ስድስተኛው የታሪካችን ክፍል የአልኩት ፤ ከአጼ ፋሲለደስ ንግሥና በኋላ ፤ እ.አ.አ. በ1633 ዓ.ም. ጀምሮ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር እስከ 1901[1] ዓ.ም. የእሚቆየውን ፤ በጠቅላላው ወደ 276 የእሚጠጉ አመታት የያዘውን ዘመን ነው ።
በእዚኽ መጽሐፍ አውድ ፤ ይኽ ክፍል በተለምዶ ዘመነ መሣፍንት ተብሎ የእሚጠራውን እና እ.አ.አ. በ1755 ዓ.ም. ጀምሮ በ1855 ዓ.ም. የእሚያልቀውን ዘመን የእሚተካ እና የእሚያስፋፋ ወይንም የእሚያካትት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ።
ይኽም የሆነበት ምክንያት ፦ የዘመነ መሣፍንት መገለጫ የሆነው ፤ መዓከላዊ መንግሥቱ ተዳክሞ የተለያዩ የአከባቢ ሉዕላን ፤ የቤተመንግሥቱን ወይንም የመዓከላዊ መንግሥቱን ለመቆጣጠር የእሚፈለጉበት አካኼድ ፤ የተጀመረው እ.አ.አ. በ1560 ዓ.ም. ፤ ባሕረ ነጋሽ ይስሐቅ ከፖርቹጋሉ ቄስ ኦቪዬዶ ጋር አምጾ እና አሲሮ ፤ ከ’ሕጋዊው’ ነጋሢ ውጭ ሌላ ነጋሢ ከሾመበት ግዜ አንስቶ እንጂ የተለምዶው ዘመነ መሣፍንት ከእሚጀምርበት እ.አ.አ. 1755 ዓ.ም. እቴጌ ምንትዋብ ከልጇ እያሱ ሞት በኋላ በአደራ ስልጣን ከያዘችበት ግዜ አንስቶ አይደለም በእሚል እሳቤ ነው ።
በእርግጥ ፤ ይኽን ማለት ከባሕረ ነጋሽ ይስኃቅ አመፅ በኋላ ፤ በእኛ አቆጣጠር እስከ 1901 ዓ.ም. ድረስ የዘመነ መሳፍንቱ ውጣ ውረድ በቋሚነት ሳይቋረጥ ነበር ማለት አይደለም ።
የእየ አከባቢው ኃያላን ገዢነት ወይንም የቀኝ አዙር ገዢነት ፤ በባሕረ ነጋሽ ይስኃቅ እ.አ.አ. በ1560 ዓ.ም. ከጀመረ በኋላ ፤ ንጉሥ ፋሲለደስ እ.አ.አ. በ1632 ዓ.ም. እስከ ነገሠበት ግዜ ድረስ ወይንም ለ70 ዓመታት ያኽል ፤ ይኸው የመሐከሉን ፖለቲካ በእጅ አዙር የመቆጣጠር አካኼድ ቀጥሎ ፤ ከአጼ ፋሲለድስ ንግሥና በኋላ ልማዳዊው ዘመነ መሣፍንት እስከ ጀመረበት እ.አ.አ. 1755 ዓ.ም. ድረስ አንጻራዊ መረጋጋት ሰፍኖ ነበር ። ሆኖም ግን እ.አ.አ. 1755 ዓ.ም. ጀመረ የእሚባለው የዘመነ መሳፍንቱ አባዜ ፤ በኢትዮጲያ ታሪክ ውስጥ ፤ በባሕረ ነጋሽ ይስሐቅ የጀመረው የቀኝ አዙር አመራር ወይንም ዘመነ መሣፍንት እንደገና በድጋሚ ያገረሸበት ግዜ እንጂ ዘመነ መሣፍንት እንደ አዲስ ክስተተ የጀመረበት አይደለም ።
ስለ እዚኽ በመሐል መቆራረጥ ቢኖሮም ፤ የእየ አከባቢ ሉዕላን የመዓከላዊ መንግሥቱን በቀኝ አዙር የእሚዘውሩበት አካኼድ ፤ እንደ ፖለቲካዊ ስልት በሐገረ ኢትዮጵያ ፤ በባሕረ ነጋሽ ይስሐቅ እ.አ.አ. በ1560 ዓ.ም. ጀምሮ ፤ እንደ ግዜው እና እንደ ኹኔታው ሲጎላ እና ሲደበዝዝ ቆይቶ ፤ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ጋብ የአለው አጼ ቴውድሮስ እ.አ.አ. በ1855 ዓ.ም. ወደ ንግሥና ከመጡ ወዲኽ ነው ።
አጼ ቴውድሮስ ከመጡም በኋላ ፤ ከባቢያዊ ሉዕላኑ ፤ እንደ ቀደሙ አንጋሽ እና አፍራሽ መሆን ከመፈለግ አልፈው ፤ ራሳቸውን እኔ ነኝ ንግሥናው የእሚገባኝ በእሚል የዙፋን ሽሚያ ውስጥ ገቡ እንጂ ፤ ከባቢያዊ ሉዕላኑ የመሐሉን ፖለቲካ በተናጠል ለመቆጣጠር የመፈለጋቸው ኹኔታ ወይንም የረጋ መዓከል የመፍጠሩ ትግል እስከ አጼ ምንሊክ መምጣት ድረስ አላቆመም ነበር።
በሌላ አገላለፅ ፤ የዘመኑ ፖለቲካ ባሕረ ነጋሽ ይስሐቅ ከአስጀመረው አካኼድ ፤ በመሐል መጣ ኼደት የአለበት ግዜ ቢኖርም ፤ በባሕረ ነጋሽ ይስኃቅ ከጀመረበት አንስቶ እስከ አጼ ምንሊክ ድረስ ፤ የቅርፅ እንጂ የይዘት ለውጥ አል አደረገም ነበር ።
ይኽም በመሆኑ ፤ ይኽ መጽሐፍ ታሪኩን ከእሚዘግብበት ግብ አንፃር ፤ ዘመነ መሣፍንት ወይንም ከባቢያዊ ሉዕላን ፤ በአንድም በሌላም መንገድ የመንግሥትን ስልጣን ለመቆጣጠር የእሚኼዱበት አካኼድ ከአጼ ቴውድሮስ በኋላ የአበቃ ሰአይሆን እስከ አጼ ምንሊክ የቀጠለ ነው ።
አጼ ቴውድሮስ ከተሰው በኋላ ፤ በጎንደሩ አጼ ተክለ ጊዮርጊስ እና በትግሬው ራስ ዮሐንስ መካከል የዙፋን ትግል ተካኺዷል ፤ አጼ ዮሐንስም ከነገሡ በኋላ ፤ በአጼ ዮሐንስ ፣ በንጉሥ ተክለ ኃይማኖት እና በንጉሥ ምንሊክ መካከል በግልፅ እና በህቡ የተደረገ የዙፋን ግብግብ ነበር ። በአጼ ምንሊክ ግዜም ይኸው ግብግብ የነበረ ቢሆንም ፤ የአጼ ምንሊክን አልጋ እንደ አይረጋ ሲያደርገው ግን አይታይም ።
ይኽም በመሆኑ ፤ ዘመነ መሣፍንት ወይንም የዘመነ መሣፍንት መገለጫ የሆነው ፖለቲካ እንደ ልማዳዊው አባባል ፤ በአጼ ቴውድሮስ መምጣት እ.አ.አ. 1855 ዓ.ም. ሰአይሆን ያበቃው ፤ አጼ ምንሊክ ንግሥና በአበቃበት እ.አ.አ. በ1913[2] ዓ.ም. ነው ።
ይኽም ማለት ፤ መንግሥት በክፍል አምስቱ በደረሰበት ዘርፈ ብዙ ጥቃት ፤ ከሸዋ ወደ ጎንደር መዓከሉን ከአዞረ በኋላ ፤ ፖለቲካው አዲስ መልክ ይዞ ፤ የተለያዩ ሐገራዊ ሉዕላን (የውጭ እገዛም ተጨምሮበት) መዓከላዊ መንግሥቱን በእጅ አዙርም ሆነ በቀጥታ ከጠባብ ከባቢያዊ ፍላጎታቸው ተነስተው ለመቆጣጠር የአደርጉት አፍራሽ አካኼድ ፤ ትርጉም በአለው መልኩ ተቀልብሶ ፤ መንግሥት እንደ ገና የረጋ መዓከል የኖረው ፤ መናገሻውን ዳግም ከጎንደር ወደ ሸዋ ከአዞረ በኋላ ነው።
ስለ እዚኽ በእዚኽ መጽሐፍ አውድ ፤ የዘመናዊ ፖለቲካ ፓርቲ ምሥረታ ህፀፅ የነበረው ፤ የዘመነ መሣፍንት ፖለቲካ ፤ ከልማዳዊው የዘመነ መሣፍንት ቀደም ብሎ ጀምሮ ከእርሱም ዘግየት ብሎ የእሚጨርስ ነው ወይንም በእዚኽ መጽሐፍ አውድ ዘመነ መሣፍንት እ.አ.አ. በ1560 ዓ.ም. ጀምሮ እ.አ.አ. በ1913 ዓ.ም. ነው የእሚያበቃው ።
በእርግጥ እንደ እሚታየው ፤ ስድስተኛ የአልኩት ክፍል ፤ ከላይ በተቀመጠው ምክንያት እ.አ.አ. በ1560 ዓ.ም. ቢጀምርም ፤ ይኽንን ክፍል ግን ፤ አጼ ፋሲለደስ ንግሥና ‘ማግስት’ እ.አ.አ. 1633 ዓ.ም. ነው የአስጀመርኹት ። ይኽን የአደረግኹት ፤ የግዜው ሰሌዳ እና የታሪኩ ሰሌዳ በመደራረቡ እና ክፍል አምስት የአልኩት እና ኢትዮጵያ እንደ ሐገር የመቀጠሏን ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ የአስገቡት አራት ክስተቶች ፤ እ.አ.አ. ከ1529 ዓ.ም. ጀምረው እስከ 1632 ዓ.ም. በመቀጠላቸው ነው ።
ያም ማለት ምንም እንኳን ዘመነ መሣፍንት በእኔ እምነት እ.አ.አ. በ1560 ዓ.ም. ቢጀምርም ፤ የዘመነ መሣፍንት ፖለቲካ ፤ ክፍል አምስት ላይ የትኩረታችን መዓከል ከነበሩት የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ውስጥ ካስገቡ ችግሮች መካከል የእሚመደብ አልነበረም ።
ምክንያቱም ፦ የዘመነ መሣፍንት ዋንኛው የፖለቲካ አጀንዳ እኔ የእምፈልገው ሰው ይንገስ ወይንም በተለያዩ ሉዕላን መካከል ዙፋኑ ለእኔ ነው የእሚገባኝ በእሚል የእሚደረግ ትግል እንጂ ፤ ኢትዮጵያን በእጅ አዙር የመግዛት ወይንም ኢትዮጵያን እንደ ሐገር ማክሰምን ታሳቢ የአደረገ አልነበረም ። ትግሉ ሐገርን ቢያዳክምም ፤ ሐገር ማዳከሙ የጎንዮሽ ችግር እንጂ የትግሉ ግብ አልነበረም ።
ያም ማለት ፤ ክፍል አምስቱ ሊያስቀምጥ የፈለገው ፤ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ሕልውና ሊያከስሙ የነበሩ ክስተቶች ሲሆን ፤ ክፍል ስድስቱ ደግሞ በተለያዩ የሐገር ውስጥ የፖለቲካ ኃይላት መካከል የተካኼደውን ትልቁን የፖለቲካ ስልጣን ለመቆጣጠር የተካኼደውን ብስለት ጎደል ትግል እና አሉታዊ ውጤቱን ለመዘገብ የፈለገ ነው ።
እነ እዚኽ የተለያዩ ኹለት ይዘት የአላቸው ታሪኮች ግን ፤ በግዜ ስንከፋፍላቸው እ.አ.አ. ከ1529 – 1632 እና 1560 – 1913 ዓ.ም. በአሉ፟ት ግዜያት ውስጥ በቅደም ተከተል በመከስታቸው በግዜ አንጻር ይደራረባሉ (Overlap) ።
ይኽም በመሆኑ ክፍፍሉን በግዜ ማድረጉ ፤ ረጅሙን የሐገራችንን ታሪክ በግዜ ቀመር እየከፋፈሉ በእነዚያኽ የግዜ ቀመሮች ውስጥ የተከናወኑ ወሳኝ ኹነቶች በእሚዘገቡበት አግባብ ሲቀመጡ ፤ ለመረዳት ቀላል ስለ እሚያደርገው ታሪኩን በግዜ መከፋፈሉ ይመረጣል ፤ በመሆኑም የግዜ ክፍፍሉን ትክክለኛነት ለመጠበቅ ክፍል ስድስቱን ፤ በትክክል ከጀመረበት እ.አ.አ. ከ1560 ዓ.ም. ይልቅ ከ1633 ዓ.ም. አስጀምሬዋለኹ ።
በሌላ አገላለፅ ኹነት ተኮር የታሪክ ቅደም ተከተል (Event based chronology) አቀራረብ የእሚፈልገው ሰው ይኽንን ክፍል ስድስትን ፦ አኹን ከእሚገኝበት ክፍል 6 ፡ ከጎንደር ዳግም ወደ ሸዋ (ከ1633 ዓ.ም. - 1901 ዓ.ም.) ይልቅ ክፍል 6 ፡ የአልተሳካ የፖለቲካ ፓርቲ ምሥረታ ጥረት በኢትዮጵያ (ከ1560 ዓ.ም. - 1901 ዓ.ም.) በእሚል ቢገነዘበው ይችላል።
ይኽም በመሆኑ ፤ ስድስተኛው የታሪካችን ክፍል ፤ የግዜ ቀመሩን ለመጠበቅ የእሚመቸው ስያሜ ፤ የኢትዮጲያን ፖለቲካዊ ማዕከል ከሸዋ ወደ ጎንደር እንደገናም ዳግም መልሶ ከጎንደር ወደ ሸዋ የተዛወረበትን አግባብ የእሚያንጸባርቀው ቢሆንም ፤ በሐገራችን በወቅቱ የነበረው ዋነኛ ፖለቲካዊ ኹነት ፤ የአልተሳካ የፖለቲካ ፓርቲ ምሥረታ ጥረት ነበር ።
በእዚኽ ዘመን የነበረው የኢትዮጵያ የፖለቲካ የእሚያጠነጥንበትን ዋነኛ ጉዳይ ምን ነበር? ብለን የጠየቅን እንደ ሆነ ፤ የእምናገኘው መልስ ፦ ዙፋኑ ላይ እኔ የእምደግፈው ሰው ይቀመጥ ወይንም ወደ ማብቂያው ላይ ደግሞ ሕጋዊው ነጋሢ እነ ነኝ በእሚል ለዙፋን የእሚደረግ እሽቅድምድም የእሚስተዋልበት የነበረ ነው የእሚል ነው ።
ይኽ ዓይነቱ አካኼድ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲ ምሥረታ ህፀፅ ነው።
የፖለቲካ ፓርቲን አመጣጥ እና እድገት የእሚያጠኑ ሰዎች ፤ ምንም እንኳን የፖለቲካ ፓርቲ ወይንም አንጃ ወይንም ማሕበር ፤ በለጋነት የሰው ልጅ ፖለቲካዊ ታሪክ ጅማሬ አከባቢ አንስቶ መኖሩን ቢቀበሉም ፤ የዛሬውን ዘመናዊ ቅርፅ ለመያዝ የጀመረው ከአውሮፓዊያን ህዳሴ በኋላ ፤ በሰብዓዊ እኩል ነጻነት አስተሳሰብ ተቃኝተው የተለያዩ ቡድኖች ጠንካራ ፖለቲካዊ መዓከለን ለመቆጣጠር ወይንም ጥያቄያቸውን እንዲያደመጥ ለማድረግ የተደራጀ እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመሩ በኋላ መሆኑን ነው።
የሰው ልጅ ማሕበረሰባት የፖለቲካ ታሪካቸውን የእሚጀምሩት ፤ በቤተሰብ ፣ በመንደር ፣ በጎጥ ወይንም በነገድ ደረጃ ፤ ይኽ ነው የእሚባል የተደራጀ መንግሥት ሳይኖራቸው ፤ እንደ አራሽ ወይንም እንደ ከብት አርቢ ሕዝብ በጋርዮሽ ከእሚኖሩበት ነው ።
ከእዚያኽም በመቀጠል በእዚኽ ኹኔታ ያልተደራጀ እና ያልተማከለ መንግሥት ይዞ መኖሩ ፤ የእሚያመጣባቸው ውስንነት እና የእሚፈጥርባቸው ችግሮች ፤ በእየግዜው እያዳበሩ ከእሚመጡት ፦ የመደራጀት ፣ ጦርነት የማድረግ ፣ ሰፊን አከባቢ እና ሕዝብ የማስተዳደር ፣ ወዘተ ፤ አቅማቸው ጋር ተዳምረው ብዙ ሕዝብ የሰፈረበትን ሰፊ አከባቢ አማክሎ ማስተዳደር እና ከጥቃት መከላከል የእሚያስችላቸውን ፤ እንደ ንጉሣዊ አገዛዝ የአሉ፟ የተማከሉ ፖለቲካዊ ስረዓትን ያቋቁማሉ።
አንድ ግዜ ግን ፤ ይኽን ሰፊ ሕዝብን አማክሎ ማስተዳደር እና ራሱንም ከመሰል ፖለቲካዊ አስተዳደር ጥቃት መከላከል የእሚችል መንግሥት ወይንም ንጉሣዊ ስረዓት ከአቋቋሙ በኋላ ፤ በእዚኽም መልኩ በተዋቀረ ማሕበረሰብ ውስጥ የእሚገኙቱን ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ከአጣጠሙ እና እንደ ቤተሰብ እና እንደ ግለሰብ ራሳቸውን ፤ በእውቀትም በቁስም ከአነጹ በኋላ ፤ በእዚኽ ዓይነት ፓለቲካዊ ውቅር ውስጥ የእሚኖሩ ሕዝብ ቀጣይ የፖለቲካ ፍላጎታቸው ፤ ይኽ ባለ ብዙ አቅም ትልቅ መንግሥት ፤ ይኽን ታሪካዊ እና አስፈላጊ ፤ ትልቅ እና ሰፊ ቦታዎችን አረጋግቶ የማስተዳደር አቅም የአለው መንግሥት ፤ በአብዛኛው ሰፊውን ሕዝብ ከፖለቲካው እያገለለ እና ያለተጠያቂነት (without accountability) በስልጣን ላይ ሆኖ የእሚያደርስባቸው የተለያየ ዓይነት በደል ፤ በግብታዊነት አምጸው መንግሥቱን እንዲጥሉት ያደርጋቸዋል ወይንም ደግሞ በተለይ ከሰብዓዊ የክርስትና መልዕክት በኋላ ፤ በተለያዩ መንገዶች እየተደራጁ መንግሥትን ለማቀብ እና ጥያቄያቸውን እንዲያደምጥ ግድ የእሚሉበት መንገድ ወደ መቀየስ እንዲመጡ ያደርጋቸዋል።
ያለ ሰብዓዊነት ጽንሰ ኃሳብ እንዲኹ አምጸመው መዓከላዊ መንግሥታቸውን ሲያፈርሱ ፤ በአብዛኛው በታሪክ እንደ ሆነው ፦ ስልጣኔዎችን በማጥፋት ፣ የተጀመሩ መልካም ሥራዎችን በማቋረጥ ፣ ሰፊ ሕዝባዊ ዘጸዓት በመፍጠር ፣ ወዘተ ፤ ማሕበረሰባቸውን እና ስልጣኔያቸውን ወደ ፍርሥራሽ ክምርነት ይቀይረዋል።
በአንጻሩ ደግሞ በሰብዓዊ እና በዴሞክራሲያዊ እሴቶች ታጥቀው ፦ በነፃነት በመናገር ፣ በመጻፍ ፣ በመጠየቅ ፣ በመደራጀት ፖለቲካዊ ተሳትፎ ማድረጋቸው ፤ መንግሥታቸው ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ አስፈላጊነት የአለውን አንድነት በማስጠበቅ ስም ፤ የዜግነት ተሳትፎዋቸውን የእሚያግድ እና የኢከነሚያዊ እድገታቸው ደንቃራ እንድ አይሆን ወይንም ትልቅ ፣ አፋኝ እና አባካኝ መንግሥት እንድ አይሆን ፤ የመንግሥታቸውን ስልጣን በተፈጥሮ ሕጉ አግባብ ማቀብ እና ተደማጭነታቸውን መጨመር ሲችሉ ፤ ይኽን ትልቅ እና አስፈላጊ ፈርጣማ ጡንቻውን ለመቆጣጣር የእሚያስችል ሕዝባዊ ወይንም ዴሞክራሲያዊ ሕገመንግሥት እና በእዚኽ ሕገመንግሥት የእሚዋቀረውን መንግሥት በተግባር ለመቆጣጠር ደግሞ የዜጎች ፖለቲካዊ ተሳትፎ አካል የሆነውን የፖለቲካ ፓርቲ የእሚያቋቁሙበት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ ።
አስቀድመን ደጋግመን እንደ አልነው ፤ ከኹለተኛው ፖለቲካዊ አደረጃጀት ወደ ሦሥተኛው አደረጃጀት ፤ ማለትም ብዙ የሕዝብ ብዛት የአለበትን ሰፊ አከባቢ አማክሎ የእሚያስተዳድር አንድ መንግሥት ወደ ጠንካራ ብሔራዊ ነገር ግን ሕዝባዊ ወይንም የዜጎችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት የእሚያከብር መንግሥትነት ለእሚያደርገው ሽግግር ፤ የክርስትና የሰብዓዊነት መልዕክት መተኪያ የሌለው ሚና ተጫውቷል።
የክርስትና ሰብዓዊ መልዕከት የሰዎችን ፖለቲካዊ ግንዛቤ እና አደረጃጀት በመሠረታዊነት እስኪ ለውጥ ድረስ የነበረው የዓለም ሕዝብ ታሪክ ፤ ታላላቅ መንግሥታት ይነሳሉ ፣ ይገናሉ ከእዛም ይከስማሉ የእሚል ነበር። የግብጽ ፣ የባቢሎን ፣ የአሶር ፣ የፐርዢያ ፣ የግሪክ ፣ የሞንጎል ፣ የሮም ፣ ወዘተ ፤ ታሪክ ይኽ ነበር።
ቅድመ የሰብዓዊ መልዕክት የነበሩ እነ እዚኽ መንግሥታት በአደጉ ቁጥር አብሮዋቸው የጭቆና ፣ የብዝበዛ ፣ የስልጣን ፣ የዝና እና የኃብት ሽሚያው በኢሰብአዊ አግባብ አብሮ ስለ እሚያድግ ፤ ምንም እንኳን አንድ አንድ ግዜ በሌላ ተቀናቃኝ የመጨፍለቁ እድል ቢኖርም ፤ በአብዛኛው ግን ኢሰብአዊነታቸው እና ጨልምተኝነታቸው በእሚፈጥረው ውስጣዊ መብላላት ፤ ከውስጥ የእሚዘብጡ ናቸው።
ምንም እንኳን ድህረ ክርስትና የአለው የሰብዓዊነት አስተሳሰብ የአስቻለው ዘመናዊው ሕዝባዊ እና ጠንካራ መንግሥት እንደ ቀደሞቹ ኢሰብዓዊ ጠንካራ መንግሥታት በግዜ በእሚገባ አልተፈተነም የእሚሉ አንድ አንድ ኃያሲያን ቢኖሩም እስከ አኹን በዓለውና ከ3 እስከ 4 መቶ በዓሉት ዓመታት የታዩት ልምዶች (Trend) አግባብ ሲመዘን ፤ ዘመናዊ ሰብዓዊ/ሕዝባዊ እና ጠንካራ መንግሥት በአንድ አጋጣሚ ሰብዓዊነት/ሕዝባዊነቱን እስከ አልለቀቀ ድረስ ፤ ይኽ ነው የእሚባል ወደ ፍርሥራሽ ክምርነት ሊቀይሩት ይችላሉ የእሚባሉ ነገሮችን አሳማኝ በሆነ መልኩ ማቅረብ የእሚችል ፖለቲካዊ እውቀት የለም።
ይኽም ማለት ፤ እስከ አኹን በአለው ታሪክ ፤ ስኬታማ የእሚባለው የሰው ልጆች መንግሥታዊ ዝግመት የእሚያሳየን ፤ ያለ አንድ መዓከላዊ መንግሥት በተበታተነ ኹኔታ ከመኖር ወደ አንድ በተማከለ መንግሥት ወደ እሚመራ ብሔራዊ ሕዝብነት ፤ ከእዛም ክርስትና በአቀበለው የሰብዓዊነት መልዕክት ቆስቆሻነት ደግሞ ከእዚኽ በተማከለ ብሔራዊ መንግሥት ከመመራት ወደ የዜጎቹን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት ወደ እሚያከበር ብሔራዊ መንግሥት ነው የተሸጋገሩት ።
ሠንጠረዥ 9 ፡ የዘመናዊ ፖለቲካ ፓርቲ ስረዓት (የሕዝባዊ መንግሥት) ምሥረታ ኺደት ።
ይኽም በመሆኑ ለተሳካ የፓርቲ ስረዓት ምሥረታ የተደላደለ እና ሰፊ አከባቢን አመካሎ የእሚያስተዳድር ብሔራዊ መንግሥት እና ይኽንንም ብሔራዊ መንግሥት ከሕዝብ ጥቅም አንጻር ለመጠምዘዝ ፖለቲካዊ ዝግጅት የአላቸውን የአስተሳሰብ ቡድኖች የእሚፈልግ ነው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ፅንሰትም ከእዚኽ ቅድመ ኹኔታ ወይንም ሉዓላዊነታቸው ከተረጋገጠ እና ውጤታማ አስተዳደር ከእሚገኝባቸው ሐገራት ውጭ የእማይታሰብ ነው ፦
“… ከእርሱ አስቀድመው ፤ ትልልቅ አከባቢዎችን እና ሕዝብን ለማስተዳድር የእሚያስችሉ ብቸኛ መንገዶች ከነበሩት የዘውድ እና የመኳንንት ስረዓቶች ጋር ነው (የፓርቲ ስረዓት) አመሰራረቱን እና ሚናውን ማነፃፀር የእሚቻለው ።”
“… with monarchy and oligarchy, the only forms of government which prior to its appearance were available for the administration of great territories and populations, it may be fitly compared in the incidence and efficiency of its functions. [117] “
ከእዚያኽም የሰብዓዊነት መልዕክት በእሚፈጥረው መነቃቃት ፤ ይኽንን ጠንካራ ብሔራዊ መንግሥት ከሕዝብ ፍላጎት አንጻር ለመጠምዘዝ የእሚፈልጉ የኃሳብ ማሕበራት ወይንም ፖለቲካዊ ፓርቲዎች ይፈጠራሉ ። ዊልበርት አበት ፤ የፖለቲካ ፓርቲ ጠንካራን መንግሥት ፤ በሕዝብ ፍላጎት አንጻር መጠምዘዣ መሳሪያ መሆኑን እንደ እዚኽ ይገልፀዋል ፦
“… በጠንካራ አስተዳደር እና ከሕዝብ ፍላጎት አንፃር ተጠምዛዥነት መካከል ሊሆን የእሚችል ተግባራዊ ሚዛን … ብሔራዊ ይዘት የአላቸውን አስተያየቶች ወደ መንግሥታዊ ተግባር ለመለወጥ ፤ መዓከላዊውን ስልጣን ሕዝባዊ ፍላጎቶችን የእሚያደምጥ ለማድረግ እና በእዛም ለማስቀጠል የእሚያስችል ፤ እስከ አኹን የተደረሰበት ምርጥ ዘዴ ።”
“… a practical compromise between strong administration and popular control suited to its needs, … the best contrivance yet proposed to convert national opinion into governmental action, to make and keep central authority sensitive to popular will. [117] “
ይኽን መልክ የአለው የፖለቲካ ፓርቲ ምሥረታ ኺደት ራሱ በብዙ ሐገራት እንደ እሚሆነው የዘመናዊ ፓርቲ ምሥረታ ፍኖተ ካርታ ከሆነው በሰብዓዊ አስተሳሰብ ተቃኝቶ ሳይሆን በፋሽንነት ከሰብዓዊ መርኹ ውጭ በኩረጃ ብቻ ሲደረግ ኺደቱ ወደ አሉታዊ የፖለቲካ ፓርቲ ምሥረታ ሊቀየር ይችላል።
ይኽም ማለት አዎንታዊ የፖለቲካ ፓርቲ ስረዓት ምሥረታ ኺደት መጨረሻው በሰብዓዊነት አስተሳሰብ እየተመራ መንግሥትን ሕዝባዊነት ማላበስ እና መንግሥትን የሕዝብ ድምጽ እንዲያደምጥ የእሚያደርግ ሲሆን አሉታዊ የፖለቲካ ፓርቲ ምሥረታ ጥረት ደግሞ መንግሥትን ሕዝባዊ ለማድረግ ወይንም መንግሥትን ከሕዝብ ድምጽ አንጻር ተጠምዛዥ ለማድረግ በእሚል ቢደረግም በአመቺ ኹኔታ ፣ ግዜ እንዲኹም በትክክለኛው ሳይንሳዊው መርኽ እና ይኽንን መርኽ በአግባቡ በተረዱ መሪዎች የእማይመራ ከሆነ በአንድ ሐገር ውስጥ መንግሥትን ሕዝባዊነት የእሚያላብስ የፖለቲካ ፓርቲ ስረዓት ምሥረታ የእሚያስችል ሰአይሆን ሐገርን በእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ዘፍቆ እንደ ኹኔታው በውጤቱ ፤ ሐገራትን የእሚከልስ ሲከፋም ሐገራትን የእሚበታትን እና የእሚያፈርስ ይሆናል።
አንድ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ወይንም የፖለቲካ ፓርቲ ፤ በእንቅስቃሴው በእሚፈጥረው ንዝረት ፤ ሆን ብሎም ይኹን በስህተት ሐገርን ወደ ማፍረስ ወይንም ሐገርን አረጋግቶ ሕዝብን በሳይንስ እና በቁስ እያስታጠቀ የአለውን ጠንካራ መንግሥት አዳክሞ መሠረታዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት ከገታው ፤ አፍራሽ የፓርቲ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ሆኗል ማለት ነው ።
ተገቢው ቅድመ ኹኔታ በሌለበት በፋሽሽንነት ብቻ ተኮርጆ በሕዝባዊ እንቅስቃሴ ስም የእሚደረግ የፖለቲካ ፓርቲ ስረዓት ምሥረታ ኺደት ፤ ከአንድ አንድ አፍራሽ የፖለቲካ ፓርቲ እንቅስቃሴ ይሆናል ።
ይኽም ነው ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፤ የሐገርን አንድነት እና ሉዓላዊነት አስጠብቆ መቀጠል የእሚችል መዓከላዊ ወይንም ብሔራዊ መንግሥት (state) ላይ የእሚበቅሉ ቅርንጫፎች እንጂ በራሳቸው ህልውና እና መሠረት የሌላቸው አደረጃጀቶች የእሚያደርጋቸው ።
የተገነባ ሐገር የፖለቲካ ፓርቲን ያፈራል እንጂ የፖለቲካ ፓርቲ ሐገርን አያቋቁምም ።
በእርግጥ በአንድ አንድ ምክንያቶች በፖለቲካ ፓርቲ የእሚመራ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ፤ በግብ ደረጃ ፤ ሐገርን መበተን እና መንግሥትን ማፍረስ ፤ የሕዝባዊ እንቅስቃሴው ግብ ሊሆን ይችላል ወይንም ግባቸው ይኽ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ ። ለምሳሌ ፦ ማርክሲስቶች ፣ ስረዓት አልበኞች (Anarchists) ፣ ወይንም በተለያየ ግላዊ የስነ ልቦና ምክንያት ፤ በሕዝባዊ እንቅስቃሴ ሐገራትን ማፍረስ እና መንግሥታትን መበተን ግባቸው የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊኖሩ ቢችሉም ፤ አዎንታዊ የፖለቲካ ፓርቲ የእምንለው የተመሠረተች እና የተደላደለች ሐገር ላይ የእሚፈጠሩ ሕዝባዊ አደረጃጀቶችን ነው ።
እነ እዚኽ ዓይነቶቹ ሕዝባዊ እንቅስቃሴን ሐገርን ለማፍረስ እና መንግሥትን ለመበተን የእሚጠቀሙበት የፖለቲካ ፓርቲዎች ፤ ስሪታቸው ወይንም ‘ፍጥረታቸው’ እንጂ አፍራሽ የፖለቲካ ፓርቲ የእሚያደርጋቸው ፤ የፓርቲ ፖለቲካቸው (በፓርቲዎች መካከል የእሚደረገው ፉክክር) አይደለም ።
የእዚኽ መጽሐፍ ተደራሾች ደግሞ በአንዳች ዓይነት ቆልማማ ርዕዮት ወይንም በግላዊ ስነ ልቦና ችግር ምክንያት ሐገር የእምትባለው ውቅር በራሷ ወይንም ይችኽ (አንዲቷ) ሐገር ፤ የእማታስፈልግ እና መጥፋት የአለ፟ባት ናት ብለው የእሚያምኑ ጋጠወጦች (Eccentrics) አይደሉም።
የእዚኽ መጽሐፍ ተደራሾች ፤ ሐገር የሰው ልጆች መልካም የመሻት ውጤት የሆነች እና በውስጧ ለእሚኖሩት ሕዝብ ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ሕልውና አስፈላጊ የሆነች ፣ መቀጠል የአለ፟ባት አደረጃጀት ነች ብለው የእሚያምኑ ሰዎች ናቸው።
ምክንያቱም ፦ በቀደሙት ምዕራፎች ላይ እንደ አልነው ፤ ሐገራት ወደ መሆን የእሚመጡት ፤ አንድ የሆነ ንጉሥ ወይንም ጀግና ፤ አንድ ቀን ሲነቃ የሆነ ሐገር ልመስርት ብሎ በማሰቡ ወይንም የሆነውን አንድ ጦርነት በማሸነፉ ሰአይሆን ፤ ዘመን እና ትውልድ ተሻጋሪ ፤ ለአንድ ሐገር ሕዝብ ሕልውናዊ ቀጣይነት አስፈላጊ የሆኑ ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ምክንያቶች በመኖራቸው ነው ።
ስለ እዚኽ ፦ የፖለቲካ ፓርቲ ስረዓት ምሥረታ ቅደም ተከትለን ስናይ ፦ ሕዝብ በቤተሰብ ፣ በመንደር ፣ በሰፈራ ፣ ወዘተ ፤ ፖለቲካዊ ህልውናቸው ይጀምርና ፤ ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ግንዛቤአቸው ከማስፈጸም አቅማቸው ጋር ሲዳብር ፤ ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ፤ በሰፊ አከባቢ ላይ የአሉ፟ ሕዝብን አማክለው የእሚያስተዳድሩ መንግሥታት የአሉ፟በት ሐገር ወይንም አንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ይፈጥራሉ።
በእዚኽ መልኩ እንደ ሐገር ተቋቁመው እና በአብዛኛው ንጉሣዊ ስረዓት መስርተው ከአበቁ በኋላ ፤ በግዜ በሰብዓዊነት የፖለቲካዊ ስረዓታቸውን ከቃኙ ፤ የሰብዓዊነት አስተሳሰብ በእሚፈጥረው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ እና የእውቀት አብዮት ፤ ጠንካራ ብሔራዊ መንግሥታቸውን ወደ ሕዝባዊ ብሔራዊ መንግሥት የአሸጋግሩታል።
በታሪክ አጋጣሚ ደግሞ ፤ የሰብዓዊነት አስተሳሰብ የፖለቲካ ስረዓቶችን አወቃቀር መለውጥ ግድ ከአለበት ግዜ በፊት ከነበሩ ፤ በስረዓታቸው ስሪታዊ ኢሰብአዊነት ምክንያት በግዜ ኺደት በእርስ በእርስ ጦርነት ፣ በክዳት ፣ በግብታዊ ሕዝባዊ አመጽ ፈራርሰው ወደ ክምርነት ይቀየራሉ።
የሰብዓዊነት አስተሳሰብ የፖለቲካ ስረዓቶችን አወቃቀር መለውጥ ግድ ከአለበት ግዜ በኋላ ኖረውም ፤ ለሕዝባዊ መንግሥት ምሥረታ የእሚያስፈልጉት ፦ ብሔራዊት ሐገር ፣ ይችኽን ብሔራዊት ሐገር አማክሎ የእሚያስተዳድር ጠንካራ ብሔራዊ መንግሥት ፣ የሕዝባዊ መንግሥት አስፈላጊነት እና ምንነት የገባቸው የፖለቲካ አመራሮች ፣ ወዘተ ፤ በሌሉበት ኹኔታ ፤ የፖለቲካ ፓርቲ ምሥረታ ኺደትን በፋሽንነት ብቻ ቀድተው በሕዝባዊ መንግሥት ምሥረታ ስም የፖለቲካ ፓርቲ ስረዓት ምሥረታ የእሚያደርጉ ሰዎች በአሉበት ኹኔታም ፤ የፓርቲ ምሥረታው ኺደት አሉታዊ በመሆን ፤ ብሔራዊውን መንግሥት አጓጉል በማዳከም ለፖለቲካ ፓርቲ ምሥረታ ቅድመ ኹኔታ ከሆኑት ነገሮች አንዱን እና ቀዳሚውን ጠንካራ ብሔራዊ መንግሥት ይጎዳሉ ከከፋም የፖለቲካ ፓርቲ ምሕዳሯን ፥ ሐገርን ራሷ በማፍረስ ይጠናቀቃሉ።
ለእዚኽም ነው ፤ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ሚናው አዎንታዊ እንዲሆን የሐገርን ፋይዳ የአለምንም ብዥታ ተረድቶ እና በተመሠረተች ፣ በተደላደለች ፣ አንድነቷ እና ሉዓላዊነቷ በተከበረች ሐገር ላይ ፤ ተጨማሪ እሴት ለመጨመር በእሚል አስተሳሰብ እና አስተሳሰብ ብቻ መቃኘት የአለበት ።
ለአዎንታዊ ፓለቲካ ፓርቲዎች ቅድመ ኹኔታው ይኽ ቢሆንም ፤ የሐገርን ፅንሰኃሳብ ፤ በፅንሰ ኃሳብነት ተቀብለው እና በሕዝባዊ እንቅስቃሴ መንግሥትን ለመጠምዘዝ የእሚፈልጉ ፤ በስሪታቸው ወይንም ‘በተፈጥሮዋቸው’ አዎንታዊ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን ፦ በአልዳበረ ማሕበረሰብ ውስጥ በጥራዝ ነጠቅ የለውጥ ናፋቂነት እና ከውጭ የለውጥ ኃይሎች በእሚደረግላቸው እገዛ ፤ የለውጥ ኃሳብ ተሸካሚ ሆነው ፤ የተዳከመን መንግሥት ምርኮኛቸው አድርገው ለውጥን ለመጫን ሲንቀሳቀሱ ግን ፤ ምንም እንኳን ግባቸው እና ዓላማቸው ወይንም ስሪታቸው አፍራሽነት ባይሆንም ፤ አፍራሽ ወይንም አሉታዊ የፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ ገብተዋል ማለት ነው ።
ሕዝብ እንግዲኽ ፦ በእዚኽ መልኩ ከቤተሰብ ፣ ከጎጥ ፣ ከመንደር ወይንም ከነገድነት ወደ በሰፊ አከባቢ ላይ የእሚገኙ ፤ ኢከነሚያዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳ የአላቸው ሐገር ወደ መሆን እስኪ ሸጋገሩ ፤ በሺ የእሚቆጠሩ ዓመታት ፤ እንዲኹም እነ እዚኽን ዘውዳዊ ትልልቅ ሐገራት አኹን ወደ እምናውቃቸው ሕዝባዊ ሐገራት እስኪ ያሸጋግሩ (ከተሸጋገሩም) ደግሞ እንደ እዚኹ በሺ እሚቆጠሩ ዓመታት ፈጅተዋል ።
ኢትዮጵያም እንደ ሐገር ፤ አንደኛው ወይንም የመጀመሪያው ከአልነው የታሪካችን ክፍል መጨረሻ አንስታ ፤ ኹለተኛውን የፖለቲካ ሽግግር የአደረገች በመሆኑ እና ይኽ የታሪካችን ክፍል በእሚጀምርበት በ16/17ኛው መዕተ ዓመት ፤ እነ ኢዛናን መሰል ነገሥታት ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ከተባሉ ከ1 ሺ ዓመተታ በላይ በመቆጠሩ ፤ ይኽም በዘመነ አክሱም የተጀመረ የኢትዮጵያ ንጉሣዊ ስረዓት ምንም እንኳን የክርስትና ሰብዓዊ መልዕክት በፈጠረው መደናገር ቢዘምም ፤ በእነ አምደ ፅዮን ዘመን ዳግም እንደገና እጅግ የደረጀ እና ከሰኃራ በታች በአለው ጥቁር አፍሪካ የወቅቱ ጠንካራ መንግሥት የነበረበት ደረጃ ላይ በመድረሱ ፤ በእዚኽ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ፤ በሰው ልጆች የፖለቲካ ታሪክ ኺደት የመጨረሻው እና ሦሥተኛው ደረጃ ወደ ኾነው ፤ በፖለቲካ ፓርቲ መሳሪያነት መንግሥታቸውን ሕዝባዊ ለማድረግ ቅድመ ኹኔታ የሆነውን ጠንካራ ብሔራዊ መንግሥት ግንባታ ጉዳይ በአመርቂ ኹኔታ በማጠናቀቃቸው ፤ ‘ተፈጥሮዋዊው’ ቀጣዩ ዀኔታ ሕዝባዊ መንግሥትን የእሚያስችለው የፖለቲካ ፓርቲ ስረዓት ግንባታ ውስጥ መግባት ነበር ።
በዘመናዊው ዓለም ሕዝብ ፤ መንግሥታቸውን በፖለቲካ ፓርቲ መሳሪያነት ሕዝባዊ የአደረጉ ሐገሮችም ታሪክ ይኽንኑ የእድገት ቅደም ተከተል የእሚያሳይ ነው ።
ከእላይ እንደ አልነው ፤ የፖለቲካ ፓርቲን አመጣጥ እና እድገት የእሚያጠኑ ሰዎች ፤ ምንም እንኳን የፖለቲካ ፓርቲ ወይንም አንጃ ወይንም ማሕበር ፤ በለጋነት የሰው ልጅ ፖለቲካዊ ታሪክ ጅማሬ አከባቢ አንስቶ መኖሩን ቢቀበሉም ፤ የዛሬውን ዘመናዊ ቅርፅ ለመያዝ የጀመረው ፤ በሐገረ እንግሊዝ ተኃድሶ (Reformation) ከእሚባለው ኃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ እንደሆነ ነው የእሚስማሙት ።
በፖለቲካ ፓርቲ አጀማመር ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ የጻፈው ዊልበር ሲ. አበት (Wilbur C. Abbott) ፤ የዘመናዊ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምሥረታ ህፀፅ በ16ኛው ምዕተ ዓመት አከባቢ ከተኃድሶ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ መጀመሩን ያስቀምጣል ፦
“እነ እዚኽ ኃሳቦች የተገነጠሉበትን እና በአንዱ መገንጠያ ላይ እየተቋጠሩ ወይንም እየተጋገሩ ፤ ዘመናዊውን ስረዓት የመስረቱበትን አኳኋን ለመረዳት ቢያንስ ቢያንስ እስከ ተኃድሶው ግዜ ወደ ኋላ መኼድ አለብን ።”
“For a point of departure of those ideas and conditions whose crystallization produced the modern system, we must go back at least as far as the reformation. [117]“
ዘመናዊው ስረዓት የእሚለው ፤ የሕዝባዊ መንግሥቱን እና እርሱን የእሚያስችሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች የአሉ፟በትን ስረዓት ነው።
ይኽ በሐገረ እንግሊዝ የተኃድሶ ዘመን የእሚባለው እና ለዘመናዊ የፓርቲ ስረዓት ምሥረታ እንደ መገንጠያ ሆኖ እየቀረበ የአለው ክስተት (እ.አ.አ. 1534 ዓ.ም.) ፤ የአውሮፓዊያን ህዳሴ ትሩፋት የሆነው ዘመን ሳይንስ በሰጣቸው እውቀት እና እርሱንም ተከትሎ በተፈጠረ የጠያቂነት መንፈስ ፤ የነቃው የሕብረተሰብ ክፍል ከእዚኽ በፊት ሳያንገራግር ይቀበል የነበረውን ኃይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ አካኼድ ፤ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ትችት ወይንም ሙግት በመጀመሩ የመጣ አዲስ ማሕበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ አወቃቀር ነው።
ስለ ተኃድሶው ከእላይ የጠቀስነው ዊልበር አበት እንደ እዚኽ ይላል ፦
“ታላቁ ተኃድሶ ብለን የእምንጠራው እንቅስቃሴ ፤ በኃይማኖት እና በእውቀት መስክ ፤ ዜጎች በተናጠል በራሳቸው አመዛዝኖ እና ምርምር የደረሱበትን ግንዛቤ ይዘው የነገሠው ባለስልጣን የእሚያራምደውን የእማይጠየቅ ቀኖና የመቃወም ኺደት ነው ። … ውጤቱም ሐገሪቱን ፦ በኢከነሚው ፣ በእውቀት ፣ በማሕበራዊ ፣ በኃይማኖታዊ እና በፖለቲካዊ መስክ እንደገና የሰራ ነበር ።“
“The great movement that we call the Reformation was essentially on its religious and intellectual side a protest against enthroned authority by private judgement which founded itself on reason and investigation as against dogma. … the result was the remaking of the nation, economically, intellectually, socially, religiously, and politically. [117]“
በእዚኽ ዘመን በተገኘው እውቀት ላይ የተመሠረተ ጠያቂነት ፤ በሐገረ እንግሊዝ ተጠያቂ የአደረገው አንዱ እና ዋነኛው ጉዳይ ፤ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለረዥም ግዜ ይዛ የቆየችው ፦ ‘የሮማው መንበር በሐዋሪያው ጴጥሮስ የተመሠረተ በመሆኑ ፤ በዓለም ላይ ያሉ ቤተክርስቲያኖች ኹሉ ፤ በእዚኽ መንበር አስተዳደር ስር መሆን አለባቸው’ የእሚለውን ነበር ።
የሮማው መንበር በእዚኽ እድሜ ጠገብ ቀኖናው እና ትልቅ የማስተዳደር አቅሙ የመላው አውሮፓን ክርስቲያናዊ መንግሥታት በስሩ አድርጎ እና ይኽም አውሮፓዊ የአስተዳደር መረብ ፤ በእያንዳንዱ ሐገራት ውስጥ ኃይማኖታዊ ቀኖና እና የስነ ምግባር ቁጥጥር ለማድረግ መብት ሰጥቶት ስለ ነበር ፤ በእየ ሐገሩ የአውሮፓ ህዳሴ ትሩፋት የሆኑ (በዋናነት የዜጎች ተፈጥሮዋዊ እኩል ነጻነት ላይ የተመሠረቱ) በሳይንሳዊ እውቀት ላይ የተመሠረቱ አዲስ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እና ፖለቲካዊ አስተሳሰቦች ይዘው ይኽንን የሮማው መንበር ፤ ‘የዓለም ቤተክርስቲያኖች ኹሉ በእኔ የአስተዳደር መንበር ስር መሆን አለባቸው’ ከማለቱ የተነሳ የእሚፈቅዳቸው እና የእሚያግዳችው ነግሮች ከኃይማኖታዊ ጉዳዮችም ውጭ ማሕበራዊ እና ኢከነሚያዊ ይዘት የነበራቸው በመሆናቸው ፤ የዘመኑ ሊህቃን መጽሐፍ ቅዱስን እና የአዕምሮን ፍርድን ወይንም አመክንዮን አጣምረው ፤ የሮማው መንበር ይኽ የዓለም ዓቀፍ የክርስትና ማዕከል ነኝ የእሚለው ነገር መሠረት እንደ ሌለው በመሞገት ፤ ለዘመናት ቆይቶ የነበረውን ልማድ የእሚቃረን በዘመኑ እውቀት የተቃኘ የአስተዳደር እና የስነ ምግባር አስተሳሰብ ማራመድ ጀመሩ ።
ይኽ የተራማጅነት ወይንም የለውጥ ፍላጎት ግን ፤ እንደ ማንኛውም የለውጥ እንቅስቃሴ ሐገራዊ የሆኑ ወግ አጥባቂያን ተቃውሞ ነበረበት ።
በአንድ በኩል የተኃድሶ እንቅስቃሴ መሪዎች (ጴንጤዎች) ፤ ከማዕከሉ የተለየው አዲስ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረዳታቸውን ስህተት ነው እያለ ከእሚከሳቸው የካቶሊክ መንበር ተነጥለው በገባቸው መንገድ አምልኮዋቸውን ለማድረግ ፤ ይኽን አዲስ የአምልኮ መንገዳቸውን የእሚፈቅድ አዲስ ዓይነት የቤተክርስቲያን አደረጃጀት ሲፈልጉ ፤ ወግ አጥባቂያኑ ወይንም የቆየው የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ደግሞ ከሮማው መንበር ጋር ለመቆየት በመፈለጋቸው የተፈጠሩት ውጥረቶች ፤ ከሌሎች ብዙ ደጋፊ ምክንያቶች ጋር በመሆን ሕዝብን ለኹለት ከፈሉት ።
ሕዝብ በእዚኽ መልኩ ተከፋፍሎ መሐል መጥፋቱ ፤ የአሳሰበው መንግሥት ደግሞ ከኹለቱ ጎራዎች አስታራቂ ኃሳቦችን ሰብስቦ ለዘብተኛ ጎራ ለመፍጠር በመነሳቱ ሌላ ሦሥተኛ ጎራ እንዲኖር አደረገ ።
ይኽም ኹኔታ የወቅቱን የእንግሊዝ መንግሥት ከሌሎች ምክንያት ጋር ተዳምሮ ፤ በቅርፅ ካቶሊካዊት በይዘት ደግሞ ‘ጴንጤናዊት’ የሆነችውን የአንገሊካን ቤተክርስቲያን ወደ ማቋቋም እንዲመጣ አደረገው፦
“የካቶሊክ ወግ አጥባቂያን እና የካቶሊክ ተኃድሶ መሪዎች ለኹለት በመከፈል ካቶሊክ እና ተቃዋሚዎች (ፕሮቴስታንት ወይንም ጴንጤ) ሆኑ ። ዙፋኑም ከጳጳሱ ፍፁማዊ ስልጣን ራሱን በማግለል ፤ በእንግሊዝ የሮም ቤተክርስቲያን እንድ እትፈርስ እና እውቅና እንደ አይኖራት በማድረግ ፤ የአማካዩን ቦታ የያዘች ፤ በስተመጨረሻ በቅርፅ የካቶሊክን ቤተክርስቲያን የእምትመስል በቆኖና ግን ፕሮቴስታንት የሆነችውን ፤ የአንገሊካን ቤተክርስቲያን በመንግሥት ተቋቋመች ። ይኽም ከኹሉም አንጃዎች ለዘብተኛ የሆኑትን ሰዎች ሲይዝ ፤ እጅግ ፅንፈኛ የሆኑት ካቶሊኮች እና ትንሽ ቀደም ያሉት ፕሮቴስታንቶች ወይንም በኋላ ንፁህተኞች የተባሉት ፤ ራሳቸውን ገሸሽ የአደረጉበት ሆነ ።”
“Catholic conservatives and Catholic reformers gave way to the sharper division of Catholic and Protestant. The crown broke away from papal supremacy, the Roman in England was disestablished and disowned, and finally replaced by an Anglican church set up by the government, which, largely Catholic in form and organization but protestant in doctrine, occupied the middle ground. This included moderate men of all groups, but from it the more extreme Catholics and the more advanced Protestants, or Puritans as they came to be called, alike stood aloof. [117]“
በእዚኽ ኺደት ፤ ኹላችንም እኩል እና ነጻ ፍጥረቶች በመሆናችን በነጻነት የማሰብ እና በኃሳባችን ዙሪያ ተሰባስበን የእሚመስለንን ማድረግ እንችላለን የእሚለው የሰብዓዊ እኩልነት ትሩፋት የሆነው አስተሳሰብ ፤ በአንድ በኩል ፅንፈኛ ወይንም ስር ነቀል ለውጥ ፈላጊዎች ፣ በሌላ በኩል ፅንፈኛ ወግ አጥባቂያን ፥ ከእነርሱ መካከል ደግሞ መንግሥት ከለውጥ ፈላጊዎቹ እና ከወግ አጥባቂያኑ ለዘብተኞቹን በመያዝ አንድ ጎራ በመፈጠር ፤ በኃይማኖቱ መስክ ፤ በእዚያኽን ወቅት በሐገረ እንግሊዝ ሦሥት ጎራ ፈጠረ ማለት ነው።
ይኽም ፤ የወቅቱ የእንግሊዝ መንግሥት በ16ኛው ምዕተ ዓመት በዋናነት ከፕሮቴስታንት እና ካቶሊክ አክራሪዎች በደረሰበት ጫና ፤ ከኹለቱም በመነጠል ፤ ለካቶሊኮችም ለፕሮቴስታንትም መኻከለኛ የሆነች አንገሊካን (ኢንግሊዛዊ) የእምትባል ቤተክርስቲያን በማቋቋም መሐሉን እንዲይዝ አደረገው።
በእዚኽ የታሪክ አጋጣሚ እንደ እሚታየው ፤ በሐገረ እንግሊዝ የሆነው ነገር ፤ እያደገ በመጣው የነጻነት እና የእኩልነት እውቀት ዜጎች እየተበረታቱ ፤ ከአንድ መዓከል የእሚተላለፍላቸውን ኃይማኖታዊ እና ልማዳዊ አሰራር መጠየቅ በመጀመራቸው ፤ ለረዥም ዘመን የተለመዱ አሰራሮች ለእሚቀርብባቸው መጠነ ሰፊ እና በአብዛኛው ፍትኃዊ ጥያቄ ተገቢ መልስ ማቅረብ የእማይችሉ በመሆናቸው ህልውናቸው ጥያቄ ውስጥ የገባበትን ኹኔታ ነው ።
ይኽም ግብግብ በሰብዓዊ እውቀት በታነጸው የሕዳሴው ማሕበራዊ ሳይንስ እውቀት አማካኝነት በግዜ ኺደት ፤ መንግሥት ፍትኃዊ የሕዝብ ጥያቄዎችን እንዲያደምጥ የእሚያደርጉት እና ሕዝባዊ ድጋፍ የአላቸው አሰራሮች ወደ ብሔራዊ አጀንዳነት የእሚቀየሩበትን የፖለቲካ ፓርቲ ስረዓት ግንባታ እንዲያቋቁሙ አስቻላቸው።
በሐገረ እንግሊዝ ለፖለቲካ ፓርቲዎች መመሥረት ምክንያት የኾነው ይኽ ጠያቂነት በዋናነት ፤ ሰው ኹሉ በእግዚአብሔር ፊት እኩል ነው በእሚለው አስተሳሰብ ተቃኝቶ ፤ ለምሳሌ ፦ የሮማው ጳጳስ የእማይከሰስ ፣ የእማይጠየቅ የዓለም ዓቀፏ ቤተክርስቲያን ብቸኛ ሉዓላዊ መሪ በመሆኑ ምንም ዓይነት ብያኔ ቢያሳልፍ በተገዢነት ከመቀበል ውጭ እርሱን መጠየቅ አመጸኝነት እና እምቢተኝነት ነው ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ምዕመናን በግላቸው አንብበው እንዲረዱ አይፈቀድላቸውም ይልቁንም ቀሳውስት እያነበቡ እንዲያስተምሩዋቸው ነው የእሚገባቸው ፣ ወዘተ ፤ የእሚሉትን የተዋረድ አስተሳሰቦች ፤ በክርስትና ሰብዓዊነት ምክንያት ጥያቄ ውስጥ በመግባታቸው የመጣ ነው።
በሌላ አገላለጽ የክርስትና የአስተሳሰብ እምረታ ፤ ነባራዊውን አሰራር ፤ ክርስትና ከእሚያስተምረው የሰብዓዊ እኩልነት የተነሳ እንዲጠየቅ በማድረጉ ፤ ኺደቱ በግዜ ኺደት ፖለቲካዊ በኃሪ እየተላበሰ በኃሳብ ዙሪያ እየተደራጁ መንግሥትን ማቀብ ፣ ግድ ማለት ፣ ሕዝባዊ ማድረግ እየሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምሥረታን አበሰረ።
ከላይ በተጠቀሰው ጽሑፍ ላይ በሐገረ እንግሊዝ የተከናወነው ይኽ ታላቁ ተኃድሶ ፤ በኃይማኖት ጉዳይ ብቻ ሳይወሰን የመጠየቅ ልማዱ እየተስፋፋ ፤ ኹሉንም የማሕበራዊ እና የእውቀት መስኮች የእሚነካ ስለ ነበር ፤ ጠያቂነቱ ከኃይማኖቱም በረት ወጥቶ ሌሎቹን እንደ ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ገፅታ የአላቸውን ማሕበራዊ ጉዳዮች ስለ ነካ ፤ መላ ሐገረ እንግሊዝን ለዘመናዊ ፖለቲካዊ እና ኢክኖሚያዊ አሰራር በእሚያመች መልኩ እንደ ገና ሊያዋቅራት ችሏል ።
ይኽን መሰሉ ኺደት ነው እንግዲኽ እንግሊዝን ፤ በዘመናዊው ዓለም የመጀመሪያው ዘመናዊ ፓርቲ መፍለቂያ ሐገር የአደረጋት ።
ግለሰቦች በሰብዓዊው እውቀት በመታነጻቸው ፤ በፖለቲካውም ሆነ በኢከነሚው መስክ የእሚመስላቸውን የግላቸውን ኃሳብ እየቋጥሩ እና በኃሳብ ዙሪያ ሆኖው ፤ የእማይጠየቁ እና ኹሉም ሳይጠራጠር ይቀበላቸው የነበሩ የተለያዩ ቀኖናዎችን መገዳደር የጀመሩበት ማሕበራዊ ንቃት ፤ አንደኛ ለመንግሥት ራሱ አዎንታዊ ለውጦችን ለማምጣት የእሚያግዘው በመሆኑ (ለምሳሌ ፦ በሐገረ እንግሊዝ ንጉሡ ከሮማዊ ጳጳስ የብረት አገዛዝ ራሱን እንዲያላቅቅ እና አስተዳደራዊ ነጻነቱን እንዲያገኝ በር ከፍቶለታል) እና ወግ አጥባቂያኑን ተከትሎ ፍትኃዊውን ሕዝባዊ ጥያቄ ቢያፍን ከጥቅሙ ይልቁ ጉዳቱ የእሚያመዝን መሆኑን በመረዳቱ ፤ ሐገረ እንግሊዝ ዘመናዊ የፖለቲካ ፓርቲ የጀመረባት ሐገር ለመሆን አብቅቷታል ።
እንግሊዝን ለእዚኽ ታሪካዊ ስኬት የአበቃት ወይንም በዘመናዊ ዓለም የመጀመሪያቱ ወደ ሕዝባዊት ሐገርነት የተሸጋገረች ሐገር መሆን የቻለችው ግን ፦ የክርስትና ሰብዓዊነት መልዕክት ፖለቲካዊ ቃና መያዙ ከፈጠረው መነቃቃት በተጓዳኝ ፤ በተፃራሪ ሕዝባዊ የፖለቲካ ኃይላት መካከል የእሚደረገው ግብግብ መሸከም የእሚችል መንግሥት የነበራት በመሆኑ ነው ።
ምንም እንኳን ፤ ኢትዮጵያ በዘመነ መሣፍንት ወይንም በእዚኽ የታሪካችን ክፍል መጀመሪያ ላይ ፤ ኢትዮጵያ ፥ እንግሊዝ ደርሳበት ከነበረው ማሕበረሰባዊ እድገት ላይ በበቂ ኹኔታ ደርሳ የነበረች ቢሆንም ፤ ለምሳሌ ፤ በ16ኛው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ ላይ ኢትዮጵያ ፦
• ሰፊ ግዛት የእሚያስተዳድር ለብዙ መቶ ዓመታት የቆየ ንጉሣዊ መንግሥት
• ሐገራዊ ይዘት የአለው አንድ የክርስትና እምነት
• ኃይማኖታዊ ቀኖናዎችን በግል የመተርጎም እና አቋም የመያዝ እንቅስቃሴ
• ከአውሮፓ ሕዳሴ የእውቀት መዓከላት ጋር ግንኙነት በማድረግ ራሱን ከወቅቱ ዓለማዊ ክስተቶች ጋር በማዛመድ ላይ የእሚገኝ መንግሥት እና የሊህቃን ማህበራት
የነበራት ቢሆንም ፤ በኢትዮጵያው ውስጥ የተጀመረው አንጀኝነት ፤ በግዜ ኺደት ወደ ውጤታማ የፖለቲካ ፓርቲ እና ወደ ሕዝባዊ መንግሥትነት ሐገሪቱን ከማሸጋገር ይልቅ ፤ በአሉታዊ የፖለቲካ ፓርቲ ምሥረታ ኺደት አንጀኝነቱ ማብቂያ ወደ ሌለው ወደ ተራ ጎጠኝነት እና የስልጣን ሽሚያ እንድ እታመራ ነው የአደረጋት ።
እንደ እሚታወቀው ፤ ዘመነ መሣፍንት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲን ስረዓት አስጀምሮ እና የኢትዮጵያን መንግሥት ወደ ሕዝባዊነት አሸጋግሮ አይደለም የተጠናቀቀው ።
ይልቁንም ፤ የለውጥ እንቅስቃሴው ኃዲዱን ስቶ ፤ በክፍሉ አምስቱ የታሪካችን ክፍል የአየናቸው አራት ትላልቅ ሱናሚዎች በከፍተኛ ደረጃ የአናወጡትን ብሔራዊ መንግሥት ፤ በእዚኽ ዘመን የእየ አከባቢው ጎበዝ አለቆች እና ሉዕላን ከራሳቸው ጠባብ ከባቢያዊ ፍላጎት አንጻር ለመቆጣጠር የእሚያደርጉት ጥረት ፤ ብሔራዊ መንግሥቱን ይባሱን አዳክሞት ፤ ብሔራዊ መንግሥቱ ይኽንን በሰብዓዊ ርዕይ ተቃኝቶ የእሚካኼድ መንግሥትን አደብ የማስገዛት እና ፍትኃዊ ፖለቲካዊ ተሳትፎ የማሳደግ ጥያቄ የእሚመራ ሳይሆን በጠባብ ጎጠኝነት ፣ ባንዳነት እና አጨብጫቢነት እየተመሩ ብሔራዊ መንግሥቱን ከጠባብ ጎጦኛ ፍላጎት አንጻር የመቆጣጠር ፍላጎት አክስሞ ፤ ብሔራዊ መንግሥቱን በአዲስ መልክ በማማከል እና በማጠናከር ከአልተጠናቀቀ ፤ በተለይ እንደ አፍላል ውኃ እየተንደረደረ ከመጣው ቀኝ ግዛት ጋር ተዳምሮ የሐገሪቱን ህልውና የእሚያከስም በመሆኑ ፤ ዘመኑ በአጼ ምንሊክ የተማካለ ጠንካራ መንግሥት በመፍጠር ነው የተጠናቀቀው።
በሌላ አገላለፅ ከላይ በአስቀመጥነው የማሕበረሰብ ፖለቲካዊ እድገት ቅደም ተከተል መሠረት ፤ ከቤተሰብነት ፣ ከመንደርነት ወደ መንግሥትነት ፣ ከመንግሥትነት ወደ ሕዝባዊ መንግሥትነት የነበረው ሽግግር ፤ በዘመነ መሳፍንቱ ፖለቲካ አፍራሽነት ፤ ከጠንካራ መንግሥትነት ወደ ሕዝባዊ መንግሥትነት ሊደረግ ይገባው የነበረው ሽግግር ሙሉ በሙሉ ከሽፎ ፤ በእዚኽ አፍራሽ ኺደት የተዳከመውን እና ለሕዝባዊ መንግሥት ቅድመ ኹኔታ የሆነው ጠንካራ ብሔራዊ መንግሥት (State) ዳግም በመመሥረት ነው የተጠናቀቀው ።
ይኽ ዘመን በ1901 ዓ.ም. ሲጠናቀቅ ፤ እንደ ስኬት የታየው ነገር ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት እ.አ.አ. በ1529 ዓ.ም. ወደ ነበረበት ጥንካሬ መመሉሱ ሆኖ ነበር ። እንደ ኢትዮጲያ አቆጣጠር በ1901 ዓ.ም. ወደ ፊት ተራምደን ፦ በፍትሐዊ እና ገለልተኛ ሕዝባዊ ምርጫ የእሚሰየሙ ሕግ አውጭዎች (ፓርላማ) እና የመንግሥት አስፈጻሚዎች ፣ በዘመናዊ መልኩ የተደራጀ ጦር ፣ ዘመናዊ የኢከነሚ ስረዓት ፣ ዘርፈ ብዙ ሕዝባዊ አገልግሎት የእሚሰጡ ተቋሞች ፣ ወዘተ ፤ ገንብተን መገኘት ሲኖርብን ፤ ስኬታማ ክለሳ ለማድረግ ነበር የተገደድነው ።
ይኽ የሕዝባዊ ዕንቅስቃሴ መልክ የነበረው የኢትዮጵያ ዘመነ መሣፍንት ፤ መንግሥት በክፍል አምስቱ የታሪካችን ክፍል እጅግ በመዳከሙ እና አጣብቂኝ ውስጥ ከመግባቱ የተነሳ በሐገር ውስጥ የተፈጠሩ አራት ክስተቶች ፤ በዓለም ዓቀፉ አውድ እንግሊዝን በማሳያነት ተጠቅመን ከአሳየነው የፖለቲካ ፓርቲዎችን የእሚያስችለው ሕዝባዊን መንግሥት ከመፍጠር ኺደት በተቃራኒ ፤ ቀድሞውንም ተዳክሞ የነበረውን የኢትዮጵያን ሕዝብ እና መንግሥት እስከ እነ ጭራሹም አዳክሞት ፤ ብቸኛው የመዳ፟ኛው መንገድ ፤ መንግሥትን እንደገና ወደ ቅድመ እ.አ.አ. 1529 ዓ.ም. ጥንካሬው መመለስ አድርጎት አልፏል ።
ይኽ የፖለቲካ ፓርቲ ምሥረታ ጅማሮ ፤ በኢትዮጵያ ልዩ ኹኔታ ኃዲዱን ስቶ ፤ በአፍራሽነት እንዲ ደመደም ከአደረጉት አራት ክስተቶች የመጀመሪያው ፦ ሰፊው (አብዛኛው) የኢትዮጵያ ሕዝብ በመንግሥት መዳከም ምክንያት ማሕበራዊ እድገቱ የተገታ በመሆኑ ነው ።
ምንም እንኳን የወቅቱ የኢትዮጵያ ማሕበረሰብ ፤ በዘመኑ መመዘኛ ቀላል የእማይባል እውቀት የነበረው ቢሆንም ፤ በእዛኽን ዘመን የነበረው የእውቀቱ ልክ ግን እንደ ማንኛውም የወቅቱ እና ወደ ዘመናዊው ስረዓት በሽሽግግር ላይ እንደ ነበረ አውሮፓዊ ገና በማበብ ላይ የነበረ እንጂ እየመጣ የአለውን ለውጥ በአግባቡ ተረድቶ ፤ ጥቅም ከጉዳቱን ለይቶ ፤ የእሚወሰደውን ወስዶ የእሚጣለውን የእሚጥልበት ደረጃ ላይ የደረሰ አልነበረም ። በሌላ አገላለጽ ፤ አውሮፓዊያንም ኢትዮጲያ በእዚኽ ዘመን በገባችበት ታሪካዊ አጣብቂኝ ውስጥ ቢገቡ እና የማሕበረ ኢከነሚ እድገታቸው ቢቀነጭር ፤ ወደ ሕዝባዊ መንግሥት የተሳካ ሽግግር አያደርጉም ነበር።
ምክንያቱም ፦ በአውሮፓ ራሱ ፤ ትርጉም በአለ፟ው መልኩ የሕዝባዊ መንግሥት አስተሳሰባቸው በሰብዓዊ አስተሳሰብ ተቃኝቶ ትርጉም የአለው እምርታ ማሳየት የጀመረው በ17ኛው ምዕተ ዓመት መጨረሻ እና በ18ኛው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ አከባቢ ነው ።
ይኽም ማለት ፤ በወቅቱ በእየግዜው እየጨመረ የመጣው የሳይንስ ብርሀን ሰዎችን ወደ ለውጥ መግፋት የጀመረው ቀደም ብሎ በ15ኛው እና በ16ኛው ምዕተ ዓመታት ቢሆንም ፤ የወቅቱ እውቀት በአግባቡ ዳብሮ ትርጉም በአለው እና አዎንታዊ በሆነ መልኩ ተቀባይነት የአለው የማሕበራዊ ሳይንስ እውቀት እስኪሆን ከመቶ ያላነሱ ዓመታት ፈጅቷል ።
ይኽም ማለት ፤ የአንድ ሐገር ሕዝብ ከለውጡ ተጠቃሚ ለመሆን ቢያንስ ይህንን መቶ ዓመት ፤ማለትም 17ኛው ምዕተ ዓመትን ፤ በእየግዜው እየዳበረ ከእሚኼደው በሰብዓዊነት አስተሰሰብ በመቃኘት ላይ በእሚገኘው ከማሕበረ ሳይንስ እውቀት ጋር መቆየት አለበት ። በታሪክ አጋጣሚ ከእዚኽ እውቀት ማዕከል ጋር እትብቱ ከተቆረጠ ፤ መጀመሪያ ላይ በያዛቸው ፍንጣቂ እውቀቶች ብቻ ውጤታማ ሽግግር ማድረግ አይችልም ። ትምህርት ‘አቋርጦ’ የወጣ ሰው ፤ ከቀጠለው እኩል ሊመረቅ እንደ እማይችለው።
ኢትዮጵያም መንግሥት ክፍል አምስት ላይ በዘረዘርናቸው ሳንካዎች ክፉኛ በመዳከሙ እና ከካቶሊክ ጀስዊቶች ጋር መግባባት ሳይቻል ቀርቶ ከሰፊው የአውሮፓ የእውቀት ማዕድ ጋር የነበረው ግንኙነት ስለ ተስተጓጎለ ፤ የሐገር ግንባታው መዋቅራዊ ሽግግሩን በእሚያስችል መልኩ ሊቀጥል አልቻለም ። ይኽም ለውጡን ካከሸፉ ምክንያቶች ቀዳሚው ሆነ ።
ይኽ ማለት ግን የወቅቱ የኢትዮጵያን በኃይማኖታዊ ጉዳይ ወይንም የአውሮፓ ሕዳሴ መነሻ ለነበረው ፤ መንፈሳዊ መሠረት ላለው እንደ የሰባዊነት (Humanism) ላሉት እውቀቶች ባይተዋር ነበር ማለት አይደለም ።
ለማሳያነት ፤ በክፍል አምስት የታሪካችን ክፍል ላይ እንደ አነሳነው ፤ በፖርቹጋል የኢትዮጵያ መልዕክተኛ ሆኖ የኼደው ስጋ ዘዓብ ፣ የልብነ ድንግል ፣ የገላውዴዎስ መከራከሪያዎች እና መጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ፤ የካቶሊኮችን አስተምህሮ እሚያስከነዳ እንጂ የእሚተናነስ አልነበረም ።
በክፍል አምስት ላይ የአስቀመጥነው ፤ የማቲዎ ስላቫዶር ስለ ስጋ ዘዓብ ያስቀመጠው ምስክርነት ለእዚኽ ማሳያ ነው ፦
“በቤተመንግሥት ቲዮሎጂያንስ ማንጓጠጥ ከደረሰበት እና ስጋወደሙ እንደ አይወስድ ከተከለከለ በኋላ ፤ ኢትዮጵያዊው ለመጀመሪያ ግዜ እ.አ.አ. በ1540 ዓ.ም. የታተመውን ‘የኢትዮጵያዊያኖች እምነት’ የእሚለውን ጽሑፍ ለመድረስ ወሰነ ። ሐተታውም ፤ ኑፋቄ ተብሎ የቀረበበትን ክስ በጥልቀት ማስረዳት የእሚቃወም ፣ የኢትዮጵያን ክርስቲያናዊ እምነት ጤናማናት የእሚያስረግጥ እና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የአዕምሮ ጥበት የእሚያወግዝ ነበር ። ከእዚኽም በተጨማሪ ከእዚኽ በእሚሰፉ ፤ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ያላትን ግንኙነት በመዳሰስ ፤ በአውሮፓ ለአሉ፟ የተኃድሶ ቤተክርስቲያኖች ሆደ ሰፊነት እንዲኖራት የእሚመክር ነበር ። እንዲያውም ስጋ ዘአብ ፤ የፀረ ተኃድሶ እንቅስቃሴ ተቺ የእሚባለው ቃል ራሱ ሳይፈጠር ፤ [3]የፀረ ተኃድሶ እንቅስቃሴ ተቺ ተብሎ መወሰድ የእሚችል ሰው ነው ። ከእዚኽም የተነሳ ፤ ዳሚያዖ ዲ ጎይዝ የእሚባለው ፤ በኤራስመስ ባሕል መሠረት የክርስቲያናዊ ሰብዓዊነት አግባብ የሰለጠነው የፖርቹጋል ሊህቅ እና የቤተመንግሥት ታሪክ ጸሐፊ ድጋፍ አግኝቷል ።”
“After suffering the scorn of court theologians and being denied communion, the Ethiopian decided to author The Faith of the Ethiopian, first published in 1540. The account was a thorough refutation of the accusation of heresy, affirmed the theological soundness of Ethiopia’s Christian traditions, and denounced the narrow-mindedness of the Catholic Church. It also speaks to the broader issue of Catholic relations with other Christians and suggests an accommodating attitude vis-à-vis the reformed churches in Europe. Zaga Za’ab can in fact be considered an ante-litteram critic of the Counter-Reformation: as such, he found the support of Damiao de Gois, Portugese intellectual and foremost court historian trained in the Erasmian tradition of Christian humanism. [32]“
ስለ እዚኽ ፦ ስጋ ዘአብ ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ዴዝዲርየስ ኤራስመስ (Desiderius Erasmus) ነበር ማለት እንችላለን ። እንደ ገናም ፤ ኢትዮጲያ በፍትሐ ነገሥት መዳኘት ጀመረች የእሚባልበትም ዘመን ፤ ቢያንስ ከ14ኛው ምዕተ ዓመት የእሚጀምር በመሆኑ ፤ በፍትሐ ነገሥት ውስጥ የተንጸባረቀው የፍትሕ ፣ የሰብዓዊነት እና የርትዕ ልቀት ፤ ኢትዮጲያ በወቅቱ ትልቅ ማሕበራዊ የእድገት ደረጃ ላይ ደርሳ እንደ ነበረች ዓይነተኛ ማሳያ ነው። በፍትሐነገሥትን ውስጥ የእሚንጸባረቀውን የማሕበራዊ አስተዳደር ጥበብ በጥቂቱ በመጽሐፉ በምዕራፍ አራት ላይ ፤ ሕግ እና ሕገመንግሥታዊነት በኢትዮጵያ በእሚለው ንዑስ ስር ለመዳሰስ ተሞክሯል።
ይኽም ማለት ፤ ምንም እንኳን ፤ የካቶሊክ ጀስዊቶቹ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ የእሚያነሱዋቸው እውነትነት የአላቸው አንዳንድ ጉድለቶች ቢኖሩባቸውም ፤ ዓይነቱ ይለይ እንጂ ተመሳሳይ ጉድለት በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ የአለ፟ በመሆኑ በወቅቱ የቀኖና ጥራት ፤ ኢትዮጵያኖቹ ይሻሉ ይሆናል እንጂ ከጀስዉቶቹ አያንሱም ።
በተፈጠረው የፖለቲካ ድልድይ መሰበር እና ዘላቂነት በነበረው ውስጣዊ አለመረጋጋት ምክንያት ኢትዮጵያዊያኖች በጀመሩበት ቆመው እንዲቀሩ በመገደዳቸው ግዜ በጨመረ ቁጥሩ ከአውሮፓ አቻዎቻቸው ጋር የአላቸው ልዩነት በእየግዜው እየሰፋ ቢኼድም ፤ በለውጡ መጀመሪያ ላይ ፤ በማሕበራዊ ጉዳይ ኢትዮጲያዊያኖች ከአውሮፓ አቻዎቻቸው የእሚያንሱ አልነበሩም ።
ለምሳሌ ፦ የጀስዊት ቄሶች በዓለም ዙሪያ በእሳት የተቃጠሉት ፣ በጨውማ እና ሙቅ የባሕር ውኃ ውስጥ እንጨት ላይ ተሰቅለው ፤ በእዚኽ በጨውማ ሙቅ ባሕር ውኃ ስጋቸው እየተገሸለጠ የሞቱት ፣ በአጠቃላይ ራሳቸው ብዙ መከራ የዓዩበት እና ሌሎቹንም ብዙ መከራ የዓሳዩበት ፤ አንድ ጉዳይ “የዓለም ክርስቲያኖች በሙሉ በሮማው መንበር ስር መሆን አለባቸው” በዓለም ላይ አዲስ የእሚጀመሩም ሆኑ ተመስረተው የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት በሮማዋ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን መንበር ስር መሆን አለባቸው በእሚል እምነት የዓለምን ቤተክርስቲያናት በሮማዋ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ስር ማድረግ አንዱ እና ዋነኛው እምነታቸው ነው።
ይኽ የቆየ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቀኖና ግን ፤ በእዚኽ ዘመን በአብዛኛዎቹ የስነ መለኮት ተመራማሪያን ውድቅ የተደረገ የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም ላይ የተመሠረተ ነው ። ጀስዊቶቹ ይኽን ቀኖና ይዘው ነው ፤ ለ70 ዓመታት ያለማቋረጥ የኢትዮጵያን ሕዝብ እና መንግሥት ‘ሲዋጉ’ የሰነበቱት ።
በተመሳሳይም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ፤ ሐዋሪያው ማርቆስ መሠረታት በእምትባለው የአሌክሳንደሪያዋ መንበር ስር ለዘላለም መሆን አለባት የእሚል ምንም ዓይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወይንም ሌላ አሳማኝ ምክንያት የለም ። በታሪክ አጋጣሚ ፤ ፍሬምናጦስ እግረ መንገዱን አትናሲያስ ጋር በመኼዱ እንጂ ፤ አትናስያስን ትቶ አንጾኪያ ወይንም ሮም ቢኼድ ኖሮ የኢትዮጵያ ዖርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በሮም መንበር ስር ትሆን ነበር ፤ ይኽም ደግሞ አስቀድመን እንደ አልነው ፤ የግንዛቤ እጥረት እና ሌሎች እኩይ ምክንያቶች ተደርበውበት እንጂ ተኃድሶው ዘመነ መሣፍንትን ያቀጣጠለውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና የፖርቹጋል/ስፔን ጀስዊቶችን ግጭት ማስከተል አልነበረበትም ። አስቀድመን ሉዶልፍን አጣቅሰን እንደ አሳየነውም አጼ ፋሲለደስም የአለው ይኽንኑ ነበር።
ይኽ የተኃድሶ እንቅስቃሴ በተዳከምንበት ወቅት በመካኼዱ ምን ያኽል እንደ ጎዳን ለማሳየት ፤ ኢትዮጵያዊያን ከአሌክሳንደሪያው የማርቆስ ወንበር አንቀይርም ብለው ለብዙ መቶ ዓመት ፦ የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፈ ጦርነት የአካኼዱት ፣ ከጀስዊቶ ቄሶች ጋር ሆድ እና ጀርባ ሆነው ከአውሮፓ የእሚፈልጉዋቸውን ብዙ ግብዓቶች ያጡት ፣ በአጠቃላይ ብዙ ውድ ዋጋ የከፈሉበት አንዱ ጉዳይ ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከአሌክሳንደሪያው መንበር ተላቃ የሮማው መንበር ስር ትጠቃለል የእሚለውን የጀስዊቶች ግብዣ እምቢ በማለታቸው ነበር ።
ይኽ ፤ ይኽን ኹሉ ዋጋ የአስከፈላቸው ቀነዓዊነታቸው ግን ፤ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ፤ የማንም የውጭ ኃይል ማባበል እና ግዴታ ሳይኖር ፤ ኢትዮጵያዊያኖች በራሳቸው ፍላጎት እና ምክንያት ፤ በአንድ ጉባኤ ከመንበሩ ተለይተዋል ። ዛሬ ኢትዮጵያ የራሷን ጳጳስ የእምትሾም እንጂ ፤ ከአሌክሳንደሪያ ጳጳስ የእምትጠብቅ አይደለችም ።
ኹለቱም ፤ የለውጥ ጅማሮ ላይ እንደአሉ ተቃራኒ ኃይሎች ሲጋጩ ፤ አልለወጥም የእሚለውም ፤ በግድም ቢሆን ትለወጣታለኽ የእሚለው ፤ የግንዛቤ እጥረት በእሚያመጣው እልከኝነት የእሚጋጩ ነበሩ ። ይኽም ማለት ፦ የወቅቱን ኢትዮጵያዊያን ፤ አንዳንድ መሐይም ፈረንጆች እንደ እሚሉት ፤ ኋላ ቀር ወግ አጥባቂነት እና የጀስዊት ቄሶቹን ደግሞ መሲኽነት የእሚያሳይ አይደለም ። በእሚጋጩበት ጉዳይ የካቶሊክ ጀስዊቶቹም ፤ የኢትዮጵያ ወግ አጥባቅያን ያኽል ወይንም ከእነርሱ በባሰ መኃይም ነበሩ ።
እንዲያውም ይኽ ፤ ካቶሊኮችን ከኢትዮጲያ ነገሥታት እና ቀሳውስት ጋር ያጋጫቸው ፤ እውቀት አልባ እልኸኝነትን ለማረም መነሳት ነው ለአብዛኛው አውሮፓ ተኃድሶ ማለት ።
ይኽን መሰሉ የካቶሊኮቹ አንገተ ደንዳናነት ነው እጅግ የተሰጠ የካቶሊክ መነኩሴ የነበረውን ማርቲን ሉተርን ፤ እነ እዛኽን 96 ነጥቦችን የያዘ ጽሑፍ ጽፎ ፤ የተቃዋሚዎቹ (Protestant ወይንም ጴንጤዎችን) እንቅስቃሴ እንዲጀምር የአደረገው ።
በአውሮፓ ታሪክ እ.አ.አ. ከ1618 – 1648 ዓ.ም. ለቆየው እና የሰላሳ ዓመቱ ተብሎ የእሚታወቀውን ፤ ቅዱሱ የሮማው ኢምፓየር በእሚባለው የሮማው መንበር በእሚያስተዳድረው ግዛት ውስጥ ፤ በአውሮፓ ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ ወደ 8 ሚልየን ሕዝብ የፈጀው ጦርነት ፤ በካቶሊኮች እና በፕሮቴስታንቶች (ተቃዋሚዎች ወይንም ጴንጤዎች) መካከል የተካኼደውም ፤ ካቶሊኮቹ ጴንጤዎቹን በእዚኽ ኹሉም የክርስትና እንቅስቃሴ በሮማው መንበር ስር መሆን አለበት ብለው አላንቀሳቅስ በማለታቸው ነው ።
ከእላይ እንደ አየነውም የእንግሊዝ ተኃድሶ እንቅስቃሴ ፤ ከሮም መንበር መገነጠልን ዋነኛ መገለጫው የአደረገው የካቶሊኮች ኹሉም እኛን ይምሰል ዝብዘባ ሽሽት ነው ።
ብዙ አውሮፓዊያን እየተሰደዱ በኋላ ‘ሕዝባዊ’ ወደ ሆነችው ሰሜን አሜሪካ እንዲኼዱ የአደረጋቸው ፦ ብቸኛዋ ፣ እውነተኛዋ ፣ የዓለም ቤተክርስቲያኖች ኹሉ ከአስተዳደር ቀንበሯ ስር ሊሆኑባት የእምትገባው የሮማዋ መንበር ነች የእሚለውን የካቶሊኮችን ዕቡይነት ሽሽት ነው ።
ይኽም ማለት ፤ የወቅቱ ኢትዮጵያዊያን ጀስዊቶቹን እንቢ ማለታቸው ፤ አጉል የወግ አጥባቂነታቸው እና ስልጣኔ ጠልነታቸው ምልክት ተደርጎ በፍፁም መታየት አይችልም ። ኢትዮጵያ ጀስዊቶችን እምቢ በማለቷ ኋላ ቀር ስለሆነች ስልጣኔን ገፋች ከተባለ ፤ እንግሊዞች ፣ ደቾች ፣ ጀርመኖች ፣ ጃፓኖች ምን ሊባሉ ነው?
በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊያኖቹም ሆኑ ጀስዊቶቹ ልክ ስለ ነበሩ አይደለም ፤ ኹለቱም የመነቃቃት ዘመን ደጅ ላይ ስለነበሩ ፤ የነበረባቸው የግንዛቤ እጥረት ነው ነገሩን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ የመራው ።
በእርግጥ ኢትዮጵያ በወግ አጥባቂነቷ በግዜ ኺደት ፤ የውስጥ ፖለቲካዋ ከአቅም በላይ በሆኑ ውጫዊ ምክንያቶች ለአደጋ ተዳርጎ እና አስፈላጊው የውጭ ግንኙነት ድልድይ መሰበር ምክንያት ፤ የኋላ ቀርነት እንቅልፍ በማንቀላፋቷ የዓለም መሳቂያ ስለ ሆነች ፤ አንዳንድ መኃይም ፈረንጆች ፤ ኢትዮጵያ የጀስዊትን ተኃድሶ እምቢ ስላለች ዋጋ ከፈለች የእሚለው እየያቸውን እውነት አስመስሎታል ።
ኢትዮጵያ ምናልባት ከደረሰችበት ንቃት ወርዳ ፤ ከአውሮፓ ሊገኝ ለእሚችለው እውቀት እና ቴክኖሎጂ ስትል ፤ በግዜያዊነትም ቢሆን ፤ በመንፈሳዊ እውቀት ከእርሷ ልጆች ለእሚያንሱት እነ ቤርሙዴዝ እና ኦቪዬዶ እሺ ብላ በሐገሯ ላይ ጳጳስ አድርጋቸው ቢሆን ኖሮ ፤ ከመንፈሳዊ እውቀት ልቀታቸው የተነሳ ሰአይሆን ፤ ጀስዊቶቹ ማመቻቸት በእሚችሉት የወቅቱ የእውቀት እና የስልጣኔ መዓከል ከሆነው ዓውሮፓ ጋር የእሚከፈተው የትብብር መንገድ ፤ ሕዝቧን በእውቀት እና በቁስ የማስታጠቋ ጉዳይ እንዲቀጥል አድርጎ ኢትዮጲያ በረዥም ዘመን ከተፈተነችበት ማሕበራዊ ፈተና መቋቋም የእምትችልበት አቅም ገንብታ ፤ ቢያንስ ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አከባቢ አንስቶ ከአውሮፓ ጋር ተቀራራቢ ደረጃ ላይ መድረስ ትችል ይሆን ይሆናል ።
ይኽ እንደ አማርጭ ሊቀርብ ቢችልም ፤ ይኽ አማራጭ ግን ፡ ፟የእኔ እምነት እናንተ እንደ እምትሉት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌለው ከንቱ ባሕል አይደለም ብሎ ከአውሮፓ የመጡ የቲዖሎጂ ምሩቃንን በበቃ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንታኔ ዝም የእሚያሰኝ እና ይኽንን እምነቱን ለመከላከል መድብል የእሚጽፍ ንጉሥ ገላውዴውስ እንደ ቤርሙዴዝ ዓይነት ወሽካች ቄስ ነኝ ባይን የኢትዮጲያ ጳጳስ ለማድረግ ወይንም የሮማዋ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አለ ቦታዋ ደርሳ የእምነት ነጻነት አፋኝ ሆናለች እና ቀኖናዋን ትመርምር ብሎ መከላከያ የእሚጽፍ ሊቅ ያፈራች የኢትዮጲያ ቤተ ክርስቲያን የሮማዋን ቤተክርስቲያን የበላዬ ኹኚ ማለት ምን ያኽል እጅግ ፈታኝ ሊሆን እንደ እሚችል ከመገንዘብ ጋር ነው አብሮ መታየት የአለበት።
የትኛውም ስትራቴጂክ አስተሳሰብ ትልቅ እና ታሪካዊትን ቤተክርስቲያን ለአጭበርባሪዎች በግዚያዊነትም ቢሆን ልስጥ ብሎ ማሰቡ ፈታኝ እንደ እሚሆን መታሰብ አለበት።
ኢትዮጲያ ይኽን መሰል ንቃት ከነበራት ምነው ይኽን ያኽል በሌላው ጉዳይ በአውሮፓዊያኖች ላይ ተደጋፊ ሆነች ቢባል ለእዚኽ ከእዚኽ ቀደም ከአነሳነው ኢትዮጲያ ከእምትገኝበት ጂዖፖለቲክስ ሌላ ምክንያት የለም።
አውሮፓዊያን ከኢትዮጲያ የተሻለ ጂዖፖለቲክስ ውስጥ በመኖራቸው ምንም እንኳን ለረዥም ዘመን በጦርነት እና በብዙ ማሕበራዊ ቀውስ ውስጥ ቢኖሩም የእሚገኙበት አከባቢ በብዙ መልኩ ለረዥም ዘመን በእውቀት ፣ በንግድ እና በባሕል ልውውጥ ተሳስረው እንዲተጋገዙ የእሚያግዳቸው ስለ ነበረ ራሳቸውን ለማሻሻል የተሻለ እድል የነበራቸው በመሆኑ ነው።
ልክ የኃይለ ሥላሴ መንግሥት የኹኔታው መመቻቸት ሐገራዊ አቅማችንን እንድንገባ ሲያስችለን ፤ ከ200 ዓመታት ገደማ በኋላ ፤ በአንድ ጉባኤ ያለምንም ብዙ ችግር ፤ በሊህቃኑ እና በቀሳውስቱ ይኹንታ ፤ ኢትዮጵያ የራሷን ጳጳስ መሾም መጀመር አለባት ብሎ እንደ አደረገው፤ የኢትዮጲያ ሕዝብ እና መንግሥት ኹኔታው ቢያመቸው ኖሮ ፤ ማሕበራዊ እና ኢከነሚያዊ መዋቅሩንም በተመሳሳይ መንገድ ፤ ከዛሬ መቶ ዓመት እና ከእዚያኽ በፊት ቀስ በቀስ እያረመው ይመጣ ነበር።
ስለ እዚኽ ፤ ዘመነ መሣፍንት ወደ ውጤታማ የሕዝባዊ መንግሥት ምሥረታ እንዳይሸጋገር የአደረገው የመጀመሪያው ወይንም አንደኛው ምክንያት በተቀጨ የማሕበራዊ የእድገት ምህዳር ውስጥ ስለ ተካኼደ ነው ።
ኹለተኛው ምክንያት ፤ ሐገራዊ የለውጥ ፈላጊዎች እና አራማጆች ፤ የመጀመሪያው ማሕበራዊ እድገት መቀንጨር በወለደው ማህይምነት ፤ ከባንዳ የእማይተናነስ አካኼድ የእሚኼዱ በመሆናቸው ነው ። በስሜት ኮርኳሪ የውጭ ኃይላት ሽንገላ እየተደለሉ ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የተዳከመው እና እንደ እዚኽ የተበዘበዘው ፤ ትክክለኛውን የዘመናዊነት መንገድ እምቢ ስላለ ነው በእሚል ራሳቸውን ለከፍተኛው ተጫራች ክፍት አድርገው ፤ ከውጭ በእሚያገኙት እገዛ የመዓከላዊ መንግሥቱን የእነርሱ ምርኮኛ ለማድረግ ሞኝ ስለሆኑ ነው ።
እንደ ሐገር መዳከማችን ፤ በጋራ የገጠመን ከእኛ በላይ የሆነ ችግር የፈጠረብን ነው የእሚለውን ከመገንዘብ ይልቅ ፤ የውጩን መንገድ መከተል ከአለመፈለግ የመጣብን ነው የእሚል ጥራዝ ነጠቅ ትንተና ይዘው ፤ መሳሪያ እና የፈረንጅ አማካሪ ከእሚልክላቸው ኹሉ ጋር ወደ ማሽቃበጥ መግባታቸው ነው ኹለተኛው ምክንያት።
በመንግሥት ላይ ማመፃቸው ፣ ይኼኛው አካኼድ ይሻላል ማለታቸው ፣ የስልጣን ይገባኛል ጥያቄ ማንሳታቸው ፣ ወዘተ ፤ ወይንም በለውጥ ፈላጊነታቸው ምክንያት ከመንግሥት ጋር መጋጨታቸው አይደለም ችግሩ ። ለውጥ ፤ በተለይ ሽግግራዊ እና መዋቅራዊ ለውጥ ፤ በብዙ አስቸጋሪ ትግል የእሚመጣ በመሆኑ ፤ በእዚያኽን ወቅት መሰል ግጭቶች መበራከታቸው በራሱ ብዙም የእሚያስደንቅ አይደለም ።
በሐገረ እንግሊዝ በለውጡ ዘመን ፤ ክሮም ዌል የእሚባለው የሕዝባዊ መንግሥት ደጋፊ ባላባት ፤ ወግ አጥባቂ የነበረውን ንጉሡ ቻርልስ በጦርነት አሸንፎ እና ንጉሡን ይዞ ፤ በፓርላማ ጥፋተኛ አስብሎ ፤ አንገቱን አስቀልቶ ገድሎታል ። በተለያየ የዓለም ክፍል ፤ መኋሉ እና ዳሩ በለውጥ ስም በአደረጉት ትግል ብዙ ደም ፈሷል ። ይኽ በዓለም ሕዝብ ታሪክ የአለ፟ ነገር በመሆኑ ፤ የኢትዮጵያውን ዘመነ መሣፍንት ክስተት ፤ የመሐል እና የዳር ግጭት መሆኑ ወይንም ዳሩ መሐሉን እንደ ፍላጎቱ ለመቆጣጠር መፈለጉ ልዩ አያደርገውም ።
የኢትዮጵያን ዘመነ መሣፍንት ልዩ የእሚያደርገው ፤ ጥቂቶቹ እና ጥራዝ ነጠቅ እውቀት ይዘው የለውጥ አቀንቃኝ የእሚሆኑት ሰዎች ፤ የፈረንጅ አጨብጫቢ መሆናቸው ነው ። ለውጥ ወይንም የስረዓት ሽግግር ኺደት እንጂ ክስተት አለመሆኑን ያልተረዱ እና የውጭ ኃይ ባይ የአላቸው የጎበዝ አልቆች የእሚመራ የለውጥ አካኼድ መሆኑ ነው ሌላው እና ኹለተኛው የኺደቱ ክሽፈት ምክንያት።
ኢትዮጵያ እሺ ብላ ጳጳስ ከአሌክሳንደሪያ ከእምታመጣ ይልቅ ከሮም ብታመጣ ፣ በግዕዝ ከመቀደስ ይልቅ በላቲን ብትቀድስ ፣ ዖሮቶዶክሳዊ የቤተ ክህነት የካህናት ልብስ በካቶሊካዊት ብትቀይር ፣ እነ ቤርሙዴዝ መሳይ ወሽካቾች ወይንም እንደ ሜንዴስ የአሉ እብሪተኞችን ብትታገስ ፣ ወዘተ ፤ ከኋላ ቀርነት ተስፈንጥራ ወጥታ አውሮፓዊ እምትሆን ስለ መሰላቸው ነው ። ወይንም ይኽን እንደ ዘመናዊነት እና እንደ ለውጥ በማየታቸው ነው ።
የእየ አከባቢው ሉዕላን ፦ የተፈለገው ለውጥ ለምን አስፈለገ? እንዴትስ ሊተገበር ይችላል? ኢትዮጵያ ማን ነች? ጥንካሬዋ እና ድካሟ ምንድነው? የሐገርን አንድነት እና ሉዓላዊነት ከማስከበር አኳያ የእኔ ኃላፊነት ምንድነው? ግዜው በመንግሥት ላይ የእማምፅበት ነው ወይንስ መንግሥትን የእማግዝበት ነው? ወዘተ ፤ ብለው ሳይጠይቁ በአጠቃላይ የእሚፈለገውን ለውጥ በአግባቡ ሰአይረዱ ፤ አንተ እኮ ተራማጅ ነህ ፣ ለአዲስ ኃሳብ ክፍት ነህ ፣ ወዘተ ፤ የእምትለው ፤ የውጮቹ አድናቆት ፤ መሳሪያ እና ምክር የእሚሰጣቸውን ኹሉ ጓዴ እያሉ ፤ የዘመነ መሣፍንት የጎበዝ አለቆች ሆነው ፤ በመክረማቸው ፤ መጨረሻው ሐገርን ወደ ሕዝባዊት ሐገር ማሸጋገር ሰአይሆን ፤ በአራቱም አቅጣጫ የአለው መስፍን ፤ መሳሪያ እና አማካሪ ለእሚሰጠው ኃይል አሸርጋጅ ሆኖ ፤ ሐገርን በመሣፍንት ጦርነት ሲያራኩት ከረመ ።
ሦሥተኛው ፤ እነ እዚኽን አሸርጋጅ መሳፍንቶች ፤ በምክር እና በትጥቅ የእሚያስታጥቁዋቸው የውጭ ኃይላት ፤ በዋናነነት በወዳጅ እና በጠላት ጎራ የእሚፈረጁ ቢሆንም ፤ የወዳጁ ጎራ ራሱ ከእውነትኛ የጓዳዊነት ወይንም ለኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ ከአለ፟ እውነተኛ ወንድማዊ ፍቅር የእሚመነጭ ሰአይሆን ፤ ሲሆን እንደ ሙሴ ቀይ ባሕርን ከፍለን ሕዝብ አሻገርን በእሚል ታሪክ ለመሥራት ሰአይሆን ደግሞ ከነዋይ ፍቅር የተነሳ የእሚደረጉ ድጋፎች የነበሩ መሆኑ ነው ።
ራሳቸውን በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጠላትነት ፈርጀው እንደ ነበሩት ተርኮች እና ወደ በኋላም ላይ ጣሊያኖች የአሉ፟ት በኢትዮጵያ ውስጥ መከፋፈልን የእሚያመጣውን ፤ የተለያዩ መስፍኖችን የማስኮብለል ጉዳይ ሥራዬ ብለው የያዙት ፤ በለውጥ ደጋፊነት ፣ ለተበደለ አዛኝ በመምሰል ፣ ወዘተ ፤ አማጺ መስፍኖችን በማስታጠቅ እና በመምከር ፤ መንግሥት ላይ የሐገር ውስጥ አማጺ የእሚያስታጥቁት ፤ ሐገር በእርስ በእርስ ሽኩቻ ከደከመች በኋላ ፤ ኢትዮጵያን ለራሳቸው ፖለቲካዊ ጥቅም ለመቆጣጠር ከአላቸው ፍላጎት የተነሳ ነው ።
ወዳጅ የእሚመስሉት እንደ ፤ እነ ፖርቹጋል ፣ ስፔን እና በኋላ ይመጡ የነበሩት አብዛኛዎቹ የካቶሊክ እና አንድ አንድ የጴንጤ ሚሽነሪዎች ደግሞ ፤ ሲሆን ወደ ንፋቄ ውስጥ የገባቸውን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ወደ እውነተኛው የካቶሊክ ወይንም የጴንጤ መንገድ በብዙ ተጋድሎ መለስኩ በማለት የእሚገኘውን ጀብደኝነት ፍለጋ ፤ በእዛውም ደግሞ በእዚኽ ትልቅ ሕዝብ ላይ መንፈሳዊ መሪ ከመሆን የእሚገኘውን ዝና ወይንም ጥቅም ከመፈለግ ነው ።
እውር እውርን ቢመራው ተያይዞ ገደል እንደ እሚባለው ፤ የውጭ የለውጥ ኃይሎቹም ፤ በእነርሱ ማባብያ ተኮርኩረው የእሚነሱት ሐገራዊ የለውጥ ቀቢፀ ተስፈኞችም ፤ ትልቁን ስዕል አይተው ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ እና መንግሥት ዘላቂ ጥቅም አስበው የእሚያደርጉት ፤ ራዕይ የአለው የለውጥ ግፊት ሰአይሆን ፤ ሴረኝነት እና ቀቢፀ ተስፈኝነት የእሚነዳው ለውጥ በመሆኑ ፤ ለለውጥ በእሚደረግ ትግል ስም ፤ የሽግግር ምህዳርን በግጭት ውስጥ ነክሮ ሐገርን ወደ ኋላ የእሚከልስ ሆኗል ።
የመጨረሻው እና አራተኛው ምክንያት ፦ በእዚኽ መልኩ ፤ ማን ምንን ለምን እንደ ጀመረው እና ለምን እንደ እሚያስቀጥለው ሳያውቅ ፤ በለውጥ ስም የመሳሪያ እና የአማካሪ ማግኘት ከተጀመረ ወዲኽ ፤ የአበጋዝነት እሽሽቅድድም (Arms race) የኢትዮጵያ መሣፍንት መገለጫ የመሆኑ ጉዳይ ነው።
በእዚኽ ዘመን ወደ ኋላ ላይ የአሉ፟ የእዚኽን ዘመን ታሪክ ለማንበብ እድል የአለው ሰው ሊያስተውለው እንደ እሚችለው ፤ ከሰሜን እስከ ደቡብ ፤ ከደቡብ እስከ ምዕራብ የነበሩ የሐገሪቱ መሣፍንት ፤ አንዱ ከአንዱ ተደብቆ መሳሪያ ለማስገባት እና ለ’ጉብኝት’ የእሚመጣ ፈረንጅ እርሱ ጋር እንዲመጣ ለማድረግ የነበረው ግብግብ በግልፅ ያየዋል ።
ስለ እዚኽ ፤ ዘመኑ መዓከላዊውን መንግሥት (state) ለመገንባት እና ከጠንካራ ብሔራዊ መንግሥት ወደ ሕዝባዊ መንግሥት የእሚደረገውን ሽግግር ምንነት በአግባቡ ለመረዳት የእሚጨነቅ ማንም ሳይኖር ፤ ይልቁንም መዓከላዊውን መንግሥት አዳክሞ ፤ በለውጥ ፈላጊነት እና ተራማጅነት ስም ፤ የራስን ከባቢያዊ ኃይል አጠናክሮ ፤ ማዕከላዊውን መንግሥት ምርኮኛ ማድረግ የወቅቱ ዋነኛ ፖለቲካዊ አጀንዳ ሆነ።
ይኽም አካኼድ ፤ አጼ ቴውድሮስ መጥተው ፤ መዓከላዊውን መንግሥት መያዝ እና ማጠናከርን አዲሱ የወቅቱ ፖለቲካ መገለጫ እስኪ ያደርጉት የቀጠለ ነበር ።
ከእዚያኽም በኋላ ፤ መዓከላዊው መንግሥት በአጼ ምንሊክ ትርጉም በአለው መልኩ እስኪ ጠናከር ፤ የእየ አከባቢው መሣፍንት ፤ በመዓከላዊ መንግሥት አሻንጉሊት ከማስቀመጥ ፤ መዓከላዊ መንግሥቱን ቀጥታ ተቆጣጥሮ ንጉሥ ነገሥት ዘኢትዮጲያ የእሚያስብለውን ወንበር ለመያዝ ግብግብ ውስጥ ገባ እንጂ ፤ ከከባቢያዊ አስተሳሰብ አልወጣም ነበር ።
እንግዲኽ ፤ በእነ እዚኽ አራት ምክንያቶች ፤ ስድስተኛው የታሪክ ክፍል ፤ ሕዝባዊ መንግሥት መስርቶ መጠናቀቅ ሲገባው ፤ የሕዝባዊ መንግሥት መሠረት የሆነውን ጠንካራ መዓከላዊ መንግሥት ለዘመናት በመጎነታተል ሲያዳክም ኖሮ ፤ እንደ አጼ ቴውድሮስ የአሉ፟ ቅድመ ንቃት የአዳበሩ የሐገር ሰዎችን ፤ ይኽ አካኼድ ኢትዮጵያን ለቀኝ ገዢዎች በላልቶ ከመስጠቱ በፊት ብቸኛው መዳኛው መንገድ ፤ ይኽን የተዳከመ መዓከላዊ መንግሥት እንደገና አጠናክሮ ፤ በክለሳ ቢያንስ ወደ ቅድመ 1529 ዓ.ም. (እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር) አቋሙ መመለስ ነው ፤ በእሚለው አግባብ እንዲሰሩ አደረጋችው ።
ይኽ በአይሆን እና በመንግሥት መዳከም ምክንያት ፤ ማሕበራዊ እድገታችን በአይቀጭ ኖሮ ወይንም የለውጥ ግፊቱ ፤ የእድገት ኺደቱ በቀነጨረ ማሕበረ ኢከነሚያዊ ምሕዳር ውስጥ ከውጭ ወደ ውስጥ የእሚንቆረቆር በአይሆን እና በስተመጨረሻም ከባቢያዊ መሣፍንት ወደ አበጋዝነት እሽቅድድም ውስጥ በአይገቡ ኖሮ ፤ ኢትዮጵያ የእዚኽ ዘመን ጅማሮ ላይ የዘመናዊ ፓርቲ መፍለቂያ የሆነችው እንግሊዝ ጋር ተመሳሳይ ኹኔታ ላይ የነበረች በመሆኑ ከአውሮፓዊያኖቹ እኩል ባይሆንም እንኳን የዛሬ መቶ ዓመት ገደማ ወደ ውጤታማ የፓርቲ ስረዓት ግንባታ ውስጥ መግባት ነበረባት ።
በመዓከላዊ መንግሥቱ ምሥረታ ጉዳይ ብንመጣ ፤ እንግሊዝም የሮም አውራጃ ከነበረችበት ግዜ አንስቶ ፤ ኢትዮጵያ የራሷ መዓከላዊ መንግሥት የነበራት በመሆኑ ፤ በእዚኽ አንፃር ከብሪታኒያ የእምትሻል እንጂ የእምታንስ አይደለችም ።
ለዘመናዊው የተፈጥሮ እና ማሕበራዊ ሳይንስ መፍለቂያ የሆነችው ቤተክርስቲያን እና የተለያዩ ተቋሞቿም ፤ ከየትኛውም የክርስቲያን ሐገር በፊት እና በአልተናነሰ ኹኔታ በመላ ሐገሪቱ ተሰራጭተው ፤ ማሕበራዊ አንድነት በመፍጠር ፣ ስነ ጽሑፍ እና እውቀት በማስፋፋት ፣ ወዘተ ፤ ትልቅ ሥራ የእሚሰሩበት ደረጃ ላይ ደርሰው ነበር ። የአውሮፓዊያን ሕዳሴ ዩንቨርስቲዎች እውቀቶች የፈለቁበት የአውሮፓ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቤቶች (The basis of the Scholasticism, the schools) ፤ በኢትዮጵያ የቄስ ትምህርት ቤት የእምንላቸው ናችው።
እነ እዚኽ የቄስ ትምህርት ቤቶች ፤ በእዚኹ ፖለቲካችን ባቀነጨረው ምክንያት በመቀንጨራቸው ፤ ለዘመናዊነት በእምንጣደፍበት ግዜ ፤ እንደ ርካሽ እና ተራ ነገር አይተን ብንወረውራቸውም ፤ በውስጣቸው የያዙት ጥበብ ፤ እንደ አውሮፓዊያን ዓይነት አመቺ ማሕበረ ኢከነሚያዊ ምሕዳር ቢያገኙ ኖሮ ፤ ልክ እንደ አውሮፓዊያን አቻዎቹ አድጎ ፤ የዛሬዎቹን መደበኛ ትምህርት ቤቶች እና ዩንቨርስቲዎች የእሚመራው የሰባዊያን አስተሳሰብ መፍለቂያ መሆኑ የእማይቀር ነው ፤ ምክንያቱም ፦ የዛሬዎች የአውሮፓ ትላላቅ የእውቀት መዓከላት መሰረታቸው ይኸው የቄስ ትምሕርት ቤት ወይንም በአውሮፓዊያኖቹ school በመሆኑ።
የኢትዮጵያ የቄስ ትምሕርት ቤት ትምሕርተ ስረዓት ፤ ከንብባ ጀምሮ ሊቅ ብሎ እስከ እሚያወጣቸው ድረስ የአሉት ደረጃዎች ፤ እንደ አንዳንድ ሰዎች እምነት ፤ ከዘመናዊ እና ከአንደኛ ደረጃ እስከ ዩንቨርስቲ ድረስ ከአሉት ዘመናዊ የትምሕርት ስረዓቶች ጋር ብዙ ትዩዩነት የአለው ነው።
ምንም እንኳን ፤ የእንግሊዝን ማሕበረሰብ ያከፋፈውለው ፤ ከእናት ካቶሊክ ቤተክርስቲያን እንለይ ወይንስ አንለይ የእሚለው ጥያቄ ቢሆንም እና በኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ከእናት አሌክሳንደሪያ ቤተክርስቲያን እንለይ ወይንስ አንለይ የእሚለው ቢሆንም ማሕበረስቡን ለኹለት የከፈለው ፤ ጉዳዩ ብዙ ተመሳሳይነት አለው ።
በወቅቱ ኢትዮጵያ ፤ እንደ ፍሎረንስ ከአሉ፟ የአውሮፓ ህዳሴ መዓከላት ጋር የአላ፟ት የትብብር ማዕቀፍም ቀላል አልነበረም።
እንደገናም ፤ ቀላል የእማይባሉ እና ጠንካራ አቅም ያዳበሩ መሳፍንቶች ራሳቸውን በተለያየ ጎራ አሰልፈው ፤ መንግሥትን መሞገት የእሚችሉ እና የእሚሞግቱበትም ዘመን ነበር ።
በአጭሩ ፤ እንግሊዝን የፖለቲካ ፓርቲ መፍለቂያ የአደረጋት ቅድመ ኹኔታ በኢትዮጵያም በእዚያኽን ወቅት በበቂ ኹኔታ ነበር ።
ኢትዮጵያ ግን እድገቱ በተቀጨ ማሕበረሰብ እና በእዚኽም በተደካመ መንግሥት እየተመራች ፤ ለእርሷ በእማይበጅ ጂዖፖለቲክስ ውስጥ ታሥራ ፤ ይኽ የለውጥ ምጥ ስለመጣባት ፤ ሕዝባዊ መንግሥት የመመሥረት ጉዞዋ ፤ ወደ ኋላ አንድ ደረጃ ተከልሶ ተጠናቀቀ ።
ምንም እንኳን ፤ አኹን ላይ ሆነን ስናየው ፤ በወቅቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ የገጠመው ፈተና ፤ በተለያዩ ዘዴዎች ሊታለፍ የእሚችል ነበር ብለን ልናስብ ብንችልም ፤ የወቅቱ ፖለቲካዊ እና የአደረጃጀት እውቀት ሊሸከመው ከእሚችለው በላይ የሆነ ፈተና በመሆን ፤ ኹኔታው ለወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ለፖርቹጋሎች ማጎብደድም ሆነ አርበኛ መሆን እጅግ ትልልቅ ዋጋ የእሚያስከፍሉ ኹለት አስቸጋሪ አማራጮች ሆኑበት ።
በፔድሮ ፓኤዝ ተፅኖ ወደ ካቶሊክ ያዘነበለው ዘድንግል ፤ ከሐገሬው ሰው በደረሰበት ተቃውሞ በጦርነት ሞተ ፤ እርሱን የተካውን ያዕቆብ በጦርነት አሸንፎ ወደ ስልጣን የመጣው ሰሶኒዮስ ፤ ምንም እንኳን በነበረው ወታደራዊ አቅም ፤ የካቶሊክ እምነት በሕዝቡ ላይ መጫን የእሚያስችልበት ደረጃ ላይ ቢያደርሰውም ፤ ይኽ በኃይል የተደረገ ጫና የፈጠረው እልቂት ፤ የተባለው ለውጥ ለሕዝቡ ተብሎ እንጂ በሕዝቡ ላይ የእሚመጣ መሆን የለበትም ከእሚለው መሠረታዊ መርህ ጋር ስለ እሚጋጭ ፤ ስልጣኑን በገዛ ፈቃዱ ለልጁ እንዲያስረክብ አደረገው ።
በኢትዮጵያ ፤ ምናልባትም በአፍሪካ ፤ ሰሶንዮስ የመጀመሪያው ስልጣኑን ለሕዝብ ሲል በበጎ ፈቃዱ የለቀቀ ትልቅ ንጉሥ ሳያደርገው ይቀራል?
ሰሶኒዎስ እ.አ.አ. በ1632 ዓ.ም. ስልጣኑን ከለቀቀ በኋላ ፤ ፋሲለድስ ፣ የፋሲለደስ ልጅ ቀዳማዊ ዮሐንስ እና የዮሐንስ ልጅ ቀዳማዊ እያሱ በተከታታይ እስከ እ.አ.አ. 1706 ዓ.ም. ፤ ጎንደርን መዓከል አድርገው ለ74 ዓመታት በተነፃፃሪነት የተረጋጋ ግዜ አግኝተዋል ። ሆኖም ፤ በእዚኽም ግዜ ቢሆን የተኃድሶ እና የወግ አጥባቂው ትግል ህቡ ገባ እንጂ አልሞተም ነበር ።
ምክንያቱም ፦ ኢትዮጵያ በፍጥነት እየተለወጠ በመጣው ዓለም ፤ ይኽ የእስላሙ ዓለም ኢፍትኃዊ ከበባ የፈጠረባትን ኢከነሚያዊ እና ፖለቲካዊ ኋላ ቀርነት ሰብራ ከአልወጣች ፤ ድህነቱ እና ኋላ ቀርነቱ ፤ ቀናለታለኹ የእምትለውን ኃይማኖቷን ጨምሮ ከእነ ሕዝቦቿ ሊያጠፋት መቃረቡ ፤ ጥቂትም ፖለቲካዊ ንቃት ለእሚያዳብረው ሰው በእየግዜው ግልፅ ሆኖ የእሚታይ ነበር ።
ስለ እዚኽ ፦ ባሕሎች እና ልማዶቻችን ችግር ባይኖርባቸውም እንኳን ፤ እያስከፈሉን የአለው ዋጋ እጅግ ብዙ በመሆኑ ፤ የእሚከፈለውን ዋጋ ከፍለን ከዓለም ሕዝብ ጋር መስተካከል አለብን የእሚል የእሚንቀለቀል ስሜት በእየግዜው እና በየቦታው ብቅ ይል ነበር ።
በእዚኽ ስድስተኛው የታሪካችን ክፍል ፤ ከቀዳማዊ እያሱ መሞት እስከ ዳግማዊ ዮሐንስ ፤ ማለትም እ.አ.አ. ከ1706 – 1769 ዓ.ም. የተለያዩ ነገሥታት የነገሡ ሲሆን ፤ በእዚኽ ወቅት የተኃድሶ እንቅስቃሴ በማድረግ ሊጠቀሱ የእሚችሉት ፤ የቀዳማዊ እያሱ ልጅ የሆነው በካፋ እና ባለቤቱ ምንትዋብ ናቸው ።
በካፋ ፤ ፀረ ፊውዳል ባላባቶች እንቅስቃሴ በማድረግ ሲታወስ ፤ የፖርቹጋል ዝርያ የአለ፟ባት እና የንጉሥ ምናሴ የልጅ ልጅ የሆነችው እቴጌ ምንትዋብ ፤ ለካቶሊክ ታደላለች የእሚል ክስ የእሚደርስባት የነበረ ቢሆንም ፤ ዳግማዊ እያሱ (ልጇ) ከሞተ በኋላ ፤ ገዳም እገባለኹ ስትል የወቅቱ መኳንንቶች በሞግዚትነት አምስት አመት አገር እንድትመራ ግድ ያሏት ነበረች ።
ከእዚኽ አጭር ዘገባ እንደ እምናየው ፤ የካቶሊኮቹ እንቅስቃሴ በፋሲለድስ ከተዘጋ በኋላ በሐገር ውስጥ ቀላል የእማይባል የካቶሊክ ቅሪት በመኖሩ ፤ የተኃድሶው ኃሳብ አቅም አግኝቶ ገንፍሎ አይውጣ እንጂ ያቆመበት ወቅት አልነበረም ።
ሆኖም ፤ እ.አ.አ. በ1632 ዓ.ም. ከፋሲለደስ አንስቶ እስከ በካፋ ወንድም የንግሥና ዘመን እ.አ.አ. 1769 ዓ.ም. ፤ ለ137 ዓመት በተነፃፃሪነት መረጋጋት ስለቻለ ፤ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የከተማ ታሪክ ፤ የመጀመሪያዋ ትልቅ ዘመናዊ ከተማ ጎንደርን ገንብተው ድህረ ሸዋ አዲሲቷ የኢትዮጲያ ፖለቲካዊ ማዕከል (ዋና ከተማ) አድርገው ፤ ታውቂነቷ ከአገሪቱ ድንበር እስኪሻገር ድረስ አሳድገዋታል ።
ምንም እንኳን ጎንደር ፤ የንግድ ፣ የፖለቲካ ፣ የሳይንስ እና የዲፕሎማሲ ማዕከል ብትሆንም እና ያለፈው መቶ ዓመት በተነፃፃሪነት ሰላም ቢሆንም ፤ ድንገት ግን ፤ መንግሥት ግምጃ ቤቱ ተራቁቶ እና ኃይሉ ተዳክሞ ፤ በባሕረ ነጋሽ ይስሀቅ የጀመረው መዓከላዊ መንግሥቱን የአከባቢዎች ተገዢ የማድረግ አባዜ እንደ ገና በሙሉ ኃይል ተጀመረ ።
እንደ ፖል ሔንዝ ፤ እ.አ.አ. በ1755 ዓ.ም. የዳግማዊ እያሱ ንግሥና አንስቶ ወይንም ልማዳዊው የዘመነ መሣፍንት ከእሚጀምርበት ግዜ አንስቶ ፤ አጼ ቴውድሮስ እስከ ተነሱበት እ.አ.አ. 1855 ዓ.ም. ፤ 28 ነገሥታት ነግሰዋል ። በወሎ ፣ በትግራይ እና በጎንደር ቤተመንግሥት ውስጥ በአሉ፟ የፖለቲካ ኃይላት አንጋሽ እና አውራጅነት ። ይኽም ማለት በመቶ አመቱ በአማካይ እያንዳንዱ ነጋሢ የ 3 ዓመት ተኩል የስልጣን እድሜ ነበረው ማለት ነው ።
ያም ሆነ ይኽ ግን ፤ በእዚኽ ዘመን አፍራሽ የሆነው የፓርቲ ፖለቲካ ፤ ከሐገራዊ ራዕይ አንፃር ሰአይሆን ከጠባብ ግዜያዊ ፍላጎት ተነስቶ ፤ የመዓከላዊ መንግሥቱን የእርሱ ፍላጎት እስረኛ በማድረግ አፍራሽ ሚና ተጫውቷል እንጂ ይኽ አፍራሽ ሚናው የኢትዮጵያን ታሪካዊ አንድነት ወደ እሚያፈርስበት ደረጃ አልደረሰም ነበር ። ፖል ሔንዝ ከእዚኽ በታች እንደ ጠቀሰው ፤ በዘመነ መሣፍንት ምንም እንኳን የኢትዮጲያን ህልውና ፈተና ውስጥ የነበረ ቢሆንም ፤ ኢትዮጲያ ግን ፈርሳ ነበር ሊባል አይችልም ይላል ፦
“ከብዙ ጉዳዮች አንፃር ፤ የ1800ዋ ኢትዮጵያ ፤ በፅኑ ውስጥዊ ችግር የተያዘች እና ውስጣዊ ትሥሥሯም የላላበት አንድነታዊ ጥንካሬዋን በግልፅ ሊያሳይ በእማይችል መልኩ ደካማ ሐገር ነበረች ። ቢሆንም ፤ እንደ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሐገራት የነገዶች ጥርቅምቅም አልነበረችም ። … የኢትዮጵያ ግዛታዊ ሐገርነት ከባህላዊ ክርስትናዊ ልማዱ እና ከአክሱም ዝክር ጋር እንደተጠበቀ ነበር ።”
“From many points of view, Ethiopia of 1800 was a weak state with serious internal problems and little visible cohesion. It was not, however, like many other areas of Africa, the home of a mere conglomeration of … tribes. … The idea of the Ethiopian Empire remained intact with its traditions of faithfulness to Christianity and the legacy of Aksum. [35]“
በእዚኽ የታሪክ ክፍል ፤ መዓከላዊው መንግሥት ከገባበት የጎጥ እስርቤት መፈታቱን ያበሰረው ፤ የአጼ ቴውድሮስ እ.አ.አ. በ1755 ዓ.ም. መምጣት ነው ። የአጼ ቴውድሮስን ወደ ስልጣን መምጣት ፤ ከስር ነቀል የተሕድሶ እንቅስቃሴያቸው ነጥሎ ማየት የእሚቻል አይደለም ።
ይኽም በመሆኑ ፤ ተኃድሶውን አስፈላጊ የአደረገው ነባራዊ ሁኔታ ባለመቀየሩ ፤ እ.አ.አ. ከ1559 ዓ.ም. አንስቶ የለውጥ ወይንም የተኃድሶ ፖለቲካ ፤ እስከ ምንሊክ ድረስ ከፖለቲካዊ ምህዳሩ አልጠፋም ማለት እንችላለን ።
የአጼ ቴውድሮስ የተኃድሶ እንቅስቃሴ ፤ የፅንፈኛ ፕሮቴስታንት መልክ የተላበሰ እና ለውጥን እምቢ በማለታችን ፤ ሐገራችን ወደመች ፤ በስልጣኔ ቀደምት የነበርነውን ሰዎች ዓለም ጥሎን ነጎደ የእሚል መንፈስ የሚንፀባረቅበት ነበር ።
ይኽም የአጼ ቴውድሮስ ዜና መዕዋል ጸሐፊ የነበሩት ደብተራ ዝናብ ፤ አጼ ቴውድሮስ የተነሱበትን ምክንያት ፤ የቴውድሮስ ታሪክ በእሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ በአስቀመጡበት አኳኋን የእሚታይ ነው፦
“… ዘመዶቻቸውም እጅግ ድኃ በበደሉ ግዜ ፤ የአበሻ ሰዎች ኹሉ ፤ ፍርድን ፣ መልካም መሥራትን ፣ እግዚአብሔርን መፍራት በተው ግዜ ፥ በስም ክርስቲያን ተብለው በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ፈንታ ፤ አስማት ፣ ምንዝርና ፣ ስካር ፣ ቧልት ፣ ጥመት ፤ በአደረጉ ግዜ ፤ እግዚአብሔር አምላክ ቀናዒ ነውና ፤ ንጉሥ ቴውድሮስን አስነሳ ኹሉን የእሚቀጣ። [118]“
አጼ ቴውድሮስን የተኩት ፤ አጼ ዮሐንስ ደግሞ ፤ የአጼ ቴውድሮስ ፍፁም ተቃራኒ ሆነው ፤ የወግ አጥባቂዎቹ ፅንፈኛውን ጥግ ይዘው ፤ ኃይማኖታዊ ልዪነቶችን ለመታገስ ፍላጎት የሌላቸው ነበር የሆኑት ።
አጼ ዮሐንስን የተኳቸው ፤ አጼ ምንሊክን ስንመለከት ፤ የመንግሥታቸው መገለጫ በእሚመስለው ፦
‘በአለህበት ርጋ እና ግባ’
በእሚለው አባባላቸው ነው ።
አጼ ምንሊክ ፤ ታማኝ የኢትዮጵያ ዖርቶዶክስ እምነት ተከታይ ከመሆን ውጭ የእሚታይባቸው ሌላ መልክ በአይኖርም ፤ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ አንድነት ላይ ችግር የእማያስነሳውን ፤ ማንኛውም ኃይማኖታዊም ሆነ ሌላ ልዩነት ፤ ኹሉም በእየጎጡ ይዞት እንዲቀጥል እና አንዱ ሌላውን እንደ አይረብሽ የማድረግ አቅጣጫ ነበር ሲከተሉ የነበሩት ።
ይኽን መሰሉ ፤ በሳል የዘመናዊ ፖለቲከኛ አካኼድ በመከተላቸው ፤ ኢትዮጵያን ሦሥት ቦታ ሊሰነጥቅ ይችል የነበረው ፤ የቀኝ ገዢዎች እንቅስቃሴ ይልቁንም የኢትዮጵያን መንግሥት አጠናክሮት እንዲያልፍ ሆኗል ።
ኢትዮጲያ ፤ በብቸኝነት ወይንም ከአብዛኛው የዓለም ሕዝብ በተለየ ፤ አስተዳደራዊ ነጻነቷን እና መንግሥታዊ ውቅሯን ይዛ ፤ የዘመንን ኹሉ ውርጭ እና ቁር ተቋቁሟ እዚኽ መድረስ የቻለቸው ፤ በእድል ፣ በአጋጣሚ ወይንም በተዓምር ሰአይሆን ፤ በእየ ዘመኑ እየተነሱ ፤ ዘመኑን የእሚመጥን መልስ መስጠት የእሚችሉ መሪዎች ፤ በታሪክ አጋጣሚ ደጋግማ ማግኘት በመቻሏ ነው የእሚል ነገር እንድ እንል የእሚያደርገንም ፤ እንደ እዚኹ እንደ አጼ ምንሊክ የአሉ እና ይኽን አውሎ ንፋስማ ኢትዮጵያ ማለፍ አትችልም ሲባል ፤ እንደ ተዓምራዊ ደንቅል ድንገት ተነስተው የመርከቡን ሸራ መወጠር የእሚችሉ መሪዎች በእየዘመኑ ለማግኘት በመታደሏ ነው ።
ኢትዮጲያ ኢዛናን ፣ ካሌብን ፣ መራ ተክለ ኃይማኖትን ፣ ይኩኖ አምላክን ፣ ዘራ ያዕቆብን ፣ አምደ ጽዮንን ፣ ገላውዴዎስን ፣ ሰሶንዮስን ፣ ፋሲለደስ ፣ ቴውድሮስን ፣ ዮኋንስን ፣ ምንሊክን ፣ ወዘተ ፤ የመሳሰሉ ፤ እጅግ አስደናቂ መሪዎች ለማግኘት የታደለች ሐገር ሆናለች።
የአጼ ምንሊክ ፤ ይኽን መሰል ዘመን ቀደም የአመራር ክህሎት ፤ እነ እዚኽን ብቻ ሰአይሆን ፤ ኢትዮጵያን በማዘመን እና የኢትዮያን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በድጋሚ በማጠናከር ኺደት ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የእሚወስዱትን ኃይለ ሥላሴን ፤ መሠረታዊ እውቀታቸውን ፤ ሐረር ከእሚገኙ የካቶሊክ ቄሶች ማግኘት እንዲችሉ አመቺ ኹኔታ የፈጠረ ነበር ።
ስለ እዚኽ ፦ ይኽ ስድስተኛው የታሪካችን ክፍል እ.አ.አ. በ1550 ጀምሮ በ1913 ዓ.ም. በአጼ ምንሊክ ንግሥና ማብቂያ ድረስ ቀጥሏል ። በኢትዮጵያ ልዩ ኹኔታ ያለ አግባብ ቢራዘመም እና የታሰበለትን ግብ በአያሳካም ፤ ነገሮች ተፈጥሮዋዊ ኺደታቸውን የእሚከተሉበት ኹኔታ ቢኖር ኖሮ ፤ ታሪካዊ ክፍሉ በስተመጨረሻ ወደ ሕዝባዊ መንግሥት ምሥረታ የእሚያሸጋግሩንን ጠንካራ እና ታሪካዊ የፖለቲካ ፓርቲዎችንን ይመሠርት ነበር ።
ነገሮች አልሰመሩም እና ደጋግመን እንደ አልነው ፤ ይኽ ሳይሳካ መቅረት ብቻ ሰአይሆን ፤ የፓርቲ ምሥረታ እንቅስቃሴው ባልተረጋጋ ኢከነሚያዊ ፣ መንግሥታዊ እና ፖለቲካዊ ሐገራዊ ኹኔታ የመጣ ታሪካዊ ጫና ስለነበር ፤ ኺደቱ ሐዲዱን ስቶ ፤ ሐገሪቱን ይበልጥ የአዳከመ እና ህልውናዋን አደጋ ላይ የጣለ ሆኖ አልፏል ።
በሦሥቱ አዋኃጆች ፦ አጼ ቴውድሮስ ፣ አጼ ዮሐንስ እና አጼ ምንሊክ የተሰራውም ሥራ ፤ ወይንም ይኽ የታሪክ ዘመን የተጠናቀቀው ፤ በኢትዮጵያ ልዩ ኹኔታ በአጉል ሰዓት የጀመረው የፓርቲ ፖለቲካ ህፀፅ ፤ የአደረሰባትን ድካም አስወግዶ ፤ አዎንታዊ የፖለቲካ ፓርቲ ስረዓት ምሥረታ የእሚያስችለውን ቅድመ ኹኔታ ፥ የተማከለች አንድ ኢትዮጵያን አረጋግቶ መምራት የእሚችል ጠንካራ መዓከላዊ መንግሥትን በመፍጠር እና በማደላደል የሆነውም ለእዚኽ ነው ።
ስለ እዚኽ ፤ ከፖለቲካዊ ሽግግር አንጻር የሦሥቱ አዋኃጆች ሚና የነበረው ፤ ኢትዮጵያን እ.አ.አ. በ1529 ዓ.ም. ወደ ነበረችበት ጥንካሬ መመለስ ነበር ።
ከእነዚኽ ሦሥት ነገሥታት አንስቶ ፤ የኢትዮጵያን አንድነት ማረጋገጥ የእሚችል ፤ የዘመኑን ጫና መቋቋም የእሚችል ፤ ሐገራዊ መንግሥት የቀጠለ ቢሆንም ፤ የዓለም ዓቀፉ ፖለቲካ የሚለዋወጥበት ፍጥነት እና የነበረብን ታሪካዊ የኋላ ቀርነት እዳ ፤ ወደ ሕዝባዊ መንግሥት የእምናደርገውን ጉዞዋችንን ኹለት ወደፊት አንድ ወደ ኋላ እየአደረገብን ይመስላል ፤ እ.አ.አ. ከ1901 ዓ.ም. እስከ አኹን በአለው ከመቶ ትንሽ በእሚበልጠው ዘመን ።
ከእዚኽ በእሚቀጥሉት ሦሥት ክፍሎችም ፤ በኃይለ ሥላሴ ፣ በደርግ እና በኢሕአዴግ ወይንም በሦሥቱ አዘማኝ መንግሥታት መሪነት ፤ ዳግም የጠነከረውን መንግሥት ሕዝባዊ ከማድረግ አንፃር የተመዘገቡ ስኬቶችን እና ጉድለቶችን እናያለን ።
እስከ ዳግማዊ ምንሊክ ዘመን ማብቂያ ድረስ የአሉ፟ት አብዛኛዎቹ የሐገራችን ታሪክ መጽሐፍት ፤ የተጻፉት በውጭ ዜጎች በመሆኑ እና በኢትዮጲያዊያንም የተጻፉ አብዛኛዎቹ የታሪክ መዛግብቶች ይኽንን አካኼድ ስለ ተከትሉ ፤ እስከ ምንሊክ ዘመን ማብቂያ የአሉ፟ትን ታሪኮች ፤ ከነበሩበት ወደ ኢትዮጲያ አቆጣጠር ለመቀየር ከመሞከር በአሉበት ማቆየት መርጫለሁ።ስለ እዚኽ፦እንደ ኢትዮጲያ አቆጣጠር እስከ 1901 ዓም ለአሉ፟ት ዓመታት ፤ ታሪኩ የቀረበበት ክፍፍል የአውሮፓዊያንን አቆጣጠር መሠረት የአደረገ ሲሆን ፤ ከእዚያኽ ወዲኽ የአለ፟ው ክፍፍል ግን የኢትዮጵያን አቆጣጠር መሠረት የአደረገ ነው። ↑
ምንም እንኳን በሕጋዊ አግባቡ የአጼ ምንሊክ ንግሥና የአበቃው ፤ ሕይወታቸው እንደ አለፈ በአደባባይ በተነገረበት እ.አ.አ. በ1913 ዓ.ም. ወይንም በኢትዮጲያ አቆጣጠር በ1906 ዓ.ም. ቢሆንም ፤ ታመው ቤት መቅረት የጀመሩት እና የእርሳቸውንም መታመም ተከትሎ ፤ እርሳቸውን የመተካቱ ፖለቲካ የጀመረው እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1901 ዓ.ም. ነው። ይኽም በመሆኑ ፖለቲካዊ የግዜ ሰንጠረዡ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1901 ዓ.ም. ነው እንዲ ጀምር የአድረግኹት ፤ ምንም እንኳን በሕጋዊ መንገድ ንግሥናቸው ያበቃበትን ዘመን 1906 ዓም ወይንም እ.አ.አ 1913 ዓም ቢሆንም። ↑
ይኽ ጸረ ተኃድሶ ወይንም በእንግሊዘኛው counter-reformation የእሚባለው ፤ ከላይ በሐገረ እንግሊዝ ተከሰተ የአልነውን ዓይነት ከሮማው ጳጳስ አምባገነናዊ ኃይማኖታዊ አገዘዛ በመላቀቅ የተለያዩ ማሻሻያዎችን የእማድረግ ኺደቱን በወግ አጥባቂነት ወይንም ለሮማው ጳጵስ ታማኝ ሆነው ማንኛውንም የተኃድሶ እንቅስቃሴ የመቃመም ኺደት ሲሆን ፤ ስጋ ዘአብ ደግሞ ይኽንን ተኃድሶውን የእሚቃወሙትን ሰዎች (SigaZeab was opposing or criticizing those people who oppose the reformation, that even, before such criticism of the counter reformation was getting traction or for that matter before it even begins) ራሳቸው የእሚተች ነበር። ↑