ሕ ገ ክ ራ ሲ

marketing-image

3.2.9. ክፍል 9 ፡ ዘመነ ኢሕአዴግ (ከ 1983 ዓ.ም. – አሁን)

በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ1950ዎቹ አከባቢ ጀምሮ የመጡት አብዮታዊ እንቅስቃሴዎች ፦ የተማሪው አብዮተኞች (የአዲስ አበባ ፣ የሰሜን አሜሪካ ፣ የአውሮፓ ፣ ወዘተ) ፣ ደርግ ፣ ሕወሐት ፣ ሻዕቢያ (ሕዝባዊ ግንባር) ፣ ግገሐት (ግንባር ገድሊ ሐርነት ትግራይ) ፣ ተሐኤ (ተጋድሎ ሐርነት ኤርትራ ወይንም ጀብኃ) ፣ ኢዴሕ (የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሕብረት ወይንም ኢዲዩ (EDU)) ፣ ወዘተ ወይንም ኹሉም በኢትዮጵያ በእዚኽ ወቅት ዘመናዊ የፖለቲካ ፓርቲ ወይንም እንቅስቃሴ መልክ ይዘው የተጀመሩት ፖለቲካዊ ተቋማት በአንዱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ግንድ ላይ የበቀሉ ፤ የተለያዩ የአንዱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቅርንጫፎች በመሆናቸው ተዛማጅ ናችው።

እነ እዚኽ ፖለቲካዊ ድርጅቶች እና እንቅስቃሴዎች በሐገሪቱ ፤ የወቅቱ የሐገሪቱ እና ዓለም ዓቀፋዊው ፖለቲካዊ ድባብ በእዚኽ መልኩ በብዛት እና በተናጠል እንዲ ፈሉ ከአደረጋቸውም በኋላ ፤ በተለያየ ምክንያት አንዳንዶቹ ከሌሎቹ ይልቅ ተቀራርበው ፤ በእዚኽ ምህዳር ውስጥ የራሳቸውን ንዑስ ቡዳን ወይንም የትብብር ማዕቀፍ እንዲያቋቁሙ የሆኑበት ኹኔታም ነበር ። ለምሳሌ ፦ ወዝሊግ (ወዝ አደር ሊግ) ፣ መኢሶን (መላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ) ፣ ደርግ ፣ ወዘተ ፣ አንድ የራሳቸው ንዑስ ቡድን ነበራቸው ፤ ኢሕአፓ መጀመሪያ ላይ ከሕግሐኤ (ሕዝባዊ ግንባር ሐርነት ኤርትራ) በኋላ ላይ ከተሐኤ (ተጋድሎ ሐርነት ኤርትራ) ጋር የአበረበት ግዜያት ነበሩ።

ከእዚኽም የተነሳ ፦ ምንም እንኳን ፤ በእዚኽ ክፍል ዋናው ትኩረታችን ፤ የሕወሐት/ኢሕአዴግ የስልጣን ዘመንን መቃኘት ቢሆንም እና በአኹኑ ሰዓት ኤርትራም ከኢትዮጵያ የተነጠለች እና ራሷን የቻለች ሐገር ብትሆንም ፤ የሕወሐት/ኢሕአዴግን የስልጣን ወቅት እና ፖለቲካዊ ፋይዳውን በአግባቡ መረዳት የእምንችለው ፤ በተወሰነ ደረጃ የሻዕብያን (ሕዝባዊ ግንባርን) ፖለቲካዊ ዝግመት ከሕወሐት/ኢሕአዴግ ጋር አያይዘን ስናይ ነው የእሚል እምነት አለኝ ፤ ምክንያቱም ፦ እነ እዚኽ ኹለት ድርጅቶች በወቅቱ ፤ እንደ አሸን ከፈሉት እና በእዚኽ ፖለቲካዊ ድባብ ውስጥ የራሳቸው ልዩ ቡድን ከፈጠሩ የተለያዩ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች እና ድርጅቶች ፤ ምንም እንኳን እጅግ ውጣ ውረድ የበዛበት ቢሆንም ፤ ትብብራቸው ዘልቆ ለድል እንዲያበቃቸው ከአስቻሉዋቸው ምክንያቶች አንዱ በመሆኑ።

እነ እዚኽ ኹለት ድርጅቶች ፤ ሕወሐት እና ሻዕብያ ፤ ምንም እንኳን በፖለቲካ ፕሮግራማቸው እጅግ የተለያዩ ቢሆንም ዋናው ለትብብር እንዲነሳሱ የአደረጋቸው ነገር ፤ በነባራዊው የኢትዮጵያ ኹኔታ የፖለቲካ ጥያቄያችንን ማስመለስ የእምንችለው ፤ ኢዴሞክራሲያዊ የሆነውን የኢትዮጵያ መንግሥት በነፍጥ ኃይል ስን አስገድደው ወይንም ስናስወግደው ነው የእሚል እምነት በመያዛቸው ነው።

ሕወሐት በፕሮግራም ደረጃ የአለው ፖለቲካዊ ፕሮግራም የእሚለው ፤ ኢትዮጵያ በኢዴሞክራሲያዊ አግባብ የተለያዩ ነገዷቿን የእሚጨቁን ፣ በአሉታዊ ኢምፔሪያሊዝም ተጽኖ ስር የአለ ወይንም ለባዕዳን ካፒታሊስቶች እና መንግሥቶቻቸው የእሚያጎበድድ ፣ በቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም (መንግሥታዊ ስልጣንን ለግል ጥቅም በመጠቀም) የላሸቀ እና በእዚኽ በተዛባ ፖለቲካዊ ምህዳር ላይ በዝባዥ ንዑስ ከበርቴ እያበቀለ ያለ መንግሥታዊ መዋቅር የአላ፟ት ሐገር በመሆኗ ፤ በግራ ዘመም ፖለቲከኞች ዘንድ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ወይንም ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት (National Democratic Revolution or People’s Democratic Revolution) የእሚባለው አብዮት ተካኺዶ ፤ ከኢትዮጵያ ነገዳዊ ጭቆና ፣ የኢምፔሪያሊዝም አሉታዊ ተጽኖ ፣ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም እና ንዑስ ካፒታሊስት ተወግዶ ፤ በማዕከላዊ የመንግሥት አመራር ወይንም በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ወደ ካፒታሊስት ስረዓት መሸጋገር አለባት የእሚል ድርጅት ነው።

የሻዕብያ ፖለቲካዊ ፕሮግራም በተቃራኒው ከሕወሐት በመለየት የእኔ ጥያቄ ኢትዮጵያ ከደረሰባት ስረዓታዊ መላሸቅ ወጥታ ወደ ካፒታሊዝም ስረዓት እንዴት እንአሻግራት በእሚለው ጉዳይ ላይ የእሚያተኮር ሰአይሆን ፤ ኤርትራ የኢትዮጵያ ቀኝ ግዛት በመሆኗ ፤ ኤርትራ ከኢትዮጵያ በሪፈረንደም እንድትገነጠል ወይንም የኤርትራ ሕዝብ ሪፍረንደም እንዲያካኺድ እና እንዲገንጠል የእሚያስችለው ኹኔታ እንዲፈጠር ነው የእምታገለው የእሚል ነው።

የእነ እዚኽን ኹለት ፖለቲካዊ ድርጅቶች ዋነኛ የፖለቲካ ፕሮግራም ስናነጻጽር ፤ ምንም እንኳን የሕወሐት/ኢሕአዴግ ተቃዋሚዎች ሕወሐት/ኢሕአዴግ ገንጣይ አስገንጣይ እና ጸረ ኢትዮጵያ ነው ቢሉም ፤ ሕወሐት በአንዲት ኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ አንድ ዓይነት ፖለቲካዊ ስረዓት ለመትከል የሚታገል እና ሻዕብያ በተቃራኒው ከእነ አካቴው ከኢትዮጵያ መገንጠልን የእሚፈልግ በመሆኑ ፤ ቢያንስ በፕሮግራም ደረጃ ሕወሐት አፍቃሪ ኢትዮጵያ ወይንም በኢትዮጵያ አንድነት የእሚያምን ድርጅት እና ሻዕብያ ጸረ ኢትዮጵያ ነው ባይባልም ከኢትዮጵያ መነጠል የእሚፈልግ ድርጅት መሆናቸው ስለ እሚታይ ፤ ሕወሐት አስገንጣይ ፣ ገንጣይ ወይንም ጸረ ኢትዮጵያ የእሚባል ፕሮግራም አለው ሊባል የእሚችል ድርጅት አይደለም።

ሕወሐትን በተመለከተ ፤ ብዙ የሕወሐት አባላትን ጨምሮ ለተለያዩ ኢትዮጵያዊያን ግልጽ ያልሆነው ወይንም በስህተት የእሚቀርበው የሕወሐት ጉዳይ ፤ በእዚኽ መልኩ ውስብስብ የሆነው ፤ በእኔ እምነት ከላይ በተገለጸው የብሔራዊ/ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ላይ ተገቢው ግንዛቤ ከአለመኖር ነው።

ብሔራዊ/ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ደርግ በአጭሩ “ዴሞክራሲያዊ አብዮት” ሲለው የነበረና እና በኋላ ላይ ሕወሐት/ኢሕአዴግ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” የአለው ነው። ስያሜዎቹን የተመለከትናቸው እንደ ሆነ አንዱ ወይንም ደርግ ዴሞክራሲ የእሚለውን ቃል ከአብዮት በፊት በማምጣቱ ፤ ሌላው ወይንም ሕወሐት/ኢሕአዴግ አብዮትን ከዴሞክራሲ በፊት በማምጣቱ እንጂ ፤ ኹለቱም ስያሜዎች ዴሞክራሲ እና አብዮቱ የእሚሉት ቃላት የአሉዋቸው ናቸው።

የስያሜዎቹ ቃላቶች ከቅደም ተከተል በስተቀር አንድ መሆን ብቻ ሳይሆን ኹለቱም ስያሜዎች ፤ ማለትም ፦ የደርጉ “ዴሞክራሲያዊ አብዮት” እና የሕወሐቱ/ኢሕአዴግ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” አንድ እና ተመሳሳይ ፖለቲካዊ አስተሳሰብን የእሚገልጹ ናቸው።

“ዴሞክራሲያዊ አብዮት” ወይንም “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” የእሚሉት ስያሜዎች የፈጠሩት ዴሞክራሲ እና አብዮት የእሚሉትን ቃላት በተናጠል የተመለከትን እንደ ሆነ እንደ ውኃ እና እሳት አብረው ሊኼዱ የእማይችሉ ቃላት እንደ ሆኑ እንመለከታለን።

አንድ የፖለቲካ ማሕበረሰብ ወይንም የፖለቲካ ቡድን ዴሞክራሲን ለማስፈን አብዮት ሊያካኺድ ቢችልም ዴሞክራሲን አብዮታዊ ማድረግ ወይንም አብዮትን (ፖለቲካዊ አብዮትን) ዴሞክራሲያዊ ማድርግ የእማይቻል በመሆኑ ፤ ስያሜውን በአዋቀሩት ቃላት የተመለከትነው እንደ ሆነ በተቃርኖ የተሞላ እና ትርጉም አልባ ነው።

እንደ እሚታወቀው ዴሞክራሲ የእሚታወቅ የግዜ ገደብ የሌለው በዋናነት የሕግ የበላይነት እና ሰብዓዊ እኩልነት የሰፈነበት ስረዓት ነው ፤ በተቃራኒው አብዮት (ፖለቲካዊ አብዮት) ደግሞ አንድ የእማይፈልገን ፖለቲካዊ ስረዓት በኃይል ለማስወገድ የእሚደረግ በመደበኛ የሕግ የበላይነት የእማይገዛ ፤ የእሚጀምርበት እና የእሚያበቃበት ግዜ የአለው ፤ የፖለቲካ ስረዓት በኃይል የመለወጫ መንገድ ነው።

ስለ እዚኽ ፦ ዴሞክራሲ እና አብዮት ፤ በእሚወክሉት ኃሳብ ምክንያት መጎራበት የእማይችሉ ቃላት በመሆናቸው ፤ “ዴሞክራሲያዊ አብዮት” ወይንም “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” የእሚለው ስያሜ ፤ በስያሜነት ልክ እንደ “የጥቁር ነጭ” ዓይነት በእንግሊዘኛው “Oxymoron[1]” የእሚባለው ዓይነት ስያሜ ነው።

ይኽ ኦግዚሞሮናዊ ስያሜ የአለው ፤ የሕወሐትን ፖለቲካዊ ፕሮግራም እና ጠባይ የእሚወስነው እና የእዚያኽን ዘመኑን ፖለቲካዊ ድባብ ለመረዳት እጅግ የእሚያግዘው ፤ በአጭሩ “ዴሞክራሲያዊ አብዮት” እና “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” በሙሉ ስያሜው “ብሔራዊ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይንም ሕዝባዊ አብዮታዊ ዴሞክራሲ” የእሚባለው ስያሜ የእሚወክለው እና እኔ ከእዚኽ በኋላ ለአጻጻፍ አመቺነት የሕወሐት/ኢሕአዲጉን ስያሜ “አብዮታዊ ዴሞክራሲን” ብቻ የእምጠቀምበት ፤ ፖለቲካዊ ፕሮግራም ፤ ምንጩ ፣ ይዘቱ እና ፋይዳው ምንድ ነው የእሚለውን ፤ በመሠረታዊ ጭብጡ ላይ በማተኮር ለመመልከት እንሞክር።

የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ምንጭ ማርክሲዝም እና የማርክሲዝም መክሸፍ ናቸው።

ፖለቲካዊ ጽንፈኝነት በእሚለው የመጽሐፉ ምዕራፍ አንድ ንዑስ ላይ እንደ አየነው ፤ የማርክሲዝም ርዕዮት አንዱ አምድ የሆነው ቀኖና ፤ የታሪክ ቁሳዊነት (Historical Materialism) ነው። በእዚኽ የታሪክ ቁሳዊነት መሠረት ፤ የሰው ልጆች የማሕበረ ኢከነሚ (Political Economy) መዋቅር ፤ በጥንታዊ ጋርዮሽ ጀምሮ ከእዚያኽም ወደ ባሪያ አሳዳሪ ስረዓት ፥ ከባሪያ አሳዳሪ ስረዓት ወደ ፊውዳሊዝም ፥ ከፊውዳሊዝም ወደ ካፒታሊዝም ፣ ከካፒታሊዝም ወደ ሶሻሊዝም እና በስተመጨረሻ ወደ ከምኒዝም ነው እንደ እሚል ተመልክተናል።

በማርክሲዝም መሠረትም ይኽ ኺደት የእማይነቀነቅ ተፈጥሮዋዊ መሠረት ባለው የሙግት ቁሳዊነት (Dialectical Materialism) ውላጅ በሆነው የመደብ ትግል አስተውሎ የእሚመራ እና አማራጭ የሌለው ብቸኛው እና ሊለወጥ የእማይችለው የሰው ልጅ ፖለቲካዊ ዝግመት ታሪካዊ ትንታኔ ነው።

ይኽን የማርክስን የታሪክ ገለጻ ተቀብለው ፊውዳሊዝም በካፒታሊዝም ከተተካ በኋላ በካፒታሊስት ሰረዓት ውስጥ የአለው ቅጥረኛ በሥራ እጦት እና ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የደሞዝ ክፍያ ጉልበቱ እየተበዘዘ የድኃ ድኃ ስለ እሚሆን ፤ ሶሻሊስታዊ አብዮት ካፒታሊስታዊው ስረዓት ውስጥ ይመጣል ብለው ሲጠብቁ ፤ ነገሩ የተገላቢጢሽ ሆነና በካፒታሊስት ስረዓት ውስጥ የአለው ሠራተኛ በኑሮው ከግዜ ወደ ግዜ እየተሻሻለ እና በዴሞክራሲያዊ ስረዓት መብቱ ከግዜ ወደ ግዜ በስፋት እየተከበረ በመምጣቱ ፤ በቀጣሪዎችህ ላይ አምጽ የእሚለው የማርክሲዝም ውትወታ ፤ ጆሮ ሲያጣ ፤ ማርክሲስቶች የካፒታሊስቱ ሠራተኛ “ኃሳዊ የመደብ አስተውሎ false class consciousness” አዳብሯል ለእዚኽ ነው ከጥቅሙ በተጻራሪ ቆሞ ሶሻሊስታዊ አብዮት ለማስነሳት እምቢ የእሚለው ከአሉ በኋላ ፤ በማርክሲዝም መሠረት ሶሻሊስታዊ አብዮት በእማይቻልባቸው ወይንም ወደ ካፒታሊዝም የስልተ ምርት ላይ በአልደረሱ ሐገራት ፤ በቀኝ ግዛት እና በኢምፔሪያሊዝም አማካኝነት ከኋላ ቀርነት ወደ ካፒታሊስት ሐገርነት ከመሸጋገር እንደ አይዘገዩ ወይንም ጨንግፈው እንደ አይቀሩ ቅድመ ሶሻሊስታዊ አብዮት ያስፈልጋቸዋል የእሚል እና በካፒታሊስቱ ስረዓት ውስጥ ሶሻሊስታዊ አብዮት ይነሳል የእሚለውን እና የከሸፈውን የማርክስን ትንበያ አዲስ ተለዋጭ የአብዮት ተስፋ የእሚሰጠው ማሻሻያ አደረጉለት።

ይኽ ቅድመ ሶሻሊስታዊ አብዮት የእሚመጣው እና በእዚኽ ዘመን በማርክስ የታሪክ ቁሳዊነት ደረጃ መሠረት የካፒታሊስት ስረዓት ስልተ ምርት ላይ የአልደረሱ ሐገራት ፤ ወደ ካፒታሊስታዊ ስረዓት በፍጥነት እና በእርግጥ እንዲ ደርሱ የእሚደረገው አብዮት ነው እንግዲኽ ፤ አብዮታዊ ዴሞክራሲ።

ይኽን አብዮት የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሮዝደንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም ፤ ትግላችን በእሚለው መጽሐፋቸው ላይ እንደ እዚኽ ይገልጹታል ፦

“እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ ሐገሮች ማሕበራዊ ለውጥ ኺደት ይበጃል ተብሎ የታመነበትን የአዲሱን ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት መርህ በመከተል የሶሻሊስት አብዮት ለማካኼድ በእድገት ኋላ ቀርነት ምክንያት የተጓደሉትን ቅድመ ኹኔታዎች በኺደት ለሟሟላት እንዲቻል የተመራ ትግል ነው። [112]”

የተበረዘው ማርክሲዝም (ሌኒንዝም ወይንም ማዖይዝም) ይኽን የእሚለው ፤ እንደ ኢትዮጵያ የአሉ ኋላ ቀር ሐገራት ከሌሎቹ ሐገራት ዘግይተው የካፒታሊስታዊ ስረዓት ግንባታ ላይ የአልደረሱት ፤ በከፊል በውስጣዊ ስረዓታቸው መበስበስ እና የካፒታሊዝሙ ዓለም በቀኝ ግዛት እና በኢምፔሪያሊዝም አማካኝነት በእሚያደርስባቸው አሉታዊ ተጽኖ ነው ፤ በእሚል ነው።

ይኽ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ይዘቱ እንደ እየ ሐገራቱ ልዩ ኹኔታ የሚለያይ ቢሆንም ፤ በዋናነት ግን የእሚከተሉትን ዋና ዋና ችግሮች ለመንቀስ እና ለማስወገድ የእሚደረግ ትግል ነው ፦

  • ጸረ ኢምፔሪያሊዝም - ዓለም ዓቀፋዊ ይዘት የአላቸው ትልልቅ የንግድ ድርጅቶች ፖለቲካዊ ኃይልን ከሙስና ጋር በማያያዝ የሌሎች ሐገራትን አንጡራ ኃብት ለመበዝበዝ የእሚንቀሳቀሱበት አግባብ ማስወገድ
  • ጸረ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም - በዋናነት የኢምፔሪያሊስቶች አጎብዳጅ የሐገር ውስጥ መንግሥታዊ መዋቅር ለግላዊ ኢከነሚያዊ ጥቅም ሲል ሐገራዊ ሐብትን እና ክብርን አሳልፎ የእሚሰጥበትን አኳኋን ማስወገድ
  • ጸረ ኋላ ቀር ስረዓት - እንደ ፊውዳሊዝም ያሉ ኋላ ቀር እና ጨቋኝ ፖለቲካዊ ስረዓቶችን ማስወገድ
  • ጸረ ቀኝ ግዛት - ማንኛውንም ዓይነት የቀኝ ግዛት ማስወገድ

ከገለጻው ማየት እንደ እምንችለው አብዮታዊ ዴሞክራሲ መነሻው ማርክሲስታዊው ጎራ ቢሆንም ፤ ይዘቱ ከማርክሲዝም ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው እና በውስጥ የያዛቸው እንደ ጸረ ቀኝ ግዛት እና ኋላ ቀር ስረዓትን የማስወገድ ጉዳይ ዓለም ዓቀፍ እውቅና እና ተቀባይነት የአለው ጉዳይ ነው።

እውነታው ይኽ ቢሆንም ቅሉ ፤ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ተብሎ እና ዝርዝር ፕሮግራም እና እቅድ ተዘጋጅቶሎት ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የእሚካኼደው ፤ በዋናነት ከምኒስት ነን በእሚሉ የፖለቲካ ቡድናት ነው ። ለእዚኽም ፦ ማለትም ይኽ ከማርክሲዝም ጋር ይኽ ነው የእሚባል ልዩ የእሚያገናኘው ነገር የሌለው ፖለቲካዊ አካኼድ በዋናነት ማርክሲስት ወይንም ከምኒስት ነን በእሚሉ ፖለቲካዊ ቡድናት እንዲዘወተር የአደረገው ፤ በዋናነት የቀዝቃዛው ጦርነት ነው።

ይኽም ማለት እነ ሌኒን በራሺያ እ.አ.አ. 1918 ዓ.ም. ሶሻሊስታዊ አብዮት አካኼደን ከአሉ በኋላ ፤ ከፊል በማርክሲዝም ዓለም ዓቀፋዊነት ከፊል ደግሞ አብዮታቸው የመሠረተው መንግሥት የተፈጠረበትን ዘርፈ ብዙ የህልውና አደጋ[2] ለማስወገድ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በእየ ሐገሩ አብዮት እየቀሰቀሱ ፤ የእነርሱ አጎብዳጅ እና ተንጠልጣይ መንግሥት ማቆም ይፈልጉ ስለ ነበር ፤ በአንጻራዊነት ኋላ ቀር የሆነ ማሕበረሰባት ውስጥ የእሚገኙ ነቃ ያሉ ተማሪዎችን ፣ የመንግሥት ሰራተኞችን ፣ ወታደሮችን ፣ ወዘተ ፤ በእዚኽ “ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት” ወይንም “አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ” አስተሳሰብ እያጠመቁ ለአብዮተኝነት ይቀሰቅሱ ፣ ያነሳሱ ፣ ይመለምሉ ፣ ያግዙ ስለ ነበር ነው።

የምዕራቡ ዓለም ወይንም በዋናነት አሜሪካ ፤ በጸረ ቀኝ ግዛት ትግል ከዓለም ላይ የእሚቀድማት ማንም ሐገር የለም። በዓለማችን ላይ የመጀመሪያውን በሕዝባዊ መንግሥት አስተሳሰብ ፤ ማለትም
፦ በጸረ ቀኝ ግዛት ፣ በጸረ ኢምፕሪያሊዝም ፣ በጸረ ፊውዳሊዝም ፣ በጸረ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ፣ ወዘተ ፤ መርኽ የተቃኘ መንግሥት ለመመሥረት እውነተኛ ሕዝባዊ አብዮት በማድረግ እስካዘሬ ድረስ አቅሙ የአልደበዘዘ ሕዝባዊ መንግሥት በማቋቋም ከአሜሪካ የእሚወዳደር የለም።

ለእዚኽም አሜሪካ በሐገሯ ውስጥ የመጀመሪያውን እና ዓለም እንደ ምሳሌ የእሚያየውን የፀና ሕዝባዊ መንግሥት ከመመሥረቷ በአሻገር ፤ በመጀመሪያ ሊግ ኦፍ ኔሽንስ በኋላም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲመሠረት የአንበሳውን ድርሻ የተጫወተች መሆኗ ሊስተባበል የእማይችል ታሪካዊ ኃቅ ነው።

በእርግጥ አንድ ግዜ የቀዝቃዛው ጦርነት ከተፋፋመ በኋላ እና የሞስኮው ጂንጎይስት ከምኒዝም ፤ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሰበብ ብሶትን እያባባሰ ዓለምን የጦርነት አውድማ በማድረግ የካፒታሊዝምን መስፋፋት እገድባለኹ ብሎ ሲነሳ ፤ አሜሪካኖች ወይንም ምዕራቡ ዓለም ህልውናቸውን ለማስጠበቅ ፤ ማንኛውም የሆነ ጸረ ከውሚንዝም የሆነ መንግሥት ወይንም ትግል ወደ እሚደግፉበት ኹኔታ መጥተዋል።

ይኽም የአሜሪካ ምላሽም ይመስላል ፤ ከራሺያው ከምኒስታዊ ጂንጎይስት አስተሳሰብ እና ከሌሎች አንዳንድ ምክንያቶች ጋር ተዳብሎ ፤ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በሞስኮ ማዕከልነት የእሚመመራ በዋናነት የግራ ዘመሞች ወይንም ከምኒስት ነን የእሚሉ የፖለቲካ ኃይላት የትግል መመሪያ እንዲሆን የአደረገው።

ይኽን ዓይነት መነሻ እና ይዘት የአለው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይንም በአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ የእሚመራ አብዮት ፤ በ20ኛዋ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ የእሚያስፈልግ አብዮት ግን አልነበረም ወይንም ይኽን መሰል አብዮት ግድ የእሚል ፖለቲካዊ ምህዳር በ20ኛው ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ ውስጥ አልነበረም ።

ቀደም በአሉት የታሪካችን ክፍል እንደ ቃኘነው በቀኝ ግዛት እና በኢምፔሪያሊዝም አደጋ ኢትዮጵያ ከ10ኛው ምዕተ ዓመት አንስታ ስትናወጥ የቆየች ቢሆንም ፤ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ከአጼ ቴውድሮስ አንስቶ ፣ አጼ ዮሐንስ እና አጼ ምንሊክ ፤ በዘመናዊ ፖለቲካዊ ሳይንስ አስተሳሰብ በአይመሩም በታሪካዊው የኢትዮጵያ አርበኝነት ፤ በተከታታይ በአደረጉት ትግል ፤ ቀኝ ግዛትን ፣ ኢምፔሪያሊዝምን ፣ ከእነ እዚኽም አደጋዎች የእሚመነጨውን ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ፤ ድንበር ላይ መክተው ለማቆም የተሳካ ሥራ መሥራት ችለዋል።

ለእዛም ነው ፤ ቀኝ ግዛት ዓለምን በአጥለቀለቀበት በእዚኽ ሰዓት ፤ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ምን አልባት ብቸኛ የእሚያደርጋትን ፤ ከ2 ሺ ዓመታ በላይ የቆየውን አስተዳደራዊ ነጻነቷን ጠብቃ መቆየት የቻለቸው።

ኃይለ ሥላሴ ከአጼ ምንሊክ የተረከቧት ኢትዮጵያ ፤ የመጣው የቀኝ ግዛት ሱናሚ ኤርትራን ቢቀማቸውም ፤ የዓለማችንን ታላላቅ ቀኝ ገዢዎች ፦ ብሪታኒያ ፣ ፈርንሳይ ፣ ጣሊያን ፤ ድንበር ላይ ገትራ የአቆመች እና እየተለወጠ በመጣው የዓለም ዓቀፉ ፖለቲካዊ ድባብ ፤ የመጀመሪያው የዓለማችንን የነጻ ሐገሮችን የእርስ በእርስ ግንኙነት በሕግ አግባብ እንዲመራ ግድ የእሚለው ሊግ ኦፍ ኔሽንስ ሲቋቋም ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ነጻነቷ እውቅና ተስጥቶት የሊጉ አባል ከሆኑ ፤ በአፍሪካዊያን የእምትመራ ብቸኛ እና ቀዳሚ አፍሪካዊት ሐገር ሆናለች።

ላይቤሪያና እና ደቡብ አፍሪካ በእዚያኽ ወቅት የሊግ ኦፍ ኔሽንስ አባል ቢሆኑም ፤ ደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ ስር የነበረች እና በወቅቱ ቀኝ ግዛት ተብላ መገለጽ የእምትችል እና ላይቤሪያ ከአሜሪካ በተመለሱ ጥቁሮች ሰፈራ የተመሠረተች ፤ የዳግም ኮሎናይዜሽን ሐገር በመሆኗ ፤ እውነተኛ አፍሪካ በቀል ፤ ነጻ የሊግ ኦፍ ኔሽንስ የመጀመሪያዋ ሐገር ኢትዮጵያ ነች በእኔ እምነት ።

ምንም እንኳን ከእዚያኽ በኋላ ለአስምስት ዓመት የቆየው የጣሊያን ወረራ ቢከሰትም ይኽም ቢሆን በሐገር ውስጥ ተጋድሎ እና በዓለም ዓቀፍ ወዳጅ ሐገራት እገዛ ተግፎ ፤ ከእዚያኽ በኋላ ፤ ኢትዮጵያ ከፋም ለማም በሕገመንግሥት የእሚመራ ዘውዳዊ እና ኢትዮጵያዊ መንግሥት የአላ፟ት ፣ ከተነሳችበት አንጻር በጣም ዘመናዊ የእሚባል 40 ሺ ወታደር የአለው ፤ በዘመናዊ ታንኮች እና ሌሎች ከፍተኛ መሳሪያዎች የታጠቀ ፤የእራሱ አየር ኃይል የአለው ፤ በብዙ ዘመናዊ የውትድርና ሳይንስ አዋቂዎች ፤ የሐገሪቱን የውስጥ እና የአጎራባች የጸጥታ ስጋቶች መመከት የእሚችል መከላከያ ሠራዊት ፣ ፖለቲካዊ እና ማሕበራዊ መዋቅሯን በእየግዜው እያሻሻለች ያለች (ዘገምተኛ ቢሆንም) ፣ በዓለም ዓቀፍ ትብብር በእየ ሐገሩ የእራሷ ዲፕሎማቶች የአስቀመጠች ፣ ወዘተ ፤ ሐገር በመሆኗ ሕይወት ቀጣይ የመሻሻል ኺደት በመሆኑ እና ዓለም ከደረሰበት ደረጃ ኢትዮጵያ ብዙ ክፍተት የነበረባት ሐገር ብትሆንም ፤ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ1940 ዓ.ም. በኋላ ፤ የቀኝ ግዛት ፣ የኢምፔሪያሊዝም ፣ የቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ፣ የፊውዳሊዝም ፣ ወዘተ ፤ ስጋት የአለባት ሐገር የእምትባል አልነበረችም።

እንዲያውም በእዚኽ ግዜ ፤ ኢትዮጵያ በቀኝ ግዛት የተነጠቀችውን ኤርትራ ፤ በዴፕሎማሲያዊ አቅም መልሳ የአገኘችበት ወቅት በመሆኑ ፤ ኢትዮጵያ በእዚኽ ወቅት በፍጹም በቀኝ ግዛት ፣ በኢምፔሪያሊዝም ፣ በቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ፣ በፊውዳሊዝም ፣ ወዘተ ፤ የህልውና ስጋት የተጋረጣባት ወይንም እነ እዚኽ ነገሮች ፤ ሐገሪቱ ወደ ካፒታሊስቱ ስረዓት የእምታደርገውን ግስጋሴ የአለ አግባብ የአዘገዩባት ልትባል የእምትችል ሐገር አልነበረችም።

በአጭሩ ኢትዮጵያ በእዚኽ ወቅት ፣ ቻይና ፣ ቪየትናም ፣ ደቡብ አፍሪካ ወይንም መሰል ሐገራት ጋር ልትመሳሰል የእሚገባት አልነበረችም።

አብዮታዊ ዴሞክራሲን ከማርክሲስታዊ የቃላት ትብትቦቹ ከአላቀቅነው (Without its Marxian Jargons) ብሔርተኝነት ማለት ነው። ብሔርተኝነት ስንል ሕወሐት/ኢሕአዴግ አጥብቦ በአቀረበው ነገዳዊ ብሔርተኝነት (Ethnonationalism) ሰአይሆን ፤ የሐገርን ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ሕልውና ማስቀደም የእሚለው ወይንም ሐገራዊ የሆነው ብሔርተኝነት ማለት ነው።

በቀላል ቋንቋ ፤ በኢትዮጵያ አውድ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የደርግ “ኢትዮጵያ ትቅደም” ወይንም በእንግሊዘኛው “Ethiopia First” ማለት ነው።

ይኽም የእሚሆንበት ምክንያት ከእላይ እንደ አልነው ፤ የማርክስ የታሪክ ቁሳዊነት የእሚገልጸው የሶሻሊስታዊ አብዮት የእሚሰራ ከሆነ የእሚሰራው መጀመሪያ አንዲት ሐገር ስትኖር እና በኋላ ቀርነት ረመጥ ውስጥ ከአዘቀጣት ማሕበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ወጥታ የካፒታሊስት ስረዓት የገነባች እንደ ሆነ ነው ፤ ይኽም በመሆኑ ፤ እንደ ኢትዮጵያ የአሉ ኋላ ቀር ሐገራት ማርክስ የእሚገልጸው የሶሻሊስት አብዮት (ከካፒታሊስታዊ ስልተ ምርት ወደ ሶሻሊስታዊ ስልተ ምርት የእሚያሸጋግረው በሠራተኛው የእሚመራው አብዮት) ከመደረጉ በፊት ፤ ሐገሪቱ እንደ ሐገር ጠንካራ መንግሥት ገንብታ ፤ ከኋላ ቀር ስረዓት እና ከዓለም ዓቀፍ አደጋ ተላቃ ማሕበረ ኢከነሚዋን መገንባት አለባት ማለት በመሆኑ ነው።

አንድነቷ የተጠበቀ ጠንካራ ሐገር ከሌለች የካፒታሊስት ስረዓት ሊገነባ አይችልም ፤ የካፒታሊስት ስረዓት ከአልተገነባ ደግሞ የሶሻሊስት አብዮት ሊኖር አይችልም ፤ ምክንያቱም ካፒታሊዝም ላይ መድረስ የሶሻሊስት አብዮት ቅድመ ኹኔታ በመሆኑ ።

ይኽም ቅደም ተከተል ነው በካፒታሊስቱ ስረዓት ውስጥ የሠራተኛው ወይንም ሶሻሊስታዊ አብዮት ይነሳል የእሚለው ማርክሲስታዊ ትንቢት የከሸፈበት ማርክሲስታዊውን ጎራ ፤ መጀመሪያ ሐገር ወይንም በኢትዮጵያ አውድ “ኢትዮጵያ ትቅደምን” የአመጣው።

በሌላ አገላለጽ ፤ “ማርክሲዝም እያልኽ ከመቀባጠርኽ በፊት መጀመሪያ ካፒታሊስት ኹን” የእሚል የጨዋ መወረፍ ነው ፤ አብዮታዊ ዴሞክራሲ።

ከእላይ እንደ አልኹት ግን በኢትዮጵያ ኹኔታ ፤ በ20ኛው ምዕተ ዓመት ፤ በኢትዮጵያ ላይ በቀኝ ግዛት ፣ በኢምፔሪያሊዝም ፣ በቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ፣ በፊውዳሊዝም ፣ ወዘተ ፤ የተጋረጠ እና ኢትዮጵያን እንደ ኢትዮጵያ ሊያሟሟት ወይንም ሊያከስማት ነው ሊባል የእሚችል አደጋ አልነበረም።

ይኽ አባባል ልክ እንደ ሆነ የበለጠ ለማጠናከር ፤ የእኛ ሐገር የወቅቱ አብዮተኞች በተደረገባቸው ቅስቀሳ ምክንያት የጨለማ መብራታችን ናቸው እያሉ እንደ ትልቅ ተምሳሌት ያዩዋቸው ከነበሩ እና በእዚያኽ ወቅት ዜና ከነበሩ ከቻይና ፣ ከቪየትናም እና ከደቡብ አፍሪካ የወቅቱ የፖለቲካ ኹኔታ አኳያ እንየው።

ከምኒስት ነኝ ብሎ በአደረገው ትግል እና በአስመዘገበው ድል በስሙ የተሰየመ አንድ የማርክሲዝም ዘውግ የተሰጠው የቻይናው ማዖ ፤ ቻይና መጀመሪያ ወይንም ቻይና ትቅደም የእሚል አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፕሮግራም እንዲይዝ የእሚያስገድደው ፖለቲካዊ ኹኔታ ነበር።

በእዚኽ ረገድ ሐገሩን ቻይናን በዘውዳዊ ስረዓት ከ300 ዓመታት በላይ የገዛው የኪንግ (Qing) ስርወ መንግሥት በተከተለው ኋላ ቀር ፖሊሲ ምክንያት እንደ ኢስት ኢንዲየስ ለአሉት ኢምፔራሊስታዊ ዓለም ዓቀፍ የንግድ ሸሪኮች ተሸንፎ ቻይናን ኢፍትኃዊ በሆነ መልኩ ለተለያዩ የንግድ ሽርክናዎች ከፋፍሎ እንዲሰጥ የተገደደበት ኹኔታ ፤ ኮንሴሽን የእሚባል ኢፍታኃዊ የንግድ እና የሰፈራ መብት የተሰጣቸው ዓለም ዓቀፍ የንግድ ተቋማት ቻይናን የተከፋፈሉበት ፣ ኦፕየም ጦርነት በእሚለው ተሸንፎ ሆንግ ኮንግ የመሰሉ የቻይና አካል አከባቢዎችን በቋሚነት ለብሪታኒያ እንዲሰጥ የተገደደበት ፣ ወዘተ ፣ ኹኔታ ነበር።

በ20ኛው ምዕተ ዓመት መጀመሪያዎች ላይ ይኽንንም ስርወ መንግሥት በአብዮት አስወግዶ እና የተለያዩ ባላንጣ መሳፍንቶችን አሸንፎ ሐገሪቱን በአንድ አስተዳደር ስር አድርጎ ወደ ሪፐብሊክነት የቀየራት ኩውሚንታንግ (Kuomintang) ወይንም “ብሔርተኛው (የቻይና) ፓርቲ)” በጣም ደካማ የነበረ እና የኢምፔርሊያዝሙንም ሆነ እያቆጠቆጠ የመጣውን እና የጎሪላ ጦርነት የጀመረውን የከምኒስት ፓርት ማሳደብ የአልቻለ የነበረ ነው።

ቻይና በእዚኽ መልኩ በውስጣዊ ኋላ ቀርነት እና በአሉታዊ ዓለም ዓቀፋዊ ኢምፔሪያሊዝም ተጽኖ ስር እያለች ፤ ጎረቤቷ እና የቻይና 1/10ኛ የሕዝብ ቁጥር የአላ፟ት ጃፓን ፤ ታይዋን እና ማንቹሪያ የመሳሰሉ የቻይናን ግዛቶች በኃይል ከመያዝ አልፋ ፤ መላው ቻይናን በአሰቃቂ መንገድ ወራ ቻይናን ቀኝ ግዛቷ የአደረገችበት ኹኔታ ነበር።

የጃፓንን ቀኝ ግዛት ለመቀልበስ የከምኒስት ፓርቲው ፤ ከኮውሚንታንግ (Kuomintang) ፓርቲው ጋር የጋራ ግንባር ፈጥሮ የቀኝ ግዛቱን በጋራ መቀልበስ ቢችሉም ፤ ከውሚንታንጉ በተለያዩ የውጭ ሐገር ኃይላት ቀስቃሽነት ፤ ለጸረ ቀኝ ግዛት ትግሉ ግንባር የፈጠረውን የከምኒስት ጦር ፤ ትጥቅ ማስፈታት ፣ ማሰር እና መረሸን በመጀመሩ ፤ የከምኒስት ፓርቲው ራሱን ለማዳን በድጋሚ የእርስ በእርስ ጦርነቱን መጀመር ነበረበት ።

ይኽም በመሆኑ ፤ የቻይናው ከምኒስት ነኝ የአለው ማዖ ፤ ስለ ከምኒዝም ከማውራቱ በፊት ሐገሩን ከቀኝ ግዛት ፣ ከኢምፔሪያሊዝም እና ከአዝግ ፊውዳሊዝም ማላቀቅ ግድ ስለ ሆነበት እና ይኽንን የቻይና ብሔርተኝነት ስሜቱን የእሚወክልለት ማርክሲስታዊ ትንታኔ በአለመኖሩ ፤ ማርክሲስት ነኝ ነገር ግን በቻይና ኹኔታ ስለ ማርክሲዝም ከማውራቴ በፊት ፤ ብሔራዊ/ሕዝባዊ አብዮት በማስነሳት ጸረ ቀኝ ግዛት ፣ ጸረ ኢምፔሪያሊዝም ፣ ጸረ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም እና ጸረ ፊውዳሊዝም ትግል በቻይና ማደረግ አለብኝ የእሚል ሆነ።

ይኽም ኹኔታ ፤ የቻይናው ከምኒስት ፓርቲ ከምኒስት ከመሆኔ በፊት ብሔርተኛ (የቻይና) መሆን እና መጀመሪያ አንዲትን ከአሉታዊ የውጭ ተጽኖ ነጻ የወጣችን እና በጠንካራ መዓከላዊ ብሔራዊ አስተዳደር ስር የሆነች ቻይናን ለመፍጠር የትጥቅ ትግልም ቢሆን እንዲያደርግ የእሚያስገድደው እናቱ ላይ የተደቀነ የጸረ ቻይና አፈሙዝ ነበር።

እንደ እዚኹም የቪይቴናምን ኹኔታ የተመለከትን እንደ ሆን ፤ ምንም እንኳን የቬይትናም ሕዝብ የራሱ ዘውዳዊ ስረዓት በማቋቋም ቢጀምርም ፤ ከ2 ሺ በላይ የሆነውን የታሪኩን ረጅሙን ዘመን ፤ በቻይና ፣ በፈረንሳይ እና በጃፓን የቀኝ ግዛት ስር የቆየ ነው።

በ19ኛው ምዕተ ዓመት የወቅቱ የቪይትናም አስተዳደር እና ባሕላዊ እምነት ለሚስዮናዊ አገልግሎት በመጡ እና በእነርሱ ሚስዮን ምክንያት ወደ ክርስትና እምነት የመጡ ቬትናማዊያን ላይ የእሚያደርሰውን በደል ለማስቀረት የመጣው የፈረንሳይ ጦር ፤ እራሱን የቬይትናም ቀኝ ገዢ አድርጎ ለውጦ ቪየትናም በፈረንሳይ ቀኝ ግዛት ስር እንድትገባ የአደረገ ነበር።

እንደ ገና በእዚያኽ አከባቢ በተደረገ የአከባቢው ኃያላን ጦርነት ፤ ጃፓን ጦሯን ቪየትናም የእምታሰፍርበት ኹኔታ ሲፈጠር ፤ ፈረንሳይ መንግሥታዊ አስተዳደሩን ልትይዝ እና ጃፓን ጸጥታውን የማረጋጋት ሥራ እንድትሰራ በመስማማታቸው ፤ ጃፓኖች ጸጥታውን ለማስከበር በአመጡት ወታደር ፤ የቬትናምን ብሔራዊ ነጻነት ከመግፈፍ አልፈው ፤ የሐገሪቱን የተፈጥሮ ኃብት እያጋዙ የእሚሸጡበት ኹኔታ ነበር።

እነ እዚኽ ኹኔታዎች በቪየትናም ፤ የቪየትናም ብሔራዊ ፓርቲ ወይንም የቪየትናምን ብሔራዊ ነጻነት የማስመለስ ትግል የእሚመራ የሽምቅ ውጊያ መሪ ፓርቲ እንዲፈጠር አደረገ። ከእዚኽም በኋላ በእዚኽ የብሔራዊ ነጻነት ታጋይ ፓርቲ ውስጥ አለመግባባት ሲፈጠር ፤ ሆ ቺሚኒ ከእዚኽ ፓርቲ በመውጣት ከምኒስታዊ የሆነ ነገር ግን አንዲት ብሔራዊ ቪየትናምን ማረጋገጥ ግቡ የአደረገ ቪየትሚንህ (Viet Minh) የእሚባል ፓርቲ ወይንም በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የእሚመራ ፓርቲ አቋቋመ።

የቪየትናም የጸጥታ ኃላፊ የነበረችው ጃፓን በኹለተኛው የዓለም ጦርነት ስትሸነፍ እና ከጦርነቱ ስትወጣ በመላው ቬየትናም ኹከት በመበራከቱ ፤ የኹለተኛው ዓለም ጦርነት አሸናፊዎች ፤ ምንም እንኳን ቪየትናም የፈረንሳይ ቀኝ ብትሆንም ለግዜው ፤ ሰሜናዊ ቬየትናም በቻይና ደቡባዊ ቪየትናም ደግሞ በብሪትሽ ስር ትኹን ቢሉም ፤ የሆ ችሚኒው ቪየት ሚንህ የተፈጠረውን ክፍተት ተጠቅሞ ሰሜናዊ ቪየትናምን ተቆጣጥሮ የቪየትናምን ነጻነት አወጀ።

ይኽም በቪየትናም እ.አ.አ. ከ1945 እስከ 1954 ዓ.ም. የቆየ ጦርነትን ቀስቅሶ ፈረንሳይ በኹለተኛው የዓለም ጦርነት በጀርመን ወረራ በደረሳባት ጉዳት ምክንያት የቪየትናሙን ጦርነት ልታስቀጥል ስላልቻለች ፤ ሆ ቺሜኒ የኃይል ሚዛኑ ወደ እርሱ ስለ አጋደለ ፤ ኹኔታው በሰላም በእርቅ እንዲቋጭ እና ፈረንሳይ በኢንዶቻይና (ቪየትናም) የአላት ቀኝ ግዛት እንዲቆም ፤ ሆ ቺሜኒ ሰሜናዊ ቪየትናምን እንደ ያዘ እንዲቆይ ፤ የቀረው በፈረንሳይ ስር የነበረው የቪየትናም አካል ፤ ደቡባዊ ቪየትናም ፣ ካምቦዲያ እና ሌዑስ ተብሎ እንዲከፋፈል ተደረገ ፤ ደቡባዊ ቬየትናም እና ሰሜናዊ ቪየትናም በአንድ አስተዳደር ስር ከሕዝባዊ ምርጫ በኋላ ይመጣሉ በእሚል።

ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት አንስቶ በጀመረው የቀዝቃዛው ጦርነት ምክንያት ፤ መላው ቬየትናም በከምኒስት አስተዳደር ስር ከወደቀች ፤ ከምኒዝም በካምቦዲያ ፣ ሌዑስ ፣ ወዘተ ፤ ይስፋፋል ብለው በመፍራት በእሚመስል ፤ ቃል የተገባለት እና ቬትናምን አዋህዶ አንዲት እና ሉዓላዊት ቪየትናምን ይፈጥራል የተባለው ምርጫ ሳይደረግ ፤ በደቡባዊ ቪየትናም መፈንቅለ መንግሥት ተደረገ ተብሎ ፤ በደቡባዊ ቪየትናም በምዕራባዊያን የእሚደገፈው አዲስ መንግሥት ተቋቋመ ፤ አሜሪካም የእዚኽ መንግሥት ደጋፊ ሆነች ።

አንዲት ነጻ ብሔራዊት ቪየትናምን መመሥረት ግቡ የአደረገው እና ሰሜናዊ ቪየትናምን የተቆጣጠረው ሆ ቺሜኒ ይኽን ሕገ ወጥ የአለውን ደቡባዊ መንግሥት ፤ የአንዲት ነጻ ብሔራዊት ቪየትናም ጠላት በእሚል ጦርነት ስለ አወጀበት ፤ በወቅቱ ከምንም በፊት ጸረ ከምኒዝም የሆነው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ፤ ቪየትናም በከምኒዝም ስር እንደ አትወድቅ ሲል ፤ ይኽንን ደቡባዊ መንግሥት ለማገዝ በእሚያደርገው ጦርነት ተስቦ ፤ ከሆ ቺሚኒ ጋር ጦርነት የገባበት ኹኔታ ተፈጠረ።

ይኽም በመሆኑ የቪየትናሙ ሆ ቺምን ፤ የነበረበት ፖለቲካዊ ምህዳር ፤ ለሐገሩ ብሔራዊ አንድነት ሲል እና አምንበታለኹ በእሚለው ከምኒስታዊ ፍልስፍና ምክንያት የተጋረጠበትን አደጋ ለመጋፈጥ ፤ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የእሚመራ ወይንም “ቬትናም መጀመሪያ ወይንም ቬትናም ትቅደም” በእሚል የእሚመራ ትግል እንዲያደርግ ግድ የእሚለው ወይንም የህልውናው ስጋት የሆነ የአሉታዊ ኢምፔሪያሊዝም ፣ የቀኝ ግዛት እና ባንዳ የሆነ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም (መንግሥታዊ ሙሰኝነት) አናቱ ላይ የተደቀነ አፈሙዝ ነበር ማለት ይቻላል ፤ ምንም እንኳን ይኽ አደጋ በዋናነት ፤ ለነጻ እና ሉዓላዊ ቪየትናም ከመታገሉ ይልቅ ከምኒስት በመሆኑ የተደቀነበት ቢሆንም።

ደቡብ አፍሪካ ፤ እንደ ቻይና እና ቬትናም ላቅ የአለ፟ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ በአይኖራትም ፤ በቀኝ ግዛት የተመሠረተችው ደቡብ አፍሪካ ፤ ከልማዳዊ ቀኝ ግዛት በተለየ ኹኔታ ቀኝ ገዢ የነበሩት መሪዎቿ ፤ መነሻ ሐገራቸውን በመተው ወይንም ራሳቸውን ከፖለቲካዊ እናት ሐገራቸው በመነጠል ራሳቸውን ደቡብ አፍሪካዊ የአደረጉበት እና በእዚኽ በመሠረቱት ደቡብ አፍሪካ በእሚባል ሐገር ውስጥ ነዋሪ የነበረውን ሕዝብ ፤ አፓርታይድ የእሚባል ስረዓት ዘርግተው ከገዥዎቹ ማሕበረሰብ (ከነጩ) በፖለቲካው ፣ በኢከነሚው እና በማሕበራዊ መንገድ ነጥለው በድህነት ፣ በኋላ ቀርነት እና በጭቆና ቀንበር ውስጥ የአኖሩበት ኹኔታ ስለነበር የነበረው ፤ ከእዚኽም በአሻገር ይኽ አፓርታይድ ስረዓትን የዘረጋ መንግሥት ፤ ከነጮቹ የደቡብ አፍሪካዊያን አንጻር ዴሞክራሲያዊ እና የነጻ ገበያ ስረዓት አራማጅ በመሆኑ ፤ የአፍሪካው ብሔራዊ ኮንግረስ ፤ በከምኒዝም ከማመን በአለፈ ፤ መሬት ላይ በአለው ፖለቲካዊ ምሕዳር ፤ ጸረ ኢምፔሪያሊዝም ፣ ጸረ ቀኝ ግዛት ወይንም በደቡብ አፍሪካ ልዩ ኹኔታ ፤ ጸረ አፓርታይድ ትግል እንዲያደርግ ግድ የእሚለው ፤ በአናቱ ላይ የተደቀነ የህልውና አደጋ አፈሙዝ አለ።

ስንጠቀልለውም እነ እዚኽ ሦሥት ሐገራት ወስጥ የተስተዋሉት በዋናነት ከምኒዝም መመሪያችን ነው የእሚሉ የብሔራዊ (ሐገራዊ) ነጻነት ታጋዮች ፤ በማርክሲስታዊ የታሪክ ቁሳዊነት ትንታኔ መሠረት ፤ ከካፒታሊዝም ወደ ሶሻሊዝም በሶሻሊስታዊ አብዮት ከመሸጋገራችን በፊት መጀመሪያ ለሶሻሊስታዊ አብዮት ምሕዳር የሆነችው እና የካፒታሊዝም ስረዓት ሊገነባ የእሚችልባት ብቸኛው ሕዋስ ፤ አንዲት ብሔራዊ ሐገር መጀመሪያ መረጋገጥ አለባት ብለው ፤ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት (ምንም ብለው ይሰይሙት ፣ ለምንም ምክንያት ብለው ይሰይሙት ብዙም ትርጉም የለውም) የማድረግ መሬት የአለው ፖለቲካዊ ኹኔታ ግድ ይላቸዋል።

ከእላይ እንደ አይነው ግን ፤ በ1960ዎቹ በኢትዮጵያ ከእነ እዚኽ ሐገራት ጋር የእሚነጻጸር ምንም ዓይነት ችግር በኢትዮጵያ የአልነበረ በመሆኑ ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ኢትዮጵያን እናድን ፥ ኢትዮጵያ ትቅደም ወይንም መጀመሪያ ኢትዮጵያ የእሚያስብል የቀኝ ግዛት ፣ የኢምፔሪያሊዝም ፣ የቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም አደጋ በአለመኖሩ ፤ ይኽን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግድ የእሚል ፖለቲካዊ ምህዳር አልነበረም።

በእዚኽ መጽሐፍ ለማስቀመጥ እንደ ተሞከረው ፤ ኢትዮጵያ የዘመናት የሕዝባዊ መንግሥት ትልሟ እንኳን በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ይቅርና አኹንም የአልተሳካ እና ይኽም የኢትዮጵያ ዋነኛ ችግር መሆኑ እንደ ተጠበቀ ሆኖ ፤ በ1960ዎቹ ኢትዮጵያ ፤ “ኢትዮጵያ ትቅደም” የእሚያስብል የቀኝ ግዛት ፣ የኢምፔሪያሊዝም ፣ የቢሮክራሲያዊ ካፒታሊስም አደጋ ብቻ ሳይሆን የሌለባት ፤ መንግሥት ራሱ ፊውዳላዊውን ስረዓት መታገል የጀመረበትም ኹኔታ ነው የነበረው።

በእዚያኽን ወቅት ኢትዮጵያ ፊውዳላዊት ስረዓት የአለባት ሐገር ተብላ ልትገለጽ የእምትችል ቢሆንም ፤ የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ይኽንን ፊውዳላዊ ስረዓት ፤ ከአብዮቱ እጅግ ቀደም ብሎ በ1950ዎቹ በአዋጅ ሽሮታል። ይኽን ኹኔታ የሕወሐት መሥራች ከሆኑት ሰዎች አንዱ የሆነው አረጋዊ በርኼ እንዲኽ ይነግረናል ፦

“ማንኛውም ባለ ጉልት በጉልት በተሰጠው ቦታ ላይ ከእሚኖሩ ነዋሪዎች (ጭሰኞች) የጉልበት ሥራ እና የስጦታ ግብር መጠየቅ ይችላል። የዘውድ ስረዓቱ በ1966 ሲወድቅ ፤ በ1950ዎቹ ይኽ ስረዓት በአጼ ኃይለ ሥላሴ የተሻረ በመሆኑ ፤ የስረዓቱ አንዳንድ ቅሪቶች እና የቤተክህነት ጉልት ብቻ ነበር የነበረው።“

“Any gulti holder had the right to demand services and expect gifts from the peasants on that land. This system was abolished in the 1960s by the late Emperor Haile Selassie, but vestiges remained in isolated cases, only church gulti existed at the time of the collapse of the Emperor’s reign in 1974. [124]”

እውነታው ይኼ ቢሆንም ፤ አንዳንድ አላዋቂዎች ፤ የነብርን ጭራ አይዙ ከያዙም አይለቁ በእሚል ፤ አንድ ግዜ ፖለቲካ ውስጥ ገብቻለኹ በእሚል ፤ የተነሱበት ሰባራ ፖለቲካዊ ትንታኔ ከንቱ ሲሆንባቸው ፤ ፖለቲካዊ ህልውናቸውን ለማስቀጠል ፤ የኢትዮጵያ ኹኔታ አብዮታዊ ዴሞክራሲን የእሚጋብዝ አለመሆኑ በእየ አደባባዩ የተቃውሞ ውርጅብኝ ሲያስወርድባቸው ፤ በቀኝ ግዛት እና በፊውዳላዊ ስረዓት መካከል የአለው ልዩነት ራሱ ጠፍቶባቸው ፤ ሌኒን ስለ ራሻ የተናገረውን ቀድተው (ኮርጀው) ኢትዮጵያ የነገዶች እስር ቤት ነች እንደ አሉት ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ቀኝ የተገዙ ነገዶች አሉ ኹሉ እስከ ማለት ስለ ደረሱ ፤ አብዮታዊ ዴሞክራቶቹ ፤ የአለ አግባብ በኢትዮጵያ ኹኔታ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግድ ነበር ቢሉ ብዙም አይገርምም ።

አብዮታዊ ዴሞክራሲን በሕወሐት እና በጠቅላላው በኢትዮጵያ የተደረገው አብዮት መመሪያ አድርገን በእዚኽ መልኩ ከአስቀመጥነው ፤ ለብዙዎች ጥያቄ ሊሆን የእሚችለው ጉዳይ ፤ ኹሉም የወቅቱ የኢትዮጵያ አብዮተኞች በእዚኽ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፕሮግራም የእሚመሩ ከሆኑ ፤ በመሐከላቸው የነበረው ያ የብዙ ሰዎችን ደም ያፈሰሰው መጠፋፋት ከየት ሊመጣ ቻለ የእሚለው ይመስለኛል።

ለእዚኽ መልሱ ፤ በመካከላቸው ካለው የስልጣን ሽሚያ እና በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፕሮግራም ላይ ከአላቸው የግንዛቤ ብዥታ በተጨማሪ ፤ በዝርዝር እና አንዳንዴም ጥቃቅን ልዩነቶች ምክንያት ነው።

ለምሳሌ ፦ ኢሕአፓ ልከ እንደ ሕወሐት ኹሉ ፤ የዴሞክራሲያዊ አብዮቱ ወይንም አብዮታዊ ዴሞክራሲው ፤ የነገዶች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል ማክበርን ፤ ከጸረ ኢምፔሪያሊዝም ፣ ጸረ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ጋር አብሮ ማካተት አለበት ብሎ የእሚያምን ነው። አረጋዊ በርኼ ፤ የሕወሐት መሥራች ፣ ለረዥም ግዜ ግንባሩ ውስጥ በከፍተኛ አመራርነት የቆየ እና የአንድ ወቅት የግንባሩ መሪ ይኽን ይላል ፦

“በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) እና በሕወሐት ውስጥ የነበሩት ዋና ዋና መሪዎች የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ቁጥቋጦዎች ናቸው። ፖለቲካዊ ቋንቋቸውም ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ የሆነ ማርክሲስታዊውን ቀኖና የእሚከተል እና ኹለቱም “የብሔሮች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል” የእሚቀበሉ እና በተመሳሳይም ለሶሻሊስታዊ ሽግግር የእሚጮኹ ናቸው። ለኹለቱም ቡድኖች ፤ ኢትዮጵያ መብታቸው በዴሞክራሲያዊ አግባብ መከበር ያለባቸው የተለያዩ ብሔረሰቦች እስር ቤት ነች[3]። ይኽንንም ግብ ለማሳካት ፤ ኢሕአፓ በአንድ ፓርቲ ፥ ማለትም በእርሱ ስር የጋራ ትግሉ መመራት አለበት ሲል ፤ ሕወሐት በበኩሉ ትግሉ በተናጠል በእየ ነገዱ መደረግ አለበት በማለቱ ነው የእሚለያዩት።”

“Leading elements in both the Ethiopian People’s Revolutionary Party (EPRP) and TPLF were off-shoots of the Ethiopian student movement. Their political language was more or less the same Marxist rhetoric, both advocating ‘the right of nations to self-determination including and up to secession’, at the same time crying for socialist transformation. To both groups, Ethiopia was a prison of numerous nationalities whose freedom could be attained in a democratic Ethiopia. To achieve this objective, the EPRP sought first a unity of struggle under its party, while the TPLF gave primacy to the components of the whole. [124]”

ይኽም ማለት ሕወሐት እና ኢሕአፓ ልክ እንደ መኢሶን ፣ ደርግ ፣ ወዝሊግ ፣ ወዘተ ፤ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊያን ከመሆንም በአሻገር ፤ ለምሳሌ ፦ ከደርግ በተለየ ፤ በነገድ ጉዳይ አንድ ዓይነት አቋም ሲኖራቸው ፤ የእሚለያዩት ዴሞክራሲያዊ አብዮቱ ወይንም አብዮታዊ ዴሞክራሲው መካኼድ የአለበት በተናጠል በእያንዳንዱ ነገድ ተደርጎ ነው በኋላ ላይ ወደ አንድነት መምጣት የአለበት (ሕወሐት) እና የለም ሲጀምርም የተናጠል ትግል በአንድ ሐገር ዓቀፍ ሶሻሊስታዊ ፓርቲ መመራት ነው የአለበት (ኢሕአፓ) በእሚል ብቻ ነው።

ሕወሐት የነገድ ግንባሮቹ በተናጠል ተመስርተው ከአበቁ በኋላ ነው ኢሕአዴግ የእሚሆኑት ሲል ፤ ኢሕአፓ የለም ኢሕአፓ ብለው ጀምረው ነው በእርሱ ውስጥ መፈልፈል የአለባቸው አለ። በአጭሩ ታክቲካዊ ወይንም ለድል የእሚያበቃው አካኼድ የቱ ነው በእሚለው ጉዳይ ላይ መለያየት እንጂ የፖለቲካ ፕሮግራም ልዩነት የላቸውም።

ስለ እዚኽ ፦ ሕወሐት አብዮታዊ ዴሞክራት በመሆኑ ወይንም ኢትዮጵያ ኢምፔሪያሊዝም ፣ ቀኝ ግዛት ፣ ንዑስ ከበርቴ ፣ ፊውዳሊዝም ፣ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ፣ ነገዳዊ ቅራኔ የእሚባሉ ችግሮች ተደራርቦው በኋላ ቀርነት ረመጥ ውስጥ ሊደፍቋት ነው እና ኢትዮጵያን እንታደግ የእሚል በመሆኑ ፤ ገንጣይ ፣ አስገንጣይ ወይንም ጸረ ኢትዮጵያ የእሚያስብለው የፖለቲካ ፕሮግራም የለውም።

ምንም እንኳን ነገዳዊ ጭቆና በኢትዮጵያ አለ ይኽም የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል ድረስ በእሚል አግባብ ብቻ እና ብቻ ነው ሊፈታ የእሚችለው በማለቱ እና ይኽንን የሌሎቹ ትግሎቹ ፤ ማለትም ፦ የጸረ ፊውዳሊዝም ፣ የጸረ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ፣ ወዘተ ፤ ትግል መጠቅለያ ለማድረግ ቢሞክርም ፤ የአካኼድ ጉዳይ እንጂ ፤ በኢትዮጵያ ነገዳዊ ጭቆና አለ እና ይኽም የራስን እድል በራስ በመወሰን መብት እስከ መገንጠል ድረስ በእሚል አግባብ ብቻ እና ብቻ ነው ሊፈታ የእሚችለው በማለት ኢሕአፓም የእሚስማማ በመሆኑ ፤ ይኽን እንደ ማሳያ ተጠቅሞ ፤ ሕወሐት ገንጣይ ፣ አስገንጣይ እና ጸረ ኢትዮጵያ ነው ማለት አይቻልም።

የኢሕአፓ ቁንጮ የእሚባሉት ብርሐነ መስቀል ረዳ ፣ ተስፋዬ ደበሳይ ፣ ዘሩ ክህሸን ትግሬዎች እንደ ሆኑ ልብ ሊባል ይገባዋል።

ከእላይ እንደ አልነው በኢትዮጵያ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ወይንም በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የእሚመራን አብዮት ግድ የእሚል ፖለቲካዊ ድባብ አልነበረም ፤ ምክንያቱም ፦ በኢትዮጵያ አብዮት በእሚነሳበት ግዜ ፦ ፊውዳሊዝም ፣ ቀኝ ግዛት ፣ ኢምፔሪያሊዝም ፣ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ፣ ሐገራዊ አቆጥቋጭ ካፒታሊዝም (ንዑስ ከበርቴ) የኢትዮጵያ ሐገራዊ ህልውና ሊያሰጋ በእሚችልበት ኹኔታ ፤ የአልነበረ በመሆኑ ብለን አስቀምጠናል።

ሕወሐትም በኢትዮጵያ በዋናነት አብዮታዊ ዴሞክራሲን ግድ የእሚለው ከእነዚኽ በባሰ ማለትም ከፊውዳሊዝም ፣ ከኢምፔሪያሊዝም ፣ ከቀኝ ግዛት ስጋት ፣ ከቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ፣ ወዘተ ፤ በባሰ ነገዳዊ ጭቆና በመኖሩ ነው የእሚል እና ይኽን ነገዳዊ ጭቆና ማስቀረት እና ኢትዮጵያ በተማከለ አስተዳደር ወደ ካፒታሊዝም ስረዓት ግንባታ መውሰድ የእሚቻለው ፤ ነገዶችን በነገዳቸው አደራጅቶ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብታቸውን እስከ መገንጠል ድርስ ስናከብር ነው እንደ እሚል እና ከሌላው ስረዓታዊ ችግሮች በላይ ነገዳዊ ቅራኔ ላይ ማተኮሩ ከሌሎቹ የወቅቱ አብዮታዊ ዴሞክራሲያን እንደ እሚለየው አይተናል።

ሕወሐት ይኽን ቢልም ቅሉ የሕወሐት ነገድ ተኮር አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፤ እንደ ዋናው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ቀላል የእማይባል መላምታዊ (Theoretical) ስህተት እና ከሐገሪቱ ተጨባጭ ኹኔታ ጋር በፍጹም የአለመናበብ ችግር የአለበት ነው።

የሕወሐት ነገድ ተኮር አብዮታዊ ዴሞክራሲ ችግር የእሚጀምረው ነገድን ብሔር ብሎ ከመሰየሙ ወይንም ከመተርጎሙ ነው። በመደበኛ ቋንቋ ወይንም በመደበኛ ግንዛቤ ፤ ኹሉም ፦ የባሕል ፣ የቋንቋ መመሳሰል ኖሮዋቸው በአንድ አከባቢ በብዛት የእሚገኙ ሕዝብ ብሔር በአይባሉም ሕወሐት ግን የስታሊንን ትርጉም መሠረት አድርጌ ነው በማለት ፤ የጋራ ቋንቋ ፣ ባህል ፣ ወዘተ ፤ የአላቸው የተለያዩ የኢትዮጵያ ነገዶች ፤ ብሔሮች እንጂ ነገዶች አይደሉም አለ።

የሕወሐት መሥራች አባል እና ከምሥረታው አንስቶ ለቀጣዩ አስር ዓመት በላይ የሕወሐት ከፍተኛ አመራር ሆኖ የቆየው አቶ አረጋዊ በርኼ (ዶ/ር) ፤ ሕወሐት የኢትዮጵያን ነገዶች ብሔር ብሎ ለመሰየም የስታሊንን ትርጉም እንደ ወሰደ በእዚኽ መልኩ ይነግረናል ፦

“የሕወሐት መገንጠያ ነጥብ ስታሊን ብሔርን የተረጎመበት አግባብ ነው ‘በታሪካዊ ዝግመት[4] የመጣ ፣ የተረጋጋ የቋንቋ ጋርዮሽ፣ እና የጋራ መኖሪያ ፣ ኢከነሚያዊ ሕይወት እና በጋርዮሽ ባህል የእሚገለጽ ስነልቦናዊ ውቅር።’ በእዚኽም ትርጓሜ መሠረትም ፤ ትግራይ ብሔር ተብላ መጠራት እና የራሷን እድል በራሷ መወሰን መብት ባለቤት መሆን ትችላለች ተብሎ እምነት ተያዘ።”

“The TPLF’s departure point is was Stalin’s definition of a nation ‘a historically evolved, stable community of language, and territory, economic life and psychological makeup manifested in the community of culture.’ Based on this definition, it was believed that Tigray constituted a nation which had the right to self-determination. [124]”

ይኽ ሕወሐት ስታሊንን መሠረት አድርጎ ትግራይን ነገድ ሳይሆን ብሔር ነች ለማለት የኼደበት አካኼድ ፤ “ሊበሏት የአሰቧትን አሞራ ጅግራ ነሽ ይሏታል” እንዲባል ፤ ስታሊንን ከአውድ እና ከስታሊን ኃሳብ ፊጹም ተቃራኒ በሆነ መልኩ በመጥቀስ ፤ ትግራይን ብሔራዊ ህልውና ለማላበስ የተደረገ ፤ የግንዛቤ እጥረት መገለጫ ወይንም ተራ ፖለቲካዊ ማታለል መሆኑን ፤ ሕወሐት ትግራይን ብሔር ሲል መሠረት የአደረኩት የስታሊንን “ብሔራዊ ጥያቄ እና ማርክሲዝም” የእሚለውን መጽሐፍ ነው የአለውን መጽሐፍ በማንበብ ማየት ይቻላል።

ከእላይ አረጋዊ በርኼ የአስቀመጠልን የሕወሐት የትግራይ ብሔርተኝነት መሠረት ነው የአለው የስታሊን ኃሳብ ፤ በስታሊን እንደ እዚኽ ተቀምጧል ፦

“አኹን የብሔርን መለያ ጠባዮች ዘርዝረን ጨርሰናል።

ብሔር በታሪክ ኺደት የተዋቀረ ፣ የረጋ የሕዝብ ጋርዮሽ ሆኖ በጋራ ቋንቋ ፣ የመኖሪያ ስፍራ ፣ ኢከነሚያዊ ህወይወት ፣ እና በጋራ ባህል መዋቅር የእሚንጸባረቅ የጋራ ስነ ልቦናዊ መዋቅር ኖሮት የተገነባ ነው።”

“We have now exhausted the characteristic features of a nation.

A nation is a historically constituted, stable community of people, formed on the basis of a common language, territory, economic life, and psychological make-up manifested in a common culture. [125]”

ከእዚኽ የስታሊን ኃሳብ ልናይ እንደ እምንችለው ፤ ስታሊን ይኽንን ኹሉንም የብሔር መለያ ጠባይ ናቸው የአላቸውን ባሕሪያት እያንዳንዳቸውን በተናጠል ከተነተነ እና ከአብራራ በኋላ ነው ፤ አንድ ሕዝብ ወይንም ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ እነ እዚኽን ቅድመ ኹኔታዎች ከአሟላ ነው ብሔር ልንለው የእምንችለው እያለ መሆኑን እንረዳለን።

በእዚኽም መሠረት ፤ ስታሊን በታሪክ ኺደት የተዋቀረ (Historically constituted) ሲል ዝም ብሎ ማንኛውንም ታሪካዊ ኺደት እያለ ሳይሆን ፤ የታሪክ ቁሳቂነት የእሚባለውን የማርክሲዝም ታሪካዊ ኺደት እያለ ነው። የስታሊን መጽሐፍም ፤ ማርክሲዝም እና የብሔር ጥያቄ የእሚል ነው።

እንግዲኽ ስታሊን ፤ ብሔር አንዱ መለያ ጠባዩ በታሪካዊ ኺደት የተዋቀረ ነው ሲል ፤ ማንኛውንም ታሪካዊ ኺደት እና ደረጃ ሳይሆን ፤ በተለየ ኹኔታ ፤ በማርክስታዊው የታሪክ ቁሳዊነት ትንታኔ መሠረት ፤ ድህረ ካፒታሊዝም በኋላ የእሚመጣውን ሕዝባዊ ውቅር እያለ ነው። ይኽንንም በግልጽ በእዚኹ መጽሐፉ ውስጥ አስቀምጦታል ፦

“ብሔር በአንድ በተወሰነ የካፒታሊዝም ስረዓት ማንሰራራት በእሚባል ታሪካዊ ክፍለ ዘመን ላይ የእሚገኝ ፈርጅ እንጂ እንዲኹ የተገኘው ማንኛውም ታሪካዊ ፈርጅ አይደለም። የፊውዳሊዝም ዘመን መጥፋት እና የካፒታሊዝም ማበብ በተመሳሳይ ህዝብን ወደ ብሔርነት የማዋቀር ኺደት ነው። ለምሳሌ ፦ በምዕራባዊ አውሮፓ የእምንመለከተው ነገር ይኽ ነው። ብሪትሾች ፣ ፈረንሳዮች ፣ ጀርመኖች ፣ ጣሊያኖች ብሔር በመሆን መቀረጽ የጀመሩት ከካፒታሊዝም የድል ግስጋሴ እና በፊውዳላዊ ክፍፍል ላይ ድል መቀናጀት በጀመረ ማግስት ነው።”

“A nation is not merely a historical category but a historical category belonging to a definite epoch, the of epoch of rising capitalism. The process of elimination of feudalism and development of capitalism is at the same time a process of the constitution of people into nations. Such, for instance, was the case in Western Europe. The British, French, Germans, Italians and others were formed into nations at the time of the victorious advance of capitalism and its triumph over feudal disunity. [125]”

ይኽም ብቻ ሰአይሆን ፤ የረጋ የሕዝብ ጋርዮሽ ሆኖ የጋራ ቋንቋ ፣ ኢከነሚያዊ ህይወት እና በጋራ ባሕል የእሚንጸባረቅ የጋራ ስነልቦናዊ መዋቅር ሲል ፤ ይኽ አባባሉ ነገድን እማይወክል እንደ ሆነ በግልጽ ፤ ብሔር ማለት ነገድ አይደለም በእሚል እንደ እዚኽ አስቀምጦታል ፦

“ብሔር ምንድ ነው ?

ብሔር በቀዳሚነት አንድ ጋርዮሽ ነው ፤ አንድ የተወሰነ የሕዝብ ጋርዮሽ ነው።

ይኼ ጋርዮሽ ግን የዘር ወይንም የነገድ ጋርዮሽ አይደለም። ዘመናዊ ብሔራዊ ጣሊያን ከሮማኖች ፣ ከቲውቶንስ ፣ ከኢትሩስካን ፣ ከግሪክ ፣ ከአረብ ፣ ወዘተ ፤ የተወጣጣች ነች። ብሔራዊት ፈረንሳይ ፤ ከጎውሎች ፣ ከሮማኖች ፣ ከብሪትኖች ፣ ከቲውቶኖች ፣ ወዘተ ፤ የተውጣጣች ነች። ተመሳሳይ ነገርም ስለ ብሪትሾች ፣ ስለ ጀርመኖች እና ስለ ሌሎችም መባል ይችላል የተለያየ ዘር እና ነገድ ከአላቸው ሕዝብ ተወጣተው ስለ ለተመሠረቱ ብሔራዊ ሐገራት ።

ስለ እዚኽ ፦ ብሔር ከዘር ወይንም ከነገድ ጋር የተያያዘ ነገር አይደለም ፤ በታሪክ ኺደት የተዋቀረ የሕዝብ ጋርዮሽ ነው። …. ብሔር ማለት ድንገታዊ ወይንም ግዜያዊ ስብስብ ማለት ሳይሆን የረጋ የህዝብ ጋርዮሽ ነው።”

“What is a nation?

A nation is primarily a community, a definite community of people.

This community is not racial, nor is it tribal. The modern Italian nation was formed from Romans, Teutons, Etruscans, Greeks, Arabs, and so forth. The French nation was formed from Gauls, Romans, Britons, Teutons, and so on. The same must be said of the British, the Germans and others, who were formed into nations from people of diverse races and tribes.

Thus, a nation is not a racial or tribal, but a historically constituted community of people…. a nation is not a casual or ephemeral conglomeration, but a stable community of people. [125]”

ስለ እዚኽ ፦ በስታሊን መሠረት ፤ ምንም እንኳን የጋራ ቋንቋ ፣ የጋራ መኖሪያ ፣ በጋራ ባሕል የእሚንጸባረቅ የጋራ ስነ ልቦናዊ ውቅር የብሔር መገለጫ ቢሆንም አንድ የሕዝብ ስብስብ ይኽን ስለ አሟላ ብሔር ሊባል እንደ እማይችል በግልጽ አስቀምጧል።

በአጭሩ ለስታሊን የጋራ ቋንቋ መኖር የብሔር አንድ መለያ ጠባይ ነው ሲል ፤ ይኽ የጋራ ቋንቋ አንድ የጋራ የአፍ መፍቻ ቋንቋ የመኖርን ጉዳይ የእሚያመለክት ሰአይሆን ፤ በታሪካዊ ዝግመት አንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ከፊውዳላዊ ስረዓት ወደ ካፒታሊዝሙ ስረዓት ሲሸጋገር ፤ የካፒታሊዝሙ ስረዓት በእሚፈጥረው ፤ ኢከነሚያዊ እና ፖለቲካዊ ትስስር የእሚፈጠረውን ፤ አንድ የጋራ መግባቢያ ቋንቋ ማለቱ እንጂ ፤ ከቤተሰብ ወይንም ከትውልድ ስፍራ የእሚወረሰውን አንድ የአፍ መፍቻ ቋንቋን የእሚመለከት አይደለም።

ይኽ ኹኔታ በጋራ ባሕል የእሚገልጽ የጋራ ስነልቦናዊ ውቅር የእሚለውንም የእሚመለከት ነው። አንድ ማሕበረሰብ በሕጸጽነት ወይንም በእንግሊዘኛው (Primordial) የሆነ አንድ ማሕበረሰብ የእሚኖረውን በጋራ ባሕል የእሚገለጸውን የጋራ የስነ ልቦና ውቅር ሰአይሆን ድህረ ካፒታሊዝም በኢከነሚያዊ እና ፖለቲካዊ ትስስር የእሚፈጠረውን በአንድ የጋራ ባሕል የእሚንጸባረቀውን ወይንም ካፒታሊዝም ሰራሽ የሆነውን በአንድ ባሕል የእሚገለጸውን የጋራ ስነ ልቦናዊ ውቅር እያለ ነው።

ስለ እዚኽ ፤ ሕወሐት ትግራይን ብሎም የኢትዮጵያን ነገዶች ብሔር ናቸው እና የብሔር ጥያቄ ማንሳት ይችላሉ የአልኩት በስታሊን ትርጉም ላይ ተመስርቼ ነው ሲል ፤ ስታሊን ነገዶች ራሳቸውን ብሔር እንዳይሉ እና ይኽም ከማርክስ የሙግት ቁሳዊነት (Dialectical Materialism) ጋር ፍጹም የእሚጋጭ ነው ብሎ በግልጽ የአስቀመጣቸውን ቅድመ ኹኔታዎች አውቆ ወይንም ከግንዛቤ እጥረት በመዘንጋት ነው።

ስለ እዚኽ፦ እንደ ስታሊን ከሆነ ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ አይደለም አንድ ነገድ ወይንም በኢትዮጵያ አንድ አከባቢ የእሚኖር ሕዝብ ቀርቶ ዋናዋ እና ከዓለማችን ጥንታዊ ሐገራት ጎራ የእምትመደበው ኢትዮጵያ እራሷ ወደ ካፒታሊዝም ስረዓት ለመግባት የእምትላላጥ በመሆኗ ፤ በስታሊን ትርጉም መሠረት ማንኛውም የኢትዮጵያ ነገድ ብሔር ነኝ ብሎ የብሔር ጥያቄ ማንሳት ወይንም የራሴን እድል በራሴ የመወሰን መብት ልጎናጸፍ ይገባል ማለት አይችልም።

ከእላይ እንደ አልነውም በኢትዮጵያ ውስጥ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የእሚመመራው አብዮት ያስፈልጋል የተባለውም ኢትዮጵያን ከኋላ ቀርነት ረመጥ ውስጥ በአብዮት ጎትቶ ወደ ካፒታሊዝም ስረዓት ውስጥ ለማስገባት ነው እንዳልን ግልጽ በመሆኑ ፤ አይደለም አንድ ንዑስ ነገድ መላው ሐገሪቱም ወደ ካፒታሊዝም ስረዓት አይደለም የዛኔ ዛሬም በሙላት እንደ አልገባች ግልጽ በመሆኑ ፤ የሕወሐት የስታሊን ነው ዋሴ አባባል መሠረት አልባ ነው።

ይኽም በመሆኑ በመላምት ደረጃ (Theoretically) ብሔር ነኝ ማለት የእሚችል ነገድ ወይንም አከባቢ አይደለም ያን ግዜ ዛሬም በኢትዮጵያ ውስጥ የለም።

ከኖረም በኢትዮጵያ መኖር የእሚችለው ፤ ብሔርተኛ ካባ የለበሰ ነገዳዊነት (Tribalism) ነው መኖር የእሚችለው ወይንም ነገዳዊ ብሔርተኝነት (Ethnonationalism) ነው መኖር የእሚችለው።

በአንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ውስጥ የትጥቅ ትግልን ግድ የእሚል ዓይነት ነገዳዊ ብሔርተኝነት ሊኖር የእሚችለው ደግሞ ለምን አፍ መፍቻ ቋንቋዬ ብሔራዊ ቋንቋ አልሆነም ወይንም የእኔ ነገድ የፖለቲካ ውክልና ያንሰዋል ዓይነት ጥያቄዎች በማንሳት ሰአይሆን ፤ በተለያየ መዋቅራዊ ችግር ምክንያት ዜጎች ነገዳዊ ማንነታቸውን መሠረት የአደረገ እና በግልጽ ስረዓታዊ በሆነ መልኩ የእሚተገበር ፦ ኢከነሚያዊ መብት ገፋፋ ፣ ፖለቲካዊ መገለል ፣ መፈናቀል ፣ መሰደድ ፣ ጭፍጨፋ ወይንም የዘር ማጥፋት ሲደርሳባቸው እና ይኽም በዓለም ዓቀፍ ማሕበረሰብ ዘንድ እስከ መወገዝ የደረሰበት ኹኔታ ሲኖር ነው።

ይኽ በእሚሆንበት ግዜ ፤ ይኽ ነገድ በኋላ ቀር አስተሳሰብ እና በትምክህት ከሌላው የሕበረተሰብ ክፍል ጋር አብሮ እንደ አይኖር የእሚያግደው እና መሠረታዊ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቱን በቋሚነት እና በስርዓታዊ አግባብ የእሚገፈፍበት ኹኔታ በመኖሩ እና ነባራዊው ፖለቲካዊ ስረዓትም ይኽንን ችግር ለመፍታት ፈቃደኛ በእማይሆንበት ግዜ ፤ አንድ ነገድ ተገዶ ወደ ነገዳዊ ብሔርተኝነት ፤ ተቀባይነት በአለው አግባብ ሊገባ ይችላል። ለምሳሌ ፦ ሲንጋፖሮች በነገዳዊ ስብጥራቸው ምክንያት በማሌዝዎች አንፈልጋችኹም ውጡ ተብለው ተገደው ነው ወጥተው ሲንጋፖርን የመሠረቱት ።

ይኽ ከአልሆነ ግን ወይንም አንዱ ነገድ ከሌላው ነገድ በቋሚነት እና በስረዓታዊ መዋቅር የተደገፈ ፣ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በእሚያስወግዝ መልኩ ፤ መሠረታዊ የነገድ አባላቱን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት በአደባባይ እየጣሰ ፤ ነጥሎ ለኢከነሚያዊ አድቃቂ ድህነት እና ኋላ ቀርነት በእማይዳርግበት ኹኔታ ፥ ማንነትን መሠረት የአደረግ እስር ፣ እንግልት ፣ ጭፍጨፋ ፣ ወዘተ በሌለበት ኹኔታ ፤ ነገዳዊ ብሔርተኝነት ትርጉም አልባ ወይንም ተራ የጠብ አጫሪነት አካኼድ ነው የእሚሆነው።

ሕወሐት ይኽን የነገድ ፕሮግራሙን ትግራይ ብሔር ነች ብሎ በእሚቀርጽበት ግዜ በኢትዮጵያ ውስጥ በትግሬ ላይ ይኽን መሰል መንግሥታዊ እና ማሕበራዊ ክፋት እንደ አልነበር የወቅቱ የኢትዮጵያ ታሪክ መመልከት ብቻ በቂ ነው።

የሕወሐት አባት የእሚባለው እና በነበረው ፖለቲካዊ ስልጣን እና ማሕበራዊ ተቀባይነት ሕወሐት እንዲደራጅ እና የትጥቅ ትግሉን እንዲጀምር የአንበሳውን ድርሻ የተጫወተው ገሰሰው አየለ (ስኹል) ፤ ሕወሐት ነፍጥ በእሚያነሳበት እና በእሚደራጅበት ወቅት ፤ የትውልድ አከባቢውን አክሱምን ወክሎ በከፍተኛ ድምጽ ተመርጦ ፤ የኃይለ ሥላሴ ፓርላማ ውስጥ ተወካይ የነበረ ሰው ነው። ይኽን የእሚያረጋግጥልን ሌላ ሰው ሳይሆን ፤ ከስኹል ጋር አብሮ ሕወሐትን የመሠረተው አረጋዊ በርኼ ነው ፦

“በ1960ዎቹ የሽሬ ሕዝብ ግልብጥ ብሎ ለእርሱ (ለስኹል) ድምጽ በመስጠት በኢትዮጵያ ፓርላማ እንዲወክላቸው አደረጉት።”

“In the early 1970s, the people of Shire had overwhelmingly voted for him to represent them in the Ethiopian parliament. [124]”

ከእዚኽ በአሻገር በታሪክ ኹሉ እንደ እሚታወቀው የትግራይ ሕዝብ በእራሱ ተወላጆች እንጂ ከሌላ ቦታ በመጣ አስተዳዳሪ ተዳድሮ የእማያውቅ ነው ፤ ሕወሐትም ለትጥቅ ትግል ሲወጣ ፤ የትግራይ ገዢ የአጼ ዮሐንስ የልጅ ልጅ የሆኑት ልዑል ራስ መንገሻ ናቸው።

በወቅቱ የዘውዳዊ መንግሥትም ውስጥም ሆነ ከእዚያኽ በፊት በነበሩት ረዥም ዘመናት ፤ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ነበሩ። በመላው ኢትዮጵያም የትግራይ ተወላጅ በመላ ሐገሪቱ እንደ ማንኛውም ዜጋ እየኖረ የነበረ እና ማንም ትግሬ በመሆኑ ይኽ ነው የእሚባል ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወይንም ነገድ የተለየ መንግሥታዊ እና ስረዓታዊ በደል የእማይደርስበት የነበረ ነው።

ስለ እዚኽ ፦ ምንም እንኳን ሕወሐት ፤ ሌኒንስታዊ የሆነውን የብሔር አቋም በመያዙ ፤ ትግራይን ገንጣይ ፣ ኤርትራን አስገንጣይ እና ጸረ ኢትዮጵያ የእሚያስብለው በአይሆንም ፤ የያዘው ነገዳዊ አቋም ግን ልክ እንደ አብዮታዊው ዴሞክራሲው ከኢትዮጵያ ነባራዊ ፖለቲካዊ ኹኔታ ጋር የእማይኼድ ወይንም የኢትዮጵያን ነባራዊ ፖለቲካዊ ችግር የእሚያንጸባርቅ አቋም አይደለም።

እንዲያውም ሕወሐት ትግራይን ብሔር የእሚይደርገውን ትርጉም “ማርክሲዝም እና ብሔራዊ ጥያቄ (Marxism and The National Question)” ከእሚለው የስታሊስን መጽሐፍ ነው የአገኙኹት ብሎ ለያዘው ጠባብ ነገዳዊ ብሔርተኝነት ፕሮግራም ምስክር አድርጎ የእሚጠራው መጽሐፍ ፤ የሕወሐትን ነገድን ብሔር የአደረገበትን አግባብ ፈጽሞ የእሚያጣጥል ብቻ ሰአይሆን ፤ ብሔርተኝነት በጠቅላላው የሶሻሊዝምን ትግል የእሚያዳክም እና አንዳንዴም ለመላው የሰው ልጅ የጥፋት ምንጭ የሆነ በመሆኑ ፤ በአንድ መንግሥት በእሚያድሩ ነዋሪዎች ውስጥ የነገድ ጭቆና ከአለ እንኳን ፤ ችግሩ መፈታት የአለበት ለኹሉም ዜጎች ዴሞክራሲያዊ እና ሰብዓዊ መብቶች (እርሱ ሲቪክ መብቶች የእሚላቸውን) በማስፋፋት እንጂ በብሔር ተድራጅቶ የራስን እድል በራስ መወሰን ማዕቀፍ መሆን እንደ ሌለበት ነው የእሚለው።

እንደ ስታሊን ፤ ሕወሐት በጥራዝ ነጠቅ እና ግልብ ትርጉም ብሔር የአደረጋቸው ነገዶች ሰአይሆን በጠቅላላው የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ፤ ለሶሻሊስት አብዮትም ሆነ ለአንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ብልጽግና ጠንቅ ነው። ሕወሐት የእሚጠቅሰው ስታሊን መጽሐፉን ከእዚኽ በታች በአለው ገልጻ ነው የእሚጀምረው፦

“የጸረ አብዮተኝነት ዘመን ዝናብ በራሻ “ነጎድጓድ እና መብረቅ” ብቻ አይደለም በውስጡ ይዞ የመጣው ፤ ነገር ግን በንቅናቄው ውስጥ ግራ መጋባት እና በጋራ ኃይል ላይ እምነት ማጣትንም ጨምሮ ነው። ሕዝብ “በብሩሕ መጻኢ” ላይ እስከ አመነ ድረስ ፤ በብሔሩ ሳይወሰን ጎን ለጎን ሆኖ በጋራ ታግሏል - መጀመሪያ እና መጀመሪያ የጋራ ጉዳያችን ብሎ! ነገር ግን ጥርጣሬ በሕዝብ ልብ ውስጥ ሲሰርግ ፤ እያንዳንዱ ወደ ብሔሩ ድንኳን በመከተት ፤ ተለያየ - እያንዳንዱ ሰው በእራሱ ብቻ ይተማመን ተባለ ! ከእነ እዚኽም ቀዳሚው እና የመጀመሪያ “የብሔር ጥያቄ” ሆነ።

የ”የብሔር ጥያቄ” ከሌሎቹ[5] በፊት እና በቀዳሚነት…ሰፊውን የሠራተኛውን ሠራዊት ለማጥለቅለቅ እንደ እሚያሰጋ ማዕበል በእየግዜው ኃይሉ እየጨመረ በማስገምገም ላይ ነው።

በእዚኽ አስቸጋሪ ግዜ ሶሻል ዴሞክራሲ ከፍ ያለ ተልዕኮ አለው - ብሔርተኝነትን/ነገዳዊነትን መታገል እና ሰፊውን ሕዝብ ከእዚኽ ወረርሽኝ መታደግ። ”

“The Period of counter-revolution in Russia brought not only “thunder and lightning” in its train, but also disillusionment in the movement and lack of faith in common forces. As long as people believed in “a bright future”, they fought side by side irrespective of nationality – common questions first and foremost! but when doubt crept into people’s hearts, they began to depart, each to his own national tent – let every man count only upon himself!

The “national question” first and foremost…The wave of nationalism swept onwards with increasing force, threatening to engulf the mass of the workers. And the more the movement for emancipation declined, the more plentifully nationalism pushed forts its blossoms.

At this difficult time Social-Democracy had a high mission – to resist nationalism and to protect the masses from the general “epidemic. [125]”

ይኽን ተከትሎ ፤ ስታሊን የራስን እድል በራስ መወሰን የእሚለውን መብት ፤ እርሱ ብሔር (ከሕወሐት የብሔር ትርጉም ጋር የእሚለይ መሆኑ ይሰመረበት) ለእሚላቸው ፤ አንዳንድ ግዜ ሶሻሊስቶች ማክበር የአለባቸው ቢሆንም ይኽ ግን ወጥ የሆነ አቋም መሆን የለበትም ነው የእሚለው ፦

“አንድ ብሔር የራሱን ሕይወት በራስ ገዝነት አግባብ የማስኬድ መብት አለው። ከአስፈለገም የመገንጠል መብት አለው። ይኽ ማለት ግን ያ ራስ ገዝነት ፣ ወይንም የመገንጠል መብት በኹሉም ኹኔታ እና በማንኛውም ግዜ ለብሔሩ ይበጀዋል ማለት አይደለም ፤ ማለትም ፦ ለብዝኃኑ ፣ ማለትም ፦ ለለፍቶ አዳሪው። እንበል እና ፤ በመላው ካውኮዥያ የእሚገኙት ታርታሮች በሸንጎዋቸው በሙላኽዎቻቸው[6] እና በቤዮቻቸው ተባብለው ፤ የቀድሞውን ስረዓት ለመመለስ እና ለመገ፟ንጠል ፈለጉ። የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት በእሚለው ሐረግ መሠረት ይኽን የማድረግ ሙሉ መብት አላቸው። ጥያቄው ግን ይኽ ኹኔታ የለፍቶ አዳሪውን የታርታር ሕዝብ ጥቅም ያስጠብቃል ወይ? ነው። ሶሻል ዴሞክራሲስ ፤ የራስን እድል በራስ የመወሰን መፍትኼ በእሚል ፤ ሙላኽዎች እና ቤዮች የሰፊውን ሕዝብ አመራር ሲይዙ ፤ ምን ገዶኝ ብሎ ይመልከት?

ሶሻል ዴሞክራሲ የብሔሮች ፍላጎት ላይ ጣልቃ በመግባት ተጽኖ ማሳደር አይገባውም ? አንድ ቁር፟ጥ የአለ፟ እቅድ ይዞ በመምጣት ለእዚኽ ጥያቄ ፤ ለታርታር ሰፊው ሕዝብ የእሚበጅ እና የእሚሻል መፍትኼ ይዞ መምጣት የለበትም?

ለለፍትቶ አዳሪው ሰፊው ሕዝብስ የእሚበጀው መፍትኼ የቱ ነው ? ራስ ገዝነት ? ፌደሬሽን ? ወይንስ መገንጠል?

እነ እዚኹ ኹሉ ችግሮች መፍትኼያቸው አንድ ብሔር ራሱን በእሚያገኝበት ተጨባጭ በሆኑ ታሪካዊ ኹኔታዎች ላይ የእሚደገፍ ነው።

ከእዚያኽም በላይ ደግሞ ኹኔታዎች እንደ ማንኛውም ነገር ይቀያየራሉ ፤ በአንድ የተለየ ወቅት ትክክል የሆነ ውሳኔ በሌላ ግዜ የእማይገባ ሊሆን ይችላል።

በ19ኛው ምዕተ ዓመት መካከል ላይ ማርክስ የራሻዋ ፖላንድ[7] እንድትገነጠል ይደግፍ ነበር ፤ ይኽም የማርክስ አቋም ትክክል ነበር ምክንያቱም የተራቀቀው ባሕል ከኋላ ቀሩ እና እያጠፋው ከአለው ባሕል መላቀቅ ስለ ነበረበት። እናም በእዚያኽ ሰዓት ጥያቄው መላምታዊ ጉዳይ ፣ የትምህርት ቤት ጥያቄ ሰአይሆን ፥ ተግባራዊ እና በእርግጥም በእውን የነበረ ጥያቄ ነበር...

በ19ኛው ምዕተ ዓመተ መጨረሻ ላይ ደግሞ የፖላንድ ማርክሲስቶች የፖላንድን ከራሺያ መገንጠል ተቃውመው ቆመው ነበር ፤ እነርሱም ትክክል ነበሩ ፤ ምክንያቱም ከእዚያኽ ወዲኽ በነበረው ኃምሳ ዓመት በራሻ የጎሉ ለውጦች ተካኺደው ራሻን እና ፖላንድን በኢከነሚው አና በባሕሉ ረገድ ተቀራራቢ ኹኔታ ላይ አምጥተዋቸው የነበረ በመሆኑ። ከእዚኽም በላይ ፤ በእዚኽ ወቅት የመገንጠሉ ጥያቄ ከተግባራዊ ጥያቄነት ፤ በጥያቄው ዙሪያ ትምህርታዊ ክርክር ማድረግ ከእሚያስደስታቸው ሊህቃን በስተቀር ሌላ ማንንም የእማያስደስት ጥያቄ ወደ መሆን ተለውጦ ነበር።

ይኽ በእርግጥ ፤ አንዳንድ ውስጣዊ እና ውጫዊ ኹኔታዎች ፤ የፖላንድን ጥያቄ ተገቢነት የአለው የዘመኑ ጥያቄ የእሚያደርጉበት ኹኔታ ሊፈጥሩ አይችሉም ማለት አይደለም።”

“A nation has the right to arrange its life on autonomous lines. It even has the right to secede. But this does not mean that it should do so under all circumstances, that autonomy, or separation, will everywhere and always be advantageous for a nation, i.e., for its majority, i.e., for the toiling strata. The Transcaucasian Tatars as a nation may assemble, let us say, in their Diet and, succumbing to the influence of their beys and mullahs, decide to restore the old order of things and to secede from the state. According to the meaning of the clause on self-determination they are fully entitled to do so. But will this be in the interest of the toiling strata of the Tatar nation? Can Social-Democracy look on indifferently when the beys and mullahs assume the leadership of the masses in the solu­tion of the national question?

Should not Social-Democracy interfere in the matter and influ­ence the will of the nation in a definite way? Should it not come forward with a definite plan for the solution of the question, a plan which would be most advantageous for the Tatar masses?

But what solution would be most compatible with the interests of the toiling masses? Autonomy, federation, or separation?

All these are problems the solution of which will depend on the concrete historical conditions in which the given nation finds itself.

More than that; conditions, like everything else, change, and a decision which is correct at one particular time may prove to be entirely unsuitable at another.

In the middle of the nineteenth century Marx was in favor of the secession of Russian Poland; and he was right, for it was then a question of emancipating a higher culture from a lower culture that was destroying it. And the question at that time was not only a theoretical one, an academic question, but a practical one, a question of actual reality. . . .

At the end of the nineteenth century the Polish Marxists were already declaring against the secession of Poland; and they too were right, for during the fifty years that had elapsed profound changes had taken place, bringing Russia and Poland closer eco­nomically and culturally. Moreover, during that period the question of secession had been converted from a practical matter into a matter of academic dispute, which excited nobody except perhaps intellectuals abroad.

This, of course, by no means precludes the possibility that certain internal and external conditions may arise in which the question of the secession of Poland may again come on the order of the day. [125]”

ስለ እዚኽ ፦ በእዚኽ መጽሐፍ ምዕራፍ አንድ ላይ እንደ አየነው ፤ ሕወሐት ዋስ የእሚጠራው ስታሊን ፤ ከሕወሐት ጋር በብሔር ትርጓሚውም ብቻ ወይንም ስታሊን ነገድ እና በአንድ ከካፒታሊስት ስረዓት በፊት የእሚገኝ ሕዝብ ብሔር ሊባል አይችልም በማለቱ ብቻ ሰአይሆን የእሚለየው ፤ አንድ ብሔር ሊባል የእሚችል ሕዝብ ራሱ ፤ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ያለ ምንም ቅድመ ኹኔታ እንዲኹ ፤ በሻሞ የእሚታደል ነገር አይደለም ፤ በእሚልም ይለያል።

እንደ ስታሊን ብሔርተኝነት ወይንም ነገድን ብሔራዊነት ማላበስ (ነገዳዊ ብሔርተኝነት Ethnonationalism) ፤ ለባሕል ፣ ቋንቋ ፣ ወዘተ ፤ ጥበቃ በእሚል ፤ ዜጎችን በባሕል እና በጋርዮሽ ጠባይ አግባብ ማድረግ የተለያየ ችግር አለው ብሎም ይተቸዋል ፦

“…ብሔራዊ/ነገዳዊ የባሕል ራስ ገዝነት የእማይመች ነው። በመጀመሪያ ደረጃ አርተፊሻል እና ሊተገበር የእማይችል ነው ፤ ምክንያቱም አርተፊሻል በሆነ መንገድ ፤ የታሪክ ኺደት ፥ ኃሳባዊ ሳይሆን እወነተኛ የታሪክ ኺደት[8] ፤ ነጣጥሎ በኹሉም የሐገሪቱ አቅጣጫ የበተናቸውን ሰዎች ሰብስቦ አንድ ለማድረግ የእሚፈልግ በመሆኑ። በኹለተኝነት ፤ በብሔርተኝነት ዙሪያ በብሔራዊ ባህላዊ አጥር ወደ “ድንበር ማካለል” አስተሳሰብ የእሚያመራ እና ብሔርተኝነትን የእሚያፋፍም በመሆኑ ፤ ብሔሮችን “ማደራጀት” ፣ “ባህላዊ ልዩነቶችን” “መጠበቅ” እና ማልማት - የእሚሉት ነገራት በሙሉ ከሶሻል ዴሞክራሲ ጋር የእማይኼዱ ናቸው።”

“…cultural-national autonomy is unsuitable. Firstly, it is artificial and impracticable, for it proposes artificially to draw into a single nation people whom the march of events, real events, is disuniting and dispersing to every corner of the country. Secondly, it stimulates nationalism, because it lead to the viewpoint in favor of the “demarcation” of people according to national curiae, the “organization” of nations, the “preservation“ and cultivation of “national peculiarities” – all of which are entirely incompatible with Social-Democracy. [125]”

ስታሊን ቀጠል አድርጎም ፤ ብሔራዊ ጭቆናን ከባህል ፣ ቋንቋ ፣ ወዘተ ፤ ጭቆና ጋር አያይዞ ፤ ሕዝብን የብሔራዊ/ነገዳዊ ባህል ራስ ገዥነት አግባብ ማዋቀር ፤ አንዳንድ ግዜ ፤ ወደ ዘር ማጥፋት እና ጭፍጨፋ ሊያመራ ስለ እሚችል የሠራተኛውን ትግል በላብ እና በደም ጎርፍ ውስጥ ሊያሰጥመው ይችላልም ይላል ፦

“ነገር ግን የጭቆና ፖሊሲ እዛኽ ጋር ብቻ አያቆምም። ከጭቆና “ስረዓት” ሕዝብን በሕዝብ ላይ ወደ ማስነሳት ፤ የጭፍጨፋ እና የዘር ማጥፋት ሰረዓት የአመራበት ግዜ ጥቂት አይደለም። በእርግጥ የኋላኛው አጋጣሚ በኹሉ ቦታ እና ኹል ግዜ የእሚቻል አይደለም ፤ ሲቻል ግን - መሠረታዊ የሆኑ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በአልተከበሩበት ኹኔታ ውስጥ - ብዙ ግዜ እጅግ አስፈሪ በኋሪ የእሚላበስ እና የሠራተኛውን አንድነት በደም እና በላብ ለማስጠም የእሚያሰጋ ነው።”

“But the policy of persecution does not stop there. It not infrequently passes from a “system” of oppression to a “system” of inciting nations against each other, to a “system” of massacres and pogroms. Of course, the latter system is not everywhere and always possible, but where it is possible – in the absence of elementary civil rights – it frequently assumes horrifying properties and threatens to drown the cause of the unity of the workers in blood and tears. [125]”

ከእዚኽም የተነሳ ስታሊን በጠቅላላው በንዑስ ብሔርተኝነት ላይ የአለውን ትችት ፤ በእዚኽ መልኩ አስቀምጦታል ፦

“ስለ እዚኽ ፦ ብሔርተኛ ዓይነቱ አደረጃጀት የብሔርተኛ ጠባብ ጭንቅላት መፍለቂያ እና የቆሞ መበስበሻ ትምህርት ቤት ነው።”

“Therefore, the national type of organization is a school of national narrow-mindedness and stagnation. [125]”

በእዚኽ መልኩ ፤ የራስን እድል በራስ መወሰን መብት ፤ ልዩ ጠባይ ለአላቸው ለእሚባሉ ሕዝብ ሲሰጥ ፤ ለማርክሲስታዊ የሠራተኛው አብዮት አሉታዊ ተጽኖ ነው የእሚኖረው ምክንያቱም ፤ ሕዝብን በሕዝብ ላይ በማነሳሳት የዘረ መጠፋፋት ሊያስከትል ከመቻሉ እና ይኽ ሕዝብን መከፋፈል ሠራተኛው በአንድነት እንዳይቆይ ከመከፋፈሉ በአሻገር ፤ ሊተገበር የእማይችል መሬት ላይ ከአለው ኹኔታ ጋር የእማይጣጣም እና አንዳንዴም ሕዝብን በሕዝብ ላይ ማስነሳትን ሊያመጣ ይችላል የእሚለው ስታሊን ፤ የብሔራዊ ጭቆና ብቸኛው እና ኹነኛው መፍትኼ ዴሞክራሲን ማስረጽ እንጂ የቱም ዓይነት (ባሕላዊም ሆነ ፖለቲካዊው) የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ አይደለም ይላል ፦

“በጠቅላላውም አንድ ሰው በእርግጠኝነት እንደ እዚኽ ማለት ይችላል ፤ አንድ ሐገር ይበልጥ ዴሞክራሲያዊት እየሆነች ስትኼድ የብሔረሰቦች ነጻነት ላይ የእሚደርሰው ጫና እየቀነሰ እና ይኽን መሰሉ ጫና እንደ አይደርስ የእሚያደርገው ዋስትናም ከግዜ ወደ ግዜ እየጎለበተ የእሚኼድ ነው።…ስለ እዚኽም ፤ በንዱ[9] ተቋማቱ[10] ለብሔረሰቦች የባሕል እድገት በራሳቸው ዋስትና ናቸው ሲል የተሳሰተ ወይንም ኃሳዊ አቋም እየያዘ ነው ማለት ነው።”

“One may say with certainty that the more democratic a country is the fewer are the encroachments made on the freedom of nationalities and the greater are the guarantees against such encroachments. … Thus, the Bund adopts a false position when it asserts that institutions by themselves are able to guarantee complete cultural development for nationalities. [125]”

በእዚኽ ስታሊን እየ አለ የአለው ፤ አንዳንድ የኦስትሪያ ማርክሲስቶች ፤ የቋንቋ ፣ የባሕል ፣ ልዩነት በኦስትሪያ ውስጥ የፈጠረውን ችግር ፤ እያንዳንዱ ብሔር የራሱ የባሕል እና የቋንቋ ተቋም አቋቁሞ ፤ ባህሉን እና ቋንቋውን እንዲያሳድግ ቢፈቀድለት ችግሩ ይፈታል ማለታቸው ስህተት ነው ፤ ይኽ አካኼድ እንዲያውም መከፋፈልን አና ትርፍ አልባ መቧደንን ነው የእሚያመጣው ፤ በቋንቋ ፣ በባህል ፣ ወዘተ ፤ ልዩነት የእሚመጣ ችግር መፈታት የአለበት ጠቅላላው የዜጎችን የሰብአዊ እና የዴሞክራሲያዊ መብትን በማስፋፋት ነው እየ አለ ነው።

“ብዝኃኑ አናሳውን ይጨቁናሉ ተብሎ ሊሰጋ ይችላል። ይኽ ስጋት ተቀባይነት የእሚኖረው አሮጌው ስረዓት በአንድ ሐገር የእሚቀጥል ከሆነ ብቻ ነው። ለሐገሪቱ ፍጹም ዴሞክራሲ ስጣት የእዚኽ ስጋት ምንጭ እልም ብሎ ይጠፋል።”

“It may be feared, therefore, that the minorities will be oppressed by the national majorities. But there will be ground for fear only if the old order continues to prevail in the country. Give the country complete democracy and all ground for fear will vanish. [125]”

“አናሳው የእሚከፋው ብሔራዊ አንድነት ስለሌለው ሰአይሆን የአፍ መፍቻ ቋንቋውን የእሚጠቀምበት መብት ስለሌለው ነው። የአፍ መፍቻ ቋንቋውን የእሚጠቀምበት መብት ስጠው መከፋቱ በራሱ ግዜ ይተናል።

አናሳው የእሚከፋው ብሔራዊ አንድነት ስለሌለው ሰአይሆን የሕሊና ነጻነት (የኃይማኖት ፣ ነጻነት) ፣ የመንቀሳቀስ ፣ ወዘተ ፣ ነጻነት ስለሌለው ነው ፤ እነ እዚኽን ነጻነቶች ስጠው መከፋቱን ያቆማል።”

“A minority is discontented not because there is no national union but because it does not enjoy the right to use its native language. Permit it to use its native language and the discontent will pass of itself.

A minority is discontented not because there is no national union, but because it does not enjoy liberty of conscience (religious, liberty), liberty of movement, etc. Give it these liberties and it will cease to be discontented. [125]”

ለእዚኽም ማሳያ ፤ ስዊዘርላንድ ውስጥ አናሳ ቁጥር የአለ፟ው የጣሊያን ማሕበረሰብ አለ ፤ ይኽ ማሕበረሰብ ግን ፤ ከስዊዘርላንድ ዴሞክራሲያዊነት የተነሳ ብሔራዊ ጭቆና ደረሰበት ሲባል ሰምተን አናውቅም ይላል ስታሊን ፦

“በእዚኽ ጉዳይ ስዊትዘርላንድን ማንሳት አያስፈልግም ፤ ምንም እንኳን የቡርዥዋ ዴሞክራሲ ቢሆንም ፤ በዳበረው ዴሞክራሲያዋ ምክንያት ፤ ብሔረሰቦች አናሳ ይኹኑ ብዙኃን በነጻነት ይኖራሉ።… በዴሞክራሲያዊዋ ስዊዘርላድ ይኽ መሆን የቻለው እንዴት ነው ? ስፕሪንገር በእሚለው መሠረት “ብሔራዊ(ነገዳዊ) ምክርቤት” የእሚባሉ ለእዚኽ ዓላማ የተቋቋሙ የባሕርል ተቋማት ስለ አሉ ነው ? አይደለም ፤ ምክንያቱም ፦ እንደ እዚኽ ዓይነት ተቋማት በእዚያኽ ስለ ሌሉ። ነገር ግን ፤ በእዚያኽ አናሳ ቁጥር የአላቸው ጣሊያኖች ፤ ከእዚኽ የተነሳ ባሕላዊ ጥቅማቸው ተጎድቷል? ጥቅማቸው ተጎድቷል የእሚል እሮሮ ግን ሰው እየሰማ አይደለም።”

“There is no need to mention Switzerland, where, thanks to her highly developed, although bourgeois democracy, nationalities live in freedom, whether they are minority or a majority…. But what is the position in this respect in democratic Switzerland, for example? Are there special cultural institutions in Switzerland on the pattern of Springer’s “National Council”? No, there are not. But do not the cultural interests of, for instance, the Italians, who constitute a minority there, suffer for that reason? One does not seem to hear that they do. [125]”

ስለ እዚኽ ፦ እንደ ስታሊን የብሔር ጭቆና ከአለ የእሚፈታው በየትኛውም ዓይነት የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ሰአይሆን ፤ ፍጹም ዴሞክራሲ ወይንም ዴሞክራሲያዊ እና ሰብዓዊ መብቶች (Civil Rights) በማስፋፋት ነው። ብሔራዊ ጭቆናን ለመታገል በእሚል ብሔርተኛ የሆነ የባሕል ወይንም ፖለቲካዊ ተቋም መመሥረት በየትኛውም ዓይነት ፖለቲካዊ ርዕዮት ውስጥ ከተጨባጭ ኹኔታው ጋር በተጣጣመ መልኩ ሊተገበር የእማይችል ፣ ሕዝብን የእሚከፋፍል እና አንዳንዴም የዘር ጭፍጨፋ መሰል እልቂቶችን ሊያስከትል የእሚችል አፍራሽ ፖለቲካዊ አካኼድ ነው እንደ ስታሊን።

ከእዚኽ መሰሉ ትንታኔ በአሻገርም ግን ፤ አንድ ግዜ የሳተን ኃይል መመለስ ከባድ ሆኖ እንጂ ፤ ሕወሐት በኢትዮጵያ ውስጥ የአለው ዋነኛ ቅራኔ በነገዶች መካከል የአለ፟ ቅራኔ ነው ብሎ ሲለፍፍ ፤ ከላይ ከገለጽነው ከኢትዮጵያ የወቅቱ የነገዳዊ መስተጋብር ኹኔታ በአሻገር ፤ በራሱ በሕወሐት ውስጥ በዘመኑ ኹሉ የፈተኑትን ችግሮች ብንመለከት ፤ ከአማራ ፣ ከአፋር ፣ ከኤርትራ ወይንም ከወላይታ ሕዝብ ጋር የገባው ቅራኔ ሳይሆን ፤ ከእራሱ የትግራይ ተወላጆች የመጣ መሆኑ ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ዋነኛው ቅራኔ ነገዳዊ ቅራኔ የእሚለው እምነቱ ፤ ድርቅና እንጂ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ፣ ኢከነሚያዊ ፣ ማሕበራዊ ፣ ወዘተ ፤ ምክንያት የሌለው ባዶ አቋም መሆኑን ሊያሳዩት ይገባ ነበር።

ሩቅ ሳንኼድ ፤ ሕወሐት በድርጅትነት ታሪኬ ለመጀመሪያ ግዜ የአጋጠመኝ ቀውስ (ሕንፍሽፍሽ) የእሚለውን ብንወስድ ፤ ከመጀመሪያው ወታደራዊ ስልጠና በኋላ ፤ የተደረገው የመሳሪያ ክፍፍል እና የኃላፊነት ድልድል ፤ በድርጅቱ ውስጥ የነበሩ ከገበሬው የሕብረተሰብ ክፍል የመጡትን ሰዎች ፤ ጥሩ ጥሩውን መሳሪያ እና ኃላፊነት ፤ ወረቀት ላይ መጻፍ እንጂ ጠብ መንጃ መተኮስ ለእማይችለው ተማሪ ሰጡት በእሚል ፤ የሕወሐት መሥራች አባት በእሚባለው ስኹል ታናሽ ወንድም መሪነት ፤ ገበሬው የታጋዩ ክፍል ተማሪውን የታጋዩን ክፍል ለመገደል በመነሳታቸው የተከሰተ ነው።

የነገድ ቅራኔ የኢትዮጵያ ጠንቅ ነው በእሚለው ድርጅት ውስጥ የመደብ ቅራኔ ሊያፈርሰው ተነሳበት ።

ይኽ ቀውስ ዓይነተኛ የመደብ ግጭት ማሳያ እንጂ የነገዳዊ ቅራኔ የወለደው ቀውስ አይመስልም ፤ ይኽም በመሆኑ ሕወሐት የትግራይ ሕዝብ ዋነኛው ችግር ፤ ከሌላዊ ኢትዮጵያዊ ሕዝብ የእሚደርስበት መገለል ነው የእሚለው አቋሙ ባዶ ጉም መሆኑን ሊያሳየው ይገባ ነበር ፤ ምክንያቱም በእዚኽ መልኩ በራሱ በትግራይ ተወላጆች መካከል ከተፈጠረው ቅራኔ የባሰ ቅራኔ የትግራይ ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የገባበትን ኹኔታ ሊያቀርብ ስለ እማይችል።

ከእዚያኽ በመቀጠል ሕወሐት የተጋጨው እና ከመጋጨትም አልፎ የተጋጨውን ድርጅት የደመሰሰው የሌላ አከባቢ ድርጅት ሳይሆን ትግራይን ከኢትዮጵያ መገንጠል አላማዬ ነው የእሚልን ግገሐት (ግንባር ገድሊ ሐርነት ትግራይ) የእሚባልን የትግራይ ድርጅት ነው። ሕወሐት ይኽን ድርጅት ትጥቁን የአስፈታኹት እና በፍትኃዊ ዳኝነት አመራሮቹን የረሸንኹት ፤ የእዚኽ ድርጅት አመራሮዎች ፤ የድርጅታቸው አባል የሆኑ ሌሎች የትግራይ ተወላጆችን ፤ በስልጣን ጥመኝነት በተለያየ ግዜ የአለ አግባብ ስለ ገደለ ነው ብሎ ያስቀምጣል።

ሕወሐት ይኽንን የትግራይን ድርጅት ለመደምሰስ የተነሳበት ምክንያት ምንም ይኹን ምን ግን ፤ በእራሱ ምስክርነት ፤ በእነ እዚኽ የትግራይ ተወላጆች ላይ እርምጃ የወሰደው ሌላ የኢትዮጵያ ነገድ ወይንም አካል ሳይሆን ፤ የራሱ የትግራይ ተወላጆች ናቸው።

እንደ ደገናም ፤ ሕወሐት የራሱን የትግራይን ልጆች አለአግባብ ረሽኗል የእሚለውን ጉዳይ ከሌሎች ፖለቲካዊ ምክንያት ጋር አዳብለው ነው ፤ በድርጅቱ ታሪክ ኹለተኛ የእሚባለውን እና ድርጅቱን ለኹለት ለመሰንጠቅ የሞከረ ቀውስ የእሚባለው ኹለተኛው ሕንፍሽፍሽ የተከሰተው።

ከእዚያኽ በመቀጠልም የሕወሐት መሥራች እና አባት የእሚባለውን ስኹልን የገደለው ጠርናፊት የእሚባል ሌላ የትግራይ ድርጅት ነው። ሕወሐትም ይኽንን የስኹልን ግድያ ለመበቀል ነው ፤ ወደ አምስት መቶ የእሚጠጋ ወታደር የነበረው እና ጠርናፊት የእሚባለው ድርጅት ላይ ድንገት ዘምቶ ድርጅቱን የአጠፋው።

ከእዚያኽም በኋላ ፤ ከሕወሐት ጋር ለረዥም ግዜ የተዋጋው እና ሌላውን እና ተወዳጁን መሐሪ ተክሌ (ሙሴ) የእሚባለውን የድርጅቱን መሪ የገደለው ፤ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሕብረት (ኢዴሕ) የእሚባለው ድርጅት የእሚመራው የነበረው ፤ የቀድሞ የትግራይ መሪ በነበሩት በልዑል መንገሻ ነበር።

እንደ ገናም ሕወሐትን በእኔ ስር ተጠቃለል የለም በአንተ ስር አልጠቃለልም ይልቁንም ትግራይን ለቀኽ ውጣልኝ እና ከአባቶቼ እና ከራሴ ትውልድ ስፍራ የት ሊኽድልህ በእሚል የቅርብ ምክንያት ተጋጭተው ከ3 ዓመታት ላላነሰ ከሕወሐት ጋር የተዋጋው ኢሕአፓ መሪዎች እና አንዳንድ ወሳኝ አባላቱ የትግራይ ልጆች ናቸው። የኢሕአፓ ቀዳሚ መሥራች ብርኃነ መስቀል ረዳ ፣ እና የድርጅቱ ተከታታይ መሪዎች ተስፋዬ ደበሳይ ፣ ዘሩ ክኽሸን የትግራይ ተወላጆች ናቸው። ሕወሐት እና ኢሕአፓ በእሚታኮሱበት ግዜ ፤ ዘሩ ክሕሸን የኢሕአፓ መሪ ነበር።

ሕወሐት በረኃ ከወረደም በኋላ ከመቶ ከእማይንሱ ሽፍታዎች ጋር የተዋጋው ፤ በትግራይ ከተንሰራፉ የትግራይ ሽፍታዎች ጋር እንጂ ከሌላው የኢትዮጵያ ነገድ ሽፍታዎች ጋር አይደለም።

ሕወሐት በታሪኩ ፤ እንደ ማንኛውም ጎሬላ ከኢትዮጵያ መንግሥት ውጭ ትግራዊ ከአልሆኑ የፖለቲካ ቡድን ጋር የተዋጋው ፤ ተሐኤ (ተጋድሎ ሐርነት ኤርትራ) ከእሚባል የሻዕብያ ተቀናቃኝ ከሆነ የኤርትራ ነጻ አውጪ ግንባር ጋር ነው ፤ እሱም ነገድን መሠረት በአደረገ ቅራኔ በኤርትራ እና በትግራይ ሕዝብ መካከል በነበረ ግጭት ሳቢያ ሳይሆን ፤ ተሐኤ (ተጋድሎ ሐርነት ኤርትራ) ከሌላው የኤርትራ ነጻ አውጪ ግንባር ፥ ሻዕብያ ጋር ተቃርኖ ውስጥ በመሆኑ እና ሕወሐት ከሻዕቢያ ጋር በማበሩ እንዲኹም ተሐኤ (ተጋድሎ ሐርነት ኤርትራ) እንደ ግገሐት ፣ ኢዴሕ የመሳሰሉ ሌሎች የሕወሐት ተቀናቃኝ የትግራይ ፖለቲካዊ ብድናትን ያግዝ ስለ ነበረ ነው ።

በአጭሩ ሕወሐት በኢትዮጵያ በነገዶች መካከል የአለው ቅራኔ ዋነኛው እና ከፍተኛው ቅራኔ ነው ሲል ፤ ራሱ ከሌሎች የትግራይ ተወላጆች በእሚመሩ ፖለቲካዊ እና ማሕበራዊ ተቋማት ጋር የገባውን ግጭት እንደ መማሪያ ቢወስድ ኖሮ ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የአለው (ከአለ፟ም) የነገድ ቅራኔ ፤ በነገዶች አባላት መካከል እርስ በእርሳቸው ከእሚያደርጉት እና ሊኖር ከእሚችለው በላይ የከፋ በአለመሆኑ ፤ ነገዳዊ ቅራኔ ተኮር የሆነው ፖለቲካዊ ፕሮግራሙ በፍጹም የኢትዮጵያን የወቅቱን ወይንም ታሪካዊውን ኹኔታ የእማያንጸባርቅ መሆኑን ሊያስተምረው ይገባ ነበር።

የሆነ ሆኖ ፤ ሕወሐት አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ በመሆኑ እና በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፕሮግራሙ ላይ ይበልጥ የአተኮረበት የነገዳዊ ብሔርተኝነት ፕሮግራም ፤ ከሌሎቹ የወቅቱ የኢትዮጵያ አብዮተኞች በጥቃቅን ጉዳዮች ከአልሆነ ይኽ ነው የእሚባል ልዩነት የሌለው በመሆኑ ፤ ምንም እንኳን ከእላይ እንደ አልኹት ፤ በ20ኛው ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ ውስጥ ሐገርን በማዳን ሊገለጽ የእሚችለውን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግድ የእሚል እና ሕወሐት እንደ እሚለው በኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ጥያቄ ማንሳት የእሚያስችል የማሕበረ ኢከነሚ እድገት በአለመኖሩ እና ነገዳዊ ብሔርተኝነቱን (Ethnonationalism) ለእዛውም በትጥቅ ትግል ለማራመድ ግድ የእሚል ምንም ዓይነት ገኃዳዊ ኃቅ በአይኖርም ፤ የሕወሐት ፕሮግራም እንደ ደርጉ እና ሌሎቹ የወቅቱ አብዮተኞች ኹሉ ፤ ለኢትዮጵያ የእማይበጅ እና በኢትዮጵያ ላይ የታሪክን መንኮራኩር ወደ ኋላ የእሚያንኮራኩር አካኼድ በመሆኑ ሊወገዝ የእሚገባው እንጂ ሕወሐትን ከሌሎቹ የወቅቱ አብዮተኞች ነጥሎ ትግራይን መገንጠል የእሚፈልግ ፣ ሌሎች በኢትዮጵያ ውስጥ የመገንጠልን ጥያቄ እያነሱ ከኢትዮጵያ እንዲገነጠሉ ለማድርግ የእሚሰራ ጸረ ኢትዮጵያ ድርጅት ነው የእሚያስብለው አይደለም።

በእዚኽ የሕወሐት ፕሮግራም ገልጻ ላይ ጥያቄ ሊያስነሱ የእሚችሉት ፦

  • ሕወሐት በእኛ አቆጣጠር በ1968 ዓ.ም. የፖለቲካ ግቤ ከኢትዮጵያ ውስጥ ነገዳዊ ጭቆናን ማስወገድ ሳይሆን ነጻ ትግራይን መመሥረት ነው የአለበት እና
  • ከኤርትራ ሕዝብ በላይ ለኤርትራን ነጻነት ተቆርቋሪ የሆነበት እና ፖለቲካዊ የስልጣን ድንበሩን ተላልፎ የኤርትራ ሕዝብ ሪፍረንደም እንዲያደርግ እና የኤርትራ ሕዝብ በሪፍረንደም ለመገንጠል ከወሰነ በኋላ የኤርትራን ነጻነት እውቅና ለመስጠት ከዓለም ሕዝብ መንግሥታት ኹሉ ቀዳሚው መሆኑ ናቸው።

እነ እዚኽ ኹለት ታሪካዊ ክስተቶች የሕወሐትን ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ጥያቄ ውስጥ ሊያስገቡ የእሚችሉ ቢሆንም ፤ በእኔ እምነት እነ እዚኽን ክስተቶች ጠጋ ብለን የተመለከትናቸው እንደው ፤ የሕወሐትን ጠባብነት እና ግዜያዊ ጥቅመኝነት ችግር የእሚያንጸባሩቅ እንጂ የሕወሐትን ገንጣይ አስገንጣይነት እና ጸረ ኢትዮጵያዊነት የእሚያንጸባርቁ አይመስሉም።

የመጀመሪያውን ጉዳይ ማለትም ፦ ነጻ ትግራይን የመመሥረቱን ጉዳይ የተመለከትን እንደሆን ፤ ሕወሐት ይኽን ፕሮግራም ፤ ነጻ ትግራይን መመሥረት እፈልጋለኹ ይል የነበረውን ግገሐት (ግንባር ገድሊ ሐርነት ትግራይ) በደመሰሰ ማግስት እና ለ6 ወር ብቻ የያዘው እና ከስድስት ወር በኋላ የተተወ ፤ ከእዚያኽም ከአስር ዓመት በኋላ ፤ ማለትም በእኛ አቆጣጠር በ1977 ዓ.ም. በድርጅታዊ ምልዓተ ጉባኤ ከአስር አመት ቀደም ብሎ ይኽንን መሰል ዝንባሌ ፤ ማለትም ፦ ነጻ ትግራይን ለመመሥረት መፈለጉ ፤ የጠባብነት ችግር ውጤት መሆኑን ገምግሞ በግልጽ ራሱን በግልጽ የአወገዘ በመሆኑ ፤ ሕወሐት በራሱ ግንዛቤ ተራምዶ ወይንም ፖለቲካዊ ፣ ታሪካዊ ፣ ወዘተ ፤ ገኃድ ኃቆች አስገድደውት ይኽንን ፕሮግራም ይዞ ሊቀጥል እንደ እማይችል በግልጽ የአመነ በመሆኑ ፤ ገጠመኙ ወይንም ታሪካዊው ክስተቱ ፤ የሕወሐትን ኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ይበልጥ የእሚያጠናክር እንጂ ገንጣይ ፣ አስገንጣይ እና ጸረ ኢትዮጵያ የእሚያስብለው አይመስልም።

በ46 ዓመታት የድርጅታዊ እድሜ ውስጥ አንድ አቋም ለ6 ወር እድሜ ብቻ ይዞ ፤ ከእዛኽም ይኽን ፕሮግራም በስህተትነት ከ45 በላይ ለሆኑ አመታት እንደ አወገዙ መቆየት ፤ የሕወሐትን ብሔርተ ኢትዮጵያዊነት የእሚያጸና እንጂ ተቃራኒውን የሚያጸና አይሆንም።

ኤርትራን በተመለከተ ፤ ሕወሐት ከኤርትራ ሕዝብ በላይ የኤርትራ ሕዝብ ነጻነት ተቆርቋሪ ሆኖ የሻዕብያን አቋም ከሻዕብያ ከእራሱ በላይ ማራገቡ ፣ የኤርትራን ሪፍርንደም በመፍቀድ እና በዴሞክራሲያዊ ሕዝባዊ ምርጫ ሳይሰየም በፊት የኤርትራን ነጻ ሐገርነት እውቅና ለመስጠት ቀዳሚው ሐገረመንግሥት በመሆኑ ፤ በኤርትራ ጉዳይ አጼ ምንሊክ የሰሩትን ዓይነት ታሪካዊ ስሕተት ለመሥራቱ ምንም በአያጠራጥርም ፤ ይኽ የሕወሐት ስህተት ሕወሐት ገንጣይ አስገንጣይ ነው የእሚለውን ክስ ማጠናከሪያ ሆኖ መቅረብ የእሚችል አይደለም።

ሕወሐት የኤርትራ ሕዝብ አፈሙዝ አያዘቀዝቅም እና መሰል ቅስቀሳዎች በማድረግ ፤ ሻዕብያ ከደርግ መንግሥት ጋር ድርድር ውስጥ እንደ አይገባ ከፍተኛ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ መክፈቱ ወይንም ከኤርትራ ሕዝብ በላይ ለኤርትራ ሕዝብ ተቆርቋሪ መስሎ መታየቱ ፤ ከደርግ ጋር በእሚደረገው የትጥቅ ትግል ኹነኛ አጋሩን ለአለማጣት እና ድህረ ደርግ የስልጣን ተቀናቃኝ ሊሆነው የእሚችለውን ኃይል ከኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ምህዳር ውስጥ ለማስወጣት ከመፈለግ ወይንም ከጠባብ ጥቅመኝነት እንጂ ለኤርትራ ነጻነት ከመቆርቆር ይመነጫል ተብሎ አይታሰብም።

ሕወሐት ምንም እንኳን በራሳቸው የትግራይ ተወላጅ በሆኑ (በአብዛኛው) ሰዎች ቢመሠረትም ፤ ሻዕብያ በወታደራዊ እና በፖለቲካው መስክ ፤ ሕወሐት እንደ ድርጅት እንዲያቆጠቁጥ እና ህልውናው እንዲቀጥል ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።

ይኽም ብቻ ሰአይሆን ፤ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ1973 ዓ.ም. ገደማ በኋላ ፤ ከሻዕብያ እና ከሕወሐት በስተቀር ደርግን በፖለቲካውም ሆነ በወታደራዊው መስክ ሊገጥመው የእሚችል ሌላ ምንም ዓይነት ተቃዋሚ የአልነበረ በመሆኑ ፤ ሻዕብያ ከደርግ ጋር ቢደራደር እና ነፍጥ ቢያወርድ ፤ ጉዳዩ የሕወሐትን ክስመት ሊያስከትል የእሚችል በመሆኑ ፤ ሕወሐት ከሻዕብያ እና ከኤርትራ ሕዝብ በላይ ፤ የኤርትራ ሕዝብ የነጻነት ጥያቄ ከኤርትራ ሕዝብ በላይ ያሳስበኛል ብሎ ፤ ከባለቤቱ የአወቀ ቢሆን ፤ ይኽ አቋሙ ፤ ከኃይል ሚዛን ስሌት እንጂ ፤ ከጸረ ኢትዮጵያዊነት አንጻር ብቻ መታየት የእሚችል አይሆንም።

ጉዳዩ ሕወሐት በኢትዮጵያ ውስጥ ለፖለቲካ ስልጣን የእሚጋደል የስልጣን ፈላጊ ድርጅት እንጂ የጸረ ኢትዮጵያዊነቱን የእሚያሳይ አይመስልም።

ከድልም በኋላ ፤ ሕወሐት የኢትዮጵያ መንግሥት ሲሆን ፤ የኤርትራን ሪፍረንደም ለመፍቀድ እና ከሪፍረንደም በኋላ ለነጻ ኤርትራ እውቅና ለመስጠት ቀዳሚው ሉዓላዊ መንግሥት ለመሆን የተሯሯጠበት አካኼድ ፤ በሳል የሆነ የወቅቱን የኃይል ሚዛን ንባብ (ጠባብም ቢሆን) እና የድርጅቱን ግዜያዊ ጥቅመኝነት በሽታ የእሚያንጸባርቅ እንጂ ገንጣይ ፣ አስገንጣይ እና ጸረ ኢትዮጵያ ነው የእሚያስብለው አይመስልም።

እንደ እሚታወቀው ፤ በሕወሐት እና በሻዕብያ መካከል ፤ በተለይ መጀመሪያ ላይ የደቀ መዝሙር እና የመምህር ዓይነት ግንኙነት የነበረ እና የኹለቱም ድርጅቶች ወታደራዊ አቅም እና ድል አብሮ ያደገ በመሆኑ ፤ በእኛ አቆጣጠር በ1983 ዓ.ም. ሕወሐት አዲስ አበባ ሲገባ በሻዕብያ ታንከኞች የታጀበ እና ሻዕብያም ከሕወሐት ቀደም ብሎ አስመራን እና መላውን ኤርትራን የተቆጣጠረ በመሆኑ ፤ በወቅቱ በአለው የኃይል ሚዛን ፤ በመላ ሐገሪቱ ከ100 ሺ በላይ የእሚሆን የደርግ ሠራዊት ፈርሶ በተበተነበት እና ሕወሐት ራሱን እንደ መንግሥት ለማቋቋም ደፋ ቀና በእሚልበት በእዚያኽ ወቅት ፤ ከሻዕብያ ጋር ምንም ዓይነት ግጭት ውስጥ ለመግባት መሞከር ከአጉል ጀብደኝነት እና ራስን ለማጥፋፋት ከመሯሯጥ ተለይቶ ሊታይ ስለ እማይችል ፤ የወቅቱ ኹኔታ ሕወሐትን ዝም ከማለት የአለፈ ምንም ማድረግ እንደ እማይችል የእሚነግረው ነው።

ይኽም በመሆኑ ፤ ሕወሐት ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ሳይገባ በፊት ፤ ሻዕቢያ ደርግን ከኤርትራ አስወጥቶ ፤ ሕወሐት አዲስ አበባ ገብቶ ስልጣን ሲይዝ ፤ ሻዕቢያ ከሕወሐት አዲስ አበባ መግባት ትንሽ ቀደም ብሎ መላው ኤርትራን በወታደራው ኃይል ተቆጣጥሮ የራሱን አስተዳደር አቁሞ ፤ በግዜያዊነትም ቢሆንም ኤርትራን የመያዙን ሥራ በራሱ ሰርቶ የጨረሰ በመሆኑ ፤ ሕወሐት ኤርትራን አስገነጠለ ሊባል አይችልም።

ይኽን ተከትሎ ግን ፤ ሕወሐት ኤርትራዊያን በእዚኽ በተዛባ እና በተወናበደ የማሕበራዊ ፖለቲካ ምሕዳር ውስጥ ሆነው ሪፍረንደም እንዲያደርጉ እና ከእዚያኽም በኋላ ኤርትራ ከኢትዮጵያ የተገነጠለች አዲስ ሐገር መሆኗን እውቅና በመስጠት ቀዳሚ ለመሆን በመሯሯጡ ፤ ልክ አጼ ምንሊክ የሰሩትን ዓይነት ታሪካዊ ስኽተት ሰርቷል።

ምክንያቱም ፦ ሕወሐት ኤርትራን ቆርሶ ለሻዕቢያ ባይሰጥም እና በወቅቱ ኃይል ሚዛን አስገዳጅነት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ብትገነጠልም ፤ ሻዕቢያ ኤርትራን ለመገንጠል የተነሳበት ታሪካዊ እና ፖለቲካዊ ትንታኔ ግን ታሪካዊም ሆነ ፖለቲካዊ ብስለት የእማይታይበት ግልብ ፖለቲካዊ አቋም እንደ ሆነ የኢትዮጵያን ታሪክ የእሚያውቅ እና መሠረታዊ የሆነ አከባቢውን ፖለቲካ ግንዛቤ የአለው ማንም ሰው ሊረዳው የእሚችለው በመሆኑ ፤ ሕወሐት በእዚያኽ አስቸጋሪ እና የአለተረጋጋ የሐገሪቱ ፖለቲካዊ ምሕዳር ውስጥ የኤርትራን ሪፍረንድም ተሯሩጦ መፍቀድ እና ከእዚኽም ሪፍረንደም በኋላ ኤርትራ ነጻ ሐገር ነች በእሚል እውቅና ለመስጠት መሽቀዳደም አልነበረበትም።

የሻዕብያ ሰዎች ፤ ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት በመሆኗ ከኢትዮጵያ መገንጠል አለባት ሲሉ ከእሚያቀርቧቸው ታሪካዊ ኹነቶች መካከል ፦

  1. የዛሬዋ ኢትዮጵያ አጼ ምንሊክ የሰሯት ነች የእሚለውን ሰንካላ አባባል ተከትለው ፤ ኤርትራ በታሪኳ የኢትዮጵያ አካል ሆና አታውቅም
  2. አጼ ምንሊክ ፤ እ.አ.አ. 1889 ዓ.ም. ጣሊያን ኤርትራን ይዞ እንዲቆይ እና ከመረብ እንደ አይሻገር በእሚል ከጣሊያን ወራሪ ጋር የኤርትራን ቅኝ ግዛትነት በመቀበል ስምምነት አድርገዋል
  3. ኤርትራ ከጣሊያን ወረራ አስቀድሞ ፤ ቢያንስ ከ16ኛው ምዕተ ዓመት አንስቶ በኦቶማን ተርኮች እና በግብጾች ቀኝ ስትገዛ የኖረች ናት
  4. በኤርትራ የነበረው የቀኝ ግዛት ለኤርትራ ሕዝብ ከሌላው ኋላ ቀሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተሻለ ማሕበረ ኢከነሚ ባለቤት እንዲሆን አስችሎታል

የእሚሉት ዋነኞቹ ናቸው።

እነ እዚኽ ከእላይ በሻቢያ ካድሬዎች የእሚቀርቡት የኤርትራን የኢትዮጵያ ቀኝነት እና የኤርትራን የመገንጠል ጥያቄ ተገቢ የእሚያደርጉ አስረጂ ተብለው የቀረቡ ሐተታዎች ፤ ከባዶ ፕሮፖጋንዳነት የአለፈ ከኤርትራ ታሪክ እና ነባራዊ ማሕበረ ኢከነሚ ኹኔታ ጋር ይኽ ነው የእሚባል ተጨባጭ ተዛማጅነት የአላቸው አይደሉም።

በእዚኽ መጽሐፍ የቀረበው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ታሪክ ዳሰሳ አጼ ምንሊክ ከ2 ሺ ዓመት በላይ የእሚቆይ ታሪክ የአላ፟ት ኢትዮጵያ የኋለኛው ዘመን ንጉሠ ንገሥት እና ከብዙዎቹ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ሐናፂ ከሆኑት የኢትዮጵያ ነገሥታት አንዱ የሆኑ እንጂ የኢትዮጵያ ፈጣሪ እንደ አልሆኑ ለማሳየት በቂ ይመስለኛል።

ይኽም አይበቃኝም የእሚል ማንም ሰው የኢትዮጵያ ታሪክ በአግባብ የተመዘገበ በመሆኑ የተወሰኑ የኢትዮጵያን ታሪክ ላይ የተጻፉ መጽሐፍትን ማገላበጡ የሻዕብያ ካድሬዎች ፕሮፖጋንዳ ባዶነት ሊያስረዳው ይችላል።

ይኽም በመሆኑ ፤ ኤርትራ እ.አ.አ. 1889 ዓ.ም. በጣሊያን ሙሉ በሙሉ ከተያዘችበት ግዜ በፊት የኢትዮጵያ አካል የአልሆነችበት ታሪክ የለም። ለእዛኽም ነው በኢትዮጵያ ዘውዳዊ ስረዓት ውስጥ ፤ እንደ አጼ ፣ ራስ ፣ ደጃዝማች ፣ ዋግሹም ፣ ወዘተ ፤ ባሕረ ነጋሽ የእሚለው የማዕረግ ስም ቢያንስ ከ500 ዓመታት በላይ የቆየ ቋሚ የማዕረግ ስም የሆነው።

ጣሊያኖች ቀይ የእሚል ትርጓሜ የአለውን የግሪክ ቃል ተከትለው ፤ በቀይ ባሕር ላይ የእሚገኝ የጣሊያን ቀኝ ግዛት ለማለት ፤ አከባቢውን ኤርትራ[11] ብለው እስከ እሚሰይሙት ፤ የዛሬው ኤርትራ ምድር ፤ በመረብ ወንዝ እና በቀይ ባሕር መካከል የእሚገኝ የኢትዮጵያ ግዛት በመሆኑ ፤ ባሕርመላሽ ወይንም ምድሪባሕሪ ተብሎ ይጠራ የነበረ በመሆኑ ፤ ይኽንን አከባቢ የእሚያስተዳድረው ሰው ፤ በኢትዮጵያ ዘውዳዊ ስረዓት ውስጥ ባሕረ ነጋሽ ተብሎ በእሚጠራው የሹመት ስም ለእሚታወቀው ሰው የእሚሰጥ የሹመት ስም ነው።

ለምሳሌ ፦ ከግራኝ ወረራ መቀልበስ በኋላ ፤ ክፍል ዓምስት እና ስድስት በእሚሉት የታሪካችን ክፍል ላይ እንደ አየነው ፤ የግራኝን ወረራ በመቀልበሱም ሆነ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ዝግመት ውስጥ የዘመነ መሣፍንት ፖለቲካን በማስጀመር ፤ ባሕረ ነጋሽ ይስኃቅ ፤ የነበረው ሚና እጅግ ወሳኝ የነበረ ነው።

በእርግጥ ባሕረ ነጋሽ ይስኃቅ ከአጼ ገላውዴዎስ ሞት በኋላ ፤ እኔ የእምደግፈው ሰው ይንገስ ብሎ በተለያዩ ግዜያት ፤ ከጀስዊቶች እና ከኦቶማን ተርኮች ጋር በማበር ፤ ከአጼ ገላውዴውስ በኋላ ከነገሡት አጼ ምናሴ እና አጼ ሰርጸ ድንግል ጋር የተዋጋ እና በእዛም የተሰዋ ቢሆንም ፤ የግጭቱ ምንጭ የኢትዮጵያ ፖለቲካ መመራት የአለበት በእዚኽ አግባብ ነው የእሚል ሐገራዊ (Domestic) እንጂ በኹለት አጎራባች ሐገሮች መካከል የነበረ አልነበረም። ባሕረ ነጋሽ ይስኃቅ የሐገሬ ፖለቲካ ያገባኛል ብሎ ነው የተጋጨው።

አጼ ዓምደ ጽዮንም ከባሕረነጋሽ ይስኃቅ 200 ዓመታት ቀደም ብሎ በ14ኛው ምዕተ ዓመት ከሸዋ ተነስቶ ምጽዋ ድረስ ኼዶ ተዋግቶ ሕዝቤን ታደግኹ እንደ አለ አይተናል።

ይኽም መዓከላዊው መንግሥት የተዳከመበትን ዘመነ መሳፍንቱን እንኳን እንመልከት ለማለት እንጂ የኢትዮጵያ ነገሥታት መናገሻ አክሱም ከነበረበት ወቅት እስከ ዘመኑ መሳፍንቱ የዛሬው ኤርትራ የኢትዮጵያ ግዛት አካል እንደ ነበር የወቅቱን የኢትዮጵያን ታሪክ በዳሰስንበት ክፍል ላይም ሆነ በሌሎች የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ በተጻፉ መጽሐፍት በግልጽ የተቀመጠ ነው።

በእርግጥ ከግራኝ ወረራ መክሸፍ በኋላ ፤ የኦቶማን ተርኮች ፤ ኢትዮጵያን በተለያዩ አቅጣጫ ማጥቃታቸውን በመቀጠላቸው ፤ በወቅቱ ኢትዮጵያ የተፈጠረባትን አንጻራዊ ደካማነት እና በአንጻራዊነት ቱርኮቹ በባሕር ኃይል የአላቸውን የበላይነት ተጠቅመው ፤ የቀይ ባሕር ወደቦች በተለይም ምጽዋን ይዘው ፤ ከእዚያኽ በመነሳት ወደ ዛሬዋ ኤርትራም ሆነ ወደ ሌላው የኢትዮጵያ አከባቢ ሰርገው ለመግባት ፣ አንጀኞችን ለማነሳሳት እና ለማስታጠቅ ፤ ለብዙ መቶ ዓመታት ሲጥሩ የነበረ መሆኑ ይታወቃል።

ኦቶማን ተርኮቹም ቢሆን የኤርትራን ወደቦች ተቆጣጠሩ እንጂ ዋናውን የኢትዮጵያ አካል የሆነውን የኤርትራ መሬት መላውን ኤርትራ ተቆጣጠሩ ሊባል በእሚችልበት አኳኋን አልያዙም።

ለመያዝ የተለያየ ሙከራ አድርገዋል ፤ ሰርገው እየገቡ ምሽግ ቆፍረው ተዋግተዋል ፣ ተላላኪ እና ሰርጎ ገብ ለማስታጠቅ እና ለማዝመት መኮረዋል ፤ በሞከሩ ቁጥር ግን ከአጼ ሰርጸ ድንግል አንስቶ እስከ አሉላ አባነጋ እና አጼ ዮሐንስ ከኢትዮጵያ ነገሥታት እና ጀነራሎቻቸው ጋር ለ4 መቶ ዓመታት ሲዋጉ ፤ በእዚኽም የረዥም ዘመን ውጊያ ፤ ሙከራቸው ኹሉ በሽንፈት እየተጠናቀቀ እግሬ አውጭኝ ሲሉ የነበረ በመሆኑ ፤ የኦቶማን ተርኮች እና የእነርሱ ተላላኪዎች (Minions) የነበሩት ግብጾች ፤ ቀቢጸ ተስፈኞች እንጂ ኤርትራን ቀኝ የገዙ የውጭ ኃይላት አልነበሩም።

በኤርትራ ትይዩ የአሉ የኢትዮጵያን ወደቦች እና አጎራባችች ድንበሮችን መቆጣጠር እና ዋናውን ኤርትራን (ምድሪባሕሪን) መያዝ ለየቅል ናቸው።

የኤርትራን ወደቦች ሰአይሆን ዋናውን የኤርትራን ምድር ለመጀመሪያ ግዜ ቀኝ የገዙት ፤ የአጼ ዮሐንስን የእ.አ.አ. 1889 ዓ.ም. መሞት ተከትሎ ፤ አውሮፓዊያኖቹ ጣሊያኖች ናቸው።

በታሪክ እንደ እምናውቀው ፤ አርፋጅ ቀኝ ገዢ የሆነችው ጣሊያን ፤ በጥቁር አፍሪካ ብቸኛ ቀኝ የአልተገዛች ሐገር ኢትዮጵያ በመሆኗ ፤ ቅኝ መያዝ የእምችለው ኢትዮጵያን ነው ብላ በማሰብ ቢያንስ ከወደ ዘመነ መሳፍንቱ ማብቂያ መዳረሻ ማለትም እ.አ.አ. 1830ዎቹ አንስታ በኢትዮጵያ እና አከባቢዋ ላይ አሰሳ ስታደርግ የነበረ በመሆኑ ፤ እ.አ.አ. በ1869 ዓ.ም. በአንድ የጣሊያን ካምፕኒ ስም በዛሬው አሰብ አከባቢ የገዛችውን ቦታ ፤ እ.አ.አ.በ1882 ዓ.ም. የጣሊያን መንግሥት ንብረት አድርጋ በመቀየር ፤ አሰብን ላይ የአለውን ይኽንን ቦታ የጣሊያን ግዛት በማድረግ ጀመረች።

በእዚኽ መልኩ ፤ ጣሊያን ወደ ዋናው የኢትዮጵያ ምድር ለመዘርጋት አሰብን አንገት ማስገቢያ አድርጋ ስትጠብቅ ፤ የኦቶማን ተርኮች የዓለም ልዕለ ኃያልነት በፖርቹጋል በኋላም በእንግሊዝ ከተተካ በኋላ ፤ እንግሊዞች ከአጼ ዮሐንስ ጋር የነበራቸውን ስምምነት ችላ ብለው ፤ ቱርኮች በ16ኛው ምዕተ ዓመት መጨረሻ አከባቢ የያዙትን ምጽዋ እ.አ.አ. በ1885 ዓ.ም. ሲለቁ ፤ እንግሊዞች ምጽዋን ለጣሊያን አሳልፈው ለመስጠት በመወሰናቸው ፤ ኹኔታው አሰፍስፋ አሰብ ላይ ስትጠብቅ ለነበረችው ጣሊያን ወደ ዋናው የኢትዮጵያ ምድር ለመግባት የተሻለ ኹኔታን ፈጠረላት።

ከእዚኽ በኋላ ፤ ጣሊያኖችም እንደ ቱርኮች ከምጽዋ እየተነሱ ወደ ዋናው የኢትዮጵያ ምድር (ኤርትራ) ለመግባት ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርጉ ፤ ከወቅቱ የኤርትራ ገዢ ከነበሩት ራስ አሉላ ጋር ተደጋጋሚ ውጊያ አድርገው ፤ ሙከራቸው በራስ አሉላ አሸናፊነት ስለ ከሸፈ ፤ ጣሊያኖቹ እንደ አሰቡት በቀላሉ ዋናውን የኢትዮጵያን ምድር መያዝ አልቻሉም።

ከእዚኽ በኋላ ግን ፤ ጣሊያኖቹ የአጼ ዮሐንስን ከፍተኛ የውጭ በተለይም የአውሮፓዊያንን ትብብር ፈላጊነት በመረዳታቸው ፤ በራሳቸው ተንኳሽነት የደረሰባቸውን ሽንፈት ፤ አሉላ አባ ነጋ እንደ ክርስቲያን ሳይሆን አምላክ እንድ ሌላቸው አረማዊያን ነው የእሚዋጋው እና ይኽም ኢትዮጵያን በአውሮፓዊያን አስጠልቷታል በእሚል ለአጼ ዮሐንስ በመክሰስ ፤ በአጼ ዮሐንስ እና በአሉላ አባነጋ መካከል የነበረውን ግንኙነት በማሻከር ፤ አሉላ አባነጋ ከአጼ ዮሐንስ ሽሽት ሸዋ ምንሊክ ጋር እንዲገቡ በማድረጋቸው ፤ በሰሜኑ ግንባር የአሉላ አባነጋ ከመሪነት መነሳት በወታደራዊ መስኩ ከፍተኛ የአመራር ክፍተት በመፍጠሩ ጣሊያኖቹ በምሥራቅ እና ደርቡሾቹ በምዕራብ ኢትዮጵያን እንዲያጠቁ የተመቻቸ ኹኔታ ፈጠረላቸው።

አጼ ዮሐንስም ደጀናቸውን አሉላ አባነጋን በማጣታቸው ፤ በእየ አቅጣጫው ተወጥረው ፤ ከምጽዋ ተነስቶ ወደ ኤርትራ ለመግባት ድንበር ላይ ምሽግ ቆፍሮ ከተቀመጠው የጣሊያን ጦር ጋር ለመዋጋት ወደ ኤርትራ ቢዘምቱም ፤ የጣሊያኑ ጦር ለ1 ወር ከምሽግ በአለመውጣት ትልቁ የአጼ ዮሐንስ ጦር በስንቅ እጥረት እና በሐሩርማ መልካዓ ምድሩ አስቸጋሪነት ምክንያት ተሰላችቶ እንዲመለስ ሲያደርግ ፤ ከእንግሊዞች ጋር በገቡት ውል ምክንያት ፤ በራስ አሉላ አዝማችነት ፤ በድርቦሾች ተከቦ የነበረውን የእንግሊዝ ጦር በማስለቀቃቸው የአቄሙት ደርቡሾች ፤ በእዚኹ ግዜ አጼ ዮሐንስን ለመበቀል በምዕራብ ጥቃት በመጀመራቸው ፤ ከእዚኽ የአንድ ወር ከበባ የተመለሱት አጼ ዮሐንስ ለእዚኽ የበቀል ጥቃት ምላሽ በደርቡሾች ላይ ሲዘምቱ ፤ መተማ ላይ በተደረገ እና በአሸነፉት ጦርነት አለ አግባብ ከአዋጊነት ይልቅ የተራ ወታደር ዓይነት ተዋጊ በመሆን ወደ ጠላት ምሽግ ሲገቡ በተባራሪ ጥይት ተመትተው እ.አ.አ. 1889 ዓ.ም. ተሰው።

አጼ ዮሐንስ በአሸነፉት ጦርነት በተባራሪ ጥይት ተመተው ከቀናት በኋላ ሲያርፉ ፤ በንጉሳቸው ሞት የተደናገጠው ጦራቸው ድሉን ከድል ሳይቆጥር ሲበተን ፤ ተሸናፊው የደርቡሽ ጦር መልሶ አሳዳጅ ሆኖ ፤ የንጉስን አስክሬን ከጠባቂዮቻቸው በመንጠቅ ፤ በታሪክ እንደ እምናውቀው ራሳቸውን ቆርጦ ወሰደ።

ድሮውንም ጣሊያኖቹ አኮብኩበው ስለ ነበር ፤ አጼ ዮሐንስ በእዚኽ መልኩ መተማ ላይ ሲሰው ፤ በሐገሪቱ ውስጥ የተፈጠረውን የስልጣን ክፍተት እና በመሐል ሐገር የነበረውን የስልጣን ፍትጊያ ተጠቅመው ፤ ከመረብ በላይ የአለውን ምድሪባሕር ኤርትራ ብለው ሰይመው ቀኝ ግዛታቸው አደርጉት።

ልክ እንደ ሕወሐቱ ፤ አጼ ምንሊክ ኤርትራ በጣሊያን ቁጥጥር ስር እንድ ትወድቅ ምንም የተጫወቱት ቀጥተኛ ሚና ባይኖርም ፤ ቦታው የኢትዮጵያ ታሪካዊ አካል እና ሕዝቡም ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ፤ የወቅቱን የኃይል ሚዛን እና በውጭ ግንኙነት የእሚያገኙትን ጥቅም አስበው በእሚመስል መልኩ ፤ ለጣሊያን የኤርትራ ቀኝ ግዛት እውቅና በመስጠት ፤ ከጣሊያን ጋር አንተም ከመረብ አትለፍ እና እኔም ከመረብ አላልፍም በእሚል የድንበር ውል በመዋዋላቸው ፤ ሕወሐት የሰራውን ዓይነት ታሪካዊ ስሕተት ሠሩ።

አጼ ምንሊክ ፤ የወቅቱ የኃይል ሚዛን እና የስልጣን ክፍተት አመቺ ኹኔታ ፈጥሮሎት ፤ ምድሪባሕርን ተቆጣጥሮ ኤርትራ የእምትባል የጣሊያን ቅኝ ግዛት የመሠረተውን የጣሊያን ጦር ቀጥታ መግጠሙ ፤ ከወታደራዊ ፣ ኢከነሚያዊ እና ፖለቲካዊ ስሌት አንጻር የእማያዋጣ ነው ብለው ቢያሰሉም እንኳን ፤ መርብን እንደ ጦር ግንባር (DMZ or Demilitarized Zone) ነበር ማየት የነበረባቸው እንጂ ከመረብ መለስ የአለውን ግዛት ግዛቴ እና ሕዝቡም ሕዝቤ ነው ብዬ የይገባኛል ጥያቄ አላነሳም የእሚል መሆን አልነበረበትም።

ስለ እዚኽ ፦ ምድሪባሕሪ ወይንም ኤርትራ ከ2 ሺ ዓመት በላይ በሆነው ታሪኳ ለመጀመሪያ ግዜ ከትልቋ ኢትዮጵያ ተነጥላ በባዕድ አስተዳደር ስር የገባችው እ.አ.አ. 1889 ዓ.ም. ነው።

ከእዚያኽ በኋላ ጣሊያን በኹለተኛው የዓለም ጦርነት ከጀርመን ጋር ስታብር ቆይታ በጦርነቱ ወቅት የኹለተኛው የዓለም ጦርነት ሳይጠናቀቅ በፊት ቀድማ በሽንፈት ከጦርነቱ ስለ ወጣች ፤ ጣሊያን እና የቀኝ ግዛቶቿ በዓለም ዓቀፉ ጸረ ናዚ እንቅስቃሴ ሕብረት ጦር ስር በመውደቁ ፤ የኹለተኛው ዓለም ጦርነት ላይ ከአሸናፊዎቹ ወገን የሆነችው እንግሊዝ ኤርትራን እ.እ.አ. በ1941 ዓ.ም. ከጣሊያን አስለቅቃ እስከ እ.እ.አ. 1950 ዓ.ም. በሞግዚትነት ስታስተዳድር ከቆየች በኋላ ፤ ጉዳዩ በተባበሩት መንግሥታት ታይቶ ፤ የኤርትራ ሕዝብ ሪፈረንደም አድርጎ ከኢትዮጵያ ጋር በፌደሬሽን እንዲቀላቀል ተደረገ።

ይኽም በመሆኑ የዛሬው የኤርትራ አከባቢ እና ሕዝብ ከነበረው 2 ሺ ዓመታት በላይ ታሪክ ከኢትዮጵያዊ እና ከወገኑ ተነጥሎ በባዕድ አስተዳደር ስር የሆነው ለ61/62 ዓመታት ብቻ ነው።

ከእዚኽ በኋላ በዓለም ፊት ኤርትራዊያን ሪፈረንደም አድርገው ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ኤርትራዊያንም ኢትዮጵያዊያን ዳግም ሆነዋል።

ይኽም በመሆኑ ፤ ምንም እንኳን ፤ አጼ ምንሊክ እንደ ሕወሐቱ በታሪካዊ ስሕተትነት በእሚመዘገብ አኳኋን ፤ ታሪካዊ የግዛታቸውን አካል ፤ በባዕድ መያዙን በይኹንታ ቢቀበሉትም እና ኤርትራም ለ61/62 ዓመታት በጣሊያን እና በኋላ ላይ በብሪትሾች አስተዳደር ስር ብትቆይም ፤ የጣሊያን እና የብሪትሽ አስተዳደር ከአበቃ በኋላ የኤርትራ ሕዝብ በሪፈረንደም ከኢትዮጵያ ጋር የተቀላቀለ በመሆኑ ፤ ይኽም ብቻ ሰአይሆን ኤርትራ በጣሊያን ቀኝ ግዛት በኋላም በብሪትሾች የሞግዚት አስተዳደር ለ61/62 ዓመታት ብትቆይም ከእዚኽ ቀኝ ግዛት በፊት መላው ኤርትራ የኢትዮጵያ ታሪካዊ አካል በመሆን ከ2 ሺ ዓመታት በላይ የኖረ በመሆኑ ፤ ይኽ ታሪካዊ ክስተት ፤ የኤርትራን ሕዝብም ሆነ የኤርትራ ፖለቲካዊ ኃይላት ፤ ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ነች በእሚል ከኢትዮጵያ ቀኝ ግዛት ነጻ ለመውጣት የነፍጥ ትግል ለማድረግ የእሚያስችል አሳማኝ ምክንያት ሆኖ መቅረብ አይችልም።

እ.አ.አ. በ1960ዎቹ ፤ አንዳንድ የኃይለ ሥላሴ አማካሪዎች ፤ እንደ ኤርትራ ያለች ትንሽ ግዛት ከኢትዮጵያ ጋር ኮንፌደሬሽን ተብላ መቆየቷ ፤ ለክብሮ እና ለዝናዎ አይመጥንም እና የኤርትራ ፓርላማ ከኢትዮጵያ ጋር ተዋሕደን የኢትዮጵያ አውራጃ እንኹን እንዲሉ አስገድዷቸው ብለው ኃይለ ሥላሴን ስለ መከሩዋቸው ፤ ኃይለ ሥላሴ የኤርትራን ፓርላማ ከበው በማስገደድ ኤርትራን ከኮንፌደሬሽን አውጥተው የኢትዮጵያ አውራጃ በማድረጋቸው ነው ፤ ሻዕቢያ ተበሳጭቶ ነፍጥ በማንሳት የቀኝ ግዛት ትግል የአደረገው የእሚለው አባባልም ፤ ከታሪካዊ ስሕተትነቱ በአሻገር ነባራዊውን ፖለቲካዊ እውነታም የእሚያንጸባርቅ አይመስልም።

እንደ እሚታወቀው ጀብኃ የእሚባለው የኤርትራን ነጻ አውጪ ቡድን ኤርትራ የኢትዮጵያ ቀኝ ግዛት ነች ብሎ ከ1966 አብዮት 13 ዓመታት ቀደም ብሎ በኃይለ ሥላሴ መንግሥት ላይ ነፍጥ የአነሳው በዋናነት ኢትዮጵያ ከእስራኤል ጋር የአላት መልካም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የአበሳጫቸው ፤ መገኛቸውን ግብጽ የአደረጉ የአረብ ብሔርተኞች እና የእስልምና ዳሬሰላም ምኞት አራማጅ የሆነ የአረቡ እና የሙስሊሙ ፖለቲከኞች የጀብኃን መሥራች አባላት በኹለንተናዊ መስኩ ድጋፍ በማድረጋቸው ነው። ሻዕብያም ከጀብኃ ውስጥ ወጥቶ እራሱን የቻለ ቡድን የሆነው ፤ በዋናነት በሙስሊሞች እና በእስላማዊ አስተሳሰብ በእሚመራው ጀብኃ ውስጥ ክርስቲያን የሆኑት ኤርትራዊያኖች አብሮ ለመቀጠል የእማያስችል ብቻ ሰአይሆን ለህይወታቸውም የእሚያሰጋ ኹኔታ በመፈጠሩ ነው።

ይኽም በመሆኑ ፤ ኮንፌደረሼን ከፈረሰ ፤ ኮንፈዴሬሽኑ አስፈላጊ ከሆነ ኮንፌደረሽንን ለመመለስ ይሰራል እንጂ ፤ ኮንፌደሬሽን ፈረሰ በእሚል ለኢትዮጵያም ፣ ለዛሬዋ ኤርትራም ሆነ ለአከባቢው ፖለቲካ በእማይመጥን እና በእማይበጅ መልኩ ፤ ኮንፌደሬሽን ፈርሷልና ፤ መሠረት የለሽ የቀኝ ግዛት የውሸት ታሪክ ተጎንጉኖ የትጥቅ ትግል ውስጥ አይገባም።

ኃይለ ሥላሴ በዳተኝነት ፤ የአላንዳች በቂ እና አሳማኝ ምክንያት ፤ የነበረውን ኮንፌደሬሽን ዓይነት ወዋቅር አፍርሰው ኤርትራን የኢትዮጵያ አውራጃ አደርጉዋት ቢባል እና ይኽም ምክንያተ ቢስ እብሪተኝነት በኤርትራ የፖለቲካ ኃይላት ላይ ቅሬታ ሊፈጥር ቢችልም ፤ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ውሕደት የእልክ እና እኔ እበልጥ ፣ እኔ እበልጥ በእሚል ፤ የታጠቁ ኃይላት ውረድ እንውረድ የእሚባባሉበት ጉዳይ ሰአይሆን ፤ በአከባቢው ጂኦግራፊ ፣ ጂኦፖለቲክስ እና በኹለቱ አከባቢ ነዋሪ በሆነው ሕዝብ ታሪካዊ ትስስር ፣ ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ እጣፈንታ ምክንያት ፤ ለጋራ ጥቅማቸው እና ዋስትናቸው አብረው ለመኖር የእሚገደዱ ከመሆናቸው የእሚመጣ በመሆኑ ፤ የኃይለ ሥላሴን ግብታዊ እርምጃ (ግብታዊ ከሆነም) እንደ ምክንያት ጠቅሶ ፤ የሻዕቢያን የቀኝ ግዛት ትርክት ማንቆለጳጰስ ከተጨባጨ ፖለቲካ (realpolitik) አንጻር ትርጉም አልባ ነው።

ይኽን ከእሚሉት እና የሻዕቢያ የቀኝ ግዛት ትግል ከንቱ ትርክት ከእሚዘግቡት ጽሑፎች አንዱ የሆነው ፤ ሻዕቢያ 29 ዓመታት ከቀኝ ግዛት ለመውጣት ብሎ የተጋደለው ፤ ተመልሶ ከኢትዮጵያ ጋር በኮንፌደሬሽን መሰል ፌደሬሽን ለመተሳሰር ነው ብሎ ይነግረናል።

ይኽም ፦ የሻዕቢያ ኤርትራ የኢትዮጵያ ቀኝ ግዛት ነች እና ነጻ ሐገር መሆን አለባት የእሚለው ትርክት ፤ መሬት ላይ የአለውን ተጨባጩን የአከባቢውን ፖለቲካ እና የአከባቢውን ሕዝብ ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ፍላጎት ከግምት የአላስገባ ፤ ከንቱ አስተሳሰብ ለመሆኑ ማሳያ ነው ፦

“[12]አኹን በተገላቢጦሽ ፤ ኤርትራዊያን ከኢትዮጵያ ለመነጠል በነቂስ በሪፈረንደም ከወሰኑ በኋላ ፤ ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ወደ ቀድሞው የእ.አ.አ. 1952[13] ዓ.ም. ኹኔታ ተመልሰዋል። በኹለቱ ሐገራት መሐከል የጋራ ገበያ ፣ ነጻ እንቅስቃሴ ፣ ወደብ የመጠቀም ፍጹም ነጻነት አለ። ከእዚኽም በላይ ፡ በኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ ኤርትራዊያኖች ከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ የአሉ ሰዎች የአሉ እና በኹለቱ ሐገራት መካከል የአለው ፖለቲካዊ ግንኙነትም መልካም የእሚባል ነው። በሌላ አገላለጽ ፤ ኮኽን ይላል ፤ ኃያ ዘጠኝ ዓመታት ሙሉ ተዋግተው ሲያበቁ ወደ መጀመሪያው ኹኔታ ነው የተመለሱት።”

“Now, ironically, after the Eritreans voted overwhelmingly in favor of independence, Ethiopia and Eritrea have in many ways returned to the situation of 1952. There is a common market between them, freedom of movement, and complete access to ports. Furthermore, there are Eritreans in high position in the Ethiopian government, and political relations between the two states are very close. In other words, Cohen commented, they had twenty-nine years of war only to return to the original arrangment. [126]”

ከቀኝ ግዛት በኋላ ኤርትራ ከቀኝ ገዢዎች የወረሰችው ፤ በአንጻራዊነት በወቅቱ በኢትዮጵያ ከነበረው የእሚሻል ሕገ መንግሥት እና እየዳበረ የነበረ ኢከነሚያዊ ልምላሜ ቢኖርም ፤ ይኽ የማሕበረ ኢከነሚ ሽግግር የኤርትራ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ተሸጋግሮ የደረሰበት የማሕበረ ኢከነሚ ልማት በአለመሆኑ እና ከቀኝ ገዢዎቹ ወይንም ከቀኝ ገዢዎቹ ኢከነሚያዊ አቅም እና እውቀት ሲነጠል በአለበት ተንገራግጮ የቆመ ፣ የቆመ ብቻም ሰአይሆን የዘበጠ በመሆኑ ፤ የኤርትራ ሕዝብ የኢትዮጵያ ሕዝብ በብሔራዊነት ከእሚገኝበት የማሕበረ ኢከነሚ ልማት ተሻግሮ ኼዷል እና ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ትቀጥል ማለት ትክክል አይደለም ማለት ፤ የኤርትራ ሕዝብ ላይ የታሪክን መንኮራኮር ወደ ኋላ ማንኮራከር ነው የእሚለው ምክንያትም ፤ ተመልሼ በጣሊያን ቀኝ ወይንም በእንግሊዝም ሞግዚትነት ስር ልግባ ለማለት ከአልሆነ ፤ ከኢትዮጵያ ጋር አልዋኃድም ለእሚለው አሳማኝ ምክንያት አይሆንም።

ኤርትራ የጣሊያን ኢንደስትሪያል ፓርክ ነበረች እንጂ የኤርትራ ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ በላይ በማሕበራዊ እድገቱ ልቆ ኼዷል የእሚባልበት ደረጃ ላይ አልነበረም። ይኽ ባይሆን ኖር የኤርትራ ወደቦች ፤ ለክራይ አገልግሎት ብቻ የእሚያገለግሉ ሆነው እንደ እዚኽ ባዶዋቸውን አይሆኑም ነበር።

ስለ እዚኽ ፦ ሕወሐት ኤርትራን አላስገነጠለም ፤ ምክንያቱም ፦ የኤርትራን መገንጠሉን ጉዳይ ሻዕቢያ በብዙ ምክንያት ከላይ በተቀመጠው ስኹት በሆነው የኤርትራ ነጻነት ትንታኔው ተመስርቶ ከኃይለ ሥላሴ እና ከደርግ ጋር የአደረገው ትግል ፍሬ አፍርቶለት ፤ አስቀድሞ በጠመንጃ (በግዜያዊነት) ቢሆንም ራሱን የኤርትራ መንግሥት የአደረገ በመሆኑ።

ከእላይ እንደ አልነው ፤ ሻዕቢያ ኤርትራ የኢትዮጵያ ቀኝ ግዛት በመሆኗ መገንጠል አለባት የእሚልበት ፖለቲካዊ ትንታኔ መሠረት አልባ ተራ ትንታኔ በመሆኑ ፤ በግዜያዊ የኃይል ሚዛን ሻዕቢያ ኤርትራን ሙሉ በሙሉ ቢቆጣጠርም እና ሕወሐትም ከወቅቱ ፈታኝነት እና ከኃይል ሚዛን ስሌት አንጻር ፤ ሻዕቢያን የመገንጠል ጥያቄኽን አቁም በእሚል ነፍጥ ማንሳት በአይጠበቅብትም እና በአይችልም ፤ ኤርትራ ከትግራይ እኩል የኢትዮጵያ አካል በመሆኗ እና የኤርትራ መገንጠል ፤ ለኤርትራ ፣ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአከባቢው ሕዝብ ከእሚፈይደው ይልቅ የእሚያደርሰው ጉዳት የእሚበልጥ በመሆኑ ፤ ሕወሐት/ኢሕአዴግ መወቀስ የአለበት ፤ የአለ ታሪካዊ መሠረት እና በቂ ፖለቲካዊ ግንዛቤ ፖለቲካዊ የስልጣን ድንበሩን ተላልፎ የኤርትራን ሪፈረንደም መፍቀዱ እና የኤርትራን ነጻ ሐገርነት እውቅና ለመስጠት በመሸቀዳደሙ ታሪካዊ ስሕተት የሰራ በመሆኑ ነው እንጂ ኤርትራን አስገነጠለ በእሚል አይደለም ፤ በኹለቱ መካከል ከፍተኛ ልዩነት አለ።

ሕወሐት በስኹት ስሌት የኤርትራን ሪፍረንደም ለመፍቀድ እና ከሪፍረንደሙ በኋላ ለኤርትራ እውቅና ለመስጠት መሸቀዳደሙ ጸረ ኢትዮጵያ ሰአይሆን ሊያስብለው የእሚችለው ፤ የሻዕብያን ፖለቲካዊ ዕብዩነት ተጠቅሞ ለተራ ግዜያዊ ፖለቲካዊ የበላይነት በወቅቱ ብቸኛ ተቀናቃኝ ሊሆነው የእሚችለውን የሻዕቢያ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አቅም ፤ በሪፈረንደም ስም ከኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ምሕዳር ውስጥ ቆልፎ በውጭ በማቆየቱ ነው።

በእርግጥ በተሳሳተ ፖለቲካዊ ትንታኔ ላይ የተመሠረተው የሻዕብያ የመገንጠል ፕሮግራም ለራሱ ለሻዕብያ ፣ ለኤርትራ ሕዝብ እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጎጂ በመሆኑ ወይንም ይኽ መሰሉ የሻዕቢያ አቋም ስኹት በመሆኑ ፤ ራሱ በቀደደው ቀዳዳ ቢሆንም ሕወሐት ሻዕብያን ገፍቶ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ የአስወጣው ፤ ሕወሐት ይኽንን የሻዕቢያ ስሕተት ተግንዝቦ ጉዳዩን ለሕዝብ ጥቅም በእሚውልበት አግባብ ከመያዝ ይልቅ ፤ ግዜያዊ የፖለቲካ ጥቅምን በአሰላ መልኩ በማዞር መጠቀሙ ጉዳዩን አንዱ እና ትልቁ የሕወሐት ግዜያዊ ጥቅመኝነት በሽታ ውጤት የሆነ እና ብዙዎችን የጎዳ ፖለቲካዊ ውሳኔ አድርጎታል።

ይኽንን የታሪካችንን ክፍል በተመለከተ ፤ ሕወሐት ነጻ ትግራይን ለመመሥረት የእሚሰራ እና ጸረ ኢትዮጵያ የሆነ የፖለቲካ ድርጅት አይደለም በእሚል ፤ የሕወሐት እና የቅርብ ዘመዱን የሻዕብያን ፖለቲካዊ ፕሮግራም እና የተወሰኑ ተግባራት ስንቃኝ ፤ አንድ የእሚፈጠር ጥያቄ ቢኖር ፤ ሕወሐት እና ሻዕብያ ፤ ይኽን መሰል ስኹት የሆነ እና ከስትራቴጅካዊ ጥቅም አስተሳሰብ አንጻር ፤ ለኤርትራም ፣ ለትግራይም ፣ ለመላው ኢትዮጵያዊ እና ለአከባቢው ሕዝብ የእማይበጁ የፖለቲካ ፕሮግራም እንዴት ሊይዙ ቻሉ ? የእሚለው የመጀመሪያው ይሆናል።

በእዚኽም መሠረት ፤ እነ እዚኽ ኹለት ድርጅቶች (ሕወሐት እና ሻዕብያ) በተለያየ መልኩ ፤ ስትራቴጅካዊ አስተሳሰብ የእማይታይበት ጠባብ ከባቢያዊ ፖለቲካዊ ፕሮግራም የይያዙት በእሚከተሉት ምክንያቶች ይመስለኛል ፦

  • መዓከላዊው ወይንም ብሔራዊው የኢትዮጵያ መንግሥት በታሪክ እዳ ምክንያት በኋላ ቀርነት እና በወግ አጥባቂነት ተተብትቦ ፤ እነ እዚኽ ኹለት የኢትዮጵያ አከባቢዎች ከሌላው የኢትዮጵያ አከባቢዎች በተለየ አኳኋን ፤ ከአላቸው ጂኦግራፊ የተነሳ ተጋላጭ ከሆኑበት የህልውና ስጋት ሊታደጋቸው የእሚችልበት አቋም ላይ የአልነበረ በመሆኑ
  • ይኽ እነ እዚኽን ኹለት አከባቢዎች በተለየ ኹኔታ ተጋላጭ የአደረገው የኢትዮጵያ መንግሥታዊ ከርካሳነት ችግሩ ሐገራዊ በመሆኑ ፤ ይኽንን ችግር ለመፍታት የዘመናዊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የጀመሩት ሌሎቹ የሐገር ውስጥ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ፤ በነበረባቸው ደካማነት እነ እዚኽን ኹለት ድርጅቶች ማቀፍ የእሚችሉበት አቋም ላይ በአለመገኘታቸውና
  • ራሳቸው የእነ እዚኽ ድርጅቶች ጠንሳሾች እና አናጺዎች እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ፖለቲከኛ ተራማጅ ቢሆኑም ኋላ ቀር የሆነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ክፋዮች በመሆናቸው ከያዙት ጠባብ ፖለቲካዊ ፕሮግራም የተሻለ ለመያዝ የእሚያበቃ የእውቀት አቅም የሌላቸው በመሆናቸው

የተዳከመው የኢትዮጵያ ፖለቲካ የኤርትራ እና የትግራይን ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለየ ኹኔታ ለሕልውና አደጋ መጋረጡ ፤ የኤርትራን በጣሊያን ቀኝ ከመያዝ በላይ አጉልቶ የእሚያሳየው ታሪካዊ ክስተት የአለ አይመስለኝም።

ከእላይ እንደ አልነው የጣሊያን ጦር የአጼ ዮሐንስን ሞት ተከትሎ ወደ ኤርትራ መሰስ ብሎ ሲገባ ፤ በተለያየ ምክንያት የተወጠረው የኢትዮጵያ መንግሥት ፤ ኹኔታውን በፊርማ ከማጽደቅ ያለፈ ሌላ ምንም መፈየድ የእሚችለው ነገር አልነበረም ፤ ይኽም ብቻ ሰአይሆን የወቅቱ የኃይል ሚዛን ድንበር የማስከበሩን ሥራ ከመሥራት ቢያግደውም እንኳን የወቅቱ አስተዳደር ፤ ታሪካዊ ግዛቱ ተቆርጦ በባእድ እጅ ሲወድቅ እና ወገን ሕዝቡ በባዕድ አስተዳደር ስር ሲገባ ፤ የወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ወግ የአለው የዲፕሎማሲያዊ ክርክር እንኳን ማድረግ የእማይችልበት ደረጃ ላይ የነበረ ነው።

ይኽም ኤርትራን ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል በተለየ በቀኝ ግዛት ስር የወደቀች የኢትዮጵያ ክፍል እንድትሆን አድርጓል።

ሚዛናዊ ለመሆን ኤርትራ በእዚኽ ደረጃ ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል በተለየ ኹኔታ ተጋላጭ እንድትሆን በማድረጉ ረገድ የወቅቱ የአጼ ምንሊክ መንግሥት ቀጥተኛ ሚና እንደ ሌለው በስፋት የቃኘነው ከአክሱም ውድቀት በኋላ የአለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዝግመት የእሚነግረን በመሆኑ ፤ የኢትዮጵያ መዓከላዊ ወይንም ብሔራዊ መንግሥት መዳከሙ የኤርትራን ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለየ ለጥቃት ተጋላጭ አድርጎታል ስንል ፤ ጉዳዩ የአጼ ምንሊክን መንግሥት ብቻ በቀጥታ የእሚመለከት ሰአይሆን ፤ ጠቅላላው እና ከአክሱም ውድቀት በተለይም ከግራኝ ወረራ ማግስት የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት በአብዛኛው ከእርሱ ቁጥጥር ውጭ በሆነው በዓለም ዓቀፉ ፖለቲካ ምክንያት ግዛታዊ አንድነቱን እና ፖለቲካዊ ሐመልማሉን (Vitality) ትርጉም በአለ፟ው ኹኔታ ለማስቀጠል የእሚቸገርበት ኹኔታ ላይ እንደ ነበር ለማለት ነው።

ከአጼ ምንሊክ በኋላ ተከታትለው የመጡት የኃይለ ሥላሴ እና የደርግ መንግሥታትም ፤ አንዱ እጅግ ኋላ ቀር እና ወግ አጥባቂ በመሆኑ ከዘመናዊው ዓለም ጋር መራመድ አይችልም ተብሎ ፤ ዓለም ዓቀፋዊ አጋሮቹ ጭምር ገሸሽ አድርገውት በአብዮት የወደቀ ፤ ኹለተኛውም የበላይ ጠባቂው የሆነው የሞስኮ መንግሥት ፤ ወደ ውድቀቱ መቃረቢያ ላይ ፤ ከአሜሪካ ጋር የአለው ግንኙነት ሲሻሻል ፤ የአሜርካን እገዛ ከጠየቀበት ጉዳይ አንዱ ፤ በኢትዮጵያ በአለው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ለደርጉ መሳሪያ መጓጓዝ ደክሞኛል እና የኢትዮጵያን የእርስ በእርስ ጦርነት ለማስቆም አግዙን ብሎ አሜሪካን የጠየቀበት በመሆኑ ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መንግሥታት እየከፋ በኼደው ዘመናዊ ፖለቲካ ውስጥ ይበልጥ እየሰለሉ እንደ ነበር ማሳያ ነው ፤ ምንም እንኳን አብዮታዊ ዴሞክራቶቹ በእሚሉበት አግባብ በአይሆንም ፦

“ሆኖም ፤ በ1980ዎቹ መጨረሻ አከባቢ ከሶቭየት ሕብረት ጋር የአለው ግንኙነት መሻሻል ሲያሳይ ፤ የተዋኃዱት ግዛቶች (አሜሪካ) ከባቢያዊ ግጭቶችን መፍታት የእሚያስችሉ ትብብሮችን ጥንቃቄ በሞላበት አኳኋን የማድረግ አካኼድ መከተል ጀመረች። በእዚኽም ወቅት ፤ ለሶቭየቱ እጅግ አስከፊ የነበረው ግጭት ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ነበር ፤ በተለይ ደግሞ መሳሪያ በማቅረቡ ረገድ ሶቭየቱ ላይ ከፍተኛ ሸክም ሆኖ ስለነበር።”

“However, as relations with the Soviet Union began to improve in the late 1980s, the United States adopted a policy of cautious cooperation in resolving any regional conflict. At that time, the Soviets' worst problem was the conflict in Ethiopia, particularly due to the heavy burden of arms delivery. [126]”

የኃይለ ሥላሴ መንግሥት የጣሊያን መንግሥት በኹለተኛው የዓለም ጦርነት ከተሸናፊው ወገን ጋር በማበሩ አሸነፊው ኃይል በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የጣሊያንን ቀኝ ግዛቶች ከጣሊያን መንግሥት በመውሰድ ቦታ ቦታ እያስያዘ በአለበት ወቅት በመጥፎ ታሪክ እና እርሱም በአስከተለው ሐገራዊ ፖለቲካዊ ቆሽማዳነት ምክንያት ለባዕድ ተላልፋ የተሰጠች ኤርትራ ፤ ቀን ዘንበል ሲል እና ታሪክ እንደገና ሲስተካከል ፤ ኤርትራን ከታሪካዊ አኳላ ከኢትዮጵያ ጋር በሪፈረንደም መልሶ ማስተሳሰሩ ተገቢ ነው ተብሎ ፤ በተባበሩት መንግሥታት የበላይ ጠባቂነት (Under the auspices of the United Nations) ኤርትራ በሪፍረንደም እንደገና ከኢትዮጵያ ጋር ስትተሳሰር ፤ ኤርትራን የተረከበው የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ታሪክ ከአወረሰን ቆሽማዳነት በአለመላቀቁ ፤ በአግባቡ ራሱን አደራጅቶ እና አጠንክሮ ኤርትራን መያዝ ስለ አልቻለ ፤ ከእዚኽ በኋላ በታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች እየታገዘ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ነጻ ማውጣት ብሎ ትግል የጀመረውን እና በዋናነት በእስላሚስቶች የእሚመራውን ጀብኃን መቆጣጠር እንኳን አልቻለም ነበር።

ጀብኃ ግብጽ ከእሥራኤል ጋር በአደረገችው እና የስድስቱ ቀን ጦርነት በእሚባለው ጦርነት ተሸንፋ ትልቅ ስፋት የአለውን የሳይናይን በርኃ በእሥራኤል በመነጠቋ እና ኢትዮጵያ ደግሞ ከእሥራኤል ጋር በእዚያን ወቅት መልካም ግንኙነት የነበራት በመሆኑ ፤ የጠላቴ ወዳጅ ጠላቴ ነው በእሚል ፤ ኢትዮጵያን በጠላትነት ፈርጃ ፤ ጀብኃን ኤርትራ የአረብ ሙስሊም ምድር ነች በእሚል ኤርትራን ከኢትዮጵያ እንዲ ገነጥል እንደ አደራጀችው ነው የጀብኃ ታሪክ የእሚያነግረን። ይኽም ማለት ፦ የኤርትራ ነጻነት ትግል ፅንሰት የኤርትራ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ከመፈለጉ የመነጨ ሳይሆን ፤ በእስራኤል የደረሰባትን ሽንፈት በእስራኤል ወዳጅ በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ ለመወጣት በፈልገችው ግብፅ ፣ እንደ ባዝ ፓርቲ በአሉ የአረብ ብሔርተኞች እና በዳሬሰላም ወይንም በሐገራት ድንበር የእማይከለከል የእስላማዊ ሰፊ መንግሥት መመሥረት በእሚፈልጉ የእስልምና ኢምፓየር ፈላጊዎች አጋጋይነት የተጀመረ ነው ማለት ነው።

ለነገሩ በእዚያን ወቅት በኤርትራ ውስጥ ብቻ ሰአይሆን ፤ የሱማሊያው ዚያድ ባሬም ፤ ውስጥ ውስጡን በአረቦች እየታገዘ እና በራሻያ የጦር መሳሪያ ታጥቆ ፤ ኦጋዴን ፣ ባሊን እና ሲዳሞን ከኢትዮጵያ በመውሰድ ፤ ታላቋን ሱማሊያን የመገንባት ፍላጎት ስለ ነበረው ፤ በኦጋዴን የሱማሌ እና በባሊ ደግሞ የኦቦ ኦሮሞ የእሚባሉ እና እስላማዊ የኦሮሞ መንግሥት ለመፍጠር የእሚፈልጉ ኃይላትን የመገንጠል እንቅስቃሴውችን ያግዝ ነበር ፤የኤርትራ ኹኔታ ከኹሉም የከፋ ቢሆንም።

ይኽም በመሆኑ የኤርትራ ሕዝብ ሊከላከለው የእማይችል እና በረዥም ታሪካዊ ምክንያት የተንኮታኮተ ብሔራዊ መንግሥትን ሲጠብቅ የሕዝብነት ታሪኩን ያለፍላጎቱ ላዩ ላይ እስላማዊ መንግሥት ሊመሰርቱበት አቅደው ነፍጥ ያነሱ እና ብሔራዊ መንግሥት ሊያግዳቸው ያልቻለውን ኃይላት ዝም ቢል ፤ እንደ ሕዝብ ሕልውናው አደጋ ውስጥ ይገባል።

የትግራይንም የወቅቱን ኹኔታ ብንመለከት ፤ እንደ ኤርትራ በውጭ ኃይሎች የእሚታገዝ እና የእሚያሰጋ እንደ አክራሪ እስላማዊ እንቅስቃሴ ዓይነት በአይኖርም ፤ በላሸቀ መንግሥታዊ መዋቅር እና አደራረግ ምክንያት ፤ በትግራይ ውስጥ ከፍተኛ የሽፍታ ችግር እንደ ነበር እና ሕወሐት በትጥቅ ትግሉ መጀመሪያ ግዜ ፤ ከመንግሥት በላይ ለህልውናው ስጋት የነበረው በመቶ የእሚቆጠሩ እና በመላው ትግራይ ዱር ተበትነው የነበሩ እና የትግራይን ሕዝብ በተጽኖ ስር አድርገው የነበሩ ሽፍታዎች እንደ ነበሩ አረጋዊ በርኼ ይነግረናል ፦

“በትግራይ የነበሩት ሽፍታዎች እጅግ በጣም ብዙ የነበሩ እና ሕዝቡን በመዝረፍ እና ለአበሳ በመዳረግ ራሳቸውን የእሚደጉሙ ነበሩ። ለእለት ምግባቸው ሲሉ የገበሬውን ከብት ያርዳሉ ፤ የጠየቁት ነገር ሳይቀርባላቸው ሲቀር ፤ ሴቶች ይደፍራሉ ፣ ዘረፋ እና ቤት ማቃጠል ድረስ ይኼዳሉ። ሕግ በእማይደርስበት እና ከሕግ በላይ በዱሩ እየኖሩ ፤ የእሚቃወማቸውን ማንኛውንም ሰው ይገድላሉ። አንዳንዶቹ ሽፍታዎች እንዲያውም ራቅ በአለው ገጠራማ አከባቢ ስር የሰደዱ እና ከገበሬው የዘረፉት ጠቀም ያለ ኃብት የአላቸው ሆነው በደንብ የተደላደሉ እና የራሴ የእሚሉት እና ራስገስ ዓይነት መንደር የአላቸው ናቸው። እንደ አሻቸው ግብር ፣ ቅጣት እና ዋጆ ይበይናሉ ይቀበላሉ። በእየመንደሩ የአላቸውን ቤተሰብ የመረጃ ምንጫቸው አድርገው ፤ ይኽን መረጃ ለእሚሰጣቸው ቤተሰብ ጥበቃ ያደርጋሉ። በኋላ ኢዴሕን ሲቀላቀል የሻለቃነት ማዕረግ የተሰጠው እና ሽፍታ እያለ፟ ራሱን ደጃዝማች እያለ ይጠራ የነበረው አለምሸት ተወልደ ለእዚኽ አንዱ ማሳያ ነው። ራቅ በአሉት ገጠራማ አከባቢዎች ፤ በተከዜ እና በመረብ ወንዝ ፉካዎች ውስጥ ነጋዴዎችን እና ገበሬውን እየ በዘበዙ እና እየ አዋረዱ ራሳቸውን የእሚደጉሙ በወቶዎች የእሚቆጠሩ ሽፍታዎች ነበሩ።”

“The criminal shiftas in Tigray were numerous and lived off robbery and subjecting people to torment. They slaughtered peasants’ animals for a day’s meal, raped women, robbed and burned down houses whenever their demands were not met. They also killed anybody who dared to stand in their way, living in the bush outside and above the law. Some of the shiftas were well established in the remote rural areas, with the sizeable wealth they had amassed from the peasantry, and they even had a quasi-autonomous territory that they ruled at will. They levied tax, fines or ransom as they wished. They used family connections as their intelligence network; and in return, family members were protected from intrusion by other shiftas. Alemshet Tewolde, who gave himself the title of dejazmach, which was changed to major when he joined the EDU later on, was just one well-known example. Along the river of gorges in Tekeze and Mereb and deep in the rural areas, there were hundreds of such shiftas who lived off exploiting and humiliating peasants and merchants. [124]”

ይኽም ማለት ፦ በመላው ኢትዮጵያ በተለይም ደግሞ በኤርትራ እና በትግራይ የመንገሥት ተደራሽነት በመቀነሱ (Due to Absentee state) ፤ ከኢምፔሪያሊዝም፣ ከቀኝ ግዛት ፣ ከቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ፣ ከፊውዳሊዝም ፣ ወዘተ ፤ የእሚመጣ የህልውና ስጋት በአይሆንም ፤ ተራ የውስጥ አመጸኞች የሕዝብን ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ህልውና ያቀነጨሩበት ኹኔታ በመኖሩ ፤ ኹኔታው እንደ ሻዕብያ እና ሕወሐት ለአሉ የፖለቲካ ድርጅቶች አመቺ መራቢያ ምሕዳር ሰጥቷቸዋል።

ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀ ፣ በዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስ በሰለጠኑ ወታደራዊ አመራሮች የእሚመራ በወቅቱ የነበራት ኢትዮጵያ ፤ ፖለቲካዊ ተነሳሽነቱ ቢኖር ፤ ታንክና እና አውሮፕላን በማዝመት ሳይሆን ፤ ለእዚኽ ዓላማ ተብሎ ፤ ማለትም፦ ሽፍታን ከትግራይ ለመንቀል በእሚል ፤ መቶ መቶ ወታደር የአለው አራት ኃይል ፤ በዘመናዊ የመገናኛ ዘዴ ፣ አመራር እና ስንቅ አቅርቦት እያገዘች በቋሚነት ብታሰማራ ኖሮ ፤ ችግሩን ከስሩ መንቀል ትችል ነበር። ሐገሪቱ ይኽን ማድረግ የእምትችልበት አቅምም ነበራት ።

ይኽም በመሆኑ ፤ የኢትዮጵያ ቀኝ ግዛት ስለ ሆንኩ ከኢትዮጵያ ነጻ መውጣት አለብኝ ወይንም በኢትዮጵያ ነገዳዊ ጭቆና ስለ አለ ይኽን ማረም አለብኝ የእሚለው ምክንያታቸው ተራ እና በዘላቂነት መስፈርት ሚዛን የእማይደፉ በመሆናቸው ፤ ቢሳኩም ከግዜያዊ እሳት ማጥፋት የአለፈ ዘላቂ መፍትኼ መሆኑ የእማይችሉ ምርጫዎች ቢሆኑም ፤ ከዓለም ዓቀፍ መመዘኛ አንጻር እየተዳከመ እና ከወቅታዊ አቅሙ በታች ሆኖ እየተገኘ የመጣው የኢትዮጵያ ብሔራዊ መንግሥት ፤ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ማባበያ ጋር ተዳምሮ በመላ ሐገሪቱ የተገንጣይነት አባዜ የአሰፈነው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ምሕዳር ፤ የኤርትራ እና የትግራይ ተወላጆች ዝም ብለው ከአዩት ፤ የጎጠኝነቱ እንቅስቃሴ በጽንፈኞች አንዳንዴም በእስላሚስቶች እጅ ገብቶ የሕዝባቸውን ሕልውና አደጋ ላይ ሊጥል የእሚችል በመሆኑ ፤ በጅጅና ቆሞ መንቀሳቀስ ያቀተውን መንግሥት ተስፋ ከማድረግ ይልቅ ፤ ከባቢያዊ የመከላከል አቅምን ገንብቶ ራስን ከአጥፊ ጽንፈኛ ለመከላከል መንቀሳቀሱ ተገቢ እና ከወቅቱ ኹኔታ አንጻር ብቸኛም መፍትኼ ሊባል የእሚችል ይመስላል።

መንግሥት እና ዘመናዊ ጦር በአለው ሐገር ፤ አንድ ትግራይን በእሚያክል ክፍለ ሐገር እንዴት ሽፍታ ፤ መደበኛውን ዜጋ አላስወጣ አላስገባ ብሎ ፤ ሕዝብ ከድህነቱ ላይ በእሚከፍለው ግብር እየተባባለ ፤ በግዜያዊነት ሰአይሆን ለዓመታት ይኖራል?

በእርግጥ በወቅቱ የሽፍታ ችግር የትግራይ ብቻ ሰአይሆን በመላው ሐገሪቱም እጅግ አስጊ ደረጃ ላይ የደረሰ እና ደርግ ራሱ ሽፍታው ላይ መዝመት የተርብ ቀፎ መንካት ነው የእሚሆነው ብሎ ፤ ሽፍታውን አብዮት ጥበቃ በማድረግ ከሽፍታነት እንደ አወጣው ይታወቃል።

ሆኖም ሕወሐት ገና በጨቅላነቱ ሽፍታን ጠራርጎ ከትግራይ ማስወጣት ከቻለ ፤ መንግሥት ይኽንን በመላ ሐገሪቱ ማድረግ ይሳነው ነበር የእሚባል አይደለም ፤ መንግሥቱ በቁም ጃጅቶ የአገዛዝ አቅሙ ጥቅም አልባ ሆኗል ከአልሆነ በስተቀር።

ስለ እዚኽ ፦ የኢትዮጵያ መንግሥት በታሪክ ኺደት በደረሰበት መንኮታኮት እና ይኽም መንኮታኮት በኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ላይ በፈጠረው የአቅም መሳሳት ምክንያት ፤ የኤርትራ እና የትግራይ ሕዝብ በእሚገኙበት ጂኦግራፊ እና በኢትዮጵያ ጂኦፖለቲካስ ምክንያት ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለየ ለሕልውና አደጋ የተጋለጡ እንዲሆኑ በማድረጉ ፤ በታሪክ አጋጣሚ የትግል ቆራጥነቱ እና አቅሙ የነበራቸው የትግራይ እና የኤርትራ ልጆች ራሳቸውን ይበጀኛል በአሉት መንገድ አደራጅተው እና የመከላከል አቅማቸውን ገንብተው የተጋረጠባቸውን የሕልውና አደጋ በግዚያዊነትም ቢሆን ማንሳት ችለዋል ፤ ማንሳት ችለዋልም ብቻ ሳይሆን ፤ ሕልውናቸውን ለማስጠበቅ የጀመሩት ትግል የፈጠረላቸው አቅም በኢትዮጵያ እና በአከባቢው ፖለቲካ ላይ ለዓለፉት 30 ዓመት የአንበሳውን ድርሻ የእሚጫወቱ አድርጓቸዋል።

የእነ እዚኽ ድርጅቶች ስኬት ግን የእሳት የማጥፋት ዓይነት ወይንም ግዜያዊ መፍትኼ እንጂ ፤ ለትግራይ እና ለኤርትራም ብሎም ለኢትዮጵያ እና ለአከባቢው ሕዝብ የእሚበጅ ዘላቂ መፍትኼ አይደለም።

ምክንያቱም ፦ በእኔ እምነት ፦ በመላው ኢትዮጵያ ኹነኛ ዴሞክራሲያዊ ስረዓት ሳይገነባ እና ይኽም ፖለቲካዊ ስረዓት በእሚፈጥረው አመቺ ኹኔታ የሐገሩቱን ማሕበረ ኢከነሚ ትርጉም በአለው መልኩ ሳይተሳሰር እና ሳይሸጋገር ፤ በአጭሩ ኢትዮጵያ በጽኑ ዴሞክራሲያዊ መሠረት ላይ ተመስርታ ወደ ቀደመው ግዛታዊ አንድነቷ በመመለስ በማሕበረ ኢከነሚያዊ ልማት ገስግሳ ፤ ከውጭም ከውስጥም ከእሚቃጣባት እና ሊቃጣባት ከእሚችል ማንኛውም አደጋ ራሷን በአስተማማኝ ኹኔታ መከላከል የእምትችልበት እና ለዜጎቿ ምቹ መኖሪያ መሆን የእምትችልበት ኹኔታ ላይ ሳትመጣ ፤ የኤርትራን እና የትግራይም ሆነ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አስተማማኝ የህልውና ዋስትና ሊያገኝ አይችልም።

ይኽም በመሆኑ ፤ የሻዕቢያ እና የሕወሐት በግዜያዊነትም ቢሆን የተወሰነ እረፍት ለእነ እዚኽ አከባቢ ሕዝብ ማምጣት ቢችሉም ወይንም ምርጫቸው በግዜያዊ ታክቲክነት ተቀባይነት ሊኖረው ቢችልም ፤ በስትራቴጂክ አስተሳሰብ ደረጃ ዘላቂ መፍትኼ በአለ መሆኑ ፤ ሕወሐት እና ሻዕብያ የተናጠል ራስን ከማዳን እንቅስቃሴያቸው በተጓዳኝ ፤ በኢትዮጵያ ደረጃውን የጠበቀ ዴሞክራሲያዊ ስረዓት እንዲገነባ እንደ ባለጉዳይ (Natural stake holders) እና እንደ ኢትዮጵያዊ መሥራት ነበረባቸው።

ስለ እዚኽ ፦ ሕወሐት እና ሻዕብያን ነገዳዊ አደረጃጀት እና ተገንጣይነት ዓይነት ጠባብ ፖለቲካዊ ፕርግራም እንዲይዙ የገፋቸው የመጀመሪያው ምክንያት የኢትዮጵያ ማሕበረ ኢከነሚ ድቀት የፈጠረባቸው የህልውና ስጋት ይመስላል።

ከእላይ እንደ አልነው ፤ እነ እዚኽ ኹለት ድርጅቶች ፤ ይኽን መሰል ጎጠኛ ፕሮግራም ከእሚይዙ በስትራቴጅካዊ አስተሳሰብ ተቃኝተው ባለመብት በመሆናቸው በመላው ኢትዮጵያ አካታች የሆነ ዴሞክራሲያዊ ስረዓት ለመገንባት ከእሚፈልጉ ሌሎች የሐገሪቱ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር መሥራት ነበረባቸው ማለት ግን አብረው ሊሰሩዋቸው የእሚችሉ ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በኢትዮጵያ ነበሩ ማለት አይደለም ።

እኔ በአለኝ እውቀት ፤ የኢትዮጵያ የዘመናዊ ፖለቲካዊ ፓርቲዎች እድገት ፤ እንደ ፓርቲው አባላት እና አመራሮች የግል ዕይታ አንፃር ከተጻፉ ብዙ እና ጠቃሚ መጽሐፍት በአሻገር ፤ በነጻ እና ገለልተኛ ተመራማሪዎች ፤ የተደረገ ጥናት ስለ አልገጠመኝ በልበ ሙሉነት መናገር በአይቻልም ፤ መንግሥት ሆኖ የእሚቆመው ኃይልም (የኃይለ ሥላሴ መንግሥትም ሆነ ደርግ) ፣ እንደ ኢዴሕ እና ኢሕአፓ የነበሩት እና የኃይለ ሥላሴን መንግሥት እና ደርግን በነፍጥም ለመታገል ሜዳ ወጥተው የነበሩት የመላ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ፓርቲዎች ፤ በውስጣቸው በነበረው የስልጣን ሽኩቻ ፣ የመክዳት ችግር ፣ ድርጅታዊ ዴሞክራሲያዊ አልባነት ፣ ወዘተ ፤ ምክንያት ፦ እንኳን ተጨማሪ አቅም የአላቸውን አዳዲስ አባላት ሊስቡ ፤ ራሳቸውም እንደ ድርጅት መቆም አቅቶዋቸው የተፈረካከሱበት ኹኔታ በመኖሩ ፤ ሕወሐት/ኢሕአዴግ እና ሻዕቢያን በእነ እዚኽ መሠረት የለሽ ትርክቶቻችኹ ላይ የተመሠረተውን እርባና ቢስ የነገድ ብሔርተኝነት እና የተገንጣይነትን ፖለቲካዊ ፕሮግራም ይዛችኹ ከእምትታገሉ ፤ ከስትራቴጅካዊ አስተሳሰብ ደረጃ የተሻለ የእሚመስል ፕሮግራም ከያዙት እና በመላ ኢትዮጵያ በመሰላቸው መንገድ ፍትኃዊ ስረዓት ለመገንባት ከተነሱት እንደ ኢሕአፓ ፣ ኢዴሕ ፣ መኢሶን ፣ ወዘተ ፤ ጋር ተዳብላችኹ ትግል አላደረጋችኹም ሊባል የእሚችል አይመስልም ።

ለምሳሌ ፦ ብዙዎቻችን እንደ እምናወቀው ፤ ብኋላ ኢሕዴን (ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) ፣ ከእዛኽ ብአዴን እና አኹን አዴፓ ሆኛለኹ የእሚለው ቡድን ፤ ኢሕአፓ አንጃ የእሚለው እና መንዝ ላይ የተደመሰሰው በብርሐነመስቀል[14] ይመራ የነበረው ሠራዊት ሰአይሆን ፤ በዘሩ ክሸን የእሚመራው እና የኢሕአፓ ወታደራዊ ክንፍ ማለትም ኢሕአሠ (የኢትዮጲያ ሕዝብ አብዮታዊ ሠራዊት) የእሚባለው እና በአሲምባ የመሸገው ቅሪት ነው።

የኢሕአፓ ሕዝባዊ ክንፍ በከተማ ውስጥ በቀይ ሽብር ከተመታ እና እነ ተስፋዬ ደበሳይን[15] መሰል የፓርቲው አመራሮች ከተገደሉ በኋላ ፤ የተረፉት አመራሮች ወደ አሲምባ በመግባት ፤ ኢሕአሠን ተቀላቅለው የትጥቅ ትግሉን ለመቀጠል ሞክረዋል። ሆኖም ወታደራዊ ክንፉ እና የተወሰኑ እና ከቀይ ሽብር የተረፉት ፖለቲካዊ አመራሮቹ ትግሉን ለማስቀጠል ቢሞክሩም እንደ ብዙዎቹ ዘገባ በኢሕአፓ ውስጥ የአለው ፖለቲካዊ አየር አል አሠራ ስለ አላቸው ፤ ትግል አቋርጠን አንሰደድምም እጃችንም ለደርግ አንሰጥም የአሉ፟ት የተወሰኑ አባላት ፤ ራሳቸውን ከኢሕአፓ ኢሕዴን ብለው በመሰየም ፤ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ጋር ለመተባበር በመወሰናቸው የመጣ ነው ።

ይኽን የአነሳኹበት ምክንያት ፤ በስትራቴጂክ ተባባሪነት ደረጃ ፤ እንደ ኢዴሕ እና ኢሕአፓ ወይንም ሌሎች መሰል በሐገሪቱ ውስጥ የነበሩ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ከሕወሐት/ኢሕአዴግ እና ሻዕብያ ጋር ለትብብር የእሚያስተሳሥራቸው ነገር ቢኖርም ፤ መሠረታዊ ድርጅታዊ ጠባያቸው ግን በፍፁም አብሮ ሊያሰራቸው የእሚችል አልነበረም ፤ የራሳቸው ነባራዊ አባላትም ድርጅታቸው አላኖር እና አላሰራ ብሎዋቸው ድርጅቱን ያፈረሱት በመሆኑ ።

ይኽም ሌላው እና ኹለተኛውም ምክንያት ሊሆን ይችላል ሕወሐት እና ሻዕብያን በጎጥ እስር ቤት ውስጥ የአቆያቸው።

የሕወሐት እና የሻዕብያ መሪዎችም እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ማሕበራዊ እና ፖለቲካዊ ሕልውናቸው ከመላው ኢትዮጵያ ህልውና ጋር በከፍተኛ ደረጃ የተጣመረ በመሆኑ ፤ ከእዚኽ ከያዙት ጠባብ የጎጠኝነት ፕሮግራም ይልቅ እንደ ሌሎቹ ድርጅቶች ለምን ሐገራዊ ርዕይ የአለው ፕሮግራም ሳይዙ ቀሩ ለእሚለው ጥያቄ ሦሥተኛው መላምታዊ መልስ ፤ ተፈጥሮዋዊ ከሆነው የፖለቲካዊ አስተሳሰብ ልዩነት በአሻገር ፤ የእነ እዚኽ ድርጅት መሪዎች እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ፤ የአደጉበት እና የላሸቀው የኢትዮጵያ ማሕበረ ኢከነሚ የጫነባቸው የማሕይምነት እዳ ሊሆን ይችላል።

ስለ እዚኽ ፦ እነ እዚኽ ሦሥት ጉዳዮች ፤ እነ እዚኽን ኹለት ድርጅቶች ፤ ይኽንን መሰል ጠባብ እና ከስትራቴጅክ አስተሳሰብ አንጻር ከጥቅሙ ጉዳቱ የእሚመዝን ጠባብ የፖለቲካ ፕሮግራም እንዲይዙ የአደረጋቸው ይመስለኛል።

ለምን ይኽን መሰል ጠባብ ፕለቲካዊ ፕሮግራም ያዙ የእሚለውን ጥያቄ በእዚኽ ከመለስን ፤ ቀጥሎ የእሚመጣው ጥያቄ የእሚሆነው ፤ እነ እዚኽ ኹለት ድርጅቶች ይኽንን ጠባብብ ፕሮግራም ይዘው ፤ በርዕዮት ጥራት ፣ በድርጅት ስፋት ፣ በድርጅታዊ ኃብት ፣ ወዘተ ፤ ከእነርሱ በእጅግ ከእሚበልጡት የወቅቱ የሐገሪቱ ፖለቲካ ኃይላት በላቀ ኹኔታ ፤ በኃይለ ሥላሴ (ሻዕብያ) በኋላም በደርግ ዘመን ከግዜ ወደ ግዜ እየተጠናከሩ ኼደው ፤ ውጤታማ ሊባል የእሚችል የትጥቅ ትግል በማድረግ እና ከደርግ ውድቀት ማግስት ፤ ራሳቸውን ብቸኛ እና ተቀናቃኝ አልባ የኢትዮጵያ (የኢትዮጵያ + ኤርትራ) የፖለቲካ ኃይላት ማድረግ ሊችሉ በቁ? የእሚለው ኹለተኛው ይሆናል።

በእኔ እምነት ይኽንን ኹለተኛውን ጥያቄ በመመለስ ፤ ለእነ እዚኽ ኹለት ድርጅቶች ከአንጻራዊ ዝቅተኛ ኹኔታ ውስጥ በመውጣት የአለፈው 30 ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ አቅጣጫ ወሳኝ የሆኑ ሐገራዊ ፖለቲካዊ ኃይላት ከአደረጉዋቸው ምክንያቶች መካከል ፤ የእሚከተሉት ሦሥቱ ዋነኞቹ ናቸው ፦

  1. በዋናነት በገበሬው የተዋቀረ እና የተራዘመ የትጥቅ ትግል በማድረግ ለድል መብቃት የእሚለውን (Peasant army struggle) የትግል ስልት ፤ በአግባቡ ተረድተው ይኽንን ስልት የእሚመጥን የትግል ጽናት እና ስነምግባር በማዳበራቸው
  2. ደርግ የራሻው ሞስኮ ተንጠልጣይ በመሆኑ ፤ በቀዝቃዛው ጦርነት ምክንያት አሜሪካ ከደርግ ተቃራኒ የእምትቆም በመሆኑ ፤ ምንም እንኳን እነ እዚኽ ኹለት ድርጅቶች ማርክሲስት ነን ቢሉም የደርግ ጠላት በመሆናቸው የአሜሪካን ቀጥታ ድጋፍ በአይሆንም ተዘዋዋሪ ድጋፍ የእሚያገኙ በመሆኑ
  3. ቀዝቃዛው ጦርነት የሶቭየት ውሕደት (Soviet Union) መክሰም በማስከተሉ ፤ የደርግ መንግሥት ከሞስኮ የእሚያገኘው የትጥቅ እና ሌሎች እገዛቸው መቋረጣቸው ናቸው።

ሕወሐት እና ሻዕብያ እንከተለዋለን ብለው የመረጡት በዋናነት በገበሬ የእሚካኼድ የተራዘመ የትጥቅ ትግል ማድርግ የእሚለው የትግል ስልታቸው ፦ ለዴሞክራሲያዊ መዓከላዊነት መገዛት ፣ የለመዱትን እና የእሚመቸውን የከተማ ኑሮ ለአንድ እና ለኹለት ዓመታት ሳይሆን ለ10 ዓመታት እና ከእዚያኽ በላይ ለሆነ ግዜ በመተው ራስን የገጠሩ ኑሮ ውስጥ መክተት እና ፈታኙን የትጥቅ ትግል ኑሮ ከ10 ዓመታት በላይ ለመኖር በሕይወት መቁረጥን የእሚጠይቅ ነው።

የሕወሐት እና የሻዕብያ አመራሮች እና ታጋዮች ፤ ይኽንን የትግል ስልት ለ16 እና ለ29 ዓመታት በተከታታይ ለመከተል የእሚያበቃቸው ስነ ምግባር አዳብረው ፤ በብዙ መስዕዋትነት እና በጠንካራ ጽናት ይኽንን ትግል መቀጠል መቻላቸው ፤ ለድል ከአበቃቸው ምክንያት ቀዳሚው ነው።

በተራው ይኽን መሰል ወይንም ይኽን የእሚመጥን የትግል ስልት ፣ ድርጅታዊ ስነ ምግባር እና የታጋይነት ጽናት በሌሎቹ የወቅቱ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ አለመኖር ሌሎቹን ድርጅቶ አዳክሞ ከትግሉ ሜዳ አስወጣቸው። ይኽም ብቻ ሰአይሆን ፤ እነ እዚኽ ድርጅቶ ይኽንን የገበሬው እጅ ውስጥ የመግባት ስልት መምረጣቸው ፤ በትላልቆቹ ድርጅቶች ውስጥ በከተማ እና በገጠር ከእሚደረገው የመጠፋፋት ትግል እንዲሰወሩ ፤ ስለ እዚኽም ህልውናቸው እንዲቀጥል እድል ፈጠራላቸው።

ከእዚያኽ በመቀጠል የእነ እዚኽን ኹለት ቡድኖች ከነጠባቡ ፖለቲካዊ ፕሮግራሞቻቸው ጋር ለድል ያበቃቸው ፤ ደርግ ራሱ የራሻው ከምኒስት ፓርቲ ተንጠልጣይ በማድረግ ፤ የራሻው ከምኒስት ፓርቲ ተወካይ በኢትዮጵያ በመሆኑ ፤ በእዚያኽን ወቅት በነበረው ቀዝቃዛው ጦርነት ሳቢያ ፤ ምንም እንኳን እነ እዚኽ ኹለት ድርጅቶች እንደ ደርጉ ማርክሲስት ነን የእሚሉ ቢሆንም ፤ ደርግ የመላው ኢትዮጵያ ስለ እዚኽም በአንጻራዊነት ትልቅ ፖለቲካዊ ምሕዳር ላይ የተንሰራፋ ትልቅ ከምኒስታዊ መንግሥት በመሆኑ ፤ ደርግን ከጣልን በኋላ ፤ ስለ ሕወሐት እና ሻዕብያ እንጨነቃለን በእሚል ፤ አሜሪካኖቹ እነ እዚኽን ኹለት ድርጅቶች በቀጥታ ባይረዱም ጠላት አድርገው አለመፈረጇቸው ፤ ለድል እንዲበቁ ከአደረጋቸው ምክንያት ሌላው ኹለተኛው ነው፦

“እ.አ.አ. በ1974 ዓ.ም. ከተደረገው የመፈንቅለ መንግሥት በኋላ ፤ አዲሱ የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም መንግሥት በአቅጣጫ ማርክሲስት ሌኒንስት በመሆን የሞስኮ ተንጠልጣይ እና ተደጋፊ በመሆኑ ፤ ኢትዮጵያ በቀዝቃዛው ጦርነት አሰላለፍ ውስጥ ወገንተኝነቷ ተለወጠ። ሶቭየቶች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፏቸው ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ በመምጣት ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ለኢትዮጵያ ማቀበል ውስጥ ገቡ። ይኽም የተዋኃዱትን ጎዛቶችን (አሜርካንን) በግልጽ ከኤርትራ ነጻ አውጭዎቹ ጋር እንድታብር አደረጋት ። ይኽ ቢሆንም ፤ የኤርትራ ነጻ አውጭዎቹ ራሳቸው ማርክሲስት ነን ይሉ ስለ ነበር ፤ ጉዳያቸው ከዋሽንግተን ፤ መሳሪያ እንዲጋዝላቸው የእሚያደርግ ዓይነት ወገንተኝነትን የእሚያስከትል ግን አልነበረም።”

“The 1974 coup in Ethiopia led to a change of sides in the Cold War game as the new government of Mengistu HaileMariam, Marxist-Leninist in orientation, became a client of and dependent on Moscow. The Soviets became increasingly involved in Ethiopian affairs and started massive flow of arms to the government. This led the United States to sympathize more openly with the Eritrean cause. There were no large arms transfer to the Eritreans, however, not least because the Eritrean rebels also referred to themselves as Marxists, which not help their cause in Washington. [126]”

ይኽም አሜሪካንን ፤ እንደ ሶቭየቶቹ ቀጥታ የጦር መሳሪያ በማቅረብ በአይሆንም ፤ በተለያየ መልኩ አማጺያኖቹን እንድታግዝ ሲያደርግ ቆይቶ ፤ በቀዝቃዛው ጦርነት የአሜሪካን ተቃራኒ ሆነው የዓለም ዓቀፉን ከምኒዝም የእሚመሩት የከምኒስት ፓርቲ መሪዎች ፤ ርዕዮታቸው በተግባር ተፈትኖ ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ሰብዓዊም ሆኑ ቁሳዊ እድገት በዘላቂነት በትልሙ መሠረት ሊያመጣ እንደ እማይችል እና ይኽንን ርዕዮት ይዘው ከእዚኽ በኋላ መቀጠል እንደ እማይችሉ ፤ በውስጥ መግባባት ላይ ሲደርሱ ፤ በወቅቱ የሶቭየት ሕብረት መሪ ሚካኼል ጎርቫቾው አማካኝነት ፤ የአወቃቀር ለውጥ እና ግልፅነት (Perestroika and Glasnost) በተባለው አዲስ ፕሮግራማቸው ፤ የሕትመት ነፃነትን በመፍቀድ እና በኢከነሚው እና በፖለቲካው ረገድም የአወቃቀር ለውጥ በመፍቀዳቸው ወይንም አምባገነናዊ ስረዓታቸውን ከሰላማዊ ሕዝብ በታንክ ከመከላከል ስለተመለሱ ፤ በራሺያ አብዮት የሶቭየት ውሕደት ሐገር የተደረጉ እና የራሳቸው ሐገርነት ከእዚያኽ ቀደም የነበራቸው ፤ የባልካን ፣ የቦልቲክ ፣ የኮውከስ እና የኤሽያ አከባቢ ሐገራት ፤ ከውሕደቱ እየወጡ የራሳቸው ሪፐብሊክ መሆን ጀመሩ ፣ ጀርመኖች ለ50 ዓመት ገደማ የከፈላቸውን ግንብ አፍርሰው ምዕራብ እና ምሥራቅ የእሚለውን ክፍፍል አጥፍተው ተዋኃዱ ፣ ወደ ስድስት የእሚጠጉት የይጎዝላቪያ ሐገራትም እንደ እዚኹ ወደ ትንንሽ 6 ሐገራትነት ተቀየሩ ፤ በሶማሊያ ዚያድ ባሬ ሐገር ጥለው ተሰደዱ ፤ በኢትዮጵያም ከ15 ዓመት ትግል በኋላ እስከ 1981 ዓ.ም. በትግራይ ወረዳዎች ተወስኖ የነበረው ሕወሐት እና ከ28 ዓመታት ትግል በኋላ በሳሕል ተራሮች የቆየው ሻዕብያ ፤ ከ1981 ዓ.ም. ወይንም በፈረንጆቹ ከ1989 ዓ.ም. ጀምሮ ሕወሐት ኢሕአዴግ የእሚባለውን ግንባር ፈጥሮ እና ከውስጡ ሰዎችን እያወጣ አዳዲስ የነገድ ድርጅቶችን እያዋቀረ ፣ ሻዕብያም በድል ላይ ድርብ ድሎችን በፍጥነት እያገኘ ፤ ከኹለት ዓመት በአነሰ ግዜ ፤ ትግራይን እና ኤርትራን ሙሉ በመቆጣጠር እና ከእዚያኽም ፤ የሞስኮን “ማሸለብ” ተከትሎ የህልውናው መሠረት የሆነው የሞስኮው ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ርዳታ ሲነጥፍ ፤ በእየግንባሩ በእሚያደርገው ጦርነት እየተፈታ ትጥቁን ጥሎ የእሚሸሸውን የደርግ ወታደር እግር በእግር እየተከተሉ በዋናነት ሕወሐት ፤ በግንቦት 20,1983 ዓ.ም. አዲስ አበባን ተቆጣጠረ ።

ሻዕቢያም በተወሰኑ ሜካናይዝድ ብርጌዶቹ ኤርትራን ከመቆጣጠር በአሻገር ከሕወሐት ጋር አብሮ አዲስ አበባ ቢገባም ፤ የመገንጠልን ዓላማ አራማጅ በመሆኑ እና አስቀድሞም አስመራን የተቆጣጠረም በመሆኑ ፤ ወደ አዲስ አበባ አብሮ የገባው በአጋዥነት ነበር።

ስለ እዚኽ ፦ ምንም እንኳን እነ እዚኽ ኹለት ድርጅቶች ፤ የትግል ስልታቸው የአደረጉትን ገበሬን መሠረት የአደረገ የነፍጥ ትግል ለማድረግ ፤ በሕይወታቸው ቆርጠው እና ስልቱን የእሚመጥን ድርጅታዊ ስነምግባር ማዳበራቸው ፤ ከእነ ጠባብ ፖለቲካዊ ፕሮግራማቸው በገጠራማው ኢትዮጵያ ከመንግሥት እና ከሌሎች ተቀናቃኞች ሰውሮ በማቆየት ለድል ቢያበቃቸውም ፤ ከእዚኽ በላይ እንደ አየነው ግን ድርጅቶቹ ባላቸው ጥንካሬ ብቻ ለድል መብቃት እንደ አልቻሉ እናያለን።

ከታሪካዊ ሰንካላነት የተነሳ እና የእርሱም ትሩፋት በሆነው የአልበቁ ፖለቲከኞች ምክንያት የኢትዮጵያ ፖለቲካ አጓጉል መዳከሙ ፤ በእዚኽ የሽምቅ ውጊያ ፋሽን ባለፈበት ዘመን ፤ የሽምቅ ተዋጊዎች እንዲፈሉ በመፍቀዱ ፣ የፖለቲካዊ አመራር ደካማነት እና የዓለም ዓቀፉ ፖለቲካ ማዕበል ገፍተውት እንጂ ፤ በኢትዮጵያ ኹኔታ ሽምቅ ተዋጊ ብሔራዊውን የኢትዮጵያ መንግሥት በኃይል መገርሰስ እንዲችል የእሚያደርግበት ኹኔታ በጣም ጠባብ ነው።

ለእዚኽም ፤ ማርክስ ሀሮልድ የተባለው የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፊ ፤ የአሜሪካውን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እና መከላከያ ምኒስትር ጠቅሶ ፤ የአቀረበው ኃሳብ ፤ ይኽን የእሚያጠናክር ይመስለኛል ፦

“የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የኦጋዴኑ ችግር እና ሌሎች እሱን መሰል ችግሮች መፈታት የእሚችሉት በማሕበረኢከነሚ ልማት እና ራስን በራስ የማስተዳደርን በመፍቀድ ነው የእሚል ኃሳብ አቀረበ። ይኽንንም ተክትሎ በዋሽንግተን በእየ ክፍለ ሐገሩ የልማት ጥረቶችን ለማገዝ ፣ አስቀድሞ ስምምነት የተደረሰባቸው የጦር መሳሪያዎች ለማቅረብ ፣ ቀለል ያሉ የሰርጎ ገብነት ጦርነት መከላከል የእሚያስችሉ አጋዥ ስንቆችን ለማቀበል እና 40 ሺ ወታደር የአለውን የሐገሪቱን መከላከያ ሐገር የመከላከል ሥራውን በአግባቡ መወጣት በእሚያስችልበት ቁመና ላይ ለማምጣት ፈጣን እንቅስቃሴ ውስጥ ተገብቶ ነበር። የአሜሪካኑ የመከላከያ መሥሪያ ቤት ፤ ይኽ ቁጥር ፤ የሶማሌውን እና በእየ ግዜው እያደገ የመጣውን የኤርትራውን ሰርጎ ገብነት ጦርነት በቁጥጥር ስር ለማዋል በቂ ነው ብሎ አምኗል።”

“The State Department therefore suggested that the Odagen problem, and others like it, could be solved through socioeconomic development and by the grant of self-rule. Washington was ready therefore to support development projects in the provinces, to speed up the delivery of weapons already authorized, and to provide relatively inexpensive logistical support for the counterinsurgency warfare and to bring the Ethiopian army to its operational strength of forty thousand. That number, the Pentagon reckoned, could countain the Somalis and the growing insurgency in Eritrea. [65]”

ምንም እንኳን ይኽ የማርክስ ኃሮልድ ኃሳብ ፤ የኃይለ ሥላሴን መንግሥት የእሚመለከት ቢሆንም ፤ መሠረታዊ አስተሳሰቡ በሆነ ዘመን በስልጣን ላይ በአለው መንግሥት የእሚወሰን አይደለም።

ከእላይ እንደ ተጠቀሰው ዘገባ ፤ የኃይለ ሥላሴ መንግሥት በፖለቲካዊ አመራሩ ረገድ መሥራት የእሚገባውን ሥራ ቢሰራ ኖሮ ፤ በአንጻራዊነት የታጠቀው ደካማ የጦር መሳሪያ (የወቅቱ የኢትዮጵያ ሠራዊት በዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስ የእሚመራ ፣ ባለ ሜካናይዝድ ብርጌድ እና ታንከኛ ክፍል የአለው ፣ የራሱ የአየር ኃይል የአለው መሆኑ እንደ ተጠበቀ ሆኖ) እና በመከላከያ ውስጥ 40 ሺ ወታደር ብቻ የነበረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ፤ የኤርትራውን ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያ ሊነሱ የእሚችሉ የገንጣይ እንቅስቃሴዎች እና እንደ ሱማሊያዊ ዚያድ ባሬ ከአሉ፟ ኢትዮጵያውን መውረር እንፈልጋለን ከእሚሉ የውጭ ኃይላት ኢትዮጵያን ለመከላከል በጣም በቂ ነው።

ይኽ ከሆነ ፤ የደርግ ፖለቲካዊ መኃይምነት ከዓለም ዓቀፉ ፖለቲካዊ ምሕዳር መቀየር ጋር አብሮ በአይመጣ ኖሮ ፤ ከ200 ሺ በላይ በአግባቡ የታጠቀ ፣ በወታደራዊ መኪና ፣ በታንክ ፣ በተወንጫፊ ሚሳይሎች ፣ በመድፍ ፣ ወዘተ ፤ ሜካናይዝድ የሆነ ፣ ራሺያ ሰራሽ በሆኑ በሚግ እና በሱኮይ የጦር ጀቶች ፣ በተለያዩ አጥቂ እና መጓጓዣ ሄሊኮፕተሮች ተገንብቶ ፣ ቀላል የእማይባል ወታደራዊ እወቅት በአላቸው ጀነራሎች የእሚመራ የኢትዮጵያ ሠራዊት ፤ የሽምቅ ተዋጊ የእሚያሰጋው አይደለም።

ይኽም በመሆኑ ፤ የእነ እዚኽ ኹለት ድርጅቶች ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ስኬት ፤ በዋናነት እድሜ ጠገቡ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግር የወለደው እና የአስቻለው ሆኖ ፤ በዓለም ዓቀፋዊ ፖለቲካዊ ማዕበል የተገፋ እና የታጋዮቹ ስነምግባር እና ጽናት የአገዘው ድል ነው ማለት የእምንችል ይመስለኛል።

እነ እዚኽ ኹለት ጠባብ ድርጅቶች በእዚኽ መልኩ ተሳክቶላቸው የያዙትን ጠባብ የፖለቲካ ፕሮግራም መተግበራቸው የተወሰነ አዎንታዊ ውጤት ቢኖረውም ፤ በዋናነት እና በዛላቂያዊ አስተሳሰብ ረገድ ግን ፤ የብዙ ዘመን የኢትዮጵያን (ኢትዮጵያ + ኤርትራ) የሕዝባዊ ወይንም ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ጥማት በ30 ዓመት የአዘገየ እና ብዙ ተዛማጅ የሆኑ የጎንዮሽ ችግሮችን የአስከተለ ነው ፤ የእሚል እምነት ነው የአለኝ።

እነ እዚኽ ፤ ኹለት ድርጅቶች ተሳክቶላቸው የፖለቲካ ስልጣን ይዘው የፖለቲካ ፕሮግራሞቻቸውን በመተግበራቸው የተገኘው ዋንኛ መልካም ትሩፋት ፤ አንጻራዊ ሐገራዊ ሰላም ነው። የእነርሱ ወገን በእማያሻማ መልኩ ወታደራዊ ድል በማግኘቱ ፤ ከእነ እዚኽ ድርጅቶች ድል ማግስት ኢትዮጵያ ከ20 ዓመታት በላይ ሲንጣት እና ሲያደማት ከነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት እረፍት አግኝታለች።

ይኽም ፤ ምንም እንኳን ተመሳሳይ ነገር ስለ ኤርትራ ማለት በአይቻልም ፤ ከኤርትራ መለስ በአለችው ኢትዮጵያ ፤ በብዙ ኢትዮጵያዊያኖች ፣ በውጭ የኢትዮጵያ ወዳጆች እና በአመቺ ዓለም ዓቀፋዊ ኹኔታ በመታገዝ ፤ በሐገር ዓቀፍ ደረጃ ከፍተኛ መጠን የአለው የኢከነሚያዊ ልማት ሥራ እንዲሰ፟ራ እና የተወሰነም ቢሆንም ፖለቲካዊ ነጻ እንቅስቃሴ እንዲቻል አድርጓል።

በመሠረተ ልማት እና በማሕበራዊ አቅም ግንባታ ፤ ኹለት ብቻ የነበሩ የመንግሥት ዩንቨርስቲዎች ፤ በ20 ዓመት ውስጥ በ15 እጥፍ አድገው ከ30 በላይ ደርሰዋል ። ከዩንቨርስቲ በታች ባሉት የትምህርት ተቋማትም በመላ ሐገሪቷ ፤ ለቁጥር በእሚያታክት ኹኔታ ፤ ብዙ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል ፤ በትልቋ ኢትዮጵያ ደካማ መሠረት ልማት ፤ የአንደኛ ደረጃ የትምህርት ሽፋንን ከ90% በላይ ደርሷል ፤ ዛሬም የዛፍ ጥላ የመማሪያ ክፍላቸው የሆኑ የኢትዮጵያ ልጆች እንደ አሉ ቢነገርም ።

በጤናው መስክ ፤ ትላልቅ ሆስፒታሎችን ጨምሮ እስከ ጤና ኬላዎች ድረስ በሐገሪቱ ከፍተኛ የጤና ተደራሽነትን የማሳደግ ሥራ ተሰርቷል ።

በመንገድ ግንባታ ፣ በከተሞች እድገት ፣ የግል መስኩን ፦ በትምህርት ፣ በጤና ፣ በባንክ ፣ በንግድ ፣ በሪል ስቴት ፣ ወዘተ ፤ በስፋት በማሳተፍ በሐገር ደረጃ ትላልቅ ኃብት እና ተቋማት ተፈጥረዋል ።

በሐገር መከላከያ እና ደህንነት ተቋማት ግንባታም ፤ መጠነ ሰፊነት የአላቸው ብዙ ሥራዎች ተሰርተዋል።

በአጠቃላይ ፤ ጠቅላላ ሐገራዊ ምርት ፤ በተለይ ሕወሐት/ኢሕአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ በአሉት ኹለተኛው አስር አመታት ገደማ ፤ በዓመት 10% በላይ በማደግ ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ፤ ሐገሪቱ በዘመናዊ ታሪኳ ለመጀመሪያ ግዜ በፈጣን ኢከነሚያዊ እድገት ላይ ከአሉ፟ የዓለም ሐገራት ተርታ የገባችበት እና በሐገር ዓቀፍ ደርጃ ሐገራዊ ምርት እና የማምረት አቅም ፤ በ20 ዓመታት የስልጣን ቆይታ ከእጥፍ በላይ የአደገበት ነበር ።

በኃይለ ሥላሴ ዘመን ብቅ ብቅ ማለት ጀምረው ወድያው በተዳፈኑት የሕትመት ነፃነት ጉዳይ ብንመጣ ፤ የ1997 ዓ.ም. ምርጫ ተከትሎ መንግሥታዊ ስደት ሳይነሳባቸው በፊት ፤ በሰፊ ነፃነት ፤ ከዘውድ ስረዓት አራማጁ እስከ ካፒታሊዝም ስረዓት አራማጁ ደጋፊ የሆኑ ፤ በመሰላቸው መንገድ የእሚጽፉ ከ70 ያላነሱ ጋዜጦች እና መጽሔቶች ነበሩ ።

በፖለቲካ ፓርቲ ማደረጀት እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴው መስክ ፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ፤ ደርግ በስልጣን ከተደላደለ በኋላ እስኪያግዳቸው ድረስ ፤ በአብዮቱ ማግስት በትንሹም ቢሆን ሲንቀሳቀሱ ከነበሩበት ኹኔታ በተሻለ ፤ ስማቸውን እንኳን ለመያዝ እስኪያስቸግረን ድረስ ፤ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመስርተው ፤ የይስሙላም ቢሆን ፤ የብዝኃን ፓርቲ መልክ የአለው እና የተለያዩ ፓርቲዎች ፤ በመንግሥት ሚድያ ላይ ፤ ተከራክረው እና የብዙ ሕዝብ ተሳትፎ የነበረው 5 ሐገራዊ ምርጫ አካኺዷል ።

ምንም እንኳን በአምስቱም ምርጫዎች ሕወሐት/ኢሕአዴግ ከ80% በላይ የሕዝብ ድምጽ አግኝቻለኹ በእሚል ራሱ አሸናፊ የሆነባቸው ምርጫዎች ቢሆኑም ፤ ከእዚኽም በላይ አውራ ፓርቲ ካልሆንኩ እያለ በአደባባይ የሞኝ ዘፈኑን ሲዘፍን ቢኖርም።

ይኽ የእነ እዚኽ ኹለት ጠባብ ድርጅቶች ፖለቲካዊ ስኬት አዎንታዊ ውጤት ሲሆን ፤ በጠባብነታቸው ምክንያት በኹለቱ ድርጅቶች ውስጥ ትርፍ አልባ በቀልተኝነት እና ዘላቂ አስተሳሰብ የሌለው ጥቅመኝነት በመኖሩ እነ እዚኽ ድርጅቶ በትልቁ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሚናቸው ካልደበዘዘ ፣ እንደ ገና በአዲስ አግባብ ከአልተዋቀሩ ወይንም ከአልከሰሙ የእሚያቆም የእማይመስል ፤ ለራሳቸው ለድርጅቶቹ ፣ ለኤርትራ ፣ ለትግራይ እንዲኹም ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ የአሳር ምንጭ እየሆነ እና ሆኖ ሊቆይ የእሚችል መናቆር መኖሩ እና የጠባብነታቸው ኢዴሞክራሲያዊነት የኢትዮጵያን (ኢትዮጵያ + ኤርትራ) ሕዝብ ፤ የዴሞክራሲያዊ ወይን የሕዝባዊ መንግሥት ህልም ቢያንስ በ30 ዓመት ያዘገየ ሆኗል።

በሕወሐት እና በሻዕብያ መካከል ፤ በእንግሊዘኛ የፍቅር-ጥላቻ (love-hate) ዓይነት ግንኙነት ነው የአለው።

ምንም እንኳን ፤ በእኔ እምነት በእነ እዚኽ ድርጅቶች መካከል ለአለው ፤ ለእዚኽ ዓየነት የፍቅር-ጥላቻ ግንኙነት እና ለእሚያስከትለው አሉታዊ ተጽኖ ዋናው ምሕዳር ዋናው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በዴሞክራሲያዊ እና አካታች በሆነ መልኩ በአለመታነጹ ምክንያት ቢሆንም ፤ እነ እዚኽ ድርጅቶች ፈርጥመው የጎበዝ አለቃ ዓይነት መሆናቸው እና አጓጉል እርስ በእርስ መነቋቆር ውስጥ መግባታቸው ግን አሌ የእማይባል ነው።

አንዳንዶች በኹለቱ መካከል የአለውን ይኽን የፍቅር-ጥላቻ ግንኙነት በአግባቡ ለመረዳት እነ እዚኽ ድርጅቶች ከመመሥረታቸው በፊት እነ እዚኽ ድርጅቶች እንወክለዋለን በእሚሉት ሕዝብ መካከል የአለውን ግንኙነት መረዳት አስፈላጊ ነው ሲሉ የእሚሰማ ቢሆንም ፤ በእኔ እምነት ይኼ ተራው እና ላይ ሕወሐትን በተመለከተ በኢትዮጵያ ውስጥ በነገዶች መካከል ነፍጥ ለማንሳት የእሚያበቃ ታሪካዊ ጠብ በተለየ ኹኔታ የለም ብዬ ለማሳየት እንደ ሞከርኹት ፤ በኤርትራ እና በትግራይ ሕዝብ መካከል በሻዕብያ እና በሕወሐት መካከል የአለውን ቆልምልም ግንኙነት ግድ የእሚል ተጨባጭ ምክንያት የለም ፤ በመላው ኢትዮጵያ ኹነኛ ዴሞክራሲያዊ ስረዓት አለመኖር ከአፋፋመው መኃይምነት እና ድህነት በስተቀር።

የእነ እዚኽን ድርጅቶች አፈጣጠር ስናይ ፤ ሻዕብያ አንጋፋ እንደ ሆነ እና ሕወሐት በራሳቸው በትግራይ ተወላጆች ቢመሠረትም ፤ ሻዕብያ አንጋፋ በመሆኑ በአለው የልምድ እና ዙሪያ መለስ የአቅም የበላይነት ፤ የመጀመሪያዎቹን የሕወሐት ታጋዮች ከማሰልጠን ጀምሮ የእሚያግዝ ስለ ነበር ፤ ጅማሮው ላይ በኹለቱ መካከል የነበረው ግንኙነት የመምህር እና የደቂቃን (Teacher & disciple) ይዘት የነበረው እንደ ሆነ ነው የእምናየው።

ከእዚኽም በተጨማሪ ሻዕብያ ለሕወሐት ብቻ ሰአይሆን ከሕወሐት እጅግ ለገዘፈው እንደ ኢሕአፓ ለአለው ድርጅትም ኮትኳች እና አጋዥ የነበረ በመሆኑ እና የሕወሐትም ፕሮግራም በትግራይ ብቻ የተወሰነ በመሆኑ ፤ ሕወሐት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ይኽ ነው የእሚባል ተጽኖ ማምጣት የእሚችል ነው ተብሎ የእማይገመት በመሆኑ ፤ መገንጠል ለእሚፈልገው ሻዕብያ ፤ በተገኘው መልኩ ደርግን የእሚዋጉ እና የእሚያዳክም ማናቸውንም ነገር ማድረግ ከእሚል እንጂ ፤ ሕወሐት ገዝፎ ተፎካካሪ ብሎም አንድ ቀን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባለቤት ይሆናል በእሚል እምነት አይመስልም የትብብራቸው መሠረት።

ይኽም በመሆኑ ፤ የኹለቱ ድርጅቶች ግንኙነት በታላቅ እና በታናሽ ፣ በአዛዥ እና ታዛዥ ፣ በአጋዥ እና ታጋዥ ፣ ወዘተ ፤ ዓይነት የተቃኘ ነበር ጅማሮው ላይ።

በግዜ ኺደት ግን ፤ በእኔ እምነት በዋናነት በአቶ መለስ ልዩ ፖለቲካዊ ተሰጥዖ (የሌሎቹን የሕወሐት አመራሮች ሚና ለማሳነስ ሳይሆን) ፤ ደርግን በማዳከም ተስፋ የተጣለባቸው እነ ኢዴሕ (የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሕብረት) ፣ ኢሕአፓ (የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ) ፣ ወዘተ ፣ “ግዙፍ” ፓርቲዎች እየተዳከሙ ፤ በአንጻሩ የተናቀው እና ብዙ ርቀት አይጓዝም የተባለው ሕወሐት ከግዜ ወደ ግዜ እየ ጎለበተ መኼዱ ፤ በኋላም ከተፈረካከሰው ኢሕአፓ (የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ) ወጥቶ ራሱን ኢሕዴን (የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) ከአለው ድርጅት ጋር በመዋኃድ ፤ ሕወሐት የነገድ ፌደራላዊ ፕሮግራሙን በመላው ኢትዮጵያ ለመተግበር ሲንቀሳቀስ እና ዉሕደቱም በሕወሐት የበላይነት የእሚመራ ሲሆን ፤ የመምሕር እና የደቂቃን የነበረው የሕወሐት እና የሻዕብያ ግንኙነት ፤ የመምሕር እና የደቂቃን ሆኖ መቀጠል አልቻለም።

ይኽም ለውጥ ፤ እኔ ነኝ ለእዚኽ የአበቃውኽ በእሚለው ሻዕብያ እና ስለ ትላንት ሳይሆን ስለ ዛሬ እናውራ በእሚለው ሕወሐት መካከል የነበረውን ግንኙነት በማጎመዘዝ የመጀመሪያው ይመስላል።

ከእዚኽ በኋላ ግን በአልተጠበቀ ኹኔታ የሞስኮው መክሰም ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ከፈጠረው ከፍተኛ የአወቃቀር ለውጥ የተነሳ ፤ ሕወሐትን ከኋላ ጎትቶ በማውጣት ዋነኛ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ተዋናይ አደረገው ፤ ይኽንን ኹኔታ ፤ በለንደን ሲደረግ የነበረው ድርድር የእሚያሳየው ይመስለኛል።

ደርግ ከመውደቁ ትንሽ ቀደም ብሎ ፤ ደርግ ራሱ ሕወሐትን አላውቀውም እኔ እምደራደርው ከሻዕብያ ጋር ብቻ ነው እስከ እሚል ድረስ ፤ ሕወሐት እዚኽ ግባ የእሚባል አማጺ አልነበረም።

የወቅቱ አማጺያንን እና ደርግን ለእሚያደራድሩት ሰዎች ፤ ዋነኛ ግባቸው የነበረውም ፤ የተኩስ አቁም እና አብሮ የመሥራት አካኼድ እንጂ ለኤርትራ የፌደራል መንግሥትነት ስልጣንን መስጠት አልቀበለም የእሚለውን ደርግን እና በሪፍረንደም ከመገንጠል በስተቀር ወደ ተኩስ አቁም የእሚያመጣኝ ምንም ዓይነት ነገር የለም የእሚለውን ሻዕብያ አግባብቶ ፤ ለኤርትራ ፌደረላዊ መንግሥትነትን በመፍቀድ የተኩስ አቁምን ወይንም የኤርትራውን ጦርነት ማብቃት ነበር።

በእዚኽ መሐል ፤ በደርጉ ከመጤፍም የእማይቆጠረው እና ፖለቲካዊ አቅሙ ከወታደራዊ ጥንካሬው ጋር እየፈረጠመ የመጣው ሕወሐት/ኢሕአዴግ እኔ ተኩስ የእማቆመው ፤ በመላው ኢትዮጵያ የነገድ ፌደራሊዝም የተዘረጋ እንደ ሆነ ነው የእሚል አቋም ይዞ ብቅ አለ።

ድርድሩ በእዚኽ ቁልፍልፍ ውስጥ እያለ ፤ በጦር ሜዳ የአለው ኹኔታ በከፍተኛ ፍጥነት እየተለወጠ ፤ ሻዕብያውም ሙሉ ኤርትራን የተቆጣጠረበት እና ሕወሐት/ኢሕአዴግም በአስገራሚ ፍጥነት ወደ አዲስ አበባ የተጠጋበት ኹኔታ በመፈጠሩ ፤ ድርድሩ ሳያልቅ ደርግ በእራሱ ግዜ ፈረሰ።

ከእዚኽ በኋላ ብቸኛ የተደራጀ እና አቅም የአለው ኢትዮጵያዊ ድርጅት በመሆን ሕወሐት/ኢሕአዴግ በደርግ ቦታ ኢትዮጵያን ወክሎ ተደራዳሪ በመሆን ፤ ኤርትራዊያን ሪፍረንደም አድርገው ከወሰኑ ከኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ እንዲገነጠሉ እፈቅዳለኹ በማለቱ ፤ ድርድሩ በእዚኽ መልኩ የእርስ በእርስ ጦርነቱን የሚያበቃ ሆኖ ተፈጸመ።

ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ፋይዳውን ሳያሰላ ለ29 ዓመታት ኤርትራን ከኢትዮጵያ መገንጠል ፈልጋለኹ ሲል የነበረው ሻዕብያ ፤ የእኔ ደቀ መዝሙር በአለው ሕወሐት ፤ መገንጠል አይደል የፈለከው ይኸው እንካ ተባለ።

በእዚኽ መልኩ ሻዕብያ እና ሕወሐት ለ29 እና ለ16 ዓመታት በተከታታይ ያደረጉት ጦርነት ሲጠናቀቅ ፤ አስመራ ላይ ሻዕብያ አዲስ አበባ ላይ ደግሞ ሕወሐት የነገሡበትን ኹኔታ ፈጠረ።

ይኽም የአልተጠበቀ ኹኔታ ፤ ኮትኩቶ አሳድጎ ከእራሱ በላይ የሆነውን ትልቁን ወንበር ለሕወሐት በመስጠቱ የተቆጨ የእሚመስለው ሻዕብያ እና በወቅቱ ብቸኛ ተቀናቃኝ ሊሆነው የእሚችለውን ሻዕብያ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጭ አድርጎ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በፈለገው መልኩ ማሽከርከር የእሚፈልገው ሕወሐት ፤ ቀጥታ የይገባኛል እና የጥቅም ግጭት ውስጥ ገቡ።

ሻዕብያ በስም ተገንጥያለኹ ብሎ በተግባር ከኢትዮጵያ ማሕበረ ኢከነሚ ጋር ተሰፍቶ መኖር ፈለገ ፤ ሕወሐትም ተገንጥያለኹ ከአልኽ በምን አግባብ ነው ከእኛ ማሕበረ ኢከነሚ ጋር እሰፋለው የእምትለው ፤ ወደብ ከሆነ እንደ ማንኛውም ሸቀጥ በብር እንገዛዋለን አለ።

ኹለቱም ድርጅቶች መሠረታዊ ጠባብነታቸው በፈጠረባቸው ግዜያዊ ጥቅመኝነት እና በቀልተኝነት ምክንያት ፤ አንዱ ተገንጥያለኹ ብሎ እያቅራራ በስውር ተዋህዶ ጥቅሙን ሊያስጠብቅ ፤ ሌላውም መገንጠልን ክብር አድርጎ የአየ ይኽንን ጠባብ ፤ ራሱ በቀደደው ቀዳዳ ከማሕበረ ኢከነሚው አስወጥቶ ፤ በመላው ኢትዮጵያ ላይ እስከ እሚችለው ብቸኛ የበላይ ኃይል ለመሆን በመንቀሳቀሳቸው ግንኙነታቸው ይባሱን ሻከረ።

እዚኽ ጋር መታየት የአለበት ፤ የኹለቱም ፕሮግራም ጠባብ ከመሆኑ የተነሳ በግዜያዊ ተራ ጠቅመኝነት እና በቀልተኝነት ተቀስፎ ቢያዝም ፤ በአንጻራዊነት የሕወሐቱ ፕሮግራም ኢትዮጵያዊ ስለሆነ ፤ ለሕወሐት በተለይ በአቶ መለስ አመራር ምክንያት ምንም በእማያሻማ መልኩ የበላይነቱን ሰጠው።

ይኽም በእዚኽ መልኩ የሻከረ ግንኙነት ውሎ አድሮ ፤ አዲስ የኤርትራን ብር መታተም ተከትሎ በኹለቱ ሐገራት ገንዘብ የምንዛሪ መጠን መወሰን ፣ በአሰብ ወደብ አጠቃቀም ፣ በአዋሳኝ ቦታዎች ላይ በአሉ አከባቢዎች ድንበር አከላል ፤ የገቢ እና የወጪ ንግድ አስተዳደር ፣ በድንበር ላይ በአለ የዜጎች እንቅስቃሴ ፣ ወዘተ ፤ ላይ አለመግባባት በመፈጠሩ ጉዳዩ በኹለቱም ወገን ወደ 80 ሺ ሰዎች የጨረሰውን በእኛ አቆጣጠር በ1991 ዓ.ም. የተካኼደውን የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት አስከተለ።

ጦርነቱ በድርድርም ከአለቀ በኋላ ፤ ለጦርነቱ መነሻ በቅርብ ምክንያትነት የቀረበው የድንበሩ ጉዳይ በፍርድ ቤት በተወሰነበት አግባብ እንኳን ሊፈታ ስለ አልቻለ ፤ ኹለቱ ሐገራት እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ በድኃ ኢከነሚያቸው ላይ ፤ ብዙ አሉታዊ ጫና በእሚያሳርፍ መልኩ ትልልቅ ክፍለ ጦር ድንበራቸው ላይ በተጠንቀቅ አቁመው ተፋጠው ቆይተዋል።

በዋናነት በታሪካዊ ምክንያት በቀነጨረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምክንያት ገነው በእሚከተሉት ጠባብ ፖለቲካ ምክንያት ወደ ጎበዝ አለቃነት የተቀየሩት እነ እዚኽ ኹለት የፖለቲካ ድርጅቶች ፤ ከነባራዊ ኹኔታ አንጻር ሲታይ ፤ የመላው ኢትዮጵያ በዴሞክራሲያዊነት ወደ ተፈጥሮዋዊ አቋሙ በመመለሱ ምክንያት ፖለቲካዊ ፋይዳቸው በመላው ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከእሚኖረው ሚና ውጭ በተናጠል የእሚኖረው አቅም ከአልደበዘዘ ፤ ከእነ እዚኽ ድርጅቶች አንዱ ወይንም ኹለቱም እስከ አልከሰሙ ድረስ ፤ ለድርጅታቸውም ሆነ እን ወክለዋለን ለእሚሉት የኤርትራ እና የትግራይ እንዲኹም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጤና መሆን የእሚችሉ አይመስሉም።

ፖለቲካዊ ጠባብነታቸው ወርዶ ወርዶ ፤ በከፍተኛ አመራሮቸው ደረጃ ፤ እኔ ነኝ ምሥራቅ አፍሪካን አረጋግቼ የአለኹት ፣ አንተ አይደለኽም እኔ ነኝ የእሚል ተራ ብሽሽቅ ውስጥ የገቡበት ኹኔታ ነው የአለው።

የመላው ኢትዮጵያ ብሎም የመላው ምሥራቅ አፍሪካ እጣ ፈንታ በራሱ በመላው ከአልሆነም በአብዛኛው ኢትዮጵያ ወይንም መላው የምሥራቅ አፍሪካ ሕዝብ እንጂ ፤ በትግራይ እና በኤርትራ መወሰን የሌለበት እና የእማይቻል መሆኑን ራሱ መገንዘብ እስኪሳናቸው ድረስ ነው ፤ ጠባብነቱ ዓይነ ህሊናቸውን ያሳወረው።

ከእዚኽ በአሻገር ግን የኤርትራው ሻዕብያ በአፍሪካ አሳፋሪ የሆነ አምባገነናዊ ስረዓት በመገንባት እና የኤርትራን ኢከነሚ ከትልቁ የኢትዮጵያ ገበያ በመነጠሉ በአለበት አፍዝዞት ፤ ሲረከባት ከነበረችው ኤርትራ ብዙም የአልራቀች ኤርትራን ይዞ ፤ ለዘመኑ የእማይመጥን መንግሥት መሆኑን እና የረዥም ዘመን የሕዝቡን የዴሞክራሲ ጥረት ፤ በአፍሪካ ዴሞክራሲ አይሰራም በእሚል የማኃይም አባባል አጣጥሎ አለ።

ሕወሐትም በተንጻጻሪነት ፦ በኢትዮጵያ ስፋት ፣ በብዙ ኢትዮጵያዊያን ፣ በውጭ የኢትዮጵያ ወዳጆች እና በዓለም ዓቀፉ ድባብ ምክንያት በተነጻጻሪነት የተሻለ ኢከነሚያዊ እድገት እና ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ቢያስችልም ፤ በእሚከተለው ጠባብ የነገድ ፖለቲካ እና ይኽንንም ተከትሎ በአቋቋመው ብርቅዬ (Indigenous) መኃይመነት የተንጸባረቀበት ነገዳዊ ሕገመንግሥት ምክንያት እንደ ኤርትራዊያን ወገኑ የኢትዮጵያም ሕዝብ ዘመኑን የእሚመጥን የዴሞክራሲያዊ ፍላጎቱ ቢያንስ በ30 ዓመት የዘገየበት ሆኗል።

ይኽም በመሆኑ ምንም እንኳን እነ እዚኽ ድርጅቶች ወደ ፖለቲካ ስልጣን በመምጣታቸው በመላው ኢትዮጵያ (ኢትዮጵያ + ኤርትራ) አንጻራዊ ሰላም ቢኖርም እና ይኽም በተለይ በኢትዮጵያ የተሻለ ኢከነሚያዊ እና ፖለቲካዊ ምሕዳር ለመፍጠር/ለመገንባት ቢያስችልም ፤ እነ እዚኽ ኹለት ጠባብ ድርጅቶች በእሚከተሉት ጠባብ የፖለቲካ ፕሮግራም እና ይኽም ጠባብ ፕሮግራማቸው በአላበሳቸው ግዜያዊ ጥቅመኝነት እና በቀልተኝነት ምክንያት ፤ እነ እዚኽ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ውስጥ በእሚፈጠር አካታች ዴሞክራሲያዊ ስረዓት አማካኝነት ከአልደበዘዙ ፣ ፈርሰው እንደ ገና በአዲስ መልክ በሕዝባዊ እና ስትራቴጅካዊ አስተሳሰብ ከአልተዋቀሩ (reconstruct) ወይንም እንደ ድርጅት ከአልከሰሙ በስተቀር ፤ ለኤርትራ ፣ ለትግራይ እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጻኢ ቋሚ ስጋት ሆነው እና የኢትዮጵያን (ኢትዮጵያ + ኤርትራ) ሕዝብ ዴሞክራሲውያዊ መንግሥት ህልም ቢያንስ በ30 ዓመት የማዘግየት ሥራ እየሠራ ነው የአለው ፤ ግዜያዊ ወታደራዊ ስኬታቸው።

  1. Oxymoron according to WordWeb dictionary “Conjoining contradictory terms (as in 'deafening silence')” ተብሎ ተተርጉሟል ፤ ይኽንን ትርጉም ወደ አማርኛ ስንመልሰው ፦ ኦግዚሞሮን ማለት ‘የእሚያደነቁር ጸጥታ’ ዓይነት የተቃራኒ ቃላት ተዳብሎ ነው ፤ የእሚል ነው እሚሆነው። ↑

  2. ይኽንን አብዮታቸው የመሰረተው መንግሥት የተደቀነበትን የህልውና አደጋ የአሜሪካው ዲፕሎማት ረጅሙ ቴለግራም እና በኋላ ላይ የራሻ ጠባይ መነሻዎች በእሚል ከጻፋቸው ጽሕፎች ላይ በመውሰድ ጂንጎይዝም እና ሐገር በእሚለው ንዑስ ርዕስ ስር በመጽሐፉ ምዕራፍ አንድ ላይ የተቀመጠውን ማብራሪያ መመልከት ይቻላል። ↑

  3. ይኽ “ኢትዮጵያ የብሔሮች እስር ቤት ነች” የእሚለው አባባል ሌኒን እ.አ.አ. በ1914 ዓ.ም.“On the Question of National Policy” በእሚል ርዕስ በጻፈው ሐተታ ላይ “Russia is a prison of Nations” የእሚለው አባባል ለብዙ ሰዎች ግልጽ ሆነላቸው በማለት ከጻፈው ላይ ተቅድቶ የራሻ ስም በኢትዮጵያ ስም የተተካበት ፤ ማርክሲዝምን ሳያላምጡ በእሚውጡ የዘመኑ አብዮተኞች የተዛመተ ፤ በመጀመሪያ በሌኒን ራሻን ለመግለጽ የቀረበ አባባል ነው። ↑

  4. ይኽ ታሪካዊ ዝግመት የእሚለው ፤ ከማርክሲዝም የታሪክ ቁሳዊነት አንጻር ነው ወይንም በእዚኽ ቦታ ላይ ስታሊን በታሪካዊ ዝግመት የመጣ የእሚለውን አባባል በአግባቡ ለመረዳት የማርክስን የታሪክ ቁሳዊነት ትንታኔ ማወቅ ግድ ይላል። ↑

  5. ጸረ ሠራተኛ አብዮት ከሆኑት እንቅስቃሴዎች። ↑

  6. ሙላኽ እና ቤይ የእሚባሉት ፤ በቀድሞው የኦቶማን ተርክ ስረዓት ውስጥ የእሚገኙ የስልጣን እርከን ዓይነቶች ሆነው ፤ በእኛ ሐገር ቄሰገበዝ እና ሐገር ገዢ ከእሚለው ኃሳብ ጋር ተቀራራቢነት ያላቸው ናቸው። ↑

  7. ምዕራፍ አንድ ላይ ሮዛ ሉክሰምበርግ ይኽን የማርክስን እምነት ከዴይሊ ትሪዩብን የአሜሪካ ጋዜጣ ላይ ከወጣ የማርክስ ጽኹፍ ውስዳ ማርክስ በጀርመን ስር ያለው ፖላንድ በጀርመን ስር ይቆይ በራሺያ ውስጥ ያለው ፖላንድ ግን ይገንጠል ማለቱን እንደ አስቀመጠችው አይተናል። ↑

  8. ይኽ ከሙግት ቁሳዊነት እና ከታሪክ ቁሳዊነት አንጻር የተቀመጠ አገላለጽ ነው። ↑

  9. የኦስትሪያ ሕዝባዊ መማክርት ተቋም። ↑

  10. የብሔረሰቦችን ባሕል እንዲንከባከቡ በብሔረሰቡ አባላት የእሚቋቋሙ ፖለቲካዊ ይዘት የሌላቸው የባሕል ከምሺኖች። ↑

  11. ግሪኮች የቀይ ባሕርን “Erythras Thalasses” ወይንም የኤርትራ ባሕር ብለው በቋንቋቸው ስለ እሚጠሩት ፤ ከግሪክ ብዙ ቃላቶቹን በእሚወስደው እንግሊዘኛ የእሚቀርቡ አንዳንድ ድርሳናት የቀይ ባሕር Red Sea (ሬድ ሲ) ከእሚለው ስያሜ በተጨማሪ Eritrean Sea (ኤርትሪያን ሲ) በእሚል ስያሜ ሲጠሩት የእሚስተዋለውም ፤ ይኽንን የግሪኮቹ ስያሜ ተከትሎ ነው። ለእዚኽም ነው ጣሊያኖቹ ምድሪባሕር ወይንም መረብላሽን ፤ ኤርትራ ብለው የሰየሙት። በግሪክ ውስጥም ዛሬም ኤርትራ የእምትባል ከተማ አለች ። ↑

  12. ይኽ ገለጻ ፤ ኤርትራ በሪፈረንደም ከኢትዮጵያ በ1985 ዓ.ም. ከተገነጠለች እና የ1991 ዓ.ም. ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት የአለውን ወቅት የእሚመለከት ነው። ↑

  13. ኮንፌደሬሽኑ በኃይለ ሥላሴ ከመፍረሱ በፊት ወደ ነበረበት ኹኔታ። ↑

  14. የኢሕአፓ አደራጅ ከምቲ ግንባር ቀደም አባል ፣ የመጀመሪያው የድርጅቱ ፖሊት ቢሮ አባል እና የመጀመሪያው የፓርቲው መሪ ፤ ብርሐነመስቀል መንዝ ላይ ከተያዘ (እንደ እርሱ በፈቃዱ እጁን ከሰጠ በኋላ) ለደርግ መርማሪዎች የሰጠው ቃል በእሚል በእሚዘዋወረው ጽኹፍ መሠረት ፤ ኢሕአፓ አንጃ እና ክሊክ በእሚል ከተከፋፈለ ወዲኽ ብርሐነመስቀል ራሱን እንደ ኢሕአፓ እንደ እማይቆጥር እና ኢሕአፓ ተብሎ መጠራት እንደ እማይፈልግ ፤ ፓርቲውም ይኽን ስም ይዞ የቆየው እርሱ ክሊክ የእሚላቸው ተስፋዬ ደበሳይ እና ዘሩ ክህሸን መሰል የፓርቲው አመራሮች በፈጠሩት ችግር ምልዓተ ጉባኤውን ሰብስቦ የፓርቲውን ስም መቀየር የእማይቻል በመሆኑ እንጂ ኢሕአፓ የእሚባል ‘ሕጋዊ’ ፓርቲ ሕልውና በአንጃ እና በክሊኩ ከተከፋፈለ ወዲኽ አብቅቷል። ↑

  15. እንደ ወቅቱ ዘገባ ፤ የትግራይ ተወላጅ የሆነው ተስፋዬ ደበሳዬ ከአንድ ሌላ የኢሕአፓ አመራር ጋር ሳለ ፤ የደርግ የቀይ ሽብብር አሳሽ ቡድን አምባሳደር ቲአቲር ጋር አግኝቶት እጅ ወደ ላይ ሲለው አመንትቶ በመሸሹ አብሮት የነብረው አመራር እዚያው ሲገደል እርሱ እግሩ ላይ ተመትቶ እያነከሰ ወደ ፎቅ ላይ በመውጣት ከፎቁ ላይ ራሱን ከስክሶ እንደ ሞተ ነው የወቅቱ ታሪኮች የእሚነግሩን። ↑