ሕ ገ ክ ራ ሲ

marketing-image

2.2.1. መንግሥታዊ ትርክቶች እና የዜጎች ማሕበረሰባዊ አህድነት

ከ 5 ሺ ዓመታት በጥቂት በእሚበልጠው የፖለቲካ ታሪኩ ፤ የሰው ልጅ ከአዳበራቸው የፖለቲካ እውቀቶች መካከል ፤ በእዚኽ ንዑስ ክፍል ‘የግለሰቦች ወይንም የዜጎች ማሕበራዊ አህድነት’ ብለን እንደ እምናየው ፖለቲካዊ እውቀት ፤ ፖለቲካዊ ታሪኩን በወሳኝነት የቀየረ ፖለቲካዊ እውቀት የለም ማለት ይቻላል።

የግልሰቦችን የፖለቲካዊ ማሕበረሰብ አህድነትን መቀበል ማለትም ፦ በዋናነት የሰው ልጅ በማንኛውም ማሕበራዊ ይዘቱ እና ደረጃው ሰአይወሰን ፤ በሰውነቱ ብቻ በእኩልነት የተጎናጸፋቸው የተወሰኑ ሰብዓዊ መብቶች እና ክብሮች እንደ አሉ ተቀብሎ ፤ እነ እዚኽን መብቶች አውቆ ማክበር እና ማስከበር የአንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ፖለቲካዊ መሠረት መሆኑን መቀበል ነው።

አንድ ሰው የቆዳ ቀለሙ ምንም ይኹን ምን ፣ የእሚናገረው ቋንቋ ይኽኛውን ይኹን ያንኛውን ፣ የእሚከተለው ኃይማኖት ይኑረው አይኑረው ፥ የእሚከተለውም ኃይማኖት የትኛውን ዓይነት ይኹን ፣ የኢከነሚ ደረጃው ዝቅተኛ ይኹን ከፍተኛ ፣ በትምህርት ደረጃው ሊቀ ሊቃውንት ይኹን ወይንም መኃይም ፣ ጾታው ወንድ ይኹን ወይንም ጾታዋ ሴት ይኹን ፣ ወዘተ ፤ በአጠቃላይ ማሕበራዊ ይዘቱ እና ደረጃው ከየትኛውም ክፍል ቢሆን ፤ ሰው በመሆኑ ብቻ የተጎናጸፋቸው የተወሰኑ መብቶች እና ክብሮች አሉት ማለት ነው።

ይኽንን አቋም በጥሩ ኹኔታ እና በውብ ቃላት ፤ እ.አ.አ. በ1776 ዓ.ም. በታወጀው የአሜሪካን የነጻነት አዋጅ (The Declaration of Independence) የእሚባለው ሰነድ ላይ በእዚኽ መልኩ ተቀምጦ እናገኘዋለን ፦

“እኛ ፤ ሰዎች ኹሉ እኩል ሆነው መፈጠራቸውን ፥ በፈጣሪያቸውም ማንም ሊገ፟ፋቸው የእማይችላቸው የተወሰኑ መብቶች የተቸሩ መሆኑን ፥ ከእነ እዚኽም መካከል ፦ ህይወት ፣ ነጻነት እና መሻታቸውን መከተል ተጠቃሽ እንደ ሆኑ ፤ መስካሪ እና አስረጂ የእማያስፈልጋቸው በራሳቸው ግልጽ እውነቶች መሆናቸውን እንቀበላለን - ”

“We hold these Truths to be self-evident, that all Men are created equal, that they are endowed by their Creator with certain unalienable Rights, that among these are Life, Liberty, and the Pursuit of Happiness-“

ይኽ አስረጂ እና መስካሪ ሰአያስፈልገው በራሱ ግልጽ የሆነው የዜጎች የማሕበራዊ አህድነት እውነት ግን ወደ አደባባይ ሰአይወጣ እና የሰው ልጆችን ማሕበራዊ አወቃቀር እና አስተዳደር በእማይወስንበት ኹኔታ ተዳፍኖ በእሚበዛው የሰው ልጅ ፖለቲካዊ ታሪክ ዘመን ውስጥ የቆየ ነው።

በታሪክ ወደ ኋላ መለስ ብለን ፤ የእዚኽን አስተሳሰብ ታሪካዊ ዝግመት ስንቃኝ ፤ የኃሳቡ መስፋፋት በዋናነት ከክርስትና እምነት መስፋፋት ጋር የተያያዘ ሆኖ እናገኘዋለን።

ቅድመ ክርስትና የነበረው ዓለም ፦

  • በወትድርና ሳይንስ
  • በሰዋሰው ፣ በአነጋገር ፣ በሙግት ፣ የአስተዳደር ፣ ወዘተ ፤ ሳይንስ
  • በፍልስፍና
  • በተፈጥሮ ሳይንስ
  • በኪነ ሕንጻ
  • የታሪክ እና ሕግ እውቀት ፣ ወዘተ ፤

ብዙ እውቀት የአዳበረ እና ዛሬ ለአለንበት ስልጣኔ መሠረት ቢሆንም ፤ በሰዎች ሰብዓዊ እኩልነት ጉዳይ መሠረታዊ የግንዛቤ መዛበት የእሚስተዋልበት እና ይኽም በኃይማኖታዊ ፣ በትምህርት ፣ በማሕበራዊ አደረጃጀቱ ፣ ወዘተ ፤ ውስጥ በስፋት የእሚስተዋል ነበር።

አርስታትልን መሰል በሳል ፈላስፋ ፦

“ባሪያ ማገናዘብ የእሚችል የዓዕምሮ ክፍል የለውም ፤ “

“For the slave has no deliberative faculty at all; [1] “

እንደገናም በድጋሚ በሌላ ቦታ ላይ ፦

“… ባርነት ግን ተፈጦሮዋዊ ኹኔታ ነው ፥ “

“...; and where as the slave exists by nature, [1] “

ብሎ በድፍረት በመጻፍ ፤ ነጻነት ሰዎች በተፈጥሮ በእኩልነት የእሚጋሩት ተፈጥሮዋዊ መብት መሆኑን መገንዘብ እንደ አልቻለ አሳይቷል ።

በ4ኛው ምዕተ ዓመት[1] ፤ ስለ ፕሌቶ የእሚተርክ መጽሐፍ ፤ ፕሌቶ ታዋቂ በአደረገው አካዴሚያ በእሚባለው ትምሕርት ቤቱ ደጅ ላይ ፦ “የጂዖሜትሪ እውቀት የሌለው ሰው ደጄን እንደ አይረግጥ (“Let none ignorant of geometry enter my door”)” የእሚል ጽሑፍ እንደ ነበር ይዘግባሉ።

ይኽም የፕሌቶ ትምክህተኛ የእሚመስል አባባል የተጠቀሰበት አግባብ ፤ በተለይ “ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይመጣ እና ይጠጣ” ከእሚለው እና በኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 7 ቁጥር 37 ላይ ከተነገረው ወይንም በጠቅላላው የሰውን ጾታ ፣ ዘር ፣ የኢከነሚ ደረጃ ፣ ወዘተ ፤ መሠረት የአደረገ ልዩነት ሰአያደርግ “ወደ ዓለም ኹሉ ኺዱ” ከእሚሉት እና መሰል የክርስትና መልዕክቶች ጋር ተነጻጽሮ ስናየው ፤ የቀድሞው የእነ ፕሌቶ ዓለም በሰብዓዊነት አንጻር ክፍተት እንደ ነበረበት ያሳየናል።

ምክንያቱም ፦ ይኽ የፕሌቶ አባባል ፤ ጂዖሚትሪ የእውቀት ኹሉ ቁልፍ በመሆኑ ጂዖሜትሪን መማር የእሚፈልግ ወደ እዚኽ ይምጣ ሰአይሆን የእሚለው ፤ ጂዖሜትሪን አታውቅም እና ደጄን እንደ አትረግጥ የእሚል በመሆኑ በውስጡ የመልከኛ ትምክህት (Aristocratic Arrogance) የእሚንጸባረቅበት እና የሰብዓዊነት አስተሳሰብ የእሚጎድለው መሆኑ ግልጽ ነው።

ከግሪኮቹ ወጣ ስንል ፤ በጥንታዊነቱ ከእነ አርስታትልም ትንሽ ቀደም የእሚለውን እና እስከ ዛሬም ድረስ የብዙ ሕንዶች ኃይማኖት የሆነው የኂንዱ እምነት ፤ በውስጡ በያዘው የደረጃ ስረዓት (The Indian Caste System) መሠረት ፦ መሪነት ፣ ክህነት ፣ የቀን ሰራተኝነት ፣ ወዘተ ፤ ከቤተሰብ የእሚወረስ እና በግለሰቦች ነጻ ምርጫ የእማይወሰን የተፈጥሮ ድንጋጌ ነው ብሎ በማስተማር ፤ ሰዎች በኂንዱ ስረዓት ከተደነገገባቸው ደረጃ እንደ አይወጡ የእሚያግድ በመሆኑ ፤ የሰዎችን ተፈጥሮዋዊ እኩልነት መገለጫ የሆኑትን ፤ የሰዎችን የተወሰኑ ሊገፈፉ የእማይችሉ/የእማይገቡ ፤ ለምሳሌ ፦ የነጻ ምርጫ መብት የእማይቀበል ነው።

ይኽ የኂንዱዎች የደረጃ ስረዓትም ፤ ሕንድ ከእንግሊዝ ቀኝ ግዛት እ.አ.አ. 1947 ዓ.ም. ነጻነቷን እስክ ታውጅ እና ይኽንን ጎጂ ባሕላዊ እምነቷን በሕግ እስክታግድ ድረስ ፤ ስረዓቱ በሕንድ ማሕበረሰብ ውስጥ ያለምንም መቋራረጥ እና መሸራረፍ ፤ ከ2 ሺ ዓመታት ባላይ ሲሰራ ነበር።

እስከ ቅርብ ግዜ በጉዳዩ ላይ የእሚወጡ ሪፖርቶችም ፤ ምንም እንኳን ይኽ የደረጃ ስረዓት ከሕንድ ነጻነት ጋር ተያይዞ በሕግ ቢሻርም ፤ በማሕበረሰብ ውስጥ ከቆየበት እድሜ እና ከአለው ኃይማኖታዊ ገጽታ የተነሳ ፤ እስከ አኹንም በማሕበረሰብ ውስጥ በተለያየ መልኩ እየተንጸባረቀ ፤ የማሕበረሰቡን ልማት እየጎዳ እንደ ሆነ ይዘግባሉ።

አንዳንድ የሕንድ ሙሕራን ተብዬዎችም ይኽ ስረዓት ፤ የተፈጥሮ ኹኔታን የመግለጽ እንጂ ሰዎች የአልሆኑትን ነገር በግድ የእሚጭን በአለመሆኑ ፤ እንደ ኋላ ቀርነት እና ችግር ሊታይ አይገባም ብለው ፤ ጥናታዊ ጽሑፍ የእሚጽፉ በመሆናቸው ፤ በርግጥም ጉዳዩ እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ የሕንድ ማሕበረሰብ ችግር የነበረ መሆኑን ያሳያል።

እ.አ.አ. 1933 ዓ.ም. በጉዳዩ ላይ የጻፈ ከእነ እዚኽም ሙህራን መካከል አንዱ እንደ እዚኽ ይላል፦

“…የኂንዱ እምነት ተከታዩ እንዲኽ ያምናል ፤ … ደረጃዎቹ የተፈጠሩት ለማሕበረሰብ ስለ እሚያስፈልጉ ነው … ። ስለ እዚኽ ፦ ማሕበራዊ ደረጃው ፤ ሰው የፈጠረው ወይንም የሆኑ ክፉ ሰዎች ሌሎችን ለመጨቆን ከመፈለግ የመነጨ አይደለም ፥ አንዳንድ ተጓዥ ጸኃፍት እንደ እሚሉት ። በኂንዱዎች ትንታኔ ደረጃው በሰው ተፈጥሮ ውስጥ የአለ ነው”

“… The Hindus hold that human character is such that mankind may be classified into these groups … The castes, therefore, are not artificial nor result from the wicked desire of some persons to dominate others as has often been alleged by travelers. It has its origin in human nature as the Hindus analyze it. [75]“

ይኽ የሕንዶች ብቻ ችግር ማለት ወይንም ኢሰብዓዊነት የቀደመው ዓለም ችግር ብቻ ነው ማለትም አይደለም ፤ ለምሳሌ ፦ የደቡብ አፍሪካው አፓርታይድ ስረዓት የአንዳንዶች የቅርብ ትውስታ ነው ።

አፓርታይድ የእሚለው የአፍሪካነስ ቃል (Apartheid = Apart + heid, heid is dutch equivalent for the English ‘hood’, apart in different hoods) ወይንም በአማርኛ በመልክ በመልክ መከፋፈል ወይንም ዘርን መሠረት በአደረገ ኹኔታ በመንደር መነጠል የእሚል ትርጉም የያዘ በመሆኑ ፤ ዋናው ኃሳቡ ፦ የተለያየ ዝርያ የአላቸውን ሰዎች በዘር ጎራቸው ማስፈር የእሚል ኃሳብ ያነገበ ነበር ።

አፓርታይድ ይኽን የእሚያደርገው ደግሞ ፤ በወቅቱ የፖለቲካ ስልጣኑን የያዙት ሰዎች ፥ ምንም እንኳን በቁጥር ትንሽ ስለ ሆንን ዴሞክራሲ ስልጣናችንን ያሳጣናል የእሚለው ስሌት የእራሱ የሆነ የተሰወረ ከፍተኛ ሚና ቢኖረውም ፤ እኛ እና ሌሎቹ ሰዎች በስልጣኔ ደረጃችን እኩል ነጻ አይደለንም ብቻ ሰአይሆን ፤ በሰብዓዊነት ደረጃችን ራሱ እኩል አይደለንም ብሎ ከማመንም እንደ ሆነ እና በዳርዊን የዝግመታዊ ለውጥ ቲየሪ መሠረት ፤ ነጮቹ ከጥቁሮች ይልቅ የተሻለ እና የተጣራ ደረጃ ላይ ደርሰናል ብለው ያምኑም ስለነበረ ነው ፦

“ይኽ የዳርዊን ቲየሪ (የዝግመታዊ ለውጡ ቲየሪ) ነጮች ፤ ራሳቸውን በዝግመታዊ ለውጡ መመዘኛ ፤ በቴክኖሎጂ ልህቀታቸው እና በቅኝ ግዛቶቻቸው መስፋፋት እንደተንፀባረቀው ፤ ከፍተኛው ደረጃ ላይ እንደሆኑ እንዲያምኑ አደረጋቸው ።”

“This theory of Darwinism made whites believe that they were at the top of the evolutionary scale which was exhibited through their advancement in technology and imperial expansion. [76]”

በእርግጥ ከእነ እዚኽ በዘመናዊው የማሕበረሰብ ሳይንስ እውቀት ታንጫለሁ በእሚሉት ሰዎች ዘንድ ሰዓይቀር ፤ የሰዎች ተፈጥሮዋዊ ሰብዓዊ እኩልነት ጉዳይ በእዚኽ መልኩ የእሚዘነጋው በአብዛኛው በጭፍን ጥላቻ እና ጎጠኝነት አስተሳሰብ ቢሆንም ፤ አንዳንድ ግዜ ጥሩ በእሚመስሉ ነገር ግን ስሁት በሆኑ የአስተሳሰብ መፋለሶች (fallacies) ምክንያትም ነው።

ለምሳሌ ፦ ኮንፊሸሳዊው የማሕበረሰብ ሕግ ሰዎችን ፤ ሕግ አውጥቶ ይኽን ይኽን ከአደረጋችሁ ትቀጣላችሁ ብሎ ለማስተዳደር መሞከር ሞኝነት ነው ፤ ምክንያቱም ምንም ዓይነት ሕግ ቢወጣ ሰዎች መለኞች ስለ ሆኑ የሕጉን ቅጣት እንዴት አድርገው እንደ እሚያመልጡት በማሰብ ፤ ሕጉን ይጥሱታል። ይኽ እንደ አይሆን ትክክለኛው መላ ፤ ሰዎችን ስነ ምግባር አስተምራቸው እና ስነ ምግባሩን ሲጥሱ ህሊናቸው እንዲወቅሳቸው ከአደርግህ ፤ በህሊና ሕግ እየተገዙ ሕግ አክብረው ይኖራሉ ይላል።

የኮንፊሸስ አባባል ስብስቦች ተብሎ በእሚዘዋወረው ጽሑፍ ፤ መዕራፍ ኹለት አባባል ሦሥት (2.3) ላይ ፤ ኮንፊሸስ እንደ እዚኽ ይላል፦

“መምህሩ አለ ፥ ‘አዋጅ እየ አወጣህ ፥ በቅጣት ማስፈራሪያነት ልትመራቸው ሞክር ፤ ምንም ሐፍረት ሳይሰማቸው አዋጁን ይጥሱታል። መልካም ጠባይን እና ስነምግባርን በማስተማር ምራቸው ፤ የእሚያፍሩበት ሕሊና ይኖራቸዋል ኃላፊነታቸውንም ይወጣሉ።”

“The Master said, ‘Guide them with policies and align them with punishments and the people will evade them have no shame. Guide them with Virtue and align them with li (propriety) and the people will have a sense of shame and fulfill their roles. [28]”

ይኽ ከእዚኽ በላይ የተቀመጠው አባባል ፤ የቻይናን ሕዝብ ጥንታዊ ጠቢብነት የእሚያሳይ እና ሰዎች በስነ ምግባር ሳይታነጹ በፊት ፤ ሕግ በእሚደነግገው ቅጣት ብቻ ለማስተዳደር መሞከር እንዴት አድካሚ እንደ ሆነ የእሚያስረዳ እና በአንድ ማሕበረሰብ ውስጥ የስነ ምግባርን ሚና በእሚገባ የእሚገለጽ ነው በአንድ በኩል።

በሌላ በኩል ግን ፤ በመንግሥታዊ ሕግ እና በስነ ምግባር አስተምህሮ መካከል የአለው ልዩነት እምብዛም በመሆኑ ፤ ይኽ ኮንፊሸሳዊ አባባል ሰው ሊረዳው የእሚገባው ፤ ሕጉን ሳያስተምሩ ወይንም ሕዝብ ሕጉን መረዳት በእሚችልበት ኹኔታ በእውቀት ሳይገነባ በፊት ፤ ሕግ አውጥቶ ሕጉን እማያከብር ሰው ይቀጣል ማለት ፤ ውጤት አልባ ነው ፤ ምክንያቱም ፦ በሕጉ ጽንሰ ኃሳብ ያልታነጸ ሰው ሕጉን ሊያከብረው አይችልም በእሚለው ሊሆን ቢገባውም ፤ ይኽ ኮንፊሸሳዊ አባባል ፤ ከሌላዎች የኮንፊሸስ የማሕበራዊ ግንኙነት ስነ ምግባራዊ መመሪያዎች ጋር ተያያዞ ፤ ለምሳሌ ፦ ምንዝሩ አለቃውን ማክበር አለበት በእሚል ወይንም ምንዝሩ አለቃውን ማክበሩ ስነ ምግባር ነው በእሚል ፤ ሰዎች ለሺ ዓመታት በቆየ በእዚኽ ስነ ምግባራዊ አስተምህሮ ምክንያት ፤ ስነ ምግባርን ለማክበር ሲሉ መሠረታዊ ሰብዓዊ ነጻነታቸውን እና ክብራቸውን የእሚገፍ አለቃ ወይንም ባለስልጣን እንዲያከብሩ አድርጓቸዋል።

ይኽም በግዜ ኺደት ፍጽማዊ ወይንም አምባገነናዊ መንግሥታት ፤ መንግሥታት በመሆናቸው ብቻ ጨቋኝ ሆነው እንዲቀጥሉ ፤ በስነ ምግባር ስም ሕዝቡን አስሮ ፤ መሠረታዊ የሰብዓዊ ነጻነታቸውን እና ክብራቸውን የማስከበር ጥያቄ እንኳን እንደ አይጠይቁ አድርጓቸዋል።

በአጠቃላይ ፤ ልጅ አባቱን መታዘዙ ፣ ሠራተኛው አለቃውን መታዘዙ ፣ ሰርቶ ኃብት የአፈራው ሰው በበአለ ኃብትነቱ መከበሩ ፣ ተምሮ በእውቀቱ አንድ ደረጃ የደረሰው ሰው በእውቀቱ መከበሩ ላይ አይደለም ችግሩ ፤ እንዲያውም በአንድ ማሕበረሰብ ውስጥ ይኽን መሰል መከባበር ከሌለ ማሕበረሰቡ መሰንበትም አይችልም።

ይኽ የስነ ምግባር አስተምህሮ እና ማሕበራዊ ተዋረድ ግን ፤ የሰዎች ተፈጥሮዋዊ ነጻነት እና ክብር የእሚጋፋ መሆን የለበትም ነው ። ልጅ አባቱን መታዘዝ አለበት ፤ ይኽ ማለት ግን አባት ልጁን ይታዘዘኝ በእሚል ሰበብ አባት ልጁን ማሰቃየት ይችላል ማለት አይደለም ፣ ሠራተኛ አለቃውን ማክበር አለበት ፤ ሠራተኛ አለቃውን ማክበሩ ግን መሠረታዊ ሰብዓዊ ነጻነቱን እና ክብሩን ፈጽሞ በእሚያሳጣው አግባብ መሆን የለበትም።

እንግዲኽ በእዚኽ መልኩ ፤ ሲለው በእውቀት መሰል አቀራረብ ፣ በሌላም ግዜ በዘር ግንድ ፣ አንዳንዴም በኃይማኖታዊ ፣ ባሕላዊ ፣ ስነምግባራዊ አስተምህሮዎች ምክንያት ፤ ሰዎችን በተፈጥሮዋቸው እኩል ናቸው የእሚያስብሉዋቸውን እና ከሰዎች በምንም መልኩ ሊገፈፉ የእማይገቡ ተፈጥሮዋዊ ወይንም በፈጣሪ የተሰጡ መብቶችን በእሚጥስ መልኩ ለብዙ ሺ ዓመታት በእሚመራው እና በተዋቀረው ዓለም ውስጥ ነው ፤ ሰው ኹሉ ያለ ምንም ቅድመ ኹኔታ በእግዚአብሔር ፊት እኩል ነው የእሚለው የክርስቶስ ኢየሱስ አስተምህሮ የመጣው።

እንደ እሚታወቀው ኢየሱስ ክርስቶስ በነበረበት ዘመን ፤ በወቅቱ በነበሩት የኃይማኖት እና የፖለቲካ መሪዎች ወይንም በማሕብረሰብ ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ናቸው ከእሚባሉት ሰዎች ጋር ብዙም ግንኙነት የአልነበረው እና መነሻውን ፣ ውሎውን እና ኑሮውን ዝቅተኛ ከእሚባሉት የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር የአደረገ ፤ በኋላ በእርሱ ትምህርት ዓለምን የአነቃነቁት ደቀ መዛሙርቶቹም በእዛኽ ዘመን መመዘኛ የተናቁ የእሚባሉ (አሳ አጥማጅ ፣ ቀረጥ ሰብሳቢ ፣ በሰላሳ ብር ሰው እሚከዳ ፣ አማጺአን (ቀናዒ) ) ዓይነት ሰዎች የሆኑ ነበሩ።

ይኽን መሰል ማሕበራዊ ዳራ የአለው ኢየሱስ መንፈሳዊ (ኃይማኖታዊ) መሲህ እንደ መሆኑ ፤ ይዞት የመጣው መልዕክት በዋናነት ኃይማኖታዊ ቢሆንም ቅሉ ፤ የሰዎችን ሰብዓዊ እኩልነት በእሚመለከት ኢየሱስ ያንጸባረቃቸው ባሕሪያት እና አስተምህሮቶች ግን በግዜ ኺደት ትልቅ ፖለቲካዊ ፋይዳ የአላቸው ሆነዋል።

ለምሳሌ ፦ ኢየሱስ በመጣበት ዘመን የነበሩ የአይሁድ እምነት ተከታይ ዘመዶቹ ፤ በኃይማኖታዊ አስተምህሮዋቸው መሠረት ፦ እግዚአብሔር የአይሁድ አምላክ ብቻ የእሚመስላቸው የነበሩ በመሆናቸው ፤ ኢየሱስ እግዚአብሔር ዓለሙን እንዲሁ ወድዷል ብሎ ሲናገር ሲሰሙ እና እነርሱ የአይሁድ ብቻ አምላክ የአደረጉትን እግዚአብሔር[2] የዓለም ሕዝብ ኹሉ አምላክ ሲያደርግባቸው ፤ ለዘመናት ተመስርተውበት የነበረውን እኛ እና እነርሱ የእሚለውን አስተሳሰባቸውን በከፍተኛ ደረጃ የእሚፈትን ነበር።

ይኽም ብቻ ሰአይሆን ፤ ራሳቸውን በአላቸው ኃይማኖታዊ ትምህርት እና መሰጠት መመዘኛ ደረጃ አውጥተው ፤ አንዳቸውን ከሌላ በላይ ጻድቃን እና የተከበሩ አድርገው በእሚያቀርቡበት እና ራሳቸውን ጻድቅ ፤ እንደ እነርሱ ዓይነት ኃይማኖታዊ ትምህርት እና መሰጠት የሌለውን ሌላውን ሰው ኃጢያተኛ ብለው ዝቅ ዝቅ አድርገው በእሚመለከቱበት ኹኔታ ፤ ኢየሱስ ብዙ አወቅን እና ተመራመርን ለእሚሉት ለራሳቸው የእሚያስገርም ኃይማኖታዊ እውቀት እና መንፈሳዊነት ኖሮት ፤ ራሱን ኃጥአተኛ ተብለው ከተወገዙ እና ሰው ከእሚያገላቸው ፦ ቀረጥ ሰብሳቢ ፣ ሴተኛ አዳሪ ፣ በበሽታ ምክንያት ያለ ማቋረጥ ደም የእሚፈሳቸው ሴቶች (ስለ እዚኽም ርኩስ ከእሚባሉ) ፣ ከለምጻሞች ፣ ወዘተ ፤ ጋር ሰብዓዊነታቸውን የአከበረ ግንኙነት በማድረግ የአሳየው የሰብዓዊ እኩልነት የእሚያጎላ ተግባር ፤ በጥንቃቄ በተደነገገ ኃይማኖታዊ ደረጃ የተዋቀረውን ኃይማኖታዊ ስረዓታቸውን እና ግንዛቤአቸውን የእሚፈታተን ነበር።

ኃብት ሰብስበው በእሚሰጡት ምጽዕዋት እና በእሚያቀርቡት መስዕዋት ብዛት ፤ እግዚአብሔርን ማባበል እና በደላቸውን የእሚያስትሰርዩ ለእሚመስላቸው የገንዘብ አፍቃሪያን ፤ በገንዘቡ የእሚመካ ሰው ወደ መንግሥተ ሰማያት ከእሚገባ ይልቅ ፤ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብታልፍ ይቀላታል ወይንም ድሆች ብፁዐን ናቸው የእግዚአብሔርን መንግሥት ይወራሱሉና ብሎ በማስተማር ፤ በእግዚአብሔር ፊት ሰዎች የአላቸው የኃብት ልዩነት ምንም እንደ አልሆነ በማሳየት ፤ የዘመኑ ኃይማኖተኞች በባለ ኃብት እና በነዳያን መካከል የእሚያደርጉትን ልዩነት በመሻር ፤ ሰዎች በኢከነሚ ደረጃቸው ሰአይወሰኑ ወደ እግዚአብሔር በእኩልነት መቅረብ እንደ እሚችሉ ማሳየቱም እንደ እዛው ከፍተኛ እንደምታ ነበረው።

እነ እዚኽን እና መሰል አስተምህሮዎች እና ምልልሶች ይዞ የመጣው ኢየሱስ ፤ አስተምህሮዎቹ እና ተግባሮቹ ፤ ራሳቸውን በከፍተኛ ደረጃ የእሚያከብሩትን የወቅቱን ኃይማኖታዊ መሪዎች በከፍተኛ ደረጃ በማስቆጣቱ ፤ በተንኮል አሲረው ፤ ሕዝብ ያስታል ፣ ለመንግሥት ቀረጥ አትክፈሉ ይላል ፣ አምላክ ነኝ ይላል ፣ ቄሳር እያለ እርሱ እኔ ንጉሥ ነኝ ይላል ፣ ወዘተ ፤ በእሚል ለወቅቱ መንግሥት ከሰው በሞት አስቀጡት።

በእርሱ የአመኑት እና የእርሱ ደቀ መዛሙርት ሆነው የቆዩት በአብዛኛው ዝቅተኛ ከተባለው የማሕበረሰብ ክፍል የመጡት የእርሱ ደቀ መዛሙርቱም ፤ ከትንሳኤው በኋላ ፤ ከእኔ የሰማችሁትን ትምህርት ማንንም ሳትፈሩ አስተምሩ ብሎ ስለ አዘዛቸው ፤ ከእርሱ የሰሙዋቸውን ከላይ የዓየናቸውን ዓይነት ትምህርቶች ሲያስተምሩ ፤ ኢየሱስን በመግደላችን ይኽ ትምህርት ይጠፋል ብለው የነበሩት የቀድሞዎች የአይኹድ ኃይማኖት መሪዎች ጋር ስለ አጋጫቸው ፤ በደረሰባቸው ስደት ፤ ከኢየሩሳሌም ተሰደው ወደ ተለያየ የዓለም ክፍል ተበተኑ።

በእዚኽ መልኩ በወቅቱ በነበረው ዓለም የተበተኑት የክርስቶስ ደቀመዛሙርት በትምህርታቸው ልዩ ቃና ታዋቂነታቸው እየበረታ ሲመጣ ፤ የዛሬዋ ቱርክ ውስጥ በእምትገኝ አንጾኪያ በተባለች ከተማ ፤ ክርስቶሳዊያን ወይንም የክርስቶስ ተከታዮች (ደቀ መዝሙሮች) ለማለት ክርስቲያኖች ተብለው አዲስ ስያሜ ተሰጣቸው።

እነ እዚኽ ክርስቲያኖች ፦ አይሁዶቹ ራሳቸውን አይሁዳዊ ሌላውን የዓለም ሕዝብ አሕዛብ ብለው ኃይማኖታዊ አጥር በሰሩበት ፣ ሮማዊያኖቹ በእዛን ወቅት በእጅግ ተስፋፍቶ ብዙውን የዓለም ክፍል በአካለለው ግዛታቸው ውስጥ የሮማ ዜግነት የአለው እና የሌለው ብለው በሰዎች መካከል ግልጽ የሆነ የተለያየ የሕግ መዓቀፍ በዘረጉበት ፣ ግሪኮች ራሳቸውን ግሪካዊ እና ሌላውን የዓለም ሕዝብ በሙሉ ባርቤሪያዊ (አረማዊ ፣ አረመኔ ) ብለው ከፋፍለው እና ከግሪክ ውጭ የአለውን ሰው እንደ ሰው በእማያከብሩበት ፣ አብዛኛው የዓለም ማሕበረሰብ በማሕበረሰቡ ውስጥ ባሪያ እና ጨዋ የእሚል ማሕበራዊ ክፍፍል በእሚያደርግበት ዘመን ላይ ፤

“አይሁዳዊ ወይንም የግሪክ ሰው የለም ፥ ባሪያ ወይንም ጨዋ ሰው የለም ፥ ወንድም ሴትም የለም ፤ ኹላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና።”[3]

የእሚለውን የክርስቶስ ኢየሱስ መልዕክት ፤ በወቅቱ የነበረውን ባሕላዊ ፣ ፖለቲካዊ ፣ ኃይማኖታዊ አጥር ኹሉ እየተሻገሩ ፤ ለዓለም ሕዝብ ኹሉ በእኩልነት ማዳረስ ሲጀምሩ ፤ ምንም እንኳን መልዕክታቸው በመሠረታዊነት ኃይማኖታዊ ቢሆንም እና በእግዚአብሔር ፊት ይኽን መሰሉ የዘር ፣ የማሕበራዊ ደረጃ ፣ የጾታ ፣ የባሕላዊ ኃይማኖት ወይንም የእዚኽ ከተማ ዓምላክ ይኽ ነው የእዚያኛው ከተማ ዓምላክ ይኽ ነው ዓይነት ልዩነት ፋይዳ ቢስ ነው ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሰውን በሰብአዊነቱ እንጂ በእዚኽ መሰሉ የቅርጽ እና ግዜ አመጣሽ ልዩነቱ አይደለም የእሚመለከተው የእሚል ቢሆንም ፤ የቀደመው ዓለም እንደ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ተዋቅሮበት ለነበረው የጎጠኝነት አጥር በፍጹም የእማይስማማ መልዕክት ነበር መልዕክታቸው።

ከእላይ እንደ አልነው ፤ የቀደመው ዓለም ፤ በተፈጥሮ ሳይንስ እውቀት ፣ በኪነ ሕንጻ ፣ በወታደራዊ ሳይንስ ፣ በተለያዩ የፍልስፍና እውቀቶች ፣ ወዘተ ፤ ከፍተኛ እመርታ የነበረው እና ለዛሬው የሰው ልጅ ስልጣኔ ግብዓት የሆኑ ብዙ ሳይንሳዊ እና ሞያዊ እውቀት ያካበተ ቢሆንም ፤ ከሰበዓዊነት አንጻር ፤ ከእላይ በአልነው መሠረት ፤ ባሪያ እና ጨዋ ፣ ሮማዊ እና ሮማዊ የአልሆነ ፣ ግሪክ እና ባርቤሪያ ፣ አይሁድ እና አሕዛብ ፣ ወንድ እና ሴት ፣ ወዘተ ፤ በእሚል ማሕበረሰቡን ከፋፍሎ ፤ በእዚኽም ያልተጠቀሱ ሌሎች ብዙ የሰዎችን ተፈጥሮዋዊ የነጻነት እኩልነት እና ክቡርነት የእሚቃረኑ ወይንም የእማይቀበሉ ስለ እዚኽም ኢሰብዓዊ የሆነ አስተሳሰቦች እና አወቃቀሮች የነበሩት በመሆኑ ፤ የሰብዓዊ እኩልነትን መልዕክት ይዞ የመጣው ክርስትና ፤ ምንም እንኳን መልዕክቱ መንፈሳዊ ወይንም ኃይማኖታዊ ብቻ ቢሆንም ፤ የቀደመው ዓለም ፖለቲካዊ አወቃቀር ኢሰብዓዊ መሆኑን በግልጽ የእሚያሳይ ነበር።

ይኽን መሰል የፍቅር እና ሰው አክባሪነት የያዘው ክርስትና ፤ በመልዕክቱ ሰብዓዊነት ፤ በቁጥሩ ብዙ በሆነው እና በተገለለው ማሕበረሰብ ውስጥ ተቀባይነቱ እየሰፋ የሕዝብ ኃይማኖት መሆን ጀመረ። ውሎ አድሮም የተከበሩ የእሚባሉ እና ነገሥታት ኹሉ ሳይቀሩ ክርስቲያን መሆን ጀመሩ።

ይኽንም ተከትሎ ፤ የክርስትና ሰብዓዊነት ሰዎች በቀደመው ልማዳዊው ኢሰብዓዊ አስተሳሰባቸው እንዲቀጥሉ ሊፈቅድላቸው ስለ አልቻለ ፤ ቀስ በቀስ ፤ የቀደመው ዓለም ኢሰብዓዊ ማሕበራዊ ውቅር በአለበት መቀጠል የእማይችል ሆነ።

በጦርነት የማረካቸውን ባሪያ አድርጎ ጉልበታቸውን በመበዝበዝ ፣ ከእኔ ውጭ ናቸው የእሚላቸውን ማንኛውንም ሕዝብ መውረር ፣ መዝረፍ ፣ መጨፍጨፍ ፣ ማፈናቀል ፣ ወዘተ ፤ እንደ ወንጀል ሳአይሆን እንደ ጀብድ በማየት ፣ በራሱ ማሕበረሰብ ውስጥ ጥቂቶችን ብቻ የተለየ ጥቅም እና ስልጣን ባለቤቶች በማድረግ ሌላውን ድኃውን ፣ ባለ እዳውን ፣ እስረኛውን ፣ ወዘተ ፤ እንደ ሰው በአለመቁጠር ፤ ስልጣኔውን እና ጥንካሬውን የገነባው ያንን ቅድመ ክርስትና የነበረ ዓለም ፤ የስልጣኔው መሠረት የነበረው ኢሰብዓዊነት በክርስትና በመጋለጡ ፤ ራሱን እንደ ገና በአዲስ መልክ በሰብዓዊነት መርህ አግባብ እንደ ገና ከአላዋቀረ ፤ ስልጣኔው መቀጠል እንደ አይችል አደረገው።

ከእዚኽም የተነሳ ከ5ኛው ምዕተ ዓመት በኋላ ክርስትና የተስፋፋባቸው የቀደመው ዓለም ስልጣኔዎች ፤ መንግሥታቸው የስልጣኔው መሠረት የሆነውን ኢሰብአዊነቱን በክርስትና ምክንያት እየአቆመ ሲኼድ ፤ የወቅቱ መንግሥት እና ስልጣኔ በኢሰብአዊ መርኽ ላይ የተዋቀረ በመሆኑ እና ይኽን ኢሰብአዊ አወቃቀራቸውን በሰብአዊ አግባብ የእሚተኩበት አዲስ እውቀት ስለ አላዳበሩ ፤ ስልጣኔያቸው ቀስ በቀስ መዝበጥ ጀመረ።

ይኽም በመሆኑ ፤ ቀላሉ ፣ ግልጹ እና አዲሱ የክርስትና መልዕክት ፤ የቀደመውን ዓለም መዋቅር ያዛባ ሆነ ። የግብፅ ፣ የባቢሎን ፣ የፋርስ ፣ የግሪክ እና የሮም እውቀቶች ኹሉ ተደምረው ፤ በጣም ቀላል እና መሠረታዊ የሆኑትን ፦ባለ እንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የእሚሉትን የክርስቶስን ህግጋት ሰአይሆን ባለ እንጀራህን አትግደል ፣ አትስረቅ እና አትዋሽ የእሚሉትን የሙሴን ሕግጋት እንኳን መስተካከል አቃተቸው ።

ያ ኹሉ መጽሐፍ ፣ ምርምር ፣ እውቀት ፣ ግዜ እና ትምህርት ፤ አትግደል ፣ አትስረቅ እና አትዋሽ መሰል ፤ ቀላል ፣ ግልፅና እና ለኹሉም ሰው ሊገባ የእሚችል ሰብዓዊ (Humanitarian) እውቀት ሆነው መምጣት አቃተው።

ከእዚኽም የተነሳ ፤ ሰብዓዊነት ላይ ተማክሎ ፤ ይኽ መሠረታዊ እና የተራው ሕዝብ እውቀት ሆኖ የመጣው የክርስትና አስተምህሮ ፤ በቅለቱ እና በሕዝብ ዘንድ የአለው ተቀባይነት በፍጥነት ስለ ጨመረ ፤ በዘመኑ የነበረውን ምድራዊ ሳይንሳዊ እውቀት (The Secular or Temporal Knowledge) ሸፈነው ።

ቅድመ ክርስትና የነበረው ዓለም ፤ ምንም እንኳን ታላላቅ ታሪክ የተመዘገበቡት ወቅት ቢሆንም ፤ ኃብት ወይንም ወታደር የሌለውን ሰው ህይወት ከመጤፍ ለማይቆጥሩት ጥንታዊ ኃያላን ፦ የሰው ክብሩ በኃብቱ አይለካም ወይንም ነዳያን ብፁዓን ናቸው የእሚለው የክርስትና አስተምህሮ እና አስተሳሰብ ፤ በባሪያ ንግድ ፣ በቀኝ ግዛት ፣ በጉልበት ብዝበዛ ስልጣኔውን መስርቶ ትልልቅ ታሪክ ሲሰራ የነበረውን ይኽን ቀዳማዊ ዓለም መሠረቱን አናወጠው ።

የቀደመው ዓለም በእዚኽ መልኩ በክርስትና ሰብዓዊነት ምክንያት ሲናወጥ ፤ በጥሩ ጅማሮ ላይ የነበሩት ሌሎች የማሕበራዊ እና የተፈጥሮ ሳይንስ እውቀቶቹ አብረው በመንኮታኮታቸው ፤ የክርስትና መልዕክት ኹሉንም የእውቀት መስኮች ሸፈነ።

በእርግጥ ክርስትና የሰብዓዊ እኩልነት መልዕክት ፦ ጂኦሜትሪ ወይንም የኪነ ህንፃ ጥበብ ፤ አይጠቅምም ፣ አይረባም ወይንም ትክክል አይደለም አል አለም ፤ ነገር ግን የሰው ልጅ ክብሩ እነ እዚኽን በማወቅ እና ባለ ማወቁ አይለካም ፤ ሰው በሰውነቱ ክቡር ነው ፤ ስለ እዚኽ ፦ ቢማርም በአይማርም ፣ የእዚኽ ሐገርም ሆነ የእዚያም ሐገር ሰው ቢሆን ፣ ኃብት ቢኖረው በአይኖረው ፤ ክቡር ነው ፤ ስለ እዚኽ ፦ አትግደለው ፣ አትስረቀው ፣ አትዋሸው ወይንም አትበድለው ምክንያቱም እግዚአብሔር ፤ የሰውን ዘር ፣ የቆዳ ቀለሙ ሳይወስነው ፣ የእውቀት ደረጃው ሳይገድበው ፣ የኃብት ደረጃው ሳይአግደው ፤ ያለምንም ቅድመ ኹኔታ ኹሉንም ሰው እኩል ይወዳል ስለ እዚኽ አንተም ባለ እንጀራህን እንደ ራስኽ ውደድ የእሚል መልዕክት ይዞ ነው የመጣው ።

ይኽ የቀደመው ዓለም ፍልስፍና የገነባውን ማሕበራዊ ስረዓት ያፈራረሰ እና ዓለም እንደ ገና በአዲስ መልክ መዋቀር እንደ አለባት የአሳሰበ የክርስትና የወንድማማችነት መልዕክት ፤ በጣም ቀላል እና ግልፅ የወንድማማችነት ስብከት ፤ የሰው ልጅ በክህደት ፣ ያለፍርድ እንደ ቅጠል በእሚረግፍባት ፣ ሰቆቃ እና በደል እጅግ ከመብዛታቸው የተነሳ የሰውን ህይወት እና ክብር በአራከሱባት ዓለም ፤ የቀደመውን ዓለም ማሕበራዊ እሴት በማስጣል ፤ የሰዎችን ዓዕምሮ በብቸኝነት ተቆጣጠረ ።

ከእላይ እንደ አልነው ፤ ምንም እንኳን ክርስትና ሳይንስ መጥፎ ነው በአይልም ፤ የመልዕክቱ ጥንካሬ የወቅቱ የሰለጠነውን ዓለም ሕዝብ በወንድማማችነት መልዕክቱ በደስታ ስለ አናወዛቸው ፤ ከእዚኽ በኋላ ጦርነት የእማይኖር ፣ ክህደት የእማይኖር ፣ ሐኪም የእማያስፈልግ ፣ ድልድይ እና ህንፃ የእማያስፈልግ ይመስል ፤ አዳዲሶቹ ክርስቲያኖች በብዙ ሺ ዓመታት የዳበሩ የሳይንሳዊ እውቀቶች አብረው ከጨቋኙ ፣ ከትምክህተኛው ፣ ሰው ከእሚንቀው የቀደመው ዓለም ኢሰብዓዊነት ጋር አብረው ወረወሩት ።

የእንግሊዘኛው አባባል እንደ እሚለው ፤ ህፃኑን ከታጠበበት ውኃ ጋር አብረው ደፉት ።

ክርስትና በፍጥነት እየገሰገሰ ፤ በታሪክ እንደ እምናውቀው ፤ በሮም ፣ በአክሱም እና በአርሜንያ ፥ ነገሥታቶቻቸው ሳይቀር የክርስትና እምነት ተከታይ መሆን በመጀመራቸው ፤ በተቀራራቢ ግዜ (እ.አ.አ. ከ 300 – 350 ዓ.ም.) ቤተክርስቲያን እና መንግሥት ተዋህደው ፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ በነባሪው የመንግሥት ፍልስፍና ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳረፍ ጀመረ ።

ይኽን መሰሉን የክርስትና አስተምህሮ ተፅኖ ተከትሎ ፥ ተፅኖዋ እየናረ የመጣችው ቤተክርስቲያን ፤ አካዳሚያ (ፕሌቶ የመሠረተው) እና ሊስየም (አርስታትል የመሠረተው) የእሚባሉትን የግሪክ ፈላስፎች ትምህርት ቤቶችን የአረማዊያን (የጣዖት አምላኪዎች) ትምህርት ቤቶች በማለት እና የቀደመውን ዓለም ሳይንሳዊ እውቀት የጣዖት አምላኪያን ትምህርት ብላ እየኮነነች እና እየዘጋች ፤ በቤተክርስቲያን ስር በእሚተዳደሩ እና በዋናነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይዘት በአላቸው አስተምህሮዎች ላይ በእሚያተኩሩ ትምህርት ቤቶች (schools) (እንደኛ ሐገሩ ቄስ ትምህርት ቤት) ተካቻቸው ።

በመናናቅ ፣ በመገዳደል ፣ በዘረፋ ፣ በትምክህት የዛለው የዓለም በርኃ ፤ የፍቅር ዝናብ ሲዘንብበት ፤ ሌላውን ምድራዊውን ኃላፊነቱን ረስቶ በመልዕክቱ ዝናብ ሲረሰርስ እና በምድራዊ ‘ገነት’ ውስጥ ሲኖር ፤ የቀደመው ዓለም ምድራዊ እውቀት ኹሉ ችላ ስለ ተባለ ፤ መንግሥታት ኃላፊነታቸውን ችላ አሉ ፣ ወታደሩ ደከመ ፣ ድልድዩ ዘበጠ ፣ ህንፃ ፈራረሰ ፤ ዓለም ሳያስበው ምንም እንኳን በሰብዓዊ እሴት ላይ እንደ ገና ቢታነጽም ፤ እነ እዚኽ ሰብዓዊ እሴቶች ፤ የቀደመውን ኢሰብአዊ ማሕበራዊ ተቋማት በአዲሱ የሰብዓዊ እሴት እንደገና እንዲዋቀሩ ስለ አላደረገ ፤ ዓለም በሌላው መስክ የኋላ ቀርነት እንቅልፍ አንቀላፋ ።

እ.አ.አ. ከ1737 – 1794 ዓ.ም. የኖረው ኤድዋርድ ጊበን (Edward Gibbon) የተባለው ታዋቂ የሮም ታሪክ ጸሐፊ ስለ ኢትዮጵያ ሲናገር “ዙሪያቸውን ኹሉ በኃይማኖታቸው ጠላቶች ተከበው ፤ መላውን ዓለምን ረስተው እና በመላው ዓለምም ተረስተው ፤ ኢትዮጵያዊያኖች ለ1 ሺ ዓመት አሸለቡ” እንደ አለው ፤ ኢትዮጵያዊያኖች ብቻ ሰአይሆን ለ1 ሺ ዓመት የአሸለቡት ፤ መላው የክርስትና ዓለም ነው ፤ ከ5ኛውም ምዕተ ዓመት በኋላ ለ1 ሺ ዓመት የአሸለበው።

በታሪክ እንደ እምናውቀው ፤ ሮም በስልጣኔ ገሥግሣ ፤ ለእዚኽ ዘመን እንኳን የእሚያስገርመውን ከለሲየም (Colosseum)[4] ተብሎ የእሚታወቀው ታላቁ ስታዲየም የገነባች እና የእምትጠቅም ከመሆን አሽቆልቁላ ፤ በ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሮም ከወደቀች በኋላ ፤ የሮም ነዋሪዎ ይኽንን ድንቅ የኪነ ህንጻ ውጤት ፤ እንደ ካባ እየቆፈሩት የጎጆቻቸው መቀለሻ ድንጋይ የእሚለቅሙበት አድርገውት ነበር።

ቀዳሚ ስልጣኔ የነበረው እና በወንጌል ተለውጦ አማኝ የሆነው ፤ የክርስቲያኑ ዓለም ኹሉን ነገር በእዚኽ መልኩ እርግፍ አድርጎ ትቶ ፤ ከንጉሥ እስከ ጭፍራው የቤተክርስቲያን ሰው ሲሆን ፤ የሳይንሳዊ እውቀታቸው ማሕበራዊ እድገት ወደ ማምጣት ደረጃ ያል-አደረሳቸው እና የዕለት ተዕለት ኑሮን ማሸነፍ ትልቅ ፈተና የሆነባቸው ፤ ከክርስትና ዓለም ውጭ ያሉ ሕዝብ ‘የመነኑ’ ነገሥታት መናገሻ የኾነውን የክርስቲያኑን ዓለም ወረሩት ።

የሮማ ነገሥታት ይኽ ሲሆን ፤ አትኩሮታቸውን የመጀመሪያው ክርስቲያን የሮም ኢመፐረር በኾነው ቆስጠንጥን (Constantine) ስም በተሰየመችው ኮንስታንቲኖፖል ላይ አድርገው ፤ በክርስትና መልዕክት ራሳቸውን እያሰከሩ ፤ ሮም እየተዳከመች ስትኼድ እና በኋላም ስትወረር ፤ ግዜያዊ መከላከል ከማድረግ ያልዘለለ ሙከራ በማድረግ ፤ ስለ ቀደመው ዓለም ብዙም ግድ እንደ ሌላቸው አሳዩ ።

ብዙም ሳይቆይ የእስልምና እምነት ፤ በእዚኽ መልኩ በክርስቲያኖች ችላ የተባለውን የቀረውን ዓለም በአጭር ግዜ በመቆጣጠር ፤ ከእዚኽ ቀደም ኃያላን የነበሩ ነገሥታት ‘መንነው’ የተውትን ዓለም ተቆጣጠረው ።

ከእዚኽም የተነሳ ፤ ነገሥታት ‘ከመነኑበት’ ከ500 ዓ.ም. እስከ 1500 ዓ.ም. ድረስ የአለው ይኽ ዘመን እንግዲኽ ፤ በክርስቲያኑ ዓለም ፤ መንግሥት ደክሞ ፤ ቤተክርስቲያን የአየለችበት በመሆኑ እና ትምህርትም በዋናነት ኃይማኖትን ለማጥናት በእሚያስችል መልኩ የተቀረፀ በመሆኑ ፤ ሰው መንፈሳዊውን ነገር በመከተል ምድራዊውን ሳይንስ እና እውቀት ፈፅሞ ችላ የአለበት እና የመንግሥት ሚና ቀስ በቀስ በቤተ ክርስቲያን የተተካበት ነበር ።

ከእዚኽም የተነሳ ቤተክርስቲያን ትላልቅ ህንፃ ስትገነባ ፣ ካህናቱ እጅግ ክቡራን ሲሆኑ ፤ ሰፊው ሕዝብ መንፈሳዊ ትምህርት ብቻ እያገኘ ምድራዊ ኑሮው ግን ከመልካም አስተዳደር ዕጦት ፣ ከመሠረታዊ ፍላጎቶች አለመሟላት ፣ ወዘተ ፤ የተነሳ ፤ የምድራዊው ነገር ቸልታ አውሮፓን አዝብጦ ሕዝቡን ለመከራ እና ለድህነት በመዳረጉ ፤ ይኽን የመካከለኛ ዘመን ቆይታ የታሪክ ምሁራን የጨለማው ዘመን ይሉታል ።

በእዚኽ የጨለማው ዘመን ቤተክርስቲያን የቀድሞውን ዘመን የአካዳሚያ እና የሊስየም ትምህርቶችን ችላ በማለት አትኩሮቷን ኹሉ ወይንም የአትኩሮት ማዕከሏን ስነ-መለኮት ወይንም ታውሎጊያ በማድረግ ፤ በፍልስፍናው ትምህርት መስክ የስኮላስቲክ ዘመን የእሚባለውን ከ500 ዓ.ም. እስከ 1500 ዓ.ም. የቆየውን ዘመን ውስጥ ገባች።

ይኽ የስካላስቲክ ዘመን የእሚባለው ፤ ምንም እንኳን አመክንዮ (reason or logic) አስፈላጊ እንደሆነ ቢያምንም እና በትምህርት ስረዓቱ ውስጥ ቢያካትታቸውም ዋናው ትኩረቱን የአደረገው መንፈሳዊው ትምህርት ላይ በመሆኑ ፤ አመክንዮን የትኩረቱ መዓከል የኾኑትን መንፈሳዊ ቆኖናዎችን ለመመሥረት ነበር የተጠቀመበት ። በምክንያት ቢያምንም ፣ አመክንዮን ቢያጠናም የእሚያጠናቸው ፤ ለምሳሌ ፦ መልዓክት አካላቸው ከምን ተሰራ ? መንፈሳዊ አካላት መልዓክትን ጨምረው ምን ያኽል ቦታ ይፈልጋሉ ? ማማተብ ያስፈልጋል ወይንስ አያስፈልግም ? ወዘተ ፤ ዓይነት መንፈሳዊ ጥያቄዎችን መመለስን ብቻ ታሳቢ የአደረገ ነበር ።

በግዜ ኺደት ግን ፤ እንደ እዚኽ ዓይነት ፥ በመርፌ ጫፍ ላይ ስንት መልዓክት መደነስ ይችላሉ ዓይነት ስኮላስቲክ ወይንም የገዳም (የቄስ ተማሪ) ምርምሮችን እንዲያደርጉ ስዋሰው ( Grammar ) ፣ አመክንዮ ( Logic ) ፣ ሙግት (Dialectic ) ፣ ዲስኩር (Rhetoric) ፣ ምንባብ ( Reading ) ፣ ወዘተ ፤ ያጠኑ ተማሪዎች ፤ በእዚኽ ኺደት ያዳበሩት እውቀታቸው ከመንፈሳዊ ውጭ ላሉ ፤ ለተለያየ የጽህፈት ሥራ ተፈላጊ እየ አደረጋቸው በመምጣቱ የዘመነ ስኮላስቲክ ምሁራን ከመንፈሳዊ ዓለም ውጭ በምድራዊም ህይወት ተፈላጊነታቸው እየጨመረ ስለ መጣ ፤ አይቀሬው የምድራዊው መንግሥት አስፈላጊነት ራሱን እየ አሳየ መጣ ።

የግንባታ እውቀት ፣ የህክምና እውቀት ፣ የታሪክ እውቀት ፣ የአስተዳደር እውቀት ፣ ወዘተ ፤ አስፈላጊነት ከፊሎቹን ስኮላስቲኮች ፤ እነ እዚኽን እውቀቶች ፤ ምንም እንኳን ለመንፈሳዊ ሕይወት ቀጥታ ፋይዳ በአይኖራቸውም ለዕለታዊ ኑሮ አስፈላጊ በመሆናቸው መጠናት አለባቸው የእሚሉ አደረጋቸው ።

ለምሳሌ ፦ በሽታ በፀሎት ብቻ ነው መፈወስ የአለበት ወይንስ በህክምና ሳይንስ እውቀትም መታከም አለበት ? የእሚለው ኃሳብ ወይንም ይኽን መሰሉ ክርክር ዘመነ ስኮላስቲስዝምን ፤ ለሰዋዊ ችግር ሰዋዊ መፍትኼ ተገቢ ነው የእሚሉ ሰዎችን ማምጣት በመጀመሩ ፤ ኹኔታው ዘመነ ኂውማኒዝም (Humanism) ወይንም ሰባዊነት አስከተለ ።

በዘመነ ሰባዊነት ፤ ለሰብዓዊ ችግር ፤ መንፈሳዊ መፍትኼ ብቻ ሰአይሆን ሰዋዊ መፍትኼም ይገባል ተባለ ። ይኽም የአስተሳሰብ እመርታ ፤ ከእዚያኽን ግዜ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ፤ የሰውን ችግር በሰው አዕምሮ መፍታት በእሚል ተቃኝቶ የተፈጥሮ እና የማሕበራዊ ሳይንስ መስኮችን በማስተዋወቅ ፤ ለሰው ችግር ሰዋዊ መፍትኼ በማፈላለግ ላይ አተኩሯል ።

በእዚኽ መልኩ ፤ ዘመነ ሰባዊነት ፤ ዘመናዊው የማሕበራዊ ሳይንስ የክርስትናን የሰብዓዊነት በዓማከለ መሠረት የቀደመው ዓለም በተነጻጻሪነት ከእርሱ በተሻለ አዳብሮዋቸው የነበሩትን የተፈጥሮ እና የማሕበራዊ ሳይንስ እውቀቶች ጠቃሚነታቸው እና አስፈላጊነታቸውን በመረዳት ፤ በትምህርት ስረዓቱ ውስጥ አካተታቸው።

በእዚኽም አግባብ የዘመናዊ ሳይንስ ፤ ማሕበራዊውም ሆነ ተፈጥሮዋዊው ፤ ከቤተክርስቲያን በክርስትና ሰብዓዊ መልዕክት ተቃኝቶ ወይንም ተዋጅቶ እንደገና ተኃድሶ እንደ አዲስ አንሰራራ።

ሰብዓዊ ችግሮችን ከእምነት በአሻገር በሰብዓዊ ምርምር እና እውቀት ለመፍታት መሞከር ፤ በመንፈሳዊ እውቀት ላይ ብቻ አተኩሮ የነበረውን ዘመን ሶኮላስቲስዝምን ወደ ዘመነ ሰባዊነት አሸጋገረው።

ሰባዊነትም በእዚኽ መልኩ የራሱን ዘመን ከአስጀመረ እና ራሱን ከስኮላስቲኮቹ ከነጠለ በኋላ ፤ ሰባዊነት ራሱ ደግሞ ተፈጥሮ የእግዚአብሔር ሥራ ስለሆነ መንፈሳዊ ሕይወት ከተፈጥሮዋዊ ህይወት ጋር ስለ እማይጋጭ ወይንም አመክንዮ ከመንፈሳዊ የእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ስለ እማይጋጭ ፤ የተፈጥሮ ሳይንስ ምርምር ከመንፈሳዊው ጥናት በተጓዳኝ ፤ የሰውን ልጅ ሰቆቃ ለመቀነስ ቢውል መልካም እንጂ ክፉ አይደለም በእሚሉ እና የለም ኃይማኖት ራሱ የሰው ልጅ ችግር ምንጭ በመሆኑ መንፈሳዊነት ሰባዊነት ከእሚፈቅደው የሰውን ችግር በሰው ምርምር እና ጥናት መፍታት ይገባል ከእሚለው ሰባዊነት ጋር መዳበል የለበትም በእሚሉ ኹለት ጎራዎች ተከፈለ።

ይኽም ማለት ፦ በውስጡ ጽንፈኛ አንጃ በመፈጠሩ ፤ ሰባዊነት በለዘበተኞች እና በጽንፈኞች ጎራ ለኹለት ተከፈለ።

ለዘብተኞቹ “እውነት ኹሉ የእግዚአብሔር እውነት ነው” ወይንም አንድ እውነት ምንም እንኳን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በአይኖርም ፤ እንደ እግዚአብሔር እውነት መቀበል አለብን ምክንያቱም ፦ እግዚአብሔር እውነት ስለሆነ ከእግዚአብሔር ውጭ የሆነ እውነት የለም ብለው መንፈሳዊነትን ከአመክንዮ ወይንም ከሳይንሳዊነት ጋር አብረው ሲቀበሉ ፤ ጽንፈኞቹ ሰባዊያን ደግሞ ፤ ኃይማኖትን እሰከ እነ ጭራሹም በመቃወም ፤ ያለ መንፈሳዊ ጥናት በሳይንሳዊ ጥናት እና እውቀት ፤ የሰውን ችግር በተፈጥሮ እና ማሕበራዊ ሳይንስ እውቀት ብቻ እንፈታለን በማለት በታሪክ ዘመነ አመክንዮ (Age of Reason) የእሚባለውን አስጀመሩ ።

ሰብዓዊነት እና የወንድማማችነት መንፈስ ለማዳበር ፣ ስነ ምግባር ለማዳበር ፣ የሥራ ሰው ለመሆን ፣ በአጠቃላይ የምድራዊ ሕይወት ችግራችንን ለመፍታት ፤ መንፈሳዊ እውቀት አያስፈልግም ሳይንስ በቂ ነው የእሚሉት እና አንዳንዴም ኃይማኖት ለሰው ልጅ ኹለንተናዊ እድገት እንቅፋት በመሆኑ መጥፋት አለበት እስከ ማለት የእሚደርሱት ጽንፈኛ ሰባውያን ናቸው ማለት ነው ።

ከእዚኽ የሰባዊያን የጎራ ክፍፍል ተነስተን ፦ ዘመናዊው ትምህርት ቤት ወይንም ዩንቨርስቲ ፤ ስነመለኮትን ነጥሎ የእሚያስቀር ከሆነ በፅንፈኞቹ ሰባዊያን ማዕከል ተምሳሌት የተሰራ ነው ማለት እንችላለን ። ሚዛናዊው ዩንቨርስቲ ሰባዊያን እና መለኮታዊያን የእሚገኙበት ወይንም ሳይንስም ስነመለኮትንም በአንድ ግቢ ውስጥ በትምህርትነት የእሚሰጥበት ነው ።

በሌላ አገላለፅ ፤ ምንም እንኳን ክርስትና ጅማሮው ላይ ከሰብዓዊ እሴት ውጭ ተገንብቶ የሰው ልጆች ስቆቃ ምንጭ የነበረውን የቀደመውን ዓለም ስረዓት በወንድማማችነት መልዕክቱ ቢንደውም ፤ ይኽ የክርስትና የሰብዓዊነት መልዕክት ፤ ከክርስትና መንፈሳዊ እሴት ጋር የእማይጋጩትን እና እንዲያውም የሰው ልጅ አጋዥ የነበሩትን የተለያዩ ምድራዊ እውቀቶች ከአሮጌው ኢሰብዓዊው ስረዓት ጋር አብሮ ስለ አስወገዳቸው ፤ ከክርስትና በኋላ የነበረው የክርስቲያኑ ዓለም ፤ በመንፈሳዊ እውቀት የበረታ እና በሳይንሳዊ (ሰባዊ) እውቀት የቀነጨረ ስለ አደረገው ፤ በእዚያኽ ዘመን ቁሳዊው የሰው ህይወት እንዲ ጎሳቀል ማድረጉ ነበር ፤ ሰባዊያን እንዲነሱ ምክንያት የሆነው ።

እነ እዚኽም ክርስትና ቢያንስ ለ1 ሺ ዓመታት ከናኘ በኋላ የመጡ ሊህቃን ፤ ከፊሎቹ ወይንም ክርስቲያን የሆኑት ፤ በመጀመሪያዎቹ የክርስቲያን ኃያላን ችላ የተባለውን ሳይንስ ፤ የክርስትናን የሰብዓዊነት መልዕክት ሳይለቁ ከሳይንሱ ጋር ማጣጣም በመጀመራቸው ወይንም በአመጡት የሰባዊ (Humanism) አስተምህሮዋቸው ፤ የዘመናዊው ዓለም ስልጣኔ ቀያሽ እና መሐንዲስ ሆነዋል ፤ ከላይ እንደ አልነው ምንም እንኳን ፤ ከፊሎቹ ክርስትና ያስተዋወቀውን የሰብዓዊነት መልዕክት ያለክርስትና ፥ በክህደት_ዓምላካዊነት (Atheism) ይዘው መቀጠል የፈለጉ ቢኖሩም ።

በአጠቃላይ ፤ ፈጣሪን አከበሩም ካዱም ወይንም በውስጣቸው የኃይማኖተኛ እና የከኃዲያን ጎራው እንደ አለ ሆኖ ፤ ሰባዊ የእሚባሉት ከመንፈሳዊ አጥር በመውጣት የተፈጥሮ ሕግን ፣ የጤናን ጉዳይ ፣ ስነመንግሥት እና ሕዝብ አስተዳደር በአጠቃላይ የዘመናዊ ዩኒቨርስቲ ማሕበራዊ እና ተፈጥሮዋዊ ሳይንስ ብሎ የእሚያስተምራቸውን ትምህርቶች ፤ ሰዋዊ እውቀት ለሰው ምድራዊ ችግር መፍቻ ለማድረግ በማሰብ ፤ ማጥናት ጀመሩ ።

የሰውን ችግር በሰው ተፈጥሮዋዊ ክህሎት እና ጥበብ የመፍታ አካኼድ ሆነ ሰባዊነት ፤ እንደ ሳይንሳዊ መስክ።

እንግዲኽ ይኽ የሰባዊያን መነቃቃት ነው ፤ ዘመነ ሳይንስ ወይንም የአውሮፓ ህዳሴ የእሚባለውን ዘመን አስጀማሪ ። እንደ አልኩት ፤ ምንም እንኳን ፥ እግዚአብሔር አያስፈልገንም ያሉ ሰባዊያን ቢኖሩም ፥ እግዚአብሔር እና ሳይንስ አይጋጭም የአሉትም የአሉ፟ በመሆናቸው ፤ የአሉ፟ መሆን ብቻ ሰአይሆን በህዳሴው እንቅስቃሴ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻም የተጫወቱት እነርሱ በመሆናቸው (Thomas Hobbes, Jhon Locke, Rene Descartes, Isaac Newton, Adam Smith, etc) ፤ የዘመናዊውን ዓለም ፖለቲካ ንድፍ የሰሩት ሰዎች በእግዚአብሔር የአመኑት ሰባዊያን ወይንም እግዚአብሔር እና እውነተኛ ሳይንስ አይጋጭም የአሉትም ናቸው ።

በክርስትና ዘዋሪነት ፤ ሰዎች ኹሉ እኩል ሆነው ተፈጥረዋል ፤ በፈጣሪያቸውም በማንም ሊገፈፉ የእማይገባቸው የተወሰኑ መብቶች ተጎናጽፈዋል ፤ ከእነ እዚኽም መካከል ፦ የህይወት ፣ የነጻነት እና መሻታቸውን የመከተል መብቶች ናቸው ፤ በእሚለው የሰብዓዊነት መርህ ተቃኝቶ በአዲስ ኃይል እንደ ገና የመጣው ዘመናዊ የተፈጥሮ እና የማሕበራዊ ሳይንስ ፤ በአውሮፓ ከ15ኛው ምዕተ ዓመት በኋላ የጀመረውን እና አሁን የእምንገኝበት ዓለም ስልጣኔን የመሠረተው።

በእዚኽ የዘመናዊ ስልጣኔ የማዕዘን ድንጋይ በሆነው ፤ የሰብዓዊ እኩልነት ወይንም የሰዎች የማሕበራዊ አህድነት መልዕክት አንጻር ፤ ከ 5 ሺ ዓመታት በጥቂት በእሚበልጠው የሰው ልጅ የስልጣኔ ታሪክ ውስጥ የነበሩ ዋና ዋና መንግሥታዊ ትርክቶችን ለመቃኘት ፤ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የነበሩ መንግሥታዊ ትርክቶች ባሕላዊ እና ሳይንሳዊ በእሚል ኹለት ጎራ ልእንከፍላቸው እንችላለን።

በጠቅላላው ባሕላዊ እና ሳይንሳዊ በእሚሉት አባባሎች መካከል የአለው ልዩነት ፦ ባሕላዊው አንድ ክስተት ሆኖ በመገኙቱ ብቻ ወይንም አንድን ብኺል በአንድ አጋጣሚ ተብሎ በመገኘቱ ብቻ እንደ ብቸኛ ትክክለኛ ክስተት እና እውነት ፤ ያለ ምንም ጥያቄ ተቀብሎ ፤ በአለበት የእሚያስቀጥለውን ነው።

ሳይንሳዊነት ደግሞ ከእዚኽ በተቃራኒ ፤ አንድን ክስተት ወይንም ብኺል/እውቀት በአለበት ተቀብሎ ሊያስቀጥለው ቢችልም እንኳን ፤ ክስተቶች እና ብኺሎች/እውቀቶች ተገቢ እና በአለቡት መቀጠል የአለባቸው መሆናቸውን ወይንም አለመሆናቸውን ፣ መሻሻል ፣ መለወጥ መቻል አለመቻላቸውን ፤ የተለያዩ ዓይነት ጥያቄዎች ጠይቆ ፤ እነ እዚኽን ክስተቶች እና ብኺሎች የአላቸውን ኹኔታ ፤ በግዜ ቀመር ውስጥ በተጨባጭነት ከአላቸው ገጽታ ጋር በማመሳከር ፤ ወደ አንድ ድምዳሜ ለመድረስ የእሚሞክር ነው።

በመንግሥታዊ ትርክትም አኳያ ፤ ባሕላዊ ትርክቶች አንድ መንግሥት በታሪካ አጋጣሚ በስልጣን ላይ በመገኘቱ ምክንያት ወይንም በአንዱ ዓይነት ባሕላዊ እምነት ወይንም አስተምህሮ መሠረት የተመሠረተ በመሆኑ ፤ ያለ ምንም ጥያቄ በነበረበት ደረጃ እና አኳኋን እንደ ትክክለኛ ወስዶት እና ምርምራዊ ጥያቄዎችንም እያደፈነ ፤ በአለበት ያለ ምንም የለውጥ ተነሳሽነት በአለበት ለመቀጠል የእሚፈልገውን ትርክት ነው።

በአንጻሩ ሳይንሳዊ የእምንለው መንግሥታዊ ትርክት ደግሞ ፤ ምንም እንኳን መንግሥት ሳይንሳዊው የእውቀት መበርበሪያ ዘዴ ሳይዳብር በፊት የነበረ ቢሆንም ፤ መንግሥትን እንደ አንድ የጥናት ርዕስ ወስዶ ፤ መንግሥት እንዴት ሊፈጠር እንደ ቻለ ፣ የመንግሥት አስፈላጊነት ከምን እንደ እሚመነጭ ፣ የመንግሥትነት ስልጣን ምንጭ ምን እንደ ሆነ ፣ ወዘተ ፤ ለመረዳት ፤ ዙሪያ መለስ ጥናት እና ምርምር ከአካኼደ በኋላ ፤ መላምቱን ከታሪካዊ እውነታዎች ጋር አዋዶ ፤ ስለ መንግሥት አንድ ወጥ የሆነ የአስተሳሰብ ወይንም አመክንዮዋዊ ስረዓት (Ideological Framework) የእሚያስቀምጠውን ነው።

ከእዚኽም የተነሳ ፤ ሳይንስ ራሱ እንደ እውቀት መበርበሪያ ዘዴ ፤ በአግባቡ ተድራጅቶ ከተዋወቀ ከ500 ዓመት በላይ የእማይበልጥ እድሜ የነበረው በመሆኑ ፤ ከ15ኛው ምዕተ ዓመት በፊት የነበረው መንግሥታዊ ትርክት በሙሉ ፤ ባሕላዊ መንግሥታዊ ትርክት ነበር ማለት እንችላለን።

ይኽም ማለት ፤ ከ5 ሺ ዓመት በጥቂት ከእሚበልጠው የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ወደ 4,500 ገደማ ለእሚሆኑት ዓመታት የሰው ልጅ ፤ በባሕላዊ እውቀት የተቃኘ መንግሥታዊ ትርክት ነው የነበረው ማለት እንችላለን።

ምንም እንኳን ባሕላዊው የመንግሥት አስተሳሰብ ከዓለም ላይ እልም ብሎ ጠፍቷል በአይባልም ወይንም ባሕላዊው የመንግሥት ትርክት በአለበት የአለባቸው ወይንም ቀላል የእማይባል የባሕላዊ መንግሥት አስተሳሰብ ቅሪትን በመንግሥት ስሪታቸው ውስጥ ፤ በተለያየ መንገድ የእሚያንጸባሩቁ መንግሥታት ዛሬም መኖራቸው እሙን ቢሆንም ፤ በመንግሥት ብቻ ሰአይሆን በሌላውም ዘርፍ የሳይንስ የበላይነት የናኘበት ዘመን ላይ ስለ እምንኖር እና አብዛኛው ዓለም ይተግብረውም አይተግብረውም ፤ ሳይንሳዊውን የመንግሥት አስተሳሰብ ከሞላ ጎደል እንደ ትክክለኛ ስለ እሚቀበለው ፤ ከ15ኛው ምዕተ ዓመት በኋላ የአለውን ዘመን የሳይንሳዊው መንግሥታዊ ትርክት ዘመን ልንለው እንችላለን።

በአጭሩ መንግሥታዊ ትርክቶች ፦

  1. ባሕላዊ እና
  2. ሳይንሳዊ

በእሚል ኹለት ዋነኛ ጎራዎች ይከፈላሉ ።

በመላው ዓለም ፤ ከ15ኛው ምዕተ ዓመት አስቀድመው ፤ በተለይ ከ5ኛው ምዕተ ዓመት በፊት ለነበሩት አብዛኛዎቹ መንግሥታት ፤ ከባሕላዊ መንግሥታዊ ጎራ የእሚመደበው ዋነኛ መንግሥታዊ ትርክታቸው ፤ መለኮታዊ ምንጭ አለው የእሚባል እና ነገሥታቱ ወይንም ነጋሢዎቹ ዓማልክት ናቸው ወይንም የዓማልክት ዝርያ አላቸው የእሚል ንግርት ነበር ። ከእዚኽ ባሕሪያቸው ተነስተን በእዚኽ ዓይነቱ ትርክት መንግሥታቸውን የእሚመሰርቱትን ወይንም ይኽንን ትርክት በአንድ የታሪክ አጋጣሚ የመሠረቱትን መንግሥት ለማስቀጠል የእሚጠቀሙበትን መንግሥታት ፤ ዓምልካዊያን መንግሥታት ብለን ልእንሰይማቸው እንችላለን ።

እነ እዚኽ ፥ ዓምላካዊያን የተባሉት መንግሥታት ፤ ራሳቸውን የዓማልክት ዘር ወይንም ዓማልክት እንደ ሆኑ ትንግርታዊ ንግርት የእሚያስነግሩና ፤ ዓምላክ ወይንም የዓምላክ ዝርያዎች በመኾናቸውም ፤ ሕዝቡ የእነርሱ ተፈጥሮዋዊ ገባር እና ተገዢ እንደ ሆነ በማስቀመጥ የእሚገዙ መንግሥታት ናቸው ።

በእዚኽም ምክንያት ፦ የእነ እዚኽ ዓማልክታዊ መንግሥታት ተቀባይነት (legality) የእሚመነጨው ፤ ነጋሢዎቹ በእሚገዙዋቸው ሕዝብ ልማዳዊ የአምልኮ ባሕል መሠረት ፤ ዓምላክ ወይንም የአንዱ ዓምላክ ልጅ ወይንም በዘር ግንዱ ውስጥ የተካተቱ ናቸው ብሎ ልማዳዊው ወይንም ባሕላዊው አምልኮ የእሚያስተምር በመሆኑ ነው።

ሕዝቡም ከነበረበት የእውቀት ማነስ በመነሳት ፤ በደል ሲያንገሸግሸው ይዓምፅ ይሆናል እንጂ ፤ ነገሥታቱ ዓማልክት እና የዓማልክት ዘር መሆናቸውን እና ከእዚኽም የተነሳ ፤ እርሱ ገባር እነርሱ ነገሥታት መሆን እንደ አለባቸው የእሚለውን የእዚኽን ትርክት ይዘት ተጠራጥሮ ወይንም ጉዳዩ ጥያቄ ፈጥሮበት ሲከራከር አይታይም ። ይኽ እንግዲኽ ከግብፅ እስከ ህንድ በኋላም በግሪክ እና በሮም ፤ ከ 3 - 4 ሺ ዓመታት ፤ የዓለም ቀዳሚ እና ኃያል የፖለቲካ ፍልስፍና እና የመንግሥት መመሥረቻ መርህ ነበር ።

እነ እዚኽ መለኮታዊ መንግሥታት ፤ ዓምላክ ነኝ ወይንም የዓምላክ ዘር ነኝ የእሚለው የመንግሥታቸው ፍልስፍና ፤ ለእዚኽ ዘመን ሰው ጆሮ የእሚኮረኩር ቢሆንም ፤ እነ እዚኽ መንግሥታት በእዚኽ ትርክት እየተመሩ ስልጣን ይዘው ወይንም ስልጣናቸውን አስቀጥለው ፥ ብዙ በደል ቢፈፅሙም ፤ ዘመናዊው ወይንም ዳግማዊው ስልጣኔ እስኪ መጣ ድረስ ፦ ትላልቅ ጥንታዊ ስልጣኔ ያስጀመሩ ፣ ያስቀጠሉ እና ለዳግማዊ ስልጣኔ መምጣት ቅድመ ኹኔታ ያዘጋጁ መንግሥታት ናቸው ።

ምንም እንኳን ፤ አንዳንዶቹ ወይንም አብዛኛዎቹ ፤ በእነ እዚኽ ነገሥታት ወይንም መንግሥታት የተፈፀሙት በደሎች እጅግ ጭካኔ የተሞላባቸው እና በእነ እዚኽ መንግሥታት ስር የእሚኖረው አብዛኛው ሕዝብ ፤ የመንግሥታቸው ጥንካሬ እና አቅም ሲጨምር በተመሳሳይ የአብዛኛው መደበኛ ሕዝብ ሰቆቃ አብሮ የእሚጨምርበት አጋጣሚ ጥቂት በአይሆንም ፤ በመንግሥት ግንባታ እና በአጠቃላይ በሰው ልጅ ስልጣኔ እድገት ላይ የተጫወቱት ሚና ቀላል አልነበረም ።

ጥንታዊቷ ግብፅ ለ3 ሺ ዓመታት ሳይቋረጥ የዓለም የስልጣኔ ጉልላት ሆና የቆየችው እና እስከ ዛሬ ድረስ የቱሪስት መስህብ የሆኑ ድንቅ ሥራዎችን የከወነችው እና በዝንጀሮዎች ወይን እና ፍራፍሬ የማስለቀም ሥራ ትሰራ እንደ ነበር የእሚነገርላት ግብፅ ፤ ራሳቸውን ዓምላክ ነን በእሚሉ ፈርዖኖች እየተመራች ነው ።

የእዛኔውን ዓለም በሰላሳ ሺ ጦር ብቻ ፤ በብልሀት እና በጀግንነት ገዝቶ እና ለመጀመሪያ ግዜ ውቂያኖስ ተሻጋሪ ግዛት (International Empire) መሥርቶ ሔለናይዝድ[5] የአደረገው የግሪኩ ፦ ታላቁ አሌክሳንደር ፤ ሔርኩለስ የእሚባለው የግሪኮች ዓምላክ የልጅ ልጅ ነኝ እያለ ነው ፤ ይኽን ድንቅ ታሪክ የከወነው ። በዓለም ላይ የአስተዳደር ጥበብን እና የኪነ-ህንፃን ትልቅ ቦታ ያደረሱት ሮማውያኖች ፤ እነ ቄሳር እና ኔሮን ፤ እንደ ዓምላክ እያመለኩ ነው ያንን አስገራሚ ስልጣኔ የመሩት ።

የእነ እዚኽን ዓምላካዊያን መንግሥታት የተመሠረቱበት ንግርታቸው ወይንም የተነገረላቸው የነጋሢነት ንግርት በተራው እና በመደበኛው ሰውም ብቻ ሰአይሆን በዘመናቸው እውቅ በሆኑ ሙህራን እንኳን ተቀባይነት የነበረው ነው ። ለምሳሌ ፦ የቀድሞውን ዓለም ታላላቅ ሰዎች ግለ ታሪክ የጻፈው እና የታሪክ እውቀቱ እና የአጻጻፍ ችሎታው በመጽሐፉ ውስጥ በግልጽ የእሚታይለት ፕሉታርክ ፤ ስለ ታላቁ አሌክሳንደር ሲጽፍ ፥ አሌክሳንደር የኼርኩለስ ልጅ እንደሆነ የተረጋገጠ ነው ይላል ፦

“ዓላማዬ የንጉሥ አሌክሳንደርን እና… ህይወት መጻፍ በመሆኑ ፤ የእነ እዚኽ ሰዎች ገድል እጅግ ብዙ በመሆኑ ፤ ዝርዝሩን በመተው እጅግ ጉልህ የሆኑት የህይወት ታሪኮቻቸው ላይ ብቻ እንደ እማተኮር አንባቢዎቼን አስቀድሜ ካለ አስጠነከሁ ተወቃሽ እሆናለው ። ልብ ሊባል የእሚገባው ዓላማዬ ዜና መዋዕል መጻፍ ሳይሆን የሰዎቹን ህይወት መጻፍ ነው ። ከእዚኽም የተነሳ ፤ ትልቅ የእሚባሉት ጀብዶች በሙሉ ስለ ጀብደኛው መልካም ወይንም ክፉ ጠባይ ለአይነግሩን ይችላሉ ፤ አንዳንድ ግዜ ፥ ስሜት የእሚገለፅባቸው ወይንም ቀልድ የእሚቀለድባቸው ገጠመኞች ፤ ጀግኖች ከተሳተፉበት ትልቅ ከበባ ፣ ከታጠቁአቸው መሳሪያ ወይንም ከአካኼዱአቸው ጦርነቶች በላይ ስለ ሰዎቹ ባሕሪ እና ዝንባሌ የበለጠ ሊነግሩን ይችላሉ ።…

ኹሉም እንደ እሚስማማበት ፥ አሌክሳንደር በአባቱ ወገን ክራነስ ከእሚባለው ወላጁ የኼርኩለስ ዘር ግንድ አለው ፤ በእናቱ በኩል ደግሞ ኒዮቶሌመስ በእሚባለው ወላጇ ከአኪየስ የእሚመጣ የዘር ግንድ አለው ።”

“It being my purpose to write the lives of Alexander the king, and of … the multitude of their great actions affords so large a field that I were to blame if I should not by way of apology forewarn my reader that I have chosen rather to epitomize the most celebrated parts of their story, than to insist at large on every particular circumstance of it. It must be borne in mind that my design is not to write histories, but lives. And the most glorious exploits do not always furnish us with the clearest discoveries of virtue or vice in men; sometimes a matter of less moment, an expression or a jest, informs us better of their characters and inclinations, than the most famous sieges, the greatest armaments, or the bloodiest battles whatsoever…It is agreed on by all hands, that on the father's side, Alexander descended from Hercules by Caranus, and from Aeacus by Neoptolemus on the mother's side. [77]“

በእዚኽ የፕሉታርክ ታሪክ ላይ የተቀመጡት ኼርኩለስ እና ኤኪየስ የእሚባሉት ሰዎች ሳይሆኑ በግሪክ የዓማልክት ሰንሰለት ውስጥ የአሉ፟ ዓማልክት ናቸው ።

በሌላ ማሳያም ፤ ሔርኩለስ እና ኤክየስ ከእሚባሉት ዓማልክት ተወልጃለኹ የእሚለውን አሌክሳንደር አሰልጥኖ ፤ ለእዚኽ ታላቅ ታሪካዊ ጀብድ የአበቃው ፤ የፍልስፍና አባት ከእሚባሉት ቀዳሚ የሆነው አርስታትል ነው ።

ረጅሙን የሰው ልጅ ታሪክ በበላይነት ተቆጣጥረው የነበሩት እነ እዚኽ ዓምላካዊያን የአልናቸው መንግሥታት ፤ ከተነሳንበት ዜጎችን የማሕበራዊ አህድነት ከመቀበል አንጻር ስንመለከተቻው ፤ ዜጎች የማሕበራዊ አህድ ናቸው የእሚለው ፤ የማሕበረ ሳይንስ እውቀት ራሱ አዲስ የማሕበረሰብ ሳይንስ አንኳር አድርጎ ያመጣው ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ከ15ኛው ምዕተ ዓመት በኋላ የተከሰተው የዘመነ ሳይንስ በመሆኑ ፤ ከመንግሥታዊ ትርክታቸው ግብታዊነት እና በባሕላዊ ትርክት ላይ ከመመሥረት በአሻገር ፤ ለኃሳቡም ባይተዋር ናቸው።

ለኃሳቡ ባይተዋር ቢሆኑም ቅሉ ፤ የመንግሥታዊ ትርክታቸው በዋናነት ፤ የተወሰኑ ዓምላክ የሆኑ ወይንም ዓምላካዊ ዝርያ የአላቸው አሉና መንገሥ የአለባቸው እነርሱ ብቻ ነው በእሚል ላይ በወጥነት የተመሠረተ በመሆኑ ፤ የዜጎችን የማሕበረሰብ አህድነት ኃሳብን በፍጹም ተጻራሪ የሆነ መንግሥታዊ ትርክት እንደ አላቸው ግልጽ ነው።

ይኽ የዓምላካዊያኑ ፖለቲካ ግን ፤ በክርስትና መንፈሳዊ እና ሰብዓዊ የወንድማማችነት መልዕክት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ፤ ዓምላክ ወይንም የዓምላክ ዘር ነኝ እና መንግሥቴን ሳትጠይቁ ዝም ብላችሁ ተገዙ የእሚለው ትርክታቸው ንቃቱ እየዳበረ በመጣው ማሕበረሰብ ተቀባይነቱ እየደከመ መጣ ።

በኋላም በክርስትና ሰብዓዊ መልዕክት ምክንያት የተጀመረው የአውሮፓዊያን ሕዳሴ በፈጠረው የእውቀት አብዮት ፤ ስነ መንግሥት ሚስጥረ ሙዳይ እና በጥቂት መንፈሳዊ መሪዎች የእሚታወቅ ከመሆን ወጥቶ የምድራዊው የፍልስፍና እና የሳይንስ መስክ የጥናት አጀንዳ በመሆን ፤ በጉዳዩ ላይ ፍላጎት የአለው ኹሉ የእሚወያይበት እና ኃሳብ የእሚሰነዝርበት ሆነ ።

በእርግጥ ፤ ከአውሮፓ ህዳሴ አስቀድሞ ፤ በምዕራብ የግሪኮቹ ፕሌቶ እና አርስታትል ስለ መንግሥት በስፋት ያጠኑ እና የጻፉ ፤ እንዲሁም በምሥራቅ የቻይናው ኮንፊሸስ መንግሥታዊ ፍልስፍናን የተመለከቱ የተለያዩ ብኺሎች የአሉት ቢሆንም ፤ የስነ መንግሥት ጥናት እና ምርምር ኃይማኖታዊ ይዘት ከአላቸው ንግርትነት ውጭ እና በአሻገር ፤ ከአውሮፓ ህዳሴ አንስቶ ነው ፤ ሰፊ ማሕበራዊ መሠረት የአለው የምድራዊ ሳይንስ የጥናት እና የእውቀት መስክ በኋላ ላይም የተለያዩ የእሚታወቁ ራስቻይ (Self-Contained) መንግሥታዊ ርዕዮቶች(Ideologies) ወደ መሆን ያደገው።

እንግዲህ ከአውሮፓ ህዳሴ ማግስት አንስቶ ፤ የስነ መንግሥት ጉዳይ ፤ ከሚስጥረ ሙዳይነት ወደ ሕዝብ የእውቀት መስክነት ከመጣ በኋላ ፤ መለኮታዊ ሹመት ከእሚል የስነመለኮት ትንታኔ ወይንም አስተምህሮ አንስቶ የጥንቱን የግሪኩን ዴሞክራሲ አቧራውን አራግፎ ፤ በዘመኑ እውቀት አሻሽሎ እና ከዘመኑ ኹኔታ ጋር አዋዶ እስከ መጠቀም የእሚደርስ ፤ ፈርጀ ብዙ ሳይንሳዊ በአልነው ጎራ የእሚመደቡ መንግሥታዊ ትርክቶች ተፈጥረዋል ።

የባህላዊ ኃይማኖት መሠረት የአለውን የዓምላካዊያኑን የመንግሥት መመሥረቻ ትርክት ሳይንሳዊነት ከተካው በኋላ ፤ ሳይንስ ያስተዋወቃቸውን የመንግሥት መመሥረቻ ትርክቶች ወይንም ሳይንሳዊ የመንግሥት ትርክቶችን በዋናነት በአምስት መክፈል ይቻላል ፤ እነርሱም ፦

  1. ስነመለኮታዊያን
  2. አምባገነናዊ ማሕበራዊ ውል
  3. የሠራተኛው አምባገነናዊነት
  4. ልማታዊ መንግሥት
  5. ዴሞክራሲያዊ ማሕበራዊ ውል

ስነ-መለኮታዊኑ ምንም እንኳን እንደ ዓምላካዊያኑ ኹሉ ሐይማኖተኛ ቢሆኑም ፤ ፍልስፍናቸው ፥ ለብዙ መቶ ዓመታት ፤ የተገለጠ የእግዚአብሔር ፍፁም ፈቃድ ተብሎ በእሚታመንበት እና በስፋት በተጠና እንደ መፀሐፍ ቅዱስ በአለ መጽሐፍ ትርጓሜ እና ትንታኔ ላይ በመመሥረቱ ፤ ከሳይንሳዊያኑ ጋር አንድ ላይ ብናየው ተገቢ ነው ።

ከእዚያኽም በአሻገር ፤ ትንሽ ቀደም ብለን ለማየት እንደ ሞከርነው ፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊው የስነ-መለኮት ትምህርት ፤ ለቀሩት አራቱ የሳይንሳዊ መንግሥት ትርክቶች መነሻ ለሆነው ዘመናዊ የማሕበረሰባዊ ሳይንስ እውቀት መዳበር ከፍተኛ ሚና የአለው በመሆኑ ወይንም በአውሮፓ የነበሩ የስነመለኮት ትምህርት ቤቶች ፤ ለዘመናዊ ፍልስፋና እና ለፖለቲካ ሳይንስ የትምህርት መስክ መነሻ እና መፍለቂያ የነበሩ በመሆናቸው ፤ ስነመለኮትዊውን ትርክት ከሳይንሳዊያኑ ጋር ደርቦ መመልከቱ ተገቢ ይአደርገዋል ።

በእዚኽም መሠረት ፤ ከባሕላዊ የመንግሥት ትርክት በተቃራኒ በአሉት ሳይንሳዊ በአልኩዋቸው ጎራ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ፤ በአማኝ ሰባዊያን ጎራ የእሚካተቱ ስነ-መለኮታዊያን ሲሆኑ ፥ የእነ እዚኽ ስነ-መለኮታዊያን ፤ የመንግሥት ፍልስፍና ነገሥታት ዓማልክት ናቸው ወይንም የዓማልክት ዝርያ አለባቸው በአይልም ፤ ትክክለኛው የመንግሥት ስልጣን ፤ በተገለጠው የአምላክ ፈቃድ መሠረት ከእግዚአብሔር ሹመት መቀበል ነው ብለው የእሚያስተምሩ ናቸው ።

ለምሳሌ ፦ ከእነ እዚኽ ስነ-መለኮታዊያን ከአልኩዋቸው መካከል የእሚመደበው ፥ የእንግሊዙ ሮበርት ፊልመር ፤ ይኽ እግዚአብሔር የሾመውን ሰው ለማወቅ ፤ የመጀመሪያው ቤተሰብ (በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት) የተዋቀረበትን አግባብ ማየት ነው ።

እርሱ እንደ እሚለው ፦ አዳም የቤቱ ራስ ወይንም መሪ የነበረ በመሆኑ ፤ ለቤቱ ንጉሥ ነበር ። ከእርሱ በኋላም ፤ የልጅ ልጆቹ እየበዙ ሲኼዱ ፤ የኹሉም ወላጅ አባት በመሆኑ በዘር ማንዘሩ ላይ ንጉሥ ነበር ። በእየ አከባቢውም የአለ ንጉሥ ፤ እንደ ውልደት ቅደም ተከተሉ ፤ የመጀመሪያው ወይንም የበኩር ልጁ የበለጠ ለዙፋን የቀረበ በእሚሆንበት አግባብ የተከፋፈለ ነው ከአዳም ጀምሮ ።

ኖህ ከጥፋት ውኃ በኋላ ፤ የብቸኛው ቤተሰብ ስለ እዚኽም የዓለም ንጉሥ ስለ ነበረ ፤ የሜድትራኒያን ባሕር መካከል አድርጎ አውሮፓን ለሴም ፣ ኢስያን ለያፌት ፣ አፍሪካን ለካም ሰጥቷል ፤ ንጉሥ ስለ ሆነ ይላል ። በእነ እዚኽም አህጉራት የእነ እዚኽ ሦሥቱ አበዎች የልጅ ልጆች ፤ በውልደት ቅደም ተከተል ነግሰዋል ወይንም መንገሥ አለባቸው ።

የሮበርት ፊልመር የፖለቲካ ስልጣን ምንጭ ትንታኔ ፤ ከመጽሐፉ ርዕስ ጀምሮ የአባቶች ግዛት (Patriarcha) የእሚል ሆኖ ፤ ስልጣን ከአባቶች ወደ በኩር ልጅ ወይንም እንደ ኹኔታው በእዚኽ የውልደት ቅደም ተከተል የእሚኼድ ነው የእሚል በመሆን ፤ ይኽንንም የድምዳሜውን ትክክለኛነት (ሳይንሳዊነት) ለማስረገጥ ከመጽሐፍ ቅዱስም ከዓለማዊም ታሪክ የእሚያጣቅስ ነው ።

ከእዚኽም የተነሳ ፤ እንደ ሮበርት ፊልመር እና መሰሎቹ ትንታኔ ፤ መንግሥታት የተስፋፉ ቤተሰብ በመሆናቸው እና በመጽሐፍ ቅድሱ አስተምህሮ አባት የቤቱ ራስ ወይንም ንጉሥ በመሆኑ ፤ ንጉሥነት በታሪክ ኺደት የተስፋፋ አባትነት በመሆኑ ፤ ነገሥታት እና የልጅ ልጆቻቸው ብቻ እንደ ነገሡ መቀጠል አለባቸው ።

ይኽም በመሆኑ ፤ ልክ ልጅ አባቱን ወይንም ታናሽ ወንድም ታላቅ ወንድሙን መምረጥ እንደ እማይችለው ፤ ሕዝብ መሪውን ወይንም ንጉሡን መምረጥ የለበትም ፤ ከስነመለኮታዊያን ጋር በእሚመደበው የሮበርት ፊልመር መንግሥታዊ ትርክት መሠረት።

ሰዎች ግን ፤ ‘የአወቁ’ እየመሰላቸው ከእዚኽ ዓምላካዊ አሰራር ወጥተው ፤ መንግሥት በሕዝብ ምርጫ ይቋቋም ከአሉ ፤ በነፃነት ስም ጋጠወጥነት ያስፋፋሉ።

ሮበርት ፊልመር ፤ ይኽን ኃሳቡን እንደ እዚኽ ያስረዳዋል ፦

“ … እንዲኽ እያሉ አስረግጠው የእሚናገሩ ሌሎች የተማሩ [6]ሰዎች ፤

የሰው ልጅ በተፍጥሮ ከማንም ገዢነት ውጭ ነፃነትን ታጥቆ እና በነፃነት ነው የተወለደው ፤ ከእዚኽም የተነሳ የወደደውን ዓይነት መንግሥት የመምረጥ መብት አለው ፡ ከእዚኽም የተነሳ ማንም ባለ ስልጣን በሌሎች ላይ የአለውን ስልጣን መጀመሪያ የአገኘው ከሕዝብ መልካም ፈቃድ ነው ።

ይኽ አስተምህሮ መጀመሪያ የተፈለሰፈው በትምህርት ቤቶች ነው (The school of the scholastics በእኛ ሐገሩ አውድ በቄስ ትምህርት ቤቶች) ፤ ከእዚያኽም በኋላ በቀጣይነት ከመጡ የካቶሊክ ስነመለኮት ተማሪዎች ተስፋፍቷል ። የተኃድሶ ቤተክርስቲያኒቱ የስነ መለኮት ሊቆችም ይኽን ኃሳብ ያስተናግዱታል ፤ ለስጋና እና ደም ተስማሚ ነውና ፤ ተርታውም ሕዝብ በእየቦታው በስስት በጉያው ይዞታል ፤ እነ እዚኽ ስጋዊያን ይኽን ነፃነት እጅግ እያከበሩ ፤ ልክ የሰው ልጅ እርካታ ኹሉ ነፃነት ውስጥ የእሚገኝ አስመስለው ይዘውታል ፤ የአዳምም የመጀመሪያ ውድቀት የነፃነት ፍላጎት እንደነበረ ማስታወስ ተስኗቸው ።”

“...other learned men, which affirms,

Mankind is naturally endowed and born with Freedom from all subjection, and at liberty to chose what Form of Government it please : And that the Power which any one Man hath over others, was at first bestowed according to the discretion of the Multitude.

This tenet was first hatched in the Schools, and hath been fostered by all succeeding Papists for good Divinity. The Divines also of the Reformed Churches have entertained it, and the Common people every where tenderly embrace it, as being most plausabile to Flesh and blood, who magnifie Liberty, as if the height of human Felicity were only to be found in it, never remembering That the desire of Liberty was the first Cause of the Fall of Adam. [78]“

ምን አልባት ከእዚኽ በላይ የተቀመጠውን የሮበርት ፊልመር የነፃነት ተቃውሞ ለመረዳት ትንሽ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ይፈልግ ይሆናል ፤ ጭብጡ ግን ፦ የመጽሐፍ ቅዱሱ አዳም ውድቀት ወይንም ከኤደን ገነት ለመባረሩ ምክንያቱ ፤ ከእግዚአብሔር አገዛዝ ራሱን ለማላቀቅ እና ነፃ መሆን መፈለጉ ነው ። ይኽ የነፃነት ፍላጎት ደግሞ ስጋዊ/ምድራዊ እንጂ መንፈሳዊ ስለ አልሆነ ፤ ደስታ የእሚሰጥ ቢመስልም መጨረሻው ግን ውድቀት ነው ።

ስለ እዚኽ ፦ እግዚአብሔር ከደነገገው አባቶች ወይንም የእነርሱ በአምላካዊ ድንጋጌ የመጣ በውልደት ቅደም ተከተል የአገኙትን ነጋሢነት ወይንም ወራሽ ንጉሥ የእሚኾኑበትን አግባብ ሕዝብ ተቃውሞ ፤ ነፃ ሰዎችን ነን እና መንግሥት በእኛ ምርጫ ይቋቋም ሲል ፤ አዳምን የጣለው ተመሳሳይ ሐጥያታዊ ‘የነፃነት’ ምኞት እየተመኘ ነው የእሚል ነው ።

ፊልመር ቀጠል አድርጎም ፤ ይኽ ዓይነቱ መሪውን ሕዝብ መምረጥ አለበት የእሚለው ስሁት አባባል በመጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምሮ የተወገዘም ብቻ ሰአይሆን (እንደ እርሱ መጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም) ፤ ከእኛ ቀደም የነበሩ ጥንታዊ ስልጣኔዎች ልምድም የእማይደግፉት በመሆኑ ፤ ልምድም የአረጋገጠው ይመስላል ይላል ፦

“… ይኽ ዓይነቱ ልማድ በጥንታዊ አባቶች እና የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ዘንድ አይገኝም ፡ ከቅዱስ ቃሉ ቆኖና እና ታሪክ ጋርም ፤ እንዲሁም ከእራሱ ከተፈጥሮ ሕግም ጋር ይጋጫል ። ይኽ ጉዳይ ፤ ከእዚኽም የተነሳ በስነ-መሎከታዊ ትንታኔ ወይንስ በምድራዊ ፖሊሲ ጉዳይ የበለጠ የከፋው ለማለት እንኳን ያስቸግራል ።”

“...yet it is not to be found in the Ancient Fathers and Doctors of the Primitive Church: It contradicts the Doctrine and the history of the Holy Scriptures, the Constant Practice of all Ancient Monarchies, and the very principles of the Law of Nature. It is hard to say whether it be more erroneous in Divinity, or dangerous in Policy. [78]“

ፊልመር ከተፈጥሮም ሕግ ይቃረናል የእሚለው ፤ በእዚኽ መጽሐፍ ምዕራፍ አንድ ላይ ፤ በነፃነት ዴሞክራሲ የተብራራውን የነፃነት ሕግ ሰአይሆን ፤ ሕዝብ እንደ ሕዝብ መረን ነው የእሚለውን ልማዳዊ እና በአብዛኛው ከእርሱ ቀደም የነበሩ ምሁራን የሕዝብን ባሕሪ የእሚገልፁበትን ኹኔታ ነው ። እርሱንም እንደ እዚኽ ያስቀምጠዋል ፦

“ጥንታዊ ሕዝባዊ መንግሥታት የእሚባሉት ውስጥ ወይንም በአቅራቢያቸው ከኖሩት ፤ ቲውሲድደስ ፣ ዜነፎን ፣ ሊቪ ፣ ሲሴሮ አና ሳልሱትን በመሰሉት ጸኃፍት ከተገለፁት በላይ ፤ የሕዝብን ባሕሪ በተሻለ ኹኔታ እንዴት ልገልፀው እንደ እምችል አላውቅም ። ስለ እዚኽ ፦ የእነርሱን አንዳንድ ዓረፍተ ነገሮች እዋሳለሁ ።

ከሕዝብ በላይ የእማያስተማምን ምንም ነገር የለም ፤ ኃሳባቸው እንደ ማዕበል ድንገተኛ እና ተለዋዋጭ ነው ፤ እውነት ወይንም ፍርድ የእሚባለው ነገር እነርሱ ጋር የለም ፤ ምንንም ነገር በጥበብ ተመርተው አይደለም የእሚፈርዱት ነገር ግን በአመፅ እና በችኮላ ነው ወይንም እውነት እና ውሸት የእሚባል ክፍፍል አያውቁም ። ልክ እንደ ከብት መንጋ ፤ ከፊታቸው ቀድሞ የኼደውን ነው የእሚከተሉት ፤ ክፉውን እና ደካማውን ነገር የማሞገስ ችግር አለባቸው ፤ ተባለ የእሚባል ነገር ይስባቸዋል ፤ በእዚኽም በማንኛውም የውሸት ክስ ሰው ለመወንጀል እና ለመፍረድ ፈጣን ናቸው ፤ ኹሉንም ዜና ለማመን ቅርብ ናቸው ፤ በተለይ ደግሞ አሳዛኝ ከሆነ ፤ ዝናም በጣም ይወድዳሉ ፤ በተለይ ደግሞ ምንጩ የእማይታወቅ ወሬ ከሰሙ ለማመን በጣም ይቀላቸዋል ፤ ከእዚያኽም የራሳቸው መቀባጠር የፈጠረውን ክፋት ይፈሩታል ፤ ኹል ግዜ ነውጥ እና አዲስ ለውጥ በጉግት ይፈልጋሉ ፤ የፀጥታ እና የርጋታ ጠላት ናቸው ፤ እምቢተኛ እና እቡዩን ኹሉ ነገር ወንዳ ወንድ እና ደፋር ብለው ይቆጥሩታል ፤ መጠነኛውን እና አርቆ አሳቢውን ቀርፋፋ ይሉታል ፤ እያንዳንዱ የራሱን ብቻ ነው የእሚያስበው ፤ የጋራ መልካም ግብን ዝቅ አድርጎ ነው የእሚመለከተው ፤ ሸፍጥ እየቀረበ ሲመጣ ልክ እንደ ነጎድጓድ ነው የእሚያዩት ፤ ኹሉም እኔን ብቻ አይንካኝ እንጂ ይላሉ ፤ ይኼ ተፈጥሮዋቸው ነው ፥ ወይ እንደ ባሪያ ዝቅ ብለው መገዛት አለባቸው ወይንም በትምክህት መግዛት አለባቸው ፤ አማካይ የእሚባል ነገር አያውቁም ። እነዚያኽ ጥንታዊ ጸኃፍት ባለ ብዙ ጭንቅላቱን ይኽን አውሬ እንደ እዚኽ አድርገው ነው የሳሉት ። መንግሥታቸው ደግሞ ምን እንደ እሚመስል ልተርክላችሁ። በሴራ ስለ እሚጀመር ፤ የእሚቀጥለው በጦር ብርታት ነው ፤ ያለ ጦርነት መቆም አይችልም ፤ በሩቅ ከአለ ጠላት ይኹን በሐገር ውስጥ ከአለ ወዳጅ ጋር ፤ ብቻ ጦርነት መኖር አለበት ። ብቸኛው መንግሥታቸውን የእሚያቆየው ነገር ፤ በቅርብ አንድ ኃይለኛ ጠላት መኖሩ ነው ፤ በንጉሥ ፈንታ የእሚገዛቸው እርሱ ነው ፤ ንጉሥ በመካከላቸው በአይኖራቸውም ፤ የንጉሡን ሥራ የእሚሰራ አንድ ነገር ያስፈልጋል ፤ ምክንያቱም ፦ የጋራ ጠላታቸው የእሚደቅንባቸው አደጋ ራሳቸው ከእሚያወጡት ሕግ ይልቅ በአንድነት ያቆማቸዋል ።”

“I know not how to give a better Character of the people, than can be gathered from such Authors as lived amongst or near the Popular States; Thucydides, Xenophon, Livy, Tacitus, Cicero, and Salsut, have set them out in their Colours. I will borrow some of their Sentences.

There is nothing more uncertain than the People; their Opinion are as variable and sudden as Tempests; there is neither Truth nor Judgment in them; they are not led by Wisdom to judg of any thing, but by Violence and Rashness; nor put they any Difference between things True and False. After rhe manner of Cattle, they follow the herd that goes before; they have a Custom to always favor the Worst and Weakest; they are most prone to Suppositions, and use to Condemn men for Guilty upon any false Suggestion; they are apt to believe all News, especially if it be sorrowful; and like Fame, they make it more in the Believing; when there is no Author, they fear those Evils which themselves have feigned, they are most desirous of New Stirrs and Changes, and are Enemies of to Quiet and Rest; Whatsoever is Giddy or Head-strong, they account Man-like and Courageous; but whatsoever is Modest or Provident, seems sluggish; each Man hath a care of his Particular, and thinks basely of the Common Good; they look upon Approaching Mischiefs as they do upon Thunder, only every Man wisheth it may not touch his own Person; it is the Nature of them, they must Serve basely, or Domineer proudly; for they know no Mean. Thus do they paint to the Life this Beast with many Heads. Let me give you the Cypher of their Form of Government; As it is begot by Sedition, so it is nourished by Arms: It can never stand without Wars, either with an Enemy abroad, or with Friends at Home. The only Means to preserve it, is, to have some powerful Enemies near, who may serve instead of a King to Govern it, that so, though they have not a King amongst them, yet they may have as good as a King Over them: For the Common Danger of an Enemy keeps them in better Unity, than the Laws they make themselves. [78]“

ሮበርት ፊልመር ስለ ሕዝባዊ መንግሥት ያቀረበውን ገለፃ ስንመለከት ፤ ሮበርት ፊልመር እንደ ፕሌቶ በሕዝባዊ ወይንም ዴሞክራሲያዊ መንግሥት እና በመንጋ መካከል የአለውን ልዩነት የመለየት ችግር እንደ አለበት እና ዴሞክራሲን ከመንጋ አስተሳሰብ ጋር እንደ አምታታው ግልፅ ነው ። ስለ እዚኽ አንባቢው የነጻነቱን ዴሞክራሲ ከመንጋ መሰል ሕዝባዊ እንቅስቃሴ የእሚለይበትን አግባብ መረዳት ይጠበቅበታል ።

በሮበርት ፊልመር ማሳያነት የቀረበው ይኽ የስነመሎኮታዊ የስነ መንግሥት ፍልስፍና ጭብጡ ከኢትዮጲያው ክብረነገሥት ጋር ብዙ የእሚያመሳስለው ነገር አለው። ለምሳሌ ፦ ክብረ ነገሥትን ወደ እንግሊዘኛ የተረጎመው የእንግሊዙ የታሪክ ተመራመሪ ሰር ዋሊስ ባጅ (Sir Wallis A. Budge) ፤ በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ኢትዮጲያ ውስጥ የእሚነገር አፈታሪክ ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የንጉሥ ሰለሞን የልጅ ልጆች ለምን መንገሥ እንደ አለባቸው የእሚያስረዳበት ምክንያት ፤ የክብረነገሥቱን መንፈስ ያንጸባርቃል በእሚል ያስቀመጠውን አፈታሪክ እንደ ማሳያ እንመልከት ፦

“በኢትዮጵያ ውስጥ የእሚገኝ አንድ ገድል ላይ ፤ እግዚአብሔር አዳምን ሲፈጥር በሰውነቱ ውስጥ “እንቁ” እንደ አስቀመጠ እና ይኽንም “እንቁ” ወደ ተመረጡት ቅዱስ ሰዎች ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ እንዲኼድ እንደ አደረገ ይላል ። ይኽም ‘እንቁ’ ከንጉሥ ሰለሞን በንግሥት ሳባ አማካኝነት ፤ ወደ ሰለሞን ልጅ ወደ ሆነው እና ከንግሥት ሳባ ወደ ተወለደው ምንሊክ ተሸጋግሯል … ኢትዮጵያዊ ይስኃቅ[7]ም ይኽንን እምነት ይዞ ፤ በክብረ ነገሥት ውስጥ ፤ ከቀዳማዊ ምንሊክ የተወለዱት የኢትዮጲያ ነገሥታት መለኮታዊ ምንጭ አላቸው ብሎ ያስቀምጣል።”

“There is extant in Ethiopian literature a legend to the effect that when God made Adam He placed in his body a “Pearl,” which He intended should pass from it into the bodies of a series of holy men, one after the other, … Now this “Pearl” passed through the body of Solomon by the Queen of Sheba, were sons of Solomon, an ancestor of … and Menyelek, the son of Solomon by the Queen of Sheba, …,. And Isaac the Ethiopian, holding this view, maintains in the Kebra Nagast that the kings of Ethiopia who were descended from Menyelek were of divine orgin, …. [79]“

ስለ እዚኽ ፦ በፊልመር እና መሰሎቹ (የእኛ ሐገሩን ክብረ ነገሥት ጨምሮ) የስነመለኮት አስተምህሮ ፤ ንግሥና እንደ ተስፋፋ አባትነት ወይንም በመሰል መንፈሳዊ መመዘኛ የእሚመጣ በመሆኑ ፤ ተገቢው ስልጣን በእዚኽ መልኩ የተላለፈ ስልጣን ነው ፤ ለእዚኽም እምነታቸው ማስረጃነት መጽሐፍ ቅዱስን እና ሌሎች መጽሐፍትን በማስረጃነት ይጠቅሳሉ።

ለስነ መለኮታዊያኑ ፤ ስልጣን የሕዝብ ነው ወይንም ሕዝብ የመረጠውን መሪ መሾም ይችላል የእሚለውን አስተሳሰብ የእሚያራምዱ ፤ የኃይማኖት ሰዎችም ሆኑ ዓለማዊ ተመራማሪዎች ፤ ለመንፈሳዊውም ፣ ለተፈጥሮ (ከላይ በተቀመጠው አግባብ) እና ለታሪክ ምስክርነት ልባቸውን የዘጉ ሰዎች ናቸው ።

በእዚኽም መሠረት ለስነ መለኮታዊያኑ ፤ ፖለቲካዊ ስልጣን ለተወሰኑ ሰዎች በአምላክ የተሰጠና እና በተዋረድ የእሚተላለፍ አንዳቸ ዓይነት መንፈሳዊ ውርስ ነው !

ግለሰቦች የማሕበራዊ አህድ መሆናቸውን ከመቀበል አንጻር ፤ ስነ መለኮታዊያኑን ስንመዝናቸው በጉዳዩ ላይ የአላቸው አቋም ፤ በዋናነት ዜጎችን ተፈጥሮዋዊ የማሕበረሰብ አህድ ናችሁና ፤ ተፈጥሮዋዊ ነጻነታቸሁ ሊከበር እና መንግሥትም በእናንተ ይኹንታ በምርጫችሁ የእሚመሠረት መሆን አለበት ብሎ ማለት ፤ በነጻነት ስም የእሚደረግ ዋልጌነት እና አላዋቂነት ነው ብለው የእሚሞግቱ ሆነው እናገኛቸዋለን።

በስነመለኮታዊው የመንግሥት ትርክት አቀንቃኝነት መድበን የአየነው ሮበርት ፊልመርም ፤ ነጉስነት የተስፋፋ እና ተወራራሽ አባትነት ነው ብሎ ፤ ስነ መሎኮታዊ እና ሳይንሳዊ ሙግት የጀመረው ፤ ይኽንን የሰዎችን ተፈጥሮ እኩል ነጻነት የመንግሥት መመሥረቻ የማድረግን መርህ በመቃወም ነው ፦

“የሰው ልጅ በተፍጥሮ ከማንም ገዢነት ውጭ ነፃነትን ታጥቆ እና በነፃነት ነው የተወለደው ፤ ከእዚኽም የተነሳ የወደደውን ዓይነት መንግሥት የመምረጥ መብት አለው ፡ ከእዚኽም የተነሳ ማንም ባለ ስልጣን በሌሎች ላይ የአለውን ስልጣን መጀመሪያ የአገኘው ከሕዝብ መልካም ፈቃድ ነው ።

…የተኃድሶ ቤተክርስቲያኒቱ የስነ መለኮት ሊቆችም ይኽን ኃሳብ ያስተናግዱታል ፤ ለስጋና እና ደም ተስማሚ ነውና ፤ ተርታውም ሕዝብ በእየቦታው በስስት በጉያው ይዞታል ፤ እነ እዚኽ ስጋዊያን ይኽን ነፃነት እጅግ እያከበሩ ፤ ልክ የሰው ልጅ እርካታ ኹሉ ነፃነት ውስጥ የእሚገኝ አስመስለው ይዘውታል ፤ የአዳምም የመጀመሪያ ውድቀት የነፃነት ፍላጎት እንደነበረ ማስታወስ ተስኗቸው።“

“Mankind is naturally endowed and born with Freedom from all subjection, and at liberty to chose what Form of Government it please: And that the Power which any one Man hath over others, was at first bestowed according to the discretion of the Multitude.

… The Divines also of the Reformed Churches have entertained it, and the Common people every where tenderly embrace it, as being most plausabile to Flesh and blood, who magnifie Liberty, as if the height of human Felicity were only to be found in it, never remembering That the desire of Liberty was the first Cause of the Fall of Adam. [78]“

ሮበርት ፊልመር ፤ ይኽንን ኃሳብ ፥ መለኮታዊ የሆነው የአምላክን የአባትነት ተፈጥሮዋዊ ድንጋጌ የእሚፃረር እና በመንግሥታዊ ጉዳይ ላይ በቂ እውቀት ስለ ሌለው ስሜቱን በመከተል በቀላሉ ሊታለል የእሚችለውን ሕዝብ ፤ ነፃ ነኽ እና የእሚመስልኽን ሰው የመንግሥት ስልጣን እንዲይዝ መምረጥ ትችላለህ ማለት ፤ ሕዝብን መረን በማስወጣት ስረዓት አልበኝነትን እንዲ ነግስ የእሚያደርግ አስተሳሰብ በመሆኑ ፤ የሰዎች ተፈጥሮዋዊ የነጻነት እኩልነት የመንግሥት መመሥረቻ መርሕ መሆን የለበትም ብሎ ተቃውሞታል ።

ይኽም ብቻ ሰአይሆን ፤ እንደ ሮበርት ፊልመር ፤ አንድ ተራ አንጥረኛውን ሥራህን በአግባቡ መሥራት ትችላለህ ብለን እየ አመንነው ፤ እንዴት ብዙ እውቀት እና ትምህርት የእሚጠይቀውን የመንግሥት ሥራ የእሚሰሩትን ሰዎች ፤ ሥራችሁን መቆጣጠር አለብን ማለት እንችላለን ፤ ይልቁንም የእሚያዙንን እየሰማን መታዘዝ ነው ያለብን እንጂ ብሏል ፦

“አንድ ተራ የእሚባል አንጥረኛ በውስጠ ታዋቂነትም ቢሆን በሞያው ይታመናል ፤ ታዲያ እንዴት አንድ ልዑል እጅግ ጥልቅ በሆነው ፥ የተግባራቱ እና የእንቅስቃሴዎቹ መነሻ እና መጨረሻቸው የመደበኛውን ሰው ዓይን በእሚያጨናብሩበት እና ሕዝብን የማስተዳደሩ ጉዳይ ፤ በጉዳዩ ላይ በጥንቃቄ ከተማሩት ሰዎች በስተቀር ከመደበኛው ሰው ችሎታ በላይ የሆነበትን የመንግሥት ምስጢር ላይ አይታመንም ...”

“An implicit faith is given to the meanest artificier in his own craft, how much more is it then due to a prince in the profound secrets of government, the causes and ends of the greatest politique actions and motions of state dazle the eyes, and exceed the capacities of all men, save only those that are hourly versed in the managing public affairs... [78]“

ጉዳዩ ግን ውስብስብ የሆነውን የመንግሥትን ሥራ የእሚሰሩትን ሰዎች የአለማመን እና እያንዳንዱ ሥራችሁን እንቆጣጠር የማለት እና የአለማለት ሰአይሆን ፤ ይኽንን ኃላፊነት ለመወጣት ወይንም ሞያዊ ተዓማኒነታችሁን ለማግኘት ፤ መንግሥታዊ አገልግሎቱን ከእምታቀርቡለት ሕዝብ ይኹንታ ማግኘት አለባችሁ የማለት እንጂ ።

አንጥረኛውንም ቢሆን ፤ ደንበኛው መርጦ እንጂ ሥራውን የእሚሰጠው ፤ አንጥረኛው እኔ በውልደት ወይንም በመለኮታዊ ሲመት አንጥረኛ ሆኛለሁ እና ከእኔ ሌላ አንጥረኛ ጋር መኼድ አትችልም ብሎ ሕዝብን እንዲያስገድድ አንፈቅድለትም።

መንግሥት ዴሞክራሲያዊ መሆን አለበት ሲባልም ፤ ሕዝብም እንደ ሕዝብ ራሱን የቻለ ከፍተኛ ሞያዊ እውቀት የእሚጠይቀውን የፖለቲካ ሥራ ያለ ሞያው እና እውቀቱ እኔ ልቆጣጠረው እንዲል ሰአይሆን ፤ መንግሥት የሕዝብ አገልጋይ በመሆኑ ፤ የአገልግሎታቸው ተጠቃሚ የሆነው ሕዝብ ይኽንን መንግሥታዊ አገልግሎት የእሚሰጡትን ሞያተኞች መምረጥ አለበት ማለት ነው።

ሕዝብ ፦ የሕክምና ዕውቀት በአይኖረውም በጤና ገበያው ውስጥ (In the health sector or market) የትኛው ሐኪም ሊያክመው እንደ እሚገባ ይመርጣል ፣ የእደ ጥበብ ባለሞያ ባይሆንም የትኛው የእደ ጥበብ ባለሞያ እንደ እሚሻለው ይመርጣል ፤ በተመሳሳይም ሕዝብ ፖለቲከኛ በአይሆንም የትኛው ፖለቲከኛ የሕዝብ አስተዳደር ሥራውን እንዲሰራለት መምረጥ አለበት ፤ ይችላልም።

ስለ እዚኽ ፦ ስነመለኮታዊያን የእምንላቸው ፤ አንድ የሆነው የስነ መለኮት አስተመህሮ ወይንም የመጽሐፍ ቅዱስ (ከክርስትና ውጭ ላሉት የእምነታቸውን ቅዱስ መጽሐፍ) አስተምህሮ ወይንም የአስተመህሮ አተረጓጎምን የፖለቲካ ስልጣን ምንጭ ትርክት የእሚያደርጉትን ነው።

ከጥንታዊ ዓምላካዊያን የእሚለዩትም ፤ ነገሥታቶችን ወይንም ገዢዎችን እንደ አምላክ ወይንም የአምላክ ዘር ሰአይሆን የእሚቀበሉዋቸው ፤ በአምላክ ለእዚኽ ሥራ እንደ ተመረጡ እና እንደ ተሾሙ ሰዎች በመሆኑ እና ለትርክታቸውም የተጻፈ አምላካዊ ፈቃድ እና አዕምሮዋዊ አመክንዮን አዳብለው በመጠቀማቸው ነው።

ከእላይ በአጭሩ የቀረበው ፤ የአቶ ሮበርት ፊልመር ፤ ነገሥታት የአባትነት ስልጣን ወራሾች በመሆናቸው ከእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው እና ሕዝብ መረን ስለ ሆነ መሪውን መምረጥ አይችልም የእሚለው ቀኖና ፤ ከጆን ሎክ በደረሰበት ነቀፋ ፤ ብዙም ተቀባይነት ሰአያገኝ ተዳፍኖ የቀረ ኃሳብ ሆኗል ። ከእዚኽም የተነሳ ( ቢያንስ በዓለም ዓቀፉ ሳይንሳዊ የፖለቲካ ሙህራን ዘንድ ) ሮበርት ፊልመር ብዙም የእሚጠቀስ ምሁር አልሆነም ።

ጆን ሎክ ፤ የሮበርት ፊልመርን የስነ መንግሥት አመክንዮ ለመተቸት የጻፈውን መጽሐፍ እንዲህ በማለት ነው የጀመረው ፦

“ባርነት የሰው ልጅ ሊገኝባቸው ከእሚችላቸው ወራዳ እና መከራ የሞላባቸው ኹኔታዎች ውስጥ አንዱ ነው ፤ ባርነትም ፥ ደግነት እና ጀግንነት ከተጎናፀፈው የሐገራችን ባሕሪ ጋር በፍፁም ተቃራኒ ነው ፤ ታዲያ አይደለም አንቱ የተባለ የእንግሊዝ መኳንንት ተራውም እንግሊዛዊ ባርነት መልካም ነገር ነው ይላል ተብሎ አይጠበቀም ። እንደ እውነቱ ከሆነ ፤ የእሚያነሳው ጉዳይ እና ርዕሱ ፣ የመጽሐፉ ሽፋን ፣ የተሰጠው አድናቆት መጽሐፉን በአትኩሮት እንድ አየው በአያደርጉኝ ኖሮ ፤ የኔሮ[8] ውዳሴ ብሎ መጽሐፍ እንደ ጻፈው ወይንም እንደ ሌላው ዓይነት የቀልድ እና የቧልት መጽሐፍ ፤ የሰው ልጆችን ኹሉ ባሪያ ናችሁ በማለት እንደ እሚቀልድ መጽሐፍ ነበር ማየት የነበረብኝ ። ከእዚያኽ በኋላም መጽሐፉን ፤ እንደ አገኘው ዝና ፤ የእሚገባውን አትኩሮት ሰጥቼ አነበብኹት ፤ ነገር ግን የሰውን ልጆች ባሪያ ናችሁ ብሎ ለማሰር በእሚፈልገው መጽሐፍ ውስጥ ፤ አሸዋ ላይ የተሳለ የገመድ ምስል እንጂ ሰዎችን ባሪያ አድርጎ ሊያስር የእሚችል ምንም ዓይነት እውነተኛ ገመድ አላገኘሁም ፤ ማንም አዕምሮ የአለው ሰው በአሸዋ ላይ የተሳለ የገመድ ምስል ፥ ምንም በጥንቃቄ እያንዳንዷ ቀለበት ብትሳልም እና ጥርት ብላ ብትቀመጥም ያስረኛል ብሎ አይፈራውም ፤ ምናልባት ባሪያ ሊያደርጋቸው የፈለገው ሰው ፤ የአሸዋ ላይ የገመዱን ምስል አይናቸው ላይ በትኖ ለግዜው ሊያሳውራቸው ከአልሆነ ።”

“Slavery is so vile and miserable an estate of man, and so directly opposite to the generous temper and courage of our nation, that it is hardly to be conceived that an Englishman, much less a gentleman, should plead for it. And truly I should have taken sir Robert Filmer’s Patriarcha, as any other treatise, which would persuade all mere that they are slaves, and ought to be so, for such another exercise of wit as was his who writ the encomium of Nero; rather than for a serious discourse, meant in earnest: had not the gravity of the title and epistle, the picture in the front of the book, and the applause that followed it, required me to believe that the author and publisher were both in earnest. I therefore took it into my hands with all the expectation, and read it through with all the attention due to a treatise that made such a noise at its coming abroad; and cannot but confess myself mightily surprised that in a book, which was to provide chains for all mankind, I should find nothing but a rope of sand; useful perhaps to such whose skill and business it is to wise a dust, and would blind the people, the better to mislead them; but in truth not of any force to draw those into bondage who have their eyes open, and so much sense about them, as to consider that chains are but an ill wearing, how much care soever hath been taken to file and polish them. [71]“

ጆን ሎክ ፤ ከእላይ በተቀመጠው መልኩ ፤ የሮበርት ፊልመር መጽሐፍ ሰዎችን ባሪያ ናችሁ ብሎ ለማሳመን ቢሞክርም ፤ አሳማኝ ሥራ ሊሰራ አልቻለም ከእዛኽ ይልቅ ፤ ይኽን የተናቀ አስተሳሰብ በእዚኽ ዘመን በማቀንቀኑ ፤ የምፀታዊ ቀልድ መጽሐፍ ነው የመሰለው በማለት ፤ በመጽሐፉ ውስጥ የተነሱትን ኃሳቦች ተራ በተራ እያጣቀሰ ስለ አጣጣለ እና የእዚኹ መጽሐፉ ኹለተኛ ክፍል ላይ (The Second Treatise of Government) በእሚለው ላይ በግሩም ብቃት የዘመናዊውን የነጻነቱን ዴሞክራሲያዊ መንግሥት እንደ ትክክለኛው የስነ መንግሥት መርህ ስለ አስቀመጠ ፤ የሮበርት ፊልመር እና የመሰሎቹ ኃሳብ ብዙም ርቀት አልኼደም ።

ከሮበርት ፊልመር ቀጠል አድርጎ ፤ ይኽንን የሰዎችን ተፈጥሮዋዊ ነጻነት እኩልነት የመንግሥት መመሥረቻ መርህነት በመቃወም ፤ ፍፁማዊ የፖለቲካ ስልጣን የእሚገባቸው ሰዎች አሉ ፤ እነርሱም ሰይፍ የታጠቁ የውርስ ነገሥታት ናቸው ብሎ ፤ ጆን ሎክ እንደ አለው ፥ የአሸዋ ላይ የባሪያ ማሰሪያ ገመዱ አል አስር ሲለው ፤ አሸዋውን በሰዎች ዓይን ላይ በትኖ ፤ ማሰር በአይችልም ማጨናበስ የፈለገው ቶማስ ሆብስ ነው ።

ቶማስ ሆብስ ፤ የሮበርት ፊልመር እና መሰሎቹ ፤ ነገሥታት ከአዳም ሲወርዱ ሲዋረዱ የመጡ የአባትነት ክብር ወራሾች ናቸው ወይንም በአንዳች ዓይነት መመዘኛ በአምላክ የተሾሙ ስዩመ እግዚአን ናቸው እና ይኽን ስልጣናቸውን ማንም ሊጠይቀው አይገባም የእሚለው ትርክት እንደ እማያስኼድ ስለ ተረዳ ፤ እውነት ነው መንግሥት የሰዎች ልባዊ ስምምነት ውጤት እንጂ ፤ ከሌሎች ሰዎች የተለየ ፤ ተፈጥሮዋዊ መንግሥት የመሆን መብት የአላቸው ሰዎች ከመኖራቸው አይመጣም ብሎ ጀመረ ፦

“የጋራኃብት (መንግሥት ፣ ብሔራዊ ሐገር) የእሚቋቋመው ፤ ብዛት የአላቸው ሰዎች ተሰብስበው ፤ በአብላጫ ድምፅ አንድን ሰው ወይንም የሆኑ ሰዎች ስብስብን (ፓርቲ ወይንም ማሕበር) በውክልና ፤ እርስ በርሳቸው በሰላም እንዲ ኖሩ እና አንዳቸው አንዳቸውን እንደ አያጠቁ ለመከላከል ፤ እነርሱን ወክለው የማድረግ እና የመፍረድ ስልጣንን ለመስጠት ሲዋዋሉ ነው ይባላል ።”

“A commonwealth is said to be instituted when a multitude of men do agree, and covenant, every one with every one, that to whatsover man, or assembly of men, shall be given by the major part the right to present the person of them all, that is to say, to be their representative; shall authorize all the actions and judgements of that man, or assembly of men, in the same manner as if they were his own, to the end to live peaceably amongst themselves, and be protected against other men. [26]“

ሆብስ ምንም እንኳን ይኽን ብሎ ቢጀምርም ፤ ቀጠል አድርጎ ግን ፤ ይኽን ዓይነቱን ማሕበራዊ ውል መዋዋል የእሚችሉት ሕዝብ ግን ፤ ከእዚኽ በፊት ንጉሥ የሌላቸው ወይንም በዘውድ ስር የእማይኖሩ ሕዝብ ናቸው በማለት የመጀመሪያውን ፤ በአንድ ዘመን ላይ በሕይወት የእሚገኙ እኩል ነጻ ሰዎች ይኹንታ ነው የመንግሥት ስልጣን ትክክለኛ ምንጭ የእሚለውን የመንግሥት መመሥረቻ ትርክት የእሚቃወምበትን ምክንያት አስቀመጠ ፦

“…ስለ እዚኽም ፦ በንጉሥ ስር የእሚያድሩ ሕዝብ ካለ ንጉሡ ፈቃድ ንጉሡን ማውረድ ወይንም ንጉሡን በሌላ ሰው በመተካት ፤ ወደ መንጋ ትርምስ መመለስ አይችሉም ።”

“...And therefore, theh that are subjects to a monarch cannot without his leave cast off monarchy and return to the confusion of a disunited multitude, nor transfer their person from him that beareth it to another man ... [26]“

ሆብስ ፤ በንጉሥ ስር ያሉ ሰዎች ወይንም ዜጎች ለምን የድሮውን ውል ሰርዘው ሌላ አዲስ ውል ማቆም እንደ እማይችሉ የእሚሰጠው ማብራሪያም ሉዓላዊ ወይንም ፍጹማዊ ነገሥታት ፤ ይኽንን በትውልድ ተወራራሽ ፍጹማዊ ንግሥናቸውን የአገኙት ፤ ጅማሮው ላይ እኩል ነጻ የሆኑ ሰዎች ፤ ይኽ ሰው እና የልጅ ልጆቹ በእኛ እና በልጆቻችን ላይ ይንገሡብን ብለው ከነጋሢው ቤተሰብ ጋር ውል ስለ ተዋዋሉ እና ንጉሡም በእዚኽ ቀዳሚ ውል ምክንያት በግዜ ኺደት የአዳበረው ኃይል ስለ አለው ፤ አዲሱ ትውልድ አባቶቹ በታሪክ አጋጣሚ ለንጉሥ የሰጡትን ተወራራሽ ፍፁማዊ የስልጣን ውል ፤ እኛ ዛሬ የእምንገኝ ሰዎች እኩል ነጻ ነን እና በእዚኽ ጉዳይ በአባቶቻችን ውል አንገዛም ብለው ማፍረስ የእማይችሉ በመሆናቸው ነው ፤ የእሚል ነው።

ለእዚኽም እምነቱ ምክንያቱን ሲያስረዳም ፤ ንጉሡ ይኽንን ስልጣኑን በውል የተቀበለው በመሆኑ እና እርሱ ተሳታፊ የሆነበትን ውል ፤ ሰዎች የአለ እርሱ ፈቃድ ቢያፈርሱ ፤ ውል አፍራሾቹን መቅጣት የእሚችልበት (ኃይል) ስለ አለው ፤ ይኽን ስምምነት ያለ እርሱ ፈቃድ የእሚያፈርሱትን ቢቀጣ ማንም ወንጀለኛ ብሎ ሊጠይቀው የእማይችል በመሆኑ ነው ይላል።

ከእዚኽም በተጫማሪ ውሉ ያለ እዚኽ መሰል ፍጹማዊ ባለስልጣን ከንቱ የወረቀት ላይ ጽሕፈት ሆኖ ነው የእሚቀረው ይላል ፦

“…፡ ውሎች ቃል እና ትንፋሽ ብቻ ስለ ሆኑ ፤ የማስገደድ ፣ የማቀብ እና የመከልከል አቅም የላቸውም ፤ ይኽ የአለው በሕዝብ ስም ንጉሡ የታጠቀው ሰይፍ ነው ።”

“...: that covenants being but words, and breath, have no force to oblige, contain, constrain or oblige any man, but what it has from the public sword; [26]“

በእዚኽም መሠረት ፤ ሆብስ አምባገነናዊ ማሕበራዊ ውል ትክክለኛው የመንግሥት ትርክት ነው በሎ የእሚከራከረው ኹለት ቢህሎችን መሠረት አድርጎ ነው ፦

  • አንደኛው ፤ በመደበኛ የሕግ ዳኝነት ውል አፍራሽ የእሚቀጣ በመሆኑ ፤ ንጉሡ ወይንም አንድ ነባራዊ/ልማዳዊ አምባገነናዊ መንግሥት ፤ ፖለቲካዊ ስልጣኑን የያዘው በአንዳች ዓይነት ማሕበራዊ ውል አግባብ በመሆኑ ይኽም ማለት ውል ተዋዋይ በመሆኑ ፤ ውሉ ያለ እርሱ ስምምነት ፤ ሰዎች ኹሉ እኩል ነጻ ናቸው እና እነ እዚኽ እኩል ነጻ ሰዎች የእሚቸሩት ይኹንታ ነው የመንግሥት ስልጣን መሠረት በእሚል ፤ ነጋሢው በታሪክ አጋጣሚ በውል የተቀበለውን ፍጹማዊ ንግሥና ፤ እርሱ እሺ ከስልጣኔ አውርዱኝ ብሎ ሳይስማማ በፊት ከስልጣኑ ቢሽሩበት ውል እያፈረሱ በመሆኑ ሊቀጣቸው ሙሉ መብት አለው ፤ የእሚል ሲሆን ።
  • ኹለተኛ አስገዳጅ ኃይል በሌለበት ኹኔታ ውሎች ከተራ ወረቀት ላይ የተጻፉ ቃላቶች ወይንም ድምጽነት ያለፈ ፋይዳ ስለ እማይኖራቸው ፤ ማሕበራዊ ውል እንዲከበር ፍጹማዊ የሆነ አምባገነን መንግሥት በማስፈለጉ ነው የእሚል ነው።

መንግሥት ምንም እንኳን ከመለኮት ሲመት የእሚመጣ ሳይሆን በሕዝብ ስምምነት የእሚቆም በመሆኑ ፤ አንድ የተመሠረተ መንግሥት በአንዳች ዓይነት ማሕበራዊ ስምምነት የተቋቋመ በመሆኑ እና ይኽም ማሕበራዊ ስምምነት ተከብሮ ስረዓት አልበኝነት (Anarchism) የእሚጠፋው ይኽንን ማሕበራዊ ውል በበላይነት የእሚያስከብረው ፍጹማዊ ወይንም አምባገነናዊ ስልጣን ሲኖር ነው የእሚለው የሆብስ ፤ አምባገነናዊ ውል መንግሥትን ለማጽደቅ ያቀረባቸው መከራከሪያዎች ከግንዛቤ እጥረት እና ከመሠረታዊ የአስተሳሰብ ተፋልሶ ምክንያት የእሚመጡ ችግሮች አሉበት ።

እንደ እምናስታውሰው ፤ ሆብስ ራሱ የተስማማበት እና የገለጸው ፦ የተፈጥሮው ኹኔታ ኹሉም የመሰለውን የማድረግ ተፈጥሮዋዊ ነፃነት ወይንም መብት የተጎናፀፈበት ሲሆን ፣ የተፈጥሮው ሕግ ደግሞ ይኽ የተፈጥሮ ኹኔታ ወደ ግጭት እንደ አያመራ ወይንም የተፈጥሮ/የጦርነት ኹኔታን እንደ አያስከትል ፤ በአመዛዝኖዋዊ ፍርድ ይኽን የተፈጥሮ ነፃነት ፤ የመብቱ ባለቤት የኾነውን ሰው ነፃነት እና ንብረትን ከማስከበር እንደ አያልፍ የእሚያደረግበት መሆኑን አስቀምጠናል ።

በእዚኽም ላይ በመመሥረት ነው መንግሥት ይኽንን የተፈጥሮ ሕግ ነጸብራቅ የሆነውን ሕግ አክብሮ እንዲያስከብር ፤ ለእዚኽ ኃላፊነት በሕዝብ ተመርጦ የእሚሾመው።

ይኽም ማለት ፤ መንግሥት ይኽ በአመዛዝኖ የእሚደረስበትን የተፈጥሮ ሕግ ፤ በማወቅም ሆነ በስህተት የእሚጥሱትን ፤ ጋጠወጥ (Eccentric) ሰዎች እና ኹኔታዎችን ለማሳደብ የእሚመጣ በመሆኑ ፤ አንድ ግዜ ውል አስረሀል እና ንጉሡም ከአንተ በላይ ኃይለኛ ስለሆነ ፤ ንጉሡ ከተፈጥሮ ሕግ አግባብ ውጭ ምንም ዓይነት በደል ቢያደርስብህም እንኳን ውሉን ማፍረስ አትችልም ማለት አይደለም ማለት ነው ።

ስለ እዚኽም በመደበኛ ሕግ ውል የእሚዳኝበትን ማለትም ፦ በመደበኛ ሕግ አግባብ ኹለት ነጻ ሰዎች በፈቃዳቸው ያደረጉትን ሕጋዊ ውል ፤ አንደኛው ሰው በተናጠል ቢያፈርስ የእሚቀጣበትን አግባብ በማጣቀስ ፤ ማሕበረሰብ አንድ ግዜ ከአንድ የነጋሢ ትውልድ ጋር ውል ከአሰረ ፤ ንጉሡ ሳይስማማ ይኽንን ውል በማፍረስ ንጉሡን ይውረድ ወይንም አንዳች ዓይነት ማስተካከያ ያድርግ ብሎ ማስገደድ ፤ ውልን ማፍረስ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ማለት አይቻልም።

ምክንያቱም ፦ የእምንነጋገርበት የማሕበራዊ ውል ፤ የግድ የተፈጥሮ ሕግ ነጸብራቅ የሆነውን ሕግ በመሆኑ ፤ አንድ ግዜ ተዋውለኃል እና ውልን የእሚያፈርስ ደግሞ ሕገ ወጥ ስለ ሆነ ፤ የተዋዋልከው ውል የእሚጎዳህ ሆኖ ቢገኝ እንኳን ይኽን ውል የማፍረስ መብት የለህም የእሚባልበት አይደለም።

ይኽንንም ኃሳብ ፤ ዴሞክራሲያዊነት እና ሐገር በእሚለው በምዕራፍ አንድ ውስጥ በነበረው ክፍል ላይ ጆን ሎክን አጣቅሰን አስቀምጠነዋል ፦

“ ሕግ አውጭው ፤ ለአንድ ሰው ወይንም ለብዙ ሰዎች የተሰጠ ይኹን ፣ ስልጣኑ የህይወት ዘመን ይኹን በግዜ የተገደበ ፣ ወይንም በሐገሪቱ ውስጥ የአለ የመጨረሻው የስልጣን አካል ቢሆንም እንኳን ፤ በመጀመሪያ እና መጀመሪያ በሰዎች ህይወት እና ንብረት ላይ ፍፁማዊ ዘፈቀደ መሆን አይችልም ። ምክንያቱም ፦ ለአንድም ይኹን ለብዙ ሰዎች የእሚሰጠው ይኽ ስልጣን ፤ እያንዳንዱ ሰው ወደ ማሕበረሰብ ውስጥ ከመቀላቀሉ በፊት ፤ በተፈጥሮ ኹኔታ ውስጥ እያለ የነበረው ስልጣን ፤ በጋራ ተደማምሮ የተላለፈ በመሆኑ ፤ ከማሕበረሰቡ አባላት ተፈጥሮዋዊ ስልጣን ሊበልጥ አይችልም ። ምክንያቱም ፦ ማንም ሰው ከአለው ስልጣን በላይ ለሌላ ሰው ሊሰጥ አይችልም ፤ ማንም ሰው ደግሞ የእራሱን ህይወት በፈለገው ሰዓት የማጥፋትም ሆነ የሌላውን ሰው ህይወት እና ንብረት የመቀማት የዘፈቀደ ስልጣን የለውም ፤ ሕጋዊ በአለ ስልጣኑም ከእዚኽ ያለፈ ስልጣን ሊኖረው አይችልም ። ስልጣናቸውም የማሕበራዊ እድገት ከማስመዝገብ ያለፈ ግብ ሊኖረው አይችልም ። የደህንነት ዋስትና ያለፈ ስልጣንም አይደለም ፤ ስለ እዚኽ ነዋሪዎቹን የማጥፋት ፣ ባሪያ የማድረግ ወይንም የማደህየት እቅድ የአለው ሊሆን አይችልም ፤ ማሕበረሰብ ውስጥ የተፈጥሮ ሕግ መሥራት አያቆምም ፤ ነገር ግን የማሕበሩ ሕግጋት ከእርሱ ጋር በተቻለ መጠን እንዲ-መሳሰሉ ይደረጋሉ እንጂ ፤ ከእዚኽም የተነሳ በተጻፉ የሰዎች ሕግ ፤ የተፈጥሮ ሕጉ እንዲከበር ግልፅ ቅጣት ይደነገጋሉ ፤ እንዲ ከበሩ ። ስለ እዚኽ ፦ የሰው ልጆች የዘላለም ሕግ ሆነው ይኖራሉ ፤ ለሕጋዊ ባለ ስልጣኖች ይኹን ለነዋሪዎቹ ። ለሌላ ሰዎች የእሚወጣው ሕግ ፤ በአውጭውም ላይ ተፈፃሚ በእሚሆንበት ግዜ የእማይጎረብጣቸው መሆን አለበት ፤ ይኽም ከተፈጥሮ ሕግ ጋር የእሚስማማ መሆን አለበት ።”

“Though the legislative, whether placed in one or more, whether it be always in being or only by intervals, though it be the supreme power in every commonwealth, yet, first, it is not, nor can possibly be, absolutely arbitrary over the lives and fortunes of the people. For it being but the joint power of every member of the society given up to that person or assembly which is legislator, it can be no more than those persons had in a state of Nature before they entered into society and gave it up to the community. For nobody can transfer to another more power than he has in himself, and nobody has an absolute arbitrary power over himself, or over any other, to destroy his own life, or take away the life or property of another. A man, as has been proved, cannot subject himself to the arbitrary power of another; and having, in the state of Nature, no arbitrary power over the life, liberty, or possession of another, but only so much as the law of Nature gave him for the preservation of himself and the rest of mankind, this is all he doth, or can give up to the commonwealth, and by it to the legislative power, so that the legislative can have no more than this. Their power in the utmost bounds of it is limited to the public good of the society. It is a power that hath no other end but preservation, and therefore can never have a right to destroy, enslave, or designedly to impoverish the subjects; the obligations of the law of Nature cease not in society, but only in many cases are drawn closer, and have, by human laws, known penalties annexed to them to enforce their observation. Thus the law of Nature stands as an eternal rule to all men, legislators as well as others. The rules that they make for, other men’s actions must, as well as their own and other men’s actions, be conformable to the law of Nature. [71]“

እንደገናም በሌላ ስፍራ ላይ በእዚኹ ጉዳይ ጆን ሎክ እንደ እዚኽ እንደ አለ አጣቅሰናል ፦

“ ኹሉም ዓይነት ስምምነት አይደለም ፤ በሰዎች መካከል የአለውን የተፈጥሮ ኹኔታ የእሚያስቆመው ፤ ነገር ግን ኹሉም በጋራ ከኹሉም ጋር አንድ ማሕበረሰብ በመሆን አንድ ሐገር የእሚፈጥሩበት እንጂ ፤ ከእዛኽ ውጭ የአሉት ሰዎች የእሚገቡባቸው ተስፋዎች እና ውሎች ፤ መልሰው የተፈጥሮ ኹኔታ ውስጥ ነው የእሚያመጡዋቸው ።”

“for it is not every compact that puts an end to the state of Nature between men, but only this one of agreeing together mutually to enter into one community, and make one body politic; other promises and compacts men may make one with another, and yet still be in the state of Nature. [71]“

ምን አልባት ይኽ የጆን ሎክ ገለጻ ከተንዛዛ ፤ ኹኔታውን ቀለል በአለ ምሳሌ ለማስረዳት ፤ በአንድ የነጻነት ዴሞክራሲ ስረዓት በተዋቀረ ማሕበረሰብ ውስጥ የእሚኖሩ ሰዎች ፤ ባሪያ አሳዳሪ እና ባሪያ ለመሆን መዋዋል አይችሉም ። ምናልባት ግን በሆነ አጋጣሚ ኹለት ነጻ የሆኑ ሰዎች ፤ አንዱ ራሱን ባሪያ አድርጎ ሊሸጥ ሌላውም አሳዳሪው ሊሆኑ ሊዋዋሉ ብችሉም እንኳን ውላቸው በሕገመንግሥቱ መሠረት በተዋቀረው ፍርድ ቤት እውቅና አይኖረውም።

አንድ ግለሰብም በፈቃዴ ራሴን ፤ በባርነት እንደ እቃ እንድገዛ እና እንድ እሸጥ ፣ የጉልበት ብዝበዛ ፣ የመብት ረገጣ ፣ ወዘተ ፤ እንዲደረግብኝ ከእገሌ ጋር ውል አስሬአለው ብሎ ውል ቢያስር ፤ ይኽ ውል በዴሞክራሲያዊ ስረዓት የመንግሥት ተቋማት ውስጥ እውቅና አይኖረውም።

ይኽም ብቻ ሰአይሆን ፤ በእዚኽ መልኩ ራሱን ባሪያ አድርጎ ለመሸጥ ውል የአሰረ ሰው ፤ አንድ ቀን ኃሳቡን ለውጦ ባርያ አልሆንም ብሎ ውሉን ቢያፈርስ ፤ ውል አፈረስክ ብሎ በሕጋዊ አግባብ ሊከሰሰበት እና ሊቀጣበት የእሚችልበት ሕጋዊ አግባብ የለም።

ስለ እዚኽ ፦ ሆብስ ውል የአፈረሰ ይቀጣል በእሚለው ጠቅላላ የሕግ መርህ ተመስርቶ ፤ አንድ ንጉሥ በውል ፍጹማዊ ወይንም አምባገነናዊ ንጉሥ ከተደረገ በኋላ ፤ ውሉ የተፈጥሮ ሕግን የእሚጻረር ቢሆንም እና ንጉሡን ጨቋኝ ቢያደርገውም ፤ ውል መከበር አለበት እና ውሉን ማፍረስ ሕገ ወጥነት የእሚለው ክርክር ፤ የዜጎችን የማሕበራዊ አህድነት አውቆ ከእሚያከብረው የማሕበራዊ ውል አስተሳሰብ አንጻር ትክክል አይደለም።

ከሕጋዊ ውሉ ክርክርምም በአሻገር ፤ ማሕበራዊ ውል እንዲከበር ፤ ዜጎች በመላው የንጉሡን ሰይፍ መፍራት አለባቸው የእሚለው የሆብስ የአምባገነናዊ ማሕበራዊ ውል ትርክት ማጽደቂያ መከራከሪያም ትክክል አይደለም።

አብዛኛው ሕዝብ አመዛዝኖ ፤ የእማይታዘዘውን ሕግ ፤ በውስን ሕግ አስከባሪ ኃይላት ማስከበር አይቻልም ። ሆብስ ራሱም እንዲኽ እንደ አለ ጠቅሰናል ፦

“ይኽንም ተከትሎ ፤ የተባለ ፥ ጠቅላላ ተቀባይነት የአለው ምክንያታዊነት ነው ፤ የማግኘቱ ተስፋ እስከ አለ ድረስ ፤ ሰው ኹሉ ሰላምን ለማግኘት መጣር አለበት ፤ በእዚኽ መልኩ ፈልጎ ሰላምን ሊያገኘው ከአልቻለ ግን ጦርነት የእሚሰጠውን ርዳታ እና ጥቅም መፈለግ አለበት ።”

“And consequently, it is a precept, or general rule of reason: that every man ought to endeavor peace, as far as he has hope of obtaining it; and when he cannot obtain it, that he may seek and use all helps and advantages of war [26].”

በአጭሩ ንጉሡ ሰይፍ ያነሳል እና ሕዝብ ሆይ ዝም በል የእሚለው የኃይል መከራከሪያ ፤ ሕዝብም ሰይፍ ማንሳት የእሚችል በመሆኑ ትክክለኛ መከራከሪያ አይደለም ፤ መጀመሪያዊንም የውሉ መኖር የአስፈለገው አንዱ ሌላውን በኃይል የእሚጨቁንበት እና ይኽም የእርስ በእርስ ግጭትን ወይንም ሰይፍ የመሳሳልን ኹኔታ መልሶ እንደ አያመጣው በመሆኑ።

የመንግሥት ስልጣንም ከሰይፍ ስለት ወይንም ከመሳሪያ አፈሙዝ የእሚመነጭ ከሆነ ፤ ሕጋዊ ወይንም ተቀባይነት የአለው ስልጣን አይደለም ። ይኽንን ኹኔታ የፈረንሳዩ ፈላስፋ ጃን ጃክ ሩሶ እንደ እዚኽ ያስረዳዋል ፦

“ሰው ነፃ ሆኖ ተወልዶ ሳለ ፤ በእየቦታው በሰንሰለት ታስሯል ። የፍጥረት ኹሉ አለቃ ነው የእሚልም ይኖራል ፥ እውነታውን ግን ከእነርሱ በላይ ባሪያ ሆኗል ። ይኽ ኹኔታ እንዴት መጣ ? አላውቅም ። ይኽንን ግን ምን ሕጋዊ ያደርገዋል ? ይኽንን ጥያቄ ነው ለመመለስ የእማስበው ፦

“ኃይልን ብቻ እና ኃይል ሊያደርግ የእሚችለውን ከግምት ውስጥ ከአስገባሁ ፤ ይኽን ማለት እችላለሁ ፦

‘ሰው እንዲታዘዝ ግዴታ ከመጣበት መታዘዙ መልካም ነው ፥ ይኽን ግዴታ ማሽቀንጠር ከቻለ ግን ማሽቀንጠሩ የበለጠ መልካም ነው ። ይኽን የማድረግ መብቱ ጥያቄ ውስጥ ከገባ ፥ መብቱ መጀመሪያ በተገፈፈበት አግባብ ፥ ማለትም በኃይል ፥ መብቱን እንደ አስመለሰ መናገር ይችላል ። መብቱን ለመግፈፍ በቂ የሆነው ኹኔታ መብቱን ለማስመለስም በቂ ይሆናል ፤ መብቱን ለመግፈፍ በቂ ምክንያት ከሌለ ፤ በተመሳሳይ አግባብ መብቱን ያስመለሰበትን መንገድ መንቀፊያ በቂ ምክንያት መኖር አይችልም ።’

ማሕበራዊ ስረዓት ግን የኃይል ጉዳይ ተደርጎ መወሰድ የለበትም ፤ ሌሎቹ መብቶች ኹሉ የእሚንተራሱበት መብት በመሆኑ ።”

“Man is born free, and everywhere he is in chains. Here’s one who thinks he is the master of others, yet he is more enslaved than they are. How did this change come about? I don’t know. What can make it legitimate? That’s a question that I think I can answer.

If I took into account nothing but force and what can be done by force, I would say:

‘As long as a people is constrained to obey, it does well to obey; as soon as it can shake off the yoke, it does even better to shake it off. ·If its right to do so is challenged, it can answer that·: it gets its liberty back by the same ‘right’—·namely, force·—that took it away in the first place. Any justification for taking it away equally justifies taking it back; and if there was no justification for its being taken away ·no justification for taking it back is called for·.’

But the social order ·isn’t to be understood in terms of force; it· is a sacred right on which all other rights are based. [47]“

ሩሶ እንደ እሚለው ፤ ነፃ ሆኖ የተወለደ ሰው በእየቦታው በባርነት ይገኛል ወይንም ያለ ፈቃዱ ከተፈጥሮዋዊ ሕግ በተፃራሪ ሰዎች በላዩ እየገዙ ይጨቁኑታል ። ይኽ የሆነው በኃይል የመጣበት ግዴታ ከሆነ ፤ ሰውየው ለእዚኽ ኹኔታ ኃይል ከሌለው ተገዢ ይኹን ፥ ኃይል ካለው ግን ይኽንን በኃይል የተጫነበትን ቀንበር ቢያስወግድ ማንም አመፀኛ ብሎ ሊከሰው አይገባም ምክንያቱም ፤ መብቱ በኃይል ከተገፈፈበት በኃይል መብቱን ማስመለሱ ትክክል ነው ። እንዲኽ ዓይነቱ የኃይል ሰጣ ገባ ግን ፤ ለማሕበራዊ ስረዓት የመወያያ ርዕስ ሆኖ መቅረብ የለበትም ፤ ምክንያቱም ፦ በእዚኽ መሠረታዊ የጋራ ግንዛቤ ላይ ተንተርሰን ስለ ሆነ ስለ ሌላው ማሕበራዊ ጉዳይ ማውራት የእምንችለው ፤ ማሕበራዊ ውሉን በተመለከተ ሕዝባዊ ስምምነት እንጂ አስገዳጅ ኃይልን ብቻ ታሳቢ ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ ያስረዳናል ።

ስለ እዚኽ ፦ ሆብስ እንደ እሚለው የንጉሡ ውል መከበር የአለበት ሰይፍ ስለታጠቀ ከሆነ ፥ ወይንም የስልጣኑ ሕጋዊነት የእሚመነጨው ከወታደራዊ አቅሙ ከሆነ ፤ ይኽንን አስገዳጅ ኃይል በኃይል ማስወገድም ተገቢ ይሆናል ።

በሆብስ የቀረበውን የአምባገነናዊ ማሕበራዊ ውል ትርክት ፤ ዜጎችን የማሕበረሰብ አህድ አድርጎ ከመቀበል አንጻር ስንመዝነው ፤ በአመክኖያዊ ተፋልሶ (fallacious reasoning) ምክንያት የዜጎችን ማሕበራዊ አኃድነት ሳይቀበለው ሲቀር እናያለን።

ሆብስ ኹሉም ዜጎች በተፈጥሮ እኩል ነጻነት የአላቸው ዜጎች መሆናቸውን እና ይኽንንም ተፈጥሮዋዊ እኩል ነጻነታቸውን በሕይወት ለመቆየት እና ሕይወታቸውን ይገባል ብለው በእሚሉት መልኩ ለማሻሻል ይጠቁመብታል የእሚለውን በውብ ቋንቋ በመግለጽ ኃሳቡን በአግባቡ እንደ ተረዳው ግልጽ ቢሆንም ፤ ይኽ ግንዛቤ የእሚያስከትለውን ፤ ትክክለኛው መንግሥት በተፈጥሮ እኩል ነጻ የሆኑ ዜጎች ህይወታቸውን እና ንብረታቸውን የስረዓት አልበኝነት ከእሚያስከትለው አደጋ ለመከላከል የእሚያቆሙት ነው ፤ የእሚለው ድምዳሜ ላይ ግን መድረስ አልቻለም።

ከእዛኽ ይልቅ ዜጎች ራሳቸውን መከላከል የእሚችሉት ከሌላ ዜጋ ብቻ እንጂ ከመንግሥት ከእሚደርስባቸው በደል አይደለም በማለት መንግሥታት ምንም አምባገነን እና ጨቋኝ ቢሆንም እንኳን ያለ መንግሥት መኖር ስለ እማይቻል እና ኃይላቸውም ትልቅ ስለሆነ ፤ በአምባገነን እና በጫቋኝ መንግሥት ስር የአለ ሕዝብ ፤ ዝም ብሎ ከመገዛት ሌላ አማራጭ የለውም ወይንም ራስን ከአደጋ የመከላከል መብቱን ራሱን ከጨቋኝ መንግሥት ለመከላከል መጠቀም አይችልም ወይንም የለብትም የእሚል ያልበቃ መከራከሪያ አቅርቧል።

የእማይከሰስ ፣ የእማይለወጥ እና ተቀናቃኝ የሌለው ስልጣን ባለቤት ፤ ለአንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ህልውና መተኪያ የሌለው አማራጭ ነው የእሚለው የፖለቲካ አስተሳሰብ ፤ ራሱን በተለያየ መልክ እየቀያየረ ለረዥም ዘመን የቆየ አስተሳሰብ ወይንም የፖለቲካ ትርክት በመሆኑ ፤ የሆብስ ውል ተኮር አምባገነናዊ መንግሥት ትርክት ከከሸፈም በኋላ መልኩን ቀይሮ መጥቷል ።

የፖለቲካ ስልጣን ፤ በአዕምሮ ፍርድም መረጋገጥ የእሚችል አባታዊ የመለኮት ፈቃድ ነው እና ንጉሡ በአንዳች ዓይነት ማሕበራዊ ውል የመጣ ሰይፍ ስለ ታጠቀ ምንም በደለኛ ቢሆንም እንኳን በአምባገነንነት የመንገሥ ብቸኛ መብት አለው የእሚሉ የነበሩት ኹለቱ ቀዳሚ ትርክቶች ፤ በነፃነት ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ምክንያት ተቀባይነት እያጡ ሲኼዱ ፤ በሳይንሳዊው ጎራ ስር በሶስተኝነት የመጣው ትርክት ፤ የፖለቲካ ስልጣን በባሕሪው ፤ ጥቂት ሰዎች ሰፊውን ሕዝብ ለመጨቆን የእሚጠቀሙበት በመሆኑ ፤ የፖለቲካ ስልጣን ወይንም መንግሥት የእሚባለው በፍፁም የእማያስፈልግ ነው ፤ ሆኖም ግን መንግሥት አል አስፈላጊ ሆኖ እስኪ ጠፋ ሰፊው ሕዝብ ጥቂቶቹን ፤ የቀድሞውን ገዢዎቹን እየጨቆነ መቆየት የአለበት በመሆኑ ፤ ሰፊው ሕዝብ የቀድሞ ገዢዎቹን የእሚጨቁንበት መሳሪያ ስለ እሚያስፈልገው ፤ መንግሥት እስከ እነ አካቴው ከስሞ እስኪ ጠፋ ብዙኃኑ ጥቂቱን የእሚጨቁኑበት መሳሪያ ነው በእሚል ነው ።

ይኽ በሳይንሳዊ የመንግሥት ትርክት ዝርዝር ውስጥ በሦሥተኛነት የእሚመጣው እና ከአምባገነናዊ የስነመንግሥት መላምት ጎራ የእሚመደበው ከላይ ያስቀመጥነው የስነ መንግሥት መላምት ፤ የማርክሲዚም ስነ-መንግሥት ትርክት ነው ፦

“…መንግሥት ማለት የገዢው መደብ የመግዣ እጅ ነው ፥ … መንግሥት ራሱን ከማሕበረሰብ በላይ የእሚያደርግ እና ከግዜ ወደ ግዜ ራሱን ከማሕበረሰቡ እየነጠለ የእሚኼድ ከሆነ (በመሆኑ) ፤ ጭቁኑን መደብ በአመፅ አብዮት እና መንግሥት የእሚባለውን እና የእዚኽ መነጠል መገለጫ የሆነው ነገር እስከ እነ አካቴው በማጥፋት ከአልሆነ በስተቀር ነፃ ማውጣት አይቻልም።”

“...that the state is an organ of class rule, …if it is a power standing above society and “alienating itself more and more from it”, it is clear that the liberation of the oppressed class is impossible not only without a violent revolution, but also without the destruction of the apparatus of state power which was created by the ruling class and which is the embodiment of this “alienation” [29]“

መንግሥት የጭቆና መሳሪያ ከሆነ የእሚለው ገለፃ ፤ ከሌኒን መጽሐፍ እና ከጠቅላላው የማርክሲዝም መላምት አንፃር ፤ መንግሥት ከአፍራሽ በኃሪው ሊቀየር ወይንም ሊሻሻል የእሚችል ኹኔታዊነትን አመልካች ሰአይሆን ፤ ምንም ማድረግ በእማይቻልበት ወይንም በስሪት ወይንም ተፈጥሮዋዊ ባሕሪ የተነሳ ራሱን ከማሕበረሰብ በላይ የእሚያደርግ እና ራሱን ከማሕበረሰብ እየነጠለ የእሚኼድ መሆኑን አማራጭ በሌለበት ኹኔታ እንደእዛ መሆኑን ገላጭ ነው ( the statement ‘if it is a power standing above society and alienating itself more and more from it’ is not a conditional statement, rather it is a reification of what is, according to Marxism, to be the state and essence of all forms of non-socialist governments or reiterating the fact that according to Marxism all forms of non-socialist governments are destined to be unnecessary powers that stand above society and alienate themselves from it more and more, which makes them superfluous and a legitimate target to be removed by and through violent socialistic revolution ) ።

ይኽም በመሆኑ ፤ በማርክሲዝም የስነ-መንግሥት አመክንዮ ፤ መንግሥት በአመፅ አብዮት ከተወገደ በኋላ ፤ የሠራተኛው አምባገነንነት ይሰፍናል ፤ ይኽም የሠራተኛው አምባገነንነት ፤ የግል ንብረትን ሽሮ ፣ ፀረ አብዮተኞችን አስወግዶ ፣ ሠራተኛውን ለደሞዝ ሰአይሆን ለሥራ ፍቅር የእሚሰራ ከአደረገው በኋላ ፤ የሰው ተፈጥሮ ተቀይሮ ክፍያውን ወይንም ጥቅሙን እያሰበ የእሚሰራ ሰአይሆን ፤ ሥራ የኑሮ ዘዬው ስለ ሆነ የእሚሰራ ሰው ሲፈጠር ፤ የመንግሥት አስፈላጊነት ይጠፋል ወይንም ከሶሻሊዝም ወደ ከምኒዝም እንሸጋገራለን ብለው ይመልሳሉ ።

በሌላ አገላለፅ የቡርዡዋውን መንግሥት በአብዮት አፍርሰን የሠራተኛውን መንግሥት ወይንም የሶሻሊዝም መንግሥት ወይንም የሠራተኛው አምባገነንነት ግን በግዜ ኺደት በራሱ ግዜ ይከስማል ነው የእሚሉት ፦

“እንደ ኤንግልስ አባባል ፥ የቡርዡዋው መንግሥት አይደለም በራሱ ግዜ የእሚከስመው ፥ ይልቁንም የቡርዥዋው መንግሥት በሠራተኛው አብዮት ይደመሰሳል ። በራሱ ግዜ የእሚከስመው ፤ ከሠራተኛው አብዮት በኋላ የእሚመጣው የሠራተኛው መንግሥት ወይንም መንግሥት መሰል አደረጃጀት ነው ።”

“According to Engels, the bourgeois state does not “wither away”, but is “abolished” by the proletariat in the course of the revolution. What withers away after this revolution is the proletarian state or semi­state. [29]“

ይኽ መንግሥት መሰል ወይንም የሠራተኛው መንግሥት ፤ የቡርዣውን መንግሥት ከደመሰሰ በኋላ ፤ በምን ያህል ግዜ ይከስማል ወይንም የሠራተኛው መንግሥት ከስሞ ፤ ምድራዊው ገነት ለመፈጠር ምን ያህል ግዜ ይፈጃል ለእሚለው ጥያቄ ፤ የእሚስጡት መልስ ፦

“በምን ፍጥነት እና በእንዴት ያለ ቅደም ተከተል እንደ እሚከስም አናውቅም ፤ አንድ ቀን እንደ እሚከስሙ ግን አስረግጠን እናውቃለን ።”

“We do not know how quickly and in what succession, but we do know they will wither away. [29]“

የእሚል ነው ።

ይኽ ኹሉ የማርክሲዝም ዙሪያ ጥምጥም ግን ፤ አንድ እና አንድ ጭብጥ ነው የአለው ፤ እርሱም ፤ የማብቂያ ዘመኑ የእማይታወቅ እና ‘የጭቆና’ ኃይሎች እና ፀረ አብዮተኞችን የእሚጨቁን ፤ የሠራተኛው አምባገነን የእሚባል ፤ ፍፁማዊ አምባገነን መንግሥት ማቆም ነው ።

በእዚኽም መሠረት ፤ የሠራተኛው መንግሥት አምባገነን መንግሥት የስልጣን ሕጋዊነት ወይንም ቅቡልነት የእሚመነጨው ፤ ጨቋኙን በተጨቋኙ ገልብጦ ተጨቋኙን ጨቋኝ ማድረግ ተገቢ ነው ወይንም ጥቂቶች ብዙዎችን ይጨቁኑ ከነበረበት ፤ የዘመን ገደብ ለሌለው ነገር ግን በግዜያዊነት በእሚል ፤ ብዝኃኑ ጥቂቶችን መጨቆን አለበት ከእሚል ማርክሲስታዊ አስተሳሰብ የእሚመነጭ ነው ።

በተርታ ቃላት ፤ በሠራተኛው አምባገነን (Dictatorship of the proletariat) መንግሥት ፍልስፍና ፤ መደባዊ የሆነ ፖለቲካዊ በቀል ነው የስልጣን ሕጋዊነት ምንጭ ።

ይኽንንም የፖለቲካዊ በቀል ኃሳብ ሌኒን ሲያስረዳ ፦

“በተጨማሪም ፥ ከካፒታሊዝም ወደ ሶሻሊዝም በእሚደረገው ሽግግር ጭቆና አስፈላጊ በመሆኑ የእሚቀር አይደለም ፤ ነገር ግን በእዚኽ ግዜ የእሚሆነው ጭቆና ብዙኃኑ በዝባዥ ፤ ጥቂቶች ደግሞ ተበዝባዥ የእሚሆኑበት ነው ። እንደ ለየ፟ት የአለ መሳሪያ ፤ ለየ፟ት የአለ የጭቆና ማሽን ፤ ‘መንግሥቱ’ ፤ በእዚኽ የሽግግር ወቅት አስፈላጊነቱ አይቀርም ። በእርግጥ ይኼ መንግሥት የተለመደው ዓይነት መንግሥት አይደለም ፤ ምክንያቱም ፦ ጥቂቶቹን በዝባዦች በብዙኃኑ የደሞዝ ባሪያዎች መጨቆን በተነጻፃሪነት ቀላል ፣ ያልተወሳሰበ እና ተፈጥሮዋዊ ስለ ሆነ ፤ የባሪያዎችን ፣ የጭሰኞችን ፣ የምንደኞችን አመፅ ከመጨቆን ያነሰ ደም የእሚያፈስ ፤ ስለ እዚኽም የሰውን ልጅ ጥቂት ዋጋ የእሚጠይቅ ነው ።”

“Furthermore, during the transition from capitalism to communism suppression is still necessary, but it is now the suppression of the exploiting minority by the exploited majority. A special apparatus, a special machine for suppression, the “state”, is still necessary, but this is now a transitional state. It is no longer a state in the proper sense of the word; for the suppression of the minority of exploiters by the majority of the wage slaves of yesterday is comparatively so easy, simple and natural a task that it will entail far less bloodshed than the suppression of the risings of slaves, serfs or wage­laborers, and it will cost mankind far less. [29]“

የማርክሲዝም ፍልስፍና ፤ በማሕበረሰብ ውስጥ ምንም ዓይነት የመደብ ልዩነት ከአለ፟ ፤ አንዱ መደብ ሌላውን መደብ መጨቆኑ የእማይቀር ስለ ሆነ ፤ የመደብ ልዩነቶች ኹሉ እስኪ ጠፉ (ከእላይ እንደ አልነው በቲየሪው መሠረት መጥፋታቸው አይቀርም ነው እንጂ መቼ እንደ እሚጠፉ አይታወቅም ወይንም መንግሥት ከጀመረ ጀምሮ መንግሥት በአንድም በሌላም መልኩ ያልነበረበት ማሕበረሰብ በታሪክ ታይቶ አይታወቅም ) ብዝኃኑ ጥቂቱን በመጨቆን ፤ ወደ መደብ አልባ ወይንም የከምኒዝም ገነት የእሚደረገው ታሪካዊ ኺደት መምራት አለበት ።

ስለ እዚኽ ፤ የሠራተኛው አምባገነንነት ፤ በምዕራፍ አንድ ላይ በአስቀመጥነው ፤ የካርል ማርክስ የሙግት ቁሳዊነት (Dialectical Materialism) ዘዋሪነት ፤ ታሪክ ፥ ከቡርዡዋው ስረዓት ወደ ከምኒዝም ገነት በእሚኼድበት ወቅት ፤ የታሪክ ቁሳዊነት (Historical Materialism) አንድ ደረጃ በሆነው በሶሻሊስታዊ መንግሥት ውስጥ ፤ ሠራተኛው (ብዙው) ቡርዡዋውን (ጥቂቱን) ‘በግዜያዊነት’ የእሚጨቁንበት ነው ።

ይኽም ማለት ፤ በጣም አሳጥረነው አንድ ማሕበረሰብ ከካፒታሊዝም ወደ ከምኒዝም እስኪ ሻገር (ከተሻገረም) ቢያንስ አንድ መቶ አመት በላይ መፍጀቱ ስለ እማይቀር ፤ የሠራተኛ አምባገነንነት ቢያንስ ለአንድ መቶ ዓመታት ፤ የቀድሞ ጨቋኞቹን እየጨቆነ በስልጣን ላይ ፍጹም አምባገነናዊ መንግሥት ሆኖ ይቆያል ፤ በመርህ ደረጃ ።

ይኽን የሠራተኛውን አምባገነንነት የስልጣን ሕጋዊነት ምንጭ ትንታኔ እንደ ተገቢ ወይንም ሕጋዊ የስልጣን ምንጭነት ለመቀበል ፤ አንድ ሰው የሙግት ቁሳዊነት እና የታሪክን ቁሳዊነት የእሚባሉትን የካርል ማርክስ ፍልስፍና ትክክለኛነት መቀበል አለበት ወይንም የሠራተኛውን አምባገነንነት ፍልስፍና ለመረዳት የማርክስን የታሪክ ትንታኔ መረዳት ግድ ይላል ።

ያም ማለት ፤ ፀሐይ ኹል ግዜ በምሥራቅ እንደ እምትወጣው ፤ ለምሳሌ ፦ ከካፒታሊስት ስረዓት ወደ ከምኒስት ስረዓት በሶሻሊዝም በኩል መሸጋገር ፤ ማንም ሊያስቀረው የእማይችል ፤ ተፈጥሮዋዊ ሕግ መሆኑን መቀበል ግድ ይላል ።

የሠራተኛውን አምባገነንነት ትርክት ፤ የዜጎችን የማሕበረሰብ አህድነት ከመቀበል አንጻር ስንመዝነው ፤ ትርክቱ ፥ ዜጎች በተፈጥሮዋዊ እኩል ነጻነታቸው አማካኝነት ከእሚሰጡት ይኹንታ ነው የፖለቲካ ስልጣን የእሚመነጨው የእሚለውን ብኺል የእማይቀብል ሆኖ እናገኘዋለን ።

በመጀመሪያ ደረጃ ለማርክሲዝም የፖለቲካ ስልጣን ምንጩ በደም አፋሳሽ አብዮት የተደረገ መንግሥት ግልበጣ እንጂ የዜጎች ይኹንታ አይደለም።

ከእዛኽም በመቀጠል የመደብ በአላንጣነትን የእሚሰብክ እና ሰዎች በእሚገኙበት የኢከነሚ ደረጃ መሠረት አንዱን ወዳጅ ሌላው ጠላት አድርጎ የእሚበይን እና የጠላት መደብ አባላት ናቸው የአላቸውን ሰዎችን የአለምንም ሰብዓዊ ደንብ እና ርሕራሔ ለማጥፋት የተዘጋጀ በመሆኑ ማርክሲዝም ከሰብዓዊነት አንጻር አረሜናዊ (Barbaric) ስረዓት መሆኑ ይታያል።

በሶስተኝነት ፤ የመደብ ጠላቶቹን አሸንፎ እና አጥፍቶ በእሚፈጥረው ማሕበረሰብ ውስጥ ፤ ዜጎች ተፈጥሮዋዊ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተጠቅመው ሕይወታቸውን በእሚመስላቸው መንገድ እንደ አይመሩ በማርክሲስታዊ አስተሳሰብ ብቻ መመራት አለባቸው ብሎ ግድ የእሚል በመሆኑ ፤ ማርክሲዝም በጽንሰ ኃሳብ እና በተግባር ደረጃ ፤ ኢሰብዓዊ ወይንም የዜጎችን የማሕበረሰብ አህድነት የእማይቀበል አረመኔያዊ (Barbaric) ስረዓት ነው።

እነ እዚኽ ከላይ የዘረዘርናቸው ሦሥቱ ፤ ማለትም ፦ የስነመለኮታዊያኑ ፣ የአምባገነን ውል እና የሠራተኛው አምባገነንነት ፤ አሁን በአለንበት ዘመን አንፃር ሙሉ ለሙሉ በአይባልም ፤ በአብዛኛው የዓለም ክፍል ተቀባይነታቸው የደበዘዘ እና እንደ ተገቢ የፖለቲካ አማራጭ የእሚወስዳቸው እያጡ በመምጣታቸው ፤ ሙልጭልጩ አምባገነንነት ፤ በፈረንጆቹ 1970 አከባቢ ብቅ የአለው የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ በእሚል ትርክት ካባ ነው።

በእዚኽ በልማታዊ መንግሥት ትርክት መሠረትም ፤ ልክ እንደ ሌሎቹ ሳይንሳዊ እና አምባገነናዊ ትርክቶች ፤ የፖለቲካ ስልጣን በተፈጥሮ እኩል ነጻነት ከአላቸው ዜጎች ይኹንታ ሰአይሆን ፤ የፖለቲካ ስልጣንን ፈጣን እድገት ማስመዘገቢያ መሳሪያ አድርጎ ከማመን ይመነጫል የእሚል ነው።

በልማታዊ መንግሥት ውጥን እና በውጥኑ ዝግመታዊ እድገት ላይ የታተመ አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ ፤ ልማታዊ መንግሥትን እንደ እዚኽ ይገልጸዋል ፦

“’ልማታዊ መንግሥት’ የእሚለው ሐረግ ፤ የኢከነሚያዊ እድገት አቅጣጫ እና ፍጥነት ላይ ጣልቃ የእሚገባ መንግሥትን የእሚያመላክት ነው ። የልማታዊ መንግሥት በዋናነት ፤ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ኹለተኛው ግማሽ ላይ ምሥራቅ ኤስያዊያን ይከተሉት ከነበረው የኢከነሚ ፖሊሲ ፥ በተለይ ደግሞ ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት በጃፓን ከነበረውን የኢከነሚ ሟደል ጋር የተያያዘ ነው ።”

“The term developmental state refers to a state that intervenes and guides the direction and pace of economic development. The developmental state is mainly associated with the type of economic policies followed by East Asian governments in the second half of the twentieth century and, in particular, with the post World War II Japanese economic model. [80]“

የልማታዊ መንግሥት ዋነኛ ትርክት ፤ የግል ባለ ኃብቶች በትርፍ ሕግ የእሚገዙ ስለ ሆኑ ፤ የልማት ኃይልነታቸው ማሕበራዊ ተደራሽነት የለውም ። መንግሥት ግን በትርፍ ሕግ “ስለ እማይገዛ” በትንሽ ወይንም በዜሮ ትርፍ ፤ የሕዝብን ተጠቃሚነት ግብ የአደረጉ የኃብት ግንባታ ሥራ ሊሰራ የእሚችል በመሆኑ ፤ በልማቱ ረገድ ኋላ ቀር በሆኑ ሐገራት ፤ የፖለቲካ ስልጣን የእሚይዙ ሰዎች ለዜጎች ተፈጥሮዋዊ እኩል ነጻነት ቦታ ሰአይሰጡ ፤ ፈጣን ልማት ማምጣት ይገባል የእሚሉ ሰዎች የፖለቲካ ስልጣን ይገባቸዋል የእሚል ነው ።

የልማታዊ መንግሥት ፤ ማርክሲስታዊ በእሚመስለው ፀረ ትርፍ ግንዛቤው ፤ በሕጋዊ የንግድ ልውውጥ የእሚገኘውን ትርፍ መፈለግ እንደ ማሕበራዊ እድገት ማነቆነት ብቻ ሰአይሆን የእሚመለከተው ፤ በንግድ የእሚገኝ ኢከነሚያዊ ትርፍን መጸየፍ ፤ ትክክለኛው ለፖለቲካ ስልጣን መብቂያ መስፈርት እንደ ሆነ አድርጎ ነው ፦

“በልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ ዙሪያ የተጻፉ ጽሁፎች ፤ ልማታዊ መንግሥትን ከደካማ (በንግዱ ማሕበረሰብ እና በፖለቲካ ሊህቃን ለእሚደርስበት ጫና የእሚያጎነብስ) ወይንም በዝባዥ መንግሥት (የሕዝብን ኃብት ለግል ጥቅም የመበዝበዝ እና የማባከን ዝንባሌ የአለው) መንግሥታት ጋር በአንጻራዊነት ይቀመጣል ።”

“In the literature, it is also contrasted with weak states (that easily bow to the pressure mounted on them by the business or political elite) or predatory states (that tends to be extractive and exploitative of public resources for private purposes). [81]“

ከእዚኽም የተነሳ የልማታዊ መንግሥት ትርክቱን ፦ መንግሥት ወይንም የልማታዊ መንግሥት ባለ ስልጣናት ፤ የንግድ ትርፍ የእሚጠየፉ እና በኢከነሚያዊ አርበኝነት ራሳቸውን እየጎዱ ለሕዝብ የእሚሰሩ አልሚ ስለሆኑ ፤ ልማት ተፋፍሞ ሐገር በኢከነሚ እስክ ትጠነክር ፤ በእነዚኽ መንግሥታዊ “መነኮሳት” የተገነባው መንግሥት እኩል ነጻነት በአላቸው ዜጎች በምርጫ ከስልጣን የእማይወርድ ሆኖ መቆየት አለበት ፤ ምክንያቱም ፦ በምርጫ ከተወገደ ይኽንን በመሰዕዋትነትን የጀመረውን የልማት ሥራ ማስቀጠል አይችልም በእሚል አስተሳሰብ የተቃኘ ነው ።

በእርግጥ ፤ ከስሙ እንደ እምንረዳው ፤ ልማታዊ መንግሥት የእሚለው ስያሜ ፤ ራስን የማዋደድ የፕሮፖጋንዳ ህፀፅ በውስጡ እንደ አለው መገመት ይቻላል ። ምክንያቱም ፦ የለየለት የጥፋት ኃይል ከአልሆነ በዘመናዊ የመንግሥት ግንዛቤ ፤ የልማት እንቅፋት መንግሥት የእሚባል መንግሥት የእማይታሰብ ነው ወይንም እንደ ማንኛውም አዎንታዊ ማሕበራዊ ተቋም ኹሉ መንግሥት ፤ የዜጎችን ኢከነሚያዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ሰብዓዊ ልማት ለማረጋገጥ የእሚቋቋም መሆኑ ሰፊ ሕዝባዊ መግባባት የአለበት ጉዳይ ነው ።

ከእላይ እንደ ተቀመጠው ፤ ምንም እንኳን ለጥቂት ቡርዥዋ (ባለኃብት እና ምሁር) ስለ እማናጎበድድ ፣ የሕዝብን ኃብት ለግል ጥቅም የመመዝበር እና የማባከን አካኼድን ስለ እምናወግዝ እና ትርፍን በእሚጸየፉ የንግድ/የልማት ተቋማት ውስጥ ተሰማርተን ለመሥራት የእሚያበቃ ስነምግባር ስለተላበስን ነው ራሳችንን ልማታዊ መንግሥት የእምንለው ቢሉም ፤ እውነታው ግን የዋሽንግተን ስምምነት ወይንም ኒዮሊበራሊዝም የእሚባለውም ሆነ የማሕበራዊ ደህንነት መንግሥት (welfare state) የእሚባሉት የመንግሥት አስተሳሰቦችም ፤ ፈጣን ፣ ‘ፍትሐዊ’ ፣ ከሙስና እና ምዝበራ የፀዳ እና በጥቂት ሰዎች ስግብግብ ጥቅም ፍላጎት የእማይዘወር የኢከነሚ እድገት ማስመዝገብ ዋነኛ የፖሊሲ ግባቸው ነው ምንም እንኳን እነ እዚኽ የኋለኞች ስረዓት አቀንቃኞች የተሻለ የኢከነሚ ሳይንስ ግንዛቤ ስለ አላቸው ኢከነሚያዊ ትርፍ በራሱ ርካሽ እና ልዕንጸየፈው የእሚገባ ነገር እንደ አልሆነ መቀበላቸው ከዓይነተኞቹ ልማታዊያን የእሚለያቸው ቢሆንም።

በአጠቃላይ ፥ የእሚታወቁት የመንግሥት አስተሳሰቦች ፤ ከምዝበራ የፀዳ ፍትሐዊ እና ፈጣን ኢከነሚያዊ እድገት ማስመዝገብ የፖለቲካቸው ዋነኛ ፥ የአንዳንዶቹም ብቸኛ ግብ ነው ።

ለምሳሌ ፦ የነፃነት ዴሞክራሲ የልማት ዋነኛ ግብዓት እንደ ሆነ በብዙ ዓለም ዓቀፍ እርዳታ ሰጭዎች ዘንድ የእሚንጸባረቅ እምነት ነው ፦

“… በእርዳታ ሰጪዎች ክበብ አከባቢ … የነፃነት ዴሞክራሲ ለልማት ዓይነተኛ አነቃቂ ነው የእሚል አዎንታዊ ምልከታ አለ ።”

“…there is an optimistic view, common among aid circles …, that liberal democracy is a powerful stimulus to development … [82]“

ስለ እዚኽ ልማትን ግብ ማድረግ ፤ የልማታዊ መንግሥታት ብቻ ልዩ መለያ ተድርጎ የእሚወሰድ በአለ መሆኑ ፤ ልማታዊነትን ከሌሎቹ መንግሥታት ዓይነቶች የተለየ መለያ ማድረጉ በበቂ አሳማኝ ምክንያት ላይ የተደገፈ አይደለም ።

ከግብ አንፃርም ብቻ ሰአይሆን ፤ ልማታዊያን መንግሥትታ ፤ ምዝበራን ፣ ብክነትን ፣ ኃላፊነት አለመወጣትን እንታገላለን ፤ ስለ እዚኽም ልማታዊያን ነን ማለታቸው ፤ ከሌሎች ወይንም ከጠቅላላው መንግሥት ከእሚታወቅበት መገለጫ የተለየ በአለመሆኑ ፤ ልማታዊያን መገለጫችን ነው የእሚሉት የልማት አርበኝነት ለልማታዊያን የተተወ ወይንም ልማታዊያን የእኛ ብቻ መገለጫ ነው ሊሉት የእሚችሉት ጉዳይ አይደለም ።

ይልቁንም በማንኛውም የሰው ልጅ ተቋም ውስጥ በኃላፊነት የእሚቀመጥ ሰው (ወይንም ሰዎች) ፦ ደካማ አፈፃፀም ሊኖረው ፣ መዝባሪ ሊሆን ወይንም በተቃራኒው ጥሩ አፈፃፀም የአለው እና ከምዘበራ የራቀ ሰው ሊሆን ይችላል ።

ስለ እዚኽ ፦ አንድ መንግሥት የትኛውንም የስነ መንግሥት ቲየሪ ቢከተል ፤ ቲየሪው ወደ ተግባር በእሚወርድበት ግዜ አስፈፃሚዎቹ ፤ ደካማ ፣ መዝባሪ ወይንም ብቁ እና ኃቀኛ አስፈፃሚ መሆናቸው አይቀርም ፤ ሰዎች ስለ ሆኑ ።

አይ እኔ ወይንም እኛ ፤ ኃላፊነታችንን በአግባቡ የእምንወጣ ብቻ አይደለንም ፤ ነገር ግን ፦ እንደ ሰው ድካም እና ጥንካሬ የአለን ሰአይሆን ጥንካሬ ብቻ የአለን ፣ የግል ፍላጎት እና ጥቅም የእማይገዛን ልዩ ፍጥረት ነን ማለት ከሆነ ልማታዊያኑ የፈለጉት ፤ ይኽ የእሚታወቀው ፤ የፖለቲካዊው ሰው ስብዕና በአለመሆኑ ፤ ለየት ባለ ኃይማኖታዊ (የልዕለ ተፈጥሮ ትንታኔ ወይንም ሜታፊዚካል (Metaphysical) ዘርፍ የእሚመደብ) እንቅስቃሴነት እንጂ በሰው ፖለቲካ መፈረጅ የለበትም ።

በስተመጨረሻም ፤ የኢከነሚ ፖሊሲ የሌለው መንግሥት በአለመኖሩ ፤ ዓይነቱ ይለያይ እንጂ የመንግሥት ኢከነሚያዊ ጣልቃ ገብነት የእማይቀር ነገር በመሆኑ ፤ በኢከነሚ ውስጥ የእሚደረግ ስልታዊ እና ኢከነሚያዊ እምርታን ታሳቢ የአደረገ ፤ ጣልቃ ገብነትን እንደ እንድ ልዩ መለያ በመውሰድ ፤ በኢከነሚ ውስጥ ስልታዊ ጣልቃ ገብነት ስለ እምናደርግ ልማታዊ ነን ማለትም የእሚቻል አይደለም ።

ለምሳሌ ፦ በዘመናችን የንግድ ጦርነት በእሚለው እሳቤ መሠረት ፤ አንዳንድ መንግሥታት ፤ የሐገራቸው አምራቾች በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆነው እንዲያሸንፉ ፤ ግብር ይቀንሳሉ ፣ ኪሳራ ይሸፍናሉ ፣ በጀት ይደጉማሉ ፣ ወዘተ ። ከእዚኽም የተነሳ ፤ ከእነ እዚኽ ከገበያ መርህ ውጭ ፤ ከፍተኛ መንግሥታዊ ድጎማ ከአለባቸው ሐገራት የእሚመጡ ምርቶች ላይ ፤ ተቀባይ ሐገራት ከፍተኛ የገቢ ቀረጥ ይጥላሉ ወይንም በገበያው ውስጥ ጣልቃ እየገቡ አንዳንዱን እቃ ውድ ያደርጉታል ወይንም ርካሽ ያደርጉታል ።

እነ እዚኽ መንግሥታት በገበያው ውስጥ ፤ ሐገር በቀል አምራቾችን ከውጭ በመሰል መንግሥት ጣልቃ ገብነት ‘ርካሽ’ እንዲሆኑ ከተደረጉ ሸቀጦች ለመከላከል የእሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት ፤ ልማታዊ መንግሥት አያስብላቸውም ወይንም መንግሥት በኢከነሚ ውስጥ የእሚያደርገው ጣልቃ ገብነት ኹሉ መንግሥትን ልማታዊ አያስብለውም ፤ ስለ እዚኽ በኢከነሚ ላይ ስልታዊ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የልማታዊ መንግሥት ብቻ መገለጫ አይደለም ።

በአጠቃላይ ለልማት የእማይሰራ ፣ በኢከነሚ ውስጥ ልማትን ታሳቢ አድርጎ ጣልቃ የእማይገባ ፣ የተለያዩ ሙሰኛ የተፅዕኖ ቡድኖችን የእማይታገል ፣ ሙስና እና ምዝበራ ፈተና ያልሆነበት መንግሥት ፤ የሰው መንግሥት በዓለም ላይ ከሌለ ፤ አንድ መንግሥት እነ እዚኽን አደርጋለሁ እና ከሌሎቹ መንግሥታት ዓይነቶች ተለይቼ ልማታዊ መንግሥት ተብዬ ልጠራ ይገባኛል እንዲል የእሚያስችለው አንድም አሳማኝ የኢከነሚ ወይንም የልማት አጀንዳ የለም ።

ከፕሮፖጋንዳ ፋይዳው ያለፈ ፤ ልማትን ግብ ማድረግ ፤ ይኽንንም ልማት ለማሳካት ፤ ምዝበራን ፣ ደካማ አፈፃፀምን እና ብክነትን መከላከል የተለየ የልማታዊያን መንግሥታት መገለጫ በአይሆንም ፤ እነ እዚኽን ኢከነሚያዊ ግቦች ለማሳካት ፤ የእማይከሰስ ፣ የእማይለወጥ እና ተቀናቃኝ የሌለው ‘የተራዘመ’ የፖለቲካ ስልጣን ያስፈልገናል ብለው ማቅረባቸው ወይንም ፈጣን ኢከነሚያዊ እድገትን ለማሳካት አምባገነናዊ የመንግሥት ስልጣን ያስፈልገናል ማለታቸው ነው እውነተኛው የልማታዊ መንግሥታት ትርክት መገለጫ።

ከእዚኽም የተነሳ ፤ የልማታዊ መንግሥታት ትርክት ልዩ መገለጫ ፤ ልማትን ምክንያት የአደረገ ኢከነሚያዊ እና ፖለቲካዊ አምባገነናዊነት ነው።

ስለ ልማታዊ መንግሥታት ተፈጥሮዋዊ አምባገነንነት አንድ ጥንታዊ ጽሑፍ እንደ እዚኽ ይላል፦

“…እነርሱ (የምሥራቅ ኤስያ ልማታዊ መንግሥታት) እንደ እዚኽ ያለ መጠነ ሰፊ የተራዘመ ጣልቃ ገብነት ማድረግ የቻሉት ፤ በጣም የደረጀ አምባገነናዊ አገዛዝ ስለ ነበራቸው እና ምንም ዓይነት ሕዝባዊ አፈንጋጭነትን ስለ እማይፈቅዱ ነበር (የነጋዴዎች ማሕበር በተለይ የተከለከሉ ነበሩ ) ።”

“… They (East Asian Developmental States) were able to sustain such extensive state involvement for a prolonged period has been ascribed to a system of highly authoritarian rule and intolerance of public dissent (trade unions, in particular, were disallowed). [80]“

ስለ እዚኽ የልማታዊ መንግሥት ትርክት ፤ ኢከነሚያዊ ልማትን ሰበብ የአደረገ የፖለቲካ ስልጣን ሞኖፖሊ ትርክት ነው ።

ይኽ የስልጣን ሞኖፖሊን ትርክት ፤ ካባ፟ው እየተገፈፈ አምባገነናዊነቱ እርቃኑን እየታየ ሲመጣ ፤ ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት በእሚል ለማለዘብ የእሚደረግም ሙከራ የሞከሩ አሉ ። ይኽ ማለዘቢያ ግን ፤ ዞሮ ዞሮ ሐቁን አይቀይረውም ።

ምክንያቱም ፦ የዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ የእሚፈልገው ፤ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ኹል ግዜ እያሸነፈ መቀጠል የእሚችል ‘አውራ’ ፓርቲ የመፍጠር ኺደት ነው ። በሌላ አገላለፅ ፤ ከስልጣን የእሚያወርደው ወይንም ‘ለልማት’ ሲል እንደ ፈለገ የእሚያዝበትን የስልጣን የበላይነት የእማይነካበትን የመድብለ ፓርቲ እና የምርጫ ስረዓት የማቆም ኺደት ማለት ነው ። ያም ማለት ፤ ይኽን ቅድመ ኹኔታ የእሚፈታተን ዴሞክራሲ ከመጣ ልማታዊው መንግሥት ወደ ተፈጥሮዋዊ ፀረ ዴሞክራሲያውነቱ ይመለሳል ማለት ነው ።

ስለ እዚኽ ፦ ልማታዊ መንግሥት እንደ መንግሥታዊ ትርክት ፤ ከፊቱ ዴሞክራሲያዊ የእሚል ቅጥያ ገባበትም አልገባበትም ፤ የእማይከሰስ ፣ የእማይለወጥ እና የእማይከፋፈል የፖለቲካ ስልጣን ማስቀጠያ ትርክት ነው ።

ይኽም የልማታዊያን መንግሥት ትርክት ፤ ዜጎች በተፈጥሮ እኩል ነጻ በመሆናቸው ፤ የፖለቲካ ስልጣን ምንጭ እና ፋይዳ ፤ ከእዚኽ የዜጎች ተፈጥሮዋዊ ነጻነት የተነሳ በዜጎች ሆንታዊ ምርጫ የእሚመጣ እና ፋይዳውም የዜጎችን በህይወት የመኖር መብት እና ንብረትን የማስጠበቅ ሥራ መሥራት ነው የእሚለውን ብኺል ወይንም የእዚኽ ብኺል መሠረት የሆነው የዜጎችን የማሕበራዊ አህድነት መርሕ የእማይቀበል ያደርገዋል።

በስተመጨረሻ ፤ በሳይንሳዊው በአልኩዋቸው ወይንም መንግሥትን የስልጣን ተቀባይነት የእሚያገኝበትን ፣ በማሕበረሰብ ውስጥ የአለው እና ሊኖረው የእሚችለውን ድርሻ ወይንም ሚና እና የመንግሥትን የስልጣን ድንበር ሳይንሳዊ ጥያቄዎችን ጠይቆ በመመለስ ላይ የእሚንተራሱ ፤ የመንግሥት ትርክት ጎራዎች ፤ የመጨረሻው የነፃነት ዴሞክራሲ (Liberal Democracy) ነው ።

ቀደም ብለን እንደ አልነው ፤ በታሪክ እንደ እሚታወቀው ፤ ዴሞክራሲ በሺ የእሚቆጠሩ ዘመናት ዕድሜ የአለው ጥንታዊ የመንግሥት አወቃቀር መንገድ ቢሆንም ፤ የአወቃቀሩ ፍልስፍናዊ መሠረት ዳብሮ ተጓዳኝ ችግሮችን መፍታት በእሚችልበት ደረጃ በአለመድረሱ ፤ ተራ ግዜያዊ እና ኹኔታዊ ማበር የእሚፈጥረው መንግሥት ማዋቀሪያ በመሆን ፤ ቀጣይነቱ በወቅታዊ የኃይል አሰላለፎች የእሚወሰን የነበረ ፤ አንዳንዴም የመንጋነት አደጋ የእሚያጋጠመው የነበረ ነው ።

በዘመነ ሳይንስ ግን ፤ የዴሞክራሲ ሳይንሳዊ መሠረት ዳብሮ እና አወቃቀሩ ተጓዳኝ ችግሮችን ሊፈቱ በእሚችሉበት ኹኔታ ስለ ተደረገ ፤ በግዜያዊ ኹኔታዎች የእሚገደብበት አጋጣሚ ከአልሆነ ሳይንሳዊ አማራጭ የአልተገኘለት ዘላቂ የሐገር ማዋቀሪያ እና ማስተዳደሪያ መንገድ ሆኗል ።

የነፃነት ዴሞክራሲ መንግሥት ትርክት ፤ ሦሥት ቀላል እና ግልፅ በሰው ተፈጥሮዋዊ ባሕሪ ላይ ተመስርተው የእሚከሰቱ ኹኔታዎችን በማስቀመጥ ፤ እነ እዚኽን ከሰው ተፈጥሮዋዊ ባሕሪ የእሚመነጭ ኹኔታዎች የአላቸው ትሥሥር እና መስተጋብር የመንግሥት መመሥረቻ እና የመንግሥትን ተቀባይነት ማረጋገጫ ይአደርጋቸዋል ።

የነጻነት ዴሞክራሲ መንግሥት ትርክት ፤ ከእዚኽ በታች ጠቅለል ብለው በተቀመጡት ነጥቦች መገለጽ ይችላል ፦

  • ሰው በተፈጥሮው እኩል ነጻነት አለው ፤ ይኽንም ነጻነቱን በህይወት ለመቆየት እና ኑሮውን ለማሻሻል ይጠቀምበታል (የተፈጥሮ ነጻነት) ፤
  • ይኽ በኹሉም ዘንድ ያለ እኩል ነጻነት ግን በተፈጥሮ ሕግ ከአልተገራ የሰውን በማሕበረሰብ ውስጥ በህይወት የመቆየት እና ኑሮን የማሻሻል ግብ ያሰናክላል (የተፈጥሮ ኹኔታ) ፤
  • ሰውም በአመዛዛኝ አዕምሮው ተመርቶ ፤ የተፈጥሮ ነጻነቱ የጉዳቱ ምክንያት እንደ አይሆንበት ፤ ወደ ተፈጥሮ ሕግ በመድረስ ፤ የተፈጥሮን ሕግ አክብሮ የእሚያስከብር መንግሥት ያቋቁማል ወይንም ማሕበራዊ ውል ያሥራል (የተፈጥሮ ሕግ)፤

የእሚሉ ናቸው።

በሳይንሳዊ የነፃነት ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ፤ ሰው እንደ ማንኛውም ህይወት የአለው ፍጥረት ፤ በህይወት የመኖር ወይንም የመቆየት ደመ ነፍሳዊ ፍላጎት አለው ። ከእዚኽ በመቀጠለም ፤ ራሱን በህይወት ለማቆየት እና ህይወትን ለማጣጣም ፤ የእሚችለውን ፣ ይገባል ወይንም ይበጃል የአለውን ነገር ለማድረግ የማንንም ፈቃድ እንዲጠይቅ የእሚያስገድደው ምንም ዓይነት ተፈጥሮዋዊ አስገዳጅ ኹኔታ የሌለበት በመሆኑ ፤ ተፈጥሮ ከአስቀመጠችበት ገደብ ውጭ ፤ በተፈጥሮ እኩል ነጻ ነው።

ኹሉም ሰው በህይወት መኖር መፈለጉ እና በህይወት ለመኖርም በእሚመስለው መልኩ የመንቀሳቀስ ነፃ ፍቃድ እና በህይወት ለመኖር የእሚያስችሉ ክህሎቶች የተገናፀፈ መሆኑ ፤ ይኽ ተፈጥሮዋዊ ነፃነት እና ችሎታ ፤ በአመዛዛኝ አዕምሮ ወይንም ዘላቂ ጥቅምን ታሳቢ በአደረገ ኹኔታ ከአልተመራ ወደ ግጭት እና ብጥብጥ ያመራል ።

ሰው ግን ተፈጥሮዋዊ የማገናዘብ ችሎታ ስለ አለው ፤ የእርሱ ነፃነት የሌላውን ሰው ነፃነት እንደ አይጋፋ ፥ የሌላም ሰው ነፃነት የእርሱን ነፃነት እንደ አይጋፋ ወይንም ኹሉም የራሱን ብቻ በእሚያስብበት ኹኔታ ስረዓት አልበኝነት እንደ አይነግስ እና የመኖር ህልሙ አደጋ ውስጥ እንደ አይገባ ፤ ነፃነት የግጭት ሰአይሆን የትብብር መንሴ እንዲሆን ማሕበራዊ ውል ያሥራል ።

ይኽ ማሕበራዊ ውል በስህተት ወይንም ሆን ብለው ውሉን በእሚያፈርሱ ሰዎች ተፈፃሚነቱ አደጋ ውስጥ እንደ አይገባ ፤ መንግሥትን የእዚኽ ማሕበራዊ ውል አስከባሪ ወይንም አስፈፃሚ አድርጎ በአብላጫ ድምፅ ይሾመዋል ። ስለ እዚኽ ፦ በነፃነት ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ፤ መንግሥት ሌላ የውጭ ኃይል ሰአይሆን ማሕበራዊ ውልን የእሚንከባከብ የሕዝብ ተወካይ ነው ።

ይኽ የተፈጥሮ ሕግ ወይንም የሰውን በህይወት የመኖር ተፈጥሮዋዊ ፍላጎት ለማሳካት ሰው ይበጃል የአለውን የማሰብ እና የማድረግ ተፈጥሮዋዊ ነፃነት እና ህይወቱ እንዲሁም ለህይወት የእሚያስፈልጉት ነገሮች አደጋ ላይ ሲወድቁ የመከላከል ተፈጥሮዋዊ ነፃነት ወደ ስረዓት አልበኝነት እንደ አያመራ ፥ አመዛዛኙ ሰው ፡ ይኽ ተፈጥሮዋዊ ነፃነቱ የሌላውን ሰው ተመሳሳይ ነፃነት እንደ አይጋፋ ፥ የሌላውም ሰው ተመሳሳይ ነፃነት የእርሱን ነፃነት እንደ አይጋፋ የእሚደርስበት መግባባት ፤ የአንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ፤ ከፍም ዝቅም ሊል የእማይችል ፤ ቋሚ እና የፀና መሠረት እና የህልውናውም ምክንያት ነው ፤ የእሚል ነው የነፃነት ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ወይንም ትርክት።

የአንድ ሐገርም ሕገ-መንግሥት ይኽ ፤ የተፈጥሮ ሕግ ወይንም ማሕበራዊ ውል ፤ በጠራ እና በቀላሉ ሰዎች ሊገነዘቡት በእሚችሉበት አኳኋን የእሚገለፅበት የውል ሰነድ ማለት ነው ። መንግሥትም የእሚዋቀረው ይኽንን ውል ሳይሸራረፍ ማክበር እና ማስከበር እንዲችል ነው ። ማለትም ፥ የተለያዩ የመንግሥት አካላት ሲዋቀሩ የእዚኽን ማሕበራዊ ውል ወይንም የተፈጥሮ ሕግ መንፈስ በእማይጣረስ ፣ በእማይቀለብስ እና በእማያስት ይልቁንም በእሚያከብር እና በእሚያስከብር አግባብ ነው ።

ይኽ ማሕበራዊ ውል ወይንም የተፈጥሮ ሕግ ፤ የመንግሥት መነሻም መድረሻም ነው ። ስለ እዚኽ መንግሥት ጦር ቢገነባ የእሚገነባው ይኽንን ቅዱስ ውል ከውጭ ወራሪ ለመጠበቅ ነው ፣ የስለላ ድርጅት ቢያቋቁም በእዚኽ ቅዱስ ስምምነት ላይ ከውጭም ከውስጥም ሊመጡ የእሚችሉ አደጋዎችን ለማነፍነፍ ነው ፣ የሐገር ውስጥ ፖሊስ ቢገነባ ይኽንን ቅዱስ ማሕበራዊ ስምምነት በመጣስ የአንዱን ወይንም የተወሰኑትን አባላት የእሚጎዱትን ስረዓት ለማስያዝ ነው ፣ ፍርድ ቤት ቢያቋቁም ይኽ ቅዱስ ውል ያከበረውን ተፈጥሮዋዊ መብቴ ተገፏል የአለውን ሰው ሙግት ለመዳኘት ነው ፣ ፓርላማ ቢያቆም ሕግ አውጪዎች ይኽን ማሕበራዊ ውል ሳይሸራርፉ ተጨማሪ ሌሎች እሴቶችን እንዲጨምሩ ነው ፤ በአጠቃላይ ኹሉም ነገር በእዚኽ ቅዱስ ስምምነት ዙሪያ ያጠነጥናል ፦

“አባላቱን እና ንብረታቸውን ከጉዳት የሚጠብቅ አንድ ማሕበር መመሥረት ፤ ይኽንም በማድረግ ፤ እንደ ማሕበር አንድ ሆነው ሲተባበሩ ፤ ተፈጥሮዋዊ ነፃነታቸው ግን እንደ ተጠበቀ ሆኖ ራሳቸው የራሳቸው አለቃ ብቻ እንደሆኑ ይቀጥላሉ”

“Find a form of association that will bring the whole common force to bear on defending the protecting each associate's person and goods, doing this in such a way that each of them, while unitting himself with all, still obeys only himself and remains as free as before. [47]“

የትኛውም መንግሥት ይኽንን ማሕበራዊ ውል ወይንም የተፈጥሮ ሕግ የማሻሻል ፣ የመቀየር ወይንም ችላ የማለት መብት የለውም ።

በዋናነት የትኛውም መንግሥት ፤ ይኽንን ውል ለማክበር እና ለማስከበር ይቋቋማል ፤ ስልጣኑም የእዚኽ ማሕበራዊ ውል ወይንም የተፈጥሮ ሕግ ድንበር ላይ ያቆማል ፤ ለእዛም ነው ሕገ-መንግሥት የሕጎች ኹሉ የበላይ የእሚሆነው እና የትኛውም በአንድ ሐገር ውስጥ የአለ፟ የሕግ አካል ፤ ከሕገ-መንግሥቱ የእሚፃረር ሕግ ማውጣት ወይንም መተግበር የእማይችለው ፤ ሕገመንግሥቱ የተፈጥሮው ሕግ አካዊ አምሳል (embodiment) ነውና።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ፣ የሕዝብ ማሕበራት ፣ የሞያ ማሕበራት ፣ ወዘተ ፤ ይኽ ተፈጥሮዋዊ ሕግ ወይንም ማሕበራዊ ውል በእሚያከብርላቸው መብት ተጠቅመው እና በእሚያስቀምጥባቸው ግዴታ ተወስነው ወይንም ይኽን ሕገ-መንግሥት ፥ የተፈጥሮ ሕግ ፥ ማሕበራዊ ውል አክብረው ወይንም እንቅስቃሴያቸው የእዚኽን ማሕበራዊ ውል ድንበር የእማይጥስ ሆነው የተሻለ የፖሊስ አማራጭ ፣ የተሻለ ምርት ማሳደጊያ ስልት በመቀየስ ፣ የተሻለ የግንባታ ዘዴ በማስተዋወቅ ፣ የተሻለ የማስፈፀም ብቃት በማሳየት ፣ ወዘተ ፤ ራሳቸውን ከተፎካካሪያቸው የተሻለ አድርገው ለማቅረብ ሊሰሩ ይችላሉ ፤ ከእዚያኽ ውጪ ግን ፤ ይኽን የተፈጥሮ ሕግ ወይንም ማሕበራዊ ውል ከማክበር እና ከማስከበር ውጪ በምንም መልኩ በተፃፃሪነት መቆም አይችሉም ።

ምክንያቱም ፦ ሰው ህይወቱን እና ንብረቱን ፤ ከሕገ-ወጥነት አደጋ ከመከላከል የአለፈ የፖለቲካ ስልጣንን የእሚፈልግበት ወይንም የፖለቲካ ስልጣንን በውክልና ለሌሎች የእሚሰጥበት ሌላ ተቀባይነት የአለው ምክንያት ስለሌለው ።

የነፃነት ዴሞክራሲ (Liberal Democracy) ማለት ይኽ ነው ።

በእዚኽም ምክንያት ፦ ዴሞክራሲ ማለት የአብዛኛው ሰው ድምፅ ወይንም የብዙኋኑ አገዛዝ ብቻ አይሆንም ። በኢትዮጵያ ውስጥ 100 ሚሊየን ሕዝብ ቢኖርና እና 99, 999, 999 (ዘጠና ዘጠኝ ሚሊየን ዘጠኝ መቶ ዘጠና ዘጠኝ ሺ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ዘጠኙ) ምርጫ አሸንፈው ፣ ወታደሩን ተቆጣጥረው ፣ መንግሥት መሥርተው ፣ ሕግ አውጥተው ከእነርሱ ጋር የአልሆነውን አንዱን ዜጋ ከማሕበራዊ ውሉ ወይንም ከተፈጥሮው ሕጉ ውጪ ፤ ህይወቱን ፣ ንብረቱን ወይንም ነፃነቱን እንዲያጣ ማድረግ አይችሉም ። ምክንያቱም ፦ በነፃነት ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ስልጣን ማሕበራዊ ውሉን ማስከበሪያ እንጂ ማፍረሻ መሳሪያ ስለ አልሆነ ።

የማሕበራዊ ውሉ ወይንም የተፈጥሮ ሕጉ ጥንካሬ ከማንኛውም ቡድን ጥንካሬ በላይ ነው ።

ጥያቄው በሆነ ታሪክ አጋጣሚ ሰዎች ይኽን የተፈጥሮ ሕግ ሊጥሱ ይችላሉ ወይንስ አይችሉም አይደለም ፤ ይልቁንም ልክ አንድ የፖለቲካ ማሕበረሰብ ፤ ይኽንን ማሕበራዊ ውል ወይንም የተፈጥሮ ሕግ ሲጥስ ፤ የተፈጥሮ ኹኔታ (State of War) ይፈጠራል ፤ በእዚኽም ዜጎች በተፈጥሮ ሕግ ፥ በማሕበራዊ ውል ወይንም በተለምዶ እንደ እሚባለው በሕግ የበላይነት መመራት አቁመው በበትር ወደ መመራት ገብተዋል ማለት ነው ። ሰዎች ፤ የመንግሥት ባለስልጣናትን ጨምሮ ማሕበራዊውን ውል ሲያፈርሱ ፤ የራሳቸውን የደህንነት ዋስትና ውል ቀደው በመጣላቸው ፤ ነገ ተመሳሳይ ነገር በራሳቸው ላይ እንዲሆን እየጋበዙ ነው ።

ዜጎች ሕጋዊ ከለላ ፣ የሕግ የበላይነት ፣ የተፈጥሮው ውል ፣ ማሕበራዊ ውል አለመከበሩን ሲያዩ ፤ ተፈጥሮዋዊ ህይወታቸውን እና ንብረታቸውን ከአደጋ የመከላከል ፍላጎታቸው እና ነፃነታቸው ፤ ራሳቸውን ከእንዲህ ዓይነቱ መንግሥት ፣ ማሕበር ወይንም ግለሰብ ለመከላከል በመሰላቸው መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ይአደርጋቸዋል ፤ ያን ግዜ የጦርነት ኹኔታ ተመለሰ ማለት ነው ።

ይኽም የማሕበረሰብ አህድ ከሆኑ ሰዎች ተፈጥሮዋዊ ባሕሪ እና ጥቅም ጋር የእሚዛመደው የነፃነት ዴሞክራሲ መርህ ፤ ማሕበረሰብ ማወቀሪያ ሲሆን ሕዝባዊ ጥበቃ እና ከለላ የአለው በመሆኑ ፤ በባሕሪው ፅኑ እና ቀጣይነት የአለው ይሆናል ።

ከእዚኽም የተነሳ ፤ በነፃነት ዴሞክራሲ ውስጥ ፤ ሕግ እና ስረዓት ከሰዎች በጎ ፍቃድ ወይንም ቅንነት ሰአይሆን ከመሠረታዊ ጥቅም እና ጉዳትን የማስላት አመዛዛኝነት የእሚመነጭ በመሆኑ የሕግ ማዕቀፉ አፈንጋጮችን እንጂ መላውን ማሕበረሰብ በማስገደድ ወይንም በማሳደብ ላይ ስለ እማይሰማራ ውጤታማነቱ ከፍተኛ ነው ።

መሠረታዊ የሆነው ደስታን ጨምሮ ህመምን የመቀነስ የሰው ፍላጎት ፤ የተፈጥሮ ሕግ ነፀብራቅ የሆነውን ማሕበራዊ ውል እንዲመርጥ በአመዛዛኝ አዕምሮው ግድ ይለዋል ፤ ምክንያቱም ፦ ማሕበራዊ ውሉ በእማይከበርበት ግዜ የእሚፈጠረው የተፈጥሮ ኹኔታ ወይንም የጦርነት ኹኔታ ፤ በተደጋጋሚ የጠቀስነውን ከታች የአለውን በቶማስ ሆብስ የተገለፀውን ስለ እሚመስል ፦

“... በእዚኽ ኹኔታ ውስጥ ፤ ሰው ትርፍ በእሚያስገኝ ማንኛውም ሥራ ላይ አይሰማራም ምክንያቱም ትርፉን ለመጠቀም ዋስትና ስለ እማይኖረው ። በእዚኽም ምክንያት ፣ በምድር ላይ ምንም የባህል መዳበር አይኖርም ፣ በንግድ ከውጭ ተገዝቶ የእሚገባ እቃ አይኖርም ፣ ጥሩ ህንጻ አይገነባም ፣ ትላልቅ ነገሮችን ከስፍራ ስፍራ የእሚያንቀሳቅሱ ማሽኖች አይኖሩም ፣ በምድር ኹሉ ላይ እወቀት አይበዛም ፣ ግዜ ትሩጉም የለሽ ይሆናል ፣ ኪነጥበብ አያድግም ፣ ትምህርት አይበዛም ፣ ማሕበረሰብ አይሰነብትም ፤ ከእዚኽ ኹሉ የከፋው ደግሞ ፤ ማብቂያ የሌለው ስጋት ፣ በአሰቃቂ ኹኔታ የመገደል አደጋ ማንዣበብ ፣ እና የሰው ህይወት ፤ ብቸኛ ፣ ነዳያን ፣ አስቀያሚ ፣ አውሬ መሰል እና አጭር ትሆናለች ።”

“In such condition there is no place for industry, because the fruit thereof is uncertain: and consequently no culture of the earth; no navigation, nor use of the commodities that may be imported by sea; no commodious building; no instruments of moving and removing such things as require much force; no knowledge of the face of the earth; no account of time; no arts; no letters; no society; and which is worst of all, continual fear, and danger of violent death; and the life of man, solitary, poor, nasty, brutish, and short [26]“

ይኽም በመሆኑ እስከ ዛሬ ከእሚታወቁት መንግሥታዊ ትርክቶች ውስጥ የነጻነቱ ዴሞክራሲ (Liberal Democracy) ብቻ ነው ፤ የዜጎችን የማሕበራዊ አህድነት ተቀብሎ የእሚያከብር ፤ የፖለቲካ ርዕዮት ሆኖ የተገኘው።

ስን አጠቃልል ፦ በእዚኽ ንዑስ ክፍል ላይ ፤ ከጥንታዊው ዓለም ስልጣኔ ጀምረን እስከ አለንበት ዘመናዊ ዓለም የነበሩትን ፤ ዋነኛ የነበሩ መንግሥት መመሥረቻ ትርክቶችን አይተናል ።

ሠንጠረዥ 5 ፡ 5 ሺ ዓመታት በላይ በቆየው የሰው ልጅ ፖለቲካዊ ታሪክ ውስጥ የተስተዋሉ ዋነኛ መንግሥታዊ ትርክቶች።

መጀመሪያ የዓየነው እና የጥንታዊ ዓለም ብቸኛ ሊባል የእሚችለው ትርክት የነበረው ፤ ዓምላካዊያን በአልናቸው መንግሥታት የእሚቀነቀነው እና በዋናነት ማን መንገሥ አለበት የእሚለው ጉዳይ ላይ የእሚያተኩረው እና የእሚነግሱት ዓምላክ የሆኑ ወይንም የዓምላክ ዘር የአለባቸው ሰዎች ናቸው የእሚለውን ነው።

ስለ እዚኽ ፦ የእነ እዚኽ መንግሥታት ተቀባይነት የእሚመጣው ሕዝቡ ከአለው በኃላዊ ኃይማኖት ስለ ሆነ ፤ ነገሥታቱ ዓምላክ ወይንም የዓምላክ ዝርያ የአለባቸው በመሆናቸው የእማይጠየቁ ፣ የእማይቀየሩ እና ብቸኞች ናቸው ።

ንግሥናቸውም ምንም ዓይነት ጥያቄ እና ምርምር የእማይደረግበት ፤ የእማይጠየቅ እና የእማይመረመር ዓምላካዊ ድንጋጌ ሆኖ ፤ ኹሉም ሰው ያለ ምንም ጥያቄ አሜን ብሎ የእሚቀበለው ነው ። ይኽ የመለኮታዊያኑ መንግሥታዊ ትርክት ፤ ለ 3 እና 4 ሺ ዓመታት በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በበላይነት የቆየ እና ምርምር ላይ ሰአይሆን በጥንታዊ አፈታሪክ ላይ የተመሠረቱ ባህላዊ ኃይማኖቶች ላይ የተመሠረተ በመሆኑ አንድ ራሱን የቻለ ጎራ አድርጌ ፤ ከሳይንሳዊው በተቃራኒ ባሕላዊ በእሚል ራሱን እንደ ቻለ አንድ ጎራ አቅርቤዋለሁ ።

ኹለተኛው ጎራ ፤ ሳይንሳዊ የመንግሥት ትርክት ጎራ ሲሆን ፤ ይኽ በዋነኝነት ፤ ከ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወዲህ የመጣ እና አመክንዮዋዊ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረቱን የእሚያካትት ነው ። ሳይንሳዊ ጎራ ውስጥ የአሉ፟ት የመንግሥት ትርክቶች ፦

  • የመንግሥት ስልጣን ምንጭ ምንድ ነው ?
  • የመንግሥት የሥራ ድርሻ እና የስልጣን ጥግ የት ነው ?
  • የመንግሥት መዋቅር ምን መምሰል አለበት ?

እና መሰል ጥያቄዎችን በመጠየቅ እና ለእነ እዚኽም ጥያቄዎች ፤ መንፈሳዊ መሠረት ቢኖራቸውም እንኳን በአመክንዮ የተደገፉ ያም ሳይሆን ደግሞ መንፈሳዊውን ትተው ወይንም ተቃውመው ፤ ሙሉ በሙሉ በአመክንዮ ላይ ብቻ የተመሠረቱ ትንታኔዎች በማቅረብ ፤ የፖለቲካ ርዕዮት ወይንም ትርክት በመፍጠር ላይ የተመሠረቱ ናቸው ።

በእዚኽ በሳይንሳዊ ጎራ የመጀመሪያ የዓየነው ፤ ስነመለኮታዊያኑን ሲሆን ፤ እነ እዚኽ ስነመለኮታዊያን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወይንም ሌሎች የተጻፉ ኃይማኖታዊ መጽሐፍትን እና ታሪካዊ ምንጮችን በማጣቀስ ፤ የስልጣን ምንጭ አንድ ዓይነት መለኮታዊ ሲመት ነው የእሚሉ ናቸው ።

ዓምላካዊያኑ ፤ ነገሥታቱን ዓማልክት ወይንም የዓማልክት ዝርያዎች ሲያደርጉ ፤ ስነ-መለኮታዊያኑ የነገሥታቱን ሰውነት ተቀብለው ፤ ነገር ግን በትውልድ ሐረጋቸው ወይንም እንደ እሚያምኑበት እምነት አንዳች ዓይነት አምላካዊ ቅባ ቅዱስ የተቀቡ ወይንም ለግዜው በአንዳች ዓይነት መንፈሳዊ መስፈርት መሠረት የተመረጡ ስለ ሆኑ ፤ ከሌሎች ሰዎች ተለይተው ንጉሥ እንዲሆኑ በአምላክ ተሹመዋል ይላሉ ፤ ልዩነታቸውም ነገሥታቶቻቸውን ወይንም መሪዎቻቸውን ዓምላክ በማድረጋችው እና ዓምላክ ሳይሆን በአምላክ የእሚሾም ሰው በማድረጋቸው ነው ።

ከስነ መለኮታዊያኑ በመቀጠል የአሉ፟ት በሳይንሳዊ ጎራ የእሚመደቡት ፤ አምባገነናዊ የማሕበራዊ ውል አስፈፃሚ መንግሥት ትርክት የእሚያራምዱት ናቸው ። በእነ እዚኽ ሰዎች ሙግት መሠረት ፤ የማሕበራዊ ውል ፤ የእማይከሰስ ፥ የእማይለወጥ አና ብቸኛ የስልጣን ባለቤት የሆነ ኃይል በሌለበት መከበር ስለ እማይችል ፤ ሰዎች ስረዓት አልበኝነት ከእሚያደርስባቸው ችግር ይልቅ አምባገነናዊ መንግሥት ሊያደርስባቸው የእሚችለው ችግር ስለ እሚቀል ፤ እንዲኹም አንዳንድ አምባገነናዊ ነገሥታት ይኽንን ንግሥናቸው በውል ያገኙት በመሆኑ ፤ በሐገር ውስጥ ጸጥታ እና ደህንነት እንዲከበር ፤ ሰይፍ የታጠቁ መንግሥታት ምንም እንኳን ከተፈጥሮ ሕግ አግባብ ውጭ ቢመጡምና ዜጎችን ቢበድሉም ፤ ውልን ለማክበር ሲባል እና ማንም በአመጽ ቢነሳባቸው ለመቅጣት የእሚያስችላቸው ሰይፍ እንዲጠቀሙ ስልጣን በውል ስለ ተሰጣቸው ፤ አምባገነንነታቸው በአይመችም በዜጎች ዘንድ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ አይገባም የእሚሉት ናቸው ።

በእነርሱ እምነት ፤ ማሕበራዊው ውል የእሚከበረው ከተፈጥሮዋዊ የኃይል ሚዛኑ ተነስቶ ሰአይሆን የእሚፈራ እና የውሉን ተፈፃሚነት የእሚቆጣጠር ውጫዊ ኃይል ስለአለ፟ ነው ፤ የእሚል ነው ። ወይንም ማሕበራዊው ውል በአመዛዝኖ የእሚመረጥ ሰአይሆን በውጫዊ የቅጣት ኃይል ፍራቻ የእሚከበር ነው ። እውነታው ግን ፥ በውጫዊ ኃይል አስገዳጅነት የእሚከበር ወይንም የእሚጫን ውል ፤ የጦርነቱን ኹኔታ ስለ እሚመልሰው ፤ አንድ ማሕበረሰብ ተገዶ እንዲያከብር የተደረገውን ውል ኃይሉ ሲበረታ ማፍረሱ አይቀርም ። ስለ እዚኽ የሕጉን ቀንበር ለመስበር የእሚደረገው መገለባበጥ ይቀጥላል ማለት ነው ።

የማሕበራዊ ውል ፍልስፍና ግን ፤ ሕጉ ተፈጥሮዋዊ በመሆኑ ፤ የእሚከበረው ወይንም ሕዝብ የእሚያከብረው ፤ ከማገናዘቡ የተነሳ ነው ወይንም እያንዳንዱ ጥቅሙን እና ጉዳቱን አስልቶ ማክበሩ የበለጠ እንደ እሚጠቅመው በማየት ነው ። እንደ እዚያኽ በአይሆን ወይንም ማሕበራዊ ውሉ ፤ በራሱ ወይንም በስሪቱ ከጉዳቱ ጥቅሙ በአይአደላ ኖሮ ተመራጭ አይሆንም ነበር ወይንም ሕዝባዊ መሠረት አይኖረውም ነበር ። የእዚኽ ማሕበራዊ ውል አስከባሪ የእሚሆነው መንግሥት የእሚመጣው ሕዝቡ ውሉን ስለ እሚመርጠው እና ስለ እሚፈልገው እንጂ ይኽ ማሕበራዊ ውል ሳይፈልገው በእርሱ ላይ የእሚጫንበት ስለ ሆነ አይደለም ።

የፖሊስ ኃይል በከተማ ውስጥ ስርቆትን የእሚከላከለው ፤ ሰው ኹሉ በመስረቅ ስለ እሚያምን ወይንም ኹሉም ሰው ሰራቂ ስለሆነ አይደለም ወይንም አትስረቅ የእሚለው ሕግ ፤ የሐገሬው ሕዝብ በሙሉ ሳይፈልግ በመንግሥት የመሳሪያ ኃይል የተጫነበት ሕግ ስለ ሆነ አይደለም ። መደበኛው ሰዋዊ ግንዛቤ ፤ መስረቅ የቻለ ይስረቅ የእሚል ኹኔታ ውስጥ ከመኖር ፤ እኔም ያንተን አልሰርቅም አንተም የእኔን አትስረቅ የእሚለው ኹኔታ ውስጥ መኖር በድምሩ የተሻለ ህይወት እና ንብረቱን ከአደጋ እንደ እሚከላከልለት ስለ እሚገነዘብ ነው ። ይኽ የማመዛዘን ፍርድ የእሚቀበለው የተፈጥሮ ሕግን እንዲያስከብር መንግሥት የእሚቆመው ፤ ሕጉ በእሚጣስበት ወቅት ተከታትሎ የእሚያስከብረው መኖሩ አስፈላጊ ስለ ሆነ ነው ።

ሕጉ ተፈጥሮዋዊ ቢሆንም መፈፀሙ ግን ተፈጥሮዋዊ አይደለም ወይንም በግንዛቤ ወይንም በትምህርት የእሚታወቅ እና በዜጎች ፈቃድ የእሚፈጸም ነው ። ያልተማረው ወይንም ያላወቀው ወይንም ይኽንን ሕግ በግድፈትም ወይንም በአንድም በሌላ ምክንያት ሕጉ የእሚያስከትለውን ጥፋት አመልጣለሁ ብሎ በማሰብ ከተለመደው መንገድ መውጣት ሲፈልግ ፤ የሕጉን ቅጣት በአግባቡ እንዲ ያስፍፅምበት ነው መንግሥት የእሚቆመው ። የተፈጥሮው ሕግ ኹሉም ሰው ወይንም ከፍተኛ መጠን የአለው ብዙኃኑ ፤ በአመዛዝኖ የእሚመርጠው በአይሆን ፤ መንግሥት ከሕዝብ በብዛት ከአልበለጠ ፣ እስር ቤቶች ከመኖሪያ ቤቶች በቁጥር ከአልበዙ ፣ ወዘተ ፤ መንግሥት ሕጉን ሊያስከብረው አይችልም ።

ከአስገዳጅ የማሕበራዊ ውል በመቀጠል ፤ በሳይንሳዊ ትርክቶች ፈርጅ በሦሥተኛነት ያየነው ፤ የሠራተኛው አምባገነንነት የእሚለውን ትርክት ነው ። ይኽ ትርክት በማርክሲስታዊ የታሪክ ዑደት ትንታኔ ፤ ወይንም ውኃ ከ100 ዲ.ሴ በላይ ሲሞቅ ይተናል እንደ እሚለው በእማይለወጥ የተፈጥሮ ሕግ ፤ በሰው ልጅም የታሪክ ኺደት ፤ ሠራተኛው የቡርዣውን ኃብት በአብዮታዊ አመጽ መቀማቱ የእማይቀር ስለ ሆነ ፤ ይኽንንም ኃብት ቀምቶ በዘላቂነት በእኩልነት እስኪ ያከፋፍለው እና ራሱን ከቡርዣ ስነልቦና አጽድቶ ከምኒስት እስኪሆን ፤ በታሪካዊ ወይንም ተፈጥሮዋዊ ሕግ አስገዳጅነት ሠራተኛው አምባገነን መንግሥት ይሆናል የእሚል ነው ።

የሠራተኛው አምባገነንነት የእሚለው ትርክት ፤ ሙሉ በሙሉ የማርክስን የታሪክ ቁሳዊነት ፍልስፍና ላይ የተመሮከዘ በመሆኑ ፤ የሠራተኛውን አምባገነንነት ትርክት ለመቀበል ፤ የታሪክ ቁሳዊነት ትርክትን መቀበል የግድ ይላል ። የካርል ማርክስ የታሪክ ቁሳዊነት ፍልስፍና ግን ታሪክ እስከ አኹን የመጣበት ኺደት ጋር ቀጥታ ስለ እሚጣረስ ሳይንሳዊ እውነትነቱ ከመጀመሪያውም ተቀባይነት ያጣ ነው ።

ለምሳሌ ፦ ማርክስ ፥ ዘመነ ባርነት ሲያልፍ ነው ዘመነ ፊውዳል የእሚመጣው ቢልም ፤ እነ እዚኽ ኹለት ስረዓቶች በጋራ የኖሩበት ታሪካዊ ወቅት ፤ ከጥንት እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ ፤ በታሪካዊ ማስረጃ ማጣቀስ ስለ እሚቻል ፤ መላምቱ ሳይንሳዊ ከመሆን ይልቅ የዘፈቀደ ድምዳሜነቱ ያደላል ።

አኹን በእምንኖርበት ዘመን ፤ በጣም ኋላ ቀር የኢከነሚ ደረጃ ላይ ከእሚገኙት አንስቶ እስከ በመረጃ ቴክኖሎጂ እና በአገልግሎት ሰጪነት ላይ ኢከነሚያቸው እስከ ተገነባባቸው የማሕበረ ኢከነሚ ደረጃ ላይ እስከ አሉት ሐገራት ውስጥ ከ30 ሚልየን በላይ ሰዎች በተለያየ ዓይነት ዘመናዊ ባርነት ፤ ማለትም ፦ ያለ ፈቃዳቸው እንደ እቃ የእሚሸጡበት ፣ ሥራቸውን በፈቃዳቸው መቀየር የእማይችሉበት ፣ ያለ ክፍያ የእሚሰሩበት ፣ በፈቃዳቸው ወደ ፈለጉበት የእማይንቀሳቀስቡት እና መሰል ቁጥጥር በሌሎች ሰዎች በህይወት ዘመናቸው ኹሉ የአለባቸው ፤ ሰዎች እንደ አሉ ብዙ ጥናቶች ያሳያሉ።

ይኽም ማለት ፤ ባርነት እንደ ስልተ ምርት እና የምርት ግንኙነት ፤ በተለያየ ኢከነሚያዊ መዋቅሮች ውስጥ እና ዘመን ሳይሽረው የኖረ አስከፊ ማሕበራዊ ችግር እንጂ ማርክስ እንደ እሚለው የመደብ ግጭት የወለደው እና ሕዝብ በወል የእሚሻገሩት የማሕበራዊ እድገት ደረጃ አይደለም ማለት ነው። ሶሻሊስት ሶቭየት ሕብረት ራሷ ፤ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን ጉላግ (Gulag) በእሚባለው እስር ቤት ያለ ፍትሐብሔር ወይንም ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ዳኝነት አጉራ ፤ እስኪ ሞቱ ድረስ እና ያለምንም የመብት ከለላ ፤ ከባርነት በእማይተናነስ ወይንም በከፋ ኹኔታ ያለ ክፍያ እየ አሰራች ጉልበታቸውን ስትበዘብዝ ነበር ።

ትሮትስኪ የእሚባለው እና በራሻ አብዮት ከሌኒን ያልተናነሰ ሚና የነበረው እና ራሱ እኔ እና ሌኒን በአንኖር ኖር አብዮት አይኖርም ብሎ የተናገረው ሰው ፤ ስለ እዚኽም በማርክሲዝም እውቀቱ እና በማርክሲዝም መሠረት በራሻ አብዮት ለማስነሳት እና የሶሻሊስቱን መንግሥት ለመመሥረት ከሌኒን እና ስታሊን የእማይተናነስ የአንበሳ ድረሻ የነበረውን ፤ ከሌኒን ሞት በኋላ ከጆሴፍ ስታሊን ጋር የስልጣን ግብግብ ውስጥ በመግባቱ ፤ ወደ ጉላግ ከመላ፟ክ በትግል አምልጦ ፤ የላቲን አሜሪካ ውስጥ ተሸሽጎ ሲኖር ፤ ስታሊን በላከበት ገዳዮች አናቱ በፋስ ተፈልጦ ፤ የሕክምና ርዳታ ሊታደገው ሳይችል ቀርቶ ሞቷል።

ሶቭየት ሕብረት ፤ በእዚኽ መልኩ ፤ አብዮት ልጆቿን ትበላለች በእሚል ብኺል ሳይቀር ፤ በሚልየን የእሚቆጠሩ ከቡርዣው ወይንም በራሻው ኩላኩ (Kulak) እስከ አብዮተኛው የአሉ፟ትን ኹሉንም ዓይነት ፖለቲካዊ በአላንጣዎች ፤ በእዚኽ መልኩ በጉላግ ውስጥ ያለፈቃዳቸው አጉራ ፣ በትንሽ ምግብ እጅግ አድካሚ ሥራ እንዲሰሩ ታደርግ ስለ ነበር ፤ ብዙዎች በእዚኽ አስቸጋሪ ኹኔታ ለእጅግ ከባድ የጉልበት ሥራ በመጋለጣቸው በሥራ ብዛት እንደ ሞቱ ብዙ ታሪካዊ ማስረጃዎች አሉ።

ይኽም ኹኔታ ፤ በማርክሲስታዊ አብዮት ወደ ሶሻሊዝም ተሻግሬያለሁ ስትል በነበረችው ሶቭየት ሕብረት ውስጥ ባርነት በጤና እና በሰላም ተደላድሎ ሲኖር የነበረ ለመሆኑ ማስረጃ ስለሆነ ፤ የሶቭየት ሕበረት ሕዝብ በማርክስ ቲየሪ መሠረት በአብዮት በወል ባርነትን እንደ አልተሻገረው ታሪካዊ ማሳያ ነው።

ይኽ የማርክሲዝም ስህተት ሳይሆን በወቅቱ የማርክሲዝምን አብዮት የመሩት ሰዎች ችግር ነው ሊባልም የእሚችል ታሪካዊ ክስተትም አይደለም ፤ ምክንያቱም ፦ በማርክሲዝም መሠረት ፤ ባርነትን መሻገር ወይንም ከአንድ የስልተ ምርት ወደ ሌላ ስልተ ምርት የእሚደረገው ሽግግር በመሪዎች ስብዕና ወይንም በሰዎች የፖለቲካ አስተሳሰብ የእሚወሰን ሰአይሆን በነባራዊ ቁሳዊ ኹኔታ አስገዳጅነት የእሚመጣ ነው ተብሎ የእሚቅርብ በመሆኑ ፤ ማንም ይኽንን የማርክሲዝም ርዕዮት መሠረታዊ ተፋልሶ ማሳያ ሊሆን አይችልም ብሎ ሊከራከራከር አይችልም ፤ ሶሻሊስታዊ አብዮት በተካኼደባት ምድር ላይ ባርነት በጉላግ ውስጥ በግልጽ ለዓመታት ቀጥሏልና።

የሰው ልጅ በምንም ዓይነት ቁሳዊ ኹኔታ ውስጥ ቢኖር ፤ ባርነትን ሊሻገረው አይችልም። ሊቀንሰው ፣ ሊቀጣጠረው እና ወንጀል ሊያደርገው ይችላል ፤ ባርነት እንደ ስልተ ምርት እና እንደ ማሕበራዊ ችግር ግን ከሰው ልጅ ማሕበረሰብ ውስጥ ሊጠፋ የእሚችል ነገር አይደለም። ልክ እንደ ወንጀል ፣ እንደ ድህነት ፣ እንደ ሱሰኝነት ፣ እንደ ጽንፈኝነት እና መሰል ማሕበራዊ ችግሮች የሰው ማሕበረሰብ እስከ አለ ይኖራል ፤ ቢያንስ እስከ ዛሬ የነበረው ወደ 5 ሺ ዓመታት ወይንም ከእዚያኽ በላይ የቆየው የሰው ልጅ ታሪክ የእሚያሳየው ይኽንን ነው።

ይኽም በመሆኑ ፤ ቀደም ብለን ቶማስ ማልተስን ጠቅሰን ፤ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ድምዳሜውን የእሚያግዙ ቅድመ ኹኔታዎች መዘርዘር ወይንም ድምዳሜ በታሪካዊ እውነታ ላይ መደገፍ አለበት የእሚለውን መሠረታዊ አመክኖዋዊ አስተሳሰብ መርኽ እንደ አሳየነው ፦

“ወደ አንድ ሙግት ውስጥ በእምገባበት ወቅት ፤ በሳይንሳዊ መርህ ላይ የእማይመሠረቱ ፤ በሬ ወለደ ወይንም አቡኑ ሰጡኝ ዓይነት መከራከሪያዎችን ከጥያቄ ማውጣት አለብኝ ። ሰው ኼዶ ኼዶ ፤ አንድ ቦታ ላይ ሰጎን ይሆናል ብሎ እንደ እሚያምን ፤ አንድ ሰው ሊነግረኝ ይችላል ። እንዲኽ የእሚለኝን ሰው በአግባቡ አይሆንም ብዬ ልሞግተው አልችልም ። ይኽን ዓይነቱ ሰው ግን ፤ የማመዛዘን አቅም የአለውን ማንኛውንም ሰው በኃሳቡ ከማሳመኑ በፊት ፦ የሰው አንገት ቀስ በቀስ እየሰለለ እና እየረዘመ መኼዱን ፥ ከንፈሩም እየጠጠረ እና እየሾጠጠ መኼዱን ፥ እግሩ እና እጁ በእየ ቀኑ ቅርፃቸው እየተለወጡ መሆናቸውን ፥ ፀጉሩም ወደ ላባ ሰበዝነት እየተቀየረ መሆኑን ማሳየት አለበት ።”

“In entering upon the argument, I must premise that I put out of the question, at present, all mere conjectures, that is, all suppositions, the probable realization of which cannot be inferred upon any just philosophical grounds. A writer may tell me that he thinks man will ultimately become an ostrich. I cannot properly contradict him. But before he can expect to bring any reasonable person over to his opinion, he ought to shew that the necks of mankind have been gradually elongating, that the lips have grown harder and more prominent, that the legs and feet are daily altering their shape, and that the hair is beginning to change into stubs of feathers. [20]“

ካርል ማርክስ ፤ ማሕበረሰብ ከባሪያ አሳዳሪ ወደ ፊውዳል ፣ ከፊውዳል ወደ ቡርዡዋ ፣ ወዘተ ፤ ነው የኼደው ካለ ፤ ታሪክ ይኽንን ኺደት መመስከር አለበት ። የታሪክ ኺደት ግን እርሱ የእሚለው ዓይነት ፍሰት ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃም ሆነ በተናጠል በአንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ውስጥ ፤ የሌለው መሆኑ እሙን ነው ። ስለ እዚኽ ፦ ከታሪክ ቁሳዊነት የእሚቀዳው ፤ ከካፒታሊዝም ወደ ሶሻሊዝም ለመሻገር ፤ የሠራተኛው አምባገነንነት መንግሥት የግድ ነው የእሚለው መንግሥታዊ ትርክት ሳይንሳዊ መሠረት የሌለው የደፈና ድምዳሜ ነው ።

ሳይንሳዊ በአልነው ፈርጅ ያሉት እነዚኹ ሦሥቱ የመንግሥት ትርክቶች ፤ በኃሳብ ሙግት ብቻ ሰአይሆን ፤ የአለከልካይ ተተግብረውም ፤ ማሕበራዊ ጤና እና እድገት ከማስመዝገብ ይልቅ እልቂት እና ሰቆቃ በማስከተል ሲወገዱ ፤ አራተኛው የመጣው ሳይንሳዊ ትርክት የልማታዊ መንግሥት ትርክት ነው ። የልማታዊ መንግሥት ትርክት ፤ በዓለም ላይ ከኢንደስትሪው አብዮት በኋላ በኃብታም እና ድኃ ሐገራት መካከል የተፈጠረው የብልፅግና ልዩነት ፤ በድኃ ሐገር የእሚገኙ መንግሥታት በኢከነሚው ላይ ቀጥተኛ እና ንቁ ተሳትፎ ካል አደረጉ ፤ ልዩነቱ ሊጠብ አይችልም ከእሚል አስተሳሰብ የእሚመነጭ ነው ።

ስለ እዚኽ ፦ በልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ ፤ በድኃ ሐገራት መንግሥት ይኽን የኃብት ደረጃ ልዩነት የማጥበብ ኃላፊነት ስለ አለበት ፤ ሰብዓዊ መብት እና ዴሞክራሲ ኹለተኛ ደረጃ አጀንዳ ሆነው መንግሥት ልማትን እስክ ያረጋግጥ ፤ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ቢኖርም በአይኖርም ፤ በምርጫ ከስልጣን መውረድ የለበትም የእሚል ነው ።

የዜጎችን የማሕበራዊ አህድነት ከመቀበል አንጻር ሲታይ ፤ ልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ የመንግሥትን ህልውና በዋናነት ፈጣን ማሕበራዊ ልማት ከማስመዝገብ ጋር ስለ እሚያይዘው ፤ የዜጎች ማሕበራዊ አህድነት ፤ ማለትም ፦ የዜጎች ተፈጥሮዋዊ መብት በተፈጥሮ ሕጉ ብቻ ሲገደብ ማክበር እና ማስከበር የእሚለውን ጉዳይ ብዙም ትኩረት የእሚሰጠው አይደለም።

በሳይንሳዊው ዘርፍ የመጨረሻው ያየነው መንግሥታዊ ትርክት ፤ የነፃነት ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት ትርክት ነው ።

በእዚኽ ትርክት መሠረት ፥ መንግሥት ፤ ዜጎች የተፈጥሮ ነጻነታቸው የአለ ተፈጥሮዋዊ ሕግ ገሪነት ከእሚፈጥርባቸው የተፈጥሮ ኹኔታ ለመውጣት በአመዛዛኝ አዕምሮዋቸው የተፈጥሮ ሕጉን በማግኘት ፤ ይኽን የተፈጥሮ ሕግ አክብሮ የእሚያስከብር ተወካይ አካል በማቋቋማቸው የእሚፈጠር ነው።

ተፈጥሮ ለዜጎች የአገናጸፋቸው ተፈጥሮዋዊ ነጻነት በዋናነት ሕይወታቸውን በእሚመስላቸው መንገድ እንዲመሩ እና ራሳቸውን ከጥቃት መከላከልን ታሳቢ የአደረገ ቢሆንም ፤ ይኽ የተፈጥሮ መብታቸው በጋራ በእሚኖሩበት ግዜ በተፈጥሮ ሕግ ከአልተገዛ ፤ ኹሉም የራሱን በእሚከታተልበት ግዜ ፤ የመብቱን ድንበር ተላልፎ የሌላውን ዜጋ ሕይወት እና ንብረት አደጋ ላይ እንድ አይጥል ፤ በዜጎች መካከል በተፈጥሮ ሕግ ማዕቀፍ ውስጥ የእሚያዳኝ ሦሥተኛ እና ገለልተኛ አካል አስፈላጊ ነው።

ይኽ የሦሥተኛ እና የገለልተኛ አካል ዳኝነት አስፈላጊነት ነው ፤ ለነጻነቱ ዴሞክራሲ የመንግሥት ጽንሰ ኃሳብ አንኳር።

የዜጎችን የማሕበራዊ አህድነት ከመቀበል አንጻር ሲታይ ፤ ከነጻነቱ ዴሞክራሲ ውጭ ፤ በባሕላዊውም ሆነ በሳይንሳዊ ጎራ ውስጥ ያሉት ትርክቶች በሙሉ ፤ የዜጎችን የማሕበራዊ አህድነት የእማይቀበሉ ናቸው።

  1. ይኽም ታሪክ ፕሌቶ ከሞተ ከ700 ዓመታት በላይ በኋላ በመሆኑ ፤ የእዚኽን ታሪክ ተዓማኒነት የእሚጠራጠሩ ሰዎች አሉ። ↑

  2. እግዚኣብሔር የእሚለው የአማርኛ ቃልም ፤ እግዚአ + ብሔር ፦ የዓለም ኹሉ ወይንም የብሔሩ ኹሉ (የሐገሩ ፣ የሕዝቡ ወይንም የዓለም ኹሉ) ጌታ የእሚል እና አዶናይ ከእሚለው የእብራይስጡ የአምላክ ስም ጋር የእሚዛመድ ነው። ↑

  3. የሐዋሪያው ጳውሎስ መልዕክት ወደ ገላትያ ሰዎች ምዕራፍ 3 ቁጥር 28። ↑

  4. ምንም እንኳን በእዚኽ ስቴድየማቸው ውስጥ የሮም ነዋሪዎች በመዝናኛነት ከእሚዩት ነገር አንዱ ሰዎች ከአውሬ ጋር እንዲ ጋጠሙ ተደርጎ ስጋቸው በአውሬዎሽ ሲበጣጠስ እና ሰዎች በተለያየ ስለት የታገዘ አሰቃቂ የመገዳደል ውድድር ሲያደርጉ መመልከት ቢሆንም። ↑

  5. ኼለናይዜሽን ፤ የግሪክን ቋንቋ ፣ ባህል እና ፍልስፍና የማስፋፋት ኺደት ነው። ↑

  6. የስኮላስቲክ ዘመን ጀመሪ ሰባዊያንን ነው። ↑

  7. ይስኃቅ ክብረ ነገስትን ፤ የቀድሞው የግዕዙ ጠፍቶ ስለ ነበር ፤ ከነበረበት ከአረብኛ ወደ ግዕዝ በ15ኛው ምዕተ ዓመት የተረጎመው ሰው ነው ። ↑

  8. ኔሮ በጣም ጨካኝ የሮማ ንጉሥ ስለነበር ፤ የኔሮ ውዳሴ ማለት ምፀት ነው የእሚሆነው ። ↑