ሕ ገ ክ ራ ሲ

marketing-image

4.3.2. የሕዝባዊ ሕገመንግሥት ንድፍ

ለመነሻ የእሚሆን ፤ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ መንግሥት ሕገመንግሥት ንድፍ

መግቢያ

እኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፤ ሐገራችን ኢትዮጵያን ፦ በእዚኽ ሕገመንግሥት ውስጥ በክፍል አንድ ላይ የተዘረዘሩት ፤ የዜጎች ተፈጥሯዊ መብቶች ፤ ያለ ምንም ልዩነት ለኹሉም ዜጎች በእኩልነት የእሚከበሩባት እና ያለ ሕግ አግባብ ፤ መንግሥትን ጨምሮ በማንኛውም ኃይል ፤ እማይገፈፉባት ፤ ሐገር እንድትሆን እና ኹላችንም በብሔራዊ አንድነት ስሜት ተነሳስተን ጠንካራ እና ዘመናዊ ማሕበረ ኢከነሚ በመገንባት ሐገራችንን ኢትዮጵያን ከዓለም ቀዳሚ ስልጣኔዎች ጎራ ለማሰለፍ እና ለማቆየት እንዲኹም የሐገራችንን ደህንነት እና ልማት ከውስጥም ከውጭም ጠላት ለመከላከል ያስችለን ዘንድ ፤ ይኽን ሕገመንግሥት ፤ የሐገራችን ሕገመንግሥት አድርገን አቁመናል።

ክፍል 1

የዜጎች ተፈጥሯዊ መብቶች ዝርዝር


  1. በእዚኽ የመብት ሰነድ ውስጥ የእሚዘረዘሩ መብቶች ፤ ለኹሉም ኢትዮጵያውያን ፤ እንደ ፦ ዘር ፣ የቆዳ ቀለም ፣ ጾታ  ፣ ቋንቋ ፣ ኃይማኖት ፣ ፖለቲካዊ ወይንም ሌላ ዕምነት በመያዝ ፣ በመጡበት ነገድ ወይንም ማሕበረሰብ ፣ ባላቸው የንብረት መጠን ፣  የትውልድ ኹኔታ ወይንም ሌላ ማንኛውም መደብ ወይንም ደረጃ ሳይገደቡ ፤ ኹሉም ኢትዮጵያውያን ሰው ሆነው በመፈጠራቸው በእኩልነት የተጎናጸፏቸው መብቶች ናቸው።
  2. የሰው ክቡርነት መብቶች ፦
    1. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፦ ሕይወቱን ያለ ምንም ስጋት በነጻነት እና በመተማመን የመኖር መብቱ የተጠበቀ ነው። 
    2. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በባርነት ሊያዝ ፣ ሊያድር እና ሊሸጥ አይችልም።
    3. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፤ መንግሥትን ጨምሮ በማንም ጥበቃ ሥር በእሚሆንበት ግዜ ፤ ከእሚያሰቃይ እና ክብሩን ከእሚነካ ኢሰባዊ አያያዝ የመጠበቅ መብቱ የተከበረ ነው።
    4. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፤ ግለሰባዊ ሰውነቱ ፣ ነጻነቱ እና ንብረቱ ክቡር በመሆኑ ፦ እራሱን ጨምሮ ፥ ንብረቱ እና መኖሪያ ቤቱ ፣ በጽኹፍ ወይንም በድምጽ የእሚያደርጋቸው ግንኙነቶቹ ፤ ከፈቃዱ ውጭ ፤ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ፤ በግለሰብ እና በንዑስ ቡድን ደረጃ ፤ በማንም ሊበረበር አይችልም።
  3. በሕግ ፊት እኩል የመታየት መብት
  4. ኢትዮጵያውያን በሙሉ ፤ በነጠላ ወይንም በቡድን በሕግ ፊት በእሚቀርቡበት ግዜ በዜግነታቸው ብቻ በሕግ ፊት ያለ ምንም ልዩነት በእኩልነት ይታያሉ። 


4. የሕግ ከለላ መብቶች

  1. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፤ በእዚኽ የመብት ዝርዝር ውስጥ የተዘረዘሩት መብቶቹ ፤ ከሕግ አግባብ ውጭ ቢገፈፉበት ፤ ተመጣጣኝ ካሳ የማግኘት መብት አለው።
  2. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፤ ያለ ሕግ አግባብ ፦ በቁጥጥር ስር ሊውል ወይንም ለእስር ሊዳረግ አይችልም። 
  3. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፤ በምንም ምክንያት ፤ ዜግነቱን ፤ ያለፈቃዱ በሕግ ሊገፈፍ ወይንም ከሐገር ሊባረር አይችልም።
  4. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፤ በመንግሥት ፦ በቤትኽ ወታደር አሳድር ፣ ወታደር ቀልብ ወይንም ለመንግሥታዊ አገልግሎት ፤ በሕግ ከተደነገጉ ፦ ግብሮች ፣ ቀረጦች ፣ ወዘተ ውጭ ፤ ክፍያዎችን ወይንም ግልጋሎቶችን አቅርብ ሊባል አይችልም።
  5. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፤ መጠናቸው እና ዓይነታቸው በሕግ የተወሰኑ ፤ የነፍስ ወከፍ ጠብ መንጃዎችን እና ሽጉጦችን ፤ የሕግ መወስኛው ቤት ፤ በሕግ ወይንም የሐገሪቱ ርዕሰ ብሔር (ፕሬዝደንት) ከሕግ መወሰኛው ክልከላ ጋር በእማይጋጭ ፤ በተጻፈ ትዕዛዝ ፤ ከመኖሪያ ቤቱ ውጭ ባሉ ፤ በአዋጅ ከእሚከለክሏቸው ቦታዎች በስተቀር ፤ እራሱን ፣ መኖሪያ ስፍራውን እና ንብረቱን ከድንገተኛ አደጋ ለመከላከል የመታጠቅ መብት አለው።
  6. የተከሳሽ መብቶች
  7. እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በእሚከሰስበት ግዜ ፤ በእዚኽ ሕገመንግሥት አግባብ ፤ በሕዝብ ምርጫ የተቋቋመ መንግሥት ባቋቋመው ፤ ነጻ እና ገለልተኛ ፍርድ ቤት ፤ በሕዝብ ምርጫ የተቋቋመው ሕግ አውጭው ባጸደቀው ሕግ አግባብ የመዳኘት መብቱ የተጠበቀ ነው። 
  8. አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ላይ በፍርድ ቤት ክስ ከመመስረቱ በፊት ፤ ክሱ ኹለት ዓመት እና ከእዚያ በላይ በእስር ሊያስቀጣ የእሚችል ከሆነ  ፤ ከ16 እስከ 24 አባላት ባሉት ፤ ተከሳሹ የተከሰሰበት ፍርድ ቤት ፤ በእሚገኝበት የምርጫ ክልል ፤ ምርጫ ከመረጡ ዜጎች መካከል በዕጣ ተመርጠው በእሚመጡ ፤ የዜጎች የክስ መርማሪ ቡድን ፤  ክሱ ተመርምሮ ፤ ዜጋው ሊከሰስ ይችላል የእሚለው ፤ በእነ እዚኽ የዜጎች የክስ መርማሪ ቡድን በ3/4ኛ ድምጽ መጽደቅ አለበት። 
  9. በዜጋው ላይ ክስ ከተመሰረተበትም በኋላ ፤ ዜጋው የተከሰሰበት ክስ ኹለት ዓመት እና ከእዚያ በላይ በእስር ሊያስቀጣ የእሚችል ከሆነ ፤ እንደ እዚኹ ፤ ተከሳሹ ፤ ክሱ በተመሰረተበት ፍርድ ቤት የምርጫ ክልል ፤ ምርጫ በመረጡ እና በእጣ ተመርጠው በእሚመጡ 12 የዜጎች የዳኝነት ቡድን ወይንም መንግሥት በእሚሾመው ዳኛ መርጦ የመዳኘት መብት አለው።
  10. ማንኛውም የተከሰሰ ኢትዮጵያዊ ፤ በነጻ እና ገለልተኛ ፍርድ ቤት ተዳኝቶ ጥፋተኛ ሆኖ እስከ አልተገኘ ድረስ ፤ ነጻ ዜጋ ነው።
  11. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የእሚከሰስበት የሕግ አንቀጽ ፤ የተከሰበት ጥፋት ከተፈጸመ በኋላ በጸደቀ የሕግ አንቀጽ ሊሆን አይችልም።
  12. ማንኛውም የተከሰሰ ኢትዮጵያዊ ፤ ፤ በፈቃዱ ራሱ ለመወከል በመፈለግ ለፍርድ ቤት ጠበቃ አልፈልግም ብሎ  በእሚያስታውቅበት ግዜ በስተቀር ፤ ያለ ጠበቃ ሕግ ፊት መቅረብ ስለሌለበት ፤ የራሱን ጠበቃ ማቆም እንደ እማይችል በፍርድ ቤቱ ከተረጋገጠ ፤ ከመንግሥት ጠበቃ የማግኘት መብት አለው።
  13. በግዜያዊነት በመንግሥት በቁጥጥር ስር ውስጥ የገባ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፤ በ48 ሰዓት ፍርድ ቤት ቀርቦ ክስ ሊመሰረትበት ይገባል ፤ ያ ሊሆን ካልቻለ ፤ ከ48 ሰዓታት በኋላ ከእሥር መለቀቅ አለበት።
  14. አንድ ኢትዮጵያዊ በሕግ ጥፋተኛ ሆኖ ሲገኝ ፤ የእሚበይንበት ቅጣት በተከሳሹ እና በንብረቱ ላይ ብቻ የተወሰነ ሆኖ ፤ ቅጣቱ ፤ በጥፋቱ ተሳታፊ ያልሆኑ ፦ የቤተሰብ አባሎቹን ፣ ወዳጆቹን ፣ የንግድ ወይንም የሥራ አጋሮችን ሰውነትም ሆነ ንብረት ሊነካ የእሚችል መሆን አይችልም።
  15. በሐገሪቱ በሕዝብ ምርጫ በተቋቋመው ሕግ አውጭ አካል ፤ በወጣ ሕግ ፤ የዋስትና መብት በእሚያከለክል ክስ ከተከሰሱ ዜጎች ውጭ ፤ ኹሉም የተከሰሱ ዜጎች ያልተጋነነ ዋስትና አቅርበው በዋስ የመለቀቅ መብት አላቸው።
  16. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በእራሱ ላይ እንዲመሰክር አይገደድም።
  17. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በአንድ ጥፋት ኹለት ግዜ ተከሶ ሊቀጣ አይችልም።
  18. በእስር ላይ የእሚገኝ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፦ በቤተሰቦቹ ፣ በወዳጆቹ ፣ በጠበቃዎቹ እና በሌሎች ሰብዓዊ እንቅስቃሴ በእሚያደርጉ ተቋማት የመጎብኘት መብቱ የተጠበቀ ነው።


  1. ፍላጎትን የመከተል መብቶች 
    1. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፤ በፈለገው የሐገሪቱ አከባቢ በማንኛውም ግዜ ፤ የመንቀሳቀስ ፣ የመኖር እና የመሥራት መብቱ የተጠበቀ ነው። 
    2. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፤ ከ2 ዓመት በላይ ነዋሪ በሆነበት ክልል ፤ የነዋሪነት ዕውቅና የማግኘት መብቱ የተከበረ ነው። 
    3. አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ፤ በአንድ ግዜ ፤ ከአንድ የኢትዮጵያ ክልል በላይ በነዋሪነት መታወቅ አይችልም።
    4. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በፈለገው ሰዓት ከሐገር የመውጣት እና ወደ ሐገር ውስጥ የመግባት መብቱ የተጠበቀ ነው። 
    5. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፤ የቤተሰብ ሕጉ በእሚፈቅደው አግባብ ፤ የወደደውን ሰው አግብቶ ትዳር የመመስረት መብቱ የተጠበቀ ነው።
    6. ማንኛውም ከ18 ዓመት በላይ የሆነ ኢትዮጵያዊ ፤ ነዋሪ በሆነበት ክልል ፤ በምርጫ ሕጉ አግባብ እድሜው ሲፈቅድ ፦ በአከባቢ ፣ በክልል ወይንም በሐገር ዓቀፍ ደረጃ ለእሚደርጉ ፤ የመንግሥት ኃላፊነት ምርጫዎች ፤ በመራጭነት እና በተመራጭነት የመሳተፍ መብቱ የተከበረ ነው። 
    7. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የፈለገውን ዓይነት ፦ የንግድ  ፣ የኃይማኖት ፣  የፖለቲካ ፣  ወዘተ ፤ ማሕበር በፈቃዱ የመመሥረት ወይንም የመቀላቀል እንዲኹም የትኛውንም ዓይነት ማሕበር ተገዶ እንዲቀላቀል ያለመደረግ መብት አለው።
    8. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፦የእሚሠማራበትን የሞያ መስክ  ፣ የእሚከፈለውን ክፍያ ፣ የእሚሠራበትን ቦታ እና ኹኔታ የመምረጥ መብት አለው።
  2. የንብረት እና የአዕምሮ ፈጠራ መብት 
    1. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፤ በግልም ሆነ በማሕበር ተደራጅቶ ፤ የግል የንብረት ባለቤት የመሆን መብቱ የተጠበቀ ነው። 
    2. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የአዕምሮ ፈጠራው ፤ በአዕምሯዊ ንብረትነት ተመዝግቦ ሕጋዊ የንብረት ጥበቃ የማግኘት መብቱ የተጠበቀ ነው።
    3. የኢትዮጵያዊ ዜጋ ንብረት ፤ ለማሕበራዊ ግልጋሎት አስፈላጊ ሆኖ ፤ በሕግ አግባብ ንብረቱ በመንግሥት በእሚወሰድበት ግዜ ፤ መንግሥት ለዜጋው ፤ በወቅቱ የገበያ ዋጋ ተመጣጣኝ ክፍያ ሊሰጠው ይገባል።
  3. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፦ የኃሳብ ፣  የህሊና  እና የኃይማኖት ነጻነት አለው። ስለ እዚኽም ፦
    1. የመረጠውን ኃይማኖት የመከተል መብቱ የተጠበቀ ነው።
    2. የመረጠውን ፖለቲካዊ ወይንም ሌላ ኃሳብ በግልም ሆነ ከመሰል ዜጎች ጋር በሕብረት የማቀንቀን መብቱ የተጠበቀ ነው።
    3. ኃይማኖቱንም ሆነ ኃሳቡን በፈለገው ግዜ የመቀየር መብቱ የተጠበቀ ነው።
    4. ኃይማኖቱን እና ኃሳቡን በጽሑፍ ፣ በድምጽ ወይንም በምስል አድርጎ በመረጠው ዘዴ የማስተላለፍ መብቱ የተጠበቀ ነው።
    5. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በፈለገው የዕውቀት መስክ ተሠማርቶ የመማር እና ዕውቀት የማግኘት መብቱ የተጠበቀ ነው።
  4. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፤ ከእዚኽ ሕገመንግሥት ጋር የእማይቃረን ባሕሉን የመግለጽ እና የማሳደግ መብቱ የተረጋገጠ ነው።

ክፍል 2

የሕግ መወሰኛ ቤት

አንቀጽ 1

የሕግ መወሰኛው ቤት


  1. የሕግ መወሰኛው ፤ ቤት ሀ (ቤተእንደራሴ) እና ቤት ለ (ቤተዣኖ) በእሚባሉ በኹለት ቤቶች ተከፍሎ ይዋቀራል።
  2. የእንደራሴዎች እና የዣኖዎች ምርጫ ፤ የምርጫ ሕግ በእየክልሉ መንግሥት ይጸድቃል ። የምርጫ ሕጉም ቀጥታ በሕዝብ የእሚደረግ ምርጫ ሆኖ ፤ አብዛኛውን ቀጥታ የሕዝብ ድምጽ ያገኘው እጩ አሸናፊ የእሚሆንበት መሆን አለበት ፤ ሆኖም የፌደራሉ ሕግ መወሰኛው ምክርቤት ፤ ምርጫው የእሚካኼድበትን ቦታ ከእሚደነግገው እና የምርጫውን ቀጥተኝነት እና አብዛኛውን ድምጽ ያገኘ እጩ ያሸንፋል ከእሚለው አንቀጽ በስተቀር ፤ ሕጉን ሊያሻሽለው ይችላል።
  3. የሕግ መወሰኛው ምክርቤት ፤ በዓመት አንድ ግዜ የመሰብሰብ ግዴታ ሲኖርበት ፤ ይኽም የመጀመሪያው ስብሰባው ፤ በመስከረም ወር የመጨረሻ ሰኞ ይሆናል። 
  4. የሕግ መወሰኛ ምክርቤቱ የትኛውንም ስብሰባዎቹን ፤ ለእዚኽ ተግባር ተብሎ በተገነባው ህንጻ ውስጥ ብቻ ነው ማድረግ የእሚችለው ፤ በጦርነት  ወይንም በተፈጥሮ አደጋ ሕንጻው ከጥቅም ውጭ እስከ አልሆነ ድረስ ፤ እንደ እዚያ በእሚሆንበት ግዜ ፤ በአዋጅ በግዜያዊነት የስብሰባ ቦታ ይቀየራል ፤ ስብሰባው በቀድሞው ቦታ መካኼድ እስኪችል።
  5. ኹለቱም ቤቶች ፤ ስብሰባ ለማካኼድ አብዛኛው አባል መገኘት አለበት። ሆኖም ትንሽ ቁጥር ያላቸው አባላት ፤ ምልዓተ ጉባኤው (ኮረሙ) እንዲገኝ መጠየቅ እና ይኽ ሳይሆን ሲቀር ፤ በመተዳደሪያ ደንባቸው መሠረት ፤ ሳይገኙ የቀሩት አባላቱ እንዲቀጡ ሊያደርጉ ይችላሉ።
  6. እያንዳንዱ ቤት የራሱን መተዳደሪያ ደንብ ያጸድቃል። 
  7. ኹለቱም ጉባኤዎች የየስብሰባቸው ቃለ ጉባኤ ይይዛሉ ፤ ውሳኔ ያለፈበት ጉባኤ ከሆነ ፤ በ20 እጅ የአባላቱ ጥያቄ ፤ ውሳኔውን ከደገፉት እና ከተቃወሙት ወይንም በድምጸ ታዕቅቦ ካለፉት አባላቱ ዝርዝር ጋር ፤ ይኽንንም ቃለ ጉባኤ ፤ ምስጢራዊ ነው የእሚሉትን ክፍል አስቀርተው ፤ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ አለባቸው።
  8. ኹለቱም ቤቶች ሳይስማሙበት ፤ አንዱ ቤት ፤ ከ3 ተከታታይ ቀናት በላይ በአንድ ጉዳይ ላይ ስብሰባ ማድረግ አይችልም።
  9. የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት አባላት የእሚያገኙት ክፍያ እና ጥቅማ ጥቅም በሕግ ይወሰናል።
  10. የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት አባላት ፦ ሐገር በመክዳት ፣ በከፍተኛ ወንጀል ወይንም በሐገር መንግሥት ላይ ነፍጥ በማንሳት ክስ ካልተመሰረተባቸው በስተቀር ያለ መከሰስ መብት አላቸው ፤ እንዲኽ በእሚሆንበት ግዜ ፤ ቤቱ በአብዛኛው ድምጽ ያለ መከሰስ መብታቸውን ያነሳል።
  11.  የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት አባላት ፤ በስብሰባ ላይ በእሚያነሱት ኃሳብ በሕግ ሊከሰሱ አይችልም።
  12. የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት አባል ሆኖ የተመረጠ ሰው ፤ የመንግሥት ቅጥረኛ ሠራተኛ ወይንም ሹመኛ ባለስልጣን ወይንም ከእዚኽ ሌላ ለሌላ መንግሥታዊ ኃላፊነት ለመመረጥ እጬ ሆኖ መቅረብ አይችልም። እንደ እዚኹም  ፤ የመንግሥት ቅጥረኛ ሠራተኛ ወይንም ሹመኛ ባለስልጣን ወይንም በሌላ የመንግሥት ኃላፊነት ላይ በምርጫ ተመርጦ የተቀመጠ ዜጋ ፤ ለሕግ ወሰኛው ምክር ቤቶች በእጩነት መቅረብ አይችልም።
  13. አንድ የሕግ ረቂቅ በቤተእንደራሴው ወይንም በቤተዣኖው ሊቀርብ ይችላል ፤ ለፊርማ ወደ ሐገሪቱ ርዕሰ ብሔር ከመኼዱ በፊት ግን ፤ በኹለቱም ቤቶች በአብዛኛ ድምጽ ማለፍ አለበት።
  14. አንድ የሕግ ረቂቅ ፤ በኹለቱም ቤቶች ፤ በአብዛኛው ድምጽ ካለፈ ፤ ሕግ ሆኖ የእሚጸድቀው ፤ በሐገሪቱ ርዕሰ ብሔር ፊርማ ነው። አንድ ረቂቅ በእዚኽ አግባብ ፤ ለርዕሰ ብሔሩ ለፊርማ በእሚቀርብበት ግዜ ፤ ረቂቁ ከቀረበበት ቀን በኋላ ባሉት 10 የሥራ ቀናት ውስጥ ፤ ርዕሰ ብሔሩ ፤ በረቂቁ ላይ ቅሬታ ካለው ፤ በረቂቁ ላይ ቅሬታ አለኝ ብሎ ፤ ያለውን ቅሬታ በጽሑፍ በአባሪነት በማያያዝ ለሕግ መወሰኛ ቤቱ ሊመልሰው ይችላል። አንድ የሕግ ረቂቅም ፤ በእዚኽ አግባብ ወደ ሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ከተመለሰ ፤ የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ፤ ቅሬታውን ያገናዘበ ስብሰባ በረቂቁ ላይ አድርጎ ፤ ቅሬታውን ተቀብሎ እርማት በማድረግ ፤ ረቂቁን በድጋሚ ለርዕሰ ብሔሩ ይመልሳል ፤ የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ቅሬታውን ካልተቀበለ እና ረቂቁ የኹለቱንም ቤቶች ⅔ ድጋፍ ካለው ረቂቁን ያለ ርዕሰ ብሔሩ ፊርማ ሕግ አድርጎ ያጸድቀዋል ፤ ካልሆነ ሕጉ ውድቅ ይሆናል። ርዕሰ ብሔሩ ፤ ለፊርማ የቀረበለትን ረቂቅ ሕግ ፤ ረቂቁ ከቀረበበት ቀን በኋላ ባሉት 10 የሥራ ቀናት ፤ ረቂቁን ወደ ሕግ መወሰኛው ቤት ካልመለሰው ወይንም በፊርማው ካላጸደቀው ፤ ረቂቁ በቀጥታ ሕግ ሆኖ ይጸድቃል። ይኽ አሠራር ፤ ለሕግ ረቂቅ ሆነ ለሌሎች የሕግ መወሰኛ ቤቶቹ ውሳኔዎች የእሚተገበር ይሆናል።

 

አንቀጽ 2

ቤት ሀ (ቤተእንደራሴው)


  1. እያንዳንዱ ክልል  ፤ በሕዝብ ቁጥሩ ብዛት መሠረት ፤ የተደለደለትን መጠን እንደራሴዎች  በእየ 5 ዓመቱ አስመርጦ ፤ ያቀርባል።
  2. የየክልሉ  ተመራጭ እድሜው ከ27 ዓመት በላይ እና በእሚመረጥበት ግዜ የክልሉ ነዋሪ መሆን አለበት። 
  3. የተለቀቀ ወንበር ሲኖር ፤ መለቀቁ እንደ ታወቀ ፤ የመንግሥት አስፈጻሚው ፤ ክልሉ ምርጫ አካኺዶ ክፍተቱን እንዲሞላ በማዘዝ ምርጫ እንዲያካኺድ ያደርገዋል።
  4. ቤቱ የራሱን አፈጉባኤ ይመርጣል።
  5. የተቀጠሩ  ፣ የተሾሙ ወይንም የተመረጡ የመንግሥት ባለስልጣናት ጥፋት አጥፍተዋል ሲባል ፤ ምርመራ አድርጎ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ የእሚያደርገውን ምርመራ ማስጀመር የእሚችለው ይኽ ቤት ሀ (ቤተእንደራሴ) ነው።

አንቀጽ 3

ቤት ለ (ቤተዣኖው)


  1. እያንዳንዱ ክልል በእየ ስድስት ዓመቱ 4 የዣኖው አባላትን ወይንም ዣኖዎችን አስመርጦ ያቀርባል።
  2. በእዚኽ ሕገ መንግሥት አግባብ የእሚደረገው የመጀመሪያ ምርጫ ከተካኼደ እና ዣኖው ከተመሠረተ በኋላ ፤ የእያንዳንዱ ክልል 2 ዣኖዎች በእጣ ተመርጠው ፤ ከ3 ዓመት በኋላ ደግመው ለወንበራቸው እንዲወዳደሩ ይደረጋል ፤ ከእዚኽም በኋላ ፤ የዣኖው ግማሹ ወንበር በእየ 3 ዓመቱ ለምርጫ ዳግም የእሚቀርብ ይሆናል።
  3. በዣኖው ውስጥ ክፍት ወንበር ሲፈጠር እና ክፍተቱ በምርጫ በአፋጣኝ ካልተሞላ ፤ አስፈጻሚው በግዜያዊነት ወንበሩ ላይ ተሿሚ ሊያስቀምጥበት ይችላል።
  4. ለዣኖነት ለምርጫ የእሚቀርበው ሰው እድሜው ከ35 ዓመት በላይ እና በእሚመረጥበት ግዜ የክልሉ ነዋሪ የነበረ መሆን አለበት።
  5. የሐገሪቱ ምክትል ርዕሰ ብሔር ፤ የዣኖው ፕሬዝዳንት ይሆናል ፤ ሆኖም ዣኖው እኩል ሲከፈል ሚዛን ለመድፋት ካልሆነ ድምጽ መስጠት አይችልም።
  6. ዣኖዎቹ የተለየ ሞያዊ ዕውቀት የእሚፈልጉ ሕግጋትን ለማርቀቅ  ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸውን ሞያተኞች በአማካሪነት መቅጠር ይችላሉ ፤ ምክትል ርዕሰ ብሔሩ በእማይኖርበት ግዜም አዲስ ፕሬዝደንት መምረጥ ይችላሉ።
  7. የመንግሥት ቅጥረኞች ፣ ሹመኞች ወይንም ተመረጮች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም ተብሎ በሕዝብ ተወካዮች ምርመራ እንዲደረግባቸው ሲወሰን ፤ ምርመራውን አካኺዶ ብይን ማሳለፍ የእሚችለው በ2/3 ኛ ድምጽ ዣኖው ነው ። የሐገሪቱ ርዕሰ ብሔር ከሆነ በእዚኽ መልክ የእሚመረመረው ፤ የሐገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመኃል ዳኛ የጉባኤው ሰብሳቢ ይሆናል።
  8. ዣኖው በምርመራ ጥፋተኛ ብሎ የወሰነበት የመንግሥት ቅጥረኛ ፣ ሹመኛ ወይንም ተመራጭ ፤ በዣኖው ሊጣልበት የእሚችለው ከፍተኛ ቅጣት ከኃላፊነት መነሳት እና ከኃላፊነቱ ጋር ተያይዘው የመጡ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን ማሳጣት ነው። ሆኖም በዣኖው ጥፋተኛ ተብሎ ከኃላፊነቱ የተነሳው የመንግሥት ቅጥረኛ ፣ ሹመኛ ወይንም ተመራጭ ፤ በጉዳዩ በሕግ እንደ አይጠየቅ በተለየ ኹኔታ በሕግ የተሰጠው ያለ መከሰስ መብት ከሌለው በስተቀር ፤ በአቃቢ ሕግ ወይንም በሌላ ከሳሽ በመደበኛ ፍርድ ቤት ሊከሰስ ይችላል። 

አንቀጽ 4

የሕግ መወሰኛ ቤቱ ስልጣን


  1. መንግሥት የእሚቁቋመው ፤ በዋነኝነት ፤ በእዚኽ ሕገ መንግሥት ውስጥ በክፍል 1 ላይ የተዘረዘሩትን የዜጎች መብቶች አክብሮ ለማስከበር በመሆኑ ፤ የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ፤ ከተፍጥሮ ሕግ አግባብ ውጭ ፤ በእዚኽ ሕገ መንግሥት ውስጥ በክፍል 1 ላይ የተዘረዘሩትን የዜጎችን ተፈጥሯዊ መብቶች በአንድም በሌላም ምክንያት የእሚሽሩ ሕጎች ሊያጸድቅ አይችልም።
  2. የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ፤ የክልል መንግሥታት ፤ በእዚኽ ሕገመንግሥት ክፍል 1 ላይ የተዘረዘሩትን ፤ የዜጎችን ተፈጥራዊ መብቶች አክብረው የእሚያስከብሩ እንዲሆኑ እና በነጻ እና በፍትኃዊ ምርጫ ስልጣን ይዘው ፤ በሕግ አውጪ ፣ በሕግ ተርጓሚ እና በሕግ አስፈጻሚ አግባብ እንዲዋቀሩ ፤ በእዚኽም ኹሉንም ዜጎች በእኩልነት እና በፍኃዊነት የእሚያገለግሉ ሕዝባዊ እና ዴሞክራሲያዊ መንግሥታት እንዲሆኑ በሕግ ደንግጎ ተፈጻሚነቱን ይቆጣጠራል።
  3. በክልሎች ውስጥ ፦ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጠር ፣ ከእዚኽ ሕገመንግሥት የእሚቃረን መንግሥታዊ አደረጃጀት ሲፈጠር ፣ የክልል መንግሥት የፌደራል መንግሥቱን እርዳታ በቀጥታ ሲጠይቅ ፤ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ ገብቶ ፤ ሕገመንግሥታዊ ስረዓቱን እንዲመልስ ፤ በ2/3ኛ ድምጽ መደንገግ ይችላል።
  4. በዣኖ እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የእሚዋቀረው የሕግ ወሰኛው ቤት ፤ በሐገሪቱ ውስጥ ፤ ብቸኛው እና የመጨረሻው የመንግሥታዊ ሕግ አጽዳቂ አካል ነው።
  5. የሕግ መወሰኛ ቤቱ በሐገር ዓቀፍ ደረጃ የእሚወሰኑ ፤ የግብር እና የቀረጥ መጠንን የእሚወስኑ ሕጎችን ያወጣል።
  6. የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግሥት ከሐገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የእሚበደራቸውን ብድሮች የእሚተዳደሩበትን ሕግ ያጸድቃል።
  7. የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግሥት እና የኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥታት ፤ እርስ በእርሳቸው ወይንም ከውጭ ሐገር ጋር የእሚያደርጉትን ንግድ የእሚያስተዳድሩ ሕጎችን ያጸድቃል።
  8. በኢትዮጵያ ውስጥ ዜግነት የማግኛ ሕጎች ያጸድቃል።
  9. በኢትዮጵያ ውስጥ ገንዘብ የእሚታተምበትን ፣ ደህንነቱ የእሚጠበቅበትን እና የምንዛሪ መጠን የእሚወስንበትን መንገድ የእሚደነግጉ ሕጎችን ያጸድቃል።
  10. በኢትዮጵያ ውስጥ ፤ የንግድ ምርቶች እና አገልግሎቶች  ጥራት እና ደረጃ የእሚተዳደሩበትን ሕጎች ያጸድቃል።
  11. የአዕምሮ ፈጠራ ንብረት ባለቤትነትን የእሚያስተዳድር ሕግ ያጸድቃል።
  12. የተለያዩ የአስፈጻሚው መንግሥታዊ ተቋሟት የእሚቋቋሙበትን ሕግ ያጸድቃል።
  13. ፍርድ ቤቶች እና ሌሎች የፍትሕ ተቋማት የእሚቋቋሙበትን ሕግ ያጸድቃል።
  14. ፍርድ ቤቶች የእሚጠቀሙባቸውን ፦ የፍትሐ ብሔር ፣ የወንጀለኛ መቅጫ ፣ የቤተሰብ ፣ የንግድ ፣ ወዘተ ሕጎች ያጸድቃል።
  15. በሐገሪቱ ውስጥ የእሚቋቋመው የመከላከያ ሠራዊት ፦ የምድር ጦሩን ፣ የአየር ኃይሉን ፣ የባሕር ኃይሉን ፣ የስፔስ ኃይሉን ፣ የሳይበር ኃይሉን ፣ ወዘተ የእሚቋቋምበት እና የእሚተደዳደርበትን ሕግ ያጸድቃል።
  16. የጦርነት አዋጅ ያውጃል ።
  17. የፌደራል መንግሥቱ ፤ ከክልል መንግሥታቱ ፤ የፌደራሉን ጦር ማስፈርን ጨምሮ ሌሎች ፌደራላዊ የመንግሥት ተቋሟት ፤ መንግሥታዊ ሥራቸውን ለመሥራት የእሚፈልጉትን ቦታዎች ከክልል መንግሥታት የእሚያገኙበትን ሕግ ያጸድቃል።
  18. የሐገሪቱ ርዕሰ ብሔር ፥ በአደጋ ፤ ለምሳሌ ፦ ኮማ ውስጥ ቢገባ ወይንም በሌላ ምክንያት ፤ በዕሚታይ መልኩ ኃላፊነቱን መወጣት ቢሳነው እና ይኽንንም ለሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ማሳወቅ ቢሳነው ፤ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ፤ እረፍት ላይ ቢሆን እንኳን ፤ በድንገተኛ ስብሰባ በ24 ሰዓት ውስጥ ተመልሶ ፤ በ ⅔ ኛ ድምጽ ፤ ርዕሰ ብሔሩን በግዜያዊነት በምክትል ርዕሰ ብሔሩ ፤ ምክትል ርዕሰ ብሔሩም በተመሳሳይ ምክንያት ርዕሰ ብሔሩን ሊተካው እማይችል ከሆነ ፤ ከእዚኽ በፊት በሕግ መወሰኛው ምክርቤት የወጣው የመተካካት ሕጉ በእሚደነግገው መሠረት ፤ ቀጣዩን ሰው ርዕሰ ብሔር አድርጎ ይተካል። ከእዚኽ ኹነት በኋላ ፤ የስልጣን ዘመኑ ከመጠናቀቁ በፊት ፤ ርዕሰ ብሔሩ ፤ በጽሑፍ ለሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ፤ ወደ ኃላፊነቴ መመለስ እችላለኹ ብሎ በጽሑፍ ካሳወቀ ፤ የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት እረፍት ላይ ቢሆን እንኳን በድንገተኛ ስብስባ በ48 ሰዓት ውስጥ ተመልሶ ፤ በ ⅓ ኛ ድምጽ ርዕሰ ብሔሩን ወደ ስልጣን መመለስ አለበት ፤ የሕግ መወሰኛው ምክርቤት በ ⅓ ኛ ድምጽ ርዕሰ ብሔሩን ወደ ስልጣን መመለስ ካልቻለ ፤ ርዕሰ ብሔሩ ፤ ከ5 በሳይንሳዊ ሕክምና ዕውቅና ካላቸው እና ገለልተኛ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የጤና ባለሞያዎች ፤ ርዕሰ ብሔሩ ኃላፊነቱን ለመወጣት የእሚያስችለው አካላዊ (3 ዶክተር) እና አዕምሮዋዊ ( 2 ዶክተሮች) ብቃት አለው የእሚል ፤ የታተመ እና የተፈረመበት የሕክምና ማስረጃ ለሕግ መወሰኛው ምክር ቤት አቅርቦ ፤ ቀጥታ ወደ ስልጣኑ ይመለሳል ፤ ርዕሰ ብሔሩ ይኽን መሰሉን የሕክምና ማስረጃ ወይንም ⅓ ኛውን የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ድጋፍ ማግኘት ካልቻለ ፤ ማግኘት እስኪችል ድረስ ፤ ተተኪው ሰው እስከ ስልጣን ዘመኑ ማብቂያ ድረስ በስልጣኑ ላይ ይቆያል።
  19. በየትኛውም የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ፤ ተቀጥሮ ፣ ተሹሞ ወይንም ተመርጦ ወደ ስልጣን የመጣ ዜጋ ፤ ከሕግ መወሰኛው ዕውቅና ውጭ ፤ ከውጭ ሐገር መንግሥት ምንም ዓይነት ቁሳዊ ፣ የገንዘብ ፣ የስልጣን ወይንም የክብር ሽልማት እንደ አይቀበል የእሚደነግግ ሕግ ያጸድቃል።
  20. በፌደራል ክልሎች መካከል የእሚደረጉ ንግዶች ምንም የተለየ ግብር ፣ ቀረጥ ወይንም ሌላ ተጨማሪ ክፍያ እንዲከፍሉ የእሚያደርግ ሕግ ፤ የሕግ መወሰኛው ማውጣት አይችልም።
  21. የፌደራሉ መንግሥት ፤ በሐገር ደረጃ ፤ በክፍል አንድ ላይ የተዘረዘሩትን የዜጎች ተፈጥሯዊ መብቶች አክብሮ ለማስከበር እና ከእዚኽ ቀዳሚ ሥራው ጋር የእማይጻረሩ ሌሎች ብሔራዊ እና ማሕበራዊ ፋይዳ ያላቸውን ሥራዎች ለመሥራት የእሚያስችሉትን ሌሎች ሕጎችን ፣ ደንቦችን እና አሠራሮችን ያጸድቃል።

ክፍል 3

ሕግ አስፈጻሚው


  1. የሐገሪቱን መንግሥታዊ ተቋማት የማስተዳደር እና ሕገመንግሥቱ ከሐገሪቱ ሕጎች ጋር ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው የማድረጉን ሥራ ፤ በእየ ስድስት ዓመቱ ፤ በሐገር ዓቀፍ ምርጫ ፥ ከምክትሉ ጋር አብሮ የእሚመረጠው ፤ የሐገሪቱ ርዕሰ ብሔር (ፕሬዝደንት) ይሆናል።
  2. አንድ ዜጋ ፤ ከኹለት ግዜ በላይ ፤ በርዕሰ ብሔርነት (በፕሬዝደንትነት) ሊመረጥ አይችልም።
  3. ርዕሰ ብሔሩ (ፕሬዝደንቱ) ፥ ምክትል አድርጎ የእሚመርጠው ሰው ፤ ርዕሰ ብሔሩ (ፕሬዝደንቱ) ከእሚኖርበት ክልል የተለየ ሌላ የኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የእሚኖር ዜጋ መሆን አለበት።
  4. ርዕሰ ብሔሩ (ፕሬዝደንቱ) ከምክትሉ ጋር የእሚመረጥበት አግባብ ፦
    • እያንዳንዱ የፌደራሉ ክልል ፤ እንደራሴ ፣ ዣኖ ወይንም ሌላ መንግሥታዊ ኃላፊነት ላይ የሌሉ ፤ ኢትዮጵያዊ ሆነው የተወለዱ ዜጎችን ፤ በክልሉ የሕግ መወሰኛ ቤት በኩል ፤ የርዕሰ ብሔሩ እና የምክትሉ መራጭ አድርጎ ይመርጣል።
    • የመራጮቹ ብዛት ፤ የፌደራሉ ክልል ፤ በቤተእንደራሴው እና በቤተዣኖው ያለው መቀመጫ ድምር ይሆናል።
    • እያንዳንዱ ክልል ፤ መራጮቹ የእሚመረጡበትን እና የእሚመርጡበትን የምርጫ ሕግ እራሱ ይደነግጋል። ሆኖም የፌደራሉ ፤ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ፤ ምርጫው የእሚካኼድበትን ቦታ ከእሚውስነው አንቀጽ በስተቀር የምርጫ ሕጉን ሊያሻሽለው ይችላል።
    • የርዕሰ ብሔሩ እና የምክትሉ ምርጫ የእሚደረግበት ቀን ፤ በሐገር ዓቀፍ ደረጃ አንድ ቀን መሆን አለበት።
    • ክልሎች ምርጫውን በእዚኽ አግባብ ፤ ካከኼዱ በኋላ ፤ መራጮቹ ፦ እያንዳንዱ የርዕሰ ብሔር እና ምክትሉ ጥምር እጬ ያገኘውን ድምጽ ፤ በሰንጠረዥ አስቀምጠው እና በክልሉ አሸናፊውን በይነው ፤ ውጤቱን በክልሉ የሕግ መወሰኛ አጸድቀው ፤ ውጤቱን ደህንነቱ በተጠበቀ አግባብ ፤ ለቤተዣኖው ፕሬዝደንት ፤ ይልካሉ።
    • የፌደራሉ የቤተዣኖው ፕሬዝደንትም ፤ የፌደራሉ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤትን ፤ ቤተዣኖውን እና ቤተእንደራሴውን ፤ ምልዓተ ጉባኤ በአንድ ላይ ሰብስቦ ፤ ከክልሎች የተላከለትን የምርጫ ውጤት ፤ በጉባኤው ፊት በመክፈት እና የእያንዳንዱን ክልል የምርጫ ውጤት በመናገር ፤ በሐገር ዓቀፍ ደረጃ ፤ አብዛኛ ድምጽ አግኝቶ ያሸነፈውን ፤ የርዕሰ ብሔር እና የምክትል ርዕሰ ብሔር ጥምር አሸናፊ ብሎ ያውጃል። የቤተዣኖው ፕሬዝደንት የቀረበለትን የእየ ክልሉ ምርጫ ውጤት ማወጅ እና አሸናፊውን የመግለጽ ኃላፊነቱን አልወጣም የማለትም ሆነ የመጣለትን የክልል ውጤት አልቀበለም የማለት መብት የለውም።
    • አብዛኛውን ድምጽ ያገኘ ፤ የርዕሰብሔር እና የምክትል ርዕሰ ብሔር ጥምረት ፤ በእማይኖርበት ግዜ ፤ ⅓ኛ እና ከእዚያ በላይ የሆነ ከፍተኛ ድምጽ ያገኘው የርዕሰብሔር እና የምክትል ርዕሰ ብሔር እጬ ጥምረትን አሸናፊ ብሎ ያውጃል።
    • ⅓ ኛ እንኳን ድምጽ ያገኘ የርዕሰብሔር እና የምክትል ርዕሰ ብሔር ጥምረት እጬ ካልተገኘ ፤ የፌደራሉ ሕግ መወሰኛው ምክርቤት ፤ እያንዳንዱ የፌደራሉ ክልል አንድ መራጭ ፥ ከዣኖዎቹ እና ከእንደራሴዎቹ መካከል እንዲወክል ያደርግና ፤ እነ እዚኽ መራጮች ፤ የርዕሰ ብሔሩን እና የምክትሉን ጥምረት እንዲመርጡ ይደረጋል።
    • በእዚኽ መልኩ ፤ አዲሱ ተመራጭ ርዕሰ ብሔር ሥራ የእሚጀምርበት ዓመት ህዳር 30 በፊት ርዕሰ ብሔሩ እና ምክትሉ መመረጥ ካልተቻለ ፤ በሥራ ላይ የእሚገኘው ምክትል ርዕሰ ብሔር ፤ የሐገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሆኖ እስከ እሚቀጥለው ምርጫ ይሠራል።
  5. ለርዕሰ ብሔርነት እና ለምክትል ርዕሰ ብሔርነት የእሚወዳደሩት ሰዎች ፤ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሆኑ ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ20 ዓመት በላይ የኖሩ እና ባለፈው 10 ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ የኖሩ ፣ እድሜያቸው ከ35 ዓመት በላይ የሆነ እና ሐገር በመክዳት ተከሰው በ2 ዓመት እና ከእዚያኽ በእሚበልጥ የእስራት ወይንም ተመጣጣኝ ቅጣት ያልተቀጡ ሊሆኑ ይገባል።
  6. ርዕሰ ብሔሩ በገዛ ፈቃዱ ስልጣኑን በእሚለቅበት ወይንም በሞት በእሚለይበት ግዜ ምክትል ርዕሰ ብሔሩ ፤ ርዕሰ ብሔር ይሆናል።
  7. ርዕሰ ብሔሩ ፤ በፈቃዱ ወይንም በሌላ ምክንያት ስልጣኑን ቢለቅ ፤ በእዚኽ ሕገ መንግሥት አግባብ ፤ በ24 ሰዓት ውስጥ መተካት አለበት።
  8. ምክትል ርዕሰ ብሔሩ በገዛ ፈቃዱ ስልጣን በእሚለቅበት ወይንም በሞት በእሚለይበት ግዜ ፤ ርዕሰ ብሔሩ ፤ በቤተዣኖው እና በቤተእንደራሴው አብዛኛ ድምጽ ይኹንታ ፤ ምክትል ርዕሰ ብሔር ይሾማል። ቤተዣኖው እና ቤተእንደራሴው ፤ አብዛኛውን ድምጽ የእሚሰጠውን እጬ እስኪያገኝ ፤ ርዕሰ ብሔሩን በእርሱ ምርጫ በግዜያዊነት ሾሞ ይሠራል።
  9. ምክትል ርዕሰ ብሔሩ ፤ በፈቃዱ ወይንም በሌላ ምክንያት ስልጣኑን ሲለቅ ፤ በእዚኽ ሕገ መንግሥት አግባብ በ48 ሰዓት ውስጥ መተካት አለበት።
  10. በስልጣን ላይ ያለ ርዕሰ ብሔር በጤና እክል ምክንያት ኃላፊነቱን መወጣት ካልቻለ ፤ ለቤተእንደራሴው አፈ ጉባኤ እና ለቤተ ዣኖው  ፕሬዝደንት በጽሑፍ አሳውቆ ፤ ኃላፊነቱን ፥ ጤናው እስኪመለስለት ድረስ ፤ ለምክትል ርዕሰ ብሔሩ ሊያስተላልፍ ይችላል።
  11. ርዕሰ ብሔሩ እና ምክትሉ ፤ በስልጣን ዘመናቸው ፤ የእማይቀነስ እና የማይጨመር ክፍያ እና ጥቅማ ጥቅም ያገኛሉ።
  12. ርዕሰ ብሔሩ ፤ ይኽን ሕገመንግሥት ፤ በእዚኽ ሕገመንግሥት የተቋቋሙት የፌደራሉ እና የክልሎች ሕግ መወሰኛው ምክር ቤቶች ካጸደቁት ሕገመንግሥት የእሚጻረር አሠራር ወይንም ተቋም ሊያቋቁም አይችልም።
  13. ርዕሰ ብሔሩ ኃላፊነቱን ሲረከብ ይኽን ቃለ መኃላ ይፈጽማል ፦ 'የኢትዮጵያን ሕዝባዊ መንግሥት ርዕሰ ብሔርነት ኃላፊነት ለመወጣት እና ይኽንን ሕገ መንግሥት አክብሬ ለማስከበር  አቅሜ የፈቀደውን ኹሉ በታማኝነት እና በትጋት ለማድረግ ቃል እገባለኹ።' 

አንቀጽ 2

የርዕሰ ብሔሩ ስልጣን


  1. ርዕሰ ብሔሩ ፦ ምድር ጦሩን ፣ ባሕር ኃይሉን ፣ ዓየር ኃሉን ፣ የሳይበር ጦሩን ፣ የስፔስ ጦሩን ፣ ባጠቃላይ ኹሉንም የእሚያካትተውን የሐገሪቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ነው።
  2. ሐገር ላይ ድንገተኛ የጦርነት አደጋ ከተጋረጠ ፤ ለ3 ወር ብቻ ሊቆይ የእሚችል ጦርነት ማወጅ ይችላል። ይኽ የአወጀው ጦርነት ፤ ከ3 ወር በላይ ከቆየ ፤ ሊቆይ የእሚችለው በሕግ መወሰኛው ምክርቤት የ2/3 ድምጽ ብቻ ነው።
  3. በክልሎች ውስጥ ፤ ጸረ ሕገመንግሥታዊ አካኼዶች አሉ ብሎ ካለ ፤ ለ1 ወር የእሚቆይ ሕግ የማስከበር ሥራ ማዘዝ ይችላል ፤ ሕግ የማስከበሩ ሥራ ከ1 ወር በላይ እሚቆይ ከሆነ ፤ ሊቀጥል የእሚችለው በቀጥታ የክልል መንግሥቱ ጥያቄ ወይንም በፌደራሉ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ⅔ ኛ ድምጽ ነው።
  4. በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት የተቋቋሙ ፤ ከፍርድ ቤቶች ውጭ ያሉ እና በግልጽ በሕግ ተጠሪነታቸው እና ተጠያቂነታቸው ለሌላ የተደረገ የአስፈጻሚነት ድርሻ ከሌላቸው መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች በስተቀር መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች በሙሉ ተጠሪነታቸው እና ተጠያቂነታቸው ለርዕሰ ብሔሩ ነው። 
  5. ርዕሰ ብሔሩ ፦ ዳኞችን ፣ አምባሳደሮችን ፣ ምኒስትሮችን ፣ ዳይሬክተሮችን ፣ ከምሺነሮችን ፣ መልዕክተኞችን ፣ እና ማንኛውንም ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣን የመሾም ስልጣን አለው። ሆኖም የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ፤ ሹመቶቹ በርዕሰ ብሔሩ ጠቋሚነት በቤተ ዣኖው አብዛኛው ድምጽ ነው እሚጸናው ብሎ በሕግ ሊደነግግ ይችላል። 
  6. የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት እረፍት ላይ ሆኖ ፤ በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት መጽናት ያለበት ኃላፊነት ክፍት ከሆነ ፤ ምክር ቤቱ ከእረፍት እስኪ መለስ ፤ ኃላፊነቱን በግዚያዊነት እንዲወጣ ያለ ምክር ቤቱ ይኹንታ ርዕሰ ብሔሩ አዲስ ባለስልጣን ሊሾም ይችላል።
  7. ርዕሰ ብሔሩ ፤ ለሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ፤ ቢያንስ በዓመት አንድ ግዜ የመንግሥቱን አፈጻጸም እና መጻኢ አቅጣጫ የእሚያመልክት ሪፖርት ያቀርባል። ምክር ቤቱም ፤ መንግሥቱን በእሚመለከት ፤ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ እንዲያቀርብ እና ጥያቄ እንዲመልስ ርዕሰ ብሔሩን ሊጠራው ይችላል። እንዲኽ በእሚሆንበት ግዜ ፤ ስብሰባው መች እንደ እሚሆን ርዕሰ ብሔሩ ይወስናል።
  8. ሕገመንግሥቱን እና በእዚኽ ሕገ መንግሥት የተቋቋመው የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት የእሚያጸድቃቸውን ሕጎች ፥ መንግሥትን ጨምሮ ሕዝቡ ፤ አክብሮ እያስከበረው መሆኑን እና የተላያዩ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ኃላፊነታቸውን ባግባቡ እንዲወጡ ማድረግ የርዕሰ ብሔሩ ኃላፊነት ነው።
  9. ርዕሰ ብሔሩ (ፕሬዝደንቱ) ፤ በቤተዣኖው ተመርምሮ ጥፋተኛ ተብሎ ከስልጣን የተነሳን ዜጋ ወደ ስልጣን መመለስ አይችልም።
  10. ርዕሰ ብሔሩ (ፕሬዝደንቱ) በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብሎ የተቀጣን ዜጋ ፤  በይቅርታ መፍታት ይችላል።
  11. ርዕሰ ብሔሩ (ፕሬዝደንቱ) ፤ በሥልጣን ላይ እስከ አለ ፤ በቤተ እንደራሴው ከሳሽነት ፤ በቤተዣኖው ምርመራ ፤ ከስልጣኑ ለማወረድ ከእሚደረግበት ምርመራ ውጭ ፤ በመደበኛ ፍርድ ቤት ያለመከሰስ መብቱ የተከበረ በመመሆኑ ፤ በሥልጣን ላይ እስከ አለ ድረስ ፤ በመደበኛ ፍርድ ቤት ሊከሰስ አይችልም።
  12. ርዕሰ ብሔሩ (ፕሬዝደንቱ) ፤ ሕገመንግሥቱን እና የሐገሪቱን ሕግ አክብሮ በማስክበር ፤ ቀዳሚ ዜጋ እና የመጨረሻው አስፈጻሚ ባለስልጣን በመሆኑ ፤ በስልጣን ዘመኑ ፤  የርዕሰ ብሔርነት (በፕሬዘዳንትነት) ኃላፊነቱን በእሚወጣበት ግዜ ፤ በእዚኽ ሕገመንግሥት እና የሕግመወሰኛው በእሚያጸድቃቸው ፌደራላዊ ሕጎች አግባብ መሆን አለበት ፤   በመሆኑም ርዕሰ ብሔሩ (ፕሬዝደንቱ) የርዕሰ ብሔርነት (ፕሬዝደንትነት) ኃላፊነቱን በእሚወጣበት ወቅት ፤ ሕገመንግሥቱን እና የሕግ መወሰኛው ያጸደቀውን የፌደራል ሕግ ተላልፎ ከተገኘ ፤ በይርጋ ነጻ ካልሆነ ፤ ከሥልጣን ከወረደ በኋላ ፤ በነጻ እና ገለልተኛ ፍርድ ቤት ሊከሰስ እና ጥፋተኛ ተብሎ ከተገኘ ፤ በሕጉ አግባብ ሊቀጣ ይችላል። በተመሳሳይም ፤ ርዕሰ ብሔሩ ( ፕሬዝደንቱ ) ከሥልጣን ላይ እያለም ሆነ ፤ ወደ ስልጣን ሳይመጣ እና ከስልጣን ከወረደ በኋላ ፤  ከርዕሰ ብሔርነት (ከፕሬዘደንትነት)  ኃላፊነቱ ጋር ያልተያያዙ እንደ ዜጋ የፈጸማቸው ወንጀሎች ካሉ ፤ በይርጋ ነጻ ካልሆነ ፤ ከሥልጣን ከወረደ በኋላ ፤ በነጻ እና ገለልተኛ ፍርድ ቤት ሊከሰስ እና ጥፋተኛ ተብሎ ከተገኘ ፤ በሕጉ አግባብ ሊቀጣ ይችላል።

 

  1. ርዕሰ ብሔሩን እና ምክትል ርዕሰ ብሔሩን ጨምሮ ፤ ማንኛውም በቅጥር ፣ በሹመት ወይንም በምርጫ የመጣ የመንግሥት ባለስልጣን ፤ በቤተእንደራሴው አብዛኛው ድምጽ ጥያቄ ፦ ሐገር በመክዳት ፣ በሙስና ወይንም ከአመራር የእማይጠበቅ ከስነምግባር አግባብ ውጭ የሆነ ወራዳ ተግባር ፈጽመዋል በእሚል ክስ ቀርቦባቸው እና በዣኖው ምርመራ ተደርጎባቸው ፤ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ፤ በዣኖው 2/3ኛ ድምጽ ድጋፍ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ሊደረጉ ይችላል። 

ክፍል 4

ሕግ ተርጓሚው


  1. በኢትዮጵያ ውስጥ የመጨረሻው ሕግ የመቶርጎም እና ብያኔን የማሳለፍ ስልጣን ፤ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና በየደረጃው የእሚቋቋሙ ዝቅተኛ ፍርድ ቤቶች ናቸው።
  2. የተሾሙ ዳኞች የስነምግባር ጉድለት እስከ አላሳዩ ድረስ በሹመታቸው ላይ ይቆያሉ።
  3. ዳኞች ፤ ከተሾሙ በኋላ የእማይቀንስ ፤ የአገልግሎት ክፍያ እና ጥቅማ ጥቅም ያገኛሉ።
  4. ሕግ የመተርጎሙ እና ብያኔ የማሳለፍ ስልጣኑ ፦ ይኽን ሕገ መንግሥት ማዕቀፍ አድርገው የእሚወጡ ማናቸውንም መንግሥታዊ ሕጎች ያካትታል ።
  5. የፌደራል ክልል መንግሥት ፤ የክልሉ ነዋሪ ዜጋ ባለሆነ ሰው ሲከሰስ ፤ ክሱ በክልሉ ፍርድ ቤት ብቻ ነው የእሚዳኘው።
  6. በፌደራል ክልል እና በፌደራል ክልል መካከል እንዲኹም በፌደራል ክልል እና በተለያዩ የፌደራል ክልል ነዋሪዎች መካከል የእሚደረግ ክስ በፌደራሉ ፍርድ ቤት ይዳኛል።
  7. የመንግሥት ቅጥረኞች ፣ ሹመኞች ወይንም ተመራጮች ፤ ከውጭ ሐገር መንግሥታት በእሚኖራቸው ጉዳይ የእሚፈጠር ክስ ፤ በፌደራል ፍርድ ቤቱ ብቻ ይዳኛል።
  8. በእየ ክልሉ የእሚፈጠሩ ክሶች ፤ በክልል ፍርድ ቤቶች የእሚዳኙ ይሆንና ፤ የፌደራሉ ፍርድ ቤት ፤ በእየ ደረጃው የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ይሆናል።
  9. በሕግ ተርጓሚውው ሐገር የመክዳት ወንጀል ተብሎ የእሚታወቀው ፤ በሐገር ላይ ጦርነት የማወጅ እና የመፈጸም እንዲኹም በሐገር ላይ ጦርነት ላወጁ እና ለእሚያደርጉ የውጭ ጠላቶች ምንም ዓይነት እገዛ ማድረግ ነው።

ክፍል 5

የክልል መንግሥታት


  1. የአዲስ አበባ ክልል ፤ የፌደራሉ መንግሥት መቀመጫ ክልል ይሆናል።
  2. የክልል መንግሥታት ፤ ከውጭ መንግሥት ጋር ቀጥታ የውጭ ግንኙነት ወይንም ሕብረት መፍጠር አይችሉም።
  3. የክልል መንግሥታት ገንዘብ የማተም ስልጣን የላቸውም።
  4. የክልል መንግሥታት ፖለቲካዊ የክብር ማዕረግ መስጠት አይችሉም።
  5. የክልል መንግሥታት ፤ በፌደራሉ መንግሥት ከእሚጣለው ግብር እና ቀረጥ ውጭ ፤ በገቢ እና በወጪ ንግድ ላይ ግብር እና ቀረጥ መጣል አይችሉም።
  6. የክልል መንግሥታት የራሳቸው ጦር መገንባት አይችሉም።
  7. የክልል መንግሥታት ፤ ድንገተኛ ወረራ ሲፈጸምባቸው በሕዝባዊ ሚሊሻ የመከላከል ሥራ ለመሥራት ካልሆነ ፤ በሌላ ክልልም ሆነ በሌላ የውጭ ሐገር ላይ ጦርነት ማወጅ አይችሉም።
  8. የክልል መንግሥታት ፤ በሕግ መወሰኛው ምክርቤት ውሳኔ ፤ ካልሆነ ከሌላ ክልል ጋር ምንም ዓይነት ሕብረት መፍጠር አይችሉም።
  9. በአንድ የክልል መንግሥት የእሚሰጥ መንግሥታዊ ሰነድ ፤ በኹሉም የሐገሪቱ ክልሎች ተቀባይነት ይኖረዋል። የፌደራሉ የሕግ የመወሰኛ ምክር ቤትም እነ እዚኽ ሰነዶች በእየ ክልሉ የእሚዘጋጁበትን አግባብ ሊወስን ይችላል።
  10. የአንድ ክልል ነዋሪ ፤  በሌሎች የሐገሪቱ ክልሎች ኹሉ እኩል መንግሥታዊ አገልግሎት የማግኘት መብት አለው።
  11. ከአንድ ክልል ወንጀል ፈጽሞ ወደ ሌላ ክልል የሸሸ ወንጀለኛ ፤ በክልሉ መንግሥት ጠያቂነት ለክልሉ መንግሥት ተላልፎ ይሰጣል።
  12. በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት አብዛኛው ድምጽ እና በክልል ነዋሪዎች አብዛኛው ድምጽ ፤ አዲስ ክልል ሊቋቋም ይችላል።
  13. የክልል መንግሥታት ሕዝባዊ እና ዴሞክራሲያዊ የመሆን ግዴታ አለባቸው ፤ በመሆኑም የክልል መንግሥታት ፤ ዋና ተግባራቸው ፤ በእዚኽ ሕገ መንግሥት ክፍል 1 ላይ የተዘረዘሩትን የዜጎችን ተፈጥሯዊ መብቶች ፤ ለነዋሪዎቻችው ያለምንም ልዩነት አክብሮ ማስከበር ሆኖ ፤ ከእዚያኽ በተጨማሪ የእሚሠሯቸው ሥራዎች ከእዚኽ ቀዳሚ እና ክቡር ዓላማ ጋር የእማይጻረር መሆን ሲኖርበት ፤ መንግሥታቸው (ሕግ አውጭው እና ሕግ አስፈጻሚው) በነጻ እና ፍትኃዊ ምርጫ የእሚቋቋም ሆኖ ፤ አወቃቀሩም በሕግ አውጪ ፣ በሕግ አስፈጻሚ እና በሕግ ተርጓሚ የተከፋፈለ መሆን ይኖርበታል። 

 

ክፍል 6

ሕገ መንግሥቱን የተመለከቱ ደንቦች


  1. በእዚኽ ሕገ መንግሥት ውስጥ ፤ በተባዕት ጾታ የተጻፉት ጾታ አመልካቾች እና ተውላጠ ስሞች በሙሉ ፤ በእንስት ጾታ ተተክተው ሊነበቡ ፣ ሊጻፉ እና ሊጠቀሱ ይችላሉ።
  2. ይኽ ሕገመንግሥት የኢትዮጵያ የመጨረሻው የበላይ ሕግ በመሆኑ ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ፤ በፌደራልም ሆነ በክልል ደረጃ የእሚወጡ ሕጎች ፣ አዋጆች ፣ ድንጋጌዎች ፣ ትዕዛዛት ፣ ወዘተ ፤ ከእዚኽ ሕገ መንግሥት ጋር የእሚስማሙ እና ሕገ መንግሥቱን የእማይጻረሩ ሊሆኑ ይገባቸዋል።
  3. እንደራሴዎች እና ዣኖዎች ፣ የፌደራል ክልል ምክር ቤት አባላት ፣ እንዲኹም በእየ ደረጃው የእሚገኙ ከፍተኛው የመንግሥት ባለስልጣናት እና ዳኞች ፤ ኃላፊነት በእሚረከቡበት ግዜ ፤ ይኽንን ሕገመንግሥት አክብሮ በእሚያስከብር አግባብ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ቃለ መኃላ መግባት አለባቸው።
  4. ሕገ መንግሥቱ ፤ በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ፤ ⅔ ኛ ድምጽ ወይንም በ ⅔ የክልል የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቶች የማሻሻያ ኃሳብ ሊቀርብበት እና በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት  ¾ ኛ ድምጽ ወይንም በ ¾ ኛ ክልሎች የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቶች አብዛኛ ድምጽ ሊሻሻል ይችላል።