ሕ ገ ክ ራ ሲ

marketing-image

3.2.1. ክፍል አንድ ፡ ቅድመ አክሱም (ከጥንተ ጥንት - 575 ዓ.ም.)

ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ለመኾን በአደረገችው ረጅሙ ፖለቲካዊ ዝግመት ውስጥ ፤ የመጀመሪያው ወሳኝ ኹነት የእሚሆነው ፤ በምሥራቅ በቀይ ባሕር ተከልሎ ፤ በምዕራብ ከደቡባዊ ግብፅ እስከ ምድር ወገብ በተዘረጋው ሰፊው የምሥራቅ አፍሪካ ክልል ውስጥ ፤ የአክሱም ነገሥታት ፤ በአክሱም ማዕከላዊነት አከባቢውን ሕዝብ በአንድ የጋራ ፖለቲካዊ አስተዳደር ውስጥ ለማስገባት የቻሉበት ኹኔታ ነው ።

እንደ ብዙ ታሪክ አጥኚዎች ፤ ከላይ በተጠቀሰው አከባቢ ፤ ሰዎች መስፈር የጀመሩት ከዛሬ 5,200 እስከ 6,000 በአሉት ዓመታት ውስጥ ነው። ስለ እዚኽ ፦ የዛሬዎች ኢትዮጵያዊያኖች መነሻ የሆኑት ሕዝብ ፤ ከክርስቶስ ልደት ከ3,200 – 4,000 ቀደም ብለው በዓሉት ዓመታት አከባቢው ላይ ፤ ከዛሬዋ ሰሜን ሱዳን እስከ ደቡብ አረቢያ በነበረው ሰፊ አከባቢ ላይ ፤ የተበታተኑ ሰፈራዎች እና ከተማዎች በመቆርቆር መስፈር ጀምረዋል ማለት ነው።

ምንም እንኳን አከባቢው የዛሬ 5 እና 6 ሺ ዓመታት ገደማ ቢሰፈርበትም እና የተወሰኑ ጥንታዊ ስልጣኔዎች ቢጀመርበትም ፤ በአከባቢው ታዋቂነት የአላቸው ትልልቅ ከተማዎች መታየት የጀመሩት ፤ ሰፈራው ከተጀመረ በሺ የእሚቆጠሩ ዓመታት ከአለፉ በኋላ ነው።

ይኽም በመሆኑ ፦ ነፓታ ፣ ዳዕማት መሰል መዓከላት አከባቢው ላይ መታየት የጀመሩት ፤ ከክርስቶስ ልደት 900 እና 1000 ዓመታት ቀደም ብሎ ወይንም ሰፈራው ከጀመረ ከወደ 2 ሺ ዓመታት በኋላ ነው ።

እነ እዚኽም የአከባቢው ነዋሪዎች ወደ በኋላ ላይ እየቆረቆሩዋቸው የመጡት ጉልህ መንደሮች እና ከተሞች ፤ በረጅሙ የታሪክ ኺደት ፥ ልክ በሌሎቹ የዓለም ሕዝብ እንደ እሚሆነው ፤ ሲጀመሩ ፣ ሲሻሻሉ አንዳንዴም ሲፈርሱ እና በተለያየ ምክንያት ነዋሪዎቻቸው ጥለዋቸው ተሰደው ባዶዋቸውን ሲቀሩ ቆይተው ፤ በግዜ ኺደት በአቅራቢያቸው ካለው ሕዝብ የእሚያልፍ እና ለብዙ መቶ ዓመታት የእሚቆይ የተጽኖ ወይንም የኃይል እና የስልጣኔ መዓከላት ለመሆን በቅተዋል ።

ለምሳሌ ፦ ከክርስቶስ ልደት በፊት 900 ዓመት አከባቢ ፤ በዛሬው ሱዳን ነፓታ ፣ በዛሬዎቹ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ደዓማት ፣ በደቡብ አረቢያ ሳባ ፤ የእሚባሉ ሰፈራዎች ተመስርተው ፤ እርስ በእርስ በንግድ እና በባህል ተሳስረው ለተወሰኑ መቶ ዓመታት ከቀጠሉ በኋላ ፤ የሱዳኗ ነፓታ በሜሮ ከክርስቶስ ልደት 5 ወይንም 4 መቶ ዓመት በፊት ፣ ዳዕማት ቀስ በቀስ ከክርስቶስ ልደት በፊት በመቶኛው ዓመት አከባቢ በአክሱም እየተተኩ መጥተዋል ።

እነ እዚኽ ትልልቆቹ እና የእሚታወቁት ናቸው ማለት እንጂ ፤ ከእነ እዚኽ የእሚያንሱ ሰፈራዎች እና ከተማዎች በተወሰኑ የምሥራቅ አፍሪካ አከባቢ ፤ በተጠቀሰው ዘመን ተበትነው የነበሩ መሆናቸው ይታወቃል ።

በግዜ ኺደት ግን ፤ አንድ አንዶቹ እነ እዚኽ ሰፈራዎች እና ከተሞች ፤ ከሌሎች ይልቅ እየበረቱ እና የተፅዕኖ ክልላቸው እየሰፋ ፤ ራሳቸውን የተፅዕኖ መዓከል ወደ ማደረግ መጥተዋል ።

ይኽ ሲሆን ፤ ከእዚኽ ቀደም በአለው ክፍል ላይ እንደ አየነው ፤ በእዚኽ ሰፊ የምሥራቅ አፍሪካ አከባቢ ተበታትነው በሰፈራ የተጀመሩት ከተሞች ነዋሪ ሕዝብ ፤ በግዜ ኺደት ቢያንስ ከክርስቶስ ልደት 5 መቶ ዓመት ቀደም ብሎ በወል በግሪክ እና በሮማኖች ፤ ኢትዮጵያዊያኖች ተብለው መጠራት ጀምረዋል ።

ለምሳሌ ፦ በዛሬዋ ሱዳን ውስጥ የእምትገኝው እና ነፓታን የተካችው ሜሮ ፤ ከክርስቶስ ልደት በፊት 500 ዓመት በፊት በነበረው ሔሮድተስ ፤ የኢትዮጵያ ከተሞች እናት ተብላ ተገልፃለች ፦

“…ከእዚኽ በኋላ ሜሮ ወደ እምትባል ታላቅ ከተማ ትመጣለህ ። እንደ እሚባለው ከሆነ ፥ ይኽቺኽ ከተማ የኹሉም ኢትዮጵያዊያን እናት ከተማ ናት ።”

“...and after this you will come to a great city called Meroe. This city is said to be the mother-city of all other Ethiopians: [5] “

ሜሮ በሔሮድተስ የኹሉም ኢትዮጵያዊያኖች እናት ከተማ ተብላ የተገለፀችበት መንገድ ፤ የአከባቢው ነዋሪዎች በግሪኮቹ ኢትዮጵያዊያን ተብለው የእሚጠሩ መኾናቸውን እና ሜሮም ከብዙ የኢትዮጵያን ከተሞች መካከል ትልቋ ከተማ እንደ ሆነች ወይንም በዘመናዊ አውዱ እንደ ዋና ከተማነት (A Capital City) የታየች በመሆኑ ፤ ሌሎች ብዙ የኢትዮጵያዊያን ከተሞች ያሉ መሆናቸውን ያሳየናል ።

ከሜሮ ከፍ ብሎ በስተሰሜን እና ከሜሮ በብዙ መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ ፥ ቲብስ በእምትባለው ከተማ የነበረው የኢትዮጵያዊያን ስልጣኔ ፤ የተለያዩ መሠረታዊ እውቀቶች መፍለቂያ እንደነበረች ፥ ቮለኒ ይናገራል ፦

“የአንፀባራቂዋ ከተማ አፅሞች ናቸው ፤ የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ኩራት የነበረችው ፡ እንሆ ቲብስ ፥ … ፥ የመጀመሪያዋ የሳይንስ እና የኪን መፍለቂያ ከተማ ፥ ትንግርታዊ የሆኑ እና የሰው ዘር ሳይገነዘባቸው ዛሬም ድረስ የእሚገዙት አስተሳሰቦች የፈለቁባት ። … የከተሞች እናት ፤ የሰው ልጅ ፈራሽነት ማስታወሻ ። እዚኽ ነበር ፤ ሌላው ዓለም አረማዊ/አረመኔ በነበረበት ወቅት ሳይንስን እና ኪንን የፈጠሩት…“

“These heaps of ruins, said he, that you observe in this narrow valley, laved by the Nile, are all that remain of the opulent cities that gave luster to the ancient kingdom of Ethiopia. Here is the monument of its splendid metropolis, Thebes … the progenitor of cities, the memento of human frailty. It was there that a people, since forgotten, discovered the elements of science and art, at a time when all other men were barbarous... [85]”

እንደ ቮልኒ ፤ ይኽችኽ በጣም ጥንታዊ የሆነችው የኢትዮጵያዊያን ከተማ ቲብስ ነች ፤ በዓለም ላይ ፤ የመጀመሪያዋ ከተማ ስልጣኔ ። እንደ ገናም የቲብስ ኢትዮጵያዊያኖች ናቸው ፤ ከአባይ ሙላት እና ከእርሻ ሥራቸው ጋር የከዋክብትን አመጣጥና አካኼድ በማገናዘብ ፤ ስነ ከዋክብትን ያስጀመሩት ይላል ቮለኒ ፦

“እንግዲኽ የቲብስ ኢትዮጵያዊያን ናቸው ፥ የሙላት ከዋክብት ወይንም አኳሪስ [1]ብለው ፤ እነ እዚኽ ከዋክብት በሰማዩ ላይ በእሚታዩበት ወቅት አባይ የእሚሞላ መሆኑን ለማመለከት ይኽንን የኮከብ ስብስብ የሰየሙት ። በሬ የእሚባለውን የከዋክበት ስብስብም ፥ እርሱ በእሚታይበት ወቅት በበሬ የማረስ ግዜ ነው ብለው የሰየሙት ። አንበሳ የእሚለውንም ስብስብ ፥ አንበሳው በውኃ ጥማት ተንድቶ ውኃ ለመጠጣት ወደ አባይ ወንዞች ዳርቻ የእሚመጣበትን ወቅት ለማመልከት የሰየሙት ። የዛላው ስብስብ ከዋክብት የእሚለውንም ፥ የመከር መሰብሰቢያውን ግዜ ለማመልከት የሰየሙት ። የበጎቹ ከዋክብት ፣ የፍየሎቹ ከዋክብት የእሚሉትንም ፤ እነ እዚኽ የተወደዱ እንስሳት ልጆቻቸውን የእሚወልዱበትን ወቅት ለማሳየት የሰየሙዋቸው ። እንዲኽ አድርገው ነው እንግዲኽ ፤ ትልቁን ችግር አስቀድመው የፈቱት ።”

“Thus the Ethiopian of Thebes called stars of inundation, or of Aquarius, those under which the river began to overflow ; stars of the ox or bull, those under which it was convenient to plough the earth; stars of the lion, those under which that animal, driven by thirst from the deserts, made his appearance on the banks of the Nile; stars of the sheaf, or of the harvest maid, those under which the harvests were got in; stars of the lambs, stars of the goat, those under which those valuable animals brought forth their young; and thus was a first part of the difficulty resolved.” [85]“

እነ እዚኽ በዛሬዋ ሱዳን ከእሚገኙ ሜሮ እና በዛሬዋ ግብፅ ደቡባዊ ጫፍ ከእምትገኘው ቲብስ በአሻገር ፤ በዛሬ ኤርትራ እና ትግራይ አከባቢም ፤ ከአክሱም አስቀድሞ ዳዕማት ፣ በከፊልም ቢሆን በደቡብ አረቢያ ሳባ ፣ ወዘተ ፤ የእሚባሉ ፤ ከእነ እዚኽ ስልጣኔዎች ጋር ተቀራራቢ ዘመን ላይ የሆኑ እና ከእነ እዚኽ ስልጣኔዎች ጋር ተዛማጅ የሆኑ ፤ የኢትዮጵያዊያን ወይንም ከኢትዮጵያዊያን ጋር የተያያዙ ስልጣኔዎች እየተነሱ ጠፍተዋል ፦

“በአመዛኙ ፤ ደዓማት የእሚባለው ፖለቲካዊ መሐበረሰብ ፤ የጽሑፍ እና የከርሰ ምድር ጥናት በቋሚነት እንደ እሚያሳዩት ፤ መጀመሪያ ላይ የእዚኽ መንግሥት አንኳሩ የነበረው ፤ በደቡብ አረቢያኖች ዘዬ በ 700 ቅ.ክ. የተገነባው ግዙፍ ቤተመቅደስ የነበረበት የኃ አከባቢ እንደ ሆነ ነው … ከክርስቶስ ልደት በፊት በነበረው እልፍ ዓመት የኋለኛው አጋማሽ ላይ ፤ ይኼ ቅድመ አክሱም ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ፤ የሰፋሪዎች ቁጠር እየቀነሰ በመምጣቱ እና ግዙፍ ህንፃዎቹ ነዋሪ እያጡ በመምጣታቸው ፤ በአክሱም-የኃ አከባቢ ከስሟል ።”

“Most likely, the D’MT polity arose in central Tigray, as archaeological and epigraphic evidence consistently suggest that at the very beginning the core of the state was located in the region of Yeha, where a monumental temple in South Arabian style was built around 700 BC … In the second half of the 1st millennium BC, the pre-Aksumite polity collapsed in the Aksum–Yeha region, as the settlements sharply decreased in size and monumental buildings were abandoned. [90]“

በረዥም ዘመን የተፈጠረውን ፤ የዛሬውን የድንበር ክፍፍል ተከትለው አንዳንድ ሰዎች ፤ የሜሮ እና የቲብስ ስልጣኔ የሱዳኖች እና የግብፅ በቅደም ተከተል ፣ የኃ እና አክሱም የኢትዮጵያ ፤ እንደ እዚኹም የደቡብ አረቢያ የሳባ ስልጣኔዎች የየመን ወይንም የአረቦች እንደ ሆነ ለማስቀመጥ ቢዳዳቸውም ፤ እኔ እንደ እሚመስለኝ ፥ እነ እዚኽ አካባቢዎች በታሪክ ዛሬ የያዙትን ፖለቲካዊ ቅርፅ ሳይዙ በፊት ፤ አስቀድመን በአሳየነው አግባብ ፤ በወል ኢትዮጵያ በእሚባለው አከባቢ እና ኢትዮጵያዊያን በእሚባሉት ሕዝብ የተቆረቆሩ ስልጣኔዎች ኾነው የተጀመሩ እና ከመቆርቆራቸው አንስተው ፤ በአክሱም ስር እስኪማከሉ ድረስ ፤ ረዥም ዘመን የቆየ ማሕበራዊ እና ኢከነሚያዊ ትስስር የነበራቸው ናችው ። ይኽንን ግምት ፤ የአከባቢውን ሕዝብ ጥንታዊ ስብጥር ላይ የተደረገ አንደ ጥናት እንደ እዚኽ ያስቀምጠዋል ፦

“በጥንታዊው ዘመን ፤ የተለያዩ የሰሜን ኢትዮጵያ ሕዝብ በምሥራቅ ወይንም በምዕራብ ፤ ከድቡብ አረብያ ወይንም ከአባይ ሸለቆ እና የሱዳን ሕዝብ ጋር ግንኙነት ነበራቸው የእሚለው እሳቤ ፤ አንድ ሰው ወደ አዕምሮው የትግራይ ተራራማ ቦታዎች ፤ ከህንድ ፣ ከምሥራቅ አፍሪካ እና ከሜድትራኒያኑ ዓለም ፤ የእሚነሱት የንግድ መስመሮች የእሚገናኙበት ቦታ ላይ መገኘቱን ሲያታውስ ፤ ኃሳቡ የበለጠ ግልፅ ይሆናል ።”

“The idea that, in Antiquity, the different populations of North Ethiopia had contacts with either the East or the West, South Arabia or the Nile Valley and Sudan, is obvious as one may call to mind that the Highlands of Tigrai are situated at the focal point of the trade routes between India, East Africa, and the Mediterranean world. [91]“

የታሪክ አጥኝዎች የጥንታዊው ዘመን (The Age of Antiquity) የእሚሉት ፤ ስነ ጽሑፍ ከዳበረበት ከክርስቶስ ልደት 3,200 በፊት ጀምሮ እስከ ከክርስቶስ ልደት 400 ዓመታት ገደማ የአለውን (3,200 ቅ.ክ. _ 400 ዓ.ም. or 3,200 B.C. - 400 AD) ወደ 3,600 ዓመታ የእሚጠጋ ግዜ በመሆኑ ፤ ከእላይ በተጠቀሰው ጽሑፍ ፤ በጥንታዊው ዘመን ፤ በሰሜን ሱዳን ፣ ትግራይ እና ኤርትራ እንዲኹም ደቡብ አረቢያ መካከል ከጥንት የጀመረ ግኑኝነት ነበር ሲል ፤ ይኽ ግንኙነት ማሕበራዊ እና ኢከነሚያው ትስስር ታሪክ ከጀመረበት ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ3,200 ዓመት ጀምሮ እስከ ከክርስቶስ ልደት በኋላ እስከ አለው 400 ገደማ ዓመታት በአለው ግዜ ውስጥ የተካኼደ ነው ማለት ነው ።

ከእዚኽም እድሜ ጠገብ ታሪካዊ ቁርኝት ተነስተው ፤ የተለያዩ የአክሱም ነገሥታት ፤ በተለይ አከባቢው በአክሱም መዓከላዊነት ከተማከለ በኋላ ፤ ሱዳን ፣ ኢትዮጵያ እና ደቡብ አረብያ ታሪካዊ የግዛታችን አካል ናቸው ይሉ እንደ ነበር በታሪክ የተመዘገበ ነው። ስለ እዚኽ ጉዳይ ጆርጅ ሐትኪ የተባለ ሰው እንደ እዚኽ ይላል ፦

“ከእዚኽም የተነሳ ፤ ንጉሥ ካሌብ እና የእርሱ ተከታይ ዋዜብ (እ.አ.አ. 540 – 560 ዓ.ም.) ኩሽ እና ኑባን በደቡብ አረቢያ ከእሚገኝ ሰፊ መሬት ጋር እኩል ፤ በዘውዳቸው አስተዳደር ስር እንደ አሉ ግዛቶች መዘርዘራቸው ሊያስገርመን አይገባም ።”

“It is no surprise, then, to find Kālēb and his son and successor Wa‘zeb (c. 540-560 CE) laying claim to Kush and the Noba in their royal titles, side by side with their parallel claims to vast tracts of territory in South Arabia. [92]“

ስለ እዚኽ ፦ በጥንተ ጥንት ከላይ የጠቀስነው ሰፊው የምሥራቅ አፍሪካ እና የደቡብ አረቢያ ፤ በአክሱም መዓከላዊነት ከመማከሉ በፊት ፤ ለኹለት እና ሦሥት ሺ ዓመታት የቆየ ኢከነሚያዊ እና ማሕበራዊ ትስስር የነበራቸው ተዛማጅ ሕዝብ ይኖሩበት እንደ ነበረ እና ይኽም ሕዝብ ፤ በተለይ ከግብጽ በስተደቡብ የአለው ፤ በግሪኮች እና በሮማኖች ቢያንስ ከክርስቶስ ልደት 500 ዓመታት ቀደም ብሎ ፤ በኢትዮጵያዊነት ይጠራ እንደ ነበር ብዙ ታሪካዊ ማስረጃ ሊቀርብበት የእሚችል ወይንም የእማያከራክር ታሪካዊ ኃቅ ነው ።

በታሪክ ኺደት ግን ፖለቲካዊ ማሽኑ አቅሙ ሲጨምር እና ሰፊ ቦታን ማስተዳደር እየቻለ ሲመጣ ፤ በተለይ በአክሱም የገናነት ዘመን ፤ ከግብፅ በስተደቡብ የአለውን አከባቢ ፤ የዛሬን ኹለቱኑም ሱዳኖች ፣ ኢትዮጵያን ፣ ሶማሊያን እንዲሁም ከቀይ ባሕር በስተምሥራቅ የመንን የእሚያካትት ቦታ ፤ በአክሱም መናገሻነት መመራት ጀመረ ። በእዚኽም መሠረት ምንም እንኳን በእየ መሐሉ መቆራረጥ ፣ አመፅ ፣ ወዘተ ፤ ቢኖርም ፤ አክሱም ቢያንስ ከክርስቶስ ልደት በኋላ ፤ ከ300 – 550 በአለው ዘመን ውስጥ ፤ ተቀናቃኝ የሌለው የአከባቢው ፖለቲካዊ መዓከል ሆና ቆይታለች ።

በእዚኽም ኢትዮጵያዊነት ከተበታተነ ሕዝብነት ወደ አንድ ፖለቲካዊ ማሕበርሰብነት ፤ ቢያንስ በእዚያኽ ዘመን እንደ ተቆረቆረ በማስረጃ የተረጋገጠ ታሪክ ነው ። አክሱማዊ ነገሥታት ይኽን አከባቢ በእሚገዙበት ወቅት ፤ ራሳቸውን የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትም ብለው መጥራት ጀምረዋል ። ይኽም በኢትዮጲያዊያን የፖለቲካ ጉዞ ውስጥ ወደ ሕዝባዊ መንግሥት በአደረጉት ጉዞ ፤ የመጀመሪያው እና ወሳኙ ምዕራፍ ነው ።

አከባቢው ፤ በአክሱም መሪነት ወደ አንድ ፖለቲካዊ መሐበረሰብነት መምጣት መጀመሩን ከእሚያሳዩን ታሪኮች አንዱ ፤ እንደ ስትዋርት ሙንሮ ኄይ ( Stuart Munroe Hay ) ፤ የአክሱሙ ንጉሥ ኢዛና ወይንም ከእርሱ በፊት የነበረው ኡሳና ( ? ) ፤ በአከባቢው ያሉትን ሌሎች ነገሥታት ፤ በአክሱም መዓከልነት ለማዋቀር የተንቀሳቀሰበትን ዘመቻ ውሎ በእሚተርክበት ታሪክ ላይ ፤ ራሱን ንጉሥ ነገሥት ብሎ እንደጠራ ስለ እሚነግረን ፤ ይኽ ንጉሠ ነገሥት የእሚለው ቃል ፤ ቢያንስ ከኢዛና ወይንም ከእርሱ ቀደም ብሎ የነበረው የአክሱም ንጉሥ ፤ በስሩ ወይንም ለእርሱ የእሚገብሩ ሌሎች ነገሥታት መኖራቸውን ስለ እሚያሳየን (ይኽ ንጉሠ ነገሥት የእሚለው ስልጣን የወቅቱ ፖለቲካዊ መዝገበ ቃላት ውስጥ መገኘቱ በራሱም) የተለያዩ የኢትዮጵያ አከባቢዎች ፤ በአክሱም ነገሥታት ፤ ንጉሠ ነገሥትነት ፤ ወደ አንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብነት መለወጣቸው ማሳያ ነው ፦

“ … እለ አምዳ ፥ ብስ...ስ.ም ፥ የአክሱም ፣ የሕምያር ፣ የሪያዳን ፣ የሳባ ፣ የሳህለን ፣ የፅያሞ ፣ የቤጃ እና የካሱ ንጉሥ ፤ ንጉሠ ነገሥት ፤ የእማይበገረው የማህሬም ልጅ ። ግዛቱን መልሶ ሊያፀና እና በስረዓት ሊያደርገው ለዘመቻ ወጣ ። ታዘው የገቡለትን ፤ ምህረት አደረገላቸው ፤ አምፀው እምቢ ያሉትን ለሞት ዳረጋቸው ።”

“. . . Ella Amida, Bisi...s.m, king of Aksum, Himyar, Raydan, Saba, Salhen, Tsiyamo, Bega and of Kasu, king of kings, son of the invincible Mahrem. He departed on campaign to re-establish his empire and put it again in order. Those who obeyed him, he spared; those who resisted him, he put to death. [86]“

በእዚኽ ከኢዛና በፊት በነበረው ስሙ በእማይታወቅ የአክሱም ንጉሥ የዘመቻ ገድል ላይ የተዘረዘሩት ፤ ካሱ ወይንም ኩሽ (ሱዳን) ፣ አክሱም ፣ ሕምያር (ደቡብ አረቢያ) ፣ ወዘተ ፤ በመሆናቸው የእዚኽ በአክሱም ያለ ንጉሠ ነገሥት የግዛት የእሚያካትታቸው ቦታዎችን በአግባቡ ያሳያል ።

ይኽ በ330 ዓ.ም. አከባቢ በነበረው ወይንም ከእርሱ ትንሽ ቀደም ብሎ የነበረው ግዜ ላይ ሲሆን ፤ ከኹለት መቶ ዓመታት በኋላ በንጉሥ ካሌብ ዘመን ፤ ማለትም በ6ኛው ምዕተ ዓመት ፤ ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው እና መላ ኢትዮጵያን የመጎብኘት እድል የአጋጠመው ኮስማስ ፤ ኢትዮጵያ ብሎ ሲል ይኽን ከላይ የጠቅስነውን ሰፊ አከባቢ መሆኑ እና ራሳቸውን ኢትዮጵያዊያን ብለው መጥራት የጀመሩት አክሱማዊያን ፤ ኢትዮጵያ ሲሉ በእዚኽ አውዱ መሆኑን ስለ እሚያሳይ ፤ አከባቢው ወደ አንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብነት ተቀይሮ ፤ በእነ ካሌብ ዘመንም ፤ ማለትም ወደ 200 ዓመታት ገደማ ለእሚጠጋ ግዜ በእዚኽ ኹኔታ እንደ ቆየ ያሳያል ። በጉዳዩ ላይ የኮስማስን መጽሐፍ ወደ እንግሊዝኛ የተረጎሙት የእንግሊዞቹ የሐልይኩት ማሕበረሰብ ፤ እንደ እዚኽ ይላሉ ፦

“(ኮስማስ) ኢትዮጵያ ብሎ ሲል ፤ ከደቡብ ግብፅ አንስቶ እስከ ምድር ወገብ የእሚደርሰውን ነው ፤ በአዱሊስ ወደብ ስላለው ጽሑፍ በእሚያወራበት ወቅት ፤ በመሐል በአስቀመጠው አስተያየት ፤ ይኽንን አከባቢ በወርዱም በስፋቱም እንደ ቃኘው እናውቃለን ። በእዚያኽ ወቅት የኢትዮጵያ ፤ የንግድ ፣ የኃይማኖት እና የትምህርት ማዕከል የነበረች ዋና ከተማዋም አክሱም ነበረች ። ኮስማስ ጥሪዉን ተከትሎ ሲኼድ ከጎበኛት ከተማ አንዷ ነበረች ።… በንጉሡ ግቢም ጥሩ ፊት እንደ አገኘ ፤ የግሪክን ቋንቋ መናገር የእሚችለው ክርስቲያን የሆነው የሐገሬው ንጉሥ በግዛቱ በነፃነት እንዲንቀሳቀስ ፈቅዶለታል ።”

“By the name of Ethiopia he (Cosmas) he designates in a general way the vast region which stretches southward from Egypt down towards the equator; and from an incidental remark which he drops when treating of the Adulitic inscription on the throne, we learn that he had traversed it almost throughout its length and its breadth... The capital of Ethiopia at that time was Axum, an important centre of commerce, and also of religion and learning. It was one of the places which Cosmas, in pursuit of his calling, visited, ... he was well received at the Court, and was permitted by the king, who professed the Christian faith and could speak Greek, to travel freely through his dominions. [87]“

ይኽ መጠነ ሰፊ አከባቢ ፤ ቢያንስ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ400 ዓመታት ውስጥ በአክሱም መዓከላዊነት ተማክሎ እና አክሱማዊያንም የስብስቡን ስም ኢትዮጲያ ወይንም ሐበሻ የእሚለውን እንደ ራሳቸው መጠሪያ ተቀብለው ፤ ራሳቸውን የኢትዮጵያ ነጉሰ ነገሥት ለማለታቸው ፤ እላይ ከአስቀመጥነው የኢዛና ወይንም ከእርሱ በፊት የነበረው ኡሳና ( ? ) ዘመቻ ከዘረዘራቸው ግዛቶች እና ኮስማስ በዘመነ ካሌብ በአካል በመገኘት ያየው አከባቢ ፤ አከባቢው ኢትዮጲያ በእሚል ስያሜ ቢያንስ ከንጉሠ ነገሥት ኢዛና እስከ ንጉሠ ነገሥት ካሌብ ድረስ ፤ ማለትም ቢያንስ ለ200 መቶ ዓመታት በአክሱም መዓከልነት ይመራ እንደ ነበር ያሳየናል።

በተጨማሪም ፤ ኮስማስ ንጉሥ ካሌብ ወደ ደቡብ የመን ወይንም ደቡብ አረቢያ ሊዘምት እየተዘጋጀ በነበረበት ወቅት ላይ በመሆኑ የደረሰው ፤ በኮስማስ ኢትዮጵያ ተብሎ ከተጠቀሰው ሰፊው ምሥራቅ አፍሪካ በተጨማሪ ፤ ልክ ከላይ እንደ አልነው ደቡብ አረቢያም የእዚኽ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ አካል እንደ ነበር በድጋሚ ያሳየናል ።

የኮስማስ መጽሐፍ ሌላም የእሚነግረን ታሪክ አለው ። ይኽም ታሪክ ኮስማስ በንጉሠ ነገሥት ካሌብ ዘመን ወደ ኢትዮጲያ በመጣበት ወቅት ፤ በአዱሊስ ወደብ ላይ ይገኝ የነበረ የአክሱም ንጉሥ የአደረገውን ዘመቻ የእሚተርክ የድንጋይ ጥርብ ላይ የተቀመጠ ገድል ፤ በንጉሡ ትዕዛዝ የመገልበጥ እድል አጋጦምት ነበር ። ኮስማስ በገለበጠው በእዚኽም ጽሑፍ አንድ የኢትዮጵያ ንጉሥ በዘመቻ ያስገበራቸውን ሕዝብ ይዘረዝራል ። ኮስማስ ይኽን የመገልበጥ ትዕዛዝ ከንጉሡ የተቀበለበትን አግባብ እና ጽሁፉ የእሚዘክረው ዘመቻ የአካለለውን ድንበር ጥግ እንዲያሳየን ፤ በእዚኽ ጽሑፍ ከካሌብ በፊት የነበረው የአክሱም ንጉሥ ያስገበራቸውን አከባቢዎች ዘለል ዘለል እያልኩ አስቀምጣለሁ ፦

“በኢትዮጵያ የባሕር ጠረፍ ፥ ከየብሱ ኹለት ማይል (3.2 ኪሎ ሜትር ያኽል) ርቀት ላይ ፤ አዱሌ የእምትባል ከተማ አለች ። ይኽችኽ ከተማ የአክሱማዊያኖች ወደብ ስትሆን ፤ ከአሌክሳንደሪያ እና ከኢላንቲክ ሰርጥ (አቅባ ሰርጥ) የእሚመጡ ነጋዴዎች ያዘወትሯታል ። በእዚኽ ቦታ ላይ ፤ ወደ አክሱም በእሚወስደው መንገድ ከእምነበረድ ድንጋይ የተሰራ ወንበር አለ … ከወንበሩ በስተጀርባ እንደ ገበታ ያለ የባሰነት ድንጋይ አለ … ወንበሩ እና ገበታው በግሪክ ፊደላት ግጥም ተደርጎ ተጽፎባቸዋል ። እኔም በእዚኽ ሐገር በነበርኩበት ወቅት … እለ አፅበሐ ፣ የአክሱማዊያን ንጉሥ የነበረው ፤ በሆመራይት (የመን) ላይ ለመዝመት ዝግጅት ሲያደርግ ነበር … ስሙ አባስ ለእሚባለው ፤ የአዱሊስ ወደብ ገዢ ለነበረው ሰው ፤ … በወንበሩ ላይ የአለውን ጽሑፍ ገልብጦ እንዲልክለት ያዘዋል ። ገዢውም እኔን እና በእዛኽ የነበረ ሌላ ነጋዴ ፤ የመገልበጡን ሥራ እንድ እንሰራ ላከን … እኛም ኼደን ጽሁፉን ገለበጥን … ነገር ግን ተመሳሳይ ግልባጭ ለእራሳችን አስቀረን ። ጽሁፉ እንዲኽ ይነበባል ፦

የእሚከተሉትን ሕዝብ ወጋሁዋቸው ፤ በጦር ኃይልም ለእኔ እንዲገቡልኝ አደርግኳቸው ።… ጋምቤላውን አስገባሁ ፤ ከእዛም በመቀጠል ግብፅን በእሚዋሰኑት … ላይ ዘመትኩ … ከእዛም በመቀጠል በሩዋሲ ነገድ ላይ ዘመትኩ … ይኽን … ሕዝብ አስገባሁ ፥ ውኃ በሌለበት ለጥ ባለው ምድር በነጭ እጣን ሐገር የእሚኖሩትን። (ከእዛኽም ወደ ባህሩ በመግፋት) ሶሌቶች አጋጠሙኝ ፤ እነርሱንም አስገብቼ ፥ የባህሩን ጠረፍ እንዲጠብቁ አሳስቤ ተመለስኹ። ከገቡልኝ በኋላ ለእኔ እንዲገብሩ እያደርግሁ ግዛታቸውን መለስኹላቸው ። ከእነርሱ አከባቢ የነበሩ ብዙ ነገዶች በፈቃዳቸው እየገቡ ገበሩልኝ ። ከእዚያኽም በኋላ ወደ አረብ ምድር ፤ የባሕር ኃይል እና የምድር ጦር ላክሁኝ ፤ ከቀይ ባሕር በወዲያ ማዶ በእሚኖሩት ላይ ፥ የእነ እዚኽንም ገዥዎች ከአስገባውኋቸሁ በኋላ ፤ የመሬት ግብር እንዲገብሩ እና በባሕርም በየብስም የእሚደረግ ጉዞ እንደ አያውኩ አሳሰብኳቸሁ ።”

“On the coast of Ethiopia, two mile of from the shore, is a town called adule, which forms the port of the Axomites and is much frequented by traders who came from Alexanderia and Elantic gulf (Aqaba). Here is to be seen a marble chair…Now when I was in this part of the country…, Elesbaan (i.e. king Caleb or Ele Atsbaha), who then was King of the Axomites, and was preparing to start on an expedition against Homerites…wrote to the governor of Adule directing him to take copies of the inscriptions on the chair…, and to send them to him. Then the Governer, whose name was Abbas, applied to myself and another merchant…we went and copied the inscriptions…but we kept like copies for ourselves. The inscription, …ran thus:-

I made war upon the following nations, and by force of arms reduced them to subjection… the Gambela…I proceeded next against …who adjoin the borders of Egypt…The tribes of Rhausi I next brought to submission: a … race spread over wide waterless plains in the interior of frankincense country. [Advancing thence towards the sea] I encountered the Solate, whom I subdued, and left with instructions to guard the coast…Upon their submission I restored the territories to them, subject to the payment of tribute. Many other tribes besides them submitted of their own accord, and became likewise tributary. I sent a fleet and land forces against the Arabitae and … who dwelt on the other side of the Red Sea, and having reduced the Sovereigns of both, I imposed on them a land tribute and charged them to make travelling safe both by sea and by land. [87]“

እንደ ኢትዮጵያዊው ታሪክ ጸሐፊ ፤ ሰርጌው ሐብለሥላሴ ፤ ኮስማ በዓይን ህመም ምክንያት በገበታው መጀመሪያ ላይ የነበረውን ፥ ከላይ የተጠቀሰውን ዘመቻ የአደረገውን የእዚኽን ኢትዮጵያዊ ንጉሥ ስም ሰአይገለብጥ ስለ ቀረ ፤ ይኽንን ሰፊ ግዛት ያስገበረ ወይንም ያስገባ ፤ ከንጉሥ ካሌብ በፊት የነበረው አክሱማዊ ንጉሥ ማን እንደ ሆነ በውል የእማይታወቅ በመሆኑ ፤ ዘመቻው ከ500 ዓ.ም. ቀደም ብሎ መካኼዱ ቢታወቅም በምን ያኽል ቀደም እንደ እሚል በትክክል ማስቀመጥ አይቻልም ።

በእዚኽ ግዛት የማጠናከር ዘመቻ የተካተቱት ቦታዎችም በጣም ጥንታዊ ስሞች በመሆናቸው ፤ በትክክል የሁሉንም ቦታዎች ማወቅ ቢያዳግትም ፤ ግብፅ ፥ ጋምቤላ እና ወደ ህንድ ውቂያኖስ የእሚዳረሰውን የአፍሪካ ቀንድ ብዙዎች የእሚስማሙባቸው በመሆናቸው ፤ ዝርዝሩን ትተን ፤ ስሙ ያልተጠቀሰው አክሱማዊ ንጉሥ ፤ ከግብፅ ደቡባዊ ድንበር እስከ ጋምቤላ ፤ ከእዛም እስከ በርበራ ወደብ ሱማሊያ እንዳስገበረ ይታያል ። በደቡብ አረቢያም ፤ የመንን ከእዚያም መካ እና መዲናንም የእሚጨምር ክልል እንዳስገበረ ይናገራል ።

ስለ እዚኽ ፦ የኢትዮጵያ ግዛት ፥ አክሱም የከፍታዋ ጉልላት ላይ ከደረሰችበት ግዜ አንስቶ ፤ የንጉሥ ካሌብ ደጅ አዝማች የነበረው አብረኃ ኹለተኛው ልጅ ማስሩክ ፤ በፐርዥያ እስከ ተሸነፈበት ፤ በብዙ ታሪክ አጥኝዎች ግምት እ.አ.አ. 575 ዓ.ም. የአፍሪካን ቀንድ በመላው እና ከፊል የደቡብ አረቢያ ክፍል በእሚያካትት ኹኔታ ቢያንስ ለኹለት መቶ ዓመታት በአክሱም መዓከላዊ አስተዳደር ስር ቆይቷል ።

ከላይ እንደ አልነው ፤ አከባቢው ከኢዛና ጀምሮ በቀጣይነት በአክሱማዊያን የተማከለ በመሆኑ ፤ ይኽ ስሙ ያልተጠቀሰ አክሱማዊ ንጉሥ ፤ ከላይ በአዱሊሱ የድንጋይ ላይ ገበታ ላይ የተቀመጠው ከኢዛና በረዥም ዓመታት ቀደሞ ብሎ የነበረ አክሱማዊ ንጉሥ ይሆን ይሆናል እና ይኽ አከባቢ ከኢዛናም ቀደም ብሎ በአክሱማዊያን አስተዳደር ስር ሊሆን ይችላል በእሚል እሳቤ እንጂ ፤ ኢዛና እና በእርሱ ዘመን አከባቢ የነበሩ የአክሱም ነገሥታት ፤ ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ በሰሜን ምዕራብ እስከ ሜሮ ፥ በደቡብ እናርያ ድረስ ይዘምቱ እንደ ነበር ፤ የተለያዩ የድንጋይ ላይ የተጻፉ ዜና መዋዕሎች ያሉ በመሆናቸው ፤ እነ እዚኽ አከባቢዎች ፤ ቢያንስ ከኢዛና እስከ ካሌብ ወደ 200 ለእሚጠጋ ዓመት ፤ ኢትዮጵያ ተብለው በአንድ ፖለቲካዊ ማዕከል ፥ በአክሱም ስር እንደነበሩ የተረጋገጠ ታሪካዊ ኃቅ ነው ።

ማለትም ፤ በኮስማስ የቀረበለን የአዱሊሱ ጥርብ የድንጋይ ገበታ ላይ የተቀመጠው ዘመቻ ፤ ከኢዛና ቀደም ባለ ንጉሥ ተካኼዶ ሊሆን ይችላል በማለት ነው ያስቀመጥነው ። ይኽ የአክሱም ንጉሥ ከኢዛና በፊት የነበረ ከሆነ ፤ አከባቢው በአክሱም ተማክሎ ኢትዮጲያ መባል ከኢዛና ቀደም ብሎ ጀምሯል ማለት ነው ፤ ካለሆነም ግን አከባቢው ቢያንስ ከንጉሠ ነገሥት ኢዛና ጀምሮ ፤ ማለትም የዛሬ 1,700 ዓመት ጀምሮ ኢትዮጲያ ተብሎ እና ነገሥታቱም የኢትዮጵያ ንገሠ ነገሥታት ተብለው በአክሱም መናገሻነት ተዋቅሯል ማለት ነው ። ለእዚኽም የተለያዩ ታሪካዊ ማስረጃዎች አሉ ።

ይኽ ሰፊ አከባቢ ፤ በአክሱማዊያን መዓከልነት መመራት ብቻ ሰአይሆን ፤ እንደ ስቱዋርት ማኑሮ ሔይ ፤ ቢያንስ ንጉሠ ነገሥት ኢዛና ፤ ራሱን የኢትዮጵያ ንጉሥ ይል እንደነበረ እና በአብዛኛው አክሱማዊያን ሲባል ፤ ከኢትዮጵያዊ ነጥሎ የመጥራት ዝንባሌ ሰአይሆን ፤ መናገሻቸውን ለማመለከት እንደሆነ ያስቀምጣል ፦

“ሕዝቡ ፥ ምናልባትም የተለያዩ ሕዝብ ‘አክሱማዊያንም’ ጨምሮ ፤ ሐበሻም ተብለው ይጠሩ እንደነበር እና ሐገራቸውም ሐበሻት ትባል ነበር ። ከእዚኽ ሐበሻ ከእሚለው ቃል ነው ፤ አሁን ፋሽኑ የአለፈበት አቢስንያ[2] የእሚለውን ስያሜ እኛ (አውሮፓዊያን) ያመጣነው ። ነገር ግን ፥ በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኹለት ቋንቋ በተጻፈ ረዥም የማዕረጉን ዝርዝር በያዘ የድንጋይ ላይ ጽሑፍ ፥ ሐበሻት የእሚለውን ወደ ግሪክ ሲተረጉም ኢትዮጵያ እያለ ነበር ። …የአክሱም ነገሥታት … ኢትዮጵያ የእሚለውን ስም ሕዝባቸውንም ሐገራቸውንም የእሚጠሩበት ስም ሆኗል ።”

“The people, or perhaps a group of peoples including the `Aksumites', were also called `Habasha', and the name for their country, Habashat, is that from which we derive the now out-of- fashion name `Abyssinia'. However, already by the fourth century AD the Aksumite king Ezana, in his long list of titles in a bilingual inscription…, uses the word `Ethiopia' in the Greek version as the translation for `Habashat'. …, the kings of both Aksum … used the name `Ethiopia' to refer to their own countries and peoples [86].”

ይኽም ማለት ፤ የውጩው ዓለም ብቻ ሰአይኾን ኢትዮጵያዊያን ወይንም ሐበሻ የእሚለን ፤ የአክሱም ነገሥታት ይኽንን ስያሜ ፤ የዓማከሉት አዲሱ የፖለቲካዊ ማሕበረሰባቸው ሕጋዊ ስምነቱን ተቀብለው ፤ ራሳቸውን ኢትዮጵያዊያን ማለት ጀምረዋል ።

ጠቅለል ስናደርገው ፤ በሰፊው ምሥራቅ አፍሪካ በዘመነ አክሱም ፤ የተለያየ መጠን እና ፋይዳ የአላቸው የተለያዩ ስልጣኔዎች ፣ መንደሮች ፣ ግዛቶች ፤ በተበታተነ ኹኔታ ከነበሩበት ፤ በአንድ ላይ ተዋህደው ፤ በአንድ ፖለቲካዊ ማዕከል መመራት ጀምረዋል ።

ስለ እዚኽ ፤ በዘመነ አክሱም ኢትዮጲያዊነት ከሕዝብነት ወደ መንግሥትነት ወደ ሐገርነት ወደ ብሔርነት ተሸጋግሯል ማለት ነው ።

ይኽም ማለት ፤ በዘመነ አክሱም ፤ ከሞላ ጎደል እነ እዚኽን የተለያዩ ኢትዮጵያዊያን በአንድ ፖለቲካዊ አስተዳደር ስር ማድረግ እና በእነ ኢዛና ፤ ምናልባትም ከእነ ኢዛና ትንሽ ቀደም ብሎ ፤ የንጉሠ ነገሥት ማዕረግ ተዋውቆ (ያም ማለት ፤ በአንድ ንጉሥ ስር የተለያዩ ንጉሶች መኖራቸውን ያመለክተናል) እና የተዋሐደ ወይንም በአንድ ፖለቲካዊ አስተዳደር ስር የሆነ ግዛት ወይንም ፖለቲካዊ ማንነት ተፈጥሯል ።

ከላይ በኮስማስ ከተጠቀሰው ፤ ስሙ የእማይታወቅ ንጉሠ ነገሥት ፤ ከኢዛና ትንሽ ቀደም ሊል ይችላል እናም አከባቢው በአክሱም መሪነት መማከል የጀመረው ከኢዛና ቀደም ብሎ ነው እንድ እንል ሊያስብለን ከእሚችሉ ምክንያቶች ሌላኛው ፤ ከንጉሠ ነገሥት ኢዛና ወደ ሀምሳ ዓመት ገደማ ቀደም ብሎ ፤ ማለትም እ.አ.አ. በ270 ዓ.ም. አከባቢ ፤ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ካሉ ኃያላን መንግሥታት አንዷ እንደ ሆነች የእሚያሳዩ ነገሮች መከሰት መጀመራቸው አንዱ ነው ።

ከእነ እዚኽም ክስተቶች አንዱ ፤ ማኒ የእሚባል ማኒክያን የእሚባል እምነት መሥራች ፤ ስለ ወቅቱ የዓለም ኃያላን እንደ ተናገረ የእሚዘገበው ነው ፦

“ማኒ የእሚባለው የፋርሶች (ፐርዢያኖች/ኢራን) ኃይማኖታዊ መሪ ፤ ማኒኪያን የተባለው ኃይማኖት መሥራች እና እንደ አውሮፓዊያኖቹ አቆጣጠር በ 276 ወይንም በ 277 ዓ.ም አከባቢ የሞተ ፤ ተከታዮቹ ፦ በዓለም ላይ ከአሉ ትላልቅ መንግሥታት አራቱ ቀዳሚዎች ፦ ፋርስ ፣ ሮም ፣ አክሱም እና ሳይሎስ ፥ ይኽ ሳይሎስ ምናልባት ቻይና ይሆናል ፤ እንደ ሆኑ ይናገር ነበር ብለው ይዘግባሉ ።”

“The Persian religious leader Mani, founder of the Manichaean religion, who died in 276 or 277AD, is reported by his followers to have described the most important kingdoms of the world as comprising Persia, Rome, Aksum and Sileos, the latter possibly China. [86]“

ከአክሱም የእሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት ፤ ከእነ ሮም ፣ ቻይና እና ፋርስ ጋር እኩል ፤ የዓለም ልዕለ ኃያል ከተባለ ፤ ከወቅቱ ዓራት የዓለም ኃያላን አንዱ የአደረገው ፤ ይኽንን ትልቁን የምሥራቅ አፍሪካን እና ደቡብ አረቢያን የጨመረውን አከባቢ የእሚያስተዳድረው የአክሱም መንግሥት እነዚኽን አከባቢዎች ፤ ምናልባትም ከ270 ዓ.ም. ቀደም ብሎ ማስተዳደር ጀምሮ ስለ ነበር ይኾናል ብለን እንድንገምት ያስችለናል ።

እንደ ማንኛውም የስልጣኔ አጀማመር ፤ በተበታተነ ኹኔታ ፤ በትንንሽ ከተሞች በእዚኽ ሰፊ ፤ የምሥራቅ አፍሪካ በእሚባል አከባቢ የጀመረው የኢትዮጵያዊያኖች ስልጣኔ ፤ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ 2 እና 3 መቶ ዓመታት ውስጥ ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እውቅና የአለው ፤ የጋራ መንግሥት የአለው አንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ሆኗል ።

ምንም እንኳን ፤ እነ እዚኽ እና መሰል ታሪኮች ፤ ኢትዮጵያ በጣም ጥንታዊ እና ትልቅ ከእሚባሉት የዓለም ሐገራት አንዷ እንደ ሆነች ቢመሰክሩም ፤ በአለፉት ብዙ መቶ ዓመታት ፤ በዓለም ዓቀፍ መድረክ ኋላ ቀር ከእሚባሉት የዓለም ሐገራት የእምንመደብ ስለ ሆነ ፤ አንዳንድ ሰዎች ፥ የኋላውን ታሪካችንን የጥንቱን ነፀብራቅ እያደረጉ ፤ ስለ ጥንት ታሪካችን የእሚነገረው በሙሉ የፈጠራ እና የግነት አፈ ታሪክ አድርገው በመውሰድ ሲያጣጥሉት ይታያሉ ።

በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ አንድ ጥንታዊ ጽሑፍ የአሳተመች ፤ የውጭ ዜጋ ፥ በእዚኽ ረገድ የገጠማትን እንዲኽ አስፍራዋለች ፦

“አንድ ኢትዮጵያዊ ወዳጄ ፤ አንድ ግዜ እንደ እዚኽ ብሎ ቀለደ ፦ ‘ምንም ዓይነት ጥያቄ ኢትዮጵያዊውን ስትጠይቂው ፤ ‘እንዴት መሰለሽ የዛሬ ሦሥት ሺ ዓመት …’ ብሎ ነው ንግግሩን የእሚጀምርልሽ ። …”

“An Ethiopian friend once joked that no matter what question you ask an Ethiopian, the answer always begins, “Well, three thousand years ago . . . [93]“

የእዚኽ ወገናችን ምፀት ፤ በአንድ አንድ መሠረት የለሽ የግነት ታሪኮች ከመሰላቸት ይሁን ወይንስ ከሌላ የእሚለውን ትተን ፤ ቴክኖሎጂ ባልተራቀቀበት ዘመን እነዛኽን ከተሞች የገነባ እና ይኽንን የእሚያኽል ሰፊ አከባቢ አማክሎ ያስተዳደረ ሕዝብ ፤ መሰል ፖለቲካዊ ደረጃቸው ከእርሱ በብዙ መቶ ዓመታት ዘግይተው በጀመሩ ሐገራት እንደ እዚኽ በእሚያስገርም ርቀት መከንዳቱ ጥያቄ ቢፈጥርብን አያስገርምም ።

ትላንት ወይንም በጥንቱ ታሪክ ፤ ከትላልቆቹ ጎራ ከነበርን ፤ የዛሬው ወይንም በተነፃፃሪነት የቅርቡ ዘመናችን ታሪክ እንዴት ከኋላዎቹ አስመደበን ? ወይንም ለምን እንደ እዚኽ ኋላ ቀር ሆንን ? ብለን መጠየቃችን እና የጥንቱን የገናናነት ታሪክ መጠራጠራችን ጤናማ ነው ። መጠራጠራችን እና መጠየቃችን ግን ፤ ያለ በቂ ታሪካዊ መሠረት ፤ የጥንቱ ታሪካችን የውሸት ግነት ብቻ ነው ወደ እሚል መሠረት የለሽ ፍረጃ እና ክኽደት ሊያመራን አይገባም እንጂ ።

በዓለም ሕዝብ ታሪክ ስልጣኔዎች ፤ የመጀመር ፣ የማደግ ፣ ኋላ የመቅረት አንድ አንዴም የፍርሥራሽ ክምር ሆነው መጥፈታቸው ዓለማዊ ገፅታ የአለው ክስተት መሆኑን መረዳት አለብን ።

በመካከለኛው ምሥራቅ ፤ ባቢሎን ፣ ሶሪያ እና በአፍሪካ ግብፅ በጣም ድንቅ የነበሩ ስልጣኔዎች የነበሩ ሲሆን ፤ እነ እዚኽ ጥንታዊ እና ታላላቅ ስልጣኔዎች ግን ፍርሥራሽ ሆነው ጠፍተው በሆነ አጋጣሚ አጥኚዎች እስኪ ያገኙዋቸው ድረስ ፤ እንደ ነበሩ እንኳን አይታወቅም ነበር ። ስለ እዚኽ ፦ ትልቅ የነበረች ኢትዮጵያ ፤ በታሪክ አጋጣሚ ዛሬ ኋላ ቀር ብትሆን ፤ እሰይ ደግ አደረግሽ የእሚያስብል ባይሆንም ፤ የቀደመው ታሪካችን ውሸት ፥ ማስመሰል እና ግነት የሞላበት ነው ሊያስብለን በራሱ በቂ አይደለም ።

መሰል ክስተቶች ፤ ከታሪክ ማማ ላይ መውደቅ ፤ ያሉ እና ወደ ፊትም የእሚኖሩ ፤ ዓለም ዓቀፋዊ ክስተቶች እንጂ የተለየ የኢትዮጵያ ኹኔታ ብቻ አይደሉም ።

ፍርሥራሾች (Ruins) ፤ በእሚለው መጽሐፉ ፥ ቮልኒ ለማሳየት የፈለገው ሐቅ እና ለመመለስ የፈለገው ጥያቄ ፦ በአንድ ወቅት እጅግ ታላላቅ የነበሩ ስልጣኔዎች ወደ ሙታን መንደረነት የመለወጣቸውን ታሪካዊ ኃቅ እና ይኽም ለምን እንደ እሚሆን ነው ። ምንም እንኳን የቮለኒ የተንጋደደ ኃይማኖታዊ ግንዛቤ መጽሐፉን ብዙም ተወዳጅ እንደ አይሆን ቢያደርገውም ።

በእዚኽው መጽሐፉ ፥ ፓልሜራ ስለ እምትባለው ጥንታዊት የሶሪያ ከተማ ቮለኒ እንደ እዚኽ ይላል ፦

“በአንድ ወቅት አንፀባሪቂ ከነበረችው ከተማ የቀረው አሳዛኝ አፅም ነው ፥ ከኃያሉ መንግሥቷ የቀራት ቢኖር የደበዘዘ ትዝታዋ ነው ! … የበለፀገው የንግድ መዓከልነተዋ ወደ አስከፊ ድህነት ተቀይሯል ። የነገሥታት ቤተ መንግሥቶች የሚዳቋ መቆያ ሆነዋል … ስንት ክብር በእዚኽ ተጋረደ ፥ ስንት የሰው ድካም ባክኖ እንደ ቀረ ። ... እንዲኽ ነው እንግዲኽ የሰው ልጅ ሥራ የእሚመክነው ፥ መንግሥታት ፣ ኃያላን እብስ የእሚሉት !።”

“And now a mournful skeleton is all that subsists of this opulent city, and nothing remains of its powerful government but a vain and obscure remembrance! ... The opulence of a commercial city is changed into hideous poverty. The palaces of kings are become the receptacle of deer . . . What glory is here eclipsed, and how many labors are annihilated! . . .Thus perish the works of men, and thus do nations and empires vanish away! [85]“

ስለ እዚኽ ፦ ስልጣኔዎች ይነሳሉ ፤ ይገናሉ ከእዛኽ ይሻሻሉና ይቀጥላሉ ወይንም ጭራሽ ይጠፋሉ ፣ አንዳንዴም በአሉበት እየረገጡ ይኖራሉ ፤ ይኽ የተለመደ እና ዓለም ዓቀፋዊ የሆነ የሰው ልጆች የታሪክ ዑደት ነው ።

ስለ እዚኽ ፦ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ የጥንቱ ኢትዮጵያ እንደ አልሆነች እና ዛሬ ያለችው ኢትዮጵያ ፤ የድሮውን ታሪካዊ የጥቁር አፍሪካዊያን ስም ፤ ከዘመነ መሣፍንት በኋላ በውዳጅ የወሰደች እና ከድሮው ኢትዮጵያ ጋር ቁርኝት እንደ ሌላት ለማስቀመጥ የእሚሞክሩ ሰዎች ፤ የጀማሪ ታሪካዊ እውቀት እንኳን የሌላቸው ሰዎች ናቸው ።

የአክሱም መንግሥትም ፤ ራሱን የቻለ ፥ ከኢትዮጵያ የተነጠለ ስልጣኔ እንደሆነ እና በውል በአይታወቅም ኢትዮጵያ ፤ ለዛሬዋ ኢትዮጵያ ስያሜ የሆነው በቀርብ ነው ማለት ፤ ሮም ጣሊያን አይደለችም እንደ ማለት ነው ።

አክሱም ፤ ከኢትዮጵያ ከተሞች አንዷ እና በታሪክ አጋጣሚ ደግሞ ለረዥም ግዜ የኢትዮጵያዊያኖች መናገሻ ከተማ የነበረች ነች ፤ የእሚለው ኃሳብ ነው ፤ ታሪካዊ መሠረት የአለው ገላፃ ።

ከእላይ እንደ አየነው ኢትዮጵያዊያን ፤ ኢትዮጵያዊ የእሚለውን ስያሜም ቢያንስ ፤ ኢዛና ከነገሠበት ዘመን አንስቶ ፤ በወል ራሳቸውን ለመጥራት ይጠቀሙበት እንደ ነበር ፤ በእዚኽ ስም የእሚጠራው መንግሥታቸውን ከግብፅ በስተደቡብ የአለውን ኑብያ ፣ የዛሬዋን ኢትዮጵያ ፣ ወዘተ ፤ የእሚጨምር እና የውጪውም ዓለም ኢትዮጵያዊ ብሎ ይኽንን አከባቢ እና ሕዝብ ቢያንስ ከዛሬ 1,700 ዓመት ቀደም ብሎ ያውቀው እንደነበር በታሪክ የተመዘገበ ነው ።

ለምሳሌ ፦ ፕሮኮፕየስ የተባለው በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ፤ የታሪክ ጸሐፊ የነበረው ፤ የአክሱም ንጉሥ ካሌብ ፤ በደቡብ የመን ሕመራይቶች ላይ የአደረገውን ዘመቻ በእሚዘግብበት ወቅት እንዲኽ ብሏል ፦

“… ንጉሳቸው አክሱም ስለ እሚኖር አክሱማዊት የተባሉት ኢትዮጵያዊያን ።”

“… The Aethiopians who are called Auxomitae, because their king resides in the city of Auxomis. [94]“

ይኽም ማለት ፤ በአንዳንድ ጥንታዊያን መዛግብት ውስጥ ፤ የአክሱም መንግሥት ሲባል ቢታይም ፤ ልክ በእዚኽ በእኛ ዘመን በተለያዩ ግዜያት አሜሪካ ለማለት ዋሽንግተን ፥ ቻይና ለማለት ቤይጂንግ ወይንም ራሺያ ለማለት ሞስኮ እንደ እሚባለው ዓይነት ገላፃ እንጂ ፤ ዋሽንግተን ሲባል አሜሪካ ፣ ሞስኮ ሲባል ራሺያ ፣ ቤይጂንግ ሲባል ቻይና እና አክሱም ሲባል ኢትዮጵያ ማለት መኾኑ መስረታዊ የመጀመሪያ ደረጃ እውቀት ለአለው ሰው ግልፅ ነው ።

ስለ እዚኽ ፦ በመላው ምሥራቅ አፍሪካ ይኖር የነበረው ሕዝብ ፤ በውል ከእማይታወቅ ግዜ እና ቢያንስ ከክርስቶስ ልደት 500 ዓመት ቀደም ብሎ ጀምሮ በወል ስሙ ኢትዮጵያ ተብሎ ይጠራ እንደ ነበር ፤ ኢትዮጵያም በአክሱም መናገሻነት ፤ አንድ ዓለም ዓቀፋዊ እውቅና እና ገናናነት የአላት ፤ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ሆና ከቆመች ቢያንስ 1,700 የሆናት መሆኑ የተረጋገጠ ታሪክ ነው ።

ምንም እንኳን በረጅሙ እና ፈታኙ ታሪክ ፤ ደቡብ አረቢያን ከአካተተው ፤ መላው ምሥራቅ አፋሪካ (ኹለቱ ሱዳኖች ፣ ኢትዮጵያ ፣ ሱማሌ እና የደቡብ አረቢያ) ላይ ተንሰራፍቶ ከነበረበት ኹኔታ ፤ የኢትዮጵያ ድንበር ዛሬ የእምናውቀውን ብቻ ቢሆንም በእዚኽ ስም እና በታሪካዊ ፖለቲካዊ መሪዎቹ ስር ይዞ መቀጠል የተቻለው ።

የቀሩት ኹለቱ የቀድሞ ኢትዮጲያ አካላት ፦ በምዕራብ ሱዳን እና በምሥራቅ ደቡብ አረብያ ፤ በታሪክ ኺደት የራሳቸውን አዲስ ፖለቲካዊ ማንነት እያየያዙ ፤ ከትልቋ ኢትዮጵያ የተነጠሉ እና አዲስ የራሳቸው ፖለቲካዊ መዓከላት ሆነዋል ።

ይኽም የኢትዮጲያ ታሪክ ኢትዮጵያን ፥ የዛሬዋን ኢትዮያን ፤ ይኽን መሰል የፀና እና የቆየ ፖለቲካዊ ማሕበረሰባዊ አንድነቷን ፥ መጠኑ በተለያየ ግዜ ሲሰፋ እና ሲጠብ ቢኖርም ፥ ሳይቆራረጥ እና በውጭ ወራሪ ኃይል ሳይያዝ ለረዥም ዘመን አቆይታ መያዟ ፤ በዓለም ታሪክ ብቸኛዋ ሐገር ሳያደርጋት አይቀርም ።

በአለፈው 2 ሺ ዓመት ፤ የፖለቲካ ማዕከሉን ብቻ ከመቀየር በቀር ፤ በማንም ውጫዊ ኃይል አስተዳደር ስር ሳይገባ ፤ በአንድ አከባቢ ላይ ከ1600 ዓመታት በላይ ፤ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ የቆየ ሐገር ወይንም ሕዝብ ፤ ከኢትዮጵያ በስተቀር ያለ አይመስልም ።

ለማጠቃለል ፦ ከላይ በአጭሩ ለማስቀመጥ እንደ ተሞከረው ፥ በተበታተነ መልኩ ሲኖሩ የነበሩ ፤ በወል ስማቸው ኢትዮጵያዊ ተብለው የእሚታወቁ ሕዝብ ፣ ግዛቶች ፣ ከተማዎች እና ስልጣኔዎች ፤ በዘመነ አክሱም ፥ በአንድ ፖለቲካዊ አስተዳደር ስር እንደ መጡ ከእዚያኽም እስከ ዘመነ አክሱም በተለይ በ4ኛው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ አንስቶ ራሳቸውን ኢትዮጵያዊያን ብለው መጥራት መጀመራቸውን እና የውጩም ዓለም ኢትዮጵያዊያን ብሎ እንደ አወቃቸው ወይንም ኢትዮጵያ እንደ አንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ እንደ ተመሠረተች አይተናል ።

ይኽ በአክሱም መዓከልነት ፤ ይኽን ሰፊ አከባቢ አማክሎ የእሚያስተዳድር የፖለቲካ ወዋቅር መፍጠር መቻል ፤ እንደ ሕዝብ የዴሞክራሲያዊ ሐገር ግንባታ ፤ የመጀመሪያው ዳዴያችን ነበር ።

አስቀድመን እንደ አልነው ፤ በዓለም ሕዝብ ታሪክ ፤ ሲጀመሩ ዴሞክራሲያዊ ሐገር ሆነው የተጀመሩ ሐገራት የሉም ። በታሪክ ቤተሙከራነት ፥ ይኽን ሲያነሱ ያንን ሲጥሉ ከርመው ነው ፤ ዛሬ ዴሞክራሲያዊ የእምንለው የመንግሥት አስተሳሰብ ላይ የደረሱት ። በእዚኽ የታሪክ ቤተሙከራ ውስጥ ፥ ወደ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት በእሚደረገው ግስጋሴ ፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ ፤ አቅም የአለው የተማከለ ፖለቲካዊ ማዕከል መፍጠር ነው ።

መዓከል ግን እንዲያው ዝም ብሎ አይፈጠርም ፤ ያንን መዓከል አስፈላጊ የእሚያደርገው ፖለቲካዊ ፥ ኢከነሚያዊ እና ማሕበራዊ ፍላጎት መኖር እና ይኽንን ፍላጎት ተረድቶ ፤ ይኽንን ፍላጎት እውን ለማድረግ ወይንም ለመተግበር የእሚችል ተቋም እና አመራር መፈጠር አለበት ።

የአክሱም መንግሥት ፥ በታሪክ ይኽንን የመዓከልነቱን ሚና ለመጫወት የአስቻለው ፤ የተረዳው ብሎም የአሳካው የመጀመሪያ ማሕበራዊ ፍላጎት ፤ በባሕርም በየብስም ለእሚጓዙ ነጋዴዎች የእሚያመች ሰላም እና ደህንነት የማረጋገጥ ፍላጎትን ነበር ። የአክሱም መንግሥትም ፥ ይኽንን ሰላም እና ደህንነት በሰፊ ክልል ውስጥ ማስከበር የእሚችል ፤ ወታደራዊ አቅም ገንብቶ ፥ በየብስም ሆነ በባሕር የእሚደረጉ ንግዶች በሙሉ ፤ ‘ያለምንም’ ስጋት እንዲደረጉ ማድረግ መቻሉ ወይንም ይኽንን ማሕበራዊ ሸቀጥ (public good) አስፈላጊነት መረዳት እና ማሳካት መቻል ነበር የህልውናው መሠረት ።

በሰፊው ምሥራቅ አፍሪካ ፥ ከሌሎች አከባቢዎች በተለየ ፤ ይኽንን ክፍተት መረዳት እና ይኽንንም ክፍተት ለመሙላት አክሱም ለምን እንደቻለች የእሚያስረዳ በቂ ታሪካዊ ጥናት ስለ አልተገኘ ፥ አክሱም ከሌላው የአከባቢው ከተሞች በተለየ ለምን በእዚኽ መልኩ የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያን የወል ፖለቲካዊ መዓከል መሆን እንደ ቻለች ማስቀመጥ ትንሽ ይከብዳል ።

ዋናው ቁም ነገር ግን ፤ አክሱም ይኽን ማሕበራዊ ፍላጎት ማቅረብ ወይንም ማገልገል በመቻሏ ፤ ብቸኛ ሕጋዊ ቀረጥ ሰብሳቢ በመሆን ኃይሏን የበለጠ አጎልብታ የመጀመሪያው የወል የኢትዮጵያዊነት ማዕከል ሆናለች ።

ኹለተኛው ፥ የአክሱምን ማዕከላዊነት ያጠናከረው እና የዛሬዋን ኢትዮጵያ በአንድነት ለማስተሳሰር የጠቀመው ፤ ሌላው የአክሱም ዘመነ መንግሥት ስኬት ፤ ክርስትናን ተቀብሎ ፤ ክርስትናን የመንግሥቱ ኃይማኖት ማድረጉ ነው ።

ስቱዋርት ሙንሮ ኄይ ፤ ሩፍነስ የተባለ በእነ ኢዛና ዘመን አከባቢ የነበረ የላቲን ታሪክ ጸሐፊን ዋቢ አድርጎ ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መሰራቹ አባ ሰላማ ክሳቴብርኃን (ፍሬምናጠስ) ወደ ኢትዮጵያ የመጣበትን እና ክርስትና በተመዘገበ ታሪክ በኢትዮጵያ ውስጥ የጀመረበትን አግባብ በተረከበት ክፍል ላይ እንደ አስቀመጠው ፤ ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ቤተመንግሥት መግባት ያቻለው ፤ ሕንድን ለመቃኘት የፈለገ አንድ በጢሮስ የነበረ ፈላስፋ ፤ በልጅነታቸው ሰብዓዊ ሳይንስ (Humanities) የእሚያስጠናቸውን ዘመዶቹን ፍሬምናጦስ እና ኤደስየስ ይዞ በቀይባሕር ላይ በመጓዝ ላይ ሳለ ታንኳቸው በኢትዮጵያ ወታደሮች ተማርኮ ልጆቹ ፍሬምናጦስ እና አዲስየስ በምርኮኝነት የኢትዮጵያ ቤተመንግሥት አገልጋይ በመኾናቸው ነው ።

ከእነ እዚኽ ኹለት ብላቴኖች አንዱ ፤ ፍሬምናጦስ የልዩ ችሎታ ባለቤት በመኾኑ ፤ በቤተ መንግሥት ከማገልገልም አልፎ በቤተ መንግሥት ውስጥ ትልቅ ተሰሚነት የአለው አማካሪ ኾኖ ስለነበር ፤ በእዚኽ ወቅት ፤ አብሮ አደጉን ንጉሥ ኢዛናን ወደ ክርስትና ለማምጣት ችሏል ።

ፍሬምናጦስ ኢዛናን ወደ ክርስትና ከማምጣቱም በአሻገር ፤ በወቅቱ ለንግድ እና ለተለያየ ሥራ ወደ ኢትዮጵያ የእሚመጡ ሌሎች የውጭ ዜጎችን ጨምሮ ኢትዮጵያዊያኖች ለፀሎት የእሚሰበሰቡበት ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያ መስርቶ የነበረ በመኾኑ ፤ ከኢዛና ንግሥና ወይንም ኢዛና ውደ ዙፋን ከመጣ በኋላ ፤ ከምርኮ ተለቆ ወደ ሐገሩ እንዲመለስ ሲፈቀድለት ፤ ወደ ሐገሩ ሲመለስ እግረ መንገዱን ወደ ግብፅ አሌክሳንድሪያ ገብቶ ፤ በኢትዮጵያ የጀመረው ቤተክርስቲያን ያለ መጋቢ ቀርቶ እንደ አይጎዳ ፤ በግብፅ አሌክሳንደሪያ በአለችው መንበር ኢጵስ ቆጶስ ወደ ነበረው አትናስያስ ጋር ኼዶ አትናስያስ ለቤተክርስቲያኒቱ መጋቢ እንዲሾም አሳሰበው ።

የአሌክሳንደሪያው ጳጳስ አትናስያስም ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘፍጥረት ምዕራፍ 41 ላይ ፦ የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ በግብፅ በግዞት በነበረበት ወቅት ፤ የፈርዖንን የሰባት ዓመት የጥጋብ እና እርሱንም ተከትሎ የእሚመመጣውን የሰባት ዓመት ረኃብ ያለመበትን ሕልም ከፈታ በኋላ ፤ ለግብፁ ንጉሥ ፈርዖን ፦ ጥበበኛ ሰው ፈልገኽ ሹም ሲለው ፤ ፈርዖንም ከአንተ የተሻለ ጥበበኛ የለኝም እና አንተኑ ሾሜኻለው እንዳለው ፦

ዘፍጥረት 48፡ 33 ፦

“አኹንም ፈርዖን ብልህና አዋቂ ሰውን ይፈልግ፥ በግብፅ ምድር ላይም ይሹመው። … ፈርዖንም ሎሌዎቹን እንዲኽ አላቸው፡— በውኑ የእግዚአብሔር መንፈስ የአለበትን እንደ እዚኽ ያለ ሰው እናገኛለንን?”

ለመሰረታት በኢትዮጵያ ላለችው ቤተ ክርስቲያን መጋቢ ሹምላት የአለውን ፍሬምናጦስ ፤ አትናሲያስ ይኽንን የመጽሐፍ ቅዱሱን ታሪክ መሠረት በማድረግ የመሠረትኻትን ቤተክርስቲያን እና እንደ አትጎዳ ፤ መጋቢ ሹምላት ብሎ ከእሚያስብላት ከአንተ የተሻለ ሰው የእማይኖር በመሆኑ አንተው ራስኽ ምራት ብሎ ሾመው ፦

“ከእዚያኽም አትናሲየስ (በቅርቡ ኢጵስ ቆጶስ ኾኖ ስለ ነበር) ፤ የፍሬምናጦስን ቃል እና ተግባር በጥንቃቄ ከአጤነ በኃላ ፤ በቀሳውስቱ ጉባኤ ፤ ‘እነ እዚኽን ነገሮች መከወን የእሚችል በውኑ የእግዚአብሔር መንፈስ የአለበትን እንደ እዚኽ ያለ ሰው እናገኛለንን’ በማለት ፤ ለእዚኽ አገልግሎት በመለየት ፤ በእግዚአብሔር ፀጋ ወደ መጣበት እንዲ መለስ ግድ አለው ።”

“Then Athanasius (for he had recently assumed the episcopate) having carefully weighed and considered Frumentius’s; words and deeds, declared in a council of the priests: `What other man shall we find in whom the Spirit of God is as in thee, who can accomplish these things’; And he consecrated him, and bade him return in the grace of God whence he had come. [86]“

ከእዚያኽን ግዜ አንስቶ እስከ አጼ ኃይለ ሥላሴ ግዜ ድረስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፤ ሐዋሪያው ማርቆስ የመሰረታት ነች በእምትባለው ፤ የአሌክሳንደርያዋ ቤተክርስቲያን መንበር ስር የቆየችበት ታሪካዊ ምክንያትም ይኽ ነው ።

እዚኽ ጋር ክርስትና ማለቴ ፥ ከፍተኛ የእውቀት እጥረት በአለበት እና የመገናኛ መንገዶች (Communication infrastructure) ውስንነት ከፍተኛ ጋሬጣ በሆኑበት በቀደመው ዓለም ፤ እንደ ክርስትና ያለ ሰፊ ቀኖና የአለው ኃይማኖት ፥ አንድ የፖለቲካዊ ማሕበርሰብ አመለካከት በመፍጠር ውስጥ የአለውን ሚና በማስመልከት ነው ።

የአክሱም መንግሥት ፤ ክርስትናን የመንግሥቱ መዓከል ከአደረገ ወዲኽ ፤ በአክሱም ማዕከላዊነት እና አጋዥነት ፤ የኃይማኖት ቀናዒያን ፥ በአብዛኛው ከውጭ እየመጡ ፥ መላ ሐገሪቱን ክርስትናን በማስተማር ለማዳረስ ስለ ሰሩ ፥ የአክሱም መንግሥት ፤ ከአቀረበው የሰላም እና ደህንነት ግልጋሎት በአሻገር ፤ አንድ የማሕበረ ኢከነሚ ለመፍጠር በእሚደረገው ጉዞ ውስጥ ፤ ሰዎችን የእሚያስተሳስር የጋራ እሴት መዓከል በመሆንም ታሪካዊ ሚና ተጫውቷል ።

በእዚኽ መልኩ ራሱን አጠናክሮ ኃይሉን የገነባው የአክሱም መንግሥት ፤ ኢዛና ክርስትናን ከተቀበለ በኋላ ፤ ኃይማኖትን ማስፋፋት ፤ ኹለተኛው ማሕበራዊ ግቡ አድርጎታል ። ይኽ በወቅቱ ፥ በሐገር ውስጥ ሕዝብ ከማስተሳሰር ፋይዳው በአሻገር ፤ ኢትዮጵያን ፥ በዓለም ዓቀፍ መድረክ ፥ በቀዳሚነት ክርስትናን የተቀበሉ ሐገራት ‘የክብር መዝገብ’ ውስጥ በማስመዝገብ ፥ ቀጣይነት በአለ፟ው መልኩ በኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥም ትልቅ ሚና የአለ፟ው ታሪክ ነው።

ምንም እንኳን ፥ እንደ መጽሐፍ ቅድሱ ፤ ከእሥራኤል ሕዝብ ውጭ ፤ ክርስቶስ ከአረገ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ፤ ማለትም ከ 50 ዓ.ም. ቀደም ብሎ ፤ የመጀመሪያው ወንጌል የተሰበከለት ኢትዮጵያዊ ፥ ህንደኬ የተባለችው ንግሥት በጅሮንድ ቢሆንም ፤ የተመዘገበ ታሪክ ወይንም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የሆነ ማስረጃ የአለው የክርስትና ታሪክ በኢትዮጵያ የተጀመረው ፤ በንጉሠ ነገሥት ኢዛና ዘመን ነው ።

በመጽሐፍ ቅድሱ የተጠቀሰችው ሕንደኬ ፤ ከላይ በገለፅነው አውድ ኢትዮጵያዊ ለመሆኗ ምንም ጥርጥር በአይኖረውም ፤ ንግሥት ህንደኬ ፥ ንግሥተ ነገሥታት ዘኢትዮጵያ ትሁን ወይንም ከተለያዩት የኢትዮጵያ ዙፋኖች የአንዱ ንግሥት ትሁን ወደ ፊት የታሪክ ጥናት የእሚመልሰው ይሆናል ።

በተመዘገበው ታሪክ ኢትዮጵያ በንጉሥ ኢዛና ዘመን ክርስትናን ተቀብላ የመንግሥት ኃይማኖት ማድረጓ ፤ ከሮማዊ ቆስጠንጥኒዎን እና ከኢትዮጵያው ኢዛና ፤ ክርስትናን ቀድሞ የተቀበለው ማነው የእሚለውን አከራካሪ የአደረገው ቢሆንም ፤ ኹለቱም ግን እ.አ.አ. ከ310 እስከ 350 ባለው ዓ.ም. ውስጥ ፤ ክርስቲያን ሆነው ፤ ክርስትናን የመንግሥታቸው ኃይማኖት አድርገዋል ። በእኔ ግምት ፤ ኢዛናን የአሳደገውም ሆነ ወደ ክርስትና የአመጣው ፍሬምናጦስ (አባ ሰላማ) ስለ ሆነ ፤ ኢዛና በትረ ስልጣኑን ከያዘበት አንስቶ ወይንም ትንሽ ቀደም ብሎ ክርስቲያን ነበር ብሎ ማሰብ የእሚቻል ይመስለኛል ።

እንግዲኽ ፤ ኢትዮጵያ ወደ ሕዝባዊ መንግሥት የእምታደርገውን ዝግመት ፤ የመጀመሪያ እርምጃ እርሱም ፦ አንድ የጋራ ፖለቲካዊ መዓከል መመሥረት ፤ በእዚኽ የመጀመሪያ የታሪካችን ክፍል በአልኩት ወቅት ፤ ከላይ ለማስቀመጥ በመኮርነው አግባብ እ.አ.አ. ከ330 ዓ.ም. ላይ ተጠናቋል ።

የአክሱም መንግሥት ግን እነ እዚኽን ኹለት ቀዳሚ ማሕበራዊ ሸቀጦች ለሕዝብ በማቅረብ የኢትዮጵያዊያን የመጀመሪያው የጋራ ፖለቲካዊ መዓከል ራሱን ከማድረግ ስለ አለፈ ወይንም በእነ እዚኽ ኹለት እሴቶች ብቻ ስለ ተወሰነ ከ6ኛው ምዕተ ዓመት ማገባደጃ አከባቢ አንስቶ ፤ ከእዚኽ በመቀጠል የእምናየው ኹለተኛው እና ነውጥ የበዛበት የታሪካችን ክፍል ተጀምሯል ።

  1. አኳ Aqua ውኃ ከእሚለው ጋር የእሚያያዝ ነው። ↑

  2. የመካከለኛው ዘመን አውሮፓዊያኑ ፥ ሐበሻ ለማለት በስህተት አበሲያ ይሉ ስለነበር ፤ በዛም በእንግሊዘኛ የቃል ርቢ ሕግ ከህዝብ ስም ወደ ሐገር ስም ሊለውጡት ሲሞክሩ አብሲንያ ሆነ ። ↑