ሕ ገ ክ ራ ሲ

marketing-image

3.2.4. ክፍል 4 ፡ ዘመነ ሸዋ (ከ 1270 ዓ.ም. – 1527 ዓ.ም.)

አራተኛው የታሪካችን ክፍል የአልኹት ፥ እ.አ.አ. ከ1270 እስከ 1527 ዓ.ም. የአለውን ወደ ሦሥት መቶ ዓመታት የእሚጠጋ እና በአክሱም የነበረው ሰለሞናዊው ስርወ መንግሥት ፤ በጁዲት እና እርሱንም ተከትሎ በዛግዌ ስርወ መንግሥት ከደረሰበት ሽንፈት አገግሞ እንደገና የፖለቲካ ስልጣኑን ተቆጣጥሮ ፤ ያለ አስጊ ተቀናቃኝ ዳግም ሐገር የመራበትን ዘመን ነው ።

ይኽ ዘመንም ፤ የዛሬዋ ኢትዮጵያ መልከዓ ምድራዊ እና ፖለቲካዊ ቅርፅ የያዘችበት ዘመን በመሆኑ ፤ ዘመኑን በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ዝግመት ውስጥ ፤ ልዩ ታሪካዊ ስፍራ ይሰጠዋል ።

ከእዚኽ በፊት በነበሩት ፤ ሦሥት የታሪክ ክፍሎች ዳሰሳ መረዳት እንደ እምንችለው ፤ በሰፊው ምሥራቅ አፍሪካ እና በደቡብ አረቢያ ፤ ከ3,000 ዓመታት በፊት በተበታተነ የሕዝብ ሰፈራ የጀመረው የአከባቢው ፖለቲካዊ ታሪክ ፤ በግዜ ኺደት ፤ እነ ቲብስ ፣ ሜሮ ፣ የኃ እና መሪይብ (የመን ሳባ) የመሳሰሉ ታሪካዊ እና ትላልቅ ከተማዎችን ማቋቋም ጀምሮ ፤ ከእዛኽ በኋላ ፤ ወደ ክርስቶስ ልደት መዳረሻ አከባቢ የተመሠረተችው አክሱም ፤ ቀስ በቀስ አከባቢውን ኹሉ ዓማክላ ማስተዳደር የእምትችልበት ትልቅ የፖለቲካዊ አቅም ገንብታ ፤ ቢያንስ በ4ኛው ምዕተ ዓመት መባቻ ላይ ከነገሠው ኢዛና አንስቶ ንጉሥ ካሌብ እስከ ነበረበት የ6ኛው ምዕተ ዓመት ድረስ ፤ የአከባቢው ፖለቲካዊ ፣ ኢከነሚያዊ እና ኃይማኖታዊ መዓከል ኾና ነበር ።

ከንጉሥ ካሌብ በኋላ ፤ በተለይም ከ6ኛው ምዕተ ዓመት ፤ መጨረሻ አንስቶ ግን ፤ የአክሱሙ መንግሥት ከላይ በጠቀስነው መደናበር ከውስጥ እየተዳከመ ፤ ከአክሱም በስተ ምዕራብ ፥ በዛሬዋ ሰሜን ሱዳን እና ከአክሱም በስተ ምሥራቅ ፥ በዛሬዎቹ የመን እና የተወሰኑ የሳኡድ አረቢያ ውስጥ በአሉ፟ት ቦታዎች ላይ የነበረውን ፖለቲካዊ ተፅኖ ሙሉ በሙሉ እየ አጣ ፤ ከእዛኽም በቆይታ በአክሱም ራሱ ህልውናውን አስጠብቆ መቆየት የእሚችልበት ኹኔታ በመጥፋቱ ፤ ራሱን ለማዳን ወደ ዛሬዋ ኢትዮጵያ መሐል አከባቢ መቀመጫውን በማዛወር ላይ እያለ በተፈጠረ የታሪክ አጋጣሚ ፤ የፖለቲካ ስልጣኑ ወደ ዛግዌ ስርወ መንግሥት በመሸጋገሩ ወይንም የአክሱሙ ሰለሞናዊ ስርወ መንግሥት ወደ መሐል ኢትዮጵያ በማዛወር ኺደት ላይ እያለ የፖለቲካ ስልጣኑን ስለ አጣ ፤ ለቀጣዩ 323 ዓመታት ገደማ ፤ ዛግዌ በስልጣን ላይ በነበረበት ዓመት ኹሉ ፤ የአክሱሙ (አሁን የሸዋ የሆነው) ሰለሞናዊ ስርወ መንግሥት ፤ በሸዋ ተወስኖ የቀረበት ኹኔታ ነው የተፈጠረው ።

እነ እዚኽ ፤ አክሱማዊያን ነገሥታት ግን ፤ አንድ ግዜ በሸዋ ተወስነው እንዲቀሩ ከሆኑ በኋላ ፤ ሸዋ ላይ በቆዩባቸው ዓመታት ፤ ከሸዋ በስተ ደቡብ ፥ በደቡብ ምሥራቅ እና በደቡብ ምዕራብ ፤ አዲስ ፖለቲካዊ ትስስር እና አወቃቀር በመፍጠር ፤ ራሳቸውን በኢከነሚ ፣ በወታደር እና በፖለቲካ በማደርጀታቸው ፤ ለ323 ዓመታት ገደማ ተነጥቀው የቆዩትን የፖለቲካ ስልጣን ፤ ከዛግዌ ስርወ መንግሥት መልሰው መረከብ ችለዋል ።

ምንም እንኳን ይኽ ፤ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ጂዖግፊያዊ እና ፖለቲካዊ ቅርጿን የያዘችበት ዘመን ወይንም የታሪክ ክፍል በጣም ፈጣን በሆኑ ታሪካዊ ኩነቶች የተሞላ እና ብዙ ትዕይንት የተከናወነበት ከመኾኑ የተነሳ ፤ ይኽንን ታሪካዊ ኺደት የመሩ እና ያስቻሉ ፤ በፖለቲካዊውም ሆነ በመንፈሳዊው ዓለም ፤ እንደ አጼ ይኩኖ አምላክ ፣ አጼ ዘራ ያዕቆብ ፣ አጼ ዳዊት የመሳሰሉ ታላላቅ ነገሥታት የነገሡበት እና በመንፈሳዊው መስኩም እንደ አቡነ ተክለ-ኃይሞኖት ፣ ኢየሰስ ሞዓ እና አባ ኤዎስጣቴዎስ/ዮስጣቴዎስ ፤ የመሳሰሉ ድንቅ ሰዎች ተነስተውበት የነበረበት ዘመን ቢሆንም ፤ እ.አ.አ. ከ1314 – 1344 ዓ.ም የነገሠው ንጉሠ ነገሥት አምደ ፅዮን ከእነ እዚኽ ኹሉ ኢትዮጵያዊ ኃያላን እጅግ ጎልቶ እና ላቅ ብሎ የታየበት ዘመን ነበር ፤ ይኽ ዘመን ።

ኦለንደርፍ (Ullendorf) የተባለውን የብሪታኒያ ዜግነት የአለው ፤ የኢትዮጵያ አጥኚ ( Ethiopianologist ) ጠቅሶ ፤ ፖል ኼንዝ እንደ አለው ፦

“አምደ ፅዮን ፥ ኢትዮጵያ በዘመኗ ኹሉ ከነበሯት ነገሥታት ኹሉ ላቅ ብሎ የእሚታይ እና በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአፍሪካ ቀንድ ብቸኛው የበላይ አካል የነበረ ነው ።”

“Amde Tseyon was one of the most outstanding Ethiopian kings of any age and a singular figure dominating the Horn of Africa in the fourteenth century [35]“

አምደ ፅዮን ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ኮከብ ከአልሆነም የእዚኽ ክፍል ኮከብ የእሚያደርገው ፤ እ.አ.አ. በ 970 ዓ.ም. አከባቢ ጀምሮ ፤ አክሱማዊ ነገሥታት በሸዋ ሆነው ፤ ራሳቸውን ማደርጀት እና ራሳቸውን በማደርጀት በገነቡት አቅም የፖለቲካዊ መሪነቱን ከዛግዌ መቀበል እና በስተ መጨረሻም ፤ ዛሬ የእምናውቃትን ኢትዮጵያ ፤ በኢከነሚ ፣ በፖለቲካ እና በማሕበራዊ ገመድ ማስትሳሰር የመጨረሻ ግባቸው አድርገው ለረዥም ዘመን ሲያከናውኑት የነበረውን ‘ዘመቻ’ ፤ ወደ ንግሥና በመጣ በ18ኛው ዓመቱ አከባቢ ፤ ማለትም እ.አ.አ. በ1332 ዓ.ም. ‘የዘመቻው’ የመጨረሻ አካል የሆነውን ፤ የዛሬዋን ኢትዮጵያ አካላዊ ቅርጽ የመበየኑ ሥራ ላይ ፤ ማህተሙን ወይንም የመደምደሚያውን ዓለት ማስቀመጥ በመቻሉ ነው ።

አምደ ፅዮን ፤ እ.አ.አ. ከ1332 ዓ.ም. በኋላ በእርሱ መሪነት ፤ የዛሬውን የኢትዮጵያ አከባቢዎች በሙሉ በሸዋ መዓከልነት አስተሳስሮ ፤ ኢትዮጵያን እንደ አንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ማዋቀር ችሎ ነበር ፦

“ወደ ስልጣን ከመጣበት እ.አ.አ. ከ1314 ዓ.ም. አንስቶ ከሙስሊሞች ጋር ጦርነት እስከ ገባበት እ.አ.አ. 1332 ዓ.ም. ድረስ ፥ በእሚንተከተከው ኃይሉ በመላው ሐገሪቱ በአደረገው ጦርነት ፤ አምደ ፅዮን ኹሉንም የንግድ መንገዶች እና እነ እዚኽ መንገዶች የእሚያዳርሱዋቸውን (የእሚያገለግሉዋቸውን) ቦታዎች በሙሉ ተቆጣጥሯል ።”

“Between his accession to power in 1314 and the Muslim wars in 1332 ‘Amde-Syon’s energetic campaign throughout the countey had brought him full control of the different trade routes and the interior provinces which they served. [98]”

ምስል 6 ፡ እ.አ.አ. 1332 ዓ.ም. አምደ ጽዮን የእሚያስተዳድራቸው የወቅቱ የንግድ መስመሮች። ምንጭ ፦ [97]።

በዓምደ ፅዮን ዘመን ፤ የቀደሙት እነ ኢዛና እና ካሌብ መሰል ታላላቅ አክሱማዊ ነገሥታት ፤ በአፍሪካ ከነበራቸው አስተዳደራዊ ክልል ፤ ከሸዋ አስተዳደር ውጭ የነበረው ፤ የዛሬ ሰሜናዊ ሱዳን ብቻ ነበር ። በዛሬዎቹ ፥ ኢትዮጵያ ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ ያለ ዓምደ ፅዮን ፈቃድ የእሚሆን ነገር አልነበረም ።

ስለ እዚኽ ፦ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ምንሊክ የሰሯት ሳትሆን ፤ አምደ ፅዮን እ.አ.አ. በ1344 ዓ.ም. ለኢትዮጵያዊያን ከአስረከባቸው ኢትዮጵያ ፤ አጼ ምንሊክ ማትረፍ የቻልዋት ኢትዮጵያ ነች ።

የሸዋው መንግሥት ፤ ከደረሰበት ውድቀት በእንዲኽ ዓይነት መልኩ ማንሰራራት የቻለው እና ይኽንንም ትልቅ ታሪካዊ ገድል መፈፀም የቻለው ፤ ከስልጣን የተወገደበትን ዘመን ፤ ራሱን ለማጠናከር ስለ ተጠቀመበት ንው ።

ሸዋ የገባው አክሱሙ ሰለሞናዊ ስርወ መንግሥት ፤ በአስተሳሰቡ ረገድ የአመጣቸው ኹለት ለውጦች ፤ ቢያንስ ከአክሱም ውድቀት ቀድሞ የነበረውን ጥንካሬውን መልሶ እንዲያገኝ አስችሎታል።

በእዚኽ ረገድ የመጀመሪያው ፤ የአስተሳሰብ እመርታው ፤ ቤተ ክርስቲያን በፖለቲካው ጉዳይ ለመንግሥት የእምትገዛ እንጂ ፤ በመንፈሳዊውም ሆነ በፖለቲካው ጉዳይ እንደ ቀደመው የበላይ ሆና ፤ ኹሉን የእምትገዛ እንደ አትሆን ማድረግ በመቻሉ ነው። በአጭሩ ፤ ምንም እንኳን የሰብዓዊ ዴሞክራሲው እንደ እሚያደርገው ፤ ኃይማኖት እና መንግሥትን በአይለይም ፤ ኃይማኖታዊ መሪዎች ግን ፖለቲከኞቹን በኃይማኖታዊ ቀኖና መቆጣጠር እንደ አይችሉ ማድረግ በመቻሉ ነው።

የሸዋ ነገሥታት ፤ ይኽን ትዳር መመሥረት አትችልም ፣ ያንን ማድረግ አትችልም ወይንም ይኽን ብታደርግ አውግዝኃለው የእሚሉዋቸውን መንፈሳዊ መሪዎች ፤ ለማጋዝ ብዙም አያመነቱም ነበር።

በኹለተኝነት ፤ ምንም እንኳን ኼዶ ኼዶ መጨረሻው መፍረስ ቢሆንም ፤ በሰብዓዊነቱ አስተሳሰብ ሳይገደቡ እና የክርስትና ውርሳቸውን ሳይዘነጉ ፤ ትልቅ መንግሥት መገንባት ፤ በግዜያውነትም ቢሆን ለህልውና አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት በመንቀሳቀሳቸው ነው።

የአክሱሙ ስርወ መንግሥት በመራ ተክለኃይማኖት በትረ ስልጣኑን ከተነጠቀ በኋላ ፤ በእነ እዚኽ ኹለት አስተሳሰቦች ራሱን ቃኝቶ ወደ ፖለቲካው መንበር እንደ ገና እስኪመጣ ኅቡዕ ገባ ማለት ይቻላል ። ሸዋ ላይ ገዢ ሆኖ እንደ ተቀመጠ ቢታወቅም ፤ እነ እዚያኽን የዛግዌ ስርወ መንግሥት በስልጣን ላይ የቆየባቸውን 323 ዓመታት በምን ዓይነት ኹኔታ እንደ አሳለፋቸው በቂ ታሪካዊ ገለፃ ማግኘት ይቸግራል ።

የአክሱም ስርወ መንግሥት ፤ የመጨረሻ ንጉሥ ከነበረው ድል ናዖድ ፤ የሰለሞኑ ስርወ መንግሥት ነጋሢ ሆኖ ፤ ከዛግዌ የመጨረሻ ንጉሥ ይትባረክ በትረ ስልጣኑን እስከ ተረከበው ይኩኖ አምላክ ፤ መንገሥ የነበረባቸው እና ያልነገሡ ፤ የአክሱሙ ስርወ መንግሥት ነጋሢዎች አስር ነገሥታት እንደ ነበሩ እና በየረር[1] (አዲስ አበባ) እንደ ነበሩ አንዳንድ ታሪኮች ቢሉም የነበራቸው ቆይታ ምን መልክ እንደ ነበረው ብዙ ሲሉ አይሰማም ።

እነ እዚኽ የአክሱም ነገሥታትም ፤ እዚኽ ሸዋ በነበሩባቸው ለእነ እዚኽ ያኽል ዓመታት ለዘመናት በቆየ ልምድ ፦ ሕጋዊ ነጋሢዎች ናቸው ተብለው በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን እውቅና ስለ አላቸው ፦ የቤተክርስቲያን ከለላ ፣ የተለያዩ አካላት እገዛ ፣ የዛግዌ ስርወ መንግሥት ‘መልካም ፈቃድ’ ታክለውበት ፤ በሸዋ ለረዥም ዘመን ፤ ድምፃቸውን አጥፍተው እንዲ ቀመጡ በተገደዱበት ወቅት ነው እንግዲህ ዳግም ወደ መንበረ ስልጣኑ ሊመልሳቸው የእሚችለውን እና የዛሬዋን ኢትዮጵያ ቅርፅ ለማስያዝ የእሚያበቃቸውን አቅም ሸዋ ላይ ሆነው የገነቡት ።

ለእዚኽም አቅም ግንባታ ዋንኛ ምንጫቸው ደግሞ ፤ ከሸዋ በስተ ደቡብ ፤ በምሥራቁም ሆነ በምዕራብ ፤ የነገሥታቱን ሸዋ መግባት ተከትለው የበቀሉት የሙስሊም ሱልጣኔቶች እና የባህላዊ እምነት ተከታዮች (አረማዊያን) የሐገሬው ሕዝብ መንግሥታት ናቸው ።

የአክሱሙ ስርወ መንግሥት ወደ ሸዋ ገብቶ መኖር ከቀጠለ በኋላ ፤ በደቡብ ምሥራቅ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ፤ ከእዚያኽ በፊት በአልነበረ መልኩ ወይንም የአክሱሙ መንግሥትን ሸዋ መግባት ተከትሎ በእሚያስብል ዓይነት ፤ አዳዲስ የፖለቲካዊ ማዕከሎች ሲፈጠሩ ይታያል ።

ይኽም ደግሞ ፤ የአክሱሙ ስርወ መንግሥት ፤ በገባበት መደናበር ከስልጣን ቢወገድም ፤ የፖለቲካ እና የኢከነሚ ስበት ማዕከል የመሆን ‘ተፈጥሮዋዊ’ ባሕሪውን የአልለቀቀ ወይንም ቢያንስ ንቆ የተወውን መንገድ መልሶ መከተል የእሚችል በመሆኑ ፤ በሸዋ በቆያባቸው ግዜያት በኺደት ፤ እነ እዚኽ እርሱን ተከትለው ፤ በደቡብ ምሥራቅ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የተመሠረቱ አዳዲስ የፖለቲካ ማዕከላት ከራሱ ጋር አስተሳስሮ እና በእዚኽም ራሱን የእነ እዚኽ ንዑስ መዓከላት የጋራ ማዕከል አድርጎ ፥ ሸዋን አኹን እስከ አለንበት ዘመን ድረስ የኢትዮጵያ ብሎም የአከባቢው (የአፍሪካ ቀንድ) ማዕከል ሆኖ እንዲቀር አድርጎታል ።

ከ10ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አስቀድሞ ፥ ማለትም የአክሱሙ ስርወ መንግሥት ደቡብ ደቡብ ማለት ከጀመረመበት ግዜ አንስቶ ፤ የአለውን ዘመን ስንመለከት ፤ በደቡባዊ ምሥራቅም ሆነ በደቡባዊ ምዕራብ ኢትዮጵያ ይኽ ነው የእሚባል ፖለቲካዊ ፋይዳ የአለው የፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ወይንም ማዕከል የእማይስተዋልበት እና በዛሬዋ ኢትዮጵያ ደቡብ ምዕራብ ጫፍ ይገኝ ከነበረው ከእናርያው መንግሥት በስተቀር ፤ ሌላ በታሪክ የተመዘገበ ፖለቲካዊ አወቃቀር ያልነበረበት አከባቢ የነበረ ነው ።

የአክሱም ነገሥታት በሸዋ ተራሮች ላይ መሸሸግ ከጀመሩ በኋላ ግን ፤ እናርያ አድጎ ዳሞት (ሐድያን ፣ ወላይታን ፣ ሲዳማን ፣ ወዘተ ፤ የእሚያጠቃልል) የእሚባለውን ትልቅ የደቡብ መንግሥት ያቋቋመበት ፤ በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ፤ ከዘይላ ወደብ እስከ ሸዋ ተራሮች ግርጌ ደግሞ ወደ ሰባት የእሚሆኑ የሙስሊም ሱልጣኔቶች የተመሠረቱበትን ኹኔታ እናያለን ።

ከእናርያ ጉያ የወጣው የዳሞት መንግሥት ከ10ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እስከ 13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው የቆየው ፤ የሐድያው ሱልጣኔት ፥ ከዳሞት መክሰም በኋላ መጥቶ እና በደቡባዊ የዳሞት ጫፍ የአለውን አነስተኛ ክልል ይዞ እስከ 15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቆይቶ ከስሟል ። በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ አቅጣጫ ከተመሠረቱት የሙስሊም ሱልጣኔቶች የመጀመሪያው የሆነው ፤ የኢፋት ሱልጣኔትም ከሐድያው ጋር ተመሳሳይ ግዜ እና እድሜ የነበረው ነው ፤ ኢፋቱ ሲዳከም የአዳሉ ሊተካው ቢሞክርም እርሱም እንደ እዛው ከስሟል ።

በአጠቃላይ ፦ እናርያ ሲቀር ፤ ዳሞት ፣ ሐድያ ፣ ደዋሮ ፣ ፈጠጋር ፣ ኢፋት ፣ ባሊ ፣ ወዘተ ፤ መንግሥታት ወይንም ሱልጣኔቶች ወደ ሸዋ ራሱን ከአዛወረው የሰለሞኑ ስርወ መንግሥት በኋላ የተመሠረቱ እና ቆይታቸውም ከ10ኛው እና 15ኛው ክፍለ ዘመን የሆነ እና ከእዚኽ በኋላ ፤ በኹሉም ላይ የሸዋ ታማኝ የተሾመባቸው ፤ ተጠሪነታቸው ቀጥታ ለሸዋው የሆኑ መንግሥታት ነበሩ።

ይኽም ማለት ፤ የወቅቱ ታሪክ አሁን በዓለው ተዓማኒ መረጃ መሠረት ስንመዝነው ፤ በአንዳንድ ተንታኞች ከእሚቀርበው ትንታኔ በተቃራኒ ፤ ከእናርያ በስተቀር ፤ ከሸዋው መንግሥት በስተ ደቡብ ምሥራቅ እና ምዕራብ የተነሱት መንግሥታት ፤ በሸዋው ይኹንታ ራሳቸውን የቻሉ ሆነው የተቋቋሙ እና በኋላ ላይም በተፈጠረ አለመግባባት ኹሉም በሸዋ ስር የገቡ እንጂ ፤ እነ እዚኽ አናሳ መዓከላት ከሸዋው አክሱማዊ መንግሥት በፊት ኖረው የነበሩ እና የሸዋው አክሱማዊ መንግሥት ወደ እነርሱ ለመስፋፋት በመፈልጉ ወይንም እነርሱን በእርሱ ስር ለማድረግ ከመፈለጉ የተነሳ ከእራሱ ጋር ያዋኃደቸው አለመሆናችው ነው ።

ይልቁኑም ከእዚኽ በታች እንደ እምንመለከተው ፤ ለዛሬዋ ኢትዮጵያ ቅርጽ የሰጠው ግጭት ፤ ከሸዋው ተስፋፊነት የመነጨ ሰአይሆን ፤ በሸዋ እና በእነ እዚኽ አናሳ የፖለቲካ መዓከላት መካከል ፤ በመሐል የእሚፈጠር የተለያየ ዓይነት የጥቅም ግጭት እና የአለመግባባት (Communication gap) የእሚፈጥራቸው የእማያባሩ ግጭቶች ፤ የኃይል ሚዛኑ ወደ አመዘነበት ሸዋ እንዲጠቃለሉ እንደ አደረጋቸው ነው የእሚታየው ።

የእነዚኽ መንግሥታት አጀማመር ፣ እድገት ፥ በኋላም ከሸዋው መንግሥት ጋር የገቡት ግጭት እና በእዚኽ የታሪካችን ክፍል በስተመጨረሻ አከባቢ በሸዋው መንግሥት ‘መዋጣቸውን’ ስናይ የእሚያንፀባርቀው ይኽንን ነው ።

አረባዊ የሆኑት እና በግዜ ኺደት በሸዋው የተጠቀለሉት ፤ የሸዋውን መንግሥት ተከትለው በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጲያ መብቀል የጀመሩት የሙስሊም ሱልጣኔቶቹ ወደ ዛሬይቱ ኢትዮጵያ እንዲ መጡ ያደረጋቸው እና ለተወሰነ ዓመታትም ቢሆን ሱልጣኔት እንዲገነቡ ያስቻሉዋቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ ።

ከእነዚኽም ምክንያቶች አንዱ እና ቀዳሚው ፤ ኢትዮጵያ ከአረብ ምድር ጋር ቅድመ አክሱም ጀምሮ የነበራት ተፈጥሮዋዊ እና ታሪካዊ ቁርኝት ነው ። በቀደሙት ክፍላት እንደ አየነው የአረቡ ምድር ከመላው ምሥራቅ አፍሪካ ጋር ለሺ ዓመታት የቆየ ትስስር የአለው እና ቀላል ለእማይባሉ ዓመታትም ፥ ከ200 ዓመታት በላይ ፤ በአክሱም ነገሥታት አስተዳደር ስር የነበረ ነው ። ከእዛኽ በአሻገር ፤ እንደ እምናውቀውም ፤ በኢትዮጵያ እና በአረቡ ምድር (የአረቦቹ መሽመጥ: The Arabian Peninsula) ጋር የእሚለየን ‘ጠባቡ’ እና አንዳንዴም ከ22 ኪሎሜትር የእማይዘል ርቀት የአለው እና በትናንሽ ጀልባ ሰዎች ሊሻገሩት የእሚችሉት ቀይ ባሕር ነው ።

ስለ እዚኽ ፦ ምንም እንኳን ፤ ኹለቱ ሕዝብ ፤ በታሪክ አጋጣሚ ፍፁም ተቃራኒ ኃይማኖታዊ ቅርንጫፍ የእሚከተሉ መሆናቸው ፤ እጅግ ተቃራኒ ሕዝብ ‘ቢያስመሰላቸውም’ ወይንም ‘ቢያደርጋቸውም’ ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና የአረቡ ዓለም ሕዝብ የአለው ትስስር ታሪካዊ እና ‘ተፈጥሮዋዊ’ ነው ።

ይኽም በኹለቱ ሕዝብ መካከል የአለው ፤ በሺ ዓመታት የእሚቆጠር ፖለቲካዊ እና ማሕበራዊ ቁርኝት እንዲሁም የአለንም ጂዖግራፊያዊ ቅርበት ፤ እነ እዚኽን የሙስሊም ሱልጣኔቶች ወደ የዛሬዋ ኢትዮጵያ የአክሱሙን መንግሥት ተከትለው እንዲመጡ እና ብዙ ነዋሪ በሌለበት በዋናነት ክርስቲያን በአልሆነው አከባቢ እና የባህላዊ እምነት ተከታዮች በአሉባት ኢትዮጵያ ፤ የሙስሊም ሱልጣኔት መስርተው ፤ ሱልጣን በመሆን እንዲቆዩ ያደረጋቸው አንደኛው ምክንያት ነው ።

ሌላው እና ኹለተኛ ሊባል የእሚችለው ምክንያት ፤ አንዳንድ የታሪክ መዝገቦች እንደ እሚሉት ፤ የአንዳንዶቹ ሱልጣኔቶች መሥራች አረቦች ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት የቅርብ ምክንያት የሆናቸው ፤ ሙስሊሞች ከነብዩ መሐመድ መሞት በኋላ ፤ ነብዩ መሐመድን ማን ሊተካ ይገባል በእሚለው ጉዳይ ተለያይተው አንጃ በመፍጠር ሲጋጩ ፤ በእዚኽ ግጭት ተሸናፊው አካል ፤ ወደ ተለያየ አከባቢ ሲሰደድ ፤ ከእነዛኽ ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ በመኖራቸው ነው ይላሉ ።

እነ እዚኽ ፥ በስደት የመጡ የነብዩ ዘመዶች ፥ በታላቁ የእስልምና የመስፋፋት እንቅስቃሴ መዓከል ውስጥ የነበሩ እና ብዙ የፖለቲካ ግንዛቤ የአላቸው ሰዎች በመሆናቸው ፤ ማለትም ተሸንፈው ቢወጡም ፤ የመጣው ተርታው ሰው ሰአይሆን የፖለቲካ ግንዛቤ የአላቸው በመሆናቸው ፥ በኢትዮጵያ ውስጥ የአለውን ኹኔታ ተጠቅመው ፖለቲካዊ ሚና እንዲ ኖራቸው ወይንም ሱልጣኔቶቹን ለመመሥረት ኹኔታው የፈቀደላቸውን ያኽል መንቀሳቀሳቸውም አይቀርም ።

ለምሳሌ ፦ የባሊ ሱልጣኔት መሥራች የሆኑት ሼኽ ሁሴን ፤ ቁሬሽ እንደ ሆኑ እና ከነብዩ መሐመድ ጋር የስጋ ዝምድና እንደ አላቸው ይላል አንድ ጥናት ፦

“...የሼኽ ሁሴን አባት ፥ ሼኽ ኢብራኺም አል ማላኪ ሼኽ አብዱላህ ፤ አቡ ጣሊብ የእሚባሉት እና የነብዩ መሀመድ አባት ወንድም (የነብዩ መሐመድ አጎት) 12ኛ የልጅ ልጅ ናቸው ።”

“...the father of Sheik Hussein, Sheik Ibrahim al-Malkai Sheik Abdulla is the 12th descendant of Abu Talib, the paternal uncle of Prophet Mohammed. [99]“

ለእዚኽም ነው ፤ ሙሉ ለሙሉ ሊባል በእሚችል ኹኔታ ፤ ከሸዋ በስተ ደቡብ ምሥራቅ የተመሠረቱት እና በአጠቃላይ በመላው ኢትዮጲያ በግዜያዊነትም ቢሆን ብቅ እያሉ የጠፉት ስልጣኔቶች ፤ በነበሩባቸው ግዜያት ኹሉ በአረቦች የተመሠረቱ እና በአረቦች ይመሩ የነበረው ።

የእነ እዚኽ የሙስሊም ሱልጣኔቶች ወደ ዛሬይቱ ደቡባዊ ምሥራቅ መምጫ ምክንያቶቻቸው ከእላይ የዘረዘርናቸው ፦ ታሪካዊ ቁርኝት ፣ ጂዖግራፊያዊ ቅርበት ፣ ፓለቲካዊ ስደት ሲሆኑ ፤ ከእነ እዚኽ ውጫዊ ምክንያቶች በአሻገር በቅርብ ምክንያትነት ደግሞ ከሸዋው መንግሥት ጋር የዓቆራኛቸው ፤ በወቅቱ በነበረው የዓለም ማሕበረ ኢከነሚ መዋቅር ምክንያት ፤ ብቸኛ የዓለም ዓቀፉ ንግድ አዋቂ እና የንግድ እቃ አስተላላፊነቱን ሥራ ከእነርሱ በተሻለ ኹኔታ ሊሰራው የእሚችል ሌላ በአለመኖሩ ፤ በኹኔታው ተስበው ራሳቸውን ለሸዋው መንግሥት አጋዥነት ለማቅረብ የእሚፈልጉበት አጋጣሚን ስለ እሚያሰፋው ነው።

“ከእነ እዚኽ ሰሜናዊ ወደባት መካከል ስለ ዘይላ ብዙ ይታወቃል። ይችኽ ከተማ ከአረቦቹ ሰሜናዊ ሰፈራ መካከል ከፍተኛ ፖለቲካዊ ፋይዳ የአላ፟ት ነች ፤ የከተማዋም ኢከነሚያዊ ብልጽግና የእሚመጣው የቀድሞዋ አቢሲኒያ ከአረቦች እና ከሩቅ ምሥራቅ ሐገራት ጋር የእምታደርገው ንግድ የእምታደርግበት ዋነኛ ወደብ በመሆኗ ነው።”

“Of these northern ports most is Known of Zeila. This town was politically the most important of the Arab settlements in the north and owed its economic prosperity to its geographical position as one of the chief ports of early Abyssinia in the trade with Arab and the Orient. [100]”

ታደሰ ታምራት ፤ በ14ኛው ምዕተ ዓመት ፤ የሸዋዎቹ ነገሥታት ፤ የሙስሊም ነጋዴዎችን የንግድ አዋቂነት ይጠቀሙበት እንደ ነበረ እንዲህ ይለናል ፦

“(የሙስሊም ነጋዴዎች) በንጉሡ ገንዘብ ፤ በህንድ ፣ ግብፅ እና በግሪክ ሕዝብ መካከል ይነግዱ ነበር ። የዝሆን ጥርስ ፣ እጅግ በጣም ጥሩ የሸዋ ፈረሶች ፣ ንፁህ ቀይ ወርቅ ከእናርያ እየሰጣቸው … ሙስሊሞቹም ይኽን ይዘው… ወደ ግብፅ ፣ ግሪክ እና ሮም እየኼዱ ፤ በአረንጓዴ እና ቀይ ድንጋይ እንዲኹም በወርቃማ አበባ ያጌጡ ልብሶች (ወርቀ ዘቦ ወይንም ግምጃ) ያመጡለት ነበር ።“

“(The Muslim traders) did business in India, Egypt, and among the people of Greece with the money of the King. He gave them ivory, and excellent horses from Shewa and red, pure gold from Enarya...and these Muslims...went to Egypt, Greece and Rome and exchanged them for very rich damasks adorned with green and scarlet stones and with the leaves of red gold, which they brought to the king. [98]“

ይኽም በመሆኑ ፤ ብዙ ግዜ በአንድ ግቢ እና ሲበዛ በትንሽ ሰፈር የተወሰነው የሙስሊም ሱልጣኔቶቹ ሱልጣኔት በመላው ኢትዮጲያ የእሚመሠረተው ፤ በሸዋዎቹ ነገሥታት ይኹንታ ነበር። ለምሳሌ ፦ የኢፋት ሱልጣኔት በመባል የእሚታወቀውን ሱልጣኔት ፤ የመሠረተው ወላስማ የእሚባለው ሰው ፤ ሱልጣኔቱን ለመመሥረት ያስቻለው ይኩኖ አምላክ እንደሆነ ነው የእሚታመነው ፦

“በሌላ ስሙ ፥ ኡመር ተብሎ የእሚታወቀው እና በታሪክ ኢፋት የእሚባለው ሱልጣኔት መሥራች … ራሳቸው ሙስሊም በሆኑ መስካሪዎች … መሠረት … ኡማር ወላስማ ራሱ አብዛኛው የስልጣኑ ምንጭ የክርስቲያኑ ንጉሥ (ይኩኖ አምላክ) ነው።”

“Walasma, also called ‘Umar, was the first historical ruler of the Muslim principality of Ifat....according to ... informants who were Muslims themselves, even Umar Walasma owed much of his power to the Christian king [98].”

ይኽም ፤ ከሱልጣኔት መሥራቾቹ የራስ ፍላጎት በአሻገር ፤ ወደ ሸዋ የዞረው የአክሱሙ ስርወ መንግሥት የእነርሱን ፤ የዘመኑን ንግድ እውቀት እና ትስስር መፈለጉም ፤ እነ እዚኽ የአረብ ሱልጣኖች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ እና ሱልጣኔታቸውን እንዲ መሰርቱ የእሚያደርጋቸው ሌላው ምክንያት ሆኖ እናገኘዋለን ።

የሸዋው መንግሥት ፤ መዓከል ቀየረ እንጂ ፥ ፖለቲካዊ ፍልስፍናው እና ፖለቲካዊ ስሪቱ አክሱማዊ የነበረ ነው ፦

“እንደ ሌሎቹ የመንግሥቱ ተቋሞች ኹሉ ፥ የአምደ ፅዮን ጦር መዋቅር ፥ አክሱም በገናነቷ ዘመን የነበራት አወቃቀር ቀጥታ ግልባጭ ነው የነበረው ።”

“Like many other institutions of his Empire, the organization of Amde-Siyon’s army was a direct replica of that of the Kingdom of Axum at the time of its greates splendor [98].”

ስለ እዚኽ ፦ የሸዋው መንግሥት ኢከነሚያዊ ፍልስፍና እና እርሱንም የእሚመራበት ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አወቃቀሩ ፤ የቀድሞዋ አክሱም ከእምትመራበት ፍላስፍና የተቀዳ ነበር ።

እንደ እሚታወቀው ፥ የቀድሞው የአክሱም መንግሥት የኢከነሚ ፍልስፍና ፤ በወታደራዊ ኃይል ፥ የእቃ አቅርቦት ሰንሰለቱን በሙሉ በመቆጣጠር ፤ የንግድ ኺደቱ እንደ አይስተጓጎል ማድረግ እና ይኽንንም አገልግሎት ፤ ለነጋዴው ማሕበረሰብ (ከባቢያዊም ሆነ ዓለም ዓቀፋዊ) በማቅረብ ከእዚኽ ንግድ በእሚገኘው ፈርጀ ብዙ ጥቅም ሐገርን ማሳደግ እና መንግሥትን ማጠናከር ታሳቢ የአደረገ የነበረ ነው ።

ይኽን የቀደመውን የአክሱምን የኢከነሚ ፍልስፍና ፤ በምዕራፍ አንድ ላይ ያየነው ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ቤተክርስቲያን መሥራች አባት የሆነው ፍሬምናጦስ (አባ ሰላማ) ፤ ወደ ኢትዮጵያ የመጣበት መንገድ በደንብ የእሚያሳየው ይመስለኛል ፦

“እንደ ታሪከኛው ሩፊነስ ፤ ፍሬምናጦስ ፥ በእዚያኽን ግዜ ብላቴና ነበር ፤ ሲጓዝበት የነበረበት መርከብ ፤ በኢትዮጵያ የእሚተዳደር ወደብ ላይ ለስንቅ ይቆማል ። በወቅቱ በነበረው የፖለቲካዊ ግንኙነት መሰንጠቅ (በኢትዮጵያ እና ሮም ) ፤ መጓጓዣው ተይዞ መንገደኞቹ ይገደላሉ ። ፍሬምናጦስ እና ኦዲሲየስ ፥ የፍሬምናጦስ ወዳጅ ግን እድለኛ ነበሩ ፤ እነርሱ ብቻ እንዲ ተርፉ ይደረጉና ፤ በኋላ ወደ ንጉሡ በእስረኝነት ይወሰዳሉ ።”

“According to the historian Rufinus, the ship in which Frumentius, then a boy, was travelling, landed at a port, presumably under Ethiopian control, for provisions. But apparently due to a rift in political relations, the vessel was seized and the occupants slain. Frumentius and his companion Aedesius were lucky, as they alone were spared, and subsequently taken to the king as prisoners. [86]“

በእዚኽ ዘገባ እንደ እምናየው ፤ የመጀመሪያዎቹ አክሱማዊያን ፤ በቀይ ባሕር ላይ የእሚደረገውን ሐገራዊ እና ዓለም ዓቀፋዊ የንግድ እንቅስቃሴ ተቆጣጥሮ ሰላማዊነቱን በማረጋገጥ ራሳቸውን ተጠቃሚ ማድረግ የቆየ እና መሠረታዊ የሆነ የኢከነሚ ፍልስፍናቸው መሆኑን ሲያሳየን ፤ በአንድ አደጋ በእሚመስል እድል (A Blessing in disguise) ደግሞ ፤ በአንዱ ጉዳይ ከሮማ መንግሥት ጋር የነበራቸው ቅራኔ ፤ የሮም ግዛት ከነበረችው ጢሮስ (የዛሬዋ ሶርያ አከባቢ) ተነስቶ በቀይ ባሕር ላይ የእሚጓዘውን መርከብ ፤ አክሱማዊያን በሮማዊያን ላይ የጣሉትን ማዕቀብ የጣሰ በመሆኑ ፤ ለጥቃት ተዳርጎ ፤ ከጥቃቱ የተረፉት ልጆች ፤ ፍሬምናጦስ እና ኢድሲየስ የቤተ መንግሥት አገልጋይ ሆነው በምርኮ እንዲወሰዱ አድርጓል ።

በእዚኽ ኹኔታ የኢትዮጵያ ቤተመንግሥት ውስጥ በልጅነቱ የገባው ባለ ትልቅ አዕምሮ እና ጠባየ መልካሙ ፍሬምናጦስ ፤ ክርስትናን በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያ ቤተመንግሥት ውስጥ እንዲስፋፋ በማድረግ ፤ ኹኔታው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን መሥራች መንፈሳዊ አባት እንዲሆን አደረገው ።

ፍሬምናጦስ በእዚኽ መልኩ ምርኮኛ ሆኖ ፤ በንጉሡ ቤት ውስጥ ሲያገለግል በአሳየው ላቅ ያለ ጥበብ ፤ ከኢዛና አባት መሞት በኋላ ፤ ኢዛና ለአቅመ መንግሥት እስኪ ደርስ የቤተ መንግሥቱን ጉዳይ በአደራ ይመራ ስለ ነበር ፤ አብሮ አድጉን ኢዛናን ወደ ክርስትና ለማምጣት እና በኢትዮጵያ ውስጥ ቤተክርስቲያን ለመመሥረት እንዲችል አድርጎታል ። በእዚኽም ታሪካዊ ሥራው ፤ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ መጋቢ በኋላም ፤ በአሌክሳንደሪያው ጳጳስ አትናስያስ ሹመት የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጳጳስ ሆኖ ፤ ክሳቴብርኃን አባ ሰላማ (The Enlightener, father of peace) በእሚለው የሐገርኛ የማዕረግ ስም እንዲጠራ እድርጎታል ።

ይኽ አባ ሰላማን ወደ ኢትዮጵያ የአመጣው አጋጣሚ ፤ የወቅቱ የአክሱሙ መንግሥት ፤ የአከባቢውን የንግድ ልውውጥ ደህንነት ለማስጠበቅ እና ይኽንንም ግልጋሎት በማቅረቡ የእሚገባውን ጥቅም ለማረጋገጥ ፤ የዘመኑን የዓለማችንን ልዕለ ኃያላን ሮማዊዎችን እንኳን መገዳደር የእሚችል ፤ አቅም የነበረው መኾኑን ስለ እሚያሳይ ፤ በወቅቱ የአክሱሙ መንግሥት የአከባቢውን የንግድ መስመር የመጠበቅ እና በበላይነት ማስተዳደር ፤ የፖለቲካዊ እና የወታደራዊ መዋቅሩ ግንባታ ማጠንጠኛ ፤ ዋነኛ የኢከነሚ ፖሊሲው እንደ ነበር ያሳየናል ።

ይኽን መሰሉ ፥ የቀድሞው የአክሱም መንግሥት ወታደራዊ እና ኢከነሚያዊ ፍልስፍና ፤ እንደ ሌላው የመንግሥቱ ፍልስፍና ኹሉ ተከትሎት ሸዋም ስለ መጣ ፤ የሸዋው መንግሥት ፤ ለአረቦቹ ሱልጣን እንዲሆኑ እየፈቀደ ስልጣን ወይንም ከለላ የእሚሰጣቸው ፤ የወቅቱን የዓለም ዓቀፍ ንግድ ከተቆጣጠረው እስላማዊ አገዛዝ ጋር በአላቸው የቋንቋ ፣ የባህል እና የንግድ ቅርርብ ፤ የሐገሬውን ንግድ መስመር ከዓለም ዓቀፍ ንግድ መስመር ጋር እንዲያስተሳስሩለት እና በእዚኽም ንጉሡ ወይንም ስርወ መንግሥቱ የለመደውን በሰፊ የንግድ ገበያ ላይ የእሚኖረውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከአለው ልማዳዊ ፍላጎት ነው ።

ከላይ እንደ አልነው አረቦቹም በተራቸው ፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የአላቸው ታሪካዊ እና ተፈጥሮዋዊ ቁርኝት ፣ በሐገራቸው የአለውን የውስጥ ግጭት ሽሽት ፣ ኃይማኖታቸውን በኢትዮጵያ ውስጥ የማስፍፋት ፍላጎት ፣ በአረብነታቸው በወቅቱ የዓለምን ወሳኝ የየብስ እና የባሕር መንገድ በብቸኝነት ከተቆጣጠረው የሙስሊም እና የዓረብ ሰንሰለት ጋር የአላቸውን ልዩ ግንኙነት ወይንም ዝምድና በመጠቀም የኢትዮጵያን ገበያ ከወቅቱ የዓለም ዓቀፉ ገበያ ጋር ለማስተሳሰር የእሚያስችላቸው የላቀ እድል የአላቸው መሆኑ ፣ ወዘተ ፤ ለእነ እዚኽ የሙስሊም ሱልጣኔቶች ፤ ከሸዋ እስከ ሱማሊያዋ ወደብ ዘይላ በአለው የንግድ መስመር ላይ እንዲ መሠረቱ ምክንያት ሰአይሆን አልቀረም ።

የጋራ ጥቅም አስተሳሰብ ውስጡ አለው ።

የሙስሊም ሱልጣኔቶቹ ፤ ከሸዋ ተራሮች ግርጌ አንስቶ እንደ ዘይላ እስከ አሉት የቀይ ባሕር ወደቦች ድረስ ፤ በደቡባዊ ምሥራቅ ኢትዮጲያ የደረቅ ወደብ አገልግሎት በመስጠት ዓይነት ከሆነ የተመሠረቱት ወይንም የሱልጣኔቶቹ የህልውናቸው መሠረት ለሸዋ መንግሥት የእሚያቀርቡት የንግድ አገልግሎት እና ለእዚኽም የሸዋው መንግሥት የእሚሰጣቸው ከለላ ከሆነ ፤ በምንም መመዘኛ ፤ ተስፋፊው ሸዋ ሰለቀጣቸው የእሚለው ትንታኔ መሠረት ቢስ ነው ማለት ነው።

የሸዋው መንግሥት ፤ የሙስሊም ሱልጣኖቹን ፤ የውጭውን ንግድ እንዲያስተባብሩ እና ቴክኖልጂ እና ኃብት እንዲያቀርቡለት እንደ አቋቋመው ፤ ዳሞት የሆነው እናሪያን ደግሞ ፤ የሐገር ውስጥ የጥሬ እቃ (የእዛኽን ዘመን ጥሬ ዕቃ) እና የሰው ኃይል አቅርቦት ፤ እንዲመሩለት እንደ አደራጃቸው ነው የእሚመስለው ።

እንግዲኽ ፤ በእዚኽ የማሕበረ ኢከነሚ ፍልስፍናው ተመርቶ ፤ የአክሱሙ/ሸዋው መንግሥት እነ እዚኽን የንግድ መስመር ሰንሰሎቶችን በመፍጠር እና በማስተዳደር ፤ እጅግ ትልቅ ኃብት አካብቶ ፤ ይኽን ኃብቱን በመጠቀም ፤ ሸዋን የአፍሪካ ቀንድ የኢከነሚ እና የፖለቲካ ማዕከል አድርጓታል ፦

“አምደ ፅዮን ፥ አስገራሚ ኃብቱን ፤ ትልቁን ሠራዊቱን በመገንባት መላ ሐገሪቱን በአንድ ላይ አስተባብሮ በእርሱ ስር ማድረግ እንዲችል አስችሎታል ።”

“Amde-Siyon used his fabulous wealth in building his huge army and consolidating his power throughout the Empire [98].”

ከእዚኽም የተነሳ ፤ ለምሳሌ ፦ አምደ ፅዮን ፤ በየትኛውም የኢትዮጵያ (በመላው ምሥራቅ አፍሪካ ቢሆንም) ዘምቶ ፤ ሕዝቡን ከጥቃት መከላከል ፤ አፈንጋጮችን ማስገባት እና አከባቢውን ፤ ያለችግር አማክሎ ማስተዳደር ችሎ ነበር ። ለምሳሌ ፦ በእዛ ይኽ ነው የእሚባል መሠረተ ልማት በአልነበረበት ወቅት ፤ ከሸዋ ተነስቶ ፤ የኤርትራ ወደቦች ድረስ ዘምቶ ፤ ጠላት አባሮ መመለስ የእሚችልበት አቅም ነበረው ። ታደሰ ታምራት ፤ በእዚኽ ዘመን አምደ ጽዮን ስለ አደረገው ዘመቻ ከእሚዘግበው የአምደ ጽዮን ዜና መዋዕል ላይ ይኽን ይጠቅስልናል ፦

“እኔ አምደ ፅዮን ወደ ኤርትራ ባሕር ኼድሁ ። እዛኽም ከደረስኩ በኋላ በዝሆን ላይ ተቀምጬ ወደ ባህሩ ዘለቅኹ ። ጦር እና ቀስቴን ይዤ ጠላቶቼን ገደልኹ ፤ ሕዝቤንም ታደግኹ ።”

“I, King Amde-siyon, went to the sea of Eritrea. When I reached there I mounted on an elephant and entered the sea. I tool up my arrow and spears, killed my enemies, and saved my people. [98]“

የሸዋው መንግሥት በእዚኽ ኹኔታ ፤ እርሱን ተከትለው የመጡ የደቡብ ምሥራቅ እና የደቡብ ምዕራብ መንግሥታት መዓከል አድርጎ በማደላድሉ እና በማደራጀቱ ፤ የከባቢው ጠንካራ ኃይል መሆኑን አሳይቷል ። ይኽም ብቻ ሰአይሆን ፥ ተቋም የመፍጠር አቅሙንም አሳይቷል ። በአምደ ፅዮን ዘመን ፤ የመንግሥቱ አቅም እና ሥራው በመብዛቱ ፤ በእዛኽ ዘመን በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ወደ 15 ክፍል (ዲፓርትመንት) አቋቁሞ ፤ ጠንካራ የአስፈፃሚ አካል ፈጥሯል ።

እንደ እሚታወቀው አሜሪካኖቹ መንግሥታቸውን በዲፓርትመንት ሲያዋቅሩ ፤ አውሮፓዊያን በሚንስተር መሥሪያ ቤት ያዋቅራሉ ፤ የእኛም ሐገር መንግሥት ወደ ዘመናዊ መንግሥት ሲመጣ የአውሮፓን መንግሥት በምሳሌነት በመውሰድ ስለ ሆነ ፤ ሚንስተር እና ካቢኔ የእሚለው የመንግሥት አወቃቀር ነው ለዘመናዊው ኢትዮጵያዊ ቅርብ የሆነው ፤ ስለ እዚኽ ፦ አምደ ፅዮን ክፍል (ቤት) የአላቸው ምንም እንኳን ቃል በቃል ትርጓሜ ከአውሮፓዊያኖቹ ምኒስተር መሥሪያ ቤት ይልቅ ለአሜሪካኖቹ ዲፓርትመንት ፅንሰ ኃሳብ ቢቀርቡም ፤ ለዘመናዊ ኢትዮጵያዊ በእሚቀለው አገላለፅ ፤ ዓምደ ፅዮን ሚንስተር መሥሪያ ቤቶች እና ተጠሪነታቸው ለእርሱ የሆኑ እነ እዚኽን ሚንስተር መሥሪያቤቶች የእሚመሩ ሰዎች የያዘ የሚንስትሮች ካቢኔ አቋቁሞ ነበር ማለት እንችላለን ። ስለ እዚኽ የአምደ ጽዮን መንግሥት አወቃቀር ፤ ታደሰ ታምራት እንደ እዚኽ ይላል ፦

“ … የእየ ራሳቸው የሥራ ድርሻ የአላቸው … በአሥራ አምስት ቤቶች የተዋቀረው … የንጉሡ ግቢ ከአውራጃ አውራጃ ፤ ስፍራ በእየ ግዜው ይቀይር ነበር ።”

“...Organised in...fifteen ‘houses’ each of which had its own special responsibility....The court itself appears to have been continuously moving from one province to another. [98]“

እነ እዚኽ ቤቶች ፤ የእየ ራሳቸው የሥራ ድርሻ ፣ የእየ ራሳቸው ዋና ኃላፊ እና ምክትል የአላቸው ሆነው ፦ የግምጃ ቤት አስተዳደር ፣ መንግሥታዊ ፕሮቶኮል አጠባባቅ ፣ የወታደራዊ ትጥቅ እና ፈረሶች አስተዳደር ፣ ወዘተ ፤ ጋር የተያያዘ ሥራ የአላቸው ናቸው ፦

“በእያንዳንዱ ‘ቤት’ ላይ ፤ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በተመለከተ ቀጥታ ለንጉሡ ተጠሪ የሆኑ ፤ ኃላፊ እና የኃላፊው ረዳት ይሾማሉ ።”

“At the head of ‘each’ house were appointed a chief and an assistant chief who were directly answerable to the king for carrying out the specific responsibility assigned to their house. [98]“

ስለ እዚኽ ፤ በእየ ግዜው እየተራቀቀ መኼድ ቢቀረው እንጂ ፥ የሸዋ መንግሥት በአምደ ፅዮን ዘመን የነበረው አደረጃጀት ፤ በይዘቱ ከዘመናዊ መንግሥት አይተናነስም ነበር ።

ከእዚኽ በተጨማሪ ፤ የወቅቱን የሸዋውን የመንግሥት አደረጃጀት ውስብስብነት ፤ ለማሳየት ሊጠቀስ የእሚችለው ሌላው ፤ እንደ ቄስ አልቫሬዝ ዘገባ ፤ በ16ኛው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ አከባቢ ፤ በንጉሥ ልብነ ድንግል ዘመን (ከዓምደ ፅዮን ንግሥና ወደ 150 ዓመታት በኋላ) በቤተ መንግሥቱ ዙሪያ 200 ሺ ሰው ይሰፍር የነበረ መሆኑ ነው ። ይኽም ማለት ፤ በዘመናዊ ኢትዮጵያ ከአብዛኛው ከተሞች በላይ ሰዎች በዙሪያው ይሰፍሩ ነበር ማለት ነው ።

ይኽም በመሆኑ ፤ ንጉሡ በእሚሰፍርበት ቦታ ፤ የአለው ፖለቲካ ፣ ተራ ሌብነት ፣ ንግድ ፣ የሕግ ማስከበር ፣ ዳኝነት ፣ ወዘተ ፤ በአንድ ሜትሮፖሊታን ውስጥ ከእሚታይ ውስብስብ ማሕበራዊ ክስተት ጋር ተመጣጣኝነት የአለው አስገራሚ የታሪክ ትዕይንት መዓከል ጋር ያመሳስለዋል ፥ ወይንም የመጽሐፍ ቅዱሱን ታሪኩ ለእሚያውቁ ሰዎች ፤ በእዚኽ የታሪክ ክፍል ላይ የነበረው የሸዋው መንግሥት አሰፋፈር ፣ እንቅስቃሴ እና ኹናቴ ፤ የእሥራኤል ልጆች ፤ ሙሴ ከግብፅ ምድር አውጥቶ በምድረበዳ እየመራቸው በነበሩበት ወቅት ፤ የኖሩበትን ኹኔታ ነው የእሚመስለው ።

ለምሳሌ ፦ ሰፈራው አከባቢ መቀየር ወይንም መንቀሳቀስ ሲፈልግ ፤ በመላው ሰፈር ውስጥ ‘ንጉሥ ኼደ! ንጉሥ ኼደ!’ ፤ የእሚል ጩኸት በመንድሩ ይስተጋባል ፤ ከእዚያኽ ሙሉ መንደሩ ድንኳኑን ነቅሎ ፤ ቀድሞ የተነሳውን የንጉሡ ነጭ ድንኳን እየተከተለ ፤ ይኽ የንጉሥ ነጭ ድንኳን በመድረሻው ቦታ ላይ እስኪ ተከል ይጓዛል ። ኹኔታውን አልቫሬዝ እንደ እዚኽ ገልፆታል ፦

“ከንጉሡ ጋር ሰፈር በቀየረ ቁጥር አብረው የእሚጓዙት ሰዎች ቁጥር ለማመን የእሚያስቸግር ነው … በጉዞዋቸውም በጣም ብዙ እና ጥቅጥቅ የአሉ በመሆናቸው የአንድ ትልቅ ከተማ ለንግሥ በዓል የወጣ ሕዝብ ሆነው ፤ በአደባባዩ ብቻ ሰአይሆን የከተማው እያንዳንዱ መንገድ በሰው ግጥም የአለበት ነው የእሚመስለው ። ሕዝቡም እንዲኽ ዓይነት ነው ፤ ከአስር አንድ እጁ ጥሩ የለበሱ ናቸው ፤ ከአስር ዘጠኝ እጁ ተርታው ሕዝብ ነው ፥ ወንድም ሴትም ፥ ወጣትም ፥ ድኃውም … ኃብታሙም ድንኳናቸውን ይዘው ነው የእሚጓዙት ። አብረው ስለ እሚጓዙት ትልልቅ ጌቶች እና መኳንንቶች እያልኩ አይደለም ፤ ምክንያቱም ፦ እነ እዚኽ ራሳቸው ፤ ለመቁጠር የእሚያታክት መናገሻ ከተማ ወይንም መልሰተኛ የድንኳን ከተማ ፣ ብዙ ጭነት ፣ በቅሎ ጫኝ ይዘው ነው የእሚንቀሳቀሱት ። በእግር አብረው ስለ እሚጓዙት ምን ማለት እንደ እምችል አላውቅም ። እኛ ፖርቹጋሎች እና ፍራንኮች ስለ በቅሎዎቹ ብዛት ኹል ግዜ ስለ እምናወራ … የንጉሡ ጓዝ ከኃምሳ ሺ በቅሎ በታች ሊጫን አይችልም ፤ ከፍ ሲልም መቶ ሺ በቅሎ ይደርሳል ።…ፈረስ ብዙ አይደለም ፤ ጫማ ስለ እማያደርጉላቸው ፈረሶቹ ይቆስላሉ ።… ንጉሡ ረዥም ከሆነ የእሚጓዘው ፤ የተለቀቀው ሰፈር ቆስለው በተተው ፈረሶች ይሞላል ፤ ከእዛኽ በፈለጉ ግዜ መጥተው ፈረሶቹን ይወስዱዋቸዋል ።

ቀሲስ ዮሐንስ ብዙ ግዜ ቀጥ ያለ መንገድ አይኼድም ፤ ወዴትም እንደ እሚኼድ ማንም አያውቅም ። ይኽ ኹሉ ሕዝብ ፤ ዝም ብለው አንድ ነጭ የተተከለ ድንኳን እስኪ ያዩ ይከተሉና ፤ ድንኳኑን ከዓዩ ፤ ኹሉም በእየተመደበላቸው ስፍራ ይሰፍራሉ ። … ወደ 13 የእሚሆኑ ቤተክርስቲያናት አብረው ከንጉሡ ጋር ይጓዛሉ ።”

“The people who continually go on the road with the Court is a thing scarcely credible: …, and the people are so many and so close together that they look like a procession of Corpus Domini in a great city, without diminution in any part of the road. The people are of this kind; the tenth part of them may be well-dressed people, and the nine parts common people, both men and women, young people, and poor, ... The rich bring very good tents. I do not speak of the great lords and great gentlemen, because each of these moves a city or a good town of tents, and loads, and muleteers, a matter without number or reckoning. I do not know what to say of those on foot. We Portuguese and the Franks often talked of these mules, because in the winter that is coming, as is reported, for many lords go to pass the winter at their lands, the Court cannot move with less than fifty thousand mules, and from that upwards, the number may reach a hundred thousand. There are very few horses, and the led mules are twice or thrice as many as the others, these are not reckoned in the number of mules. Of the horses many are very handsome, and as they are not shod, they soon founder, so they do not travel upon them: neither do I reckon these, therefore I say very few horses. If the Prester travels far, the villages remain full of foundered horses, and afterwards they take them away at leisure. I do not reckon the mules with packs the male mules serve as well for the saddle as the female; they serve in one manner only, those that are saddle mules for the saddle, and the pack mules for packs. There are also a quantity of ponies’ for packs, but they founder like the horses. There are many asses which serve better than the ponies, and many pack oxen, and in many districts camels which carry large loads, these in the flat lands.

Prester John rarely travels in a straight direction, nor does anyone know where he is going. This multitude of people travels along the road until they find a white tent pitched, and there they settle down each in their own places. Frequently Prester John does not come to this tent, but sleeps in the monasteries and large churches which are in the country. In the tent which is thus pitched they do not neglect to make solemn observances of instrumental music and chaunts, yet not so perfect as when the lord is there: moreover, the churches always travel with the Court, and there are thirteen of them [101].”

የሸዋውን መንግሥት የመዋቅር ውስብስብነት እና የእሚያንቀሳቅስውን ኃብት መጠን ለማሳየት ፤ ይኽንን እግረ መንገድ ጠቀስኩት እንጂ ፤ የንጉሡ ሰፈር በራሱ ብዙ ሊባልለት የእሚችለው ነገር የአለው ነው ። በእዚኽ መልኩ በእዚያኽን ዘመን በምደረ አፍሪካ የተዋቀረ መንግሥት ፥ የአከባቢው ከፍተኛ ኃይል ቢሆን ብዙም አያስገርምም ።

ሸዋ የገባው አክሱማዊው መንግሥት ፤ በእዚኽ መልኩ ‘ህቡዕ’ ገብቶ ራሱን ሲያደራጅ ቆይቶ ወይንም ሸዋን የአክሱሙ አዲሱ ማዕከል አድርጎ እና ሸዋንም ፤ የእነዚኽ ከእርሱ በስተደቡብ የተነሱት ንዑስ ማዕከላት የጋራ ማዕከል በማድረጉ በአገኘው ወይንም በገነባው ወታደራዊ እና ኢከነሚያዊ ሚዛን የበላይነት ፣ የአለውን የታሪካ­ዊ ተቀባይነት ፣ የቤተክርስቲያን ድጋፍ ፣ ወዘተ ፤ አስተባብሮ ፤ በስተመጨረሻ ፤ ቤተክርስቲያንን ሲሶ መንግሥት ለማድረግ ተስማምተው ፤ በኹለቱ ታላላቅ ሐገራዊ መንፈሳዊ መሪዎች ፤ በአቡነ ተክለ ኃይማኖት እና በእየሱስ ሞዓ እገዛ ፤ ዛግዌ ገባር ሊሆን ይኩኖ አምላክ የሰለሞናዊውን ስርወ መንግሥት ወክሎ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ ሊሆን ተስማምተው ፤ ከእላይ እንደ አልነው በሸዋ ሆነው ኢትዮጵያን ሊገዙ መልሰው በትረ ስልጣኑን ተረክበዋል ።

እንደ ሰርጌው ሐብለ ሥላሴ ፤ ሸዋዎቹ ደቡብ ምዕራቡንም ምሥራቁንም አደርጅተው አቅም ስለ ገነቡ ፤ ይኽን አቅማቸውን ከድርድር ጋር አጣምረው ነው ፤ ያለ ደም መፋሰስ ፤ የሰለሞኑ ስርወ መንግሥት በትረ ስልጣኑን ከዛግዌው ስርወ መንግሥት በመረከብ ፤ እ.አ.አ. በ1270 ዓ.ም. ይኩኖ አምላክ ንጉሠ ነገሥት የሆነው ብሎ ይገምታል ።

የሸዋው መንግሥት በእዚኽ መልኩ ፤ የደቡቦቹን መንግሥታት አስተባብሮ እና ሌሎች ፖለቲካዊ መሳሪያዎቹን ተጠቅሞ ፤ ወደ ኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትነት መንበረ ስልጣን ራሱን በድጋሚ ከአመጣ በኋላ ፤ በተለያየ ምክንያት ፤ ከእነ እዚኽ ክልላዊ መንግሥታት ጋር ይገባ የነበረውን ግጭት ፤ እንደ ‘ጥሩ’ አጋጣሚ በመጠቀም ፤ የእነ እዚኽን ክልላዊ መንግሥታት ፤ በእሚመቸው መልኩ በማዋቀር ወይንም በመንግሥታቱ ላይ የእርሱ ታማኝ የሆኑ ሰዎችን በመሾም ፤ መላ ሐገሪቱ ላይ የነበረውን ፖለቲካዊ ስልጣን አጠናክሯል ።

ስለ እዚኽ ፥ የሸዋው መንግሥት ወደ ስልጣን ዳግም ከመጣ በኋላ በ60 ዓመታት ውስጥ ፤ ወይንም በአምደ ፅዮን ዘመን ፤ በተለይ እ.አ.አ. ከ1332 ዓ.ም. በኋላ ፥ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ክልል ፥ የእኔ ነው በማለት ሰአይሆን ፤ አስተዳደራዊ ተቋም የተገነባባቸው ፣ አስተዳደሩን የእሚያገለግል የመንግሥት ጦር የሰፈረበት ፤ የኢትዮጵያ ሕጋዊ ግዛት አድርጎ አዋቅሮ ጨርሶ ፤ ከእዚያኽም 200 ዓመታት በኋላ መጥቶ በተለይ በሸዋው መንግሥት እና በጠቅላላውም በመላው ኢትዮጵያ ትልቅ ውድመት እስከ አደረሰው የግራኝ ወረራ ድረስ ፤ የሸዋው መንግሥት ፤ ከሰፈረበት ከሸዋ ሆኖ ያለ ምንም ተቀናቃኝ የኢትዮጵያ መሪ ሆኖ ነበር ።

በእዚኽም ፤ በሰፊዋ እና ከፍተኛ የመሠረት ልማት እጥረት በነበረባት ከ13ኛው እስከ 15ኛው ምዕተ ዓመት በነበረችው ኢትዮጵያ ፤ ከኤርትራ እስከ ባሊ ፣ ከእናሪያ እስከ በርበራ የአለውን አከባቢ ሕዝብ ፤ በአንድ ፖለቲካዊ ኢከነሚያው ማሕበረሰብነት ማስተሰሳሰር በመቻላቸው ፤ የወቅቱ የሸዋ ነገሥታት ፤ ምንም ጥርጥር በእማያስፈልገው ኹኔታ ፥ ጥንቅቅ ያለ ሐገር የመገንባት የፖለቲካ ግንዛቤ የአላቸው ፤ የተዋጣላቸው አጼዎች (ሐገር አናጺዎች) የሆኑ ስለ መሆናቸው ፤ ትልቅ ማሳያ ነው ።

ከላይ እንደ አልነው ፤ የሸዋው መንግሥት በእዚኽ መልኩ ራሱን አጠናክሮ እና ሸዋን የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ መዓከል በማድረግ ዛሬ የእምናውቃትን ኢትዮጵያ ከአደረጀ በኋላ ፤ በደቡብ ምሥራቅ እና በደቡብ ምዕራብ የነበሩት መንግሥታት ፤ ከስመው የአዲስቱ የኢትዮጵያ አወቃቀር አካል እንዲሆኑ ተደርገዋል ።

በእዚኽ ንዑስ ክፍል ደጋግመን እንደ አነሳነው ፤ እነ እዚኽ መንግሥታት የአዲስቱ የኢትዮጵያ አወቃቀር አካል የሆኑበት መንገድ ፤ ተስፋፊው የሸዋ መንግሥት ሆን ብሎ ስለ ጨፈለቃቸው ነው የእሚል ትንታኔ በተለያዩ ሰዎች የእሚቀርብ ቢሆንም ፤ ከላይ በአጭሩ ለማለት እንደ ሞከርኩት እነ እዚኽ መንግሥታት ፤ መነሻቸው ራሱ የሸዋ መንግሥት ከመሆኑ በአሻገር ፤ በራሳቸው ምክንያት የእሚያጭሩት ጠብ ፤ በፖለቲካውም ሆነ በወታደሩም መስክ ከእነርሱ የተሻለውን የሸዋውን መንግሥት ፤ ይኽን ኃይሉን ተጠቅሞ በመላ እንዲቆጣጠራቸው እንደ አመቻቸለት ነው የዘመኑ ታሪክ የእሚያሳየው ።

ወደ ሰባት ይሆኑ ከነበሩት የሙስሊም ሱልጣኔቶች ኹሉ ቀዳሚ ፣ ትልቅ እና ጠንካራ የነበረውን የኢፋት ሱልጣኔት ብንወስደው ፥ ከሸዋ ነገሥታት ጋር የያዘው ግጭት መጀመሪያ አንዱ ምክንያት ፤ የንጉሡ ነጋዴ የነበረ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ፥ ከእነ ቅፍለቱ በሙስሊም ስልጣኔቶቹ መታገቱ ነው ።

ታደሰ ታምራት ፥ ከእዚኽ የእገታ ድራማ በስተጀርባ ፤ እኛ እያለን እንዴት ሌላ ሰው ታስነግዳለህ የእሚል ጉምግምታ መፈጠሩ ፤ ሊሆን እንደ እሚችል ግምቱን ያስቀምጣል ፦

“ነጋዴዎቹ (የንጉሡ) ራሳቸው ሙስሊም ስለ እሚሆኑ ፥ ክስተቱ እነ እዚኽ የንጉሡ ወኪሎች የእሚያገኙት ዳጎስ ያለ ትርፍ ያጫረው ቅናት እንደ እሚሆን ግልፅ ነው ።”

“These merchants were most probably muslims themselves, and the incident was clear case of jealousy..of large profits which these royal agents were doubtless making [98]“

የወቅቱ ታሪካዊ ድባብም ፤ እነ እዚኽ በዋናነት እንደ ደረቅ ወደብ ተመስርተው በዋና የንግድ እቃ አስተላላፊነት በእሚገኘው ገቢ የኢከነሚ ህልውናቸው የተመሠረተ ሱልጣኔቶች ፤ የሸዋው መንግሥት የእሚያደርገው ማንኛውም ተለዋጭ የንግድ አማራጭ ሊያበሳጫቸው እና ወደ መሰል ጠብ አጫሪነት ሊመራቸው እንደ እሚችል ግልጽ ነው ።

ያልተጻፈ የንግድ ስምምነት በመካከላቸው ቢኖርም እንኳን ፤ የንግዱ ዓለም መርህ የተሻለውን አትራፊ መንገድ መፈለግ ስለ ሆነ ፤ የሸዋው መንግሥት ለምን ሌሎች አማራጭ ሊፈልግ እንደ እሚችል እና ይኽም የመተካት ስጋት ሱልጣኔቶቹን ለጠብ ሊያነሳሳቸው እንደ እሚችል መገመት ቢቻልም ቅሉ ፤ የሙስሊም ሱልጣኖቹ በእዚኽ ምክንያት ጠብ ማንሳታቸው ግን ተገቢ ወይንም ብቸኛ እና ተገቢ አማራጭ ነበር ማለት ግን አይቻልም።

ከእኛ ውጭ እንዴት ሌላ ሰው የንጉሡ የንግድ አጋር ይሆናል ከእሚለው በአሻገርም ፤ የሙስሊም ሱልጣኔቶቹ የአላቸውን ብቸኛ የንግድ አስተላላፊነት ሥራ ወደ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ለመቀየር ጅኃድን ማስፈራሪያ ለማድረግ የእሚሞክሩበት አካኼድ ሌላ ግጭቱን አባባሽ ምክንያት እንደ ነበርም ይታያል።

ታደሰ ታምራት ፤ ስለ እዚኽ ጉዳይ እንደ እዚኽ ይላል ፦

“…የሙስሊም መሪዎቹ ፥ ዋና ዋናዎቹ የንግድ መስመር የእሚያልፍበት አከባቢ አለቆች ነበሩ ። ይኽ የክርስቲያኑ መንግሥት በሙስሊሞች አገልግሎት እና መልካም ፈቃድ ላይ የአለው ተደጋፊነት ፥ በተለይ ግንኙነት በእሚሻክርበት ወቅት ለፖለቲካ ዓላማ ሊውል ይችላል ። ይኽም ኹኔታ ይመስላል ፤ በአምደ ፅዮን እና በኢፋቱ መሪ መካከል ጦር አማዛዥ የቅርብ ምክንያት የሆነው ።”

“...Muslim rulers were masters of the areas through which the main trade routes passed. This technical dependence of the Christians on the service and goodwill of the Muslims was easily liable to be used for political purposes especially in times of hostile relations. This appears to be the immediate reasom which sparked off the first major military encounter between Amde Siyon and the ruler of Ifat. [98]“

በአጠቃላይ ፤ የኢትዮጲያ ብቸኛ የንግድ አስተላላፊ ሆነው ፤ ለረዥም ዘመን የቆዩ የተወሰኑ የሙስሊም ሱልጣኔቶች ፤ የአላቸውን ብቸኛ የንግድ አስተላላፊነት የእሚሰጣቸውን ተጽኖ ያለ አግባብ መጠቀማቸው ፤ የሸዋውን መንግሥት ሌሎች የንግድ አጋር ፥ ምንም እንኳን አዲሶቹ የንግድ አጋሮች ራሳቸው ሙስሊሞች ቢሆኑም ፤ እንዲ ፈልግ ማድረጉ ፤ ነባራዊውዎቹን ሱልጣኔቶች በአንድ በኩል ከእኛ ውጭ አማራጭ የለኽም የእሚለው እብሪታቸው በሌላ በኩል በሌላ ሙስሊም የመተካት አደጋው የእሚፈጥርባቸው ስጋት ፤ ከኃይማኖታዊ አክራሪነታቸው ጋር ተዳብሎ ፤ ልክ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ የዖሮሞ ወረራ ከእነርሱ ወስዶ በእሚመስል አኳኋን የተከተለውን እቅድ ፤ እያንሰራራ በአለ፟ው የሸዋ መንግሥት ላይ በመተግበር ፤ በጅኃድ ኢትዮጵያን ለማስለም ሲንቀሳቀሱ እንጂ የሸዋው መንግሥት ለመስፋፋት ከአለው ጉግት ሲውጣቸው አይደለም የእሚታየው ።

በራሱ እና ለራሱ ጥቅም የተቋቋሙ ከባቢያዊ መንግሥታት ፤ የተቋቋሙበት ምክንያት ሳይነጥፍ ሰይፍ የእሚያስመዝዝ ምክንያትም የለም ።

ለምሳሌ ፦ ከእነዚኽ በአንዱ ግጭት ፤ የኢፋቱ ሱልጣን ፤ ከአምደፅዮን ጋር ሊዋጋ ሲመጣ ፥ ግዜያዊ ግጭት ሰአይሆን ፤ መላው ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር አስቦ ሲንቀሳቀስ ይታያል ፦

“…ከድል በኋላ የክርስቲያኑን ግዛት ላይ የእሚሾሙ የሙስሊም ገዥዎች አጨ ፤ …አንጎት (ወሎ) …አምሐራ…ሸዋ ።“

“...nominate his own Muslim governors’ foe all the provinces of the Christian Kingdom....Angot (Welo), ... Amhara, ... Shewa. [98]“

ይኽም ማለት ፤ ጦርነቱ የእሚያስተባብረው ሱልጣን ፤ ጦርነቱን የእሚያስተባብርበት አግባብ ፤ መላው የክርስቲያኑን ሐገር ተቆጣጥሮ ፤ በእያንዳንዱ የክርስቲያን ግዛት ላይ የእሚሾማቸውን ሰዎች አዘጋጅቶ ፤ የመኼድ በመሆኑ ፤ ይኽ አካኼድ ፤ የተጠቂ ወይንም የተከላካይ አካኼድ ሰአይሆን ፤ የወራሪ አካኼድ ያስመስለዋል ።

ይኽም በመሆኑ ወይንም እነ እዚኽን የወቅቱን ታሪካዊ ኩነቶች ስናይ ፤ የሸዋው መንግሥት በግጭቱ መጀመሪያ ላይ የስረዓት አልበኝነት ተከላካይ እንጂ ተስፋፊ ወይንም ጠብ ፈላጊ አይመስልም ።

የዖሮሞ ሕዝብ ከግራኝ ወረራ መክሸፍ በኋላ ፤ ከዛሬው ሶማሊያ ተነስቶ ፤ ወሎ ፣ ቱልማ እና ሜጫ የእሚባሉትን ነገዶቹን በእጣ አከፋፍሎ የክርስቲያን ኢትዮጵያ ግዛት ፤ ሸዋ (ቱለማ) ፣ ወደ አምሐራ ሳይንት ወይንም አንጎት (ወሎ) ፣ ወደ ቀድሞ ዳሞት የዛሬ ወለጋ (ሜጫ[2]) ፣ ወዘተ ፤ ብሎ ሰርጎ የገባበት አካኼድ ፤ ይኽንን በአምደ ጽዮን ዘመን ፤ የሙስሊም ሱልጣኔቶቹ ተሸንፈው የከሸፈባቸውን እቅድ እንደ ገና ትንሳኤ በመስጠት ፤ መሆኑ ከእቅዶቹ መመሳል ይታያል ።

ይልማ ደሬሳ ፤ ስለ እዚኽ የዖሮሞ መስረግ ቅርፅ ዝርዝር እንዲኽ ይላሉ ፦

“ … የስደቱ አመራር በእጣ እንዲወሰን ተስማሙ ። ከሦሥቱ ነገዶች መካከል አንዱ ፤ ከአዋሽ በስተሰሜን በእሚገኘው አገር ላይ እንዲቀር ፤ ኹለቱ ነገዶች በስተ ሰሜን ምሥራቅ እና ከአዋሽ በስተ ምዕራብ ወደ እሚገኘው አገር እንዲሰደዱ ተወሰነ ። … እጣው ከአዋሽ በላይ የእሚገኘው አገር ለቱልማ ነገድ ሰጣቸው ። … ለሜጫ ነገድ ዕጣ የሰጣቸው ፤ ከአዋሽ በስተደቡብ እና በስተ ምዕራብ የነበረውን አገር ስለ ሆነ ፤ ሜጫዎች አዋሽን ተሻግረው ወደ ምዕራብ መጓዝ ጀመሩ ። … ። ሜጫዎች አዋሽን ተሻግረው ወረራ ከመጀመራቸው ቀድሞ ፤ በአባይ እና በግቤ ወንዞች መካከል የእሚገኘው አገር ለኹለት ታላላቅ ግዛቶች ተከፍለው የቆዩ ናቸው ። እነ እዚኽም ግዛቶች ዳሞት እና ቢዛሞ ይባሉ ነበር ። በዚያን ዘመን ፤ ዳሞት የተባለው አውራጃ ፤ በአባይ እና በአዋሽ መካከል የእሚገኘው ሐገር ነው ። ቢዛሞ ፤ ዛሬ ወለጋ የተባለው ጠቅላይ ግዛት የእሚገኝበት ምድር ነው ። … የወሎ ነገድ ግን የደረሰው እጣ ፤ በስተ ምሥራቅ ሰሜን የአለው አገር ስለ ነበረ ፤ ያማራውን ሐገር አቋርጦ ለመዝመት ቀላል ሆኖ አላገኘውም ። ስለ እዚኽ ፤ ከዝቋላ አቅራቢያ ፤ ወደ ቆላው ሐገር ላይ ከገሰገሰ በኋላ ፤ በይፋት በስተ ምዕራብ አድርጎ ወደ ሰሜን በመጓዝ ከቆላው እንደ ገና ወደ ግራ ተመልሶ ፤ አንጎት የተባለውን የታወቀ የንጉሠ ነገሥት ግዛት ወሮ ያዘ ። [102]”

ይኽ በይልማ ደሬሳ ፤ በዝርዝር የተቀመጠ የዖሮሞ ወረራ አካኼድ ፤ ላይ ታደሰ ታምራት ፤ የአዳሉ ሱልጣን አምደ ፅዮንን ሊወጋ ሲመጣ ፤ ይዞት ከመጣው እቅድ ጋር የአለውን ተመሳሳይነት እና የወረራው እቅድ በሐገሪቱ መልከዓ ምድር እውቀት የበሰለ መሆኑን ላስተዋለ ሰው ፤ የዖሮሞው መስረግ የቆየው እና የከሸፈው የሙስሊም ሱልጣኔቶቹ ወረራ እቅድ ጥራዝ ቁጥር ኹለት መሆኑን ሊረዳ ይችላል ።

ሊውስ የተባለ ተመራማሪ የዛሬው የሱማሌ ሕዝብ ከ10ኛው ምዕተ ዓመት በኋላ የዛሬው ሱማሊያን ወሮ መኖሪያው እንዴት እንደ አደረገ በእሚተርከው ጽኹፉ ላይ ፤ ከሱማሌ ሕዝብ ጋር ከፍተኛ ታሪካዊ ቁርኝት የአለው የኦሮሞ ሕዝብ መጀመሪያ በእዛው በሱማሊያ በኋላም ከግራኝ ወረራ በኋላ በኢትዮጲያ እንዴት እንደ ተሰራጨ ሲገልጽ ፤ በእነ እዚኽ ኹለቱ ሕዝብ በአከባቢው ለአደረጉት ስርጭት ፤ የሶማሌ ጎሳ ለእሚባሉት መሪዎች የሆኑት በሱማሌዎች መካከል ሰፍረው ራሳቸውን ሱልጣን የአደረጉት አረቦች የአላቸውን ወሳኝ ሚና እንደ እዚኽ ይገልጸዋል ፦

“በስተመጨረሻ አብዛኛዎቹን የቀድሞዎቹን የዘንጊ ሕዝብ ከአፈናቀለው እና ዛሬ በሶማሊላንድ እና በኢትዮጲያ ውስጥ የአሰራጫቸውን የእነ እዚኽ የካም ሕዝብ ስብጥር ከማየታችን በፊት በሶማሊያ የባሕር ጠረፍ ላይ የነበሩትን የአረብ ሰፈራዎች በተወሰነ ደረጃ መቃኘት ተገቢ ነው። ምክንያቱም፦ አረቦቹ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ፤ ምንም እንኳን ተጽኖውን በተወሰነ ደረጃ ቢገድብበትም እንኳን በዘላኑ አከባቢ ሳይቀር እንዲዳረስ የአደረገው የበለጠ የተማከለ አስተዳደር ፤ ከእዚኽም በላይ አብሲንያን በ16ኛው ምዕተ ዓመት በተበታተኑ እና አንድነት በሌላቸው ዘላን ጎሳዎች ለመውረር የአስቻለውን የአንድነት ምክንያት የሆነውን እስልምና የአስተዋወቀ በመሆኑ። በተዘዋዋሪ እንዲያውም በቀጥታ ሊሆን ይችላል አረቦችን በውስጡ ማስገባቱ የሱማሌ እና የጋላ ሕዝብ ዛሬ ለያዘው ስርጭት መነሻ ምክንያት ነው።”

“Before following the great Hamitic advance south which displaced much of this earlier Zengi population, and led eventually to the present distribution of peoples in Somaliland and in part to those in Ethiopia, it is necessary to refer briefly to the early phases of Arab settlement on the Somali coast. This is essential since Arab colonization introduced a more diversified technological culture; a more centralized system of government which, however restricted its influence, nevertheless made itself felt even in nomadic areas; and finally and most importantly brought Islam, they unifying force which played such an important part in the conquest of Abyssinia by scattered and disunited nomads in the sixteenth century. And indirectly if not directly the absorption of Arabian settlers stimulated the movements of expansion of the Somali and Galla. [100]”

ለእዚኽም ነው ፤ የዖሮሞ ወደ ኢትዮጵያ መስረግ እና ዖሮሞ ሕዝብ ይኽን ወደ ኢትዮጵያ የመስረግ እንቅስቃሴ ሊፈፅም በተነሳበት ግዜ የተዋወቀውን ፤ ልክ አንጎት የተባለውን የንጉሡን ግዛት ‘ወሎ’ ብሎ እንደ ሰየመው ዓይነት በመላ ኢትዮጵያ ፤ በእየደረስበት ቦታ ያሉ ቦታዎችን ስም የእሚቀይር እና የአከባቢውን ነዋሪዎች በጉዲፈቻ በእሚባለው ስረዓት የትውልድ ሐረጋቸውን እየቀየረ ፤ የትውልድ እና ታሪካዊ ማንነታቸውን በማጥፋት የእሚውጠውን ስረዓት ፤ ይዞ የመጣው ፤ አጋጣሚ በሆነ የዖሮሞ ሕዝብ ታሪካዊ እድገት ሰአይሆን ፤ በወቅቱ የነበረውን የዖሮሞን ሕዝብ ፤ በፀረ ኢትዮጵያ ቅኝት ቃኝቶ ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ህልውና ማክሰም ግባቸው ያደረጉ የፀረ ኢትዮጵያዊያን የወቅቱ የሙስሊም ሱልጣኖች የቆየ ግብ አካል የእሚያስመስለው ።

ዖሮሞው ፤ የሙስሊም ሱልጣኔቶችን እቅድ ፤ እንዴት ሊወርስ ይችላል ቢባል ፤ የሙስሊም ሱልጣኔቶቹ ፤ በእዚኽ አከባቢ መሐበራዊ መሠረት ስለ አልነበራቸው ፤ ረዥም ዘመን በቆየው ግጭት በተባባሰው የክርስቲያን ኢትዮጵያ ጥላቻቸው ፤ በሌላ ሕዝባዊ ‘ቅጥረኛ’ ተጭነው ፤ ክርስቲያን ኢትዮጵያን ማውደም የተለመደ አካኼዳቸው በመሆኑ ነው ።

ከዖሮሞም መስረግ በፊት ፤ የሙሲልም ሱልጣኔቶቹ ፤ በክርስቲያኑ ላይ የእሚያዘምቱት ፤ የአከባቢውን ሰው መሆኑ የታወቀ ነው ። ታደሰ ታምራት ፤ ከሙስሊም ሱልጣኔቶቹ ጋር የእሚደረገው ውጊያ ፤ በዋናነት በሙስሊም ሱልጣኔቶች በክፍያ ፣ በቅስቀሳ ፣ በሴራ ፣ ወዘተ ፤ ካስከተቱት ሠራዊት ጋር እንጂ ቀጥታ ከሱልጣኔቶቹ ጋር ስለ አለ መሆኑ ፤ ሱልጣኔቶቹ ማሕበራዊ መሠረት የሌላቸው እና ከክርስቲያን ሸዋ ጋር ለመጋጨት የእሚያበቃ አቅም የሌላቸው ስለ መሆናቸው እንደ እዚኽ ይላል ፦

“ሪፖርቱ … ንጉሡ ከሙስሊም ወታደሮች ጋር እየተዋጋ እንደ ነበር አያመለክትም … የሙስሊም መንግሥታት የተባሉት … የእሚመስለው ፥ የአረማዊያን መንግሥት ሆነው ፥ በእዚያኽ ቁጥራቸው እየበዛ የመጣባቸው የሙስሊም ነጋዴዎች የሰፈሩበት ነው ።”

“The … report ...does not at all imply that the king was fighting against Muslim troops. ...Muslim state...may have been infact a pagan kingdom in which a growing number of Muslim merchants have been settling; [98]“

እንደ ገናም ፤ ሐገራዊ የታሪክ ድርሳኖች ፤ ለምሳሌ ፦ ከሐዲያው ንጉሥ ጋር ሸዋ ግጭት ውስጥ የገባው ፤ በኋላ አምልጦ ወደ ኢፋት የገባ የሙስሊም ነጋዴ ፤ ለሸዋው ንጉሥ ግብር አትገብር ብሎ የሐዲያውን ንጉሥ በመምከሩ ነው ይላል ። ይኽም ማለት ፤ የሙስሊም ሱልጣኔቶቹ በጅኃድ እሳቤ ይኹን ወይንም ልንተካ ነው በእሚል ስጋት ወይንም በኹለቱም ፤ ክርስቲያኑን ኢትዮጵያ ለማውደም ወይንም ለመውረስ ይጠቀሙ የነበረው ፤ ክርስቲያን ያልሆነው ሕዝብ ነበር ፤ የራሳቸው ሕዝባዊ መሠረት የሌላቸው በመሆኑ ፦

“… አማኖ የተባለው ፣ የሐድያው መሪ ፤ ወደ ንጉሥ ደጅ አልመጣም የተለመደውንም ግብር አላገባም አለ ። ይኽንም እንዲያደርግ በ’ሐሰተኛ’ የሙስሊም ነብይ ተመክሮ ነበር…”

“...the ruler of Hadya, called Amano, refused to come to king’s court and submit the usual tributes. He was encouraged in this by a Muslim ‘false prophet’ [98]“

የዖሮሞን ለየት የእሚያደርገው ፤ ከግራኝ ወረራ በኋላ ፤ በከፍተኛ ደረጃ የተዳከመች ኢትዮጵያ ፤ ከውስጥ በካቶሊኮች ውትወታ እና የእርስ በእርስ ጦርነት ፣ ከውጭ የግራኝን ሞት መበቀል በእሚፈልጉት የአዳል ሱልጣኔት ጦርነት እና የቱርክ ወረራ ተወጥሮ በነበረበት ሰዓት ፤ ራሱ የዖሮሞ ሕዝብ ወደ 10ኛው ምዕተ ዓመት አከባቢ ይኖርበት ከነበረው የዛሬዋ ሶማሊ ላንድ በዛሬዎቹ የሱማሊ ሕዝብ እና ከዖሮሞ እና ከሱማሌ ሕዝብ አስቀድሞ በዛሬዋ ሱማሌ ይኖሩ ከነበሩ የባንቱ ሕዝብ ለዘመናት ይደረግበት በነበረው ጦርነት ምክንያት ከስፍራ ስፍራ ሲሰደድ በመቆየቱ ፤ በወቅቱ ኢትዮጲያ የገባችበትን መዳከም አጋጣሚ ፤ ነባራዊ የሙስሊም ሱልጣኔቶች እድሜ ጠገብ የወረራ እቅድ እና ታሪክ ደምሳሹን የገዳ ስርዓት በጸረ ኢትዮጵያ የወቅቱ ሱልጣኔቶች እየታገዘ ይዞ ፤ ከእርሱ በፊት ከነበሩት ተመሳሳይ ሙከራዎች ይልቅ ስኬታማ መሆኑ ነው ።

በወቅቱ የነበረው ኹኔታ ምን ያኽል ፈታኝ የነበረ መኾኑን የእሚያሳየው ፤ በወጣትነቱ ግራኝን የተዋጋው እና የገደለው አጼ ገላውዴዎስ ፤ የግራኝን ሞት ለመበቀል የተነሱትን አዳሎች እንደ ገና ድል ለማድረግ እና በእዚያው ግዜ አከባቢ ወደ ኢትዮጵያን መስረግ የጀመሩት ዖሮሞዎችን ለማስቆም እየተዋጉ ሳሉ መሰዋታቸው ፤ አንዱ ነው ። ይኽንንም ታሪክ ይልማ ደሬሳ እንዲኽ ያስቀምጡታል ፦

“ የንጉሠ ነገሥቱን ግዛት ፤ ከእስላሞች እና ከዖሮሞዎች ወረራ የማዳን ተስፋም ፤ በጀግናው ንጉሥ መሞት ምክንያት በ፲፮ኛው (16ኛው) መቶኛ ዘመን ውስጥ ሳይፈፀም ቀረ ። [102]”

እነ እዚኽን ታሪካዊ ኹኔታዎች ከግምት ስናስገባ የግጭቱ ምንጭ የሸዋ ተስፋፊነት ነው ከእሚለው ይልቅ ፥ የሙስሊም ሱልጣኔቶቹ ተፈላጊነታቸው እየቀነሰ በመኼዱ ከመቆጣት ፣ ከአላቸው ኃይማኖታዊ ፅንፈኝነት ተነስተው በጅኃድ ለማስለም እና ፀረ ኢትዮጵያዊነት ከፈጠረባቸው ጽንፈኝነት የእሚመነጭ ግጭት ነው የእሚለው የበለጠ እውነት ይመስላል ።

የሙስሊም ሱልጣኖች በአሉበት ቦታ ፥ የንግድ መስተጓጎል እና የአከባቢ መሪዎችን ማሳመፅ የጦርነቶቹ መነሻ ሲሆን ፤ በአብዛኛው አረማዊያን በአሉበት የኢትዮጵያ ክፍል የግጭት መነሻ ፤ ከሸዋ ውጭ በአለው ዳሞት ግዛት ውስጥ በእሚኖሩ በክርስቲያኖች ላይ የእሚደርስ ግድያ ፣ ዘረፋ ፣ ማፈናቀል ፣ ወዘተ ፤ ናቸው ።

ለምሳሌ ፦ የአስርኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አከባቢ ፤ የዳሞት ንግሥት የሆነች ሴት ፤ በዳሞት ውስጥ ይኖሩ በነበሩ ክርስቲያኖች ላይ ጥቃት በማስነሳቷ ፤ ከሸዋ ከክርስቲያን ነገሥታቱ ጋር ግጭት ውስጥ ገብታ እና በእዚኽም ግጭት ፤ ለሸዋ ነገሥታት ፈተና ሆና ነበር ፦

“ንግሥቲቱ እና አረማዊ ተከታዮቿ ቤተክርስቲያናትን አውድሙ ክርስቲያኖችን ገደሉ ። የክርስቲያን ንጉሥ ራሱ ፥ በእዚኽ ግጭት ህይወቱን ሳያጣ አይቀርም ።”

“The queen and her pagan followers destroyed churches and killed Chriatians. The Christian king himself probably lost his life in the conflict,... [98]“

እነ እዚኽ ከሸዋ በታች በአሉ ከባቢያዊ መንግሥታት ጋር የእሚደረጉ ግጭቶች ፤ መጨረሻ ላይ ፤ በተለይ በአምደ ፅዮን ዘመን ፤ አምደ ፅዮንን መላውን ኢትዮጵያን ያለ ተቀናቃኝ በቀጥታ እንዲቆጣጠር ቢያስችሉትም ፤ የጦርነት ትንሽ የለውም እና ከላይ እንደ አለው ዘገባ ፤ በሦሥት መቶ ዓመታት ውስጥ የተወሰኑ የሸዋ ነገሥታትን ህይወት እስከ ማሳጣት የደረሱ ነበሩ ።

በሌላም ታሪክ ፤ አምደ ጽዮን የተደረገበትን አንዱን ከበባ እንደ እዚኽ ያስቀምጠዋል ፦

“በመግደል እና በጦርነት ሞያተኛ የሆኑ ፤ ወርጂ እና ገበል ፥ ሊዋጉኝ መጡ ፤ …ሙስሊሞችም አብረው ነበሩ ። የክርስቲያኑን ምድር ፥ መንዝንና ዝጋንም አጠፉት ። እነ እዚኽ ኹሉ አንድ ላይ ተባብረው ፤ ከበቡኝ ።”

“The people called Werjih and Gebel, who are experts in killing and war, came to fight me …. were] also Muslims. And the land of the Christians was destroyed, and the land of Ziga and Menzih. All these leagued against me and surrounded me. [98]“

እነ እዚኽ ከሸዋ በስተ ደቡብ የአሉ፟ አከባቢዎች ፥ የሙስሊሞቹም ይሁኑ የአረማዊያኖቹ ፤ በሸዋው መንግሥት ጥላ ስር ፤ ከመጀመሪያው አንስተው ፥ ማለትም ከፍጥረታቸው አንስቶ ቢሆኑም ፤ ከሸዋው መንግሥት ጋር ፤ ከእላይ እንደ አልኩት ፥ በተለያየ ምክንያት ግጭት ውስጥ እየገቡ ፥ በክርስቲያኑ መንግሥት ላይ ወይንም በክርስቲያኖች ላይ ጉዳት ለማድረስ መንቀሳቀሳቸው ፤ የሸዋው መንግሥት በእየግዜው እየ አዳበረው በመጣው ኹለንተናዊ አቅም ምክንያት ፤ አከባቢውን ማለትም መላውን ኢትዮጵያ ተቆጣጥሮ የራሱ ሰዎች በመሾም እነ እዚኽን መንግሥታት ለእርሱ ተጠሪ እንዲሆኑ ለማድረግ አስችሎታል ።

በእዚኽም መሠረት ፤ የሸዋው መንግሥት እነዚኽን ‘ትንኮሳዎች’ አስከትሎ የእሚሰጠው ምላሽ ፤ የመጀመሪያው ፥ አከባቢውን በኃይል በመቆጣጠር የሹም ሽር ማድረግ ነው ።

ለምሳሌ ፦ ይኩኖ አምላክ (ከዛግዌ ስልጣኑን የተረከበው የመጀመሪያው የሰለሞናዊ ስርወ መንግሥት ንጉሥ) ፤ ሞቶሎሚ የተባለውን የዳሞት ንጉሥ ከዳሞት አንስቶ በእናርያ ላይ እንደ ሾመው ወይንም ዳሞትን ፤ ዳሞት እና እናርያ ብሎ ለኹለት እንደ ከፈለው ይነገራል ፦

“መቶሎሚን የእናሪያ ንጉሥ አድርጎ በመሾም ፤ …ከግቤ ወንዝ ማዶ የአለውን ምድር ሰጠው።”

“appointed (motelamy) King of Ennarya...and gave him the land beyond Gibe river. [98]“

ወደ መጨረሻ ላይ ደግሞ ፤ እነ እዚኽ ኹሉም አከባቢዎች ፤ በቀጥታ ከሸዋ በእሚሾም ሰው ወደ እሚተዳድሩበት ኹኔታ ሲመጡ ይታያል ።

ይኽ ዓይነቱ አሰራር ፥ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ውጤታማ የነበረና እና ምንም እንኳን እዚኽም እዛኽም የእሚነሱ ተደጋጋሚ ግጭቶች እንደ አይነሱ ማድረግ በአይችልም ፥ ግጭቶቹ ወደ ከፋ ደረጃ እንደ አይደርሱ የአደረገ መፍትኼ ሲሆን ይታያል ።

ይኽ ሹም ሽር ስልት ግን በሙስሊም ሱልጣኔቶች ዘንድ ውጤታማ አልነበረም ። ለምሳሌ ፥ የኢፋቱን መሪ ሰብረ አዲን ከተሸነፈ በኋላ ፤ እሱ ታስሮ ወንድሙ የእርሱን ቦታ እንዲይዝ ነበር የተደረገው ፦

“ሰብረ ኢድ-ዲን እጅ ከሰጠ በኋላ እርሱ እና ጓደኛው እንዲኹም አጋሩ የነበረው የደዋሮው[3] ንጉሥ ፤ ታስረው ፤ የእርሱ ወንድም ጀማልዲን ‘የሙስሊሞች ኹሉ ንጉሥ’ ተብሎ ተሾመ ።”

“Sabr Ed-Din surrendered and was imprisoned together with his friend and ally, Hayder, King of Dewaro, and his own brother Jemaldin was appointed “King of all the Muslims. [98]“

ይኽን መሰሉ ሹም ሽር ግን በደቡብ ምዕራብ ያመጣውን ዓይነት ውጤት ፤ በሙስሊም ሱልጣኔቶች አከባቢ አላመጣም ። ይልቁንም ፥ ግጭቱ ከግዜ ወደ ግዜ ራሱን እያደሰ እንዲመጣ በማድረግ ፤ በውጤቱም የሙስሊም ሱልጣኔቶችም ከመሐል እየተገፉ እየተገፉ ወደ ዛሬዋ ሶማሊያ ዘይላ ወደብ እንዲመሽጉ አደረጋቸው ።

በኋላም ከዘይላ እየተነሱ በሸዋው መንግሥት ላይ መዝመታቸውን ስለ አላቆሙ ፤ በአምደ ፅዮን ዘመን ተገፍተው የዛሬዋ ሱማልያ ዘይላ እንዲገቡ የተገደዱት ሱልጣኔቶች ከግራኝ በፊት የእሚያስነሱት ግጭት መቋጫውን ያገኘው ፤ የሸዋው መንግሥት እስከ ዘይላ ድረስ ዘምቶ እ.አ.አ. በ1402/3 ዓ.ም. ፤ ማለትም በአጼ ዳዊት ዘመን ፤ የአዳሉን ሱልጣን በመግድሉ እና አከባቢውን በመቆጣጠሩ ነው ፦

“በመደምደሚያው ግጭት ፤ ሰዓድ አዲን ላይ እስከ ዘይላ የእሚደርስ ማሳደድ ተደርጎበት ፤ እ.አ.አ. በ1402/3 ዓ.ም. ተይዞ በእዚያኽ ተገድሏል ።”

“In the final encounter Sa’ad Ad-Din was pursued by the king’s troops as far as Zeila where he was captured and killed in 1402/3. [98]“

ከእዚኽም በኋላ ፤ በሙስሊም ሱልጣኔቶቹ ላይ ሳይቀር ፤ የክርስቲያን ገዢዎች ሲሾሙ ይታያል ። በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ የኢፋት ገዢ ክርስቲያን ነበር ፦

“…በኢፋት ላይ የነበረ የክርስቲያን ገዢ ፥ …”

“A … Christian governor of Ifat … [98]“

ይኽ አራተኛው የታሪካችን ክፍል ፤ የአክሱሙ መንግሥት ራሱን ከአክሱም ወደ መካከለኛው ኢትዮጵያ ከአዞረ በኋላ ያጣውን ፥ ግልፅ የመንግሥት ስልጣን በድጋሚ ከአስመለሰ በኋላ ፤ የዛሬዋን ኢትዮጵያን ፤ በንግድ ፣ በኃይማኖት ፣ በፖለቲካዊ አስተዳደር አስተሳስሮ ፤ የዛሬይቱን ኢትዮጵያ ለእኛ ያስረከበበት ነው ።

በእዚኽ መልኩ በብዙ መስዋትነት እንደገና የተገነባች ኢትዮጵያ ግን ፤ የመጀምሪያው የአክሱም መንግሥት በተለያየ ምክንያት በቸልታ የተወው ቀይ ባሕር እና መጋቢዎቹ የባሕር ላይ መንገዶች በግዜ ኺደት ፤ በሌሎች እጅ በመግባታቸው ፤ ኢትዮጵያን ፥ አንዳንዱ እስከ ዛሬም ላልለቀቃት ብዙ ችግር ሲዳርጋት ኖሯል ።

ሕዝብ ወይንም መንግሥታት ፤ ጠባብ ዓለም ዓቀፋዊ ግንዛቤ ሲኖራቸው ፤ ከእሚሰሩዋቸው ስህተቶች አንዱ በዓለም ዓቀፉ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ የራሳችንን ደሴት ሰርተን መኖር እንችላለን ወይንም ደግሞ እንደ አንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ፤ ከዓለም ሕዝብ ጋር በተለያየ አስተሳሳሪ ገመድ እንደ ተያያዘ ተዋናይ ሰአይሆን ራሳቸውን የተናጠል ተዋናይ አድርጎ በማሰብ ፤ ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ሲፈልጉ የእሚገቡበት ፤ ሳይፈልጉ ደግሞ ራሳቸውን ከእዚኽ ግንኙነት በተናጠል ‘በራሳቸው ጉዳይ ላይ ብቻ አተኩረው (Supposedly, minding their own business)’ ወይንም አትድረሱብኝ አልደርስባችኹም ወይንም የእኔን አትፈልግ እኔም የአንተን አልፈልግም ብለው መኖር እንደ እሚችሉ አድርገው ወደ ማሰብ መምጣት ነው ።

እውነታው ግን ፤ ዓለም ዓቀፍ ፖለቲካ ፤ በእዚኽ መልኩ በአንድ ወገን ምርጫ ብቻ የእሚወሰን ሰአይሆን የብዙ ወገኖች ፍላጎት እና ምርጫ የአለበት የራሱ መርኽ እና መመሪያ የአለው ፤ ራሱን የቻለ አንድ ትልቅ ‘ዓለም’ ፤ ስለ እዚኽም ፦ በዓለም ዓቀፍ ፖለቲካ መነካት የምርጫ ጉዳይ የሆነ አይደለም ።

ልክ አንድ ግለሰብ ፤ በእሚኖርበት መሐበረሰብ ውስጥ ፤ በፖለቲካው ሳልነካ፟ እና ፖለቲካውን ሳልነ፟ካ የራሴ ደሴት ሆኜ መኖር እችላለሁ ማለት እንደ እማይችለው ፤ ሐገራትም በዓለም ዓቀፉ ግንኙነት መስክ ፤ የተናጠል እና የመሐል ቤት አቋም ይዤ እገኛለሁ ማለት የእሚችሉበት አይደለም።

እኛ እንደ ፈለግነው እንደ መርጥነው መኖር አንችልም ፤ ምክንያቱም በእዚኽች ዓለም ላይ ብቻችንን አንኖርም ። ይኽችኽ ዓለም ከብዙ የዓለም ሕዝብ ጋር የእምንጋራት የጋራ ምድር ነች ። ጦርነት አልፈልግም የእሚለው እንደ አለባት ጦርነት ፈላጊውም አለባት ፣ በንግድ መተሳሰር የእሚፈልገው እንደ አለባት በንግድ መተሳሰር የእማይፈልገው አለባት ፣ የንግድ እና የፖለቲካ ሕብረት የእማይፈልገው እንደ አለባት የንግድ እና የፖለቲካ ትስስር ያለኽ የእሚለውም አለባት ፣ በፍትኽ እና በርትዕ ሊኖርባት የእሚፈልገው እንደ አለባት ቀምቶ እና በኃይል ገዝቶ መኖር የእሚፈልገው አለባት ፣ የተማረው እና ተራማጁ እንደ አለባት መኃይሙ እና ወግ አጥባቂው አለባት ።

ስለ እዚኽ ፦ በእዚኽ ባለ ብዙ ደርዝ ግንኙነት በአለባት ዓለም ውስጥ ፤ እኛ የእምንፈልገውን ሰአይሆን ፤ የእሚቻለውን እና የእሚበጀውን የመምረጥ ኃላፊነት የሐገራት መሪዎች ነው ። ትልቅ ሕዝብ ነኝ ፣ ብዙ እና ጀግና ሠራዊት አለኝ ፣ ሐገሬ ለምለም ነች ፣ ወዘተ ፤ በእሚል የፈለግነውን መንገድ መምረጥ ፣ ራሴን በራሴ ችዬ እኖራለኹ ወይንም ዓለም ዓቀፋዊ አጋርነት የመፈለግ ግዴታ የለብኝም ማለት አይቻልም ፤ ቢባልም መጨረሻው ውድቀት ነው ።

ይኽም በመሆኑ የወቅቱ ፖለቲካዊ መደናበር ፤ ሐገራዊ ፖለቲካውን ከማተራመሱ በአሻገር ፤ በዓለም ዓቀፉ ግንኝነት መስክ ፤ በኢትዮጲያ መጻዒ ላይ ከፍተኛ ሚና የአለውን የቀይ ባሕርን የአክሱሙ መንግሥት ክፍቱን ትቶ ወደ ውስጥ እንዲሰበሰብ በማድረግ ፤ በግዜ ኺደት ይኽ ስትራቴጂክ ቦታ ፤ በሌሎች ሕግ በእማይገዛቸው ሰዎች እጅ እንዲገባ ስለሆነ ፤ ይኽንን የባሕር በር መተው ከአሳጣን ዘርፈ ብዙ ጥቅም በአሻገር ፤ የባሕር በሩ በኢትዮጲያ በአላንጣዎች እጅ መውደቁ ፤ ለቀጣይ ብዙ ዘመናት የኢትዮጲያ ችግር ምንጭ ሲሆን ይታያል።

ፕሮኮፕየስ በተባለ የሮም ታሪክ ጸሐፊ እንደ ተዘገበው ፤ የአክስሙ መንግሥት በደቡብ አረቢያ ወኪል ከነበረው የአብረኃ ልጅ መስሩክ በፐርዥያኖች ከመወገዱ በፊት ፤ በሮማው ኢምፐረር ጀስቲንያን ለንጉሥ ካሌብ ፤ ከህንድ ወደ ሮማ የእሚደረገውን የጨርቅ ንግድ ብቸኛ አስመጪ በመሆን አትሩፍበት ብሎ ግብዣ ልኮበት የነበረ ቢሆንም ይኽንን ግብዣ ግን የአክሱሙ መንግሥት በቸልታ አልፎታል ፦

“በእዚያኽን ዘመን የሮማው ኢመፐረር ከኢትዮጵያዊያኖች ጋር ሕብረት የመፍጠር ኃሳብ መጣለት … በእዛኽ እለ አፅበኃ (ካሌብ) ነግሶ በነበረበት ሰዓት … ኢምፐረር ጀስቲንያንም ጁልያነስ የተባለ አምባሳደር ጥያቄ አስይዞ ላከው … በኃይማኖት ጉዳይ ጋርዮሽ የአላቸው በመሆኑ በፐርዥያኖች ላይ የእሚደረገው ጦርነት ላይ ከሮማዊያን ጋር አብረው እንዲሆኑ ፤ በህንድ የእሚሸጠውን ሲልክ እየገዙ በሮም በመሸጥ ፤ ለራሳቸው ብዙ ገንዘብ እንዲያገኙ እና በእዚኽም ሮማኖች ለጠላታቸው ለፐርዥያ ገንዘብ እንደ አይከፍሉ በማድረግ እንዲጠቁሙዋቸው … ንጉሥ (ካሌብ) … ይኽን እንደ እሚያደርግ ቃል ገብቶ አምባሳደሩን አሰናበተው … ነገር ግን ምንም ሳያደርግ ቀረ ።”

“At that time the idea occurred to the Emperor Justinian to ally with himself the Ethiopiana...to injure the Persians....At that time, when Hellestheaus was reigning over the Ethiopians,...the Emperor Justinian sent an ambassador, Julianus, demanding that...on account of their community of religion ahould make common cause with the Roman in the war againat the Persians; for he proposed that the Ethiopians, by purchasing silk from India and selling it among Romans, might themselves gain much money, while causing Romans to profit in only one way, namely, that they be no longer compelled to pay their money to their enemy....the king...promising to put this demand into effect, dismissed the ambassador...but neither...did the things agreed upon by them. [94]“

ከእዚኽ ታሪክ ፤ እንደ እምናየው ፤ የትልቋ የሮም መንግሥት ፤ ወደ ንጉሥ ካሌብ ዘ አክሱም ፤ ጁልያነስ የእሚባል አምባሳደር ልኮ ፤ በሮም ግዛት ወይንም በአውሮፓ ገበያ ትልቅ ተፈላጊነት የአለውን የሲልክ ጨርቅ የእሚያቀርበውን እና ከህንድ የእሚነሳውን የሲልክ ጨርቅ ንግድ ፤ ባላንጣችን የሆኑት ፐርዥያኖች (ኢራን) ተቆጣጠረውት ስለ አሉ እና የፖለቲካ ባላንጣችን በመሆናቸው ፤ ከእዚኽ ንግድ የእሚያገኙት ትርፍ እንዲያገኙ ስለ እማንፈልግ ፤ እንደ እኛው ክርስቲያን የሆናችሁት እናንተ ይኽን ንግድ ብትይዙት ፤ እናንተም ብዙ ትርፍ ታገኙበታላችኹ እኛም የፖለቲካ ባላንጣዎቻችን የሆኑቱን ፐርዥያዊያን ወይንም ፋርሶችን (ኢራን) በእዚኽ ንግድ ፋይናንስ ከማድረግ(የገንዘብ ምንጭ መሆን) እንድናለን እና ይኽን ንግድ ያዙት ብሎ ላቀረበለት ግብዣ ፤ ንጉሥ ካሌብ ግብዣውን ተቀብሎ ፤ ነገሩን በቸልታ እንደ ተወው ነው ።

የወቅቱ የአክሱሙ መንግሥት ፤ ኹሉ ነገር በእጁ ነበር ሊባል በእሚችልበት ወቅት ፤ ይኽንን የመሰለ አትራፊ ግብዣ ለምን በቸልታ እንደ አለፈው ፤ በክርስትና መልዕክት ምክንያት ከገባበት ፖለቲካዊ መደናገር የተለዩ ፤ ሌሎች ምክንያቶች መደርደር የእምንችል ቢሆንም ፤ አንዳቸውም ግን አጥጋቢ አይሆኑም ።

ለምሳሌ ፦ የአክሱም መንግሥት ፤ ጥሩ ገቢ ሊያስገኝለት የእሚችለውን ይኽንን የባሕር ላይ ንግድ ችላ የአለው ፤ የምሥራቁ እና ብቸኛው የሐገራችን አከባቢ ፤ አንድ በዛሬዋ ሰሜን ሱዳን የእምትገኘው የስዋቂን ነጋዴ ለንግሡ ልጅ እንደ ቀለደው ፤ “በእኛ ሐገር የሌለ ሸቀጥ የለም ከንፋስ በስተቀር እንደ አለው” ፤ እጅግ ሐሩራማ ከመሆኑ የተነሳ ሸሽቶት ነው ሊባል ይችላል።

እንዲኽ እንድ እናስብ የእሚያደርገን ታሪካዊ አጋጣሚም የነበረ ነው ፤ ለምሳሌ ፦ በእነ አምደ ፅዮን ዘመን ከሙስሊም ሱልጣኔቶቹ ጋር በእሚደረገው ጦርነት አንዱ ፈታኝ ነገር ፤ የደጋው ጦር ይኽንን አየር ንብረት ተቋቁሞ መዋጋት ይሳነው እንደ ነበር መዘ፟ገቡ ነው ፦

“በአብዛኛው ጦርነት ሲካኼድበት የነበረው ፤ ቆላማው አከባቢ የውኅ እጥረት እና ሙቀት የነበረበት በመሆኑ ፥ የደገኛው ዘማች ሊታገሰው የእሚችል አልነበረም ። ዘመቻው በአጠቃላይ ፥ የመክዳት እና የማፈግፈግ ጥላ ያጠላበት ነበር ፤ ምናልባትም ይኽን መሰሉ ኹኔታ እንደ አይከሰት የአገረደው ነገር ቢኖር ፥ የነገሥታቱ ቆራጥነት እና ይኽን መሰሉ አልታዘዝ ባይ ወታደር ሲሸሽ ሊደርስበት የእሚችለውን በመፍራቱ ነው ።”

“The heat and the scarcity of water in the semi-desert regions, where the fighting largely took place, were intolerable to the highland troops, and the whole campaign was overshadowed with constant threats of desertion ፣ which were only averted by the king’s determination and by the possible dangers that awaited such recalcitrant soldiers on the long way home. [98]“

የአክሱሙ መንግሥት ለእዚኽ የሐሩራማነት ፈተና ሊሰጥ ይገባ የነበረው መፍትኼ ፤ ልክ በጦርነቱ ላይ የኋላው የሸዋው መንግሥት እንደ አሳየው ዓይነት የመቋቋም ቆራጥነት ፤ የአከባቢውን የአየር ንብረት ኹኔታ ተቋቁመው ፥ የባህሩን ጥግ ከደጋው መሐል ጋር የእሚያስተሳስሩ ሰዎች እና ኹኔታዎችን ማመቻቸት እንጂ ፤ ይኽን ሐሩር ማን ይፈልግዋል ፤ እኔ ደጋውን ከያዝኩት ገዥውን መሬት ይዣለኹ ብሎ ማፈግፈጉ ትክክለኛ ምላሽ አይሆንም ።

እንደ እሚታወቀው ፤ የአከባቢውን ተፈጥሮ ተቋቁመው ለብዙ ዘመን የኖሩ ኢትዮጵያን ያሉ በመሆናቸው ፤ ፍላጎቱ እና ስትራቴጂካዊ ግንዛቤው ከነበረ ፤ ቀላል ነበር በአይባልም ፤ ከቦታው ስትራቴጅካዊነት አንጻር እማይችል ወይንም ይኽን ያኽል ዋጋ ሊከፈልበት የእሚገባ አልነበረም የእሚባልበት ጉዳይ አይደለም ።

የተለያዩ የዓለም ሕዝብ ስንመለከትም ፤ ምንም እንኳን ፈተና ቢበዛበትም አከባቢያቸውን አሸንፈው ከአከባቢያቸው በላይ ሆነው የተገኙ ሕዝብ ፤ አድማሳቸውን አስፍተው ፤ አንዳንዶች ከባቢያዊ ሌሎች ደግሞ ዓለም ዓቀፋዊ ግንዛቤ አዳብረው ፤ ራሳቸውን ለተሻለ ህይወት አብቅተዋል ።

በተነፃፃሪ ሌሎች ደግሞ ፤ የአከባቢያቸው መልክዓ ምድር እና አየር ጠባይ ገድቧቸው ፤ የአከባቢያቸው እስረኞች ሆነው ፤ በእዚኽም የመሸሽ ልማዳቸው ምክንያት ለትውልድ ተሻጋሪ ኋላ ቀርነት አስተላላፊ እና አሉታዊ የውጭ ተፅኖ ተጋላጭ ሆነዋል ።

አረቦች ስለ ራሳቸው እንደ እሚሉት ፤ ብዙ አስቸጋሪ የዓየር ጠባይ እና ፈታኝ የምድር አቀማመጥ በትዕግስት እና በፅናት ተቋቋመው ፤ የሲራራ ነጋዴነትን ልምድ በማዳበራቸው ፤ እስልምና ከመጣ በኋላ ይኽንን ልምዳቸውን በወታድራዊ ዘዴ በማገዝ ፤ ሰፊ የዓለምን ክፍል ለረዥም ዘመን መግዛት ችለዋል ። አረቦች ይኽንን ትልቅ ተፅኖ መፍጠር የቻሉት እጅግ በርኃማ ከሆነው አከባቢያቸው ተነስተው ነው ።

ይኽ የፈጠሩት ግዛት ፤ የዓለምን የየብስም ሆኖ የባሕር የንግድ መስመር ፤ ማለትም የወቅቱን የምርት ስርጭት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እንዲ ቆጣጠሩ ስለ አስቻላቸው ፤ ይኽ ኹኔታ በቀደመው ዓለም ወደር የሌለው ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ አቅም ሰጥቷቸዋል ።

ስለ እዚኽ ፤ አክሱማዊያኖቹ በአየር ንብረቱ ተበግረው ነው ሐሩራማውን የባሕር በር ትተውት የመጡት ከተባለ ፤ የአከባቢያቸው ተገዢዎች ሆነው ነበር ማለት ነው ።

ወይንም ደግሞ ፤ የአክሱሙ መንግሥት ፤ በግዚያዊነት በአስቸጋሪው የባሕር ላይ ንግድ ከመሳተፍ ይልቅ ፦ የወርቅ ፣ የዝሆን ጥርስ ፣ የተለያዩ እንስሳት ቆዳ እና መሰል ምርቶች በቀላሉ ወደ እሚገኙበት ወደ ጥሬ እቃው መፍለቂያ መሐል ሐገር መግባት በወቅቱ በነበረው የንግድ ስሌት ፣ ጠባብ በሆነ ዓለም ዓቀፋዊ ግንኙነት እይታ እና በመሠረታዊ የስሌት ስህተት ፤ እኔ ምንጩን ከተቆጣጠርኹ ፤ አከፋፋዩ ወይንም የስርጭቱን ሥራ የእሚሰራው ብዙም ርቀት ሊኼድ አይችልም ፤ ብሎ አስልቶ ፤ የባህሩን ንግድ ለቆ የመጣው ከአልን ፤ ይኽ ስሌት ምንም እንኳን በከፊል ልክነት ቢኖረውም ፤ እንደ እዛው ደግሞ የሳተው ብዙ ነጥቦች እንዳሉ ልብ ልንል ይገባል ።

ይኽ ዓይነቱ የአክሱማዊያኑ አስተሳሰብ ፤ ኢትዮጵያን በዓለም ላይ ቀኝ ተገዝታ የእማታውቅ እና ብዙ አስገራሚ ልዩ ታሪካዊ ኃብት የአላት ሐገር አድርጎ መገንባት ቢችልም ፤ በእዚያው ልክ ደግም የእይታ ውስንነቱ እና የስሌት ስኽተቱ ያስተወው የባሕር ላይ ንግድ ፤ ብዙ መልካም እድሎችን ከማሳጣት አልፎ ኢትዮጵያን ለብዙ ታሪካዊ ጉስቁልና ዳርጓታል ።

ይኽ ፥ በሮማዊያን ቀርቦለት የአክሱማዊው መንግሥት ችላ የአለው እድል ፤ የዘመናዊው ዓለም ፋና ወጊ የሆነው ወይንም የካፒታሊዝም ስረዓት መሠረት የሆነው ፤ የደቾቹ (ሆላንድ) ኢስት ኢንዲስ (East Indies) ካምፕኒ ፤ ለአክሱም መንግሥት ቀርቦለት ችላ የተባለውን ይኽን የንግድ እድል ፤ ከሰሜን አውሮፓ ተነሰተው ፥ በምዕራብ አፍሪካ ዞረው ማሳካት በመቻላቸው ነው ዘመናዊ ካፒታሊዝም ስረዓት የተጀመረው ።

እኛ ቀጥታ ኼዳችሁ ፥ ትልቁን የሮም ኢምፓየር ገበያ አትሩፍበት ስንባል ፤ ቸልታ የሰጠነውን እድል ፤ ደቾቹ ከአንድ ሺ ዓመታት በኋላ ፤ ኹለት መቶ ሰባ ዲግሪ በእላያችን ላይ ዞረው እና እኛ ከሚፈጅብን ርቀት በብዙ እጥፍ ፈጅቶባቸው ፤ መተግበር በመቻላቸው ፤ ምንም እንኳን እጅግ ትንሽ ሐገር ቢሆኑም የዘመናዊ ካፒታሊዝም ስረዓት መሥራች በመኾን ፤ ራሳቸውን ጠቅመው ዓለምንም ወደ አንድ የተሻለ አዲስ ዘመን አሻግረዋል ።

ይኽም ብቻ ሰአይሆን ፤ የአክሱም ነገሥታት ፤ በቀይ ባሕር ላይ ተቀናቃኝ የሌለባቸው ብቸኛ የፖለቲካ ኃይል በነበሩበት ሰዓት ፤ በቀረጥ ሰብሳቢነት ብቻ ከመወሰን ይልቅ ተራማጅ ሆነው ፥ ሕጋዊ ቀረጥ ሰብሳቢ ከመሆንም በአሻገር የንግድ መርከቦችን ወደ ማሰማራት ውስጥ ቢገቡ ኖሮ ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በእዚኽ የዓለም ዓቀፍ ንግድ በመሳተፉ የእሚያዳብረው እውቀት እና ኃብት ፤ በእሚቀጥለው 1,200 ዓመታት ኢትዮጵያ እንደ ሐገር የደረሰባትን አበሳ ያስቀር ነበር በአይባል እንኳን ትልቅ የመከላከል አቅም ይገነባላት ነበር ።

ይኽ የአክሱማዊያኑ ስሕተት ፤ እነ እዚኽን መሰል ፤ መልካም አጋጣሚዎች ከማምከኑ በአሻገር ፤ የአክሱሙ መንግሥት ብቸኛውን የኢትዮጵያን የባሕር ደጅ ክፍቱን ትቶ ወደ መሐል ሐገር መግባቱ ፤ መሐል ሐገርም ላይ ሆኖ ፤ ይኽንን እርሱ ጥሎ የመጣውን በር በተቆጣጠሩት ሰዎች ላይ እንዲደገፍ አድርጎታል ።

የአክሱም መንግሥት በእዚኽ መልኩ ፤ በአንድም በሌላም ምክንያት ብቸኛው የሐገራችን የምሥራቅ የባሕር በር ፤ ክፍት ጥሎት ወደ መሐል ሲመጣ ፤ በኋላ ላይ ለዓለም ዓቀፍ ንግድ ፍላጎቱ ሙሉ በሙሉ ፤ እርሱ ጥሎት የመጣውን ‘አስቸጋሪ’ የንግድ መስመር ከእርሱ በኋላ በተቆጣጠሩት የአረብ ነጋዴዎች ላይ መደገፍ ግድ እንዲሆንበት አድርጎታል ።

ይኽም ደግሞ ኢከነሚያዊም ፖለቲካዊም ኃይማኖታዊም አጀንዳ የአላቸው ፤ በእዚኽኛው የታሪካችን ምዕራፍ ላይ እንደ ሆነው ፤ የአረብ ነጋዴዎች የአክሱምን መንግሥት ተከትለው እየመጡ ፤ የአክሱም መንግሥት ወደ ሸዋ ከዞረ በኋላ ፤ በደቡብ እና በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ የንግድ መስመሮቹን ተከትለው ፤ እነ እዚኽን ወደ ሰባት የእሚሆኑ የሙስሊም ሱልጣኔት እያቋቋሙ ፤ የገንዘብ አቅማቸውን ፣ ወዘተ ፤ ተጠቅመው ፤ ኹሉን ዓቀፍ ግጭት ከክርስቲያኑ ሰሜን ጋር እንዲገቡ እና ሐገረ ግንባታውን በአያስቀሩትም ፤ በአላስፈላጊ ኹኔታ እንዲያከብዱት አድርጎዋቸዋል ።

ይኽም ብቻ ሰአይሆን ፤ ከግራኝ አህመድ ጦርነት ጀምሮ ኢትዮጵያን ለረዥም ዘመን ያስነከሳትን ፖለቲካዊ እና ማሕበራዊ ችግሮች መነሻቸው ይኽ በአክሱማዊያን የተዘነጋው የባሕር መስመር እንዲሆን አድርጎታል። ከግራኝ አህመድ ወረራ አንስቶ እስከ ጣሊያን ወረራ እና የኤርትራ መገንጠል ምክንያት የሆነው ችግር በሙሉ ፤ የአክሱም መንግሥታት ትተውት ወደ መሐል ከመጡት ቀይ ባሕር የእሚነሳ ነው ።

እንደገናም ፤ ኢትዮጵያ ከተንጣለለው የቀይ ባሕር እና የሕንድ ውቂያኖስ ደጅ ከ80 ኪ.ሜ. በታች በሆነ ርቀት ላይ ከ100 ሚሊየን ሕዝብ በላይ መኖሪያ ሐገር ሆና ፤ የባሕር በር አልባ የሆነች ትልቅ የአፍሪካ ሐገር እና እስከ ዛሬም የባሕር በር ችግር የተያዘች ሐገር አድርጓታል ።

እንግዲህ በወቅቱ የገነነው የክርስትና መልዕክት የፈጠረው መደናገር ፤ የሐገሩ ውስጥ መንግሥትን ከማዳከሙ የተነሳ ፤ መንግሥት ከፍተኛ ስትራቴጂክ ጠቀሜታ የአላቸውን ፤ እንደ ቀይ ባሕር ያሉ ቦታዎችን ኹሉ ፤ ይኽ ነው የእሚባል አስገዳጅ ኹኔታ ሳያጋጥመው በእዚኽ መልኩ በቸልታ አሳልፎ ለሌሎች እንዲሰጥ አድርጎታል።

አረቦች ይኽን የባህሩንም ሆነ የየብሱን (የሲልኩን ጎዳና) የዓለም ዓቀፍ የንግድ መንገድ ስለ ተቆጣጠሩት ፥ ሸዋ ላይም ተሁኖ ከእዚኽ ትልቅ የንግድ ማዕከል ፤ የፖለቲካ ተፅኖ መትረፍ አልተቻለም። እንዲያውም መልኩን ቀይሮ እና ተወሳስቦ መጥቶ ፥ ከላይ እንደ አልነው ፤ ከግራኝ አህመድ ጀምሮ ሐገራዊ ፖለቲካችንን ለረዥም ግዜ የእሚያውክ ችግሮች ሁሉ መነሻ ሆኗል ።

በእርግጥ ይኽ መሰል ስህተት ክርስትና መጀመሪያ ላይ የአክሱም ነገሥታት ላይ ከአሳደረው ተጽኖ ጋር ማያያዜ ችግሩን ከኢትዮጲያ አንጻር ለመትንተን እንጂ ይኽን መሰሉ የስሌት ስሕተት ከክርስትና ጋር እና ከኢትዮጵያዊያን ጋር ብቻ የእሚያያዝ ነው ለማለት አይደለም።

ምክንያቱም ፦ በዓለም ላይ የተለያዩ ሕዝብ ከክርስትና ጋር በአልተያያዘ አኳኋን ተመሳሳይ የክተት አካኼድ ስህተት ፈጽመዋል። በመሆኑም ፤ ይኽንን የክርስትና እንቅስቃሴ መጀመሪያ ላይ የፈጠረው መደናገር በሐገር ውስጥ የአስተዳደር ጉዳይ ብቻ ሰአይሆንም በዓለም ዓቀፉ ግንኙነት መስክ አክሱማዊያንን ለመንግሥታዊ ሥራ ፈትነት እና ቸልተኝነት እንደ አጋለጣቸው ለማሳያነት እንደ አቀረብኩት ማስገንዘቡ ተገቢ ነው ።

ቻይናን እንደ ማሳያ ብንወሰድ ፤ ሐገረ ቻይና ለረዥም ዘመን ፤ በሕዝብ ብዛት ስለ እዚኽም በትልቅ ገበያነት የአለኝን የንግድ ተፈላጊነት ፤ ዓለም ዓቀፋዊ ለውጡን እና ፍላጎቱን ፤ መሠረት በአል አደረገ መልኩ ፤ ለእራሴ ይጠቅማል ብዬ በማስበው መንገድ ብቻ አካኺዳለው ብላ ፤ ከ17ኛው ምዕተ ዓመት አንስቶ ከ200 ዓመታት በላይ ለቆየ ግዜ ፤ ድንበሯን ለዓለም ዓቀፍ ንግድ የመዝጋት አካኼድ በመከተሏ ፤ በ19ኛው ምዕተ ዓመት ፤ ከእንግሊዝ ጋር ለገባቸው የዖፕየም ጦርነት ( The Opium War ) እና እርሱንም ተከትለው ለመጡ ፤ ለምሳሌ ፦ የዛሬዋን ሆንግ ኮንግ ለእንግሊዝ አሳልፋ ለመስጠት የተገደደችበትን እና ብዙ ኢከነሚስቶችን ለእሚስማሙበት እና ቻይና በኋላ ቀር የኢከነሚ ፖሊሲ ምክንያት ፤ መነሻው ላይ ከቴክኖሎጂ አንጻር ምንም እንኳን ከአውሮፓ ያልተናነሰ አቋም ላይ የነበረች ቢሆንም የኢንደስትሪ እድገቷ ፤ በዓለፈው 40 እና 50 ዓመት እንደገና እስኪ ያንሰራራ ፤ ለረዥም ዘመን በኋላ ቀርነት እንዲ መታ ምክንያት ሆኗል ።

ታሪክ እንደ እሚነግረን ፤ ይኽ በታሪክ የዖፕየም (ሐሺሽ) ጦርነት ተብሎ ለእሚታወቀው ፤ በቻይና እና በብሪትሽ መካከል እ.አ.አ. በ1844 ዓ.ም. ለጀመረው ጦርነት መነሻው ምክንያት ፤ እንግሊዞች (አውሮፓዊያን በአጠቃላይ) የወቅቱ የቻይና ምርት የሆኑትን ፦ ሻይ ፣ የሲልክ ጨርቅ እና የቻይና ሸክላዎች ፤ ለሐገር ውስጥ ገበያ መፈለጋቸው እና ቻይናዎች ወይንም የወቅቱ የቻይና መንግሥት ደግሞ እንግሊዞች የሐገራቸውን የተለያዩ የእደ ጥበብ ምርቶች በቻይና እንደ አይሸጡ በመከልከል ፤ እነ እዚኽ አውሮፓዊያን በጣም የእሚፈልጉዋቸውን ፤ ሻይ ፣ ሲልክ ጨርቅ እና ነጭ የቻይና ሸክላ ፤ በጠገራ ብር (Silver money or coin) ብቻ ከቻይና እንዲገዙ በማድረጉ ነው ።

በሌላ አገላለፅ ቻይና ፤ በኹለቱ ሐገራት መካከል የነፃ ንግድ እንዲኖር ከመፍቀድ ይልቅ ፤ እኛ ቻይናዎች የአውሮፓውያን ቅራ ቅንቦ የእደ ጥበብ ሥራዎች አንፈልግም በማለት ከአውሮፓ ጋር የእሚደረግን የንግድ ልውውጥ አግደው ፤ ስለ እዚኽ የእኛን የቻይና ምርት እናንተ የእምትፈልጉ ከሆነ ፤ የእምንሸጥላችሁ ጠገራ ብር ይዛችሁ ስትመጡ ብቻ ነው የእሚል አቋም በመያዟ ነው ።

ይኽንም የወቅቱን የቻይናን አቋም ተከትሎ ፤ ብሪትሾች ከቻይና ጋር የተሳካ የንግድ ልውውጥ ማድረግ በአለመቻላቸው ፤ የእንግሊዙ ንጉሥ ጆርጅ ሳልሳዊ (King George III) እ.አ.አ. በ1793 ዓ.ም. ወደ ቻይናው ኢምፕርረር ኪያንሎንግ (Qianlong) መልዕክተኛ በመላክ እንግሊዝ በቻይና ቋሚ አምባሳደር እንዲኖራት እና በኹለቱ ሐገራት መካከል የአለ፟ው የንግድ ኹኔታው እንዲ ይሻሻል ለጠየቀው ጥያቄ የቻይናው ኢምፐረር ኪያንሎንግ ምላሽ የእሚከተለውን ነበር ፦

“እኛ ለልዩ የፈጠራ ሥራዎች ዋጋ ሰጥተን የእማናውቅ እና ለእናንተም የፋብሪካ ምርቶች ምንም ዓይነት ፍላጎት የሌለን ነን ። ስለ እዚኽ ፤ ንጉሥ ሆይ ፤ በእዚኽ በዋና ከተማችን የእናንተ ወኪል እንዲ ቀመጥ የጠየቁት ጥያቄ ፤ በእዚኽ በእኛ ህዋዊዋ መንግሥት ሕግ የእማይፈቀድ ከመሆኑም በአሻገር ለሐገሮ አንዳች የእሚፈይደው ነገር የአለው መስሎ አይሰማንም ። “

“We have never valued ingenious articles, nor do we have the slightest need of your country’s manufactures. Therefore, O king, as regards your request to send someone to remain at the capital, while it is not in harmony with the regulations of the Celestial Empire, we also feel very much that it is of no advantage to your country. [103]“

የቻይናን ምርት በጣም የእሚፈልጉት እና የሐገራቸውን ምርት ግን በቻይና ውስጥ ተወዳድረው መሸጥ በእዚኽ መልኩ የተከለከሉት እንግሊዞች ፤ ሳይወዱ በግድ የቻይና መንግሥት በጠየቀው መሠረት ፤ የቻይናን ምርት በጠገራ ብር መግዛት ጀመሩ ።

ይኽ ግን የጠገራ ብር ክምችታቸውን ጨርሰው ፤ ከቻይና የእሚፈልጉትን ምርት የእሚገዙበት ገንዘብ ወደ ማሳጣት አመጣቸው ። በእዚኽ ችግር ውስጥ የገቡት እንግሊዞች ፤ በቻይና ገበሬ በጣም እየተወደደ የመጣውን ኃሺሽ ፤ ለቻይና ኮንትሮባንድ ነጋዴዎች በጠገራ ብር በመሸጥ ፤ በሻይ ፣ ሸክላ እና ሲልክ ጨርቅ ግዢ የተወሰደባቸውን ጠገራ ብር ፤ በሕገ ወጥ የአሺሽ ንግድ ከቻይና ከበያ ውስጥ መጠው ማውጣት ሲያስችላቸው ፤ ከእዚኽም በተጨማሪ ጉዳዩ የሐሺሽ ንግዱ ተፋፍሞ በቻይና ሕዝብ ላይ ሱሰኝነት በማሳደግ እና የጠገራ ብሩን ከቻይና ኢከነሚ ውስጥ በማውጣት ቻይናን ለማሕበራዊ እና ለገንዘብ ስረዓት ቀውስ ዳረገ ።

በእዚኽ ችግር ውስጥ የገባው ፤ የቻይናው የኩዊንግ ስርወ መንግሥት ፤ ይኽንን ማሕበራዊ እና ኢከነሚያው ቀውስ እያስከተለበት የአለ፟ውን ፤ ሕገ መጥ የሐሺሽ ንግድ ለማስቆም የኼደበት መንገድ ኹሉ ውጤት አላመጣ ብሎት ፤ በስተመጨረሻ ይኽ ጥረቱ መጀመሪያ ከእንግሊዞች ፤ በኋላ ላይ ከእንግሊዝ እና ፈረንሳይ ጥምረት ጋር ወታደራዊ ግጭት ውስጥ አስገብቶት ፤ በጦርነቱ በመሸነፉ ፤ በሰላማዊ የዲፕሎማሳዊ መንገድ እምቢ የአለውን ንግድ እንዲፈቅድ መገደድ እና እንደ ሆንግ ኮንግ የአሉ፟ ቦታዎችን የእንግሊዝ እንዲሆኑ እስከ መስጠት እና አንዳንዶች እንደ እሚሉትም ፤ ይኽ ስርወ መንግሥት ከስልጣን እንዲወገድም አድርጎታል ።

ከእዚኽ የቻይና ታሪክ ፤ እንደ እምናየው ፤ እንደ ሐገር በግዜያዊነት ያለንን ብልጫ ወይንም ተጠቃሚነት (Short term advantage) ብቻ በማየት ፤ በጠባብነት እና በማን አለብኝነት ያለ እውቀት የእምንገፋቸው የዓለም ዓቀፍ ፖለቲካዊ ኹነቶች እና ጉዳዮች ፤ ነገ ዞረው ፤ ብዙ ማሕበራዊ እና ኢከነሚያዊ የእዳ ወለድ የእሚያስከፍለን ሆኖ የእሚመጣ መሆኑን ነው ።

ምንም እንኳን ፤ የቻይናው ኹኔታ አክሱማዊያኑ ነገሥታት ከሮማው ኢምፐረር የቀረበላቸውን የንግድ ሸሪክነት ግብዣ በቸልታ ያለፉበት መንገድ ፤ ዝርዝር ኹኔታው ቢለይም ፤ የተለያየ ምክንያቱ የአለው ቸልተኝነት ፣ የዓለም ዓቀፋዊ ግኑኝነት ግንዛቤ ጉድለት ፣ ግዜያው ጥቅም እና ብልጫን ብቻ ታሳቢ አድርጎ ትልቁን ስዕል አለመመልከት ፣ ወዘተ ፤ የፖሊሲ ምርጫቸውን ተመሳሳይነት ይሰጠዋል ።

ይኽ አራተኛው የታሪካችን ክፍል ስናጠቃልልም ፦ ወደ ሸዋ ማዕከሉን የአዞረው የአክሱሙ ስረወ መንግሥት ፤ በአክሱም እያለ የክርስትና መልዕክት በፈጠረበት መደናበር ፤ ግራ ተጋብቶ እና መንግሥታዊ ኃላፊነቱን ዘንግቶ በገባበት ውስጣዊ መዝበጥ ፤ ወደ ሸዋ ዞሮ ውስጣዊ ጥንካሬውን እንደ ገና አድሶ የዛሬዋን ኢትዮጲያ ቢገነባም ፤ ከአክሱም ወደ ሸዋ ማዕከሉን እንዲ ለውጥ በአስገደደው ምክንያት ከፍተኛ ስትራቴጂክ ጠቀሜታ የነበረውን የባሕር በር ክፍት ትቶት በመምጣቱ ፤ ሸዋ ላይ ሆኖ ከእርሱ በኋላ መጥተው ይኽንን የባሕር በር እና መላውን የዓለም ዓቀፍ ንግድ በተቆጣጠሩት የሙስሊም መንግሥታት ላይ እንዲ ደገፍ ግድ ስለ አሉት ፤ በአደረገው መንሰራራት ውስጣዊ ችግሩን ቢፈታም ፤ ይኽ ክፍቱን የተተው ቀይ ባሕር ግን ቀጣይ የኢትዮጲያ ፈተና መሆኑን ግን ማስቆም አልቻለም።

አምስተኛው ከእዚኽ ቀጥለን የእምናየው የታሪካችን ክፍልም ፤ በአንድም በሌላም ምክንያት ፤ ልንቆጣጠረው የአልቻልነው የባሕር በራችን ፤ ተጠቅመው የመጡ ጠላቶች እንደ ሐገር ያደረሱብን ውድመት ታሪክ ነው ።

  1. ከየረር እስከ ጎንደር የእሚለው ፤ የአማርኛው አባባልም የነገስታቱ መናገሻ ከየረር እስከ ጎንደር የእሚዘልቅ ነው ለማለትም ነው። ↑

  2. የኢሕአዴግ ሰራዊት በዖሕዴድ ሰራዊት ወለጋን የተቆጣጠረበትን ዘመቻ ሜጫ እና ቱሉማ ብሎ የሰየመበትም አግባብ ከእዚኽ ጋር ተዛማጅ ነው። ↑

  3. ደዋሮ ፤ በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ ከነበሩት ሰባት ፤ የሙስሊም ሱልጣኔቶች አንዱ ነው ። ↑