ሕ ገ ክ ራ ሲ

marketing-image

4.2.2. የዜጎችን መብት ማስከበር የእማይችል ነው

የኢሕአዴግ ሕገመንግሥት መሠረታዊ የሆነ የሉዓላዊነት ፅንሰ ኃሳብ ግንዛቤ መፋለስ የእሚንፀባረቀብት በመሆኑ ፤ ይኽ የሉዓላዊነት ግንዛቤ መፋለስ ፤ በእዛው የኢሕአዴግ ሕገመንግሥት ውስጥ የተቀመጡ የዜጎችን መብት ፤ ማስከበር እንኳን የእማይችል እርስ በእርሱ የእሚቃረን ሰነድ ሆኗል ።

ለምሳሌ ፦ አንቀፅ 38 የኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት ፤ ዜጎች ስለ አላቸው የመምረጥ እና የመመረጥ መብት እንዲኽ ይላል ፦

“ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቀለም ፣ በዘር ፣ በብሔር ፣ በብሔረሰብ ፣ በጾታ ፣ በቋንቋ ፣ በሃይማኖት ፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ አመለከካከት ወይም በሌላ አቋም ላይ የተመሠረተ ልዩነት ሳይደረግበት የሚከተሉት መብቶች አሉት፤

 ሀ/ በቀጥታ እና በነጻነት በመረጣቸው ተወካዮች አማካኝነት በሕዝብ ጉዳይ አስተዳደር የመሳተፍ ፣
ለ/ ዕድማው 18 ዓመት ሲሞላ በሕግ መሠረት የመምረጥ ፣

ሐ/ በማናቸውም የመንግሥት ደረጃ በየጊዜው በሚካሄድ ምርጫ የመምረጥና የመመረጥ፡፡ ምርጫው ሁሉ ዓቀፍ ፣ በሁሉም እኩልነት ላይ የተመሠረተና በሚስጥር ድምጽ አሰጣጥ መራጩ ፈቃዱን በነጻነት የሚገልጽበት ዋስትና የሚሰጥ መሆን አለበት፡፡”

ይላል ።

ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ፤ ሉዓላዊ የአደረገው ይኽ ሕገ-መንግሥት ፤ ይኽን በስፋት የዘረዘረውን ዴሞክራሲያዊ መብት ግን በሐገር ዓቀፍ ደረጃ ማስከበር አይችልም ። ምክንያቱም ፦ አንድ በእዚኽ የኢሕአዴግ ሕገመንግሥት ሉዓላዊ የተደረገ እና ለአንዱ ነገድ የተቸረ ክልል ፤ በእኔ ክልል ከእኔ ብሔር ፣ ብሔረሰብ እና ሕዝብ ውጭ የአለ፟ ማንኛውም ሰው በምርጫ መሳተፍ አይችልም ቢል ፤ ሉዓላዊ ስለ ሆነ ሊከለክለው የእሚችል ማንም የለም ።

ለእዚኽም ተግባራዊ ማሳያ ፤ በ 1997 የተሻሻለው የሐረሪ ሕዝብ ክልል ሕገ-መንግሥት ፤ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ በተባለችው ኢትዮጵያ ፤ የክልሉ ሕገ-መንግሥት ዋና መንፈስ እና የተሻሻለበትን አግባብ በእሚያስረዳበት የሕገ-መንግሥቱ መግቢያው ላይ ፤ ያለ ምንም ማቅማማት እንዲኽ ይላል ፦

“የሐረሪ ሕዝብ … በራሱ ክልል በቁጥር አናሳ ከመሆኑ የተነሳ ልዩ የአወካከል ስልት ማስፈለጉን በመረዳት ።”

በሐረሪ ሕዝብ ክልል ሕገ-መንግሥት መግቢያ ላይ የአለው የእዚኽ አባባል ኃሳብም ፤ ምንም እንኳን ክልሉ ‘የእኛ’ ቢሆንም ፤ በራሳችን ክልል በመጥፎ የታሪክ አጋጣሚ አናሳ ቁጥር ያለን በመሆኑ ፤ በዴሞክራሲያው ምርጫ ኹሉም ሰው በዜግነቱ እኩል በሆነበት አግባብ ምርጫ ከተካኼደ የመዋጥ አደጋ ስለ እሚያጋጥመን ፤ በእኛ እና በሌላ የክልሉ ነዋሪ ኢትዮጵያዊ መካከል ልዩነት አድርጎ ፤ ስልጣናችንን የእሚያበዛ ለየት ያለ የአወካከል መንገድ ያስፈልገናል የእሚል ነው ።

ይኽ የሐረሪ ሕዝብ ክልል ሕገ-መንግሥት እያለ የአለው ነገር ሌላ ሰአይሆን ፤ በቁጥር አናሳ ሆኜ ሳለሁ ፤ በመላው ዓለም የተወገዘውን በሐረሪ ተወላጆች እና በሌላው ኢትዮጵያዊ መካከል በአደባባይ ልዩነት የእሚያደርገውን አፓርታይድ በማካኼድ ከሌላው የክልሉ ነዋሪ ኢትዮጵያዊ በላይ ባለ ስልጣን የእሚያደርገኝ አካኼድ መከተል አለብኝ እያለ ነው ።

የኢሕአዴጉ ሕገ-መንግሥትም ፤ ነገዶች ወይንም እርሱ ‘ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች’ የአላቸው ስብስቦች ፤ በራሳቸው ምልዑ የሆኑ የእማይከፈሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ አህዶች ናቸው ብሎ ፤ በስማቸው ክልል ቸሯቸው እና ይኽንንም ክልል ሲያሻቸው ይዘው መውጣት ይችላሉ ብሎ ይኽም ሳይበቃ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ናቸው በማለት ፤ በራስ ምሉዕ ሉዓላዊያን ስለ አደረጋቸው ፤ በሕገ-መንግሥት ውስጥ ያፀደቀውን የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብት በእዚኽ መልኩ በአደባባይ ሲጥሱ ፤ አደብ ግዙ ማለት የእማይችል ነው ።

በተናጠል ሉዓላዊ ለሆኑ ነገዶች በባለቤትነት የተሰጡ ክልሎች ፤ ይኽን መሰል አፓርታይድ ወይንም ዜጋን የማግለል ሥራ በሕገ-መንግሥት ደረጃ ሲያፀድቁ ፤ በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ይኽን መሰል የመብት ጥሰት እንደ አያደርጉ መከልከል አይቻልም ።

የተሻሻለው የሐረሪ ሕዝብ ክልል ሕገ-መንግሥት እንደው ልዩ አወካከል ያስፈልጋል ብሎም አላበቃም ፤ ይልቁንም ወረድ ብሎ በአንቀፅ 50/2 ላይ የሐረሪ የሕግ መወሰኛ (ፓርላማ) አካል ለሆነው የሐረሪ ክልል ብሔራዊ ጉባኤ አባላት የእሚመረጡት ሰዎች የእሚመረጡት ፤ በሐረሪ ክልል እና ከሐረሪ ክልል ውጭ በተለያየ የኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ በእሚኖሩ የሐረሪ ነገድ ወይንም ‘ብሔር ፣ ብሔረሰብ እና ሕዝብ’ ተወላጆች ነው ይላል ፦

“ የሐረሪ ክልል ብሔራዊ ጉባኤ አባላት ፤ በክልሉ ውስጥ እና ከክልሉ ውጭ በሌላ የኢትዮጵያ ክልሎችና እና ከተሞች ከሚኖሩ የሐረሪ ብሔረሰብ አባላት ይመረጣል ።”

ይኽም ማለት ፤ አያት ቅድመ አያቱ በኖሩባቸው እና እርሱም ተወልዶ በአደገበት የሐረሪ ክልል ፤ አይደለም በሐረሪ ክልል ከእሚኖረው በመላው ኢትዮጵያ ከእሚኖረው ጠቅላላው ሐረሪ የእሚበዛው እና የሐረር ክልል ነዋሪ የሆነው ሌላው ኢትዮጵያዊ ፤ በሕገ-መንግሥት ደረጃ ፤ መሠረታዊ እና ዴሞክራሲያዊ የሆነውን ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን ፤ በእዚኹ ሕገ-መንግሥት ተገፏል ማለት ነው ።

የሐረሪን ምሳሌ እንደ ዓይነትኛ ማሳያ ስለ እሚጠቅም አመጣነው እንጂ ፤ ትልቁ ነጥብ ፤ ይኽ የኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት በውስጡ ከያዘው ተቃርኖ የተነሳ ፤ ክልሎች በተሰጣቸው ነገዳዊነት እና ሉዓላዊነት ተጠቅመው የፌደራሉ መንግሥቱን ሕገ-መንግሥት ተብዬ ሳይጥሱ ፤ ማንኛውንም ዓይነት ኢሰብዓዊ እና ኢደሞክራሲያዊ ሕግ ከማውጣት መከላከል የእማይችል ሕጋዊ ማዕቀፍ ነው ።

በሐረር ጥቂቶች ብዙኃኑን ከምርጫ በሕገ አግደው የአናሶች የበላይ መንግሥት (Minority Dominion – AKA Apartheid) ማቋቋም ከቻሉ ፤ ሌሎች ክልሎች ብዙ ‘ሕገ-መንግሥታዊ’ የመብት ረገጣ ሊያደርጉ እንደ እሚችሉ ግልፅ ነው ።

ይኽ ደግሞ ኢትዮጵያ በሕገ-መንግሥት ደረጃ ዴሞክራሲያዊት የአልሆነች ሐገር ያደርጋታል ፤ ምክንያቱም ፦ ዜጎች በእሚኖሩበት አከባቢ ያለ ምንም የቀለም፣ የዘር፣ የነገድ ፣ የጾታ፣ የቋንቋ ፣ የኃይማኖት፣ የፖለቲካ ወይም የሌላ አመለከካከት ወይም የሌላ አቋም ላይ የተመሠረተ ልዩነት ሳይደረግባቸው ፤ በከባቢም ሆነ በሐገር ዓቀፍ ደረጃ መምረጥ እና መመረጥ የእማይችሉባት ዴሞክራሲያዊት ሐገር ስለሌለች ።

ይኽም በመሆኑ ፤ የኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት ይኽን መሰል ጉልኽ ድክመት ይዞ መቀጠል የለበትም ።