ሕ ገ ክ ራ ሲ

marketing-image

4.2.1. የኢትዮጵያን ሐገራዊ ሉዓላዊነት በማቃለል ሕዝባዊነትን የከለከለ ነው

ሕገ-መንግሥት በአንዲት ሐገር ውስጥ ፤ የሕጎች ኹሉ እናት በመሆኑ ፤ በዘመናት መካከል በሰው ልጅ ምርምር እና እውቀት የዳበሩ ኃሳቦችን በአግባቡ በተረዳና በእማያሻማ መንገድ ዜጎች በቀላሉ ሊረዱት በእሚችሉበት አግባብ ማስቀመጥ አለበት ።

ሕገ-መንግሥት ላይ የእሚቀመጡ አንቀጾች በእዚኽ መልኩ በእማይቀመጡበት እና ለፈረጀ ብዙ እና አንዳንዴም ፍጹም ተቃራኒ ትርጓሜዎች ክፍት በእሚሆኑበት ወቅት ሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ (Constitutional Crisis) ያስከትላሉ ።

የኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥትም ከሐገር ግንዛቤው አንስቶ በሉዓላዊነት እና በፌደራሊዝም ፅንሰ ኃሳቦች ላይ በአለ፟ው ብዥታ ምክንያት ሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ የእሚያስከትሉ አንቀጾችን ያስቀምጣል ።

አንድን ሐገር የወሰድን እንደ ሆን የብዙ ነገር ውሕድ መሆኗን እንረዳለን ወይንም ሐገርን የፈጠሯት ምን ምን የግንባታ አህዶች ተዋኽደው ነው? ተብለን ብንጠየቅ ፤ ብዙ የተለያዩ ዓይነት አደረጃጀቶችን ፤ በአህድነት መጥቀስ እንችላለን ።

ለምሳሌ ፦ በአህድነት ወይንም በግንባታ መዋቅርነት ተሰባስበው ሐገርን የእሚመሰሩት ነግሮችን እንደ እዚኽ እያልን መዘርዘር እንችላለን ፦ ሐገር የምድር ወይንም የመኖሪያ እና የነዋሪዎቿ ስብስብ ነች ፣ ሐገር የቤተሰብ ስብስብ ነች ፣ ሐገር የመንደሮች ስብስብ ነች ፣ ሐገር የጎጦች ስብስብ ነች ፣ ሐገር የነገዶች ስብስብ ነች ፣ ሐገር የተባዕት እና የእንስት ፆታ የአላቸው ሰዎች ስብስብ ነች ፣ ሐገር የድሆች ፥ መካከለኛ ገቢ የአላቸው እና ኃብታሞች ስብስብ ነች ፣ ወዘተ ፤ እያልን ሐገርን ሐገር ያደረጓትን ማሕበራዊ ንዑስ ቡድኖች ወይንም አህዶች ከተለያዩ የአደረጃጀት ፣ የኢከነሚ ፣ የባሕል ደርዝ አንጻር መዘርዘር እንችላለን ።

ይኽ ግን በተርታው ሰው አገላለፅ እንጂ ፤ በመጽሐፉ ምዕራፍ አንድ ላይ ፤ ዴሞክራሲያዊነት እና ሐገር በእሚለው ንዑስ ክፍል ላይ እንደ አልነው ፤ በፖለቲካ ሳይንሱ የማሕበረሰብ ስለ እዚኽም የሐገር ብቸኛው አህድ የሆነው ፖለቲካዊው ሰው መሆኑን አስቀምጠናል ።

ለእዚኽም ማሳያ አርስታትል እንዲኽ እንደ አለ አስቀምጠናል ፦

“የብዙ ነገሮች ውህድ እንደ ሆነ እንደ ማንኛውም ነገር ፤ ሐገር (መንግሥት ፥ ብሔራዊው) አንድ ውህድ ነው ፤ ተዋህደው የመሠረቱትም ዜጎቹ ናቸው።”

“But a state is a composite, like any other whole made of many parts; these are citizens who compose it. [1]”

ያም ብቻ ሰአይሆን ፤ ሐገር በግለሰብ አህድነት ሳትገለፅ እና ሳትዋቀር ስትቀር ፤ ወይንም የመዋቀሪያ አህዶች ከዜጎች ይልቅ ማንኛውም ሌላ አደረጃጀት ሲሆን ፤ ውጤቱ የማሕበረሰብ ብሎም የሐገር አህድ የሆኑትን ግለሰቦች ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በማፈን ፤ አስከፊውን የጦርነት ወይንም የተፈጥሮ ኹኔታ በተለያየ መልኩ እንደ እሚያስከትል አይተናል ።

ሆኖም በልማዳዊ አገላለፅ ሐገር የቤተሰብ ስብስብ ነች ፣ ሐገር የመንደሮች ስብስብ ነች ፣ ወዘተ ብለን ብናስቀምጥ ፤ ትርጉሙ ኹሉንም የሐገር ነዋሪዎች በእኩልነት የእሚገልፅ ከሆነ ፤ ብዙም ችግር የአለው አይደለም ።

እነ እዚኽ ለመደበኛ ውይይት ችግር የሌላቸው የሐገር አገላለጾች ግን ፤ አንዳንዶቹ ከላይ በአልነው መልኩ ከዲሞክራሲ ርዕይ ጋር ከመጋጨት በአሻገር ፤ አንዳንዶቹ አካታችም አይደሉም ።

ለምሳሌ ፦ በመደበኛ ግንዛቤ ወይንም አቅል (Common Sense) ሐገር የእያንዳንዱ ዜጋ ስብስብ ነች ወይንም ሕዝቦቿ ናት ብለን ብንል ፤ ገለፃችን አካታች ነው ፤ ምክንያቱም ፦ ማሕበራዊ የሐገር አህድ አንሶ አንሶ ከዜጋ መውረድ ስለ እማይችል እና ተሰብስቦ ተሰብስቦ ከሕዝብ ስለ እማያልፍ ።

በተነጻጻሪ ደግሞ ፦ ሐገር የቤተሰብ ስብስብ ናት ብእንል ፤ ቤተሰብ የሌለውን ሰው ምን ልናደርገው ነው? ቤተሰብ የለህም እና የሐገር አካል አይደለህም ልእንለው ነው? ሐገር የነገዶች ስብስብ ነች ብእንል ፥ ከብዙ ነገድ የወጣውን ሰው ምን ልናደርገው ነው? ሙሉ በሙሉ ከአንድ ነገድ ካልወጣህ ወይንም በስሌት የበለጠ ትስስር ወደ አለህ ነገድ ተቀላቀል ልንለው ነው? እንዲህ ብለን ቤተሰብ ፣ መንደር እና ከተማ ስንሰነጣጥቅ ልንገኝ ነው?

ምክንያቱም፦ አንድን ዜጋ የነገድ ተዋጾህ ወደ እሚበዛበት ተቀላቀል ስንለው ፤ ይኽ ዜጋ በከባቢው ከአሉት እንደ ቤተሰብ ፣ ዘመድ አዝማድ ፣ የሞያ ማሕበራት ፣ ቤት እምነት ፣ መንደር ፣ አናሳ ተዋጾ ከአለው ነገድ ፣ ወዘተ ፤ አወቃቀር ይልቅ ፤ የጎላ የነገድ ተዋጾህ ወደ አለህ የነገድ ቡድን ኺድ እያልነው ስለ ሆነ ፤ ሰውየውን እና ጠቅላላ ማሕበራዊ ስሪቱን በከፍተኛ ደረጃ እያናጋነው ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም።

ከእዚያኽ በአሻገር ቤተሰብ የሌለው ወይንም የራሱ ነገድ የሌለው ሰው ባይኖርም እንኳን ፤ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ሆኖ ፤ ሰው ያለ አንድ ህዋስ ቤተሰብ እና አንድ ነገድ የእማይፈጠር እና የእማይኖር ቢሆን እንኳን ፤ ሐገር የቤተሰብ ስብስብ የሆነችውን ያኽል የነገድ ስብስብም ፣ የወረዳ ስብስብም ፣ የቀበሌ ስብስብም መሆን ስለ እምትችል ፤ ከእነ እዚኽ ኹሉ ቡድኖች በላይ ነገድ በአህድነት ተመርጦ ሐገር የነገድ ስብስብ ነች የእሚያስብል ምንም ልዩ ምክንያት አይኖርም ።

የኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት ፤ እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ብሎ እንደ እሚጀምረው ፤ እኛ የኢትዮጵያ መንደራት ነዋሪዎች ፣ እኛ የኢትዮጵያ ወረዳዎች ነዋሪዎች ፣ ወዘተ ፤ ማለት ይቻላል ወይንም ይኽ አገላለፅ እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ከእሚለው በላይ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አካታች አጠራር ነው ፤ ምክንያቱም ፦ በመንደር ወይንም በወረዳ ውስጥ የእማይኖር ዜጋ ስለ እማይኖር።

ይኽን መሰል ማንም በመደበኛ ግንዛቤ የእሚረዳውን ኃቅ ለማብራራት የአስፈለገበት ምክንያት ፤ የኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ሲል የኢትዮጵያን ሕዝብ በአጠቃላይ በወል የእሚወክልለት አሰያየም አጥቶ ሰአይሆን ራሳቸው ተፈጥሮዋዊ የእማይከፋፈሉ አህድ (Indivisible units) ሆነው ፤ እርስ በእርስ በመተሳሰር ኢትዮጵያን የፈጠሩት እርሱ ‘ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች’ ብሎ የእሚጠራቸው ነገዶች ናቸው ከእሚል የመሐይም እምነት መሆኑን ለማስረዳት ነው ።

ነገዶች ተፈጥሮዋዊ የሆኑ የእማይከፈሉ እና በራሳቸው ተነጥለው የእሚገኙ አህዶች ናቸው (Self Contained indivisible units) የእሚለው አባባል ፤ ማንም ጉዳዪን ወስዶ ላሰበው ሰው የእማያጠራጠር አሉታዊ (Bold No) መልስ የአለው ነው ። የትኛውም የሰው ማሕበር ይኽን ልዩ በኃሪ ሊይዝ አይችልም ።

እንዲያውም ዝልግልግ እና ተቀያያሪ ከሆኑት ነገዶች ይልቅ ፤ ቤተሰቦች ፤ መንደሮች ፣ ቀበሌዎች ፣ ወዘተ ፤ በአደረጃጀት ደረጃ የተሻለ የእማይከፈሉ በራሳቸው ምልዑ የሆኑ አህድነት ባሕሪ የአላቸው ናቸው ።

የመንደሮችም ፣ የወረዳዎችም ፣ የከተሞችም ፣ የክፍለ ከተሞችም ነዋሪዎች ኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ሆኑ የእሚያውቀው ኢሕአዴግ ፤ በነበረበት ብዥታ ድንገት ተነስቶ ፤ ‘ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች’ የእሚል በዓይነቱ ልዩ የሆነ የጋራ ስብስብ ስም (Collective Noun) ፤ በመደበኛ ቋንቋ ነገድ የእሚለውን ቃል በእዚኽ ግርጅፍ የጋራ ስብስብ ስም በመተካት ፤ የኢትዮጵያ አህዶች እነርሱ ናቸው በእሚል ፤ ሕገ-መንግሥቱን እነ እዚኽ የኢትዮጵያ አህዶች ተሰብስበው በተወካዮቻቸው አማካኝነት ያፀደቁት ሰነድ ነው አለ ።

ከእዚኽ የኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት የመግቢያ ዓረፍተ ነገር ታሪካዊ ቅጥፈት (Historical Blunder) በአሻገር ፤ ፍፁም ሊባል በእሚችል የሉዓላዊነት ፅንሰ ኃሳብ መኃይምነት ፤ ሉዓላዊት በሆነች ሐገር ውስጥ ሉዓላዊ የሆኑ የስልጣን ባለቤት የሆኑት እነርሱ ናቸው በማለቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ሐገርነት ከመናቁ በአሻገር በኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝባዊ መንግሥት ለማቋቋም እንደ አይቻል አድርጓል ።

በሕገ-መንግሥቱ በአንቀፅ 8 ላይ ፦

“የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች ፣ ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው፡፡”

ይላል ። ይኽን አንቀፅ ላላስተዋለው ሰው ፤ የኢትዮጵያ ዜጋ ከየትኛውም ነገድ ወይንም ጎጥ ይኹን ፤ በዴሞክራሲያው አግባብ በአለው ውክልና ፤ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር ፤ በጋራ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ነው የእሚል ሊመስል ይችላል ።

በሕገ-መንግሥቱ አውድ ለተረዳው ሰው ግን ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የአሉ፟ ነገዶች እና ጎጦች ወይንም በሕገ-መንግሥቱ የዘፈቀደ አሰያየም ፤ ‘ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች’ በተናጠል የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ናቸው የእሚል ነው ።

ይኽን ለማስረዳት እና የእዚኽን አንቀጽ እንደምታውን ለመረዳት የተወሰኑ ነጥቦችን እናንሳ ።

በእዚኹ ከእላይ በጠቀስነው የሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 8/3 ሦሥት ላይ ፤ የ‘ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች’ ሉዓላዊነት የእሚገለፀው ፤ በተወካዮቻቸው አማካኝነት በእሚመርጡት ምርጫ ነው ይላል ፦

“ ሉዓላዊነታቸውም የሚገለጸው በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት ይሆናል ። “

ይኽም ማለት ፤ በክልልም ሆነ በሐገር ዓቀፍ ደረጃ ተወካይ የመምረጥ እና የመሰየም መብት የአላቸው የነገድ መዋቅሮች ብቻ ናቸው ማለት ነው ። ይኽም በክልሎች አወቃቀር እና በፖርላማ መቀመጫ ክፍፍልም በግልፅ ተቀምጧል ።

እንደገናም ፦ እነ እዚኽ ‘ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች’ ፤ በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ፤ በማንኛውም ግዜ የራሳቸው ክልል ማቋቋም የእሚችሉ እና እስከ መገንጠል የእሚደርስ መብት በተናጠል የአላቸው ናቸው ።

እያንዳንዱ ነገድ በተናጠል የራሱ ክልል መመሥረት እንደ እሚችል ፤ ሕገ-መንግሥቱ በአንቀፅ 47/2 ላይ እንዲኽ ይላል ፦

“ … ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች ፣ ሕዝቦች በማንኛውም ጊዜ የየራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት አላቸው ። “

እነ እዚኽ ‘ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች’ ፤ ይኽንን ያቋቋሙትን ክልል ይዘው በማንኛውም ግዜ ያለ ምንም ገደብ መገንጠል እንደ እሚችሉ በአንቀፅ 39/1 ላይ በግልፅ ተደንግጓል ፦

“ ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ፣ ብሔረሰብ ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል የአለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው ።”

ስለ እዚኽ ፤ ሕገ-መንግሥቱ በአንቀፅ ስምንት ላይ ፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው የእሚልበት አውድ ፤ ከብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝብ የተወጣጡት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ናቸው እያለ ሰአይሆን ፤ እያንዳንዳቸው ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በተናጠል የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ናቸው እያለ ነው ።

ይኽም ማለት እነ እዚኽ ነገዳዊ ክልላት የአላቸው ነገዶች ፤ በነገዳቸው ስም በያዙት ክልል ውስጥ ፤ የነገዳቸው አባል የአልሆነን ኢትዮጵያዊ ከመምረጥ እና መመረጥ መብት እስከ ማገድ የእሚደርስ ክልከላ ቢያድርጉበት ማንም የእሚያግዳቸው የለም ማለት ነው ፤ ሉዓላዊያን ናቸውና ።

ይኽን መሰል አወቃቀር ደግሞ ፤ የሉዓላዊት እና ሕዝባዊት ሐገር አወቃቀር ሰአይሆን የቀጣና አወቃቀር ነው ።

መንግሥታት ወይንም ሉዓላዊ ነን የእሚሉ ተደራዳሪዎች ፤ አንድ የጋራ ማሕበር ከአቋቋሙ በኋላ ሉዓላዊነታቸውን በእዚኽ መልክ ይዘው ሊቀጥሉ የእሚችሉት ፤ ነፃ የንግድ ቀጠና ሲያቋቁሙ ፣ የጋራ ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ ሲስማሙ ፣ ነፃ የኢከነሚ ዞን ሲያቋቁሙ ፣ ወዘተ ፤ እንጂ ፤ ሉዓላዊ መንግሥት ከአቋቋሙ በኋላ እነርሱ ሉዓላዊ ሆነው የእሚቀጥሉበት ምንም ዓይነት አግባብ የለም ።

ለምሳሌ ፦ ሦሥቱ የሰሜን አሜሪካ ሐገራት ፤ ካናዳ ፣ አሜሪካ እና ሜክሲኮ ፤ በተናጠል ሉዓላዊያን የሆኑ ሐገራት ሲሆኑ ፤ በተወሰኑ ምርቶቻቸው ላይ በድንበር የእሚደረገው ንግድ ከቀረጥ ነፃ በሆነ አግባብ እንዲሆን ፤ NAFTA (Northern America Free Trade Agreement) የእሚባል ስምምነት አድርገው ይነግዳሉ ። ይኽ የንግድ ስምምነት ፤ ሦሥቱን ሐገራት አንድ ሐገር አያስብላቸውም ፤ ምክንያቱም ፦ ሐገር ማለት ቀረጥ አልባ የንግድ ቀጠና ማለት ስለ አልሆነ ።

እንደ እዚኹም አሜሪካ እና አብዛኛዎቹ የአውሮፓ ሐገራት NATO (North Atlantic Treaty Organisation) የእሚባል ፤ በአንዱ አባል ሐገር ላይ የተደረገ ጥቃት በኹሉም ላይ እንደ ተደረገ ይቆጠራል በእሚል ኃሳብ ፤ የጋራ የመከላከያ ድርጅት ፈጥረዋል ፤ ይኽ ግን ሐገር አያስብላቸውም ፤ ምክንያቱም ፦ ሐገር ማለት የጋራ መከላከያ ስምምነት ስለ አልሆነ ።

የአውሮፓ ሕብረት ፥ የጋራ መገበያያ ገንዘብ ፣ ፓርላማ እና ፕሬዘዳንትም የአለው ህብረት ቢሆንም ፤ ሐገር አይደለም ፤ ምክንያቱም ሐገርነት ፤ በዴሞክራሲ ትንታኔ የጋራ መገበያያ ገንዘብ በመያዝ ፣ ፓርላማ እና ፕሬዘዳንት የአለው አደረጃጀት የመያዝ ጉዳይ ሰአይሆን ፤ ሐገራትን የእሚያስብላቸው ዋነኛው መለያ ፤ ዜጎቻቸው ያለ ምንም መካከለኛ ፤ በከባቢያዊም ሆነ በብሔራዊ (ሐገር ዓቀፍ) ደረጃ በቀጥታ ለሕዝባዊ መንግሥት ኃላፊነት የመምረጥ እና የመመረጥ መብት ሲኖራቸው ነው ።

ዜጎች በሐገራቸው በእሚኖሩበት በማንኛውም አከባቢ ፤ ለከባቢያቸውም መንግሥት ተወካይነት የሆነው ነገድ ተወላጅ በአለመሆናቸው ምክንያት ከእዚኽ መብት መታገድ የእሚችሉ ከሆኑ ፤ በሉዓላዊት ሐገር ውስጥ እየኖሩ አይደለም ።

ስለ እዚኽ ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ፤ ነገዶች ወይንም የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የተባሉት ፤ የኢሕአዴግ ሕገመንግሥት እንደ እሚለው ፤ የተናጠል ሉዓላዊነታቸውን እንደ ጠበቁ ፤ እነ እዚኽ ሉዓላዊያን የተባሉ ነገዶች ፤ ነፃ የንግድ ልውውጥ ስምምነት ፣ የጋራ መከላከያ ፣ የጋራ ፓርላማ ፣ ወዘተ ፤ ቢኖራቸውም እንኳን ፤ ኢትዮጵያ አንዱ ዓይነት ቀጣና እንጂ ሉዓላዊት ሐገር አይደለችም ማለት ነው ።

በእዚኽ መልኩ ፤ ከዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብት አንጻር የሐገርን ሉዓላዊነት በእሚጻረር መልኩ ፤ ነግዶችን የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ናቸው ብሎ የተወናበደው የኢሕአዴግ ሕገመንግሥት ፤ ምዕራፍ 10 የብሔራዊ ፓሊሲ መርሆዎችና ዓላማዎች በእሚለው ፤ የብሔራዊውን መንግሥት (National Government) ፖሊሲ ዓላማዎች በእሚደነግግበት ግዜ ፤ የመንግሥትን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች በተመለከተ አንቀጽ 86 ላይ እንዲኽ ይላል፦

“የኢትዮጲያን ሕዝብ ጥቅም እና የሐገሪቱን ሉዓላዊነት የእሚያስከበር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማራመድ።”

ይኽም ማለት ፤ በፍጹም መኃይምነት ፤ ኢትዮጲያ ዓለም ዓቀፋዊ ሉዓላዊት ሐገር መሆኗን ተቅብሎ ሲያበቃ ነው ፤ በኢትዮጲያ ውስጥ የአሉ፟ ነገዶች ወይንም በእርሱ አጠራር ፤ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የእሚላቸውን በተናጠል የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ናቸው የእሚለው።

ይኽ ዓይነት የሉዓላዊነት ፅንሰ ኃሳብ መዛባት የአለበት ሕገመንግሥት ደግሞ ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሉዓላዊነት ከማቃለሉ በላይ ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝባዊ ወይንም ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ለመመሥረት የእምናደርገውን ጉዞ በቀጥታ የእሚያደናቅፍ ነው ።

ይኽም በመሆኑ ፤ ዓለም በሉዓላዊነቷ የእማያውቃትን ሐገር ሉዓላዊነት ፤ በውስጧ ከአሉ፟ ነገዶች ሉዓላዊነት የእሚያምታታ እና የሐገሪቱን ዓለም ዓቀፋዊ ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ የእሚያስገባ ሕገ-መንግሥት እና የኢትዮጵያን ሕዝብ በአንድንነት እና በእኩልነት እንደ መላ ሐገሩ እኩል የጋራ ባለቤትነት የእማይቀበል ሕገመንግሥት የሉዓላዊት ኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ሊሆን አይችልም ።