ሕ ገ ክ ራ ሲ

marketing-image

3.2.7. ክፍል 7 ፡ ዘመነ ኃይለ ሥላሴ (ከ 1901 ዓ.ም. – 1966 ዓ.ም.)

ከንዑስ ርዕሱ እንደ እሚታየው ይኽ ሰባተኛው የታሪካችን ክፍል ፤ ከአጼ ምንሊክ ንግሥና ማብቂያ ገደማ ጀምሮ ፤ የእዚኽ ታሪካዊ ክፍል ዋና ባለ ታሪክ እስከ ሆኑት የአጼ ኃይለ ሥላሴ የንግሥና ዘመን እስከ እሚያበቃበት ግዜ ድረስ የእሚቆይ ነው ።

አጼ ምንሊክ በበሽታ መድከም ከጀመሩበት አንስቶ እርሳቸው ወደ ዙፋን እስኪ መጡ ድረስ የነበረውን ኹናቴ ፤ አጼ ኃይለ ሥላሴ ፤ ‘ሕይወቴ እና የኢትዮጵያ እርምጃ’ በእሚል ፤ ከ1928ቱ የጣሊያን ወረራ በኋላ ፤ በእንግሊዝ ሐገር ባዝ በእምትባለው ከተማ በስደት ላይ እያሉ በ1929 ዓ.ም. ባሳተሙት አንደኛ መጽሐፋቸው ውስጥ ይተርኩልናል ።

አጼ ምንሊክ ከ1901 ዓ.ም. ጀምሮ በሽታቸው እየጠናባቸው ከቤት መውጣት እየከለከላቸው እንደ መጣ እና ከእዛያኽ በኋላ ፤ ዙፋናቸውን በራስ ቢትወደድ ተሰማ ሞግዚትነት ለልጅ እያሱ በአዋጅ አወረሱዋቸው ።

የልጅ ኢያሱ ሞግዚት ራስ ቢትወድድ ተሰማም ፤ በሞግዚትነት ለኹለት ዓመት ከአገለገሉ በኋላ እርሳቸውም በ1903 ዓ.ም. ታመው ስለሞቱ ፤ ከ1903 ዓ.ም. ጀምሮ ልጅ እያሱ ያለሞግዚት ሐገር የመምራቱን ሥራ ለስድስት ዓመት እስከ 1909 ዓ.ም. ድረስ ይዘውት ቆይተዋል ።

አጼ ኃይለ ሥላሴ ፤ ውልደታቸው ሐረር ሲሆን ፤ በ13 ዓመታቸው ፤ በ1898 ዓ.ም. በአባታቸው በራስ መኮንን በሐረር የደጃዝማችነት ማዕረግ ተሰጣቸው ። አባታቸው ራስ መኮንንም ደጅ አዝማችነት ማዕረግ በሰጡዋቸው በወራት ውስጥ ድንገት ታመው ስለሞቱ ፤ አጼ ምንሊክ የአባታቸው የራስ መኮንን ለቅሶ አዲስ አበባ እንዲሆን በማለታቸው ፤ ኃይለ ሥላሴ ለለቅሶ አዲስ አበባ መጥተው ሳለ ፤ በእዚያው ዓመት አባታቸው ራስ መኮንን ከሌላ እናት የወለዱት ደጃዝማች ይልማ የእሚባለው ወንድማቸው ሐረር ላይ ተሹሞ ፤ እርሳቸው ከሐረር ተነስተው የፍቼ ገዢ ተደርገው በአጼ ምንሊክ ተሾሙ ።

የፍቼ ገዢ ቢሆኑም ፤ እዚኹ አዲስ አበባ ተቀምጠው በምስለኔ ፍቼን ያስተዳድሩ ነበር እንጂ ወደ ፍቼ ወርደው ሲያስተዳድሩ አልነበረም ። ከእዚያኽም በ1900 ዓ.ም. ለሐረር ገዢነት የተሾሙት ታላቅ ወንድማቸው ደጃዝማች ይልማ ሲሞቱ ፤ የሐረሩ ገዢነት በልጅነታቸው ተማርከው በአጼ ምንሊክ ግቢ ውስጥ ላደጉት ደጃዝማች ባልቻ ሲሰጥ ፤ ኃይለ ሥላሴ የሲዳሞ ገዢ ተደርገው በ16 ዓመታቸው ተሾሙ ።

እስከ እዚኽ ድረስ ፤ ደጅ አዝማችነቱ እንዲኹ መዓረግ ነበር እንጂ አይሰሩበትም ነበር ። ወደ ሲዳሞ ከወረዱ ግዜ አንስቶ ግን ይሰሩበት ጀምረዋል ።

ስለ እዚኽ የኃይለ ሥላሴ ፤ የፖለቲካ ህይወት በ1900 ዓ.ም. በ16 ዓመታቸው በሲዳሞ ጀመረ ማለት ይቻላል ። ሲዳሞም ብዙ ሳይቆዩ ፤ ከላይ እንደ አልነው አጼ ምንሊክ ፤ በ1901 ዓ.ም. በጠና ሲታመሙ ፤ ለጥየቃ ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ፤ በጥቂት ግዜ ውስጥ አዲስ የስልጣን ድልድል ስለተደረገ ፤ ከሲዳሞ ተነስተው ደጃዝማች ባልቻ ሲያስተዳድሩት የነበረው የሐረር ገዢ ሆነው በ1902 ዓ.ም. ተሾሙ ።

አጼ ኃይለ ሥላሴ ፤ ሐረር ላይ ገዢ ሆነው እስከ 1909 ዓ.ም. ለ7 ዓመት ከቆዩ በኋላ ፤ ልጅ እያሱ ከሞግዚታቸው ራስ ቢትወድድ ሞት በኋላ ስድስት ዓመት ሐገር ካስተዳደሩ በኋላ ፤ ልጅ እያሱ ኃይለ ሥላሴን ከሐረር አንስተው ከፋ ላይ ለመሾም በማሰብ አዲስ አበባ አስጠሩዋቸው ።

ከእዛኽም ኹለት ወር በአዲስ አበባ ከአቆዩዋቸው በኋላ ፤ ልጅ እያሱ ከመኳንንቶች ጋር በነበራቸው እየባሰ በመጣ ግጭት ምክንያት ፤ ለሥራ ወደ ሐረር በኼዱበት ከአልጋ ወራሽነታቸው በመሻራቸው ፤ የአጼ ምንሊክ ብቸኛ ሴት ልጅ ንግሥት ዘውዲቱ ፤ ንግሥተ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ሆነው ፤ ኃይለ ሥላሴ ደግሞ ፤ አልጋ ወራሽ እና ባለ ሙሉ ስልጣን እንደራሴ ሆነው በ1909 ዓ.ም. ተሾሙ ።

ይኽ የአልጋ ወራሽነት እና የባለ ሙሉ ስልጣን እንደራሴነት ስልጣን ፤ ምንም እንኳን ተጠሪነቱ ለንግሥት ነገሥት ዘውዲቱ ቢሆንም ፤ ሙሉ ለሙሉ ሐገር የማስተዳደሩን ኃላፊነት ለኃይለ ሥላሴ የሰጠ ነበር ። እንደ ማሳያ ፦ አኹን እንግሊዝ ውስጥ ባለው አሰራር ፤ ኃይለ ሥላሴ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ነበር ማለት ይቻላል ።

ከእዚኽ ግዜ በኋላ የአለውን ግዜ ነው ፤ የኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያ መሪነት የስልጣን ግዜ መጀመር የእሚቻለው ፤ ምክንያቱም የንጉሥነት ስሙ እና ክብሩ ሲቀር ፤ ከ1909 ዓ.ም. አንስቶ የሐገሪቱ መሪ እሳቸው ስለነበሩ ።

በእዚኽ የአልጋ ወራሽነት እና የባለ ሙሉ ስልጣን እንደራሴነት ፤ ለ12 ዓመት ገደማ ከቆዩ በኋላ ፤ ክብራቸውን ለመጨመር በ1921 ዓ.ም. ንጉሥ ሆኑ ፤ እንደገና የንግሥት ዘውዲቱን መሞት ተከትሎ በ1923 ዓ.ም. ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ሆኑ ።

ምንም እንኳን ይኽ ክፍል ፤ በግዜ ቀደም ተከተሉ ምክንያት ከ1901 ዓ.ም. ቢጀምርም ፤ ደጃዝማች ተፈሪ መኮንን ከንግሥት ዘውዲቱ ንግሥትና ጋር ተያይዞ በ1909 ዓ.ም. አልጋ ወራሽ እና ባለ ሙሉ ስልጣን እንደራሴ እስከ ሆኑበት ግዜ ድረስ የአለው 8 ዓመት ፤ በነበረው የስልጣን ሽግሽግ ምክንያት ያለመረጋጋት እና የስልጣን ፍትጊያ የእሚስተዋልበት በመሆኑ ከተነሳንበት ግብ አንፃር ብዙም የእሚባልበት ወቅት አይደለም ።

ስለ እዚኽ ፤ የእዚኽ ክፍለ ዘመን ዋና ባለ ታሪክ ፤ ከ1909-1966 ዓ.ም. ድረስ ለ57 ዓመታት ፤ በተለያየ ማዕረግ ሐገር የመሩት የአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ታሪክ ነው ማለት ይቻላል ።

የኃይለ ሥላሴ የስልጣን ዘመን ቆይታ ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በአጼ ምንሊክ የተጀመሩትን የዘመናዊ ማሕበረ ኢከነሚ ተቋማት ግንባታን በማስቀጠል እና አዳዲሶችን በማስጀመር እና በማጠናከር ሲወደስ ፤ በተሳሳተ የታሪክ እና የፖለቲካ ሳይንስ ግንዛቤ ምክንያት ፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ፖለቲካዊ የእድገት ደረጃ ጋር የእማይመጣጠን የመንግሥት አወቃቀር በመምረጥ ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሕዝባዊ መንግሥት ባለቤት የማድረግ ታሪካዊ አደራውን በአግባቡ ሳይወጣ ፤ በአብዮት ከስልጣን የተወገደበትን ኹኔታ እና እርሱንም ተከትለው በኢትዮጲያ ለመጡ የተለያዩ ፖለቲካዊ ቀውሶች ምክንያት ሆኗል የእሚለውን ወቀሳም የያዘ ነው ።

ኃይለ ሥላሴ ወደ ስልጣን በመጡበት ወቅት ፤ እንደ ተራማጅነታቸው ከውግ አጥባቂው ግፊያ ቢኖርባቸውም ፤ በአጼ ምንሊክ መሠረታቸው የተጣሉትን ፤ የዘመናዊ ማሕበረ ኢከነሚ ተቋማትን ፦ ሚንስተር መሥሪያ ቤቶችን ፣ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ፣ የስልክ እና የፖስታ አገልግሎት ፣ መኪና ትራንስፖርት ፣ ዘመናዊ ህትመት ፣ ዘመናዊ ሆስፒታል ፣ ዘመናዊ ባንክ ፣ ዘመናዊ ሆቴል ፣ ወዘተ ፤ ከነበሩበት የማሳያነት ደረጃ አንስተው በደንብ አደራጅተው ለውጤት አብቅተዋል ።

ለምሳሌ ፦ የሚንስተር መሥሪያ ቤቶች የራሳቸው ህንፃ ፣ መመሪያ ፣ በጀት ፣ ወዘተ ፤ እንዲኖራቸው በማድረግ ፤ ከእየ ምኒስተሩ ቤት አውጠተው ዘመናዊ ተቋም አድርገዋቸዋል ። አንድ በአዲስ አበባ ብቻ የነበረውን ዘመናዊ ትምህርት ቤት ፤ በመላ ሐገሪቱ በትልልቅ ከተሞች እንዲስፋፋ አድርገዋል ። አንድ ለማሳያ የነበረችውን መኪና ፤ ብዙ መኪና በማስገባት መኪና ሕዝብ የማጓጓዝ እና የጭነት ሥራ እንዲሰራ አስጀምረዋል ።

በአጼ ምንሊክ የተጀመረውን የምድር ባቡር እስከ አዲስ አበባ የማድረሱን ሥራ አስጨርሰው ሥራ ላይ እንዲውል አድርገዋል ።

በአጼ ምንሊክ የተጀመረውን የኤሌክትሪክ ጀነሬተር መብራት ፤ ከማሳያነት አውጥተው በተነጻጻሪነት ለሕዝብ እንዲዳረስ እና በውኃ ኃይል የእሚሰራ የኤሌክትሪክ ማመንጫ እንዲገነባ አድርገዋል ።

በአጼ ምንሊክ የተጀመረውን ዘመናዊ ትምሕርት ፤ ከንግሥናቸው በተጓዳኝ ራሳቸውን የትምህርት ምኒስትር አድርገው ፤ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርስቲ ድረስ የደረሰ እና የኢትዮጲያን ዘመናዊነት ጥረት በአንኳርነት የእሚመራ ሙህር ያፈራ የትምህርት ስረዓት ዘርግተዋል።

በአጠቃላይ ፤ ከእላይ የጠቀስናቸው በአጼ ምንሊክ የተጀመሩ ማሳያዎችን ፤ ከማሳያነት አሳልፈው ለፍሬ አብቅተዋል ።

በአጼ ምንሊክ ከተጀመሩት ሌላም ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መስርተዋል ፣ በሐገሪቱ ለመኪና ትራንስፖርት የእሚሆኑ የአውራ ጎዳናዎች አስጠርገዋል ፣ የሐገሪቱን መንግሥት እንደ ገና በማዋቀር መንግሥታቸውን ሕገመንግሥት የአለው የዘውድ ስረዓት በማድረግ ፥ የመጀመሪያዎቹን ፓርላማ እና ሴኔት አቋቁመዋል ፣ ፍትኃ ነገሥትን በመተው ዘመናዊ የፍትኃ ብሔር እና የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አስጀምረዋል በእዚኽም ዘመናዊ የፍርድ ስረዓት ዘርግተዋል ፣ የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አወቃቀር በማሻሻል ቤተ ክርስቲያኒቱን በጣም አጠናክረዋል ፣ በዲፕሎማሲው መስክ ፥ የመጀመሪያዎቹን ቋሚ ኢምባሲዎች እና ቆንስላዎች (Consulates) በትላላቅ የውጭ ሐገራት ከፍተዋል ፣ ኢትዮጵያን ከቀኝ ግዛት ጋር የአለተያያዘች የመጀመሪያዋ ጥቁር የሊግ ኦፍ ኔሽን አባል ሐገር አድርገዋል ።

በኢትዮጵያ ታሪክ ፤ የመጀመሪያው ባለ ዘመናዊ ሕገመንግሥት መንግሥት የአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ነው ። ዘመናዊ ፍርድ ቤቶች የእሚሰሩባቸው ፤ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያዎቹ የፍትሐብሔር እና የወንጀለኛ መቅጫ ሕግጋት የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ሥራዎች ናቸው ። በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ፓርላማ እና ሴኔት የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ነው ።

ዘመናዊ መከላከያ በሰው ኃይል እና በቁሳቁስ ተገንብቶ አየር ኃይል እና ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር የተደራጀው በኃይለ ሥላሴ ነው ።

ኢሕአዴግ መጥቶ የአዲስ አበባ መልክ እስኪለወጥ ፤ አብዛኛው የአዲስ አበባ ብሎም የኢትዮጵያ መሠረተ ልማት የኃይለ ሥላሴ ነው ፤ በአንዳንድ መሠረተ ልማቶች ዘንድ የአምስት አመቱ የጣሊያን ወረራ የሠራቸው ሥራዎቹ የአሉ፟ ቢሆንም። ኢንተርኔት እና ከምፒውተር ከአልሆነ በስተቀር ፤ ዘመናዊዋ ኢትዮጵያ መሰረቷ የተጣለው በአጼ ምንሊክ ጀማሪነት እና በአጼ ኃይለ ሥላሴ አስፋፊነት ነው ።

እነ እዚኽ የኃይለ ሥላሴ መንግሥት የእሚወደሱባቸው የለውጥ ሥራዎች ሲሆኑ ፤ ከእላይ እንደ አልነው ደግሞ ፤ በፖለቲካዊ መዋቅሩ ረገድ ፤ ኢትዮጵያን የሕዝባዊ መንግሥት ባለቤት የማድረግ ታሪካዊ እድል የአበላሸ መንግሥት በመሆኑ የታሪክ ተወቃሽ ነው ።

አስቀድመን እንደ አየነው ፤ እስከ አኹን በእሚታወቀው እውቀት ፤ ሕዝብ ጠንካራ ብሔራዊ መንግሥት የመገንባት ታሪካዊ የእድገት ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ፤ የእሚቀጥለው ፖለቲካዊ የእድገት ደረጃው የእሚጠይቀው ነገር ቢኖር ይኽንን ጠንካራ መንግሥት በሰብዓዊነት አስተሰሳሰብ የእሚመራው ሕዝባዊ መንግሥት ማድረግ ነው ።

ይኽም ደግሞ ፤ የዘመናዊው ስልጣኔ ተቋዳሽ የአልሆኑ ፖለቲካዊ ማሕበረሰባት ፤ ወደ ዘመናዊነት ለመግባት ጉዞ በእሚጀምሩበት ግዜ ፤ የእየ ሐገራቱ የፖለቲካ ሊህቃን ፤ ለእየ ሐገራቸው ይገባል ብለው የእሚያምኑት ዓይነት የፖለቲካ ስልጣን አወቃቀር ፤ ስለ ሐገራቸው ሕዝብ የፖለቲካ ዕድገት ደረጃ በአላቸው ግንዛቤ ላይ ይወሰናል ማለት ነው ።

በልማዳዊው የታሪክ ኺደት ፤ ሐገራት ወይንም ሕዝብ ከገጎጥ እና ከነገድ አደረጃጀት ወጥተው ወደ የጋራ ወይንም ብሔራዊ መንግሥት ባለቤትነት የእሚሸጋገሩት በሺ ዓመታት ቆይታ እንዲኹም ከእዚኽ ብሔራዊ ወይንም ብሔራዊ መንግሥት ምሥረታ ወደ ሕዝባዊ መንግሥት የእሚሸጋገሩት በመቶዎች ዓመታት ኺደት ነበር ።

አኹን በእምንገኝበት ዓለም ዓቀፋዊ የሰው ልጅ የታሪክ ምዕራፍ ግን ፤ በውስብስብ የዓለም ዓቀፍ ፖለቲካዊ ኺደት ምክንያት ፤ የብሔራዊ መንግሥት ምሥረታቸውን በተፈጥሮዋዊ የታሪክ ኺደት ያልመሠረቱ ሐገራትም ፤ ዓለም ዓቀፍ እውቅና የአላቸው ሐገራት ኾነው ፤ የይስሙላም ቢሆን ብሔራዊ መንግሥት አላቸው ። ለምሳሌ ፦ አብዛኛዎቹ ከቀኝ ግዛት በኋላ ፤ የተመሠረቱ ሐገራት ፤ በተፈጥሮዋዊ ታሪካዊ ዝግመታቸው ከጎጥ እና ከነገድ ቅርፅ አልባ አደረጃጀት ወጥተው ሰአይሆን የብሔራዊ መንግሥት ማቋቋም ደረጃ የደረሱት ፤ ከቀኝ ግዛት እንዲወጡ ለማድረግ ሲባል ብቻ ፤ በዓለም ኃያላን መንግሥታት ይኹንታ ነው የብሔራዊ መንግሥት እንዲኖራቸው የተደረገው ።

ይኽ የይድረስ ይድረስ ብሔራዊ መንግሥት ምሥረታ ደግሞ ፤ በዘመናዊ ዓለም ያአሉ፟ትን ብሔራዊ መንግሥታት ታሪካዊ የእድገት ደረጃዎችን ዘሎ የተከናወነ በመሆኑ ፤ ዘመናዊ ብሔራዊ መንግሥታት እንዲከተሉ የእሚመከሩዋቸው የመንግሥት አወቃቀር ስረዓቶች ፤ አምባገነናዊ የለውጥ ኃዋርያ መንግሥት እና የሕዝባዊ መንግሥት ፤ በእሚል በኹለት እንዲከፈሉ አድርጓል ።

በሐገርነት ረዥም ታሪክ ፣ የራሳቸው የስነ ጽሑፍ ስረዓት ፣ ሐገራዊ ይዘት የአለው የእወቅት መሠረት ፣ ከመንደር ሽማግሌ ያአለ፟ፈ ፖለቲካዊ አወቃቀር ፣ ወዘተ ፤ ሰአይኖራቸው ፤ ስለ እዚኽ በማሕበረሰብ አወቃቀር ረገድ በከፍተኛ የኋላ ቀርነት ደረጃ ላይ ሳሉ ፤ በኃያላን ይኹንታ ሐገር እና ብሔራዊ መንግሥት የተቸራቸው ፤ ድኽረ ቀኝ ግዛት ሐገራት ፤ በአምባገነናዊ የለውጥ ኃዋርያ መንግሥት ተጠርንፈው ፤ መንግሥታቸው ምንም የመብት ረገጣ ቢያኪያኼድም ፤ በልማት ማሕበራዊ አቅማቸውን (Social Capital) እስኪገነባ ፤ በእዚኽ አምባገነናዊ መንግሥት ስር የመቆየት ታሪካዊ ግዴታ አለባቸው ወይንም እንደ እዚያኽ እንዲያደርጉ ግልጽ የአልሆነ ምክር ይመከራሉ።

ይኽ ኹኔታ ግን ፤ በኃያላን ይኹንታ ሰአይሆን ፤ በታሪካዊ ኺደት ውጤታማ ብሔራዊ መንግሥት ገንብተው ለጨረሱ እና በተለያዩ ሌሎች ታሪካዊ ምክንያቶች ፤ የስልጣኔውን መሰላል ሳይወጡት ለቀሩት ሕዝብም የእሚያስኬድ አካኼድ ነው ማለት ግን አይደለም ። ምክንያቱም ፦ በኃያላን ይኹንታ ሰአይሆን በተፈጥሮዋዊው የታሪክ ኺደት ፤ ብሔራዊ መንግሥት የአላቸው ሐገራት ፤ በልማቱ ረገድ ኋላ ቀርነት ውስጥ ቢሆንም እንኳን ፤ ስሪታቸው የእሚፈቅደው ወይንም የእሚፈልገው ፤ መንግሥታቸው ከጥንካሬው በአሻገር ሕዝባዊነትን እንዲላበስ ነው ፤ በተለይ ደግሞ እነ እዚኽ ሕዝብ እንደ ክርስትና በአለ የሰው ክብርነት በእሚያጎላ ኃይማኖት ማሕበራዊ እሴታቸው ከተቃኘ።

ይኽም በመሆኑ ፤ በዘመናዊ ዓለም ውስጥ በልማቱ መስክ ኋላ ቀር በሆኑ ሐገራት ውስጥ የእሚገኙ ፖለቲካዊ ሊህቃን የፖለቲካ ዕድገት ደረጃቸውን የእሚረዱበት ወይንም ሕዝባዊ ማንነታቸው የእሚረዱበት አግባብ የእሚመርጡትን የመንግሥት አወቃቀር የመወሰን ትልቅ ሚና ይኖረዋል ማለት ነው ።

በእርግጥ የአንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ሊህቃን ሕዝባዊ ማንነታቸውን ማወቅ አለባቸው ስል ፤ ራስን በማወቅ ሰበብ አፍራሽ ፣ ፀረ-ሕዝብ ወይንም ፀረ-ዴሞክራሲ የሆነውን የማንነት ፖለቲካ ያራምዱ ማለቴ ሰአይሆን ፤ ፖለቲካዊ የእድገት ደረጃቸውን በአግባቡ ተረድተው ፤ እርሱን የእሚመጥን መንግሥት እንዲያዋቅሩ እና ይህንም የእሚመጥነውን መንግሥት የማዋቀር ግቡ በእሚያደናቅፍ አኳኋን ሕዝባዊ ዓላማ የአላነገቡ አፍራሽ የፖለቲካ ኃይሎች ፤ ታሪኩን በማዛባት ለእኩይ ዓላማቸው እንደ አይጠቀሙበት ፤ ሚዛናዊ የሆነ የሕዝብነት ታሪካቸውን በአግባቡ ይወቁ ለማለት ነው ።

ይኽም ታሪክን ለማወቅ የእሚደረገውም ጥረት ፤ ከታሪክ ጥናት ውጤት የእሚገኘውን መረጃ የተሻለውን ማሕበረሰብን ማወቀሪያ መንገድ የመምረጡን ጉዳይ በግብዓትነት ለማገልገል ከማሰብ እንጂ ታሪክን እየሸቃቀጡ ለፕርፖጋንዳ መሳሪያነት ለማዋል ከእሚደረግ ዓይነት የታሪክ ጥናት ዘይቤ መፅዳት አለበት ።

ይኽን መስሉ የማሕበርሰብ ፖለቲካዊ ታሪክ ጥናት ደግሞ ከየትኛውም ዓይነት ዝበት ፀድቶ ፤ በታቻለው መጠን ፤ በተዓማኒ ምንጮች ላይ ተንተርሶ የነበረውን እንደ ነበር ለማስቀመጥ የእሚሰራ ነው ። ይኽም በመሆኑ ፤ ትክክለኛውን ፖለቲካዊ አወቃቀር ለመምረጥ የእሚያስችለው ታሪክ ፤ ኋላ ቀር ለአለመባል ፤ ያልደረሰበትን የዕድገት ደረጃ ደርሼበት ነበር ለማስባል ፤ መሬት መንቀጥቀጥ ወይንም ታላቁ ጎርፍ አጥፍቶት ነው እንጂ ፤ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች የአሉ፟ት ስልጣኔ ነበረኝ የእሚል ‘ትንቢተታሪክ’ ዓይነት ጉንጉን ውስጥ አይገባም ።

በተመሳሳይም ፤ አንድ ሕዝብ የፖለቲካ አቅጣጫውን ለመምረጥ ታሪኩን በእሚያጠናበት ወቅት ፤ በታሪካዊ ሐቀኝነት ስም ፤ የቀደመውን ታሪካዊ እድገት መዘንጋትም የለበትም ። ምክንያቱም ፦ ለትክክለኛው ውሳኔ ግብዓት የእሚሆነው ትክክለኛው እና ሚዛናዊው ኃቅ እንጂ ፤ ያልሆንኩትን ነኝ ማለቱም ሆነ የሆኑትን አይደለሁም ማለት አይደለም ።

በአጠቃላይ ፤ ለፖለቲካ ማሕበረሰብ ራስን መገንዘብ ወይንም ማወቅ ሲባል የሜታፊዚካል (የልዕለ ተፈጥሮ ፍልስፍና) ጉዳይ ሰአይሆን ፤ በሳይንሳዊ መንገድ የተቀመጡ ታሪካዊ ኃቆችን ሰብስቦ እነርሱን በአግባቡ መረዳት እና መተንተን ማለት ነው ።

ወደ ኢትዮጵያ ልዩ ኹኔታ ስንመጣ ፤ ታሪካችን በጣም ረዥም እና ውስብስብ በመሆኑ እና ዘመናዊ የታሪክ አጥኝዎችም በተደራሽ ኹኔታ ታሪካችንን አዘጋጅተው በአለማቅረባቸው እና የፖለቲካ ሊህቃኖቻችንም የተገኘውንም ታሪክ በማጥናት ራሳቸውን በአለማስተማራቸው ፤ ከእዚኽም የተነሳ ስለ ሕዝባችን የፖለቲካ እድገት ደረጃ የአላቸው መረዳት የተሳሳተ በመሆኑ ፤ ከትክክለኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፖለቲካዊ የእድገት ደረጃ ጋር የእማይስማማ የመንግሥት አወቃቀር በተደጋጋሚ ሲመርጡ ኖረዋል ።

ሕዝብ ምንም ኋላ ቀር ቢሆኑም ፤ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ የአሉ፟ ፤ ባለረዥም ታሪካዊ እድገት የአላቸው እና በኹኔታዎች ሰንካላነት እና ከአመራር እጦት ኋላ ቀር የሆኑ ሕዝብ ፤ አንዳንድ ለውጦችን በቶሎ ተረድተው ሊቀበሉ እንደ እሚችሉ መገንዘብም ተገቢ ነው ። ተዳፍኗል ማለት የለም ፣ አይነሳም ፣ እንደ አዲስ ጅማሮ ከባዶ መነሳት ይፈልጋል ማለት አይደለም ።

በኃይለ ሥላሴ ዘመን ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ኋላ ቀር የነበር መሆኑ ብዙም ምርምር የእሚጠይቅ ጉዳይ አልነበረም ። የወቅቱ የኢትዮጵያዊው ኋላ ቀርነት ግን ፤ እንደ ቀረው የጥቁር አፍሪካ ሕዝብ ፣ ወይንም እንደ ሩቅ ምሥራቆቹ ሕዝብ ወይንም በላቲን አሜሪካ ከቀኝ ግዛት በፊት እንደ ነበሩት ነዋሪ ሕዝብ ዓይነት ኋላ ቀርነት አልነበረም ።

ቢያንስ ቢያንስ ከዘመናዊው ካፒታሊዝም በፊት የእሚገኘው ፤ የደረጀ የክርስቲያን የፊውዳል ወይንም የጉልት ማሕበረ ኢከነሚ እድገት ደረጃ ላይ የደረሰ እና የነበረውም የተዳፈነ የእድገት አቅም ፤ ብዙ አውሮፓዊያኖችን ያጓጓ እና ይኽንን የተዳፈነ አቅም ፤ ከፋፍቶ እና ንፋስ ሰጥቶ እንደ ገና ለማቀጣጠል ትልቅ ፍላጎት የጫረ ነበር ።

በኢትዮጵያ የነበረውም የፊውዳል ስረዓት ፤ በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ፤ አንዳንድ ጥራዝ ነጠቅ ግራ ዘመሞች እንደ እሚሉት ኢሰብአዊ እና በዝባዥ የእሚባል ሰአይሆን ፤ ከካፒታሊዝም አንጻር ኋላ ቀር መሆኑ በአያጠያይቅም ፤ ሕዝብን የአከበረ እና የሐገርን አንድነት የአጠናከረ ፤ በዓይነቱ ለየት ያለ የፊውዳል ስረዓት ነው።

እውነታው ይኽ ቢሆንም ፤ በክፍል አምስቱ እና ስድስቱ ሰንካላ ታሪክ ምክንያት ፤ ይኽ የስልጣኔ ደጅ ላይ የአለ፟ ሕዝብ ፤ በአለፈበት ፈታኝ እና የከሸፈ የለውጥ ኺደት ፤ በደረሰበት ማሕበራዊ መንኮታኮት ፤ በወቅቱ መመዘኛ ኋላ ቀር ሆኖ በመገኘቱ ፤ ተገቢው የቀድሞው ታሪካዊ ደረጃው እውቀት የሌላቸው ሊኽቃን ፤ ወቅታዊ ደረጃውን ብቻ እየተመለከቱ በሰንካላ ታሪክ የተጋረደውን እምቅ አቅሙን ሲዘነጉት ኖረዋል ።

ከኃይለ ሥላሴ ጀምሮ ኢትዮጵያን ማዘመን ላይ የአሉ፟ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይላት የሕዝባቸውን ፖለቲካዊ ንቃት የእሚረዱበት ብዥታ ፤ የማነቃቂያ አስተማሪዎች የእሚጠቀሙበት አንድ ‘ታሪካዊ ምሳሌ’ የእሚገልፀው ይመስላል ።

በእዚኽ የማነቃቂያ ታሪክ [119] ፤ የታሪኩ ባለቤት በበጎች መካከል የአደገ አንበሳ ወይንም በዶሮዎች መካከል የአደገ ንስር ተደርጎ ይቀርባል ። የታሪኩም ይዘት ፥ ታሪኩን በንስሩ ምሳሌነት ላቅርበው እና ፤ ይኽ በዶሮዎች መካከል የአደገ ንስር ፤ ከዶሮዎች ጋር በማደጉ ራሱን እንደ ዶሮ በመቁጠር ጥሬ ሲለቅም እና በቆጥ ላይ ሲኖር ይኖራል ፤ አንድ ቀን ፤ እርሱን የእሚመስለውን ንስር እስኪያይና ንስር መሆኑን እስኪያውቅ ።

‘ታሪኩን’ አይቶ ንስር መሆኑን እስኪያውቅ ፤ ከተፈጥሮዋዊ አቅሙ በታች በሰንካላ ‘ታሪክ’ ምክንያት ውድቀት ውስጥ የተገኘበት ነባራዊ ሁኔታ ፤ ተፈጥሮዋዊ ወይንም ታሪካዊ አቅሙን ጋርዶበት ነበር ፤ ስለ እዚኽ ፦ ራሱን ተቃርኖ ውስጥ አግኝቶታል ። በተፈጥሮ ንስር ሆኖ ሳለ ፤ በግንዛቤ ደረጃ የእሚያውቀው ግን ዶሮነቱን ነው ።

ኢትዮጵያዊያን የማዘመን ትግል ውስጥ የገቡት የፖለቲካ ኃይላትም ፤ እንደ እዚኽ ምሳሌ ፦ የኢትዮጵያን ሕዝብ ፖለቲካዊ የእድገት ደረጃውን ያለ መገንዘብ ችግር የነበረባቸው ይመስላል ።

በአንድ በኩል ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፤ እንደ አብዛኛው የጥቁር አፍሪካ ሕዝብ ወይንም እንደ አብዛኛዎቹ የሩቅ ምሥራቅ አረማዊ ነዋሪዎች ወይንም ከቀኝ ግዛት በፊት በላቲን አሜሪካ ይኖሩ እንደ ነበሩት ሕዝብ ፤ በሳር ጎጆ የእሚኖር ፣ ይኽ ነው የእሚባል ጥርጊያ መንገድ የሌለው ፣ የጋማ ከብቶች ዋነኛ መንቀሳቀሻ ንብረቶቹ የሆኑበት ፣ ወዘተ ፤ ዓይነት ሕዝብ ነው ፤ የሰለጠነው ዓለም መኖሪያውን በግንብ አድርጎ ፣ ከፋም ለማም መንገዶቹን ጠርጎ በመንኮራኩሩ (በጎማ) በሚነዱ መጫኛ ጋሪዎች እና መጓጓዣዎች ሲጓዝ በነበረበት ወቅት ።

በሌላ በኩል ደግሞ ፤ ይኸው ኋላ ቀር በእሚባለው ሕዝብ የልማት ደረጃ ላይ የእሚገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፤ ከመሰሎቹ ኋላቀር ሕዝብ በተለየ ፤ ሰልጥነው ቤታቸውን ግንብ ፣ መንገዳቸውን ጥርጊያ ፣ መጓጓዣቸውን ባለጎማ ፣ ወዘተ ፤ ከአደረጉት ሕዝብ ቀድሞ እነርሱ በነበሩበት ደረጃ የነበረ ፤ ምንም እንኳን ይኽ ደረጃው አኹን ጠፍቶ በሳር ጎጆም ቢኖርም ፤ ‘የባሕላዊው’ የቤተ ክህነት የትምሀርት ስረዓቱ ፣ የእውቀት መዛግብቱ ፣ በክብረ ነገሥት እና በፍትኃ ነገሥት ያጌጠው የፖለቲካ አደረጃጀቱ ጥልቀት እና የሰብዓዊ እሴቶቹ ፤ የማሕበራዊ እድገቱን ከፍታ የእሚያሳዩለት እና አንቱ የእሚያስብሉት ሕዝብ ነው ።

ይክም ብቻ ሰአይሆን ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ማዕከሉን ከሸዋ ወደ ጎንደር በማዞር ኺደት ውስጥ ወይንም ይኽንን እንዲያደርግ በአስገደደው የግራኝ ወረራ ምክንያት ፤ ከሸዋ ወደ ጎንደር ሲዘዋወር ፤ በሸዋ እና አከባቢዋ የተዋቸው ልማቶች እና ከሸዋ እስከ ጎንደር የገነባቸው ልማቶች ፤ ቀጣይነት ቢኖራቸው ፤ አንዳንድ ሰዎች ድህረ ግራኝ ሸዋ የነበረበትን አቋም አይተው ኢትዮጵያን ሊረዱ ከእሚፈልጉበት ይልቅ በጣም የተለየ ግንዛቤ ይኖራቸው ነበር ስለ ኢትዮጵያ ማሕበረ ስልጣኔ። ጎንደር እና አከባቢው ፤ በወቅቱ ከአውሮፓ ከተሞች ብዙም አይተናነስም ነበር።

ይኽም በመሆኑ ወይንም የኢትዮጵያ ሕዝብ የአለፈበት የታሪክ ውጣ ውረድ አታላይ መልክ ስለ ሰጠው ፤ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች በትክክለኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ እውቀት ከአልታገዙ ፤ ከሌላው ኋላ ቀር የዓለም ማሕበረሰብ ጋር ፈርጀውት ፤ የተሳሳተ የፖለቲካ አቅጣጫ ሊመርጡለት ይችላሉ ወይንም በእኔ እምነት ሲመርጡለት ቆይተዋል ።

ለምሳሌ ፦ በጅሮንድ ተክለኃዋሪያት የመጀመሪያው የአጼ ኃይለ ሥላሴ ሕገመንግሥት በ1923 ዓ.ም. ከፀደቀ በኋላ ፤ ስለ ሕገመንግሥት ምንነት ገለጻ በአደረጉበት ወቅት ፤ ከእዚኽ ሕገመንግሥት በፊት የነበረውን ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በጥሬ ካብ ከተሠራ ቤት ጋር ለማመሳሰል ሲፈልጉ ፦

“ ፪ (2) ኛ ፡ ንጉሡ ባለ ስልጣን ሆኖ በትክክል ተለይቶ የተጻፈ ሕግ ሳይኖረው ከትውልድ እየተሸጋገረ በቆየው ልማድ ይሠራል ። ቅጣትም ምሕረትም ለማድረግ ፤ ለመሾም ለመሻርም በአደባባይ በጉባኤ እያስፈረደ በክብር እየሸለመ ፤ በገኃድ እያሳወጀ ነው ። በድንገት በደል ነገር ቢሠራ ማገጃ አልተደረገበትም ። እንደ እዚኽ የአለው መንግሥት አብዛኙ ሕገመንግሥት ባልተቋቋመላቸው ሕዝብ መካከል ሲደረግ ቆይቶ ነበር ። ምሳሌውም በጥሬ ካብ እንደ ተሠራ ቤት ነው ። እርሱም ትዕግስት የአለው በልማድ የእሚሰራ መንግሥት ተብሎ ተሰይሟል ። የዘውድ አወራረሱ ድንገተኛ እድል ለሰጠው ነው ። [64]”

በእዚኽ በ1923ቱ ሕገመንግሥት የተቋቋመውን የኃይለ ሥላሴን መንግሥት ደግሞ ፦ ‘ምሳሌውም በድንጋይና በኖራ በአሸዋም እንደ ተገነባ ቤት ያህል ነው ።’ ብለው ልዩነቱን ለማስቀመጥ ሞክረዋል ።

እነ እዚኽ ገለፃዎቾቻው ግን ፤ ርዕዮታዊ የግንዛቤ አድማስ ጥበታቸውን ብቻ ሰአይሆን የኢትዮጵያን ታሪክ እና ነባራዊውን ኃቅ የማስተዋል ችግራቸውን የእሚያሳዩ ነገሮች አሉበት ።

አንደኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ፤ ትልቅ ፍልስፍናዊ ይዘት በአለ፟ው ክብረነገሥት እና በፍትኃ ነገሥት የእሚመራ ፤ ራመድ ያለ የዘውድ መንግሥት እንደ ነበረ አልተረዱም ወይንም በታሪክ አጋጣሚ ፤ ከማስታወስ ርቆባቸዋል ።

ኹለተኛ ፤ አዲሱ የኃይለ ሥላሴ ሕገ መንግሥት በይዘቱ ፤ ካቋቋመው የማህተም ፓርላማ እና ሴኔት በስተቀር ፤ በስልጣን መዋቅሩ ከነባራዊው የዘውድ ስረዓት በምንም የእማይለይ ነበር ።

ይኽም ብቻ ሰአይሆን ፤ ከመጀመሪያው ሕገመንግሥት በፊት የነበረው የዘውድ ስረዓት ፤ ኹኔታው ሲፈቅድለት ፤ መሠረታዊ የስልጣን ሥሪቱ ብዙም ሳይንገዳገድ ፤ የዘመናዊ መንግሥት መገለጫ የሆኑትን ሚንስተር መሥሪያቤቶቹን እና ሚንስተሮችን ማደራጀት ጀምሮ ነበር ፤ ምንም እንኳን በአጼ ምንሊክ በበሽታ መድከም ምክንያት ፤ ሳይገፋበት ቢቀርም ።

ይኽም በመሆኑ ፤ ይኽን እና መሰል የታሪክ አረዳድ ውዥንብሮች ፤ ከአስተሳሰብ አድማስ ውስንነት ጋር እየተዳመሩ ፤ የሐገሪቱን የለውጥ ኺድት ሲያዥጎረጉሩት ኖረዋል ።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእሚገኝበት ወይንም የታሪክ መጥፎ አጋጣሚ ጥሎበት ከኼደው ፤ የኋላ ቀርነት ገፅታው ተነስቶ ፤ ‘በጤናማ’ ታሪክ ኺደት መሰል ኋላ ቀርነት ላይ እንደ እሚገኙ ሕዝብ ፤ የእሚያስፈልገው ገዢ እንጂ ሕዝባዊ መንግሥት አይደለም የእሚለው አስተሳሰብ ፤ የኃይለ ሥላሴ ፣ መንግሥት መሠረታዊ የፖለቲካዊ ስሌታቸው ስህተቶች ለመሆናቸው ብዙም ጥርጥር የለውም ።

ከእላይ እንደ አልነው ፤ አጼ ኃይለ ሥላሴ ፤ እንደ እሚታወቀው ፤ በአጭር ግዜ ወስጥ ፤ በኢትዮጵያ ትልልቅ የዘመናዊነት ፕሮጀክቶችን በማስፈፀም የእሚቀድማቸው የለም ።

ይኽንንም ፤ ከነባራዊው ወግ አጥባቂ በእሚደርስባቸው ጫና ፤ እንደ ራሳቸው ገላፃ ‘በኹለት ብረት መሐል እንደገባ እንጨት በብዙ መከራ’ እንደ ሠሩትም የታወቀ ነው ፦

“ … በ1909 ዓ.ም. አላፊነቱን በተቀበልሁ ግዜ ፤ ስድስት ዓመት ሙሉ የተበላሸውን ለማቅናት ፤ ያልተጀመረውን ሥራ እንዲጀመር ለማድረግና አዲሱን ስልጣኔ ለማስገባት ፤ አሳቤና ይልቁንም አሮጌውን ልምድ ለሚወደው ሕዝብ አጋዥ ስለ ነበረው ፤ በኹለት ብረት መካከል እንዳለ እንጨት አጣብቀውኝ የተቻለኝን እየሰራው ግዜውን አሳለፈኹ ። [64]”

ይኽ ዓይነቱ የወግ አጥባቂ ክንፍ ግን ፤ የኢትዮጵያ መገለጫ ብቻ ሰአይሆን ፤ ማንኛውም ወደ ሕዝባዊ ፖለቲካ የእሚሸጋገር እና በሕዝባዊ ፖለቲካ መርሕ የእሚሰራ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ውስጥ የአለ፟ ፣ የነበረ እና የእሚኖርም ፤ የሕዝባዊ መንግሥት መገለጫ በመሆኑ ፤ ስለ መኖሩ በአያከራክርም ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፖለቲካዊ ኋላ ቀርነት መገለጫ ተደርጎ መወሰድ እንደ ሌለበት ማስቀመጡ ተገቢ ነው ።

የዘመናዊ ሕዝባዊ ፖለቲካ ጅማሮም ሆነ ገፅታ ወይንም ግራ እና ቀኝ የእሚለው የፖለቲካ ክፍፍልም ይኸው ነው ።

ከመጀመሪያው ጀምሮ ልዕልት ዘውዲቱ ንግሥት የተደረጉበትን እና ደጃዝማች ተፈሪ አልጋ ወራሽ እና ባለሙሉ ስልጣን እንደራሴ የተደረጉበትን የስልጣን አወቃቀርም ስናየው ፤ በወግ አጥባቂው እና በተራማጁ መካከል የነበረውን የኃይል ሚዛን የእሚያሳይ ነው ።

አልጋ ወራሽ እና ባለሙሉ ስልጣን እንደራሴው ፤ ምንም እንኳን መላውን የመንግሥት አስፈፃሚ የመምራት ስልጣን ቢኖረውም ፤ ለእሚያድርጋቸው ውሳኔዎች የንግሥቲቱን ይኹንታ ማግኘት ግድ መሆኑ እና ንግሥቲቱም የወግ አጥባቂው ‘ወኪል’ መሆናቸው ፤ በፍጥነት መራመድ ለእሚፈልጉት ኃይለ ሥላሴ ጫና ቢያበዛቸውም ፤ ይኽ በዘመናዊ ቋንቋ ቁጥጥር እና ሚዛን (Check & Balance) ዓይነት ኹኔታ ፤ ምንም እንደ አይሠሩ አሳስሮ ያስቀመጣቸው አልነበረም ። ኹለተኛ ከእላይ እንደ አልነው ይኽ ዓይነቱ ጫና የትኛውም በዓለም ላይ ያለ ዘመናዊ ፖለቲከኛ የእሚገጥመው እንጂ ለኃይለ ሥላሴ ልዩ አልነበረም ።

ኃይለ ሥላሴ ፤ በእዚኽ ዓይነት ፖለቲካዊ ምሕዳር ውስጥ ሆነው ፤ በስልጣን ዘመናቸው ከእላይ የዘረዘርናቸውን ፤ እንደ ዶፍ በኋላ ቀርነት ክው ብላ በነበረችው ኢትዮጵያ ላይ የወረደ የስልጣኔ ዝናብ ለማዝነብ አስችሎዋቸዋል ።

ይኽ የኃይለ ሥላሴ በስልጣኔ ዶፍ ዝናብ ሐገርን የማረስረሱ ሥራ ፤ ምንም እንኳን ኃይለ ሥላሴ ስልጣኔን በሐገር ውስጥ ለማስገባት ፤ በፋና ወጊነት የተጫወቱትን ትልቅ ሚና ቢያሳየንም ፤ የወቅቱ ዝርዝር ታሪክ ሌላ የእሚነግረን ኹለት ተጨማሪ ነገሮችም አሉት ።

አንዱ እና የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ያኽል ለለውጥ ወይንም ዘመናዊነትን ለመቀበል በበቂ ዝግጅት ላይ የነበረ ሕዝብ መሆኑን ያሳያናል ። ምንም እንኳን ኃይለ ሥላሴ እንደ አሉት ፤ ወግ አጥባቂው ከፍተኛ ድጋፍ ነበረው የእሚለው አባባል ተቀባይነት ቢኖረውም ፤ አንድ ግዜ ግን የወግ አጥባቂውን ግፊያ አልፈው ለውጥን ማስፋፋት ከጀመሩ በኋላ ፤ የለውጥ ፍላጎቱ በሕዝቡ ዘንድ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አልኼደም ።

የዘመናዊ ትምህርት ሲጀመር ፤ ሕዝቡ ጠቅላላ ልጁን የማስተማር እና ራሱም የመማር ፍላጎቱ እየጨመረ የመንግሥትን ትምህርት የማቅረብን አቅም የእሚፈታተን ሆነ እንጂ ፤ ተማሪ እየጠፋ ትምህርት ቤቶች አልተዘጉም ፣ ዘመናዊ ትምህርት አምጥቶ ባህላችንን አጠፋ ተብሎ አስተማሪ አልተገደለም ፣ ትምህርት ቤት አልተቃጠለም ፣ ወዘተ ፤ የተወሰነ ልማዳዊ ግርታ እና ጥቂትም ቢሆን ማንገራገር እና ተቃውሞ የነበር መሆኑ እንደ ተጠበቀ ሆኖ ።

የጥርጊያ መንገድ ተደርጎ ፤ በካሚዮን የጭነት አገልግሎት ሲጀምር ፤ ጠቅላላ ሐገራዊ የጥርጊያ መንገድ እና የካምዮን ማጓጓዣ ፍላጎት በይበልጥ እየጨመረ በመምጣት ፤ እነ እዚኽን ካሚዮኖች በማሸከርከር ሞያ ላይ ከእሚሰማሩት ሰዎች ጀምሮ ፤ ጠቅላላ የካምዮን ግልጋሎት እና መጠነ ሰፊ የጥርጊያ መንገዶች በእየግዜው እየጨመረ ነው የኼደው ።

በአጠቃላይ በህክምናው ፣ በህትመቱ ፣ በተቋማት ግንባታው ፣ ወዘተ ፤ የዘመናዊ ግልጋሎቶቹን ለመስጠትም ሆነ ለመቀበል የነበረው ሕዝባዊ ፍላጎት እና ተሳትፎ ማብቂያ አልነበረውም ።

ከእዚኽ ኹሉ በላይ ፤ እነ እዚኽ አዳዲስ መስኮች ከውጭ በእሚመጡ ሞያተኞች እየተመሩ ቢጀምሩም ፤ በአስደናቂ ፍጥነት ፤ በእየ ኹሉም የሥራ መስኮች ፤ ኢትዮጵያዊያኖች ተምረው ብቁ እና ተወዳዳሪ ሞያተኞች ሆነው ፤ በህክምናው ፣ በባንኪንጉ ፣ በአውሮፕላን አብራሪነቱ ፣ በአስተማሪነቱ ፣ በሹፍርናው ፣ በዘመናዊ ወታድርነቱ ፣ በጠቅላላው በኹሉም ዘመናዊ ሞያ መስክ ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እውቅና በአላቸው ተቋማት ሰልጥነው እና ተመርቀው ለመሰማራት ብዙም አልተቸገሩም ።

በጥቁር አፍሪካ ለመጀመሪያ ግዜ የራሷ አየር መንገድ እና በእራሷ ልጆች የእሚዘወሩ አውሮፕላን የነበራት ኢትዮጵያ ነች ። ይኽ ለአኹኑ ዘመን ሰው ቀላል ይመስላል ፤ የቀደመው ዓለም ለነበረበት ዝበት ግን ትልቅ እንደምታ የአለው ነው ። ምን አልባት የኹኔታውን ዓይነተኛነት ለመረዳት ፤ የጥቁር መብት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ ፤ ወደ ነፃነት የተደረገ ረዥም ጉዞ (A Long Walk to Freedom) በእሚለው መጽኃፋቸው ላይ ፤ ለመጀመሪያ ግዜ ጥቁር ኢትዮጵያዊ አውሮፕላን ሲያበር በማየታቸው ፤ ‘ጥቁር እንዴት አውሮፕላን ሊያበር ይችላል?’ ብለው ከመገረም አልፈው ጥቁር በእሚያበረውም አውሮፕላን አምኖ ለመሳፈር የፈጠረባቸውን ድንጋጤ እና ፍርኃት የገለፁበት አኳኋን ፤ ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪክ ሰንካላነት ምክንያት በልማቱ ረገዱ ከኋላ ቀሮቹ የዓለም ሕዝብ ጎራ ቢመደብም ፤ በፖለቲካዊ እና በማሕበራዊ ንቃቱ ፤ ከመሰሎቹ ኋላ ቀር ሕዝብ ላቅ ያለ እንደ ነበር የእሚያሳይ ይመስለኛል ።

ኔልሰን ማንዴላ ስለ ኹኔታው እንዲኽ ይላሉ ፦

“ ለጥቂት ግዜ በካርቱም ከአረፍን በኋላ ፤ ወደ አዲስ አበባ ለመብረር ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ተዛወርን ። በእዚኽን ግዜ ለየት ያለ ስሜት የፈጠረበኝ ኹኔታ ተከሰተ። ወደ አውሮፕላኑ ስሳፈር ፓይለቱ ጥቁር እንደሆነ አየኹ ። ከእዚያኽ በፊት የጥቁር ፓይለት አይቼ እማላውቅ ስለነበር ፤ በአየኹበት ቅስፈት ድንጋጤዬን መቆጣጠር ነበረብኝ ። ጥቁር ሰው እንዴት አውሮፕላን ሊያበር ይችላል? ከጥቂት ግዜ በኋላ ራሴን ያዝኩት ፡ ለካንስ የአፓርታይዱ የዓዕምሮ ተከርቸም ውስጥ ነበርኹ ፡ አፍሪካዊያኖች ዝቅተኞች ናቸው አውሮፕላንን ማብረርም የነጭ ሥራ ነው ብዬ ሳስብ ኖሯል ። ከእዚያኽ በኋላ በወንበሬ ላይ ተደላደልኹ እና ራሴን ቆንጠጥ አድርጌ በል እንዲኽ እንዳታስብ አልኹት ። አንድ ግዜም አየር ላይ ከወጣን በኋላ መርበትበቴ ለቀቀኝ እና …”

“We put down briefly in Khartoum, where we changed to an Ethiopian Airways flight to Addis. Here I experienced a rather strange sensation. As I was boarding the plane I saw that the pilot was black. I had never seen a black pilot before, and the instant I did I had to quell my panic. How could a black man fly an airplane? But a moment later I caught myself: I had fallen into the apartheid mind-set, thinking Africans were inferior and that flying was a white man’s job. I sat back in my seat, and chided myself for such thoughts. Once we were in the air, I lost my nervousness and … [120]“

ማንዴላን የእሚያኽል የነፃነት ታጋይ በአፓርታይድ መድሎ ምክንያት ፤ ጥቁር ፓይለት ማየት ትንግርት ሲሆንበት ብቻ ሰአይሆን ፤ ጥቁር አይችልም ብሎ ጥቁር በእሚያበረው አውሮፕላን ተማምኖ ለመሳፈር መፍራት እና መቸሩ ፤ የዘመናት በደል የፈጠረበትን የአስተሳሰብ ዝበት ለማስተካከል ራሱን መቆንጠጥ በነበረበት በእዚያኽ ሰዓት ፤ ተርታው ወይንም መደበኛው ኢትዮጲያዊ ያለምንም ችግር ፤ እንደ ማንኛውም የሰለጠነ ሕዝብ አባል ራሱን ብቁ ፓይለት ማድረግ ችሎ ነበር ።

እንደገናም ፤ የኃለ ሥላሴ መንግሥት ፤ መንግሥትን በዘመናዊ መልኩ ከአዋቀረ በኋላ ፤ እነ እዚኽን ዘመናዊ ተቋሞች ፤ በዘመኑ ትምህርት ሰልጥነው ኃላፊነቱን የእሚወስዱ ሰዎች ከሐገር ውስጥ ለማግኘት ብዙም አልቸተገረም ። የዘመናዊ ኢትዮጵያ ባለስልጣኖች ፤ በብቃት እጥረት ለውጭ ዜጋ አልተሰጡም ። የኃይለ ሥላሴ ካብኔ በሞላው ፤ በኃይለ ሥላሴ ግዜ ተምረው የበቁ የሐገር ልጆች ፤ ሚንስተሮች እና ከፍተኛ ባለ ስልጣኖች ኾነው ሥራውን በብቃት ሲያከናውኑበት የነበር ነው ።

ኢትዮጵያዊያን የመንግሥት መሥሪያ ቤት እና ሕዝባዊ አገልግልግሎት የእሚሰጡ ፤ እንደ ኃስፒታል ፣ የመዝገብ አያያዝ እና አጠባበቅ ፣ የፖሊስ ፣ የደህንነት ፣ ወዘተ ፤ ሰራተኞች ፤ ፖለቲካው እስካልረበሻቸው ድረስ ኃላፊነታቸውን በብቃት እንደ እሚወጡ ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የእሚገኙ የውጭ ሐገር ወኪሎችም ምስክርነት ነው ።

ይኽ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛ እና ፈጣን የለውጥ ተቀባይነት ግን ፤ የለውጥ ኃዋሪያውን መንግሥት የእሚመርቱን እና ከእነ ንግሥት ዘውዲቱ አንጻር ተራማጅ የነበሩትን ኃይለ ሥላሴን ራሳቸውን ፤ ወደ ወግ አጥባቂነት ቀየራቸው ። ይኽ እንደ ዶፍ የሆነው የኃይለ ሥላሴ የለውጥ ዝናብ ኹለተኛ የእሚነግረን ነገርም ፤ ይኸው የኃይለ ሥላሴን ከለውጥ ኃዋሪያነት ወደ ወግ አጥባቂነት የመቀየርን ኹኔታ ነው ።

ለእዚኽ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ ፤ የወቅቱ የኃይለ ሥላሴ መንግሥትን መዋቅር የሠሩት ሰዎች ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የነበረበትን የልማት ኋላ ቀርነት በታሪክ ሰንካላነት ምክንያት የእሚገኝበት ኹኔታ እንጂ እንደ አብዛኛው መሰል የልማት ኋላቀር ማሕበረሰባት ፤ ዘማናዊውን ስልጣኔ ለመሸከም የእሚያስችል ማሕበራዊ አቅም በአለማዳበሩ የመጣበት አለመሆኑን ፤ ታሪኩን በተቀናጀ መልኩ አጥንተው እና የዘመናዊ ፖለቲካ እውቀትን አዳብረው መገንዘብ ስለ አልቻሉ ፤ የእሚያስፈልገው አምባገነናዊ የለውጥ ኃዋርያ መንግሥት እንጂ በሕዝባዊ መንግሥት አወቃቀር አቅሙን እየገነባ ሕዝባዊ ተቋሞችን አጠናክሮ ፤ በሕዝባዊ መንግሥት አግባብ የእሚመራ መንግሥት ሊሆን ይገባል ብለው ማሰብ በአለመቻላቸው ነው ።

ምን አልባት ፤ በጅሮንድ ተክለ ኃዋሪያት ፤ በመጀመሪያው የሕገ መንግሥት ማፅደቅ ወቅት ፤ ይኽን ሕገመንግሥት ለማርቀቅ እና ለማጽደቅ እንደ ተቋቋሙት የተለያዩ ከሚቲዎች አንድ አባልነታቸው ፤ በ1923 ዓ.ም. የፀደቀውን የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ፍልስፍናዊ መሠረት በስብከት በእሚያስረዱበት ወቅት ፤ እንደ ኢትዮጵያ ለአለ፟ው ያልተማረ ሕዝብ ለበዛበት ሐገር ፤ ሕዝባዊ መንግሥት ስረዓት አልበኝነትን በማስፈን ደም አፋሳሽ ይኾናል የአሉ፟በት አግባብ ይኽን የሐገራችን የዘመናዊ ፖለቲካ ሊኽቃንን የአስተሳሰብ ዘዬ ዝበት የእሚያሳይ ነው ፦

« ፬(4) ኛ ፡ ንጉሥ የሌለበት የማሕበር መንግሥት ሆኖ ፤ የማህበሩ አለቃ ለተወሰነ ዘመን በሕዝቡ ፈቃድ የእሚሾምበት ነው ። እንደዚህ የአለው መንግሥት በሕዝቡ ስልጣን ብቻ ተገዝቶ የሚያድር የማሕበር መንግሥት ነው ።

የማህበሩ አለቃ በተወሰነ ግዜ እየተሻረ ፤ ደግሞ በሕዝቡ ፈቃድ እየ ተመረጠ ይተካል ። በማሕበር መንግሥት የማህበሩ አለቃ ሚንስተሮችም አማካሪዎቹም ፈፅሞ የእሚመረጡት በሕዝቡ መራጭነት ነው ። ማንኛውም ፈቃድ የእሚፈፀመው ሕዝብ በቃል ብዛት ወደ ቆጠረበት ወገን ነው ። መንግሥቱም የሕዝብ መንግሥት ተብሏል ። እንደዚህ የአለው \

አኳኋን በጣም ላልተማረ እና ላልስለጠነ ሕዝብ የሚፈቀድ አይደለም ። ለሰለጠኑትም ሕዝብ እንኳን ደም እያፋሰሰ በጣም አስቸግሮ ይኖራል ። [64]»

እነ እዚኽ የፖለቲካችን መኃንዲሶች ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አልተማረም እና ሕዝባዊ መንግሥት ሐገራዊ አለመረጋጋትን የእሚፈጥር እና ደም አፋሳሽ ይኾናል ብለው ብቻ ሰአይሆን የአሰቡት ፤ በእዚኽ አግባቡ ፤ የንጉሡን ስልጣን ፍፁማዊ እና የእማይጠየቅ እና የእማይለወጥ አድርጎ በአዋቀረበት ምክንያት ፤ ተራማጅ የነበሩትን ኃይለ ሥላሴ ፤ ለውጥ በዝግታ ከአልሆነ በችኮላ ከተሠራ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል እንዲሉም አድርጓቸዋል ። ኃይለ ሥላሴ ለውጥ በዝግታ እንጂ በፍጥነት መሆን የለበትም ለማለት እንዲኽ ብለዋል ፦

“በየጥቂቱ ማለት ሕፃንን ልጅ በማባበልና በማስለመድ ካልሆነ በቀር በእጁ የያዘውን ነገር ነጥቀው ቢወስዱበት ደስ አይለውም ። በማሳየት እና በማቅመስ ካልሆነ ማናቸውንም ምግብ ቢሰጡት ሊመገበው አይፈቅድም ። ጥርስም እስቲያበቅል ወተት ወይንም ሌላ ለስላሳ ምግብ ካልመገቡት ፤ ዳቦ ወይንም ስጋ ቢያቀርቡለት ሊመገበው አይችልም ።

እንደዚሁም በትምህርት ቤት ሳይማርና በዦሮውም ሳይሰማ በዓይኑም ሳይመለከት እና ሳይመረምር በልማድ ብቻ የእሚኖረውን ሕዝብ ብዙ ዘመን የኖረበትን ልማዱን በትምህርት አስለቅቆ አዲስ ልማድ እንዲቀበል ለማድረግ በመቸኮልና በጭካኔ ሥራ ሰአይሆን በትዕግስትና በትምሕርት በየጥቂቱ በቀን ብዛት ማስለመድ ያስፈልጋል ማለት ነው ። [64]”

ይኽ አካኼዳቸው ግን ፤ ውሎ አድሮ ፤ መንግሥታቸውን በአደር ባዮች ሞልቶ እና የንጉሡን ስልጣን ገደብ አልባ በማድረግ ፤ መንግሥታቸው ለሕዝብ ጥያቄ የዝሆን ጆሮ የእሚሰጥ አድርጎታል ።

በእርግጥ ፤ መንግሥትን ሕብረተስብን በእሚያሳድግበት መጠን እና በተጓዳኝ የእማያጠናክረው ለውጥ ወይንም የመንግሥትን የሐገር ደህንነት እና ሰላም የማረጋጋት አቅም የእሚያዳክም ለውጥ ፤ በዘላቂነት የሐገር ውድቀትን የእሚያስከትል መሆኑ የታወቀ ነው ።

ምክንያቱም ፤ መንግሥትን በተጓዳኝ የእማያጠናክሩ ለውጦች ፤ ብዙ ግዜ ወይንም ኹል ግዜ የውጭ መንግሥት ወይንም ካፒታል ድርጎ ውጤቶች በመሆናቸው ፤ የሐገርን ፖለቲካዊ አንድነት እና ደህንነት ፤ ሕዝባዊ ውክልና እና ወገንተኝነት ለሌለው የውጭ መንግሥት ወይንም አክሲዮን ማሕበር አሳልፎ የእሚሰጡ በመሆናቸው ፤ የቀኝ ግዛት በኃሪ እየያዙ በስተመጨረሻ ሐገራዊ ነፃነትን ገፎ ለዘላቂ ጉዳት የእሚዳርግ መሆኑ ይታወቃል ። ስድስተኛው የታሪካችን ምዕራፍም የተሰነካከለው በአንድ በኩል ይኽን መሰሉን የድርጎ ለውጥ ሽሽት ነው ።

የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ወደ ማምሻው ላይ የአመጣው ፤ የለውጥ ሽሽት እና ወግ አጥባቂነት ግን ፤ ይኽን መሰሉን የውጭ እጅ የሐገር ውስጥ መንግሥትን ዘሎ በቀጥታ የእሚያመጣቸውን ለውጦች ሰአይሆን ፤ ሕዝቡ ራሱ በፍላጎቱ እና በጥረቱ ሊያመጣ የፈለጋቸውንም ለውጦች ፤ የመንግሥትን ጠንካራነት ማስከበር በእሚል አስተሳሰብ የሕዝብን የለውጥ ፍላጎት ገሸሽ የእሚይደርገው ዓይነት ነበር ።

ይኽም ማለት ፤ ይኽ ሰባተኛው የታሪካችን ክፍል ወይንም የኃይለ ሥላሴ የንግሥና ዘመን እና በዋናነት የኢትዮጵያ የዘመናዊነት መጀመሪያ ሊባል የእሚችለው ክፍል ፤ በኢትዮጵያ መንግሥት የሕዝብን ጥያቄ መረዳት እና መመለስ የእሚችል ወይንም በድጋሚ መንግሥትን ሕዝባዊ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ጥረት ሊካኼድበት የእሚገባ ሆኖ ሳለ ፤ በተሳሳተ ታሪካዊ ግንዛቤ እና በተሳሳተ ፖለቲካዊ ትንታኔ ፤ ከሕዝባዊ መንግሥት አደረጃጀት ይልቅ አምባገነናዊ የለውጥ ኃዋሪያውን የመንግሥት አወቃቀር እንዲመርጡ የሆኑበት ወቅት ነው ።

ከእላይ እንደ አልነው ፤ ቀኝ ግዛትን ከዓለም ላይ ለማጥፋት ሲባል በዓለም ላይ በኋላ ቀርነት ውስጥ የአሉ፟ ብዙ አከባቢዎች ፤ ኋላ ቀር ብቻ ሳይሆኑ ፤ ይኽ ነው የእሚባል ታሪካዊ የመንግሥት አደረጃጀት እና የዳበረ የሰብዓዊ ክብር የማሕበራዊ እሴት ሰአይኖራቸው ፤ በኃያላን ይኹንታ ብቻ ፤ ብሔራዊ መንግሥት እንዲኖራቸው መደረጉ ፤ በዘመናዊው ዓለም ፤ በታሪክ የአላዳባረቱን ጠንካራ መንግሥት በፍጥነት እንዲያዳብሩ ሲባል አምባገነናዊ የለውጥ ኃዋሪያ መንግሥት እንዲኖራቸው ፤ ብዙ አዋቂዎች መክረዋል ፤ ይኽም ትክክል ይመስላል ።

ይኽን ‘ዓለም ዓቀፍ’ መፍትኼ ግን ፤ የሐገራችን አዋቂዎች ፤ ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ፤ በይኹንታ ብሔራዊ መንግሥት ከተቸራቸው አከባቢዎች በታሪካዊ በኃሪው እጅግ የእሚለይ ቢሆንም ፤ ከአስተሳሰብ አድማስ ጥበት ይኹን ወይንም ይኽንን ‘ዓለም ዓቀፋዊ ልማድ’ ለምድ ለማድረግ ከማለም ባልለየ መንገድ ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የእሚያስፈልገው ፤ በአጼ ቴውድሮስ ተጀምሮ በአጼ ምንሊክ ፥ በስድስተኛው የታሪካችን ምዕራፍ ተንኮታኩቶ ከነበረበት ያገገመውን እና 8 የምኒስተር መሥሪያቤቶችን አቋቁሞ ፣ ከጅቡቱ አዲስ አበባ ባቡር እያስገባ ፣ በስሱም ቢሆን ስልክ እና ቴሌግራም እያስገባ ፤ በአጠቃላይ ሐገር የማዘመን (Modernization) ሩጫ ላይ የነበረውን መንግሥት ፤ ይኽንኑ የማዘመን ሥራ እየሰሩ መንግሥታዊ አወቃቀሩን በሕዝባዊ መንግሥት መርኽ መሠረት ማድረግ ሲገባቸው ፤ ኋላ ቀር ነንን በምክንያትነት አስቀምጠው ፤ የኢትዮጲያ ሕዝብ በአምባገነናዊ የዘውድ መንግሥት ስር ነው መሆን የአለበት ብለው ፍጹማዊውን የዘውድ መንግሥት ስር እንዲሆን አደረጉት ።

የወቅቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ መኃንዲሶች ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሕዝብነት ታሪክ በአግባቡ ቢረዱ ፣ በገጠማቸው የመማር እድል የዘመኑ ፖለቲካ ሳይንስ እውቀት ቢይዙ እና ከአርበኝነትም በአሻገር በሕዝባዊ አስተሳስብ ቢታነፁ ኖሮ ይኽን አምባገነናዊ የዘውድ ስረዓት ለወቅቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የእሚመጥነው የመንግሥት አወቃቀር ነው ብለው አይመርጡለትም ነበር ።

ምክንያቱም ፦ ይኽ ዓይነቱ የለውጥ ኃዋሪያ የሆነ አምባገነናዊ የዘውድ መንግሥት የአጼ ምንሊክ መንግሥትም የደረሰበት ደረጃ ስለ ነበር ። ምንም እንኳን ነገር መደጋገም ቢሆንም ፤ ደጋግመን እንደ አልነው ፤ ከበኃረ ነጋሽ ይስሐቅ እ.አ.አ. የ1560 ዓ.ም. አመፅ ጀምሮ የነበረው የሕዝባዊነት ጅማሮ በብዙ ምክንያት ተሰነካክሎ ብሔራዊ መንግሥቱን ስለ አዳከመ ፤ ከአጼ ቴውድሮስ ጀምሮ የተሰራው ብሔራዊ መንግሥቱን መልሶ የማጠናከር ሥራ ነበር ። ይኽ ለሕዝባዊ መንግሥት ቅድመ ኹኔታ የሆነ ብሔራዊ መንግሥት መልሶ አጠናክሮ የማቋቋሙ ሥራ ፤ በአጼ ቴውድሮ ተጀምሮ በአጼ ምንሊክ ተደምድሟል ።

ከላይ እንደ አሳየነው ፤ አጼ ምንሊክ ሐገር የማደላደሉን ሥራ በመጨረሳቸው እና የወቅቱ የዓለም ፖለቲካ ለኢትዮጵያ የተሻለ ኹኔታ ስለ ፈጠረላቸው ፤ በሽታ እና እድሜ በአይቀድማቸው ፤ የዘመናዊውን ስልጣኔ በሐገር ውስጥ ማስገባት በስፋት የጀመሩት ነገር ነበር ። ኃይለ ሥላሴ የተረከቡት ይኽንን ዓይነት መንግሥት ነው ።

ከእላይ እንደ አልነው ፤ ሐገራት ጠንካራ የለውጥ ኃዋሪያ መንግሥት እንዲኖራቸው የእሚሆኑበት ምክንያቶች አንድም በተፈጥሮዋዊ የማሕበራዊ እድገት አካኼድ መሠረት ፤ የብሔራዊ መንግሥት ምሥረታው ‘ተፈጥሮዋዊ’ በኃሪ ይኽ በመሆኑ ሲሆን ኹለተኛው ደግሞ በዘመናዊ ዓለም ድህረ ቀኝ ግዛት የአሉ፟ ፤ የችሮታ ብሔራዊ መንግሥታት ፤ ምንም እንኳን መንግሥታቸው ብሔራዊ መንግሥት ቢባልም በታሪካዊ ኺደት የአልአደገ በመሆኑ ፤ የስም ብቻ ብሔራዊ መንግሥት በመሆኑ ፤ በእድገት ኺደት ማሕበረሰቡ ያልደረሰባቸውን ሥራ እንዲሰራ ፤ ጠንካራ ብሔራዊ የለውጥ ኃዋሪያ መንግሥት እንዲሆኑ የእሚገደዱ በመሆኑ ነው ።

አንድ ግዜ ግን ፤ ማሕበረሰብ በታሪክ ኺደት ይኹን በችሮታ ጠንካራ ብሔራዊ መንግሥትን አቋቁሞ ጭርሶ ፤ ሕዝብ በእዚኽ ብሔራዊ መንግሥት አስቻይነት የዘመናዊነት ጉዞውን በራሱ ተነሳሽነት መቀላቀል ከጀመረ በኋላ ፤ ይኽን ያስቻለው ጠንካራ ብሔራዊ መንግሥት ወደ ሕዝባዊነት ራሱን ከአልቀየረ ፤ ዘመን አለፍ (Anachronstic) ነው የእሚሆነው ።

ዲምኒሽንግ ማርጂናል ዩቲሊቲ (The Law of Diminishing Marginal Utility) ወይንም በአማርኛው “እየተመናመነ የእሚኼድ ተፈላጊነት” ፤ የእሚባለው የኢከነሚክስ መርህ እንደ እሚለው ፤ አንድ ፍላጎት ከረካ በኋላ ፤ ያንን ፍላጎት የእሚያረካው ሸቀጥ ተፈላጊነቱ እየቀነሰ ይኼዳል ።

ለምሳሌ ፦ ሰው ያለ ምግብ መኖር በአይችልም ፤ ሰው አንድ ግዜ የምግብ ፍላጎቱ ከረካ ፤ የቀረውን ጉልበቱን እና ኃብቱን ከምግብ ቀጥሎ ለአለ፟ው ፍላጎቱ ነው የእሚያውለው ። ስለ እዚኽ ፦ የምግብ ፍላጎትን በአጥጋቢ ኹኔታ ያረካ አንድ ኢከነሚ ፤ ምግብን ማትረፍረፍ ላይ ሰርቶ ፤ የምግብ ምርቱን በእጥፍ ቢጨምረው ፤ ያ ምግብ በውጭ ሐገር ከአልተሸጠ ፤ ከመደፋት እና መልሶ ማዳበሪያ ከመሆን የአለፈ ፋይዳ በተመረተበት ሐገር ውስጥ አይኖረውም ።

በእዚኽም መሠረት ሸቀጦች ፍላጎቱን የእሚያረኩበት ደረጃ ከደረሱ በኋላ ፤ ተፈላጊነታቸው እየቀነሰ ይኼዳል ።

በተመሳሳይም ፤ በአንዱ መንገድ ሕዝብ አንድ ግዜ ከመንደር ጥርቅምነት ወጥተው መንግሥት ወይንም ሐገር ከሆኑ በኋላ ፤ የጠንካራ መንግሥት ፍላጎታቸው ስለ እሚረካ ፤ ጠንካራ መንግሥት ማርጂናል ዩቲሊቲው ዜሮ ይሆናል ። ከእዚኽ በኋላ የእሚፈለገው መንግሥት ፤ ሕዝባዊ እና ጠንካራ መንግሥት እንጂ ፤ ጠንካራ ብቻ መንግሥት ተፈላጊነቱ አብቅቷል ።

ከእዚኽም የተነሳ ፤ አሉታዊ የፓርቲ ፖለቲካ በክፍል አምስቱ የታሪካችን ክፍል ጀምሮ አድክሞት የነበረው ጠንካራ መንግሥት በክፍል ስድስቱ የታሪካችን ክፍል መጨረሻ ላይ እንደገና ወደ ቀድሞው ጥንካሬው በመመለሱ ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የረጋ እና ጠንካራ መንግሥት ፍላጎቱ ስለተሟላለት ፤ አዲሱ እና ቀጣዩ ፖለቲካዊ አጀንዳው የነበረው ፤ አትንኩኝ ይል የነበረውን ብሔራዊ መንግሥት ፤ ጥንካሬውን ሳይለቅ ለሕዝብ ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ነፃነትን እንዲሰጠው የእሚያደርጉ የፖለቲካ ፓርቲ ስረዓት ወደ መፈለግ አድጎ ነበር ።

የኃይለ ሥላሴ ዘመን የፖለቲካ መኃንዲሶቻችን ግን ፤ ገሚስ የኢትዮጵያን ሕዝብ ታሪካዊ የእድገት ደረጃ ባለመረዳት ገሚስ ደግሞ በነበረባቸው ውስን የፖለቲካ ሳይንስ ግንዛቤ ተይዘው ፤ ሕዝባዊ መንግሥት እንኳን እንደ ኢትዮጵያ በአለ፟ ፤ ብዙ ያልተማረ በአለ፟በት ቀርቶ ፤ ብዙ የተማረ የሰው ኃይል በአለ፟ባቸው ሐገራት የረብሻ እና የደም መፋሰስ ምንጭ ነው ከእሚል ጨለምተኝነት እና ለውጥ በዝግታ ከአልሆነ አፍራሽ ይሆናል በእሚል ሰበብ ፤ አምባገነናዊ እና ለውጥን እንደ ሕዝቡ የመቀበል አቅም እና ፍላጎት ሰአይሆን ፤ በመንግሥት ኮታ በራሽን ለማከፋፈል የእሚፈልግ ወይንም ተራማጅ የነበረው መንግሥት ወደ አመለኛ ወግ አጥባቂነት የተለወጠበትን አካኼድ ተከተለ ።

ለውጥ ምንም እንኳን ፤ አብዮታዊ ከእሚሆን ይልቅ ዜጎች ሊቀበሉት በእሚችሉበት ፍጥነት እና አግባብ ሲደረግ የበለጠ ውጤታማ እና ቀጣይነት የእሚኖረው መሆኑ በአያጠያይቅም ፤ ይኽ አስተሳሰብ ግን ለይስሙላ የእሚደረጉ ለውጦችን ወይንም በዝግታ ስም ግለኝነትን ፣ ዕብሪትን ፣ ወዘተ ፤ መሸፈኛ መሆን አይችልም ማለት አይደለም ።

ለእዚኽ ማስረጃነት ፤ የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ፤ በመሬት ባለቤትነት ጉዳይ ፤ ለተነሱ የፖለቲካ ጥያቄዎች የሰጠው ምላሽ ዓይነተኛ ማሳያ ነው ። እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ አጥኚ ፤ ‘መሬት ላራሹ የእምትሹ ተዋጉለት አትሽሹ’ የእሚለው የተማሪዎች መፈክር ታዋቂ ከመሆኑ አምስት አመት ቀደም ብሎ ፤ የፊውዳል መሬት አስተዳደር ፤ ለኢትዮጵያ ገበሬዎች የድህነት ምንጭ ነው የእሚለው ጉዳይ ፤ በ1953 ዓ.ም. ታህሳስ ላይ ፤ በእነ ግራማሜ እና መንግሥቱ ነዋይ ተሞኩሮ የከሸፈውን መፈንቅለ መንግሥት የተሞከረበት አንድ ምክንያት እንደሆነ ያስቀምጣል ።

ይኽም ማለት ፤ የኃይለ ሥላሴን መንግሥት የጣለው አብዮት የመሬት ጥያቄን ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ ከመንቀሳቀሱ 11 ዓመታት በፊት ወይንም ከ1953 ዓ.ም ጀምሮ ፤ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሊህቃን ዘንድ የመሬት ባለቤትነት ስሪትን የመቀየር ፍላጎት አይሎ መፈንቅለ መንግሥትን ማድረጊያ ምክንያት እስኪሆን ድረስ መጥቶ ነበር ማለት ነው ።

እስከ ዛሬ ድረስ ፦ ‘የመሬት ባለቤትነት ስሪት መቀየር የኢትዮጵያን ገበሬ ኢከነሚ ትርጉም ባለው መልኩ ይቀይራል?’

የእሚለው ጥያቄ ፤ በተለያዩ የኢከነሚክስ ሳይንስ መርሕዎች ምክንያት ፤ አዎንታዊ መልስ በአይኖረውም ፤ በወቅቱ በኢትዮጵያ የነበረው የመሬት አስትዳደር ኢፍትኃዊነት ግን ፤ በግልፅ የእሚታይ እና መሻሻልን ግድ የእሚል እንደ ነበር መንግሥት ራሱ ቀድሞ መገንዘብ ቢሳነው እንኳን እያየለ የመጣው ሊሕቃዊ ግፊት ሊያሳየው የእሚገባው ጉዳይ ነበር ።

ምንም እንኳን ፤ መሬት እንደ ማንኛውም ኃብት ፥ ዜጎች የእሚገዙት ፣ የእሚሸጡት እና በውርስ የእሚያስተልፉት ኃብት መሆን አለበት የእሚለው ኹኔታ እስከ ዛሬ ደረስ በሐገራችን በአጥጋቢ ኹኔታ የተመለሰ የሕዝብ ጥያቄ በአይሆንም ፤ የኃይለሥላሴ መንግሥት ፤ መሬት የሌላቸው የሐገሪቱ ዜጎች ፤ በአብዛኛው ገበሬዎች ፤ ለዕለት ጉርስ የእርሻ ሥራ የእሚጠቀሙበትን መሬት በቀጥታ የማግኘት መብታቸው ይረጋገጥ የእሚለውን ጥያቄ ፤ በ1950ዎቹ መንግሥት እንዲመልሰው ከሕዝብ የቀረበለት ፤ ፍትኃዊ እና ሕዝባዊ ጥያቄ ነበር ።

ለእዚኽ እየገፋ ለመጣው ጥያቄ ፤ መልስ ለመስጠት ኃይለ ሥላሴ በ1959 ዓ.ም. የመሬት አስተዳደር የእሚባል የሚንስተር መሥሪያ ቤት አቋቁመው ፤ የፖሊሲ አማራጭ እንዲያቀርብ አደረጉ ። ምንም እንኳን ፤ ይኽ የሚንስተር መሥሪያ ቤት ብዙ መልካም የእሚባሉ የሕግ ማሻሻያዎች ቢያቀርብም ፤ በጣም ለዘብተኛ የእሚባለው ዓይነት ረቂቅ ሕግ እንኳን ፤ በወቅቱ ፓርላማ ተቀባይነት አግኝቶ ሊፀድቅ አልቻለም ነበር ። ይኽንም ኹኔታ ከላይ የጠቀስኩት ኢትዮጵያዊ አጥኚ እንዲኽ አስቀምጦታል ፦

“የሚንስተር መሥሪያ ቤቱም ፤ የሊዝ ባለ ይዞታዎችን ወደ ሙሉ ባለቤትነት በመቀየር የግል መሬት ይዞታዎችን መፍጠር የእሚያስችሉ ፣ ትልቁ የግል መሬት ስፋት ጣሪያ የእሚወስን ፣ የሰፈራ ፕሮግራሞች ጥናት እና ትንንሽ እና የተበታተኑ እርሻዎችን በአንድ ማድረግ የእሚያስችሉ የረዥም ግዜ እቅድ አቀረበ ። ከእነዚኽ ውስጥ ግን ፤ ለውሳኔ ፓርላማ ላይ መቅረብ የቻለው ፤ በጣም ለዘብተኛ የሆነው የጭሰኞች አስተዳደር ጉዳዮችን የእሚመለከተው ብቻ ነበር ፤ እርሱም ምንም እንኳን በጣም የተለሳለሰ ማሻሻያ ቢሆንም ብዙ ግዜ ውድቅ ተደረገ ። ኹሉም ከ1958 ዓ.ም. እስከ 1966 ዓ.ም. በተከታታይ ሚንስትር መሥሪያቤቱን የመሩት ሚንስትሮች (ብላታ ገ/ፃዲቅ ፣ ፊታውራሪ አባ ገብሬ ፣ ሙላቱ ዳባባ እና በላይ አባይ) ፤ አንዳቸውም የማሻሻያ ሕግጋቱን በስኬት ማስፈፀም አልቻሉም ነበር። “

“The ministry also prepared long term programs for the creation of private landowners by converting leaseholders into full owners, the establishment of ownership ceilings, the study of settlement projects and consolidation of fragmented holding. However, only the reform of tenancy regulation ever reached parliament and it, though mild enough, was rejected, any times. All the ministers (Blata G/Tsadiq, Fitawrari Ababa Gebre, Mulatu Dababa and Belay Abay), who successively took the ministerial post from 1966 to 1974, were not successful in implementing any of the reform legislation. [121]“

ይኽ ፤ የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ወይንም የንጉሡ ፤ የመሬት ስሪትን ለማሻሻል ይኽን ጉዳይ ተከታትሎ የእሚያስፈፅም የሚንስተር መሥሪያ ቤት እስከ ማቋቋም የእሚደርስ ፤ ሕዝብ አድማጭነት ፤ የአስመሰል ፖለቲካዊ ድራማ እንዲሰራ እና በውጤቱም ለራሱም ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ውድቀት የሆነው ፤ መንግሥታቸው ከተከተለው የተሳሳተ ፖለቲካዊ መዋቅር የተነሳ መሆኑን ዘርዘር አድርገን እንመልከት ።

አንደኛው ፤ ኃይለ ሥላሴ በፓርላማውም ሆነ በሴኔት ላይ በአላቸው ስልጣን ፤ የፓርላማውን ውሳኔ የእሚቆጣጠሩት እርሳቸው እንጂ ፓርላማው እንዳልሆነ ፤ የኃይለ ሥላሴ ፓርላማ እና ሴኔት ከተዋቀረበት ከመጀመሪያውም ሆነ ከተሻሻለው የኃይለ ሥላሴ ሕገመንግሥት በመነሳት ማየት እንችላለን ። ይኽም ብቻ ሰአይሆን ፤ የአስፈፃሚው አካል የሆነው የመሬት አስተዳደር ሚንስትር መሥሪያ ቤቱ ቀጥታ ለርሳቸው ሪፖርት የእሚያደርግ በመሆኑ ፤ የመሬት አስተዳደር መሥሪያ ቤቱ ከብዙ ጥናት በኋላ ያዘጋጃቸውን ሕግጋት ፤ ከኃይለ ሥላሴ ቀጥታ እውቅና ውጭ ለፓርላማ ሳያቀርብ ቆልፎ እንደ እማያስቀምጣቸው ግልፅ ነው ።

ስለ እዚኽ ፦ ፓርላማው እና የሚንስትር መሥሪያቤቶቹ ቢኖሩም ፤ እነ እዚኽ ሕዝባዊ ተቋማት ግን በቀጥታ በንጉሡ ቁጥጥር ስር ስለሆኑ ፤ የአሉ፟ት ለይስሙላ እንጂ ፤ የታቀዱበትን ዓላማ እንዲፈፅሙ እንደ አልሆነ በግልፅ ይታያል ። ያም በመሆኑ ፤ በጣም ለስላሳ የእሚባሉት የመሬት አስተዳደር ማሻሻያ ሕግጋት እንኳን ፤ መፅደቅ የአልቻሉት ፤ ለውጥ የእማይወደው ባላባት እምቢ ስላለ ወይንም ደግሞ የእርሻ መሬት ጥያቄው ተገቢ እና ሕዝባዊ ጥያቄ ሰአይሆን ሕዝብን በጭካኔ ለማሰልጠን የእሚደረግ አካኼድ የነበረ ስለ ሆነ አልነበረም ።

ይልቁንም በተሳሳተ የታሪክ አረዳድ እና ፖለቲካዊ ትንታኔ ላይ የተመሠረተው መንግሥታዊ አወቃቀር ፤ ስረዓቱን በአደርባዮች ሞልቶ እና በአንድ ሰው መልካም ፈቃድ ስር አስሮ ፤ በዝግታ ስም መንግሥትን የእርጅና እንቅልፍ እንዲያንቀላፋ የእሚፈቅድለት ከወቅቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማሕበራዊ እና ፖለቲካዊ እድገት ጋር የእማይኼድ ፖለቲካዊ መዋቅር በመመረጡ ነው ።

ይኽ አወቃቀር ፤ ለከት ከአጣ ምክንያተቢስ ልግመኝነት እና እምቢተኝነት ውጭ ፤ እጅግ ብዙ ያልታረሰ እና ሊታረስ የእሚችል መሬት ባላት እንደ ኢትዮጵያ ባለች ሐገር ውስጥ እና አንዳንድ ጥናቶች ለእራሳቸው የእሚያርሱት መሬት የሌላቸው ፤ ስለ እዚኽም ጭሰኞች ሆነው በባላባቶች እርሻ ላይ ገባር ሆነው የእሚኖሩት ገበሬዎች ፤ ከመላው የኢትዮጵያ ገበሬ ሩቡን ብቻ እንደ ነበሩ በእሚያሳዩበት ፤ ማለትም ፦ መሬት አልባው ገበሬው በአንጻሩ ጥቂት በመሆኑ ፤ መሬት የለሽ ዜጎች ለእርሻ የእሚጠቀሙበትን መሬት እንዲያገኙ መፍቀድ ፤ የወቅቱን መንግሥት እና ባለመዋሎች በወሳኝ መልኩ ሊጎዳ የእሚችልበት ምንም ዓይነት ኹኔታ በአልነበረበት ኹኔታ ፤ መንግሥት ይኽን ለእራሱም ሆነ ለሐገር ጥቅም የእሚበጀውን አካኼድ ችላ እንዲል አደረገው ።

ይኽን እና መሰል ኹኔታዎች ስናይ ፤ የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ፤ ሕዝባዊ ፣ ተራማጅ እና ዘመናዊ መንግሥትነት መጀመሪያ ላይ እንጂ አንድ ግዜ በስልጣን ላይ ከተደላደለ እና የለውጡ ስፋት እና ጥልቀት ፤ የመንግሥቱን አወቃቀር ከነበረበት ሕገመንግሥታዊ አምባገነናዊ ዘውድ ስረዓት ወደ ሕዝባዊ የዘውድ ስረዓት እንዲቀየር ግድ ይለው ሲጀምር ፤ በተሳሳተው ታሪካዊው ግምገማ እና በውስን የፖለቲካ ሳይንስ ግንዛቤው በተመረጠለት መዋቅር ምክንያት ፤ የለውጥ ኃዋሪያ ሆኖ የነበረው መንግሥት ፤ ወደ ወግ አጥባቂነት ተቀይሮ ራሱን የአብዮተኞች ሕጋዊ ኢላማ አድርጎት ነበር ።

ምንም እንኳን ይኽ ዝግመታዊ ወግ አጥባቂነት ከእላይ በጅሮንድ ተክለ ኃዋሪያት የአሉትን አጣቅሰን ለማየት እንደ ሞከርነው ፤ ከአስተሳሰብ አድማስ ውስንነት ወይንስ ከጥቂቶች የስልጣን ግለኝነት የመጣ መሆኑን በእርግጠኝነት ማስቀመጥ በአይቻልም ፤ ይኽን መሰሉ ፤ ትርፈቢስ ወግ አጥባቂነት ፤ የኃይለ ሥላሴ መንግሥት በአብዮት እንዲወድቅ የተመቻቸ ኹኔታን ፈጥሯል ።

ሆኖም ፤ ይኽ የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ሲያድበሰብሰው የነበረው የመሬት አጀንዳ መንግሥታቸውን ለጣለው አብዮት ዋና ማቀጣጠያ በመሆን ቢያገለግልም እና እኔም የኃይለ ስልሴን መንግሥት የፀረ-ሕዝባዊ መንግሥት ዝንባሌ ለማሳየት ብጠቀምበትም ፤ ቅሉ የኃይለ ሥላሴን መንግሥት የአብዮት እራት እንዲሆን የአደረገውን እና ደርግን ለስልጣን ስኬት ያበቃው ዋናው እና ብቸኛው ምክንያት ነበር ማለት ግን አይቻልም ።

ይልቁንም የኃይለ ሥላሴን መንግሥት እያደር ወግ አጥባቂነት የፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም የመንግሥታቸውን ውድቀት ያፈጠነ ሌላ ትልቅ ምክንያት አለ ። ይኽንን ሌላውን ትልቍን ምክንያት ለመረዳት ፤ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ1945 እስከ 1991 ዓ.ም የቆየውን ፤ የዓለም ዓቀፍ ፖለቲካ አካል የሆነውን ቀዝቃዛውን ጦርነት መረዳት ግድ ይላል ።

በ16ኛው ምዕተ ዓመት ፥ በአውሮፓ ህዳሴ ማግስት ፤ በብቸኝነት ተቀባይነት የአለው እና ውጤታማ የሆነው መንግሥት ሕዝባዊ መንግሥት ነው ከተባለ አንስቶ ፤ የሕዝባዊ መንግሥት አስተሳሰብ ትርጉም በአለው መልኩ የዓለም ዓቀፍ ፖለቲካ አዲሱ መገለጫ እስኪሆን ወደ ሦሥት መቶ ዓመታት ፈጅቶ ፤ በ20ኛው ምዕተ ዓመት ላይ ነው ወደ ፊት የመጣው ።

የሕዝባዊ መንግሥት አስተሳሰብ በእዚኽ መልኩ በዓለም ላይ ከጫፍ እስከ ጫፍ በተቀባይነት ከናኘ በኋላ ፤ ይኽ ሕዝባዊ መንግሥት ካፒታሊስት ወይንስ ሶሻሊስት ነው መሆን የአለበት የእሚለው ጥያቄ ዓለምን ለኹለት ከፍሎዋት ነበር ። በተለይ እ.አ.አ 1918 ዓ.ም. የሌኒን አብዮት በዓለም ላይ በግዛት ስፏቷ ተወዳዳሪ የሌላትን ራሺያን ከተቆጣጠረ በኋላ ፤ ዓለም በካፒታሊስት እና በሶሻሊስት ጎራ መከፈል ጀምራ ነበር ።

በሶሻሊስት አብዮት ፤ የእነ ሌኒን ቦልሼቪክ በራሻ የፖለቲካ ስልጣኑን እ.አ.አ. በ1918 ዓ.ም. ከያዘ በኋላ ፤ አደጋ ሊሆኑበት የእሚችሉትን ካፒታሊስቲቹ ፤ አሜሪካ እና የምዕራብ አውሮፓ ሐገራት ፤ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ሳቢያ ከገቡበት ኢከነሚያዊ እና ማሕበራዊ ቀውስ ማገገም ላይ የነበሩ ስለ ነበር ፤ የራሻው ከምኒስት ፓርቲ ፤ ከእነ ብዙ ድካሙ እና ጥፋቱም ጋር ቢሆን ፤ ራሱን አጠናክሮ እና አሻሽሎ ሶሻሊዝምን አስተሳሰብ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የበላይነት ለማስያዝ እየሰራ ነበር ።

ይኽ በእንዲኽ እያለ ፤ የአንደኛው የዓለም ጦርነት በአበቃ እና የእነ ሌኒን አብዮት የራሻ ከምኒስት ፓርቲን ወደ ስልጣን በአመጣ በ21ኛው ዓመት ፤ ሒትለር ኹለተኛውን የዓለም ጦርነት በማስጀመሩ ፤ ሒትለርን ለማሸነፍ የተቋቋመው ግንባር ውስጥ ከምኒስት ራሻ አንድ ወሳኝ ኃይል ሆና በመሳተፏ ፤ ከጦርነቱ መጠናቀቅ በኋላ ፤ በአውሮፓ የብረት መጋረጃ የእሚባለው እና ምሥራቅ አውሮፓን ከምዕራብ አውሮፓ የእሚለየው የፖለቲካ ድንበር ተፈጥሮ ፤ ዓለም በአሜሪካ እና በራሻ በእሚመሩት ፤ የካፒታሊስት እና የሶሻሊስት ጎራ ተከፍላ ነበር ።

ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ፦ እነ እዚኽ ጎራዎች ፤ የታጠቁት የጦር መሳሪያ ፤ እርስ በእርስ ቀጥታ ቢጋጩ ሊያደርስባቸው የእሚችለውን ዘርፈ ብዙ ኪሳራ ፤ ከመቶ ሚልዮን በላይ ሰዎች ህይወት ከአሰከፈላቸው ከአንደኛው እና ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት በደንብ አድርገው ስለተረዱት ፤ የተከተሉት አቅጣጫ ፤ ጦርነታቸውን በቀጥታ ወታደራዊ ፍልሚያ ከማድረግ ይልቅ ፦ በኢከነሚ ፣ በዲፕሎማሲ እና አንዳንዴም የነፍጥ ጦርነትን በሌሎች ሐገር ውስጥ የማድረግ አቅጣጫ ወይንም በተለምዶ ቀዝቃዝው ጦርነት የእሚባለውን አቅጣጫ ነበር ።

ይኽ በካፒታሊስቶች እና በሶሻሊስቶች መካከል የተጀመረው ፍጥጫ ዋና ግቡም ፤ የእኔ የማሕበረ ኢከነሚ ርዕዮት ከአንተ ርዕዮት በተሻለ ኹኔታ እና ፍጥነት ፤ ኢከነሚያዊ እድገት እና ፖለቲካዊ ፍትኃዊነት ያረጋግጣል የእሚል በመሆኑ ፤ በቻሉት መልኩ ኹሉ ሐገራትን የእነርሱ ሳተላይት ወይንም ተንጠልጣይ በማድረግ ፤ የሟዴላቸው ሰርቶ ማሳያ የማድረግ ፉክክር አንዱ የተልዕኮ ጦርነት የእሚያድርጉበት መንገድ ነበር ።

ኋላ ቀር በእሚባሉት ሐገራት ውስጥ ፤ የአሉ፟ትን ኋላ ቀር መንግሥታት በራሳቸው መንገድ በመቆጣጠር ፤ መቆጣጠር ሲሳናቸው ደግሞ ነባራዊውን መንግሥት ጥለው መሰላቸውን በማንገስ ፤ በእነዚኽ ድኃ ወይንም ኋላ ቀር ሐገራት ውስጥ የእሚገኙትን መንግሥታት የእነዚኽን የኃያላኑን የፖለቲካ እና የኢከነሚ ፖሊሲ የእሚተገብሩ በማድረግ ፤ እነ እዚኽን ድኃ እና ኋላ ቀር ሐገራት የማሕበረ ኢከነሚ የሟዴሎቻቸው ሰርቶ ማሳያ በማድረግ ፤ ከእዚኽ በእሚገኘው ስኬት ፤ ዲፕሎማሲያዊ እና ሌሎች ፈርጀ ብዙ ጥቅሞች ማግኝት ግባቸው ነበር ።

ስለ እዚኽ ፦ በቀዝቃዛው ጦርነት ፤ እነ እዚኽ የዓለም ኃያላን ፤ በዓለም ስልታዊ ጥቅም አላቸው የእሚሉዋቸውን ሐገራት እየመረጡ ፤ መንግሥታቸውን በመቆጣጠር ወይንም ነባራዊውን መንግሥት በእሚመስላቸው መንግሥት በመተካት የትግል ሜዳ ያደርጓቸዋል ።

የኃይለ ሥላሴም መንግሥት ፤ በብዙ ፖለቲካዊ እና ታሪካዊ ምክንያቶች ፤ ከአሜሪካው ካፒታሊዝም ጋር አብሮ የነበረ በመሆኑ ፤ ኢትዮጵያ የአላ፟ትን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ የተረዳው የራሺያው ከምኒዝም ፤ በእዚኹ አግባብ ኢትዮጵያን ከአሜሪካ ጎራ አውጥቶ ወደ ራሱ ጎራ ለመክተት ተንቀሳቅሷል ።

ይኽም የራሻው ከምኒስት ፓርቲ እንቅስቃሴ ነው ፤ የኃይለ ሥላሴን መንግሥት የእሚቃወሙትን የተማሪዎች አብዮት ያቀጣጠለው እና ደርግንም ወደ ስልጣን ለመምጣት ያበቃው ትልቁ እና ዋነኛው ምክንያት ።

ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት አንስቶ በአሜሪካ በእሚመራው የካፒታሊስቱ ጎራ ፤ ከከምኒስቶቹ እና ከኃይማኖት አክራሪዎች ጎራ በተቃራኒ ፤ ውስጥ የነበረው የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ፤ በሐገር ውስጥ እና ከዓለም ዓቀፍ ግንኙነት አንጻር በውጭ ጉንኙነት መስክ የተከተላቸው የተሳሳቱ ፖሊሲዎች ፤ የአሜሪካን እና የአጋሮቿን እገዛ እንዲያጣ ስለ አደረገው ወይንም አሜሪካ እና አጋሮቿ ገሸሽ በማለታቸው ፤ የራሻው ከምኒስት ፓርቲ ይኽን በቀድሞ ወዳጆቹ የተተወ እና በመሠረታዊ ባሕሪው ለእርሱ ርዕዮታዊ ጠላቱ የሆነውን የዘውድ መንግሥት ለመጣል በኢትዮጲያ ፖለቲካ ውስጥ የእሚሳተፍበትን ምቹ ኹኔታ ፈጥሮለታል።

በአሜሪካ የእሚመራው የምዕራቡ ዓለም ፤ በአስገዳጅ ኹኔታ ከአልታጠፈ በስተቀር ፤ በዋናነት በዓለም ዓቀፍ ግንኙነት መስክ የእሚከተለው የውጭ ግንኙነት ፓሊሲው ወይንም መርኹ ፤ ሐገራቱ ወደ ዴሞክርሲያዊ ስረዓት ለመግባት በእሚያደርጉት ጥረት ፥ ዴሞክራሲያዊ ሆነውም ከሆነ ደግሞ ይኽን ዴሞክራሲያዊነታቸውን በእሚያከብሩበት ልክ ይወሰናል።

ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ማግስት ፤ ጸረ ቀኝ ግዛት እና የብሔራዊ ሐገራት ሉዓላዊነትን ማክበር ቀዳሚ የውጭ ጉዳይ መርኹ የነበረው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ፤ ከጣሊያን ሽንፈት በኋላ የቀኝ ግዛት አባዜ ያልለቀቃቸው የእንግሊዝ የጦር ጀነራሎች ፤ በአዲስ አበባ ፣ በኦጋዴን እና በኤርትራ ውስጥ እጃቸውን በማስገባት ኢትዮጲያ ላይ የእሚያሳድሩትን የኢፍትኃዊ ተጽዕኖ እጅ እንዲያወጡ አሜሪካ በተጫወተችው ሚና ፤ የኢትዮጵያ ግዛታዊ ነጽነት እና አንድነት እንዲጠበቅ እንዲኹም በጣሊያን ወደ 70 ዓመት አከባቢ በጉልበት ቀኝ ተይዞ የነበረው የኢትዮጲያ ግዛት (ኤርትራ) ወደ ኢትዮጲያ እንዲመለስ ስለ አደረገ ፤ ኹኔታው ፤ የቀኝ ግዛት ኢፍትኃዊ ሰለባ የነበረውን የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ፤ የአሜሪካ ካምፕ ውስጥ አስገባው።

የአሜሪካ መንግሥት ጸረ ቀኝ ግዛት እና የብሔራዊ ሐገራት ሉዓላዊነትን የእሚያከብር ዓለም ዓቀፋዊ ስረዓት ደጋፊ ቢሆንም ፤ ከቀኝ ግዛት ተላቀው በራሳቸው ብሔራዊ ሐገራት ውስጥ የእሚመሠረቱ መንግሥታት አምባገነናዊ መንግሥታት ከእሚሆኑ ይልቅ ዴሞክራሲያዊ መንግሥታት እንዲሆኑ ይፈልጋል።

ይኽም ማለት ፤ ሐገራት በቀጣይነት ከአሜሪካ ጋር የእሚኖራቸው ግንኙነት ፤ በእየ ሐገራቱ የአለው መንግሥት ለዴሞክራሲያዊ ስረዓት ግንባታ በአለው አቋም ላይ ይወሰናል ማለት ነው።

የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ግን ጸረ ቀኝ ግዛት የሆነው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ፤ ቢያንስ ከእነ አጼ አምደ ጽዮን ጀምሮ የኢትዮጲያ ስጋት ሆኖ የቆየውን የወታደራዊ ኢምፔሪያሊዝም ስጋት ሲያነሳለት ፤ ኹኔታው ኢትዮጲያ በብዙ መቶ ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ግዜ ሕዝባዊ መንግሥት እንድትገነባ የቀረባላት አመቺ ታሪካዊ የዓለም ዓቀፋዊ ምህዳር መሆኑን ከመረዳት ይልቅ ፤ የይስሙላ ለውጥ የማድረግ አካኼዱ የአመጣለት ውጤት አድርጎ በመውሰድ ፤ ተራማጅ መሆን ሳይሆን የመምሰል አካኼዱን ገፋበት ።

እንደ እሚታወቀው ፤ ከእስልምና ውቂያኖስ በስተደቡብ ምዕራብ የእምትገኘው የክርስቲያን ደሴት (ኢትዮጵያ) ፤ በእምትኖርበት የመካከለኛው ምሥራቅ አጎራባች በሆነው የአፍሪካ ቀንድ ፤ ቢያንስ ከአምደ ጽዮን ጀምሮ ፤ በሐገር ውስጥ ኖረው ጅኃድን በእሚመኙ ፣ በቱርክ ቅጥረኞች ፣ በቱርክ በራሷ ፤ ደሕረ ቱርክ ደግሞ በጀስዊት ቄሶች ፣ በጣሊያን ፣ በፈረንሳይ እና መጨረሻ ላይ በእንግሊዝ ፤ ለአለፉት 700 ዓመታት በተከታታይ በእነ እዚኽ ሐገራት እና በጦር መሪዎቻቸው ፤ በእጅ አዙርም ይኹን በቀጥታ የመወረር አደጋ የተጋረጠባት ሐገር ነበረች።

ይኽ ጸረ ኢትዮጲያ የሆነ ዓለም ዓቀፍ ምህዳር የተቀየረው ፤ ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ፤ አመለኛ የሆኑት ቀኝ ገዢ መንግሥታት ፦ እንግሊዝ ፣ ፈረንሳይ ፣ ጣሊያን ፣ ጀርመን ፣ ወዘተ በከፍተኛ ደረጃ ተዳክመው ፤ አሜሪካ የዓለም ልዕለ ኃያል መሆኗ ሲረጋገጥ ፤ የተባበሩት መንግሥታት ፤ በሰብዓዊነት መርህ እየተመራ ፤ ጸረ ቀኝ ግዛት እና ሉዓላዊ ብሔራዊ ሐገራት የእሚኖሩበትን ኹኔታ እንዲያስችል ሆኖ እንዲዋቀር እና እንዲሰራ በማድረጓ ነው።

ይኽም ኹኔታ ፤ በእዚኽ ዘመን ዋነኛ የኢትዮጲያ የቅኝ ግዛት ስጋት የነበረው የጣሊያን መንግሥት ፤ በኹለተኛው የዓለም ጦርነት በመሸነፉ ፦

  • የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ፤ በ1928ቱ የጣሊያን ወረራ ተሰዶ በእንግሊዝ ከእሚኖርበት ፤ ከጣሊያን ሽንፈት ማግስት ወደ ሐገሩ እንዲገባ
  • ጣሊያንን ከኢትዮጲያ ግዛቶች በማስወጣት ረገድ ትልቅ እገዛ የአደረገችው እንግሊዝ አንድ አንድ የቀኝ ግዛት አባዜ የአልለቀቃቸው ጀነራሎች ኢትዮጲያን በሞግዚትነት ለማስተዳደር እና እርሱም ሳይሳካ ሲቀር ኦጋዴንን ከኢትዮጲያ ቆርሶ በመውሰድ አዲስ ሐገር ለመፍጠር የነበራቸውን ፍላጎት በሕገወጥነት ፈርጆ በመከልከል እና የኢትዮጲያ ግዛታዊ አንድነት እና ነጻነት ወይንም ሉዓላዊነት በሕግ በማስከበር
  • ከ1928 ወረራ በፊት ለ50 ዓመታት ጣሊያን ኤርትራን ከታሪካዊ የኢትዮጲያ ግዛትነት ቆርሳ በቀኝ ግዛትነት ይዛ ከቆየችበት እና ከጣሊያንም መሸነፍ በኋላ እንግሊዝ ኤርትራን በፕሮክቶሬትነት ለ10 ዓመት ከያዘችበት ኹኔታ ወደ ታሪካዊ ቤቷ ኢትዮጲያ እንድትመለስ በማድረግ

ኢትዮጲያ ለብዙ መቶ ዓመታ ከአጠላባት ወታደራዊ ኢምፔሪያሊዝም ስጋት እንድትድን የአደረገ ነበር።

ይኽም ማለት ፤ የኢሰብአዊው የቀኝ ግዛት ሰለባ የሆነቸው ኢትዮጲያ ፤ ጸረ ቀኝ ግዛት እና የሉዓላዊነት ደጋፊ የሆነው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ፤ አሜሪካ የፈጠረቸው ዓለም ዓቀፋዊ ስረዓት ለኢትዮጲያ የእሚመች እና አሜሪካን ራሷን ውነኛ የኢትዮጲያ ወዳጅ የአደረጋት ነበር።

የኃይለ ሥላሴው መንግሥት ግን ይኽን ኹኔታ ፤ የኢትዮጲያ ሕዝብ ሕዝባዊ መንግሥት እንዲገነባ ታሪክ የሰጠው እድል እና ኃላፊነት እንደ ሆነ ከመረዳት ይልቅ ፤ የእሚከተለው የወግ አጥባቂ የመንግሥት አስተዳደር ስልት የአስመዘገበለት የዲፕሎማሲ ውጤት አድርጎ በመመልከት ፤ ሕዝባዊ መንግሥትን ከመገንባት ይልቅ ፤ ከላይ በዘረዝርነው በይስሙላ ለውጡ ገፋበት ።

አሜሪካ ጸረ ቀኝ ግዛት እና የሐገራት ሉዓላዊነት አክባሪ ብትሆንም የወግ አጥባቂ ወይንም የይስሙላ ለውጥ አራማጅ መንግሥት ደጋፊ በአለመሆኗ (በተለያየ አስገዳጅ ምክንያት ይኽ የእማይሆንበት ግዜ መኖሩ እንደ ተጠበቀ ሆኖ) ፤ የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ወሎ እያደረ ጥሬ ሲሆን ፤ ከአሜሪካ ጋር የአለው ግንኙነት እየሻከረ መጣ።

በወቅቱ በኢትዮጲያ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አማካሪ እንደ ነበሩት አሜሪካዊው ጆን ስፔንሰር (John H. Spencer) ፤ ከጣሊያን ወረራ በኋላ ፤ ለኃይለ ሥላሴ መንግሥት ማንሰራራት እና መጠናከር ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርግ የነበረው የአሜሪካው እገዛ ለመንጠፉ አንዱ ምክንያት ፦ የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ከግዜ ወደ ግዜ ወግ አጥባቂ በመሆኑ እና አዲስንም ለውጥ ማምጣት በእማይችልበት ኹኔታ ፤ ሕዝባዊ ድጋፉን እየአጣ ስለ መጣ ፤ በእዚኽ መልኩ በሕዝቡ እየተጠላ ከአለ፟ መንግሥት ጋር ተባባሪ ሆኖ ላለመገኘት ከመፈለግ ነው ይላሉ [122] ።

የኢትዮጲያ ሕዝብ የአልተማረ ስለ ሆነ ፤ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት አይገባውም በእሚል ጨለምተኝነት ፤ ዘመን አለፍ የዘውድ ስረዓት በማራመድ እና ታማኝ የመንግሥት ባለሙዋሎችን በማፍራት ስልጣኑን ለማስጠበቅ የፈለገው የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ፤ ዴሞክራሲያዊ ስረዓት ሳይገነባ እዚኽም እዛም ብልጭ በእሚሉ የልማት ሥራዎች ሕዝብ አማልዬ እይዛለኹ የእሚለው አቋሙ ፤ ቀላል የእማይባል የኢከነሚ ቀውስ ውስጥ ከተተው።

ተራማጅ ነኝ እያለ ፤ ከአሜሪካ እና አጋሮቿ ፦ ለይስሙላ የልማት ፕሮጀክቶቹ ፣ ታማኝ ባለምዋሎች ለመግዛት ፣ የሐገር መከላከያ እና ጠንካራ የደህንነት መዋቅር ለመገንባት የእሚያገኘው የገንዘብ እርዳታ ፤ በወግ አጥባቂነቱ ምክንያት እየነጠፈበት ሲመጣ ፤ ይኽም ደሞዝ እንኳን በአግባቡ መክፈል የእሚችልበትን አቅም ሲነሳው ፤ ወደ ትክክለኛው የለውጥ ጎዳና ከመግባት ይልቅ ፤ የዴሞክራሲያዊ ስረዓት ገንባ ፣ የዜጎችህን ሰብዓዊ መብት አክብር ፣ ወዘተ ፤ ሰአይሉ የገንዘብ እርዳታ ይአደርጉልኛል ብሎ የአሰባቸው የአረብ ሐገራት ጋራ ለማበር ሲል ፤ ከእሥራኤል ጋር የአለውን የውጭ ግንኙነት አቋረጠ።

በእዚኽም ፤ የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ፤ በወግ አጥባቂነት ቆሞ የቀረ የጃጀ መንግሥት ብቻ ሰአይሆን ፤ ቀጥታ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጋር ተቃራኒ በመሆን ፤ የአሜሪካ ተጻራሪ ከሆኑ ኃይላት ጋር በማበሩ ፤ አሜሪካ ከእዚኽ መንግሥት ጋር የእሚኖራትን ግንኙነት በቋጣይነት አበላሸው።

በእዚኽ መልኩ ፤ በኢትዮጲያ ታሪክ ታይቶ በእማይታወቅ ኹኔታ አመቺ ዓለም ዓቀፋዊ ምህዳር ቀርቦለት ሳለ ፤ በመኃይምነት እና በወግ አጥባቂነት ፤ የቀረበለትን እድል መጠቀም እና ታሪካዊ ኃላፊነቱን መወጣት የአልቻለው የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ፤ ራሱን ለከምኒዝም አብዮት የተመቸ የሳት ራት አድርጎ አቀረበ።

የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ፤ ምንም እንኳን በለውጥ እና በተኃድሶ ጎዳና ጉዞውን ቢጀምርም ፤ ለውጡ ወደ ሐገር ውስጥ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ከማስገባት ያልዘለለ እና በፖለቲካው ረገድ የነበረው ለውጥ የይስሙላ በመሆኑ ፤ ኹኔታው ኼዶ ኼዶ ፤ እውነተኛውን ዘመኑን የፈቀደውን እና የኢትዮጵያ ሕዝብ የፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነቱ እና አቅሙ ሲጠይቀው ፤ ተራመጅ እና የለውጥ ፈላጊ ነኝ ሲል የነበረው መንግሥት ፤ በከፍተኛ የፖሊሲ ስሕተት በድንገት ከወግ አጣባቂዎች እና ከኃይማኖታዊ አምባገነኖች ጋር ለማበር ሲመርጥ ተገኘ።

ከእዚያኽም ፤ ድንገት ሻለቃ እና ከእዚያኽ በታች የስልጣን እርከን ላይ የእሚገኙ 108 የንግሡ የወታደር መኮንኖች ራሳቸውን ደርግ ብለው ሰይመው እና የደህንነት ተቋሙን ሙሉ ትብብር አግኝተው ፤ የተማሪዎችን የለውጥ እንቅስቃሴ ሰበብ አድርገው ፤ የመንግሥት ግልበጣ በማካኼድ ንጉሣዊ ስረዓቱን ሽረው ፤ በሶሻሊስት ኢትዮጵያ ፤ ራሳቸውን ግዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር አድርገው ሐገር መምራት ጀመሩ ።

ስለ እዚኽ ፦ አብዮቱን አሳቦ ወደ ስልጣን የመጣው ደርግ ፤ የመንግሥት ግልበጣውን ማካኼድ እና የመንግሥትን ስልጣን መያዝ የቻለው ፤ በራሱ ወይንም በሐገራዊ አቅሙ ፤ በየትኛውም መስክ ከኃይለ ሥላሴ መንግሥት የተሻለ ስለ ነበረ ሰአይሆን ፤ ለእዚኽ ያበቃው ረጅሙ የዓለም ዓቀፍ ከምኒዝም ፤ አብሮት ስለነበረ እና ወግ አጥባቂው የዘድ ስረዓትም ከስትራቲጅካዊ የውጭ ወዳጆቹ በእሚከተለው ወግ አጥባቂ ፖሊሲ ምክንያት ተነጥሎ የነበረ መሆኑን ማስመር ተገቢ ነው ።

ምክንያቱም ፦ የደርግ መንግሥት ፤ ይዟቸው በመጣቸው የፖለቲካ መሪዎች ፣ በአቋቋመው መንግሥት ብቃት ወይንም በአስመዘገባቸው ውጤቶች ቢመዘን ፤ ውጤቱ የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ግማሽ እንኳን አይደርስም ።

የኃይለ ሥላሴን መንግሥት ብዙ ያስወቀሰውን የመሬት ጉዳይ ብንወስድ እንኳን ፤ ደርግ ገበሬውን በሕብረት ሥራ ማሕበር ጠርንፎ ፤ መሬት በነጻ ተሰጥቶኃል እና ምርትህን ከገበያ ዋጋ በታች በርካሽ ሽጥ ፤ ለእዚኽ እና ለእዚያኽ ማሕበር ገንዘብ አዋጣ ፣ ወዘተ ፤ እያለ እፍኝ በእምታህል እርሻው ላይ አርሶ ከእሚያገኛት ገቢ ላይ እየቆነጣጠረ ፤ እንደ አንዳንዶች እምነት ከፊውዳል በአላባቶቹ በላይ እያስከፈለው ፤ ገበሬውን በአለበት አስረገጠው እንጂ ፤ ለገበሬውም ሆነ ለሐገሪቱ የተሻለ ምርታማነት የእሚያመጣ አካኼድ አልተከተለም።

የደርግ የመሬት አዋጅ በፊውዳል ወይንም በባላባቶች ስር የአለውን መሬት በመውረስ የባላባታዊ ስረዓት የነበረውን አሉታዊ ማሕበራዊ እሴት አስወግዷል ተብሎ ሊወደስ ቢችልም ፤ ይኽ ውጤት ደርግ በተከተለው የተሳሳተ የመሬት ፖሊሲ ምክንያት የተከሰተውን ሐገራዊ የግብርና ምርት ማሽቆልቆል እና ሌሎች አላስፈላጊ ማሕበራዊ ቅራኔዎች እና ቁርሾ ሳያመጣ ፤ የገበሬዎች የመሬት በአለቤትነት መብት ሲረጋገጥ አብሮ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሊወገድ የእሚችል በመሆኑ ፤ ይኼ እንደ ስኬት ሰአይሆን ፤ ለትክክለኛ ጥያቄ የተሰጠ የተሳሳተ ምላሽ ተደርጎ ነው መወሰድ የአለበት ።

የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ፤ በዘመን አለፍነቱ እና በወግ አጣባቂነቱ ፤ ሐገራዊ ሽግግሩን አላግባብ ከማዘግየት አልፎ ፤ በዘመን አለፍነቱ እና በወግ አጥባቂነቱ የአጣውን መልካም ወዳጅነት የእሚሰጠውን የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት ሲል ፤ ከኢትዮጲያ ስትራቴጂካዊ ጥቅም እና ከዓለም ሰላም የእሚቃረን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ወደ መከተል የገባ ሰነፍ መንግሥት ሆኖ ስለ ነበር ፤ ደርግ ይዞ የመጣው ነገር በአይደገፍም ፤ ይኽንን መሰል ኋላ ቀር እና ከኢትዮጲያ ጥቅም በተጻራሪ የእሚሰራ መንግሥት መወገዱ የግድ እና አግባብ ነበር ብዬ አምናለሁ።

ከእዚኽ በእሚቀጥለው እና ስምንተኛው የታሪካችን ክፍል በተባለው ላይ ፤ የኢትዮጲያ የወቅቱ ምሁራንን ሶሻሊስታዊ ውትወታ ሰበብ አድርጎ የኃይለ ሥላሴን መንግሥት በመንግሥት ግልበጣ አስወግዶ ወደ ስልጣን የመጣው ደርግ ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሕዝባዊ መንግሥት ባለቤት ለማድረግ በእሚደረገው ጉዞ ውስጥ የነበረውን ሚና የእምንቃኝበት ይኾናል ።