ሕ ገ ክ ራ ሲ

marketing-image

4.3.1. የአከላለል መርህ ሐተታ

ይኽ አራተኛው የመጽሐፉ ምዕራፍ ግብ ፤ ከእዚኽ በፊት በቀረቡት ሦሥት የመጽሐፉ ምዕራፎች ውስጥ የተነፀባረቁት ኃሳቦች እና አመክንዮዎች ላይ ተንተርሶ ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀጣይ የፖለቲካ ግብ ሕዝባዊ መንግሥትን እውን ማድረግ ነው በእሚል ፤ ይኽን ሕዝባዊ መንግሥትን የእሚያስችልን ሕገ-መንግሥት ረቂቅ ማቅረብ ነው ።

ይኽ የሕዝባዊ ሕገ-መንግሥት ረቂቅ ግን አኹን በአለ፟ው የሐገሪቱ የክልል አወቃቀር ሊተገበር የእማይችል በመሆኑ ፤ የአኹኑ አከላለል ከሕዝባዊ መንግሥት ርዕዮት አንጻር የአሉበትን ችግሮች ዘርዘረን እና ሕዝባዊ መንግሥትን የእሚያስችል አዲሱ የአከላለል መርህ ምን መምሰል አለበት የእሚለውን ያትታል ።

አንድ የፖለቲካ ኃይል ፤ የፖለቲካ ስልጣንን የእሚፈልግበት እና አንደኛውን የመንግሥት እና የክልል አወቃቀር የእሚመርጥበት አግባብ በእሚከተለው ርዕዮት ይወሰናል ።

እንደ እሚታወቀው የሕዝባዊ መንግሥት ርዕዮት ግብ ፤ ሰዎች በሰብዓዊነታቸው መመዘኛ ብቻ ፤ሐገራቸው ተብሎ በእሚኖሩበት ድንበር ክልል ውስጥ ፦ የቆዳ ቀለም ወይንም የዘር ፣ የነገድ ፣ የጎጥ ፣ የቋንቋ ፣ የኃይማኖት ፣ ወዘተ ፤ ልዩነት ሰአይደረግባቸው ፤ ኢከነሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጥቅማቸውን ፈልገው ማግኘት እንዲችሉ ምህዳሩን ማመቻቸት እና ዜጎችን ማገዝ የእሚል ነው (Enabling the citizens’ pursuit and realization of economic and political goods without discrimination) ።

በሌላ አገላለፅ ፤ የሕዝባዊ መንግሥት አስተሳሰብ ፤ ከባሕል ፣ ከኃይማኖት ወይንም ከቋንቋ ብዝኃነት ጋር ችግር የሌለው ቢሆንም እነ እዚኽ ብዝኃነቶች (Diversities) ግን የዜጎችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመጫን ፤ የዜጎችን ኢከነሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት በእማይጎዱበት መልኩ መካኼድ አለባቸው ወይንም የዜጎችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት ከባህላት ሕልውና በፊት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል የእሚል ነው ።

በተቃራኒው ለፅንፈኛ የማንነት ፖለቲካ ወይንም የነገዳዊ ብሔርተኛ ርዕዮት ተከታዩ ደግሞ ፤ ዋነኛ የፖለቲካ ግቡ ፤ ‘የባህል ፣ የቋንቋ እና የነገዳዊ ልዩነቶችን ህልውና’ ማቆየት የእሚል ግብ የያዘ በመሆኑ ፤ የእነ እዚኽን ብዝኃነቶች ህልውና ለማቆየት ሲባል የዜጎች ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ግብ መሰዋት ከአለ፟በት ለመሰዋት ዝግጁ ነው ።

አኹን በኢትዮጵያ ውስጥ የአለ፟ው ክልል አከላለል እና የቋንቋ ፖለቲካ ፤ በእዚኽ መሰሉ በፅንፈኛ የነገድ ብሔርተኝነት ርዕዮት እየተመራ ፥ ነገዶችን የክልል ባለቤት በማድረግ ነገዳዊ ብሔርተኝነትን የስልጣን ምንጭ እና ግብ እንዲሆን በእሚል እሳቤ የተሰራ በመሆኑ ፤ ከሕዝባዊ ግብ አንጻር የእሚከተሉት አራት ችግሮች አሉበት ።

የመጀመሪያው ፤ ምንም እንኳን ሕገ-መንግሥቱ ነገዶችን የእየ ራሳቸው ክልል ባለቤት ማድረግ ዋነኛ የፖለቲካ ግቡ ቢሆንም ፤ ነገዶችን የእየ ራሳቸው ክልል ባለቤት የማድረጉን ጉዳይ በወጥነት እና በፍትኃዊነት ስለ አልተከተለ ፤ 80 ነገዶች በአሉበት ሐገር የተመረጡ 8 ነገዶዎች ብቻ ናቸው የራሳቸው ክልል ባለቤት እንዲሆኑ የአደረገው ።

ይኽም በመሆኑ ወደ 70 የእሚደርሱት ወይንም 90% የእሚሆኑት የሐገሪቱ ነገዶች ፤ በእነ እዚኽ ‘ትላልቅ’ ክልላት ውስጥ ጥገኛ ወይንም ደባል ሆነው እንዲኖሩ የአደረገ ነው ። ይኽም ቀደም ብለን እንደ አሳየነው ፤ በሕገ-መንግሥቱ መሠረታዊ ባሕሪ ምክንያት ፤ ከእነ እዚኽ ክልል አልባ ነገድ ተወላጅ የሆኑ በሚልዮን የእሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ለዲሞክራሲያዊ እና ኢከነሚያዊ መብት ገፈፋዎች (disfranchisement) ተጋላጭ እንዲሆኑ የአደረገ ነው ።

በኹለተኝነት ፤ በሕገ-መንግሥቱ መሠረታዊ ባሕሪ ምክንያት ፤ ከክልል አልባ ነገድ የተወለዱ ዜጎች ብቻም አይደሉም ለዲሞክራሲያዊ እና ኢከነሚያዊ መብት ገፈፋዎች (disfranchisement) ተጋላጭ የሆኑት ፤ ይልቁንም ከባለ ክልል ነገዶችም ተወልደው ፤ በእዚኽ ሕገ-መንግሥት አግባብ ለነገዳቸው ከተቸራቸው ክልል ውጭ የእሚኖሩ ዜጎችም ናቸው ።

ነገዶችን የክልል ባለቤት በማድረግ ነገዳዊነት የስልጣን ምንጭ እና ግብ እንዲሆን የአደረገው ይኽ ሕገ-መንግሥት በተለያየ መልኩ አስቀድመን እንደ አልነው ፤ በሕዝባዊ መንግሥት አስተሳሰብ ውስጥ ፤ ዜጎች በመላ የሐገራቸው ክፍል በነጻነት የመንቀሳቀስ ፣ የመነገድ ፣ ኑሮ የመመሥረት እና በእሚኖሩበትም በእዚኽ አከባቢ ፤ ምንም ዓይነት ፦ የቆዳ ቀለም ፣ የዘር ፣ የነገድ ፣ የባህል ፣ የቋንቋ ፣ የኃይማኖት ፣ ወዘተ ፤ መድሎ ሳይደረግባቸው ፤ ለአከባቢ ሆነ ለሐገር መንግሥት በመራጭነት እና በተመራጭነት መሳተፍ ይችላሉ ፤ የእሚሉትን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጋር የእሚቃረን በመሆኑ ፤ ክልሎቹ አኹን በአሉበት አቋም ፤ የሕዝባዊ መንግሥትን በሐገር ደረጃ እውን ማድረግ አይቻልም ።

ይኽ የአኹኑ አከላለል ግን ፤ በሚልየን የእሚቆጠሩ ዜጎች ድምፅ መምከን እና ኢከነሚያዊ ማዕቅብ ውስጥ ማስቀመጥን በማስከተሉ ምክንያት ብቻ አይደለም ፤ ከሕዝባዊ መንግሥት አስተሳሰብ ጋር ተጻራሪ የሆነው ወይንም አኹን በአሉበት ቁመና ክልሎቹን ከነገድ ጎጥኝነት በሕዝባዊ ሕገ-መንግሥት መርሕ ብናላቅቃቸው ራሱ አኹን በአሉበት ቁመና ሕዝባዊ መንግሥትን የእሚያስችሉ አይደሉም ።

በእዚኽ ረገድ የመጀመሪያው ጉዳይ ፤ በክልሎቹ መሐከል ከፍተኛ አለመመጣጠን መኖሩ ፤ ክልሎች በመዓከላዊ መንግሥት ላይ የእሚኖራቸውን ተሳትፎ እጅግ የተዛባ እንዲሆን ማድረጉ ነው ። በጠቅላላው 547 ወንበር በአለው የሐገሪቱ ፓርላማ አንዳንዶቹ የሐገሪቱ ክልሎች ከ120 በላይ መቀመጫ የአላቸው ሲሆኑ ቀላል የእማይባሉት ክልሎች ደግሞ ከ40 በታች ወንበር የአላቸው ናቸው ፤ ይኽም አናሳዎቹን ክልሎች በጥቂት ትላልቅ የሐገሪቱ ክልሎች ላይ ተንጠልጣይ እንዲሆኑ በማድረግ ከፍተኛ የስልጣን መዛባት የእሚፈጥር ነው ።

ከእዚኽም በአሻገር ፤ አከላለሉ የሕዝባዊውን መንግሥት ግብ ታሳቢ ያልአደረገ በመሆኑ ፤ በሐገር ዓቀፍ ደረጃ ኢፍትኃዊ የሰው ኃብት እና ቁሳዊ ክፍፍል በእየ ክልሎቹ የፈጠረ ነው ። በአንዳንዶቹ ክልሎች የሰው ኃይሉ እና የተፈጥሮ ኃብቱ ተሰብስቦ ፤ ሌሎቹ ክልሎች ደግሞ በነገዳዊ ራስ ገዝነት ስም ጥግ ላይ ሆነው በሰው ኃብት እና በተፈጥሮ ኃብት የተመናመኑበት ነው ።

በእዚኽም የአልተመጣጠነ የሰው እና የቁስ ኃብት ክፍፍል ፤ የክልል መንግሥታትን እና ፌደራላዊ ተሳትፎዋቸውን ብቁ እና ውጤታማ ማድረግ አይቻልም ።

ይኽም በመሆኑ ፤ ከሕዝባዊ መንግሥት ሊገኝ የእሚገባውን ጥቅም ለማግኘት ፤ የተለየ ያከላለል መርሆችን መሠረት የአደረገ አከላለል እንደ እሚያስፈልግ ግልፅ ነው ።

አዲሱ የአከላለል መርህ ፤ ከአዲስ አበባ በስተቀር በአሉት ክልሎች ፤ የእሚከተሉትን የአከላል መርኽ ታሳቢ የአደረገ መሆን ይኖርበታል ፦

  1. መጀመሪያ በክልሎች መሐከል ተመጣጣኝ የሕዝብ ቁጥር መኖሩን ፣
  2. የከተሞችን የኢከነሚ እና የፖለቲካ ስበት መዓከልነት ፣
  3. የየክልል መንግሥታትን አፈፃፀም ብቃት ማሳደግን

ታሳቢ የአደረገ መሆን አለበት ።

ይኽን ደግሞ በቀላሉ ማሳካት የእሚቻለው ፤ በአኹኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ውስጥ መቶ ሺ እና ከእዚያኽ በላይ ሕዝብ ያለባቸውን ከተሞች ፤ አዲስ የእሚፈጠሩት ክልሎች ማዕከል አድርጎ በመጀመር ነው ።

ይኽን በማድረግ መጀመር ተገቢ የእሚሆንበትም ምክንያት ፤ የሐገሪቱ ትልልቅ ከተሞች የተማረ የሰው ኃይል እና የኢከነሚ ካፒታል መዓከል በመሆናቸው እና በተፅዕኖ ክልላቸው የአለውን የሰው እና የቁስ ኃብት በቀጣይነት የመሳብ አቅም ስለ አላቸው ፤ ይኽ አቅማቸው ለሕዝባዊ መንግሥት መቀመጫነት ውጤታማ ስለ እሚያድርጋቸው ነው ።

በእርግጥ አንዳንድ የሐገሪቱ አከባቢዎች ፤ ትላልቅ ከተሞች ተቀራርበው የእሚገኙበት ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ መሰል መቶ ሺ እና ከእዚያኽ በላይ ነዋሪ የአሉ፟ባቸው ከተሞች የሌሉበት በመሆኑ ፤ በእዚኽ አካኼድ ኹሉንም የሐገሪቱን ክልሎች ማዳረስ እንደ እማይቻል ግልፅ ነው ። ነገር ግን ፤ በእዚኽ አካኼድ አባዛኛውን እና ከ70 በመቶ በላይ የኾነውን የሐገሪቱን ክፍል ማካለል ይቻላል ።

በእዚኽ መርህ ሳይካለሉ የእሚቀሩትን አከባቢዎች ፤ ውጤታማ ሕዝባዊ መንግሥትን ለዜጎች በፍትኃዊነት ማድረስ የእሚለውን ሐገራዊ ግብ እንደ ጠበቀ ፤ እንደ አመቺነቱ እና እንደ አዋጭነቱ ፤ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በማስተሳሰር ፣ ከአጎራባች ጠንካራ ክልሎች ጋር በማስተሳሰር ፣ የከተማ አስተዳደር በማድረግ ፣ ወዘተ ፤ ማዋቀር ይቻላል ።

ዋናው ጉዳይ ፤ አከላለሎች በሙሉ የእሚከተሉትን ውጤቶች ታሳቢ ማድረግ አለባቸው ፦

  • ክልሎች ውጤታማ ሕዝባዊ ክልላዊ አስተዳደር ለመመሥረት የእሚያስፈልገው የሰው እና የቁስ ኃብት ማግኘት የእሚችሉ መሆናቸውን
  • የክልሎች የሕዝብ መጠን በሐገር ዓቀፍ ደረጃ ተመጣጣኝ ሆኖ ፤ በየትኛውም የሐገሪቱ ክልል ፤ በፌደራል መንግሥት ደረጃ ተመጣጣኝ ድምፅ እንዲኖረው መቻሉን
  • የክልሎች መጠን በጣም ሰፍቶ ፤ የክልል መንግሥታትን ውጤታማነት የእሚቀንስ እንዳይሆን ። በተመሳሳይም ክልሎች በጣም አንሰው ፤ የክልል መንግሥታት በውድነታቸው ምክንያት የበጀት ገደል በመሆን አላስፈላጊ አለመሆናቸውን ።

ይኽን አካኼድ ስንከተል ፤ በአማካይ ኢትዮጵያው ውስጥ ከ10 እስከ 14 የእሚሆኑ ክልሎች የእሚኖሩ ሲሆን ። እንደ አማራ እና ኦሮሚያ ያሉ ትልልቅ ክልሎች ሦሥት እና አራት ቦታ የእሚከፈሉ ይሆናል ።

እንደ አፋር ፣ ሐረር ፣ ቤንሻንጉል እና ጋምቤላ ያሉ ክልሎች ደግሞ የእሚታጠፉበት ፣ ከፌደራል ወይንም ጠንካራ አጎራባች ክልሎች ጋር የእሚዳመሩበት ፣ ልዩ ወካይ ወይንም የከተማ አስተዳደር የእሚሆኑበት ኹኔታ ይፈጠራል ።

ይኽ ሲሆን ግን ፤ በየትኛውም የሐገሪቱ አከባቢ የእሚኖር ዜጋ ፤ ተመጣጣኝ እና የተሻለ ብቃት የአለው የክልል መንግሥት ሲያገኝ ፤ በአከባቢ እና በፊደራል መንግሥት ውስጥ የእሚኖረው ውክልና እና ተጠቃሚነትም ፤ በእዚያው መጠን ተመጣጣኝ እና የተሻለ ስለ እሚሆን አትራፊ ይሆናል ።

በአጠቃላይ ዜጋው በዜግነቱ ፤ ከሌላው አከላለል ኹሉ በተሻለ ኹኔታ ፤ በክልል እና በፌደራል መንግሥት ውስጥ ሚና ይኖረዋል ከእዚያኽም በተጨማሪም የተሻለ ብቃት እና የማስፈፀም አቅም የአለው ክልላዊ እና ፌደራላዊ መንግሥት ያገኛል ።

የአኹኑ አከላለል አራተኛው እና መሠረታዊ ችግር ፤ በሕገ-መንግሥቱ ነገዳዊነት ሳቢያ በሐገር ዓቀፍ እና በክልል ደረጃ የቋንቋን ፖለቲካ ፅንፈኝነት የእሚፈቅድ በመሆኑ ፤ የቋንቋ ፖለቲካ ፅንፈኞች ፤ በሐገር ዓቀፍ ደረጃ መግባባትን የእሚያስችል አንድ ብሔራዊ ቋንቋ የመከተልን አካኼድ እንደ መብት ረገጣ የእሚያዩበትን ኹኔታ በመፍጠሩ ፤ አከላለሉ ከቋንቋ ጋር የአለው ትስስር ካልተበጠሰ ሕዝባዊ መንግሥትን ማስቻል የእሚቻል አይደለም በአለበት ኹኔታ ።

አንዲትን ዴሞክራሲያዊት ወይንም ሕዝባዊት ሐገር ፤ ያለ ብሔራዊ ቋንቋ ማሰብ ወይንም ወደ እውን ማምጣት አይቻልም ። ሐገርን በመንፈሳዊነት ወይንም በስነ ልቦና አስተሳስሮ ማቆም የእሚችለው ፤ ሰዎች በተለያየ ጉዳይ ላይ በጋራ በእሚግባቡበት ቋንቋ ተነጋግረው ፤ ወደ አንድነት ሰአይኾንም ወደ ብዙነት (Majority) መምጣት ሲችሉ ነው ።

እንደ ባቢሎን ብዙ ቋንቋ እየተነጋገሩ ፤ አንዱ አካፋ ሲል ሌላው ሲምንቶ እያለ አንዲትን የፖለቲካዊ ኢከነሚ ማሕበረሰብ በጋራ መገንባት አይቻልም ።

አንዳንድ ሰዎች ፤ በእልኽ እና በፅንፈኛ የማንነት ፖለቲካ ተቀርፀው ፤ የብዙ ቋንቋ ተናጋሪ የኾነ ማሕበረሰብ መፍጠር አለብን ብለው እንደ እሚያምኑት ፤ ኢትዮጵያን በእምታኽል የመቶ ሚልዮን እና በእየግዜው ከእዛኽ እየጨመረ የእሚኼድ ሕዝብ በአለባት እና በተለያዩ የሐገሪቱ አከባቢዎች ሰፊ ባሕላዊ ፣ ማሕበራዊ እና የቋንቋ ልዩነት በእሚስተዋልባት ሐገር ፤ ብዙ ቋንቋዎችን ብሔራዊ ቋንቋ ማድረግ አይቻልም ።

በእርግጥ ሐገራት በቁጥር ጥቂት ሕዝብ መኖሪያ በእሚኾኑበት እና ከአንድ ቋንቋ በላይ ተናጋሪ ሕዝብ በእሚኖራቸው ግዜ ፤ መሐበረሳባዊ ቅርርቡ እና ትስስሩ በመላ ሐገሪቱ አብዛኛውን የማሕበረሰብ ክፍል እነዚኺን ቋንቋዎች በተመሳሳይ ኹኔታ ተናጋሪ በእሚያደርግበት እና ማሕበረሰቡ ምንም ሳይቸገር ፤ በኹሉም ቋንቋ በጋራ መግባባት በእሚችልበት ግዜ ፤ በእዛኽች ሐገር አንድ ቋንቋ ብቻ የእሚነገርበትን ያኽል ሰዎች በብዙ ቋንቋ መግባባት ስለ እሚችሉ ወይንም የብሔራዊ ቋንቋ ብዝኃነቱ (Diversity) ለመግባባት ጋሬጣ ስለ እማይኾን ፤ ብዙ ቋንቋዋዎች በአዋጅ ሰአይኾን በማሕበራዊ መስተጋብር በጋራ Lingua Franca ወይንም የፍራንኩ[1] ቋንቋ ስለ እሚኾኑ ፤ የቋንቋ ብዝኃነቱ የጋራ ፖለቲካዊ ኢከነሚ የመፍጠሩን ኺደት በአያግዝም አያስተጓጉልም ።

በእዚኽ ኹኔታ እንኳን የፍራንክ ቋንቋው ፤ ከኹለት ቢበዛ ከሦሥት መብለጥ አይችልም ወይንም የለበትም ፤ ምክንያቱም መደበኛው ዜጋ በተፈጥሮ ብዙ ቋንቋ የመናገር ፍላጎት ፣ ይኽንም አስፈላጊ የእሚያደርግበት ተፈጥሮዋዊ ኹኔታ እንዲኹም ብዙ ቋንቋን በቀላሉ የመናገር ክህሎት የሌለው በመሆኑ ። ይኽም ብቻ ሰአይሆን ብዙ ቋንቋዎችን ብሔራዊ ቋንቋ ማድረጉም በመንግሥት በጀት እና አሰራር ላይ የእሚፈጥረው የቢሮክራሲ ጫናም ቀላል አይደለም ብቻ ሰአይሆን መንግሥትን ከዋናው ኃላፊነቱ በማቦዘን መንግሥትን ማዝበጥ የእሚችል ነው።

እንደ ኢትዮጵያ በአሉ ፤ የተለያየ ቋንቋ የእሚነገርባቸው የተለያዩ አከባቢዎች በአሉበት እና ዜጎችን ከእሚኖሩበት አከባቢ የተነሳ እነዚኽን ከአስር የእማያንሱ ቋንቋዎች እንዲያውቁ የእሚያስችላቸው ምንም ማሕበራዊ እና ኢከነሚያዊ ምክንያት በሌለበት ፤ የማንነት እኩልነት ይረጋገጥ በእሚል ኹሉም ሰው በወርቅ ሰኃን መብላት አለበት እንደ ማለት ያኽል ፤ ኢትዮጵያን በእምታኽል ትልቅ እና የብዝኃን ስብስብ ላይ ፤ አራት እና አምስት ወይንም ከእዚያኽ በላይ ቋንቋዎች የፍራንክ ቋንቋ በእኩልነት ይኹኑ ማለት ፤ ከመሠረተ ቢስ ምኞትነት በአሻገር ፤ በተግባር ላይ ቢውል ማሕበራዊ እና ኢከነሚያዊ እድገትን አንቆ በመያዝ ፤ ሐገርን ለአለመረጋጋት ፣ ለመብት ጥሰት ፣ ለኋላ ቀርነት የእሚያጋልጥ የፅንፈኝነት አጀንዳ እንደ እሚሆን ብዙም ጥርጥር የሌለው ነው ።

ይኽን መሰሉ ጠባብ የቋንቋ ፅንፈኝነት ይኽን የአደናቃፊነት ሚናውን እንደ አይጫዎት ፤ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ታግሎ ፤ በኢትዮጵያ ኹኔታ ወይንም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ትልቅ እና ሰፊ ብዝኃነት (Diversity) በያዙ ሐገራት ፤ ለማሕበራዊ እና ኢከነሚያዊ እድገት ተገቢ የኾነ አንድ ብሔራዊ ቋንቋ የግድ አስፈላጊ ነው የእሚለው ኃሳብ ሰፊ ሕዝባዊ ድጋፍ እንዲያገኝ እና በሕዝብ ተቀባይነት እንዲኖረው መንግሥት መሥራት አለበት ።

በእርግጥ ይኼ ፤ በሐገሪቱ ውስጥ የእሚገኙ ብዙ ቋንቋዎች ከመጨፍለቅ እና የተለያዩ የሐገሪቱ ሕዝብ በቋንቋቸው እንደ አይማሩ ፣ እንደ አይዳኙ ፣ እንደ አይናገሩ ፣ ቋንቋቸውን እንደ አያሳድጉ ከማድረግ የቋንቋ ጨፍላቂነት ጋር መምታት የለበትም ።

ከላይ በአስቀመጥነው የአከላል መርኽ ውስጥ ተካለው የእሚገኙ ማናቸውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ፤ የክልላቸው መንግሥት አቅምና የሕዝቡ ስብጥር እስከ ፈቀደው ድረስ ፤ በክልላቸው የመረጡትን ቋንቋ ከብሔራዊ ወይንም ከፍራንኩ ቋንቋ እኩል እና በተጨማሪ ፤ የሥራ ፣ የትምሕርት እና የዳኝነት ቋንቋ ሊያደርጉት ይችላሉ ።

በእዚኽ ኹኔታ ውስጥ ግን ፤ አንድ ብሔራዊ ቋንቋ ፤ በኹሉም የሐገሪቱ ክልል የእሚታወቅ ፣ የእሚነገር ፣ ዜጎች የእሚዳኙበት ፣ ኃሳባቸውን የእሚያቀርቡበት መኾን አለበት የእሚለውን ግን መፃረር የለበትም ።

የአንዲት ሉዓላዊት ሐገር የቋንቋ ፖሊሲ ይኽን ካልመሰለ ፤ አንድ የበለፀገ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ለመገንባት የእሚደረገውን ጥረት ኾን ብሎ እያስተጓጎሉ ፤ ለምን ሐገራዊ ማሕበራዊ እና ፖለቲካዊ እድገት ወደ ፊት መራመድ አቅቶት ፤ በግጭት ፣ በሴራ ፣ በሳቦታጅ ፣ ወዘተ ፤ እንደ እሚጨናገፍ ቁጭ ብሎ መወያየት ነው ።

ስለ እዚኽ ፤ በኢትዮጵያ ኹኔታ አንድ ብሔራዊ ፤ የትምህርት ፣ የሥራ ፣ የዳኝነት ፣ ወዘተ ፤ ቋንቋ ኖሮ ፤ ይኽ የፍራንክ ቋንቋ ግን ፤ ከላይ በተባለው መርኽ መሠረት በእሚካለሉ ክልሎች ውስጥ ፤ በእየ ክልሉ ባሉ ሕዝብ ስብጥር እና የክልሉ መንግሥት አቅም እና የክልሉ ሕዝብ ፍላጎት ፤ ተጨማሪ አንድ ቢበዛ ኹለት ቋንቋዎችን ፤ ከፍራንኩ ቋንቋ በተጓዳኝ እና በእኩልነት የክልሉ የሥራ ቋንቋ ማድረግ ይቻላል ።

የአኹኑ ሐገራዊ አከላለል ችግሮች እና እንዴትም መሻሻል እንደ አለበት ይኽን ከአልን ፤ በእዚኽ ‘ቁሳዊ’ ሐገራዊ ምህዳር ውስጥ ሕዝባዊነትን የእሚያስችለውን ሕገ-መንግሥት ንድፍ እንመልከት ።

  1. ምንም እንኳን የፍራንኩ ቋንቋ ቀጥተኛ ትርጉሙ የፍራንኮች ወይንም የፈረንጆቹ ቋንቋ ቢሆንም ፤ የፍራንኩ ቋንቋ ማለት የተለያየ ቋንቋ ያላቸው ሰዎች በጋራ ለመግባባት የእሚጠቀሙበት ቋንቋ ማለት ነው ። የአማርኛው ሰም እና ወርቅም ጋር አያይዘነው ፤ የንግድ ወይንም የፍራንኩ ቋንቋም ብንለው የእሚያስክኼድ ይመስለኛል ። ↑