ሕ ገ ክ ራ ሲ

marketing-image

4.2.3. የመገንጠል አጀንዳ አራማጅ ነው

እጅግ ግድየለሽነት የተንፀባረቀበት የኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 39 እንደ እዚኽ ይነበባል ፦

“ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ፣ ብሔረሰብ ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል የአለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው፡፡”

በመጀመሪያ ደረጃ ፤ የሕዝብ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ለመገንጠል የእሚውል ከሆነ ፤ በመርህ ደረጃ የእሚቀመጥ ሰአይሆን ፤ በተግባር የእሚገለፅ ፤ መሬት ላይ የእሚገኙ የሕዝብን ፍላጎት ፣ የማስፈፀም አቅም እና ዘርፈ ብዙ የተመቻቹ ኹኔታዎችን የእሚፈልግ ነው ።

አንድ ሕዝብ ወይንም አከባቢ የመገንጠል መብት ያለገደብ አለህ ስለተባለ አይገነጠልም ፤ የመገንጠል መብት የለህም ስለ ተባለም ከመገንጠል አይቀረም ። ፍላጎቱ እና አቅሙ ከአለ፟ ፤ መብቱ በወረቀት በሕግ ተደነገገለትም አልተደነገገለትም ከመገንጠል የእሚመልሰው የለም ፤ ይኽም በመሆኑ መብቱን መደንገጉ ፋይዳቢስ ነው።

ስለ እዚኽ ፦ ሌኒን እንደ አለው ፤ መገንጠል ትችላለህ ስንለው ከመገንጠል ይመለሳል የእሚለው አባባል ፤ ክርክር ያሳምር ይሆናል እንጂ ለተግባራዊ ፖለቲካ የእሚፈይደው አንዳች ነገር የለውም ። የሕገ-መንግሥቱ ደጋፊዎች እንደ እሚሉት ፤ የትኛውም ሕዝብ የመገንጠል ፍላጎቱ እና አቅሙ እየአለው ፤ የመገንጠል መብትህ ያለገደብ የተከበረ ነው ስለተባለ ከመገንጠል ይመለሳል ብሎ ማሰብ ፤ ብዙም የእማያስኼድ መሆኑ ለብዙ ሰው ግልፅ ነው ።

ከእዛኽ በመቀጠለም ፤ ይኽንን ‘መብት’ ለአንድ ‘ብሔር ፣ ብሔረሰብ እና ሕዝብ’ ብቻ ማን ሰጠው? የአንድ ‘ብሔር ፣ ብሔረሰብ እና ሕዝብ’ ገሚሱ እገነጠላለኹ ቢል ፤ አይ ኹላችኹም በአንድነት ከአልተገነጠላችኹ ፤ ገሚሳችኹ ብቻ መገንጠል አትችሉም ማለት ይቻላል?

ነገዶች ወይንም ‘ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝብ’ መገንጠል የእሚችሉ ከሆነ ፤ ለምን ወረዳዎች መገንጠል አይችሉም? ለምን ዞኖች መገንጠል አይችሉም? ለምን ክፍለ ከተማዎች መገንጠል አይችሉም? ልምን ክፍለ ሐገራት መገንጠል አይችሉም ? በአጠቃላይ ፤ ይኽ ቡድን መገንጠል ይችላል ይኽኛው ደግሞ አይችልም ብሎ ማንም መደንገግ አይችልም ፤ ምክንያቱም ይኽ በዘርፈ ብዙ ቅድመ ኹኔታዎች የእሚወሰን ውስብስብ እና እንደ ኹኔታው በተናጠል የእሚታይ እንጂ እንደው በጀመዓ ይኽን መሰሉ ቡድን መገንጠል ይችላል የእሚባልበት ጉዳይ አይደለም ፤ ይኽም በመሆኑ መገንጠል በራሱ (per se) ከመብት ጎራ የእሚፍረጅም አይደለም።

ከእዚኽ የተነሳ ፤ ‘የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል መብት ያለገደብ የተከበረ ነው’ ብሎ በሕገ-መንግሥት ከማስፈር እና ከአለማስፈር አንፃር ፤ ዋናው ፖለቲካዊ ጥያቄ ፦ እንደ ሕገ-መንግሥቱ በነገድ እንደ ወሰነው ሰአይሆን ነገድ አልባ የሆነውን እና በድንጋጌ ሰአይሆን በሌሎች እንደ ፖለቲካዊ ፣ ኢከነሚያዊ ፣ ባህላዊ እና ዓለም ዓቀፍ የኃይል አሰላለፍ ባሉ ወቅታዊ እና ውስብስብ ጉዳዮች ላይ የእሚደገፍን ኹኔታ ፤ በመብት ደረጃ መደንገጉ ጥቅሙ ምንድነው? ጥቅምስ ከሌለው ጉዳቱ ምንድነው? የእሚሉት ኹለት ጥያቄዎች ናቸው ።

በእዚኽም ረገድ ፤ የመገንጠል መብት እንደ መዋሐድ መብት ፤ ከዜጎች ፣ ከሰዎች በዛም ከሕዝብ የመምረጥ መብት የእሚቀዳ እንጂ በራሱ የመገንጠል መብት የእሚባል መብት የለም ።

በመርህ ደረጃ ደግሞ ዋና መብቶች ሲከበሩ ከዋናው መብቶች የእሚመነጩ መብቶች በሕግ እስከ አልተከለከሉ ድረስ በተወራራሽነት የእሚከበሩ በመሆናቸው ፤ እንደ ሕገ-መንግሥት ባሉ መሠረታዊ መብቶች በእሚዘረዘሩበት ሰነድ ላይ እያንዳንዱ ቅጂ መብት አይዘረዘርም ።

የዜጎችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት የእሚያከብር ሕገ-መንግሥት ፤ ዜጎች መገንጠልንም ጨምሮ ሌሎች ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን እንዲያደርጉ የእሚፈቅድ በመሆኑ ፤ ቅጂውን የመገንጠልን መብት በልዩ ኹኔታ መዘርዝር በመርህ ደረጃ አስፈላጊ አይደለም ። በሌላ አገላለፅ ፤ የመገንጠል እንቅስቃሴ እንደ ማንኛውም ፖለቲካዊ አጀንዳ ፤ በአንድ ኃሳብ ዙሪያ የመደራጀት እና የፖለቲካ ፓርቲ የመመሥረት መብት ስር የእሚጠቃለል በመሆኑ እና ብልዩ ኹኔታ ‘ለብሔር ፣ ብሔረሰብ እና ሕዝብ’ ወይንም ለነገድ ብቻ የተሰጠ መብት በአለመሆኑ ፤ ከመሰል መብቶች ለይቶ እና ለነገድ ወይንም ‘ለብሔር ፣ ብሔረሰብ እና ሕዝብ’ ብቻ በመወሰን ፤ ለብቻው መደንገዱ ምንም ከጠባብነት እና ከጨለምተኝነት በአሻገር ተጨባጭ ፖለቲካዊ መሠረት እና ፋይዳ የለውም ።

ይኽም በመሆኑ ፤ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ የአሉ፟ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ውጭ ከአሉ፟ ሌሎች ሕዝብ ጋር የመቀላቀል መብት ያለገደብ አላቸው ብሎ ማስቀመጥ ፋይዳ የሌለውን ያኽል ፤ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ የአሉ፟ ማንኛውም ሕዝብ የመገንጠል መብት ያለገደብ አላቸው ማለት ፋይዳ ቢስ ነው ።

የሕዝብ መብት ከዜጎች ዋና መብት የእሚቀዳ መብት በመሆኑ ፤ የዜጎች ዋና ወይንም ተፈጥሮዋዊ ፤ የመምረጥ ዋና መብት ከተከበረ እና አመቺ ኹኔታዎች ከተሟሉ ፤ መገንጠለም መዋኋድም እንደ ታሪካዊ ክስተት እንዲሆኑ ወይንም እንዳይሆኑ መደንገግ መንግሥት ከእሚቋቋምበትም ምክንያት አንፃርም ስናየው ፤ መንግሥት ፦ ልክ ከኢትዮጵያ ጋር የመዋኋድ ፍላጎት የአላቸውን ሕዝብ እየፈለገ ከኢትዮጵያ ጋር ማዋኋድ አንድ ‘ተፈጥሮዋዊ’ የመንግሥት ኃላፊነቱ የአልሆነውን ያኽል ፤ የመገንጠል ፍላጎት የአለውን ሕዝብ በባትሪ እያፈላለጉ የእሚገነጠልበትን ኹኔታ ማመቻቸት የመንግሥት ኃላፊነት ስለ አልሆነ ፤ ይልቁንም ሐገር የመምራት ኃላፊነቱን እንዲይዝ የመረጡትን ሕዝብ አንድነት ማጠናከር ኃላፊነቱ ስለ ሆነ ፤ የመገንጠል መብትን መደንገጉ ምንም አስፈላጊነት የለውም ።

ስለ እዚኽ ፦ የመገንጠልን መብት ያለገደብ በሕገመንግሥት ማረጋገጥ ፤ በእዛኽ ላይ ከብዙ ማሕበራዊ አደረጃጀቶች መሐከል ለነገድ ወይንም ‘ለብሔር ፣ ብሔረሰብ እና ሕዝብ’ ብቻ መስጠት ፦ ተግባራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ፋይዳ የሌለው ፣ ከመርህ አንፃር አስፈላጊ የአልሆነ እና የመንግሥት ልዩ የሥራ ድርሻ በአለ መሆኑ ፤ ከዓለም ሕዝብ ኹሉ በተለየ ፤ እንደ ኢትዮጵያ ባለች ሐገር ሕገ-መንግሥት ውስጥ ይኽን ለማስቀመጥ የእሚያስገድድ አንዳች ፖለቲካዊ ወይንም ሌላ ምክንያት የለም ። በሐገራቸው ውስጥ ከ100 በላይ ነገድ የአለ፟ባቸው ቢያንስ ሐምሳ ሐገራት አሉ በዓለም ላይ ፤ የኢትዮጲያን ከእነ እዚኽ ኹሉ የዓለም ሐግራት ልዩ የእሚያደርጋት ምንም ምክንያት የለም።

ከእዚያኽ በመለስ ግን ፤ የመገንጠል መብት ያለገደብ ማረጋገጥ ፋይዳ ባይኖረውም ፤ ለፖለቲካዊ አለመረጋጋት በር የመክፍት አቅም ስላለው በሕገመንግሥት ውስጥ መካተት የለበትም ።

የእዚኽን ድንጋጌ አፍራሽነት ለመረዳት ፤ የድንጋጌውን ይዘት መረዳቱ ተገቢ ነው ።

በእዚኽም መሠረት ድንጋጌው በመጀመሪያ ፤ ልክ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ፤ ከዜጎች የመምረጥ ተፈጥሮዋዊ መብቶች እንደ እሚመነጨው ፤ የመገንጠል መብት የራስን እድል በራስ መወሰን ከእሚለው ፤ በአንድ አከባቢ ለእሚኖሩ ሕዝብ ከተሰጠው ዓለም ዓቀፋዊ መብት ይመነጫል እንጂ በራሱ የቆመ የመገንጠል የእሚባል መብት የለም ።

በመቀጠል ፤ የመገንጠል መብት የተቀዳበት ፤ የራስን እድል በራስ መወሰን መብት ፤ በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር ላይ በተቀመጠበት አግባብ ፤ ለሆኑ ሕዝብ (ነገዶች ወይንም በኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት መዝገበ ቃላት ‘ለብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች’) የተሰጠ መብት ሰአይሆን በአንድ አከባቢ ለእሚኖሩ እና በነገድ ስብጥራቸው የአልተወሰነ የአንድ አከባቢ ሕዝብ መብት ነው ። በጉዳዩ ላይ የታተመ የአሜሪካን የሰላም ጥናት መዓከል ያሳተመው ሪፖርት እንደ እዚኽ ይላል ፦

“እስካዛሬም ፥ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ለአከባቢ እንጂ ለሕዝብ የተሰጠ መብት አይደለም ።”

“Still, self-determination applied to territories and not to peoples. [42]“

ይኽን መብት ግን በእዚኽ አከባቢ የእሚኖረው ሕዝብ ይኼ ሕዝብ ብቻ ነው በእሚል ተተርጉሞ ፤ አንድ የሆነውን ሕዝብ ይኽን አከባቢ ይዞ የመገንጠል መብት አለው በእሚል ከተተረጎመ ፤ ሕዝብን በእማይጨበጥ የማንነት ትርጓሜ ሕዝብን በሕዝብ ላይ አከፋፍሎ በማነሳሳት ይኽ አከባቢ የእኔ ነው ፥ የእኔ ነው በእሚል በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ፤ የአለመረጋጋት እና የግጭት አረንቋ እንደሚፈጥር ይኸው ሪፖርት ፤ እንደ እዚኽ አስቀምጦታል ፦

“በቅርብ ዓመታት ፤ በሐገራቸው ውስጥ አናሳ የሆኑ ቡድኖች ፤ ‘የራስን እድል በራስ መወሰነን’ እያጣቀሱ ፤ በሐገራቸው ራስ ገዝ ለመሆን ፤ አንዳንድ ግዜም የመገንጠል ጥያቄ እያነሱ ፤ ይኽን ግባቸውን ለመከተል ወደ አመፅ እየገቡ ነው ። … በእዚኽ ጉዳይ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ አመፅ የመፋፋሙ እድል ፤ ራሺያ እና ቻይናን የመሳሰሉ ትልልቅ ግዛቶች በእዚኽ ሊነኩ የእሚችሉ መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ ፤ የበለጠ ትልቅ እየሆነ ይኼዳል ።”

“In recent years, many groups that constitute minorities in their states have invoked the ‘right to self-determination’ in their demands for autonomy – or, in some cases, secession – and have resorted to violence to pursue their aims. … The potential for violence and international instability becomes even more obvious when one considers that some still very large empires, such as Russia and China, are likely to be affected by these movements. [42]“

ከእዚኽ እንደ እምንመለከተው ፤ የራስን እድል በራስ ከመወሰን መብት ፤ የእሚቀዳው የመገንጠል መብት ፤ በኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት ውስጥ የተንፀባረቀበት አግባብ ፤ በተበባበሩት መንግሥታት ድንጋጌ ከተካተተው ውጪ ፤ የአንድ አከባቢ ሰአይሆን የሆኑ ‘ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች’ ነው በእሚለው አንደምታው በመሆኑ ፤ በሐገር ደረጃ ብቻ ሰአይሆን ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ፤ ለዓለም ሕዝብ የደህንነት እና የሰላም ስጋት በሆነበት መልኩ ነው የተቀመጠው ።

ይኽ አንቀፅ 39 በኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት ውስጥ በአለበት አግባብ ፤ ራሺያን እና ቻይናን የእሚያኽሉ ትልልቅ ዓለም ዓቀፋዊ ሚና የአላቸውን ሐገራት ከአሰጋ ፤ ኢትዮጵያንም ሊያሰጋ እንደ እሚችል ምንም ጥርጥር የለውም ።

በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ፤ ለከባቢ የተሰጠን የራስን እድል በራስ መወሰን መብት ለከባቢ ሰአይሆን ለሕዝብ ፣ ዓለም ዓቀፍ እውቅና የሌለውን የመገንጠል መብት እንደ እዚኹ ለሕዝብ ሰጥቶ ፤ ለአሉታዊ ፖለቲካዊ ውትወታ በር መክፈት የአንድ ሕገ-መንግሥት መስረታዊ ዓላማ ጋርም በቀጥታ የእሚቃረን ነው ።

ይኽ እንግዲኽ ከፍ ባለ የፖለቲካ ሳይንስ አስተሳሰብ ስንመዝነው ነው ። የፖለቲካ ሳይንስ ትንታኔውን ትተነው እንደው በአመዛዛኝ አዕምሮም ስናየው አይደለም ሐገር ፤ ትዳር መመሥረት እና ማፍረስ እጅግ በዙ ቅድመ ኹኔታ የእሚፈልግ መሆኑ ግልፅ ነው ።

ይልቁንም ፤ በዘመናት ኺደት እርስ በራሱ የተሳሰረ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ማሕበረሰብ ውስጥ ፤ ብዙ ነገር የእሚጋሩ ነገዶችን ወይንም ‘ብሔሮችን ፣ ብሔረሰቦችን እና ሕዝቦችን’ የፖለቲካዊ ማሕበረሰቡ አደረጃጀት ወይንም የክልል አወቃቀር ማዕከል ከተደረጉ በኋላ ፤ በሕገ-መንግሥት ደረጃ መገንጠል ትችላላችሁ ብሎ መደንገግ ፤ ለኢትዮጵያ ታሪካዊ የውጭ ጠላቶች ሐገር ማተራመሻ ረዥም በትር ማቃበል ነው ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ቢያንስ ለ400 መቶ ዓመታት ያልኖረ ነገድ የለም ። በእዚኽ ረዥም የጋራ የኑሮ ዓመታት ደግሞ ፤ ሰፊ ቁጥር የአለው ከስፍራ ስፍራ የአልተንቀሳቀሰ ፤ የሕብረተሰብ ክፍል የለም ። እንደ እዚኽ በረዥም ዘመን ኺደት በተበወዘ ሕዝብ መሐከል ፤ በወረቀት ላይ አስምረህ በፈጠርኸው ድንበር እና ይኽም የወረቀት ላይ ድንበር የሕዝብን ነገዳዊ አሰፋፈር እና ስብጥር በፍፁም በእማይወክል እና ሊወክል በእማይችልበት ኹኔታ ፤ በሌላ አገላለፅ ፤ የውሸት ድንበር ሰርተህ ፤ እርሱም ሳይበቃህ ፤ ካስፈለገህ ይኽን አወዛጋቢ ድንበር የእኔ ነው ብለህ መገንጠል ትችላለህ ማለት ፤ የሕገ-መንግሥቱ ደጋፊዎች ለማለት እንደ እሚፈልጉት ፤ የመገንጠል አጀንዳ ለእሚያራምድ ፖለቲከኛ ከእዚኽ አጀንዳው እንዲመለስ በማድረግ ነገር የእሚያበርድ ሰአይሆን ፤ ቀቢፀ ተስፈኛውን እና ይኽንን ቀቢፀ ተስፈኛውን ተቀጣሪ ለማድረግ የእሚፈልግ ፀረ-ሰላም ኃይል ወይንም የሐገር ጠላት ለአፍራሽ ተግባሩ የፕሮፖጋንዳ አቅም መፍጠር መቻሉ ግን አሌ የእማይባል ነው ።

አይደለም እንደ ኢትዮጵያ ለአለ፟ ጥንታዊ ሐገር እና በእዚኽም ረዥም ቆይታ በጣም በተሰባጠረ ማሕበረሰብ ውስጥ ይቅርና ፤ አኹን በአሉት ዓለም ዓቀፍ እውቅና በአላቸው ሐገራት ድንበር ላይ ፤ ማንነትን መሠረት የአደረገ የእማያወዛግብ ድንበር መሥራት አይቻልም ።

ስለ እዚኽ ፤ ሐገርን በእምታኽል የብዙ መቶ ዓመታት የደም እና የላብ ስሪት ፤ ማዋቀሪያ ሊሆን የእሚገባው ሰነድ ፤ ነገዶች ይዘው ሊገነጠሉ የእሚችሉትን ድንበር በእማያሻማ መልኩ ሳይወስን (ሊወስንም አይችልም ) ፤ ሐገርን ከህንፃ አቅልሎ ፤ ስንፈልግ እንጋጠማለን ስንፈልግ እንለያያለን ማለቱ ፤ የሐገር ግንባታ ሚናውን በአግባቡ እንዳይወጣ ያደርገዋል ብቻ ሰአይሆን ግጭትን ማበረታቻ አድርጎታል ።

በኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት ላይ ያለንን ትችት ስናጠቃልል ፦ እነ እዚኽን ሦሥት የኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት ስህተቶች ፤ ከመሠረታዊ የሕዝባዊ መንግሥት አስተሳሰብ ጋር አብረው ሊኼዱ የእማይችሉ በመሆናቸው እና የኢትዮጵያን ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ጉዞ የእሚያደናቅፉ በመሆናቸው ፤ ከእነዚኽ እና መሰል ዝበቶች የፀዳ ፤ አዲስ ሕዝባዊ ሕገ-መንግሥት እንደ እሚያስፈልግ ግልፅ ነው ።