ይኼ ኹለተኛው የታሪካችን ክፍል ፤ በክፍል አንዱ የታሪካችን ምዕራፍ ቢያንስ ለኹለት ምዕተ ዓመታት አክሱምን መናገሻው እና የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ መዓከል አድርጎ በስልጣን ላይ የቆየው ሰለሞናዊ ስርወ መንግሥት ፤ በደረሰበት ፖለቲካዊ ውድቀት ፤ ከግዜ ወድ ግዜ ወደ በመንግሥታዊ ሥራ ፈትነት እና እብሪተኝነት በመዝበጥ ፤ ከውስጥ ተዳክሞ ፤ መናገሻውን እንዲቀይር እና ለግዜውም ቢሆን ከስልጣን የተወገደበትን ኹኔታ የእሚመለከት ነው ።
ይኽ የአክሱሙ ስረወ መንግሥት አንፀባራቂ ገናነት መዝቀጥ የጀመረበት እና ነባራዊ ንጉሣዊ መሪዎቹ ፤ መናገሻቸውን ከአክሱም ወደ ሸዋ ለማዞር የተገደዱበት እና የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥታትነት ስልጣናቸውን በዛግዌ ስረወ መንግሥት መሪ እስከ ተነጠቁበት የአለው ግዜ ፤ ጥርት ብሎ የእሚታወቅ በአይሆንም ፤ በእኔ አስተያየት ይበልጥ አስማሚ ይሆናል ያልኹት ፤ የአብረኃ ኹለተኛው ልጅ መስሩክ በየመኖች አመፅ እና በፋርሶች (ፐርዢያ/ኢራን) እርዳታ ከየመኗ ሰንዓ ከስልጣን ከተወገደበት እ.አ.አ. 575 ዓ.ም. ጀምሮ ፤ በብዙዎች ዘንድ የዛግዌ ስረወ መንግሥት ፤ ከሰለሞኑ ስርወ መንግሥት ውጭ የሆነ የኢትዮጵያ አዲስ ስረወ መንግሥት ሆኖ የፖለቲካ ስልጣኑን ወሰደ እስከ እሚባልበት ፤ እንደ ሰርጌው ሐብለሥላሤ እ.አ.አ. 970 ዓ.ም. የአለውን 395 ዓመታት ውስጥ የእሚጠቃለል ነው ።
የተለመዱትን የታሪክ መጽሐፍት የቃኘን እንደ ሆን ፤ የአክሱም መዝመም መነሻ ምክንያቶች ናቸው ብለው የእሚዘረዝሩዋቸው ፦ የአየር ንብረት ለውጥ ፣ የተፈጥሮ ኃብት መመናመን ፣ የአክሱም መንግሥት ባሕር ኃይል በፋርስ (ፐርዢያ/ኢራን) በመውደሙ ፤ አክሱም በቀይ ባሕር ላይ የነበራትን የበላይነት ፥ በእዚያኽም የቀረጥ ገቢዋን በማጣቷ ግምጃ ቤቱ ነጥፎ ፣ በድቡብ አረቢያ የነበረው የአክሱም አስተዳደር በፋርስ መንግሥት ተሸንፎ ከእዚያኽ መባረሩ የሞራል ውድቀት አስከትሎ ፣ ወዘተ ፤ የእሚሉ ናቸው።
በአክሱም እና አከባቢው የአየር ንብረት በመለወጡ እና ባሕላዊ የተፈጥሮ ኃብት አጠቃቀም ፤ አከባቢውን አራቁቶት ፤ አከባቢው ለትልቅ መንግሥት መኖሪያነት አመቺ እንደ አይሆን በማድረጉ ነው በአክሱም የነበረው የኢትዮጲያ መንግሥት የወደቀው የእሚለው መላምት ፤ ለአከባቢ ጥበቃ ፕሮፖጋንዳ የእሚመች ቢሆንም ፤ ከሱዳኗ ሜሮ እስከ የመኗ ሰንዓ ፥ ከኤርትራዋ አዱሊስ እስከ ደቡባዊ ኢትዮጲያ እናርያ ድርስ ሰፊ አከባቢን አማክሎ የእሚያስተዳድር አንድ መንግሥት መንግሥታዊ ጥንካሬው በሌላ ምክንያት ከአልተጎዳ በስተቀር ከአክሱም መቶ እና ኹለት መቶ ኪሎሜትር ርቀት ላይ ፤ ብዙ ለም አከባቢዎች እያሉ ፤ በአክሱም እና አከባቢዋ የአየር ንብረት ለውጥ እና የተፈጥሮ ኃብት መመናመን ምክንያት ለውድቀት ይዳረጋል የእሚለውን መላምት ለመቀበል ትንሽ ያዳግታል።
የአየር ንብረት ለውጥ እና የተፈጥሮ ኃብት መመናመን ፤ በቅርብ ርቀት ለይ አመቺ የአየር ንብረት እና የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ኃብት በእሚገኝበት አከባቢ ፤ ቢበዛ የመናገሻን ለውጥ ማስከተል እንጂ አንድን መንግሥት ለማፍረስ በቂ ቅድመ ኹኔታ መሆን አይችልም።
በባሕር ኃይሉም ጉዳይ ስንመጣ ፤ ምንም እንኳን የአክሱሙ መንግሥት የቀይ ባሕርን በበላይነት ቢያስተዳድርም እና በመርከብ ጦር እየላከ ባሕር ተሻግሮ ግዛት ቢይዝም ፤ እንደ አብዛኛዎቹ የወቅቱ ታሪክ ዘገባዎች ፤ የአክሱም መንግሥት በምድር ጦር የበረታ እንጂ ይኽ ነው የእሚባል የባሕር ኃይል የአሉት እና በባሕር ላይ ጦርነትም የእሚታወቅ መንግሥት አልበረም (It was not a naval power)። እንዲያውም ለወታደራዊ ዘመቻዎች ራሱ ፤ መንግሥት ከነጋዴዎች የእሚከራያቸውን መርከቦች ነበር የእሚጠቀመው እንጂ የራሱ የባሕር ኃይል ገንብቶ የእሚያስተዳድር መንግሥት አልነበረም ፤ ቋሚ የባሕር ኃይል የመገንባት እና ይዞ የመቆየትም ጉዳይ ፤ ግልጽ እና ቀጥተኛ የባሕር ላይ አደጋ እና ከፍተኛ የኢከነሚ አቅም ከሌለ ፤ ሊያስፈልግ ይችላል በእሚል ብቻ በቀላሉ የእሚገነባ እና የእሚያዝም አይደለም ።
በእኔ እምነት ከእነዚኽ ግድ የለሽ ከሆኑ እና አክሱምን የጣላትን ችግር ከውጭ (externalise) በማድረግ ፤ እውነተኛ ውስጣዊ መንግሥታዊ ችግሩን ከእሚሸፍኑ መላምቶች ይልቅ ፤ ትክክለኛው የአክሱም ውድቀት ፤ በወቅቱ ከተከሰተው ዓለም ዓቀፋዊ የፖለቲካ ስረዓት ችግር ጋር የእሚያያዝ ነው። የአክሱም ወድቀት ፤ ከሮማው አቻው ጋር መያያዙም እንደው የአጋጣሚ ጉዳይ ሰአይሆን ፤ እነ እዚኽ ኹለት የወቅቱ ክርስቲያናዊ ስልጣኔዎች ከእሚገኙበት ተመሳሳይ የማሕበረ ኢከነሚ ኹኔታ የተነሳ ፤ ከገጠማቸው ተመሳሳይ ችግር የተነሳ ይመስለኛል።
ይኽም ማለት ፤ የአክሱም መንግሥት ውድቀት ምክንያት ፤ የስረዓት ውድቀት ውጤት ነው ልክ እንደ ሮማው አቻው።
የሰው መንግሥት በእሚል በአቀረብነው የእዚኽ መጽሐፍ ምዕራፍ ኹለት ላይ ፤ በእግዚአብሔር ፊት አይሁዳዊ ወይንም የግሪክ ሰው ፣ ባሪያ ወይንም ጨዋ ፣ ወንድ ወይንም ሴት ፣ ወዘተ ፤ የእሚል ክፍፍል የለም ፤ እግዚአብሔር ሰውን ከእነ እዚኽ ዓይነት ልዩነቶቹ በአሻገር ፤ ሰውን ኹሉ በሰዉነቱ እኩል ነው የእሚመለከተው የእሚለው እና የቀደመውን ዓለም የዘር ፣ የኃይማኖት ፣ የማሕበራዊ ደረጃ ፣ የጾታ ፣ አጥር የአፈረሰ የክርስትና መልዕክት በግዜ ኺደት ቀስ ብሎ ወደ ማሕበረ ፖለቲካዊ ስረዓት ውስጥ በመስረግ ፤ የቀደመው ዓለም የተዋቀረበትን የአስተሳሰብ መሠረት በመናዱ ፤ ዓለም ወደ ፊት መቀጠል ከፈለገች ፤ ማሕበረ ፖለቲካዋን በአዲስ መልኩ የእዚኽ መልዕክት ጭብጥ በሆነው በሰዎች ሰብዓዊ እኩልነት ላይ ራሷን እንደ ገና ማዋቀር እንዲኖርባት እንደ አስገደዳት አይተናል።
ይኽ የሰብዓዊነት የክርስትና መልዕክት የአመጣው አዲስ ኹኔታ ግን ፤ ማለትም የቀደመውን ዓለም የአስተሳሰብ ስረዓት ማስረጀት እና አዲስ ዓይነት ዓለምን የማዋቀሪያ መንገድ አስፈላጊነት ማሳሰብ ግን ፤ የሰው ልጆች የፖለቲካ እውቀት በእዚኽ የሰብዓዊነት አስተሳሰብ ዳብሮ ፤ አዲስ ማሕበረሰብን የማወቀሪያ መንገድ እስኪ ቀምር ድረስ ፤ የቀደመውን ስረዓት አፍርሶ ፤ አዲስ የእሚተካውን ስረዓት ሰአያቀርብ ፤ ዓለምን በማሕበረ ኢከነሚያዊ ፍርሥራሽ ላይ የተወ ነበር ፤ ጅማሮው ላይ ።
በአጭሩ መጀመሪያ ላይ ፤ የክርስትና የወንድማማችነት መልዕክት ፤ ለፖለቲከኞች ፦ አሮጌውን ስረዓት አስረጅቶ እና ከመንገድ አስወግዶ ፤ አዲሱን ስረዓት ፈልጋችሁ አግኙት የእሚል የቤት ሥራ ሰጥቶ የተወ ነው የሆነው።
ከእዚኽም የተነሳ ፤ የክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑት እንደ ሮም እና አክሱም በአሉት ጥንታዊ ከተማዎች ውስጥ የእሚገኙት የቀደመው ፖለቲካዊ አስተሳሰባቸው በውስጣቸው የአረጀባቸው ፖለቲከኞች ፤ ፖለቲካ ራሱ ያስፈልጋል ወይ ከእሚለው ጥያቄ አንስቶ ወደ ፊት ምን ዓይነት ፖለቲካዊ ርዕዮት መከተል እንደ አለባቸው አለማወቅ በእሚፈጥርባቸው ግራ መጋባት ውስጥ ነበር ራሳቸውን የአገኙት።
ለምሳሌ ፦ በኋላ በእዚኽ ምዕራፍ ውስጥ ሕግ እና ሕገመንግሥታዊነት በኢትዮጲያ በእሚለው የምዕራፍ አራት የመጀመሪያው ንዑስ ክፍል ላይ እንደ እምናየው ፤ የሮማው ንጉሥ ቆስጠንጢን የክርስትና የፍቅር መልዕክት የቅጣትን በትር መጠቀም ግድ ከእሚለው የመንግሥት ስልጣን ጋር ይቃረናል ብሎ በማሰብ በንግሥና መቀጠል ተቸግሮ እንደ ነበር ይነግረናል ፦
“የሰማዕት ዘመን ከተፈፀመ በኋላ … ቆስጠንጢኖስን ንጉሥ በአደረጉት ጊዜ እርሱ እኔ መንግሥትን አልሻም አላቸው ። የክርስቶስ መንገድ እና የዓለም መንገድ ልዩ ነውና ። የክርስቶስ መንገድ እና የተረጋገጠች ትዕዛዙ ግን ፦ ጠላቶቻችሁን ውደዱ ፣ ለእሚቀሙዋችሁም በጎ አድርጉ … ይኽን እና የእሚመስለውን ትላለችና ። … ይኽን ትዕዛዝ እተው ዘንድ ፍርድንና ያለ ምሕረት በጊዜው ዕዳ መክፈልን አዝዝ ዘንድ ፣ ለተበደለውም ከበዳዩ መበቀልን አዝዝ ዘንድ እንዴት ይቻለኛል ? [95]”
በአክሱማዊያን ነገሥታት ታሪክ ፤ በሐገር ውስጥም ሆነ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ታዋቂነት የአለው ፤ የንጉሥ ታዜና ልጅ ንጉሥ ካሌብ ፤ ንግሥናውን በፈቃዱ ለቅቆ እና የንግሥና ዘውዱን በኢየሩሳሌም በቅዱሱ መቃብር[1] (Holy Sepulcher) ግድግዳ ላይ እንዲሰቀል ልኮ ፤ ገዳም እንደ ገባ ፤ በሐገር ውስጥ እና በውጭ ሐገር ታሪኮች እንደ ተዘገበ ፤ ሰርጌው ሐብለሥላሤ ይነግረናል ፦
“የካሌብን የንግሥና ፍጻሜ በተመለከተ ፤ የኢትዮጵያ እና የግሪክ የታሪክ መጽሐፍት ንጉሥ ካሌብ ዙፋኑን በገዛ ፈቃዱ ለቅቆ ወደ አባ ጴንጤሊዎን ገዳም ገብቶ እንደ መነነ በመተረክ አንድ ዓይነት (ተመሳሳይ) ዘገባ ይዘዋል። የንግሥና ዘውዱንም በቅዱሱ መቃብር ላይ እንዲንጠለጠል ወደ ኢየሩሳሌም ልኮታል።”
“Concerning the end of Caleb’s reign, Ethiopian and Greek sources agree that Caleb voluntarily abdicated the throne and entered monastic life in the hermitage of Abba Pentelewon, where he ended his days. He sent his crown to Jerusalem to be hung on the Holy Sepulcher. [96]”
በአጠቃላይም ፤ በክርስትና የሰብዓዊነት መልዕክት የጥንታዊው ስልጣኔ (The Classical Period Civilization) ከተናወጠ እና የክርስትና ዕምነት በዓለም ላይ ከአየለ በኋላ ፤ ፖለቲከኞች ራሳቸውን በዋናነት በእሚከተሉት ሦሥት የአስተሳሰብ ጭለማ ውስጥ የአገኙት ይመስላል ፦
የሐገራችን ብኺል እንደ እሚለው ግን “ብርሌ ከነቃ አይሆንም እቃ” ነውና ነገሩ ፤ ክርስትና አንድ ግዜ ፦ መስካሪ እና አስረጂ የእማይስፈልገውን (The Self-evident truth) የሰዎችን ሰብዓዊ እኩልነት እውነት አንድ ግዜ ወደ ሰዎች ግንዛቤ ከአመጣ በኋላ ፤ በእዚኽ መልዕክቱ ፤ ነባራዊውን ፖለቲካዊ ስረዓት የፈረሰባቸው የዘመኑ ፖለቲከኞች ከመናኝነት እስከ ቀዳማዊውን ኢሰብዓዊ ስረዓት ዳግም የመመለስ መንገድ ቢፈልጉም ፤ ከችግሩ መውጫው ብቸኛው መንገድ ብርሌውን ወደ እቶኑ መልሶ እንደ ገና በአዲስ እና የሰዎችን ሰብዓዊነት በአካተተ መልኩ መሥራት ብቸኛ አማራጭ በመሆኑ ፤ የክርስቲያኑ ዓለም ራሱን እንደ ገና በእዚኽ የሰብዓዊ እኩልነት ወይንም የሰብዓዊነት መርህ ፤ እንደ ገና እስኪያዋቅር ድርስ ከ1 ሺ ለእሚበልጡ አመታት በማሕበረ ኢከነሚ ቀውስ ውስጥ እንዲዳክር ግድ ሆኖበት ነበር።
ይኽም ፤ ሰዎች የፖለቲካዊ እውቀታቸው ዳብሮ ፤ የፖለቲካ ወይንም የማሕበረሰብ ሳይንስ በሰብዓዊነት አግባብ እንደ ገና ታሽቶ እስኪወጣ ፤ መላው የቀደመው የሰለጠነው እና ክርስትያን ዓለም ፤ በፈላስፎች ዘመነ ስኮላስቲዝም በታሪክ አጥኝዎች የጨለማው ዘመን የእሚባለው ውስጥ ለእሚቀጥለው አንድ ሺ ዓመታት እንዲ ዳክር አድርጎታል ።
ይኽ ኹኔታ ነው ታላቋን ሮም በ5ኛው ምዕተ ዓመት ላይ ወደ ፖለቲካዊ መደናበር ውስጥ አስገብቶ ፤ ከነበረችበት ከፍታ ላይ የጣላት ።
ድህረ ክርስትና ከተፈጠሩ ሦሥት የፖለቲካ ድንብርብር ጎራዎች በሦሥተኛነት የጠቀስነው ኹኔታ ፤ በክርስትና ምክንያት የተፈጠረው አጉል መንፈሳዊነትን መቃወሙ ትክክል ቢሆንም በአማራጭነት ይዞ የመጣው ወደ ቀደመው ቆፍጣና እና ኢሰብአዊ መንግሥት ከአልተመልስን በውድቀት ረመጥ ውስጥ እንነከራለን የእሚለው እምነት ህፀፁ አኹንም በአንድ አንድ ዘመናዊ ፖለቲከኞችም ዘንድ ይስተዋላል።
ይኽን አስተሳሰብ የዘመናዊ ፖለቲካ ሳይንስ አባት የእሚባለው የጣሊያኗ ፍሎረንስ ከተማ ፖለቲከኛ ፤ ኒኮል ማክያቬሊ (Nicole Machiavelli) በስፋት በማብራራት ይታወቃል። ከእዛም በኋላ ይኽ ዓይነቱ ጸረ ክርስትና አመለካከት እስከ አሁንም በአንዳንድ ሰዎች ፖለቲካዊ የህሊና ጓዳ (In the back of their political consciousness) ውስጥ ይስተዋላል።
ማክያቬሊ ፤ በሊቪ ታሪክ ላይ የቀረበ ሐተታ (Discourse on Livy) በእሚለው መጽሐፉ ላይ ፤ የክርስትና ፖለቲካዊ እንድምታ በኹለት ከፍሎ አስቀምጦታል።
እንደ ማክያቬሊ ፤ ቤተክርስቲያን ምንም እንኳን መንፈሳዊ ተቋም ብትሆንም ፤ እጅግ ተስፋፋታ ምድራዊውን መንግሥት ከሐላፊነቱ አንሳፋለች ፤ ማንሳፈፏ በራሷ ችግር ነው በአይባልም ፤ ከመሠረታዊ ባሕሪዋ የተነሳ የአንሳፈፈችውን የመንግሥት መዋቅር በአግባቡ መተካት በአለመቻሏ ከፍተኛ ክፍተት ፈጥራ ፤ ለጦር አበጋዝነት በር ከፍታለች።
ከእዚያኽም በአሻገር ፤ በተሳሳተ የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓገም ላይ የተመሠረተው አስተምህሮዋ ፤ ምድራዊ ሕይወትን የእሚያስንቅ እና ሰማያዊውን የእሚያስናፍቅ በመሆኑ ፤ ፖለቲካዊ ተነሳሽነት እና ተሳታፊነት በመግደል ፤ ፖለቲካዊ ማሕበረሰባትን ለሥራ ፈትነት እና ለዝብጠት ዳርጓል የእሚል ነው።
ማክያቬሊ እነ እዚኽን ኃሳቦቹን በእሚከተለው መልኩ አቅርቧቸዋል ፦
“ምንም እንኳን በእዚኽ ምድራዊ ኢምፓየር ውስጥ ብትገኝም እና ብትይዘውም (ቤተክርስቲያን) ፤ የኢምፓየር ፍጹማዊ ገዢ በመሆን የልዑሉን ቦታ ልትተካ የእሚያስችላት ጀግንነት ሊኖራት አልቻለም … ስለ እዚኽም ፤ ቤተ ክርስቲያን በራሷ መላ ጣሊያንን መቆጣጠር ስለ አልቻለች እና ሌላም እንዲቆጣጠራት ስለ እማትፈቅድ ፤ ጣሊያን በአንድ ገዢ (ራስ) ስር እንደ አትመጣ የእሚከለክል እንቅፋት በመሆን ፤ ይልቁንም በተለያዩ ልዑላን እና ገዢዎች ስር በመሆኗ ምክንያት በመከፋፈሏ ተደካማ ለአረማዊያን እና ሊያጠቃት ለእሚፈልግ ለማንም ተጋላጭ እንድትሆን አድርጓታል።”
“For although it has inhabited and held a termporal empire there, it has not been so powerful nor of such virtue as to be able to seize the tyranny of Italy and make itself prince of it.... Thus, since the church has not been powerful enough to be able to seize Italy, nor permitted another to seize it, it has been the cause that [Italy] has not been able to come under one head but has been under many princes and lords, from whom so much disunion and so much weakness have arisen that it has been led to be the prey not only of barbarian powers but of wohover assaults it. [97]”
ማክያቬሊ በእዚኹ መጽሐፍ ሌላ ስፍራ ላይ ፤ ከእላይ እንደ አልነው ፤ የክርስትና አስተምህሮ ፤ ከምድራዊ መንግሥት አስተሳሰብ ጋር የእማይጣጣም ነው ለማለት ይኽን ብሏል ፦
“ጥንታዊያኖቹ ሰዎች ከዛሬዎቹ ሰዎች ይልቅ የነጻነት አፍቃሪ እንዴት ሊሆኑ ቻሉ ብዬ ሳስብ ፤ ልዩነቱ ዛሬም ሰዎችን ደካማ ከእሚያደርጋቸው ፤ በእኛ እና በጥንታዊያኖቹ ኃይማኖት መካከል ከአለው ልዩነት የእሚመነጭ ይመስለኛል። የእኛ ኃይማኖት ፤ እውነቱን እና የእውነቱን መንገድ አሳይቶን ፤ የእዚኽን ዓለም ክብር ዝቅ አድርገን እንድንመለከተው አድርጎናል ፤ በተቃራኒው አህዛቦቹ ምድራዊውን ነገር እጅግ አክብረውት እና ሊሰጥ የእሚችለውን ትኩረት ኹሉ ስለ እሚሰጡት ፤ በተግባራቸው እጅግ ቆራጥ(ጨካኝ) ናቸው። ይኽንን ፤ በትህትና ስም ስውር ግብዝነት እየ አንጸባረቀ ተግባራዊ ቆራጥነት እና መነቃቃት ከእሚጎድለው እና በጣም ታላቅነት ከእሚታይበት የእነርሱ እና የእኛ የመስዕዋት ስረዓት ፤ ከእምናገኘው ልዩነት ጀምሮ ልናየው እንችላለን። በእነርሱ የመስዕዋት ስረዓት ውስጥ መወጣጠርም ሆነ ግብዝነት በብዛት ኖሮት ፤ በእዚኽም ላይ መስዕዋታቸው ፤ ከእሚሰውት እንስሳት ብዛት የተነሳ በደም እና በጭካኔ የተሞላ ነው። ይኽም ትዕይነት አስፈሪ በመሆኑ ተመልካቹንም እንደ እዛ ያደርገዋል። ከእዚኽ በተጨማሪ ፤ የጥንታዊያኖች ኃይማኖት ሰዎች የጦር አዝማች ወይንም የሕዝብ ገዢዎች ያልሆኑትን ፤ በሰማዕትነት አክብሮ አይዘክራቸውም።
የእኛ ኃይማኖት የእሚያከብራቸው ደግሞ ትሁት እና አሰላሳይ ዓይነት የሆኑትን ሰዎች ነው። ስለ እዚኽም ትልቁን ዋጋ ፤ በትህትና ፣ በድህነት እና ሰዋዊውን ነገር በመጠየፍ ላይ አድርጎታል ፤ ሌሎቹ ግን ትልቁን ዋጋ በመነቃቃት/በቅልጥፍና ፣ በአካላዊ ብርታት እና ሌሎች ማንኛውም ሰዎችን ጠንካራ በእሚያደርጉ ነገሮች ላይ አድርገዋል። የእኛ ኃይማኖት በራስህ ጥንካሬ እንዲኖርህ ከጠየቀህ ፤ አንድ የሆነ ጠንካራ የሆነ ነገር የእምታደርግበት ጥንካሬ እንዲኖርህ ሰአይሆን ብዙ መከራ መቋቋም የእሚችል ጥንካሬ እንዲኖርህ ነው የእሚጠይቅህ ።
ይኽን መሰሉ ህይወት ዓለምን ደካማ እየአደረገ ፤ ሕዝበ ጉባኤው መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ሲል በትሩን በበትር ከመመለስ ይልቅ በትሩን መቋቋም መምረጡን ሲያዩ ፤ ጠርንፈው ሊያስተዳድሩት ለእሚፈልጉት ወንጀለኛ ሰዎች ግዳይ አድርጎ አቅርቦታል። ምንም እንኳን ዓለም አልጫ (ፈሪ ) ቢሆንም ፤ ይኽ የሆነው ከሌላ ከምንም ሰአይሆን ከፈሪነታቸው የተነሳ ኃይማኖታችንን ከጀግንነት ይልቅ ሥራ ፈትነት በእሚያበረታታ መልኩ በተረጎሙት ሰዎች ነው[2]። ትንሽ ቢያስቡ እና ትርጓሜያቸውን በደንብ ቢያጤኑት እና አባት-ሐገራችንን (እናት ሐገራችንን) ከፍ ከፍ እንድ እናደርገው እና እንድ እንከላከለው እንደ እሚፈቅድልን ቢያስቡበት ኖሮ ፤ ሐገራችንን እንድ እንወድ ፣ እንድ እናከብር እና ሐገራችንን ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከል በእምንችለው መልኩ ኹሉ እንድ እንዘጋጅ ፤ ኃይማኖታችን እንደ እሚፈልግ ይረዱ ነበር። እነ እዚኽም ትምህርቶቻቸው እና የስህተት ትርጓሜያቸው በቀደመው ዓለም እንደ ነበሩት ዓይነት ብዙ ሕዝባዊ መንግሥታት እንደ አይኖሩ እና በጥንታዊው ሰዎች ዘንድ ይስተዋል የነበረው የነጻነት አፍቃሪነት እንደ አይኖር አድርጓል።
ነገሩ እንዲኽ ቢሆንም ፤ የሮማው ኢምፓየር ፤ በነበረው ጦር ታላቅነት ፤ እነ እዚኽን ኹሉ ሕዝባዊ መንግሥታት እና ማሕበራዊ የሕይወት ዘዬዎች በሙሉ አጥፍቷል ፤ ምንም እንኳን የሮማው ኢምፓየር በኼደበት የዓለም ክፍል ኹሉ በእዚኽ መልኩ ለነጻነታቸው አንገተ ደንዳና የሆኑ ሕዝባዊ ከተማዎች ቢገጥሙዋቸውም ። ምንም እንኳን ይኽን የአደረገው የሮማው ኢማፓየር ዛሬ ቢወድቅም ፤ እነ እዛኽ ሕዝባዊ መንግሥታት ፤ በኢምፓየሩ ጥቂት ቦታዎች ከአልሆነ በስተቀር ራሳቸውን እንደ ገና አዋቅረው ወደ ቀደመው የሕዝባዊነት ኹኔታቸው መመለስ አልቻሉም። ይኽም በጣም በአልተለመደ እና ጽንፍ የወጣ ጀግንነት ከአልሆነ በስተቀር ፤ ሮማዊያኖች ሊያሸንፉዋቸው እንደ እማይችሉ የነበረ እናያለን።”
“Thinking then whence it can arise that in those ancient times people were more lovers of freedom than in these, I believe it arises from the same cause that makes men less strong now, which I believe is the difference between our religion and the ancient. For our religion, having shown the truth and the true way, makes us esteem less the honor of the world, whereas the Gentiles, esteeming it very much and having placed the hightest good in it, were more ferocious in their actions. This can be inferred from many of their institutions, beginning from the magnificence of their sacrifices as against the humility of ours, where there is some pomp more delicate than magnificent but not ferocious or vigorous action. Neither pomp nor magnificence of ceremony was lacking there, but the action of the sacrifice, full of blood and ferocity, was added, with a multitude of animals being killed there. This sight, being terrible, rendered men similar to itself.
Besides this, the ancient religion did not beatify men if they were not full of worldly glory, as were captians of armies and princes of republics. Our religion has glorified humble and contemplative more than active men. It has then placed the highest good in humility, abjectness, and contempt of things of human; the other placed it in greatness of spirit, strength of body, and all other things capable of making men very strong. And if our religion asks that you have strength in yourself, it wishes you to be capable of more of suffering than of doing something strong.
This mode of life thus seems to have rendered the world weak and given it in prey to criminal men, who can manage it securely, seeing that the collectivity of men, so as to got to paradise, think more of enduring the beatings than of avenging them. And although the world appears to be made effeminate and heaven disarmed, its arises without doubt more from the cowardice of the men who have interpreted our religion according to idleness and not according to virtue. for if they considered how it permits us the exaltation and defense of the fatherland, they would see that it wishes us to love and honor it and to prepare ourselves to be such that we can defend it. These educations and false interpretations thus bring it about that not as many republics are seen in the world as were seen in antiquity; nor, as a consequence, is as much love of freedom seen in peoples as was then.
Still, I believe the cause of this to be rather than the Roman Empire, with its arms its greatness, eliminated all republics and all civil ways of life. And although that empire was dissolved, the cities still have not been able to put themselves back together or reorder themselves for civil life except in very few places of that empire. However that may be, in every least part of the world the Romans found a conspiracy of republics very armed and very obstinate in defense of their freedom. This shows that without a rare and exteme virtue the Roman people would never have been able to overcome them. [97]”
ማክያቬሊ ፤ በእዚኽ ክፍላ ላይ እያለ የአለው ፤ በአንድ በኩል ክርስትና ብትህውና በመስብክ አልጫ አድርጎናል ብሎ በሌላ በኩል ደግሞ የጥንታዊያኖቹ ሮማኖች የጦርነት ጀግንነት ፤ በምድራዊ ኃሳብ ተሞልተው ለነጻነታቸው እና ለክብራቸው የእሚጋደሉትን ጀግኖችም አምበርክኳል እያለ ነው።
ያው በእዚኽ ውስጥ ፤ አልጫ የአደረገንን የተሳሳተ የክርስትና ትርጓሜ ትተን ፤ በጀግንነት የቀደመችውን የሮማን ኃይልነት (ነጻነት ናፋቂ እና ጀግኖቹን እንኳን የእሚያበረክከውን) አዲስ ፖለቲካዊ ጨካኝነት እንመልሰው እያለ መሆኑ ግልጽ ነው።
ምንም እንኳን ማክያቬሊ የክርስትና እምነት ተከታይ ቢሆንም እና የራሱ የሆነ እና አንደ አንድ ኣንድ ኃያሲያን እምነት ወደ ክሀዲ አምላኪነት (Atheism) የእሚጠጋ የክርስትና እምነት የያዘ ቢሆንም (መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች በእግዚአብሔር መንፈስ ተመርተው እንደ ጻፉት የእሚጠራጠር ክርስቲያን ነው ይባላል) ፤ በፈጣሪ ለማመኑ እና ኃይማኖት በመላው መጥፎ ነው ብሎ ለአለማመኑ ምንም ጥርጥር የሌለው ቢሆንም ፤ የክርስቲያን መንግሥታት ለእንደ እዚኽ ዓይነት ትርምስ የተጋለጡት ፤ በተጨባጩ ዓለም ከአለው የፖለቲካ እውነታ ጋር የእማይጣጣም የክርስትና አስትምህሮ ወይንም የወንድማማችነት መልዕክት ስለ አላቸው ነው በእሚል ፤ ወደ ቀደመው እንደ ሮማዊዎች ዓይነት ታላቃነት እና ስልጣኔ መመለስ የእሚቻለው ፤ ሰብዓዊ የሆነውን የክርስትና መሠረት የአለውን አስተምሮ ከፖለቲካዊ ስረዓታችን በማውጣት እና ወደ ቀደመው “ቆራጡ” የእማያወላዳው አመራር በመመለስ ነው ብሎ ቢልም [12] ወይንም ማክያቬሊ እና ከእርሱ በፊትም ሆነ ከእርሱ በኋላ ፤ መንፈሳዊ ህይወት የእሚታረዱ በጎች ነው የአደረገን ብለው ፤ ጭካኔን ቢሰብኩም እና ስብከታቸውም ቀላል የእማይባል ተከታይ ቢያገኝም ፤ ድህረ ክርስትና አብረው እንደ መጡት ፤ መመነን እና የጥገና መንግሥታት ፤ የጭከናው መንግሥትም የፖለቲካዊ ድንብርብር ውጤት በመሆኑ ፤ ዓለም በተለይም የክርስቲያኑ ዓለም እንደ ገና በሰብዓዊ የክርስትና መልዕክት አግባብ ራሱን እንደ ገና እስኪያዋቅር ወይንም ይኽን ማሕበረሰብ ማዋቀሪያ መንገድ እስኪያገኝ ፤ የስረዓት ውድቀት ከአስከተለው ፖለቲካዊ የጭለማ ድንብርብር ውስጥ ሊወጣ አልቻለም።
ይኽም በመሆኑ ፤ የአክሱም ውድቀት ምንጩ ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ፤ ድህረ ክርስትና በቀደመው ዓለም የነበሩ የክርስቲያን ስልጣኔዎች ፤ የገቡበት ፖለቲካዊ ግራ መጋባት የወለደው ውድቀት አካል ነው የእሚለው መላምት ነው የበለጠ ወደ እውነቱ የቀረበው ፤ በእኔ እምነት ።
ለእዚኽም ፤ የአክሱም መንግሥት ይኽ ነው የእሚባል ፤ የውጭ በአላንጣ ሰአይመጣባት ከግዜ ወደ ግዜ ፤ ከነባራዊው ልምዱ በአፈነገጠ መልኩ ፤ በገባበት ፖለቲካዊ መደናበር ፦ በመንግሥታዊ ሥራ ፈትነት እና ፍርደ ገምድልነት ፤ ከውስጥ እየተፈረካከሰ ፤ ለውድቀት እንደ ተዳረገ ፤ የእሚከተሉት ታሪካዊ ክስተቶች የእሚያሳዩን ይመስለኛል ፦
ይኽም ማለት ፦ ለአክሱም ውድቀት ምክንያቱ ፤ እንደ ሌላው ክርስቲያናዊ ስልጣኔ ፤ የዜጎችን ሰብዓዊ እኩልነትን የእሚቀበለው የሕዝባዊ ፖለቲካ ባለ መዳበሩ ምክንያት ፤ የክርስትና እምነት የፈጠረው ፖለቲካዊ መደናበር ውጤት ነው።
የመጀመሪያውን ክስተት ስንመለከት ፤ የደቡብ አረብያው የአክሱም ወኪል ወይንም ክልላዊ መንግሥት በፐርዥያ በወታድራዊ ኃይል ተሸንፎ እንዲወገድ የአደረገው ፤ በመጀመሪያ በእዛ የቀረው የአክሱም ኃይል ፤ በጎጥ አመፅ ራሱን ከአክሱም መንግሥት ነጥሎ እና ለአክሱም ግብር በመገበር ብቻ ለመወሰን በመፈለጉ እና ይኽንንም አንፃራዊ ነፃነቱን ከአገኘ በኋላ ፤ በስልጣን ላይ በቆየባቸው ወደ ኃምሳ ለእሚጠጉ ዓመታት ፤ በአስተዳደራዊ በደል የአከባቢውን ነዋሪ በማስመረሩ ነው ።
በደቡብ አረቢያ የነበረው የአክሱም ወኪል መንግሥት ወይንም ክላላዊ አስተዳደር ፤ ይኽን መሰሉ ፥ የተደራጀ እምቢተኝነት በማዘዣ መዓከሉ ላይ ለማሳየት መነሳቱ ደግሞ ፤ እንዲኹ ድንገት የእሚመጣ ሰአይሆን ፤ ከእላይ በገለጽነው አግባብ ፤ መዓከላዊ መንግሥቱ ስርዓታዊ መደናበር ውስጥ ከመግባቱ እና በእዚኽም በመዳከሙ የእሚመጣ ነው።
በእርግጥ አንዳንድ ግዜ ፤ ዋናው እና ትልቁ መንግሥት ወደ ጨቋኝነት ሲለወጥ ፤ ጎጥ ትክክለኛ እና ፍትኃዊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሊሆን ቢችልም ፤ እነ አብረኃ በደቡብ አረብያ የጀመሩት ጎጥ ግን ፤ በማን አለብኝነት እና ከዘራፊነት ስነ ልቦና የመነጨ ፤ ተራ አመፅ እና እምቢተኝነት እንጂ ፍትኃዊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አይመስልም ነበር ።
ስለ ኹኔታው የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረን ፤ የአብረኃ ስርወ መንግሥት የፖለቲካ ስልጣኑን ከያዘበት ጀምሮ ፤ በአከባቢው ነዋሪዎች ጋባዥነት ፤ በፐርዢያ የጦር መሪዎች እገዛ በኃይል ከመወገዱ በፊት ፤ በነበረው ወደ 50 ዓመት ለእሚጠጋ ዓመታት ፤ የነበረውን ኹኔታ እንይ ።
በዛሬዋ የመን ፤ በእዚኽ ወቅት የነበረውን የአብረኃን ስርወ መንግሥት ፤ በ6ኛው ምዕተ ዓመት ወደ ደቡብ አረቢያ የስልጣን መንበር ላይ እንዲመጣ ምክንያት የሆነው ፤ በንጉሥ ካሌብ ዘመን በስልጣን ላይ የነበረው እና ለአክሱም ተጠሪ የነበረው የአከባቢው ንጉሥ ፤ ክርስቲያን ስለ አልነበረ ፤ በደቡብ አረቢያ (የመን እና አከባቢያዋ) የእሚገኙ ክርስቲያኖች እና ከእዚኽ ከአክሱም የኼዱ ነዋሪዎች ላይ መከራ እና ስደት ማስነሳቱ ፤ ንጉሠ ነግስት ካሌብን በሕምያሩ ንጉሥ ላይ እንዲዘምት ስለ አደረገው ነው ።
በአንድ ወገን የአሉ፟ት የወቅቱ ታሪክ ተራኪዎች ፤ ይኽ በክርስቲያኖች ላይ የደረሰው ስደት አስቆጥቶዋቸው ፤ ንጉሥ ካሌብን በእዚኽ ጨካኝ የሕይመር ንጉሥ ላይ እንዲ ዘምትበት የጠየቁት የአሌክሳንደሪያው ጳጳስ እና የሮማው የወቅቱ ኢመፐረር ናቸው የእሚሉ የአሉ፟ ሲኖሩ ፤ በሌላ ወገን ደግሞ አይ ካሌብም ይኽን በክርስቲያኖች እና በአክሱማዊያን የአከባቢው ነዋሪዎች ላይ ይደርስ የነበረውን ስደት በራሱ ግዜ ሰምቶ ስለ ነበር እና ክርስቲያኖቹን መታደግ አለብኝ ብሎ ስለ አሰበ ፤ በራሱ ተነሳሽነት ነው የዘመተው ይላሉ ።
ብቻ ከኹለት በአንዱ ምክንያት ፤ ንጉሥ ካሌብ ፥ ይኽንን ክፉ የእሚያደርገውን የደቡብ አረቢያ ንጉሥ ለመቅጣት ፤ ወደ እዚያኽ በመዝመት ፤ በዳዩን ንጉሥ ከስልጣኑ አውርዶ በቦታው ሌላ የእዛው የአከባቢውን ተወላጅ ንጉሥ አድርጎ ሾሞ ዘመቻውን ያጠናቅቃል ፦
“በእርሱም ቦታ ፤ የሕመራዊያን ተወላጅ የሆነ ፥ ስሙ እስሚፋውስ የእሚባል ፤ ክርስቲያን የሆነ ንጉሥ ከአስቀመጠ በኋላ (አፄ ካሌብ ማለት ነው) ፤ በየዓመቱ ለኢትዮጵያ ግብር እንዲከፍል አሳስቦት ወደ ሐገሩ ተመለሰ።”
“He (Emperor Caleb) then set up in his stead a Christian king, a Homerite by birth, by name Esimiphaeus, and after ordaining that he should pay a tribute to the Ethiopian every year, he returned to his home. [96]“
ነገር ግን ዘመቻው በእዚኽ መልኩ በድል ከተጠናቀቀ በኋላ ፤ ይዞት ከዘመተው ጦር የተወሰነው ኃይል አባላት ፤ ወደ ሐገራቸው ከንጉሡ ጋር ከመመለስ ይልቅ ፤ የእዚያኽን ሐገር አዲስ ተሿሚ ንጉሥ እያገለገሉ በእዛኽ ለመቅረት ይወስናሉ ።
ፕሮኮፕየስ የተባለው ሮማዊ ታሪክ ጸሐፊ ፤ አንኼድም ብለው የቀሩት ባሮች እና የወንጀል ዝንባሌ የአላቸው ፤ ደቡብ አረብያን ለራሳቸው ማድረግ የፈለጉ አፈንጋጭ የንግሱ ካሌብ ጦር ሠራዊት አባላት ናቸው ይላል ፦
“በኢትዮጵያ ሠራዊት ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ባሮች እና የወንጀል ዝንባሌ የነበራቸው ንጉሡን ተከትለው ለመመለስ በፍፁም ፈቃደኞች አልነበሩም ፤ ምክንያቱም ፦ እጅግ በጣም መልካም ስለ ነበረች የህመራይቶችን መሬት ለራሳቸው ማድረግ ፈልገው የነበረ በመሆኑ ።”
“In this Ethiopian army many slaves and all who were readily disposed to crime were quite unwilling to follow the king back, but were left behind and remained there because of their desire fir the land of the Homerite; for it is an extremely good land. [94]“
በእርግጥ ይኽ በእዚያኽ የቀረው የንጉሥ ካሌብ የጦር ክፍል ፤ በእምቢተኝነት በእዚያኽ ይቅር የእሚል እና የለም ከመጀመሪያውም ንጉሥ ካሌብ በእዚያኽ እንዲቆዩ ስለ ፈለገ በእዛኽ እንዲቆዩ ስለ አደረጋቸው ነው በእዚያኽ የቀሩት የእሚል የተለያየ ታሪካዊ ዘገባ አለ ። ለምሳሌ ፦ እንደ ሰርጌው ሐብለሥላሤ አምፀው አንመለስም ብለው ሰአይሆን ንጉሥ ካሌብ ራሱ አዲሱን ተሿሚ ንጉሥ እንዲያግዙ ፈልጎ በእዚያኽ ትቶዋቸው ነው ይላል ።
እነ እዚኽ ሰዎች እዚያኽ ከቆዩ በኋላ የአደረጉት ድርጊት ግን ፤ የአክሱሙን መንግሥት ሕግ እና ስረዓት ለማስከበር የአለውን ፈቃድ እና ዝግጁነት የተፈታተነ ሆኖ ነበር ።
እነ እዚኽ ሰዎች ፤ ንጉሥ ካሌብ በእዛኽ ትቶዋቸው በተመለሰ በጥቂት ግዜ ውስጥ ፤ ንጉሥ ካሌብ የሾመውን የሐገሬውን ንጉሥ ከስልጣን አውረደው በማሰር ፤ ከመካከላቸው አብረኃ የእሚባለውን ኢትዮጵያዊ አንግሰው የየመኑን መንግሥት ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠራሉ ።
ይኽ የአስቆጣው ንጉሥ ካሌብ ፤ አማፂያኖቹን አደብ ለማስያዝ ኹለት ግዜ ጦር ቢልክባቸውም ፤ በተከታታይ የላከው ጦር ስለ ተሸነፈ እና አዝማቾቹም ስለ ተገደሉ ፤ በሦሥተኛ ንጉሡ ራሱ ሊዘምት ዝግጅት ሲያደርግ ፤ አደጋ ውስጥ እንደ ገባ የተረዳው አብረኃ ፤ እኔ በአንተ ላይ አላመፅኹም ፤ ብቻ ግብር እየገበርኹ በንግሥናው ልቀጥል በእሚል ይቅርታ በመጠይቁ ፤ ንጉሡ ይቅርታውን እና ግብሩን ተቀብሎ ፤ አብረኃ እንዲቀጥል ይስማማል ።
አብረኃም በየመን ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ፤ መናገሻውን ሰንዓ ከተማ በማድረግ ፤ ሰንዓ ውስጥ ትልቅ ቤተክርስቲያን ገንብቶ ፤ የተለያዩ የደቡብ አረቢያ ነገዶች ወደ ሰነዓ እንዲ መጡ እና ሰነዓ የአከባቢው ዋና ከተማ እንድ እትሆን መወትወት ይጀምራል ።
ይኽ የአብረኃ ውትወታ ግን ፤ የክርስትና ኃይማኖትን ለማስፋፋት ከአለው ኃይማኖታዊ ቅናት ብቻ የመነጨ አይመስልም ።
ምክንያቱም ፦ ጠቅላላ የአመራር ዘዬው ሲታይ ፥ ኃይማኖታዊ ዝንባሌ የአለው ሰው የእሚያደርጋቸው አይመስሉም ።
በአክሱማዊያን ነገሥታት የተለመደውን እና ፍትኃዊ የሆነውን የእየ አከባቢው ተወላጅ የሆኑ ሰዎች አከባቢያቸውን እንዲ ያስተዳድሩ የማደረጉን አካኼድ በመተው እና ያለ ምንም በቂ ምክንያት ከራሱ ከንጉሥ ትዕዛዝ እና ፈቃድ ውጪ (በአመፅ) ፤ ንጉሥ የሾመውን የአከባቢው ንጉሥ አውርዶ በማሰር ፤ በኃይል እና ከፍትኽ አግባብ ውጭ ራሱን የአከባቢው ንጉሥ ከማድረጉ በአሻገር ፣ በእዚኽ መልክ ወደ ስልጣን ከመጣም በኋላ ፤ ለወታደሮቹ የነዋሪውን ሚስቶች እንዲ ደፍሩ መፍቀዱ ፣ ከእርሱም በኋላ ኹለት ልጆቹ ፥ የአክሱም እና መስሩክ ፤ ተመሳሳይ አንዳንዴም ከአባታቸው የባሰ በደሎች በመፈጸም ፤ የሐገሬውን ሕዝብ ከማስመረራቸው የተነሳ የነዋሪው እሮሮ እስከ ፐርዥያ መድረሱ ፤ አንድ ጥሩ የእሚባል የወቅቱ ክርስቲያን ሐይማኖተኛ ነጋሢ የእሚያሳየው ባሕሪ አይደለም ።
እነዚኽም ባሕሪያቱ እንኳን ጥሩ ኃይማኖተኛ ፤ ታማኝ እና ፍትሕን ለማገዝ በእዛ የቀሩ ክፈለ ጦር አዛዥ ስለ እማያስመስለው ፤ አብረኃ እና ግብረ አበሮቹ የፖለቲካ ስልጣን ባላጊዎች እንጂ የኃይማኖት ቀናዕያን አልነበሩም ፤ የእሚለውን ግምት ይበልጥ ያጠናክሩታል ።
በእዚኽ መልክ የአብረኃ መንግሥት ራሱን በሕዝቡ ላይ ሾሞ ፤ የእሚያደርሰው በደል ነዋሪዎቹን ሲያስመርር ፤ በሌላ በኩል ደግሞ አዲስ እና ትልቅ ቤተክርስቲያን ገንብቶ ፤ ሰነዓን የደቡብ አረቢያ ፖለቲካዊ እና ኃይማኖታዊ መዓከል ለማድረግ መፈለጉ ፤ እውነተኛው የዓምልኮ መዓከል የእኛ ነው ከእሚሉት የመካ ነዎሪዎች ጋር አጋጨው ።
በአብረኃ የተቆጡት የመካ ነዋሪዎች ፤ የሰራውን ቤተክርስቲያን በእዳሪ ስላረከሱበት ፤ ኹኔታው መካ ከእሚኖሩት እና ካባ የእሚባለውን ቦታ ቅዱስ አድረገው ከእሚያዩት ቁሬሾች ጋር ግጭት ውስጥ ያስገባዋል ።
ንጉሥ አብረኃም ፤ የሰራኹትን ቤተ ክርስቲያን ያረከሱትን ሰዎች ለመቅጣትም ሆነ ወደ ፊት ሰነዓን የክርስትና መዓከል ለማድረግ መፍትኼው ኼዶ ካባን ማፍረስ እና የአከባቢው ሕዝብ ተቀናቃኝ የዓምልኮ መዓከል እንዳይኖረው ማድረግ መፍትኼ ይሆናል ብሎ በማሰብ ፤ ወደ ስምንት የእሚጠጉ ዝሆኖች (ካባውን በዝሆኖች ለመጎተት ይመስላል) ይዞ የመካ ቁሬሾች ላይ ይዘምታል ።
ንጉሥ አብረኃ ፤ መካ እስኪ ደርስ ፤ በመንገድ የገጠመውን ጦርነት ኹሉ አሸንፎ ፤ ወደ ከተማዋ ደጅ ከደረሰ በኋላ ፤ ለነዎሪዎቹ ፥ እኔ የመጣኹት እናንተን ልወጋ ሰአይሆን በእዚኽ የእሚመለከውን የጣዖት ዓምልኮ ለማስቆም እና ይኽንን ካብ ለማፍረስ ነው ፤ ስለ እዚኽ ፦ እናንተን አልነካም ፤ ካባውን ላፍርሰው? ይላቸዋል ።
በእዚያኽ ከእሚኖሩ የሐገሬው ሽማግሌዎች አንዱ የኾኑት አብዱል አል ሙጣሊብ (የነብዩ መሐመድ አያት) ፤ በጉዳዩ ላይ ከአብረኃ ጋር ለመደራደር በመጡበት ወቅት ፤ ከታች የአለውን የእሚስብ ታሪካዊ ምልልስ (Conversation) ያደርጋሉ። ይኽንን ምልልስ ሰርጌው ሐብለ ሥላሴ እንደ እዚኽ ዘግቦታል ፦
“አብዱል አል ሙጣሊብ ይመልሳሉ ፡ ‘እግዚአብሔር ፊት እንላለን ፥ እኛ ጦርነት አንፈልግም ፥ አቅሙ የለንምና ። ይኽ የእግዚአብሔር ቅዱስ ቤት ነው ፥ የወዳጁ የአብረሐም ቤት ነው ፤ ቤቱን እና መቅደሱን መጠበቅ የእርሱ ሥራ ነው ፤ እርሱ ከተወው ፥ እኛ ልንጠብቀው አንችልም ።’ ከእዚኽ በኋላ ፥ በመልዕክተኛ እየተመሩ ኢትዮጵያዊያኖች ወደ ሰፈሩበት መጥተው በንጉሡ ፊት ይቆማሉ ። አብረኃም ምን እንደ ፈለጉ ይጠይቃቸዋል ። አብዱ አል ሙጣሊብም በመመለስ ‘ንጉሡ የወሰደብኝን 200 ግመሎች እንዲ መልስልኝ እፈልጋለሁ ።’ ይላሉ ፤ አብረኃም በአስተርጓሚው በኩል እንዲኽ ይላል ፦ ‘ገና ሳይኽ ወድጄህ ነበር ፤ አሁን ግን መናገር ጀመርኽ እና ርካሽ ሰው መሆንህን አየሁ ፥ አንተና እና አባቶችህ የእምታከብሩትን መቅደስ ላፈርስ መጥቻለሁ ስልህ ፤ ስለ እርሱ ከማውራት ይልቅ የተወሰደብኝ 200 ግመል ይመለስልኝ ትላለህ ?’ አብዱ አል ሙጣሊብም መልሰው ‘ግመሎቹ የእኔ ናቸው ፥ መቅድሱ ግን የእሚከላከለው የራሱ በአለቤት አለው’ ፤ አብረሐም ጮኽ ብሎ ‘ከእኔ ግን ሊከላከለው አይችልም’ አለ ። እርሳቸውም መልሰው ‘ያ የአንተ ጉዳይ ነው ፤ አኹን ለእኔ ግመሎቼን መልስልኝ ።’ አብዱ አል ሙጣሊብ ግመሎቻቸውን አስመልሰው ወደ ቁሬሾች ተመለሱ ።”
“Abdul al-Muttalib replied: “By God, we seek not war, for which we are unable. This is God’s holy house, and the house of Abraham his friend; it is for Him to protect His house and Sanctuary; if he abandons it, we cannot defend it.” Then Abdu al-Muttalib was led by the envoy to Ethiopian camp and stood before the king. Abreha asked him what he wanted. Abdu al-Muttalib replied: “ I want the king to restore to me 200 camels of mine which he has taken away”, Abreha said to the interpreter: “ Tell me: You pleased me when I first saw you, but now that you spoken to me, I hold you cheap. What do you speak to me of 200 camels which I have taken and omit to speak about the temple venerated by you and your fathers which I have come to destroy?”. Then said Abdu al-Muttalib: “The camels are mine, but the temple belongs to another, who will defend it”. When Abraha Exclaimed, “He cannot defend it from me”, he replied: “That is your affair; only give me back my camels”. Having recovered his camels, Abdu al-Muttalib returned to Quraish. [96]“
በእዚኽ መልኩ ፥ የአብረኃ ጦር በመካ ደጅ ሰፍሮ በእሚደራደርበት ወቅት ፤ እንደ ሰርጌው ሐብለሥላሤ ፥ በጦሩ መሐከል ፦ ኩፍኝ መሰል ወረርሽኝ በመነሳቱ ፤ አብረኃ ካባውን ሳያፈርስ ወደ ሰነዓ ተመልሷል ። ይኽ ክስተት ፥ በቁርዓን ምዕራፍ 105 ወይንም የዝኆን (አብረኃ ካብውን ለማፍረስ ይዞ የመጣቸውን ዝሆኖች አመልካች ይሆናል ) ምዕራፍ ላይ ፤ የካባው ጠባቂ ዓምላክ ካባውን ሊያፈርሱ በመጡ ሰዎች ላይ በሽታ የእሚያመጣ ጠጠሮች የእሚያንጠባጥቡ ወፎች አምጥቶ በወረርሽኝ አቃጥሎዋቸዋል በእሚል ተዘግቦ ይገኛል ፦
(የዝኆን ምዕራፍ)
“በዝሆኑ ባለቤቶች፣ ጌታህ እንዴት እንደ እሚሠራ አላወቅህምን? ተንኮላቸውን በጥፋት ውስጥ (ከንቱ) አላደረገምን? (አድርጓል)።በነሱም ላይ መንጎች የኾነችን፤ (አዕዋፍ)። በነሱም ላይ መንጎች የኾነችን፤ (አዕዋፍ)።ቅጠሉ እንደተበላ አዝመራም አደረጋቸው።”
ከእዚኽ ፥ አብረኃ ካባን ለማፍረስ ያልተሳካ ዘመቻ ጋር አብሮ የእሚነገረው ንግርት ፥ አህሙዴ የተባለው የአብረኃ ዝሆን ፥ ወደ ካባ አቅጣጫ በእሚነዳበት ግዜ ፤ አልኼድም ብሎ ይቀመጥ ነበር የእሚል ነው ። ሙስሊሞች ፤ የዝሆን ዓመት የእሚሉት እና የእስልምና ቀን አቆጣጠር የእሚጀምርበት ፤ ከአብረኃ ዝሆኖች አንዱ ፤ አህሙዴ ወደ ካባው አልኼድም ብሎ ተኛ ተብሎ የእሚነገርበት ይኽ ዓመት ነው ። አንዳንድ ሰዎች ነብዩ መሐመድም በእዚኽ ዓመት እንደ ተወለዱ ያምናሉ ፤ ማለትም 570 ዓመታት ከክርስቶስ ልደት በኋላ ።
አብረኃ በእዚኽ መልኩ ፤ በሰነዓ ከቆየ በኋላ ፤ ከእርሱ በኋላ ፥ የአክሱም እና መስሩክ የእሚባሉት ልጆቹ ተከታትለው ነግሰዋል ።
ይኽ የንግሥናቸው ዘመን ግን ፤ የአከባቢው ሕዝብ ብዙ በደል የደረሰበት ወቅት ስለ ነበር ፤ የአከባቢው ነዋሪዎች የፐርዥያ ንጉሥ ፤ ከጨካኞቹ የሐበሻ ነገሥታት እንዲያድናቸው ደጋግመው ልመና አቀረቡ ።
የፐርዥያው ንጉሥ ፤ እኔ ባሕር ተሻግሬ እምዘምትበት ምንም ምክንያት የለም በእሚል ፤ ደጋግሞ የእገዛውን ልመና በቸልታ ቢያልፈውም ፤ የአብረኃ እና የልጆቹ በደል ያንገፈገፋቸው የየመኒዎች ውትወታ ፤ የፐርዢያው ንጉሥ አማካሪዎችን ፤ ንጉሡን በአመጽ በእስር ላይ የእሚገኙ ወታደሮቹን ቢልክ ምንም እንደ እማይጎዳ እንዲ መክሩት አድርጎ ፤ በፐርዥያ ንጉሥ ላይ አምጸው በእስር ቤት የነበሩ ወታደሮቹን ፤ በእዚኽ የየመንን ሕዝብ ከአብረኃ ስረወ መንግሥት ነጻ ለማውጣት በእሚደረገው ጦርነት ላይ የእሚሳተፉ ከሆነ ከፍርዳቸው ነጻ እንደ እሚሆኑ በመንገር ፈቃደኛ የሆኑትን የፐርዢያ ንጉሥ ወታደሮች በመስሩክ ላይ አዝምቶ ፤ መስሩክን አሸንፈው ።
የፐርዥያም ጦርም ፤ ከድሉ በኋላ ፤ በእዛያኽ ከነበሩት ኢትዮጵያዊ ወታደሮች አብዛኞቹን በመግደል ፤ ከእዚያኽ አከባቢ የኢትዮጵያን ኃይል በቋሚነት በማስወጣት ራሳቸውን በገዢነት ተኩ።
የአክሱሙ መንግሥትም ፤ ምናልባት ፥ አብረኃ እና ከእርሱም በኋላ ልጆቹ ፤ እያሳዩ በመጡት እምቢተኝነት ምክንያት ፤ ምንም ዓይነት እገዛ ሊያድርግላቸው እንደ እማይፈልግ መገመት እንችላለን ።
ስለ እዚኽ ፦ በጉዳዩ ላይ ሊቀርብ የእሚገባው ትክክለኛ ትንታኔ የእሚመስለው ለኹለት ምዕት ዓመታት እና ከእዚያኽ በላይ ፤ ‘በመልካም’ አስተዳደራዊ ግንኙነት ከኢትዮጵያ ጋር የነበረው ደቡብ አረቢያ ፤ በፐርዥያኖች ውጊያ ከኢትዮጵያ ጋር የአለው የግንኙነት ገመድ በመበጠሱ ኢትዮጵያ ሞራላዊ ውድቀት ደረሶባት ሰአይሆን ፤ የዘመኑ ፖለቲካዊ ድንብርብር ያስከተለው ሐገራዊ አስተዳደራዊ ድክመት ፤ የእማይሆኑ ሰዎች የፖለቲካ ስልጣናቸውን ለአጉል ተግባር ሲጠቀሙበት አይቶ ማረም እንዳይችል ማድረጉ ስለ እሚታይ የአክሱም መንግሥት ከውስጥ እየተዳከመ እንደ ነበር ያሳየናል ።
ለአክሱም መክሰም መጀመር ምክንያት ከሆነ መሆን የአለበት ይኽን አዲስ ባዕድ ፖለቲካዊ አካኼድ የጀመረበት ፖለቲካዊ መደናበር እንጂ ፤ በእዚኽ ኢፍትኃዊ አካኼድ የተመረረው ሕዝብ እሮሮ የጋበዘው የፕርዥያ ኃይል መሆን የለበትም ።
ጥፋተኛም ቢሆኑ መሸነፍ የሞራል ውድቀት የማስከተሉ ጉዳይ የእማይቀር ቢሆንም ፤ ከእዚኽ ሩቅ ምክንያት ይልቅ ፦ እድሜ ጠገቡ እና ብዙ የፖለቲካ ልምድ የአለው የአክሱሙ ስረወ መንግሥት ፤ ይኽን መሰል የተደራጀ እና የቆየ አመጽ መታገሱ እና እነ እዚኽም አመጸኞች ፍትኃዊ አማጽያን ሳይሆኑ ፤ በወታደር ኃይል ጥቅም እና ዝና ፈላጊዎች መሆናቸው ፤ ለአክሱም መንግሥት መወደቅ የቅርብ ምክንያቱ ስረዓቱ ከውስጥ መዝበጥ እና መበስበስ መጀመሩ መሆን አለበት።
ኹለተኛው ፤ የአክሱም መንግሥትን ለገባበት ፖለቲካዊ መደናበር ማሳያነት ሊሆን የእሚችለው ታሪካዊ ክስተት ፤ ምናሴ እና ቪክቶር የእሚባሉ ኹለት ፥ ከሶርያ የመጡ አታላዮች ፤ በአክሱም መንግሥት ብሎም በቤተክርስቲያን ላይ የፈፀሙት አሳፋሪ ማታለል ነው ።
የእነዚኽ ኹለት አጭበርባሪ ‘መኖክሴዎች’ ታሪክ ፤ በ10ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ እንደ ሆነ ነው የታሪክ መጽሐፍቶቹ የእሚሉት ። ታሪካቸውም ፤ በኢትዮጵያ ስንክሳር ፥ በመጋቢት ሦሥት ቀን ተጽፎ የእሚገኝ ሲሆን ፤ ሰርጌው ሐብለ ሥላሴ ፥ ክርስቲያን የሆነው የግብፁን ሲቨረስ አል ሙቃፋ የተባለውን የግብፅ ታሪክ ጸሐፊም ፤ በእዚኽ ታሪክ ላይ ማስረጃ አድርጎ ያቀርበዋል ።
ታሪኩ በአጭሩ ፤ በእዚኽ ዘመን ላይ የነበረ የኢትዮጵያ ንጉሥ ወደ ሞት ሲቃረብ ፤ በወቅቱ ሊቀ ጳጳስ የነበሩትን አባ ጴጥሮስን ጠርቷቸው ፤ ዘውዱን ይሰጣቸው እና እኔ ከአለፍኩ በኋላ ፤ እርሶ የክርስቶስ ተወካይ ስለ ሆኑ ፤ ታላቅ እና ታናሽ ከኾኑት ከኹለቱ ልጆቼ ፤ የተገባውን ልጅ መርጠው ያንግሱ ብሎ አደራ ይሰጣቸዋል ፦
“… ንጉሡም ጳጳሱን አስጠርቶ ፤ የመንግሥቱን ዘውድ እና ኹለቱን ልጆቹን ከሰጣቸው በኋላ እንዲኽ አላቸው ፦ ‘እርሶ ፥ የታላቁ እግዚአብሔር ፥ የንጉሡ የክርስቶስ የምድር ኹሉ ስልጣን ኹሉ የሆነበት ፤ የእርሱ ምድራዊ ወኪል ኖትና ፤ መንግሥቴን እና ኹለቱ ልጆቼን አደራ ሰጥቼዎታለሁ ፤ የጌታን ፈቃድ እንዲያስተምሯቸው እና ከኹለት አንዱን የእሚገባው ቢኖር ፥ የዋኃት እና መልካም የሆነውን ዘውዱን ይጫኑበት ።”
“,... he(the king) summoned the meteopolitan (mutran) and delivered to him the crown of the kingdom and his two sons and said to him :’Thou art the vicar of the King Christ, the Great God, by whose authority are all the kingdoms of the world. Behold, I have delivered to thee my kingdom and my two sons, and I have committed them into thy hands so that though mayest direct them by the will of the Lord, and upon one of them whom thou shalt judge to be worthy, gentle and good, place the crown of the kingdom’. [96]“
በእዚኽ መልኩ ከንጉሡ አደራ የተቀበሉት ጳጳስም ፥ ከመኳንንቱ ጋር ከተማከሩ በኋላ የንጉሡን ታናሹ ልጅ ያነግሳሉ ።
ከእዚኽ በኋላ ፤ ምናሴ እና ቪክቶር የእሚባሉ ፤ ኹለት መነኮሳት ነን የእሚሉ ወስላቶች ፤ ከአሌክሳንደርያው ጳጳስ ደብዳቤ ይዘን መጥተናል ብለው ፤ አኹን ያሉት ጳጳስ ማለትም አባ ጴጥሮስ ፥ ኃሰተኛ እንደ ሆኑ እና ያለ አግባብ ታናሹን እንደ አነገሡት እና በእዚኽም የአሌክሳንድሪያው ጳጳስ እንደ አዘኑ የእሚያሳይ ደብዳቤ አምጥተው ለመኳንንቱ ያቀርባሉ ።
አታላይ ‘መነኩሴዎቹ’ ለምን እንደ መጡ የተለያየ ነገር ቢባልም ፤ ለምሳሌ ፦ ታላቅ ሆኖ ሳለ ታናሹ ንጉሥ በመድረጉ የተቆጣው ታላቅ ወንድም ፤ ለእዚኽ ምክንያት ናቸው የአላቸውን አባ ጴጥሮስ ከመንገድ በማስወጣት እርሱ ስልጣኑን ከታናሽ ወንድሙ መቀማት ስለ ፈለገ ፤ በስውር ቀጥሮዋቸው ነው ይባላል ፤ ዋናው ግን ፦ በወቅቱ የነበሩት ፤ ባለ ስልጣናት በእነዚኽ አሳቾች የመጣውን ደብዳቤ እንደ እውነተኛ ወስደው ፥ ሊቀ ጳጳስ ጴጥሮስን እና የነገሠውን ታናሽ ወንድም ወደ ግዞት ወስደው ፤ ታላቅየውን ንጉሥ ፣ አጭበርባሪዎቹን ምናሴን እና ቪክቶርን ፤ ሊቀ ጳጳስ እና አጋዥ አድርገው በቅደም ተከተል ይሾማሉ ። ከእዚኽ በኋላ ግን የምናሴ ረዳት ቪክቶር ከሚናስ ጋር ተጣልቶ ፤ የአለውን ዘርፎት ስለጠፋ ፤ ሚናስ ይቀራል ።
የእነዚኽ ሰዎች በእዚኽ መልክ ማጭበርበር እና የእውነተኛው ጳጳስ አባ ጴጥሮስ መታሰር ወሬ አሌክሳንደሪያ ሲደርስ ፤ ኮስማ የተባለው የአሌክሳንደሪያ ጳጳስ ተቆጥቶ እንዴት እኛ የላክነውን ጳጳስ ታሥራላችሁ የእሚል መልዕክት ይልካል ።
ንጉሡም መልዕክቱ እንደ ደረሰው ፤ አጭበርባሪውን ጳጳስ ሚናስን በማስገደል ፤ አባ ጴጥሮስን ከግዞት ሊያስወጣ ሲልክ ፤ ጳጳሱ በግዞት እንዳሉ ሞተው ነበር እና ወደ መንበራቸው መመለስ አልተቻለም ።
በእዚኽ የተበሳጩት የአሌክሳንደሪያ መንበር የቤተክርስቲያን መሪዎች ፤ ለኢትዮጵያ ጳጳስ አንልክም ብለው ፤ ቢያንስ ለእሚቀጥለው ኃምሳ ዓመት ኢትዮጵያ ከአሌክሳንደሪያ ጳጳስ ሳታገኝ ቆይታለች ።
በእዚኽ መልኩ ፤ በቀላሉ ተጭበርብሮ የሹም ሽር የእሚደረግበት መንግሥት ፤ ከአጉል ኃይማኖታዊ የዋህነት የተነሳ የፖለቲካ ስልጣን ሹመት እና ሽረትን ጉዳይ በሙሉ ለመንፈሳዊ ተቋም አሳልፎ የሰጠ መንግሥት ፤ ፈር በለቀቀ ኃይማኖተኝነት ከግዜ ወደ ግዜ ከምድራዊ መንግሥትነት ወደ መንፈሳዊ ቅርንጫፍነት ራሱን ቀይሮ ውስጣዊ የአስተዳደር ፣ የቁጥጥር እና በጠቅላላ መንግሥታዊ ኃላፊነት የዘነጋ መንግሥት እየሆነ መሆኑን የእሚያሳይ በመሆኑ ፤ የአክሱም መንግሥት በአጉል መንፈሳዊነት ከግዜ ወደ ግዜ ከውስጥ እየዘበጠ የመጣበት ዘመን ላይ ለመሆኑ ሌላ ማሳያ ነው ።
አንድ ትልቅ እና ለረዥም ዘመን ሰፊ አከባቢን ያስተዳደረ መንግሥት ፤ ንጉሥን የመምረጥ ዓይነት ታላቅ ኃላፊነት ለአንድ ጳጳስ አሳልፎ የመስጠት እና በእንደዚኽ ዓይነት ፖለቲካዊ መጨብረበር ውስጥ በቀላሉ የእሚጠለፍ መሆኑ ፤ ስረዓቱ በአንድ ውስጣዊ ሕመም ላይ እንደ አለ ማሳያ ነው።
የአክሱም መንግሥት ፤ በክርስትና ምክንያት ከገባበት ፖለቲካዊ መደናበር የተነሳ ፤ መሠረታዊ የቁጥጥር እና የሚዛን እንዲኹም ጠቅላላ የመንግሥት አስተዳደሩ ጉዳይ ከልብ መሥራት ተስኖት የነበረ መሆኑ በተደጋጋሚ ይታያል።
በእዚኽ መልኩ ፤ በአቡነ ጴጥሮስ በግዞት መሞት ምክንያት ፤ ከአሌክሳንድርያው መንበር ጋር ቅሬታ ውስጥ የገባው የአክሱም መንግሥት ፤ ውስጣዊ አመፅ እያየለበት ሲኼድ ፣ የዮዲት ጉዲት ጥቃት በአክሱም ከፍተኛ ውድመት ሲያስከትልበት ፣ ወዘተ ፤ በአቡነ ጴጥሮስ መሞት ምክንያት እግዚአብሔር ተቆጥቶን ነው በእሚል ፤ በአንድ ወቅት የአክሱም ገባር ለነበረው እና አኹን ግን ከአክሱም ይልቅ ተዓማኒ ለሆነው በዛሬው ሱዳን ለእሚገኘው ጊዮርጊስ (George) ለእሚባለው የሜሮ ንጉሥ ፤ የአሌክሳንደሪያ መንበር ይቅርታ አድርጎ ጳጳስ እንዲልክልን አማልደን የእሚል ደብዳቤ ወደ መጻፍ ገባ ።
የአክሱሙ መንግሥት ለገባበት ቀውስ ፤ መፍትኼ ይሆናል ብሎ በማሰብ ፤ የሜሮን ንጉሥ ከግብፅ አሌክሳንደሪያ መንበር አማልደኝ ብሎ ይኽን ደብዳቤ መጻፉ ፥ በግብፃዊያን ታሪክ ጸኃፍት እንዲሁም በኢትዮጵያ ስንክሳር ህዳር 12 ቀን በተጻፈው ስር ይገኛል ፦
“…የአቢሲንያው (የሐባሻው) ንጉሥ ፥ ወደ ኑብያው (ኑባው) ፥ ወጣቱ ንጉሥ ጆርጅ(ጊዮርጊስ) መልዕክት ላከ ። እግዚአብሔር እርሱን እና ሕዝቡን እንዴት እንደ ቀጣቸው አስታወቀው … እባክኽ በምስር ላለው ጳጳስ ፥ በምድራችን ላይ የአለው ይኽ ፈተና እንዲ ወገድ ፥ ለእኛም ለምድራችንም ፍትሐት እንዲ ያደርግልን እና ጳጵስ እንዲሾምልን ደብዳቤ ጻፍለት ።”
“...The king of Abyssinia (al-Habasha) sent to the king of Nubia (An-Nubah), a youth whose name was George (Girgis), and made known to him how the Lord chastened him, he and the inhabitant of his land...and that thou shouldest write a letter on thy part to the father, the patriarch, in Misr to beg him to absolve us and to absolve our lands, and to pray for us, that God may remove from us and from our country this trial, and may grant to us that he (the patriarch) may consecrate for us metropolitan (mutran), [96]“
ሰው ኹሉ እንደ እሚያምንበት እምነት ፤ ለተፈፀመ በደል እና የፍርድ መዛባት ፤ እግዚአብሔር አዝኖ ወይንም ተቆጥቶ ይኽ ደርሶብናል ብሎ ማሰቡ ፤ ከፖለቲካ ሳይንስ አንፃር ፤ ሕዝብን በደልን ለማስወገድ እና ፍትሕን ለማስፈን እንዲንቀሳቀስ እስከ አደረገው ድረስ እንደ መልካም የእሚታይ ቢሆንም ፤ ይኽ ነው የእሚባል የኹኔታ ዳሰሳ ሰይአደርጉ ፤ በይቅርታ እና በአማላጅ ደብዳቤ ፣ በፀሎት ብዛት ወይንም በሌላ ፤ የችግሩን መንስኤ ሰአይሆን ውጤቱን ለማስቀረት መሞከራቸው ፤ አክሱማዊው ስረወ መንግሥት ፈር በለቀቀ መንፈሳዊነት እንደ ስረዓት መደናገር ውስጥ እንደገባ እንደገና ሌላ ማሳያ ነው ።
ይኽ ፤ የራስን ምግባር መዝኖ ፤ ንሰኃ ከአስፈለገም ተግባርን በንሰኃ ከማስተካከል ይልቅ ፤ ምልጃ እና ፀሎት በማብዛት ፤ ውድቀትን ኹሉ ከእግዚአብሔር ቁጣ ጋር አያይዞ ይቅርታን በመለመን ካባ ፤ የስንፍናን እንቅልፍ ማንቀላፋት ፤ በሶስተኝነት የጠቀስነው የአክሱም መንግሥት ፤ ፖለቲካዊ ኪሳራ ውስጥ መኖሩን ማሳያ ታሪክ ነው ።
ለእነዚኽ በተደጋጋሚ እየተከሰቱ የአክሱምን መንግሥት ከውስጥ እየገዘገዙ ለነበሩ አለመረጋጋቶች ኹሉ ፤ ምክንያቶቹ አዲሱ የክርስትና መልዕክት በፈጠረበት መደናበር ከግዜ ወደ ግዜ እየተዳከመ የመጣው የመንግሥት ቤሮክራሲ እና የፍትሕ አስተዳደር ችግር እንደ ሆኑ ሊያሳዩ የእሚችሉት ፤ ከአልናቸው ችግሮች በአራተኛነት ሊጠቀስ የእሚችለው ታሪካዊ ማሳያ ፤ የዮዲት ጉዲት ታሪክ እና ወደ ዛሬዋ ደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ፤ የአፍሪካን ምዕራባዊ የባሕር በር ለማግኘት የተላከው የቅኝት ወታደሮች ታሪኮች ናቸው ።
ከሌሎች መሰል ውስጣዊ አመፃዎች ፤ በዮዲት ጉዲት የደረሰበት ውድመት ፤ ለአክሱም መንግሥት የውድቀቱ መጨረሻ ምክንያት ነው ተብሎ በታሪክ በተደጋጋሚ ስለ እሚነገር ፤ የጉዲት ታሪክ ይበልጥ አትኩሮት ያገኛል እንጂ ፤ በእዚኽ ኹለተኛው የፖለቲካዊ ዝግመታችን ታሪክ ክፍል በአልነው የግዜ ሰሌዳ ወደ መጨረሻው ዓመታት አከባቢ ፤ የአክሱሙ መንግሥት ከዮዲትም ቀድም ብሎ የተለያዩ ሐገራዊ አመፆች በርትተውበት አንዳንዴ እንዲያውም ፤ የአክሱም ነገሥታት ራሳቸው በጀነራሎቻቸው ስር ወደ መሆን ዝቅ የአለበትም ግዜያት ነበሩ ።
በኢትዮጵያ ታሪክ ፤ አጼ የእሚለውን ስም አስተዋወቀ የእሚባለው (እንደ ሰርጌው ሐብለ ሥላሴ ፤ የቃሉ ምንጭ ‘ሐፀነ’ ፣ አነፀ ወይንም አሳደገ የእሚል ትርጉም ካለው የግዕዝ ቃል ነው) ፤ ሐፃኒ ዳንኤል ንጉሡን ከስልጣን አውርዶ ግዜያዊ (De facto) አስተዳደር ሆኖ ነበር ።
ጉዲት ግን ፤ ነገሥታቱን በመወሰን ብቻ ሳትወሰን ፤ የአመጿ ጥግ ፤ የአክሱም ነገሥታትን መናገሻ በቋሚነት እንዲቀየሩ እስከ ማስገደድ የደረሰ ክበደት እና ረዥም ቆይታ የነበረው ነው ። የጁዲት ታሪክ ፥ ከኢትዮጵያ ውጭ ባሉ ብዙ ታሪኮች ቢጠቀስም ፤ እንደ ሰርጌው ኃብለ ሥላሴ ፤ በገድለ አብረኃ እና አፅብኃ በእሚል በሐገራችን ገዳማት ባሉ መዛግብት ላይ ታሪኩ በዝርዝር ተቀምጧል ።
ጠቅለል የአለው የጁዲት ጉዲት ታሪክ ይኽን ይመስላል ፦ ጁዲት ከመኳንንት ዘር ብትሆንም በአልታወቀ ምክንያት ኮማሪት ሆና በነበረበት ወቅት አንድ ዲያቆን ያፈቅራታል ። እርሷም ከእኔ ጋር የእምትሆነው ፥ በእዚኽን ያህል ወርቅ ነው ስለ አለችው ፤ በፍቅሯ የወደቀው ዲያቆን ፤ በጥያቄዋ መሠረት ከቤተክርስቲያን ወርቅ ሰርቆ ያመጣላታል ። የጠፋውም ወርቅ ሲጣራ እርሷ ጋር እንደሆነ ተደርሶበት ፤ ቁንጅናሽ ነው ዲያቆኑን ያሳተው ስለ እዚኽ እርሱ አይፈረድበትም ተብላ ፤ አንድ ጡቷ ተቆርጦ ከሐገር እንድትባረር ትደረጋለች ። የኼደችውም ወደ ሶሪያ ነው ይላል ታሪኩ ።
እንደ ታሪኩ ፤ እጅግ ውብ ስለ ነበረች በሔደችበት በሶሪያ ከነበረው ንጉሥ ተወዳጅታ ፤ የኢትዮጵያን ንጉሥ የእምትበቀልበት ቀን ስትጠብቅ ፤ ንጉሡ ወደ በረኃ ዘምቶ ፤ ነጋሪ ሳይቀር ፤ ጦሩ እና ንጉሡ በውኃ ጥም እንደ አለቁ ስለ ሰማች ፤ በውጭ ያገኘችውን እርዳታ ይዛ ፤ ወደ ሐገሯ ተመልሳ ፤ ያው በታሪክ የእምናውቀው ቤተክርስቲያ ማቃጠል ፥ የአክሱምን ሐውልቶች ማፍረስ ፦ ለምሳሌ የወደቀውን የአክሱም ኃውልት እርሷ ነች የጣለችው ይላል ሐገራዊ ገድሉ ፤ በአጠቃላይ ፤ የአክሱምን ከተማ ማውደም ውስጥ ገባች ፤ ያን ግዜም የአክሱም ፅዮን ታቦት ፤ ከእርሷ ሽሽት ወደ ዝዋይ ተወሰደ ።
ታቦቱም ፥ ከጁዲት የ40 ዓመት ንግሥና በኋላ ፤ አንበሳ ወድም በእሚባለው ንጉሥ ወደ አክሱም እስኪ መለስ ድረስ በእዚያው በዝዋይ ቆይቷል ።
ይኽም የዮዲት ጉዲት ታሪክ ፤ የወቅቱ የአክሱማዊያን ኃይማኖተኝነት ፈር ለቆ ፤ ምድራዊ ፍትኽን የእሚያዛበትን አግባብ የእሚያሳይ ይመስለኛል።
ጉዲትን በአሳፋሪ እና በኢፍትኃዊ መንገድ ቀጥቶ ለእዚኽ ቁጣ ያነሳሳት ይኽ እየዘበጠ የመጣ የአክሱም አስተዳደር ፤ በውድቀቱ መባቻ ላይ ፤ ሌላም ተመሳሳይ ፍርደ ገምድልነት ፤ በገዛ በራሱ ጀነራሎች ላይ እንደፈፀመ የእሚተርክ ታሪክ አለ ።
በአንዱ የንጉሡ ጀግና ጀነራል ላይ የደረሰው በደል ይኽን ይመስላል ፦ የመጨረሻው የአክሱም ንጉሥ ድል ናዖድ ፤ ግብፆች እና ግሪኮች በሕብረት ፤ ወደ አስረኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አከባቢ ፤ ከቀይ ባሕር እና ከሜድትራንያን ሌላ ፤ ከአክሱም በስተ ደቡብ እና በስተ ደቡብ ምዕራብ ፤ በምን ያህል ርቀት ላይ ባሕር እንደ እሚገኝ ለማወቅ ቅኝት ለመላክ ስለ ተስማሙ ፤ ንጉሥ ድል ናዖድም ለእዚኹ ዓላማ ሦሥት ክፍለ ጦር ፤ ለቅኝት ልኮ ነበር ። በእዚኽም መሠረት ፤ አንደኛው ክፈለ ጦር ወድ ስናር (የዛሬ ደቡብ ሱዳን እና የተወስኑ የኢትዮጵያ አጎራባች ቦታዎች) ፣ ኹለተኛው ወደ እናርያ እና ሦሥተኛው ወደ ሸዋ ተልከዋል ፦
“እርሱም ሦሥት ወታደራዊ መሪዎቹን ከብዙ ወታደሮች ጋር ወደ ሦሥት አቅጣጫ ላከ ። አንዱ ወደ ሸዋ ፣ ሌላኛው ወደ እናርያ እና ሦሥተኛው ወደ ስናር ።”
“Then he sent three military leaders with many soldiers (to three different directions), one towards Shewa, another towards Enarya and the third towards Sennar. [96]“
በሰርጌው ዘገባ ፤ የትኞቹ በረኃ አግዶዋቸው እንደ ተመለሱ በአይቀመጥም ፤ ኹለቱ ጀነራሎች በርኃ አግዶዋቸው ሲመለሱ አንዱ ግን ፤ አሁንም ታሪኩ የት ደርሶ እንደ መጣ በአይልም ፤ ከብዙ ግዜ በኋላ ከአንዱ የውኃ ዳር ደርሶ ፤ ለመድረሱም ማሳያ እንዲሆን እጅግ ረዥም ቀርከኃ ይዞ ይመለሳል ።
ብዙ ፈተና አልፎ የተመለሰ ይኽ ብቸኛ ጀነራል ግን ፤ እግዚአብሔር ከጉዳት ጠብቆ አድርሶ መልሶኛል በማለቱ የተቆጣው ድል ናዖድ[3] ፤ እግዚአብሔር አይደለም እኔ ነኝ አድርሼህ የመልስኹህ በማለቱ እና ጀነራሉም ፤ የለም አንተ አይደለህም እግዚአብሔር ነው ብሎ በመመለሱ ፤ በተፈጠረው አለመግባብት ፤ ጀነራሉ በንጉሡ ትዕዛዝ እንደታሰረ ነው ታሪኩ የእሚለው ።
ይኽም የድል ናዖድ ትዕቢት ፤ መነኮስታን እንዳሳዘነ እና እነርሱም ንጉሡን ቢመክሩትም አልሰማም እንደ አለ በመፅናቱ ፤ እንዲኽ በማድረግህ የሴት ልጅህ ልጅ ነው ዙፋኑን የእሚወርሰው ስለ ተባለ ፤ የመነኮሳቱ ‘ትንቢት’ እንደ አይፈጸም ድል ናዖድ ፤ አዲስ የተወለደች ሴት ልጁን ሰው ሳይሰማ በስውር ፤ በአውሬ እንድትበላ በዱር ውስጥ ይጥላታል።
መራ ተክላኃይማኖት የእሚባለው የንጉሡ የጦር መሪም በአጋጣሚ ልጅቷ በተጣለችበት ሲያልፍ አግኝቷት በመውሰድ ፤ ንጉሡ የአደረገውን ነገር ሳያውቅ ፤ ሴት ልጅ በዱር ውስጥ ተጥላ እንደ አገኘ እና ቤቱ እንደ ወሰዳት ለንጉሡ ይነግረዋል ። ንጉሡም ነገሩ አስደንግጦት ፤ እውነቱን ይነግረው እና እንዲያሳድጋት ይፈቅድለታል ። ልጅቷ ከአደገች በኋላ ፤ የመራ ተክለኃይማኖት ሚስት በመሆኗ ፤ ከግዜ በኋላ መራ ተክለኃይማኖት እና ንጉሥ ሳይግባቡ ቀርተው ወደ ግጭት ሲያመሩ ፤ መራ ተክለኃይማኖት በማሸነፉ እና ራሱን ንጉሥ በማድረጉ ፤ የዛግዌ ስርወ መንግሥት በመራ ተክለ ኃይማኖት ጀምሮ እና ተጥላ ከነበረችው የንጉሥ ልጅ (መሶብ ውርቅ) የእሚወለዱት ልጆች የዛግዌን ስርወ መንግሥት ወራሽ እንደ ሆኑ ነው ታሪኩ የእሚለው ።
እነ እዚኽ ፤ በሰርጌው የቀረቡልን በሐገራችን በእየገዳማቱ የእሚገኙ ታሪኮች ፤ አንድ ሰው ታሪካዊ ትክክለኝነታው ቢጠራጠርም እንኳን ፤ ማለትም ፦ እውነት ዮዲት ጡቷ ተቆርጣል? ይኽ መልካም የሰራ የጦር ጀነራል ያለ አግባብ ታስሯል? ድል ናዖድስ ሴት ልጁን በዱር ጥሏል? ወዘተ ፤ የእሚሉት ጉዳዮች ፤ ሊያከራክሩ ቢችሉም ፤ የወቅቱ የአክሱም መንግሥት ግን ፤ ከገባበት ፖለቲካዊ መደናበር የተነሳ ፤ በሥራ ፈትነት ፣ በአጉል መንፈሳዊነት ፣ በፍርደ ገምድልነት በአጠቃላይ ከእላይ ድሕረ ክርስትና ክርስቲያናዊው ስልጣኔ ገባባቸው የአልናቸው ሦሥቱ መደናበሮች በአስከተሉበት አሉታዊ ተፅዕኖ በመንግሥታዊ ዝቅጠት ውስጥ ገብቶ እንደ ነበር ያሳየናል ።
ምክንያቱም ፦ የተለያዩ የወቅቱ ታሪክ ጸኃፍት ፤ በኃፃኒ ፣ በጉዲት ፣ ስሙ በአልተጠቀሰው ጀነራል እንደ ገናም በንጉሡ ሴት ልጅ መጣል ፤ እያንፀባረቁ የአሉ፟ት ጭብጥ ፤ የዘገባቸው ታሪካዊ ትክክለኛነት መጠርጠር የፈለገ ሰው ሊጠረጥረው ቢችልም እንኳን ፤ የዘመኑን መንፈስ ወይንም የመንግሥቱን መተራመስ ፤ በተለያየ ወቅት በቋሚነት የታሪካዊ ዘገባቸው ጭብጥ ማድረጋቸው ፤ በወቅቱ ከነበረው ፖለቲካዊ ድባብ የተነሳ እንደ ሆነ እንድንገምት ያደርገናል ።
ይኽን መሰሉ ዓይነቱ መደናበር የእሚፈጥረው ስረዓታዊ ቀውስ የእሚወልደው ስረዓት አልበኝነት ከሌለ ፤ አንዲት ንግሥት ሐገሯን በእዚኽ መልኩ እንድታወድም ፣ ጀነራሎች ንጉሳቸው ላይ በተደጋጋሚ በአመጽ የእሚነሱበት ኹኔታ ፣ ለረዥም ዘመን ተድላድሎ የቆየ መንግሥት ፤ ይኽ ነው የሚባል የውጭ ባላንጣ ሳይመጣበት በእየ ግዜው የጥቃት እና የስደት ሰለባ የእሚሆንበት ፣ ወዘተ ፤ ምክንያት የመኖሩ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው ።
በአጠቃላይ መንግሥታዊ መዋቅሩ እና የፍትሕ አስተዳደሩ ርዕዮታዊ በሽታ ከአልገጠመው ፤ ለረዥም ዘመን የቆየ እና የፀና መንግሥት ፤ ያለ እነ እዚኽን መሰል ውስጣዊ የመዝበጥ ችግሮች እንዲሁ ተሳዳጅ የእሚሆን አይመስልም ።
ስለ እዚኽ ፦ አክሱም ከግነት ወደ ክስመት የኼደችበትን እና ኹለተኛው የታሪካችን ምዕራፍ የአልነው ክፍል ፤ የአክሱሙ መንግሥት ፤ ለግነት ያበቁትን ፤ በመላው ምሥራቅ አፍሪካ እና ደቡብ አረቢያ የአሉ፟ትን ፤ የንግድ አቅርቦት ሰንሰለት ደህንነት ማረጋገጥ እና ሰላማዊ የክርስትና መስፋፋትን ከጥቃት መከላከል ላይ የተገነባው ታላቅነቱ ፤ በክርስትና ሰብዓዊ መልዕክት ምክንያት በተፈጥረው ፖለቲካዊ መደናገር ፤ የትኛውን የፖለቲካ አቅጣጫ መከተል እንደ አለበት መገንዘብ ስለ አልቻለ እና እስኪችል ድረስ ፤ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን በብቃት መወጣት ተስኖት ከውስጥ በመዝበጡ ፤ የዕዝ ማዕከሉን ወደ ሸዋ አዙሮ እና ራሱን በአዲስ መልክ አደራጅቶ እስኪ መጣ ፤ የዛግዌ ስርወ መንግሥት ሐገርን የመምራት ታሪካዊ ኃላፊነቱን ተረክቦ ፤ ሦሥተኛው የታሪካችን ክፍል መሪ ሆኗል ።
ሦሥተኛ ፤ የአልኩትም የታሪካችን ክፍል ይኽን የዛግዌን መንግሥት ዘመን የእሚመለከት ይሆናል ።
በኢየሩሳሌም የእሚገኘው የኢየሱስ አስክሬን እስከ ትንሳኤው ለሶስት ቀን የቆየበት መቃብር። ↑
በ16ኛው ምዕተ ዓመት በዝዋይ ገዳም ይኖሩ የነበሩት ኢትዮጲያዊ መነኩሴ ፤ አባ ባህሬይ ፤ የዖሮሞ ሕዝብ እንዴት የክርስቲያኑን ኢትዮጲያ ወረረ ለእሚለው ጥያቄ መልስ በእሚሰጡበት ወቅት ፤ ከአስቀመጡዋቸው መላምቶች አንዱ ፦ አንዳንዱ መነኩሴ መነኩሴ የሆነው በእውነት መመንኮስ ፈልጎ ሳይሆን በመንፈሳዊነት አመካኝቶ ወደ ጦር ሜዳ ከመዝመት ለመራቅ ነው ፤ በእንደ እዚኽ ዓይነት የአልበቁ ምክንያቶች ከውትድርና በእሚሸሹ ሰዎች ምክንያት የጦር ሠራዊታችን ቁጥር ከሕዝባችን አንጻር በማነሱ ነው ፤ በቁጥር በእሚያንሰው የኦሮሞ ሕዝብ የተወረርነው በለው የአቀረቡት ምክንያት ፤ ከእዚኽ የማክያቬሊ ኃሳብ ጋር ይመሳሰላል ። አባ ባሕሬይ እንዲኽ ይላሉ ፦ “ከእነ እርሱ ውስጥ አንዱ ፥ ቁጥር የሌላቸው የመነኮሳት ወገን ነው ። እንደ እዚኽ ታሪክ ጸሐፊና ብጤዎች በልጅነቱ በትምህርት ላይ ሳለ መነኩሴዎች ሲደልሉት የእሚመነኩስ አለ ፤ ውጊያ ፈርቶ የእሚመነኩስ አለ ።” ↑
ድል ናዖድ የአክሱም የመጨረሻው ንጉሥ በመሆኑ ፤ ከላይ በማክያቬሊ የተጠቀሰው ፤ አጉል መንፈሳዊነታችን ጎድቶናል ከእሚል ወይንም እግዚአብሔር እግዚአብሔር እያለን ተሳዳጅ ሆነን ከእሚል የተሳሳተ አመለካከት የመነጨ እብሪት ይመስላል ፤ ለእዚኽ ዓይነት ባሕሪ የዳረገው። ↑