ሕ ገ ክ ራ ሲ

marketing-image

3.2.8. ክፍል 8 ፡ ዘመነ ደርግ (ከ 1966 ዓ.ም. – 1983 ዓ.ም.)

ስምንተኛው የታሪካችን ክፍል የእሚሸፍነው ፤ እስከ አኹን ከአየናቸው የታሪካችን ክፍፍሎች በተነፃፃሪነት ትንሽ የሆነውን ፤ ከ1966 ዓ.ም. አንስቶ እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ የአለውን ወይንም ደርግ በስልጣን ላይ የቆየባቸውን 17 ዓመታት ነው ።

ምንም እንኳን ፤ ለደርግ መምጣት ምክንያት የሆነው አብዮት ውስጥ ውስጡን ከ1966 ዓ.ም. ቀደም ብሎም ሲብላላ የነበረ መሆኑ ቢታወቅም ፤ በተመዘገበ ታሪክ በኢትዮጵያ አብዮቱ የፈነዳው በእዚኹ ዓመት በመሆኑ ፤ ይኽኛው የታሪክ ክፍል በእዚኽ ዓመት እንዲጀምር ሆኗል ።

ሌላው ነገር ፤ ምንም እንኳን ይኽ ዘመን በኦፊሴል የደርግ ዘመን ቢሆንም ፤ እንደ እሚታወቀው ፦ደርግ ፥ በታማሪዎቹ ተጀመረ የእሚባለው የከምኒስታዊ አብዮት እንቅስቃሴ ሌላው ገጽታ ወይንም እንደ ተማሪ አብዮተኞቹ ድንገተኛ መጥፎ ዱብዳ ፥ እንደ ደርጉ ደግሞ የአብዮቱ ጠበቃ ፤ በመሆኑ ይኽ ዘመን በእሚቃኝበት ወቅት በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ጉዞ ውስጥ ከነበራቸው ሚና አንፃር ፤ የተማሪዎቹ የአብዮት እንቅስቃሴ ከደርጉ እንቅስቃሴ ያነሰ ሽፋን ሊሰጠው አይችልም ።

ስለ እዚኽ ፤ በእዚኽ ክፍል የተማሪዎቹን አብዮት ፤ ከደርግ እኩል ፤ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ዝግመት ላይ የነበረውን ድርሻ እንያለን ።

ይኽን ስምንተኝው የታሪካችንን ክፍል ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ሕዝባዊ መንግሥት ምሥረታ የእሚያድርገውን ጉዞ ፤ የወቅቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተዋኒያን ፦ አብዮተኛ ተማሪዎቹ እና ደርግ ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ፤ ምድራዊ ገነትን በብዙ ዘመን ምናልባትም በብዙ መቶ ዓመታት ግዜ ውስጥ መፍጠር ከእሚፈልገው የዓለም ዓቀፍ ከምኒዝም ጋር አቆራኝተውት ፤ አንገብጋቢ የኢትዮጵያን ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች በይደር የተውበት ነበር ።

የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ፤ ሕዝባዊ ከመሆን በወግ አጥባቂነት ከተገታ ፤ የእዚኽ ዘመን የፖለቲካ ተዋንያን ደግሞ ፤ ከዓለም ዓቀፉ ከምኒዝም ጋር በመጠላለፋቸው የኢትዮጵያን የሕዝባዊ መንግሥት ራዕይ በይደር ትተውታል ።

በእዚኽ ክፍልም ይኽ የሆነበትን አግባብ እናያለን ።

እንግሊዝ የዘመናዊ ሕገመንግሥታዊ መንግሥት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የተጀመሩባት ሐገር እንደሆነች ፤ እላይ ስለ ፖለቲካ ፓርቲዎች በአወራነው ክፍል ላይ አስቀምጠናል ።

ተምሳሌት በሆነቸው እንግሊዝ ፤ ሕዝባዊ መንግሥት የመመሥረት ታሪካዊ ዝግመታቸው እንደ እሚያሳየን ፤ እ.አ.አ. ከ1215 ዓ.ም. አንስቶ የተበታተኑ የመብት ጥያቄዎች በተለያየ መንገድ ሲነሱ ቆይተው ፤ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ፤ በአግባቡ የተለያዩ ፓርቲዎች ከተቋቋሙ በኋላ ፤ እነ እዚኽ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኃሳባቸውን ከነፍጥ እና ከጠብ ውጭ ፤ በሰላማዊ መንገድ ወደ እሚያራምዱበት እና ወደ እሚያስፈጽሙበት የፖለቲካ ስረዓት መሸጋገር የቻሉት ፤ በዋናነት በነጻነቱ ዴሞክራሲ አግባብ ፤ መንግሥትን የዜጎችን ተፈጥሮዋዊ ሰብዓዊ መብቶች አክብሮ አስከባሪ እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ ወደ ስልጣን እንዲ መጣ የእሚያደርግ የፖለቲካ ስረዓት መገንባት በመቻላቸው ነው።

ያም ማለት ፤ በአግባቡ ያልተቀናጁ ወይንም በቂ የፍላስፍና መዋቅር የአልተገነባላቸው ፤ ምንጫቸው ፦ ‘ሰዎች ተፈጥሮዋዊ ሰብዓዊ እኩልነት አላቸው’ የእሚለው አስተሳሰብ የሆኑ ፦ ያለ ሕግ አግባብ የአለመታሰር መብትን ማስከበር ፣ በድምፅ ብልጫ የአልፀደቀ ግብር መጠን አለመቀበል እና መሰል ፍትሐዊ እና ሕዝባዊ ጥያቄዎች ፤ ከግዜ ወደ ግዜ ሰዎች በአንድነት እያበሩ መንግሥትን የእሚጠይቁዋቸው ጥያቄዎች ከሆኑ በኋላ ነው የሕዝባዊ መንግሥት ጥረት ወይንም ዘመናዊ የሕዝባዊ መንግሥት አፈጣጠር የጀመረው ።

በጠንካራው መንግሥት ላይ ፤ ይኽን መሰሎቹ ፍትሐዊ የሕዝብ ጥያቄዎች ፤ ግፊት እያሳደሩ ሲመጡ ፤ በእየ ግዜው አዳዲስ ጥያቄ የእሚጠየቀው እና በእዚኽም ስልጣኑ እየተሸረሸረ የመጣው መንግሥት ፤ እነ እዚኽን አዲስ የፖለቲካ ባህሎች በቋሚነት የእሚያስተዳድርበት አዲስ የፍልስፍና መዋቅር የአልነበረው በመሆኑ ፤ ኹኔታው የተኃድሶ መሪዎችን እና መንግሥትን ከኹለት መቶ ዓመታት በላይ ለቆየ ፤ በእየግዜው ለእሚያገረሽ የእርስ በእርስ ጦርነት የዳረገ ነበር ።

በሐገረ እንግሊዝ ከእዚኽ መሰል ማሕበራዊ ቁልፍልፍ መውጣት የቻሉት ፤ ቀደም ብለን እንደ አልነው ፤ በግዜ ኺደት የሕዝብን ፍትሐዊ ጥያቄ መሠረት አድርገው የእሚዋቀሩ ፓርቲዎች ከግጭት በስተቀር በሰላማዊ መንገድ ልዩነታቸውን የእሚፈቱበት ማዕቀፍ በመቀረፁ ነው ።

ያም ማለት ፓርቲዎች ከመንግሥት ጋር በነፍጥ የእሚዋጉ የፖለቲካ ኃይሎች ከመሆን ወጥተው ፤ በቅስቀሳ እና የሕዝብ ድጋፍ በማስተባበር ፦ የዜጎች ተፈጥሮዋዊ ሰብዓዊ መብቶች ፤ በመንግሥት እንኳን ያለ አግባብ ሊሻሩ አይችሉም የእሚል ፤ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ (Bill of Rights) በአለበት ፖለቲካዊ ምሕዳር ውስጥ ፤ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን አክብሮ ከማስከበር በአሻገር ወይንም በእዚኽ ፖለቲካዊ ምሕዳር ውስጥ ሆነን በሌሎች ሐገራዊ ጉዳዮች ላይ የተሻለ የፖሊሲ አማራጭ አለን ፣ እነ እዚኽንም ፖሊሲዎች በተሻለ ኹኔታ ማስፈጸም የእሚችሉ እጭዎች አሉን በማለት ፤ በፍትሐዊ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተወዳድረው የመንግሥትን ስልጣን መረከብ የእሚችሉበት ያም ሳይሳካ ሲቀር ፤ መንግሥትን ከሕዝብ ጥቅም አንጻር በመተቸት በስልጣን ላይ ያለ መንግሥት ሕዝብን እንዲያደምጥ ሊያስገድዱ የእሚችሉበት አሰራር ወደ ማስተዋወቅ መጡ ።

የሕዝባዊ መንግሥት ምንነቱ እና ፋይዳውም ይኼው ነው ፦መንግሥት የዜጎችን ተፈጥሮዋዊ ሰብዓዊ መብቶች አክብሮ አስከባሪ እና ወደ ፖለቲካ ስልጣን የእሚመጣውም ራሱን በአሰራር ፣ በአደረጃጀት ፣ በማስፈጸም ብቃት እና በፖሊሲ ጥራት ተወዳዳሪ አድርጎ አቅርቦ ፤ ማን የፖለቲካ ስልጣን ይያዝ እና የትኛው አሰራር ይሻላል የእሚለውን ጥያቄ በኃይል ከመፍታት ይልቅ ፤ በፓርቲ ተደራጅቶ እና ሕዝብን አንቀሳቅሶ ፤ ያለ ኹካታ ፤ በሕዝብ ድምፅ ብላጫ ፤ የበለጠው ሕዝብ የደገፈውን ሰው እና አሰራር በማፅደቅ መፍታት ነው ።

ስለ እዚኽ አስቸጋሪው ታሪካዊ ሕዝባዊ የመሆን ኺደትን በአንዲት ብሔራዊ ሐገር ሆና ተመስርታ በአበቃች ሐገር ውስጥ ፤ በቅደም ተከተል ብናስቀምጠው ፦ የተበታተኑ ሕዝባዊ ጥያቄዎች ማንሳት ፣ በእነዚኽ ጥያቄዎች ዙሪያ አንጃ ፈጥሮ መጋጭት ወይንም መዋጋት ከእዚያኽም በስተመጨረሻ ፤ እነዚኽን ሕዝባዊ ጥያቄዎች ከአፍራሽ ግጭት እና ጦርነት ውጭ ፤ የዜጎችን ተፈጥሮዋዊ ሰብዓዊ መብቶች ሳይሸራርፉ ፤ በአሰራር የእሚመለሱበትን መንገድ ወይንም ሕገመንግሥት ማቆም ናቸው ።

ይኽ ተፍጥሮዋዊ ሕገመንግሥትን የማርቀቅ ኺደት ግን ጠንካራ መንግሥት ኖሮ ኺደቱ የእሚፈጥረውን ከፍተኛ መናወጥ መቋቋም ከአልቻለ ፤ ሐገር እስከ መበተን የእሚያደርስ አደጋ ያመጣል ፤ ለእዛያም ነው የኢትዮጵያ ኹኔታ ፤ በክፍል አምስት እና ስድስቱ የታሪካችን ክፍል ላይ እንደ አየነው ከእንግሊዝ በተለየ ኹኔታ የተፈፀመው ።

ይኽ የፖለቲካ ታሪክ ተፈጥሮዋዊ የአመጣጥ ኺደት ፤ በእዚኽ ኺደት ውስጥ የዳበረው ፖለቲካዊ እውቀት ከመዳበሩ በፊት በመሆኑ ፤ በእዚኽ ዘመን ያሉ ሕዝብ ፤ ጠንካራ ብሔራዊ መንግሥት የመገንባት ኺደቱን ከጨረሱ ፤ ያንን መሰል ፈታኝ ኺደት ከማለፍ ይልቅ ፤ ኺደቱን ከአናቱ ፤ ማለትም ፦ የዜጎቾን ተፈጥሮዋዊ ሰብዓዊ መብት በእሚከበረበት ምሕዳር ውስጥ ፤ የተለያየ ኃሳብ እና ስብጥር የአላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎችን የእሚያስተናግድ ሕገመንግሥት ከመቅርፅ መጀመር ይችላሉ ፤ ምክንያቱም ፦ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት አክብሮ እያስከበረ ሕዝባዊ መሠረት እና ፋይዳ የአለው ሕዝባዊ ጥያቄ ይዘው የእሚነሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የእሚሰተናገዱበት ሕገመንግሥት የቱ እንደሆነ ከታወቀ የቆየ በመሆኑ ።

ስለ እዚኽ ፦ ጠንካራ ብሔራዊ መንግሥት በታሪካዊ ዝግመት ተገንብቶ በአለባቸው ሐገራት ፤ ዘመናዊ ዴሞክራሲያዊ የመሆን ትግል ከቀደምቱ ይለያል ። እንደ በፊቶቹ የተበታተኑ የመብት ጥያቄዎችን ይዞ ፤ በእነዚያኽም ጥያቄ ዙሪያ አንጃ ፈጥሮ ፤ የዜጎችን ተፈጥሮዋዊ ሰብዓዊ መብት ማክበር የስረዓቱ አንኳር ሰአያደርጉ በእሚነሱ ፖለቲካዊ አጀንዳዎች ላይ ፤ ሞት ቀረሽ ትግል አድርጎ ፤ ከእዚያኽም ከብዙ ትግል እና ደም መፋሰስ በኋላ ፤ የዜጎችን ተፈጥሮዋዊ ሰብዓዊ መብት በእሚከበርበት ፖለቲካዊው ምሕዳር ውስጥ ሌሎች ፖለቲካዊ ልዩነቶችን በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የእሚዳኝ ሕገመንግሥት ወደ መጻፍ መምጣት ሰአያስፈልግ ፤ ከሕገመንግሥት ወደ ፓርቲ ግንባታ መግባት ይቻላል ።

ዴሞክራሲያዊ ታጋዮች ይኽን ሕገመንግሥት እና በእዚኽ ሕዝባዊ መንግሥት ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ከማቋቋም ጀምረው ፤ በእዚኽ ኺደት ውስጥ እውነታኞዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲፈጠሩ ፤ ሕጋዊ መዋቅሩ ተዘጋጅቶ የእሚጠብቃቸው በመሆኑ ከእነርሱ ቀደም ከነበሩት ይልቅ በተነፃፃሪነት በቀላል ትግል ለፍሬ መብቃት እንዲችሉ ሲሆኑ ፤ የፀጉር አቆራረጥ ፋሽን እና የአውራ መንገድ ስፋት መጠን የፖለቲካ አጀንዳ አድርገው የፖለቲካ ፓርቲ ለመሆን የእሚጣጣሩ ቀቢፀ ተስፈኞች ደግሞ በጠንካራው መንግሥት አቅም በዴሞክራሲያዊ አግባብ ፤ ሐገርን በጦርነት ፣ በአመፅ ፣ በረብሻ የእሚያምሱ ሰአይሆን ፤ የውዳጅ የእረፍት ቀን ማህበራት ሆነው እንዲቀሩ ይሆናል ።

ስለ እዚኽ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ፤ ጠንካራ ብሔራዊ መንግሥታት በአሉባቸው ሐገራት የነበሩ የፖለቲካ ትግሎች በሙሉ ፤ ከዴሞክራሲ ግንባታ አንፃር መሆን የነበረባቸው ፤ በመጀመሪያ የዜጎችን ተፈጥሮዋዊ ሰብዓዊ መብቶች አክብሮ በማስከበር መሠረት ላይ ፤ ዘመኑን የእሚመጥን ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት አካላት የእሚዋቀሩበትን እና ወደ ፖለቲካ ስልጣን የእሚመጡበትን አግባብ የእሚደነግግ ሕገመንግሥት በማቆም መጀመር ነበረበት ። በእዚኽም ሰብዓዊ እና ሕዝባዊ መንግሥት ወይንም የፖለቲካ ፓርቲዎችን እድገት የእሚፈቅድ ፖለቲካዊ ምሕዳር ውስጥ የፖለቲካ ማሽኑ ራሱ ፤ በታሪካዊ ኺደት ኹለት ቢበዛ ሦሥት ሕዝባዊ ትልልቅ ፓርቲዎችን ይፈጥራል ።

ስለ እዚኽ ፤ ጠንካራ ብሔራዊ መንግሥት የማቆም ደረጃ ላይ የደረሱ ዘመናዊ ሐገራት ውስጥ የእሚደረገው ፤ ዘመናዊው የፖለቲካ ትግል የመጀመሪያ ግብ ፤ በሰባዓዊ ዴሞክራሲያዊ አግባብ የተዋቀረ መንግሥት የመፍጠር ትግል ነው ።

በኢትዮጵያም ይኽን የዴሞክራሲ ትግል አመቺ እና ግዜያዊ የእሚያደርገው ጠንካራ ሐገራዊ መንግሥት ፤ ከግራኝ ወረራ ዘመን አንስቶ በዘርፈ ብዙ ውስጣዊ እና ውጫዊ ምክንያት ከተዳከመበት ተነስቶ ፤ በአጼ ምንሊክ ንግሥና እንደገና ወደ ተገቢው ጥንካሬው የመመለሱ ኺደት በመጠናቀቁ ፤ በኃይለ ሥላሴ መንግሥትም መሠረታዊ የስልጣን መዋቅሩ ትርጉም በአለው መልኩ ሳይቀየር ይኽኑን ብሔራዊ መንግሥት የማጠናከሩ ሥራ የቀጠለ በመኾኑ ፤ የተራማጅ ተማሪዎቹ እንቅስቃሴ እና ደርግ መንግሥት ከኃይለ ሥላሴ ይልቅ ፤ ለሕዝባዊ ሽግግር ይበለጥ የተመቻቸ ኹኔታ ላይ ነበር የመጡት ።

ስለ እዚኽ አብዮተኛው ትውልድ እና ደርግ ፤ የዓለም ዓቀፉ ከምኒስት ቅርንጫፍ ሆነው በእሚረባው በእማይረባው ከእሚራኮቱ ፤ ዳብሮ የጨረሰውን ሕዝባዊ ሕገ መንግሥት በማቆም ቢጀምሩ ኖሮ የኢትዮጵያን ሕዝብ ዕድሜ ጠገብ ርዕይ ያሳኩ ነበር ።

አመቺ ኹኔታው በእዚኽ መልክ የነበረ ቢሆንም ፤ ይኽን ኺደት በመምራት በሕዝባዊ ሕገመንግሥት የተዋቀረ መንግሥት የመመሥረት ታሪካዊ እድሉ የነበራቸው ፤ የሶሻሊስት አብዮተኞች ፥ ተማሪው እና ደርግ ፤ በእሚከተሉት የከምኒስት ርዕዮት ምክንያት ሌላ ዓይነት ጠንካራ (ሕዝባዊ የአልሆነ) መንግሥት መመሥረት የእሚፈልጉ በመሆኑ ፤ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊው መንግሥት የመገንባት ኺደታችንን እንደገና በ17 ዓመት እንዲዝገይ አድርገውታል ።

አብዮተኛው ትውልድ ከነበረበት ተራ የጀብደኝነት እና የስልጣን ሽሚያ[1] በአሻገር ከእሚከተለው ማርክሲታዊ ርዕዮት የተነሳ ፤ ሕዝባዊ ጥያቄዎችን መመለስ ሰአይሆን ፤ ሕዝባዊ ጥያቄዎችን የጀብደኝነታቸው ማሳያ ፣ የስልጣን ሽሚያ ማካኼጃ እና የማርክሲስታዊው ርዕዮት ማራመጃ ነው የአደረጓቸው። በሌላ አገላለፅ አብዮታቸው አንገብጋቢ የሕዝብ ጥያቄዎችን ማራገብ እና በእነዚኽ የሕዝብ ጥያቄዎች ተሳፍሮ ፤ ድብቅ አጀንዳ የእሚያራምድ ነበር ።

ማርክሲዝም በፍጥረቱ ወይንም በይዘቱ የዘላለም የፍትሕ እቅድ የያዘ ፖለቲካዊ ርዕዮት በመሆኑ ፤ ግዜያዊ የፍትሕ ጥያቄዎች ዘላለማዊ የፍትሁን ጥያቄ ለመመለስ የእሚያግዙ ግብዓቶች እንጂ በራሳቸው ሊመለሱ የእሚገባቸው ወይንም በራሳቸው ተገቢ የፖለቲካ ግብ አድርጎ ስለ እማያያቸው ፤ ግዜያዊ ሕዝባዊ ጥያቄዎችን ተጠቅሞ ማርክሲስታዊ ትግልን ፤ ወይንም መንግሥት ፣ የመደብ ልዩነት እና ኃይማኖት የሌለበትን ምድራዊ የከምኒስት ገነት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የመፍጠር ትግልን ፤ ማካኼድ እንደ አሳፋሪ እና ወራዳ የፖለቲካ ሸፍጠኝነት አያየውም ።

ይኽ ምን ማለት እንደ ሆነ እናብራራው ።

አብዮተኛው ትውልድ ፤ ምንም እንኳን ከሕዝብ ፍቅር እና ለፍትሕ ከአለ፟ው ቀናዒነት የተነሳ ፤ የአብዮት እንቅስቃሴውን አድርጌአለሁ ቢልም ፤ ከእሚከተለው የሶሻሊስት ርዕዮት አንፃር ፤ ለእርሱ ፍትሕ ማለት ፤ በማርክስ ቲየሪ የሶሻሊዝምን ስረዓት ገንብቶ ከእዚያኽም ሦሥት መቶም ዓመት ይፍጅ አንድ ሺ ፦ መደብ ፣ መንግሥት ፣ ኃይማኖት እና ሞያ አልባ የሆነችውን እና ኹሉም ሰው እንደሥራው መጠን ሰአይሆን እንደ ፍላጎቱ መጠን ኹሉን ኢከነሚያዊ አቅርቦት እንደ አሻው የእሚያገኝባት የከምኒዝምን ገነት መፍጠር ስለ ሆነ ፤ እርሱ ግዜያዊ የእሚላቸው ፤ መሠረታዊ የሕዝብ ጥያቄዎች ተመለሱ አልተመለሱ ብዙም አይገደውም ።

በአጭሩ የወቅቱ ትውልድ አባላት በፖለቲካ አካኼዳቸው ከሳይንሳዊ የሰብዓዊ ሳይንስ ግንዛቤ የጸዱ ናቸው።

ለአብዮተኛው ትውልድ ፤ ሕዝብ በመረጠው እንደራሴ ይተዳደር ፣ መሬት ለአራሹ ይሰጠው ፣ የኃይማኖት ነፃነት ይከበር ፣ የሕዝብ የራስን እድል በራስ መወሰን መብት ይከበር ፣ ዜጎች ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ይከበር ፣ ወዘተ ፤ የፖለቲካ ትግል ማቀጣጠያ ግብዓቶች እንጂ በራሳቸው ግቦች አይደሉም ።

ለምሳሌ ፦ የከምኒስት ፓርቲ ሕዝባዊ መንግሥት ይመስረት ብሎ ሰልፍ ሊወጣ ይችላል ፤ በእዚኽ ሰልፍ ሰበብ አብዮት አድርጎ ነዋሪውን መንግሥት ጥሎ ራሱ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ግን በእርሱ ጥሪ የድጋፍ ሰልፍ እንዲያደርግ ከአልሆነ ፤ የትኛውም አካል ምንም ዓይነት ጥያቄ ለመጠየቅ ሰልፍ ቢወጣ ፤ ልክ እንደ እነርሱው በገለልተኛ ምርጫ በቀጥታ በሕዝብ በተመረጡ እንደ ራሴዎች የእሚዋቀር ፓርላማ ይኑረን በእሚል ራሱ ቢወጣ ፤ ሰልፈኛውን ፀረ አብዮተኛ ብሎ እስከ ሞት በእሚደርስ የተለያዩ ቅጣቶች ነው የእሚቀጣው ።

በአጭሩ ማርክሲዝም ሕዝባዊ መንግሥት ይመስረት የእሚለውን ኃሳብ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ለመፍጠር ይጠቀምበታል እንጂ በእውነት ለሕዝባዊ መንግሥት ምሥረታ የእሚታገል ፖለቲካዊ ርዕዮት አይደለም ።

“ማሕበሩ (ግንባሩ ፣ ድርጉ ፣ የጭቁኑ ሕዝብ ሞግዚቱ ፣ ወዘተ) የሥራ እንጂ የፓርላማ ንትርክ አካል በአለ መሆኑ ፤ ሕግ አውጭም አስፈፃሚም ራሱ መሆን አለበት ።”

“The Commune was not to be a working, not a parliamentary, body, executive and legislative at the sametime. [29]“

ስለ እዚኽ ፦ በአብዮተኛው ትውልድ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ተሳታፊው ግለሰብ ወይንም ተማሪው እንደ ግንዛቤ ደረጃው ፤ በእነዚኽ የፍትሕ ጥያቄዎች እውነተኝነት አምኖ ወይንም ተስቦ የገባ የሶሻሊስት አብዮት ማካኼጃ ግብዓት ነው ወይንም እነዚኽን ርዕሶች ለትልቁ አጀንዳ ማሳኪያ እንጂ በራሳቸው የትግሉ ግብ አለመሆናቸውን አውቆ በማርክሲዝም መሠረት ሶሻሊዝምን ከእዛኽም ከምኒዝምን ለመገንባት የእሚጥር ነው ።

ከእዚኽም የተነሳ ፦ በተማሪው አብዮተኛ ካምፕ ውስጥ አንድ ዓይነት ቋንቋ የእሚናገሩ ፤ ነገር ግን በፍፁም ሊታረቁ የእማይችሉ ኹለት ተቃራኒ የፍትሕ ግንዛቤ የነበራቸው ጎራዎች መኖራቸው መታወቅ አለበት ። ለምሳሌ ፦ ኹለቱም መሬት ለአራሹ ብለው ይላሉ ፤ ይኽ መፈከር ለአንደኛው ጎራ ፤ የመሬት ባለቤትነት መብት ስለሌለው በሌሎች እርሻ ላይ እንዲሰራ የእሚገደደው እና ጉልበቱ የእሚበዘበዘው ገበሬ የራሱን መሬት አግኝቶ ለሰው ከመሥራት ይልቅ ራሱ የራሱ ምርት ተጠቃሚ እንዲሆን የእሚል ትርጉም የአለው ሲሆን ፤ ለሌላኛው ጎራ ደግሞ ፤ በማርክሲዝም መሠረት ገበሬውን የራሱ መሬት ባለቤት ማድረግ እንደ እማያስፈልግ እያወቀ[2] ነገር ግን ይኽን ማነቃቂያ ተጠቅሞ መንግሥትን ከስልጣን ማውረጃ እና የሶሻሊስትን ስረዓት መገንቢያነት አድርጎ ለመጠቀም የእሚያስበው ናቸው ።

ስለ እዚኽ እንደ አብዮተኛው የንቃት ደረጃ ፤ በተማሪዎቹ አብዮተኞች ውስጥ ፤ መሠረታዊ ክፍፍል ነበር ።

ይኽን ስል ፤ የአብዮተኛው ትውልድ ትልልቅ ጎራዎች አመራሮች ፤ ማለትም ፦ ኢሕአፓ ፣ መኢሶን ፣ ወዝሊግ እና ደርግ አመራሮች ወይንም በጣት የእሚቆጠሩት የእየ ፓርቲ የአስፈጻሚ ወይንም የፖሊት ቢሮ አባላት እንደ መሬት ላራሹ ወይንም የፖለቲካ ፓርቲ ብዙኃነት የእሚሉት ጉዳዮች ፤ ሕዝብ ማነቃቂያ እንጂ የፖለቲካ ትግላቸው ግብ እንደ አልሆኑ ፤ ወይንም ስልጣን ቢይዙ/ሲይዙ እነ እዚኽን ጥያቄዎች የእሚያነሱ ሰዎችን አሳደው እንደ እሚያጠፉ አንዳችም ብዥታ አልነበረባቸውም ።

ለምሳሌ ፦ የደርጉ ሊቀመንበር ፤ የቀድሞው የኢትዮጲያ ፕሬዝደንት ፤ መንግሥቱ ኃይለማሪያም ፤ ኢሠፓ ከተመሠረተ በኋላ ፤ ከተቃዋሚዎች ጋር እንደራደር እና ዴሞክራሲያዊ አሰራር እንዘርጋ ለእሚለው በፓርቲያቸው ስብሰባ ላይ ለቀረበ ጥያቄ ፤ ይኽ ጠበል ቅመሱ አይደለም ሲሉ በአደባባይ ተደምጠዋል።

ከእነዚኽ ፓርቲዎች ማዕከላዊ ከሚቲ አባል ውጭ የአለው የፓርቲዎቹ አባል ግን ፤ የማርክሲዝምን ፍልስፍና በእሚረዳበት አግባብ ፤ ሕዝባዊ ጥያቄዎችን መመለስ ግቡ አድርጎ ይወስዳል ወይንም የሶሻሊስት አብዮት ማካኼጃ ግብዓት አድርጎ ይወስዳል ።

ለምሳሌ ፦ የተማሪው አብዮተኛ መሪዎች ፤ ‘መሬት ላራሹ የእምትሹ ተዋጉለት አትሽሹ’ እያሉ ሰልፍ አስተባብረው አብዮት ከአቀጣጠሉ በኋላ ፤ እነርሱ አቀጣጠልን በእሚሉት አብዮት ፤ የመንግሥትን የላዕላይ እና የታዕታይ መዋቅር ፤ ከአራተኛ ክፍለ ጦር ማዘዣው ሆኖ ሲያፈራርስ የነበረው ደርግ ፤ አፈሙዙን ወደ እነርሱ ሳያዞር በፊት ፤ መንግሥትን የማፍረስ ስውር ሥራው ተጠናቆ ኃይለ ሥላሴ በግልፅ ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ፤ አዲስ የእሚዋቀረው መንግሥት ፤ የመሬትን ጥያቄ እንዴት መመለስ አለበት በእሚለው ጉዳይ ላይ የአብዮተኛው ተማሪ መሪዎች በአሉበት ሲወያዩ ፤ የአብዮተኛው ትውልድ መሪዎች አቋም የእሚከተለው ነው የነበረው ፦

“መሠረታዊው የመሬት አስተዳደር ማሻሻያ ጥያቄ ፤ ፖለቲካውን እና የመሬት አስተዳደር ማሻሻያውን ለማያያዝ ነው እንጂ ኢከነሚውን በአንድ ወገን ፖለቲካውን በሌላ ወገን የመለየት ጉዳይ አይደለም ፤ የመሬት አስተዳደር ማሻሻያ በራሱ አስፈላጊ ስለ ሆነ አይደለም የመሬት አስተዳደር ማሻሻያ ያስፈለገው ። የመሬት አስተዳደር ማሻሻያ ችሮታ አይደለም ። ለጭሰኛው የተሰጠ የበጎ አድራጎት ምፅዋት አይደለም ። በአዋጅ ፣ በመልካም ምኞት ፣ በደግ አሳቢነት ፣ ከኃይማኖታዊ ምኞት ፣ ወዘተ ፤ የእሚመጣ አይደለም ። እጅግ የጋለ የመደብ ትግል ነው ።”

“The fundamental question is to link the politics and the economics of land reform and not separate the economic alone, in one category, and politics in another, there is no land reform for its own sake. Land reform is not a gift. It is not a philanthropic handout to the peasants. It does not come by declaration, by good intentions, by pious wish, etc. it is the most furious class struggle. [121]“

በእዚኽ አቋማቸው በግልፅ እንደ ተቀመጠው ፤ ገበሬውን የመሬት ባለቤት ማደርግ የእምንፈልገው የግድ መሬቱን ፤ በማርክሲስት ርዕዮት መሠረት የመደብ ጠላታቸው ከሆነው ባላባት በጉልበት ቀምተን ለገበሬው በመስጠት ነው እንጂ ፤ ባላባቱ መሬቱን እንደ ያዘ ቆይቶ ፤ ባል አባት ለአልሆነው ገበሬ ሌላ መሬት ይሰጠው የእሚለውን አካኼድ በፍፁም አንቀበልም ነበር ያሉት ።

በኃይለ ሥላሴ መንግሥት ምክንያተ ቢስ ወግ አጥባቂነት ፤ በእሚኖርበት ሐገሩ የመሬት ባለቤት የመሆን ሰብዓዊ መብቱን የተነፈገበትን ዜጋ መብት ማስከበር የትግሉ ግብ የሆነባቸው አብዮተኞች መኖራቸው በአይካድም ፤ የአብዮተኛ ተማሪው መሪዎች ግን የመሬትን ጥያቄ ፤ የገበሬው የመደብ ጠላት የእሚሉትን ባላባቱን ማጥፊያ እንጂ ገበሬውን የመሬት ባለቤት ለማድረግ እንዳልሆነ ጠንቅቀው የእሚያውቁ ስለ ነበሩ ፤ የመሬት አስተዳደር ማሻሻያ በራሱ አስፈላጊ ስለሆነ አይደለም የመሬት አስተዳደር ማሻሻያ ያስፈለገው በማለት ፤ የመሬትን ጥያቄ የመጠፋፋት የመደብ ትግሉ አካል ሆኖ እንጂ በራሱ ገበሬውን የመሬት ባለቤት ለማድረግ እንደ አልፈለጉት ፤ ከላይ በዓለው ታሪካዊ ክፍል ስለ አስቀመጡ ፤ ማንኛውንም የመብት ጥያቄም በእዚኽ መልኩ የእሚያዩ እንደ ነበሩ መረዳት ይቻላል ፤ ምንም እንኳን ለእያንዳንዱ የመብት ጥያቄ ከእዚኽ የተለየ መደለያ ወይንም ማስተባበያ የእሚሰጡ ቢሆንም ።

በእዚኹ ከእላይ በአለው አቋማቸው ፤ ‘እጅግ የጋለ የመደብ ትግል ነው’ የእምትለው አባባል ፤ እንዲኹ በአጋጣሚ የተባለችም ሳትሆን ፤ ከታች ተቀንጭቦ ከተጠቀሰው እንደ ከምኒስት ማንፌስቶ ከአሉ፟ ፤ የማርክስዚም ፍልስፍና የተወሰዱ መሆናቸው ፤ ኹለቱን በማስተያየት ያለ ብዙ ምርምር መረዳት ይቻላል ፦

“ከእዚኽ በፊት የነበሩ ማሕበረሰባት ታሪክ ኹሉ የመደብ ትግል ታሪክ ነው ። ነፃ እና ባሪያ ፣ ባላባት እና ጭሰኛ ፣ ጌታ እና ሎሌ ፣ አለቃ እና ምንዝር ፤ በአጭሩ ጨቋኝ እና ተጨቋኝ ፤ ማብቂያ በሌለው ተፃራሪነት ተፋጠው ፤ አንዳንዴ በግልፅ አንዳንዴ በስውር እየተጋጩ ፤ ግጭቱ አብዮታዊ የሆነ ማሕበራዊ አዲስ አወቃቀር የፈጠረበት ወይንም ተቃራኒ መደቦቹ በፍፁም የተጠፋፉበት ነው ።”

“The history of all hitherto existing society is the history of class struggles. Freeman and slave, patrician and plebeian, lord and serf, guild-master and journeyman, in a word, oppressor and oppressed, stood in constant opposition to one another, carried on an uninterrupted, now hidden, now open fight, a fight that each time ended, either in a revolutionary reconstitution of society at large, or in the common ruin of the contending classes. [18] “

ለእዚኽም ነው ፤ ሐገራችን ኢትዮጵያ ከ400 ዓመት የከሸፈ የሕዝባዊ መንግሥትነት ትግል ወጥታ እንደ ገና አዲስ እድል ሲያጋጥማት ፣ በዘመናዊ መልክ የተዋቀረ መንግሥት ሲኖራት ፣ ልጆቿ የዘመናዊ ትምህርት ተምረው ዘመናዊ የፖለቲካ ሳይንስን መረዳት የእሚችሉበት አቅም ሲያዳብሩ ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የነበረበት መነጠል ተቀርፎ ከዓለም ሕዝብ ጋር ሲቀላቀል ፤ በአጠቃላይ ጠንካራውን መዓከላዊ መንግሥት ሕዝባዊ ወይንም ዴሞክራሲያዊ የማድረግ ፤ ለእዚያኹም እንደ ጥንቱ አባቶቻችን በደም እና በአጥንት ሰአይሆን ፤ በሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ፤ የከምኒዝም ቫይረስ ወደ ሐገራችን በመግባቱ ፤ አንድ ግዜ እንደገና የሕዝባዊ መንግሥት ራዕያችን የጨነገፈው ።

ሕዝባዊውን ጥያቄ ግብ አድረገው የተንቀሳቀሱ ፤ የዘመኑን ከከፍተኛው አመራር ውጭ የነበሩ መደበኛ አብዮተኞች ትተን ምክንያቱም ፦ የስውር የማርክሲዝም አጀንዳ መጠቀሚያ እንጂ የሐገሪቱ ፖለቲካዊ አቅጣጫ ወሳኞች ስለ አልነበሩ ፤ ይኽ የሕዝባዊ መንግሥት የማግኘት ታሪካዊ ህልማችን የከሸፈው ፤ በዋናነት የአብዮተኛው ትውልድ የፖለቲካ አመራሮች የዓለም ዓቀፉ የከምኒስት ኢንተርናሽናል ቅጥረኞች በመሆናቸው ነው ።

በእርግጥ በርዕዮት ደረጃ ፤ እነዚኽ የተማሪው አብዮት መሪዎች ፤ ሐገር (ኢትዮጵያን ጨምሮ) የቡርዥዋ ማሕበረ ኢከነሚ ስሪት በመሆኗ መጥፋት አለባት ብለው የእሚያምኑ በመሆናቸው ፤ ራሳችንን የዓለም ዓቀፉ ከምኒዝም ቅርንጫፍ በማድረግ ሐገራችንን ለማፍረስ መሥራታችን ፤ ዓለም ዓቀፋዊ የሰው ልጆችን ወንድማማችነት የእምናምን ፤ ዘር ፣ ቆዳ ፣ ኃይማኖት እና ዜግነት ሳንለይ ለሰው ልጆች ኹሉ ፍትሕ እንዲሰፍን ከአለ፟ን ፍላጎት የተነሳ ስለ ሆነ ባንዳ አይደለንም ቢሉም ፤ ከጤናማው የሐገር ግንዛቤ አንፃር ወይንም ፍትሐዊ በሆኑ የሐገራት ሕግ ፤ በባንዳነት እና በወንጀል ከመከሰስ ሊድኑ አይችሉም ።

እናት እና አባቱ ፤ በፍትሕ እና በልፋት ያካበቱትን ንብረት የእሚበ፟ላ እና የእሚለበስ እስከ አይኖር ዘርፎ እና ሸጦ ፤ የሽያጩን ገቢ ፤ ድህነትን ከዓለም ላይ አጠፋለሁ ብሎ ለእሚሰራ ለአንድ ዓለም ዓቀፍ በጎ አድራጎት ድርጅት ገቢ የአደረገ ቀቢፀ ተስፈኛ ወጣት ፤ እናት እና አባቱን በመክዳት እና በመወንጀል የእሚከሰስ ከሆነ ፤ የአብዮተኛው ትውልድ መሪዎች በባንዳነት እና በወንጀል የእሚከሰሱ ናቸው ። ምክንያቱም ፦ የእሚያውቁትን እናት እና አባትን አደህይቶ የእማያውቃቸውን ድሆች ማብላት የእሚባል ፍትሕ ስለሌለ ።

እኛ ኢትዮጵያዊያኖች እንደ ሰው ፤ አርስታትል እኛ ሰዎች ማሕበራዊ ወይንም ፖለቲካዊ ፍጥረት ነን እንደ አለው ፤ መልካም የእምንለውን ነገር የእምንፈልግ ሰዎች ፤ ከብቸኝነት ወጥተን መንደርን ፈልገን እና ገንብተን ፣ ከመንደር ወጥተን እና ፈልገን ሐገር ገንብተን ፣ ከሐገርም አልፈን እና ዴሞክራሲያዊ ሐገር ፈልገን ፤ ዴሞክራሲያዊ ሐገር ለመሆን የአደርግነው ጥረት ፤ የዓለም ሕዝብ ኹሉ ዴሞክራሲ ሲያገኝ ዴሞክራሲ ታገኛለህ እስከ እዚያኽ ግን የዓለም ዓቀፍ ዴሞክራሲያዊ ትግል ግብዓት ትሆናለህ የእሚሉ ቀቢፀ ተስፈኞች ቀሙት ።

ስምንተኛው የታሪካችን ምዕራፍ ፤ የአብዮተኛው ትውልድ ፖለቲካዊ አመራሮች እና ደርግ ፤ በዓለም ዓቀፍ ከምኒስት አሳዳሪዎቻቸው እየተመሩ ፤ ይኽን የኢትዮጵያ ሕዝባዊ መንግሥት የመመሥረት ታሪካዊ ህልም የቀሙበት ታሪክ ነው ።

በእርግጥ ለእዚኽ ታሪካዊ ውድቀት ፤ ምክንያት የለሹ የኃይለ ሥላሴ እምቢተኝነት ወይንም የመንግሥታቸው መጃጀት እና አልንቀሳቀስ ባይነት ፤ ከአብዮተኛው ትውልድ መሪዎች ትምክኽት እና ቀቢፀ ተስፈኝነት እኩል ተጠያቂ ቢሆንም ፤ የእዚኽ የታሪካችን ክፍል ትኩረት የኃይለ ሥላሴ መንግሥት በአለመሆኑ ፤ አብዮተኛው ትውልድ አመራሮች እና ደርግ ማለታችን ፤ ለእዛው ነው ።

የኃይል ሥላሴ መንግሥት ፤ አንድ ነገር ለአይጎዳው ፤ ራሱ ያቋቋመው የመሬት አስተዳደር መሥሪያ ቤት የእሚያቀርብለትን የመሬት አስተዳደር ሕግጋት ቢያፀድቅ ፣ ቢያንስ የታችኛውን ፓርላማ ከመላው ዜጋ መሐከል ቀጥታ በሕዝብ በእሚመረጡ ተወካዮች ቢገነባው እና መሰል ማስተካከያዎችን ቢያደርግ ኖሮ ፤ መዓከላዊ መንግሥቱ የበለጠ ስለ እሚጠናከር እና ሕዝባዊ ስለ እሚሆን ፤ ስውር አጀንዳ የነበራቸው ከምኒስቶች ሕዝብ የእሚያነሳሱበት አጀንዳ አረንቋ በከፍተኛ ደረጃ ይጠፍባቸው ነበር ።

በእሚያሳዝን መልኩ ፤ ግዜ እና ኹኔታው አልፈቀደምና ፤ ኃይለ ሥላሴም አልሰሙም ፣ ተማሪውም መጨረሻው አልታየውም ፣ ደርጉም ከባዱን መንገድ ለመውሰድ አላቅማማም ።

ከአብዮተኛ ተማሪዎቹ አመራሮች የፖለቲካ ግንዛቤ እና አቋም ተነስተን ፤ ምንም እንኳን አብዮታችንን ደርግ ቀማን ቢሉም ፤ ደርግ ወደ መደርኩ ባይመጣም እና እነርሱ እንደ ጠየቁት ፤ የኃይለ ሥላሴን መንግሥትን ከስልጣን አውርዶ ወደ ካምፑ ቢመለስም ኖሮ ፤ ተማሪዎቹ ራሳቸው ከደረግ ያነሰ አምባገነናዊ መንግሥት አይገነቡም ነበር ወይንም የተመሪዎቹ መንግሥት ከደርግ የእማይተናነስ ጨፍጫፊ እና አምባገነን ነበር የእሚሆነው ።

ይኽን ለማሳየት የተወሰኑ ነጥቦች ላንሳ ። ከላይ በግልፅ እንደ አስቀመጥነው ፤ የተማሪዎቹ አብዮት በማርክሲዝም መርህ የእሚመራ በመሆኑ ከማርክሲዝም ዓለም ዓቀፋዊ ግብ አንፃር ፤ የኢትዮጵያ ነዳያን ጥያቄ በትልቁ መጽሐፍ ውስጥ አንድ የውጣ በመሆኑ ፤ መሬት ለአራሹ ፣ የሰብዓዊ መብት ፣ ወዘተ ፤ ጥያቄዎች ትግል ከማቀጣጠያነት የአለፈ ዓላማ ስለ ሌላቸው ፤ አንድ ግዜ ተማሪዎቹ ስልጣን ከያዙ በኋላ ፤ የሠራተኛው አምባገነንነት በእሚል ፍፁማዊ አምባገነን መንግሥት የመመሥረታቸው ጉዳይ ፤ በእሚከተሉት ርዕዮት እና ለርዕዮቱ በነበራቸው ታማኝነት ምክንያት የእሚያጠያይቅ አይደለም ። መንግሥት ሳይሆኑ በእየ ፓርቲያቸው የነበረው የፓርቲ አወቃቀር ፣ የፓርቲ ፕሮግራም ፣ የትግል ዕቅድ እና አፈፃፀም ለእዚኽ ማረጋገጫ ነው ።

ይኽን ኹኔታ ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ እና ኢሕአፓ እና መኢሶን መካከል ለተፈጠረው የመጠፋፋት ግብግብ ፤ በዋነኛ ምክንያትነት የእሚጠቀሰው የመሬት ጉዳይን እንውሰድ ።

እንደ ወቅቱ ታሪካዊ ዘገባ ፤ ኢሕአፓ የማዖን የመሬት ፖሊሲ አራማጅ ሲሆን ፤ መኢሶን ደግሞ የራሻዉን የቦልሽቪክ የመሬት ፖሊሲ አራማጅ ነበር ። እነ እዚኽ የተለያዩ የተባሉት ኹለት የመሬት ፖሊሲዎች ደግሞ በመንግሥት ሲተገበሩ ፤ የደርግ እና የኢሕአዲግ የመሬት ፖሊሲዎች ናቸው በቅደም ተከተል ። ደርግ የራሺያውን የቦልሼቪክ ፖሊሲ ሲተገብር ፤ ኢሕአዴግ የማዖን የመሬት ፖሊሲ ነው የተገበረው ።

ከእዚኽም ተነስተን ፤ ኢሕአፓም ሆነ መኢሶን ፤ ገበሬውን ባለመሬት ማድረግ ግድ የእማይሰጣቸው ጉዳይ መሆኑን ብቻ ሰአይሆን ፤ በእዚኽም ገበሬውን የመሬት ባለቤት የማስመሰል ማታለያ የሆነው የመሬት ፖሊሲያቸው ፤ ገበሬውን ብሎም ሊህቁን እንዴት እናታለው በእሚለው ላይ እንጂ በይዘቱ ምንም ልዩነት የለውም ። እ.አ.አ. በ2003 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኢከነሚክስ ማሕበር በአደረገው ጥናት ላይ እንደ አስቀመጠው ፤ በደርግ እና በኢሕአዴግ የመሬት ፖሊሲ ስሪት ላይ የቅርፅ ካልሆነ የይዘት ልዩነት እንደሌለ አስቀምጧል ፦

“… በ1982 ዓ.ም. ‘ቅይጥ ኢከነሚ’ የእሚለውን ተከትሎ የመጡትን የኋላ ላይ የደርግ ማሻሻያዎችን ከግምት ውስጥ ከአስገባን ፤ ነገሮች ከመለወጥ ይልቅ በአሉበት እንደ አሉ ነው ያሉት ።”

“… if those belated policy changes made by the Derge following its 1990 ‘mixed economy’ reform are taken into consideration, more has stayed the same than changed. [123]“

ኹለቱም የመሬት ፖሊሲዎች በተግባር ይኽ ነው የእሚል ልዩነት ከአልነበራቸው ፤ አብዮተኞቹ መኃይማን ናቸው ከአላልን በስተቀር ፤ ሚዛን በእማይደፋ ልዩነት ለእዚያኽ መሰል ግብግብ እንደ እማይዳረጉ መገመት እንችላለን ።

እናም በእዚኽች ትንሽ የውጣ የእምታኽል ልዩነት ወይንም እርሷን ሰበብ አድርገው ፤ መኢሶን እና ኢሕአፓ የመሬት ፖሊሲያችን ዋነኛ ልዩነታችን ብለው ፤ ኢሕአፓ መኢሶንን ከደርግ ጋር በጠላትነት ፈርጆ መኢሶኖችን ከደርግ እኩል ሲገድል ነበር ፤ መኢሶን ከደርግ ጋር ሆኖ በቀይ ሽብር ኢሕአፓን ሲገድል ነበር ፤ በኋላ መኢሶን ራሱ በደርግ እስኪገደል ድረስ ። ይኽንን ኹኔታ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የከምኒዝምን ታሪክ በጥልቀት አጥንተው ‘ጥቁሩ የከምኒዝም መጽሐፍ’ በእሚል መጽሐፍ ያሳተሙ የተመራማሪዎች ብድን እንደ እዚኽ አስቀምጠውታል ፦

“ደርግ ኢሕአፓን ነጭ ሽብር ጀመረ በማለት ከደመሰሰ በኋላ ፤ መኢሶንን በቀይ ሽብር ዘመቻ ፈር የለቀቀ የጭከና ተግባር ፈፀመ ብሎ መኢሶንን ደመሰሰ ። ሐይሌ ፊዳ ፤ ከመኢሶን መሪዎች አንዱ የነበረ እና የደርግም የፖለቲካ ቢሮ አባል ሲሆን … በፈረንሳይ ትምህርት ላይ ሳለ ከከምኒዝም ጋር ተዋወቀ … እ.አ.አ. በ 1977 ዓ.ም. ከታሰረ በኋላ የገባበት ጠፋ ።”

“Derg liquidated EPRP for starting white terror, then MEISON for being harsh on red terror. Haile Fida, one of the leaders of MEISON and a member of the Derg political bureau, acquired his Marxist-Leninist tendencies while studying in France … arrested in 1977 and disappeared. [23]“

እንደ የከምኒዝም ጥቁሩ መጽሐፍ ጸኃፍት ሐይሌ ፊዳ ፤ ቀይ ሽብርን በመፈፀም ግንባር ቀደም የነበረውን ቀበሌ ፤ በደርግ የፖሊት ቢሮ አባልነቱ ፤ ለኢትዮጵያ ያስተዋወቀው እና ያዋቀረው እርሱ ነበር ።

ይኽ ታሪካዊ ክስተት ፤ ምንም እንኳን አብዛኛው የወቅቱ የተማሪዎች እንቅስቃሴ አካል የነበረው ተማሪው ለእዚኽ እንግዳ ሊሆን ቢችልም ፤ የወቅቱ የተማሪዎች እንቅስቃሴ መሪዎች እንደ ከምኒስት ሪዕዮት አራማጅነታቸው ከደርግ የተለየ አካኼድም ሆነ ኹኔታ ለኢትዮጵያ ሊፈጥሩላት የእማይችሉ እንደ ነበር ጥሩ ተግባራዊ ማሳያ ነው ። ምክንያቱም ፤ በርዕዮት ደረጃ ምንም ልዩነት የሌላቸው መኢሶን እና ኢሕአፓ ፤ አንዱ በደርጉ ጉያ ውስጥ ሆኖ ሌላኛው ከውጭ ሆኖ ለመጠፋፋት የእሚጋጩት ፤ የኃሳብ ልዩነት ነድቷቸው ሰአይሆን ፤ የከምኒዝም ፍልስፍና ይኽን እንዲያደርጉ ግድ ይላቸው ስለ ነበር ነው።

በእዚኽ መልኩ ፤ ተማሪዎቹን እርስ በእርስ ከአማታ ብኋላ ፤ ደርግ ኃይሌ ፊዳን ራሱ በቀይ ሽብር ወቅት ከመጠን አልፏል በማለት አስወግዶት እና እርሱንም ብቻ ሰአይሆን መኢሶንን እንደ ድርጅትም ከመንገድ አስወግዶ የፖለቲካ ስልጣኑን በእጁ አስገብቶ አገሪቱን ለቀጣዪ 17 ዓመት መርቷል ። በእዚኽ ድንገታዊ በእሚመስል አጋጣሚ የመጣው ደርግም ፤ ድንገታዊ ክስተት ሰአይሆን ፤ ራሱም እንደ አስወገዳቸው የተማሪዎች አብዮተኛ ፤ የዓለም ዓቀፉ የከምኒዝም ስሪት መሆኑ መታወቅ አለበት [3]።

አንድ አንድ ምንጮች እንደ እሚሉት እና አንድ አንዶችም እንደ እሚመስላቸው ፤ ደርግ ፥ በሰኔ 21, 1966 ዓ.ም. በኢትዮጵያ አቆጣጠር በድንገት በተሰበሰቡ የጦሩ ተወካዮች የተመሠረተ ግብታዊ ሥብሥብ ሰአይሆን ፤ ምን አልባትም ከተማሪዎቹ እንቅስቃሴ ቀደም ብሎ በህቡ ብዙ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረ አካል ነው።

ተማሪው እና ተማሪውን በፀረ አብዮተኛ ስም ሰይሞ ያሳደደው ደርግ ፤ እንዴት ኹለቱም የአንዱ የዓለም ዓቀፍ ከምኒዝም ስሪቶች ሊሆኑ ይችላሉ? ብሎ ለእሚጠይቅ ሰው መልሱ ፤ ‘አብዮት ልጆቿን ትበላለች’ የእሚለውን የዓለም ዓቀፉን ከምኒዝም አባባል ማጥናት መልሱን ይሰጠዋል ።

ተማሪውን ፀረ አብዮተኛ ብሎ ደምስሶ ፤ ራሱን የአብዮቱ ባለ አደራ የአደረገው ደርግ ፤ ልክ እንደ ተማሪዎቹ ኹሉ ፤ የዓለም ዓቀፉ ከምኒዝም ቅርንጫፍ መሆኑን ፤ በዓለም ዓቀፉ ከምኒዝም መሠረታዊ አሰራር ፣ ታሪካዊ ክስተቶች እና መዛግብቶች ማሳያነት የእሚታይ ነው ።

የመጀመሪያው ፤ ኢሕአፓን ለማጥፋት ፤ በደርግ ጽሕፈት ቤት በመኢሶን አስፈፃሚነት የተካኼደው ቀይ ሽብር ፤ እንደው በአጋጣሚ የተጀመረ እና የኢትዮጵያ ልዩ ኹኔታ የፈጠረው ክስተት ሰአይሆን ፤ በራሻ ከተካኼድው ተመሳሳይ ቀይ ሽብር የተኮረጀ ነበር ። ስለ ራሻው ቀይ ሽብር ፤ ጥቁሩ የከምኒዝም መጽሐፍ እንዲኽ ይላል ፦

“ቀይ ሽብር (የራሻው) ‘በከምኒስት ፓርቲ አመራሮች ላይ ለተደረገ የመግደል ሙከራ ፤ ፓርቲው ምንም ሳያቅድ በሕዝቡ ቁጣ የመጣ ነው’ የእሚል ሽፋን ሊሰጡት ሞክረዋል”

“...gives the lie to .... claims that the Red terror “was a general and spontaneous reaction of indignation by the masses to the attempted assassinations of 30 August 1918, and began without any initiative from the central organizations [23]“

ቀይ ሽብር ፤ ኢሕአፓዎች በከተማ ውስጥ ነጭ ሽብርን በማድረጋቸው ማለትም በከተማ ውስጥ ባለስልጣን መግደል በመጀመራቸው ሕዝቡ አታስጨርሱን አስታጥቁን አለ ተብሎ ፤ ስለ እዚኽ ሕዝቡ በቁጣ ጀመረው ተብሎ በራሺያ እንደ ተጀመረው ፤ በተመሳሳይ መንገድ በኢትዮጵያም አብዮቱ ራሱን ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት የአሸጋገረበት ነው ተብሎ ፤ ኢሕአፓዎች በከተማ ውስጥ የመንግሥትን ባለስልጣን መግደል ጀመሩ ተብሎ (በርግጥም መግደላቸው በራሳቸው በኢሕአፓዎችም የእሚታመን ነው) ፤ በተመሳሳይ ቀይ ሽብር ተካኺዶባቸዋል ።

ይኽም ብቻ ሰአይሆን የእሚከተሉት ፤ የዓለም ዓቀፍ ከምኒዝም እንቅስቃሴ ላይ ከተደረገ ጥናታዊ ሪፖርት ላይ የተወስዱ ነጥቦች ፤ ደርግ በጥቂት እና በተደራጀ ኃይል ፤ በፍፁማዊ አመራር እየተመራ ፤ በሐገር ውስጥ የተፈጠሩ አለመረጋጋቶች እና የእርስ በእርስ ጦርነቶችን አስታኮ (የኤርትራውን የመገንጠል እንቅስቃሴ ፣ የባሌውን አመፅ ፣ የወሎ ረኅብ ፣ ወዘተ) ፤ የፖለቲካ ስልጣንን በእኩዴታ የያዘበት አግባብ ፤ የዓለም ዓቀፉ ከምኒዝም የዘመቻ መመሪያ የተካኼደ ያኽል ፤ ከመመሪያው ጋር ተመሳሳይ ነው ።

ጥቁሩ የከምኒዝም መጽሐፍ የከምኒስት ፓርቲዎች ወደ ስልጣን የእሚመጡበትን መንገድ እንዲኽ ያስቀምጠዋል ፦

“… ጦርነት ፤ ይልቁንም በሐገር ደረጃ የመንግሥት መዋቅር መክሰም… ለከምኒስቶች ስኬት ቅድመ ኹኔታ ነው …(ምክንያቱም)… ጥቂት እና ስነምግባር የአለው ትንሽ የተደራጀ ቡድን የአለጥርጥር ስልጣን መያዝ ስለ እሚችል።”

“...War, or more precisely, the national collapse of the state organisation...has been a basic condition for the victory of Communist revolutiom...[this is necessary because]...a small but well-organised and discipline group is inevitably able to take authority in its hands... [23]“

እንደገናም እንደ የከምኒዝም ጥቁሩ መጽሐፍ ፤ ኹለተኛው የከምኒስት ኢንተርናሽናል ኮንግረስ ወይንም ስብሰባ በኋላ የወጣው ፤ የከምኒስት ኢንተርናሽናል ማንፌስቶ ፤ ከምኒስት ኢንተርናሽናል የሠራተኛውን አምባገነንነት ማስፈን የእሚችለው ፤ በወታደራዊ ስነ ምግባር በተዋቀሩ ጥቂት የተደራጁ ኃይላት ዓማካኝነት መሆኑን እንደ እዚኽ አስቀምጦታል ፦

“የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲህ በጋመበት በአኹኑ ሰዓት ፤ የከምኒስት ፓርቲ ሚናውን መጫወት የእሚችለው ፤ በፍፁም ማዕከላዊነት ተዋቅሮ ፣ የወታደር ዓይነት እንደ ብረት የጠነከረ ስረዓት ይዞ ፣ ይኽም ማዕከላዊ አወቃቀር የሚያጥረገርግ ኃይል ተላብሶ ፣ ተቀናቃኝ የሌለው ስልጣን ተላብሶ ፣ የአባላቶቹን ሙሉ ድጋፍ ሲያገኝ ነው ።”

“At the present moment of hard-fought civil war, the communist party will be able to fulfil its role only if its organized in a totally centralized fashion, if its iron discipline is as rigorous as any army, and if its central organization has sweeping powers, is allowed to extend uncontested authority, and enjoys the unanimous confidence of its members. [23]“

Thesis on tactics ወይንም የታክቲክ ጥንስስ በእሚለው የዓለም ዓቀፍ ከምኒዝም ሰነድ ላይ ፤ ዓለም ዓቀፉ የከምኒዝም ፓርቲ ሊሠራ የእሚገባቸውን ሥራዎች ሲዘረዘር ፤ ከአስቀምጣቸው ጉዳዮች አንዱ ፦

“…ማንኛውም ፖለቲካዊም ሆነ ኢከነሚያዊ ትግል ፤ ኹኔታው ሲያመች ወደ እርስ በእርስ ጦርነት መለወጥ እንደ እሚቻል እና በእዚያኽም ወቅት ስልጣንን በኃያል መያዝ ‘የሠራተኛው’ ኃላፊነት ነው የእሚለውን ኃሳብ ማስረፅ ።”

“…inculcate the idea that any economic or political struggle, when the circumstances are favorable, can be transformed into CIVIL WAR, in the course of which it is the duty of the proletariat to seize power. [23]”

ነው ።

የዓለም ዓቀፍ ከምኒዝም ፤ በሌኒን አማካኝነት በማኒፌስቶው ወይንም በፓርቲው የመቀስቀሻ ሰነድ ላይ ፤ ስለ ዓለም ዓቀፉ ከምኒዝም ፓርቲ ሚና ይኽን ብሏል ፦

“የዓለም ዓቀፉ ፤ ከምኒዝም አብዮትን የእሚያቀጣጥል እና የሠራተኛውን አምባገነንነት የእሚያሰፍን ዓለም ዓቀፍ ፓርቲ ነው ።”

“The communist international is the international party for insurrection and proletrait dictatorship. [23]”

እነ እዚኽን ስናሰባስባቸው ፤ ካሚንተርን (ከምኒስት ኢንተርናሽናል) ሥራው ወይንም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የእሚከተለው አካኼድ ፤ የሠራተኛው አብዮት በእሚል ፤ ሕጋዊ እና ሕገወጥ አካኼዶችን አዳብሎ ፤ ሐገራትን በሽብር ፣ በእርስ በእርስ ጦርነት ፣ የተፈጥሮ አደጋዎችን በማባባስ ፣ ወዘተ ፤ ከተናጡ በኋላ ፤ በጥቂት እና በተደራጀ ኃይል ፤ ተቀናቃኝን ኹሉ በኃይል ደምስሶ ስልጣን ላይ ወኪሎቹን ማምጣት ነው ።

ይኽ ደግሞ ደርግ ወደ ስልጣን የመጣበትን ድባብ እና በጥቂት ሰዎች አደረጃጀት ሥራውን ከሠራበት መንገድ ጋር ፤ ከአጋጣሚ የእሚያልፍ ተመሳሳይነት የአለው መሆኑን ያሳያል ።

በሐገር ውስጥ ፤ ዘርፈ ብዙ ብጥብጦች በማስነሳት መንግሥት እና ሐገርን አተራምሶ ፤ ስልጣን መያዝ ዓለም ዓቀፉ ከምኒዝም በእየሐገሩ የእሚከተለው ስልት እንደ ነበር ፤ ጥቁሩ የከምኒዝም መጽሐፍ እንደ እዚኽ ይላል ፦

“በሞስኮ አጫሪነት ፤ ካሚንተርን በእያንዳንዱ ከምኒስት ፓርቲ ውስጥ የታጠቁ ቡድኖች አስገባ ፤ በስልጣን ላይ የአለውን መንግሥት ላይ አብዮት እና የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲያስነሱ ። ከእዚኽ በተጨማሪም ፤ ለዓለም ዓቀፍ ወንድሞቹ በሶቭየት ሕብረት ራሺያ የተጠቀመባቸውን የሽብር ታክቲኮችም (ቀይ ሽብር ለምሳሌ) አስተማራቸው ።”

“At Moscow’s instigation, the commintern installed an armed group within each communist party, to prepare for revolution and civil war against the reigning powers. It also introduced to its brethern to the same police tactics and terror that was used in the U.S.S.R [23]“

በእዚኽ መልኩ ፤ እነ ደርግ እና መሰል ሌሎች የከምኒስት ፓርቲዎች ፤ የዓለም ዓቀፉ ከምኒዝም ቅርንጫፍ ሆነው ፤ በተቀጣጠሉት ሽብሮች እና የእርስ በእርስ ጦርነቶች አሳበው የፖለቲካ ስልጣን ከያዙ በኋላ ፤ ታክቲኩን ተጠቀምንበት አኹን በሐገራችን ጉዳይ እኛው እንወስናለን ብለው ነፃ የእሚሆኑ ሰአይሆን ፤ አሰልጥኖ በአብዮት ለስልጣን ለአበቃቸው የዓለም ዓቀፉ ከምኒዝም ቅርንጫፍ መሆን ብቻ ሰአይሆን ፤ እንደ ሐገር መሪ ሉዓላዊነታቸውን ሙሉ ለሙሉ ትተው ፤ ለዓለም ዓቀፉ ከምኒዝም ፍፁም ታዛዥ ይሆናሉ ፦

“በእየ ሐገሩ የአሉ፟ት ከምኒስት ፓርቲዎች ፤ ከተቋማዊ አወቃቀር አንፃር የዓለም ዓቀፉ ከምኒዝም ንዑስ የሆኑት ፤ በግዜ ኺደት ለሞስኮው የመስገዳቸው ኹኔታ እየጨመረ ይኼድ እና በመጨረሻ ፤ ሉዓላዊነታቸውን በሙሉ እርግፍ አድርገው የተውና የካሚንተርን ተላላኪ ይሆናሉ ። ይኽ ሰጋጅነት ፤ ተቋማዊም ፖለቲካዊም በመሆኑ ፤ በእየፓርቲዎቹ ዋና ዋና ውሳኔዎችን ካሚንተርን[4] እየወሰነ ፤ በስተመጨረሻ የፖሊሲ ውሳኔዎች በሙሉ በካሚንተርን ይወሰናል ።”

“The communist parties (of each nation), which from an institutional point of view were merely the national sections of the international, rapidly become more and more subordinate, before surrendering to the CommIntern. This subordination was both political and organizational, as the commintern came to make all major decisions for these parties, and ultimately decides all question of policy. [23]“

ይኽም መረጃ ላይ የተመሠረተ ትንታኔም ብቻ ሰአይሆን ደርግ ራሱን ፤ እነ ሌኒን ያካኼዱት የራሺያው የጥቅምት አብዮት ወራሽ ነኝ ብሎ ፤ የዓለም ዓቀፉ ከምኒዝም ተገዢ እንደነበር የተመዘገበ ታሪክ ነው ፦

“ራሱን የታላቁ ‘የጥቅምት አብዮት’ ወራሽ ነኝ በማለቱ ፤ ኢሠፓ በውስጠ ፓርቲ ስምምነት የዓለም ዓቀፍ ከምኒዝምን የመቀላቀል ሽልማት ተሰጥቶታል”

“Calling itself the heir of the great “October revolution” the EWP was accorded complete integration into the system of world communism through inter-party agreements. [23]“

ለእዛም ነው ፤ ይኽ ነው የእሚባል ትምህርት የሌላቸው ፤ አብዛኞቹ ለምን እንደ ተስበሰቡ እንኳን የእማያውቁ ከ108 የእማይበልጡ ፣ ወታደራዊ ማዕረጋቸው ሻለቃ እና ከሻለቃ በታች የሆኑ ወታደራዊ መኮንኖች ፤ በጥቂት ንቃት በአላቸው አመራሮቻቸው እየተመሩ ሰፊውን የሐገሪቱን ሕዝብ ሰአያሳትፉ እና የኢትዮጵያን ሙህራን ኹሉ ከሐገር አስወጥተው ፤ ከእነርሱ በትምህርት እና በልምድ የእሚሻሉትን የዘውድ ስረዓት በአለስልጣናት አውርደው ፤ በቀላሉ የፖለቲካውን ማማ መቆጣጠር የቻሉት እንጂ ፤ በሐገር ውስጥ ባለው መመዘኛ ቢሆን የደርግ ካቢኔ በየትኛውም መመዘኛ ከንጉሡ ካቢኔ ተሽሎ ወደ ስልጣን ሊመጣ አይችልም ነበር ።[5]

ደርግ ከግዚያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ራሱን ኢሠፓ ብሎ ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት አሳደግኹ ሲልም ፤ ስሙን ብቻ እንጂ የቀየረው ፤ ወታደራዊ አመራር እንደሆነ ነበር የቀጠለው ፦

“አብዛኛዎቹ የኢሠፓ የፖሊት ቢሮ አባላት የቀድሞው የደርግ አባላት ናቸው ። ሙህሩ በፓርቲው ውስጥ ድርሻው በጣም ጥቂት ነበር ።”

“Most of the EWP politburo was made up of the former Durgue members. The intellegentsia constitute only a small portion of the party… [23]“

ደርግ በፖሊት ቢሮ ደረጃም ብቻ ሰአይሆን ፤ 3/4ኛ በላይ ማለትም ከ75% በላይ አባላቱ ወታደሮች እና የመንግሥት ሰራተኞች እንጂ ፤ ከሕዝቡ ጋር ምንም ንኪክ ያልነበረው ነው ፦

“ምንም እንኳን በመጀመሪያ አከባቢ ፓርቲውን ማንም ሰው መቀላቀል ይቻላል የእሚለውን ለማሳየት ጥረት ቢደረግም ፤ ሰራተኞች ከፓርቲው በገፍ በመሸሻቸው ተሳትፎዋቸው ከእሩብ (1/4ኛ) በታች ነበር ። ከ3/4ኛ በላይ (75%) በላይ የእሚሆኑት የፓርቲው አባላት ወታደሮች እና የመንግሥት ሰራተኞች ነበሩ … ምንም እንኳን ገበሬው የሐገሪቱ 85 % ቢሆንም በፓርቲው ውስጥ ተሳትፎዋቸው ከ3% አይበልጥም ።”

“Despite initial all-out efforts to show that anyone could joint party, workers stayed away in droves, making up less than 1/4th of the membership. Over 3/4th of the members consisted of soldiers and civil servants, representing the social realities of the society peasants make only 3% of the party. [23]“

ይኽም ብቻ ሰአይሆን ፤ የደርግ የ1982 ዓ.ም. የቅይጥ ኢከነሚ ማሻሻያ ፤ ከሚካኤል ጎርቫቾ ግላስኖስት (ግልጽነት እና ተጠያቂነት) እና ፕራይስቶሪካ (አዲስ አወቃቀር) ከእሚባሉት ማሻሻያ ጋር ፣ የደርግ መውደቅ ከሶቭየት ሕብረት መፈራረስ ጋር ፤ መያያዙ ፥ የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ ሰአይሆን ፤ የደርጉ መንግሥት የራሻው ሞስኮ ማዕከሉ የነበረው የከምኒስት ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ስለ ሆነ ነው ።

የሶቭየት መንግሥት እየተዳከመ እና ራሱን ለማክሰም በእሚዘጋጅበት ወቅት ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ከኢሕአዴግ ጋር በሚደረገው ጦርነት ደርግን ለማገዝ በእየ ግንባሩ የነበሩትን የራሻ ዜግነት የአላቸውን አማካሪዎቹን ማንሳት ሲጀምር ፤ የደረግ ሠራዊት መንግሥቱ ኃይለማሪያም ራሳቸው በአካል ተገኝተው ቢያዋጉትም ሊድን በእማይችል መልኩ ፤ እየፈራረሰ እና እየተዳከመ ነው የመጣው ፦

“እ.አ.አ. በየካቲት 1990 ዓ.ም. (እ.ኢ.አ. 1982 ዓ.ም.) የሶቭየት ወታዳራዊ አማካሪዎች ከጦር ግንባር እንዲነሱ ተደረጉ ። ይኽ በእሚሆንበት ወቅት የኃይል ሚዛኑ ወደ ተቃራኒው ቡድን ማድላት ጀምሮ ነበር ። በኹሉም ግምባሮች ጦሩ ማፈግፈግ ጀምሮ ነበር … መንግሥትም ለዓለም ዓቀፉ ማሕበረሰብ የድረሱልኝ ‘ጥሪ’ እያስተጋባ ነበር ።”

“The departure of Soviet Military advisers from the combat zone was announced on in March 1990. By this time the balance of power was already beginning to swing to the other side. On all fronts the army was on retreat from all popular fronts… and the regime was giving out distress signals to the international community. [23]“

ምንም እንኳን ለደርግ ሽንፈት ፤ የካሚንተርን ልዑክ የኾኑት ራሺያ የጦር አማካሪዎች መነሳትን እንደ ዋና ምክንያት ማቅረብ ላይቻል ቢችልም ፤ የካሚንተርን ልዑክ የኾኑት ራሺያ የጦር አማካሪዎች የደርግን ጦር ሲያግዙ መኖራቸው ፤ ትስስሩ ከርዮታዊ ስምምነት ያለፈ ለመሆኑ ሌላ ተጨባጭ ማስረጃ ነው ።

እናም የካሚንተርን ተወካይ በኢትዮጵያ የነበሩት እና በአንድ ወቅት ጀርመን አገር ኼደው ቃለ መጠየቅ ሲሰጡ ፦

“ያለፈውን ሴጣናዊ ውርስ ሽረን ተፈጥሮን ራሷን በቁጥጥር ስር እናደርጋለን።”

«we will liquidate the satanic heritage of the past and place nature itself under our control. [23]“

ያሉት መንግሥቱ ፤ የበላዮቻቸው በቀዝቅዛው ጦርነት ተረተው እጅ ሲሰጡ ፤ የእርሳቸውም ፖለቲካዊ ዕጣ ፈንታ በአልጠበቁት መንገድ ሐገር ለቀው ወደ ዚምቧቡዌ የኼዱበት ሆነ ።

ስለ እዚኽ ፦ ደርግ የዓለም ዓቀፉ ከምኒዝም ቅርንጫፍ በኢትዮጲያ ለመሆኑ ምንም ጥያቄ የለምውም ፤ ምንም እንኳን ስለ ተለያዩት የተማሪ አብዮተኞች ተመሳሳይ ነገር ማለት ቢቻልም።

ይኽም በመሆኑ ፤ ደርግም ሆነ የተማሪ አብዮተኞቹ ጎራ ለይተው ለመጠፋፋት ቢጋጩም እና በግጭቱ ደርግ አሸንፎ የፖለቲካ ስልጣኑን ቢይዘውም ፤ በአጋጣሚ የተማሪ አብዮተኞችም ድል ቢቀናቸው ኖሮ ተመሳሳይ የሆነው የደርግን ዓይነት ሶሻሊዝም ስለ ሆነ የእሚተገብሩት ፤ የኢትዮጲያን ብሔራዊ መንግሥት ሕዝባዊ ከማድረግ አንጻር ስለ እዚኽ የታሪክ ክፍል ማለት የእሚቻለው ፦ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፤ በታሪክ አጋጣሚ የአገኘውን ሕዝባዊ መንግሥት የመፍጠር እድሉን ፦ የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ወግ አጥባቂነት ሰበብ አድርገው አብዮት የጀመሩት ተማሪዎች እና ደርግ ፣ አጉል ጀብደኝነት ፣ የስልጣን ጥመኝነት እና ዓለም ዓቀፍ ከምንስታዊ ራዕይ ለሐገራቸው የአላቸውን ታማኝነት የሸረሸረባቸው ኃሳባዊያን ተማሪዎች እና የከምኒስት ኢንተርናሽናል ወኪል ራሱን የአደረገው ደርግ ፤ አመከኑት ።

የእሚቀጥለው እና የመጨረሻው የታሪካችን ክፍል ፤ ክፍል ዘጠኝ ፤ ከደርግ በኋላ የአለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የዴሞክራሲያዊነት ትግል ኺደት ፤ አኹን የአለበትን ደረጃ የእምናይበት ይሆናል ።

  1. ተማሪዎቹ ፦ የኢትዮጲያ ተማሪዎች ሕብረት በአዲስ አበባ ፣ የኢትዮጲያ ተማሪዎች ሕብረት በአውሮፓ ፣ የኢትዮጲያ ተማሪዎች ሕብረት በሰሜን አሜሪካ በእሚለው በሶስት ጎራ ተከፋፍለው ፤ ምንም እንኳን ሶስቱም አንዱን የማርክሲዝም ርዕዮት እንከተላለን ቢሉም ፤ ከማርክሲዝሙ ርዕዮት ራሱ ትሮትሲካይት ፣ ማዖይስት ፣ ማርክሲስት ሌንኒስት ፣ ወዘተ ፤ ብለው ተከፋፍለው ፤ በእዚኽም ክፍፍላቸው ኢሕአፓ ፣ ወዝሊግ እና መኢሶን የእሚባሉ ፓርቲ መሰል እንቅስቃሴዎች ጀምረው ፤ ገበሬው ውስጥ ገብተን ሽምቅ ውጊያ እንጀምር ፣ ከተማ ውስጥ አመጽ እና ግድያ እንአፋፋም ፣ የለም መጀመሪያ ሕዝብ እናንቃ በእሚል ተከፋፍለው ፤ በዋናነት ለጀብደኝነት እና ለስልጣን ሲባ፟ሉ ፤ ደርግ ከአደረሰባቸው ጥቃት በአሻገር እርስ በርሳቸው ተበላልተው እንደ አለቁ የወቅቱ ታሪካቸው ይነግረናል። ↑

  2. ከሚንዝም መሬትን ጨምሮ ማንኛውንም ንብረት በግል ንብረትነት መያዝ የቡርዣ የፖለቲካ ስረዓት ነው የእሚል እና የግል ንብረት ባለቤትነት መብትን መሻር ዋነኛው የስረዓቱ ግብ በመሆኑ ። ↑

  3. አንድ አንድ ሰዎች ለማስመሰል እንደ እሚፈልጉት ፤ ደርግ መንግሥቱ ኃይለማሪያም እና አብረዋቸው የነበሩት ከፍተኛ የደርግ ባል ስልጣናት ብቻ በመሆኑ እና እነ እዚኽም ሰዎች የማርክሲዝም ደቀ መዛሙርት በአለመሆናቸው ፤ በደርግ ዘመን ሶሻሊዝም በኢትዮጲያ ውስጥ በአግባቡ የአልተተገበረ አይደለም።

    የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል ነው እንጂ ደርግ ከሐገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የሆኑ እና እንደ ተማሪዎቹ በወጣትነት እሳት ብቻ ሰአይሆን የማርክሲዝም ፍልስፍና ምንነት እና በኢትዮጲያ ኹኔታ እንዴት ቢተገበር ሊሻል እንደ እሚችል የእሚያውቁ ብዙ በማርክሲዝም የበቁ አጋዦች(Functionaries) ስለነበረው ፤ የማርክሲዝም ሶሻሊዝም በኢትዮጲያ በመንግሥት ሰራተኛው ፣ በገበሬ ማሕበሩ ፣ በጥቃቅን ነጋዴው ፣ በወጣቶች ማሕበር ፣ ወዘተ ፤ እንጥፍጣፊው ሳይቀር ነው የተተገበረው ። ያው ሶሻሊዝም ዋግ እንደመታው ሰብል ቢያጠሩት አይጠራም እንጂ።

    በእኔ እምነት ደርግ የተማሪ አብዮተኞቹን አሸንፎ የበታተናቸው በወታደራዊ ጉልበት ሳይሆን በርዕዮቱ ዓለም ፤ ዓለን የእሚሉትን ርዕዮት ከእነርሱ በላይ እና እነርሱ ከአሰቡት ፍጥነት በላይ ስለተገበረው ነው ። ↑

  4. ካሚንተርን የዓለም ዓቀፉ ካምኒስት ፓርቲ መጠሪያ ወይንም የካምኒስት ኢንተርናሽናል ሌላ (ካም + ኢንተር) ስያሜ ነው። ↑

  5. በእርግጥ ከእላይ እንደ አልነው ኢሕአፓ ፣ ወዝሊግ ወይንም መኢሶን ሐገር በቀል ናቸው ማለት አይደለም ፤ ለምሳሌ ፦ ኢሕአፓ በአልጄሪያ በብርሐነ መስቀል ረዳ ፣ በኢያሱ አለማየኹ እና በክፍሉ ታደሰ አደራጅ ኮሚትነት ሲመሠረት ትሮትስካይት በእሚባሉት እና ራሳቸው 4ኛው ካሚንስት ኢንተርናሽናል ብለው በእሚጠሩት ዓለም ዓቀፍ የካምኒስት ኢንተርናሽናል ጥላ ስር እንደ ተዋቀሩ የራሳቸው የመስራች አባላቱ ምስክርነት ነው። ↑