ሕ ገ ክ ራ ሲ

marketing-image

3.2.3. ክፍል 3 ፡ ዘመነ ዛግዌ (ከ 920 ዓ.ም. – 1253 ዓ.ም.)

ሦሥተኛው ክፍል ፥ የአልኹት ፤ የታሪካችን ክፍል ፤ መራ ተክለ ኃይማኖት በተባለው ኢትዮጵያዊ የተጀመረው እና የዛግዌ ስርወ መንግሥት ተብሎ የእሚታወቀው ስርወ መንግሥት በፖለቲካ ስልጣን ላይ የቆየባቸውን ዓመታት ነው ።

የዛግዌ ስርወ መንግሥት በስልጣን ላይ የቆየባቸውን ዓመታት አስመልክቶ ፤ የተለያዩ ሐገራዊ ግምቶች ቢኖሩም ፤ እንደ ሰርጌው ኃብለ ሥላሴ ፤ ተቀባይነት የአለው የእሚመስለው የቆይታ ግዜ ፤ እ.አ.አ. ከ920 ዓ.ም. እስከ 1253 ዓ.ም. የአለው ወቅት ነው ። በእዚኽም መሠረት ፤ ስርወ መንግሥቱ ለ323 ዓመታት ያኽል የቆየ ሲሆን ፤ በእነ እዚኽ ዓመታቶች ውስጥ ወደ 16 የእሚሆኑ ነገሥታት አንግሷል ።

መራ ተክለ ኃይማኖት ስርወ መንግሥቱን ከ በኋላ ፤ የአክሱም ንጉሥ ከነበረው እና አክሱምን ለቆ መናገሻውን ወደ አምኃራ ግዛት ከአዞረው ፤ ከድል ናዖድ ሴት ልጅ ፥ መሶብ ወርቅ የወለዳቸው ልጆቹ ፤ ዙፋኑን ከአባታቸው እና ከእዛም ከወንድሞቻቸው እየወረሱ ፤ ስርወ መንግሥቱን ከ300 ዓመታት ለእሚበልጥ ግዜ አስቀጥለውታል ።

ድል ናዖድ ፥ ስልጣኑን ለማስጠበቅ እና በተለመደው የአክሱማዊያን የስልጣን ውርስ ‘ሕግ’ መሠረት የንጉሡ የወንድ ዘር ሐረግ እንጂ የሴት ልጁ የዘር ሐረግ ፤ ዙፋኑን እንደ አይወርስ በእሚል ፤ የመራ ተክለ ኃይማኖት ባለቤት ከሆነቸው ከመሶብ ወርቅ የእሚወለዱት ልጆች ዙፋኑን እንደ አይወርሱ እስከ መዋጋት የእሚያደርስ የተለያዩ ሙከራዎች ቢያደርግም ፤ ጦርነቱንም ጨምሮ በኹሉም መስክ መራ ተክለ ኃይማኖት የበላይነቱን ይዞ በመገኘቱ ፤ ለእሚቀጥሉት 323 ዓመታት ፤ የመራ ተክለኃይማኖት ወይንም የንጉሥ ድል ናዖድ የሴት ልጁ ፤ ልጆች እና የልጅ ልጆች የዛግዌ ስረወ መንግሥት ነጋሢዎች ሆነው የፖለቲካ ስልጣኑን ይዘው ቆይተዋል ።

የዛግዌ ስርወ መንግሥት ፤ ወደ ፖለቲካ ስልጣን ለመምጣቱ ዋንኛ ምክንያት ፤ የአክሱሙ ወይንም ሰለሞናዊው ስርወ መንግሥት ፤ በክፍል ኹለቱ የታሪካችን ክፍል ላይ እንደ አልነው ፤ በገባበት ፖለቲካዊ መደናበር ወይንም የስረዓት ውድቀት ምክንያት በልማዳዊው መንገድ ስልጣኑን ማስጠበቅ በአለ መቻሉ ነው ።

ምንም እንኳን ፤ በወቅቱ በነበረው ፖለቲካዊ ግንዛቤ ፤ ሰለሞናዊው ስርወ መንግሥት ብቻ ነው በኢትዮጵያ ውስጥ ሕጋዊው የፖለቲካ ስልጣን ባለቤት የእሚለው ትርክት ፤ በቤተ ክርስቲያን እና በሕዝቡ መካከል ሰፊ ተቀባይነት የአለው ቢሆንም እና ይኽም ሕዝባዊ እምነት የአክሱሙን መንግሥት ስዩመ እግዚነት በመቀበል እስከ እነ ችግሩም የእሚሸከም የነበረ ቢሆንም ፤ የአክሱሙ መንግሥት በገባበት ፖለቲካዊ መደናበር ፦ በመናኝነት ፣ በግብታዊነት እና በቀደመው ጨካኝነት መካከል በመዋለሉ ፤ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ ከመወጣት ይልቅ ፤ በመንግሥታዊ ሥራ ፈትነት እና ፍርደ ገምድልነት ተውጦ እና ይኽን ዓይነት ቀውስ ውስጥ ለምን እንደ ገባ እንኳን በአግባቡ ሳይረዳ፦ የችግሩን ምንጭ በሙሉ ውጫዊ በማድረግ ፤ አንድ ግዜ የእግዚአብሔር ቁጣ ነው ሲል ፣ በሌላ ግዜ የክርስትና ጠላቶች የአመጡብን ነው ሲል ፣ አንዳንድ ግዜ ከመካሪዎቹ ሲጣላ ሰንብቶ በስተ መጨረሻ ፤ ከዙፋኑ ባለ መዋሎቹ አንዱ እና ከእዚኽ እየተደናበረ ፍርድ ከእሚያጓድልባቸው መንግሥት ራሳቸውን ለመከላከል ከተነሱት የመንግሥቱ ባለመዋሎች መካከል የሆነው ፤ መራ ተክለ ኃይማኖት ከሰሎሞናዊው ስርወ መንግሥት ራሱን ለመከላከል በጀመረው ጦርነት ፤ የአክሱሙን ሰለሞናዊ ስረወ መንግሥት ከፖለቲካ ስልጣን በማውረድ አዲስ የራሱን ስረወ መንግሥት እንዲ መሠርት አስችሎታል ።

ከወቅቱ ታሪክ ቅኝት የእምናገኘው ምስለታ ፤ የዛግዌ ስርወ መንግሥት ፤ ታስቦበት እና ታቅዶ በውስጣዊ አመፅ ወይንም አዲስ ሕዝባዊ መሠረት የአለው ጎራ ወይንም አንጃ ተፈጥሮ እና የአክሱሙን ሰለሞናዊ ስርወ መንግሥት በኃይል ገፍቶ ፤ የተመሠረተ ስርወ መንግሥት ሰአይሆን ፤ ይልቁንም ፤ መደናበር ውስጥ የገባው ሰለሞናዊ ስርወ መንግሥት ምክንያተ ቢስ ማሳደድ ተከላካይ የአደርገው መራ ተክለ ኃይማኖት ራሱን በስኬታማ መልኩ መከላከል በመቻሉ የመጣ ድንገታዊ ስልጣን ነው የእሚመስለው ።

ይኽም በመኾኑ ፤ የዛግዌ ስርወ መንግሥት ሰአያስበው ስልጣን በመውረሱ ፤ ስለ እዚኽም ፦ ይኽ ነው የእሚባል ሕዝባዊ መሠረት ስለ አልነበረው ስልጣን ላይ ከመጣ በኋላ ይኽን ለህልውናው አስፈላጊ የሆነውን ሕዝባዊ መሠረት ለመፍጠር ፤ በወቅቱ ተቀባይነት በነበረው ፖለቲካዊ ትርክት መሠረት ፤ ልክ እንደ ሰለሞናዊው ስርወ መንግሥት ፤ ስርወ መንግሥቱ አይኹዳዊ መሠረት እንዳ አለው ለማሳየት ፤ ብዙ ታሪኮች ሲጎነጉን ይታይ ነበር ።

ይኽ ጥረቱ ፤ የኢትዮጲያ ሕጋዊ ነጋሢዎች ፤ ንግሥት ሳባ ከእሥራኤሉ ንጉሥ ሰለሞን ከወለደችው ወንድ ልጅ (ቀዳማዊ ምኒሊክ) የእሚወለዱ ወንድ የልጅ ልጆች ናቸው የእሚለው ትርክት ፤ የሐገሪቱ ብሔራዊ ቤተክርስቲያን በሆነችው ፤ በኢትዮጲያ በአለችው ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሰፊ ድጋፍ የነበረው በመሆኑ ፤ የዛግዌ ስረወ መንግሥት ፤ በአጋጣሚ እጁ ላይ የገባውን ስልጣን ሕጋዊ ለማድረግ ፤ ስርወ መንግሥቱ እንደ ሰለሞናዊው ስርወ መንግሥት አይሁዳዊ መሠረት የአለው መሆኑን ለማሳየት እና የሰለሞናዊው ስርወ መንግሥት በኢትዮጲያ ብቸኛ ሕጋዊ ስርወ መንግሥት ነው የእሚለውን ትርክት ለማዳፈን ለምሳሌ ፦ እንደ አንዳንድ የታሪክ ዘገባዎች ፤ ትክክለኛው ነጋሢ የሰለሞኑ ስርወ መንግሥት ነው ፤ የእሚሉ ጽሕፎችን በዘመነ ዛግዌ ማሰራጨት ፤ በግርፋት እና በሞት የእሚያስቀጣ ወንጀል እስከ ማድረግ የእሚደርሱ ፤ የተለያዩ ሙከራዎች ቢያደርግም የነበረበትን የተቀባይነት ችግር ሊቀርፍ አልቻለም።

ንግሥት ሳባ ከአይሁድ ንጉሥ ከንጉሥ ሰለሞን የወለደችው ፤ ቀዳማዊ ምንሊክ የዘር ሐረግ ነው የኢትዮጵያ ሕጋዊ ነጋሢ የእሚለው ክብረ ነገሥትን ፤ የሰለሞኑ ስርወ መንግሥት ዳግም ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ከአረብኛ ቋንቋ ወደ ግዕዝ የመለሰው ይስኃቅ ፤ ምንም እንኳን አቡላዚዝ እና አቡልፋራጅ የእሚባሉ ኹለት ሰዎች ፤ ክብረ ነገሥት ከነበረበት የኮፕት ቋንቋ ወደ አረብኛ የተረጎሙት በ1216 ዓ.ም. ማለትም ቅዱስ ላሊበላ በነገሠበት ዓመት ቢሆንም ወደ ግዕዝ ሳይተረጉሙት የቀሩት የዛግዌን መንግሥት ፍራቻ ይሆናል ይላል ፦

“እኔም - አቡልፋራጅ እና አቡልላዚዝ ለምን አልተረጎሙትም ፤ በእሚለው በእዚኽ ጉዳይ ላይ ሳሰላስል ፤ ይኽን አልኹ ፤ መጽሐፉ የወጣው በዘመነ ዛግዌ በመሆኑ አልተረጎሙትም ፤ ምክንያቱም ፦ እሥራኤላዊ ሳይሆኑ የእሚነግሱ ህገወጦች ናቸው ስለ እሚል ።”

“And when I had pondered this – Why did not Abalez and Abalfarog who edited (or, copied) the book translate it? I said this; It went out in the days of Zagua, and they did not translate it because this book says: Those who reign not being Israelites are transgressors of the Law. [79]“

ይኽ የይስኃቅ ዘገባ ፤ የዛግዌ መንግሥት ፕሮፖጋንዳውን ለመቆጣጠር ምን ያኽል ርቀት እንደ ኼደ ብቻ ሰአይኾን የእሚያሳየን ፤ ምን አልባትም በይበልጥ ፤ የዛግዌው ስርወ መንግሥት የመንግሥቱን ተቀባይነት የእሚያዳክሙ ትርክቶችን ለማፈን የእሚፈፅማቸው አንዳንድ ተግባራት ፤ በሕብረተሰቡ ዘንድ ይበልጡኑ የስልጣን ቀማኛ እያስመሰለው ሳይኼድ እንደ አልቀረም የእሚያሳየን ይመስላል።

ለእዚኽም ደግሞ ዋነኛ ምክንያቱ የእሚሆነው ፤ ቤተክርስቲያን የንግሥና ቅባት ቀቢ በኾነችበት በእዚያኽ ዘመን ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ ስነ መለኮታዊ አስተምህሮ ፤ የኢትዮጲያ ሕጋዊ ነጋሢ ፤ ከእሥራኤሉ ንጉሥ ሰለሞን እና ከኢትዮጲያዊቷ ከንግሥት ሳባ የእሚወለዱት የወንድ ልጆች ናቸው የእሚል በመሆኑ ፤ የዛግዌ ስርወ መንግሥት ይዞ የእሚመጣው ማንኛውም ዓይነት መንግሥታዊ ትርክት የእሚጋጨው ከሌላ ግዜያዊ እና ውስን ተቋም ጋር ብቻ ሰአይሆን ፤ ከትልቋ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋርም መሆኑ ፤ ግጭቱ ከፖለቲካዊ ይዘቱ በአሻገር ፤ በኃይማኖታዊ ደርዙ እንደ ኑፋቄ ወይንም የስህተት ትምህርት የእሚታይ እና ይኽም መንግሥትን ከኃይማኖተኛው እና ከኃይማኖት አመራሩ ጋር የእሚያጋጨው ስለ እሚሆን ነው።

ይኽንንም እውነታ የዛግዌ መንግሥት ገብቶበት በነበረው ጳጳስ የማግኘት ችግር በእሚገባ ይስተዋላል። ምንም እንኳን ወደ አክሱም ማክተሚያ አከባቢ ፤ በቪክቶር እና ምናሴ በተፈጸመው ማጭበርበር ምክንያት የኢትዮጲያዋ ቤተክርስቲያን ከአሌክሳንደሪያ ጳጳስ የማግኘት ችግር የገጠማት ቢሆንም ፤ ይኽ ጳጳስ የማግኘየት ችግር ፤ የዛግዌው ስርው መንግሥት በሐገር ውስጥ በአለችው ቤተ ክርስቲያን ከእላይ በአልነው መልኩ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ፤ ይበልጡኑ ተባብሶ ፤ የዛግዌ መንግሥት በዘመኑ ኹሉ ለገባበት አጣብቂኝ ዋነኛ ምክንያት ሆኖ ነበር።

የዛግዌ መንግሥት ወደ ስልጣን እንደ መጣ አከባቢ ከግብፅ መንግሥት ጋር ፤ መልካም የእሚባል ግንኙነት ቢኖረውም ፤ ስርወ መንግሥቱ በኢትዮጵያዋ ቤተክርስቲያን ዘንድ ተቀባይነት የአልነበረው መሆኑ ፤ ቤተክርስቲያን አንጋሽ እና አፍራሽ በሆነችበት በእዚያኽ ዘመን ፤ ለኢትዮጲያ ጳጳስ መላክ ‘ሕገ ወጥ’ ለተባለው ለእዚኽ ስርወ መንግሥት እውቅና እንደ መስጠት የእሚቆጠር እና መጪውንም ጳጳስ ፈታኝ ኹኔታ ውስጥ የእሚከት በመሆኑ ፤ የዛግዌ ስርወ መንግሥት በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ፤ አዲስ ተተኪ ጳጳስ ከአሌክሳንደሪያ ማግኘት ቋሚ ፈተናው ነበር።

ይኽ ክስተት በተራው ፤ ጳጳስ የአልተሾመልን ፤ ሕገ ወጥ ኃይል በጉልበት ስልጣን ስለ ያዘ ነው የእሚለውን የሕዝብን ጉጉምታ አብሶት እና የዛግዌን መንግሥት አስጨንቆ ፤ ከልማዳዊው የአሌክሳንደሪያ መንበር ውጭ ከሶሪያ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳስ ለማስመጣት ከመፈለግ አንስቶ ኢትዮጵያዊ ጳጳስ ከሐገር ውስጥ ለመሾም እስከ መፈለግ ድረስ ፤ የእሚደርስ የተለያየ ጳጳስ የማግኛ መንገዶችን እንዲያፈላልግ አስገድዶታል ።

ይኽ የዛግዌ ስርወ መንግሥት የአለበት የተቀባይነት ማጣት ክፍተት ወይንም ተጋላጨነት (Vulnerability) ደግሞ ፤ በሐገር ውስጥ እረፍት ከነሳው የሕዝባዊ ማጉተምተም ጫና በአሻገር ፤ ከጵጵስና ጋር የተያያዙ ውጥረትን የእሚያባብሱ ኹኔታዎች ውስጥ እንዲገባ አድርገውታል ፦

  • እንደ ምናሴ እና ቪክቶር ዓይነት ወስላቶች መጫወቻ እንዲሆን
  • ለግብፅ የእስልምና መንግሥት ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንዲጋለጥ
  • ኢትዮጵያ ውስጥ እስልምናን ለማስፋፋት እና መስኪድ ለመሥራት የእሚፈልጉ የሙስሊም ነጋዴዎች ጫና እንዲያሳርፉበት መንገድ በመክፈት
  • ሸዋ ለከተተው ሰለመናዊ ስርወ መንግሥት የፕሮፖጋንዳ ጫና እንዲጋለጥ

አድርጎታል ።

ወደ አክሱም ማብቂያ ላይ ፤ የሶርያ አታላይ ‘መነኮሳቱ’ ምናሴ እና ቪክቶር ፤ በአክሱሙ መንግሥት ላይ የአደረጉት ማጭበርበር ፤ የኢትዮጵያ መኳንንት እና በአጠቃላይ መንግሥትም ፤ በጳጳሱ ላይ የአላቸውን ከፍተኛ ተደጋፊነት ለዓለም ሕዝብ ኹሉ ግልፅ አድርጎ ስለ አሳየ ፤ ከአጭበርባሪው ጀምሮ እስከ ፖለቲከኛው ድረስ ፤ የአሌክሳንደሪያዋ መንበር ፤ በኢትዮጵያ የነበራትን ብቸኛ ጳጳስ የመሾምን ስልጣን ለራሱ ፓለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ግብ እንዲፈልግ በማድረጉ ፤ የአሌክሳንዴሪያውን ጳጳስ የመሾም ስልጣን ፓለቲካዊ ፋይዳው ከፍ የአደረገ ክስተት ነበር ። ይኽም ፤ ኹኔታውን በተቀባይነት እጦት ለእሚቸገረው የዛግዌ ስርወ መንግሥት ተጨማሪ የፈተና ምንጭ አድርጎታል ።

በእዚኽም ፤ ዛግዌ ወደ ስልጣን ሲመጣ የነበሩት ጳጳስ ከሞቱ በኋላ ፤ ኢትዮጵያ ከአሌክሳንደሪያ ጳጳስ ሳታገኝ ለረዥም ግዜ በመቆየቷ የተፈጠረውን ክፍተት ተጠቅሞ ራሱን ጳጳስ ለማድረግ በመሞከር ፤ ከጳጳስ ጋር በተገናኘ ለዛግዌው ስርወ መንግሥት የመጀመሪያው ፈተና የሆነው ፤ ኩሪል የእሚባለው የግብፅ መነኩሴ ነው ።

ኩሪል ፥ በምናሴ እና በቪክቶር ዱካ ፤ ከአሌክሳንደሪያው መንበር ነው በሹመት የተላኩት ብሎ ፤ ሐሰተኛ የሹመት ደብዳቤ አቅርቦ ነው ፤ የጵጵስናውን ቦታ የያዘው ።

ኩሪል ፤ ጵጵስናውን በሐሰተኛ ደብዳቤው አማካኝነት ከያዘ በኋላ ፤ የቀደሞዎቹ ምናሴ እና ቪክቶርን ዘዴ በማሻሻል ፤ ብዙ መስኪድ እንዲሰራ አደርጋለኹ እና የአሌክሳንደሪያውን ጳጳስ አስገድዳችኹ ፤ ማጭበርበሬ ሳይደረስበት በፊት ፤ በሰነድ ማጭበርበር የያዝኩት ጵጵስናዬ እንዲ ጸና አድርጉ በእሚል ከግብጽ ካሊፎች ጋር በስውር እየተደራደረ ቆየ ።

ይኽንም ተከትሎ ፤ የወቅቱ የግብፅ ካሊፍ ፤ የአሌክሳንደሪያዋ ቤተክርስቲያን መሪዎች ለኩሪል ጵጵስናውን እንዲ ያፀኑለት ግድ ብሏቸው እምቢ በማለታቸው ፤ እስከ መታሰር የእሚደርስ ጫና እየ አደረሰባቸው እያለ ፤ ኩሪል ፥ በጉዳዩ መዘግየት ተስፋ በመቁረጥ ይመስላል ፤ በመሐል ወርቅ ዘርፎ በአዱሊስ በኩል ሊጠፋ ሲል ስለ ተያዘ ፤ አጨበርባሪ እና ዘራፊ ተብሎ ለግብፅ መንግሥት ተሰጠ ።

ቤተክርስቲያኒቱም ከአጭበርባሪ እና የአሌክሳንደሪያዋ ቤተክርስቲያን መሪዎችም ፤ ሐሰተኛ ጳጳስ ሹመት አናፀድቅም በማለታቸው እየደረሰባቸው ከነበረው ኢፍትኃዊ እንግልት ዳኑ ሲላቸው ፤ አጭበርባሪው እና ዘራፊው ኩሪል ተይዞ ሲሰጠው ፤ የግብፁ ካሊፍ በሞት ቀጣው ።

ይኽ ኹኔታ ፤ የኢትዮጲያዋን ቤተክርስቲያን እንዲሁም የአሌክሳንደሪያዋን መንበር ፤ ከዛግዌ ስርወ መንግሥት ጋር ሆድ እና ጀርባ እንደ እሚያደርጋቸው መገመት ይቻላል።

የኩሪል ታሪክ በእዚኽ ከአበቃ በኋላ ደግሞ ፤ የግብፅን መንግሥት የአሌክሳንደሪያዋን መንበር ፤ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ጳጳስ የመሾም የአላ፟ትን ብቸኛ ስልጣን ለፖለቲካዊ ግቡ ለመጠቀም የአለ፟ውን ፍላጎት የተረዱ የተለያዩ ምንደኞች ፤ ቀጥታ የግብፅ መሪ ጋር በመኼድ ፤ የአሌክሳንደሯ ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያ ጳጳስ አድርጋ እንድ እትሾማቸው ቢያዝላቸው ፤ እነርሱም በምላሹ ለገዢው ጠቀም ያለ ስጦታ የእሚልኩ እና የመስጊድ ግንባታ የእሚያስተባብሩ መሆኑን ቃል እየገቡ ፤ በአሌክሳንደሪያው ቤተክርስቲያን ላይ ከግብፅ ሙስሊም መሪዎቹ ብዙ ጫና በቀጣይነት እንዲደርስበት የእሚያደርጉበት ኹኔታ ተፈጠረ ።

ከእዚኽም በተጨምሪ ፤ የወቅቱ የግብፅ የሙስሊም መንግሥት የአሌክሳንደሪያውን መንበር ፤ በኢትዮጲያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያላትን ብቸኛ ጳጳስ የመሾም ስልጣን ለራሱ ፖለቲካዊ ጥቅም ለማዋል በማሰብ ኺደቱን ለመቆጣጠር በእሚያደርገው ጥረት የአሌክሳንደሪያው ቤተ ክርስቲያን ላይ ከአደረሰው ጫና በአሻገር ፤ በተለያዩ አማካሪዎች እየተመራ ፤ የዛግዌ ስርወ መንግሥት ይኽንን ወይንም ያንን ከአላደረገ ፤ በግብጽ አሌክሳንደሪያ በእምትገኘው መንበር ላይ ስደት እንደ እሚያስነሳ በማስፈራራት ፤ በእጅ አዙር የኢትዮጵያን መንፈሳዊ ህይወት በእዛኽም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የተለያየ ሙከራ እንዲያደርግ አድርጎታል ።

ለምሳሌ ፦ ወደ ኢትዮጵያ የእሚመጡ የተለያዩ ሙስሊም ነጋዴዎች ፤ በኃማኖታችን ምክንያት በደል ደረሰብን ፣ መስኪድ እንደ አንሰራ ተከለከልን ፣ ወዘተ ፤ ይኽ ሲደረግብን በእዚኽ በአሌክሳንደሪያ የአለው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የበላይ ጠባቂ መንበር (መንበረ ማርቆስ) ፤ በእምነታችን እንደ አንጠቃ አይከላከልልንም በማለት ፤ የአሌክሳንደሪያዎቹን ጳጳሶች ለግብፅ መንግሥት የእሚከሱበት ኹኔታ በመኖሩ ፤ የግብፅ መንግሥትም ይህን ኹኔታ ፤ በአሌክሳንደርያ ክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ ጫና በማድረግ ስለ ነበር የእሚመልሰው ፤ ይኽም በተዘዋዋሪ መንገድ የአሌክሳንደሪያው መንበር የዛግዌን ስርወ መንግሥት ፤ በሐገር ውስጥ በአለችው ቤተክርስቲያን ብቻ ሰአይሆን በአሌክሳንደሪያ በአለችው ቤተ ክርስቲያንም የእማይፈለግ በማድረግ ፤ የበለጠ አጣብቂኝ ውስጥ እንዲ ወድቅ ስለ አደረገው ፤ ከወቅቱ የኢትዮጵያዋ ቤተክርስቲያን ታሪካዊ ቁርኝት በአፈነገጠ መልኩ ፤ የዛግዌ ስረወ መንግሥት ጳጳስ ከሶሪያ አብያተ ክርስቲያናት ለማስመጣት ያልተሳካ ሙከራ እስከ ማድረግ አስጨንቀውታል ።

የግብፅ መንግሥት በእዚኽ መልኩ በአሌክሳንድሪያዋ መንበር ላይ ያደርግ የነበረው ጫና በኢትዮጵያ ውስጥ ፤ የፈለገውን ውጤት አል አመጣ ሲለው እስከ እነ ጭራሹም ቀጥታ ከዛግዌ ስርወ መንግሥት ጋር የዲፕሎማሲ ሰጣ ገባ ውስጥ ወደ መግባት ውስጥ የመጣበትም ግዜ ነበር ። አንድ የግብፅን ታሪክ ጸሐፊ ጠቅሶ ፤ ሰርጌው ሐብለሥላሤ ፤ በአንድ ወቅት በአንዱ የግብፅ ካሊፍ እና በዛግዌው ነጋሢ መካከል የተደረገን የኃይለ ቃል ልውውጥ እንደ እዚኽ አስቀምጧል ፦

“አንድ ታማኝ እና መልካም ሰው እንደነገረኝ ፤ ክቡርነቱ አሚር አልጉዩስ ለአብሲንያ (ለሐበሻው) ንጉሥ በደብዳቤ እንዲኽ አለው ፡ ‘ይኽን እና ይኽን ካል አደረግህ በግብፅ (ምስር) ምድር የእሚገኙትን ቤተክርስቲያኖች አወድማቸዋለሁ’ ንጉሡም በምላሹ እንዲኽ ብሎ ጻፈለት ፡ ‘አንዲቷን እንኳን የቤተክርስቲያን ድንጋይ ብትነካ ፤ እኔ ደግሞ የመካውን ድንጋይ እና ሸክላ ኹሉ ተሸክሜ አምጥቼ እሰጥኃለሁ ፤ ከእዚኽ ከአመጣሁት የመካ ክምር አንድ ድንጋይ ቢጎድል ፤ እርሱን የእሚመዝን ወርቅ እሰጥኃለሁ ።”

“A certain good, trustworthy (person) related to me that the illustrious Amir Al-Guyus said in his letter to the king of Abyssinia (al-Habasah): ‘ If thou dost not do thus and thus, I shall demolish the churches which (are) in the land of Egypt(Misr),’ He (the king) wrote to him a reply, saying:’If you demolish a single stone of the churches, I shall carry to thee of all the bricks and stones of Mecca(Makkah), and I shall deliver them all to thee, and if a single brick of it (Mecca) is missing, I shall send to thee its weight in gold. [96]“

በእዚኽ መልኩ ፤ ከውስጥም ከውጭም በነበረበት ውጥረት ፤ የተያዘው የዛግዌ ስረወ መንግሥት ፤ ከአክሱም መንግሥት በተሻለ ኹኔታ ፤ አገራዊ ጳጳሶች ለማፍራት የነበረው መልካም ሙከራም ሳንካው ስለበዛ ያሰበውን ለውጥ ለማሳካት ሳይችል እንዲቀር አድርጎታል ።

በብዙ ትግል አንድ ጳጳስ ከአገኘ በኋላ ፤ ያ ጳጳስ ሲያልፍ ፥ ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ይገባል ። በመሐል ፤ የአክሱሙም ስርወ መንግሥት ፤ አዲስ ጳጳስ ከዛግዌ መንግሥት እውቅና ውጭ ከአሌክሳንደሪያ ለማስመጣት እና ይኽን ‘ሕገወጥ’ የእሚለውን የዛግዌ ስርወ መንግሥት ለማስወገዝ እና ከስልጣን ለማስወገድ ይጥር ስለ ነበር ፤ ይኽም ኹኔታ ሌላ ተጨማሪ የውጥረት ምንጭ ሆኖበት ነበር ።

ከተለመደው ፤ የኢትዮጵያ የስዩመ እግዚ ትርክት ውጭ የፖለቲካ ስልጣን የያዘው የዛግዌ ስርወ መንግሥት ፤ በእዚኽ በጳጳስ ሹመት ብቻ የገጠመው ለብዙ ዓመታት የቆየ ፈተና ፤ ስርወ መንግሥቱ በምን ዓይነት ፈታኝ ፖለቲካዊ ምሕዳር ውስጥ እንዳ ከተተው ፤ በወቅቱ ታሪክ በእሚገባ የእሚታይ ነው ።

ይኽም ኹኔታ ፤ የዛግዌ መንግሥት ፥ በሐገር ውስጥ ፦ ከቤተክርስቲያን ፣ ሕጋዊ የስልጣን ባለቤት እኔ ነኝ ከእሚለው ከአክሱም ስርወ መንግሥት ፣ ከአታላይ ጳጳሳት ፣ ግብፅን ተጠቅመው ጫና መፍጠር ይፈልጉ ከነበሩ የሙስሊም ማሕበረሰባት ፤ በውጭ የግብፅ መንግሥት እና በወቅቱ ተፋፍሞ ከነበረው የመስቀሉ ጦርነት በእሚያሳድርበት ጫናዎች ውስጥ ሆኖ ፤ ስልጣኑን በወታደራዊ ኃይል ከማስከበር ውጭ ስኬታማ ፖለቲካዊ ሥራ መሥራት እንዳይችል ስለ አደረገው ፤ የጥረቱን ያኽል ውጤት የራቀው የዛግዌ ስርወ መንግሥት ወደ ዘመኑ መጠናቀቂያ አከባቢ ፤ ተስፋ መቁረጥ እና መሰላቸት ውስጥ እየገባ የውስጥ መከፋፈል እየበረታበት መጥቷል ።

ምንም እንኳን ፤ ከውስጥም ከውጭም በደረሰበት ግፊት ምክንያት ፤ ስልጣኑን ለማፅናት ሲል ፤ ሐገር በቀል የሆነ የእውቀት እና የኃብት መዓከል በመገንባት ፤ አልቀበልኽ ከአለው ከነባራዊው ሐገራዊ እና ዓለም ዓቀፋዊ ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ሰንሰለት የተነጠለ ፤ ራስን በራስ የመቻል የአልተሳካ ሙከራው ፤ ዋነኛው የዛግዌ መንግሥት እሴት እና መገለጫው ቢሆንም ፤ ምን አልባትም ፤ እጅግ የበዛ ግነት ወይንም የሌሎችን ሰዎች ድካም ማቃለል ከአልሆነ ፤ የዛግዌ ስርወ መንግሥት የነበረበት ይኽ የመነጠል ኹኔታ አል አሥራ ስለ አለው ፤ ስርወ መንግሥቱን ከመሠረተው መራ ተክለኃይማኖት በመቀጠል ውጤታማ ሥራ መሥራት የቻለው ንጉሥ ላሊበላ ብቻ በመሆኑ ፤ ስርወ መንግሥቱ የንጉሥ ላሊበላ መንግሥት ነበር ቢባል ትክክል ይመስላል ።

ንጉሥ ላሊበላ ወደ ስልጣን ሲመጣ ፤ በእዚኽ ኹኔታ መቆየቱ ለማንም እንደ እማይበጅ ከመረዳት በእሚመስል አካኼድ ፤ ከስልጣን ላይ ዘመዶቹን ኹሉ አስወግዶ ፤ ወደ ስልጣን እንዲመጣ ያገዙትን ሌሎች የላሊበላ አከባቢ ሰዎች መሾም በመቻሉ ፤ ከእርሱ ቀደም ከነበሩት የዛግዌ ነገሥታት የተለየ የፀና መንግሥት እንዲኖረው እና ውጤታማ ሥራ መሥራት የእሚያስችለው ኹኔታ አግኝቷል ።

ላሊበላ እ.አ.አ. ከ1133 እስከ 1173 ዓ.ም. እንደ ነገሠ የእሚነገርለት እና በነበረው ተግባራዊ አስተሳሰብ እና ትህትና ፤ የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን ራሷ እንደ ቅዱሳን የሰየመችው ፤ በመላው የኢትዮጲያ ታሪክ ውስጥ ከነበሩ እና ተራማጅ ተብለው ከእሚፈረጁ ነጋሢዎች አንዱ የነበረ አጼ ነበር።

የዛግዌውን ስርወ መንግሥት ስዩመ እግዚነት የእማትቀበለው ቤተክርስቲያን ፤ ላሊበላን ከስረዓቱ ለይታ በግለሰብ ደረጃ ስለ ነበረው መልካምነት መመስከሯ ፤ ቤተክርስቲያኒቱን የእሚያስከብራት ሲሆን ፤ ይህንን ግርዶሽ አልፎ ለእዚኽ በመብቃቱ ደግሞ የላሊበላን ትልቅነት ያሳያል ።

የላሊበላን ተራማጅነት ከእሚያሳዩት ነገሮች አንዱ ፤ ከቤተ ዘመድ አስተሳሰብ ወጥቶ ፤ ሐገራዊ እና ዓለም ዓቀፋዊ ድጋፍ የአለው መንግሥት ለመሆን ያሳየው ፖለቲካዊ ንቃት ነው ።

ኹለተኛው ፤ የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እንዲያስገነባ ያነሳሳው ፤ ብዙ ሰዎች ኢየሩሳሌምን እናያለን ብለው ጉዞ እየወጡ በእየመንገዱ ፤ ለርኃብ ፣ ለጥም እና ለሽፍታ እየተጋለጡ ይሞቱ ስለ ነበር ፤ ይኽን ለማስቀረት ኢየሩሳሌምን በኢትዮጵያ ለመገንባት ማሰቡ ነው ።

ከእዚኽም ተነስቶ ፤ በላሊበላ የተገነቡት አሥራ አንዱም የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ፤ ኢየሩሳሌምን እና የክርስቶስን ህማማት የእሚዘክሩ የመጽሕፍ ቅዱስን ታሪኮችን ታሳቢ ያደረጉ ናችው ፦

“የቤተክርስቲያናቱ ግንባታ ፤ የላሊበላ ወደ ኢየሩሳሌም የእሚደረግ የምፃተኞች ጉዞ ለመግታት የመፈለግ ጥረት አካል ነው ። ብዙ ክርስቲያኖች ከኢትዮጵያ ኢየሩሳሌም ለመኼድ ይነሳሉ ፤ እግባቸው የእሚደርሱት ግን ጥቂቶች ናቸው ። የሱዳን እና የግብፅን በርኃ ወይንም ወደ ቅድስቲቱ ምድር ለመሻገር በሙስሊም ሐገራት ውስጥ ሲያልፉ የእሚገጥማቸው አደጋ ላሊበላ የእማያውቀው ነገር አልነበረም ። ስለ እዚኽ ፦ ሮኃ የኢየሩሳሌም ምትክ ፤ ለምፃተኞቹ የደህንነት አምባ እንድትሆን ነው የታሰበችው ።”

“The construction of these churches represented an attempt by Lalibela to discourage piligrims from journeying to Jerusalem. Many Christians left Ethiopia but few reached their objective. The dangers they encountered in the deserts of the Sudan and Egypt or in passing through Muslim countries on their way to Holy Land were not unknown to Lalibela. Roha then was to be a substitute for Jerusalem, a place of safety for piligrims. [96]“

ምናልባትም ፤ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በኢትዮጵያ ታሪክ ፤ ከኃማኖታዊ ፋይዳቸው በአሻገር ፤ የሕዝብን ደህንነት እና ጥቅም ወይንም ሕዝብን ሰብዓዊ ጥቅም ታሳቢ የአደረገ የመጀመሪያው ትልቁ የመንግሥት የግንባታ ፕሮጀክት ነበር ማለት ይቻላል ።

ከዛግዌ በፊት በአክሱም የነበረው ሰለሞናዊ ስርወ መንግሥት ፤ ሕግ እና ስረዓትን በማስከበር እና ሕዝብን በማሰልጠን ትልቅ ስፍራ የነበረውን የክርስትና እምነት ከባሕላዊ እምነት ተከታዮች ኢምክንያታዊ ጥቃት በመታደግ ፤ በጠቅላላው ለሕዝብ ልማት ቅድመ ኹኔታ የሆነውን ማሕበራዊ መረጋጋት እና የእውቀት ስርጭት በማስቻሉ ፤ መተኪያ የሌለው ሕዝባዊ ሥራ የሰራ ቢሆንም ፤ በላሊበላ ታቅደው እንደ ተገነቡት ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ፤ ከኃይማኖታዊ ፋይዳቸው በአሻገር የሕዝብን ደህንነት ታሳቢ የአደረጉ የግንባታ ሥራዎች ሲሰራ አልታየም።

ይኽም የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ግንባታ ፤ ከግንባታውም የግንባታዊ መነሻ ኃሳብ ፤ ምንም እንኳን በአንድ ጥረት ብቻ ቢወሰንም ፤ በኢትዮጲያ ከእዚኽ በፊት በነበሩት የመንግሥት ፋይዳዎች ላይ አንድ እሴት የጨመረ ነበር።

በእርግጥም ላሊበላ የትልቅ አዕምሮ ባለቤት (Intellectual) እና ባለ ራዕይ መሪ የመሆኑ ጉዳይ ፤ ይኽንን ውብ እና ታሪካዊ ሕንጻ ለማነጽ ከተነሳበት ቅዱስ ሕዛባዊ ኃሳቡም በአሻገር ፥ በጠቅላላው በላሊበላ ስብዕና ውስጥ ይታዩ ከነበሩት ፦ የምሕንድስና እውቀት ፣ የግል ስነ ምግባር ፣ ጭምትነት እና ትሕትና ፣ ዘመኑ በእሚፈውቅደው ልክ በእውቀት የታጠቀ መሆን ፣ ወዘተ ፤ በደንብ የእሚታዩ ናቸው ።

ሰርጌው ኃብለ ሥላሴ ፤ ከገድለ ላሊበላ ላይ ወስዶ እንደ አስቀመጠልን ፤ ቅዱስ ላሊበላ ምንም እንኳን ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጲያ ቢሆንም ፤ በአንድ ወቅት በቤተ መንግሥት ትልቅ ግብዣ አድርጎ እንደ ጨረሰ ፤ መደበኛ ልብሱን ቀይሮ ወደ ልማዳዊው የእደ ጥበብ ሞያው እንደ ኼደ ይነገራል ብሎ ዘግቦልናል ፦

“ … አንድ ቀን ትልቅ ምሳ የማብላት ድግስ ካካኼደ በኋላ ፤ የንግሥ ልብሱን አውልቆ መደበኛ ልብስ በመልበስ ወደ ሥራ ኼደ ።”

“...one day after giving a big luncheon, he changed from his royal vestments and, putting on a simple clothes went to work [96]“

ይኽም የላሊበላ ልማዳዊ በኃሪ እንጂ የአንድ ቀን ተግባር ብቻ አይመስልም ከወቅቱ ታሪካዊ ዘገባዎች አንጻር ሲታይ።

እንደ ወቅቱ ታሪካዊ ዘገባዎች ላሊበላ የግል ገቢውን ከመንግሥት በጀት ሰአይሆን ፤ ከመንግሥታዊ ሥራው በእሚተርፈው ግዜ ፤ መልኩን ቀይሮ ገበሬ መስሎ ፤ በገበያ የእጁ ሥራ የሆኑትን ቅርፃ ቅርፆች በመሸጥ ነበር የእሚያገኘው ። የእደ ጥበብ ሞያተኛም ስለ ሆነ ይሆናል ፤ ይህን መሰል ታሪካዊ ፣ ትልቅ አና ውብ ፤ ውቅር የአብያተ ክርስቲያናት መንደር አቅዶ በመገንባት ድንቅ ታሪክ ትቶ ማለፍ የቻለው ፤ ይኽ የቤተ ክርስቲያናት መንደር በእርሱ ታቅዶ ከተተገበረ።

ይኽ ጭምትነቱ ፤ በዘመኑ የነበረ ገጣሚ ይህን ፤ ሰርጌው ኃብለ ሥላሴ ፥ ከግዕዝ ወደ እንግሊዘኛ መልሶ ያስቀመጠውን ፤ የንጉሥ ላሊበላን ትህትና እና ጭምትነት የእሚገልፅ ፤ ቅኔ እንዲ ቀኝ አድርጎታል ። እኔም እንግሊዘኛውን ወደ አማርኛ መልሼ ፤ ከግዕዙ ጋር አስቀምጨዋለሁ ፦

“እንደ ችግረኛ እና እንደ ድኃ ይሆን ዘንድ ንጉሡ ይመለሳላ ፥ ሰንጋውን ካረደ እና ወይኑን ካፈሰስ በኋላ ።”

“ካልዓንስ ውስተ ተፈግዖ በጥብሐ ላህም ወበስቴ ሜስ ወንጉሥ ምስለ ነዳያን ከመ ፅኑስ [96]”

ይኽም ፥ የመንግሥትን ግብር እና ገቢ በሙሉ ለሕዝብ አገልግሎት አውሎ ፤ ከሞያው በእሚያገኘው ገቢ መኖሩ ፤ ላሊበላን በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የቅዱሳንነት ማዕረግ ከተሰጣቸው እና ታስበው የእሚውሉበት ቀን ከተሰየመላቸው ሰዎች አንዱ እንዲሆን አድርጎታል ፦

“በቤተክርስቲያን ከቅዱሳን መካከል እንዲ ሰየም ምክንያት የሆነው ነገር ፤ በላሊበላ ገድል የመጨረሻ ገፆች ላይ ተጽፏል ። በመንግሥት ግምጃ ቤት የእሚገኘውን ኃብት አንድም ቀን ለራሱ ተጠቅሞ አያውቅም እናም ከሕዝብ የእሚሰበሰበው ግብር ኹሉ ለሕዝብ ሥራ አገልግሎት ነበር የእሚውለው ። እንዲያውም ፤ የእጅ ጥበብ ሥራውን ፤ ራሱን እንደ ገበሬ ለውጦ በመሸጥ ከእሚያገኘው ገቢ መኖር ይመርጥ ነበር ።”

“The reason for his canonization is alluded to in the last pages of his Gedle. He never used the state treasury for his private gain and taxes collected from the people were used exclusively for public works, Indeed he prefered to live on money he earned handwork which he made and sold, disguising himself as a peasant. [96]“

ከላሊበላ በኋላ ፤ የዛግዌ ስርወ መንግሥት ኹለት ነገሥታት ብቻ ያነገሠ ሲሆን ፤ ከእዛያኽ በኋላ በዩኩኖ አምላክ አማካኝነት ፤ የአክሱሙ ስርወ መንግሥት እንደገና ስልጣን ላይ መጥቷል ማለት ነው ። በእዚኽም ፥ የሰለሞናዊው ስርወ መንግሥት ለ323 ዓመታት በዛግዌ ስርወ መንግሥት ከፖለቲካ ስልጣን ተወግዶ ከቆየ በኋላ ፤ ለኹለተኛ ግዜ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ስልጣን ሲጨብጥ ፤ አራተኛው የአልኩት የኢትዮጵያ የታሪክ ክፍል ተጀመረ ማለት ነው ።

ንጉሥ ላሊበላ ሲቀር ፤ የዛግዌ ስርወ መንግሥት ፥ ለ323 ዓመታት የቆየ ባለ አደራ መንግሥት ነበር ማለት እንችላለን ። በዘመናዊ ቋንቋ ቴክኖክራት የእሚባል ዓይነት መንግሥት ቢሆንም እና በአክሱሙ ስርወ መንግሥት የተዘነጉ ሥራዎችን ለመሥራት ፍላጎቱ እና ጥረቱ የነበረውም ቢሆንም ፤ በሐገር ውስጥ ተቀባይነት በማጣቱ እና ከውጭም ትርጉም የአለው እገዛ ማግኘት በአለመቻሉ ፤ የፍላጎቱን ያኽል ሳይከውን ነው ዘመኑ የአለቀው ።

ላሊበላ ከነገሠ በኋላ ፤ ዘመዶቹን በሙሉ ከስልጣን በማንሳቱ እና በሌሎች ሰዎች በመተካቱ ፤ ቴክኒካሊ ዛግዌን የአፈረሰው ላሊበላ ነው ማለት የእሚቻል ይመስለኛል ።

በጠቅላላው የዛግዌ ስርወ መንግሥት የስልጣን ታሪክ ፤ የዛግዌውን ስርወ መንግሥት ለስልጣን የአበቃው ይኽ ነው የእሚባል ከሰለሞናዊዎቹ ነገሥታት የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ እና ፖለቲካዊ ልቀት መኖር ሳይሆን ፤ በክርስትና ሰብዓዊ መልዕክት ነባራዊው ፖለቲካዊ ርዕዮት የተናወጸበት የአክሱማዊ መንግሥት ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እንደ ሆነው ፤ ፖለቲካዊ ስረዓቱ በአዲሱ የሰብዓዊ ዴሞክራሲ አግባብ ከአልተዋቀረ በስተቀር መፍቴኼ የሌለው በመሆኑ እና ይኽም አዲስ የመዋቅር መመሪያ ለመዳበር ደግሞ የራሱ ታሪካዊ ዝግመት ውስጥ መኼድ የነበረበት በመሆኑ ፤ ይኽም ኹኔታ በታሪካዊ አስገዳጅነት ፤ በአክሱም የነበረውን ሰለሞናዊ መንግሥት የጨለማ ዘመን የእሚባለው ውስጥ እንዲ ዳክር ሲያደርገው ፤ የተፈጠረው ክፍተት ፤ ለፖለቲካ ስልጣን አዲስ የሆኑትን የዛግዌ ነገሥታት ወይንም የአክሱማዊው መንግሥት መልከኞች ፤ አንድም በስረዓታዊ ውድቀቱ ከተፈጠረው ስረዓት አልበኝነት ራስን ለመከላከል ሌላም ወይንም ምናልባትም በአፈንጋጭ የጎበዝ አለቃነት ፤ የስረዓተ አልበኝነቱን ፖለቲካዊ እና ታሪካዊ ወርድ እና ስፋት በአለመረዳት ፤ ስልጣን ብንይዝ የተሻለ ሥራ መሥራት እንችላለን ከእሚል ሸማቂነት (Opportunism) ለስልጣን የበቁበት ታሪክ ነው።

ይኽም ኹኔታ ፤ በእየ ቦታው የጎበዝ አለቆችን እና ጎጠኞችን እየፈለፈለ ፤ በነበረበት በእዛ ወቅት ፤ የመልከኞቹ ስርወ መንግሥት ሊባል የእሚችለው የዛግዌው ስርወ መንግሥት ፤ በአዲስ የስልጣን ጉጉቱ ራሱን አጠናክሮ ፤ ያለ ሕዝባዊ ድጋፍ እና የፖለቲካ ልህቀት ፤ መንግሥትን ይዞ ማቆየቱ ፤ የእሚያስመሰግነው ነው።

ከዛግዌ ዘመን የእምንማረው ፤ በፖለቲካዊ ኃይሉ እና በቴክኖክራቱ (በሞያ አደሩ ወይንም የመካከለኛ ገቢ የአለው የሕብረተሰብ ክፍል ) መካከል ፤ መግባባት እና አብሮ መሥራት ከአልተቻለ ፤ ተጓቶ መውደቅ እንጂ ወደ ፊት መራመድ የእማይቻል መሆኑን ነው ። በእዚኽም በእዚያኽም ፤ በዘመነ አክሱም ተፋፍሞ የቆየው የመንግሥት ሹመኞች ቅሬታ ፤ በዋናነት በአክሱማዊው መንግሥት ግራ መጋባት ምክንያት ለሞያተኛው መጨረሻ ላይ የፖለቲካ ስልጣንን በኃይል የመቆጣጠር እድሉን ቢሰጠውም ፤ ይኽ የመልከኞች መንግሥት ፖለቲካዊ ወይንም ሕዝባዊ ድጋፍ ስለ አልነበረው ፤ የጠየቀውን እና የአሰበውን ማሕበራዊ ለውጥ ማሳካት ሲሳነው እናያለን ።

የፖለቲካ ስልጣኑ እና ድጋፉ የአላቸው ሰዎች ደግሞ ፤ ከተፈጠረው ስረዓታዊ ውድቀት የተነሳ ፤ የአሉበት ፈታኝ ኹኔታ ቢረዱትም ፤ ችግሩን መፍታት የእሚችሉበት ማሕበረ ኢከነሚያዊ መላ ወይንም ስረዓታዊ ቀመር የአልነበራቸው መሆኑ ፤ ሕዝባዊ ተቀባይነት እንኳን ቢኖራቸውም መፍትኼ አልባ መሆናቸው ፤ ከስልጣን በግድ እንዲወገዱ ቢያደርጋቸውም ፤ እነርሱን በኃይል አስወግዶ ወደ ፖለቲካ ስልጣን የመጣው የመልከኞች መንግሥትም ፤ ሸማቂ (Opportunist) የፖለቲካ ኃይል እንጂ ሕዝባዊ መሠረት የሌለው በመሆኑ ፤ ኹኔታው ሐገሪቱን ከእጅ አይሻል ዶማ የእሚባለው ዓይነት አጣብቂኝ ውስጥ ነው የከተታት ።

በአጭሩ ፤ ሕዝባዊ ድጋፍ ለነበረው የአክሱም ሰለሞናዊ ስርወ መንግሥት መውደቅ ፣ ያለ ሕዝባዊ መሠረት የዛግዌ ስርወ መንግሥት ወደ ስልጣን መምጣት እና ያለ ሕዝባዊ ድጋፍ የፖለቲካ ስልጣን መያዝ እና በእነ እዚኽ ሦሥት ፖለቲካዊ ኹኔታዎች የሐገሪቱ ፖለቲካ አጣብቂኝ ውስጥ ለመግባቱ ዋነኛው ምክንያት ፤ ማሕበራዊ መረጋጋትን እና የሕዝብን ቀጣይነት የአለው ኑሮን የማሻሻል (ልማት) ጥያቄ ማረጋገጥ የእሚችል ፖለቲካዊ ቀመር መጥፋቱ ወይንም ከጠንካራ ብሔራዊ መንግሥትነት ወደ ሕዝባዊ መንግሥትነት የእሚደረገው ሽግግር የእውቀት ማጣት ችግር ስለ ገጠመው ነው።

ከእላይ እንደ አልነው ፤ የክርስቲያኑን ዓለም ሕዝብ ፤ የፖለቲካ ጉዞ የቃኘን እንደ ሆነ ፤ እነ እዚኽ ማሕበረሰባት ፤ የቀደመውን ኢሰብዓዊ ስረዓት ከአስወገዱ በኋላ ፤ በሕዝባዊ ወይንም በሰብዓዊ አስተሳሰብ አዲስ ፖለቲካዊ ስልጣንን እና ኢከነሚያዊ ጥቅምን የእሚያገኙበት ፣ የእሚያሳድጉበት እና የእሚያስጠብቁበት ፤ ሳይንሳዊ የሆነ መንገድ ወይንም ሟደል (Model) እስኪ ያዳብሩ ፤ ይኽ ዓይነት መክፈቻ የሌለው መቆላለፍ (dead lock) ሊወገድ የእማይችል ችግር ሆኖ ሲቆይ ይታያል ።

በእርግጥ ይኽ የክርስቲያኑ ችግር ብቻ ሰአይሆን ፤ አምባገነናዊ መንግሥት ፤ የክርስቲያኑም ሆነ ሌላው በባሕሪው ወይንም በስሪቱ ዘላቂነት የሌለው በመሆኑ ፤ በግዜያዊነት ታላላቅ ውጤቶች ሊያስመዘግብ ቢችልም ፤ ከስሩ ምድር እንደ ተደረመሰበት (Sink Hole) ሕንጻ ፤ ማንም ሳይነካው እብስ ማለቱ የእማይቀር ነው።

ለእዚኽ ይመስላል ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ፤ ከነጻነቱ ዴሞክራሲ በፊት የነበሩት ፦ የግብጽ ፣ የግሪክ ፣ የሮም ፣ የባቢሎን ፣ የፋርስ ፣ የቻይና ፣ ወዘተ ፤ ታላላቅ መንግሥታት ፤ ኼደው ኼደው በስልጣኔ እና በስልጣን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሱ በኋላ ፤ በድንገት ማንም ሳይነካቸው ፤ ከውስጥ የእሚደረመሱት ።

የክርስቲያኖቹ አምባገነናዊ ስልጣኔዎች ከእዚኽ የእሚለዩት ፤ መንግሥቱ በእዚኽ መልኩ ድንገት ከመውደቁ በፊት ፤ የመንግሥታቸው ውቅር ስህተት የአለበት መሆኑ እና ሊቀጥል የእማይችል መሆኑን ተረድተው ፤ ቢያንስ አዲሱን የሕዝባዊ ወይንም የሰብዓዊ መንግሥት ቀመር እስኪያገኙ ድረስ ፤ በገቡበት መደናገር የአፈጻጸም ብቃታቸው ቢላላም ፤ አዲሱን ሕዝባዊ እና ሰብዓዊ ቀመር እስኪያገኙ መደናበር እና የስረዓት ውድቀት ውስጥ ቢገቡም ፤ ራሳቸውን ከኢሰብዓዊነቱ መግታታቸው ፤ እንደገና ለማንሰራራት የተሻለ እድል የሰጣቸው መሆኑ ነው።

ክርስቲያን ያልሆኑት አምባገነኖች ስረዓታቸው ችግር እንደ አለበት እንኳን ሰአይረዱ ድንገት ሲጠፉ ፤ ክርስቲያን የነበሩት አምባገነኖች የስረዓታቸውን ችግር ተረድተው ነገር ግን ችግሩን የእሚያርሙበት መላ ጠፍቷቸው ፤ አዲሱን የሰብዓዊ ግንዛቤያቸውን የእሚመጥን አዲስ ቀመር አለመግኘት የእሚፈጥረው መመሪያ የማጣት እና እርሱንም ተከትሎ የአፈጻጸም ድክመት የተነሳ ፤ በጣም በተዳከመ ኹኔታ ውስጥ የእሚዳክሩበት ኹኔታ ይፈጠራል።

ይኽ ደግሞ ፤ በክርስትናው የሰብዓዊ መልዕክት ምክንያት ይኽን መሰል መዋለል ውስጥ የገባ አንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ፤ አቅሙ ጎልብቶ በተነፃፃሪነት ተቀባይነት የአለውን ፍትሕ የእሚያሰፍነው ማሕበራዊ አወቃቀር እስኪያገኘው ድረስ ፤ ሕዝባዊ ጥያቄን ይዘው ለፖለቲካዊ ለውጥ የእሚታገሉ ሰዎች የእሚፈጥሩት አለመረጋጋት እና ይኽን ሕዝባዊ ጥያቄ ፤ በስልጣን ጥመኝነት ወይንም በግንዛቤ እጥረት ፤ መመለስ በእማይችሉ ነገር ግን ስልጣናቸውን ለመከላከልም ሆነ ሕግን እና ስረዓትን ለማስከበር በአለባቸው ኃላፊነትት ምክንያት ፤ ‘በለውጥ ፈላጊው’ እና ‘በስረዓት አስከባሪው’ መንግሥት መካከል የእሚደረገው ግብግብ እንዲ ቀጥል በማድረግ ፤ ማሕበረሰቡ ወደ መዋቅራዊ መፍትኼ እስኪ ያድግ ማሕበራዊ አለመረጋጋቱ እና ሰቆቃውም እንዲ ቀጥል ያደርገዋል ፤ ምንም እንኳን እንደ ቀደመዎቹ ስልጣኔዎች ስልጣኔውን እስከ እነ አካቴው ድራሹን በአያጠፋውም ።

ስለ እዚኽ ፦ ሦሥተኛውን የታሪካችንን ክፍል ፤ በሰው ልጆች የፖለቲካ ማሕበረሰብ ዝግመት ውስጥ ፤ ከጠንካራ ብሔራዊ መንግሥትነት ወደ ሕዝባዊ መንግሥት ለማደግ በእሚያደርገው ትግል ውስጥ ፤ የእሚኖረው የእውቀት እጥረት በእሚፈጥረው ውስንነት የእሚያጋጥሙ መሐበራዊ አለመረጋጋቶች የእሚገለጽ እና ሞያ አደሩ የማሕበረሰብ ክፍል ፤ ያለ ሕዝባዊ ድጋፍ የፖለቲካ ስልጣኑን ተቆጣጥሮ ሐገር ለመምራት የሞከረበት የአልተሳካ ጥረት ልንለው የእምንችል ይመስለኛል ።

ከእዚኽ በመቀጠል የእምናየው ፤ አራተኛው የታሪካችን ክፍል ፤ በእዚኽ የአልተሳካ ጥረት ተሰላችቶ የተዳከመውን የዛግዌ መንግሥት ፤ ከስልጣን አስወግዶ የስልጣኑን መንበር ዳግም የያዘው የሰለሞናዊው ስርወ መንግሥት ፤ ዳግም ወደ ስልጣን የመምጣት ታሪክ ነው ።