሰጥተዋል ፤ ዜጎችን ተደራጅተው በመብታቸው ጥቅማቸውን ማስከበር እንዳይችሉ ግን ስልጣን የንጉሡ ነው ይላል ።

የደርግም ፤ ኹሉንም መብት ለዜጎች ይሰጥና ፤ መብት የእሚከበረው ኢሠፓ እስከፈቀደ እና አብዮትን እስካልጎዳ ነው ብሎ ፤ መብቶችን በሙሉ ባዶ ያደርጋቸዋል ።

የኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥትም ፤ ከእርሱ እንደ ቀደሙት ኹሉ ፤ ኹሉንም መብት ለዜጎች ይደነግግና ፤ ስልጣን ግን የብሔሮች ፣ የብሔረሰቦች እና የሕዝቦች ተወካዮች ነው ብሎ ፤ ዜጎችን መብት ይነሳል ።

የሦሥቱም መንግሥታት ሕገ-መንግሥቶች ፤ ሕዝብን እንደ ሕዝብ ስልጣን የነሱ ፤ የአምባገነን ሕገ-መንግሥቶች የነበሩ በመሆናቸው ፤ የሕዝባዊነት መልክ የተላበሱ አምባገነናዊ ሰነዶች ነበሩ ።

ከእዚኽ በእሚቀጥለው ክፍል ፤ ከኢሕአዴግን ሕገመንግሥት መሠረታዊ ግድፈቶች መካከል ፤ ዋነኛ ናቸው የእምላቸውን ሦሥቱን መርጠን በዝርዝር እናያለን።

  1. የፍርድ ቤቱም ቢሆን ንጉሱ በይግባኝ እና በሰበር ችሎት የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን ዳግም መስማት እና ውሳኔ መቀየር የእሚችሉበት አሰራር ነበራቸው። ↑