ሕ ገ ክ ራ ሲ

marketing-image

3.2. የኢትዮጵያ የፖለቲካ ዝግመታዊ እድገት

የእዚኽ ንዑስ ክፍል ዓላማ ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በረጅሙ ታሪኩ ውስጥ ፥ ሕዝባዊት ወይንም ዴሞክራሲያዊ ሐገር ለመሆን የኼደበትን ፖለቲካዊ ጉዞ መቃኘት ነው ። ዴሞክራሲያዊት ሐገር ሆነናል ወይ ? የእሚለው ጥያቄ አሉታዊ መልስ የአለው መሆኑ እርግጥ ሆኖ ፤ ከጀመርንበት ፥ ከዛሬ ሦሥት እና አራት ሺ ዓመት አንፃር ግን ፤ ከመቼውም ግዜ በላይ ለዲሞክራሲያዊት ሐገር ህልም መሳካት መቅረባችን ግልፅ ነው ።

ዴሞክራሲያዊት ሐገር ስንል ፥ በእዛች ሐገር ውስጥ ፤ የሰዎችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት ማክበር እና ማስከበር ፤ የፖለቲካዊ መዋቅሩ ዋነኛ እና የእማይሸራረፍ መዓከላዊ ግቡ የሆነ እና ይኽንም በእሚያስችለው የፖለቲካ ስረዓት ፤ የእሚፈጠረውን ‘ፍትሐዊ’ ኢከነሚያዊ ወይንም መሐበራዊ እድገት ነዋሪዎች ፤ ከሌሎች ፖለቲካዊ ስረዓቶች በተነጻጻሪነት በተሻለ ኹኔታ በርካታ የእሚጋሩበት ኹኔታ መፍጠር ወይንም ይኽንን ፖለቲካል ኢከነሚ ማስቻል ፤ እያልን ነው ።

ምክንያቱም ፦ የዜጎች ዴሞክራሲያዊ እና ሰብዓዊ መብቶች በአልተከበሩበት ስረዓት ውስጥ ዜጎች በእርካታ የእሚጋሩት ማሕበራዊ ዕድገት ማስመዝገብ የእሚቻል አይደለም ። ይኽም በመሆኑ ፤ ይኽ ንዑስ ክፍል ፤ እኛ ኢትዮጵያዊያን ፥ ይኽን የፖለቲካ ምህዳር ለመፍጠር የኼድንበትን ፖለቲካ መንገድ መቃኘት የትኩረቱ መዓከል ያደርጋል ።

ይህንንም ለማድረግ ፤ ከጥንተ ጥንት ወይንም ከመጀመሪያው አንስቶ ፤ ዛሬ እስከ አለንበት ዘመን የአለውን ግዜ ፤ በዘጠኝ ክፍሎች ከፋፍሎ ፤ በእየ ክፍሎቹ ፥ ዴሞክራሲያዊት ሐገር ለመፍጠር የተመዘገቡ ስኬቶች (ከአሉ) እና የነበሩ ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ፈተናዎች ይመለከታል ።

መገመት እንደ እሚቻለው ፤ ዴሞክራሲያዊት ሐገር ለመፍጠር የተደረገውን ፖለቲካዊ ጉዞ እንቃኛለን ሲባል ፤ መቼም ከረጅሙ ታሪካችን አንፃር ፤ ዴሞክራሲ የእሚለው ቃል ፥ እንኳን ለሐገራችን ፥ ለቀረውም ዓለም (ግሪኮች እና ሮማኖች ሲቀሩ) የፖለቲካ መዝገበቃላት ራሱ አዲስ ቃል እንደሆነ በመዘንጋት ሰአይሆን ፥ በእዚኽ መጽሐፍ ምዕራፍ አንድ ላይ ስለ ዴሞክራሲያዊ ሐገር ስናወራ ፥ የፖለቲካ ሳይንስ መስክ ቀዳሚ ሳይንቲስቶች ከእሚባሉት ጎራ የእሚመደበው ፤ የግሪኩ አርስታትል ፥ የሰው ግብሩ መልካም ነው ብሎ የእሚያስበውን ነገር ለማግኘት ከመፈለግ ይመነጫል ፤ ስለ እዚኽም ማሕበረሰብን ሰው ሲያቋቁም አንዳች መልካም ነው ብሎ ሊያገኘው የፈለገው ጥቅም እንደ አለው ታሳቢ በማድረግ ነው ፤ በአለበት አግባብ ፤ ይኽን የሰው ልጅ መልካምን የእሚያደርግለትን ማሕበረሰብ ለመፍጠር የኼደበትን ጎዞ እያልን ነው ፤ ዴሞክራሲም የእዛ ጥረት ፍሬ ወይንም ውጤት በመሆኑ ።

እንደ ሰው ፥ እኛም ኢትዮጵያዊያኖች ፤ ኢትዮጵያ የእምትባለውን የፖለቲካ ማሕበረሰብ ወይንም ሐገር ስንፈጠር ፥ ዴሞክራሲያዊት ሐገር እንፍጠር ብለን አስበን ለመፍጠር እንዳልተነሳን የእሚታወቅ ቢሆንም ቅሉ ፦ የእምታስረን ፣ የእምታፈናቅለን ፣ የእምታደኸየን ፣ ኋላ ቀር የእምታድርገንን ሐገር ለመፍጠር እንዳልተነሳን ግን ግልፅ ነው ።

መልካም ነው ብለን ያሰብነውን ነገር ወይንም ደስታን ስንሻ (In our pursuit of humanly possible and rational happiness) ፤ ይኽን ደስታ የእሚሰጠን ፤ ዴሞክራሲያዊ ሐገር ነው ወይንም ዴሞክራሲያዊ ሐገር በእዚኽ ፥ በእዚኽ መርህ ነው የእሚገነባው የእሚል ቅድመ-ዕውቀትም ይዘን እንዳልተነሳን መረዳት ብዙም አያዳግትም ። ነገር ግን ፥ እንደ ሰው ጤናማውን ደስታን መሻታችን ፤ ማሕበረሰባችንም ይኽንን ደስታችንን ሲሆን ማገዝ ፥ ማገዝ የእማይችል በእሚሆንበት ግዜ ፤ ይኽንን ቅዱስ ጉዞዋችንን የእሚያደናቅፍ እንደ አይሆን መፈለጋችን ግን ግልፅ ነው ፤ ሰው ነንና።

ስለ እዚኽ ፦ ዴሞክራሲያዊት ሐገር ለመገንባት የተጓዝንበትን ፖለቲካዊ ጉዞ የእሚያስቃኝ ስንል ፤ ሲሆን ይህን ሰዋዊ ደስታ የመሻት ጉዞዋችንን የእሚያግዝ ፥ እሱ ሳይቻል ደግሞ ይኽንን መልካም እና የተገባ ሰብዓዊ ደስታን የመፈለግ ጉዞዎችንን የእማያደናቅፍ ማሕበረብ ለመመሥረት የአለንን ውስጣዊ እና ተፈጥሮዋዊ መፈለግ እና መመኘት ፥ ለማሳካት የተጓዝንበት የፖለቲካ ጉዞ ማለታችን ነው ።

ዴሞክራሲን የከሰተው ፤ ይኽን ፍላጎት ፥ ይኽን መሠረታዊ ሰብዓዊ ፍላጎት ፤ በሕዝብ ወይንም በግለሰቦች ዘንድ እንዲኖር ደግሞ የፖለቲካ ሳይንስ ጠበብት መሆን አይጠይቅም ፤ ውስጣዊ የሰው ፍላጎት ስለሆነ ፤ ሰው መሆን ብቻ በቂው ነው ።

እንደ አንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ፤ ሰብዓዊ ደስታን የመፈለግ ሰብዓዊ ባሕሪያችን ፤ ይኽንን ደስታ የእሚሰጠን ወይንም በተቻለ መጠን ወደ እዚኽ ደስታ የእሚያቀርበንን ማሕበረሰብ ወይንም ማሕበራዊ ተቋም የእምንገነባበትን ጥበብን ያጎናጽፈናል እንጂ ፤ የተሻለውን ማሕበረሰብ ወይንም ማሕበራዊ ተቋም መገንቢያውን እውቀት ይዘነው አንወለድም ፤ እንደ ሰው ልጅ ።

ስለ እዚኽ ፦ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ለመሆን የተጓዘበትን የፓለቲካ ታሪክ እንቃኛለን ስእንል ፤ መንግሥት የእሚባለው ተቋም ፤ አስፈላጊ ማሕበራዊ ተቋም ሆኖ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከመጣ በኋላ ፤ በኢትዮጵያ ልዩ ኹኔታ ደግሞ ፤ ኢትዮጵያዊያኖች አንድ የጋራ መንግሥት ሆነው ከቆሙ በኋላ ፤ ይኽ መንግሥታቸው ፥ የነዋሪዎቹን ህይወት ለማቅለል እና ተፈጥሮዋዊ የእርካታ መሻት ጉዞዋቸውን ፤ ሲሆን ማገዝ ሰአይሆን የእማያደናቅፍ ሰንካራ ላለመሆን በእየዘመኑ የኼደበትን ታሪካዊ የእድገት ዝግመታዊ ጉዞ እንቃኛለን ማለት ነው ።

የሐገራችን ብሒል እንደ እሚለው ፤ ማንም ሞያን ከእናቱ ሆድ ይዞ የተወለደ የለም ። ሰዎች በውልደት የተለየ ተሰጦ ቢኖራቸውም እንኳን ፤ ያንን ተሰጦ ትርፋማ ማድረግ የቻሉት ወይንም የእሚችሉት ፤ ራሳቸውን ለማርካት በመሮጣቸው ነው ። ዴሞክራሲያዊ ሐገር እና መንግሥት ፤ ምንነታቸው እና የመገንቢያ መርሆቹን ይዟቸው የተፈጠረ ሕዝብ የለም ፥ ነገር ግን ዜጎች እንደ ሕዝብ ደህንነታቸውን ፣ ጥቅማቸውን ወይንም ፍላጎታቸውን ለመርካት ሲሮጡ ደረሱበት እንጂ ።

የነፃነት ዴሞክራሲ ትርክት ዘመናዊ መሰራች ሊባል የእሚችለው ፤ ጆን ሎክ ፥ ሰዎች አዕምሮዋቸው ዳብሮ በእውቀት የሚታጠቀው ፤ ሰዎች የእሚያረካቸውን ነገር በነፃነት እንዲከታተሉ ሲፈቀድላቸው ነው ይላል ። በሌላ አነጋገር የእሚወደውን ፥ በዘላቂነት የእሚያስደስተውን ነገር ፤ ያለክልከላይ ሲከታተል ነው ፤ ሰው ፥ የአዕምሮ እድገቱ ጎልብቶ ፤ እንደ ዴሞክራሲ ያሉ አትራፊ ማሕበርሰብን ማወቀሪያ መርህዎችን መደ ማግኘት የእሚመጣው ፦

“…ስለ እዚኽም ፦ ከፍተኛው የዓዕምሮ ብስለት ልቀት ፍፅምና ፥ በማስተዋል በሆነ እና በእማያቋርጥ ፥ እውነተኛውን እና የፀናውን ደስታ በመፈለግ ውስጥ ነው ።”

“...Therefore, the highest perfection of intellectual happiness lies in a careful and constant pursuit of true and solid happiness.”

እንደ ሕዝብ ፥ ይኽ ተፈጥሮዋዊ ደስታን መፈለግ ሰብዓዊ ባሕሪያችን እየመራን ፤ አንድ ማዕከላዊ የጋራ ፖለቲካዊ አስተዳደር ከመፍጠር ጀምሮ ዛሬ እንደ ሐገር መገንባት እስከ ቻልነው ፖለቲካዊ መዋቅር ድረስ የኼድንበትን የፖለቲካ ታሪክ ጎዞ ፤ ይኽም ጉዞ ፤ ዛሬ በዓለም ላይ በዓለው እውቀት ለሰው ልጅ የተሻለ ፓለቲካዊ ስረዓት የተባለውን ዴሞክራሲያዊ ስረዓት ጋር ለመድረስ የኼደበትን እና የቀረውን ‘ርቀት’ ፤ ከእላይ እንደ አልነው በዘጠኝ ክፍል ከፍለን በመቀጠል የእምንመለከትበት ይሆናል ማለት ነው ።