ከእዚኽ ቀደም በነበረው ዘመናዊ ሕግ እና ሕገ-መንግሥትን በኢትዮጵያ በዳሰስንበት ክፍል ላይ ፤ ከኢሕአዴግ መንግሥት በፊት የነበሩት ኹለት መንግሥታት ፤ በኃይል ተራ በተራ በመወገዳቸው ሕገ-መንግሥታቸውም አብሮ ከሥራ ውጭ ስለተደረገ ፤ ያስተዋወቁዋቸውን ሕገ-መንግሥታት የነበራበቸውን ክፍተቶች ብዙም ሳንዘረዘር ጠቅለል አድርገን አስቀመጠን ፤ ከተነሳንበት ግብ አንጻር አኹን በሥራ ላይ የአለውን የኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት በዝርዝር ለብቻው ማየቱ ተገቢ ይሆናል በእሚል በይደር ለእዚኽ ንዑስ ክፍል አቆይተነዋል ።
የኃይለ ሥላሴን መንግሥት ፤ በመንግሥት ግልበጣ የአስወገደውን ደርግን ፤ በትጥቅ ትግል አስወግዶ ስልጣን የያዘው ኢሕአዴግ ፤ ምንም እንኳን እንደ ግንባር እና ፖለቲካ ኃይል ከስልጣን የተወገደ ቢሆንም ፤ በኢሕአዴግ የተዋወቀው ሕገ-መንግሥት አኹን በሐገሪቱ በሥራ ላይ የአለው ነው ።
ይኽ የኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት ፤ ከእርሱ በፊት ከነበሩት ኹለት ኢ-ሕዝባዊ መንግሥታት ሕገመንግሥታት የእሚለ፟የው ፤ በአካኼዱ ነው እንጂ ፤ በግቡ ዜጎችን ከነጻ እና ፍትኃዊ ፖለቲካዊ ተሳትፎ በማገድ ሕጋዊ የፖለቲካ ስልጣንን በጥቂት የጥቅም ቡድኖች ውስጥ ገድቦ የእሚያቆይ እና ይኽንንም የስልጣን የበላይነቱን ለማስጠበቅ ሲል ፤ ከእርሱ ቀደም ከነበሩት ኹለት ዓምባገነናዊ አገዛዞች በተለየ የሐገርን ህልውና እና አንድነት በስጋት ላይ የጣለ ነው ።
የኢሕአዴግን ሕገ-መንግሥት በእዚኽ መልኩ የአሉ፟በትን ችግሮች ለማስቀመጥ ፤ ከፖለቲካ ሳይንስ አንጻር ሐገራዊ አንድነት ፣ ሐገራዊ ሉዓላዊነት እና ፌደራላዊ የመንግሥት አወቃቀሮችን ፤ ግልፅ በሆነ ቋንቋ አብራርቶ መጀመር ፤ ሙውታዊ (Fatal) የሆኑትን የኢሕአዴግ ሕገመንግሥት ችግሮች ለመረዳት እጅግ ስለ እሚያግዝ ፤ እነ እዚኽን ሦሥት ፅንሰ ኃሳቦች ከአብራራን በኋላ ፤ በእነርሱ ላይ ተንተርሰን ሦሥት የኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት ችግሮችን ተራ በተራ እንቃኛለን ።
ብሔራዊ አንድነት
ስለ ሐገራዊ አንድነት ጉዳይ ስንመጣ ፤ ሐገር የእሚመሠረተው ከአንድነት የእሚገኘውን ጥቅም ለመጋራት በማሰብ በመሆኑ ፤ ሐገራዊ አንድነትን ማጠናከር እና ብሔራዊ የዜግነትን ስነ ልቦና ለማዳበር መሥራት ፤ ተቀባይነት የአለው እና ተገቢ ጉዳይ ብቻ ሰአይሆን ፤ ሐገራዊ ግዴታ የሆነ የፖለቲካ አጀንዳ ነው ።
ደጋግመን እንደ አልነው ፤ የሰውን ልጅ ፖለቲካዊ ፍጥረት የአስባለው ፤ ለፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ጥቅሙ ሲል ፤ በተናጠል ወይንም በቡድን ፤ ፖለቲካዊ ደሴት ሆኖ ከመቆየት ይልቅ የአንድ ትልቅ ፖለቲካዊ ማሕበር አካል መሆንን የእሚመርጥ እና የእዚኽም ፖለቲካዊ ማሕበር አካል እና አባል መሆን የእሚያስችል ተፈጥሮዋዊ ባሕሪ እና ክህሎት የተላበሰ ልዩ ፍጥረት በመሆኑ ነው ።
ይኽ ማለት ፤ ተገቢ የሆነ የመገንጠል እና ነጻ ሐገር የመሆን ጥያቄ የእሚያነሱ የፖለቲካ ኃይላት የሉም ማለት አይደለም ። ነገር ግን ፤ እነ እዚኽ የመገንጠል እና ነጻ የመሆን ፍላጎት የአላቸው የፖለቲካ ኃይላትም ፤ ከተሳካላቸው እና ነጻ ሐገር ከመሠረቱ ፤ በእሚመሠርቱት አዲስ ነጻ ሐገር ውስጥ ፤ ሐገራዊ አንድነትን ማጠናከር እና ብሔራዊ ዜግነትን ማበረታት ፤ ሊቀር የእማይችል እና ተገቢ የፖለቲካ አጀንዳቸው መሆኑን ለማስቀመጥ ነው ።
ምክንያቱም ፦ ፖለቲካዊ ማሕበረሰባት ምንም ያኽል በመገንጠል ቢያንሱም ፤ ከሰው ተፈጥሮዋዊ ባሕሪ የእሚመነጩ ፦ የኃይማኖት ፣ የፖለቲካ አስተሳሰብ ፣ የኢከነሚ ፣ የችሎታ ፣ ወዘተ ፤ ማሕበራዊ ልዩነቶች ሊጠፉ የእማይችሉ በመሆናቸው ፤ በማንኛውም ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ውስጥ ልዩነትን ሳያጠፉ አንድነት ማጠናከር ከአልተቻለ ፤ ልዩነቱ ማሕበረሰብን አቧድኖ በማጋጨት የማሕበራዊ ሰቆቃ ምንጭ መሆኑ የእማይቀር ነው ።
የብዝኃነትት ቋት የሆነው ሐገር የእሚባለው ፅንሰ ኃሳብ እና አንድነት ሊለያዩ የእማይችሉ ናቸው ።
ስለ እዚኽ ፤ ብሔራዊ የጋራ ዜግነት መፍጠር እና ዜጎች ይኽንን ብሔራዊ ዜግነታቸውን እንዲወዱት ፣ እንዲያከብሩት ፣ እንዲፈልጉት እና እንዲጠብቁት ማድረግ ፤ በአንዲት ሐገር ስነ መዋቅር ውስጥ ተገቢ የሆነ ግብ ነው ።
በእዚኽም መሠረት ፤ ሕገ-መንግሥት በፅንሰ ኃሳብ ደረጃ ሐገር (ብሔር) ፥ መሬቱ ፥ መኖሪያው ፣ ሕዝቡ ፣ ሕግ እና ደንቡ ፣ ከመንግሥት ጋር አንድ ላይ ተዋህደው ፤ እንዴት ከመተባበር የእሚገኘውን ጥቅም ለነዋሪዎቻቸው ወይንም ለዜጎቻቸው በተናጠል እና በጋራ ማድረስ ይችላሉ የእሚለው ጥያቄ የእሚመለስበት መዋቅር (Constitution) በመሆኑ ፤ ይኼንን ተገቢ እና ቀና ግብ ለማሳካት የእማይሰራ ሕገ-መንግሥት ወይንም የሐገር መዋቅር መርህ ሰነድ (Constitution) ፤ ተገቢው ሰነድ አይሆንም ።
የመጀመሪያው ዘመናዊ የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት የሆነውን ፤ የ1923ቱ የአጼ ኃይለ ኃይለ ሥላሴ ሕገ-መንግሥት በፀደቀበት ወቅት ፤ ስለ ዘመናዊ ሕገ-መንግሥት ገለጻ እንዲያደርጉ የተመረጡት በጅሮንድ ተክለኃዋሪያት ስለ ሕገ-መንግሥት ከእዚኽ በታች የአለውን ጥሩ ገለጻ አስቀምጠዋል ፦
“እነሆ ለምሳሌ ፦ የግንብ ሕግ ከአራት ነገር የተቋቋመ ነው ። ከድንጋይ ፣ ከኖራ ፣ ከአሸዋ ፣ ከቀጥታ ሚዛን ። እንደ እዚኹም ሐገር ፣ ሕዝብ ፣ ንጉሥ ፣ ሕግ በአንድነት ተዋህደው ለመንግሥት አቋቋም መሠረት ይሆናሉ እና በአንድነት የመዋኃዳቸው ኃሳብ ሕገ-መንግሥት ተብሎ ተሰይሟል ። “
ሕገ-መንግሥት የማዋኃጃ ቀመር ሰነድ ነው ።
ይኽም ማለት ፦ ሕገ-መንግሥታዊ ውይይት ፤ ሐገር በውስጧ የተለያዩ ፤ ፖለቲካዊ ፣ ባህላዊ ፣ ኃይማኖታዊ ፣ ወዘተ ፤ ልዩነቶች የእሚገኙባት መዋቅር መሆንዋን እየተረዳ ፤ ለኹሉም የሐገሪቱ አከባቢዎች እና ዜጎች እኩል ተደራሽነት እና እኩል ተጠያቂነት የአለው ፤ አንድ ጠንካራ ብሔራዊ መንግሥት ስር መኖር ማንኛውም ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ የእሚመሠረትበት ተፈጥሮዋዊ ግብ መሆኑን በመረዳት እና በመቀበል ፤ ይኽንን ለማጠናቀር ሐገርን እንዴት ማዋቀር አለብን የእሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የእሚደረግ ውይይት ነው ።
ፖለቲካዊ ሉዓላዊነት
ኹለተኛው የእምናብራራው ፅንሰ ኃሳብ ሉዓላዊነት ነው ።
ሉዓላዊነት ማለት ፤ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ውሳኔን እና ተግባርን የመምረጥ መብት እና አቅም ነው ።
ስለ እዚኽ ፦ ከማንም ፈቃድ ሳይጠይቅ የፈለገውን ማሰብ እና የእሚመስለውን መተግበር የእሚችል ኹሉ ሉዓላዊ ይባላል ፤ በፅንሰ ኃሳብ ደረጃ ።
በእዚኽም ፅንሰ ኃሳብ መሠረት ፤ በማሕበረሰብ ውስጥ ይኽ ተፈጥሮዋዊ ባሕሪ የሰው ልጅ በኃሪ በመሆኑ ፤ በተፈጥሮ ሰው ብቻ ነው ሉዓላዊ ።
ሰው ግን ፤ በአመዛዝኖ በእሚገኘው ሕግ ፤ ከተፈጥሮ ኹኔታ (ከጦርነት ኹኔታ) ለመሸሽ ሲል እና ከመተባበር ለእሚያገኘው ጥቅም ሲል ሉዓላዊነቱን ፥ በተፈጥሮ ሕግ አግባብ ለእሚቋቋመው አካል አሳልፎ በውክልና ይሰጣል ።
ከእዚኽም የተነሳ ፤ በሕዝብ ምርጫ የእሚቋቋሙ ብሔራዊ መንግሥታት ሉዓላዊ ይሆናሉ ፤ ምክንያቱም ሉዓላዊነታቸውን በውክልና ከተፈጥሮዋዊ ሉዓላዊ ዜጎቻቸው ስለ አገኙዋቸው ።
ይኽ ፤ የዜጎች ተፈጥሮዋዊ ሉዓላዊነት ሆነ ፥ በተፈጥሮ ሉዓላዊ ከሆኑ ሰዎች በውክልና የእሚገኘው ተቋማዊ ወይንም ሕጋዊ ሉዓላዊነት ፤ በተፈጥሮ ሕግ ምክንያት ፤ ስረዓት አልባ እና ማንም እንደአሻው የፈለገውን የማድረግ ፈቃድ በመሆን የተፈጥሮ ወይንም የጦርነት ሁኔታን እንዳያስከትል ለሕግ የእሚገዛ ነው ።
ስለ እዚኽ ፦ ሰው ሰራሹ ሕጋዊ ሉዓላዊነት ወይንም ተፈጥሮዋዊን ሰው ሉዓላዊ ነው ስንል ፤ በፍትሕ ሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው ወይንም መሠረታዊውን የፍትሕ ሕግ ሳይፃረሩ የእሚመስላቸውን ማድረግ ይችላሉ እያልን ነው እንጂ ያሻቸውን ኹሉ የማድረግ ሕጋዊ መብት አላቸው እያልን አይደለም ።
በእዚኽም መሠረት ፤ ብሔራዊ ሉዓላዊ ስእንል ፤ ዜጎች ወይንም ዜጎች በውክልና ያቆሙት ሕጋዊ ሉዓላዊ ብሔራዊ መንግሥት ፤ በሰብዓዊ ሕግ ብቻ ሲገደብ በቀረው ጉዳይ ላይ የእሚመስለውን ማድረግ ይችላል እያልን ነው።
ለምሳሌ ፦ ኢትዮጵያ ሉዓላዊ መንግሥት የአለ፟ባት ሐገር በመሆኗ ፤ በሐገር ድንበሯ ውስጥ የኢትዮጵያ ዜግነት የሌለውን ሰው ወደ ሐገሯ እንዳይገባ የመከልከል ፣ የነበረም ከሆነ እና ከአልፈለገችው የማስወጣት ፣ መሬት እና ቤት እንዳይገዛ የመከልከል ፣ የመምረጥ እና የመመረጥ መብት እንዳይኖረው የማገድ ፣ ወዘተ ፤ መብት አላት ።
የኢትዮጵያ መንግሥት ይኽን ቢያደርግ በሕግ ማንም ሊጠይቀው አይችልም ፤ ምክንያቱም ሉዓላዊ ስለሆነ ።
ከእላይ እንዳልነው ግን ሉዓላዊነት ፤ የተፈጥሮ ሕግን መጣስ አይችልም ፤ ምክንያቱም ፦ የተፈጥሮ ሕግ ሲጣስ የጦርነት ኹኔታን ስለ እሚያስከትል ። በእዚኽም መሠረት ፤ ሉዓላዊት ኢትዮጵያ አንድን ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌለውን ሰው ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ መሬት እና ቤት መግዛት አትችልም ማለት እንደ እምትችለው ያኽል ፤ የኢትዮጵያ ዜግነት በአይኖረውም ከሰብዓዊ ሕግ ውጭ ልትገድለው ፣ ተቀባይነት በሌለው የፍርድ አግባብ ኹኔታ ልታስረው ፣ ወዘተ ፤ አትችልም ። ያን የአደረገች ግዜ ፤ የተፈጥሮን ሕግ ስለ ተላለፈች ፤ የሰብዓዊ መብት ጣሰች ተብሎ ፤ የጦርነት ኹኔታ ውስጥ እንደ አለች ታውቆ ጥፋተኛ ተብላ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ትወነጀላለች ።
የሉዓዊነትን ኃሳብ ስንጠቀልለው ፤ በማሕበረሰብ ሳይንስ መሠረት ፤ ብቸኛው ተፈጥሮዋዊ ሉዓላዊ ፍጥረት ሰው ሲሆን ፤ ሰዎች ግን ከተፈጥሮ ወይንም ከጦርነት ኹኔታ ለመውጣት እና ከሕብረት የእሚገኘውን ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ፤ ራሳቸውን ለተፈጥሮ ሕግ በማስገዛት ፤ ሉዓላዊነታቸው በውክልና ለብሔራዊ መንግሥታቸው ይሰጣሉ ። በሕዝብ (ዜጎች) ውክልና የተመሠረተ ሉዓላዊ ብሔራዊ መንግሥትም ፤ በተፈጥሮ ሕግ ብቻ ሲገደብ ሉዓላዊ በሆነበት ክልል ውስጥ ገደብ የሌለው ሕግን የማውጣት ስልጣን አለው ።
ስለ እዚኽ ፤ በመንግሥት ደረጃ ሉዓላዊነት በሰብዓዊነት ብቻ ሲገደብ ፤ ማንኛውምን አስተዳደራዊ ሕግጋት እና ደንቦችን የማውጣት የመጨረሻው ስልጣን ነው ።
ይም በመሆኑ ፤ ሉዓላዊነት ከዜጎች በውክልና የእሚመጣ የሐገራዊ ተቋማት ወይንም የዓለም ዓቀፍ ሐገራት መገለጫ ብቻ ነው ።
ከሐገር በታች የአሉ፟ ማሕበራት እና አደረጃጀቶች ፤ ስልጣን ቢኖራቸውም ፤ ይኽ ሕግ የማውጣት መብታቸው ግን ለሐገሪቱ ብሔራዊ መንግሥት የሕግ አውጪ አካል ለእሚያወጣቸው ሕግጋት ተገዢ የሆኑ ሕግጋትን ብቻ ነው ማውጣት የእሚችለው ።
ለምሳሌ ፦ አንድ የንግድ ማሕበር ፤ የእዚኽ የንግድ ማሕበር አባላት ከአራት መብለጥ አይችሉም እነርሱም እከሌ ፣ እከሌ ናቸው ብሎ ብሎ ሕግ አውጥቶ የማሕበሩን አባላት በአራት በመወሰን መሥራት ይችላል ። ይኽ የንግድ ማሕበር ያወጣው ይኽ ሕግ ግን ተቀባይነት የእሚኖረው ፤ ይኽንን የማሕበሩን ሕግ የእሚቃረን ብሔራዊ የንግድ ሕግ እስከ ሌለ ነው ። ያም ብቻ ሰአይሆን ፤ የሐገሪቱ ብሔራዊ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ፤ ለምሳሌ ፦ ማንኛውም የንግድ ማሕበር አስር እና ከእዛያኽ በላይ አባላት ሊኖሩት ይገባል የእሚል ሕግ በማውጣት ፤ የእዚኽን የንግድ ማሕበር ሕግ እንዲ ሻር እና አዲስ ሕግ እንዲያወጣ ሊያስገድደው ይችላል ።
በአጭሩ ሉዓላዊነት ማለት ፤ የመጨረሻው ሕግ የማውጣት ስልጣን ማለት ነው ። ያም ማለት ፤ በአንድ ሉዓላዊት ሐገር ውስጥ የተለያዩ አካላት ደንብ እና ሕግ የማውጣት መብት ቢኖራቸውም ፤ ሉዓላዊ ሊባሉ ግን አይችሉም ፤ ምክንያቱም ፦ ማንኛውም የእሚያወጡት ደንብ እና ሕግ ፤ በሉዓላዊቱ ሐገር የመጨረሻ ሕግ የማውጣት ስልጣን ላለው ፤ የሐገሪቱ ሕግ ወመሰኛ ምክርቤት መገዛት ስለ አለበት ።
ይኽም ፤ በመሆኑ በፅንሰ ኃሳብ ደረጃ ፤ በአንድ ሉዓላዊ አደረጃጀት ውስጥ ፤ ሌላ ንዑስ ሉዓላዊ አደረጃጀት ሊኖር አይችልም ።
ፌደራሊዝም
ሦሥተኛው ፅንሰ ኃሳብ ፌደራሊዝም ነው ። ፌደራሊዝም በአንዲት አንድነቷ በተጠበቀ ሐገር ውስጥ የማሕበራዊ ልዩነት በመንግሥታዊ መዋቅር አጥር ማጠሪያ መሳሪያ ሰአይሆን ፤ የሐገርን አንድነት እና ውህደትን አስጠብቆ ፤ በሐገር ውህደት ምክንያት የእሚፈጠረው ማሕበራዊ ስፋት የእሚመሰርተው መንግሥት ፤ ከስፋቱ እና ከትልቅነቱ አንፃር ውሽልሽል ሆኖ ውጤታማነቱ እንደ አይቀንስ ፤ ይልቁኑም ስፋቱ እና ትልቅነቱ የጥንካሬ ምንጭ እንዲሆን ማድረጊያ የአደረጃጀት መሳሪያ ነው ።
ይኽም ማለት ፦ የዘመናዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ከእሚዋቀርባቸው የተለያዩ መንገዶች አንዱ የሆነው ያልተማከለ መንግሥት አወቃቀር ወይንም የፌደራሊዝም አስተሳሰብ ፤ በአንድ ትልቅ ማሕበረሰብ ውስጥ የቋንቋ ፣ የባህል ፣ የውልደት ፣ ወዘተ ፤ ማሕበራዊ አጥር ከመፍጠረያ መንገድ ወይንም ከተራ ጎጠኝነት ጋር በፍጹም መምታት የለበትም ማለት ነው ።
ይልቁንም ፤ ፌደራሊዝም ያልተማከለ የፖለቲካ ስልጣን አስተሳሰብ ከእሚተገበርባቸው መንገዶች አንዱ ነው ። ያልተማከለ የመንግሥት ስልጣን አወቃቀር አስተሳሰብ መሠረታዊ መነሻ ደግሞ ፤ አንድ የፖለቲካ ስልጣን ተሰብስቦ አንድ ቡድን ወይንም አንድ ቦታ ላይ በእሚከማችበት ወቅት የአፈፃፀም መዘግየት ከማስከተሉም በአሻገር የስልጣን መባለግን ያስከትላል የእሚል ነው ።
እንደ እሚታወቀው ፤ በዴሞክራሲያዊ የመንግሥት ፍልስፍና ፤ የመንግሥት ስልጣን በአንድ ማዕከል ላይ ተማክሎ እንደ አይከማች እና በእዚኽም ምክንያት ፤ መንግሥት በሰፋ ቁጥር የአፈፃፀም አቅሙ እንደ አይዳከም እና የሙስና አሰራርን እንደ አያስከትል ፤ ኹለት ዓይነት ፤ ስልጣንን የማከፋፈያ መንገዶች አሉ ፤ እነርሱም ፦
ናቸው ።
ስልጣን ኃላፊነትን መሠረት አድርጎ ሲከፋፈል ፦ ሕግ የማውጣት ፣ ሕግ የማስፈፀም እና ሕግ የመተርጎም በእሚል ፤ የመንግሥት ስልጣናት ለሦሥት የተለያዩ የአንድ ብሔራዊ መንግሥት ቅርንጫዎች እንዲ ከፋፈሉ ይደረጋል ።
አንደኛው የእዛው መንግሥት ቅርንጫፍ ሕግን የማውጣት ኃላፊነት ይወስዳል ፣ እንደ እዚኹም ኹለተኛው የእዛው መንግሥት ቅርንጫፍ ሕግ አውጭው በአወጣው ሕግ መሠረት ብይን ይሰጣል ወይንም ሕጉን ይተረጉማል ፣ ሦሥተኛው የእዚኹ መንግሥት ቅርንጫፍ መላውን የመንግሥት አስፈፃሚ በበላይነት ይመራል ።
እነ እዚኽም ፤ የአንዱ ብሔራዊ መንግሥት ቅርንጫፎች ፤ በእዚኽ መልኩ ኃላፊነት ከተከፋፈሉ በኋላ በተለያየ ዘዴ ደግሞ እነ እዚኽ የተለያዩ ቅርንጫፎች እንዲያያዙ ተደርገው እርስ በእርሳቸው እንዲቆጣጠሩ ይደረጋሉ ።
ኹለተኛው እነ እዚኽን የመንግሥት ስልጣኖች በተዋረድ ለእየ አከባቢው ማውረድ ነው ። ይኽም ማለት ፤ በብሔራዊ መንግሥቱ የስልጣን ክፍፍል አምሳያ ፤ ከባቢያዊ መንግሥት አቋቁሞ (ሕገ አውጪ ፣ ሕግ ተርጓሚ እና አስፈጻሚ) ከባቢያቸውን ብቻ የእሚመለከተውን ጉዳይ በቀጥታ በራሳቸው እንዲወስኑ ማስቻል ነው ።
ለምሳሌ ፦ በሐገር ዓቀፍ ደረጃ ፤ ለኹሉም የትራፊክ ደንብ መተላለፎች ፤ አንድ ዓይነት የትራፊክ ቅጣት መጠን ከመወስን ይልቅ ፤ የእየ ከባቢው መንግሥታት ፤ ከአከባቢያቸው ልዩ ኹኔታ ጋር የተናበበ እና በብሔራዊ ሕጉ ባለመታሰሩ ምክንያት እንደ አከባቢያቸው ልዩ ኹኔታ ሊያሻሽሉት ፣ ሊለውጡት የእሚችሉት የትራፊክ ደንብ መተላለፍ ቅጣት መጠን እንዲወስኑ ማስቻል ፤ ከባቢያዊ መንግሥታት ፤ ለሕዝባቸው ቅርብ እንዲሆኑ ፤ ሕዝቡም ብሔራዊ መንግሥት ጋር መምጣት ሰአያስፈልገው የአከባቢውን መንግሥታት ማዘዝ እንዲችል የእሚያደርግ በመሆኑ ፤ የመንግሥትን ተደራሽነት እና ተጠያቂነት በከፍተኛ ደረጃ ይጨምረዋል ።
ይኽንን ኹለተኛውን እና የመንግሥትን ስልጣን በእየ ከባቢው ማከፋፈልን ነው ፤ ፌደራሊዝም የእምንለው ።
ስለ እዚኽ ፦ በእዚኽ አግባብ ፤ ከባቢያዊ ይዘት የአላቸው ጉዳዮችን በእየ አከባቢው ባሉ የስልጣን አካላት እንዲሰሩ ስልጣን በተዋረድ ይሰጣቸዋል ። ከእዚኽም የተነሳ ፤ ከባቢዎች በሐገራዊ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው ፤ የራሳቸው ሕግ አውጪ ፣ ሕግ ተርጓሚ እና አስፈፃሚ እንዲኖራቸው ይሆናል ።
በእዚኽ መልኩ ስልጣን በከባቢ ወደ ታች እንዲወርድ እና እንዳይማከል የእሚደረገው ግን ፤ የከባቢ መንግሥታት ከብሔራዊ መንግሥት በላይ ታማኝ በመሆናቸው አይደለም ። ይልቁንም ፤ ስልጣንን በማከፋፈል እና የስልጣን መዓከላትን በተለያየ ዘዴ በማስተሳሰር ፤ እርስ በእርሳቸው እንዲጠባበቁ እና ሚዛን እንዲኖራቸው በማድረግ ፤ አፈጻጸምን ለማሻሻል እና የስልጣን መባለግን ለመቀነስ ነው እንጂ ።
ለምሳሌ ፦ በአሜሪካን ሐገር እ.አ.አ. በ1957 ዓ.ም. ትምህርት ቤቶች በቆዳ ቀለም መለ፟የት የለባቸውም ፤ ስለ እዚኽ የጥቁር እና የነጭ የእሚባል የትምህርት ቤት ክፍፍል ይቁም እና ኹሉም ዓይነት የቆዳ ቀለም የአላቸው ተማሪዎች በእሚፈልጉበት ትምህርት ቤት ገብተው ይማሩ የእሚለውን ሐገራዊ ብይን ፤ የአርከንሶ ክልል መንግሥት ፤ የክልሉ ሕዝብ ተቃውሟል እና ነጮች እና ጥቁሮች በአንድ ትምህርት ቤት ይማሩ የእሚለውን ድንጋጌ አላስፈፅምም ብሎ ፤ የጥቁር ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቱ እንደ አይገቡ ለመከልከል የክልሉን ፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች እስከ ማሰማራት ደርሶ ነበር ።
ትንሽም የዴሞክራሲ ፅንሰ ኃሳብ የአለው ሰው ፤ መንግሥታት ስልጣን የእሚይዙት የዜጎቻቸውን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት ለማስከበር መሆኑን ስለ እሚገነዘብ ፤ የአንድ ክልል መንግሥት የአብዛኛው ሕዝብ ድጋፍ ቢኖረውም እንኳን ፤ ይኽን መሰል የመብት ጥሰት በሌሎች ዜጎቹ ላይ እንዲያደርስ ፈቃድ የለውም ።
ይኽንንም የክልል መንግሥት ኢሰብዓዊ እምቢተኝነት ለማረም የፌደራሉ መንግሥት የፌደራሉን ጦር ልኮ ፤ ጥቁር ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ማስገደድ ነበረበት ።
ይኽም ታሪካዊ አጋጣሚ ፤ ከባቢያው ወይንም የክልል መንግሥት ልክ እንደ ፌደራሉ ወይንም መዓከላዊው መንግሥት ፤ ሕገ ወጥ ፣ አፋኝ እና ጨቋኝ ሊሆን የእሚችል መሆኑን ያሳያል ።
ይኽን መሰሉም ግድፈት ሊፈታ ከእሚችልባቸው መንገዶች አንዱ ፤ በፌደራሊዝም መርህ መሠረት ፤ ልክ ስልጣን በተዋረድ ለከባቢው ባለስልጣናት እንደ ወረደው ፤ የፌደራሉ ወይንም ብሔራዊው መንግሥት ፤ የክልል ወይንም ከባቢያዊ ባለስልጣናት የስልጣን መባለግ ሲፈፅሙ ጣላቃ መግባት የእሚያስችል አሰራር ወይንም የቁጥጥር እና ሚዛን መርህ በመከተል ነው ።
የከባቢ መንግሥታት የመዓከሉን መንግሥት መገደብ እንዳለባቸው ኹሉ ፤ የመዓከሉ መንግሥት የከባቢ መንግሥታትን መገደብ አለበት ። ይኽ ፤ ቁጥጥር እና ሚዛን (check and balance) የእሚባለው የሕዝባዊ ስልጣን ማዋቀሪያ መንገድ እሳቤ የእሚገለፅበት አንዱ መንገድ ነው ።
ስለ እዚኽ ፦ በፌደራሊዝምም ሆነ በሌላ አግባብ ፤ ስልጣን ሲከፋፈል ግቡ አንደኛው የመንግሥት ቅርንጫፍ ከሌላው ይበልጥ ተዓማኒ ነው ለማለት ወይንም የሆነ የፖለቲካ ደሴት ለመፍጠር ወይንም የጎጠኝነትን ዝንባሌ ታሳቢ የአደረገ ሰአይሆን ፤ በአንድነት እሳቤ የሕዝባዊ መንግሥት ግብ የሆኑትን ውጤታማ እና ፍትሐዊ መንግሥትን ማረጋገጥን ታሳቢ የአደረገ ነው ።
በእዚኽ ኺደት ውስጥ ፤ ከባቢዎች የራሳቸው ባህል እና ልዩነት ሊያዳብሩ ይችላሉ ፤ ይኽ ግን የፌደራሊዝም ግብ ሰአይሆን ፤ የፌደራሊዝም ተረፈምርት ነው ።
በአንድ ከተማ እንኳን ፤ ፋብሪካ የእሚበዛበት አከባቢ እና የንግድ ሱቆች የእሚበዙበት አከባቢ ነዋሪዎች ተመሳሳይ የኑሮ ዘዬ የላቸውም ። ስለ እዚኽ በአንድ ትልቅ ሐገር ውስጥ የእሚኖሩ ሕዝብ ፤ እንደ እሚኖሩበት ክልል ፤ አየር ጠባይ ፣ የመሬት አቀማመጥ ፣ የኢከነሚ እንቅስቃሴ ፣ ወዘተ ፤ የተለየ አለባበስ ፣ አበላል ወይንም አጨፋፈር ቢኖራቸው ወይንም የሆነ ዓይነት የገፅታ ልዩነት ቢያዳብሩ ፤ ይኽ የፌደራሊዝም መሠረት ሰአይሆን ፤ ፌደራሊዝም ወይንም ተፈጥሮ የአስከተለው የጎንዮሽ ልዩነት እንጂ ፤ ራሱን የቻለ የፌደራል ስረዓት የፖለቲካ ግብ እና መሠረት አይደለም ።
በትልቅ ከተማ ውስጥ ፤ መሰል ልዩነቶች በሰፈር ደረጃ የእሚንፀባረቁ በመሆኑ ፤ ሜዳው ሲሰፋ ልዩነቱ መስፋቱ ልዩነቱን ፖለቲካዊ በኃሪ ሰጥቶ ለመከፋፈያነት መጠቀሙ ከፌደራሊዝም ፅንሰ ኃሳብ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ነው ።
ስለ እዚኽ ፦ ፌደራሊዝም መሰል ከባቢያዊ ልዩነቶችን ሉዓላዊነት ማረጋገጫ መንገድ አይደለም ። ይልቁንም ፌደራሊዝም ፤ ከሚዛን እና ቁጥጥር እሳቤ አንፃር ስልጣንን በከባቢ መስፈረት በተዋረድ ማከፋፈል ታሳቢነት ፤ የመንግሥትን ስልጣን በሕዝባዊ መንግሥት አሰራር አግባብ ወደ እየ አከባቢው የማውረድ አግባብ ነው እንጂ።
ከፅንሰ ኃሳብ ትንተናው በአሻገርም ፤ ፌደራሊዝም የእሚለውን የቃሉ ታሪካዊ አመጣጥ እና በዓለም ላይ የመጀመሪያውን ሕዝባዊ ፌደራላዊ መንግሥት ያቁቋሙትን የአሜሪካኖችን የፖለቲካ ታሪክ ስናይ ፤ ፌደራሊዝም በመሠረታዊነት የትብብር መዋቅር ወይንም ከአንድነት የእሚገኘውን ጥቅም ታሳቢ የአደረገ መሆኑን ነው የእምናየው ።
የእንግሊዘኛው ቃል ፌደራሊዝም ምንጩ ፤ ፎዊደስ (Foedus) የእሚባል ፤ ስምምነት ወይንም ቃል ኪዳን የእሚል ትርጉም የአለው የላቲን ቃል ነው ። ስለ እዚኽ ፦ ሰዎች ወይንም የሆኑ ማሕበራት ፤ ፌደሬት አደረጉ ስእንል ለትብብር ተስማሙ ወይንም ቃል ኪዳን ገቡ እያልን ነው ።
ይኽ ቃል በግዜ ኺደት ፤ ፊደራሊዝም ለእሚባለው የመንግሥት አወቃቀር መታወቂያ እንዲሆን የአደረጉት አሜሪካኖችም ፤ የእዚኽ መንግሥታቸው መዋቅር ዓላማ የተዋጣለት አንድነት መመሥረትን ታሳቢ የአደረገ ነው ።
የአሜሪካ ፌደራሊዝም መሥራች ከሆኑት አንዱ የሆነው ጆን አዳምስ (John Adams) ፤ ሕገ-መንግሥቱን ለማፅደቅ በእሚወያዩበት ወቅት እንዲኽ እንዳለ ተጠቅሷል ፦
“የሕዝቡ አዕምሮ ከታቀደው የመንግሥት ኃሳብ በላይ በከበረ ኃሳብ ሊያዝ አይችልም ። እንደ እሚመስለው በአስደናቂ ኹኔታ የአሜርካን ሕዝብን በስሜት እና በጥቅም/ፍላጎት እንደ አንድ ሕዝብ ለማያያዝ የተሰላ ይመስላል ።”
“the public mind cannot be occupied about a nobler object than the proposed plan of government. It appears to be admirably calculated to cement all America in affection and interest, as one great nation. [70]“
አሌክሳንደር ሐሚልተንም ቁጥር ዘጠኝ በእሚባለው የፌደራሊስት ጽሁፉ ላይ ፤ ስለ አንድነት ጥቅም እንዲኽ ብሏል ፦
“ፅኑ አንድነት(ውህደት) ለክልሎቹ ሰላም እና ነጻነት ትልቅ አቅም ይሆናል …”
“A firm union will be of the utmost moment to the peace and liberty of the states, … [70]“
ከእዚኽ ኹሉ በላይ ደግሞ ፤ የአሜሪካ ሕገ-መንግሥት መግቢያው ላይ ፤ ይኽንን ሕገ-መንግሥት ያቋቋምንበት አንድ ምክንያት የተሻለ ፍፁም አንድነት ለመመሠረት ነው ይላል ቃል በቃል ፦
“… የበለጠ ፍፁም አንድነት(ውህደት) መመሥረት ያስችለን ዘንድ ፤ “
“… in Order to form a more perfect Union.”
ስለ እዚኽ ፌደራሊዝም እንደ መንግሥት አወቃቀር ዘውግ ፤ በጠንካራ አንድነት ውስጥ የፖለቲካ ስልጣን መማከል የእሚፈጥረውን ፀረ ሕዝባዊነት ለማስቀረት የመጣ አወቃቀር እንጂ ጎጠኝነትን ወይንም ከሕዝባዊ መርህ ውጭ የአሉ፟ የፖለቲካ ደሴቶችን በአንድ የፖለቲካ ማሕበረሰብ ውስጥ ለመመሥረት ወይንም ለማክበር የመጣ አሰራር አይደለም ።
ከእዚኽም በተጨማሪ ፤ በፌደራል መርህ የአልተዋቀሩ ፤ ውጤታማ ሕዝባዊ መንግሥታት እንደ አሉ፟ ማወቅም ተገቢ ነው ።
በአኹኑ ወቅት ፤ በዓለም ላይ የአሉ፟ መንግሥታት 75% አሀዳዊ መንግሥታት ሲሆኑ ፤ ፌደራሊስት የሆኑት 25% ብቻ ናቸው ።
ለምሳሌ ፦ ጣሊያን ፣ እሥራኤል ፣ ደቡብ ኮሪያ አሀዳዊ መንግሥት ነው የአላቸው ፣ ጎረቤታችን ኬንያ አሀዳዊ መንግሥት ነው ያላት ፣ በአፍሪካ ጥሩ የዴሞክራሲያዊነት ሪከርድ የአላቸው ናይጄሪያ (በናይጄሪያ ከ200 በላይ ነገዶች ወይንም ብሔሮች የአሉ ሲሆን ናይጄሪያም የአፍሪካ ሩብ ሕዝብ መኖሪያ ወደ መሆን የተጠጋች ነች) ፣ ደቡብ አፍሪካ (ደቡብ አፍሪካ ብዙ ማሕበራዊ ልዩነት ስለ አላት ቀስተደመናዋ ሐገር ወይንም ሬንቦው ኔሽን ተብላለች) ፤ አሀዳዊ መንግሥት ነው የአላቸው ።
እስላሚክ ሪፐብሊክ ፤ ስለ እዚኽም ፦ በሸርያ ሕግ የእምትመራ እና ዴሞክራሲያዊ የአልሆነችው ሰሜን ሱዳን ደግሞ የፌደራል መንግሥት አወቃቀር ነው ያላት ።
ምን ለማለት ነው ፦ ፌደራሊዝም የፖለቲካ እክሎች ኹሉ መፍቻ ተድርጎ መወሰድ የለበትም ፤ ፌደራላዊ አወቃቀር ኖሮዋቸው ጨቋኝ የሆኑ መንግሥታት የአላቸው አሉ ፤ በተቃራኒውም እንደ ጣሊያን እና ደቡብ ኮርያ መሰል ዴሞክራሲያዊ እና አሀዳዊ የመንግሥት አወቃቀር የአላቸው ሐገራት አሉ ።
ለማጠቃለል ፦ በአንድ ሐገር ውስጥ ፤ ብሔራዊ ዜግነትን ማበረታት እና ሐገራዊ አንድነትን ማጠናከር ከመሠረታዊ የሐገርነት ፅንሰ ኃሳብ እና ከሳይንሳዊ ሕገ-መንግሥት ግብነት ሊቀየር የእማይችል ፅንሰ-ኃሳብ ነው ።
ሉዓላዊነት ወይንም በአንድ ሕዝብ ላይ ከሰብዓዊነት ጋር የእማይጻረር የመጨረሻውን ሕግ አውጭ አካል የመመሥረት መብት የዓለም ዓቀፍ ሐገራት ብቻ መገለጫ በመሆኑ ፤ ከዓለም ዓቀፋዊ ሐገርነት በታች ያሉ የትኞቹም አደረጃጀቶች ሉዓላዊያን ሊባሉ አይችሉም ።
ፌደራሊዝምም የመንግሥትን ብቃት ማሳደጊያ መሳሪያ እንጂ በአንዲት ሉዓላዊት እና ብሔራዊ ሐገር ውስጥ የማሕበራዊ አጥር መመሥረቻ መሳሪያ አይደለም ። ይኽም ብቻ ሰአይሆን ፤ ፌደራሊዝም በሌሎቹ የሕዝባዊ መንግሥት እሴቶች አግባብ ከአልተተገበረ ፤ የጭቆና ማስቀጠያ ሊሆን የእሚችል በመሆኑ ፤ በራሱ እንደ ሕዝባዊ መንግሥት መገለጫ መታየት የለበትም ።
ለመግቢያ እነ እዚኽን ሦሥት ኃሳቦች ከአብራራን ፤ በመቀጠል ከኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት ችግሮች ዋነኞቹ የእምላቸውን ሦሥቱን ተራ በተራ እናያለን ።
ሕገ-መንግሥት በአንዲት ሐገር ውስጥ ፤ የሕጎች ኹሉ እናት በመሆኑ ፤ በዘመናት መካከል በሰው ልጅ ምርምር እና እውቀት የዳበሩ ኃሳቦችን በአግባቡ በተረዳና በእማያሻማ መንገድ ዜጎች በቀላሉ ሊረዱት በእሚችሉበት አግባብ ማስቀመጥ አለበት ።
ሕገ-መንግሥት ላይ የእሚቀመጡ አንቀጾች በእዚኽ መልኩ በእማይቀመጡበት እና ለፈረጀ ብዙ እና አንዳንዴም ፍጹም ተቃራኒ ትርጓሜዎች ክፍት በእሚሆኑበት ወቅት ሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ (Constitutional Crisis) ያስከትላሉ ።
የኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥትም ከሐገር ግንዛቤው አንስቶ በሉዓላዊነት እና በፌደራሊዝም ፅንሰ ኃሳቦች ላይ በአለ፟ው ብዥታ ምክንያት ሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ የእሚያስከትሉ አንቀጾችን ያስቀምጣል ።
አንድን ሐገር የወሰድን እንደ ሆን የብዙ ነገር ውሕድ መሆኗን እንረዳለን ወይንም ሐገርን የፈጠሯት ምን ምን የግንባታ አህዶች ተዋኽደው ነው? ተብለን ብንጠየቅ ፤ ብዙ የተለያዩ ዓይነት አደረጃጀቶችን ፤ በአህድነት መጥቀስ እንችላለን ።
ለምሳሌ ፦ በአህድነት ወይንም በግንባታ መዋቅርነት ተሰባስበው ሐገርን የእሚመሰሩት ነግሮችን እንደ እዚኽ እያልን መዘርዘር እንችላለን ፦ ሐገር የምድር ወይንም የመኖሪያ እና የነዋሪዎቿ ስብስብ ነች ፣ ሐገር የቤተሰብ ስብስብ ነች ፣ ሐገር የመንደሮች ስብስብ ነች ፣ ሐገር የጎጦች ስብስብ ነች ፣ ሐገር የነገዶች ስብስብ ነች ፣ ሐገር የተባዕት እና የእንስት ፆታ የአላቸው ሰዎች ስብስብ ነች ፣ ሐገር የድሆች ፥ መካከለኛ ገቢ የአላቸው እና ኃብታሞች ስብስብ ነች ፣ ወዘተ ፤ እያልን ሐገርን ሐገር ያደረጓትን ማሕበራዊ ንዑስ ቡድኖች ወይንም አህዶች ከተለያዩ የአደረጃጀት ፣ የኢከነሚ ፣ የባሕል ደርዝ አንጻር መዘርዘር እንችላለን ።
ይኽ ግን በተርታው ሰው አገላለፅ እንጂ ፤ በመጽሐፉ ምዕራፍ አንድ ላይ ፤ ዴሞክራሲያዊነት እና ሐገር በእሚለው ንዑስ ክፍል ላይ እንደ አልነው ፤ በፖለቲካ ሳይንሱ የማሕበረሰብ ስለ እዚኽም የሐገር ብቸኛው አህድ የሆነው ፖለቲካዊው ሰው መሆኑን አስቀምጠናል ።
ለእዚኽም ማሳያ አርስታትል እንዲኽ እንደ አለ አስቀምጠናል ፦
“የብዙ ነገሮች ውህድ እንደ ሆነ እንደ ማንኛውም ነገር ፤ ሐገር (መንግሥት ፥ ብሔራዊው) አንድ ውህድ ነው ፤ ተዋህደው የመሠረቱትም ዜጎቹ ናቸው።”
“But a state is a composite, like any other whole made of many parts; these are citizens who compose it. [1]”
ያም ብቻ ሰአይሆን ፤ ሐገር በግለሰብ አህድነት ሳትገለፅ እና ሳትዋቀር ስትቀር ፤ ወይንም የመዋቀሪያ አህዶች ከዜጎች ይልቅ ማንኛውም ሌላ አደረጃጀት ሲሆን ፤ ውጤቱ የማሕበረሰብ ብሎም የሐገር አህድ የሆኑትን ግለሰቦች ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በማፈን ፤ አስከፊውን የጦርነት ወይንም የተፈጥሮ ኹኔታ በተለያየ መልኩ እንደ እሚያስከትል አይተናል ።
ሆኖም በልማዳዊ አገላለፅ ሐገር የቤተሰብ ስብስብ ነች ፣ ሐገር የመንደሮች ስብስብ ነች ፣ ወዘተ ብለን ብናስቀምጥ ፤ ትርጉሙ ኹሉንም የሐገር ነዋሪዎች በእኩልነት የእሚገልፅ ከሆነ ፤ ብዙም ችግር የአለው አይደለም ።
እነ እዚኽ ለመደበኛ ውይይት ችግር የሌላቸው የሐገር አገላለጾች ግን ፤ አንዳንዶቹ ከላይ በአልነው መልኩ ከዲሞክራሲ ርዕይ ጋር ከመጋጨት በአሻገር ፤ አንዳንዶቹ አካታችም አይደሉም ።
ለምሳሌ ፦ በመደበኛ ግንዛቤ ወይንም አቅል (Common Sense) ሐገር የእያንዳንዱ ዜጋ ስብስብ ነች ወይንም ሕዝቦቿ ናት ብለን ብንል ፤ ገለፃችን አካታች ነው ፤ ምክንያቱም ፦ ማሕበራዊ የሐገር አህድ አንሶ አንሶ ከዜጋ መውረድ ስለ እማይችል እና ተሰብስቦ ተሰብስቦ ከሕዝብ ስለ እማያልፍ ።
በተነጻጻሪ ደግሞ ፦ ሐገር የቤተሰብ ስብስብ ናት ብእንል ፤ ቤተሰብ የሌለውን ሰው ምን ልናደርገው ነው? ቤተሰብ የለህም እና የሐገር አካል አይደለህም ልእንለው ነው? ሐገር የነገዶች ስብስብ ነች ብእንል ፥ ከብዙ ነገድ የወጣውን ሰው ምን ልናደርገው ነው? ሙሉ በሙሉ ከአንድ ነገድ ካልወጣህ ወይንም በስሌት የበለጠ ትስስር ወደ አለህ ነገድ ተቀላቀል ልንለው ነው? እንዲህ ብለን ቤተሰብ ፣ መንደር እና ከተማ ስንሰነጣጥቅ ልንገኝ ነው?
ምክንያቱም፦ አንድን ዜጋ የነገድ ተዋጾህ ወደ እሚበዛበት ተቀላቀል ስንለው ፤ ይኽ ዜጋ በከባቢው ከአሉት እንደ ቤተሰብ ፣ ዘመድ አዝማድ ፣ የሞያ ማሕበራት ፣ ቤት እምነት ፣ መንደር ፣ አናሳ ተዋጾ ከአለው ነገድ ፣ ወዘተ ፤ አወቃቀር ይልቅ ፤ የጎላ የነገድ ተዋጾህ ወደ አለህ የነገድ ቡድን ኺድ እያልነው ስለ ሆነ ፤ ሰውየውን እና ጠቅላላ ማሕበራዊ ስሪቱን በከፍተኛ ደረጃ እያናጋነው ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም።
ከእዚያኽ በአሻገር ቤተሰብ የሌለው ወይንም የራሱ ነገድ የሌለው ሰው ባይኖርም እንኳን ፤ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ሆኖ ፤ ሰው ያለ አንድ ህዋስ ቤተሰብ እና አንድ ነገድ የእማይፈጠር እና የእማይኖር ቢሆን እንኳን ፤ ሐገር የቤተሰብ ስብስብ የሆነችውን ያኽል የነገድ ስብስብም ፣ የወረዳ ስብስብም ፣ የቀበሌ ስብስብም መሆን ስለ እምትችል ፤ ከእነ እዚኽ ኹሉ ቡድኖች በላይ ነገድ በአህድነት ተመርጦ ሐገር የነገድ ስብስብ ነች የእሚያስብል ምንም ልዩ ምክንያት አይኖርም ።
የኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት ፤ እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ብሎ እንደ እሚጀምረው ፤ እኛ የኢትዮጵያ መንደራት ነዋሪዎች ፣ እኛ የኢትዮጵያ ወረዳዎች ነዋሪዎች ፣ ወዘተ ፤ ማለት ይቻላል ወይንም ይኽ አገላለፅ እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ከእሚለው በላይ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አካታች አጠራር ነው ፤ ምክንያቱም ፦ በመንደር ወይንም በወረዳ ውስጥ የእማይኖር ዜጋ ስለ እማይኖር።
ይኽን መሰል ማንም በመደበኛ ግንዛቤ የእሚረዳውን ኃቅ ለማብራራት የአስፈለገበት ምክንያት ፤ የኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ሲል የኢትዮጵያን ሕዝብ በአጠቃላይ በወል የእሚወክልለት አሰያየም አጥቶ ሰአይሆን ራሳቸው ተፈጥሮዋዊ የእማይከፋፈሉ አህድ (Indivisible units) ሆነው ፤ እርስ በእርስ በመተሳሰር ኢትዮጵያን የፈጠሩት እርሱ ‘ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች’ ብሎ የእሚጠራቸው ነገዶች ናቸው ከእሚል የመሐይም እምነት መሆኑን ለማስረዳት ነው ።
ነገዶች ተፈጥሮዋዊ የሆኑ የእማይከፈሉ እና በራሳቸው ተነጥለው የእሚገኙ አህዶች ናቸው (Self Contained indivisible units) የእሚለው አባባል ፤ ማንም ጉዳዪን ወስዶ ላሰበው ሰው የእማያጠራጠር አሉታዊ (Bold No) መልስ የአለው ነው ። የትኛውም የሰው ማሕበር ይኽን ልዩ በኃሪ ሊይዝ አይችልም ።
እንዲያውም ዝልግልግ እና ተቀያያሪ ከሆኑት ነገዶች ይልቅ ፤ ቤተሰቦች ፤ መንደሮች ፣ ቀበሌዎች ፣ ወዘተ ፤ በአደረጃጀት ደረጃ የተሻለ የእማይከፈሉ በራሳቸው ምልዑ የሆኑ አህድነት ባሕሪ የአላቸው ናቸው ።
የመንደሮችም ፣ የወረዳዎችም ፣ የከተሞችም ፣ የክፍለ ከተሞችም ነዋሪዎች ኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ሆኑ የእሚያውቀው ኢሕአዴግ ፤ በነበረበት ብዥታ ድንገት ተነስቶ ፤ ‘ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች’ የእሚል በዓይነቱ ልዩ የሆነ የጋራ ስብስብ ስም (Collective Noun) ፤ በመደበኛ ቋንቋ ነገድ የእሚለውን ቃል በእዚኽ ግርጅፍ የጋራ ስብስብ ስም በመተካት ፤ የኢትዮጵያ አህዶች እነርሱ ናቸው በእሚል ፤ ሕገ-መንግሥቱን እነ እዚኽ የኢትዮጵያ አህዶች ተሰብስበው በተወካዮቻቸው አማካኝነት ያፀደቁት ሰነድ ነው አለ ።
ከእዚኽ የኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት የመግቢያ ዓረፍተ ነገር ታሪካዊ ቅጥፈት (Historical Blunder) በአሻገር ፤ ፍፁም ሊባል በእሚችል የሉዓላዊነት ፅንሰ ኃሳብ መኃይምነት ፤ ሉዓላዊት በሆነች ሐገር ውስጥ ሉዓላዊ የሆኑ የስልጣን ባለቤት የሆኑት እነርሱ ናቸው በማለቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ሐገርነት ከመናቁ በአሻገር በኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝባዊ መንግሥት ለማቋቋም እንደ አይቻል አድርጓል ።
በሕገ-መንግሥቱ በአንቀፅ 8 ላይ ፦
“የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች ፣ ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው፡፡”
ይላል ። ይኽን አንቀፅ ላላስተዋለው ሰው ፤ የኢትዮጵያ ዜጋ ከየትኛውም ነገድ ወይንም ጎጥ ይኹን ፤ በዴሞክራሲያው አግባብ በአለው ውክልና ፤ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር ፤ በጋራ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ነው የእሚል ሊመስል ይችላል ።
በሕገ-መንግሥቱ አውድ ለተረዳው ሰው ግን ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የአሉ፟ ነገዶች እና ጎጦች ወይንም በሕገ-መንግሥቱ የዘፈቀደ አሰያየም ፤ ‘ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች’ በተናጠል የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ናቸው የእሚል ነው ።
ይኽን ለማስረዳት እና የእዚኽን አንቀጽ እንደምታውን ለመረዳት የተወሰኑ ነጥቦችን እናንሳ ።
በእዚኹ ከእላይ በጠቀስነው የሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 8/3 ሦሥት ላይ ፤ የ‘ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች’ ሉዓላዊነት የእሚገለፀው ፤ በተወካዮቻቸው አማካኝነት በእሚመርጡት ምርጫ ነው ይላል ፦
“ ሉዓላዊነታቸውም የሚገለጸው በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት ይሆናል ። “
ይኽም ማለት ፤ በክልልም ሆነ በሐገር ዓቀፍ ደረጃ ተወካይ የመምረጥ እና የመሰየም መብት የአላቸው የነገድ መዋቅሮች ብቻ ናቸው ማለት ነው ። ይኽም በክልሎች አወቃቀር እና በፖርላማ መቀመጫ ክፍፍልም በግልፅ ተቀምጧል ።
እንደገናም ፦ እነ እዚኽ ‘ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች’ ፤ በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ፤ በማንኛውም ግዜ የራሳቸው ክልል ማቋቋም የእሚችሉ እና እስከ መገንጠል የእሚደርስ መብት በተናጠል የአላቸው ናቸው ።
እያንዳንዱ ነገድ በተናጠል የራሱ ክልል መመሥረት እንደ እሚችል ፤ ሕገ-መንግሥቱ በአንቀፅ 47/2 ላይ እንዲኽ ይላል ፦
“ … ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች ፣ ሕዝቦች በማንኛውም ጊዜ የየራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት አላቸው ። “
እነ እዚኽ ‘ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች’ ፤ ይኽንን ያቋቋሙትን ክልል ይዘው በማንኛውም ግዜ ያለ ምንም ገደብ መገንጠል እንደ እሚችሉ በአንቀፅ 39/1 ላይ በግልፅ ተደንግጓል ፦
“ ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ፣ ብሔረሰብ ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል የአለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው ።”
ስለ እዚኽ ፤ ሕገ-መንግሥቱ በአንቀፅ ስምንት ላይ ፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው የእሚልበት አውድ ፤ ከብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝብ የተወጣጡት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ናቸው እያለ ሰአይሆን ፤ እያንዳንዳቸው ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በተናጠል የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ናቸው እያለ ነው ።
ይኽም ማለት እነ እዚኽ ነገዳዊ ክልላት የአላቸው ነገዶች ፤ በነገዳቸው ስም በያዙት ክልል ውስጥ ፤ የነገዳቸው አባል የአልሆነን ኢትዮጵያዊ ከመምረጥ እና መመረጥ መብት እስከ ማገድ የእሚደርስ ክልከላ ቢያድርጉበት ማንም የእሚያግዳቸው የለም ማለት ነው ፤ ሉዓላዊያን ናቸውና ።
ይኽን መሰል አወቃቀር ደግሞ ፤ የሉዓላዊት እና ሕዝባዊት ሐገር አወቃቀር ሰአይሆን የቀጣና አወቃቀር ነው ።
መንግሥታት ወይንም ሉዓላዊ ነን የእሚሉ ተደራዳሪዎች ፤ አንድ የጋራ ማሕበር ከአቋቋሙ በኋላ ሉዓላዊነታቸውን በእዚኽ መልክ ይዘው ሊቀጥሉ የእሚችሉት ፤ ነፃ የንግድ ቀጠና ሲያቋቁሙ ፣ የጋራ ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ ሲስማሙ ፣ ነፃ የኢከነሚ ዞን ሲያቋቁሙ ፣ ወዘተ ፤ እንጂ ፤ ሉዓላዊ መንግሥት ከአቋቋሙ በኋላ እነርሱ ሉዓላዊ ሆነው የእሚቀጥሉበት ምንም ዓይነት አግባብ የለም ።
ለምሳሌ ፦ ሦሥቱ የሰሜን አሜሪካ ሐገራት ፤ ካናዳ ፣ አሜሪካ እና ሜክሲኮ ፤ በተናጠል ሉዓላዊያን የሆኑ ሐገራት ሲሆኑ ፤ በተወሰኑ ምርቶቻቸው ላይ በድንበር የእሚደረገው ንግድ ከቀረጥ ነፃ በሆነ አግባብ እንዲሆን ፤ NAFTA (Northern America Free Trade Agreement) የእሚባል ስምምነት አድርገው ይነግዳሉ ። ይኽ የንግድ ስምምነት ፤ ሦሥቱን ሐገራት አንድ ሐገር አያስብላቸውም ፤ ምክንያቱም ፦ ሐገር ማለት ቀረጥ አልባ የንግድ ቀጠና ማለት ስለ አልሆነ ።
እንደ እዚኹም አሜሪካ እና አብዛኛዎቹ የአውሮፓ ሐገራት NATO (North Atlantic Treaty Organisation) የእሚባል ፤ በአንዱ አባል ሐገር ላይ የተደረገ ጥቃት በኹሉም ላይ እንደ ተደረገ ይቆጠራል በእሚል ኃሳብ ፤ የጋራ የመከላከያ ድርጅት ፈጥረዋል ፤ ይኽ ግን ሐገር አያስብላቸውም ፤ ምክንያቱም ፦ ሐገር ማለት የጋራ መከላከያ ስምምነት ስለ አልሆነ ።
የአውሮፓ ሕብረት ፥ የጋራ መገበያያ ገንዘብ ፣ ፓርላማ እና ፕሬዘዳንትም የአለው ህብረት ቢሆንም ፤ ሐገር አይደለም ፤ ምክንያቱም ሐገርነት ፤ በዴሞክራሲ ትንታኔ የጋራ መገበያያ ገንዘብ በመያዝ ፣ ፓርላማ እና ፕሬዘዳንት የአለው አደረጃጀት የመያዝ ጉዳይ ሰአይሆን ፤ ሐገራትን የእሚያስብላቸው ዋነኛው መለያ ፤ ዜጎቻቸው ያለ ምንም መካከለኛ ፤ በከባቢያዊም ሆነ በብሔራዊ (ሐገር ዓቀፍ) ደረጃ በቀጥታ ለሕዝባዊ መንግሥት ኃላፊነት የመምረጥ እና የመመረጥ መብት ሲኖራቸው ነው ።
ዜጎች በሐገራቸው በእሚኖሩበት በማንኛውም አከባቢ ፤ ለከባቢያቸውም መንግሥት ተወካይነት የሆነው ነገድ ተወላጅ በአለመሆናቸው ምክንያት ከእዚኽ መብት መታገድ የእሚችሉ ከሆኑ ፤ በሉዓላዊት ሐገር ውስጥ እየኖሩ አይደለም ።
ስለ እዚኽ ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ፤ ነገዶች ወይንም የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የተባሉት ፤ የኢሕአዴግ ሕገመንግሥት እንደ እሚለው ፤ የተናጠል ሉዓላዊነታቸውን እንደ ጠበቁ ፤ እነ እዚኽ ሉዓላዊያን የተባሉ ነገዶች ፤ ነፃ የንግድ ልውውጥ ስምምነት ፣ የጋራ መከላከያ ፣ የጋራ ፓርላማ ፣ ወዘተ ፤ ቢኖራቸውም እንኳን ፤ ኢትዮጵያ አንዱ ዓይነት ቀጣና እንጂ ሉዓላዊት ሐገር አይደለችም ማለት ነው ።
በእዚኽ መልኩ ፤ ከዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብት አንጻር የሐገርን ሉዓላዊነት በእሚጻረር መልኩ ፤ ነግዶችን የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ናቸው ብሎ የተወናበደው የኢሕአዴግ ሕገመንግሥት ፤ ምዕራፍ 10 የብሔራዊ ፓሊሲ መርሆዎችና ዓላማዎች በእሚለው ፤ የብሔራዊውን መንግሥት (National Government) ፖሊሲ ዓላማዎች በእሚደነግግበት ግዜ ፤ የመንግሥትን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች በተመለከተ አንቀጽ 86 ላይ እንዲኽ ይላል፦
“የኢትዮጲያን ሕዝብ ጥቅም እና የሐገሪቱን ሉዓላዊነት የእሚያስከበር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማራመድ።”
ይኽም ማለት ፤ በፍጹም መኃይምነት ፤ ኢትዮጲያ ዓለም ዓቀፋዊ ሉዓላዊት ሐገር መሆኗን ተቅብሎ ሲያበቃ ነው ፤ በኢትዮጲያ ውስጥ የአሉ፟ ነገዶች ወይንም በእርሱ አጠራር ፤ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የእሚላቸውን በተናጠል የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ናቸው የእሚለው።
ይኽ ዓይነት የሉዓላዊነት ፅንሰ ኃሳብ መዛባት የአለበት ሕገመንግሥት ደግሞ ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሉዓላዊነት ከማቃለሉ በላይ ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝባዊ ወይንም ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ለመመሥረት የእምናደርገውን ጉዞ በቀጥታ የእሚያደናቅፍ ነው ።
ይኽም በመሆኑ ፤ ዓለም በሉዓላዊነቷ የእማያውቃትን ሐገር ሉዓላዊነት ፤ በውስጧ ከአሉ፟ ነገዶች ሉዓላዊነት የእሚያምታታ እና የሐገሪቱን ዓለም ዓቀፋዊ ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ የእሚያስገባ ሕገ-መንግሥት እና የኢትዮጵያን ሕዝብ በአንድንነት እና በእኩልነት እንደ መላ ሐገሩ እኩል የጋራ ባለቤትነት የእማይቀበል ሕገመንግሥት የሉዓላዊት ኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ሊሆን አይችልም ።
የኢሕአዴግ ሕገመንግሥት መሠረታዊ የሆነ የሉዓላዊነት ፅንሰ ኃሳብ ግንዛቤ መፋለስ የእሚንፀባረቀብት በመሆኑ ፤ ይኽ የሉዓላዊነት ግንዛቤ መፋለስ ፤ በእዛው የኢሕአዴግ ሕገመንግሥት ውስጥ የተቀመጡ የዜጎችን መብት ፤ ማስከበር እንኳን የእማይችል እርስ በእርሱ የእሚቃረን ሰነድ ሆኗል ።
ለምሳሌ ፦ አንቀፅ 38 የኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት ፤ ዜጎች ስለ አላቸው የመምረጥ እና የመመረጥ መብት እንዲኽ ይላል ፦
“ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቀለም ፣ በዘር ፣ በብሔር ፣ በብሔረሰብ ፣ በጾታ ፣ በቋንቋ ፣ በሃይማኖት ፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ አመለከካከት ወይም በሌላ አቋም ላይ የተመሠረተ ልዩነት ሳይደረግበት የሚከተሉት መብቶች አሉት፤
ሀ/ በቀጥታ እና በነጻነት በመረጣቸው ተወካዮች አማካኝነት በሕዝብ ጉዳይ አስተዳደር የመሳተፍ ፣
ለ/ ዕድማው 18 ዓመት ሲሞላ በሕግ መሠረት የመምረጥ ፣
ሐ/ በማናቸውም የመንግሥት ደረጃ በየጊዜው በሚካሄድ ምርጫ የመምረጥና የመመረጥ፡፡ ምርጫው ሁሉ ዓቀፍ ፣ በሁሉም እኩልነት ላይ የተመሠረተና በሚስጥር ድምጽ አሰጣጥ መራጩ ፈቃዱን በነጻነት የሚገልጽበት ዋስትና የሚሰጥ መሆን አለበት፡፡”
ይላል ።
ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ፤ ሉዓላዊ የአደረገው ይኽ ሕገ-መንግሥት ፤ ይኽን በስፋት የዘረዘረውን ዴሞክራሲያዊ መብት ግን በሐገር ዓቀፍ ደረጃ ማስከበር አይችልም ። ምክንያቱም ፦ አንድ በእዚኽ የኢሕአዴግ ሕገመንግሥት ሉዓላዊ የተደረገ እና ለአንዱ ነገድ የተቸረ ክልል ፤ በእኔ ክልል ከእኔ ብሔር ፣ ብሔረሰብ እና ሕዝብ ውጭ የአለ፟ ማንኛውም ሰው በምርጫ መሳተፍ አይችልም ቢል ፤ ሉዓላዊ ስለ ሆነ ሊከለክለው የእሚችል ማንም የለም ።
ለእዚኽም ተግባራዊ ማሳያ ፤ በ 1997 የተሻሻለው የሐረሪ ሕዝብ ክልል ሕገ-መንግሥት ፤ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ በተባለችው ኢትዮጵያ ፤ የክልሉ ሕገ-መንግሥት ዋና መንፈስ እና የተሻሻለበትን አግባብ በእሚያስረዳበት የሕገ-መንግሥቱ መግቢያው ላይ ፤ ያለ ምንም ማቅማማት እንዲኽ ይላል ፦
“የሐረሪ ሕዝብ … በራሱ ክልል በቁጥር አናሳ ከመሆኑ የተነሳ ልዩ የአወካከል ስልት ማስፈለጉን በመረዳት ።”
በሐረሪ ሕዝብ ክልል ሕገ-መንግሥት መግቢያ ላይ የአለው የእዚኽ አባባል ኃሳብም ፤ ምንም እንኳን ክልሉ ‘የእኛ’ ቢሆንም ፤ በራሳችን ክልል በመጥፎ የታሪክ አጋጣሚ አናሳ ቁጥር ያለን በመሆኑ ፤ በዴሞክራሲያው ምርጫ ኹሉም ሰው በዜግነቱ እኩል በሆነበት አግባብ ምርጫ ከተካኼደ የመዋጥ አደጋ ስለ እሚያጋጥመን ፤ በእኛ እና በሌላ የክልሉ ነዋሪ ኢትዮጵያዊ መካከል ልዩነት አድርጎ ፤ ስልጣናችንን የእሚያበዛ ለየት ያለ የአወካከል መንገድ ያስፈልገናል የእሚል ነው ።
ይኽ የሐረሪ ሕዝብ ክልል ሕገ-መንግሥት እያለ የአለው ነገር ሌላ ሰአይሆን ፤ በቁጥር አናሳ ሆኜ ሳለሁ ፤ በመላው ዓለም የተወገዘውን በሐረሪ ተወላጆች እና በሌላው ኢትዮጵያዊ መካከል በአደባባይ ልዩነት የእሚያደርገውን አፓርታይድ በማካኼድ ከሌላው የክልሉ ነዋሪ ኢትዮጵያዊ በላይ ባለ ስልጣን የእሚያደርገኝ አካኼድ መከተል አለብኝ እያለ ነው ።
የኢሕአዴጉ ሕገ-መንግሥትም ፤ ነገዶች ወይንም እርሱ ‘ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች’ የአላቸው ስብስቦች ፤ በራሳቸው ምልዑ የሆኑ የእማይከፈሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ አህዶች ናቸው ብሎ ፤ በስማቸው ክልል ቸሯቸው እና ይኽንንም ክልል ሲያሻቸው ይዘው መውጣት ይችላሉ ብሎ ይኽም ሳይበቃ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ናቸው በማለት ፤ በራስ ምሉዕ ሉዓላዊያን ስለ አደረጋቸው ፤ በሕገ-መንግሥት ውስጥ ያፀደቀውን የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብት በእዚኽ መልኩ በአደባባይ ሲጥሱ ፤ አደብ ግዙ ማለት የእማይችል ነው ።
በተናጠል ሉዓላዊ ለሆኑ ነገዶች በባለቤትነት የተሰጡ ክልሎች ፤ ይኽን መሰል አፓርታይድ ወይንም ዜጋን የማግለል ሥራ በሕገ-መንግሥት ደረጃ ሲያፀድቁ ፤ በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ይኽን መሰል የመብት ጥሰት እንደ አያደርጉ መከልከል አይቻልም ።
የተሻሻለው የሐረሪ ሕዝብ ክልል ሕገ-መንግሥት እንደው ልዩ አወካከል ያስፈልጋል ብሎም አላበቃም ፤ ይልቁንም ወረድ ብሎ በአንቀፅ 50/2 ላይ የሐረሪ የሕግ መወሰኛ (ፓርላማ) አካል ለሆነው የሐረሪ ክልል ብሔራዊ ጉባኤ አባላት የእሚመረጡት ሰዎች የእሚመረጡት ፤ በሐረሪ ክልል እና ከሐረሪ ክልል ውጭ በተለያየ የኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ በእሚኖሩ የሐረሪ ነገድ ወይንም ‘ብሔር ፣ ብሔረሰብ እና ሕዝብ’ ተወላጆች ነው ይላል ፦
“ የሐረሪ ክልል ብሔራዊ ጉባኤ አባላት ፤ በክልሉ ውስጥ እና ከክልሉ ውጭ በሌላ የኢትዮጵያ ክልሎችና እና ከተሞች ከሚኖሩ የሐረሪ ብሔረሰብ አባላት ይመረጣል ።”
ይኽም ማለት ፤ አያት ቅድመ አያቱ በኖሩባቸው እና እርሱም ተወልዶ በአደገበት የሐረሪ ክልል ፤ አይደለም በሐረሪ ክልል ከእሚኖረው በመላው ኢትዮጵያ ከእሚኖረው ጠቅላላው ሐረሪ የእሚበዛው እና የሐረር ክልል ነዋሪ የሆነው ሌላው ኢትዮጵያዊ ፤ በሕገ-መንግሥት ደረጃ ፤ መሠረታዊ እና ዴሞክራሲያዊ የሆነውን ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን ፤ በእዚኹ ሕገ-መንግሥት ተገፏል ማለት ነው ።
የሐረሪን ምሳሌ እንደ ዓይነትኛ ማሳያ ስለ እሚጠቅም አመጣነው እንጂ ፤ ትልቁ ነጥብ ፤ ይኽ የኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት በውስጡ ከያዘው ተቃርኖ የተነሳ ፤ ክልሎች በተሰጣቸው ነገዳዊነት እና ሉዓላዊነት ተጠቅመው የፌደራሉ መንግሥቱን ሕገ-መንግሥት ተብዬ ሳይጥሱ ፤ ማንኛውንም ዓይነት ኢሰብዓዊ እና ኢደሞክራሲያዊ ሕግ ከማውጣት መከላከል የእማይችል ሕጋዊ ማዕቀፍ ነው ።
በሐረር ጥቂቶች ብዙኃኑን ከምርጫ በሕገ አግደው የአናሶች የበላይ መንግሥት (Minority Dominion – AKA Apartheid) ማቋቋም ከቻሉ ፤ ሌሎች ክልሎች ብዙ ‘ሕገ-መንግሥታዊ’ የመብት ረገጣ ሊያደርጉ እንደ እሚችሉ ግልፅ ነው ።
ይኽ ደግሞ ኢትዮጵያ በሕገ-መንግሥት ደረጃ ዴሞክራሲያዊት የአልሆነች ሐገር ያደርጋታል ፤ ምክንያቱም ፦ ዜጎች በእሚኖሩበት አከባቢ ያለ ምንም የቀለም፣ የዘር፣ የነገድ ፣ የጾታ፣ የቋንቋ ፣ የኃይማኖት፣ የፖለቲካ ወይም የሌላ አመለከካከት ወይም የሌላ አቋም ላይ የተመሠረተ ልዩነት ሳይደረግባቸው ፤ በከባቢም ሆነ በሐገር ዓቀፍ ደረጃ መምረጥ እና መመረጥ የእማይችሉባት ዴሞክራሲያዊት ሐገር ስለሌለች ።
ይኽም በመሆኑ ፤ የኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት ይኽን መሰል ጉልኽ ድክመት ይዞ መቀጠል የለበትም ።
እጅግ ግድየለሽነት የተንፀባረቀበት የኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 39 እንደ እዚኽ ይነበባል ፦
“ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ፣ ብሔረሰብ ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል የአለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው፡፡”
በመጀመሪያ ደረጃ ፤ የሕዝብ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ለመገንጠል የእሚውል ከሆነ ፤ በመርህ ደረጃ የእሚቀመጥ ሰአይሆን ፤ በተግባር የእሚገለፅ ፤ መሬት ላይ የእሚገኙ የሕዝብን ፍላጎት ፣ የማስፈፀም አቅም እና ዘርፈ ብዙ የተመቻቹ ኹኔታዎችን የእሚፈልግ ነው ።
አንድ ሕዝብ ወይንም አከባቢ የመገንጠል መብት ያለገደብ አለህ ስለተባለ አይገነጠልም ፤ የመገንጠል መብት የለህም ስለ ተባለም ከመገንጠል አይቀረም ። ፍላጎቱ እና አቅሙ ከአለ፟ ፤ መብቱ በወረቀት በሕግ ተደነገገለትም አልተደነገገለትም ከመገንጠል የእሚመልሰው የለም ፤ ይኽም በመሆኑ መብቱን መደንገጉ ፋይዳቢስ ነው።
ስለ እዚኽ ፦ ሌኒን እንደ አለው ፤ መገንጠል ትችላለህ ስንለው ከመገንጠል ይመለሳል የእሚለው አባባል ፤ ክርክር ያሳምር ይሆናል እንጂ ለተግባራዊ ፖለቲካ የእሚፈይደው አንዳች ነገር የለውም ። የሕገ-መንግሥቱ ደጋፊዎች እንደ እሚሉት ፤ የትኛውም ሕዝብ የመገንጠል ፍላጎቱ እና አቅሙ እየአለው ፤ የመገንጠል መብትህ ያለገደብ የተከበረ ነው ስለተባለ ከመገንጠል ይመለሳል ብሎ ማሰብ ፤ ብዙም የእማያስኼድ መሆኑ ለብዙ ሰው ግልፅ ነው ።
ከእዛኽ በመቀጠለም ፤ ይኽንን ‘መብት’ ለአንድ ‘ብሔር ፣ ብሔረሰብ እና ሕዝብ’ ብቻ ማን ሰጠው? የአንድ ‘ብሔር ፣ ብሔረሰብ እና ሕዝብ’ ገሚሱ እገነጠላለኹ ቢል ፤ አይ ኹላችኹም በአንድነት ከአልተገነጠላችኹ ፤ ገሚሳችኹ ብቻ መገንጠል አትችሉም ማለት ይቻላል?
ነገዶች ወይንም ‘ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝብ’ መገንጠል የእሚችሉ ከሆነ ፤ ለምን ወረዳዎች መገንጠል አይችሉም? ለምን ዞኖች መገንጠል አይችሉም? ለምን ክፍለ ከተማዎች መገንጠል አይችሉም? ልምን ክፍለ ሐገራት መገንጠል አይችሉም ? በአጠቃላይ ፤ ይኽ ቡድን መገንጠል ይችላል ይኽኛው ደግሞ አይችልም ብሎ ማንም መደንገግ አይችልም ፤ ምክንያቱም ይኽ በዘርፈ ብዙ ቅድመ ኹኔታዎች የእሚወሰን ውስብስብ እና እንደ ኹኔታው በተናጠል የእሚታይ እንጂ እንደው በጀመዓ ይኽን መሰሉ ቡድን መገንጠል ይችላል የእሚባልበት ጉዳይ አይደለም ፤ ይኽም በመሆኑ መገንጠል በራሱ (per se) ከመብት ጎራ የእሚፍረጅም አይደለም።
ከእዚኽ የተነሳ ፤ ‘የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል መብት ያለገደብ የተከበረ ነው’ ብሎ በሕገ-መንግሥት ከማስፈር እና ከአለማስፈር አንፃር ፤ ዋናው ፖለቲካዊ ጥያቄ ፦ እንደ ሕገ-መንግሥቱ በነገድ እንደ ወሰነው ሰአይሆን ነገድ አልባ የሆነውን እና በድንጋጌ ሰአይሆን በሌሎች እንደ ፖለቲካዊ ፣ ኢከነሚያዊ ፣ ባህላዊ እና ዓለም ዓቀፍ የኃይል አሰላለፍ ባሉ ወቅታዊ እና ውስብስብ ጉዳዮች ላይ የእሚደገፍን ኹኔታ ፤ በመብት ደረጃ መደንገጉ ጥቅሙ ምንድነው? ጥቅምስ ከሌለው ጉዳቱ ምንድነው? የእሚሉት ኹለት ጥያቄዎች ናቸው ።
በእዚኽም ረገድ ፤ የመገንጠል መብት እንደ መዋሐድ መብት ፤ ከዜጎች ፣ ከሰዎች በዛም ከሕዝብ የመምረጥ መብት የእሚቀዳ እንጂ በራሱ የመገንጠል መብት የእሚባል መብት የለም ።
በመርህ ደረጃ ደግሞ ዋና መብቶች ሲከበሩ ከዋናው መብቶች የእሚመነጩ መብቶች በሕግ እስከ አልተከለከሉ ድረስ በተወራራሽነት የእሚከበሩ በመሆናቸው ፤ እንደ ሕገ-መንግሥት ባሉ መሠረታዊ መብቶች በእሚዘረዘሩበት ሰነድ ላይ እያንዳንዱ ቅጂ መብት አይዘረዘርም ።
የዜጎችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት የእሚያከብር ሕገ-መንግሥት ፤ ዜጎች መገንጠልንም ጨምሮ ሌሎች ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን እንዲያደርጉ የእሚፈቅድ በመሆኑ ፤ ቅጂውን የመገንጠልን መብት በልዩ ኹኔታ መዘርዝር በመርህ ደረጃ አስፈላጊ አይደለም ። በሌላ አገላለፅ ፤ የመገንጠል እንቅስቃሴ እንደ ማንኛውም ፖለቲካዊ አጀንዳ ፤ በአንድ ኃሳብ ዙሪያ የመደራጀት እና የፖለቲካ ፓርቲ የመመሥረት መብት ስር የእሚጠቃለል በመሆኑ እና ብልዩ ኹኔታ ‘ለብሔር ፣ ብሔረሰብ እና ሕዝብ’ ወይንም ለነገድ ብቻ የተሰጠ መብት በአለመሆኑ ፤ ከመሰል መብቶች ለይቶ እና ለነገድ ወይንም ‘ለብሔር ፣ ብሔረሰብ እና ሕዝብ’ ብቻ በመወሰን ፤ ለብቻው መደንገዱ ምንም ከጠባብነት እና ከጨለምተኝነት በአሻገር ተጨባጭ ፖለቲካዊ መሠረት እና ፋይዳ የለውም ።
ይኽም በመሆኑ ፤ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ የአሉ፟ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ውጭ ከአሉ፟ ሌሎች ሕዝብ ጋር የመቀላቀል መብት ያለገደብ አላቸው ብሎ ማስቀመጥ ፋይዳ የሌለውን ያኽል ፤ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ የአሉ፟ ማንኛውም ሕዝብ የመገንጠል መብት ያለገደብ አላቸው ማለት ፋይዳ ቢስ ነው ።
የሕዝብ መብት ከዜጎች ዋና መብት የእሚቀዳ መብት በመሆኑ ፤ የዜጎች ዋና ወይንም ተፈጥሮዋዊ ፤ የመምረጥ ዋና መብት ከተከበረ እና አመቺ ኹኔታዎች ከተሟሉ ፤ መገንጠለም መዋኋድም እንደ ታሪካዊ ክስተት እንዲሆኑ ወይንም እንዳይሆኑ መደንገግ መንግሥት ከእሚቋቋምበትም ምክንያት አንፃርም ስናየው ፤ መንግሥት ፦ ልክ ከኢትዮጵያ ጋር የመዋኋድ ፍላጎት የአላቸውን ሕዝብ እየፈለገ ከኢትዮጵያ ጋር ማዋኋድ አንድ ‘ተፈጥሮዋዊ’ የመንግሥት ኃላፊነቱ የአልሆነውን ያኽል ፤ የመገንጠል ፍላጎት የአለውን ሕዝብ በባትሪ እያፈላለጉ የእሚገነጠልበትን ኹኔታ ማመቻቸት የመንግሥት ኃላፊነት ስለ አልሆነ ፤ ይልቁንም ሐገር የመምራት ኃላፊነቱን እንዲይዝ የመረጡትን ሕዝብ አንድነት ማጠናከር ኃላፊነቱ ስለ ሆነ ፤ የመገንጠል መብትን መደንገጉ ምንም አስፈላጊነት የለውም ።
ስለ እዚኽ ፦ የመገንጠልን መብት ያለገደብ በሕገመንግሥት ማረጋገጥ ፤ በእዛኽ ላይ ከብዙ ማሕበራዊ አደረጃጀቶች መሐከል ለነገድ ወይንም ‘ለብሔር ፣ ብሔረሰብ እና ሕዝብ’ ብቻ መስጠት ፦ ተግባራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ፋይዳ የሌለው ፣ ከመርህ አንፃር አስፈላጊ የአልሆነ እና የመንግሥት ልዩ የሥራ ድርሻ በአለ መሆኑ ፤ ከዓለም ሕዝብ ኹሉ በተለየ ፤ እንደ ኢትዮጵያ ባለች ሐገር ሕገ-መንግሥት ውስጥ ይኽን ለማስቀመጥ የእሚያስገድድ አንዳች ፖለቲካዊ ወይንም ሌላ ምክንያት የለም ። በሐገራቸው ውስጥ ከ100 በላይ ነገድ የአለ፟ባቸው ቢያንስ ሐምሳ ሐገራት አሉ በዓለም ላይ ፤ የኢትዮጲያን ከእነ እዚኽ ኹሉ የዓለም ሐግራት ልዩ የእሚያደርጋት ምንም ምክንያት የለም።
ከእዚያኽ በመለስ ግን ፤ የመገንጠል መብት ያለገደብ ማረጋገጥ ፋይዳ ባይኖረውም ፤ ለፖለቲካዊ አለመረጋጋት በር የመክፍት አቅም ስላለው በሕገመንግሥት ውስጥ መካተት የለበትም ።
የእዚኽን ድንጋጌ አፍራሽነት ለመረዳት ፤ የድንጋጌውን ይዘት መረዳቱ ተገቢ ነው ።
በእዚኽም መሠረት ድንጋጌው በመጀመሪያ ፤ ልክ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ፤ ከዜጎች የመምረጥ ተፈጥሮዋዊ መብቶች እንደ እሚመነጨው ፤ የመገንጠል መብት የራስን እድል በራስ መወሰን ከእሚለው ፤ በአንድ አከባቢ ለእሚኖሩ ሕዝብ ከተሰጠው ዓለም ዓቀፋዊ መብት ይመነጫል እንጂ በራሱ የቆመ የመገንጠል የእሚባል መብት የለም ።
በመቀጠል ፤ የመገንጠል መብት የተቀዳበት ፤ የራስን እድል በራስ መወሰን መብት ፤ በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር ላይ በተቀመጠበት አግባብ ፤ ለሆኑ ሕዝብ (ነገዶች ወይንም በኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት መዝገበ ቃላት ‘ለብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች’) የተሰጠ መብት ሰአይሆን በአንድ አከባቢ ለእሚኖሩ እና በነገድ ስብጥራቸው የአልተወሰነ የአንድ አከባቢ ሕዝብ መብት ነው ። በጉዳዩ ላይ የታተመ የአሜሪካን የሰላም ጥናት መዓከል ያሳተመው ሪፖርት እንደ እዚኽ ይላል ፦
“እስካዛሬም ፥ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ለአከባቢ እንጂ ለሕዝብ የተሰጠ መብት አይደለም ።”
“Still, self-determination applied to territories and not to peoples. [42]“
ይኽን መብት ግን በእዚኽ አከባቢ የእሚኖረው ሕዝብ ይኼ ሕዝብ ብቻ ነው በእሚል ተተርጉሞ ፤ አንድ የሆነውን ሕዝብ ይኽን አከባቢ ይዞ የመገንጠል መብት አለው በእሚል ከተተረጎመ ፤ ሕዝብን በእማይጨበጥ የማንነት ትርጓሜ ሕዝብን በሕዝብ ላይ አከፋፍሎ በማነሳሳት ይኽ አከባቢ የእኔ ነው ፥ የእኔ ነው በእሚል በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ፤ የአለመረጋጋት እና የግጭት አረንቋ እንደሚፈጥር ይኸው ሪፖርት ፤ እንደ እዚኽ አስቀምጦታል ፦
“በቅርብ ዓመታት ፤ በሐገራቸው ውስጥ አናሳ የሆኑ ቡድኖች ፤ ‘የራስን እድል በራስ መወሰነን’ እያጣቀሱ ፤ በሐገራቸው ራስ ገዝ ለመሆን ፤ አንዳንድ ግዜም የመገንጠል ጥያቄ እያነሱ ፤ ይኽን ግባቸውን ለመከተል ወደ አመፅ እየገቡ ነው ። … በእዚኽ ጉዳይ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ አመፅ የመፋፋሙ እድል ፤ ራሺያ እና ቻይናን የመሳሰሉ ትልልቅ ግዛቶች በእዚኽ ሊነኩ የእሚችሉ መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ ፤ የበለጠ ትልቅ እየሆነ ይኼዳል ።”
“In recent years, many groups that constitute minorities in their states have invoked the ‘right to self-determination’ in their demands for autonomy – or, in some cases, secession – and have resorted to violence to pursue their aims. … The potential for violence and international instability becomes even more obvious when one considers that some still very large empires, such as Russia and China, are likely to be affected by these movements. [42]“
ከእዚኽ እንደ እምንመለከተው ፤ የራስን እድል በራስ ከመወሰን መብት ፤ የእሚቀዳው የመገንጠል መብት ፤ በኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት ውስጥ የተንፀባረቀበት አግባብ ፤ በተበባበሩት መንግሥታት ድንጋጌ ከተካተተው ውጪ ፤ የአንድ አከባቢ ሰአይሆን የሆኑ ‘ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች’ ነው በእሚለው አንደምታው በመሆኑ ፤ በሐገር ደረጃ ብቻ ሰአይሆን ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ፤ ለዓለም ሕዝብ የደህንነት እና የሰላም ስጋት በሆነበት መልኩ ነው የተቀመጠው ።
ይኽ አንቀፅ 39 በኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት ውስጥ በአለበት አግባብ ፤ ራሺያን እና ቻይናን የእሚያኽሉ ትልልቅ ዓለም ዓቀፋዊ ሚና የአላቸውን ሐገራት ከአሰጋ ፤ ኢትዮጵያንም ሊያሰጋ እንደ እሚችል ምንም ጥርጥር የለውም ።
በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ፤ ለከባቢ የተሰጠን የራስን እድል በራስ መወሰን መብት ለከባቢ ሰአይሆን ለሕዝብ ፣ ዓለም ዓቀፍ እውቅና የሌለውን የመገንጠል መብት እንደ እዚኹ ለሕዝብ ሰጥቶ ፤ ለአሉታዊ ፖለቲካዊ ውትወታ በር መክፈት የአንድ ሕገ-መንግሥት መስረታዊ ዓላማ ጋርም በቀጥታ የእሚቃረን ነው ።
ይኽ እንግዲኽ ከፍ ባለ የፖለቲካ ሳይንስ አስተሳሰብ ስንመዝነው ነው ። የፖለቲካ ሳይንስ ትንታኔውን ትተነው እንደው በአመዛዛኝ አዕምሮም ስናየው አይደለም ሐገር ፤ ትዳር መመሥረት እና ማፍረስ እጅግ በዙ ቅድመ ኹኔታ የእሚፈልግ መሆኑ ግልፅ ነው ።
ይልቁንም ፤ በዘመናት ኺደት እርስ በራሱ የተሳሰረ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ማሕበረሰብ ውስጥ ፤ ብዙ ነገር የእሚጋሩ ነገዶችን ወይንም ‘ብሔሮችን ፣ ብሔረሰቦችን እና ሕዝቦችን’ የፖለቲካዊ ማሕበረሰቡ አደረጃጀት ወይንም የክልል አወቃቀር ማዕከል ከተደረጉ በኋላ ፤ በሕገ-መንግሥት ደረጃ መገንጠል ትችላላችሁ ብሎ መደንገግ ፤ ለኢትዮጵያ ታሪካዊ የውጭ ጠላቶች ሐገር ማተራመሻ ረዥም በትር ማቃበል ነው ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ቢያንስ ለ400 መቶ ዓመታት ያልኖረ ነገድ የለም ። በእዚኽ ረዥም የጋራ የኑሮ ዓመታት ደግሞ ፤ ሰፊ ቁጥር የአለው ከስፍራ ስፍራ የአልተንቀሳቀሰ ፤ የሕብረተሰብ ክፍል የለም ። እንደ እዚኽ በረዥም ዘመን ኺደት በተበወዘ ሕዝብ መሐከል ፤ በወረቀት ላይ አስምረህ በፈጠርኸው ድንበር እና ይኽም የወረቀት ላይ ድንበር የሕዝብን ነገዳዊ አሰፋፈር እና ስብጥር በፍፁም በእማይወክል እና ሊወክል በእማይችልበት ኹኔታ ፤ በሌላ አገላለፅ ፤ የውሸት ድንበር ሰርተህ ፤ እርሱም ሳይበቃህ ፤ ካስፈለገህ ይኽን አወዛጋቢ ድንበር የእኔ ነው ብለህ መገንጠል ትችላለህ ማለት ፤ የሕገ-መንግሥቱ ደጋፊዎች ለማለት እንደ እሚፈልጉት ፤ የመገንጠል አጀንዳ ለእሚያራምድ ፖለቲከኛ ከእዚኽ አጀንዳው እንዲመለስ በማድረግ ነገር የእሚያበርድ ሰአይሆን ፤ ቀቢፀ ተስፈኛውን እና ይኽንን ቀቢፀ ተስፈኛውን ተቀጣሪ ለማድረግ የእሚፈልግ ፀረ-ሰላም ኃይል ወይንም የሐገር ጠላት ለአፍራሽ ተግባሩ የፕሮፖጋንዳ አቅም መፍጠር መቻሉ ግን አሌ የእማይባል ነው ።
አይደለም እንደ ኢትዮጵያ ለአለ፟ ጥንታዊ ሐገር እና በእዚኽም ረዥም ቆይታ በጣም በተሰባጠረ ማሕበረሰብ ውስጥ ይቅርና ፤ አኹን በአሉት ዓለም ዓቀፍ እውቅና በአላቸው ሐገራት ድንበር ላይ ፤ ማንነትን መሠረት የአደረገ የእማያወዛግብ ድንበር መሥራት አይቻልም ።
ስለ እዚኽ ፤ ሐገርን በእምታኽል የብዙ መቶ ዓመታት የደም እና የላብ ስሪት ፤ ማዋቀሪያ ሊሆን የእሚገባው ሰነድ ፤ ነገዶች ይዘው ሊገነጠሉ የእሚችሉትን ድንበር በእማያሻማ መልኩ ሳይወስን (ሊወስንም አይችልም ) ፤ ሐገርን ከህንፃ አቅልሎ ፤ ስንፈልግ እንጋጠማለን ስንፈልግ እንለያያለን ማለቱ ፤ የሐገር ግንባታ ሚናውን በአግባቡ እንዳይወጣ ያደርገዋል ብቻ ሰአይሆን ግጭትን ማበረታቻ አድርጎታል ።
በኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት ላይ ያለንን ትችት ስናጠቃልል ፦ እነ እዚኽን ሦሥት የኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት ስህተቶች ፤ ከመሠረታዊ የሕዝባዊ መንግሥት አስተሳሰብ ጋር አብረው ሊኼዱ የእማይችሉ በመሆናቸው እና የኢትዮጵያን ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ጉዞ የእሚያደናቅፉ በመሆናቸው ፤ ከእነዚኽ እና መሰል ዝበቶች የፀዳ ፤ አዲስ ሕዝባዊ ሕገ-መንግሥት እንደ እሚያስፈልግ ግልፅ ነው ።