ኢትዮጵያ በዓለማችን በጣም ጥንታዊ ከእሚባሉት እንደ ግብፅ ፣ ሶርያ ፣ እሥራኤል ፣ ህንድ ፣ ቻይና ከአሉት ሐገራት ጎራ የእምትመደብ ነች።
ኢትዮጲያ በጥንታዊነቷ ከእነ እዚኽ የዓለማችን ጥንታዊያን ጋር ስትመደብ ፤ በጣሊያን በእኛ አቆጣጠር ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም. ማለትም ለ5 ዓመት የቆየ ወረራ ከማስተናገድ በስተቀር ፤ በማንም የውጭ ሐገር ወራሪ አስተዳደራዊ ነጻነቷ ወይንም ሉዓላዊነቷ ሳይደፈር ከ2 ሺ ዓመት በላይ በመቆየት ደግሞ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሪከርድ ባለቤት ነች ።
ይኽ የሐገራችን ጥንታዊነት እና ነጻነት (ሉዓላዊነት) ፤ የብዙ ታሪካዊ ኃብት ባለቤት ቢያድርገንም ፤ ሐገራዊ የኃብት እና የእውቀት አቅም ገንብተን ታሪካችንን ተቁዋማዊ በሆነ እና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ አጥንተን ፤ ወጥነት በአለው መልኩ ስለ አል አስቀመጥነው ፤ ታሪካችንን በዘመናዊ መልኩ የተደራጀ እና መሠረታዊ ጥያቄዎችን የእሚመልስ ሆኖ አናገኘውም ።
በእርግጥ ፤ የተወሰኑ ታሪካዊ ርዕሶችን ወይንም አንድ የታሪክ ዘመንን የወከለ ፤ በይዘቱ ዓለም ዓቀፋዊ እና ሳይንሳዊ የሆነ ፤ በሐገራችን እና በውጭ ዜጎች የታሪክ ሙህራን የተሰሩ ፤ የተነጣጠሉ ሥራዎች አሉ። እነ እዚኽን ንዑስ እና የተነጣጠሉ ሥራዎች ፤ በቅደም ተከተላቸው ማያያዝ ፣ የተዘለሉ ርዕሶች እና ክፍሎችን መሙላት እና ወጥነት የአለው ሥራ በማቅረብ ደረጃ ግን የሐገራችን ታሪክ ብዙ ክፍተት የአለበት ነው።
ከእዚኽም የተነሳ ፤ ከፖለቲካ ፍላጎት የፀዳ ፤ የነበረውን በነበረበት ኹኔታ የእሚያቀርብ ፤ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የቀረበ ወጥ የኢትዮጵያ ታሪክ ዘገባ በአለ መኖሩ ፤ አንዳንድ ግዜ ታሪካችን በወቅቱ ስልጣን ላይ በእሚሆኑ ሰዎች ፍላጎት አግባብ ሲቀርብ ይታያል ፤ በተለይ ዘመናዊ ፖለቲካ የሐገራችንን የፖለቲካ አየር ክልል አልፎ መግባት ከጀመረ ግዜ አንስቶ።
ለእዚኽም ፦ ዘመናዊ ትምህርት በኢትዮጵያ ከተስፋፋ በኋላ ፤ መንግሥት በተለወጠ ቁጥር የእሚለዋወጠው የታሪክ ትምህርት ይዘት ልዩነት ፤ በኢትዮጵያ ኹኔታ ፥ ታሪክ ፥ ያለፈውን ኹኔታ ዘጋቢ ከመሆን ይልቅ ፤ የሆነው የፖለቲካ አጀንዳ መደገፊያ ወይንም ማራመጃ ሆኖ ሲቀርብ መቆየቱ ማስረጃ ነው ።
ይኽ የእሚሆንበት ምክንያት ደግሞ ፤ ሰፊ ተቀባይነት እና ተደራሽነት የአለው ታሪክ በእማይኖርበት ግዜ ፤ በተለይ እንደ ኢትዮጲያ በአሉ ጥንታዊ ሐገራት ፤ የታሪካቸው ርዝመት ፤ የተለያዩ የጥቅም እና የፖለቲካ ቡድናት ታሪክን ለጥቅማቸው ወይንም ለፖለቲካዊ ርዕዮታቸውን በእሚያመች መልኩ በድርሰት እንዲሞሉት ክፍተት የእሚፈጥር በመሆኑ ነው።
አማካይ ፣ ተቋማዊ እና ከዝበት የፀዳ ፤ ጥንቅቅ ያለ የታሪክ አቀራረብ ስለ ሌለን ፤ ኃላፊነት የእማይሰማቸው የተለያዩ ፖለቲከኞች ፤ ታሪካችንን ለእራሳቸው በእሚያመቻቸው መልኩ በድርሰት ሥራዎቾቻቸው መሙላታቸው ፤ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስረዓት የእምናደርገውን ጉዞ ከማዘግየት እና ከማወሳሰቡ በአሻገር ፤ በተጻራሪ የፖለቲካ ኃይላት የእሚቀርቡት እና አንዳንዴም የእሚጋጩት ታሪኮች ፤ እንደ ሕዝብ ወይንም እንደ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ፥ በታሪካችን ጉዳይ ውዥንብር እንዲፈጠረብን በማድረግም በዜጎች ላይ አላስፈላጊ እና አሉታዊ ስነልቦናዊ ጫናም ሲፈጠር ይታያል ።
ስለ እዚኽ ፦ በኢትዮጲያ ውስጥ ስለ ዴሞክራሲያዊ ስረዓት ግንባታ ውይይት በእሚደረግበት ግዜ ፤ ውይይቱ ማሕበረሰባችን በአላዋቂ ፣ በግድ የለሽ ወይንም በመሰሪ ፖለቲከኞች የድርሰት ታሪክ ከገባበት መደናገር አውጥቶ ፤ የኢትዮጲያን ታሪክ ሳይቀንስ እና ሳይጨመር ፤ በነበረበት ኹኔታ አስቀምጦ ከእሚያሳይ ታሪካዊ ዘገባ መጀመር አለበት የእሚል እምነት አለኝ።
ለእዚኽም ነው በእዚኽ ምዕራፍ ፤ ወጥነት የአለው እና በረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጉዞ ውስጥ ፤ ከፖለቲካው አንጻር ወሳኝ ድርሻ የአላቸውን ኹነቶችን የእሚዘግብ ታሪክ ለማቅረብ የእምሞክረው።
ምንም እንኳን ፤ የኢትዮጵያን ታሪክ ከስር መሠረቱ አጥንቶ እና ከመሰል ዝበት በጸዳ መልኩ እና ተቀባይነት የአለው ፤ ወጥ ታሪካዊ መጽሐፍ ለማውጣት ተቋማዊ አሰራር የእሚጠይቅ ቢሆንም ፤ ከመጽሐፉ ዓላማ አንጻር ወጥነት የአለው የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ታሪክ ማቅረቡ የራሱ ጠቀሜታ የአለው በመሆኑ ፤ ከዙሪያ መለስ ታሪካዊ ዳሰሳ ይልቅ ፤ በፖለቲካዊ ኹነቶች ላይ ብቻ በማተኮር ፤ ሚዛናዊ እና የጽሑፍ ታሪካዊ ማስረጃዎችን መሠረት የአደረገ የኢትዮጵያን ታሪክ ፤ ለማስቀመጥ እሞክራለሁ ።