መግቢያችን ላይ እንደ አልነው ፤ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ከአሉ፟ ጥንታዊ ከእሚባሉት ሐገራት ከቀዳሚዎቹ ጎራ የእምትመደብ ሐገር ነች ። ይኽም ጥንታዊነቷ ፣ ኢትዮጵያን የረዥም ዘመን ባለ ፈርጀ ብዙ ታሪክ ባለቤት እንድ እትሆን አድርጓታል ።
ይኽን የኢትዮጵያ ጥንታዊነት የእሚያስረዱ ፦ በሺህ ዓመታት የእሚቆጠር ቆያታ የአላቸው ፤ በተለያዩ መንፈሳዊ እና ዓለማዊ መጽሐፍት ውስጥ በብዛት የተጠቀሱ የጽሑፍ እንዲኹም በየኃ ፥ በአክሱም ፣ ወዘተ ፤ የእሚገኙ የቅርስ ቅሪቶች አሉ።
በጽሑፍ ከተቀመጡ ታሪኮች ፤ ኢትዮጵያ ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ፣ በጥንታዊ እና የመካከለኛው ዘመን የሐገር ውስጥ ፣ በጥንታዊ የግሪክ ፣ በታላቋ ሮም ፣ በአረብ እና ፐርዥያ ፤ ታሪክ ጸሐፊያን በአግባቡ የተመዘገቡ ታሪኮች አሉዋት ።
ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ጥንታዊ ሐገር ነች ስንል ፤ የሰው ልጅ ፖለቲካዊ ታሪክ ከጀመረበት የዛሬ አምስት እና ስድስት ሺ ዓመት አንስቶ የአለውን ታሪክ በማስመልከት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል ።
ምክንያቱም ፦ በፖለቲካዊው ሰው እና የዝግመተ ፍጥረት መላምቱ የህይወት ዑደት በቢልየን የእሚቆጠሩ ዓመታት ተከወኑ በእሚላቸው ፤ የህይወት ዑደት ምክንያት ፤ እየመጡ ጠፉ ከእሚባሉት ፤ እንደ ሉሲ ዓይነት ሰው መሰል ጦጣ ፍጥረታቱ መካከል የአለው ፤ ሊሞላ የእማይችል ልዩነት ስለ እሚያግደን ፤ ከፖለቲካዊው ሰው ወይንም ጠቢቡ ሰው (the wise man or Homo Sapiens) በፊት የነበረውን ጦጣ መሰል ፍጥረት ፤ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ጥንታዊነት ለማሳየት ልንጠቀምበት አንችልም ።
ፖለቲካዊው ሰው ወይንም ሆሞ ሳፒየነስ የሚልየኖች እድሜ ወጣት ከሆነችው ሉሲ ጋር ሰአይሆንም ፤ የአርባ እና ሀምሳ ሺ እድሜ ከነበራቸው ኒያንደርታሎችም ጋር ቀጥታ ግንኙነት የሌላቸው እና ፖለቲካዊው ሰው ፥ ‘ጠቢቡ’ ሰው ወይንም ሆሞ ሳፕየንስ ፤ ራሱን የቻለ እናም ከእነ እዚኽ ሰው መሰል ፍጥረቶች ጋር የእሚያይዝ በሳይንስ የተረጋገጠ ምንም ገመድ የሌለው ስለ ሆነ ፤ ሉሲ እና መሰል በከርሰ ምድር ቁፋሮ የእሚገኙ ሰው መሰል ፍጥረታት ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ ተደርገው ሰአይሆን መወሰድ ያለባችው ፤ የኢትዮጵያ ከርሰ ምድር ታሪክ ተደርገው ነው ።
በኢትዮጵያ ውስጥ የእሚገኝ የአንድ ዝንጀሮ ወይንም መዓድን የዝግመት ታሪክ ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፖለቲካዊ ታሪክ የአይደለውን ያኽል ፤ የሉሲም እና መሰል ቅሪት አካላት ታሪክ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፖለቲካዊ ታሪክ አካል አይደለም ።
ይኽ ፤ ፖለቲካዊው ሰው (HomoSapiens ወይንም ጠቢቡ ሰው) የዛሬ 6/7 ሺ ዓመት ወይንም ከእዛኽ ትንሽ ቀደም ብሎ (10 ሺ ዓመት እንደ ዝግመታዊያኑ) ተከስቶ ፤ የእርሱ ዝሪያዎች ከመሠረቱዋቸው ቀዳሚ ሐገራት መካከል የሆነችው ኢትዮጵያ የአላ፟ት የታሪክ ርዝመት እና ባለ ብዙ ፈርጅነት ፤ በአንድ መልኩ እንደ መልካም ጎን ሊታይ ሲችል ፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ፡ በተለያየ ምክንያት በተገቢው ጥናት የተጠናከረ በአለመሆኑ ፤ የታሪክ ተመራማሪዎች ፤ በተለያየ ወቅት የታሪካዊ ማስረጃ ውስንነት ኖሮባቸው ድምዳሜ እንዲያቀርቡ በእሚሆኑበት ግዜ ፤ ኢትዮጵያ ከእሚለው ቃል ትርጓሜ አንስቶ ፥ በተለያየ ወቅት ኢትዮጵያዊ የእሚለውን ስያሜ በመጠሪያነት እስከ ወሰዱ ወይንም እስከ ተሰጣቸው ሕዝብ ማንነት እና ኢትዮጵያ በእሚባለው ክልል ይካተት የነበረውን ቦታ ስፋት ፣ እና መሰል ታሪካዊ ርዕሶች ላይ ፤ የተለያዩ አንዳንዴም የእሚጋጩ መላምቶች የሰነዘሩበት ጉዳይ እንዲሆን አድርጎታል ።
የመጀመሪያውን ጉዳይ ፥ ኢትዮጵያ የእሚለውን ስያሜ ስንወስድ ፤ በቃሉ ምንጭ እና ትርጓሜ ላይ ፤ ቢያንስ ሦሥት ሊታረቁ የእማይችሉ የተለያዩ መላምቶች እናገኛለን ። የመጀመሪያው እና አኹን አኹን ፤ በብዙ ሰዎች እንደ ትክክለኛ ተደርጎ እየተወሰደ የአለው ፤ ኢትዮጵያ ማለት ፦ ጥቁር ወይንም በእሳት የተለበለበ የቆዳ ቀለም የእሚል ትርጉም ከአለ፟ው የግሪክ ቃል የመጣ ነው የእሚለው ነው ።
በእዚኽ ረገድ ፤ ለምሳሌ ፦ ቮለኒ የእሚባለው የፈረንሳይ የታሪክ አጥኚ ፤ ሊጠቀስ ይችላል ፦
“…ጥንታዊያኖቹ ፥ ኢትዮጵያዊ ሲሉ የቆዳ ቀለሙ የጠቆረውን ፥ ከንፈሩ ወፈር የአለውን እና ፀጉሩ ጠቅለል የአለውን መሆኑን አጠያያቂ አይደለም ።”
“For it is incontrovertible, that by the term Ethiopians, the ancients meant to represent a people of black complexion, thick lips and woolly hair. [85]“
ይኽንም መላምት ተከትሎ ፤ በጥንታዊ ታሪኮች ውስጥ ኢትዮጵያ የእሚለው ቃል የእሚወክለው ፤ መላውን ወይንም ለአንድ አንዶች ከዛሬይቱ ኢትዮጵያ ውጭ የአለውን ፤ የጥቁር አፍሪካ ሕዝብ እንጂ ከዛሬዋ ኢትዮጵያ ጋር በተለየ የእሚያገናኘው ነገር የለውም የእሚል አስተያየት አለ ።
እዚኽ ላይ ደግሞ ፤ ሐበሻ ከእሚለው የአረቡ ዓለም ኢትዮጵያን ይጠራበት ከነበረው ቃል ፤ አቢሲንያ የእሚል ስያሜን የኢትዮጵያ መጠሪያ የአደረጉት ፤ የቀኝ ግዛት ዘመን መጨረሻ አከባቢ አውሮፓዊያኖች ፤ ኢትዮጵያ ማለት ፦ የቆዳው ቀለም ጥቁር የሆነ ፣ ከንፈሩ ወፍራም ፣ ጠንካራ ፀጉር የአለው ነው ከእሚለው የተሳሳተ ግንዛቤያቸው ጋር ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ መልክ የአገኙት መልክ እና ቁመና አብሮ ስለ አልኼደላቸው ፤ ሐበሻ ወይንም በአውሮፓዊያን የሐበሻ አነባበብ ‘አብሲያ’ (አብሲንያ የእሚለው የእንግሊዘኛ ቃል የመጣበት የአነባበብ ስህተት) ፤ ኢትዮጵያ ተብሎ በጥንታዊ ጽሁፎች ውስጥ የእሚገኙት ታሪኮች ከዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋር የእሚገናኙ አይደሉም ፤ የእሚለው መሠረት የለሽ ግምት ሲጨመርበት ፤ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ እና በጥንታዊ ታሪካዊ መዝገቦች ውስጥ ተቀምጠው ያሉት የኢትዮጵያ ታሪኮች ፤ የተለያዩ ናቸው የእሚለውን ጉዳይ የበለጠ ያወሳስበዋል ወይንም አወሳስቦታል ።
አንድ አንዶች እስከ እነ ጭራሹም ፤ ሐበሻ የእሚባለው ወይንም እነርሱ አቢሲንያ የእሚሉት ፤ በዋናነት ፦ አማራው ፣ ትግሬው እና ኤርትራዊው ነው የእሚልም ነገር አምጥተዋል።
እውነታው ግን ፤ እኛ በአማርኛ ግብፅ ፤ ፈረንጆቹ በእንግሊዘኛ ኢጅብት እንደ እሚሉት ፤ ግሪኮች እና ሮማዊያኖች እኛን ኢትዮጵያ ፤ አረቦቹ ደግሞ ሐበሻ ይሉናል እንጂ ፤ ግሪኮች እና ሮማኖች ኢትዮጵያ ሲሉ እና አረቦቹ ሐበሻ ሲሉ ፤ ኹለቱም እንደ ቋንቋቸው ልዩነት ስያሜያቸው ቢለያይም ኹለቱም ፤ አንድን ሕዝብ እያመለከቱ መሆኑ ፤ በ4ኛው ምዕተ ዓመት አከባቢ በተጻፈ ጽሑፍ ላይ ፤ ንጉሠ ነገሥት ኢዛና ፤ ሐበሻ የእሚለውን ቃል ወደ ግሪክ ኢትዮጵያ ብሎ ከመተርጎሙ ተነስተን መረዳት እንችላለን።
ይኽንን ጉዳይ በተመለከተ ፤ በአክሱም ታሪክ ላይ መጽሐፍ የጻፈ ስቱዋርት ሙንሮ ኼይ (Stuart Munroe Hay) የተባለ ሰው እንደ እዚኽ ይላል ፦
“ነገር ግን ፥ በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኹለት ቋንቋ በተጻፈ ረዥም የማዕረጉን ዝርዝር በያዘ የድንጋይ ላይ ጽሑፍ ፥ ሐበሻት የእሚለውን ወደ ግሪክ ሲተረጉም ኢትዮጵያ እያለ ነበር ።”
“uses the word `Ethiopia' in the Greek version as the translation for `Habashat'. [86].”
ቀኝ ገዢ አውሮፓዊያኖቹ ፤ ኢትዮጵያን እና አብሲንያን (ሐበሻ) ያምታቱት ፤ ምናልባት ፦ የአከባቢውን ልዕለ ኃያልነትን ከአረቦች (ከዖቶማን ተርክ) ስለተረከቡት እና አረቦች ሐበሻ ይሉን ስለ ነበር ፤ እንዲሁም አውሮፓዊያኖች (ከፖርቹጋል እና ስፔን ውጭ የሆኑት) ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ፥ በተለምዶ ዘመነ መሣፍንት ተብሎ የእሚጠራው የታሪካችን ወቅት ላይ ስለ መጡ እና በእዚኽም የታሪካችን ዘመን ፤ ከግራኝ አህመድ ጦርነት በኋላ በመሆኑ ፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በዋናነት በአማራ ፣ ትግራይ እና ኤርትራ አከባቢ ላይ የተወሰነበት ወቅት ስለ ነበር ፣ ከግሪክ ጥናታቸው ኢትዮጵያ ማለት ጥቁር ማለት ነው የእሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ይዘው የመጡት አውሮፓዊያን ፤ ይኽን የተሳሳተ ግንዛቤያቸውን የእሚወክለው ከዛሬይቱ ኢትዮጲያ ውጭ የአለው አብዛኛው ጥቁር አፍሪካ ከአቢሲንያ ጋር ፖለቲካዊ ግንኙነት ሰአይኖረው ሲቀር እና እንደ ኢትዮጵያዊው (ለእነርሱ አቢስንያ) በተነፃፃሪነት የዳበረ መንግሥት እና አቅም የሌለው መሆኑ ፤ እዚኽ ላይ ደግሞ የቀኝ ግዛት ማስፋፋት ፍላጎት ፥ ከጀማሪ ዓለም አሳሽ ብዥታቸው ጋር ተዳምሮ ፤ አቢሲንያ እና ኢትዮጵያ የተለያዩ አድርገው ታሪክ እንዲጽፉ እንደ አደረጋቸው መገመት እንችላለን ።
ዋናው ቁም ነገር ፤ የመደናገሩ ምንጭ ምንም ይሁን ምን ፤ አረቦች ሐበሻ (አብሲንያ) ሲሉ እና ግሪኮች ወይንም ሮማዊያኖቹ ኢትዮጵያ ሲሉ ፤ እንዲኹም እብራይስጦች ኩሽ ሲሉ ፤ ሦሥቱም በእየራሳቸው ቋንቋ ፤ እኛን ኢትዮጵያዊያንን እያሉ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ። በእርግጥ ፤ ዕብራይስጦች ኩሽ ሲሉ ፤ በዋናነት እኛን የእሚወክል ቢሆንም ፤ ትንሽ ወረድ ብለን እንደ እምናየው ፤ በአንዳንድ አጋጣሚዎች እንደ አውዱ ፤ ኩሽ አባት ለሆናቸው ለእኛ ኢትዮጵያዊያን እና የተለያዩ ኢስያ ውስጥ ለእሚገኙ አረቦች ፣ ፐርዥያኖች ፣ ወዘተ ፤ የእሚሆንበትም ግዜ መኖሩ ግልፅ ቢሆንም ።
በኢትዮጵያ ስም ታሪካዊ ምንጭ ጉዳይ ላይ ፤ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ማለት ጥቁር ማለት ነው እንደ እሚለው መላምት ፤ ብዙ ‘ፖለቲካዊ’ ትንታኔ በአያስከትልም ፤ ኤድዋርድ ግላሰር በእሚባል የምሥራቅ ሕዝብ ተመራማሪ ፤ ኢትዮጵያ የእሚለው የኢትዮጵያዊያኖች ስያሜ ፤ አትዮብ ከእሚባል ነጭ እጣን የመጣ ነው የእሚል ፤ በኹለተኝነት መጠቀስ የእሚችል መላምት አለ ። ይኽንንም መላምት ፤ የሐልክዩት ማሕበረሰብ እንደ እዚኽ ያስቀምጡታል ፦
“ዶ/ር ግላሰር ፥ የኢትዮጵያ ስም ፤ አትዮብ (በብዙ ሲሆን ታ(ጣ)ይብ ፥ ነጭ እጣን) ከእሚል የመጣ ነው በማለት ፤ በጠቅላላው የነጭ እጣን ሐገር ነው ይላል”
“Dr. Glaser derives the name Ethiopia from atyob (the plural of taib, frankincense), so that it thus denotes generally the frankincense country. [87]“
ስለ እዚኽ ፦ እንደ ዶክተር ግላሰር ከሆነ ፤ ኢትዮጵያ ነጭ እጣን በብዛት የእሚገኝበት ሐገር በመሆኗ እና ይኽም እጣን አትዮብ የእሚባል ስለሆነ ፤ ሐገሪቱ ኢትዮጵያ ተብላለች ማለት ነው ።
እንደገናም በኢትዮጵያ ስያሜ ጉዳይ ፤ ወደ ሐገር ውስጥ ‘አፈታሪክ’ ስንመጣ ፤ በሶስተኝነት ፦ የኢትዮጵያ ስም የኢትዮጵያዊያኖች ኹሉ አባት ከሆነው ኢትዮጵስ የመጣ ነው የእሚል አፈታሪክ እናገኛለን ።
መጽሐፈ አክሱም በእሚባለው መጽሐፍ መሠረት ፤ ኢትዮጲስ አክሱም አከባቢ መዛብር በእሚባለው ቦታ የተቀበረ እና የኖህ አራተኛ የልጅ ልጅ እንደ ሆነ የተጻፈ ታሪክ አለ ፦
“በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወይንም ከእዚያኽ ትንሽ ቀደም ብሎ እንደ ተጻፈ የእሚነገርለት ፤ መጽሐፈ አክሱም የእሚባል አጠር ያለ የግዕዝ (የኢትዮፒክ)[1] መጽሐፍ … ፤ ከተማው (አክሱም) የኢትዮጲስ ፤ የኩሽ ልጅ ፣ የካም ልጅ ፣ የኖህ ልጅ መቃብር በአለበት መዛብር (‘ፍርሥራሽ’) በእሚባል ቦታ ቀደም ብሎ ተገንብቶ ነበር ።”
“The Matshafa Aksum, or `Book of Aksum' … a short Ge`ez (Ethiopic) work of the seventeenth century or a little earlier, says that the town was formerly built at Mazeber (`ruin') where was the tomb of Ityopis (Ethiopis), son of Kush, son of Ham, son of Noah. [86]“
የሐገርኛውን ብኺል ከተከተልን ፤ በእዚኽ መጽሐፈ አክሱም ላይ የተጠቀሰው ፤ ከኖህ አራተኛ የሆነው እና መቃብሩ በመዛብር የእሚገኘው ኢትዮጲስ ነው ፥ ኢትዮጵያ ለእሚለው ስያሜ መነሻ የሆነው የእሚል ነው ። እንዲኽ እንዲኽ እያልን ፥ ኢትዮጵያ በእሚለው ቃል አመጣጥ ላይ አንድ ኹለት ሌሎች መላምት መጨመር እንችላለን ።
ኹሉም መላምቶች ግን ፤ ልክ ሮም ለእሚባለው የጣልያኖች ከተማ መጠሪያው የወጣው ፤ እርሱን እና ወንድሙን ሪመስ ፤ ተኩላ እያጠባች ከአሳደገቻቸው ሮሚውለስ ነው ወይም ኄለና ለእሚባለው የግሪክ ሕዝብ መጠሪያ የሆነችው ፤ ኄለና ትባል ከነበረችው ንግሥታቸው ነው ተብለው እንደ እሚጠቀሱ የተለያዩ እና ይኽ ነው የእሚባል ታሪካዊ ማስረጃ እንደ ሌላቸው ንግርቶች ፤ ኢትዮጵያ ለእሚለው ስያሜ ምንጭነት የእሚጠቀሱትም መላምቶች ፤ በእርግጠኛ ታሪካዊ ማስረጃ ላይ የተደገፉ ሰአይሆኑ ፤ በውስን መረጃዎች ላይ የተመሠረቱ እና ርግጠኛ ያልሆኑ መላምቶች ናቸው ።
ስለ እዚኽ ፦ አስተማማኝ ታሪካዊ ማስረጃ እስኪገኝ ፤ ያለበቂ መረጃ ፤ ኢትዮጵያ የእሚለው ቃል ከእዚኽ ነው የመጣው ወይንም ከእዚያኽ ነው የመጣው ፤ የእሚል ያልተረጋገጠ ነገር ከማሰራጨት ይልቅ ፤ ተዓማኒነት በአለው ታሪካዊ ማስረጃ ላይ ተደግፎ ፤ የሐገራችን ሕዝብ ራሳቸውን ኢትዮጵያዊያን ብለው ከጠሩበት እና የውጩው ዓለምም ኢትዮጵያዊያን ወይንም ሐበሾች ብሎ ከአወቃቸው ግዜ አንስቶ ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የኼዱበትን ታሪካዊ ጉዞ ላይ ማተኮሩ ፤ በስያሜው ታሪካዊ ምንጭ ላይ ኹነኛ መረጃ እስኪገኝ ፤ የተሻለ ፍሬያማ ሥራ እንድ እንሰራ የእሚያደርገን ይመስለኛል ።
ከእዚያኽ በፊት ወይንም በኢትዮጵያ ስም ምንጭ ላይ የአሉ፟ትን የተለያየ መላምቶች ምርመራ የተሻለ መረጃ እስኪገኝ ለግዜው አቁመን ወደ ኢትዮጵያዊያን ወይንም ሐበሻ ወደ ተባሉት ሕዝብ ታሪክ ከመኼዳችን በፊት ግን ፤ ግሪኮች ወይንም ሮማዊያኖች ኢትዮጵያ ሲሉ ጥቁር ማለታቸው ነው ፤ ምክንያቱም ፦ ኢትዮጵያ የእሚለው ቃል በግሪክ ጥቁር ፊት ማለት ስለ ሆነ በእሚል ለእዚኽ መላምት በማስረጃነት የተቀመጠው ምክንያት ፤ እንደ ትክክለኛ ማስረጃነት እንደ አንቀበለው የእሚያደርጉንን ታሪካዊ እውነታዎች ተመልክተን እንለፍ ።
ኢትዮጵያ ለእሚለው ቃል ምንጭ ናቸው የእሚባሉት ግሪኮች ፤ ኢትዮጵያዊያኖችን በቆዳቸው ቀለም ምክንያት ከሆነ ኢትዮጵያዊያኖች (የተለበለበ ፊት የአላቸው) የአሉዋቸው ፤ በእዚያኽ ዘመን ግብፆችን ፣ ህንዶችን ብሎም ለግሪኮች ቅርብ የኾኑትን የቀርጤስ እና የሌቫንት ሰዎችን ጥቁሮች እንደ ሆኑ የእሚያውቁ ግሪኮች ፤ ከእነዚኽ ሕዝብ ለይተው ኢትዮያዊያንን ጥቁር የእሚሉበት ምክንያት መገኘት አለበት ።
በሌላ አገላለፅ ፤ ጥንታዊ ግብፆች ፣ ሌቫንት ውስጥ የነበሩ ከነዓናዊያን ፣ የቀርጤስ ሰዎች ፤ ከህንዶች ጋር እንደ ኢትዮጵያዊያን ዓይነት የቆዳ ቀለም የአላቸው ሕዝብ መሆናቸው ፤ በብዙ ታሪክ የተዘገበ ስለሆነ ፤ ጥንታዊ ግሪኮች እና ሮማዊያኖች እነ እዚኽን በቆዳቸው ቀለም ጥቁር የሆኑ ሕዝብ ፦ ግብፃዊያን ፣ ህንዳዊያን ፣ ወዘተ ፤ ብለው እያወቁ ፤ ኢትዮያዊያንን ለይተው ጥቁሮች ወይንም በእነርሱ ቋንቋ ኢትዮጵያዊያን ብለው እንዲጠሩ የእሚያስችላቸው አሳማኝ ምክንያት የለም ።
ለምሳሌ ፦ ከክርስቶስ ልደት 500 ዓመት ቀደም ብሎ የነበረውን ዓለም ታሪክ ለመጻፍ የሞከረው እና የታሪክ አባት የእሚባለው ግሪካዊው ሔሮድተስ ፥ ህንዶች እና ኢትዮጵያዊያን የቆዳ ቀለማቸው ተመሳሳይ እንደ ሆነ ፅፏል ፦
“እነ እዚኽ ህንዶቹ … ፣ የቆዳቸው ቀለም ከኢትዮጵያዊያኖቹ ቀለም ጋር ተመሳሳይ ነው ።”
“These Indians…, they have all one colour of skin, resembling that of the Ethiopians [5]“
የሔሮድተስ ታሪክ ፤ ህንዶች እና ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሰአይሆን ተመሳሳይ ጠየም ያለ ወይንም ጥቁር የቆዳ ቀለም አላቸው የእሚለው ፤ የእርሱ ዘመን ግብፆች እንደ ኢትዮጵያዊያን ጥቁር መሆናቸውንም ጭምር ይናገራል ።
ኮልኪስ የእሚባሉ ፥ እና በዛሬው የካውኬዥያን (ጥቁር ባሕር እና ካስፒያን ባሕር መካከል የእሚገኘው እና ካውኬዥያን ለእሚባለው የነጮች ዘር ስያሜ መነሻ የሆነው ፤ በዛሬው በራሺያ በስተደቡብ ፤ ጆርጂያ እና አርሜንያ የእሚገኙበት ቦታ) አከባቢ ይገኙ የነበሩ ሰዎች) ከግብፅ እንደ ኼዱ እና እነ እዚኽም ሰዎች እንደ ግብፆች እና ኢትዮጵያዊያኖች ቆዳቸው ጥቁር ብቻ ሰአይሆን ፤ በእዚያን ወቅት ፤ ከአብዛኛው የዓለም ሕዝብ በተለየ አኳኋን ፤ ልጆቻቸውን የእሚገርዙ እነ እዚኽ እንደሆኑ ሔሮድተስ ይናገራል ።
ሔሮድተስ ኮልኪሲያኖቹ በነጭ ሕዝብ መሐል የእሚኖሩ ጥቁሮች ስለሆኑ እና ከአከባቢው ሕዝብ የተለየ እና ከግብፅ ሕዝብ ባሕል ጋር የእሚመሳሰል የመገረዝ ባሕል ስለአላቸው ፤ ኮልኪሲያኖች ከግብፅ ነው የመጡት ብሎ ስለአሰበ ፤ ይኽን ጉዳይ በታሪክ መጽሐፉ አጣርቶ ማስቀመጥ ፈልጓል ፦
“እኔም ጉዳዩን መከታተል ስጀምር ኹለቱንም ጠየቅኩሁዋቸው ፤ ኮልኪሲያኖቹ ግብፃዊያንን ፤ ግብፃዊያኑ ኮልኪሲያዊያን ከእሚያስታውሱት በላይ ያስታውሱዋቸዋል ፤ ሆኖም ግብፃዊያኑ ኮልኪሳዊያኑ ከሶርቲስ ወታደሮቹ ገሚሶቹ ሳይሆኑ አይቀሩም የእሚል ግምት አላቸው ። እኔም ራሴ መጀመሪያ እንደ እዚኽ ገምቼ ነበር ፤ ይኽን የገመትኩት ግን ጥቁር ቆዳ እና ጥቅልል ፀጉር ስለ አላቸው ብቻ ሰአይሆን (ምክንያቱም እነደ እዚኽ የሆኑ ሌሎች ዘሮች ስለ አሉ ፤ በራሱ ምንም ማለት አይደለም) ይልቁንም ኮልኪሲያኖች ፣ ግብፆች እና ኢትዮጵያዊያኖች ብቻ ከመጀመሪያ ጀመሮ ልጆቻቸውን የእሚገርዙ በመሆናቸው ነው ። በፍልስጤም የእሚኖሩት ሲሮፍንቃዊያን እና ሶሪያዊያኖች ፤ የመግረዝ ልማዳቸውን ከግብፆች እንደ ተማሩት ራሳቸው ሲናገሩ ፤ ቴርሞዶን እና ፓርቴኒዎስ በእሚባሉት ወንዞች አከባቢ የእሚኖሩት ሶሪያኖች ደግሞ ከኮልሲያኖች እንደ ተማሩት ይናገራሉ ። የግርዘት ስረዓት የአላቸው ሕዝብ እነ እዚኽ ብቻ ሲሆኑ ፤ አደራረጉም ግብፃዊያኖች በእሚያደርጉት አግባብ ነው ። መገረዝ ኹለቱም ጋር በጣም የቆየ ልማድ በመሆኑ ፤ ግብፃዊያኖች ከኢትዮጵያዊያን ይማሩት ወይንስ ኢትዮጵያን ከግብፃዊያን ይማሩት በእርግጠኝነት መናገር በአልችልም ፤ ሌሎቹ ሕዝብ ከግብፃዊያን ጋር በአላ፟ቸው ግንኙነት ከግብፃዊያን እንደ ተማሩት ግን የታወቀ ነው ።”
“So when I had come to consider the matter I asked them both; and the Colchians had remembrance of the Egyptians more than the Egyptians of the Colchians; but the Egyptians said they believed that the Colchians were a portion of the army of Sesostris. That this was so I conjectured myself not only because they are dark-skinned and have curly hair (this of itself amounts to nothing, for there are other races which are so), but also still more because the Colchians, Egyptians, and Ethiopians alone of all the races of men have practiced circumcision from the first. The Phoenicians and the Syrians who dwell in Palestine confess themselves that they have learnt it from the Egyptians, and the Syrians about the river Thermodon and the river Parthenios, and the Macronians, who are their neighbours, say that they have learnt it lately from the Colchians. These are the only races of men who practise circumcision, and these evidently practise it in the same manner as the Egyptians. Of the Egyptians themselves however and the Ethiopians, I am not able to say which learnt from the other, for undoubtedly it is a most ancient custom; but that the other nations learnt it by intercourse with the Egyptians [5] “
ከእዚኽ የሔሮድተስ ዘገባ በግልፅ እንደ እምንረዳው ፤ ሔሮደተስ ኮልኪስያኖች ግብፃዊያን ናቸው ብዬ እንድ ገምት የአደረገኝ ፤ ኹሉቱም ሕዝብ የአላቸው ጥቁር ቆዳ እና ጥቅል ፀጉር ሰአይሆን ፤ ከሌላው የዓለም ሕዝብ በተለየ መንገድ እነ እዚኽ ኹለት ሕዝብ የአላቸው ተመሳሳይ የግረዘት ባሕል ነው ፤ ምክንያቱም እንደ ሔሮድተስ ጥቁር ቆዳ እና ጥቅልል ጸጉር የአላቸው ፤ ከግብፃዊያን ውጭ ያሉ ሌሎች ሕዝብም በዓለም ላይ መኖራችው የእሚታወቅ በመሆኑ ፤ የቆዳን ጥቁረት ብቻ የወሰድኹ እንደ ሆነ ኮልሲያኖች ግብጻዊያን ናቸው ማለት አልችልም ፤ ነገር ግን እንደ ግብፆች እና ኮልኬሲያዊያን ዓይነት ፤ ተመሳሳይ የግርዘት ልማድ የአላቸው ጥቁር ሕዝብ በእሚታወቀው ዓለም የሌሉ በመሆናቸው ፤ ከቆዳቸው ጥቁረት በአሻገር የግረዘት ባሕላቸው መመሳሰሉ እነ እዚኽ ኹለት የተለያዩ ሕዝብ ተዛማጅ እንደ ሆኑ እንድ ገምት አድርጎኛል እያለ ነው።
ስለ እዚኽ ፦ ግብፆች እንደ ኮልኪስያኖች ጥቁር ቆዳ እና ጥቅልል ጸጉር የአላቸው ናቸው ማለት ነው ።
የቆዳ ቀለም እና የፀጉር ዓይነት በግልፅ የእሚታይ በመሆኑ ፤ ሔሮድተስ ተሳስቶ ሊሆን ይችላል የእሚያስብል ምንም ነገር የለም ።
ሔሮድተስ ብቻ ሰአይሆን የሐክልዩት ማሕበረሰብ ግብፃዊያን እና ኢትዮጵያዊያን አንድ ዓይነት ጠየም ያለ ቆዳ እንደ አላቸው ይናገራሉ ፦
“ካም የእሚለው ቃል ሸክላ ማለት ነው ፥ የካም ልጆች የሆኑት እና በፀሐይ ጠየም የአለውን የኢትዮጵያን እና የግብፆችን ቆዳ የእሚያመለክት ነው ።”
“The word Ham means adust and has reference to the dark sunburnt complexions of the Ethiopians and Egyptians, of whom Ham was the progenitor. [87]“
ይኽ እንደ እሚያመለክተው ፤ ግብፆች ፣ ህንዶች ፣ ኢትዮጵያዊያኖች ፣ ኮልክሲያኖች አንድ ዓይነት ጥቁር የቆዳ የቀለም እና የፀጉር ዓይነት አላቸው ማለት ነው ።
ይኽ እንዲህ ከሆነ ፤ ቮለኒ እንደ እሚለው ፤ ግሪኮች ኢትዮጵያዊ የእሚሉት ፤ ጥቁር የቆዳ ቀለም እና ጥቅልል ፀጉር የአለውን ነው የእሚለው አባባል ብዙም ተቀባይነት የለውም ፤ ምክንያቱም ፦ ተመሳሳይ የቆዳ ቀለም እና የፀጉር ዓይነት የአላቸው ፤ ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆኑ ፡ ግብፃዊ ፣ ኮልክሳዊ ፣ ህንዳዊ የእሚባሉ ሕዝብም ተመሳሳይ የቆዳ ቀለም የነበራቸው ሕዝብ ስለ ነበሩ ።
ህንዶች ፣ ግብፆች በተለይ ደግሞ የቀርጤስ (Crete) ጥቁር መሆናቸውን የሚያውቁ ግሪኮች ፤ ከግብጽ ተሻግረው የእሚገኙትን ኢትዮጵያዊያንን በተለየ ኹኔታ ጥቁር ብለው ይጠራሉ ብሎ ለማለት ያዳግታል ። ስለ እዚኽ ፦ ብዙ የተባለለትን ፤ ኢትዮጵያ ማለት ጥቁር ቆዳ የአለው ማለት ነው የእሚለውን መላምት ችግር ስናይ ፤ በአጠቃላይ እስከ አኹን በተገኘው ታሪካዊ ማስረጃ ላይ ተመርኩዞ ፤ ኢትዮጵያ ስለ እሚለው ስያሜው ምንጭ እና ትርጓሜ ፤ ምክንያተቢስ ከሆነ መሰለኝ ያለፈ እርግጠኛ የሆነ ነገር ማስቀመጥ የእሚቻል አይመስልም ።
ኢትዮጵያ የእሚለው ቃል ግን ፤ መጀመሪያ የሆኑ ሕዝብ ስያሜ ፤ ከእዚያኽም በግዜ ኺደት በጥንታዊው ዓለም ፤ በምዕራብ ፥ ከደቡብ ግብፅ አንስቶ እስከ ምድር ወገብ በእሚደርስ ፤ በምሥራቅ ቀይ ባሕርን እና የተወሰነውን የህንድን ውቅያኖስ የእሚያዋስኑትን አከባቢዎች የእሚወክል ቦታ እንደ ሆነ ፥ ወይንም አብዛኛው የአፍሪካን ቀንድ እና ሕዝቡን ወይንም ምሥራቅ አፍሪካን የእሚወክል እንደ ሆነ ፤ የተለያዩ ታሪካዊ ጥናቶች ያሳያሉ ።
ምስል 4 ፡ በአፍሪካ የጥንታዊ ኢትዮጵያዊያን መኖሪያ ።
ምስል 5 ፡ የጥንታዊ ኢትዮጵያዊያን መኖሪያ ከዘመናዊ የአፍሪካ ካርታ አንጻር።
ኢትዮጵያ ተብለው የተጠሩ ሰዎችን ማንነት በተመለከተ ፤ ሐገራዊው ብሒል ቆርቋሪው ፤ ከኖህ አራተኛ የሆነው ፤ የኢትዮጲስ ልጆች ናቸው ነው የእሚል እንደሆነ ከላይ በግርድፉ አይተናል ። ሮውሊንሰን የተባለው ፤ የአፍሪካ ፣ ኤስያ እና ሜድትራኒያን አከባቢ ጥንታዊ ስልጣኔዎችን አጥኝም ፤ ተመሳሳይ ነገር በማለት ኢትዮጵያዊያን ፤ ከሦሥቱ የኖህ ልጆች አንዱ የሆነው የካም ልጅ የሆነው የኩሽ ልጆች እንደ ኾኑ ያስቀምጣል ።
ይኽ ድምዳሜ ፤ ሳይንሳዊ ሰአይሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቢመስልም ፤ የመጽሐፍ ቅዱሱ ታሪክ ፥ በእድሜ ቀዳሚ ስለ ሌለው እና ብዙ ግዜ ታሪኮቹ መሬት ጋር ከአለ፟ው ኹኔታ ጋር ስለ እሚስማሙ ፤ እንደ ሮውሊንሰን የአሉ፟ ፤ የጥንታዊውን ዓለም ፤ የሕዝብ ታሪካዊ አመጣጥ እና አሰፋፈር የእሚያጠኑ ሰዎች ፥ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም እንኳን የኃይማኖት መጽሐፍ ቢሆንም ፤ እንደ መነሻ ይጠቀሙበታል ።
በእዚኽም መሠረት ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የመጀመሪያው መጽሐፍ የሆነው እና ዘፍጥረት የእሚባለው መጽሐፍ ይኽንን የሕዝብን ጥንታዊ ስብጥር ለእሚያጠኑ ሰዎች ለማመሳከሪያነት ለማገልገል ዋነኛው ነው ።
በዘፍጥረት ላይ ከአሉ፟ት ዋነኛ ታሪኮች አንዱ ደግሞ የኖህ ታሪክ ነው ። በኖህ ታሪክ መሠረት ፤ ኖህ ከሦሥት ልጆቹ እና ከሚስቶቻቸው ጋር ፤ በአጠቃላይ ስምንት ሆነው ፤ በምድር ላይ ከመጣ የጎርፍ መጥለቅለቅ በመርከብ ሆነው ሲተርፉ ፤ ባለ ሦሥት ፎቅ ሆኖ ከተሰራው ትልቁ የኖህ መርከብ ውጭ የነበረ ፤ የህይወት እስትንፋሱ በአፍንጫው ውስጥ የአለ፟ ፍጥረት በሙሉ (All teresterial creatures) በአጥለቅላቂው ጎርፍ ጠፍቷል ።
ይኽ ምድርን ኹሉ ያጥለቀለቀ ጎርፍ ከዘጠኝ ወር በኋላ ሲቀንስ ፤ የኖህ ቤተሰቦች ከመረከባቸው ወጥተው ፤ የዛሬውን የዓለም ሕዝብ ወላጆች እንደሆኑ ይናገራል ፦
ዘፍጥረት ፥ ምዕራፍ 10 ቁጥር 32
(መደበኛ ትርጉም)
“የኖኅ የልጆቹ ነገዶች እንደ ትውልዳቸው በእየ ሕዝባቸው እነዚኽ ናቸው። አሕዛብም ከጥፋት ውኃ በኋላ በምድር ላይ ከእነዚኽ ተከፋፈሉ።”
Genesis : Chapter 10 Verse 32
(KJV or King James Version)
“These are the families of the sons of Noah, after their generations, in their nations: and by these were the nations divided in the earth after the flood.”
የአማርኛው መጽሕፍ ቅዱስ ፤ በእዚኽ ክፍል ላይ አህዛብ የእሚላቸው የእንግሊዘኛው Nations ወይንም በዘመናዊ አማርኛ እኛ ሕዝብ ወይንም ሐገራት ወይንም ብሔሮች የእምንለውን ነው ።
በመጽሐፍ ቅዱሱ ታሪክ ፤ ለዓለም ሕዝብ የመጀመሪያ አባቶች የሆኑት ፤ የኖህ ልጆች ሦሥት ሲሆኑ እነርሱም ፦ ሴም ፣ ካም እና ያፌት የእሚባሉ ናቸው ። ካም ፥ በኹለተኛነት የተጠቀሰው የኖህ ልጅ ፤ በተራው አራት ልጆች አሉት ፤ እነርሱም ፦ ኩሽ ፣ ምፅራይም ፣ ፉት እና ከነዓን በመባል ይታወቃሉ ። እነ እዚኽም አራቱ የካም ልጆች ፤ በዘመናዊው ዓለም ፦
ኩሽ ፦ ኢትዮጵያ
ምፅራይም ፦ ግብፅ
ፉት ፦ ሊቢያ ወይንም ኑብያ
ከነዓን ፦ የታችኛው ሶሪያ እና ፍልስጤም
እንደሆኑ ይገመታል ።
ለግንዛቤ ያኽል ፤ በመጽሐፍ ቅዱሱ ታሪክ መሠረት ፤ ኹለተኛው የኖህ ልጅ ካም አባቱ ሰክሮ አይቶ ስለናቀው ፤ አባቱ ኖህ የልጅ ልጁን ፤ ማለትም የካምን ልጅ ከነዓን እና የልጅ ልጆቹ ባሪያ እንዲሆን ረግሞታል ፦
ዘፍጥረት 9:25
“እንዲህም አለ፡— ከነዓን ርጉም ይሁን፤ ለወንድሞቹም የባሪያዎች ባሪያ ይሁን ።”
አንዳንድ ሰዎች ግን ፤ አጥረተው ካለ ማንበብ ፤ ያጠፋው ካም በመሆኑ ፤ የተረገመው ልጁ ከነዓን ሰአይሆን አባትየው ራሱ ካም ይመስላቸዋል ።
ካምም ፤ የኩሽ (ኢትዮጵያ) ፣ ምፅራይም (ግብፅ) ፣ ፉጥ (ሊብያ ወይንም ኑብያ) እና ከነዓን (ሌቫንት) አባት ስለ ሆነ ፤ መላው የጥቁር ሕዝብ ወይንም የኩሽ ዘር በሙሉ የተረገመ ይመስላቸዋል ።
በእዚኽም በተሳሳተ የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም ላይ ተንተርሰው ፤ እኛ አፍሪካዊያን በእዛም ኢትዮጵያዊያን ፤ ባሪያ ኹኑ ተብለን ተረግመናል እና ለኋላ ቀርነታችን እና ለውድቀታችን ምክንያቱ ይኽ ርግማን ስለ ሆነ ፤ ለዘላለም ኋላ ቀር ልንሆን ተበይኗል የእሚል ጨለምተኛ ሆነዋል ።
በመጽሐፍ ቅዱሱ ላይ እንደ አየነው እርግማኑ ቢኖርም ፤ የተረገመው የካም ልጅ ከነዓን እንጂ ካም ራሱ እና መላው የካም ልጆች አይደሉም ፤ ስለ እዚኽ ፦ ኩሽ ፣ ምፅራይም እና ፉጥ የእሚባሉት የካም ልጆች ርግማኑ አይመለከታቸውም ። በመጽሐፍ ቅዱሱ መሠረትም የተረገሙት የከንዓን ልጆች ፤ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋ በአብዛኛዎቻቸው ጠፍተዋል ። በመጽሐፍ ቅዱሱም መሠረት ፤ እሥራኤል ከግብጽ ወጥቶ የወረሰው ፤ እነ እዚኽ የተረገሙትን እና የጠፉትን ሰዎች መሬት ነው። ስለ እዚኽ ፦ በመጽሐፍ ቅድሱ መሠረት አኹን በእምንኖርበት ዓለም ፤ ይኽ የኖህ እርግማን የእሚመለከተው ሕዝብ የለም ።
የእርግማኑን ጉዳይ በእዚኽ አስተካክለን ፤ ወደ ጀመርነው የጥንታዊ ኢትዮጵያዊያን ሕዝብ አጀማመር ታሪክ ስንመለስ ፤ ጆርጅ ሮውሊንሰን ፤ ስለ ኢትዮጵያ እንደ እዚኽ ይላል ፦
“ኢትዮጵያ የግሪክ ቃል ሆኖ ፤ ሮማውያኖችም የእሚጠቀሙበት ሲሆን ፤ (በግሪኮች እና በሮማኖች እሳቤ) የእሚያመለክተው ፤ በተለይ ከግብፅ በስተደቡብ የአለውን እና የዛሬውን አቢሲኒያ ወላጆችን የእሚያመለክት ነው ። ትንቢተ ሕዝቄል ምዕራፍ 29 ቁጥር 10 ላይ እንደ አለው ፤ እብራይስጦችም ኩሽ የእሚለውን ቃል ሲጠቀሙ ይኽን ሕዝብ እያሉ እንደ ነበር ምንም ጥርጥር የለውም ።
( ከሕዝቄሉ ክፍል ጋር የእሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ያነፃፅሩ ፦
) ።
ሆኖም ግን ፤ እብራይስጦች ኩሽ የእሚለውን ቃል በእሚጠቀሙበት ግዜ ፤ ከእዚኽም የአለፈ ሰፊ እንደምታ ባለው አውድ ይጠቀሙበትም እንደነበር ማየት ይቻላል ። በዘፍጥረት ምዕራፍ 2 ቁጥር 13 ላይ የተጠቀሰው ፤ በግዮን ወንዝ የእሚጠጣው ገነት ኤስያ ውስጥ እንጂ አፍሪካ ውስጥ የአለ፟ አይሆንም ። ኢስያዊው (The Asiatic) ‘ኩሽ’ በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ግዜ ይጠቀሳል ፤ ለምሳሌ ነብዩ ሕዝቄል ኩሽ እና ፐርዥያን ያገናኛቸዋል (ትንቢተ ሕዝቄል ፤ ምዕራፍ 38 ቁጥር 5) ኢሳያስ ደግሞ በመዕራፍ 11 ቁጥር 11 ላይ ከኤላም ጋር ያገናኘዋል። ይኽ ኢስያዊ (Asiatic) ኩሽ፤ እንደ እሚታየው ከፊል የአረብን ምድር ( ዘፍጥረት ምዕራፍ 10 ቁጥር 7 ፣ ትንቢተ ኢሳያስ ምዕራፍ 43 ቁጥር 3 ፣ ትንቢተ ኢሳያስ ምዕራፍ 45 ቁጥር 14 ) ፣ የሜሶፕታሚያ[2] ( ዘፍጥረት ምዕራፍ 10 ቁጥር 8 – 10) እንዲኹም ከእነ እዚኽም ስፍራ በአሻገር የአለ፟ውን የምሥራቅ ክፍል ( ትንቢተ ሕዝቄል ፤ ምዕራፍ 38 ቁጥር 5 ፣ ትንቢተ ኢሳያስ ምዕራፍ 11 ቁጥር 11) የእሚሸፍን ነው ። የትውልድ ሐረግ ጸሐፊው ፥ ምናልባት ፦ ጥንታዊ የእነዚኽ አከባቢዎች ነዋሪዎች ፤ ከግብፅ በላይ ያለችው የዛሬዋ ኢትዮጵያ ፥ ከፊል አረቦች ፣ ጥንታዊ ባቢሎኖች ከእነርሱም በስተምሥራቅ ያሉ ጎረቤቶቻቸው ሲ(ክ)ስያንስ ፤ የኖህ ኹለተኛ ልጅ የሆነው የፓትሪያሪኩ (አበው) ካም የልጅ ልጆች መሆናቸውን ነው ።”
“Now, Ethiopia, which is a Greek word, adopted by the Romans, designates (according to Greek and Roman notions) especially the country lying immediately to the south of Egypt, the modern Abyssinia ; and the Ethiopians are, especially, the people of this country, the progenitors of most of the modern Abyssinians. And, undoubtedly, this tract and people were included under the term “Gush” by the Hebrews, as is evident from Ezek. xxix. 10 (compare 2 Chron. liv. 9 ; xvi. 8 ; 2 Kings xix. 9 ; Isa. xx. 3—5 ; Dan, xi. 43; and Nahum iii. 9). But there are passages which show that the Hebrew application of the term, both geographically and ethnically, was considerably wider than this. The paradisiacal “Gush,” which was watered by the river Gihon (Gen. ii. 13), must have been in Asia, not in Africa. An Asiatic “Gush “is often indicated in Scripture, as where Ezekiel joins Gush with Persia (Ezek. xxxvii. 5), and where Isaiah couples it with Elam (xi. 11). This Asiatic Gush, apparently, embraces parts of Arabia (Gen. x. 7; Isa. xliii. 3; xlv. 14); of Mesopotamia (Gen. x. 8—10), and of the region still further to the eastward (Ezek. xxxviii. 5 ; Isa. xi. 11). The writer of the genealogy, therefore, probably intends to state, that the primitive inhabitants of these various tracts, the Ethiopians proper above Egypt, a portion of the Arabians, the primitive Babylonians, and their neighbors to the eastward, the Cissians, were among the descendants of Noah's second son, the patriarch Ham” [88].
ስለ እዚኽ ፦ እንደ ሮውሊንሰን ፤ ኢትዮጵያ በዋናነት ከግብፅ በስተደቡብ የእሚኖሩትን ሕዝብ የእሚወክል ቃል ሆኖ ፤ ከዛሬይቱ ኢትዮጵያ ወይንም በእርሱ ቋንቋ አቢስኒያ ወላጆች ጋር የተገናኘ ነው ።
ከእዚያኽም በመቀጠልም ፤ ጆርጅ ሮውሊንሰን የመጽሐፍ ቅዱሱን ከሕዝቦቹ ኹኔታ ጋር አዛምዶ ፤ በመጀመሪያው ጥንት ኢትዮጵያ ፥ ከፊል አረቢያ እንዲኹም የዛሬው ኢራቅ እና ኢራን አከባቢ ሰዎች የአበው ፤ የኖህ ልጅ ሐም ወይንም ካም ትውልድ ስፍራ ሰአይሆን አይቀርም ነው የእሚለው ። ይኽ ደግሞ ፤ መጽሐፈ አክሱም አንድ ትውልድ ጨምሮበት ፤ የኩሽ ልጅ ኢትዮጲስ ልጆች ነን ከማለቱ በስተቀር (ኖህ -> ካም -> ኩሽ -> ኢትዮጲስ) የአቀመጠው ገለጻ ፤ ከሮውሊንሰን ትንታኔ ጋር በይዘቱ ተቀራራቢ እንዲሆን የአደርገዋል ።
ይኽ የሮውሊንስን ፤ ኢትዮጵያ ማለት ከግብፅ በስተደቡብ የአለውን እና የዛሬይቱን አቢሲንያ (ኢትዮጵያ) የእሚያካትት ቦታ ነው እና ኢትዮጵያዊያኖች ከመካከለኛው ምሥራቅ ነዋሪዎች ጋር ይዛመዳሉ የእሚለው ‘ሳይንሳዊ’ ግምት ግን የሮውልኒሰን ግምት ብቻ ሰአይሆን ፤ በጉዳዩ ላይ ጥናት የእሚያደርጉ የብዙዎች ስምምነትም ነው ።
ለምሳሌ ፦ ኮስማስ በመባል የእሚታወቀው ፤ ከክርስቶስ ልደት በኋላ እ.ኤ.አ. በ530 ዓ.ም. አከባቢ የነበረ ፥ የስነምድር ተመራማሪ መጽሐፍ ፥ ከነበረበት የላቲን ቋንቋ ወደ እንግሊዘኛ የተሮጎሙት እና ለእንግሊዝ መንግሥት ጥቅም የአላቸውን የጂኦግራፍ እውቀት በማነፍነፍ የእሚታወቁት ፤ ሐለይኩት ማሕበረሰብ ፤ ከእላይ ከተቀመጠው ከጆርጅ ሮውሊንሰን ጋር የእሚስማማ አመለካከት አላቸው ።
እንዲያውም ፤ እነርሱ ኮስማስ ኢትዮጲያ ሲል ይኽን ሰፊውን ምሥራቅ አፍሪካን እያለ መሆኑን አስቀምጠው ፤ በዝምድናው ረገድ ግን ከሮውሊሰን ሰፋ አድርገውት ግብፅም ፣ ህንድም ፤ ከኢትዮጵያዊያን ጋር ተመሳሳይ ሕዝብ እንደሆኑ ማስረጃዎች አሉ ይላሉ ።
ለእዚኽም ከእሚያቀርቡት ማስረጃ አንዱ ፤ በዓለም ሕዝብ ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ ፤ የቀደመውን ዓለም ወይንም ሦሥቱንም አህጉር የእሚያካትት ግዛት የመሠረተው እና ከግሪክ ተነስቶ እስከ ህንድ ሰሜናዊ ግዛት የዘመተው ፤ ታላቁ አሌክሳንደር ሳይቀር ህንድ እና ኢትዮጵያ አንድ ሕዝብ እንደሆኑ ፤ ታላቁ አሌክሳንደር እና የእርሱ ሐገር ሰዎች ግሪኮች ይኽን ያምኑ እንደነበር ይላሉ ፦
“አሌክሳንድር ህንድን ከአወቀ በኋላ ፤ በግሪኮች ዘንድ ፥ ግብፆች ፣ ኢትዮጵያዊያኖች ወይንም ኑብያኖች እና ህንዶች ከአንድ ወገን እንደሆኑ ይታመን ነበር።”
“It was supposed by the Greeks, after the conquest of Alexander had made them acquinted with India, that the Egyptians, Ethiopians or Nubians and Indians, were derived from the same Stock.”
በተጨማሪም ፥ ጥንታዊ ባቢሎናዊያን ከኢትዮጵያ ነው የወጡት የእሚል ፤ ብዙ ማስረጃ ቢኖርም ፤ ያለ በቂ ሳይንሳዊ ምክንያት ችላ እንደተባለ ይነገራል ፦
“… ጥንታዊ ባቢሎናዊያን ከኢትዮጵያ እንደ መጡ ይታመን ነበር ። ነገር ግን ፦ ይኽንን እምነት የሚደግፉ የጎሉ ማስረጃዎች ቢቀርቡም ፥ አኹን አኹን ግን ተወግዟል…”
“...has been supposed that the Early Babylonians came from Ethiopia; but though in support of this view some striking evidence was advanced, it is now rejected.... [87]“
ሔሮድተስ ፥ አሞናዊያን ወይንም የዛሬው ዮርዳኖስ የእሚባለው አከባቢ ሰዎች ፥ የኢትዮጵያዊያን እና የግብፃዊያን ድብልቅ ሕዝብ እንደሆኑ ይናገራል ፦
“…፣ እናም አሞናዊያን ፤ ከኢትዮጵያ እና ከግብፆች የተውጣጡ ሰፋሪዎች እንደ መሆናቸው ፤ ቋንቋቸው የኹለቱ ቅልቅል ነው ።”
“..., and the Ammonians do so also after their example, being settlers both from the Egyptians and from the Ethiopians, and using a language which is a medley of both tongues... [5] “
ስለ እዚኽ ፦ እነ እዚኽን ታሪካዊ ምልከታዎች ከገሐዱ እውነታ ጋር ስናዳምር ፤ ኢትዮጵያዊያን በዋናነት ኩሽ የእሚባሉት ወይንም የኩሽ የልጅ ልጆች ሲሆኑ ፤ ከግብፅ ፥ ሊብያ ፥ ሲሮፍኒቃዊያን (የጥንት ሶሪያ እና ሊባኖስ) ፣ ደቡብ አረቢያ ፣ ፐርዢያ እና ህንዶች ጋር የካም ልጆች የሆኑ ፤ እንደ ባቢሎናዊያን ላሉ ሕዝብ ደግሞ መነሻ የሆኑ ሕዝብ ናቸው ።
ይኽ እንግዲኽ ፤ በታሪክ መጀመሪያ አከባቢ የነበረውን እውነታ የእሚያሳይ ነው እንጂ ፤ ታሪክ በኺደት ስብጥሩን በተለያየ መልኩ ከቀየረው በኋላ ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የኩሽ ልጅ ኢትዮጲስ የልጅ ልጆች ብቻ ነው የአሉ፟ት ማለት አይደለም ።
እንዲያውም ፤ የአኹን ኢትዮጵያዊያኖች ፥ የሴም ዘር ከሆኑት የእሥራኤል ልጆች ፤ አይሁዶች ጋር በጣም የቆየ ትስስር እና ይኽንም ተከትሎ ቅልቅል እንደ አላቸው በዓፈ ታሪክም ደረጃ ቢሆን ይነገራል ። ይኽን አፈታሪክ ለመደገፍ መቅረብ የእሚችል ፤ በኢትዮጵያዊያን እና በአይሁድ መካከል የአለው የባህል እና የቋንቋ መመሳልም ቀላል አይደለም ።
ብዙዎቻችን እንደ እምናውቀው ፤ ለብዙ ሺ ዓመታት ኢትዮጵያን የመራት ንጉሣዊ ስርወ መንግሥት ፤ ኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ሳባ ፤ ከአይሁዳዊው ንጉሥ ዳዊት ልጅ ንጉሥ ሰለሞን የወለደችው ነው በእሚባለው ፤ ቀዳማዊ ምንሊክ ስርወ መንግሥትነት ራሱን የእሚጠራው ነው ። ይኽ ማለት ግን ፤ ኢትዮጵያዊያን ሴማዊያን ብቻ ነን ፣ ከካም ጋር ትስስር የለንም አሉ ማለት ሰአይሆን ፤ ታሪኩ እውነት ይኹንም አይኹን ፤ ከእሥራኤል ጋር ተቀላቅለናል ነው ።
ይኽ ደግሞ ፤ በዓለም ዓቀፍ የንግድ መስመር ላይ አመቺ ቦታ ላይ ለብዙ ሺ ዓመታት የአለ፟ች ለምለም ሐገር ፤ ከሌሎች የዓለም ሕዝብ ጋር ብዙ የመቀላቀሏ አንድ ምሳሌ እንጂ ብቸኛ ታሪካዊ ክስተት አይደለም ። በኢትዮጵያዊያኖች ስሪት ውስጥ ፤ የግሪክ ፣ አርመን ፣ አረብ እና ሌሎች ሕዝብ ድብልቅ ከእዚኽ ያልተናነሰ ነው ።
ይኽም ፤ የኢትዮጵያዊያን ታሪክ ብቻ ሰአይሆን ፤ አንድ ግዜ የሰው ልጅ ፤ የየብስ እና የባሕር ላይ የርቀት ወሰኖችን ፤ በተለያየ መጓጓዣ መቅረፍ ከቻለ በኋላ ፤ የሰው ልጆች ነገዳዊ ማንነት በእየገዜው የአለፈው ታሪክ አካል እንዲሆን የተገደደበት ኹኔታ ነው የአለው ።
ጆርጅ ዌልስ የተባለው ፤ ታሪክ ጸሐፊ እንደ እሚለው ፤ በታሪክ ኺደት ውስጥ ሕዝብ የእሚሰባጠሩበት አግባብ ፤ እንደ ዛፍ ቅርንጫፍ ላይገናኙ እየተለያዩ ሰአይሆን ፤ እንደ ደመና የእሚደበላለቅ እና እንደገና ደግሞ የእሚከፋፈል ቅይጥይጥ ትስስር የአላቸው እንደሆኑ ነው ፦
“የሰው ልጆች እንደ ደመና ፥ ያለ ችግር በመዋለድ እንደ እሚያያዙ ፤ ከእዛም እንደ እሚለያዩ ፥ እንደ ገናም እንደ እሚቀላቀሉ እና እንደ እሚጣመሩ ፤ ማስታወስ አለብን ። የሰው ልጆች ተመልሰው እንደ እማይዋሀዱ እንደ ዛፍ ቅርንጫፎች አይደለም የእሚሰባጠሩት ። ይኽ ፥ የሰው ልጅ ዘሮች በእየ አጋጣሚው እንደ እሚቀላቀሉ ፤ በዘላቂነት መገንዘብ ግድ ይለናል ። ይኽን ከአደረግን ጭካኔ ከተሞላበት ውዥንብር እና ወራዳ ዝበት ያድነናል ። ሰዎች ዘር የእሚለውን ቃል እንደ አሻቸው እየተጠቀሙበት ፥ በእዚያኽ ላይ ተመስርተው የቂል ድምዳሜ ላይ ይደርሳሉ ። የብሪታኒያ ዘር ፤ አውሮፓዊ ዘር እያሉ ይናገራሉ ። እውነታው ግን ፤ ኹሉም ሊባል በእሚችል ደረጃ አብዛኛው አውሮፓዊ ፥ የቡናማው ፣ የነጭ-ጥቁር ፣ የነጭ እና የሞንጎላዊ ድብልቅልቅ ያለ ቅልቅል ናቸው ።”
“We have to remember that human races can all interbreed freely and that they separate, mingle and reunite as clouds do. Human races do not branch out like trees with branches that never come together again. It is a thing we need to bear constantly in mind, this re-mingling of races at any opportunity. It will save us from many cruel delusions and prejudices if we do so. People will use such a word as race in the loosest manner and base the most preposterous generalizations upon it. They will speak of a “British” race or of a “European” race. But nearly all the European nations are confused mixtures of brownish, dark−white, white and Mongolian elements [89].”
ስለ እዚኽ ፦ ምንም እንኳን ፤ የሰው ልጅ መጀመሪያ አከባቢ ማሕበረሰብ በእሚመሠርትበት ወቅት የትውልድ ሐረግን የተከተለ የእሚሆንበት መንገድ የጎላ ቢሆንም ፤ አንድ ግዜ ግን የተለያዩ መንደሮች በመንገድ ፣ በንግድ ፣ በጦርነት ወይንም በሌላ መንገድ ከተገናኙ በኋላ የትውልድ ሐረግ እየላላ እና (ቢያንስ ለሚዛናዊ አዕምሮ) ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ፋይዳው የአላቸው ጉዳዮች የማሕበረሰብ ማስተሳሰሪያ ገመድ እየሆኑ የእሚኼዱ እንደ ሆነ ግልፅ ነው ።
እኛ ደግሞ የአለነው የሰው ልጅ ማሕበረሰብ ሆኖ መቆም ከጀመረ ቢያንስ 5 እና 6 ሺ ዓመት በኋላ በመሆኑ ፥ በእዚኽ ረዥም እና ፈታኝ ዘመናት ትውልድ እንደ አሻው ወይንም እንደ አመቸው ሲደበላለቅ እንደ ነበረ እና የውልደት ነገዳዊ ትስስር በጣም የላላበት የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንደ አለን መገመት ይቻላል ።
ከእዚኽ ተነስተን ፤ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ማለት የእምንችለው ፤ ኢትዮጵያዊያኖች ፤ ከግብፅ በስተደቡብ እና ቀይ ባሕርን በእሚያዋስነው ሰፊ አከባቢ የእሚኖሩ እና ወደ ታሪክ መጀመሪያ አከባቢ ፤ ከግብፆች ፣ ሲሮፍንቃዊያኖች ፣ ኑብያኖች ፣ ህንዶች ፣ ባቢሎናዊያን ጋር የቀረበ ዝምድና የነበራቸው ጥንታዊ ሕዝብ ናቸው የእሚለው ይሆናል ።
ከእዚኽ በተጨማሪም ፤ ኢትዮጵያ ማለት ጥቁር ሕዝብ ማለት ነው ከእሚለው ጨምሮ ፤ ኢትዮጵያ ለእሚለው ስያሜ የእሚሰጡት ትርጓሜዎች ፤ በአስተማማኝ ታሪካዊ ማስረጃ ላይ የተደገፉ መላምቶች ሰአይኾኑ ፤ መሠረተ ቢስ ትንታኔዎች በመሆናቸው ፤ እስከ አኹን በአለው ታሪካዊ እውቀት ፤ ኢትዮጵያ ማለት ይኽን ማለት ነው ብሎ በእርግጠኝነት ማስቀመጥ አይቻልም ።