ሕ ገ ክ ራ ሲ

marketing-image

2.2.2. መንግሥታዊ ትርክቶች እና የፖለቲካ ስልጣን

መንግሥትን መገንቢያ ቁሳ ቁሶች ውስጥ አንዱ የሆነውን ፤ መንግሥታዊ ትርክት ፦ ባሕላዊ እና ሳይንሳዊ በእሚሉ ኹለት ዋና ዋና ጎራዎች ከፍለን ከእዚኽ በፊት በአለው ንዑስ ክፍል ተመልክተናል ።

እነ እዚኽ ፤ ባሕላዊ እና ሳይንሳዊ በእሚል ለኹለት ከፍለን የተመለከትናቸው ስድስት መንግሥታዊ ትርክቶች ደግሞ ፤ ትርክታቸው በፖለቲካ ስልጣን ጉዳይ በአለው ትንታኔ መሠረት አምባገነናዊ እና ዴሞክራሲያዊ ብለን ለኹለት ልንከፍላቸው እንችላለን።

አምባገነናዊ ትርክቶች የመንግሥት ስልጣን ምንጭ ፣ ፋይዳ እና ድንበር የተመለከተ ድምዳሜያቸውን ለማፀድቅ የትኛውንም ዓይነት የተለያየ ምክንያት ያቅርቡ ፤ መደምደሚያችው ግን አንድ ዓይነት ነው ፤ እርሱም ፦

‘የመንግሥት ስልጣን የእማይከሰስ ወይንም ፍፁማዊ ፣ የእማይለወጥ (የእማይወሰድ) ወይንም የቆይታው ግዜ የእሚታወቅ ወሰን በሌለው ግለሰብ ወይንም ቡድን የእሚመራ ፣ የተማከለ (በአብዛኛው በአንድ ሰው ከአልሆነም በጥቂት ምርጦች ፈቃድ የእሚመራ ) መሆን አለበት’

የእሚል ነው ።

ዴሞክራሲያዊ ትርክት በተራው ፤ የመንግሥት ስልጣን ፤ ዜጎች በተፈጥሮ የአላቸውን ተፈጥሮዋዊ ፤ ህይወትን እና ንብረትን ከአደጋ የመከላለከል መብት ለመንግሥት በውክልና በመስጠታቸው የእሚመጣ በመሆኑ ፤ ይኽን የዜጎችን ህይወት እና ንብረት ከአደጋ የመከላከል መንግሥታዊ ስልጣን በአደራ የእሚረከበው አካል ፤ አደራውን በአግባቡ እንዲወጣ ፤ ተጠያቂነቱ ስልጣኑን አደራ ለሰጠው ሕዝብ መሆን አለበት ( Should be accountable to the public ) ፣ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ከአልተወጣ ወይንም ከእርሱ በተሻለ ኹኔታ ኃላፊነቱን መወጣት የእሚችል አካል ከመጣ አደራ ሰጭው ሕዝብ ስልጣኑን ወስዶ ለሌላ መስጠት የእሚችልበት አኳኋን መኖር አለበት ፣ እነ እዚኽንም ኹለት ግቦች እንዲሳኩ ፦ የመንግሥት ስልጣን ለአንድ ግለሰብ ወይንም ማሕበር ብቻ የእሚሰጥ ሰአይኾን በተለያዩ ሰዎች እና ማሕበራት መካከል መከፋፈል አለበት ወይንም አለመማከል አለበት (Decentralization of Power) እና የመንግሥትን ስልጣን በአደራ የእሚሰጠው ሕዝብ ፤ ስልጣን ሰጪ እና ነሺነቱን የእሚያረጋግጠው በነፃ እና ፍትኃዊ ምርጫ (Free and Fair election) መኾን አለበት ፤ የእሚል ነው ።

ስለ እዚኽ ፦ ጥንታዊያኑ ዓምላካዊያኑን ጨምሮ ፤ ከዴሞክራሲያዊ መንግሥት ውጭ የአሉ፟ት ፤ አራቱም ሳይንሳዊ የመንግሥት ትርክቶች ፤ አምባገነናዊ የመንግሥት ትርክቶች ናቸው ። ምክንያቱም ፦ ምክንያታቸው ይለያይ እንጂ የመንግሥት ስልጣን የእማይከሰስ ፥ የእማይለወጥ (የእማይወሰድ) ስለ እዚኽም ቆይታው ወሰን የሌለው እና የተማከለ መሆን አለበት የእሚሉ ስለ ሆኑ ።

ኹሉም አምባገነናዊ መንግሥታት ውስጥ በግልፅ ወይንም በስውር የእሚንፀባረቅ እና የእማይከሰስ ፥ የእማይለወጥ (የእማይወሰድ) ስለ እዚኽም ቆይታው ወሰን የሌለው ፣ የተማከለ ለእሚሉት የመንግሥት ስልጣን ፍልስፍናቸው መነሻ ምክንያታቸው ደግሞ፤ ‘ሰው በሰውነቱ እኩል ነፃ’ ነው ወይንም በፖለቲካው ረገድ ሰው በሰብዓዊነቱ እኩል ነው የእሚለውን ኃሳብ በመርህ ደረጃ ያለ መቀበል ወይንም በመርህ ደረጃ ቢቀበሉም እንኳን ይህን መርህ እውቅና የሰጠ አደረጃጀት አለመፍቀድ ነው ።

ይኽ የአምባገናነን መንግሥታት የስልጣን ትንታኔ ኹሉ በአንድም በሌላም መንገድ የእማይቀበሉት ፤ ሰው በተፈጥሮ በእኩልነት ነፃ ነው የእሚለው አስተሳሰብ ፤ ምንም እንኳን ፥ በተለይ በእዚኽ ዘመን ለእምንኖር ሰዎች ፤ በጣም ግልፅ የሆነ ገኃዳዊ ኃቅ ቢመስልም ፤ በሰው ልጅ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ በኹሉም ግዜ እና ስፍራ ፤ ሰፊ ማሕበራዊ ተቀባይነት ለማግኘት እና ለመሰራጨት በጣም ያዘገመ አስተሳሰብ መሆኑን ስንረዳ ፤ አምባገነናዊ የመንግሥት ፍልስፍና ፤ ልማዳዊ የሆነ የሰው ልጅ የስነ ልቦና ድክመት ላይ የእሚመሠረት ስለ እዚኽም የነቃ እና በእውቀት የታጀበ እንዲኹም በእየዘመኑ የእሚታደስ መሠረታዊ ትግል የእሚያስፈልገው መሆኑን እንረዳለን ።

አምባገነንነት በረጅሙ የሰው ልጅ ታሪክ እንደ ታየው ለማስወገድ በእውቀት የታጀበ ትግል የእሚጠይቅ ብቻም ሰአይሆን ፤ አንዴ አልፈነዋል ተብሎ የእሚተው ማሕበራዊ ፈተና አይመስልም ።

ከእላይ እንደ አልነው ፤ ይኽ ከአርስታትል እስከ ኂንዲዩዝም በኋላም የተናጠል ምሳሌ ቢሆንም እንደ አፓርታይድ በአሉ ስረዓቶች ስር ሰዶ የኖረ ዝበታዊ (Superstitious) ፤ ሰው በሰውነት እኩል አይደለም የእሚለው አመላካከት ፤ ከላይ እንደ አልነው ፤ ምንም እንኳን በተለያየ ብዙ ምክንያት በሺፋፈንም ፤ ለኹሉም አምባገነናዊ መንግሥታት የስልጣን ትርክቶች ፍልስፍናዊ መሰረታቸው ነው ።

በእዚኽም ክፍል ፤ ከላይ የተመለከትናቸው መንግሥታዊ ትርክቶች ፤ ከፖለቲካ ስልጣን አንጻር አምባገነናዊ እና ዴሞክራሲያዊ በእሚል ጎራ እንዲከፈሉ የእሚያደርጉዋቸውን ፤ በዜጎች የማሕበረሰብ አህድነት ላይ ከአላቸው አቋም አንጻር ፦

  • ሕጋዊው የፖለቲካ ስልጣን ምንጭ ምንድ ነው ?
  • የፖለቲካ ስልጣን ቀዳሚ ፋይዳ ምንድ ነው ?
  • የፖለቲካ ስልጣን ድንበር የት ነው ?

ለእሚሉት ሦሥት ጥያቄዎች የእሚሰጡትን መልስ እንቃኛለን።

ሕጋዊ የፖለቲካ ስልጣን ምንጭ በተለያዩ መንግሥታዊ ትርክቶች አንጻር ፦

በመጀመሪያነት የአየነው የጥንታዊያኑ የዓምላካዊያኑ መንግሥታት የመንግሥት ትርክት ፤ ትክክለኛው የስልጣን ምንጭ ፤ ዓምላክ መሆን ወይንም ከዓምላካዊ ዘር መወለድ ስለ እዚኽም ፤ ከሌላው መደበኛው ሰው ለየት ያለ አፈጥጠር ወይንም ፍጥረት ተላብሼዓለሁ ወይንም ነገሥታት ዓምላክ ወይንም ዓምላካዊ ዘር የአለባቸው ናቸው የእሚል ነው።

ይኽም ማለት ፤ የተወሰኑ ሰዎች ፤ ከሌላው ሰው በተለየ ዓምላካዊ ባሕሪ የተላበሱ ወይንም ደም የአላቸው ናቸው የእሚል ስለሆነ ፤ የሰዎችን ተፈጥሮዋዊ ሰብዓዊ እኩልነት የእማይቀበል ነው።

ከዓምላካዊያኑ በኹለተኛነት ለእሚመጡት ስነ መለኮታዊያን ፤ ምንም እንኳን ከዓምላካዊያኑ በተለየ ከአፈታሪካዊ ልማዳዊ ኃይማኖት ላይ ከመመሥረት ይልቅ የራሱ የሆነ ውስብስብ የአስተሳሰብ መዋቅር በአለው በተጻፈ እና የአምላክ ቃል በእሚባል መጽሐፍ እምነት ላይ መመሥረታቸው እና ከሰው ልጆች መካከል ከሌሎቹ በተለየ የአምላክ ዘር የአለባቸው ወይንም ራሳቸው ዓማልክት የሆኑ ሰዎች ናቸው የፖለቲካ ስልጣን የእሚገባቸው የእሚለውን የዓምላካዊያኑን ቢኽል አለመቀበላቸው ከዓምላካዊያኑ ቢለያቸውም ፤ ትክክለኛው የፖለቲካ ስልጣን ምንጭ ፤ የአምላክ ፈቃድ ብለው በእሚያምኑበት መጽሐፋቸው መሠረት ፤ አምላክ ለፖለቲካ ስልጣን የአጨውን ሰውን በእሚለዩበት አንዳች ዓይነት መመዘኛ ላይ የተመሠረተ ነው።

በአጭሩ ለስነ መለኮታዊያኑ ፤ የፖለቲካ ስልጣን ፤ ከአምላክ በሹመት ለተወሰኑ ለተመረጡ ሰዎች የእሚሰጥ እና ሌላውም ሰፊው ሕዝብ ፤ ወደ ፖለቲካ ስልጣን የእሚመጡ ሰዎችን በመምረጥ ውስጥ ምንም ሚና የሌለው እና ሊኖረውም የእማይገባው አድርገው ነው የእሚያምኑት።

ይኽም የስነ መለኮታዊያኑ ፤ የፖለቲካ ስልጣን ምንጭ ብኺል ፤ ሰዎች በተፈጥሮ እኩል ነጻ በመሆናቸው ፤ በአንድ ማሕበረሰብ ውስጥ ወደ ስልጣን የእሚመጣውን ማንኛውም የፖለቲካ ባለ ስልጣን ፤ በአንድም በሌላ መንገድ ፤ ከሕዝቡ ይኹንታ ብቻ እና ብቻ ነው ሊመነጭ የእሚገባው ከእሚለው ፍትኃዊ ፤ የዜጎች የማሕበረሰብ አህድነት መርህ ጋር የእሚቃረን ነው።

ከስነ መለኮታዊያኑ የስልጣን ምንጭ ትርክት አንዱ የሆነውን የአባትነቱን ትርክት ብንወስደው ፤ አባት የቤተሰቡ ‘ንጉሥ’ ነው ፤ ይኽም ንግሥና በዘር ሐረግ ውርርስ ወደ በኩር ልጅ ፤ በኩር ልጅ በእማይኖርበት ወቅት ደግሞ በእዚኽ ተዋረድ ቅርብ ለሆነው ልጅ ወይንም የስጋ ዘመድ እየተላለፈ ይመጣል ወይንም ሌላውን ትርክታቸውን ብንወስድ ፤ በአምላክ የተመረጠ ቤተሰብ ፣ የተቀባ ሰው ፣ ወዘተ ፤ መንገሥ አለበት የእሚል ነው ።

ስለ እዚኽ ፦ በስነ መለኮታዊያኑ ትንታኔ ፤ ለምሳሌ ፦ ነጋሢዎች የትውልድ ሐረጋቸውን ከሌላው ሰው ይልቅ ፤ ከአዳም ለእሚመጣው ውርስ ፤ በቡክርና የውርስ ሕግ የበለጠ አቅርበው ማሳየት የእሚችሉት ወይንም በአንዱ የኃይማኖት ቀኖና መሠረት መመረጣቸውን ወይንም መቀባታቸውን ማሳየት የእሚችሉት ናቸው ።

ለምሳሌ ፦ በሐገር ኢራን ፤ በመንፈሳዊውም ሆነ በምድራዊው ፖለቲካ የመጨረሻ ፍጹማዊ ስልጣን ባለቤት የሆነው አያቶላህ ለእሚባለው ማዕረግ የእሚመረጠው ሰው ፤ የእስልምና እምነት ጸሐፍት የሆነ ሰው ነው። ይኽም ብቻ ሰአይሆን ፤ ሰውየው ከነብዩ መሐመድ ልጅ አሊ የተወለደ መሆን የአለበት እና ለእዚኽ ሹመት ከበቃ በኋላ ኃጥያት የሌለበት ተደርጎ የእሚታይ እና የእሚያሳልፋቸውም ውሳኔዎች እንደ አምላክ ትዕዛዝ ስህተት የሌለባቸው ፍጹም ተደርገው የእሚወሰዱ ናቸው።

ይኽ የስነ መለኮታዊ ስረዓት ፤ ሰውን በሰውነቱ በአሳማኝ መንገድ ሊነፈጉ የእማይችሉ እኩል የሆኑ ተፈጥሮዋዊ መብቶች ባለቤት እንደ ሆነ ከመቀበል ይልቅ ፤ አባት እና ልጅ ፣ ታላቅ እና ታናሽ ፣ የታላቅ ቤተሰብ እና የታናሽ ቤተሰብ ፣ የተመረጠ እና የአልተመረጠ ቤተሰብ ፣ የተቀባ እና የአልተቀባ ሰው ፣ የእንትን እምነት ጸሐፍት ወይንም ሊቅ ወዘተ ፤ በእሚሉ ክብርን መሠረት በአደረጉ ፤ የወግ ክፍፍሎች ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ፤ ሰዎችን እንደ ሰብዓዊ ፍጡርነታቸው ፤ የእኩል ነፃነት እና የእኩል ተፈጥሮዋዊ መብት ባለቤት እንደ ኾኑ አድርጎ ሰአይሆን የእሚያያቸው ፤ እንደ ውልደት ቅደም ተከተላቸው ወይንም እንደ ዓምላካዊ ‘ምርጫ’ ለፖለቲካ ስልጣን የአላቸውን ተገቢነት የእሚወስን ፤ በእዚኽም በጣም በስውርም ቢሆን የሰውን ሰብዓዊ እኩልነት ከፖለቲካ ስልጣን ስሌት ውስጥ ያወጣ እና ዜጎች እጣ ፈንታቸውን በእራሳቸው የመወሰናቸውን ተፈጥሮዋዊ መብታቸውን የነፈገ ነው ።

በማንኛውም ማሕበረሰብ ውስጥ ፤ የክብር ክፍፍል መኖሩ በጣም ጤናማ እና ትክክል ነው ። አባት በአባትነቱ ፣ እናት በእናትነቷ ፣ ታላቅ በታላቅነቱ ወይንም ደግሞ በሥራው ታማኝ እና ታታሪው በታታሪነቱ ፣ የልዩ ችሎታው ባለቤት በችሎታው ፣ ወዘተ ፤ የእሚገባቸውን ክብር እና እውቅና ሊሰጣቸው ይገባል ፤ ያንንም ማድረግ ከግለሰቦቹ በአሻገር የማሕበረሰቡን ጤና እና ጥንካሬ እንዲኹም እድገት ለማረጋገጥ መተኪያ የሌለው ሚና አለው ። ነገር ግን ፤ እነ እዚኽን አክብሮታዊ ክፍፍሎች ወስዶ ፤ ከሰዎች ተፈጥሮዋዊ ነፃነት እኩልነት ይልቅ ፤ የፖለቲካ እና የኢከነሚያዊ ስረዓት ማደራጃ መርህ ማድረግ ነው ስህተቱ ።

ሰው ሰርቶ ኃብታም ስለ ሆነ መከበሩ ወይንም የአንዳች የልዩ ችሎታ ባለቤት በልዩ ችሎታው መሠረት ለአንዳች ኃላፊነት መታጨቱ ችግር የለበትም ብቻ ሰአይሆን ተገቢም ነው ወይንም ለሌሎች መሐበራዊ ልዩነቶች ተገቢውን እውቅና መስጠት በራሱ ችግር የለበትም ፤ ነገር ግን በስንፍናውም ይኹን በኪሳራ እና መሰል የንግድ አደጋ የደኸየን ሰው ፣ ወይንም በውልደት ቅደም ተከተል ታናሽ የኾነውን ልጅ ወይንም በእድሜ ታላቅ ቢኾንም እንኳን የታናሽ ልጅ በመኾኑ ፣ ወይንም በሌላ መሰል ማንኛውም ምክንያት ፤ ለፖለቲካ ስልጣን እኩል እድል የለኽም ብሎ ፤ የሰዎችን ፖለቲካዊ መብት እና ተሳትፎ በመገደብ ዜጎች የራሳቸው ፖለቲካዊ እጣ ፈንታ ካፒቴን እንደ አይሆኑ ማገድ ፤ የሰዎችን ተፈጥሮዋዊ እኩል ነፃነት የእሚጋፋ ነው ።

በእዚኽ መልኩ ነው ፤ የክብር ወይንም ወግ አጥባቂ ማሕበረሰባት (Honor Societies or Conservative Societies) ፤ የዜጎችን ተፈጥሮዋዊ መብት በመካድ ወይንም ተፈጥሮዋዊ እኩል ነፃነታቸውን በአለመቀበል ፤ ሕጋዊ የፖለቲካ ስልጣን ምንጭ የሕዝብ ፈቃድ ሰአይሆን አንዳች ዓይነት መለኮታዊ ሲመት አድርገው በመውሰድ መሠረታዊ ፖለቲካዊ ስኽተት የእሚሰሩት ።

በተለይ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ፤ የስነ መለኮታዊያኑ ትንታኔ ፤ ከአውድ ውጭ በእሚተረጎሙ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ምክንያት ፤ ስልጣን ኹሉ ከእግዚአብሔር የእሚገኝ በመሆኑ ፤ በማንኛውም መንገድ ለተገኘው እና በአምባገነንነት ወይንም በጭቆና የእሚቀጥለውን ስልጣን ፤ ዝም ብለን መገዛት አለብን የእሚለው አስተሳሰብ ፤ እስከ ዛሬም አንድ አንድ አማኞችን ሲፈታተን ይታያል።

በተለይ ከእዚኽ በታች የተዘረዘሩትን የእሚመስሉ አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክሮች ፦

  • ሮሜ 13፡1 “ነፍስ ኹሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። ከእግዚአብሔር ከአልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና ፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው።ስለ እዚኽ ባለ ሥልጣንን የእሚቃወም የእግዚአብሔርን ሥርዓት ይቃወማል ፤ የእሚቃወሙትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ይቀበላሉ።”
  • ቲቶ 3፡1-2 “ለገዦችና ለባለ ሥልጣኖች የእሚገዙና የእሚታዘዙ ፥ ለበጎ ሥራ ኹሉ የተዘጋጁ ፥ ማንንም የእማይሳደቡ ፥ የእማይከራከሩ ፥ ገሮች ፥ ለሰው ኹሉ የዋኽነትን የእሚያሳዩ እንዲሆኑ ምከራቸው።”
  • 1ኛ ጴጥሮስ 2፡13 “ስለ ጌታ ብላችኹ ለሰው ሥረዓት ኹሉ ተገዙ ፤ ለንጉሥም ቢሆን ፥ ከኹሉ በላይ ነውና።”
  • 1ኛ ጴጥሮስ 2፡14 “ለመኳንንትም ቢሆን ፥ ክፉ የእሚያደርጉትን ለመቅጣት በጎም የእሚያደርጉትንም ለማመስገን ከእርሱ ተልከዋልና ተገዙ።”
  • ዳንኤል 2፡21 “ጊዜያትንና ዝመናትን ይለውጣል ፤ ነገሥታትን ያፈልሳል ፥ ነገሥታትንም ያስነሣል ፤ ጥበብን ለጠቢባን እውቀትንም ለአስተዋዮች ይሰጣል።”
  • ዳንኤል 4፡17 “ልዑሉ በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሰለጥኑ ፥ ለወደደውም እንዲሰጠው ፥ ከሰውም የተዋረደውን እንዲሾምበት ሕያዋን ያውቁ ዘንድ ይኽ ነገር የጠባቂዎች ትዕዛዝ ፥ ይኽም ፍርድ የቅዱሳን ቃል ነው።“

ምን አልባት አንዳንድ ክርስቲያኖች ፤ የፖለቲካ ስልጣን በተፈጥሮ እኩል ነጻነት ከአላቸው ሰዎች ይኹንታ እንጂ ከእግዚአብሔር ሲመት አይመጣም የእሚለው አባባል ፤ ከላይ ከተጠቀሱት ቃለ እግዚአብሔር ጋር የእሚጋጭ ለእሚመስላቸው ሰዎች ፤ የተወሰነ ማብራሪያ ማቅረብ ተገቢ ይመስላል።

ክርስቲያን የሆኑ እና ከእላይ የተዘረዘሩትን መሰል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክሮች የፖለቲካ ስልጣን ከዜጎች ይኹንታ እንጂ ከእግዚአብሔር ሲመት አይመጣም የእሚለው አባባል ጋር የእሚጋጩ ከመሰላቸው ፤ በእዚኽ ጉዳይ ላይ የእሚከተሉትን ነጥቦች ማሳሰብ ተገቢ ይሆናል ፦

  1. መጽሐፍ ቅዱስን በትክክል ለመረዳት መጽሐፍ ቅዱስ መነበብ የአለበት ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተንጸባረቀው ከጠቅላላው የእግዚአብሔር ኃሳብ ጋር እንጂ በተናጠል በአሉ ትዕዛዞች እና ጥቅሶች መሆን የለበትም።

ለምሳሌ ፦ ዘጸዓት 20፡8-11 “የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ። ስድስት ቀን ሥራ ተግባርህንም ኹሉ አድርግ ፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ሰንበት ነው ፤ አንተ ፥ ወንድ ልጅህም ፥ ሎሌህም ፥ ገረድህም ፥ ከብትህም ፥ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ ፤ እግዚአብሔር በስድስት ቀን ሰማይንና ምድርን ፥ ባሕርንም ፥ ያለባቸውንም ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን አርፏልና ፤ ስለ እዚኽ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባርኮታል ቀድሶታልም።”

ይኽም ማለት ቃሉ የእማይለወጠው እግዚአብሔር በግልጽ ሰንበት እንዲከበር ደንግጓል ማለት ነው።

ሆኖም በአዲስ ኪዳን ላይ ደግሞ ሕግን ልፈጽም እንጂ ልሽር አልመጣኹም የአለው ኢየሱስ ፤ በማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 2፡23-27 “ በሰንበትም በእርሻ መካከል ሲያልፍ ደቀ መዛሙርቱም እየኼዱ እሸት ይቀጥፉ ጀመር። ፈሪሳዊያንም ፦ እነሆ ፥ በሰንበት ያለተፈቀደውን ስለ ምን ያደርጋሉ? አሉት። እርሱም ፦ ዳዊት ባስፈለገውና በተራበ ጊዜ ፤ እርሱ አብረውት ከነበሩት ጋር የአደረገውን ፥ አብያታር ሊቀ ካህናት በነበረ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ ፤ ከካኽናት ብቻ በቀር መብላት ያለተፈቀደውን የመሥዋዕትን እንጀራ እንደ በላ ፥ ከእርሱም ጋር ለነበሩት እንደ ሰጣቸው ከቶ አላነበባችሁምን? አላቸው። ደግሞ ፦ ሰንበት ስለ ሰው ተፈጥሯል እንጂ ሰው ስለ ሰንበት አልተፈጠረም።”

እነ እዚኽን ኹለት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የአነጻጸረ ሰው ፤ መጽሐፍ ቅዱስን በሙላቱ ሳይሆን በተናጠል ለማንበብ ከሞከረ ፤ መጽሐፍ ቅዱሱ እርስ በእርሱ የእሚጣረስ ሊመስለው ይችላል ፤ እውነታው ግን ፤ በጥንቃቄ ከተነበበ ፤ መጽሐፍ ቅዱሱ እርስ በእርሱ እየተጣረሰ ሳይሆን ፤ ሰውን አቅል ይኑራችኹ እያለ ነው።

ኢየሱስ በእዚኽ ስፍራ ላይ ፤ በግልጽ የተደነገገውን የሰንበት ሕግ መተላለፉ ላስገረማቸው ፈሪሳዊያን እየአላቸው የአለው ነገር ፤ እግዚአብሔር ሕግን የአወጣው ሰውን ለመጥቀም እንጂ ሰዎቹ በሕጉ እንዲጎዱ አይደለም። እግዚአብሔር ሰንበትን አክብሩ ሲል ፤ እረፍት ይኑራችኹ ለማለት እንጂ ሰንበት ጣዖት ሆኖባችኹ ፤ በየሰንበቱ ታጥባችሁ እና ታጥናችሁ በግድም ቢሆን ተቀመጡ ለማለት አይደለም።

ዳዊት ከንጉሥ ሳኦል ፊት በእሚሸሽበት ግዜ ተራበ ፤ በእዚኽ በተራበበት ወቅት የአገኘው የእሚበላ ነገር ፤ በሕጉ ካህናት እንጂ ሌላ ሰው እንዲበላው የአለተፈቀደ ነገር ነበር ፤ ስለ እዚኽ ዳዊት ሕጉ ይኽን እንደ አልበላ ይከለክለኛል ብሎ አልተራበም ፤ ይልቁንም ቅዱስን ምግብ አንስቶ ራቡን አስታገሰበት ፤ ከእርሱም ጋር ለነበሩት ሰዎች ሰጣቸው ፤ ይኽን በማድረጉ ወይንም በሕጉ በግልጽ ከካህን በስተቀር ማንም እንደ አይበላ የተከለከለውን ምግብ በመብላቱ ኃጥያተኛ አልተባለም። ስለ እዚኽ ፤ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ወይንም ለሰው እሚጠቅመው ከሆነ ሰው ሰንበትን ቢሽር ኃጢያተኛ አይባልም ፤ ምክንያቱም ፦ የሰንበት ሕግ ሰው እንዲያርፍበት ለሰው ተፈጠረ እንጂ ሰው ሰንበትን እንዲያከብር እና ሰንበት የሰው ልጅ ሠንሠለት እንዲሆን ሰው ለሰንበት አልተፈጠረም።

በአጠቃላይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአለው ሕግ ግቡ ሰውን መጥቀም እና መጥቀም ብቻ ነው። ከእዚያኽ በአሻገር ሕግ ምንም ጥቅም የለውም።

  1. በተመሳሳይም ፤ ስልጣን ኹሉ ከእግዚአብሔር ነው እና ለባለ ስልጣን ተገዙ ማለት ፤ የፖለቲካ ስልጣን የተፈለገበት ምክንያት ሕግ እና ስረዓትን እንዲያስከብር እና ተላላፊዎችን እንዲቀጣ ወይንም ለሰው ጥቅም እንዲሰራ እንጂ ፦

ሮሜ 13፡4 “ለመልካም ነገር ለአንተ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና።… ክፉ አድራጊውን የእሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና።”

ባለ ስልጣን ነውና ፤ ለአንተ መልካም ሳይሆን ክፉ ቢያደርግብኽ ወይንም ክፉ አድራጊውን አመስግኖ መልካም አድራጊውን ቢቀጣ ፤ ዝም ብለኽ ተገዛ ማለት አይደለም። ይኽን ለማስረዳት እግዚአብሔር በቀባቸው ላይ የተደረጉ እግዚአብሔር የፈቀዳቸው ብዙ አመጾችን ፤ ከመጽሐፍ ቅዱሱ ማቅረብ ይቻላል ፦

  • የእምነት አባት የተባለው አብራም አምስት ነገሥታት የወንድሙን ልጅ ሲማርኩበት ፤ ዘመቻ አድርጎ የወንድሙን ልጅ አስመልሷል። ዘፍጥረት 14፡8፣12፣15፣16 “የሰዶም ንጉሥና የገሞራ ንጉሥ ፥ ዞዓር የተባለች የቤላ ንጉሥም ወጡ ፤ እነ እዚኽ ኹሉ በሲዲም ሸለቆ በእነርሱ ላይ ለሰልፍ ወጡ፤…በሰዶም ይኖር የነበረውን የአብራምን የወንድ ልጅ ሎጥን ደግሞ ከብቱንም ወስደው ኼዱ።…አብራምም ወንድሙ እንደ ተማረከ በሰማ ጊዜ በቤቱ የተወለዱትን 318 ብላቴኖችን አሰለፈ ፤ ፍለጋቸውንም ተከትሎ እስከ ዳን ድረስ ኼደ። ብላቴኖችንም ከፍሎ በሌሊት እርሱ ከባሪያዎቹ ጋር ወረደባቸው ፥ መታቸውም ፥ በደማስቆ ግራ እስከ አለችውም እስከ ሖባ ድረስ አሳደዳቸው። ከብቱንም ኹሉ አስመለሰ ፥ ደግሞም ወንድሙን ሎጥንና ከብቶቹን ሴቶቹንና ሕዝቡን ደግሞ መለሰ።”
  • እጅግ ትሁት የተባለለት እና የእሥራኤልን ልጆች ከፈርዖን እጅ ነጻ ያወጣው ሙሴ በፈርዖን ላይ አምጾ ነበር ። ዘጸዓት 2፡11 12 “በእዚያኽም ወራት እንዲህ ሆነ ፤ ሙሴ ጎበዝ በሆነ ጊዜ ወደ ወንድሞቹ መጣ ፥ የሥራቸውንም መከራ ተመለከተ ፤ የግብፅም ሰው የወንድሞቹን የዕብራዊያን ሰው ሲመታ አየ። ወዲህ እና ወዲያም ተመለከተ ፤ ማንንም አላየም ፥ ግብፃዊያውንም ገደለ ፥ በአሸዋ ውስጥ ሸሸገው።” ዕብራዊያን 11፡27 “የንጉሡን ቁጣ ሳይፈራ የግብፅን ሐገር የተወ በእምነት ነበር ፤” ከእዚኽ በኋላ ሙሴ ሐገር ለቆ ሲሸሽ ፤ እግዚአብሔር የጀመርከውን ጨርስ ብሎ መልሶ ወደ ግብጽ ነው የላከው።
  • ንጉሥ ሳኦል በእግዚአብሔር ቢሾምም እንኳን ፤ እርሱ በስልጣን ላይ እያለ እና ከስልጣን ከመውረዱ ብዙ ዓመታት አስቀድሞ ፤ ከንጉሡ ፈቃድ ውጭ እግዚአብሔር ሌላ ንጉሥ በላዩ ላይ ሾሞበታል ። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 16፡1 “እግዚአብሔርም ሳሙኤልን ፦ በእሥራኤል ላይ እንደ አይነግስ ለናቅኹት ለሳኦል የእምታለቅስለት እስከ መቼ ነው? በቀንድህ ዘይቱን ሞልተህ ኺድ ፤ በልጆቹ መካከል ንጉሥ አዘጋጅቻለውሁና ወደ እሴይ ቤት ወደ ቤተልሔም እልክኃለሁ።” እግዚአብሔር በሾመው ሰው ራሱ ላይ ባላንጣ እና አማጺ አስነሳበት ማለት እንችላለን።
  • የመጀመሪያው የእሥራኤል ንጉሥ ሳኦል ምንም እንኳን በእግዚአብሔር የተሾመ ቢሆንም ፤ ከእላይ እንደ አየነው ዳዊት ላይ ቀንቶበት ዳዊትን ሊገድለው ሲፈልግ ዳዊት ፤ እግዚአብሔር የቀባው ንጉሥ ነውና የወደደውን ያድርግብኝ ብሎ ራሱን አልሰጠም ፤ ይልቅም ህይወቱን ለማዳን ሸሽቷል። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 19፡10 “ሳኦልም ዳዊትን ከግንብ ጋር ያጣብቀው ዘንድ ጦሩን ወረወረ ፤ ዳዊትም ከሳኦል ፊት ዘወር አለ ፥ ጦሩም በግንቡ ውስጥ ተተከለ ፤ በዚያም ሌሊት ዳዊት ሸሽቶ አመለጠ።”
  • የንጉሥ ዳዊት ልጅ የሰለሞን ልጅ ሮብዓም ወይንም የእሥራኤል ንጉሥ ሮብዓም ግብር አልቀንስም በማለቱ ኢየርብዓም መላውን እሥራኤል አሳምጾበታል። 1 ነገሥት 12፡16 “እሥራኤልም ኹሉ ንጉሡ እንደ አልሰማቸው ባዩ ግዜ ሕዝቡ ለንጉሡ፦ በዳዊት ዘንድ ምን ክፍል አለን? በእሴይም ልጅ ዘንድ ርስት የለንም።…ብለው መለሱለት።” ይኽም እንዲሆን እግዚአብሔር እንደ ፈቀደ መጽሐፉ ይላል።
  • ኢዩ የእሚባል የእሥራኤል ጀነራል በንጉሡ ላይ አምጾ ንጉሡን ገድሎ ነግሷል ። 2ኛ ነገሥት 9፡24 “ኢዩም በእጁ ቀስቱን ለጠጠ ፥ ኢዮራምንም በጫንቃው መካከል ወጋው ፤ ፍላጻውም በልቡ አለፈ ፥ ወደ ሰረገላው ውስጥ ወደቀ።”
  • ሐዋሪያው ጳውሎስ አንድ ባለ ስልጣን ሲያሳድደው ተሸሽጎ አምልጧል ። 2ኛ ቆሮንጦስ 11፡32 33 “በደማስቆ አርስጦስዮስ ከተባለ ንጉሥ በታች የሆነ የሕዝብ ገዢ ሊይዘኝ እየወደደ የደማስቆ ሰዎችን ከተማ ያስጠብቅ ነበር ፥ በቅጥሩ ባለ መስኮት በቅርጫት አወረዱኝና ከእጁ አመለጥሁ።” ከእግዚአብሔር ከአልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና ፤ የአለው ኃዋሪያው ጳውሎስ ፤ ይኽ ነፍሰ ገዳይ ገዢ ሊገድለው ሲፈልግ ፤ ስልጣን ኹሉ ከእግዚአብሔር ነውና የወደደውን ያድርግብኝ ብሎ እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም ፤ ይልቁንም በቅርጫት ውስጥ ተደብቆ አምልጦታል።

እነ እዚኽን እና ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ስንመለከት ፤ አንድ ክርስቲያን ምን አልባት ማለት የእሚችለው ፤ እግዚአብሔር ሲፈቅድ ወይንም ሲናገር ብቻ ነው እንጂ የእማምጸው ፤ ስልጣን ኹሉ ከእግዚአብሔር ነው እና መቼም ቢሆን በባለስልጣን ላይ አላምጽም ማለት አይደለም ፤ ምክንያቱም ፦ እግዚአብሔር ራሱ በሾማቸው ሰዎች ራሱ ላይ እግዚአብሔር የፈቀዳቸው ብዙ አመጾች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአሉ በመሆኑ።

እግዚአብሔር የሾመው ሰው አያጠፋም ብሎ ማለት ፤ አዳም የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ተላልፎ በለሱን አይበላም እንደ ማለት ነው። በእግዚአብሔር መመረጥ ወይንም መሾም የስህተት እና የተጠያቂነት አልባ ምክንያት ሊሆን አይችልም ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ተገቢ ትርጓሜ መሠረት ።

  1. ሌላውን እና የመጨረሻው ፤ እንደ እምነታችን ፤ ስልጣን ከእግዚአብሔር ነው ብእንል እና እግዚአብሔር የመረጠውን ሰው በትንቢት ፣ በራዕይ ወይንም በአንዳች መንገድ ቢናገር ፤ ይኽ እግዚአብሔር የመረጠው ሰው እንዴት ነው ወደ ስልጣን የእሚመጣው። በጦርነት አሸንፎ ፣ ተሹሞ ወይንም ተመርጦ ነው ወደ ስልጣን ሊመጣ የእሚችለው ፤ ከእዚኽ ውጭ ወደ ፖለቲካ ስልጣን ሊመጣበት የእሚችልበት መንገድ የለም።

ይኽም በመሆኑ ፤ በስልጣን ላይ የአለውን ሰው ንግሥና የእሚያጸና ወይንም የእሚያፈርስ ፤ ተገቢ የሆነ ጦርነት ፣ ሹመት ወይንም ምርጫ መኖሩ የግድ ነው ማለት ነው። በሌላ አገላለጽ እግዚአብሔር ስልጣንን እሰጣለኹ አለ እንጂ ወደ ስልጣን በእዚኽ መልክ ነው የእማመጣው ብሎ አልደነገገም ።

ቶማስ ፔይን የተባለው የአሜሪካ ነጻነት ዘመን ጸሐፊ እንደ አለው ፤ አሜሪካንን ከእንግሊዝ ነጻ ለማውጣት የእምናደርገው ጦርነት ፤ ስልጣንን የእሚሰጥ እና የእሚነሳ እግዚአብሔር ነውና ፤ በንጉሡ ላይ አታምጹ አትበሉን ፤ ምክንያቱም ፦ እግዚአብሔር ከሆነ የእሚያነግስ የእኛም ከንጉሡ የመለየት ጥረታችን አይሳካም ፤ ያም ብቻ ሰአይሆን እስከ ዛሬ በታሪክ የተደረጉ ነገሥታትን አውራጅ እና ሌላ ሿሚ አመጾች ከእግዚአብሔር ናቸው ማለት ነው ይላል ፦

“ነገሥታትን እና መንግሥታትን ማንገስ እና ማውረድ የእግዚአብሔር ብቻ ኃላፊነት ከሆነ ፤ አኹን እኛ የእምናደርገው ጥረት ከእዚኽ አያጎድለውም ፤ በእዚኽም ምክንያት ፦ ይኽ መርኹ ራሱ ፤ በነገሥታት ላይ የደረሰው ነገር በሙሉ ልክ ነው ብላችኹ እንድትቀበሉ ግድ ይላችኋል። ኦሊቨር ክሮምዌል[1] ያመሰግናችኋል። እንዲኽ ከሆነ ቻርልስ (ንጉሡም) በሰው እጅ አይደለም የሞተው ፤ እናንተም ይኽን ምሳሌ በኩራት ልትከተሉት ይገባችኋል ፤ ያለግዜው ተቀጨ ብለው የጻፉ እና ሕትመት ያሰራጩ ሰዎች ፤ በእዚኽ ቀኖና ምክንያት ፤ ነገሩን ለማመስገን እና ለማወደስ ሊገደዱ ነው። ነገሥታት ከስልጣን በአንዳች ዓይነት ተዓምር አይደለም የእሚወገዱት ፤ በሰዎች ዘንድ ከተለመደው መንገድ ውጭ መንግሥታዊ ለውጥ ሊመጣ አይችልም።”

“And if the setting up and putting down of kings and governments is God’s peculiar prerogative, he most certainly will not be robbed thereof by us; wherefore, the principle itself leads you to approve of everything, which ever happened, or may happen to kings as being his work. Oliver Cromwell thanks you. Charles, then, died not by the hands of man; and should the present proud imitator of him, come to the same untimely end, the writers and publishers of the testimony, are bound, by the doctrine it contains, to applaud the fact. Kings are not taken away by miracles, neither are changes in governments brought about by any other means than such as are common and human; [83]”

በእዚኽም መሠረት ፤ ስልጣን የእሚሰጥ እና የእሚነሳ እግዚአብሔር ነው ብሎ ፤ ማንም በተገኘው መንገድ ስልጣን እንዲይዝ በመፍቀድ እጅን አጣጥፎ ቁጭ ማለት ፤ ስንፍና እና ሥራ ፈትነት እንጂ እግዚአብሔርን መታዘዝ አይሆንም። አንድ ሰው ኃብት የእሚሰጥ እና የእሚነሳ እግዚአብሔር ነው ብሎ ፤ ሳይሰራ ቢቀመጥ ድህነት እንደ ወንበዴ ይመጣበታል እንጂ ምንም አያተርፍም በተመሳሳይም አንድ ሕዝብ ስልጣን የእሚሰጥ እና የእሚነሳ እግዚአብሔር ነው ብሎ እጁን አጣጥፎ ቢቀመጥ ፤ የጥቅም ቡድኖች እርስ በእርሳቸው እየተሿሿሙ ወይንም ሴረኞች እና ወንበዴዎች በአመጽ ስልጣን እንዲይዙ ሐገራቸውን ከፍተው ከመስጠት የአለፈ ነገር ማድረግ አይችሉም።

መጽሐፈ ምሳሌ 6፡6 11

“አንተ ታካች፥ ወደ ገብረ ጕንዳን ሂድ፥ መንገድዋንም ተመልክተህ ጠቢብ ሁን። አለቃና አዛዥ ገዢም ሳይኖራት መብልዋን በበጋ ታሰናዳለች፥ መኖዋንም በመከር ትሰበስባለች። አንተ ታካች፥ እስከ መቼ ትተኛለህ ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሣለህ ጥቂት ትተኛለህ፥ ጥቂት ታንቀላፋለህ፥ ትተኛም ዘንድ ጥቂት እጅህን ታጥፋለህ፤ እንግዲህ ድህነትህ እንደ ወንበዴ፥ ችጋርህም ሰይፍ እንደ ታጠቀ ሰው ይመጣብሃል።”

ስለ እዚኽ ፤ አንድ ክርስቲያን ስልጣን ከእግዚአብሔር ነው ብሎ እጁን አጣጥፎ በመቀመጥ ፤ ማንም በፈለገው መንገድ ስልጣን እንዲይዝ እና ስልጣኑንም በፈለገው መልኩ እንዲፈነጭበት ከመፍቀድ እና የእራሱ ግድ የለሽነት ሰለባ መሆን ሳይሆን የአለበት ፤ ስልጣን በጥቅም ቡድኖች ሴራ ሰዎች እርስ በእርስ በመሿሻም ወይንም በአንዱ ጉልበተኛ አመጽ ምክንያት ወደ አፋኞች እና አባካኞች እጅ ገብቶ ፤ እኩይ በአለ ስልጣናት ሕዝብ እንደ አያስለቅሱ ፤ ነጻ የሆኑ ሰዎች በፈቃዳቸው መርጠው ‘እግዚአብሔር የመረጠው ሰው’ ብቻ ወደ ስልጣን የእሚመጣበትን አግባብ መተግበር ነው ያለባቸው።

ያለ ሰው ተሳትፎ እግዚአብሔር የፈለገውን ወደ ስልጣን ያመጣል ተብሎ እንደ መናኝ ቢታሰብ እንኳን ፤ በጦርነት እና በሴራ ከመሥራት ይልቅ ፤ ለእግዚአብሔርም በነጻ ዜጎች ምርጫ መሥራቱ ሳይቀለው እና ለሕዝብ ሳይበጅም አይቀርም።

ሳይንሳዊ የመንግሥት ትርክት ከአልናቸው ፤ በኹለተኝነት የእሚመጣው ፤ አምባገነናዊ ማሕበራዊ ውል ትርክት ፤ በአንድ ማሕበረሰብ ውስጥ ወደ ስልጣን የእሚመጣ አንድ የፖለቲካ ኃይል ፤ የአላንዳች ዓይነት ማሕበራዊ ውል ወይንም ስምምነት የእማይመጣ በመሆኑ ፤ ይኽ በውል (ውሉ ምንም ዓይነት ይኹን) ወደ ስልጣን የመጣ ኃይልን ፤ ሕዝብ ላይ ምንም በደል ቢያደርስበትም ፤ ሕዝቡ ከውሉ አስገዳጅነት ፣ በውሉ ላይ ማመጽ ከእሚያስከትለው የነጋሢው ቅጣት ወይንም ሰይፍ እና ወሉን ማፍረስ የእሚያስከትለውን ትርምስ ፍራቻ እና ጥላቻ ፤ ይኽንን አምባገነናዊ ወይንም ፍጹማዊ መንግሥት ታግሶ መኖር አለበት የእሚል ነው።

በእዚኽ አምባገነናዊ የማሕበራዊ ውል አስተሳሰብ መሠረት ፤ ሕጋዊው የፖለቲካ ስልጣን ምንጭ አንድ እና የእሚታወቅ የሆነ መርህ ሳይሆን ፤ በአንድ የታሪክ አጋጣሚ የፖለቲካ ስልጣኑን ጨብጦ መገኘት ነው። ምክንያቱም ፦ ከአላንዳች ዓይነት ስምምነት የፖለቲካ ስረዓት እንዲሁ ስለ እማይገነባ እና ስልጣንም ስለ እማይያዝ ፤ በአንዳች እና በተገኘው አጋጣሚ የፖለቲካ ስልጣን ከተያዘ ፤ ይኼ የፖለቲካ ስልጣን ፤ በውል አስገዳጅነት ፣ የፖለቲካ ስልጣን መጨበጥ ከእሚሰጠው ኃይል እና ነዋሪ የፖለቲካ ስልጣን ማስወገድ የእሚያስከትለው አለመረጋጋት ጥላቻ ፤ በስልጣን ላይ ያለን አንድ የፖለቲካ ኃይል ፤ ብቸኛ እና ሕጋዊ የፖለቲካ ስላጣን ያደርገዋል የእሚል ነው።

ቀደም ብለን እንደ አሳየነው ፤ የእዚኽ የአምባገነናዊ ውል አስተሳሰብ ፤ የእሚቀርብበት አግባብ የተፈጥሮ ሕግ ነጸብራቅ ከሆነው የማሕበራዊ ውል አስተሳሰብ ጋር የእሚቃረን ነው ። እንደ አልነው ፤ ሰዎች ማሕበራዊ ውል የእሚያስሩት ፤ በነጻነት እየኖሩ ህይወታቸውን እና ንብረታቸውን በግላቸው ከመጠበቅ ይልቅ በእሚያቋቁሙት መንግሥት ቢጠበቅ የእሚሻል መሆኑን በመቀበል ነው ። አምባገነናዊ ማሕበራዊ ውል ያልነው ግን ፤ ከእዚኽ መሠረታዊ የማሕበራዊ ውል አስተሳሰብ በተጻራሪ የእሚቆሙ የተለያዩ በኃሪያት ያሉት በመሆኑ ወይንም አንድ ግዜ ውል ገብተኃል እና ውሉ ቢጎዳኽም ተቀበለው የእሚል በመሆኑ ፤ ይኽ አካኼዱ ውልተኞቹን መልሶ ወደ ጦርነት ኹኔታ ውስጥ የእሚመልስ በመሆኑ አግባብነት የለውም ።

ይኽም የአምባገነናዊ የማሕበራዊ ውል አስተሳሰብ ወደ እዚኽ ስህተት ውስጥ የእሚያስገባው ፤ በውስጡ ከሰዎች ተፈጥሮዋዊ እኩል ነፃነት አላቸው ከእሚለው አስተሳሰብ ጋር የእሚቃረን ኹለት አስተሳሰቦችን የያዘ በመሆኑ ነው ።

የመጀመሪያው ሰዎች ወደ ማሕበራዊ ውል የእሚገቡት ፤ ከማሕበራዊ ውል ተጠቃሚ ለመኾን ነው ። ይኽም በመኾኑ ፤ አንድ ማሕበራዊ ውል የእሚጎዳቸው እና ጥቅማቸውን የእማይስጠብቅላቸው ከኾነ ፤ በእዚያኽ ውል ውስጥ በፈቃዳቸው እንዲቆዩ የእሚያድርጋቸው ምንም ዓይነት ምክንያት የለም ።

አንድ ነጋዴ በዘላቂነት የእሚያከስረው ንግድ ውስጥ የመቆየት ምክንያት እንደ እማይኖረው ፤ አንድ ዜጋም የእማይበጀው ማሕበራዊ ውል ውስጥ በዘላቂነት ለመቆየት የእሚያስችለው ምንም አዕምሮዋዊ ምክንያት የለም ፤ የተፈጥሮ ነፃነቱም ፤ ከእሚጎዳው ነገር እየሸሸ ወደ የእሚበጀው ወይንም የእሚጠቅመው ነገር እንዲኼድ ነው የእሚያደርገው ። ይኽንንም ኃቅ አለመቀበል ፤ የሰው ልጅ ይኽን መሰሉ ሰብዓዊ እኩል ነጻነት እንደ አለው እና እንደ እሚጠቀምበት አለመቀበል ነው ።

ኹለተኛው ስኽተት ፤ ከእሚጎዳው ማሕበራዊ ውል እንደ አይሸሽ ፤ የእሚጎዳውን ማሕበራዊ ውል በኃይል የእሚያስጠብቅ ፤ ፍፁም ስልጣን የአለው መንግሥት ስለ አለ ፤ ይኽን የእሚጎዳውን ውል እሸሻለሁ ወይንም አፈርሳለሁ ቢል ፤ ሰይፍ ስለ እሚጠብቀው አርፎ ይቀመጥ የእሚለው የአምባገነናዊ ውል አመክንዮ ነው ።

ይኽ ኹለተኛው አመክንዮ ስህተት የእሚኾነውም ፤ እያለ የአለው ፤ የፖለቲካ ስልጣን ምንጭ ፤ ወታደራዊ አቅም እና ኃይል ነው በመኾኑ ነው ። አመፅን የመበተን ወይንም ስልጣኑን የመከላከል አቅም ያዳበረ ኅይል ተቀባይነት የአለው ባለ ስልጣን ነው ፤ በእዚኽ ትንታኔ መሠረት ።

በአጭሩ ፤ ሰዎች እኩል ነጻነት እና ጥቅማቸውን የማስከበር መሠረታዊ ማመዛዘን አቅም አላቸው ብሎ የእሚቀበል ማንም የፖለቲካ ኃይል ፤ ለሰዎች ይኽ ተፈጥሮዋዊ እኩልነት በእሚያጎናጽፋቸው መብት ፤ በህይወት ለመኖር እና በህይወት ለመኖር የእሚያስፈልጋቸውን ነገር ለመፈለግ ይንቀሳቀሳሉ ፤ ይኽም መብታቸው ሲገታባቸው ይኽንን መብት ለማስከበር በአንድም በሌላም መልኩ መንቀሳቀስ የእሚችሉበት እምነት ፣ ግንዛቤ ወይንም ቆራጥነት አላቸው ብሎ በመርህ ደረጃ የተቀበለ ሰው ፤ የማሕበረሰብ አባላት ለማሕበራዊ መረጋጋት ሲሉ አምባገነን መንግሥትን መታገስ አለባቸው ብሎ ሊሞግት አይችልም ። ይኽንን የእሚሞግተው ኃይል ፤ ሰዎች በመሠረታዊነት እኩል ነጻዎች እና ነጻነታቸውም ሲገፈፍ እምቢ ለማለት ውስጣዊ ቆራጥነት (ግንዛቤ) የአላቸው ናቸው ብሎ የመቀበል ችግር አለበት ማለት ነው ።

ሳይንሳዊ በአለነው መንግሥታዊ ትርክት ዘርፍ በሶስተኝነት ለአለው ማርክሲዝም ተቀባይነት የአለው የፖለቲካ ስልጣን ምንጭ ፤ በታሪክ አጋጣሚ ለደሞዝ የእሚሰራ ተቀጣሪ ሆኖ መገኘት ፤ ቀጣሪዎችን ኃብት ወርሶ እና የ’ቀጣሪዎችን’ መንግሥት በአመፅ ገልብጦ ፤ የቀጣሪዎችን ኃብት እና የንብረት ባለቤትነት መብት የእሚያከበረውን መንግሥት ስልጣን በኃይል መውሰድ መቻል በብቸኝነት ትክክለኛው እና ታሪካዊ የፓለቲካ የስልጣን ምንጭ ነው ።

ማንም ሰው ግን በታሪክ አጋጣሚ ፤ ሰዎች ቀጥሮ የእሚያሰራ ወይንም ሰዎችን ቀጥረው የእሚያሰሩ ሰዎች በአሉበት ሐገር የነበረ ታማኝ የመንግሥት አገልጋይ ከነበረ ፤ በቡርዣው መንግሥት ውስጥ እየሠራ ይኽን መንግሥት ለመጣል በእሚካሄደው አብዮት ከአልተሳተፈ ታሪካዊ ኋላ ቀር በመሆኑ የፖለቲካ ስልጣን አይገባውም ።

በማርክሲዝምም ውስጥ ፤ የፖለቲካዊ ርዕዮቱ የመሐል አምድ ፤ የሰዎች ‘ሰብዓዊ እኩል ነፃነት’ ሰአይሆን ይልቁንም ሰዎች በኢከነሚያዊ መደባቸው አግባብ የእሚፈርጅ እና በመደብ ልዩነታቸው ተቧድነው ለመጠፋፋት እንዲነሱ የእሚያበረታታ እና መደባዊ ልዩነትን ሊታረቅ የእማይችል ተፈጥሮዋዊ ተቃርኖ አድርጎ የእሚያይ በመሆኑ ፤ ማርክሲዝም በሰዎች ሰብዓዊ እኩል ነፃነት ተቃራኒ እንደ ቆመ እጅግ በጣም ግልፅ ነው ።

ማርክሲስዝም ሰዎችን በሰውነታቸው ሰአይሆን ፤ በአንድ የታሪክ አጋጣሚ በእሚገኙበት ኢከነሚያዊ መደባቸው መሠረት ፤ የፖለቲካ ስልጣን የእሚሰጥ እና የእሚነፍግ ፤ ስለ ሰዎች ተፈጥሮዋዊ እና ሰብዓዊ ነፃነት ምንም ግምት የእማይሰጥ ፖለቲካዊ ርዕዮት ነው ።

በማርክሲዝም የመንግሥት ቲየሪ ወይንም በሠራተኛው አምባገነንነት የመንግሥት ቲየሪ መሠረት ፤ የመንግሥት ስልጣን የእሚገባው ፤ በታሪክ አጋጣሚ በአንድ ግለሰብ ፋብሪካ ወይንም የንግድ ተቋም ውስጥ ተቀጥሮ የእሚሰራ ሰው መሆን ነው ።

በእዚኽም መሠረት ፤ አብዮተኛ ያልኾነ እና ተቀጥሮ የእማይሰራ ሰው ፤ የፖለቲካ ስልጣን እንዲያገኝ አይፈለግም ብቻ ሰአይኾን ፤ የመደብ ጠላት በመኾኑ ፤ በሠራተኛው አምባገነን መንግሥት መጮቆን እና መደምሰስ አለበት ።

ይኽም የማርክሲዝሙን የሠራተኛው ዓምባገነናዊ የመንግሥት ትርክት ፤ የሰዎችን ተፈጥሮዋዊ እኩል ነፃነት ከመቀበል እና ከአለ መቀበል ክርክር አውርዶ ፤ ከሰብዓዊነት አንፃር ሰዎች በሰብዓዊነታቸው በህይወት የመኖር መብት አላቸው የእሚለውን መርህ እንኳን የእማይቀብል ኢሰብአዊ ርዕዮት ያደርገዋል ።

በሳይንሳዊው መንግሥታዊ ትርክት ፤ በዓራተኝነት የአለው ፤ የልማታዊው መንግሥት ትርክት ነው ። በልማታዊያን መንግሥት ትርክት ፤ በዘመናዊው ዓለም በድሆች ሐገር የተወሰነ ሆኖ ፤ ተቀባይነት የአለው የፖለቲካ ስልጣን ምንጭ ፤ ልማታዊው መንግሥት ስልጣን በያዘበት ሐገር ፤ ከበለፀገው ዓለም ጋር የአለውን የኃብት ርቀት ፤ በኢከነሚው ውስጥ በእሚያደርገው ንቁ እና ዙሪያ መለስ ጣልቃ ገብነት ፤ ፈጣን ኢከነሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ መቁረጡ እና ያንንም እያሳካ መገኘቱ ነው ። በሌላ አገላለፅ ፤ በልማታዊያኑ አስተሳሰብ ፤ በነዳያን ሐገር የፖለቲካ ስልጣን ምንጭ ፤ ካስፈለገ የዜጎችን ተፈጥሮዋዊ መብት እና ክብር እንኳን ሽሮ ድህነትን መቅረፍ አለበት ብሎ ከማመን ነው ።

ጥንታዊ የመኳንንት አስተዳደር (Aristocracy ) ወይንም ዘመናዊ የሞግዚት አስተዳደርም ( Care taker government, proctorate or meritocracy ) ከእዚኽ የተለየ አመክንዮ የለውም ። አንተ ለአቅመ ስልጣን ስለ አልደረስኽ እኔ ልምራህ ነው ፤ የኹለቱም የእነ እዚኽ መንግሥታት የስልጣን ትርክት ። እንደ እዚኽ ዓይነቱ ለአቅመ ስልጣን አልደረስኽም እና እኔ ልምራኽ የእሚለው ፤ በተባበሩት መንግሥታት ከተደነገገው ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ሊከለከል አይገባም ተብሎ ከተደነገገባቸው ምክንያቶች አንዱን በቀጥታ የእሚጻረር ነው:-

“ፖለቲካዊ ፣ ኢከነሚያዊ ፣ ማሕበራዊ ወይንም ትምሕርታዊ ዝግጅት አለመኖር እንደ ምክንያት መቅረብ የለበትም…”

“Inadequacy of political, economic, social or educational preparedness should never serve as a pretext,…”

የዜጎችን ተፈጥሮዋዊ እኩል ነፃነት የእሚቀበል መንግሥት ፤ የዜጎችን ሕይወት እና ንብረት በፈለጉበት የመምራት ተፈጥሮዋዊ ነፃነታቸውን በፈጣን ማሕበራዊ እድገት ስም ለመቆጣጠር አይፈልግም ። የልማታዊ መንግሥት ግን በቀጥታ ይኽንን ነው የእሚያደርገው ።

ምንም ያኽል ችሎታ እና እውቀት ቢኖረን ፤ ይኽ የማስፈፀም አቅም ፤ ሕጋዊ እውቅናውን የእሚያገኘው እኩል ነፃ ሆኖ ፤ ንብረቱን እና ህይወቱን ከጥቃት መከላከል የፖለቲካ አጀንዳው ዋና ጉዳይ ከሆነው ዜጋ ይሁንታ እንደሆነ በመርህም ሆነ በተግባር መቀበል ከአልቻልን ፤ እያልን የአለነው ተፈጥሮዋዊ የነጻነት እኩልነትህን በመርህ ደረጃ ልቀበለው ብችልም እንኳን በተግባር ግን አላከብረውም ነው ።

አንተም እንደ እኔ እኩል ነጻ መሆንህን ብቀበለም ፤ እኔ በያዝኩት ልዩ እውቀት እና ችሎታ ፤ ከአንተ የተሻለ ፤ ለአንተ የእሚበጅህን አውቃለሁና ፤ ከእኔ መንገድ እና ከእኔ ውጭ ሌላውን እንድትመርጥ አልፈቅድልም ፤ የእሚል ማንም ኃይል ፤ የዜጎችን እኩል ነጻነት የፖለቲካ ስልጣን መሠረት መሆኑን የእማይቀበል መሆኑ ግልጽ ነው።

በሳይንሳዊ መንግሥታዊ ትርክት ውስጥ ፤ የመጨረሻው የነፃነት ዴሞክራሲያዉኑ ትርክት ነው ።

በነፃነት ዴሞክራሲያኑ ትርክት መሠረት ፤ የፖለቲካ ስልጣን ምንጭ ፤ የአንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ አባላትን ህይወት እና ንብረት በእኩልነት ለመጠበቅ ፤ ከአብዛኛው ሕዝብ የእሚገኝ ይሁንታ ወይንም ፈቃድ ነው ።

በእዚኽ ትርክት መሠረት ፤ የፖለቲካ ስልጣን ፤ ልዩ ፍጥረት ከመሆን ፣ የዘር ሐረግን ከመቁጠር ፣ የተደራጀ የጦር አቅም ይዞ ከመገኘት ፣ በታሪክ አጋጣሚ ተቀጣሪ በመሆን ወይንም ልማት ይቀድማል ብሎ ማሰብ ከመቻል ፣ የላቀ የሕዝብ አስተዳደር እውቀት እና ልምድ ከመያዝ ሰአይሆን ፤ በሕዝብ ፥ የተፈጥሮ ሕግ ነፀብራቅ የሆነውን ማሕበራዊ ውል ፤ በተሻለ ይንከባከባል ተብሎ ከመታመን እና የአብዛኛውን የሕዝብ ይሁንታ ከማግኘት ነው ።

ሠንጠረዥ 6 ፡ መንግሥታዊ ትርክቶች እና የሕጋዊ የፖለቲካ ምንጭ ትንታኔያቸው።

የፖለቲካ ስልጣን ፋይዳ ከተለያዩ መንግሥታዊ ትርክቶች አንጻር ፦

እነ እዚኽ የተለያዩ መንግሥታዊ ትርክቶች ፤ ከሕጋዊው የስልጣን ምንጭ ትንታኔያቸው አንፃር በእዚኽ መልክ ተለያይተው ሲያበቁ ፤ የፖለቲካ ስልጣን ባለው ፋይዳ ላይም የእየ ራሳቸው የተለያየ ትንታኔ አላቸው ።

መለኮታዊያኑ ፤ እንደ አልነው ፥ ሳይንሳዊ ባሕሪ የሌላቸው በመሆኑ ፤ የፖለቲካ ስልጣንን ፋይዳ በተመልከተ ይኽ ነው የእሚባል ነገር ማስቀመጥ አይቻልም ፤ ወቅታዊ የሆነው የስረዓቱ መሪ እንደፈለገው የእሚመራ በመሆኑ ።

የእዚኽ ሐገር ንጉሥ ፤ ልጅህን ለልጄ ብለው ፥ እምቢ አለ ብለው ፤ ዓመታት የእሚፈጅ ጉዞ አድርገው ጦርነት ሊያደርጉ ይችላሉ ወይንም የፖለቲካ ስልጣናቸው እንደ እዚኽ ዓይነቶቹን ጀብዱ የመፈጸም ፋይዳ ይኖረዋል ።

ለምወዳት ቅድመ አያቴ ፤ የመቃብር ፒራሚድ ሕዝቡ ኹሉ ሊሰራ ይገባል ይኽን እምቢ ያለ በሞት ይቀጣል ብለው ፤ ሐገሬውን ለዓመታት ፒራሚድ ሊያሰሩት ይችላሉ ። በአጠቃላይ ለመለኮታዊያኑ ፤ ስልጣን በዋናነት የነጋሢውን ማንኛውንም ምኞት ከማስፈፀም ያለፈ ይኽ ነው የእሚባል ፋይዳ የለውም ። ያ ማለት ግን ፤ እንደ ነጋሢው ግላዊ ባሕሪ እና ጠባይ ፤ ትልልቅ ሕዝባዊ ፋይዳ የአለው ተግባር አይፈፅሙም ሰአይሆን ፤ የእሚያመጡት ልማትም ሆነ ውድመት በወቅታዊ ነጋሢው ስሜት የእሚወሰን በመሆኑ ፤ ወጥነት የለውም ለማለት ነው ።

አስቀድመን እንደ አልነው ፤ እነ እዚኽን መሰል ነገሥታት ናቸው ፣ የግብጽን ፣ የባቢሎንን ፣ የፋርስን ፣ ወዘተ ፤ ስልጣኔ የመሩት ።

የስነ መሎኮታዊያኑ (አባታዊያኑ ወይንም ቅባቅዱሳዊያኑ) እና አምባገነን ማሕበራዊ ውልተኞቹ ፤ በስልጣን ፋይዳ ላይ ተመሳሳይ አቋም ነው የአላቸው ፤ ምንም እንኳን ለአቋማቸው የእሚያስቀምጡዋቸው መነሾዎች የተለያዩ ቢሆኑም ። ኹለቱም ፥ የፖለቲካ ስልጣን ፋይዳው ፤ በተፈጥሮው ወይንም በባሕሪው ለትርምስ ቅርብ በሆነ ማሕበረሰብ ወስጥ ፤ ትርምስ እንደ አይፈጠር የማቀብ ፋይዳ ነው ።

ለስነ መለኮታዊያኑ ፦ ሕዝብ በባሕሪው ሙልጭልጭ እና በነፈሰበት በመሆኑ ፥ ሕዝብ በግዚያዊ ስሜት እየተነዳ ማሕበራዊ ቀውስ እንደ አይፈጠር ፥ ተለዋዋጩ ሕዝብ ከአገኘው ጋር እንደ አይነጉድ ፤ የሰከኑ ሰዎች ሕዝቡን የማገድ ሥራ እንዲ ሰሩ ነው ።

የስነ መለኮታዊያኑ እና የአምባገነናዊ ማሕበራዊ ውልተኞቹ ፤ የፖለቲካ ስልጣን ፋይዳ ትንታኔ ፤ ከላይ ሲታይ ከነጻነቱ ዴሞክራሲ ጋር ተመሳሳይ ይመስላል ፤ ምክንያቱም ፦ ኹለቱም የፖለቲካ ስልጣን ፋይዳን ፤ ሕግ እና ስረዓትን ከማስከበር ጋር በዋናነት ስለ እሚያይዙት ። ትልቁ ጥያቄ ግን ፤ መንግሥት ሕዝብ እንዲያከብረው የእሚያስገድደው ሕግ የትኛውን ሕግ ነው ? የእሚለው ጥያቄ ነው።

ለምሳሌ ፦ መንግሥት ሕግ እና ስረዓትን በማስከበር ስም ፤ ሳልመረጥ በስልጣን ላይ ልቆይ ቢል ፣ የዜጎችን የመምረጥ እና የመመረጥ መብት ቢያግድ ፣ ዜጎች ኃሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ እንደ አይገልጹ ቢያግድ ፣ ሊፈቀድለት ይገባል? ወይንም ይኽን መሰሉን ሕግ ስለ እማከብር በስልጣን ላይ ልቆይ ቢል እና ዜጎች የመምረጥ መብቴን ፣ ኃሳቤን የመግለጥ መብቴን ፣ ወዘተ ፤ ገፈኃል እና አልቀበልህም ብለው ቢያምጹበት እና ይኽንን ፍትኃዊ የዜጎች አመጽ ለማስቆም ኃይል ቢጠቀም ፤ ተገቢነት የአለው ሕግ አስከባሪ ነው ሊባል ነው?

በአጠቃላይ ፤ መንግሥት የእሚያስፈልገው ማሕበራዊ መረጋጋትን ለማስፈን መሆኑ ተቀባይነት የአለው ቢሆንም መንግሥት ግን ይኽን ማሕበራዊ መረጋጋት ማምጣት የእሚችለው ፤ መንግሥት ለማከበርተ የእሚንቀሳቀሰው ሕግ ፤ የተፈጥሮ ሕጉ ነጸብራቅ የሆነውን ሕግ ብቻ ሲሆን ነው።

ከተፈጥሮ ሕጉ የእሚቃረንን ማንኛውንም ሕግ ለማስከበር መንግሥት ሲንቀሳቀስ ፤ በግዜያዊ የኃይል ስሌት የበላይነት ስለ አለው ፤ አንጻራዊ ሰላም ሊፈጥር ቢችልም ፤ ከመሠረታዊ የሰዎች ተፈጥሮዋዊ ነጻነት እና መብት ጋር ስለ ተጋጨ ፤ በግዜ ኺደት ወደ መሐበራዊ አለመረጋጋት እንደ እሚያመራ ጥያቄ የለውም።

የስነ መለኮታዊያኑ እና የአምባገነናዊ ማሕበራዊ ውልተኞቹ ፤ የፖለቲካ ስልጣን ትርክት ፤ ይኽንን ስለ እማይቀበል ወይንም ዜጎች መንግሥት ቢበድላቸውም እና ቢረግጣቸውም ሕግ በማስከበር ስም ማንኛውንም ተፈጥሮዋዊ ነጻነታቸውን እና መብታቸውን በቋሚነት ቢገፍባቸውም ፤ ለማሕበራዊ መረጋጋት ሲሉ ዝም ይበሉ የእሚል ስለ ሆነ ፤ ከነጻነቱ ዴሞክራሲ የፖለቲካ ስልጣን ትርክት ይለያል።

የሠራተኛው አምባገነንነት መንግሥታዊ ትርክት ፤ የስልጣን ፋይዳው ኹለት ነው ። የመጀመሪያ ፥ ከእዚኽ በፊት ጨቋኝ የነበረው እና በሠራተኛው አብዮት ከስልጣን የተወገደው መደብ ፤ ተመልሶ ወደ ስልጣን እንደ አይመጣ እና መጥፎ ልማዱን እንዳያስፋፋ ፤ እርሱን መጨቆን ነው ።

ኹለተኛው ፤ በማሕበረሰብ ተፈጥሮዋዊ ለውጥ ኺደት ፤ ሰዎች ከስግብግብነት ፣ ለክፍያ ከመሥራት ፣ የግል ንብረት ከማፍራት ፍላጎት ፣ ወዘተ ፤ ተላቀው ፤ ሥራ ህይወታቸው ስለ ሆነ ወደ የእሚሰሩበት በእዛኽም የከምኒዝም ምድራዊ ገነት እስኪፈጠር ፤ ይኽንን የታሪካው ሽግግር ኺደት በአምባገነንነት ለመምራት ነው ።

ይኽ ዓይነቱ የሠራተኛው ዓምባገነናዊነት የፖለቲካ ስልጣን ፋይዳ ትርክት ደግሞ መሠረታዊ የሆነው የዜጎችን ተፈጥሯዊ ነጻነት እና ሕጋዊ በሕይወት የመኖር እና ንብረትን ከጥቃት እና አደጋ የመከላከል መሠረታዊ ፍላጎትን በቀጥታ የእሚጥስ በመሆኑ ፤ ኢሰብአዊ ነው።

ለልማታዊያኑ የመንግሥት ስልጣን ፋይዳ ፤ በኢከነሚ ውስጥ የአለምንም ከልካይ ኃይል ወይንም ሕግ ፤ ጣልቃ እየገቡ ፈጣን የኢከነሚን እድገት ማረጋገጥ መቻል ነው ። መንግሥት ፈጣን እድገት ያመጣል ብሎ በአመነበት መስክ ጣልቃ ከመግባት የእሚያግደው ምንም ዓይነት ኃይል መኖር የለበትም እንዲያ ከሆነ በነዳያን ሐገር ውስጥ ያለ የፖለቲካ ስልጣን ፋይዳ የለውም የእሚል ነው።

የልማታዊያኑ የፖለቲካ ስልጣን ፋይዳ አስተሳሰብ ከሠራተኛው የአምባገነነት የስልጣን ፋይዳ አስተሳሰብ ብዙም የእማይለይ እና አንዳች ዓይነት የሩቅ ግብን ፤ በልማታዊያኑ ግዜ ፤ ፈጣን ኢከነሚያዊ እድገትን ታሳቢ አድርጎ ፤ የዜጎችን ተፈጥሮዋዊ ነጻነት እና ንብረት የማፍራት መብት ማፈን መቻልን ታሳቢ የአደረገ በመሆኑ ፤ ከመሠረታዊው የዜጎች ተፈጥሮዋዊ ነጻነት ሕግ ጋር በተቃራኒ የቆመ ነው።

የፖለቲካ ስልጣን ፋይዳን በተመለከተ ፤ የነፃነት ዴሞክራሲ ትርክት ከአምበገነናዊ ማሕበራዊ ውልተኞች የእሚለየው ፤ የማሕበራዊ ውሉን እንዲያስከብር ወይንም እንዲንከባከብ ወደ ስልጣን የእሚመጣው ኃይል ፤ ራሱ ከማሕበራዊ ውሉ ግዴታ ነፃ ሊሆን አይችልም በእሚለው አቋሙ ነው ። ምክንያቱም ፦ ወደ መንግሥት ኃላፊነት የእሚመጡ ሰዎች እንደ ሌላው ሰው ተመሳሳይ ባሕሪ የተላበሱ ሰብዓዊ ፍጡራን በመሆናቸው ፤ ለራሳቸው አድልተው በአደራ የተሰጣቸውን ስልጣን ከተፈጥሮ ሕጉ አግባብ ውጭ የራሳቸውን ስግብብ ጥቅም በማሳደድ ፤ ዜጎች ያለ መንግሥት እርስ በእርስ በመበዳደላቸው ሊፈጥሩ ይችሉ የነበረውን የተፈጥሮ ኹኔታ ፤ በመንግሥታዊ በደል በተመሳሳይነት ሊፈጥሩት የእሚችሉ ስለሆኑ ፤ ወደ መንግሥት ስልጣን የእሚመጡም ሰዎች ፤ እንደ ማንኛውም ዜጋ በተፈጥሮ ሕጉ መገዛት አለባቸው።

በእዚኽም መሠረት ፤ የመንግሥት ቀዳሚ ኃላፊነት ፤ ማሕበራዊ ውሉን ማስከበር ነው ፤ ነገር ግን ፤ አስከባሪው ራሱ እንደ ሌላው ሕዝብ ተፈጥሮዋዊ ሰው በመሆኑ ፤ ኃላፊነቱን በመዘንጋት ስልጣኑን የራሱን ጥቅም ማስከበሪያ እንደ አያደርገው ፤ በእዚኽም ከማሕበራዊ ውሉ ትሩፋት ፥ ሠላም እና መረጋጋት ወደ ጦርነት ኹኔታ ማሕበረሰቡን እንደ አይከልሰው ፤ የፖለቲካ ስልጣኑ ፤ አፈፃፀሙ የእሚፈተሽ ወይንም ተጠያቂነት የአለበት ፣ ኃላፊነቱን ከአልተወጣ ከኃላፊነቱ የእሚነሳበት ፣ ያልተማከለ እና ኃላፊነቱ የሚታደስ መሆን አለበት የእሚል ነው ወይንም መንግሥት ራሱ ለማሕበራዊ ውሉ ተገዢ እና የማሕበራዊ ውሉ አክባሪ መሆን አለበት የእሚል ነው ።

ሠንጠረዥ 7 :መንግሥታዊ ትርክቶች እና የፖለቲካ ስልጣን ፋይዳን የእሚተነትኑበት አግባብ።

የፖለቲካ ስልጣን ትርክቶች እና የፖለቲካ ስልጣን ድንበር ፦

የስልጣን ገደብ ወይንም ድንበር የእሚለው ላይ ስንመጣ ፤ ከነፃነት ዴሞክራሲያዊኖቹ በስተቀር ፤ ኹሉም የገደብ የለሽ ስልጣን አስፈላጊነት የእሚያምኑ ናቸው ። እንደ አልነው አምላካዊያኑ የስልጣን ትንታኔ ስለ ሌላቸው ፤ የስልጣናቸው ገደብ የነጋሢው ውሳኔ እና ፍላጎት ነው ። ከእዚያኽ በተረፈ አምባገነናዊያኑ በሙሉ ፤ የስልጣን ፋይዳ ለእሚሉዋቸው ፤ ማለትም ፦

  • ለዓምላካዊያኑ የነጋሢውን ምኞት ለማስፈጸም
  • ለስነመለኮታዊያኑ እና ለአምባገነን ውልተኞቹ ፤ ሕግ እና ስረዓት ለማስፈን
  • ለሠራተኛው አምባገነን መንግሥታት ፤ ጭቋኙን ለመጨቆን እና ከካፒታሊዝም ወደ ከምኒዝም የእሚደረገውን ሽግግር ለመምራት
  • ለልማታዊያኑ ፈጣን ኢከነሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ ፤ ያልተገደበ ኢከነሚያዊ ጣልቃ ገብነት እንደ አስፈላጊነቱ ለማድረግ

እነ እዚኽን ዓላማ በእየፈርጁ እስከ አሳካ ድረስ ስልጣንን ያለገደብ መጠቀም የእሚፈቅዱ ሲሆን በእዚኽ አጋጣሚ የእሚፈጠሩ የስልጣን መባለጎች ወይንም የመብት ረገጣዎች ትልቁ ዓላማ እስከ ተሳካ ድረስ አላስፈላጊ ነገር ግን አሳዛኝ ገጠመኝ ተብለው መታለፍ የእሚችሉ ናቸው ።

ስለ እዚኽ ፦ ለአምባገነናዊ ስረዓቶቹ ፤ ቅዱስ የተባሉት ፦ ሕግ እና ስረዓት ወይንም ፈጣን እድገት ፣ ወዘተ ፤ እስከ ተሳኩ ድረስ ፤ ምንንም ነገር ማሕበረሰብ መሸከም ይገባዋል ወይንም አለበት የእሚል አስተሳሰብ ነው የእሚያንፀባርቁት ።

የነፃነት ዴሞክራሲ ግን ከእነ እዚኽ ኹሉ በተቃራኒ ፤ የማሕበራዊ ውሉ አንኳር ከሆነው ፤ የማሕበራዊ ውልተኞቹን ወይንም የዜጎችን ፤ ህይወት እና ንብረት ደህንነት በእኩልነት ከማስጠበቅ የላቀ ቅዱስ ዓላማ የለም የእሚል ነው ወይንም ማንኛውም መልካም የተባለ ርዕይ ከእዚኽ ቅዱስ ዓላማ ጋር የእሚጋጭ ከሆነ አጥፊ ነው የእሚል ነው ።

ከእዚኽም የተነሳ ፦ማንኛውም ቅዱስ የእሚባል ዓላማ ፤ የዜጎችን ተፈጥሮዋዊ እኩል ነፃነት ማክበርን ወይንም የተፈጥሮ ሕጉን ተፃሮ ከቆመ ወደ ጦርነት ሁኔታ (State of War) ማሕበረሰብን የእሚመልስ በመሆኑ ፤ የመንግሥት ስልጣን ገደብ ወይንም ድንበር የተፈጥሮ ሕጉ መሆን አለበት የእሚል ነው ።

ሕግ እና ስረዓት ለማስከበረም ይኹን ወይንም ፈጣን እድገት ለማምጣት በእሚል ፤ መንግሥት ገደብ የለሽ ስልጣን ከተሰጠው ራሱን ወደ ጨቋኝ መንግሥት እንደ አይቀይር የእሚያግደው ነገር በአለ መኖሩ ፤ አንድ መንግሥት ራሱን በግዜ ኺደት ወደ ጨቋኝነት ከለወጠ ደግሞ ፤ ማሕበረሰብ ወደ ጦርነት ኹኔታ ስለ እሚከለስ ፤ ቁርሾዎች ወደ ለየለት ሕዝባዊ አመፅ ሲከፋም ወደ እርስ በእርስ ጦርነት እንደ አይገቡ ሊያግድ የእሚችል ሳይንሳዊ ወይንም የአመዛዝኖ ምክንያት በአለመኖሩ ፤ ማሕበራዊ ውሉ የመንግሥት ስልጣን ድንበር መሆኑ የግድ ነው የእሚል ነው ። ስለ እዚኽ ፦ የመንግሥት ስልጣን ፤ በፍፁም የተፈጥሮ ሕጉን የእሚፃረር መሆን የለበትም ወይንም የመንግሥት ስልጣን ድንበር ፤ የማሕበራዊ ውል ትሩፋቶች ጋር መሆን አለበት ።

በአጠቃላይ ፦ ከነፃነት ዴሞክራሲ ውጭ ለአሉ፟ት አምስት መንግሥታዊ ትርክቶች ፤ ስልጣን ወሰን የለሽ ከአልሆነ ስልጣን ነው ተብሎ የእማይታሰብ ነው ።

አምባገነን መንግሥታዊ ትርክቶች ተፈጥሮዋዊ እና የጋራ የሆኑትን የግለሰቦች ፤ በህይወት የመኖር ፣ የነፃ ፈቃድ ፣ የህይወት እና ንብረትን ከአደጋ የመከላከል መብቶችን ያለ ተጠያቂነት መሻር መቻል የስልጣን ፍልስፍናቸው ዋና አካል ነው ወይንም የፖለቲካ ስልጣን ግብ ይኽንን ያለ ሕግ ተጠያቂነት ማድረግ መቻል እንደ ኾነ አድርገው ይቆጥራሉ ።

ለነፃነት ዴሞክራሲ ደግሞ እነ እዚኽን ተፈጥሮዋዊ መብቶች በፍትሕ ስረዓት ሰአይሆን በፖለቲካ ስልጣን መሻር ፤ የዜጎችን የደህንነት ዋስትና ስጋት ላይ ስለ እሚጥለው ፤ ዜጎች ለመንግሥት በውክልና የሰጡትን ህይወታቸውን እና ንብረታቸውን የመከላከል መብት መልሰው ለመውሰድ ይንቀሳቀሳሉ ፤ ያም የመበደል ስሜት በግዜ ኺደት ማሕበራዊ ነውጥ ሲከፋም የእርስ በእርስ ጦርነት ያስነሳል የእሚል ነው ።

ለምሳሌ ፦ ገንዘብ ተበድሮ ንብረት ያደራጀ ወይንም ኃብት ያፈራ ሰው ፤ ብድሩን በገባው ውል መሠረት ከአልከፈለ ፤ የገባው ውል በእሚያዘው አግባብ ያደረጀውን ኃብት ፤ ፍርድ ቤት ፤ ለተበደረው ብድር መክፈያ እንዲሆን ሊያዝበት ይገባል ። ይኽ በፍርድ አግባብ የሆነ ፤ የንብረት ባለቤትነት መብት መነፈግ ነው ። አንድ ሰው በብድር ያፈራው ኃብት ብድሩን ከአልከፈለ ፤ የንብረት ባለቤትነት መብቱ ፤ ከአበዳሪው አንፃር ፤ መነፈግ የእሚችል ነው ። ስለ እዚኽ ፤ የነጻነቱ ዴሞክራሲ ፤ በመርኽ ደረጃ የእሚቀበለው እና ተገቢ የእሚለው ይኽን መሰሉን በሕግ አግባብ የሆነ የመብት ገፈፋ ብቻ ነው ።

ኸእዚኽ ውጭ ግን ፤ አንድ ዜጋ ብድሩን የከፈለበትን ወይንም ብድር የሌለበትን የራሱን ንብረት ፦ በፓለቲካዊ ስረዓት ስሪት ፤ ለምሳሌ ፦ በሶሻሊስት አብዮት ወይንም በልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ ምክንያት ወይንም ደግሞ የመንግሥት ባለስልጣናት ተጠያቂ የእሚሆኑበት አግባብ በአለመኖሩ ምክንያት ዋልጌ የመንግሥት በአለስልጣናት የዜጎችን የንብረት ባለቤትነ መብት ላይ አደጋ የእሚደቅኑ ከሆነ ፤ ወይንም በአጭር አገላለጽ ፤ የዜጎች የንብረት ባለቤትነት መብት ፤ በሕግ አግባብ ሰአይሆን በፓለቲካዊ ውሳኔ አደጋ ውስጥ የእሚገባ ከሆነ ፤ ፍትሕ የተጓደለበት ፣ ተፈጥሮዋዊ መብቱ የተነፈገበት ስለ እዚኽም ኹኔታ ሲያመቸው መብቱን ለማስከበር ጉልበትን አማራጭ የእሚያደርግ ዜጋ ተፈጠረ ማለት ነው ።

ይኽ ዓይነቱ ኹኔታ ሲደጋገም ፤ በማሕበረሰብ ውስጥ ገንፍሎ ወጥቶ ግልፅ ጦርነት በአይከሰትም እንኳን ያ ማሕበርሰብ ግን የጦርነት ኹኔታን በውስጠ ታዋቂነት እንዲይዝ የእሚያደርግ በመሆኑ ፤ ማሕበረሰቡ ፦ በሰፊ የሰው ኃይል ስደት ፣ የኃብት እና የእውቀት ሽሽት ፣ ወዘተ ፤ ለማሕበራዊ ድካም እና አለመረጋጋት ይጋለጣል ።

ይኽ በመርህ ደረጃ የእሚቀመጥ ፤ አንድ የፖለቲካ ማሕበረሰብ ሊሆን ይገባል ወይንም መምሰል አለበት ከእሚባለው አንጻር የእሚቀመጥ ትንታኔ እንጂ የመብት ረገጣ ኹሉ ወደ ግልፅ የሆነ ጦርነት ኹል ግዜ ያመራል ማለት አይደለም ። ለምሳሌ ፦ እንደ ምሥራቅ ኤስያ በአሉ ፤ ብዙ የውጭ ኃይላት የተሳተፉበት ፥ ለመግለፅ የእሚከብዱ አሰቃቂ ጦርነቶች ለረዥም ዓመታት በተካኼዱበት አከባቢ ወይንም ከእላይ እንደ ዐየነው ዓይነት እንደ የኮንፊሸሳዊ በአሉ ባሕላዊ አስተሳሰብ ለዘመናት የተያዙ ሕዝብ ለዓመታት ወይንም ለረዥም ዘመን ፤ ልማታዊ ወይንም ሌላ ዓይነት አምባገነን መንግሥታት ፦ የንብረት ፣ የህይወት ወይንም የነፃነት መብቱን ሲገፉበት ‘ሊታገስ’ ይችላል ወይንም የዓለም ዓቀፍ ፓለቲካ የኃይል አሰላለፍ በአንድ ሐገር ውስጥ አንድ አምባገነናዊ መንግሥት ከሕዝቡ ጭቆናን እምቢ የማለት አቅም በላይ ሆኖ በስልጣን ላይ እንዲቆይ ሊያደርገው ይችላል ።

ሕዝብ እንደ ሕዝብ ፤ በተፈጥሮዋዊ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ሲዝል ፤ ይኽ መዛሉ የእሚፈጥርበት ተጋላጭነት ፤ ወይንም በዓለም ዓቀፋዊ ፓለቲካ ምክንያት በግዚያዊነት ማሕበራዊ ውሉ ሲጣስ ዝም ሊል እንዲችል ሊያደርገው ይችላል።

ይኽ ግን ፤ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ፤ በመርህ ደረጃ ማሕበራዊ ውል የፖለቲካ ስልጣን ምንጭ እና ድንበር ነው የእሚለውን አያፈርሰውም ።

ሰው ተፈጥሮዋዊ የሆነ ራሱን ከጥቃት የመከላከል ባሕሪ አለው ፤ ይኽ ማለት ግን አንድ ሰው በተለያየ ምክንያት እና አጋጣሚ ፤ ተዳክሞ ወይንም ከእርሱ እጅግ የእሚገዝፍ ኃይል ተጋፍጦ ጥቃትን መከላከል አለመቻልን እንደ ታሪካዊ ማሳያ በመውሰድ ፤ ሰው በመሠረታዊነት ራሱን ከጥቃት የመከላከል ተፈጥሮዋዊ ባሕሪ አለው የእሚለውን እውነታ መቀየር አይቻልም።

ሰው ተፈጥሮዋዊ የሆነ ጥቃትን የመከላከል መብት እና አቅም አለው ፤ በተለያየ ምክንያት ግን ሰው ጥቃትን ሊታገስ ወይንም እራሱን ሊከላከል በእማይችልበት አኳኋን ለጥቃት ሊጋለጥ ይችላል።

ሠንጠረዥ 8 ፡ ፖለቲካዊ ትርክቶች እና የፖለቲካ ስልጣን ድንበር ክልል ትንታኔያቸው።

ለማጠቃለል ፦ የስልጣን ትርክቶችን ዝግመት እንደ አየነው ፤ በአምባገነናዊ ትርክቶች ጎራ ፦ ልዩ ፍጥረት የለም ከተባለ በኋላ ፣ አባትነት ወይንም አንዳች ዓይነት መለኮታዊ ሲመት ምክንያት ሆኖ መጣ ፣ አባትነት ወይንም በተለየ ኹኔታ መመረጥ የፖለቲካ ስልጣን ምንጭ ምክንያት መሆን እንደ እማይችል ሲረጋገጥ ፣ መሳሪያ መታጠቅ እና አመጽን የመበተንን ኃይል በበላይነት ይዞ መገኘት ምክንያት ሆኖ መጣ ፣ በኃይል የበላይነት የእሚረጋገጥ ስልጣን ማብቂያ ወደ ሌለው የኃይል እሽቅድድም ውስጥ ከማስገባቱ በአሻገር ቆይታው የኃይል የበላይነት እስከ አለ ብቻ መሆኑ ሲታወቅ ፣ ነዳያኑ ብዙ ስለሆነ እና ድህነቱ የጭቆና ውጤት በመሆኑ ፍፁማዊ የፖለቲካ ስልጣን የነዳያን ብቻ ነው ተባለ ፤ ነዳያኑም የፖለቲካ ስልጣንን በህይወት ለመቆየት እና ንብረት ከማፍራት ውጭ ለሌላ ጉዳይ እንደ እማይፈልገው ግልፅ እየ ሆነ ሲመጣ ፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን በብቸኝነት ተዋጊ እና ፈጣን ልማት አስመዝጋቢ ‘ጀግኖች’ ተብሎ ፤ ስልጣን የልማት አርበኞች ሊሆን ይገባል ተባለ ፤ የልማት አርበኝነት ፍፁማዊ የፖለቲካ ስልጣን ላይ የእሚደገፍ አለመሆኑ ግልፅ እየሆነ በመሆኑ ፤ አምባገነናዊ የመንግሥት ትርክት አዲስ ሌላ ምክንያት ይዞ ከአልመጣ በኃሳብ ገበያው ቦታውን እያጣ ነው ።

አምባገነናዊ መንግሥታዊ ትርክት ፦ ምክንያቱ ምንም ይኹን ምን ፤ ከሰዎች ተፈጥሮዋዊ ነፃነት ግብ ፤ እርሱም ህይወትን ማቆየት እና ህይወትን ማሻሻል ጋር ፤ በአንድም በሌላም መንገድ ስለ እሚጋጭ ፤ በእዚኽም የዜጎችን በህይወት የመኖር እና ንብረት የመያዝ መሠረታዊ ፍላጎት ወይንም መብት አደጋ ውስጥ የእሚጥል በመሆኑ ፤ የማሕበራዊ አለመረጋጋት እና የማሕበራዊ ድህነት ምክንያት ነው ።

ይኽ በመሆኑ ፤ ምንም እንኳን ፤ በተለያዩ ፖከቲካዊ እና ታሪካዊ ምክንያቶች የአተገባበር ችግር እየገጠመው ፤ የተጠበቀበትን ያኽል ውጤታማ በአይሆንም ፤ አኹን በዓለም ላይ ፤ የፖለቲካ ስልጣንን ምንጭ ፣ ፋይዳ እና ድንበር ፤ ማሕበራዊ ደህንነትን እና ፍትኃዊ እድገትን በተሻለ ኹኔታ እያስቻለ የዜጎችን ተፈጥሮዋዊ እኩል ነጻነት ከእሚያከብረው ከነፃነት ዴሞክራሲ የተሻለ ርዕዮት ያለ አይመስልም ።

  1. ኦሊቨር ክሮምዌል በእንግሊዝ ንጉሥ ላይ አምጾ ፤ ንጉሱን በጦርነት አሸንፎ እና በፓርላማ ንጉሱን ሐገር ከዳተኛ በእሚል ከሶ እና ጥፋተኛ አስብሎ አስፈርዶ ፤ አንገቱን በማስቀላት ያስገደለ ሰው ነው። ↑