ፈረንሳዊው የፖለቲካ ፈላስፋ ጃን ዣክ ሩሶ ፤ ዲስኩር በአልኩልነት ላይ (Discourse on inequality) በእሚለው አጠር ያለች መጽሐፉ መግቢያ ላይ እንደ እዚኽ ይላል ፦
“ለእኔ እንደ እሚመስለኝ፥ የሰው ልጅ ከአለው ሳይንሶች ኹሉ በጣም ጠቃሚው ፥ ነገር ግን በጣም ለጋ የሆነው የስነ-ሰው ሳይንስ ነው፡“
“Of all human sciences the most useful and the most imperfect appears to me to be that of mankind: [57]“
የማሕበራዊ ሳይንስ በአጠቃላይ የአለው እድገት ከሌሎቹ ሳይንስ መስኮች በተለየ ኹኔታ ማዝገሙ እና የእዚኽም መስክ አንድ ዘውግ የሆነው ፖለቲካዊ ሳይንስ እንደ መስክ ብቻውን ሳይንስ ሆኖ ለመውጣት ያሳየው ዝግታ ቀላል የእሚባል አይደለም ።
ማሕበራዊ ሳይንስ በእሚገባው ፍጥነት አድጎ የእርሱም አንድ ፈርጅ የሆነው የፖለቲካ ሳይንስ በግዜ ስለ አልዳበረ ፤ ለረዥም ዘመን የሰው ልጅ በአብዛኛው መንግሥትን ያቆም እና ያፈርስ የነበረው ያለ ምንም ንድፈ ኃሳባዊ መሠረት ነበር ። ከእዚኽም የተነሳ ፤ መንግሥት ወደ ስልጣን የእሚመጣበት ፣ ከስልጣን የእሚወርድበት ወይንም ባለ ስልጣናት የእሚተካኩበት ፤ ተቀባይነት የአለው እና የረጋ መንገድ በአለመኖሩ ፤ መንግሥት ኹል ግዜ ፦ በሴራ ፣ በድንገተኛ ነፍስ ግድያ ፣ በድንገተኛ ሕዝባዊ አመፅ ፣ ከውጭ በመጣ ወረራ ፣ ወዘተ ፤ የመፍረስ ቋሚ አደጋ የተጋረጠበት እና በእዚኽም መልኩ መፍረስ ብቸኛው የመንግሥት መለወጫ መንገድ የሆነበት ነበር ።
ይኽ ቀላል የእማይባል እና መተኪያ የሌለው ሚና የአለው መንግሥት ፤ ያለምንም ሳይንሳዊ መርህ አለመገንባቱ የእሚፈጥረው ማሕበራዊ ችግር ሰአያንስ ፤ ድንገት በአንድ ሌሊት በእዚኽ መልኩ መፍረሱ ደግሞ ፤ እንደገና ፤ ከሳይንሳዊ መርህ ውጭ የድሮውን ተመሳሳይ ወይንም የእሚብስ ማሕበራዊ ችግር የእሚፈጥረው ሌላ የቀደመውን ግብታዊውን መሰል መንግሥት እስኪ መሠረት ደግሞ ሕዝብ ለስልጣን በእሚደረግ ትግል ፣ ሴራ ፣ ጦርነት ፣ አመፅ እንደገና የእሚናጥበት ኹኔታ ነበር ።
እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ ፤ ከአምስት ሺ ዓመታት ገደማ በላይ የኖረው ፤ የአብዛኛው የዓለም ሕዝብ የፖለቲካ ታሪክ ይዘቱ ይኽ ነበር ።
ይኽም ማለት የሰው ልጅ የፖለቲካ ሳይንሱን ለማሳደግ ከሌላው ሳይንሳዊ መስክ በተለየ ኹኔታ መዘግየት አሳይቷል ማለት ነው።
በፖለቲካ ሳይንስ መስክ ሳይነሳዊ ስለ መሆን ስንነጋገር ፤ በተፈጥሮ ሳይንሱ መስክ እንደ አለው ዓይነት ዓለም-ዓቀፋዊ ሳይንሳዊ እውነታዎች በማሕበረ ሳይንሱ መስክ ብርቅዬ ቢሆኑም ፤ ከዶግማ ወይንም ማንም ሳይጠይቅ እንደ ዘላለማዊ እውነት ሊቀበላቸው ይገባል ከእሚባሉ አስተሳሰቦች ወጥቶ ፤ የሰው ልጅ በተመራማሪነቱ ጠይቆ ፣ ተችቶ ፣ አዳብሮ ስለ ተቀበላቸው እና በስፋት ተግባራዊ ስለ ሆኑ እና ተቀባይነት ስለ አላቸው ፦ ስለ ሕገመንግሥታዊነት ፣ ስለ ግልጽ ሕግ አስፈላጊነት ፣ ስለ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ፣ ወዘተ ፤ እየተነጋገርን መሆኑን ማስመር ተገቢ ነው።
የሰው ልጅ የማሕበራዊ ሳይንስ እውቀቱን ለማሳዳግ ፤ ከሌላው የሳይንስ ዘርፍ ይልቅ በጣም የዘገየ እንደ ነበር ፤ ከእሚያሳዩን ነገሮች አንዱ የሰው ልጅ ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የእሚዳኝበትን ሕግ እና ሐገር እንዲኹም መንግሥቱን የእሚያዋቅርበትን ሕገመንግሥት በጽሑፍ ለማስፈር የነበረበት ፈተና እና መዘግየት ነው።
የሰው ልጅ መንግሥት አቋቁሞ በሺ የእሚቆጠሩ ዓመታትን ከአሳለፈ በኋላ ነበር እነ እዚኽን ኹለት ዋነኛ መንግሥታዊ ሰነዶች ፤ ሕግ እና ሕገመንግሥትን በጽሑፍ ወደ ማስፈር የመጣው።
በሳይንሳዊ መንገድ ፤ መንግሥት መች እና የት ጀመረ የእሚለውን ጥያቄ በእርግጠኝነት መመለስ ቢያስቸግርም ፤ የሰው ልጅ እንደ ማሕበረሰብ መዋቀር ከጀመረበት ስለ እዚኽም ከዛሬ 6 ሺ ዓመታት በፊት አንስቶ ፤ መጠኑ እና ዓይነቱ ይለያይ እንጂ ፤ ያልተጻፈ የማሕበራዊ አስተዳደር መርህ የነበረው እና ይኽንን መርህ በስምምነት ወይንም በአንድ የሆነ ዓይነት ኃይል የእሚያስከብርበት አግባብ እንደ ነበረው ግን ፤ የብዙዎች ስምምነት ነው ።
ይኽ የልቦናዊ ስምምነት መንግሥት ግን ፤ ከልቦና ስምምነት ወጥቶ በእሚታወቁ እና በተጻፈ ሕግ ፤ የእሚመሠረት እና የእሚመራ መንግሥት እስኪ ሆን ፤ ቀላል የእማይባሉ ዘመናት ተቆጥረዋል።
ይኽንም የእሚያሳየን ፤ የሰው ልጅ የስነ ጽሑፍ ያዳበረው ፤ የዛሬ 5200 ዓመታት ገደማ ወይንም ከክርስቶስ ልደት በፊት 3200 ዓመታት ቀደም ብሎ ቢሆንም ፤ ይኽን የስነ ጽሑፍ ችሎታዉን ፤ ለግላዊ እና ለማሕበራዊ ሕይወቱ መቃናት ከፍተኛ ሚና ለእሚጫወተው ፤ የሕዝብ መዳኛ ሕግን በጽሑፍ ለማስፈር እስኪ ይንቀሳቀስ ፤ ስነ ጽሑፍን ከአደበረ ከ1500 ዓመታት በላይ መዘግየቱ አንዱ እና ቀዳሚው ነው።
በሌላ አገላለፅ ፤ የሰው ልጅ መንግሥትን ከተፈጥሮዋዊ ባሕሪው ተነስቶ ለመመሥረት የፈጠነውን ያኽል ፤ መንግሥት ሕዝብ የእሚዳኝበትን ሕግ እና የመሠረተውን መንግሥት መመሥረቻ መርህ ወይንም የመንግሥቱን ሕግ በጽሑፍ ለማስቀመጥ አልፈጠነም።
የመጀመሪያው የተጻፈ ሕግ ፤ በሜስፖታሚያ የነበረው የባቢሎኑ ንጉሥ ፤ ሑመራቢ ፤ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1750 ቅ.ክ.[1] በድንጋይ ጥርብ ላይ ጽፎ ያስተዋወቀው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ነው ። ይኽ የሑመራቢም ሕግ በታሪካዊ ክስተትነት የመጀመሪያው ይሁን እንጂ ፤ ሕግ የማውጣት እውቀት ትርጉም በአለው መልኩ ዳብሮ ፤ ቢያንስ አንድን ሕዝብ በቀጣይነት በአግባቡ እስኪዳኝ ፤ ከክርስቶስ ልደት በኋላ የነበረው የሮማ መንግሥት እስኪ መጣ ዘግይቷል ። ስለ እዚኽ ፦ የሰው ልጅ ፖለቲካዊ ስልጣኔ ከ3000 – 3500 ዓመታት ገደማ ከተጓዘ በኋላ ነው ፤ ሰፊ እውቅና የነበረው ሕግ አርቅቆ ፤ እርሱንም በጽሑፍ አስፍሮ በእዚኽም የተጻፈ ሕግ ማሕበረሰብን ማስተዳደር የጀመረው ።
ቀደምት የእሚባሉ የግብፅ ፣ የህንድ ወይንም የቻይናን ስልጣኔ ያጠኑ ሰዎች እንደ አረጋገጡልን ፤ መንግሥታቱ ስመ ጥር ነገሥታት አንግሰዋል ፣ ትልልቅ የጦር ኃይል ገንብተው ብዙ ዘመቻ አካኺደው ግዛት አስፍተዋል ፥ ኃብት አካብተዋል ፣ ፍርድ ቤት እና ዳኞች አቁመው ሕዝብ ዳኝተዋል ፤ ይኽን ኹሉ ትልልቅ ሥራ የሰሩ እነዚኽ ጥንታዊ መንግሥታት ግን ፤ አንድም የታወቀ የተጻፈ ሐገራዊ ሕግ ኖሯቸው ከሑመራቢ በፊት አልተገኙም ።
ለምሳሌ ፦ አስገራሚው የግብፅ ስልጣኔ ባለቤት የሆኑት ግብፃዊያን ፤ ትልልቅ ከተሞች ግንብተዋል ፣ የተለያዩ ይዘት የአላቸው የስነጽሑፍ ሥራዎች ሰርተዋል ፣ የእዛኔውን ዓለም በንግድ አዳርሰዋል ፤ ሰፊ ተደራሽነት የአለው በተዋረድ የተዋቀረ የፍርድ ቤት መዋቅር አቋቁመዋል ፤ ነገር ግን ለ 3,000 ዓመት የቆየው ይኽን መሰሉ ውስብስብ የግብፅ ስልጣኔ ፤ በታላቁ በአሌክሳንደር ፍፃሜውን እስኪ ያገኝ ድረስ ፤ አንድም የተጻፈ የወንጀለኛ መቅጫም ሆነ የፍትኃብሔር ሕግ ግን አልነበረውም ።
ያም ማለት ፤ ዳኝነቱ ኹሉ ፤ በወቅቱ በፍርድ ወንበር ላይ በተቀመጠው ፈራጅ ፤ ልምድና የልቦና ፍርድ መሠረት እንጂ ፤ ተጽፈው በተቀመጡ እና ዘመን ተሸጋጋሪ በሆኑ ሕግጋት አልነበረም የእሚካኼደው ።
ይኽ የግብፅ ገፅታ ብቻ ሰአይሆን ፤ እንደ መብረቅ ብልጭ ብሎ የጠፋው ፤ የሑመራቢም ሕግ ቢሆን ፤ የሜስፖታሚያን መንግሥታዊ አሰራር በዘላቂነት የቀየረ ክስተት ሰአይሆን አንድ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው የእሚመስለው ። ምክንያቱም ፦ ከሑመራቢ በኋላ ፤ የባቢሎን መንግሥት በተጻፈ ሕግ በቋሚነት ሲመራ የእሚያሳይ ታሪካዊ ማስረጃ የለም ።
የጥንቱ ዘመን መንግሥታት ፤ አዋጅ በጽሑፍ ሊያስተላልፉ ይችላሉ ፤ ትላልቅ ፕሮጀክቶች አዘው ሊያሰሩ ይችላሉ ፤ ሕዝባቸውን በተጻፈ እና በእሚታወቅ ሕግ ሲዳኙ ግን አይታይም ። ከሑመራቢ ትንሽ ዘግየት ብሎ የመጣውን ፤ ሙሴን እና የሙሴን ሕግ የእሚመራበትን እሥራኤልን ሳናካትት ማለት ነው ።
በአንድ በኩል ፤ የሰው ልጅ በአልተጻፈ ሕግ እየተመራ ፤ ትላልቅ የመንግሥት ተቋዋማትን እያቋቋመ እና ብዙ አስገራሚ ስልጣኔዎችን እየመስረተ መቀጠል መቻሉ የሰውን ልጅ ተፈጥሮ ትልቅነት ሊያሳይ ሲችል ፤ እስከ ጥቂት መቶ ዓመታት ድረስ ፤ የሰው ልጅ ብዙ አስገራሚ የክስተብርሀን (Enlightenment) ውጤት የሆኑ የስልጣኔ ፋናወጊ ሥራዎች ሲሰራ ፤ ግልፅ የተጻፈ እና የእሚያሠራ ሕግ ሳይኖረው መቅረቱ ፤ የሰውን ልጅ ኑሮ ምን ያህል አክብዶበት እንደ ነበር ሲታይ ፤ የሰው ልጅ በተጻፈ ሕግ ለመመራት ፤ ለምን ይኽን ያኽል ግዜ እንደ ወሰደበት መገመት ራሱ ያስቸግራል ። ስንት ነገር በግዜ ሲበራለት ይኽ ለምን እንደ ዘገየበት እንቆቅልሽ ነው ።
ትላልቅ ተቋማትን ያለ ብዙ ችግር መገንባት የቻለ የሰው ልጅ ፣ በሳይንስ እና በቴክኖሎጂ እውቀቱ ለዛሬው እውቀት እንኳን መሠረት የሆኑ ብዙ ግኝት ባለቤት የሆነው የጥንቱ ስልጣኔ ፤ ስነ ሕግ እና ስነመንግሥት እጅግ ፈታኝ ወይንም የተጋረዱበት ኩነቶች እንደ ነበሩ ታሪካዊ ኃቅ ነው ። ግሪኮች ፣ ህንዶች ፣ ቻይናዎች ብዙ ተፈላስፈዋል ፤ ብዙ እውቀትም አቆይተውልናል ፤ እነ እዚኽ እውቀቶቻቸው ግን የመንግሥታቸው መመሥረቻ እና ሕዝብ መዳኛ የተጻፉ ሕግጋት ሆነው ግን አይታይም ።
በሰው ልጅ ምድራዊ መንግሥት ታሪክ ውስጥ ፤ ከሑመራቢ በኋላ ፤ በሕዝብ ሕግ አርቅቅልን ተብሎ ፤ ከክርስቶስ ልደት በፊት 500 ዓመት ገደማ ሕግ ያረቀቀው ፤ የአቴንሱ ድሬውኮ ነው ። ይኽ በተመዘገበ ታሪክ ፤ የመጀመሪያው በሕዝብ ጥያቄ የመጣው የድሬውኮ ሕግ ፤ እጅግ የእማያፈናፍን እና ጥቅል ጎመን የሰረቀን እንኳን በሞት የእሚቀጣ ስለሆነ ፤ አስጨናቂ እና የእማያሰራ በመሆኑ ፤ ሕዝቡ ራሱ እስኪ ሽረው ብዙም ግዜ አልወሰደም ። በእዚኽ በእኛ ዘመን ድሬውኮ የእሚታወሰውም ፤ Draconian (ድሬውኮኒያን) የእሚለው ከስሙ የተወሰደው የኢንግሊዘኛ ቃል አላላውስ የእሚል ሕግ የሚገለፅበት በመሆኑ ነው ።
ድሬውኮም ምነው ፤ እንዲኽ ያለ ጨካኝ ሕግ አወጣህ ፤ ጥቅል ጎመን የሰረቀው ሳይቀር ፤ ቀላል ጥፋት ያጠፉ ኹሉ እንዴት በሞት ይቀጣ አልኽ ? ተብሎ ሲጠየቅ ፤ “ጥቅል ጎመን የሰረቀው በሞት መቀጣቱ ተገቢ ነው ፤ ከእዚያኽ የባሰ ላጠፉ ግን ከሞት የተሻለ ቅጣት አለመገኘቱ ነው ችግሩ” ዓይነት መልስ ሰጥቷል ።
ፕሉታርክ ፤ የድሬውኮ ሕግ የተሻረበትን ምክንያት እና ድሬውኮም ትንንሹንም ጥፋት በሞት የእሚቀጣውን ሕጉን የተከላከለበትን አኳኋን እንደ እዚኽ አስቀምጦታል ፦
“…፣ ምክንያቱም እጅግ የከረሩ እና ቅጣታቸውም የበዛ ነበር ፤ በሥራ መፍታት ጥፋተኛ የተባሉት በሞት እስከ መቅጣት የእሚደርስ ፤ ጥቅል ጎመን ወይንም ቱፋ (አፕል) የሰረቁትን ፤ ቤተመቅደስ እንደ ዘረፉ ወይንም ነብሰ ገዳዮች እንደሆኑ ሰዎች የእሚቀጣ ነበር ። … በአንድ ወቅት እርሱ (ድሬውኮ) ራሱ ፤ ምን ነው ለአብዛኛው ጥፋት ቅጣቱን ሞት አደረግኸው ተብሎ ሲጠየቅ ፤ ‘አነስተኛ ጥፋቶቹ ይገባቸዋል ፤ ለከፍተኛዎቹ ግን ከሞት የእሚበልጥ ሌላ የለኝም’ ብሎ መልሷል ።”
“ …, because they were too severe, and the punishments too great; for death was appointed for almost all offences, in somuch that those that were convicted of idleness were to die, and those that stole a cabbage or an apple to suffer even as villains that committed sacrilege or murder. …and he himself, being once asked why he made death the punishment of most offences, replied, “Small ones deserve that, and I have no higher for the greater crimes. [77]“
በአንድ በኩል በተጻፈ ሕግ መመራት የእሚቀርፈውን ችግር የተገነዘቡ ፤ በሌላ በኩል አፋኝ የነበረውን የድሬውኮ ሕግ አላላውስ የአላቸው አቴንስዎች ፤ የድሬውኮን ሕግ ችግር ተረድቶ የተሻለ የእሚያሰራ ሕግ እንዲያረቅላቸው ፤ ኃላፊነቱን በኹለተኛነት ሶሎን ለእሚባል ሊቅ ነበር በድጋሚ የሰጡት ። ሶሎንም ፤ የድሬውኮን ሕግ ሙሉ ለሙሉ ሊባል በእሚችል ደረጃ ቀይሮ አዲስ ሕግ ከአወጣላቸው በኋላ ፤ አሻሽልልን እንደ አይሉት ፤ አስር አመት አቴንስን ጥሎ ፤ ከሐገር ሐገር ሲዞር እንደ ከረመ የወቅቱ ታሪክ ይዘግባል ።
ሕግ ማርቀቅ ለሰው ልጅ ቀላል ፈተና አልነበረም !
ከግሪኮች በኋላ የዓለም ኃያል መንግሥት ሆነው የመጡት ሮማዊያን ፤ የተለያየ ሕግ ቢያወጡም ፤ እነርሱም ያወጡዋቸው ሕግጋት ውጤታማ እና ተቀባይነት ያልነበራቸው ናቸው ። ለምሳሌ ፦ በአንድ ወቅት በብድር ላይ የነበረው የሮማዊያን ሕግ ፤ ‘ከኹለት ወይንም ከእዚያኽ በላይ ከሆኑ ሰዎች ብድር ተበድሮ መክፈል ያልቻለ ሰው ፤ አበዳሪዎቹ ፤ ሰውነቱን ለኹለት ቆርጠው ይካፈሉ’ ይል ነበር ፦
“አበዳሪው ብቸኛ ከሆነ እና ከፈለገ ፤ በድንጋይ ላይ በተጻፉት ሕግጋት መሠረት ፤ ‘ባለዕዳውን’[2] አበዳሪው ሊገድለው ወይንም ከሮም ውጭ ወደ አለ ቦታ በባርነት ሊሸጠው ይችላል ፤ አበዳሪዎቹ ከአንድ በላይ ከሆኑ ፤ አበዳሪዎቹ የባለ ዕዳውን አካል ቆርጠው ፤ በቁጥራቸው ልክ እና በአበደሩት መጠን ልክ የባለ እዳውን አካል እኩል ሊካፈሉት ይችላሉ።”
“If only creditor was interested, he could, according to the words of the Tables, kill the ‘addictus’ or sell him into slavery beyond the borders of Rome; if a plurality of creditors, they could cut the debtor’s body into proportionate parts and each take his share. [84]”
ከእነ እዚኽ የግሪክ እና የሮም ታሪኮች የእምናየው ፤ ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበሩ ግሪክ እና ሮማዊያን ፤ የተጻፈ ሕግ ለመጠቀም ቢሞክሩም ፤ በእዛኽን ወቅቱ የእሚያወጡዋቸውን ሕግጋት መተግበር ከመፍትሔ ይልቅ የባሰ ነገሮችን የእሚያወሳስብ በመሆናቸው ፤ ሕዝቡ በቸልታ የእሚገድላቸው ሕግጋት እንደ ነበሩ ነው ።
ምናልባት ከቀደሙት ግሪክ እና ሮም ሕግ የማውጣት ኺደት ፤ ዓለም የተረፈው ነገር ቢኖር ፤ ሕግ በማውጣት እና ፍትኃዊ እና ተቀባይነት የአለው ሕግ በማውጣት መካከል የአለውን ከፍተኛ ልዩነት ነው ።
በእሚታወቅ እና በተጻፈ መርህ የእሚመራ ፤ የፍትሕ ስረዓት መኖር አስፈላጊ የሆነውን ያኽል ፤ በመጥፎ መርህ የእሚመራ የፍትሕ ስረዓት ፤ ከሕግ አልባነት በላይ ማሕበራዊ ኪሳራ የእሚያስከትልም ይመስላል ።
እንግዲኽ በእዚኽ መልኩ የሰው ልጅ ፤ የእሚያሰራ ሕግ አስፈላጊነትን ለመረዳት እና ለመቅረጽ ለረዥም ግዜ ከዳከረ ብኋላ ፤ በዓለም ላይ በአኹኑ ሰዓት ለእሚገኙት አብዛኛዎቹ ሕግጋት ፤ በይዘቱም ባይሆን በአስተላለፈው ልምድ ፤ መሠረት የሆነው ፤ ከክርስቶስ ልደት በኋላ እ.አ.አ. ከ527 - 565 ዓ.ም. በምሥራቃዊው የሮም መንግሥት በኮንስታንቲኖፖል ነግሶ የነበረው የሮማው ንጉሥ የጀስቲኒያን ሕግ ነው ።
እንግዲኽ ፤ የሰው ልጅ ስልጣኔውን ጀምሮ ስነ ጽሑፍን ከአዳበረ ቢያንስ ከ 3700 ዓመታት በኋላ ፤ ማለትም በ550 ዓ.ም ገደማ ፤ ሰፊ ተደራሽነት የአለው ፤ እየተጣቀሰ ብይን የእሚሰጥበት የተጻፈ ሕግ ፤ በምሥራቃዊ የሮም መንግሥት በባዛንቲየም ጀመረ ። ይኽም የባዛንቲየም ሮም ስኬት ፤ ከምዕራባዊ ሮም ውድቀት ዘግየት ብሎ የመጣ በመሆኑ በቢዛንትየም ተወስኖ የቀረ እና በቤዘንቲየም የነበረው ተቀባይነት ደካማ የነበረ በመሆኑ ፤ ከሌሎቹ ቀደምት ሕግጋት በተሻለ ተቀባይነት የነበረው ቢሆንም ፤ በቢዛንትየም እና በተወሰኑ ማሕበረሰብ ውስጥ ተውስኖ ቆይቶ ፤ ቀስ በቀስ ተዳፍኖ ስለ ቀረ ፤ ለሚቀጥለው 1,000 ዓመት ፤ እስከ 1500 ዓ.ም ገደማ አብዛኛው ዓለም እንደ ቀደመው ፤ በዳኞች ፣ በባላባቶች ፣ በሹማምንት ፣ ወዘተ ፤ የልቦና ፍርድ እና በአዋጅ ሲዳኝ ቆይቷል ።
በእኛ ሐገር ፤ ምንም እንኳን ፤ ፍትሐነገሥት መግቢያው ላይ ከሮማው ቆስጦንጢኖስ ፤ ማለትም ከ4ኛው ምዕተ ዓመት ጀምሮ የተዋቀረ እንደ ሆነ ቢናገርም እና እስከ ዛሬ ከኢትዮጲያ ውጭ ፍትሐነገሥትን ይጠቀምበት የነበረ ሐገር የአለ በአይመስልም ፤ የእኛ ሐገር ታሪክ አጥኝዎች ፤ እንደ ኃይማኖታዊ መጽሐፍ አይተውት ይሁን ወይንስ በሌላ ምክንያት ፤ በመጽሐፉ እድሜ ላይ ጥናት በአለማቅረባቸው ፤ በመጽሐፉ እድሜ ላይ ጥናት ያቀረቡ የውጭ ሰዎች እስከ አኹን በአገኙት ማስረጃ መሠረት ፤ ፍትሐነገሥት በኢትዮጲያ የተዋወቀው ከአጼ ዘራያዕቆብ በፊት ማለትም ፤ ከ14ኛው ምዕተ ዓመት በፊት ሊሆን አይችልም ስለ እሚሉ ፤ እኛም የአለውን የፈረንጆቹን ጥናት ተቀብለን ፤ የአውሮፓ ህዳሴ እስኪ መጣ ዓለም በፖለቲካ ጨለማ ውስጥ ነበር እንድንል እንገደዳለን ።
ሆኖም ፍትሐ ነገሥት ስለ እራሱ እንደ እሚለን ከቆስጦንጢኖስ ንግሥና ጥቂት ዓመታት በኋላ ፤ በኢትዮጲያ ፍትሐ ነገሥት በሥራ ላይ ነበር የእሚል የታሪክ ማስረጃ ከተገኘ ፤ ይኽን የዘመን አከፋፈል ኢትዮጲያ ስትቀር በእሚል እናስተካክለዋለን ማለት ነው ።
ይኽ እንግዲህ እስከ አኹን ያየነው ዝግመት ፦ የመደበኛውን የወንጀለኛ መቅጫ እና የፍትኃ ብሔርን ሕግ እንጂ ሕገ-መንግሥትን አይመለከትም ። ምክንያቱም ፦ ሕገ-መንግሥት ፤ ማሕበራዊ መስተጋብሮችን ከመዳኛ ሕግነት በአለፈ ፤ በመንግሥታዊ ፍልስፍና ላይ ተመስርቶ የመንግሥትን አወቃቀር የእሚደነግግ ፤ የተሻለ እውቀት እና ጥናት የእሚፈልግ በመሆኑ ፤ የሰው ልጅ የተጻፈ ሕገ-መንግሥትን የመንግሥት አወቃቀር መመሪያው እስኪ ያደርግ ሌላ ብዙ መቶ ዓመታት ፈጅተውበታል ።
በእዚኽ ረገድ የኢትዮጵያ ክብረ-ነግስት የመጀመሪያው የተጻፈ ሕገ-መንግሥት ነው ብዬ በአምንም[3] ፤ ይኽ በጥናት እስኪ ደገፍ ፤ የመጀመሪያው የተጻፈ ሕገመንግሥት ፤ እ.አ.አ. በ1210 ዓ.ም. የመጣው የእንግሊዞቹ Magna Carta (ማግና ካርታ) ወይንም ታላቁ ሰነድ የእሚባለው ነው ።
ማግና ካርታ ፤ ያለ ምክንያት መታሰር ፣ ድንገተኛ የግብር ጭማሪ ፣ በእስር ያለ ፍትሕ መጉላላት ያስቆጣቸው የሐገረ እንግሊዝ ባላባቶች በንጉሥ ላይ በማመፃቸው ፤ በአንድ ጳጳስ አርቃቂነት ፤ የንጉሡን ግብታዊነት በተጻፈ ሕግ ለመገደብ እና የባላባቶችን ነፃነት ለማስከበር ታስቦ የቀረበ ፤ በዋናነት የእርቅ ሰነድ ነበር ።
ማግናካርታን ዘመናዊ ሕገመንግሥትን በማርቀቅ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የእሚያሰጠው ፤ ከሳይንሳዊ ይዘቱ ይልቅ የፈጠረው ፖለቲካዊ መነቃቃት ፤ ለሳይንሳዊ ሕገመንግሥት መምጣት ፈር ቀዳጅ በመሆኑ ነው ።
ማግናካርታ ከፀደቀ በኋላ ፤ የባላባቶች እና የሕዝብ የመብት ጥያቄ ከእለት እለት እየጨመረ ስለ መጣ እና በእዚኽም ምክንያት ነገሥታቱም ታሪካዊ ስልጣናቸው በእየግዜው መሸርሸር በመቀጠሉ ፤ ኹኔታው መላው ሐገሪቱን መውጫውን ወደ እማያውቁበት አዲስ እና ፈታኝ ፖለቲካዊ ምህዳር ይዞዋቸው በመግባት ፤ ብሪታኒያ ለእሚቀጥሉት ሦሥት እና አራት መቶ ዓመታት መጥተው ብዙ ዓመታት ቆይተው በእሚሔዱ የእርስ በእርስ ጦርነቶች ውስጥ እንድትቆይ የተገደደችበት ወቅት ነበር ።
ይኽ እያደገ የመጣው የሕዝብ የመብት ጥያቄ እና ለብዙ ዓመታት ለብቻው ገኖ ይኖር የነበረው የነገሥታት ሉዓላዊነት መካከል የተፈጠረው ፍትጊያ ፤ ያስከተለው የእርስ በእርስ ጦርነት ፤ ከዘመነ ማግና ካርታ አንስቶ በእየግዜው እየጋመ ኼዶ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጡዘቱ ላይ ደርሶ ነበር ።
ይኽ ሳይንስ መራሽ አዲስ የመብት ጥያቄ ፤ ነባራዊውን እና ልማዳዊውን አሰራር በመገዳደር የፈጠረው ማሕበራዊ አለመረጋጋትም ነው ፤ እነ ሮበርት ፊልመር እና ቶማስ ሆብስ መሰል የወቅቱ ሊህቃንን ፤ በእዚኽ ዜጎች በተፈጥሮ እኩል ነጻነት የአላቸው በመሆኑ ማን መንግሥታቸው እንደ እሚሆን መምረጥ ይችላሉ በእሚለው አዲስ የመብት አረዳድ መሠረት ፤ ነባራዊውን ንጉሣዊ እና አባታዊ የስነ መንግሥት አወቃቀር ሽሮ የሕዝባዊ መንግሥት ለማቋቋም መፈለግ ፤ መጨረሻው ደም አፋሳሽ መሐበራዊ አለ መረጋጋት ነው በእሚል ፤ ከላይ በተለያየ መንገድ በገለፅነው መልኩ ፤ በሕዝብ ምርጫ የእሚቋቋመውን እና ተጠያቂነቱ ለመረጠው ሕዝብ ይኹን የተባለውን ሕዝባዊ መንግሥት ሲቃወሙት የነበረው ።
እንደ እምናስታውሰው ፤ ሮበርት ፊልመር ነገሥታት ከኹላችንም ይልቅ ለአባታችን አዳም ፤ በውልደት ቅደም ተከተል ይቀርባሉ እና ስልጣናችሁ ከሕዝብ ይሁንታ ከአልመጣ ሕጋዊ አይደለም ብለን ስንል ፤ የእግዚአብሔርን የብኩርና ድንጋጌ እየተቃወምን ነው ለማለት ሞክሯል ።
ከእዚያኽም ቀጠል አድርጎ ፊልመር ፤ በጣም አስተማማኝ ያል ኾነውን እና አመለካከቱ ያለ ምክንያታዊነት በአሉባልታ ብቻ ቶሎ የእሚቀያየረውን ሕዝብ ፤ መንግሥትን ምረጥ ማለት የእማይታሰብ ነውም ብሏል ።
ከእርሱም በኋላ ፤ ቶማስ ሆብስ ፥ የሰዎች ሰብዓዊ እኩልነት ሰአይቃወም ፤ መንግሥት ኹሉ በአንዳች ዓይነት ውል ወደ ስልጣን ስለ መጣ ፣ ስልጣን ላይ በመቆየትም ከፍተኛ ኃይል ስለ አዳበረ እና መንግሥትን ማፍረስ ወደ ድሮው መንግሥት አልባው የጦርነት ኹኔታ ማሕበረሰብን የእሚመልስ በመሆኑ ፤ ዜጎች የተፈጥሮ እኩል ነፃነት ያጎናፀፋቸውን መብት ተጠቅመው ፤ ለረዥም ዘመን ረግቶ የቆየን መንግሥት በምርጫ አውርደን እንተካ ሲሉ ፤ ማሕበራዊ አለመረጋጋትን እና የመንግሥትን የበቀል በትር ያነሳሳሉ እና መንግሥታቸው ቢበድላቸውም ዝም ብለው ይገዙ ብሎ ለመከራከር ሞክሯል።
ፊልመር እና ሆብስ ፤ ነገሥታት ስዩመ እግዚያን ናቸው እና ስልጣናቸው ፍፁማዊ ነው ብቻም ሰአይሆን ያሉት ፤ በተለይ ሮበርት ፊልመር ፤ ቀደም ብለን እንደ አልነው ፤ ሕዝብ መሪውን ይምረጥ ማለት የሕዝብን ታሪካዊ በኃሪ አለመረዳት መሆኑን አስቀምጠው ተከራክረዋል ።
ሕዝባዊነትን ከመንጋ እንቅስቃሴ ጋር የእሚያምታቱ እና ሕዝብ እንደ ሕዝብ ፖለቲካዊ ንቃት እና ጥበብ ስለ እሚጎድለው ፤ ራሱን የቻለ ጥበብ እና እውቀት ስለ እሚጠይቀው ሐገር አስተዳደር ጉዳይ በቂ እውቀት ሳይኖረው ፤ በምርጫ ወደ መንግሥት ኃላፊነት የእሚመጡ ሰዎችን እኔ ልወስን ፣ የመንግሥትን አፈጻፀም እኔ ልከታተል ከአለ ፤ እንዲኽ ዓይነቱ ፤ በመብት ስም መንግሥትን የመቆጣጠር አባዜ ከተስፋፋ ፤ መንግሥት ይጠፋ እና ኹሉም እንደ አሰኘው የእሚፈነጭበት ስረዓት አልበኝነት ያመጣል (በዋናነት በእሚኖሩበት ዘመን በእንግሊዝ ውስጥ የመብት ጥያቄ የፈጠረው አለመረጋጋት ከፈጠረባቸው ስጋት በመነሳት በእሚመስል አኳዃን) ፤ ይኽ እንደ አይሆን ሰው መርጦት ሰአይሆን ፈርቶት በመገዛት የእሚኖርለት መንግሥት ነው የእሚያስፈልገው ብለው ፤ ያመኑ ሆብስ እና መሰል የፖለቲካ ሳይንስ ሙህራን ናቸው ፤ የተለያዩ መጽሐፍ በመጻፍ የአምባገነን ማሕበራዊ ውል የአልነውን መንግሥት መመሥረቻ ፍልስፍና ፤ ለዘመናዊ አምባገነናዊ መንግሥታት ግብዓት በእሚሆን መልኩ ኃሳባቸውን ያበረከቱት ።
እነርሱንም ተከትለው የኋለኞቹ ግራ ዘመም ፖለቲከኞች ፤ ያልነቃው ሰፊው ሕዝብ (the unsconscious mass) በሊህቁ (the intellegentsia) ከአልተመራ ጥቅሙን አሳልፎ ይሰጣል ስለ እዚኽ ፤ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ፣ ወንድም ጋሼ ወይንም ሞግዚት (Vanguard ) መንግሥት ማቋቋም አለብን ብለው ጀምረው ፤ ይኽ የእንባ ጠባቂ መንግሥት ግን በዴሞክራሲያዊ መዓከላዊነት ያለ ሕግ አውጭ ፣ ሕግ ተርጓሚ እና አስፈፃሚ ክፍፍል ፤ የሰፊው እና ሠራተኛውን ጥቅም ለማስከበር የመደብ ጠላታቸውን እየጨቆነ መቆየት አለበት የእሚሉትን ፤ የሠራተኛውን አምባገነናዊ መንግሥት ወደ ማቋቋም የገቡት ።
ሰፊው ሕዝብ ንቃት ይጎድለዋል ስለ እዚኽ ፤ ልዩ እውቀት እና ችሎታ በእሚጠይቀው የሐገር መምራት ጉዳይ ላይ በእውቀት የተመሠረተ ምርጫ ማድረግ አይችልም ፣ ንቃት ስለ እሚጎድለው ጥቅሙን አሳልፎ ይሰጣል ፣ ንቃት ስሌለው እርስ በእርሱ ይበላላል ፣ ወዘተ ፤ ስለ እዚኽም ሰፊው ሕዝብ ከእርሱ የእሚሻሉ ሰዎች እንደ እረኛ ሊያስወጡት እና ሊያስገቡት ነው የእሚገባው እንጂ ነፃነቱ ተከብሮለት የራሱ መንግሥት መራጭ ከሆነ ሥራዓት አልበኝነት ይነግሳል ለአሉት ለእነዚኽ የአምባገነን መንግሥታት የፍልስፍና አባቶች ወይንም ፋና ወጊዎች መልስ ለመስጠት ነው እንግዲህ ፤ የዘመናዊው የሕዝባዊ መንግሥት አስተሳሰብ አባት የሆነው ጆን ሎክ ፤ ኹለቱ የመንግሥት ሐተታዎች (The Two Treatise of Government) የእሚለውን የፖለቲካ መጽሐፉን የጻፈው ።
ይኽም የጆን ሎክ በአምባገነኖች ላይ የቀረበ የመከላከያ ኃሳብ ፤ ለዛሬው ሕገመንግሥታዊ መንግሥት መዋቀር መሠረት በመጣል በሰው ልጅ ፖለቲካዊ ታሪክ ውስጥ ወሳኝ የመሸጋገሪያ ሥራ እንዲሰራ አስችሎታል ።
በእርግጥ ሳይንሳዊ የሕገ መንግሥት ጥናት በፕሌቶ እና በአርስታትል ፤ ከክርስቶስ ልደት በፊት አራት እና አምስት መቶ አመት ቀደም ብሎ ቢጀምርም ፤ ሳይንሳዊ ሕገ መንግሥት አድጎ እና በእነ ጆን ሎክ ዳብሮ የሕዝባዊ መንግሥት መመሥረቻ ለመሆን ወይንም በመንግሥታት ተቀባይነት አግኝቶ መተግበር የጀመረው ከአውሮፓ ህዳሴ ፤ ማለትም ከ 1500 ዓ.ም በኋላ ፤ በተለይም የጆን ሎክ ኃሳብ በአሜሪካ መሥራች በሆኑት በእነ ቶማስ ጀፈርሰን ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት በማግኘቱ ነው ።
የጆን ሎክ ፤ ለነጻነቱ ዴሞክራሲ ወይንም ለሕገመንግሥታዊ መንግሥት ሟደል (Model) መሆን የቻለው ፤ የተፈጥሮ መብት ፣ የተፈጥሮ ሕግ ፣ የተፈጥሮ ኹኔታ ፣ ወዘተ ፤ የእሚሉትን ኃሳቦች ፤ ከሌሎቹ ፖለቲካዊ ሳይንቲስቶች አስቀድሞ ስለአወቀ ወይንም እነርሱ ከእሚረዱበት በተለየ መንገድ ስለ ተረዳቸው ሰአይሆን ፤ እነ እዚኽ መሠረታዊ መርሆች ሊያስከትሉ በእሚገባው መንግሥታዊ አወቃቀር ላይ ፤ ከአምባገነኖቹ የእሚለይ አመለካከት የነበረው ስለነበረ ነው ።
በእዚኽ ረገድ ፤ የመጀመሪያውን ሕዝባዊ መሠረት የአለው እና ዘመነ ሳይንስ ያስተዋወቃቸውን ኃሳቦች በጆን ሎክ ሳይንሳዊ የስነመንግሥት ትንታኔ አግባብ አብዮት አካኺዳ ፤ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1787 ዓ.ም ሕዝባዊ መንግሥት በመመሥረት ረገድ የመጀመሪያዋ ሐገር የእነ ቶማስ ጀፈርሰኗ አሜሪካን ነች ።
ይኽ በሳይንሳዊ መርሆቹ ላይ የተመሠረተው የአሜርካን ሕገ መንግሥት እና መንግሥት ፤ ያስመዘገበው አስደናቂ ታሪካዊ እመረታ ፤ እንደ መልካም ሟደል(Model) እንዲታይ ስለ አደረገው ፤ የእርሱን ምሳሌ በመከተል ፤ በምድረ አውሮፓ መጀመሪያ የፈረንሳይን አብዮት በኋላም የራሺያን አብዮት ያነሳሳ ሲሆን ፤ ዛሬ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ፤ ዓለም ዓቀፍ እውቅና የአላቸው የዜጎች ሰብዓዊ መብት የእሚያከብሩ እና ያልተማከለ ስልጣን የእሚይዙ ዴሞክራሲያዊ መንግሥታት የእሚቋቋሙበት ሕገመንግሥት ፤ ዓለም ዓቀፋዊ ተቀባይነት እንዲኖረው ትርጉም በአለው መልኩ ፈር የቀደደው ይኸው የአሜሪካ አብዮት ነው ።
ስለ እዚኽ ፤ የሳይንሳዊ መንግሥት ፍልስፍና ፤ የዛሬ 2,500 ዓመታት ገደማ ፤ በእነ ፕሌቶ እና አርስታትል ቢጀምርም ፤ ፍልስፍናው ጎልብቶ እና ተቀባይነት ኖሮት ፤ ለመጀመሪያ ግዜ በሰነድ ላይ የሰፈረ ውጤታማ የሕዝባዊ መንግሥት መመሥረቻ ፤ የሆነው በአሜሪካን ሪፐብሊክ ምሥረታ ላይ ነው ።
ከእዚያኽን ግዜ አንስቶ ብዙ ሐገራት የአሜሪካ አካሔድ ለመድገም ቢሞክሩም ፤ የግርድፍ ኩረጃ ጉዳይ ስለ ነበረ ፤ አብዛኛዎቹ አብዮታቸው እና ሕገመንግሥታቸው የይስሙላ ሆኖ ቀርቷል ።
አኹን በአለንበት ዓለም ፤ ምንም እንኳን በዋናነት ሕገመንግሥታዊነት ወይንም የሕዝባዊ መንግሥት ሕገመንግሥት በዋናነት የነጻነቱ ዴሞክራሲ መገለጫ ቢሆንም ፤ የሕግ እና የሕገመንግሥት ፤ ይዘቱ እና የእሚመራበት ሳይንሳዊ ፍልስፍና ይለያይ እንጂ ፤ ሕግ እና ሕገመንግሥት የሌላቸው ሐገራት በጣም ጥቂት ናቸው ።
መሰል ሳይንሳዊ የመንግሥት ፍልስፍና ፤ በጠቅላላው የሰው ልጅ የፖለቲካ ታሪክ ለመዳበር የዘገየበትን ኹኔታ ስናይ ፤ በተዋወቀ በተነፃፃሪነት በአጭር ግዜ ውስጥ ፤ አኹን የደረሰበት ዓለም ዓቀፋዊ ተደራሽነት ይበል የእሚያሰኝ ነው ።
አኹን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የአለው ፈተና ፤ የሳይንሳዊ መርህ ፈርጅ ስር የእሚካተተው ፤ በግለሰቦች ተፈጥሮዋዊ ሰብዓዊ መብት ዙሪያ በዴሞክራሲያዊ መርህ የእሚቋቋም ሕዝባዊ መንግሥታት (republics) ትርክት ተቀባይነት የማግኘታቸው እና ያለ ማግኘታቸው ጉዳይ ሰአይሆን ፤ እነ እዚኽን ዓለም ዓቀፋዊ ተቀባይነት የአላቸውን አካኼዶች ለይስሙላ ደርድሮ ፤ በመሠረታዊነት እና በተግባር ግን ወደ ተለመደው ኋላ ቀሩ ዓምባገኑን የመንግሥት ዓወቃቀር የመመለስ ልማድ ነው ።
ይኽም በመሆኑ ፤ የእዚኽ ዘመኑ ሕጋዊነት እና ሕገ መንግሥታዊነት ፈተና ፤ ሕገ መንግሥት የዘመናዊ መንግሥት መገለጫ ነው በእሚል ፤ ሕገ መንግሥት የሌለው መንግሥት የለም ለማለት ቢያስደፍርም ፤ የአብዛኛዎቹ መንግሥታት ሕገመንግሥቶች ግን ፤ የዜጎችን የማሕበራዊ አህድነት ወይንም ዜጎች በተፈጥሮ እኩል ነፃነት አላቸው የእሚለውን እና ይኽም ኃሳብ የነፃነት ዴሞክራሲ መሠረት ነው የእሚለውን መርህ ችላ ያለ ሕገ መንግሥት የመቅረፅ ችግር ነው ።
ይኽም በመኾኑ ፤ የእዚኽ ዘመን ፈተና የሆነው ፤ በተለይ በሕገ-መንግሥት ረገድ ፤ በሕገ-መንግሥት ውስጥ የእሚነፀባረቁት ኃሳቦች ፤ ምንም እንኳን ሕዝብን የስልጣን ባለቤት ማድረግ ነው በእሚል መሸፈኛ ቢሆንም ፤ በተግባር ግን ከእዚኽ በተቃራኒ የእሚሆኑበት ኹኔታ ነው ።
በእዚኽ ንዑስ ክፍል ያነሳነውን የሕግ እና የሕገመንግሥት አመጥጥ ስንጠቀልለው ፤ የሰው ልጅ የመጀመሪያውን የተጻፈ መንግሥታዊ ሕግ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ 1750 ቅ.ክ. ሲያስተዋውቅ ፤ የመጀመሪያውን የተጻፈ ሕገመንግሥት (መንግሥት የመመሥረቻ ሰነድ) ከክርስቶስ ልደት በኋላ 1210 ዓ.ም. (የኢትዮያ ክብረነገሥት ሕገመንግሥት መሆኑን ለተቀበለ ደግሞ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ600 ዓ.ም. አከባቢ) ከአስተዋወቀ በኋላ ፤ በሕገመንግሥታዊ መንገድ ለመጀመሪያ ግዜ ሕዝባዊ መንግሥት የተመሠረተው ደግሞ ፤ እ.አ.አ. በ1787 ዓ.ም. በምድረ አሜሪካ ነው ።
ያም ማለት ፤ የሰው ልጅ ከ5 ሺ ዓመት ትንሽ በእሚበልጠው ፖለቲካዊ ታሪኩ ፤ ትርጉም በአለው ወይንም ታሪካዊ ተዘጋቢነት በአለው መልኩ ፤ በተጻፈ ሕግ ለመዳኘት 3,500 ዓመታት ፤ በተጻፈ ሕገመንግሥት የእሚመራ መንግሥት ለማቋቋም 4,700 ዓመታት ገደማ ፈጅተውበታል ማለት ነው ።